ስግደት

የማይሰገድባቸው ጊዜያት

የሚሰገድባቸው ጊዜያት እንዳሉት ሁሉ የማይሰገድባቸው ጊዜያትም አሉ፡፡ የግዝት በዓላት 5 ሲሆኑ የወልድ በዓል፣ የእመቤታችን በዓል፣ የቅዱስ ሚካኤል በዓል፣ ቀዳሚት ሰንበትና እሑድ ሰንበት ናቸው። ከነዚህ በተጨማሪ ከቁርባን በኋላና የበዓለ ሐምሳ ወራትም የማይሰገድባቸው ጊዜያት ናቸው። እነዚህ ስግደት የተገዘተባቸው ጊዜያት የሚከተሉት ናቸው፡፡

1ኛ. በዕለተ ቅዳሜና እሑድ

በዕለተ እሑድ

ከአልቦ ነገር ወይም ከምንም (ex- nihilo – from nothingness) የተፈጠረ ፍጥረት ሁሉ ክርስቶስ ዳግም ሲመጣ ጠፍቶ ወደ ምንምነት ሲቀየር ከማይጠፉ ከአምስቱ ፍጥረታት አንዷ ሰንበት ናት፡፡ ጌታ የተነሣባት ፣ ዳግምም የሚመጣባት ዕለት ናት፡፡ በዚህና በሌሎች ምክንያቶችም ሰንበተ ክርስቲያን እሑድ በዓል ነች፡፡ ስለዚህ በዕለተ እሑድ መስገድ የተከለከለ ነው፡፡ ይህንን ፍትሐ ነገሥቱ እንዲህ በማለት ይገልፀዋል፡- “ከአድንኖና ከአስተብርኮ በቀር እስከ ምድር መስገድን የሚተዉባቸው የታወቁ ጊዜያቶች እነዚህ ናቸው፡፡ ኒቅያ 20፣ በዕለተ እሑድና በበዓለ ሃምሳ ወራት፣…” ፍት.መን. አን. 14 ቁ. 537 ይህንን ይበልጥ ሲያጸናው በሰንበታትና በበዓላት አንቀጹ እንዲህ ሲል ደግሞታል፡- “በእሑድና በተከበሩት በዓላት ቀን ስግደት አይገባም፤ እነዚህ የደስታ ቀኖች ናቸውና” ፍት. መን. አን. 19 ቁ. 715

በዕለተ ቅዳሜ

ሌላው ከዕለታት መካከል ቅዳሜ የግዝት በዓል ተብሎ የተመረጠበት ምክንያት የሁሉ ባለቤት የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዓለማትን ሁሉ በስድስት ቀናት ውስጥ ፈጥሮ ከፈጸመ በኋላ በሰባተኛው ቀን አረፈ። ይህችንም ቀን ቀደሳት ለሰው ልጆችም በዓል አድርጎ ሰጠን። “በሰንበትም እንደ ትእዛዙ ዐረፉ።” ሉቃ 23፥56

2ኛ. በበዓለ ሃምሳ ወራት

በዓለ ሃምሳ የፍስሐና የሰላም ጊዜ ነው፡፡ ስሙ እንደሚጠቁመው ሃምሳውም ቀን በሙሉ በዓል ነው፡፡ በዓል ስለሆነም እንደ ፋሲካና እንደ ልደት እንበላበታለን እንጂ ረቡዕና አርብ ቢሆን እንኳን አንጾምበትም፡፡ በበዓልነቱ ጾም እንደተሻረበት ስግደትም እንዲሁ ይሻርበታል፡፡ ከላይ እንዳየነው ፍትሐ ነገሥቱም በፍት.መን. አን. 14 ቁ. 537 በእሑድ መስገድን ሲከለክል በበዓለ ሃምሳም እንዲሁ ከልክሏል፡፡

3ኛ. በጌታችን በዓላት

ፍትሐ ነገሥቱ “በእሑድና በተከበሩት በዓላት ቀን ስግደት አይገባም፤ እነዚህ የደስታ ቀኖች ናቸውና” (ፍት.መን. አን. 19 ቁ. 715) ካለ በኋላ “የተከበሩት በዓላት” ያላቸው የትኞቹን እንደሆነ ሲዘረዝር ትስብእት/ጽንሰት ፣ ልደት ፣ ጥምቀት ፣ ሆሣዕና ፣ ትንሣኤ ፣ ዕርገት ፣ በዓለ ሃምሳ ፣ ደብረ ታቦር በማለት ከጌታ ዘጠኝ ዐበይት በዓላት 8ቱን ይገልፃል፡፡ ሳይገለፅ የቀረው ስቅለት ነው፤ ያልተገለፀበትም ምክንያት በስቅለት ስግደት ስለማይከለከል ነው፡፡ ስለዚህ ከስቅለት በቀር በጌታ ዐበይት በዓላት (በተቀሩት በ8ቱ) ስግደት የተከለከለ ነው፡፡ ፍትሐ ነገሥቱ ይህንን ሲያጸና በአንቀጽ 14 እንዲህ ብሏል፡- “መስገድን የሚተዉባቸው የታወቁ በዓላት እነዚህ ናቸው…. ኒቅያ 32፣ በጌታችን በዓላትና በእመቤታችን በዓላት” ፍት.መን. አን. 14 ቁ. 536-537፡፡

በ29 በዓለ ወልድ ብለን የጌታን በዓላት እንደምናስብ ይታወቃል፡፡ በፍትሐ ነገሥትም የጌታችን በዓላት እንደማይሰገድባቸው ሲጠቀስ ምንም እንኳን በአንቀጽ 19 ከ9ኙ ዐበይት በዓላት ስምንቱን ቢገልፅም አንቀፅ 14 ግን “የጌታችን በዓላት የእመቤታችን በዓላት” ብሎ ማለፉን መርጧል፡፡ የጌታችን በዓላት የተባሉ ከ9ኙ የጌታ በዓላት ውጪ 9 ንዑሳን በዓላትም አሉ፡፡ እነዚህም ስብከት ፣ ብርሃን ፣ ኖላዊ ፣ ግዝረት ፣ ልደተ ስምዖን ፣ ቃና ዘገሊላ ፣ ደብረ ዘይት ፣ ጌና ፣ መስቀል ናቸው፡፡ ፍትሐ ነገሥቱ በእነዚህ ዙሪያ የዘረዘረው ግልፅ ነገር የለም፡፡ ሆኖም የጌታ በዓላት ስለሆኑና በጌታ በዓላት ደግሞ ስግደት ስለተከለከለ ፣ አባቶቻችን እነዚህን የጌታ (የወልድ) በዓላት በአንድነት ወር በገባ በ29 በዓለ ወልድ ብለን እንድናስብና፣ ዕለቱም ስለ በዓላቱ የግዝት ዕለት እንዲሆን የተደረገ ይመስላል፡፡ ስለዚህ አይሰገድበትም፡፡

4ኛ. በእመቤታችን በዓላት

በፍት. መን. አን. 14 ቁ. 536-537 ድረስ በጌታ በዓላት መስገድ እንደተከለከለው ሁሉ በእመቤታችን በዓላትም መከልከሉን ይጠቁመናል፡፡ የወልድ በዓልን እንደምናከብረው የእመቤታችንንም በዓል በ21 አስበን አንሰግድም፡፡ ስለዚህ ወር በገባ በ21 ሁሌም የግዝት በዓል ነው፤ አይሰገድበትም፡፡

5ኛ. በቅዱስ ሚካኤል በዓል

የቅዱስ ሚካኤል በዓል ከሌሎች የመላእክት በዓላት ተለይቶ መከበሩ ለምንድነው ቢሉ “የቅዱስ ሚካኤል በዓል መላእክትን ወክሎ ወርኃዊ ሆኖ እንዲከበር ታዟል” (በዓላት ፣ ዲ.ን. ብርሃኑ አድማስ ፣ ገጽ 124)፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን በ12 እንዳይሰገድና እንደ ታላላቅ በዓላት በደስታ እንዲከበር ሥርዐትን ሠርታለች፡፡

6ኛ. ሥጋና ደሙን ከተቀበሉ በኋላ

የሥርዐት ምንጫችን የሆነው ፍትሐ ነገሥት አሁንም በዚህ ዙሪያ እንዲህ ብሏል፡- “መስገድን የሚተዉባቸው የታወቁ በዓላት እነዚህ ናቸው… ሥጋውንና ደሙን ከተቀበሉ በኋላ” ይላል፡፡ ፍት. መን. አን. 14 ቁ. 536-537፡፡ ሥጋውንና ደሙን ከተቀበልን በኋላ ከሚሰገድለት እንጂ ከማይሰግደው ጋር አንድ መሆናችንን ለማጠየቅና ለቅዱስ ሥጋውና ለክቡር ደሙ ክብር ስንል ዝቅ ብለን አንሰግድም፡፡

የስግደት  ዓይነቶች ሦስት  ናቸው እነሱም፡
/ የባሕርይ ( የአምልኮ ) ስግደት
/ የጸጋ ስግደት
/ የአክብሮት ስግደት በመባል በሦስት ይከፈላል

/ የባሕርይ ስግደት፡የባሕርይ ስግደት የሚሰገደው ለእግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ጌትነትና ክብር የባሕርይው ስለሆነ ሁሉን ያስገኘ ሁሉን የፈጠረ ከሁሉ በላይ ነግሶ የሚኖር በባሕርይው ሞት በመንግስቱ ህልፈት፣ በሥልጣኑ ሽረት የሌለበት ስለሆነ ስግደት የባሕርይ ገንዘቡ ነው፡፡ ለእግዚአብሔር የምንሰግደው ስግደት ለሌላ ለማንም የማንሰግደው ነው፡፡ ‹‹ ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እሱን ብቻ አምልክ ›› ( ማቴ410 ) ( ዘጸ 613) ( መዝ 243-5 ) ‹‹ ጉልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል ›› ( ኢሳ 4523 )
/ የጸጋ ስግደት፡የጸጋ ስግደት የሚሰገደው ለቅዱሳን ሰዎች ለመላእክት የሚሰገድ ነው፡፡ እነሱም ከእግዚአብሔር በስጦታ የተሰጣቸው በመሆኑ ነው፡፡
/ የአክብሮት ስግደት፤የአክብሮት ስግደት የሚሰገደው በመንፈሳዊ ሀብትና ጸጋ ላላቸው ብቻ ሳይሆን የዕድሜ ባለጸጎችን ማክበር ታናሹ ለታላቁ መስገድ ታናሹ ታላቁን ማክበር በፍጹም ቅንነትና ግልጽነት ሰዎች እንደየማዕረግና እንደ ዕድሜ ደረጃቸው መከበር ይገባቸዋል፡፡

 ለቅዱሳን መላዕክት መስገድ እንደሚገባ፡

በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ለተልእኮ የሚመላለሱ ፈጣሪያቸውን አዘውትረው ከሚያገለግሉ መላዕክት ጀምሮ እግዚአብሔር ላከበራቸው ለወደዳቸውና ለመረጣቸው ቅዱሳን የጸጋ ስግደት ይሰገድላቸዋል፡፡ ላኪው ክቡር ከሆነ መላዕክተኛው ክቡር ነው፡፡ መልእክቱም የከበረ ነው፡፡
እግዚአብሔር ያከበረውን ማክበር የእግዚአብሔር ትእዛዝ ነው፡፡ ‹‹እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል ›› ( ማቴ 1040)፡፡ ቅዱሳን መላእክት በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ዘወትር ምስጋና የሚኖሩ ለተልእኮ የሚወርዱ የሚወጡ በተፈጥሮአቸው ረቂቃን መንፈሳውያን ኃያላን ሰማያውያን ስለሆኑ የሚያስደነግጥ ግርማና የሚያስፈራ ኃይል አላቸው ‹‹ የቃሉንም ድምጽ በሰማሁ ጊዜ ደንግጨ በምድር ላይ በግንባሬ ተደፋሁ ›› ( ዳን. 109 ) የሚላኩት ከእግዚአብሔር ስለሆነ መልእክታቸው ከእግዚአብሔር ስለሆነ ክብራቸው ታላቅ ነው፡፡ ለቅዱሳን መላዕክት የጸጋ ስግደት መስገድ እንደሚገባ ቅዱስ መጽሐፍ በሰፊው ይገልጻል የሚከተሉትም ጥቅሶች ይኸን የሚያስረዱ ናቸው፡፡

/ ጻድቁ ሎጥ ቅዱሳን መላዕክትን ባያቸው ጊዜ በፊቱ ተደፍቶ በምድር ላይ ተደፍቶ ሰግዶላቸዋል፡፡ ዘፍ 91-2
/ ኢያሱ የኢሪያኮን ግንብ ባፈረሰ ጊዜ ኢያሪኮ አጠገብ የተመዘዘ ሰይፍ ይዞ ላየው መልዐክ በፊቱ ከምድር ወድቆ ሰግዶለታል፡፡ የእግዚአብሔርም መልዐክ ያዘዘውን ትእዛዝ ያለማመንታት ፈጽሟል፡፡ኢያ 513-15
/ ባለ አህያው በለዓም ላይ የተመዘዘ ሰይፍ ይዞ በሚያስፈራ መልክ በመንገዱ ላይ የቆመ የእግዚአብሔርን መልዐክ አይቶ በፍርሃትና በድንጋጤ በግንባሩ ተደፍቶ ሰግዶአል፡፡ ዘኁ 2231፡፡ ከነቢያት እነዳዊት እነዳንኤል፣ ከሕዝቡ እነማኑሄ፣ ከወንጌላውያን እነ ቅዱስ ዮሐንስን የመሳሰሉ ብዙ ደጋግ ሰዎች ለቅዱሳን መላዕክት የሚገባውን የጸጋ ስግደት አቅርበዋል፡፡ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከላቸውን የመልካም የምስራች ድምጽ ሰምተዋል፡፡ በጎ በረከትንም አግኝተዋል፡፡1ዜና 2116 ዳን 815-17 መሳ 1320 ራዕ 1910
ማጠቃለያ፡
ቅዱሳን መላእክት ረቅቅ ፍጥረት ናቸው፡፡ በእግዚአብሔር ፊት በባለሙዋልነት የሚቆሙ ናቸው፡፡ ሉቃ 119 የእግዚአብሔርን ኃይል ለመግለጥ የሚላኩ ናቸው፡፡ አያ 513-15 የእግዚአብሔር ምህረት ይቅርታ ለሰው ልጅ፤ የሰውን ልጅ ትሩፋት ማንኛውንም በጎ ሥራ ሁሉ ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡ ናቸው፡፡ ( የሐዋ 103 ) ( ዕብ 114 ) እግዚአብሔር ቅዱሳን መላእክትን አክብርዋቸዋል፡፡ የምሰጢሩም ተካፋዮች አድርግዋቸዋል፡፡ የአምላክን ሰው መሆን የተናረ የእግዚአብሔር መልአክ ነው፡፡ ( ሉቃ 126-39 ) የመወለዱን የምስራች ለእረኞች የሰበከው የእግዚአብሔር መልአክ ነው፡፡( ሉቃ 28-14)
ሄሮድስ ሕጻኑን ኢየሱስን ለመግደል መፈለጉን ለቅድስት ድንግል ማርያምና ለጠባቂዋ ለቅዱስ ዮሴፍ በመግለፅ ወደ ግብጽ እንዲሸሹ ያደርጉት ቅዱሳን መላእክት ናቸው፡፡ (ማቴ 213 ) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃድ 40 መዓልታና 40 ሌሊት ከጾመ በኃላ በዲያብሎስ ተፈትኖ ሶስቱን አርእስተ ኃጣው ድል ባደረገ ጊዜ የድል አድራጊነቱ ምልክት የሆኑት መላእክት መተው አግልለውታል፡፡ ( ማቴ 411 ) ጌታ በተሰቀለ ጊዜ መስቀሉ ስር ተነጥፈዋል፡፡ የትንሳኤውንም የምስራች ለሰው ያሰሙ መላእክት ናቸው፡፡ ( ማቴ 281 ) ( ማር 165 )
(
ሉቃ 244 ) ( ዮሐ 2011 ) ወንጌልን ሲሰብኩ የነበሩት ሐዋርያትን ወኀኒ ቤት ከፍተው እግረ ሙቅ ፈትተው በማውጣት አይዟችሁ በማለት ይረዷቸው የነበሩ ቅዱሳን መላእክት ናቸው፡፡ ( የሐዋ 519 126 )
ሰማዕታት የአላውያን ነገሥታን ግርማ እንዳይፈሩ የሚያበረታቱ፤ ጻድቃን ግርማ ሌሊቱን ድምጸ አራዊቱን ጸብአ አጋንንትን እንዳይሳቀቁ የሚያደርጉ ቅዱሳን መላእከት ናቸው፡፡ በመጨረሻም በፍርድ ቀን ጌታን ተከትለው ይመጣሉ፡፡
ቅድስት ቤተክርስቲያንም ቤተክርስቲያን ሰርታ፣ ጽላት ታቦት ቀርጻ፣ የጸበል ቦታ በስማቸው ሰይማ ባማላጅነታቸው ትማጸናለች፡፡ ድርሳናቸውን በመጻፍ ያደረጉትን ተአምራት ሁሉ መዝግባ በማንበብ በመጸለይ ለቅዱሳን መላእክት ያላትን አክብሮት ትገልጻለች፡፡ ዕለተ ዓላቸውን በቀኖና ወስና በዓላቸውን ታከብራለች ልጆችዋንም በስማቸው ትሰይማለች፡፡ ገብረ ሚካኤል፣ ሀይለገብርኤል፤…….፡፡

 ለቅዱሳን ሰዎች መስገድ እንደሚገባ

የቅዱሳን ባለቤት ቅዱስ እግዚአብሔር በልዩ ጸጋው ለመረጣቸው ላከበራቸው ለወደዳቸውና መንፈስ ቅዱስ ላደረባቸው ቅዱሳን ሰዎች መስገድ ተገቢ መሆኑን ቅዱሳን መጻህፍት በሠፊው ይገልጻሉ፡፡
የሚከተሉትም ጥቅሶች ይኸንኑ የሚያስረዱ ናቸው፡፡
/ የንጉሡ የአክአብ ባለሟል አብጸድዩ ጌታዬ እያለ ለነቢዩ ለኤልያስ ሰግዶለታል ( 1ነገ 187 )
/ ንጉሡ አካዝያስ በመጨረሻ ከአምሳ ወታደር ጋር የላከው የሃምሳ አለቃ በኤልያስ ፊት እየሰገደ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ ነፍሴና የእነዚህ የሃምሳው ባሪዎችህ ነፍስ በፊትህ የረከሰች ትሁን ብሏል፡፡ ለነብዩ በመስገዱና የሚገባውን ክብር በመስጠቱ ልመናው ተሰምቶ እንደቀደሙት ከሰማይ በወረደ እሳት አልሞተም የወታደሮቹንም ሕይወት አድኗል፡፡ 2ነገ 27 7113
/ የኢያሪኮ ሰዎች ለነብዩ ኤልያስ በግንባራቸው ተደፍተው ሰግደውለታል፡፡( 2ነገ 215 ) ሱናማዊትዋም ሴት በችግሯም በደስታዋም ጊዜ ሰግዳለታለች፡፡ ( 2ነገ 427 እና 37 )
/ የወህኒ ቤት ጠባቂው ለቅዱስ ጳውሎስና ለሲላስ እየተንቀጠቀጠ በግንባሩ ተደፍቶ ሰግዶላቸዋል ( የሐዋ 1629 )፡፡
ሌላ መረጃ፡ ( 1 ሳሙኤል 2814) ( ዳንኤል 246-49) ( 2ሳሙኤል 11-3 ) በመንፈሳዊ ሀብትና ጸጋ ብቻ ሳይሆን የዕድሜ ባለጸጎችን ማክበር ታናሹ ለታላቁ መስገድ ታናሹ ታላቁን ማክበር በፍጹም ቅንነትና ግልጽነት ሰዎች እንደየማዕረግና እንደ ዕድሜ ደረጃቸው መከበር ይገባቸዋል፡፡ ያዕቆብ ከሶርያ ተመልሶ ከወንድሙ ከኤሳው ጋር በተገናኘ ጊዜ ለወንድሙ ለኤሳወ ሰባት /7/ ጊዜ መላልሶ ከምድር እየወደቀ ሰግዶለታል ቤተሰቡም እሱን ተከትለው ለኤሳው ተመሳሳይ ስግደት አቅርበዋል፡፡

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top