ሃይማኖት እና እምነት
ከሁሉ አስቀድሞ ሃይማኖት የሚለው ቃል እና እምነት የሚለው ቃል አንድ ናቸው? ወይስ የተለያዩ? ግንኙነታቸውና ልዩነታቸውስ ምንድን ነው? የሚለውን አጥርቶ ማየት አስፈላጊ ነው።
ሃይማኖት ምንድን ነው?
ሃይማኖት የሚለው ቃል የሚገልጸው አንድ ሰው የሚያምነው እምነት ይዘቱ ወይም አስተምህሮው (Content of Faith) ምንድን ነው? የሚለውን ነው። ይህም ማለት አምነዋለሁ የሚለው ነገር መሠረታዊ ስለሆኑት ጉዳዮች ምን ምን ይላል? የሚለውን ማለት ነው። ሃይማኖት አንድ ሰው እውነት ነው ብሎ የያዘውን ነገር ምንነት የሚያመለክት ቃል ነው። ለምሳሌም ቅዱስ ጳውሎስ ከአሳዳጅነት ከተመለሰ በኋላ “ነገር ግን፣ ቀድሞ እኛን ያሳድድ የነበረ፥ እርሱ በፊት ያጠፋው የነበረውን ሃይማኖት አሁን ይሰብካል” ሲል ይን የሚገልጽ ነው። ገላ. 1፡23 እንዲሁም “ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ . . .” (ይሁዳ 3) ሲል፣ “እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ” (ቆላ. 2፡7) ሲል ይህን የሚያስረዳ ነው።
እምነት ምንድን ነው?
እምነት ደግሞ አንድ ሰው አምነዋለሁ በሚለው ነገር ላይ ያለው መታመን ነው። እምነት አንድ ሰው እውነት ነው ብሎ ለያዘውና አምነዋለሁ ለሚለው ነገር ያለው ውስጣዊ መታመን ነው። ስለዚህ ሃይማኖት አጠቃላይነት ያለው ሲሆን እምነት ደግሞ ግላዊነት ያለው ነው።
በአገላለጽ ደረጃ ግን ሃይማኖትም እምነት፣ እምነትም ሃይማኖት እየተባሉ ሲጠሩ እናገኛለን። ይህ በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በአጠቃላይ የጽሑፍም ሆነ የንግግር ባህል በስፋት የተለመደ ነው። ይህ ማለት ግን ሁል ጊዜ ሁለቱም አንድ ዓይነት ነገር ናቸው ማለት አይደለም።
እምነት የሚለው ቃል በውስጡ ሁለት (2) ነገሮች አሉት። እነዚህም
1) የሚታመነው እውነት – የምናምነው አምላክ ማን ነው? ይህ አምላክ ስለ ራሱ ምን ብሏል? የሚመለከው ማን ተብሎ ነው? እንዴትስ ነው? አድርጉ አታድርጉ ያለውስ ምንድን ነው? በአጠቃላይ ትምህርቱ ምን ይላል? በእምነት ውስጥ የመጀመሪያው መሠረታዊ ጉዳይ ይህን የመሰሉት ነገሮች ናቸው።
ይህም የእምነቱ ይዘት (Content of Faith) ምንድን ነው? የሚለው ጉዳይ ማለት ነው። ሃይማኖት ተብሎ የሚጠራው ይህ የእምነቱ ውስጠ ይዘት ነው። አንዱን እምነት ከሌላው እምነት የሚለየው ይህ የእምነቱ ይዘት ወይም ሃይማኖት ነው። ሃይማኖት “እምነት” ተብሎ ሲጠራ ወይም ሲገለጽ ይህን ለማለት ጥቅም ላይ የዋለ መሆኑን፣ ማለትም የሚታመነው ነገር ምን መሆኑን ለመግለጽ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው።
2) ሁለተኛው ደግሞ አምነዋለሁ በሚለው አምላክ ላይ ያለው ግለሰባዊ መታመን ነው። ይህ መታመን ሃይማኖቱ ምንም ይሁን ምን አማኙ በሚያምነው ነገር ላይ ደካማም ሆነ ጠንካራ መታመን (እምነት) ሊኖረው ይችላል። ሆኖም የሚያምኑት ነገር (ሃይማኖታቸው) የተለያየ የሆኑ ሰዎች አማኞች ቢሆኑም ቅሉ፣ የእምነታቸው ይዘት (ሃይማኖት) ግን የተለያየ በመሆኑ አንድ ናቸው ሊባሉ አይችሉም። የሚያምኑ መሆናቸው ቢያመሳስላቸውም የሚያምኑት ነገር የተለያየ (እርስ በእርሱ የሚቃረንና አንዱ ለሌላው ስህተትና ክህደት የሆኑ ትምህርቶች) በመሆኑ ሃይማኖታቸው የተለያየ ነው።
በእውነተኛው ሐዋርያዊና ኦርቶዶክሳዊ ክርስትና ውስጥ ያሉ አማኞች የሚያምኑት ነገር (ሃይማኖታቸው) አንድ ነው። ሆኖም እምነታቸው ግን ከግለሰብ ግለሰብ የተለያየ ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም እምነት ማለት አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ቅርበትና በእግዚአብሔር ላይ ያለው ተአምኖ ማለት ነውና። ለምሳሌም የሚከተሉትን ዓይነት እምነቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ማየት እንችላለን።
የእምነት ዓይነቶች በመጽሐፍ ቅዱስ
ሀ) ደካማ ወይም ጎደሎ እምነት
•
“ወዲያውም ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ያዘውና፣ አንተ እምነት የጎደለህ፣ ስለምን ተጠራጠርህ? አለው።” ማቴ 14፡31
•
“እናንተ እምነት የጎደላችሁ…” ማቴ 6፡30
•
“እንዲህ የምትፈሩ ስለ ምን ነው? እንዴትስ እምነት የላችሁም? አላቸው።” ማር.4፡40
•
“በእምነት የደከመውንም ተቀበሉት፣ በአሳቡም ላይ አትፍረዱ።” ሮሜ 14፡1
ለ) የሚዘገይ እምነት
•
እርሱም፣ እናንተ የማታስተውሉ፣ ነቢያትም የተናገሩትን ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ . . “ሉቃ. 24፡25
ሐ) ውስን እምነት
•
“ማርታም ኢየሱስን፣ ጌታ ሆይ፣ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር … አለችው ዮሐ.11፡21
መ) የሚያድግ እምነት
•
“ወንድሞች ሆይ፣ እምነታችሁ እጅግ ስለሚያድግ … ስለ እናንተ እግዚአብሔርን እንደሚገባ ልናመሰግን ግድ አለብን።” 2 ተሰ. 1፡3
ሠ) ታላቅ እምነት
•
“ኢየሱስም ሰምቶ ተደነቀና ለተከተሉት እንዲህ አለ፣ እውነት እላችኋለሁ፣ በእስራኤል እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም፡፡” ማቴ.8፡10
ረ) ተራራ ማፍለስ የሚችል እምነት
•
“እውነት እላችኋለሁ፣ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፣ ይህን ተራራ፣ ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም።” ማቴ. 7፡20-21
ሰ) እንደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሥራት የሚያስችል እምነት
•
“እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል።” ዮሐ. 14፡12
እነዚህ ሁሉ በእምነታቸው ከደካማ እምነት አንሥቶ እንደ ጌታችን መሥራት እስከሚያስችለው ፍጹም የሆነ እምነት ድረስ ያሉት ግለሰቦች የእምነታቸው መጠንና ደረጃ የተለያየ ቢሆንም የሚያምኑት እምነት (ሃይማኖት) ግን አንድ ነው። በዘጠና ዘጠኝ ዓመቱ ልጅ ትወልዳለህ ሲባል ከእርሱ በፊት ለዚህ ምስክር ተደርጎ የሚጠቀስ ሌላ ማንም ሰው ባልነበረበትና የተጻፈ መጽሐፍም ሆነ አስተማሪ ባልነበረበት ዘመን ያመነው፣ ይህ እምነቱም ጽድቅ ሆኖ የተቆጠረለት አብርሃም፣ እና ከአብርሃም ጀምሮ በእርጅና ዘመናቸው ልጅ ያገኙ ብዙ ምስክሮች ባሉበትና ብዙ መጻሕፍት በተጻፉበት ዘመን እየኖረ ልጅ ትወልዳለህ ሲባል የተጠራጠረው ዘካርያስ፤ ሁለቱም የሚያመልኩት አምላክ አንድ ነው፣ የሚያምኑት ነገር አንድ ነው። ማለትም ሃይማኖታቸው አንድ ነው። ነገር ግን በዚያው አንድ ሃይማኖት ውስጥ እያሉ የእምነታቸው ደረጃ ግን የተለያየ ነበር። አብርሃም እምነቱ ፍጹም ሲሆን ዘካርያስ ደግሞ ተጠራጥሯል። ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ “አንድ ሃይማኖት” ያለው እምነትን አይደለም። እምነትማ ከላይ እንዳየነው ከሰው ሰው የተለያየ ነው። ከደካማ እምነት ጀምሮ ተራራን እስከማፍለስ ድረስ ሙሉ የሆነ የተለያየ እምነት አለና።
ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ላይ “እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው” ብሎ የገለጸው ሃይማኖትን ማለቱ አይደለም። ሮሜ 12፡3 ምክንያቱም ሃይማኖትማ ለእያንዳንዱ የማይከፈልና የማይለያይ መሆኑን “አንድ ሃይማኖት” ብሎ አስረግጦ ተናግሯል። ኤፌ. 4፡5 ስለዚህ እምነት ከሰው ሰው የሚለያይ ግለሰባዊ ነው፣ ሃይማኖት ግን ከእግዚአብሔር የተሰጠ አንድና ብቸኛ ነው። አለዚያማ ይህ ለእያንዳንዱ እንደ ተሰጠው መጠን የሆነው እምነት “አንድ ሃይማኖት” ተብሎ ከገለጸው ጋር እንዴት ይስማማል? እንደዚሁም እንደ ተሰጠንም ጸጋ ልዩ ልዩ ስጦታ አለን፤ ትንቢት ቢሆን እንደ እምነታችን መጠን ትንቢት እንናገር” በማለት እምነት እንደየ አማኙ ጸጋና የሕይወት ሁኔታ ከሰው ሰው የሚለያይ መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ አስረድቷል። ሮሜ 12:6
እምነት እንዲህ ከሰው ሰው የሚለያይ ሲሆን፣ በአንጻሩ እነዚህ በተለያየ የእምነት ደረጃ ያሉ ክርስቲያኖች የሚያምኑት እውነት – ሃይማኖት – ግን አንድ ነው። ይህች አንዲት ሃይማኖት ከሰው ሰው የማትለያይ፣ ከአንዱ ከእግዚአብሔር ለመዳናችን አንድ ጊዜ
የተሰጠች እውነት ናት። ሐዋርያው ቅዱስ ይሁዳ “ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ” ብሎ የገለጸው ይህን መሠረታዊ እውነት ነው። ይሁ. 3
በመጽሐፍ ቅዱስ ይህ ሃይማኖት እንደየ አገባቡና ዐውዱ አንዳንድ ጊዜ እምነት፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ “ትምህርት” ተብሎ ተገልጾ እናገኛለን። የግሪኩ ቃል ግሡ πιστεω – ፒስቴዎ- ሲሆን ማመን ማለት ነው። πιστιv – ፒስቲን ደግሞ እምነት ማለት ነው። ይህ የግሪክ ቃል ሃይማኖትንም፣ እምነትንም ሁለቱንም እንደየአግባቡ የሚገልጽ ቃል ነው። ከላይ እንዳየነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሃይማኖት እና እምነት የሚሉት ቃላት ብዙ ጊዜ በተወራራሽነት ጥቅም ላይ ውለው እናገኛለን። እንደዚሁም ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ሃይማኖትን διδασκαλία – ትምህርት (አስተምህሮ) በሚል ቃልም ይገልጸዋል። ለአብነትም ይህን የሚያሳዩ የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን እንመልከት።
ሃይማኖትን πιστιv – ፒስቲን – እምነት በሚለው ሲገልጸው፡-
•
“አንድ ሃይማኖት – πιστιv – ፒስቲን” ኤፌ. 4፡5
•
“… ከካህናትም ብዙ ሰዎች ለሃይማኖት ( πιστιv – ፒስቲን) የታዘዙ ሆኑ።” የሐዋ. 6፡7
•
“ቀድሞ እኛን ያሳድድ የነበረ፣ እርሱ በፊት ያጠፋው የነበረውን ሃይማኖት ( τηv πιστιv – ቴን ፒስቲን – to the Faith) አሁን ይሰብካል ተብሎ ሲነገር ይሰሙ ነበር” ገላ. 1፡23
•
“ይህም፣ ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ ከሰማችሁትም ከወንጌል ተስፋ ሳትናወጡ፣ በሃይማኖት ( τü πιστει – ቱ ፒስቴይ – in the Faith) ጸንታችሁ ብትኖሩ ይሆናል።” ቆላ. 1፡23
በእነዚህ ጥቅሶች ላይ በግሪኩ የተገለጸው ሐሳብ ሃይማኖትን የሚገልጽ በመሆኑ፣ የአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ቦታዎች ላይ “ሃይማኖት” ብሎ መተርጎሙ በግሪኩ ያለውን ሐሳብ በትክክለኛ ሁኔታ የሚገልጽ ትክክለኛ አተረጓጎም ነው።
ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ ሃይማኖትን – διδασκαλία – ዲዳስካሊያ – አስተምህሮ ወይም ትምህርት በሚለው ቃል ሲገልጸው እንመልከት።
•
“እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ( διδασκαλίας – ዲዳስካሊያስ) ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም።” ኤፌ. 4፡14
•
“ወደ መቄዶንያ በሄድሁ ጊዜ፣ አንዳንዶች ልዩ ትምህርትን ( διδασκαλειv – ዲዳስካሌይን – other doctrines) እንዳያስተምሩ . . . ልታዛቸው በኤፌሶን ትቀመጥ ዘንድ ለመንሁህ፤ .. .” 1 ጢሞ. 1፡3-4
•
“ይኸውም, . . . የብሩክ እግዚአብሔርንም ክብር እንደሚገልጥ ለእኔ አደራ እንደ ተሰጠኝ ወንጌል የሆነውን ደኅና ትምህርት ( διδασκαλία – sound teaching) ለሚቃወም .. ” 1 ጢሞ 1፡3-4
•
ለራስህና ለትምህርትህ ( τη διδασκαλίας – to the teaching) ተጠንቀቅ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ፥ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህና።” 1 ጢሞ 4፡16
•
“አንተ ግን ሕይወት ለሚገኝበት ትምህርት (τη ὑγιαινού διδασκαλίας- sound teaching) የሚገባውን ተናገር።” ቲቶ 2፡1
•
“ልዩ ልዩ ዓይነት በሆነ በእንግዳ ትምህርት [διδαχαῖς (teachings) ποικίλαις (various) και (and) ξέναις (strange)] አትወሰዱ።” ዕብ. 13:9
•
“ለሚወጣ ሁሉ በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው ( διδαχῇ τou Χριστοῦ _ abides not in the teaching of Christ) አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት። ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንም ትምህርት ( τηv διδαχῇv- the teaching) ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት፤ . .”2 ዮሐ. 9-10
•
“ወዳጆች ሆይ፣ . . . ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት ( πίστεις (Faith) üπαξ (once) παραδοθείσῃ (delivered) τη (for the) ἁγίοις (Saints) faith which was once delivered) እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።” ይሁ 3
ስለሆነም ከእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃሎች በግልጽ እንደምንረዳው፣ ሃይማኖት “እምነት” ተብሎም ተገልጿል፣ “ትምህርት” ተብሎም ተገልጿል።
ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ
መድሎተ ጽድቅ -ቅጽ-3 ገፅ 39-44