ቅዱሳት ስእላት በጥታዊቷ ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያን 

ሥዕል፦ ከክርስትና በፊት ሥዕል በቤተ አሕዛብም ሆነ በቤተ አይሁድ የታወቀና ከአምልኮት ጋር የተያያዘ ነበር። በቤተ አሕዛብ እንጨት ጠርቦ ደንጊያ አለዝቦ ማምለክ የተለመደ ነበር። እንዲያውም የሮማ ነገሥታት አማልክት ተብለው ከመመለካቸው በላይ ከሞቱ በኋላ ሥዕላቸው በደንጊያና በእንጨት እየተቀረጸ ሲመለኩ መኖራቸው በታሪክ ይታወቃል። ክርስትና በመጣ ጊዜም ከክርስትና ጋር ያጣላቸው ይኸው ልማዳቸው ነው። በክርስትና ትምህርት ይህ አምልኮ ጣዖት ነውና፤ በቤተ አይሁድም እንደ አሕዛብ ሳይሆን በታቦተ ሕጉ በጽላተ ኪዳኑ ላይ ሥዕለ ኪሩብን እንዲሥል ራሱ እግዚአብሔር ሙሴን አዝዞት ነበር። ዘጸ 25፥19። ነገሥ ቀዳ 6፥23። ሕዝ 9፥3፣ 10፥3፣ 10፥1። ሔኖ 14፥11 ዘጸ 25፥20፤ ዘፍ 3፥24። እነዚህ የኪሩቤል ሥዕሎች ከታቦቱ አይለዩም። ምክንያቱም ታቦት የእግዚአብሔር መገለጫ ዙፋን ስለሆነ የመንበረ ፀባዖት አምሳል ነው። ሥዕለ ኪሩቤልም የጸወርተ መንበር ኪሩቤል አምሳል ነውና፥ የሚሳሉትም እንደሚናተፍ አውራ ዶሮ ሁነው ነው። የንጉሥ አንጋች ንጉሡ በተቀመጠበት በዙፋኑ ፊት ነቃ፥ ቆጣ፥ ብሎ እንደሚቆም።
ሥዕል በቤተ ክርስቲያን የተጀመረበት ግን ከዚህ የተለየ ታሪካዊ ምክንያት አለው። በጥንታውያን ክርስቲያኖች ዘንድ የሥዕል ክብር እንዴት ተጀመረ። በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደ ተገለጠው የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ትምህርታቸውን ያስፋፉት ዋሻ ፈልፍለው ጉድጓድ ቆፍረው በዋሻ በፍርክታ ውስጥ ነው። ካታኮምብ (ግበ በምድር) ይሉታል፥ በዚህ ዋሻ ውስጥ የሰማዕታትን አፅም እየሰበሰቡ ጸሎት ይጸልዩ ትምህርት ያስተምሩ ነበር። በዚሁ ውስጥ ብዙ አማኞች እየመጡ የማኅበራቸው አባል መሆን ጀመሩ። በዚህ ጊዜ የክርስትናን ትምህርት አስፋፍቶ ለመስጠት በቂ መጻሕፍት አልነበሩም። እንደ ልብ ወጥቶ ለመፈለግና ለማዘጋጀት ነፃነት ስላልነበራቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንዳንድ ምሳሌዎችን በሥዕል እያሰፈሩ ማስተማር ጀመሩ። በዚህ ሁኔታ ሥዕል ማስተማሪያ ሁኖ ቆይቷል። ሥዕሎችም የሚሣሉት በምሳሌነት “ሲምቦል” ሲሆን የሚሳሉትም በአመድና በከሰል በዋሻው ዙሪያ ነው። በዋሻው ፊት ለፊት ላይ (በአፈ ጽዮን) የሚሥሉት እረኛው በጉን እንደተሸከመ አድርገው ነው። “ክርስቶስ ያመኑበትን ሁሉ በሱም አምነው የሞቱትን ሁሉ የሚያድናቸው ቸርና ታማኝ ጠባቂ መሆኑን ለማስረዳት ነው።” ሌላውን ሥዕላቸውን የሚጀምሩት በብሉይ ኪዳን ታሪክ ነው። ለምሳሌ የቀደሙ ሰዎች አዳምና ሔዋን እንዴት እንደተሳሳቱና ያሳታቸውንም እባብ በመካከላቸው እንዳለ አድርገው ይስሏቸው ነበር። ዘፍ ፫፥፩-፯ በምህላና በጸሎት ላይ ያለች የምዕመንን ነፍስ በመርከብ ውጥ ያለውን ኖኅን አስመስለው ይስሏት ነበር። ዘፍ ፯፥፩-፳፬ የአቤልን መሥዋዕት ለክርስቶስ መስዋዕትነት ምሳሌ፤ ዘፍ ፬፥፬። በውኃ ተጠምቆ መዳንን ወይም መዳን በጥምቀት መሆኑን ሲገልጡ ሙሴ በበትሩ ደንጊያውን መትቶ ለተጠሙ እሥራኤል ውኃ ማፍለቁን ይሥላሉ፤ ዘፀ ፲፯፥፮። የኢዮብ መከራ፦ የሰማዕታትና የምዕመናን መከራና ትዕግሥት ምሳሌ መሆኑን፤ ኢዮ ፩፥፳፪። የእስራኤል ጉዞ በሐቅለ ሲና የምዕመናን በዚህ ዓለም የመኖር ምሳሌ፤ የሙሴ ደብረ ሲናን መውጣት አምላኩንም ማየት፥ የምዕመናን ክብርና ልዕልና ምሳሌ፤ ሠለስቱ ደቂቅ በእሳት ውስጥ ከገብርኤል ጋር፥ ምዕመናን በዚህ ዓለም በመከራ ቢሰቃዩም ታዳጊ መልአክ የማይለያቸው ለመሆናቸው ምሳሌ፤ ኤልያስ ሐሜሌቱን ለኤልሳዕ ጥሎ ማረጉ፥ ክርስቶስ በረከቱን ለምዕመናን ሰጥቶ ለማረጉ እና ምዕመናንም በሱ አምነው ገነት መንግስተ ሰማያት ለመግባታቸው ምሳሌ፤ ዳንኤል በግበ አናብስት፥ ሰማዕታት በዐላውያን ሸንጎ ለመቆማቸው ምሳሌ፤ ጦቢት ከዓሣው ጋር፥ ምዕመኑ ከአዳኙ ከክርስቶስ ጋር ለመሆኑ ምሳሌ፤ በጥንት ግሪኮች ዓሣ ሲሉ፦ “ኢኽቲስ” ይላሉ። የዚህ ፊደል እያንዳንዱ ምህጻረ ቃልነት አለው። ኢ – ኢየሱስ፣ ኽ – ኽርስቶስ፣ ቴ – ቴው ኢዮስ፥ (የእግዚአብሔር ልጅ) ስ – ሶቴር (መድኅን) አዳኝ፥ ማለት ነው፤ ሁሉንም ቃላት አገናኝተን ስናነበው፦ “ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር መድኅን” የሚል ትርጉም ይሰጣል። ሶስና ከሁለት ዳኞች ጋር፥ ሰማዕታት በዐላውያን ነገሥታት ፊት የመቆማቸው ምሳሌ፤ ዮናስ ወደ ባሕር ሲጣል፥ አንበሪ ሲውጠውና በየብስ ሲተፋው፥ የነበረባት ጎጆ በዱባ ቅጠል ተሸፍና ሲደሰት፥ በኋላም በደረቀችበት ጊዜ ሲያዝን፥ ይህ ሁሉ በአንድ ላይ የክርስቶስን ሞትን ትንሣኤ ያስረዳል።የሐዲስ ኪዳንንም ታሪክ እንደዚሁ በግበ በምድር ውስጥ ይሥሉት ነበር። የቅዱስ ገብርኤል ብሥራት፥ የጌታ በቤተልሔም ዘይሁዳ መወለድ፥ የሰብአ ሰገል ስግደትና አምኃ፥ ሕፃኑን ለታቀፈችው ለድንግል ማርያም አምኃውን ሲያስረክቡ፥ የምድረ ግብፅ ስደት፥ ዮሴፍና ሰሎሜ ጓዛቸውን ተሸክመው አብረው ሲሰደዱ፥ የጌታ ጥምቀትና የሦስቱ ዓመት ትምህርት ከተአምራት ጋር፥ የቃና ሠርግ፥ የዕውሩ ዓይን መከፈት፥ የመጻጉዕ መዳን፥ ልብሱን ስትዳስስ ደሟ የደረቀላት ሴት (እንተ ደም ይውኅዛ)፥ በአምስቱ እንጀራና በሁለቱ ዓሣ ቡራኬ፥ አምስት ሺ ሰው መመገቡና አሥራ ሁለት ቅርጫት ማትረፉ፥ ሳምራዊት ማድጋዋን ተሸክማ ወይም ውሃውን ከዐዘቅቱ በሸንከሎዋ ስትስብ፥ ጌታ ሳምራዊትን ሲያነጋግር፥ የሰነፎቹና የብልሆቹ ደናግል ሁኔታ፥ የጴጥሮስ ክህደትና ጸጸት፥ የይሁዳ ክህደትና መምህሩን አሳልፎ መስጠት፥ በመጨረሻም ሞቱና ትንሣኤው፥ ማርያም መግደላዊትና የተነሣው፥ ክርስቶስ እመቤታችን ምስለ ፍቍር ወልዳ፥ በግራዋ በኩል ኢሳይያስ ወደሷ እያመለከተ፤ ይህም “ናሁ ድንግል ትፀንስ፥ ወትወልድ ወልደ፥ ብዬ የተናገርሁላት ይቺ ናት፤” እንደማለት ነው። ይህንና ይህን የመሳሰሉ ሌሎችም ሥዕሎች በጥንት የክርስቲያኖች መሸሸጊያ ዋሻዎች በከሰልና ባመድ ተሥለው ተገኝተዋል። ይህን ሁሉ ያደርጉ የነበረው በፊት እንደ ተባለው የሃይማኖታቸውን ታሪክ ለማስተማር ነው።
ከዚህ ሌላ የምዕመናንን ልቡና ለማጽናናት በሰማዕትነት የሞቱት ወንድሞቻቸው ዐፅም ባረፈበት አኳያ አሟሟታቸውንም በሥዕል ይገልጹት ነበር። በዚህ አኳኋን የሥዕል ክብር በቤተ ክርስቲያን እንደ ተጠበቀ እስከ ስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድረስ ከቆየ በኋላ በሥዕል ምክንያት በሮምና በቢዛንታይን ግዛት በሚኖሩ ምዕመናን ዘንድ አለመግባባት ተፈጠረ። ለዚህም አለመግባባት ዋናው ምክንያት አንዳንድ ክርስቲያኖች ሥዕሎችን ከመውደዳቸው የተነሣ አማልክት ናቸው እስከ ማለት ደርሰው ስለ ነበረ ነው፤ (ኢኮኖላትሪያ)። ሌሎች ደግሞ ወደ ሌላ ጎን በማጋደል ሥዕሎችን ጨርሰን ማጥፋት አለብን ብለው የከረረ የተቃውሞ በር ከፈቱ፤ (ኢኮኖማኺያ)። በመካከሉ ደግሞ እንደነዚያም ሳያመልኩ እንደነዚህም በጥላቻ ሳይመነችኩ የጥንቱን ትምህርት ተከትለው ሥዕሎችን የሚወዱና የሚያከብሩ ምዕመናን ነበሩ። ነገር ግን በዘመኑ የነበሩት ገዢዎች ሥዕልን ማጥፋት አለብን የሚለውን ክፍል ስለ ደገፉ ቤተ ክርስቲያን ለብዙ ዘመን ያቆየቻቸው ቅርሶቿ እና የቤተ ክርስቲያንን ጥንታዊ ኪነ ጥበብ የሚያሳዩ ሥዕሎቿ ሁሉ በእሳት ጋዩ። ብዙ ምዕመናንም በዚሁ ምክንያት አለቁ። የሥዕሎቹ መጥፋት ጉዳይ በባለ ሥልጣኖች ቢደገፍም ሥዕሎቻችን አይቃጠሉብን የሚለው ክፍል እያየለ ድምጹም እየተሰማ ሄደ፤ እንዲያውም ጠቡ እየተባባሰ ሄዶ የሮምንና የቢዛንታይንን መንግሥት የሚያናጋው ሆነ።
 ይህን በክርስቲያኖች መካከል የተነሣ ብጥብጥ በጉልበት ሳይሆን ሁለቱንም ክፍሎች በሚያግባባ የጋራ ሐሳብ ላይ ለመድረስ፥ ጠቡ በተነሣበት አካባቢ የነበሩ የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች በ፯፻፹፯ ዓ.ም. ጉባኤ አድርገው እንደ ሁለቱም ሳይሆን (እንደ ሥዕል አምላኪዎችና እንደ ሥዕል አጥፊዎች ሳይሆን) ስለ ሥዕል ክብርና ስግደት የሚገባውን ቀኖና ሠርተዋል። ከዚህም ጉባኤ በኋላ በማከታተል የተነሡ የሮማና የቢዛንታይን መለካውያን ሊቃውንት ስለ ሥዕል ክብርና የት መጣ አያሌ መጻሕፍትን ጽፈዋል። ለምሳሌ በዚያው ዘመን በዚያው አካባቢ የነበረው ስመ ጥር ሊቅ ዮሐንስ ዘደማስቆ ስለ ሥዕል ብዙ ቀዋሚና ጠቃሚ የሆኑ መጻሕፍትን ጽፏል። ዮሐንስ ዘደማስቆ እንደሚለው፦ ሥዕል በቤተ ክርስቲያን ሁለት ዓይነት ጥቅም አለው፤ ከነዚህም አንዱ በዋሻው እንደነበሩት ክርስቲያኖች ተአምራት ነክ የቅዱሳት መጻሕፍትን ታሪኮችን ማንበብ ለማይችሉ ሰዎች ለማስረዳት ሲሆን፥ ሁለተኛው ደግሞ ሃይማኖቱን ሳይፈራ እና ሳያፍር መስክሮ በሰማዕትነት የሞተ ወይም ስለ ዓለምና ስለ ራሱ በመጸለይ መላ ሕይወቱን ከፍትወታት፥ ከእኩያት፥ ከአጋንንት ጋር በመጋደል ያሳለፈውን ሰማዕት ወይም ጻድቅ በሥዕል ለማስታወስ፥ በሥዕሉም አማካይነት እያንዳንዱ ምዕመን ለሥዕሉ ባለቤት ያለውን ክብርና ፍቅር ለመግለጥ ነው።

በሥዕል ፊት ቆሞ መጸለይ ከባለ ሥዕሉ ረድኤት፥ በረከት እና ምልጃ መለመን፥ መማጠን ነው። ለሥዕል መስገድ እና ሥዕልን መሳም ደግሞ በፊት የሥዕል ተዋጊዎች ወይም ፀረ ሥዕሎች (ኢኮኖማኺ) እንደሚሉት ዛሬም ብዙ ፀረ ማርያሞች እንደሚያጥላሉት ለጣዖት መስገድ ጣዖት መሳም አይደለም። ከላይ እንደገለጥነው በሥዕሉ አማካይነት ለሥዕሉ ባለቤት ክብርና ፍቅርን ለመግለጽ ነው። ይኸውም የቤተ ክርስቲያን ሕልውና ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ የነበረ ጥንታዊ ትውፊት (Tradition) ነው። በእምነትና በፍቅር የሆነ ነገር ደግሞ ያንጻል እንጂ አይንድም። የእግዚአብሔር መንግሥት የሚወረሰው በፍጹም እምነት ቅንነት በተሞላበት ፍቅርና ትሕትና እንጂ በተጥባበ ነገር (Rationalism) አይደለምና።በምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ትውፊት መሠረት ሥዕል የሚሣለው በቀለም ነው። ላቲኖች ግን ቅርጽ ይቀርጻሉ። ስለ ሥዕል ክብር በቤተ ክርስቲያን ስለተጀመረበት ምክንያት በመጠኑ ገልጠናል። አሁን ደግሞ ስለ ሥዕል ከተነሣ ዘንድ አከራካሪ ስለሆነው የጌታና የእመቤታችን ሥዕል የትመጣ እንደዚሁ የቤተ ክርስቲያንን ትውፊት መሠረት በማድረግ በመጠኑ እንገልጣለን። 
ስለ ጌታ ሥዕል ብዙ ታሪኮችና ትውፊታዊ ትምህርቶች ይነገራሉ፤ በዚሁ መሠረት ለመጀመሪያ ጊዜ የጌታን ሥዕል የሣለው ዮሐንስ ወንጌላዊ ነው ይባላል። ታሪኩም ከሞላ ጐደል እንደሚከተለው ነው። ከ፲፬-፴፯ ዓ.ም. ሮምን ይገዛ የነበረው ጢባርዮስ ቄሣር ነው። በሱ ዘመነ መንግሥት ነው ጌታ የተሰቀለው፤ ይኸው ጢባርዮስ በልጁ መሞት በጣም አዝኖ ሬሣውን ሳያስቀብር ሰነበተ፥ ከጥቂት ቀንም በኋላ ጌታ በኢየሩሳሌም ያደርገው የነበረውን ታምራት ያውቅ ስለነበር፦ “ከጢባርዮስ ቄሣር ምድራዊ ንጉሥ የተላከች ጦማር (መልእክት) ለጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሠ ሰማይ ወምድር ትድረስ” ብሎ ልጁን እንዲያስነሣለት የምልጃ የልመና ጽሑፍ ጽፎ ይህችን መልእክትና የልጁን ሬሣ ወስደው ጐልጐታ (የጌታ መቃብር) ላይ እንዲያኖሩለት ባለወጐቹን ላከ። እነሱም ሄደው ደብዳቤዪቱንና ሬሣውን በጌታ መቃብር ላይ ሲያኖሩት ሬሣው አፈፍ ብሎ ተነሥቷል። ጢባርዮስም ከደስታው ብዛት የተነሣ የጌታን ውለታ ለመክፈል የዚህንስ ሰው እናቱን አምጥሉኝ እኔ ቋሚ ለጓሚ፥ ሚስቴ ገረድ ደንገጡር ሁነን እናገለግላታለን ብሎ እንደገና ሰው ቢልክ፥ የድንግል ማርያም ክብር ሰማያዊ እንጂ ምድራዊ ስላልሆነ ተሰውራባቸው አላገኟትም። ጢባርዮስ ግን ተስፋ እንዳይቆርጥ ዮሐንስ ወንጌላዊ በዕለተ ዓርብ በመስቀሉ ላይ እንዳየው አድርጐ ከለሜዳ አስታጥቆ ጌታን ሥሎለታል። ስለ ሥዕሉ እውነተኛነትም ለማረጋገጥ ዮሐንስ የሣለው ይህ ሥዕል “አይሁድ በኢየሩሳሌም እንደ ሰቀሉኝ አንተ ደግሞ ሁለተኛ ሰቀልከኝን?” የሚል ድምጽ አሰምቷል። ሥሎ ሲጨርስ ዮሐንስ ቢስመው ከንፈሩ ከሥዕሉ ጋር ተጣብቆ ቆይቷል። ይህ ሁሉ ከሥዕሉ የታየው ተአምራት ነው። “አይሁድ የሰቀሉት ራቁቱን ነበር፥ ከለሜዳ አስታጥቆ መሣል የተጀመረው ከዚያ ወዲህ ነው፤” እያሉ የሀገራችን ሊቃውንት ይተርካሉ።

ስለ ጌታ ሥዕል ሁለተኛው ምንጭ (መነሻ) ጴላጦስ ለጢባርዮስ ቄሣር ስለ ጌታና ስለ እናቱ ስለ እመቤታችን የላከው ሥዕላዊ መግለጫም አለ። ጲላጠስ በቅዱስ መጽሐፍ እንደሚታወቀው በፍልስጥኤም የሮማ መንግሥት እንደራሴ የነበረና በጌታም ሞት የፈረደ ነው። ወደ ጢባርዮስ ቄሣር የላከው መልእክት እንደሚከተለው ነው። “ለጢባርዮስ ቄሣር፤ ሰላም ላንተ ይሁን፥ ኢየሱስ ስለሚባለው ሰው ግርማዊነትህ ለማወቅ የጠየቀውን ለማሟላት ከዚህ የሚከተለውን እጽፍልሃለሁ። በዚህ እኔ እንደራሴህ አድርገህ በሾምኸኝ በፍልስጥኤም ምድር፥ እጅግ በጣም የተለየ መልክና ሥልጣን ያለው አንድ ሰው ተነሥቷል። ታላቅ መምህርና ነቢይም ነው ይሉታል። ደቀመዛሙርቱ ግን የእግዚአብሔር ልጅ ነው ይላሉ። ስሙ ኢየሱስ ይባላል፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ቄሣር ሆይ ይህ ኢየሱስ የተባለው ክርስቶስ በየጊዜው ድንቅ ድንቅ ተአምራትን ያደርጋል፤ ሙታንን ያስነሣል፥ ድውያንን ከማናቸውም ደዌና ሕመም ይፈውሳል። ከዚህም ጋር ጥልቅና መንፈሳዊ በሆነ ትምህርቱ መላዋን ኢየሩሳሌምን አስደንቋታል። አቋሙና አካሉ ግርማ ያለው፥ መልኩም አንጸባራቂ እና ጸጋ የተሞላበት በመሆኑ ማናቸውም የሚያየው ሁሉ ይወደዋል፥ ይፈራዋልም። አንዳንድ ጊዜ ቀላ ያለው መልኩና መሐል ለመሐል ተከፍሎ የሚታየው ጽሕሙ የሚሰጠው ውበት ፍጹም ግምት የሌለው ነው። የፊቱ ቅርጽ መልአካውያን ዓይኖቹና የጥቁር ወርቃማ ጠጉሮቹም አወራረድ በሚሰጡት የተንጸባረቀ ውበት ማንም ሰው ቢሆን ለረጅም ጊዜ አተኩሮ ሊመለከተው አይችልም። የሚመስለው እናቱን ነው። እሷም ደግሞ በዚህ ክፍለ ሀገር በማንም ላይ ያልታየ ውበትና የትሕትና መልክ ያላት ናት። ቆራጥ ከባድና የሚያከራክሩ ንግግሮቹም በውስጣቸው የሚገኘው ፍጹም የሆነ የመንፈስ ልዕልናና የዕውቀት መጠናቸው ከታላላቅ አዋቂዎች ተብለው ከሚገመቱት ሰዎች እጅግ አድርጐ የራቀ የጠለቀ ምሥጢር አላቸው። በተግሣጽና በእዝናት ጊዜም በጣም ኃይለኛ ነው። በማስተማርና በማበረታታት ጊዜ ደግሞ ትሑት ተወዳጅና ልብ የሚመስጥ ነው። ራሱን ሳይከናነብና መጫሚያ ሳይጫማ በእግሩ ይሄዳል። በሩቅ የሚያዩት አንዳንዶች ይስቁበታል፥ ነገር ግን ወደፊቱ ሲቆሙና ሲቀርቡ በመንቀጥቀጥ ያደንቁታል። ማንም ቢሆን ሲስቅ አየሁት የሚል የለም። ነገር ግን ብዙዎች ሲያለቅስ አይተውታል። የቀረቡት ሁሉ ብዙ ሥራና ፈውስ ማግኘታቸውን ይናገራሉ። ነገር ግን ገዥና ተገዥ ሁሉም (ባባቴ ፊት) በእግዚአብሔር ፊት እኩል ናቸው፥ ምንም ልዩነት የላቸውም ብሎ ስለሚያስተምር የግርማዊነትህ አጥፊ ሳይሆን አይቀርም በማለት ብዙ ሰዎች እየመጡ ይነግሩኛል። ስለዚህ ጉዳይ ብታዝዘኝ ወዲያውኑ ትእዛዝህ የሚፈጸም ይሆናል። ጤና ሁን፥ ፒ ሌንቱሎ”
በቤተ ክርስቲያን አባቶች የታሪክ መዝገብ ደግሞ ስለ ጌታ ሥዕል በተአምራታዊ አገላለጥ የተጻፉ ብዙ አስተያየቶች አሉ። ከነዚህም ውስጥ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ አውሳብዮስ እንደጻፈው አብጋር የተባለው የዑር ንጉሥ ከደዌው የተፈወሰው የጌታን ሥዕል ባየ ጊዜ ነው ይላል። ሙሉው ታሪክ እንደሚከተለው ነው። “አብጋር” ስመ መንግሥት ነው። ዓፄ ጃንሆይ እንደ ማለት ነው፤ “አባጋር” እንዲሉ ዛር አንጋሹን። ዑር በእመስጰጤምያ የምትገኝ ትንሽ ከተማ ናት። ጽርዓውያን “ኤዴሣ” ይሏታል፥ በኛም “ሮሐ” ትባላለች። አብጋሮች በዑር መንገሥ የጀመሩት ከ፩፻፴፪ – ፪፻፲፮ ከጌታ ልደት በኋላ ነው። በጌታ ጊዜ የነበረው አብጋር ዮካማ (ዑካማ) ይባል ነበር። አምስተኛው ወይም ሰባተኛው አብጋር ነው። ይህ አብጋር ዮካማ ከጌታ ጋር ይጻጻፍ እንደነበር አውሳብዮስ ይተርካል። አውሳብዮስ ታሪኩን ሰፋ በማድረግ ሲያብራራ እንዲህ ይላል። በማይድን በሽታ ተይዞ የሚሰቃይ በኤፍራጥስ ወንዝ በላይ የነገሠ አብጋር ንጉሥ ነበር። በዘመኑ ለነበረው ለጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ መልእክት (ጦማር) ጽፎ የግል ታማኙ ለነበረው ለግምጃ ቤቱ ሹም ሰጥቶ ወደ ኢየሩሳሌም ላከው። ይህ ሰው በአብጋር ቤተ መንግሥት ሥዕል በመሳል የታወቀ ነበር። ደብዳቤው እንዲህ የሚል ነው፦ “ስለ አንተና ስለምታደርገውም ተአምራት እሰማለሁ፥ ያንተ ማዳን እንደሌሎች ዐቀብተ ሥራይ ስር ምሰህ፥ ቅጠል በጥሰህ አይደለም። አንተ ያዳንኸው ተረፈ ደዌ የለበትም። እንደሰማሁት ዕውራን እንዲያዩ ታደርጋለህ፥ ልሙጻንን ታነጻለህ፥ ርኩሳን መናፍስትን ታሳድዳለህ፥ በማይድን በሽታ የተያዙትንም በምሕረትህ ትፈውሳቸዋለህ፥ ሙታንን ታነሣለህ። ስለዚህ ወደኔ እንድትመጣና ከዚህ ከሚያሰቃየኝ ደዌዬ እንድትገላግለኝ፥ ለእኔም ምሕረት እንዲደርሰኝ ይህችን የልመና ደብዳቤ ጻፍሁልህ። አይሁድ ባንተ ላይ ክፉ ነገር እንዳሰቡና ክፉ ሊያደርጉብህም እንደከጀሉ እሰማለሁ፥ ከተማዬ በጣም ትንሽ ናት፥ ትነስ እንጂ በጣም ውብ ናት፤ ለሁለታችን ትበቃናለች፥ እባክህን ና።” የሚል ደብዳቤ ጽፎ ለጌታ ላከለት። ጌታም የሚከተለውን መለሰለት። “አብጋር ሆይ፥ ሳታየኝ ስላመንህብኝ ብፁዕ ክቡር ነህ፥ ስለእኔ ተጽፏልና የሚያዩኝ እንዲንቁኝ፥ የማያዩኝ ግን እንደሚያምኑብኝ። በኔ ያመኑ ሕያዋን ሁነው ይኖራሉ። እኔም አስቀድሜ የመጣሁበትን ሥራ መፈጸም አለብኝ፥ ከፈጸምሁም በኋላ ወደላከኝ እሄዳለሁ። ከሄድኩ በኋላ ከደዌህ እንዲፈውስህና ላንተና ለቤተ ሰዎችህም የሕይወትን ቃል እንዲያስተምራችሁ ከደቀ መዛሙርቴ አንዱን እልክልሃለሁ። ከተማህም የተባረከች ትሆናለች፥ ጠላቶችህ አይገዟትም።” ብሎ መልስ ላከለት። ጌታ ካረገ በኋላ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ቶማስ (ዕፃው በእስያ ስለነበር) ከሰበአ አርድእት አንዱን ታዴዎስን ወደ ዑር ላከው፤ ታዴዎስም እዚያ እንደ ደረሰ ለጊዜው ያረፈው ጥንት በፍልስጥኤም በሚያውቀው በአንድ አይሁዳዊ ቤት ነበር። ከዚያ ሁኖ በማስተማርና ተአምራት በማድረግ ጥቂት እንደቆየ ወደ ቤተ መንግሥት ሄደ። ታዴዎስ ገና ሲገባ ንጉሡ አብጋር አስደናቂ ግርማ በታዴዎስ ገጽ ላይ አየ። በቤተ መንግሥቱ የነበሩት ባለሟሎቹና የወንድ መኳንንት፥ የሴት ወይዛዝርት ግን ምንም እንኳ ለአብጋር የተገለጸው ባይገለጽላቸውም፥ ታዴዎስ እዚያ በመገኘቱ አንክሮና ተመስጦ ሳያድርባቸው አልቀረም። ንጉሡና ታዴዎስ ሲወያዩ ከቆዩ በኋላ በመጨረሻ ታዴዎስ፦ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እጄን እጭንብሃለሁ ብሎ እጁን ጫነበት፥ በዚህ ጊዜ አብጋር ከነበረበት ሁሉ ደዌ ተፈወሰ። ታዴዎስም የሕይወትን ቃል እያስተማረ በዚያች ቦታ ብዙ ቆዩ። የከተማዪቱም ነዋሪዎች ክርስቲያኖች ሆኑ፥ አውሳብዮስ ታሪኩን ከዚሁ ላይ ያበቃል።
ሌሎች የኋላ አባቶች ግን ይህን ታሪክ ሳይለውጡ፥ አብጋር ወደ ጌታ የላከው ሰው ሠዓሊ ስለነበር፥ ወዲያው ጌታን ሲያይ ልቡ ስለተመሰጠ ሥዕሉን በንድፍ ለማስቀረት ፈለገ። ጌታን በሚያነጋግርበት ጊዜ ዓይኑን ጣል እያደረገ የጌታን ገጽ በወረቀት ነድፎት ነበር። ወደ ሀገሩ ሲመለስ ያንን ለአብጋር አሳየው፥ እሱም ባየው ጊዜ በፍጹም እምነት ከመሬት ወድቆ ሰገደ፥ ያን ጊዜም ከደዌው ተፈወሰ ይላሉ። ከዚህ በማያያዝ ይህ ሥዕል ገባሬ ተአምር ስለሆነ ሁሉ ሊሰግድለት ይገባል ብሎ በሕዝብ መሰብሰቢያ አደባባይ ከፍ ያለ ቦታ አበጅቶ እዚያ ላይ እንዲሰቀል አዘዘ፥ በአብጋርና በልጁ ዘመነ መንግሥት ሁሉም እየመጣ ለዚህ ሥዕል ሲሰግድ ኑሯል።
አውሳብዮስ ዘቂሣርያ ስለጌታ ሥዕል ሌላ ምንጭ ያመለክተናል፤ እሱ እንደሚለው፥ “በወንጌል የታወቀችው እንተ ደም ይውኅዛ ውለታ ለመክፈል ስትል የቅርጽ ሐውልት አሠርታለት ነበር” ይላል። የቤሮኒኪም ታሪክ ለጌታ ሥዕል ጥሩ መነሻ ነው። ጌታ በዕለተ ዓርብ ደሙን እያንጠፈጠፈ መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ጐልጐታ በሚወጣበት ጊዜ መስቀሉ ከብዶት፥ ደሙ ዓይኑን ጋርዶት አይታ ልቧ በሐዘን ስለተነካ ለተከተሉት ለአንዱ ቤሮኒኪ ሻሿን አውልቃ ፊቱን እንዲያድፍበት ወረወረችለት፥ አድፎ ሲመልስላት ገጹ ከሻሿ ላይ ታትሞበት ቀረ ይባላል። ስለ ጌታ ሥዕል መነሻ ታሪካዊና ተአምራታዊ ምንጮች ብዙ አሉ። ዮሐንስ ወንጌላዊና ጴጥሮስ በባዶው መቃብር ውስጥ ገብተው ባዩት ጌታ ተገንዞበት በነበረው ከፈንና (ሰበን) መጠምጠሚያ ላይ የጌታ አካል ታትሞበት ነበር፥ የሚል የቤተ ክርስቲያን ትውፊት አለ። ስለ ጌታ ሥዕል የት መጣ ከመሉ በከፊሉ ይህ ነው። ስለ እመቤታችን ሥዕል ደግሞ በመጀመሪያ የሣላት ሉቃስ ነው ይባላል። በኛም ቤተ ክርስቲያን ያሉት የመዝሙርና የጸሎት መጻሕፍት የእመቤታችንን ሥዕል ሉቃስ መሣሉን ይናገራሉ። “ሰላም ለሥዕልኪ እንተ ሠዐላ በዓዱ፥ ሉቃስ ጠቢብ እምወንጌላውያን አሐዱ፤” ይላል። 
ከወንድማችን ዘማርያም ዘለቀ የተገኘ ተጨማሪ ስለስእል የጥንታዊቷ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ
፡-St John of Damascus (ቅዱስ ዮሐንስ ዘደማስቆ) wrote:
“Some people reprove us for honouring images of the Saviour, of the Mother of God and other holy servants of Christ. But let them think for a moment. In the beginning God created humanity in his own image. Why ever should we have
such respect for one another, if not because we are made in the image of God?
In Basil’s(የባስልዮስ) words, ‘the honour paid to the image is in reality paid to its prototype,’ that is to say, to what the image represents. Thus the Jewish people revered the Tabernacle because that, much more than the rest of creation, was an image of God.
The making and the veneration of images are not a novelty. They are based on a very ancient tradition.
St Ignatius, bishop of Antioch, (ቅዱስ አግናጥዮስ ዘአንጾኪያ) made the comment: “He who possesses in truth the word of Jesus, can hear even its silence.”
Regarding the use of symbols in iconography, one of the church fathers explains: “There are no words, nor lines which could represent the Kingdom of God, as we represent and describe our world. Both theology and iconography are faced with a problem, which is absolutely insoluble –to express by means belonging to the created world, that which is infinitely above the creature. On this plane, there are no successes, for the subject itself is beyond comprehension, and no matter how lofty in content and beautiful an icon may be, it cannot be perfect, just as no word or image can be perfect. In this sense both theology and iconography are failures. Precisely in this failure lies the value of both alike; for this value results from the fact that both theology and iconography reach the limit of human possibilities and prove insufficient. Therefore the methods used by iconography for pointing to the Kingdom of God, can only be figurative and symbolical, like the language of the parables in the Holy Scriptures.” In the Coptic Church, icons follow certain symbolism that carries a theological message.
St Ambrose(ቅዱስ አምብሮስ) writes of her: “The life of Mary shines forth as from a mirror, all the beauty and chastity and the pattern of every virtue.”
Thus, it is not surprising that St Jacob of Sarug(ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ) expressed: “How could I paint the picture of this marvellous, beautiful one with ordinary colour? Too exalted and too glorious is the image of her beauty!”
Mary is found in many icons, most frequently holding Christ. And although the icons have numerous variations, she always has one hand which motions towards her son – the action that sums up her entire life to the present day.
Thus, in conclusion, icons in the Orthodox tradition are not to be taken as pieces of artistic device, but rather, as windows or doors into spiritual world. They are designed to enhance the spiritual life of the believer through emulating the virtues of the icon’s prototype. And therefore, icons can be a blessing in our lives if we use them in a spiritual way.
እግዚአብሔር ለኹላችንም ትሑት ስብእና ቅን ሕሊና አስተዋይ ልቡና ይስጠን፡፡ አሜን፡፡
ስምዓት(ምንጭ)- መጽሐፈ ጥበብ፤ ዘአስተጋብእዎ አኀው ማኅበረ ቢዘን፤ ገጽ.49-51.
– “THE SPIRITUALITY OF ICONS”, By His Grace Bishop Daniel

ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ
(በአባ ጎርጎርዮስ የተዘጋጀ፤ ፲፱፻፸፬ እና ፲፱፻፹፮ ዓ.ም. የታተመ።

የቅዱሳት ሥዕላት አሳሳል በቤተክርስቲያን

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የራሷ ፊደል ፣ዜማ፣ … ወዘተ.. እንዳላት ሁሉ የራሷ የሆነ ሥነ ሥዕላትም አሏት ፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በቤተክርስቲያን ቅዱሳን ሥዕላት እንዴት እንደሚሳሉ እመለከታለን ፡፡
ሀ. ቅዱሳን ሥዕላት በቤተክርስቲያን ከሚሳሉበት ዓላማ አንዱ ለትምህርት ነው፡፡ ምሥጢረ ሥላሴን፣ ምሥጢረ ሥጋዌን ነገረ ማርያምን፣ ክብረ ቅዱሳንን የሚያስረዱ ናቸው
ምሳሌ 1. ፡- የሥላሴ ሥዕል ሲሳል በመለኮት አንድ በአካል ሦስት መሆናቸውን ማስረዳት አለበት ፡፡ አንድነታቸውን ለመግለጥ በአንድ መንበር እንደተቀመጡ ሦስነታቸውንን ደግሞ ለመግለጥ ሦስቱም ዓለምን በቀኝ እጃቸው እንደያዙ የሦስቱም ፊት ወደ አንድ አቅጣጫ እየተመለከተ አካላዊ ገጽታቸው በተመጣጠነ ሁኔታ ይሣላል ፡፡ ብሉይ መዋዕልነታቸውን (የዘመን ባለቤት መሆናቸውን) ለማስረዳት በአምሣለ አረጋዊ ይሣላሉ ፡፡
ምሳሌ 2. የምስለ ፍቁር ወልዳ ሥዕል ሲሳል እመቤታችን ከጌታ ቀኝ ጌታን በግራዋ ታቅፋ ነው ይኸውም ‹‹ ወትቀውም ንግሥት በየማንከ ንግሥቲቱ በቀኝ ትቆማለች›› ብሎ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት የታነገረውን ያጠይቃል ፡፡ መዝ 44፡9
ምሳሌ 3. ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ መነሳቱ ሲሳል መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በስልጣኑ የተነሳ መሆኑ ለማጠየቅ የተዘጋ መቃብር የጲላጦስ ማሕተም(”ጲ“ የሚለው) ታትሞ ይታያል ማቴ 27፡ 65 ከእንግዲህ ሠላም ሆነ የሚለውን ብስራት ለማስረዳት ጌታችን ነጭ ለብሶ በትረ መስቀል እንደያዘ ይታያል ፡፡
ምሳሌ 4. ቅዱሳን መላእክት ደግሞ ከሠሩት ሥራ ዐቢይ የሆነውን በማሳየት ይሳላሉ ቅዱስ ሚካኤል ዲያብሎስን ድል ሲያደርገው ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ሲያበስራት ፣ሠለስቱ ደቂቅን ከእቶን እሳት ሲያድናቸው ፣ ቅዱስ ዑራኤል ለዕዝራ ሱቱኤል ጽዋ ልቡናን ሲያጠጣው ቅዱስ ፋኑኤል ለእመቤታችን በቤተመቅደስ ሕብስት ሰማያዊን ጽዋ ሰማያዊን ሲመግባት . . . ወዘተ
ምሳሌ 5. ቅዱሳን ጻድቃን ብዙውን ጊዜ የሚሳሉት ሲጸልዩ ወይንም ከአጋንንት ጋር ሲጋደሉ ፣ መስቀል ፣ መጽሐፍ ፣ ማዕጠንት ይዘው የደረሱበትን ደረጃ ለማጠይቅ ወይም ክንፍ አውጥተው ወይም ሲያርጉ ወዘተ ይሳላል ፡፡
ምሳሌ 6. ቅዱሳን ሰማዕታት አብዛኛውን ጊዜ በፈረስ ላይ ሆነው ይሳላሉ ‹‹ሰማይም ተከፍቶ አየው እነሆም አንባ ላይ ፈረስ የተቀመጠበትም የታመነና እውነተኛ ይባላል ፡፡ በጽድቅም ይፈርዳል ይዋጋልም ፡፡ … በሰማይም ያሉት ጭፍራዎች ነጭ እና ጥሩ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ ለብሰው በአምባላዮች ፈረሶች ተቀምጠው ይከተሉት ነበር፡፡›› ራዕ 19፡11-14 እንዳለ፡፡ ለምሳሌ
ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ቅዱስ ጊጋር፣ቅዱስ ፋሲለደስ፣ቅዱስ መርቆሪዮስ… ወዘተ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲን ቅዱሳት ሥዕላት የሥዕሉን ባለቤት ማንነት ወይም ተጋድሎ በረድኤተ እግዚአብሔር አጋዥነት የፈጸመውን የጽድቅ ሥራ በሚገባ ከማሳየት አንጻር ይሳላሉ ፡፡ የልዑል እግዚአብሔር ከሆነ ደግሞ አንድነቱን ሦስትነቱን ፣ የሰውን ልጅ ለማዳን ከቤተልሔም እስከ ቀራንዮ ያደረገውን ጉዞ ኋላም ሞትን ድል አድርጎ በገዛ ሥልጣኑ መነሳቱን ቀጥሎም ወደ የማነ አብ ( በአብ ቀኝ ) በክበበ ትስብእት በይባቤ መላእክት ማረጉን የሚገልጡ ሥዕላት ይሳላሉ ፡፡
ለ. አቋም ፡- በትውፊታቸው አሣሣል ቅዱሳን ሥዕላት አቋማቸው የተወሰነ ነው ፡፡ ሥዕለ እግዚእ / የመድኀኔዓለም / ከሆነ አክሊለ ሦክ እንደ ደፋ ቀይ ግምጃ ለብሶ አንገቱን ወደ ቀኝ አዘንሎ ይሣላል ፡፡ ሥነ ስቅለትም ከሆነ ጌታችን ቀይ ግምጃ አገልድሞ አንገቱን ወደ ቀኝ አዘንብሎ አክሊለ ሦክ እንደደፋ በቀኙ እመቤታችን በግራው ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊው ሆነው በእግረ መስቀሉ
አጽመ አዳም እንዲታይ ተደርጎ ይሣላል ፡፡
ምስለ ፍቁር ወልዳ ከሆነ ከሆነ ደግሞ እመቤታችን ጌታችንን ታቅፋ ከተሣለ በኋላ በግራና በቀኝ ቅዱስ ገብርኤልና ቅዱስ ሚካኤል ይሣላሉ ፡፡

ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤልም መላከ ዑቃቤዋ (ጠባቂ መላእክዋ ) ስለሆነ እና የመላእክት ሁሉ አለቃ በመሆኑ ሰይፍ ይዞ ከእመቤታችን በስተቀኝ ይታያል ፡፡የጌታችንን በጦር መወጋት ለማጠየቅ ጦር ይዞ የሚታይበት ጊዜ አለ ፡፡
ቅዱስ ገብርኤልምበፋንታው በአብሣሬ ትስብእት (ያበሠራት) ነውና አበባ ይዞ የጌታን መከራ ሲያጠይቅ ደግሞ መስቀል ይዞ ከእመቤታችን በስተግራ ይሣላሉ ፡፡ ነገር ግን የሥዕሉ ባለቤት እመቤታችን ናትና እርሷ ገዝፋ ስትታይ መላእክቱ ግን አንሰው ይታያሉ ፡፡
ይህም በሌሎች ቅዱሳት ሥዕላት ላይ የተለመደ ነው ፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደራጎኑን ከላይ ከጫፍ መስቀል ባለው ጦር በፈረሱ ላይ ሆኖ ሲወጋው ሲሣል ቤሩታዊት ደግሞ አነስ ብላ እዚው ላይ ትሳላለች ፡፡ ይህም የሥዕሉ ባለቤት አግዝፎ ከማሳየት አንጸር የተደረገ እንጂ የቅርበትና የርቀት መጠንን ለማንፀባረቅ አይደለም ፡፡
ሊቃነ መላእክት ሲሳሉ አለቅነታቸው ይታወቅ ዘንድ ሰይፍ ይይዛሉ ፡፡ በሙሉ ቁመት ልብሰ ተክህኖ እንደለበሱ ሆነው ይሳላሉ ፡፡ ይህም ጸሎት በሚያሳርጉ ዕጣን በማጠን በፈጣሪያቸው ፊት ስለ ሰውልጅ ምህረትን የሚለምኑ ናቸውና የክህነት ሥራ የሚሠሩ መሆናቸውን ለማጠየቅ ነው ፡፡ ሠራዊተ መላእክት የሆኑ እንደሆነ ከአንገት በላይ በግራና በቀኝ በተዘረጉ ክንፎቻቸው ቁጥራቸው
በዝቶ ይሣላሉ ፡፡ ይህ እልፍ አእላፋት ወትእልፊት አእላፋት መሆናቸውን ለማስረዳት ነው ፡፡
ቅዱሳን ጻድቃን ከሆኑ ደግሞ ከፈጸሙት ገድል ዐቢይ የሆነውን በሚያንፀባርቅ ሁኔታ ይሣላሉ ፡፡ ለምሳሌ ፡- አቡነ ተክለሃይማኖት በቀዊመ ጸሎት ብዛት እግራቸው መቆረጡን ለማሳየት በአንድ እግራቸው ቆመው ሲጸልዩ ይሳላሉ ፡፡
ከፊት ከኋላ ከግራ ከቀኝ ጦር ሰክተው ደከመኝ ብለው እንዳያርፉ ጦሩ እንዲወጋቸው ብለው ያደረጉትን ጽኑ ተጋድሎ ለማሳየት በግራና በቀኝ በኩል የጦር ምልክት ይታያሉ ፡፡ የተቆረጠውም እግራቸው እዚያው ይታይል ፡፡ በገድል ብዛት እግዚአብሔር የሰጣቸውን ስድስት ክንፍ በሚታይ ሁኔታ ይሣላል ፡፡
ሐዋርያ መሆናቸውን ለመግለጥ ደግሞ በአንድ እጃቸው መስቀል በሌላኛው ደግሞ መጽሐፍ ይሣላል፡፡
ይቆየን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ኦርቶዶክሳዊ የቅዱሳት ሥዕላት አሣሣል

ቅዱሳት ሥዕላት “ቅዱስ” እና “ሥዕላት” ከሚሉት ቃላት የተገናኘ ወይም የተሰናሰለ ቃል ሲሆን፤ሥዕል በቁሙ፣ መለክ፣ የመልክ ጥላ፣ንድፍ፣አምሳል፣ንድፍ ውኃ፣በመጽሔት፣ በጥልፍ፣በስፌት ወይም በቀለም በወረቀት ገዝፎ ተጽፎ፤ከእብን ከእፅ ከማዕድን ታንጦ፡ተቀርጦ ተሸልሞ አጊጦ የሚታይ የሚዳሰስ ነገር ነው።(ኪ.ወ.ክ፡673) ሥዕል ነጠላ ሲሆን ሥዕላት ደግሞ ብዛትን ያመለክታል።ቅዱሳት የሚለው ቃል ደግሞ “ቀደሰ” ከሚለው የግእዝ ግሥ የተወሰደ ሲሆን ትርጉሙም  ለየ፣አከበረ፣መረጠ ማለት ነው።ከዚህ በመነሳት ቅዱሳት ሥዕላት ለእግዚአብሔር የተለዩ፣የተቀደሱ፣ ልዩ፣ ምርጥ፣ንጹህና ጽሩዕይ የሆኑ የቤተመቅደሱ መገልገያ ንዋያተ ቅድሳት በመሆናቸው ቅዱሳት ተብለው ይጠራሉ።

ዳግመኛም የቅዱሳንን ታሪክና ማንነት በጊዜው ላልነበርን በመንፈስ ዓይን ፤እንድናይ ስለሚያደርጉን፤አንድም ሥጋዊውን ዓለም ከሚያንጸባርቁ ዓለምውያን ሥዕላት ፈጽመው የተለዩ በመሆናቸው፤አንድም የቅዱሳኑ ቅድስና ሥዕላቱን ቅዱስ ስላሰኛቸው፤አንድም በሥዕላቱ አድሮ እግዚአብሔር ስለሚፈጽማቸው ገቢረ ተዓምራት የተነሳ ሥዕላቱ “ቅዱሳት ሥዕላት” ተብለው ይጠራሉ።በአጠቃላይ በኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተውህዶ ቤተ ክርስቲያን “ቅዱሳት ሥዕላት” ተብለው የሚጠሩት የቅዱስ እግዚአብሔር፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ፣የቅዱሳን መላእክት፣የቅዱሳን ነቢያት፣የቅዱሳን ሐዋርያትና የሌሎች ቅዱሳን ጻድቃን ማንነት ሕይወትና ታሪክ የሚያሳዩ ሥዕሎች ናቸው።ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት እንደመሆኗ መጠን የምትፈጽማቸው አገልግሎቶችና ሥርዓቶች ዶግማና ቀኖናን እንዲሁም ትውፊትን መሰረት ያደረጉ ናቸው።ይህ ደግሞ ኦርቶዶክሳዊያን ቅዱሳት ሥዕላት በእግዚአብሔር ፈቃድ ሐዋርያዊ ቀኖናን ተከትለው የሚሳሉ የቤትክርስቲያን ንዋያተ ቅዱሳት ናቸው እንጂ እንዴው በዘፈቀደ የሚዘጋጁ የኪነጥበብ ስራወች አለመሆናቸውን ያስገነዝባል።

የቤተክርስቲያንን ሥላት ልዩ ከሚያደርጓቸው ገጽታወች መካከል አንዱ ትምህርተ ሃይማኖትን ጠብቀው መሳላቸ ነው።ዓላማቸው ወንጌልን ለመስበክ ለማስተማሪያነት ስለሆነ ሰፊውን ትምህርተ ሃይማኖት በሥዕል የሚገልጡ መሆን አለባቸው።ትምምህርተ ሃይማኖትን ያልጠበቁ ሥዕላት ከሆኑ ግን የሚያስተምሩት ትምህርት ኑፋቄ ስለሚሆን ቤተክርስቲያን አትቀበላቸውም።ለምሳሌ ቅድስት ሥልሴ ሲሳሉ አንድነታቸውና ሦስትነታቸው በሥዕል ይገለጣል።አንድነታቸውን ለመግለጽ ነደ እሣት የሚሆኑ ኪሩቤል በተሸከሙት አንድ መንበር እንደተቀመጡ ልብሳቸው ሳይነጣጠል፤ሦስትነታቸውን ዓለምን በቀኝ እጃቸው እንደያዙ ፣የሦስቱም ፊት ወደ አንድ አቅጣጫ እየተመለከቱ አካላቸው ገጽታቸው በተመጣጣኝ ሁኔታ ይሣላል። የጌታ ትንሳኤ ሲሳል መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ አለማለቱን ለመግለፅ የተዘጋ መቅብር ይታያል።በትንሳኤው ብርሃን ዓለምን የቀደሰ ነውና  ብርሃን ጨለማውን ሲገልጥ የሚያሳይ ተደርጎ ይሳላል።ሆኖም ግን በአንዳንድ የምዕራባውያን አብያተ ክርስቲያናት ሥዕላት ላይ የምንመለከተው የተከፈተ መቃብር ወይም መላእክት የመቃብሩን በር ለጌታችን ሲከፍቱለት የሚያሳይ ሥዕል ነው።ይህም በስልጣኑ አልተነሳም የሚል ትርጓሜን ይሰጣል።ይህ ደግሞ ትምህርተ ሃይማኖትን ስለሚፋልስ ቤተክርስቲያን አትቀበለውም።

በኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርቲያን ቀኖና መሰረት የቤተክርስቲያን ቅዱሳት ሥዕላት መልክና ቁመና ሲሣሉ ራሱን የቻለ ህግና ሥርዓት አለው።ቅዱሳት ሥላት ሲሣሉ በገሀዱ ዓለም የተለመደውን (realistic) የአሣሣል ዘይቤ አይከተሉም።ምክንያቱም የሥዕላቱ ዓለማ መንፈሳዊነትን መግለፅና ውክልና(religious symbols)እንጂ እውነተኛ መልካቸው እንዲህ ነው ለማለት ስለማይሳል ነው።የሚከብሩት በነፍሳቸው ባገኙት ክብር እንጂ በሥጋቸው ግዝፈትና ርቀት አይድለምና ።ከዚህ በተጨማሪ ጠይም፣ ጥቁር፣ ነጭ፣ቀይ፣ረጅም፣አጭር፣ወፍራም ወይም ቀጭን ወዘተ በሚለው ላይም አያተኩሩም።የቅዱሳት ሥዕላት ፊት ሲሳል  ሰፊና ክብ ተድርጎ ይሳላል።ሰፊና ክብ መሆኑ የፍጹምነት ምሳሌ አንድም መላ ሕይወታቸውን ለጽሎትና ለተመስጦ እንዳዋሉ ለመግለጽ ነው።ትልቅ፣ክብና ሰፊ ተደርገው መሳላቸው ለውክልና እንጂ ይህንን ይመስላሉ ለማለት ግን አይደለም።

ቅዱሳት ሲሣሉ ዓይናቸው ጎላጎላ ተደርጎ ይሣላል።ጎላ ጎላ ማለቱ ክፉውን ከደጉ፣ጨለማውን ከብርሃኑ ለይተው በተቀደሰው ጎዳና  በፍጹም አስተዋይ ልቡና የተጓዙ መሆናቸውን ለማመልከት፤አንድም ሥጋዊውንና መንፈሳዊውን ፣ረቂቁንና ግዙፉን ዓለም በግልፅ የማየት ጸጋ እንዲሁም ከሰው ልጆች ሕሊንና አእምሮ በላይ የሆነውን ረቂቅ መለኮታዊ ምስጢር በስፋት በማወቅ አቅምና ጣዕሙን የመረዳት ችሎታ ከቸሩ አምላክ በልግስና እንደተሰጣቸው እናስተውላለን።ከዚህ በተጨማሪ ዓይናቸው ጎላ ጎላ ማለቱ የተመልካቹን ምዕመን ልብ ለመሳብ፣ለመመሰጥ፣የመደመምን ስሜትና ፈሪሃ እግዚአብሔርን ለመፍጠር ይጠቅማል።ዓይኖቻቸው የሚያዩትም ወድ አንድ አቅጣጫ ብቻ ነው ።ይህም አንዲት መንግስተ ሰማያትን በአይነ ህሊና በመመልከት ለክብር እንደበቁ ለማመልከት ነው።ዳግመኛም አንዲት ርትዕት ኦርቶዶክስ ተውህዶ ሃይማኖትን ሳይፈሩና ሳያፍሩ ያለ ጥርጥር ተቀብለውና መስክረው የኖሩ መሆንቸው እንዲሁም ጥርጥር በልባቸው አለመኖሩን ያጠይቃል።የተረዳች የቀናች ሃይማኖትን ጥብቀው ያስጠበቁ በክብር  ወደ ዘላለም ርስት ያቀኑ በመሆናቸው ወደ አንድ አቅጣጫ እየተመለከቱ ይሳላሉ።ዓይን የሰውነት መብራት ናት እንዲል።(ማቴ 6፡22)

በሥዕሉ ባለቤት ራስ ዙሪያ ላይ የምንመለከተው ጸዳለ ብርሃን (አክሊለ ብርሃን) ደግሞ ቤበተክርስቲያናችን የቅድስና ማዕረግ እንደተሰጣቸው ያጠይቃል።ነገር ግን በቅድስት ስላሴና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የሚደረገው ፀዳለ ብርሃን የእግዚአብሔር ቅድስና የባህርይው መሆኑን እንደሚገልፅ መረዳት ያስፈልጋል።እኔ እግዚአብሔር አምልካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ እንዲል። (ዘሌ 19፡2፣ 1ዼጥ 1፡15-16)  በአጠቃላይ ሥዕሎቻችን በኪነ ጥበብ ዘርፍ የተለመደውን የተከያዩ ህዋሳተ አካልን ትክክለኛ መጠን ላይጠብቁ ይችላሉ።ይህ የሚሆነው  ደግሞ ሥዕላቱ ውክልና ሃይማኖታዊ ምልክቶች በመሆናቸው፤አንድም ሥዕላቱ የሚሳሉት ቅዱሳን ይህንን ይመስላሉ ይህንን ያክላሉ ለማለት አይደለምና ፤አንድም የሚያስተዋዉቁን ከመንፈሳዊው ዓለምና ጣዕመ ጻጋ ጋር እንጂ ከምድራዊው ዓለም ጋር ባለመሆኑ ነው።በመሆኑም በቅዱሳት ሥዕላቱ ላይ ሊተላለፍ የተፈለገውን  ልዩና ጥልቅ መንፈሳዊ መልክእክት በመረዳት ተገቢውን አክብሮት መስጠት ይገባል።

በቤተክርስቲያናችን ቀኖና መሰረት አብዛኛውን ጊዜ የምንጠቀማቸው ቀለማት፦ ሰማያዊ፣ቀይ፣አርንጓዴ፣ቢጫና ነጭ ሲሆኑ ቀለማቱ ራሱን  የቻለ ምስጢር ወይም ትርጉም አላቸው ።

1) ሰማያዊ፦ሰማያዊውን ሃብት ግነዘብ ለማድረግ በፈቃደ ነፍስ መመራትን ለማመልከት እንዲሁም በመንፈስ ፍሬወች ፈቃደ ሥጋን በፈቃደ ነፍስ ድል ማድረጋቸውን፤አንድም ትህትናን ያሳያል። ቅዱሳን በትሕትና ለመኖራቸው ማሳያ ነው ።በመሆኑም ይህ ቀለም መንፈሳችን በእምነት መንገድና በትህትና  የመንፈስ ፍሬዎችን ገንዘብ በማድረግ እንድንጓዝ ያስታውሰናል።

2)ቀይ፦ሰማዕትነትን ያሳያል።ይህም ቅዱሳን ነፍሳቸውን ለመከራና ለሞት አሳልፈው ስለክርስቶስና ስለቤተክርስቲያን ብለው መስጠታቸውን ለማመልከት ይህን ቀለም እንጠቀመዋለን።የመስዋዕትነት የነፃ አውጭነት ምልክት ነው።ጌታችን በሸንጎ ፊት ቆሞ የለበሰው ልብስ ቀይ ሐር እንደነበር።(ማር 15፡16-17፣ ኢያ2፡18)

 3)ቢጫ ፦ይህ ቀለም እውነተኛነትንና ብርሃንነትን ይገልፃል።እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ እንዲል (ማቴ5፡14)። ከዚህ በመነሳት ቤተክርስቲያን የቅድስና ማዕረግ ላይ የደረሱትን ቅዱሳት እውነተኞችና የዓለም ብርሃን ናችሁ ስትል በራሳቸው የብርሃን አክሊል በቢጫ አድርጋ  ትሥላለች።

4)አረንጓዴ፦ከልምላሜ ከፀደይ ጋር ስለሚያያዝ መንፈስዊ ትርጉሙ መታደስን አዲስ ሕይወትን፣ድህነትንና ተስፋን ያሳያል።በዚህ መሰረት አረንጓዴነትና ሕይወት ተወራራሽ ይሆናሉ።

5)ነጭ፦የድል አድራጊነት የንፅህና እና የፍጹምነት ምሳሌ ነው።ቅዱሳን ዓለምንና ምኞቱን ድል ያደረጉ ልበ ንጹሃን በመሆናቸው ነጭ ልብስ ለብሰው ይሳላሉ።ነጭ ልብስ ለብሰዋል ፤ከአለቆቹም አንዱ “እነዚህ ነጫጭ የለበሱት እነማን ናቸው? ከየት መጡ?” አለኝ።እኔም “አቤቱ አንተ ታውቃለህ” አልኩት። እርሱም “እሊህ ከጽኑ መከራ ነጻ የወጡ ልብሳቸውንም በበጉ ደም አጥበው ያነጹ ናቸው።”አለኝ። መለኮታዊ ክብርንም ያሳያል።ለምሳሌ በደብረታቦርና በትንሳኤ ሥዕሎች ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነጭ ልብስ ለብሶ ይሣላል።

በትውፊታዊ አሣሣል ቅዱሳት ሥዕላት ድርሰት ላይ የቅዱሳኑ አቋማቸው (በሥዕሉ ላይ የሚገኝበት ሥፍራ)የተወሰነ ነው።ለምሳሌ የስነ ስቅለት ሥዕል ከሆነ ጌታችን ቀይ ግልድም አድርጎ፤አንገቱን ወደ ቀኝ አዘንብሎ፤አክሊሊ ሦክ እንደደፋ፤በቀኙ እመቤታችን በግራው ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ሆነው።በእግረ መስቀሉ አፅመ አዳም እንዲታይ ተደርጎ ይሣላል። ምስለ ፍቁር ወልዳ ከሆነ ደግሞ እመቤታችን ጌታን ታቅፋ ከተሳለች በኋላ በግራ በቀኝ ቅዱስ ገብር ኤልና ቅዱስ ሚካኤል ይሣላሉ።ሆኖም ግን ይህ ሁሉም የሥዕል ድርሰት ላይ የቅዱሳን አቋማቸው የተወሰነ ነው  ማለት ግን አይደለም።ስለዚህ ቅዱሳት ሥዕላት ከላይ የተጠቀሱትን ቀኖናን ተከትለው  ይሣሉ ዘንድ ይገባል።እይንዳንዱ ምዕመንም የራሱ የሆነውን ትምህርተ ሃይማኖትን ታሪክንና ትውፊትን የጠበቁትን ሥዕላት ማወቅና መረዳት ይኖርበታል።ያወቀውን ደግሞ ላላወቁት በማሳወቅ አባቶች ያስቀመጡት ድንበር እንዳይደፈር መጠበቅ ይኖርበታል። የቀደሙት አባቶች የሰሩትን ድንበር አታፍርስ እንዲል ምሳ 22፡28።

ምንጭ፦ ኦርቶዶክሳዊ ቅዱሳት ሥዕላትአዘጋጅ፦ኃይለማርያም ሽመልስ ካሳ

‹‹አንተም÷ የሰው ልጅ ሆይ÷ ጡቡን ወስደህ በፊት አኑራት፤ የኢየሩሳሌምንም ከተማ ሥዕል ሳልባት፤ ክበባት›› (ሕዝ.፬፥፩)

ቅዱሳት ሥዕላት አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈጸምባቸው ንዋያተ ቅድሳት ናቸው፡፡ እስራኤላውያን ቀደም ሲል ሰዎች ድንጋይን በማዘጋጀት፣ እንጨትን በመጥረብ፣ ቆዳን በመፋቅ፣ ኅብር ባላቸው ቀለማት በመሳል ለትውልድ እንዲተላለፉ ያደርጉ ነበር፡፡ የቅዱሳት ሥዕላት አጀማመር ዘመነ ኦሪትን መነሻ ያደረገ ነው፤ አስቀድሞ ልዑል እግዚአብሔር ለነቢዩ ሙሴ በታቦተ ሕጉ ላይ ሥዕለ ኪሩብን እንዲሥል አዘዘው፡፡ ‹‹ከስርየት መክደኛውም ጋር አንዱን ኪሩብ በአንድ ወገን÷ ሁለተኛውንም ኪሩብ በሌላው ወገን አድርገህ በአንድ ላይ ትሰራዋለህ፡፡ ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ ይዘረጋሉ፤ የስርየት መክደኛውንም በክንፎቻቸው ይሸፍናሉ፤ ፊታቸውም እርስ በርሱ ይተያያል፤ የኪሩቤልም ፊቶቻቸው ወደ ስርየት መክደኛው ይመለከታሉ››፡፡ (ዘጸ. ፳፭፥፲፱-፳)

ስለ ቅዱሳትሥዕላት አጀማመር በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፡፡ ‹‹በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ ቁመታቸው አሥር ክንድ የሆነ ከወይራ እንጨት ሁለት ኪሩቤልን ሠራ፡፡ የኪሩብም አንደኛው ክንፍ አምስት ክንድ÷ የኪሩብም ሁለተኛው ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፤ ከአንደኛው ክንፍ ጫፍ ጀምሮ እስከ ሁለተኛው ክንፍ ጫፍ ድረስ አሥር ክንድ ነበረ፡፡ ሁለቱም ኪሩቤል አንድ ልክና አንድ መልክ ነበረ፡፡ የአንዱ ኪሩብ ቁመት አሥር ክንድ ነበረ÷ የሁለተኛውም ኪሩብ እንዲሁ ነበረ፡፡ ኪሩቤልንም በውስጠኛው ቤት አኖራቸው፤ የኪሩቤልም ክንፎቻቸው ተዘርግተው ነበር፡፡ የአንዱም ኪሩብ ክንፍ አንደኛውን ግንብ ይነካ ነበር÷ የሁለተኛውም ኪሩብ ክንፍ ሁለተኛውን ግንብ ይነካ ነበር፤ የሁለቱም ክንፎች በቤቱ መካከል እርስ በርሳቸው ይነካኩ ነበር፡፡ ኪሩቤልንም በወርቅ ለበጣቸው፡፡ በቤቱም ግንብ ሁሉ ዙሪያ በውስጥና በውጭ የኪሩቤልና የዘንባባ ዛፍ የፈነዳም አበባ ምስል ቀረጸ››፡፡(፩ኛ ነገሥት ፮፥፳፫-፳፱) በትንቢተ ሕዝቅኤልም ‹‹አንተም÷ የሰው ልጅ ሆይ÷ ጡቡን ወስደህ በፊት አኑራት፤ የኢየሩሳሌምንም ከተማ ሥዕል ሣልባት፤ ክበባት›› ይላል ሕዝ.፬፥፩)፡፡

በጥንት ዘመን ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪክ በዋሻ ውስጥ በሥዕል እያስደገፉ ያስተምሩ ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር ለእምነታቸው ሲሉ ለተጋደሉ እና መሥዕዋትነትን ለከፈሉ ቅዱሳን መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ሥዕል በመሣል ታሪካቸውን አስቀምጠዋል፡፡ ክርስቲያኖች ይህንን እያደረጉ ለዘመናት ከቆዩ በኋላ በስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በሮማውያን ክርስቲያኖች እና በቢዛንታይን ክርስቲያኖች ዘንድ አለመግባባት ተፈጠረ፡፡ በዚህም ዘመን ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች ቅዱሳት ሥዕላትን ምክንያት በማድረግ በሁለት ጽንፍ ተከፈሉ፡፡ የመጀመሪያዎቹ ኢኮኖላትሪያ ሲባሉ እነዚህም ክርስቲያኖች ቅዱሳት ሥዕላትን ከመጠን በላይ አብዝተው ከመውደዳቸው የተነሳ እንደ አማልክት የሚቆጥሩ ናቸው፡፡ ሁለተኛዎቹ ደግሞ ኢኮኖማኺያ ሲባሉ እነዚህም ክርስቲያኖች ቅዱሳት ሥዕላት ከነጭራሹ አያስፈልጉም በማለት ከአምልኮት ሥፍራ መወገድ አለባቸው የሚል አመለካከት የያዙ ነበሩ፡፡ ይህም አለመግባባት ለረጅም ዘመናት ከቀጠለ በኋላ በ፯፻፹፯ እ.ኤ.አ ሁለተኛው የኒቅያ ጉባኤ ተደርጎ ለቅዱሳት ሥዕላት አክብሮት እና ስግደት እንደሚገባ ተወሰነ፡፡ በዚህም ጉባኤ መሠረት ቅዱሳት ሥዕላት በቤተክርስቲያን ውስጥ የእግዚአብሔር ክብሩ መገለጫ ሁነው የሚያገለግሉ የቅድስት ሥላሴ፤ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ፤ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፤ የቅዱሳን መላእክት፤ የነቢያትና ሐዋርያት የጻድቃንና ሰማዕታት ሥዕላት ናቸው፡፡ (ዐምደ ሃይማኖት ምዕራፍ ፲፫)

በቅድስት ቤተክርስቲያን የምንገለገልባቸው ቅዱሳት ሥዕላት የተሣሉት ባለቤቱ እግዚአብሔር በመረጣቸው ሰዎች አማካኝነት ነው፡፡ ለምሳሌ ያህልም ለመጀመሪያ ጊዜ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የስቅለቱን ሥዕል ለንጉሥ ጢባርዮስ የሣለው ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ነበር፡፡ ቅዱሳት ሥዕላት ቀኖና ቤተክርስቲያንን መሠረት ያደረገ የአሣሣል እና የአጠቃቀም ሥርዓት አላቸው፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ ስለሚሰቀሉ ምእመናን በሥዕሉ ፊት በመቆም የሚጸልዩበትና ልመናቸውን የሚያቀርቡበት ነው፡፡

ቅዱሳት ሥዕላት በሚሣሉበት ወቅት አስቀድሞ የቅድስና ባለቤት ልዑል እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ይኸውም የዕውቀት እና የጥበብ ባለቤት እርሱ ስለሆነ ሥዕላቱን ለመሣል የሚያስችል ጸጋ እንዲያድለን ነው፡፡ የቅዱሳት ሥዕላት የቀለም አጠቃቀምም በሥርዓተ ቤተክርስቲያን አንድምታ ያለው እንጂ በዘፈቀደ የሚሆን አይደለም፡፡ ለምሳሌ ያህል ቀይ ቀለም ለቅዱሳን፣ ለጻድቃን እና ለሰማዕታት ወኪል የሆነ ሰማዕትነትን እና ተጋድሎን የሚያሳይ ነው፡፡ በመሆኑም በሰማዕታት ሥዕላት ላይ ቀይ ቀለም በብዛት ሊስተዋል ይችላል፡፡ ነጭ ቀለም ንጽሐ ባሕርይን ስለሚያመለክት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እና በቅድስት ድንግል ማርያም የትንሣኤ እና የዕርገት ሥዕላት ላይ ሊስተዋል ይችላል፡፡ ሰማያዊ ቀለም የእግዚአብሔርን ዘለዓለማዊ አምላክነት እና ቀዳማዊነት ስለሚያመለክት በቅድስት ሥላሴ ሥዕለ አድኅኖ ልንመለከተው እንችላለን፡፡ የቅዱሳት ሥዕላት የአሣሣል ልኬት መጠን እንደ አስፈላጊነቱ ሊተልቅ ወይም ሊያንስ ይችላል፡፡ በጸሎት መጻሕፍት ላይ የመጽሐፉን መጠን መሠረት ያደረገ ሲሆን በሕንጻ ቤተክርስቲያን ላይ ደግሞ የሕንጻውን መጠን መሠረት አድርጎ ሊቀመጥ ይችላል፡፡

ቅዱሳት ሥዕላትን ለጸሎት እና ለተለያዩ አገልግሎቶች በምንጠቀምበት ጊዜ ልናስተውላቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ፡፡ በዋነኛነትም እንዳይበላሹ እና እንዳይደበዝዙ በክብር ማስቀመጥ አስፈላጊ ነው፡፡ ሥዕላቱ የሚገልጹት የሥዕሉ ባለቤት የሆነውን አምላክ ወይም ቅዱስ፤ ጻድቅ ወይም ሰማዕት ስለሆነ ተገቢውን ክብር እና ሥርዓተ አምልኮ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ ምእመናን ትክክለኛዎቹን የሥዕሉን ባለቤቶች አውቀው እንዲያከብሩ እና እንዲማጸኑባቸው ሠዓሊዎች የሚሥሉትን ቅዱስ ሥዕል በትክክል መሣልም አለባቸው፡፡ ሆኖም በአንዳንድ የአምልኮት ስፍራዎች ይህ እየተተገበረ አይደለም፡፡ የአንድ ቅዱስ ሥዕልን በማስመሰል ሁለት ወይም ሦስት አይነት ሥዕል ይሳላል፡፡ ለዚህም ምሳሌ በቅድስት አርሴማ ሥዕል ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህም በምእመናን ዘንድ አነጋጋሪ ርዕስ ከመሆኑም ባሻገር የእርሷ ሥዕል አለመሆኑን ጭምር የሚሟገቱ ምንጮች ተነሱ፤ በስተመጨረሻ ሁላችንም የቅድስት አርሴማ ብለን የተቀበልነው ሥዕል የቅድስት ባርባራ ነው የሚል ድምዳሜ ላይም ደረሱ፡፡

ከዚያም በተጨማሪ በአሁኑ ጊዜ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ያልጠበቁ እና ከአኃት ምስራቃውያን የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሥርዓት ውጪ የሆኑ ሥዕላት በስፋት ይታያሉ፡፡ ለምሳሌ ያህልም በምዕራብ አውሮፓ በካቶሊካውያን በስፋት የሚስተዋሉ ከኦርቶዶክሳዊ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ውጪ የሆኑ ሥዕላት አሉ፡፡ ለዚህም እንደ ማስረጃ ሆኖ የሚጠቀሰው የጌታችን እና አምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሥዕል ሲሆን ባለ ሁለት ጣት ምስሎች ለሽያጭ እየቀረቡ ነው፡፡ በምስራቃውያን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ባለአንድ ጣት ሥዕሎች ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ የሚለውን የተዋሕዶ ምሥጢር ስለሚያመለክት እየተጠቀምንበት እንገኛለን፡፡ (ምሥጢረ ተዋሕዶ) ትክክለኛውን ሥዕል ለይቶ አለማወቅ አምልኮተ ሥርዐቱ ላይ ተጽዕኖ ሊፈጥር ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን የማይወክሉ ሥዕላትን ከመጠቀም ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡ በዚህም እንደ መፍትሔ ልንወስደው የምንችለው በታሪክ የወረስናቸውን የመጀመሪያዎቹን ሥዕሎች በማመሳከር፣ ካህናትንና ሊቃውንትን በመጠየቅ ልንጠቀም ይገባል፡፡

ምንጭ፡- (ዐምደ ሃይማኖት በብርሃኑ ጎበና ፳፻ ዓ.ም.)

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top