እመቤታችን ጥንተ አብሶ አላት ለሚሉ የተሰጠ መልስ – በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
የድንግል ማሪያም ዘላለማዊ ድንግልና በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ

ወላዲተ አምላክ በነገረ ድኅነት  እዚህ በመጫን ያንብቡ

✥ ስለ እመቤታችን ቅዱሳን መጻሕፍት ምን ይላሉ?   እዚህ በመጫን ያንብቡ

✥ ነገረ ማርያም  እዚህ በመጫን ያንብቡ

 

የምድር ባለጸጎች አሕዛብ ሁሉ በፊትሽ ይማለላሉ – በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
አንቺም ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ – በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ

“ማንም ሊክደው የማይችለው የቅድስት ድንግል ማርያም ንጽሕና”

በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ 

ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ንጽሕና ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ በምዕ 1፥9 ላይ “እግዚአብሔር ጸባኦት እመ ኢያትረፈ ለነ ዘርዐ ከመ ሰዶም እምኮነ ወከመ ገሞራ እመሰልነ” (አሸናፊ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በኾንን እንደ ገሞራም በመሰልን ነበር) በማለት እመቤታችን በአምላካዊ ጥበብ ከእናቷ ማሕፀን ዠምራ በአዳም በደል ከመጣው ከመርገመ ሥጋና ከመርገመ ነፍስ ተጠብቃ ያለች ንጽሕት ዘር የመኾኗንና በተጨማሪም ልዩ ስለኾነው አማላጅነቷ በመንፈሰ እግዚአብሔር በመቃኘት ትንቢት ተናግሮላታል፡፡

ይኸውም የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ንጽሕት ዘር የተባለችው ቅድስት ድንግል ማርያምን ከመርገመ ሥጋ ከመርገመ ነፍስ ጠብቆ ከሴቶች ኹሉ መርጦ፤ ለርሱ እናት እንድትኾን ለእኛ ደግም አማላጅ እንድትኾነን የሰጠን ስለመኾኑ “ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ” በማለት ነቢዩ ገልጾታል፡፡ ኢሳይያስ መርገም የሌለባት ስለመኾኑ የተናገረውን ትንቢታዊ ኀይለ ቃልን፤ ከእግዚአብሔር ተልኮ የመጣው ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት ወገን የኾነው ቅዱስ ገብርኤል ለቅድስት ድንግል ማርያም ተገልጾ ለመዠመሪያ ጊዜ የተናገራት “ተፈሥሒ ፍሥሕት ኦ ምልእተ ጸጋ እግዚአብሔር ምስሌኪ” (ጸጋን የተመላሽ ደስተኛዪቱ ሆይ ደስ ይበልሽ፤ ጌታ ካንቺ ጋር ነውና) የሚል አስደናቂ ምስክርነት ሲኾን ይኽም የተናገራት ቃል የእመቤታችንን ፍጹም ንጽሕናና ጥንተ አብሶ ካመጣው ከምልአተ ኀጢአት ፍዳ ከመርገመ ሥጋ ከመርገመ ነፍስ ፍጹም የተለየች መኾኗን ያመላከተና ለአምላክ ማደሪያነት በፍጹም ንጽሕናና ቅድስና የጸናች ምልእተ ጸጋ መኾኗን በትክክል ያረጋገጠ ነው፡፡

ክብር ይግባውና በንጹሓን ኪሩቤልና ሱራፌል ላይ ዐድሮ የሚኖር ንጹሐ ባሕርይ አምላክ በንጹሕ ስፍራ እንደሚያድር ኀጢአትን እንደሚጸየፍ በመጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታዎች ተጽፎ እናነብባለን፤ ሐዋርያው ዮሐንስም ኀጢአት ያለበት ኹሉ እንኳን ርሱን ለመውለድ ቀርቶ ጨርሶ ማየትና ማወቅ እንደማይችሉ “በርሱም ኀጢአት የለም በርሱ የሚኖር ኹሉ ኀጢአትን አያደርግም፤ ኀጢአትን የሚያደርግ ኹሉ አላየውም አላወቀውምም” በማለት እንዳስቀመጠው፤ ሰማይ ምድር የማይወስኑትን አምላክ በማሕፀኗ የተሸከመች፤ ኪሩቤል ሱራፌል ዙፋኑን በመፍራትና በመንቀጥቀጥ የሚሸከሙትን ሰማያዊ መለኮትን በዠርባዋ ያዘለች፣ በክንዷ ያቀፈች፣ ሰማይ ምድር ከፊቱ የሚሸሹትን የባሕርይ አምላክን በከንፈሮቿ የሳመችው፤ ፍጥረታትን ኹሉ በዝናብ አብቅሎ በፀሓይ አብስሎ የሚመግበውን፤ ለቅዱሳን መላእክት ርሱ የገለጸላቸው ምስጋና ምግብ ኾኗቸው እንዲኖሩ ያደረገውን ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የተካከለውን እግዚአብሔር ወልድን የድንግልና ጡቶቿንም ለማጥባት ከደቂቀ አዳም በብቸኝነት የተመረጠች ምልእተ ጸጋ የኾነች እመ ምሕረት፣ እመ ሕይወት፣ እመ መድኀኒት፣ እመ ጸባኦት፣ እመ ቃል ርሷ ፈጽሞ ጥንተ አብሶ (ጥንተ በደል) ያስከተለው የምልአተ ኀጢአት ፍዳ የለባትም፤ እንኳን የአምላክ እናት ይቅርና ለወዳጆቹ ማደሪያነት የሚያወርሳት መንግሥተ ሰማያት እንኳ ጸያፍና ርኲሰት የሌለባትና የማይቀላቀልባት እንደኾነ ዮሐንስ በራእዩ ላይ “ለበጉም በኾነው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት በቀር ጸያፍ ነገር ኹሉ ርኵሰትና ውሸትም የሚያደርግ ወደ ርሷ ከቶ አይገባም” በማለት አስተምሯልና (፩ዮሐ ፫፥፭-፮፤ ራእ ፳፩፥፳፯)፡፡
ይኽ ቅድስት ድንግል ማርያም እውነትን ከሚያውጀው ከቅዱስ ገብርኤል ለመዠመሪያ ጊዜ የሰማችው “ጸጋን የተመላሽ” የሚለው ቃል ቅድስት ድንግል ማርያም በጥንተ አብሶ ምክንያት ወደ ሰው ልጆች ከመጣው ከምልአተ ኀጢአት መርገም በእግዚአብሔር ጸጋ ከእናቷ ማሕፀን ዠምራ የተጠበቀች ጥንተ በደል ፈጽሞ ያልደረሰባት እንደነበረች የሚያስረዳ ሲኾን ይኸውም አስቀድመው የሰው ዘር መገኛዎች የነበሩት አዳምና ሔዋን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አፍርሰው የእባብን ምክር ሰምተው ዕፀ በለስን በመብላታቸው ምክንያት ጸጋቸው እንደተገፈፈ በዘፍ ፫፥፯ ላይ ስናነብብ “እነርሱም ዕራቁታቸውን እንደ ኾኑ ዐወቁ የበለስንም ቅጠሎች ሰፍተው ለእነርሱ ለራሳቸው ግልድም አደረጉ” ይላል ከዚያም እግዚአብሔር “አዳም ወዴት ነኽ?” ባለው ጊዜ አዳም ለአምላኩ “በገነት ድምፅኽን ሰማኊ ዕራቁቴንም ስለ ኾንኊ ፈራኊ ተሸሸግኹም” በማለት ጸጋው ተገፍፎ ዕርቃኑን እንደ ቀረ ተናግሯል (ዘፍ ፫፥፲)፤ በዚኽም የአዳምና የሔዋን ስሕተት ምክንያት የሰው ልጆች ከጸጋቸው ተራቁተው “ኹላችን እንደ ርኲስ ሰው ኾነናል፤ ጽድቃችንም ኹሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤ ኹላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል፤ በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል” (ኢሳ ፷፬፥፮) በሚሉበት ምልአተ ኀጢአት የሰውን ልጆች በመላ እንደ ደመና በከበበበት ዘመን ቅድስት ድንግል ማርያም ግን ምንም ዐይነት የጸጋ ጒድለት የሌለባት አስቀድሞውኑ ከእናቷ ማሕፀን ዠምሮ በመንፈስ ቅዱስ የተጠበቀች በመኾኗ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል “ጸጋን የተመላሽ ሆይ” አላት እንጂ “ወደ ፊት ይመላብሻል” አላላትም፤ በዚኽም እውነተኛ ምስክርነቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥንተ አብሶ ባመጣው የጸጋ መራቈት ውስጥ ነበረች የሚሉ የክሕደት ትምህርቶችን ሙሉ በሙሉ አጥፍቷቸዋል (ሉቃ ፩፥፳፰)፡፡

ዳግመኛም ቀዳማዊዉ አዳም መርገም ካልደረሰባት ከኅትምት ምድር እንደተገኘ ኹሉ ክብር ይግባውና ዳግማይ አዳም የተባለ ኢየሱስ ክርስቶስም ጥንተ መርገም ካልደረሰባት ከድንግል በኅቱም ድንግልና ተወልዷል፡፡ በተጨማሪም ቀዳማዊቷ ሔዋን ከአዳም ጐን ስትገኝ ምንም ጥንተ መርገም እንዳላገኛት፤ ዳግሚት ሔዋን የተባለች ቅድስት ድንግል ማርያምም ስትፀነስ ኾነ ስትወለድ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ምልእተ ጸጋ ነበረችና ጥንተ መርገም አላገኛትም፡፡ ሰው ኹሉ በበደል ጒድጓድ በወደቀበት ጊዜ ቅድስት ድንግል ማርያም ብቻ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ከእናቷ ማሕፀን ዠምራ ከጥንተ መርገም የተጠበቀች ናትና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ “ጸጋን የተመላኽ” የተባለ ወይም “ጸጋን የተመላሽ” የተባለች ከቅድስት ድንግል ማርያም በቀር ማንም የለም፡፡
“ስለ ንጽሕናዋ በስፋት የተነተኑትን የሊቃውንት ምስክርነት”
በርካታ የቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን አባቶች ይኽነን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አብነት በማድረግ ሰፋ አድርገው ስለ ንጽሕናዋ ስለ ቅድስናዋ ጽፈዋል፡- ይኽን ጽሑፋቸውን ሙሉ በሙሉ “ነገረ ማርያም በሐዲስ ኪዳን” በሚለው ባሳተምኩት መጽሐፍ ላይ ስለጻፍኩት መጽሐፉ ላይ ማንበብ ስትችሉ፤ ለፌስ ቡክ አንባቢዎች ግን በጥቂቱ ከመጽሐፉ ላይ ምስክርነታቸውን አስቀምጬዋለኊ፡፡
► (…ንጹሕና ያልተነካች ድንግል…የተከበርሽ የተደነቅሽ ድንግል ሆይ በእውነት አንቺ ከማንኛውም ሌላ ታላቅነት የበለጥሽ ነሽ፤ የቃለ እግዚአብሔር ማደሪያ ከኾንሺው ካንቺ ጋር ማን በእኩልነት ይወዳደራል?፤ ድንግል ሆይ ከፍጥረታት ኹሉ አንቺን ከማን ጋር ላነጻጽርሽ?፤ በቃል ኪዳን ከኹሉም በላይ የኾንሽ ሆይ በወርቅ ፈንታ ንጽሕናን የተጐናጸፍሽ አንቺ እውነተኛውን መና የያዘችውን የወርቅ መሶብ ነሽ ይኸውም መለኮት የተዋሐደው ሥጋ ነው) ቅዱስ አትናቴዎስ (፪፻፺፭–፫፻፸፭ (295-375) ዓ.ም)
► “ሰላምታ የተገባሽ ምልእተ ጸጋ ሆይ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ የተባረክሽ ነሽ (ሉቃ ፩፥፳፰)፤ ከሴቶች ኹሉ በእጅጉ የተዋብሽና በጣሙኑ የተቀደስሽ ነሽ፤ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው፤ ከኹሉም በላይ ቅድስት የኾንሽ ሆይ የተከበርሽና ጥሩ ነሽ፤ ጌታ ከአንቺ ጋር የኾነ ውዳሴ የተገባሽ ሆይ ተወዳዳሪ የለሽም፣ ከሞገስ በላይ የኾንሽ ሆይ ኹሉ የተትረፈረፈልሽ እግዚአብሔር ያከበረሽ ምስጋና ኹሉ ይገባሻል (ሉቃ ፩፥፵፱)… የእግዚአብሔር ማደሪያው፤ መለኮት የጠበቀሽ የተከባከበሽ ሀብት ነሽ፤ በአንቺም ውስጥ በኀጢአት ውስጥ መፅነስን ወይም በኀጢአት ውስጥ መውለድን በጭራሽ አላውጅም፤ በዚኽ ፈንታ የሔዋንን ሐዘን እንዲበቃ ያደረገው ደስታን አምጥቼያለኊ እንጂ፤ በአንቺ የመከራ ፅንስን ወይም ሕማመ ወሊድን አላውጅም… ንጽሕት፣ ድንግል፣ ነውር የሌለባት፣ ያለነቀፋ የኾነች፣ ምንም ያልነካት፣ ሕጸጽ የማይገኝባት በሥጋም በነፍስም ቅድስት፣ በእሾኽ መኻከል እንደበቀለች አበባ ናት (መሓ ፪፥፩)፤ የሔዋንን ክፋት የማታውቅ፣ የሴትነት ጠባይ ያልታየባት፣ ከመፅነሷ በፊት ለፈጣሪ የተለየች፣ የቤተ መቅደስ እንግዳ፣ የሕግ ደቀ መዝሙር የኾነች፣ በመንፈስ ቅዱስ የተቀባች፣ የመለኮትን ጸጋ እንደ ልብስ የለበሰች” ቅዱስ ቴዎዶጦስ (†፫፻፫ (303) ዓ.ም

► “የማርያም ሰውነት የምድር ላይ መቅደስ ነው፤ በርሱም በኀጢአት በሞት በምድር ርግማን ፈንታ የበረከት ዘር የተዘራበት የእግዚአብሔር መልእክተኛ በሰላምታው ይኽነን ዘር ሲዘራ የኤልሳቤጥም ሰላምታ ይኽነን አረጋገጠ…አንተ እና እናትኽ ብቻ በማንኛውም ረገድ ንጹሕ ናችኊ፤ ጌታ ሆይ በአንተ ውስጥ ምንም ነቅዕ የለም፤ በእናትኽም ውስጥ ምንም ምልክት የለም” (ቅዱስ ኤፍሬም ፫፻፮-፫፻፸፫ (306-373 ዓ.ም)

► “ማርያም ቅድስት ድንግል በእግዚአብሔርና በሰዎች ፊት በእውነትም ክብርት ናት፤ ሰማይና ምድር ሊሸከሙት የማይቻላቸው ርሱን የተሸከመች የርሷን ታላቅነቷን ስለምን አናውጅም… ጌታን የሚያከብር ኹሉ የጌታ የተቀደሰ ማደሪያውን ያከብራል፤ ማደሪያውን የማያከብር (የሚያቃልል) ጌታውን ያቃልላል (አያከብርም)፤ ርሷ ድንግል የተቀደሰ ማደሪያው ነች” (ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ፫፻፲-፬፻፫ (310-403 ዓ.ም)

► “መዠመሪያውኑ (ጥንቱኑ) በመንፈስ በሥጋዋና በነፍሷ ንጽሕት ከተደረገችው ድንግል ተፀንሶ ነበር፤ ይኽነን ሕፃን በማሕፀኗ በመሸከሟም የተነሣ ክብርን የተቀበለች ናት፤ ስለዚኽ ድንግልና በጣም የበለጠ ክብርን መጐናጸፏ በጣም አስፈላጊ ነው” (ቅዱስ ጎርጎሬዎስ ዘእንዚናዙ)

► “በእውነት ርሷ ብቻ ማንም ሊያገኘው ያልቻለውን ጸጋ በብቸኝነት አግኝታለችና “ምልእተ ጸጋ” (ጸጋን የተመላች) ትባላለች፤ ያውም በጸጋው ባለቤት የተመላ…ማርያም ድንግል ያልረከሰች ብቻ ሳትኾን ክብሯ ከቶ የማይጣስና ከማንኛውም የኀጢአት ቅንጣት የነጻች ናት…ከእግዚአብሔር እናትነት የበለጠ ምን ታላቅ ነገር አለ? በክቡሩ በራሱ ከመረጣት በላይ ምን ታላቅነት ይኖራል? ከማንኛውም ሰው አካል ጋር ሳትደርስ ከፀነሰችው ከርሷ በላይ ምን ንጹሕነት አለን?” (ቅዱስ አምብሮስ ፫፻፴-፫፻፺፯ (330-397 ዓ.ም)

► “ከዕሴይ ግንድ በትር ትወጣለች ከሥሩም አበባ ያፈራል (ኢሳ ፲፩፥፩)፤ በትሯም የጌታ እናት፣ ንጽሕት፣ ፈጽሞ ያልረከሰች፣ ያለምንም ጾታዊ ግንኙነት በብቸኝነት ልክ እንደ እግዚአብሔር አብ ፍሬን ያፈራች (ርሱ ያለእናት እንደወለደው ርሷም ያለአባት የወለደችው)…ከተባረከችው ማርያም ፊት፤ እጅግ ከፍተኛ የኾነ ንጽሕናዋ የጌታችን እናት እንድትኾን አደረጋት…ንጽሕናዋ በጣም ታላቅ የነበረ በመኾኑ የጌታችን እናት ለመኾን ታጨች፤ ሌሎች በርግጥ የጌታችን እናት ከኾነችው ከቅድስት ድንግል ማርያም በቅድስናቸው እጅጉን ምን ያኽል ያንሱ ይኾን” (ቅዱስ ጀሮም ፫፻፵፯-፬፻፳ (347-420 ዓ.ም)

► “ሰላምታ የተገባሽ ማርያም፣ የአምላክ እናት፣ ድንግልም እናትም፣ ብርሃንን የተሸከምሽ፣ ያልተመዘበረች ንዋይ (ልሕኲት)… ሰላምታ የተገባሽ ማርያም ከመላው ዓለም ኹሉ እጅግ በጣም ውድ ፍጥረት አንቺ ነሽ፤ ሰላምታ የተገባሽ ማርያም ንጽሕት ርግብ፣ ማለቂያ የሌላት የማትጠፋ ፋና ከአንቺም የፍርድ ፀሓይ ተወለደ (ሚልክ ፬፥፪)፤… በፍጹም መንፈሳዊ ቅናት በአምላክ እናት ድንግልም እናትም በኾነች በማርያም ተጋብዘው የተሰበሰቡ የቅዱሳንን ጉባኤ እነሆ አያለኊ… እኛም ሰላም እንልሻለን የእግዚአብሔር እናቱ የኾንሽ ማርያም ሆይ የመላው ዓለም የተከበርሽ ቅርስ፣ የማትጠፊ ፋና፣ የድንግልና ዘውድ፣ የኦርቶዶክስ (የቀናችው እምነት) ምርጉዝ በትር፣ የማትፈርሺ መቅደስ፣ ማንም ሊይዘው ሊሸከመው የማይችለውን ርሱን የያዝሽው ነሽ) (ቅዱስ ቄርሎስ ፫፻፸፮-፬፻፵፬ (376-444 ዓ.ም)

► “አኮ እምብዙኃን መናፍስት ዘይትቀድሓ ብዙኃት ሀብታተ እግዚአብሔር ወመክፈልተ ሠናያት አላ እምአሐዱ መንፈስ ውእቱኬ ጰራቅሊጦስ ዘዐቀባ ለድንግል እምከርሠ እማ ከመ ኢትጌጊ ለዓለም፤ አንጽሓ ከመ ኢትርሳሕ፤ ቀደሳ ከመ ኢትርኰስ፤ ወረሰያ ታቦተ ለወልድ ዋሕድ፤ አብ ሠምራ ወልድ ተሠገወ እምኔሃ ወመንፈስ ቅዱስ ከለላ” (ብዙዎች የሚኾኑ የእግዚአብሔር ሀብቶች በጎዎች ዕድሎችም የሚቀዱ ከብዙዎች መናፍስት አይደለም፤ ከአንድ ከመንፈስ ቅዱስ እንጂ፤ ያውም እስከ ዘላለሙ ድረስ እንዳትበድል ከእናቷ ማሕፀን ዠምሮ ድንግል ማርያምን የጠበቃት ጰራቅሊጦስ ነው እንዳትተዳደፍ አነጻት፤ እንዳትረክስም ቀደሳት፤ ለአንዱ የእግዚአብሔር ልጅ ማደሪያን አደረጋት፤ አብ ወደዳት፤ ወልድም ከርሷ ነፍስንና ሥጋን ነሣ፤ መንፈስ ቅዱስም ጋረዳት) (አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ፲፫፻፶፮‐፲፬፻፲፯ (1336-1417) ዓ.ም)

የመንፈስ ቅዱስ እንዚራ የተባለው ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግም ከመርገመ ሥጋ ከመርገመ ነፍስ የተለየች ምልእተ ጸጋ ስለመኾኗ በመጽሐፉ ላይ ሲተነትነው “This deed which took place in her gave me power…” (ይኽ በርሷ ውስጥ የተከናወነው ሥራ ብርታት ስለሰጠኝ፤ ስለማይሻር ውበቷ እነዚኽን ነገሮች ልናገር ችያለኊ፤ ርሷ የእግዚአብሔርን ልጅ እናት በመኾኗ ምክንያት፤ በዚኽ ምድር ፍጹም ንጽሕት የኾነች ብቸኛዋ ሴት ርሷ እንደኾነች አይቼ ጠንቅቄ አምኛለኊ፤ መልካሙን ከክፉው መለየት ካወቀችበት ጊዜ ዠምሮ፤ ርሷ በልብ ንጽሕና እና በሐሳብ እውነተኛነት ጸንታ ቆማለች፤ በሕጉ ውስጥ ካለው ጽድቅ ፊቷን አላዞረችም፤ ምድራዊዉንና ሥጋዊዉን ነገር መሻትም አላሰናከላትም፤ ከሕፃንነቷ ዠምሮ የቅድስና ባሕርያት በውስጧ ነበሩ፤ ከፍ ባለችም ጊዜ እነዚኽን አጥብቃ በጥንቃቄ አብዝታለች፤ አምላኳ ኹልጊዜ በፊቷ (ከዐይኖቿ ፊት) ነበር፤ በርሱ ይበራላት ዘንድ በርሱም ደስ ይላት ዘንድ ዐይኖቿን ከርሱ አላነሣችም፤ ርሱም ንጽሕናዋን እና የነፍሷን ንጽሕና ስላየ፤ አንዳች ክፋትም (ክፉ ነገርም) ስላልነበራት በርሷ ያድር ዘንድ ወደደ፤ እንደርሷ ያለች አንድም ሴት ታይታ ስለማይታወቅ፤ ከሥራዎች ኹሉ በላይ ታላቅና ድንቅ የኾነ ሥራ በርሷ ውስጥ ተሠራ፤ ከሴቶች ኹሉ መኻከል አንዲት ብላቴና ተፈለገች፤ ከኹሉም በላይ መልካም የኾነችውም ተመረጠች፤ ቅዱስ አብ ለልጁ እናት የምትኾን ሊያዘጋጅለት ፈለገ፤ ነገር ግን ርሱ ስለመረጣት ብቻ እናቱ እንድትኾን አልፈቀደም፤ በውስጧና በዙሪያዋ በተሰወረ ውበት የተመላች ብላቴና ልጅ፤ እንዲኹም በርሷ ውስጥ የተከሠቱትን ምስጢራት ልታይ ያስቻላት የልብ ንጽሕና የነበራት፤ አንዲት ብላቴና ወድዳና ፈቅዳ ውበት ሲኖራት፤ ያ ነው እውነተኛው ውበት ፍጽምትነቷ በፈቃዷ ሲኾን፤ የአንድ ከእግዚአብሔር የኾነ ነገር ውበት ምንም ያኽል እንኳ ታላቅ ቢኾን፤ ነጻ የኾነ የግል ፈቃድ በውስጡ ከሌለ ምስጉንነት የለውም፤ ፀሓይ ውብ ብትኾንም የሚመለከቷት ግን አያመስግኑዋትም፤ ምክንያቱም ብርሃኗን የምትሰጠው ወድዳና ፈቅዳ እንዳልኾነ ስለሚታወቅ ነው፤ በገዛ ፈቃዱና በውዴታ ውብ የኾነና ውበት ያለው ኹሉ፤ በእውነት ውብ እስከኾነ ድረስ ከዚኽ የተነሣ ብቻ ርሱ እውነትም ምስጉን ነው፤ እግዚአብሔርም የሚወድደው ውበት ከራስ ፈቃድ የኾነውን ነው፤ ርሱን ደስ የሚያሰኝ ሲኾን አንድን መልካም ፈቃድ ርሱ ያከብራል፤ እነሆ ታሪኳን እየተናገርን ያለነው ይኽቺ ድንግል፤ መልካም ፈቃድ ስለነበራት ደስ የምታሰኝና የተመረጠች ኾናለች፤ ሰው በኾነች ሴት ልጅ በኩል ርሱ ሰው ኾኖ መጣ፤ ደስ የምታሰኝ ስለነበረች ከርሷ ይመጣ ዘንድ ርሷን መረጣት፤ የርሱ ግርማ ከሰው ከሚወለዱት ኹሉ ግርማ ይልቅ ታላቅ ስለኾነ፤ እናቱ የኾነችው የማርያም ውበትም እጅግ የላቀ (የተወደሰ) ይኾናል፤ ደስ የምታሰኝና ለርሱ ምርጥ የኾነችው፤ ከትሕትናዋ፣ ከንጽሕናዋ፣ ከቀናነትዋ፣ እና መልካም ከኾነው ፈቃድዋ የተነሣ ነው፤ ከርሷ በላይ ደስ ያሰኘችው ሌላ ብትኾን ኖሮ ሌላኛዪቱን ይመርጣት ነበር፤ ርሱ ቅን ፈታሒ እና ትክክለኛ ስለኾነ አምላክ ግለሰቦችን (ለይቶ) አያከብርምና (፪ ዜና ፲፱፥፯፤ የሐዋ ፲፥፴፬)፤ አንድስ ስንኳ እንከን ወይም ጒድለት በነፍሷ ተገኝቶ ቢኾን ኖሮ፤ ሌላ እንከን የማይገኝባት እናት ለራሱ በፈለገ ነበር፤ ከውበት ኹሉ በላይ እጅግ የላቀው ይኽ ውበት፤ በመልካም ፈቃዷ ባገኘችው ብቻ ውስጥ የሚኖር ነው፤ ከዚኽ የተነሣ ኹሉም ክብርት (ግርምት) በኾነችው በርሷ መደነቁ ትክክለኛ ነው፤ አምላክ እንኳ እናቱ አድርጎ እንዲመርጣት ያደረገው እጅግ ደስ የምታሰኝ መኾንዋ ነበረና፤ ለተፈጥሮ በተሰጠው ውበት መጠን ልክ ርሷ ደስ የምታሰኝ ነበረች፤ ነገር ግን ለዚኽ ደረጃ የበቃችው በርሷ ፈቃድ ብቻ አልነበረም፤ ርሷ ለሰው የሚቻለውን ያኽል ጥረት አደረገች፤ አምላክ ከርሷ መውጣቱ (መወለዱ) ግን የርሷ ሥራ አልነበረም፤ ርሷ በቅንነቷ ወደ አምላክ በተጠጋች መጠን፤ ከነፍሷ መሻት የተነሣ ርሱም በቸርነቱ ወደርሷ ተጠጋ፤ ነገር ግን አምላክ ሥጋ ለብሶ ከርሷ መወለዱ ያ የርሱ ጸጋ (ቸርነት) ነው፤ እንዲኽ ለበዛው ምሕረቱ ምስጋና ይድረሰው! የእመቤታችን ማርያም ውበት ከስፍር (ከመጠን) ያለፈ (በላይ) ነው፤ (ምክንያቱም) ከርሷ የምትበልጥ ሌላ በዓለም ኹሉ አልተገኘችምና፤ ከዚኽ በኋላ ለርሱ የሚገባውን ለአምላክ እንስጥ፤ ጸጋውን ያለልክ በፍጥረታት ላይ አዝንቧልና፤ ዘመናት ኹሉ ለርሱ የማይበቁትን ብሉየ መዋዕል ወልድን ያመጣውን ርሱን ዕንወቀው፤ ከእናቶች ኹሉ መኻል አቻ ያልተገኛላትን እመቤታችን ማርያምን ያበጃትንም እንረዳው) ሲል የንጽሕናዋን ታላቅነትና በአምላክ የመመረጧን ነገር በስፋት ገልጾታል፡፡

በእጅጉ የሚገርመው ያለምንም የነገረ መለኮት ዕውቀት ዛሬ በጭፍኑ አንዳንድ ፕሮቴስታንቶች የካዱትን ይኽነን እውነታ የፕሮቴስታንት እምነትን የመሠረተው በጣም ብዙ የስሕተት ትምህርትም በምድራችን ላይ የዘራው ከ፲፬፻፹፫-፲፭፻፵፮ (1483-1546) ዓ.ም የነበረው ማርቲን ሉተር እንኳ ደፍሮ አላስተማረውም፤ ይልቁኑ ቅድስት ድንግል ማርያም አስቀድሞዉኑ ከጥንተ አብሶ ነጻ ስለመኾኗ በስብከቱና በመጽሐፉ ሲገልጽ፡- “It is a sweet and pious belief that the infusion of Mary’s soul was effected without original sin…” (የማርያም ነፍስ ከሥጋዋ በተወሐደች ጊዜ ከኀጢአት ፍጹም የነጻችና ጥንተ አብሶ የሌለባት፤ በእግዚአብሔር ጸጋ ያጌጠች ንጽሕት ነፍስ ኾና ነበር ከእግዚአብሔር ጋር የተዋሐደች ንጽሕት ነፍስን ተቀብላ (ገንዘብ አድርጋ) ነበር፤ በዚኽም ድንግል ለመኖር ከዠመረችበት ጊዜ (ከፅንሰቷ) ዠምሮ ከኀጢአት ኹሉ የነጻች ኾነች፤ ይኽነን ማመንም ጣፋጭ ነው… ማርያም የእውነት እናቱ ናት፤ ርሱም የእውነት ልጇ ነው፤ ስለዚኽ የርሷ ሰውነት ለባሕርዩ የሚስማማውን የእናትነት ድርሻ ተወጥቷል፤ ነገር ግን የፀነሰችውም ያለ ኀጢአት ስለኾነ ስትወልደውም ያለ ኀፍረት ያለ ምጥ ያለ ሕማመ ወሊድ ያለ ተፈትሖ ነው፤ እግዚአብሔር “በጭንቅ ትወልጃለሽ” ብሎ ለሔዋን የተናገረው መርገም ርሷን አልነካትም (ዘፍ ፫፥፲፮)) በማለት ገልጾ አስተምሮና ጽፎ ነበር (Sermon on the Day of the Conception of Mary, Mother of God, 1527)፡፡

በተጨማሪም ከ፲፱፻፳፩-፲፱፻፺፮ (1921-1996 ዓ.ም) ድረስ የነበረው የካልቪኒስት እምነትን በማስፋፋት በዓለም የሚታወቀው የካቶሊክ ቄስም የነበረው ማክስ ቱሪያን (Max Thurian) በመጽሐፉ ላይ ልክ እንደ ሉተር ኹሉ ርሱም ሊካድ ፈጽሞ የማይቻለውን የቅድስት ድንግልን ፍጹም ንጽሕና ሊክድ አልሞከረም፤ ይኽነንም ሲገልጸው “As far as [Mary] is concerned, according to the Gospel,…” (ማርያምን በተመለከተ እንደ ወንጌሉ አነጋገር ርሷ የጸጋ ሙላቱ ማሳያ ናት እንዲኹም እናቱን አስቀድማ የታቀደች ዕድፍን የማታውቅ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌም አድርጎ መርጧታል፤ ይኽ ሐሳብ ስለማርያም ልንል የምንችለውን ኹሉ የሚገልጥልን ሐሳብ ነው ይኽም ማለት በአንድ በኩል ማርያም ኀጢአት እንዳለባት ለመናገር የሚዳዳቸውን በሌላም በኩል ርሷ ከሰው ባሕርይ ፍጹም የተለየች እንደኾነች የሚናገሩትን ጭምር አፍ የሚያስዘጋ ነው፤ ጸጋን የተመላች፣ የጽዮን ሴት ልጅ፣ ሥጋን የተዋሐደ የአምላክ እናት፣ የእናት ቤተ ክርስቲያን ምሳሌ የኾነች ድንግል ማርያም ቅድስት ናት) ብሎ አስተምሯል (Mary, Mother of All Christians, page 204 [endnote], and page v 24, 25, from the chapter “Full of Grace”)፡፡

ኡልሪች እዝቪንጊሊም ንጽሕት መኾኗን በጻፈው መጽሐፍ ላይ ሲገልጽ “He who was about to remove our sins but not to make all men holy” (ኹሉን ሰው ቅዱስ ለማድረግ ሳይኾን ኀጢአታችንን ሊያስወግድልን ያለው ርሱ ራሱ ቅዱስ መኾን አለበት፤ ስለዚኽ እግዚአብሔር እናቱን ቀደሳት ምክንያቱም ቅዱስ ልጅ እንደርሱ ቅድስት የኾነች እናት ሊኖረው ይገባልና ነው፤ ኹሌም ድንግል የኾነች የድኅነታችን እናት ማርያምን በተመለከተ ክብር የሚያሳጣ፣ የሚያጐድፍ ወይም ክፋት የመላው ዐሳብ ዐስቤም ኾነ በይፋ ተናግሬ አላውቅም፤ አኹንም አላስብም፤ ይኽ ተጠራጣሪዎችና ጥልቀት ለሌላቸው ክርስቲያኖች የአምላክን እናት በተመለከተ ያለኝን ጥርት ያለ አቋም ለማሳየት በቂ እንደኾነ ተስፋ አደርጋለኊ፤ በቅዱስ ወንጌል ቃል መሠረት በሙሉ ልቤ ይኽቺ ንጽሕት ድንግል የአምላክን ልጅ እንደወለደችልንና በልደትም ኾነ ከዚያ በኋላ ለዘላለሙ ንጽሕት እና ያልረከሰች ኾና የቆየች መኾኗን አምናለኊ) በማለት ስለ ንጽሕናዋና ስለ ዘላለማዊ ድንግልናዋ በስፋት ገልጾ ነበር፡፡

በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩት ሪፎርመሮች (ፕሮቴስታንቶች) ራሳቸው የቅድስት ድንግል ማርያምን ከጥንተ አብሶ ንጽሕት መኾን ገልጸው እንደነበር መጥቀስ ካስፈለገ ከ (1504-1575) ዓ.ም የዝዊንግሊ ተከታይ የነበረው ሄንሪች ቡሊንገርም ስለዚኽ ነገር ሲገልጽ “What pre-eminence in the eyes of God the Virgin Mary…” (ከሌሎች ቅዱሳን ጋር ለማነጻጸር የምትከብድና በእጅጉ ከእነርሱ በላይ ትኾን ዘንድ የተገባት የድንግል ማርያም ንጽሕናዋ፣ እምነቷ፣ ቅድስናዋ፣ ከጒድፍ የነጻች መኾኗና መልካም ጠባይዋ ምንኛ በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ ነው … ከልደቷ ዠምሮ ንጽሕት የነበረችው የንጽሕና ቡራኬን የተቀበለች … የአምላክ እናት የመንፈስ ቅዱስ መቅደስ፣ አካሏ ንጹሕና ኀጢአት አልባ የኾነው የድንግል ማርያም የተቀደሰ ሰውነቷ በመላእክት ወደ ሰማይ እንዳረገ እናምናለን) በማለት ገልጾ ነበር (Heinrich Bullinger, cited in Thurian, page 89, 197, 198)፡፡

በፈረንሳይ ሀገርም እምነቱን ካስፋፉት ሰዎች መኻከል በጣም የሚታወቀው ከ1595-1669 ዓ.ም የነበረው ቻርልስ ድሬሊንኮርትም “We do not simply believe that God…” (እግዚአብሔር ድንግል ማርያምን ከአባቶችና ከነቢያት በላይ እንደመረጣትና እንደባረካት ብቻ ሳይኾን ከሱራፌልም በላይ ከፍ ከፍ እንዳደረጋት እናምናለን፤ መላእክት የእግዚአብሔር ልጅ አገልጋዮችና የእጁ ሥራ ውጤት ፍጥረቶቹ ናቸው፤ ድንግል ማርያም ግን አገልጋዩ ብቻ ሳትኾን የዚኽ ሕያው አምላክ እናት ናት) (Charles Drelincourt (1595-1669), cited in Thurian, page 89) በማለት ጽፎ ነበር፡፡

ዛሬ ደግሞ በሚገርም መልኩ የእምነቱ ተከታዮች በተቃራኒው እንዲኽ ብለው መናገራቸው ምናልባት በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እምነቱን የመሠረቱላቸው ሰዎች ያስተማሩትን ትምህርት እንኳ አላነበቡም? ወይም ጭራሹኑ አያውቁ ይኾንን? ወይስ ሐዋርያው “የማያውቁትን ኹሉ ይሳደባሉ” ብሎ እንደተናገረው የአምላክን ማደሪያ ሊሰድብ አፉን የከፈተውን የዘንዶውን ትምህርት ለማስፋፋት ይኾንን? (ራእ 13፡4-6) መልሱ ምንም ይኹን ምን ንስሓ ገብተው የቀናውን እምነት ተከትለው እንዲጓዙ የመጽሐፉ አዘጋጂ ምክር ነው፡፡
ምንጭ፡- ነገረ ማርያም በሐዲስ ኪዳን የሚለው መጽሐፌ ሙሉውን ከመጽሐፌ አንብቡ
መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሐዲስ ኪዳን መምህር

«መሠረቶቿ የተቀደሱ ተራሮች ናቸው» /መዝ. ፹፮፥፩/

ልበ አምላክ የተባለ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት «መሠረቶቿ የተቀደሱ ተራሮች ናቸው» ያላትም እርሷን ነው። /መዝ. ፹፮፥፩/። የተቀደሱ ተራሮች የተባሉ የእመቤታችን ወላጆችና ቅድመ አያቶች ሲሆኑ እኒህም እነ ኖኅ እና አብርሃም ናቸው። እነዚህ ሁሉ ቅዱሳን ናቸውና። ኢያቄምና ሐናም ከተቀደሱት ተራሮች መካከል ሲሆኑ የእመቤታችን አባትና እናትም ናቸው። ሁለቱም በተቀደሰ ጋብቻ ጸንተው ቢኖሩም መካን በመሆናቸው ያዝኑ ነበር። ይሁንና በስተእርጅና እግዚአብሔር ልጅ እንዲሰጣቸው ብፅዓት ገቡ። ብፅዓቱም «ወንድ ብንወልድ ወጥቶ ወርዶ አርሶ ቆፍሮ ነግዶ አትርፎ ይርዳን አንልም፤ ለቤተ እግዚአብሔር ጠባቂ አገልጋይ ይሁን እንጂ፣ ሴትም ብንወልድ እንጨት ሰብራ እንጀራ ጋግራ ውሃ ቀድታ ወፍጮ ፈጭታ ትርዳን አንልም፤ ለቤተ እግዚአብሔር ውሃ ቀድታ መሶበ ወርቅ ሰፍታ ትኑር እንጂ» የሚል ነው። እግዚአብሔርም የነገሩትን የማይረሳ የለመኑትንም የማይነሳ ቸር አምላክ ነውና ብፅዓታቸውን ፈጸመላቸው። በተቀደስ ጋብቻ ንጽሕት ቅድስት ልጅ አገኙ። ይህንንም የልደቷን ቀን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በደስታ ታከብረዋለች።

ስለእመቤታችን ቅዱሳን መጻሕፍት ምን ይላሉ?

ወላዲተ አምላክ ናት

«በእውነት ወደ ቤቴ ድንኳን አልገባም፤ ወደ ምንጣፌ አልጋ አልወጣም፤ ለጉንጮቼም ዕረፍትን አልሰጥም፣ ለእግዚአብሔር ሥፍራ፣ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያ እስከአገኝ ድረስ» /መዝ. ፻፴፩፥፫- ፭/። ዳዊት ይህን ሲናገር ሰማይ ዙፋኔ ነው ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት የሚለውን ረስቶ አይደለም። ልበ አምላክ ነውና። /ኢሳ. ፷፥፩/። ነገር ግን የያዕቆብ አምላክ ማደሪያ የእግዚአብሔር ሥፍራ የተባለች እመቤታችን ናት። ወልደ እግዚአብሔር ማኅፀኗን ዓለም አድርጎ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን አድሯልና። ስለዚህም ነው ነቢዩ ኢሳይያስ የእግዚአብሔር ከተማ የእስራኤል ቅዱስ የሆንሽ ጽዮን ይሉሻል ያለው። /ኢሳ. ፷፥፲፬/። ይህች ለዘላለም ማረፊያዬ ናት፤ መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ። /መዝ. ፻፴፩፥፲፬/። «በውስጧም ሰው ተወለደ» /መዝ. ፹፮፥፭/። ማኅፀኗን ዓለም ያደረገው እግዚአብሔር ሰው ሆነ። «ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል» / ኢሳ. ፱፥፮/። የተወለደው ሕፃን ኃያል አምላክ ስለሆነ እናቱም ወላዲተ አምላክ ትባላለች። «… ስለዚህም ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል» /ሉቃ. ፩፥፴፭/። «የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?» /ሉቃ. ፩፥፵፫/። ኪሩቤል መንበሩን ለመሸከም የሚርዱለትን /የሚፈሩትን/ እርሷ ፀንሳዋለች፣ አዝላዋለች፣ ጡቷንም አጥብታዋለችና ከኪሩቤልም የሚበልጥ የመወደድ ግርማ አለሽ አላት አባ ኤፍሬም።

የዘላለም ድንግል ናት

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሀልዮም በገቢርም /በሀሳቧም በሥራዋም/ ድንግል ናት። «ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስተውጭ ወደአለው ወደመቅደሱ በር አመጣኝ ተዘግቶም ነበር፤ እግዚአብሔርም ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም፣ ሰውም አይገባበትም። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል» /ሕዝ. ፵፬፥፩-፪/። ምሥራቅ የተባለች እመቤታችን ናት። በርም የተባለ ድንግልናዋ ነው። በተዘጋው በር /በድንግልና/ የገባው የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የተባለ መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። «እኅቴ ሙሽራ የተቆለፈ ገነት፣ የተዘጋ ምንጭ የታተመ ፈሳሽ ናት» / ኃ. ፬፥፲፪/። የተቆለፈ ገነት አላት በተከፈተ ገነት ቅዱሳን ጻድቃን ገብተው እንደሚኖሩበት በተቆለፈ ገነት ግን /ድንግልና/ መግባት የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ለማጠየቅ የተዘጋም ምንጭ አላት ምንም ትዘጋም /በድንግልና/ የሕይወት ውኃ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወልዳዋለችና።

ስግደት ይገባታል

«የአስጨናቂዎችሽም ልጆች አንገታቸውን ደፍተው ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ» /ኢሳ. ፷፥፲፬/። «ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኗ ውስጥ ዘለለ» /ሉቃ. ፩፥፵፩/። የእመቤታችን አክስት በማኅፀኗ የነበረው ፅንስ ለእመቤታችን የጸጋ፣ በማኅፀኗ ለነበረው ለጌታችን ደግሞ የአምልኮት ስግደት ሰግዷል። «ነገሥታትም አሳዳጊ አባቶችሽ ይሆናሉ። እቴጌዎቻቸውም ሞግዚቶችሽ ይሆናሉ፣ ግምባራቸውንም ወደ ምድር ዝቅ አድርገው ይሰግዱልሻል፣ የእግርሽንም ትቢያ ይልሳሉ።» /ኢሳ. ፵፱፥፳፫/።

 

አማላጃችን ናት

 

«የምድር ባለጠጎች አሕዛብ በፊትሽ ይማለላሉ» / መዝ. ፵፬፥፲፪/። «ይማለላሉ» ማለቱ ድንግል ሆይ በፊቱ ሞገስ አግኝተሻልና ከአምላካችን ከአምላክሽ ምሕረትን /ይቅርታን/ ለምኝልን እያሉ ይማፀናሉ ለማለት ነው። «በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ /ሞገስ/ አግኝተሻልና አትፍሪ።» /ሉቃ.፩፥፴/።

እግዚአብሔር ለእመቤታችን ከሰጣት ጸጋዎች መካከል አንዱ በፊቱ ቆማ ማማለድ መሆኑን እንገነዘባለን። ይህንንም ቃል የተናገረው ከእግዚአብሔር የተላከው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ነው። «የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም» /ዮሐ. ፪፥፫/። ከዚህ ጥቅስም ወረድ ብሎ ያለውን አባባል መነሻ በማድረግ «ከአንቺ ጋር ምን አለኝ» ብሏታልና አታማልድም አይባልም። ጌታ ይህን የተናገረው አታማልጅም ለማለት ቢሆን ኖሮ የለመነችውን ባላደረገላት ነበር። ቋንቋውም የእናትና የልጅ በመሆኑ ተግባብተውበታል። እንዲህ ማለቱም አንቺ ለምነሽኝ እንዳላደርግልሽ የሚያግደኝ ምን ጠብ አለኝ ለማለት ነው። አነጋገሩም ከእስራኤል ወገን ተወልዷልና የእነርሱን ዘይቤ የተከተለ ነው።

ለምሳሌ «የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ ከአንተ ጋር ምን አለኝ?» ይህንን ቃል የተናገረው ርኩስ መንፈስ /ጋኔን/ ቢሆንም ከአንተ ጋር ምን አለኝ ማለቱ መሳደቡ አይደለም። እንዲህ ብሎ

ሰይጣን እግዚአብሔርን አይሳደብምና። ትርጉሙም ወዳዘዝኸኝ እሄዳለሁ ብቻ አታሰቃየኝ ማለቱ ነው። /ማር. ፭፥፯/። «እርሷም ኤልያስን የእግዚአብሔር ሰው ሆይ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? … አለችው» /፩ኛ ነገ. ፲፯፥፲፰/። እንዲህ ማለቷ መሳድቧ አልነበረም። ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ ለማለት እንጂ። ልጇን እንዲያድንላት እየፈለገች አትሳደብምና። እንግዲህ ከእነዚህ አባባሎች የምንረዳው የእስራኤላውያን አዎንታዊ ንግግር መሆኑን ነው። ጌታችንም ለእመቤታችን ከዚህ የተለየ አልተናገረም።

የእመቤታችን ክብሯ

መትሕተ ፈጣሪ መልእልተ ፍጡራን /ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን በላይ/ ናት። «ለአንቺ የማይገዛ ሕዝብና መንግሥት ይጠፋል» /ኢሳ. ፷፥፲፪/። «በምድር ሁሉ ላይ ገዥዎች አድርገሽ ትሾሚአቸዋለሽ» /መዝ. ፵፬፥፲፮/። ከእነዚህ ጥቅሶች የምንረዳው እመቤታችንን የማያከብር፣ አማላጅነቷን የማያምን፣ የማይሰግድላትም ከእግዚአብሔር መንግሥት ዕድል ፈንታ ያጣል ማለትን ነው።

ስለነቃፊዎቿ

«ከአንቺ ጋር የሚጣሉትን እጣላቸዋለሁ» /ኢሳ. ፵፱፥፳፭/። እመቤታችንን የማያከብሩ ሁሉ አማላጅነቷንም የማያምኑ የሚጣሉት ከእርሷ ጋር አይደለም። ይልቁንም ከኃያላን ኃያል ከእግዚአብሔርም ጋር እንጂ።

ምስጋና ይገባታል

«መልአኩም ወደእርሷ ገብቶ ደስ ይበልሽ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፣ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፣ አንቺ ከሴቶች መካከል ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ አላት።» /ሉቃ. ፩፥፳፰/። «በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት በታላቅ ድምጽም ጮኻ እንዲህ አለች፣ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፣ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው።» /ሉቃ. ፩፥፵፩- ፵፪/። እንደ ኤልሳቤጥ እመቤታችንን ማመስገን የሚችለው ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ብቻ ነው። «እነሆም ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል።» /ሉቃ. ፩፥፵፰/።

እናታችን ናት

«ሰው እናታችን ጽዮን ይላል» /መዝ. ፹፮፥፭/። የሕያዋን ሁሉ እናት ተብላ የተጠራችው ሔዋን በአጠፋችው ጥፋት የሰው ዘር እናታችን ብሎ ለመጥራት የሚደሰትባትን እናት በማግኘቱ እናትነቷን ያመነባት ሁሉ ይናገረዋል። የእርሷ እናትነት ጽድቅን ለተራቡት ምግብ የሚሆነውን ለተጠሙትም መጠጥ የሚሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ያስገኘች በመሆኗ ከሴቶች ሁሉ የተለየ እናትነት ነው። እናት ለልጇ ወጥታ ወርዳ የሚበላውን እንድትሰጠው እመቤታችንም የአዳም ተስፋው እስኪሞላለት ድረስ ከመስቀሉ እግር አልተለየችም። እኛም እናትነቷን እስከመጨረሻው ሕቅታ ልናጸና ይገባል። በእናታችን በሔዋን የተነሣ እናቶች ምክንያተ ስሕተት መባላቸው ቀርቶ በእመቤታችን ምክንያት ደግሞ ምክንያተ ድኅነት ሆኑ። የቀደመችው ሔዋን ሞትን ቆርጣ ሰጠችን፣ ዳግማዊቱ ሔዋን እመቤታችን ግን ሕይወትን ወልዳ ሰጠችን፣ በሔዋን የተነሣ ከገነት ተባረርን፣ በድንግል ማርያም የተነሳ ግን ወደ ገነት ተመለስን፣ በሔዋን ስሕተት የሰው ልጅ በመበደሉ መላእክት ገነትን ዘግተው አስወጡን፣ እመቤታችን ጌታችንን ብትወልድ ግን ወደ እኛ መጥተው አብረውን ዘመሩ።

ስለዚህም ነው እመቤታችንን ከጌታ የማዳን ሥራ ነጥለን አናያትም የምንለው። ከቤተልሔም እስከቀራንዮ አብራው ነበረችና። እመቤታችን የጸጋ እናታችን ናት። ሰዎች ጸጋን ወጥተው ወርድው፣ ነግደው አትርፈው የሚያመጡት ሳይሆን እግዚአብሔር እንደሚያስፈልገን አውቆ በነጻ የሚሰጠን በረከት ነው። የሥላሴ ልጅነት ጸጋ ነው። እኛ አላመጣነውም ነገር ግን ተሰጠን። መንግሥተ ሰማያት ጸጋ ናት እኛ አልከፈትናትም ከፍቶ

ሰጠን እንጂ። ሰው ሆኖ መፈጠር ጸጋ ነው ታግለን አላገኘነውም፤ ተሰጠን እንጂ። ሥጋና ደሙ ጸጋ ነው እኛ አልተጋደልንበትም። ራሱ እንደሚያስፈልገን አውቆ ያለ እርሱም ሕይወት ስለሌለን ሰጠን እንጂ።

እመቤታችንም እንዲሁ የተሰጠችን የጸጋ እናታችን ናት። «እነኋት እናትህ» ብሎ በዮሐንስ አማካኝነት ሰጥቶናልና። /ዮሐ. ፲፱፥፳፯/። ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም የእመቤታችንን ስሟን የምትጠራው በዓላቷን የምትዘክረው እርሷንም የምታከብረው ይህን በመረዳት ነው። የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን።

አዘጋጅ፡- በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን

የአሜሪካ ማዕከል ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል ፳፻፬ ዓ.ም.

፩፦ “ የበኩር ልጅዋንም እስከምትወልድ ድረስ አላወቃትም፤” ማቴ ፩፥፳፭

ስለ እመቤታችን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ከመናገራችን በፊት፥እርሷ የእግዚአብሔር ብቻ ቤተመቅደስ፥ የ እግዚአብሔር ብቻ እናት፥ የእግዚአብሔር ብቻ ዙፋን፥ እንደሆነች ማመን ያስፈልጋል። ነቢዩ ሕዝቅኤል ይኸንን ታላቅ ምሥጢር በብሉይ ኪዳን ዘመን ኾኖ፥ዐረፍተ ዘመን ሳይጋርደው ተረድቶት ነበር። ያስረዳውም እግዚአብሔር ነው። እንዴት እንዳስረዳው ሲናገርም፦ “ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስተውጭ ወደ አለው ወደ መቅደሱ በር መለሰኝ፤ተዘግቶም ነበር።
እግዚአብሔርም አንዲህ አለኝ፥ይህች በር ተዘግታ ትኖራለች እንጂ አትከፈትም፤ ሰውም አይገባባትም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶባታልና ተዘግታ ትኖራለች፥ አለኝ” ብሏል። ሕዝ ፵፬፥፩-፪ ይህች፦ ሕዝቅኤል በመንፈሰ ትንቢት አሻግሮ ያያት፦ የተዘጋች፥ የታተመች፥ የተቈለፈች ምሥራቃዊት ቤተ መቅደስ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት። እግዚአብሔር ለነቢዩ ለሕዝቅኤል እንደነገረው ሰው ከቶ ሊገባባት የማይቻለው የእግዚአብሔር ብቻ ልዩ ቤተ መቅደስ ናት። እርሱ ብቻ ሳይከፍት ገብቶ ሳይከፍት ወጥቷል። (በድንግልና እንድትጸንሰው በድንግልናም እንድትወልደው አድርጓል)። ቅዱስ ዳዊትም፦ በጾምና በጸሎት የተገለጠለትን ምሥጢር ሲናገር፦ “እግዚአብሔር ጽዮንን (ለሥጋም ለነፍስም፥ ለጻድ ቃንም ለኃጥአንም መጠጊያ የምትሆን ድንግል ማርያምን) መርጦአታልና፥ ማደሪያውም (እናቱ፥ዙፋኑ፥መቅደሱ) ትሆነው ዘንድ ወድዶአታልና ፥ይህች ለዘለዓለም ማረፊያዬ ናት፤ መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ አለ፤” ብሏል። መዝ ፻፴፩፥፲፫-፲፬። እግዚአብሔር ለነቢዩ ለዳዊትም እንደነገረው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክ ማኅደርነት እስከምት ወልደው ድረስ ብቻ አልነበረም ምክንያቱም እግዚአብሔር ራሱ፦ “ይህች ለዘዓለም ማረፊያዬ ናት፤” ብሎአልና ነው። በመሆ ኑም በድንግልና እንደፀናች ለዘለዓለም ወላዲተ አምላክ ስትባል የምትኖር እንጂ ወደ ወላዲተ ሰብእነት የምትመለስ አይደለችም።
፪፦ በኲር፤
በኲር የሚባለው በመጀመሪያ የሚወለድ ነው። ተከታይ ልጅ ኖረውም አልኖረውም፥ በመጀመሪያ የሚወለድ የሰውም ሆነ የእንስሳት ልጅ በኲር ይባላል። ብኲርና ታላቅ በመሆኑ፥ የበኲር ልጅ ርስት (ሀብት፤ንብረት) ሲካፈል የሚደርሰው ሁለት እጥፍ ነው። ዘዳ ፳፩፥፲፭-፲፯። በወንድሞቹም ላይ ጌታ ነው፡፡ ዔሳው ብኲርናውን አቃልሎ፥ ለወንድሙ ለያዕቆብ በምሥር ንፍሮ ለውጦ፥ በረከትን በማጣቱ፥ “አባቴ ሆይ፥ ለእኔ በረከትን አላስቀረህልኝምን?” ብሎ ነበር። አባቱ ይስሐቅ ግን፦“እነሆ ጌታህ አደረግሁት፤ ወንድሞቹንም ሁሉ ለእርሱ ተገዦች አደረግኋቸው፤ ወይኑንና ዘይቱንም አበዛሁ ለት፤” ሲል መልሶለታል። ዘፍ ፳፯፥፴፮። በኦሪቱ ለሰዎችም ለእንስሳትም የበኲራት ቤዛ ልዩ ልዩ ሕግ ነበረ፤ ዘኊ ፫፥፵፪-፶፩፤፲፰፥፲፭-፲፯
ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊ ፥ቅዱስ ዮሴፍን ፦ “የበኲር ልጇን እስከምትወልድ ድረስ አላወቃትም፤” ማለቱ ስለ ብዙ ነገር ነው። በመሆኑም የመፍቻውን (የመተርጐሚያውን) ቁልፍ ማግኘት ያስፈልጋል። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱን፦ “ ከእናንተም ጋራ ሳለሁ ይህን ነገርኋችሁ። ነገር ግን አብ በስሜ የሚልከው የእውነት መንፈስ ጰራቅሊጦስ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል፤ እኔ የነገርኋችሁንም ሁሉ ያሳስባችኋል።” እንዳላቸው መንፈስ ቅዱስ ምሥጢር ገላጭ ነው።አባቶቻችን ይህንን የምሥጢር ቁልፍ በማግኘታቸው በአፍም በመጽሐፍም አስተምረው አልፈዋል። ዮሐ ፲፬፥፳፭። እንግዲህ እንደ አባቶቻችን አማናዊ ትምህርት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፦ “በኲር የሚሆን ልጇን እስከምትወልድ ድረስ አላወቃትም፤” መባሉ፦
፪፥፩፦ የመጀመሪያ ልጇን እስከምትወልድ ድረስ ማለት ነው፤
ታላቁ ነቢይ ኢሳይያስ፥ መተርጎምና ማመስጠር በማያስፈልገው ደረቅ የትንቢት ቃል፦ “እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅንም (ወልድን) ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።” ብሎ በተናገረው መሠረት ተቀዳሚና ተከታይ የሌለውን የመጀመሪያ ልጇን ወልዳለች። ኢሳ፯፥፲፬። በድንግልና ፀንሳ በድንግልና መውለዷም በመንፈስ ቅዱስ ግብር ነው። ይህንንም ከእግዚአብሔር የተላከ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል የእርሷ መፅነስና መውለድ እንደ አንስተ ዓለም አለመሆኑን አስቀድሞ ሲነግራት፦ “መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል፤(በግብረ መንፈስ ቅዱስ ነው)፤” ብሏት ነበር። ሉቃ ፩፥፴፭። በከብቶች በረት በወለደችውም ጊዜ፦ “ እነሆ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ። እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል፤ ይኸውም ቡሩክ ጌታ ክርስቶስ ነው።” የሚል የቅዱሳን መላእክት ብሥራት ለእረኞች ተነግሯቸዋል። ሉቃ ፩፥፲።
አንዳንድ ጊዜ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ፤ በኲር(የመጀመሪያ) ካለ ቀጣይ ልጅ እንደአለ አያመላክትም ወይ? የሚሉ አሉ። ለእነዚህም፥ ማለትም ባለማወቅ ለሚጠይቁትም ሆነ በክፋት ለሚጠይቁት አባቶቻችን በቅንነት መልስ ሰጥተዋል። ይህም መልስ፦ ለእነዚህ (በቅንነት ለሚጠይቁት) ትምህርት፥ ለእነዚያ (በክፋት ለሚጠይቁት) ደግሞ ተግሳፅ ነው።
፪.፪፦ ኢየሱስ ክርስቶስ የአብ የበኲር ልጅ ነው
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የበኲር ልጅነቱ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ብቻ ሳይሆን ለባሕርይ አባቱ ለእግዚአብሔር አብም ነው። ይህም፦ “እግዚአብሔር አለኝ አንተ ልጄ ነህ እኔም ዛሬ ወለድሁህ።” በሚለው ቃለ እግዚአብሔር ታውቋል። መዝ ፪፥፯። እግዚአብሔር አብ፥ እግዚአብሔር ወልድን (ኢየሱስ ክርስቶስን)፥ “አንተ ልጄ ነህ፤” ማለቱ፦ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ቅድመ ዓለም ያለ እናት ከአብ መወለዱን፥ የአብ የበኲር ልጅ መሆኑን ያመለ ክታል። “እኔም ዛሬ ወለድሁህ፤” የሚለው ደግሞ፤ ድኅረ ዓለም ያለ አባት፤ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለ ዱን፤ ለእመቤታችንም የበኲር ልጅ መሆኑን የሚያመለክት ነው።ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ይዞ የኢየሱስ ክርስቶስን የባህርይ አምላክነት፥ ፈጣሪነት፥ ከባህርይ አባቱ ከአብ ጋር ትክክል መሆኑን፥ ሲመሰክር ፦ ”ከጥንት ጀምሮ እግዚአበሔር በብዙ ዐይነት እና ጎዳና (ብብዙ ኅብረ ምሳሌና በብዙ ኅብረ ትንቢት) ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ። በኋላ ዘመን ግን ሁሉን ወራሽ ባደረገው ሁሉንም በፈጠረበት በልጁ ነገረን። እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የመልኩ ምሳሌ ሆኖ፥ (እግዚአብሔር አብን በባሕርይ የሚመስለው የባሕርይ ልጁ ስለሆነ፥ በክብርም ስለሚተካከለው)፥ ሁሉን በሥልጣኑ ቃል እየደገፈ (ከባሕርይ አባቱ ጋር በሥልጣን አንድ ስለሆነ) ኃጢአታችንን በራሱ (በተለየ አካሉ በተዋሕዶ ሰው ሆኖ ባፈሰሰው ደሙ፥ በቆረሰው ሥጋው፥ አሳልፎ በሰጠው ነፍሱ) ካነጻ በኋላ፥ በግርማው ቀኝ (በአብ ቀኝ፥ ከአብ ተካክሎ) ተቀመጠ። በዚህን ያህል መብለጥ (ፈጣሪ እንደመሆኑ) ከመላእክት በላይ ሆኖ (ፈጣሪያቸው፥ ገዢያቸው በመሆኑ) ከስማቸው የሚበልጥና የሚከብር ስምን ወረሰ። (የእርሱ ስም ፍጡር የማይጠራበት የፈጣሪ ስም ነው)። ከመላእክትስ ከሆነ ጀምሮ፥ አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወለድሁህ፤ ዳግመኛም እኔ አባት እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል ያለው ከቶ ለማነው? ዳግመኛም በኲርን ወደ ዓለም በላከው ጊዜ፥ የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉ ይሰግዱለታል፥ አለ። ስለ መላእክቱም፥ መላእክቱን ነፋሳት፥ የሚላኩትንም የእሳት ነበልባል የሚያደርጋቸው እርሱ ነው፥ አለ። ስለ ልጁ ግን፥ ጌታ ሆይ ዙፋንህ ለዘለዓለም ነው፤ የመንግሥትህ በትርም የጽድቅ በትር ነው፥ አለ፤» ብሏል። ዕብ ፩፥፩-፰፣ ፪ኛ ሳሙ ፯፥፲፬፣ ፩ኛ ዜና ፲፯፥ ፲፫፣ ዘዳ ፴፪፥፵፫፣ መዝ ፩፻፫፥፬፣ መዝ ፵፬፥፮-፯። እንግዲህ ለእግዚአብሔር አብ «የበኲር ልጅ»፥ የተባለ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ተቀዳሚም ተከታይም የሌለው የአብ የባሕርይ ልጅ እንደሆነ ሁሉ፥ ለእናቱ ለቅድስት ድንግል ማርያምም ተቀዳሚና ተከታይ የሌለው አንድ ልጅ ነው።
፪፥፫፦ ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን በኲር ነው፤
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቅዱሳን አምላክ ነው። ቅዱስ ቶማስ፦ በዓይኖቹ አይቶ፥ በእጆቹ ከዳሰሰ በኋላ «ጌታዬ፥ አምላኬም» ያለው ለዚህ ነው። ዮሐ ፳፥፳፰። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊም፦ «የእግዚአብሔር ልጅ እንደመጣ፥ እውነተኛም የሆነውን እግዚአብሔርን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንኖራለን፤ እርሱም እውነተኛ አምላክና የዘለዓለም ሕይወት ነው»። ብሏል። ፩ኛ ዮሐ ፭፥፳። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «እኒህም ልጅነት፥ ክብር፥ ኪዳን፥ ሕግና አምልኮ ያላቸው፥ ተስፋም የተሰጣቸው እስራኤላውያን ናቸው። እርሱም ከሁሉ በላይ የሆነ ለዘለዓለም ቡሩክ አምላክ ነው፥ አሜን፤» ብሏል። ሮሜ ፱፥፬-፭።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የባሕርይ አምላክ ብሎ የሚያምንበትን ኢየሱስ ክርስቶስን «የቅዱሳን በኲር፤» ብሎታል። ይኽንንም፦ «መንፈስ ቅዱስም ከድካማችን ይረዳናል፤ እንግዲያስ ተስፋችንን ካላወቅን ጸሎታችን ምንድነው? ነገር ግን እርሱ ራሱ መንፈስ ቅዱስ ስለ መከራችንና ስለ ችግራችን ይፈርድልናል። እርሱም ልባችንን ይመረምራል፤ ልብ የሚያስበውንም እርሱ ያውቃል፤ ስለ ቅዱሳንም በእግዚአብሔር ዘንድ (በሕልውና ከአብ ከወልድ ጋር አንድ ሆኖ) ይፈርዳል። እግዚአብሔር የሚወዱትን ምርጦቹን በበጎ ምግባር ሁሉ እንደሚረዳቸው እናውቃለን። ልጁ (የአብ የባሕርይ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ) በብዙ ወንድሞች (በቅዱሳን) መካከል በኲር ይሆን ዘንድ አስቀድሞ ያወቃቸውንና የመረጣቸውን እነርሱን ልጁን ይመስሉ ዘንድ አዘጋጅቶአቸዋል። ያዘጋጀውን እነርሱን ጠራ፤ የጠራቸውንም እነርሱን አጸደቀ፤ የአጸደቃቸውንም እነርሱን አከበረ፤» በማለት አብሯርቷል። ሮሜ ፰፥፳፮-፴።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፥ ኢየሱስ ክርስቶስን፥ «ለቅዱሳን በኲር» ያለው ለበጎ ነገር ሁሉ ምሳሌያቸው፥ አብነታቸው እርሱ ስለሆነ ነው። ምክንያቱም የተከተሉት የእርሱን መንገድ ነውና። የሰማዕታት አለቃ ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊገድሉት በድንጋይ ሲቀጠቅጡት፦ «ጌታዬ ኢየሱስ ሆይ፥ ነፍሴን ተቀበል፤ . . . አቤቱ፥ ይህን ኃጢአት አትቊጠርባቸው፤» ያለው የጌታውን መንገድ ሲከተል ነበር። የሐዋ ፯፥፶፱-፷። ምክንያቱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ በመስቀል ላይ ሆኖ፥ «አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው፤. . . አባት ሆይ፥ ነፍሴን በአንተ እጅ አደራ እሰጣለሁ፤» ብሏልና ነው። ሉቃ ፳፫፥፴፬፣ ፵፮። ይኽንን በተመለከተ፥ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ሲናገር፥ «በግፍ መከራን የሚቀበል ሰው እግዚአብሔርን እያሰበ ኃዘንን ቢታገሥ ጸጋን ያገኛልና። በድላችሁ የመጣባችሁን ብትታገሡ፥ ምስጋናችሁ ምንድርነው? ነገር ግን መልካም እየሠራችሁ፥ የደረሰባችሁን ግፍ ብትታገሡ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ የምታስመሰግን ይህቺ ናት። ለዚህ ተጠርታችኋልና፤ ክርስቶስም እኮ ፍለጋውን ትከተሉ ዘንድ ምሳሌውን ሊተውላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአል። እርሱ ኃጢአትን አልሠራም፤ በአንደበቱም ሐሰት አልተገኘበትም። ሲሰድቡት አልተሳደበም፤ መከራ ሲያጸኑበትም አልተቀየመም፤» ብሎአል። ፩ኛ ጴጥ ፪፥፲፱-፳፫። መምሕረ ትኅትና፥ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ የደቀመዛሙርቱን እግር ካጠበ በኋላ፦ «ያደረግሁላችሁን ዐወቃችሁን? እናንተ መምህራችን፦ ጌታችንም ትሉኛላችሁ፤ መልካም ትላላችሁ፤ እኔ እንዲሁ ነኝና። እኔ መምህራችሁና ጌታችሁ ስሆን እግራችሁን ካጠብኋችሁ እናንተም እንዲሁ የባልንጀሮቻችሁን እግር ልታጥቡ ይገባችኋል። እኔ እንዳደረግሁላችሁ እናንተም ልታደርጉ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ከጌታው የሚበልጥ አገልጋይ የለም፤ ከላከው የሚበልጥ መልእክተኛም የለም። ይህንም ዐውቃችሁ ብትሠሩ ብፁዓን ናችሁ።» ያላቸው ለዚህ ነበር። ዮሐ ፲፫፥፲፪-፲፯። ቅዱሳንም የጌታቸውን ቃል አክብረው፥ ለበጎ ምግባር ሁሉ በኲር የሆነላቸውን አምላክ መንገድ በመከተላቸው እርሱን መስለው ተገኝተዋል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ « እኔ ክርስቶስን እንደምመስለው (እንደመሰልኩት) እኔን ምሰሉ፤» ያለው ለዚህ ነው። ፩ኛ ቆር ፲፩፥፩። «ወንድሞቻችን ሆይ፥ እኔን እንድትመስሉ እማልዳችኋለሁ፤ ስለዚህም በየስፍራው በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዳስተማርሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የሄድሁበትን መንገድ ይገልጣላችሁ ዘንድ በእግዚአብሔር የታመነና ልጄ ወዳጄ የሆነ ጢሞቴዎስን ልኬላችኋለሁ።» ያለበትም ጊዜ አለ። ፩ኛ ቆሮ ፬፥፲፮። በፊልጵስዩስ መልእክቱም ላይ «ፍፁማን የሆናችሁ ሁላችሁ፥ ይህን አስቡ፤ ሌላ የምታስቡት ቢኖር፥ እርሱን እግዚአብሔር ይገልጥላችኋል። ነገር ግን በደረስንበት ሥራ በአንድነት እንበርታ። ወንድሞቼ ሆይ፥ እኔን ምሰሉ፤ እንዲህ ባለ መንገድ የሚሄዱትንም እኛን ታዩ እንደነበረበት ጊዜ ተጠባበቁአቸው፤» ብሏል። ፊል ፫፥፲፯፡፡

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top