“ሕፃናት ወደኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው” ሉቃ.18÷16 

ሀ ግእዝ፣ሁ ካይዕብ፣ ሂ ሳልስ ፣ሃ ራብዕ፣ሄ ኀምስ፣ህ ሳድስ፣ሆ ሳብዕ…እያሉ ፊደል ይቆጥራሉ።በመቀጠል ከፊደል ወደ ንባብ የዮሐንስ ወንጌል ከመጀመሪያው መልዕክተ ዮሐንስ ሐዋርያ ብለው ሙሉውን የዮሐንስ ወንጌል ከዛም ወደ መዝሙረ ዳዊት እያሉ የንባብ ኪሂላቸውን ያዳብራሉ።በተጨማሪም በንባብ ትምህርት ቤት ውስጥ የንባብ ስልቶች አሉ።እነርሱም፦

– ተነሽ    – ወዳቂ    – ተጣይ    – ሰያፍ ናቸው።

ለሕጻናት

  ከጨዋታ ሜዳ ላይ የተመረጠው ሕጻን !

 (በዲ/ን አትናቴዮስ  ዘኢትዮጵያ)

የእግዚአብሔር ስጦታ የሆናችሁ ሕጻናት፡- እንደምን አላችሁ፤እግዚአብሔር ይመስገን፤ ዛሬ ስለ አንድ ቅዱስ ሕጻን ልጅ ታሪክ እነግራችኋለሁ፡፡ ታሪኩ አስደሳችና አስተማሪ ስለሆነ በሚገባ ተከታተሉ እሺ!

ይህ ሕጻን ስሙ አትናቴዎስ ይባላል፡፡ አትናቴዎስ ማለት ፍቺው ምን መሰላችሁ ውሃ ማለት ነው፡፡ እናትና አባቱ በእግዚአብሔር የማያምኑ(አረማዊ) ነበሩ፤ እሱም ታዲያ በልጅነቱ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት ምንም አያውቅም ነበር፡፡ ታዲያ ከዕለታት አንድ ቀን የሰፈሩ ሕጻናት ተሰብስበው ደስ የሚል ጨዋታ ሲጫወቱ ቆሞ አየና እኔንም አስገቡኝ አላቸው፡፡

እነሱ ግን በድንግል ማርያም ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ ክርስቲያኖች በመሆናቸው፤ የኛ ጨዋታ እኮ መንፈሳዊ ነው፤ ስድብና መጣላት የለበትም፤ አንተ ግን ያላመንክ አረማዊ ነህ፤ ብናስገባህስ እንዴት ከእኛ ጋር መንፈሳዊ ጨዋታ መጫወት ትችላለህ? አሉት፡፡

ሕጻኑ አትናቴዎስም እሺ እኔንም ጨወታችሁን እሳተፍ ዘንድ አጥምቁኝ አላቸው፡፡ ከልጆቹም አንዱ እኔ እንደ ቄስ ሆኜ መስቀል ይዤ አሁን አጠምቅሃለሁ አለውና፤መጀመሪያ በኢየሱስ ክርስቶስ አምኛለሁ በል አለው፤ ሕጻኑ አትናቴዎስም በእርሱ በኢየሱስ ክርስቶስ   አሁን አምኛለሁ አለ፡፡ ጓደኛውም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ብሎ በውሃው 3 ጊዜ ረጨውና ከእንግዲህ ክርስትያን ሆነሃል ከእኛ ጋር አብረኸን ተጫወት አሉትና ብዙ ሰአት ተጫወቱ፡፡

በጨዋታቸው መሃልም አሁን ደግሞ ጳጳስ የመሆን ተራው ለሕጻኑ አትናቴዎስ ነው በማለት ሊቀ ጳጳስነት ሹመንሃል ብለው ወንበር ሰጡት፣ ሁሉም እየመጡም ጎንበስ ብለው ሰላምታ እየሰጡት በውሃ እያጠመቃቸው  መስቀል ያሳልማቸው ነበር፡፡

የሕጻናቱን ጨዋታ ቆም በማለት አተኩሮ የሚመለከት እለእስክንድሮስ የሚባል የአገሩ ዋና ጳጳስ ነበር፡፡ ታዲያ አብረውት ያሉት የሱ ተማሪዎች ይህን  ጨዋታ ዓይኑን ሳይነቅል ሲመለከት ጊዜ ገርሟቸው ‹‹መምህራችን አሁን ከእነዚህ ሕጻናት  ምን ቁምነገር ይገኛል ብለህ ነው እንዲህፈዘህ የምትመለከታቸው?››ብለው ጠየቁት ሊቀጳጳሱ እለእስክንድሮስም‹‹ዛሬ ይህ ሕጻን የሚሰራው የጨዋታ ስራ፤ወደ ፊት ሲያድግ እግዚአብሔር በሱ አድሮበት በዕውነት ይሰራዋል›› ብሎ ትንቢት ተናግሮለት ሄደ፡፡

የሕጻኑ አትናቴዎስ አባት ከጊዜ በኋላ ሲሞት እናቱ በሃገራቸው ረሃብ ስለነበር ልጇን አትናቴዎስን ለጳጳሱ እለእስክንድሮስ ልጄን አሳድገው፤ አስተምረውም ብላ በአደራ ሰጠችው፡፡ ጳጳሱም ተቀብሎ ሕጻኑ አትናቴዎስን ከድቁና ጀምሮ ያለውን የቤተክርስትያን ትምህርት ሁሉ እያስተማረው አሳደገው፡፡ አትናቴዎስም ትምህርቱን የሚወድ፤በጣም ጎበዝ፤ታዛዥ እና እግዚአብሔርን የሚፈራ፤ ሰውን የሚያከብር በመሆኑ ሁሉም ይወደው ነበር፡፡

እያስተማረ ያሳደገው የመንፈስ አባቱ ጳጳሱ እለእስክንድሮስ ብዙ ጊዜ ቆይቶ ሞተ፡፡ የዛኔም አትናቴዎስ ወጣት ስለነበር ሕዝቡና ካህናቱ ለሊቀ-ጳጳስነት አትናቴዎስን መርጠው ሹመውት ፓትርያርክ ሆነ ፡፡ክርስትያን ምእመኑንም በአባትነትና በትህትና ለብዙ ዓመታት አገለገለ፡፡

ሕጻናት፡- እግዚአብሔር አትናቴዎስን እንዴት አድርጎ ከጨዋታ ሜዳ ላይ መርጦ ለትልቅ ሃላፊነት እንዳስቀመጠው አያችሁ አይደል? እናንተም እንደ ሕጻኑ አትናቴዎስ ለመሆን ከፈለጋችሁ ቤተ-ክርስትያን ሄዳችሁ የእግዚአብሔርን ቃል መማር አለባችሁ፡፡ በተጨማሪም ሰፈር ስትጫወቱ ደግሞ ከጓደኞቻችሁ ጋር መጣላትና መሳደብ የለባችሁም በፍቅር እንደ አትናቴዎስ ጓደኞች መጫወት አለባችሁ እሺ፤ የዚያን ጊዜ የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ይወዳችኋል፡፡  ለታላቅ ስራም የምትመረጡ ትሆናላችሁ፡፡

    እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን እያልኩኝ ፤ ከዚህ በታች ያሉትን ጥያቄዎች እስኪ ለመመለስ ሞክሩና መልሱ ከከበዳችሁ ታላላቆቻችሁን የቤተ-ክርስትያን አገልጋዮች ጠይቃችሁ ያስረዷችኋል፡፡

ጥያቄዎች፡-

  1. ከጨዋታ ሜዳ ላይ የተጠራውና ከአረማዊነት ወደ ክርስትያንነት የተለወጠው ሕጻን ስሙ ማነው?

  2. የአትናቴዎስ ጓደኞች ጨዋታቸው ምን ዓይነት ነበር?

  3. የልጆቹን ጨዋታ በመገረም ቆሞ ያያው ማን ነበር ?

  4. አትናቴዎስን ከሕጻንነቱ ጀምሮ አስተምሮ ለሊቀ ጳጳስነት ያበቃው አባት ማነው?

  5. እኛ ሕጻናት እንደ አትናቴዎስ እግዚአብሔር እንዲወደንና እንዲመርጠን ምን ማድረግ አለብን?

የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን!

አሜን!

✥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት_ እዚህ በመጫን ያንብቡ

እግዚአብሔር አምላክ አዳምን ከፈጠረው ጊዜ አንስቶ ለአዳም እና ለልጆቹ ከሰጣቸው ስጦታዎች መካከል ወልደው የሚከብሩባቸው መንፈሳዊ በረከትን የሚስገኙላቸው እግዚአብሔርም ደስ የሚሰኝባቸው የአብራክ ክፋይ የማሕፀን ፍሬዎች ሕፃናት ድንቅ ስጦታዎች ናቸው፡፡ ከእግዚአብሔር ዘንድ ልጆች ለወላጆቻቸው ወደር የሌለው ስጦታ ሆነው ይሰጣሉ ወላጆችም ይህን ልጅ ማግኘትን እና የወላጅነትን ፀጋ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቀበላሉ፡፡ ወላጅነት ከምድር የሚሰጥ በረከት ሳይሆን የልዑል እግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ወላጅ የመሆን እና ልጆችን በስጦታ መልክ ማግኘት ከእግዚአብሔር ዘንድ ሲሰጥ ከነ ሙሉ ኃላፊነቱ ነው፡፡ በስጋ ወልዶ መተው ሳይሆን ይህንን ዓለም ያላየውን አዲሱን ብርቅዬ ፍጡር የነገውን ትልቁን ሰው በእንክብካቤ በማሳደግ መልካሙን መንገድ በማስተማር ሰው የሚሆንበትን መንገድ በማሳየት በጥበብና በሞገስ ከማሳደግ ኃላፊነት ጋር ጭምር ነው፡፡ (ምሳ 1¸8፣ 4¸10) ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ልጁ ሰሎሞንን “በርታ ሰው ሁን የአምላክህ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ጠብቅ” 1ኛ ነገ 2፣3 በማለት መክሮታል፡፡
ልጆች በፈሪሃ እግዚአብሔር ተጠብቀው፣ በስነምግባር ታንፀው፣ በጥበብ ሥጋዊ በጥበብ መንፈሳዊ በርትተው ከኃጢአት ርቀው በጽድቅ ስራ ፀንተው አምላካቸውን፣ ራሳቸውን፣ ወላጆቻቸውን፣ ቤተክርስቲያናቸውን፣ ወገናቸው ማገልግል እንዲቻላቸው ማድረግ ይኖርብናል፡፡

በአጠቃላይ ወላጅነት የጥሩ የመልካም ምግባር መምህርነት ነው፡፡ ቤተክርስትያን ደግሞ የቅድስና የእግዚአብሔር የቃሉ መዛግብት ማህደር እውነተኛይቱ የፅድቅ ወዳጅ ናት ምክንያቱም የቤተክርስትያን ራስ ክርስቶስ ነውና፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ ደግሞ “እውነትም መንገድም ህይወትም እኔ ነኝ” ይላል ዮሐ 14 ፣ 6 ወደ ቅድስት ቤተክርስትያን በመላክ ወላጆች ለልጆቻቸው መልካም የሆነን የማይጠፋ ህይወትን የእግዚአብሔርን ቃል ማውረስ አለባቸው፡፡ ስለሆነም ልጆች ከእግዚአብሔር የተሰጡን ከፍጡራን የማናገኛቸው ውድ እና ብርቅዬ ስጦታዎቻችን በመሆናቸው እንደ እንቁላል ከዚያም በሚበልጥ እንክብካቤ ልንጠብቃቸው እና ልንንከባከባቸው የሚገቡ ስጦታዎች ናቸው፡፡

ዓሣ አጥማጁ ስምዖን (ለሕፃናት)

በአንድ ወቅት ምን ሆነ መሰላችሁ ጌታችን በባህር ዳር ቆሞ ሕዝብን ያስተምር ነበር ሕዝቡም ጌታችን የሚያስተምረውን ትምህርት በደንብ ይከታተሉት ነበር፡፡ ጌታችንም ድምጹ ለብዙ ሰዎች እንዲሰማ ወደ ስምዖን ታንኳ ላይ ወጣ፡፡ በታንኳይቱም ውስጥ ተቀምጦ ሕዝቡን አስተማራቸው፡፡

ትምህርቱንም ሲጨርስ ሁሉም ሰው ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ ሲማሩ ከነበሩት መካከል አንዱ ስምዖን ነበር፡፡ ቀኑን ሙሉ ሌሊቱን ሁሉ ምንም ዓሣ ስላላጠመደ ተጨንቆ ነበር፡፡ ለምን መሰላችሁ ልጆች የስምዖን ቤተሰቦች ስምዖን የሚያመጣውን ዓሣ ይጠባበቁ ስለነበረ ነው፡፡ ስምዖን ዓሣ ሳይዝ ወደ ቤቱ ከገባ ቤተሰብ ሁሉ ሳይበላ ነው የሚያድረው ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ልጆች እግዚአብሔር የስምዖን ቤተ ሰቦች ተርበው እንዲያድሩ አላደረጋቸውም፡፡

ሌላው ደግሞ ልጆች ስምዖን ታንኳውን ጌታችን እንዲያስተምርበት ትቶለት ነበር፡፡ በጣም ታዛዥ ስለነበር እግዚአብሔር ዝም አላለውም፡፡ ጌታችን ስምዖንን መረብህን ጣልና ዓሣ አጥምድ አለው፡፡ ስምዖንም “መምህር ሌሊቱን ሁሉ ደክሜያለሁ ነገር ግን ምንም ዓሣ አልያዝኩም አንተ ስላዘዝከኝ ግን መረቤን እጥላለሁ” አለው፡፡ ስምዖን ምንም እንኳን ይሆናል ብሎ ባያምንም ለጌታችን ግን ታዘዘው፡፡ እንዳዘዘውም ባደረገ ጊዜ መረብ እስኪቀደድ ዓሣ ያዘ፡፡ ስምዖንም ይህን አይቶ ለጌታችን ሰገደለት፡፡ ከስምዖን ጋር የነበሩት ሰዎች ሁሉ በአዩት ነገር ተደነቁ፡፡

አያችሁ ልጆች ስምዖን ጌታችን ያለውን ነገር ሁሉ ስላደረገ ሌሊቱን ሙሉ ማጥመድ ያቃተውን ዓሣ መረብ እስኪቀደድ ድረስ ማጥመድ ቻለ፡፡ እኛም እግዚአብሔር አምላክ የሚያዘውን ነገር ብንሠራ ከምንፈልገው በላይ ይሰጠናል፡፡

ልጆች በመጨረሻም ዓሣ አጥማጅ የነበሩት ስምዖን ያዕቆብና ዮሐንስ ዓሣ ማጥመዳቸውን ትተው ጌታችንን ተከተሉት፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Lessons in English
Click here

✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን ✞

 ምስጢረ_ስላሴን ለህፃናት እንዲህ እናስተምር

✝️#ማን_ፈጠረን?   ☞✞ ስላሴ

✝️#ስላሴ_ስንት_ናቸው?  ☞✞ አንድም ሶስትም

✝️#ሶስትነታቸው_በምን_በምን_ነው?  ☞✞ በስም፣ በአካል፣ በግብር

✝️#አንድነታቸውስ_በምን_ነው?  ☞✞ በባህሪ፣በህልውና፣ በመለኮት፣ በፍቃድ፣ በስም፣ በአካል፣ በግብር ይህችን፣ አለም በመፍጠርና በማሳለፍ

✝️#የስም_ሦስትነታቸው_እንዴት_ነው?  ☞✞ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ

#የአካል_ሶስትነታቸው_እንዴት_ነው?  ☞✞ #አብ ፍፁም አካል ፍፁም መልክ ፍፁም ገፅ አለው።

☞✞ #ወልድ ፍፁም አካል ፍፁም መልክ ፍፁም ገፅ አለው።

☞✞ #መንፈስቅዱስ ፍፁም አካል ፍፁም መልክ ፍፁም ገፅ አለው።

✝️#የግብር_ሶስትነታቸው_እንዴት_ነው?  ☞✞ አብ=ወላዲ፤ ወልድ=ተወላዲ፤ መንፈስ ቅዱስ=ሰራፂ

✝️#አብ_ምን_ማለት_ነው?  ☞✞ አባት፦ መንፈስ ቅዱስን ያሰረጸ፤ ያለእናት ወልድን የወለደ

✝️#ወልድ_ምን_ማለት_ነው?  ☞✞ ልጅ፦ የሚወለድ፤ ያለእናት ቅድመ ዓለም፤ ያለ አባት ድህረ ዓለም ከድንግል ማርያም የተወለደ

✝️#መንፈስ_ቅዱስ_ምን_ማለት_ነው?  ☞✞ ሰራፂ፦ ረቂቅ፣ ልዩ፣ ንፁህ ሁኖ ከአብ የሰረፀ

✞✞✞•••✞✞✞•••✞✞✞

ስለ አቤልና ቃየን (ለሕፃናት)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

የተዋሕዶ ፍሬዎች፣ የሃገር ተስፋዎች እንደምን ሰነበታችኁ ልጆች? “እግዚአብሔር ይመስገን ደኅና ነን” አላችችኁ? መልካም፡፡ ትምህርት እንዴት ነው? እየጐበዛችኁ ነው አይደል? ጠንከር ብላችኁ በማጥናት ከአምናው የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንደተዘጋጃችኁ ተስፋ አደርጋለኹ፤ በርቱ እሺ?
ዛሬ አቤል እና ቃየን ስለሚባሉ ኹለት ወንድማማቾች ታሪክ ነው ይዤላችኁ የመጣኹት፡፡ ለመስማት ዝግጁ ናችኁ አይደል? በጣም ጥሩ !!!
አዳምና ሔዋን በገነት ይኖሩ ነበር፡፡ ሲበድሉ ግን እግዚአብሔር ከገነት አስወጣቸው፡፡ ደብር ቅዱስ ወደ ተባለ ቦታም ተሰደዱ፡፡ ከዚኽ ቦታ ኾነውም የገነት ሽታ እየሸተታቸው ይኖሩ ነበር፡፡ ወደ ገነት ግን መቅረብ አልተቻላቸውም፡፡ ሦስት ዓመት ሙሉም በጣም ያለቅሱና ያዝኑ ነበር፡፡

ከዚኽ በኋላ አዳም ሚስቱ ሔዋንን አወቃትና ቃየንና እኅቱን ሉድን ወለደች፡፡ ቀጥላም አቤልንና እኅቱን አቅሌማን ወለደች፡፡ ካደጉ በኋላም አቤል እረኛ ኾነ፤ ቃየን ደግሞ ገበሬ ኾነ፡፡ እረኛ ታውቃላችኁ ልጆች? ገበሬስ? እረኛ ማለት በግ፣ ከብት ወይም ፍየል የሚጠብቅ ልጅ ማለት ነው፡፡ ገበሬ ማለት ደግሞ መሬት አርሶ እኛ የምንበላውን እኽል የሚያመርት ነው፡፡ታድያ ልጆች፥ ከዕለታት በአንዱ ቀን አዳም ሚስቱን ሔዋንን ጠራትና፡- “እኅቴ ሔዋን ሆይ! ልጆቻችን እኮ አደጉ፡፡ ብናጋባቸው ምን ይመስልሻል?” አላት፡፡ እርሷም፡- “ወንድሜ አዳም ሆይ! እንዳልክ ይኹን፡፡ በሐሳብኅ እስማማለኹ እሺ” አለችው፡፡ከዚያ በኋላ “የቃየንን መንትያ ለአቤል፥ የአቤል መንትያ ደግሞ ለቃየን ትኹን” አሉ፡፡ ቃየን ግን ቀናተኛ ስለነበር “ከእኔ ጋር መንታ የኾነችው ሉድ ቆንጆ ስለኾነች ለእኔ ትኹን፡፡ የአቤል መንታ አቅሌማ ደግሞ ቆንጆ ስላልኾነች ለአቤል ትኹን” አለ፡፡ ቃየን አባቱንና እናቱን አልታዘዝም አለ፡፡ ከዚኽ በኋላ አዳም፡- “እንግዲያውስ መሥዋዕትን ሠዉና እግዚአብሔር መሥዋዕቱን የተቀበለለት ሉድን ያግባ” ብሎ መከራቸው፡፡ አቤልም በጣም ጨዋ፣ አስተዋይ፣ የዋኅና ታዛዥ ስለ ነበር እሺ ብሎ “ከእነዚኽ በጐች ንጹሕ የኾነውን ለምን አላቀርብም?” ብሎ አሰበ፡፡ ወዲያውኑም አቀረበ፡፡ ቃየን ግን ጥሩ ልጅ ስላልነበረ ከዘራው ስንዴ መርጦ ሳይኾን “እግዚአብሔር አይበላውም” ብሎ በንቀት እንክርዳድ የበዛበትን፣ ቆሻሻ የተቀላቀለበትን አቀረበ፡፡ እግዚአብሔር ግን የአቤልን መሥዋዕት ብቻ ተቀበለና የቃየንን ሳይቀበልለት ቀረ፡፡

ልጆች! ይሔኔ ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ በጣም ቀና፡፡ “እግዚአብሔር አቤልን እንጂ እኔን አይወደኝም” ብሎ ተቈጣ፡፡ እግዚአብሔርም ቃየንን ጠርቶ “ምነው ፊትኅ ጠቆረ? መልካም ብታደርግስ እንደ ወንድምኽ ደጉ አቤል ይበራ ነበር” አለው፡፡ ቃየን ግን በቅን ልቦና “አምላኬ ሆይ! አዎን መልካም ሥራ አልሠራኹም፤ ከእንግዲኅ ምን ማድረግ ይገባኛል?” አላለም፡፡ እንዲያውም ቁጣው እየበረታበት መጣ፡፡
ልጆች! ከዚኽ በኋላ ቃየን እያዘነ ሲሔድ ሰይጣን መንገድ ላይ አገኘውና “ቃየን ምነው እያዘንክ ትሔዳለኅሳ?” አለው፡፡ አይገርምም ልጆች! ሰይጣን ወዳጅ መስሎ የቀረበው ሊያታልለው እንጂ አዝኖለት እንዳይመስላችኁ፡፡ ከዚኽ በኋላ ቃየን “እኔ ያላዘንኩ ማን ይዘን? አባቴ አዳልቶ ቆንጆዋን እኅቴን ለአቤል ሰጠው፡፡ እግዚአብሔርም አዳልቶ መሥዋዕቴን ሳይቀበልልኝ ቀረ” ብሎ ለሰይጣኑ ነገረው፡፡ ሰይጣንም “ወንድምህን ግደለውና አንተ ቆንጆዋን አግብተኽ ትኖራለኽ” ብሎ ክፉ ምክር መከረው፡፡ ቃየንም “ለካ እንደዚኽም ይቻላል” ብሎ በሰይጣን ሐሳብ ተስማማ፡፡
ከዕለታት በአንዱ ቀንም ወንድሙን አቤልን ጠራውና “ና ወደ ሜዳ ሔደን እንጫወት” አለው፡፡ ከተጫወቱ በኋላ ራባቸውና ምሳ ለመብላት ተቀመጡ፡፡ ምሳቸውን ከበሉ በኋላ ውኃ ለመጠጣት አብረው ወደ ወንዝ ወረዱ፡፡ መዠመሪያ ቃየን ጠጣና አቤልን ጠጣ አለው፡፡ አቤልም ለመጠጣት ጐንበስ ሲል ቃየን ትልቅ ድንጋይ አነሣና አቤልን በድንጋይ ፈጥፍጦ ገደለው፡፡ ልጆች ሞት ለመዠመሪያ ጊዜ በሰው ልጆች የታየው ቃየን አቤልን ከገደለው በኋላ ነው፡፡

በዚኽም ጊዜ እግዚአብሔር በደመና ውስጥ ኾኖ “ቃየን ቃየን ወንድምኅ አቤል ወዴት ነው?” አለው፡፡ ቃየን ግን በትዕቢት ኾኖ “እኔ ምን አውቃለኹ፤ እኔ የወንድሜ የአቤል ጠባቂው ነኝን?” ሲል መለሰ፡፡ እግዚአብሔርም መልሶ “እንግዲኽ ጠባቂው ካልኾንኅ ስለምን ገደልከው? አኹንም ባለ ዘመን ኹሉ በምድር ኹሉ ላይ ድንጉጥና ተቅበዝባዥ ኹን” በማለት እግዚአብሔር ቃየንን ረገመው፡፡ ከዚያን ጊዜ ዠምሮ ቃየን በጣም ፈሪ፣ ሰዎችን የሚሸሽ፣ የሚጨነቅ፣ ባጠፋው ጥፋት እግዚአብሔርን የሚያፍር ኾኖ ኖረ፡፡

ልጆች! ታሪኩ ያሳዝናል አይደል? አዎ! እኛ ጥሩ ስንኾን ወላጆቻችንም ኾነ እግዚአብሔር እንደ ደጉ አቤል ይወዱናል፡፡ እንደ ቃየን ክፉ ስንኾን፣ የምንቈጣ፣ ለመማታት የምንቸኩል፣ የሰው ምክር ሳይኾን የሰይጣንን ምክር የምንሰማ ከኾነ ደግሞ ወላጆቻችን ይረግሙናል፤ አምላክም ያዝንብናል፡፡ እናንተ ግን እንደ ቃየን ሳይኾን እንደ አቤል በማስተዋል፣ በታዛዥነት፣ የተባረከ ልጅ ኾናችኁ መገኘት አለባችኁ እሺ? ጐበዞች፡፡

ልጆች! እስቲ ይኽን ጥቅስ አጥንታችኁ በቃላችኁ ለመያዝ ሞክሩ፡፡

“የኃጥአን መሥዋዕት በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፡፡ የቅኖች ጸሎት ግን በርሱ ዘንድ የተወደደ ነው” /መጽሐፈ ምሳሌ 16፡8/፡፡

ደኅና ኹኑ ልጆች!!!

ምንጭ http://mekrez.blogspot.fi/

ስለ እመቤታችን ልደት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች እንዴት ሰነበታችኁ? እግዚአብሔር ይመስገን ደኅና ነን አላችኁ? አሜን፡፡ እኔም በጣም ደኅና ነኝ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡
ልጆች! ባለፈው ጊዜ ስለምን እንደተማማርን ታስታውሳላችኁ? አቤል እና ቃየን ስለሚባሉ ኹለት ወንድማማቾች አይደል? ጐበዞች! ትክክል ናችኁ፡፡ ዛሬ ደግሞ ኹላችንም ስለምንወዳት ስለ እናታችን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ልደት እነግራችኋለኹ፡፡ ለመስማት ዝግጁ ናችኁ አይደል? ጐበዞች፡፡ እግዚአብሔር ዕውቀቱን ይግለጥልን፡፡ አሜን!!!

የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አባት ኢያቄም ይባላል፡፡ እናቷ ደግሞ ሐና ትባላለች፡፡ ኢያቄምና ሐና እግዚአብሔርን በጣም የሚወዱትና በሕጉ የሚኖሩ ደጋጐች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ሐና መካን ስለነበረች ኹለቱም ወደ ቤተ እግዚአብሔር ዕለት ዕለት በመኼድ ለዐይናቸው ማረፊያ ለልባቸው ተስፋ የሚኾን ልጅ እንዲሰጣቸው ይለምኑ ነበር፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀንም ሲያዝኑና ሲጸልዩ ውለው ወደ ቤታቸው እየተመለሱ ሳለ ርግቦች ከልጆቻቸው ጋር ደስ ብሏቸው ሲጫወቱ አዩ፡፡ ሐናም፡- “ጌታዬ! ለእንስሳ እንኳን ልጅ የሰጠኽ አምላክ ምነው ለኔ ልጅ ከለከልከኝ” ብላ ምርር ብላ አለቀሰች፡፡ እግዚአብሔርም ጸሎታቸውንና ሐዘናቸውን አየና ልጅ እንደሚወልዱ በሕልም ነገራቸው፡፡ ኢያቄምና ሐናም “ወንድ ልጅ ከወለድን ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ ይኾናል፤ ሴትም ብንወልድ ለቤተ እግዚአብሔር መጋረጃ ፈትላ ትኖራለች” ብለው ለእግዚአብሔር ቃል ገቡ፡፡ ከዚያ በኋላ ነሐሴ ሰባት ቀን ሐና እመቤታችንን አረገዘች፡፡
ከስድስት ወርም በኋላ የሐና ፅንሷ እየታወቀ መጣ፡፡ ጎረቤቶቿ መፅነሷን ሰምተው ተደነቁ፡፡ እየመጡም ማሕፀኗን ይዳስሱ ነበር፡፡ አንድ ቀንም ዐይኗ የማያይ ሴት መጣችና የሐናን ማሕፀን ዳስሳ ዐይኗን ብትነካው በራላት፡፡ በጣምም ተደሰተች፡፡ ከዚኽ በኋላ ብዙ የታመሙ ሰዎች እየመጡ የሐናን ማሕፀን እየዳሰሱ ይድኑ ነበር፡፡ በእጅጉ የሚደንቀው ደግሞ ሳሚናስ የሚባል ልጅ ከአጐቱ ቤት ሔዶ ሞተ፡፡ እመቤታችንን ያረገዘችው ሐናም የአልጋውን ጫፍ ይዛ እየዞረች እያለቀሰች ነበር፡፡ ትንሽ ቆይቶ ግን የሞተው ልጅ ተነሣ፡፡ እዚያ ቦታ የነበሩ ሰዎች ግን እግዚአብሔርን ከማመስገን ይልቅ ቅናት ያዛቸውና ሐናንና ኢያቄምን በድንጋይ ደብድበው ሊገድልዋቸው ተማከሩ፡፡
ከዚኽ በኋላ ቅዱስ ገብርኤል ለኢያቄም ተገለጸና ሐናን ሊባኖስ ወደሚባል ተራራ እንዲወስዳት ነገረው፡፡ እመቤታችንንም በዚያ በሊባኖስ ተራራ ግንቦት አንድ ቀን ወለደቻት /መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን 4፡8/፡፡ ሐናና ኢያቄምም በእጅጉ ተደስተው በተወለደች በ8 ቀኗ ስሟን ማርያም ብለው ሰየሟት፡፡

ልጆች! የእመቤታችን ልደት ለእኛ ለሰዎች ትልቅ ደስታ ነው፡፡ ለምን እንደኾነ ታውቃላችኁ? ባለፈው ጊዜ እንደነገርኳችኁ አዳምና ሔዋን ለእግዚአብሔር ሳይታዘዙ ሲቀሩ ከገነት ተባረው ነበር፡፡ ከገነት የተባረሩት ግን እመቤታችን እስክትወለድ ነው እንጂ ወጥተው በዚያ እንዲቀሩ አልነበረም፡፡ ገነት እንደገና የተከፈተልን በእመቤታችን ምክንያት ነው፡፡ ለዚኽ ነው ማርያምን በጣም የምንወዳት፡፡ እናንተስ ማርያምን ትወዷታላችኁ? እስኪ መውደዳችኁን በምንድነው የምትገልጹት? እመቤታችንን እንደምንወዳት የምንገልጸው ውዳሴ ማርያምን በማንበብ፣ ስለ እመቤታችን በመዘመር፣ ሥዕሏን በመሳም፣ እንድታማልደን በመለመን፣ ስሟን ጠርተው ለሚለምኑን ሰዎች ብር ወይም ልብስ ወይም ደግሞ የሚበላ ነገር ስንሰጥ ነው እሺ ልጆች፡፡
ልጆች! ይሔ ጥቅስ በቃላችኁ ያዙት፡፡ “ስለ ሔዋን የገነት ደጅ ተዘጋ፤ ዳግመኛም ስለ ድንግል ማርያም ተከፈተልን” /የሐሙስ ውዳሴ ማርያም/፡፡

በሉ በቀጣይ ጊዜ እስከምንገናኝ ድረስ ደኅና ሰንብቱ፡፡ እመቤታችን በምልጃዋ ትጠብቃችኁ፡፡ አሜን!!!

አትዋሹ (ለሕፃናት)

በድሮ ጊዜ ክርስቲያኖች በአንድነት ይኖሩ ነበር፡፡ በመካከላቸውም የሁሉ ገንዘብ በአንድነት ነበር አንጂ “ይህ የእኔ ገንዘብ ነው” የሚል አልነበረም ከእነርሱም አንድም ችግረኛ አልነበረም፤ ቤትና መሬት ያላቸው ሁሉ እየሸጡ ገንዘቡን ያመጡ ነበር፡፡

አምጥተውም በሐዋርያት እግር ስር ያስቀምጡ ነበር፡፡ ሐዋርያትም ለእያንዳንዱ እንደፍላጎቱ ይሰጡ ነበር፡፡ ሐዋርያት ስሙን ዮሴፍ እያሉ የሚጠሩት በርናባስ የተባለ ሰው ነበር፡፡ የእርሻ መሬትም ነበረው፡፡መሬቱንም ሸጦ ገንዘቡን በሐዋርያት እግር ስር አስቀመጠው ከሐዋርያትም ማኅበር ተቀላቀለ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ልጆች ሐናንያና ሰጲራ የተባሉ ባልና ሚስቶች ነበሩ፡፡ እነዚህ ባልና ሚስቶች መሬታቸውን ሸጡ፡፡ እርስ በርሳቸውም ተማከሩና ከሸጡት ዋጋ ግማሹን ለራሳቸው ወሰዱና የሸጥነው በዚህ ዋጋ ነው ብለው ግማሹን በሐዋርያት እግር ስር አስቀምጠው ከማኅበሩ ለማቀላቀል ይዘው ሄዱ፡፡ ያደረጉትን ማንም የሚያውቅባቸው አልመሰላቸውም ነበር፡፡ ነገር ግን ይህን ሁሉ ነገር እግዚአብሔር ያውቃል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ውስጥ ነበርና ያደረጉትን ነገር ያውቅ ነበር፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስም ለሐናንያ እንዲህ አለው “ሰውን ሳይሆን መንፈስ ቅዱስን ለምን ታታልላለህ መጀመሪያም ሳትሸጠው ያንተ አልነበረምን አሁንስ ከሸጥነው በኋላ ያንተ አይደለምን ይህንን ነገር ለምን በልብህ አሰብሀ” አለው ሐናንያም ይህን በሰማ ጊዜ ወድቆ ሞተ፤ ሰዎችም ተሸክመው ወስደው ቀበሩት፡፡ ይህ ከሆነ ከሦስት ሰዓት በኋላም ሚስቱ ሰጲራ መጣች፡፡ ባልዋ የሆነውን ሳታውቅ ገባች፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም “እስኪ ንገሪኝ መሬታችሁን የሸጣችሁት በዚህ ዋጋ ነውን” አላት፡፡ እርሷም “አዎ” አለች፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም “የእግዚአብሔርን መንፈስ ትፈታተኑት ዘንድ እንዴት ተባበራችሁ አነሆ ባልሽን የቀበሩት ሰዎች በበር ናቸው አንቺንም ይወስዱሻል” አላት፡፡ ወዲያውም ወድቃ ሞተች፤ ሰዎቹም ወስደው ቀበሩአት፡፡

ልጆች እኛም ውሸት ስንናገር እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ሥራ እየሰራን እና የሌሎች ሰዎችን እምነት እያጣን መሆኑን ልናውቅ ይገባል፡፡ የምንዋሽ ከሆነ እግዚአብሔር በጣም ስለሚወደን ከውሸታችን እንድንመለስ ይታገሰናል፡፡ ካልተመለስን ግን በረከቱን ከእኛ ይወስድብናል፡፡ ስለዚህ ይህን ማስወገድ ይገባናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

ልደተ ክርስቶስ /የገና በዓል/ – ለሕጻናት

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ደህና ናችሁ? ዛሬ ስለጌታችን አምላካችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት /ገና በዓል/ እንነግራችኋለን፡፡ በደንብ ተከታተሉን፡፡ እሺ?

ልጆች በአንድ ወቅት እንዲህ ሆነ፡፡ አውግስጦስ ቄሳር የተባለ ንጉሥ ሰው ሁሉ ይቆጠር ዘንድ አዘዘ፡፡ በትእዛዙ መሠረትም ሰው ሁሉ ሊቆጠር ወደየትውልድ ከተማው ሄደ፡፡ ዮሴፍና እመቤታችንም ሊቆጠሩ ከናዝሬት ወደ ትውልድ ሥፍራቸው ወደ ቤተልሔም ሄዱ፡፡ በቤተልሔም ሳሉም እመቤታችን የምትወልድበት ቀን ደረሰ፡፡ በዚያ ሥፍራም ብዙ እንግዳ ስለነበር እነ ዮሴፍ የሚያርፉበት ቦታ አላገኙም ነበር፡፡ ማደርያም ስላልነበራቸው በከብቶች ማደርያ በበረት ውስጥ እመቤታችን ልጅዋን ወለደችው፡፡

 በጨርቅ ጠቅልላ እዛው በበረት ውስጥ አስተኛችው፤ በዚያ ሀገር ይኖሩ የነበሩ እረኞችም ሌሊት ከብቶቻቸውን ይጠብቁ ነበር፤ የእግዚአብሔር መልአክም በእረኞቹ አጠገብ ቆመ፤ የእግዚአብሔርም ብርሃን በዙሪያቸው በራ፤ በጣምም ፈሩ፡፡ መልአኩም እንዲህ አላቸው ‹‹እነሆ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን ታላቅ የምስራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ‹‹እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት የሆነ ተወልዶላችኋል፡፡ ይኸውም ጌታ እና እግዚአብሔር የሆነ መድኃኒታችን ኢያሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እናንተም ባገኛችሁት ጊዜ ምልክቱ እንዲህ ነው፡፡ ሕፃን በጨርቅ ተጠቅልሎ በበረት ውስጥ ተኝቶ ታገኙታላችሁ ድንገትም ከዚያ መልአክ ጋር ብዙ የሰማይ መላእክት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ እነዚህ እረኞች እርስ በርሳቸው ‹እስከ ቤተልሔም እንሂድ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን ነገር እንወቅ አሉ፡፡ ፈጥነውም ሄዱ፡፡ ማርያምንና ዮሴፍን አገኙአቸው፡፡ ሕፃኑንም በበረት ውስጥ አገኙት፡፡ በአዩትም ጊዜ የነገሩአቸውን ሰምተው በጣም ተደነቁ፡፡ እረኞቹም እንደነገሩአቸው ባዩትና በሰሙት ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ‹‹በሰማይ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን በምድርም ለሰው ልጆች በጎፈቃድ ሆነ›› ብለው እያመሰገኑና እያከበሩ ወደመጡበት ተመለሱ፡፡ አያችሁ ልጆች እነዚህ ክርስቶስን ሊያዩ የመጡ ሰዎች ደስተኞች ነበሩ፤ ስለዚህ ልጆች እኛም በቤተ ክርስቲያን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት በደስታ ልናከብር ይገባናል፡፡ ከመላእክት ጋር ሆነንም ‹‹በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን›› እያልን እንዘምር፡፡ እንግዲህ ልጆች መልካም የገና በዓል ይሁንላችሁ እሺ፡፡

 ምንጭ  www.eotcmk.org

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top