ቤተክርስቲያን(Ecclesia) እና ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ (Apostolic Succession)

“ቤተክርስቲያን” የሚለው የግዕዝ ቃል ሲሆን “ቤት-” እና “ክርስቲያን” ከሚሉት ቃላት የተቀመረ ነው፡፡ ይህም በግሪክ አቅሌስያ (Ecclesia) ከሚለው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ቤት የሚለው ቃል ወገን፤ ነገድ፤ ዘር፤ ትውልድ፤ ጉባኤ፤ ማኅበር ማለት እንደሆነ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ላይ ጠቅሰዋል፡፡(ኪ.ወ.ክ ገጽ 268) የያዕቆብ ወገን ቤተ ያዕቆብ (ቤተ እስራኤል)፤የዳዊት ወገን ቤተ ዳዊት እንዲባል በመንፈሳዊና በምሥጥራዊ ልደት ከክርስቶስ የተወለዱ ምእመናንም ቤተ ክርስቲያን ይባላሉ፤ ቤተ ክርስቶስ (የክርስቶስ ወገን) እንደ ማለት ነው፡፡ ዘመናችን አማናዊቱ ቤተ ክርስቲያን ስምዋን ወስደው በሚጠሩ አስመሳዮች የተወረረችበት ወቅት በመሆኑ እውነተኛዋን ለይቶ ማወቅ ግድ ይላል፡፡ ብዙ መምህራን ቤተክርስቲያን የሚለው ቃል ሦስት ትርጉም አለው ብለው ያስተምራሉ፡፡
 
አንደኛው ትርጉም ፡- የክርስቲያን ቤት የክርስቲያን መሰብሰቢያ የክርስቲያን መገኛ ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት ክርስቲያኖች የሚጸልዩበት ሥጋ እና ደሙን የሚቀበሉበት የሚሰግዱበት ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት የጸሎት ቤት ማለት ነው፡፡ (ኢሳ. 56፡7፤ ኤር. 6፡10-16፤ ማቴ. 21፡13፤ ማር. 11፡17፤ ሉቃ. 19፡46 )
 
ሁለተኛ ትርጉም ፡– የክርስቲያን ወገን ክርስቲያን ሁሉ የሚጠራበት ስም ነው፡፡ ‹‹ ቤተ እስራኤል፣ ቤተ ያዕቆብ፣ ቤተ አሮን በማለት የሚጠሩት፡፡ (መዝ. 117፡3፤ ማቴ. 16፡18)
 
ሦስተኛ ትርጉም ፡– ቤተክርስቲያን ሲል ምዕመናንን ነው፡፡ ይህም ማለት ቤተክርስቲያን ከክርስቶስ የተገኘ እንደሆነ ነው፡፡ የክርስቲያን ወገኖች ቤተመቅደስ ማለት ነው፡፡ የእያንዳንዱ የክርስቲያኖችን ሰውነት የሚያመላክት ነው፡፡
 
ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ እንደሆናችሁ አታውቁምን›› 1ኛቆሮ. 3፡101

የቤተክርስቲያን ባሕርያት

 
“ ከሁሉ በላይ የምትሆን ሐዋርያት የሰበሰቧት አንዲት፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን” የሚለው አንቀጸ ሃይማኖት የቤተክርስቲያን ባሕርያት ለምንላቸው ጥቅል መጠሪያ ነው።
 
እነዚህም
የቤተ ክርስቲያን አንዲትነት
የቤተ ክርስቲያን ቅድስትነት
ቤተ ክርስቲያን  ኩሏዊትነት
ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊትነት

 

ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት!!
  • ቤተክርስቲያን አንዲት (አሐቲ) ናት፡፡
    • አይጨመርባትም፡ አይቀንስባትምም፡፡
    • አትከፈልም ፣ሁለት ወይም ሦስት ወይም ከዚያ በላይ አትሆንም፡፡
    • ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ …”በዚህ አለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እመሠርታለሁ” አለ እንጂ “ቤተክርስቲያኖቼን” አላለም፡፡ ማቴ 16፡18
  • በአንድ መሠረት ላይ አንዱ መሥራች የመሠረታት ስለሆነች ቤተክርስቲያን አንዲት ናት፡፡
  • ቤተክርስቲያን አንዲት ናት ሲባል በእርሷ ያለውን አንድነትም ያመለክታል፡፡
ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ናት!!
ክርስቶስ በቅዱስ ደሙ መሥርቷታል፤ አንጽቷታል፤ ቀድሷታልና ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ናት ኤፌሶን 5 ፥ 26፡፡
የቤተ ክርስቲያን ቅድስና የተገኘው ቅድስና የባሕርይ ገንዘቡ ከሆነው ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በመሆኑ ወደ እርስዋ የገቡ ርኩሳን ይቀደሳሉ እንጂ በውስጥዋ ያሉ ሰዎች በኃጢአት በክህደት ቢረክሱ እርስዋ አትረክስም፡፡
ዳሩ ግን እኔ ቅዱስ እንደሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ ባለው መሠረት በእርሱ ያመኑ በቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር የተጠለሉ ሁሉ ቅድስናን ገንዘብ ሊያደርጉ ይገባል፡፡
ኩሏዊት ናት!!
 
ቤተክርስቲያን ኲላዊት ናት ሲባል የሁሉ (ዓለም ዐቀፋዊት- Universal) እና ከሁሉ በላይ ናት ማለት ነው፡፡
ይህም በጸሎተ ሃይማኖት “እንተ ላዕለ ኩሉ” በሚለው ይታወቃል፡፡
ቤተክርስቲያን የሁሉ እንደሆነች ሁሉ ደግሞ ከሁሉ በላይ ናት፡፡
በደመ ክርስቶስ የተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የዚህ ወገን ናት የዚህ ወገን አይደለችም የማትባል በዘር፣ በቋንቋ፣ በጎጥና በቀለም እንዲሁም በቦታ የማትከፋፈል የሁሉና በሁሉ ያለች ናት፡፡
ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን የሁሉም መሆንዋን እንዲህ ሲል ገልጾታል“አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና” ገላቲያን 3፥28፡፡
ሐዋርያዊት ናት
 
ቤተክርስቲያንም ሐዋርያዊት ናት ስንል ሐዋርያዊት የሆነችው በአራት ነገሮች ነው፡፡
በአመሠራረት፤ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያኑን የመሠረተው በሐዋርያት መሠረትነት ላይ ነው “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ አንተ ብጹዕ ነህ . . . እኔም እልሃለሁ አንተ ዐለት ነህ በዚይች ዐለት ላይም ቤተ ክርስቲያኔን አሠራታለሁ የሲዖል በሮችም አይበረታቱባትም፡፡ የመንግስተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ በምድር የምታስረው በሰማይ የታሰረ ይሆናል በምድርም የምትፈታው በሰማይ የተፈታ ይሆናል”ማቴዎስ 16 ፥ 15፡፡
ቤተክርስቲያን የተስፋፋችው በእነርሱ ነው፡፡
በሢመት ሀረግ  ከሐዋርያት አንስቶ ያልተቋረጠ የሢመት ሀረግ መኖሩ ቤተክርስቲያንን ሐዋርያዊት አድርጓታል፡፡ ጌታችን ለሐዋርያቱ የሰጠው የክህነት ስልጣን ሳይቋረጥ በቀጥታ እየተላለፈ መምጣቱ አንዱ የሐዋርያዊትነቷ መገለጫ ነው፡፡
በትውፊትና በምሥጢር፡- ቤተክርስቲያን የሐዋርትን ትውፊት ተቀብላ መተግበሯ ሐዋርያዊት አድርጓታል፡፡ እንደ ሐዋርያት ሲኖዶስ አላት፡ እንደ ሐዋርያት ታጠምቃለች፡ እንደ ሐዋርያት ትቀድሳለች፡ ሥጋና ደሙን ታቀብላለች፡፡ ሐዋርያት የሠሩትን እንደ ሐዋርያት አድርጋ ትሠራለች፡፡ ከሐዋርያት የተለየ ሥርዓት ሊኖራት አይችልም፡፡ ይህ የሐዋርያዊትነቷ ሌላው መገለጫ ነው፡፡
 
በመጻሕፍት ትርጓሜ፡- ሐዋርያዊ ክትትሉን የጠበቀ የቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ ስላላት ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት፡፡ ሐዋርያት እንደተረጎሙት አድርጋ ትተረጉማለች፡፡ ሐዋርያት እንዳስተማሩት አድርጋ ታስተምራለች፡፡ ሐዋርያት ያላስተማሩትን አታስተምርም፡፡ በዚህም ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት፡፡
ሲኖዶሳዊነት
 
 ከሐዋርያዊነት የሚወረስ ጠባይ ነው።
 
ቤተ ክርስቲያን ዘክርስቶስ በቅዱስ ሲኖዶስ መመራት የጀመረችው ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ለመሆኑ ምሥክሩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡
 
የመጀመሪያው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የተደረገበትን ምክንያት ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ግብረ ሐዋርያትን በገለጸበት ጽሑፉ ላይ እንዲህ ተርኮታል፡-
አንዳንዶችም ከይሁዳ ወረዱና፥ እንደ ሙሴ ስርዓት ካልተገረዛችሁ ትድኑ ዘንድ አትችሉም ብለው ወንድሞችን ያስተምሩ ነበር፡፡ በእነርሱና በጳውሎስ በበርናባስም መካከል ብዙ ጥልና ክርክር በሆነ ግዜ ስለዚህ ክርክር ጳውሎስና በርናባስ ከእነርሱም አንዳንዶች ሌሎች ሰዎች ወደ ሐዋርያት ወደ ቀሳውስቱም ወደ ኢየሩሳሌምም ይወጡ ዘንድ ተቆረጠ።
  • ሐዋርያት ለመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን የመጨረሻው ወሳኝ አካል እነርሱ ነበሩ ::
  • ይህ ሐዋርያዊ ውርስ ባላት የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንም የመጨረሻው ውሳኔ ሰጪ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡
  • ለዚህም ነው ሲኖዶሳዊት ያልሆነች ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት አይደለችም የምንለው፡፡
 
የጵጵስና መንበር
የሐዋርያዊነት መገለጫ ጠባይ ነው።
የቤተ ክርስቲያን እርከናዊ መዋቅር ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ የነበረ መሆኑን ያስገነዝበናል ::
ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቁና ያስተዳድሩ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ጳጳሳት አድርጎ የሾማቸው ናቸው።
በሐዋርያት ያደረ ቅዱስ መንፈስ በቅዱስ ጳውሎስም ያደረ ሆኖ ሳለ ቅዱስ ጳውሎስና ሲላስ ሌሎች ሰዎችን ጨምረው ለምን? ወደ ሐዋርያት መሄድ አስፈለጋቸው? የሚለው መጠይቅና መልስ ቅዱስ ጳውሎስና ሲላስም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ለተዋቀረው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የተገዙ መሆናቸውን ያሳያል::
  • ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደ ምንረዳው የመጀመሪያው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በኢየሩሳሌም ኤጲስ ቆጶስ በሐዋርያው በቅዱስ ያዕቆብ ሊቀ መንበርነት ከ49 – 50 ዓ.ም ባለው ግዜ የተካሄደው ከላይ በተገለጸው መሠረት ከአሕዛብ ወገን ክርስትናን በተቀበሉና ከአይሁድ ወገን ክርስትናን በተቀበሉት መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት ለዚያ እልባት ለመስጠት ነበር።
  • የጵጵስና ዋና ሥራው ሕዝቡን ማስተማር፣ ከሃድያንን ወደ አሚነ ሥላሴ ማምጣት፣ ሕዝቡን ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ መመለስ፣ ደጋጉን በመልካም ሥራ ማጽናት ነው።
  • የኢትዮጵያ ጵጰስና ከመንበረ ማርቆስ የተገኘ ነው፡፡
ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ Apostolic succession
   
ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ Apostolic succession፦ ምን ማለት ነው? ያልተቋረጠ ሐዋርያዊ እምነትና ስልጣን ማለት ነው።ያልተቋረጠ ሐዋርያዊ እምነትና ስልጣን ማለት ነው።
  1ኛ ሐዋርያዊ እምነት ምን ምን ናቸው? እምነተ ሥላሴ ይህ እምነት በሥላሴ መበላለጥ አለ ከሚሉ የተለየ ነው
*እምነተ ክርስቶስ(ሥጋዌ) ይህ እምነት ኢየሱስ ሥጋና ነፍስ አልነሳም ከሚሉ የተለየ ነው
*እምነተ ጥምቀት ይህ እምነት ጥምቀት ለመዳን አይጠቅምም ከሚሉ የተለየ ነው።
*እምነተ ቁርባን ይህ እምነት ቅዱስ ቁርባን ለስርየት አይሆንም ከሚሉ የተለየ ነው።
*እምነተ ትንሳኤ ሙታን ይህ እምነት ክርስቶስ ሁሉንም እንደ ስራው ሊያስረክበው ሙታን ይነሳሉ የሚለውን የሚያምን ነው
በምን መልኩ ተላለፈ
፩ኛ. ቅዱስ መጽሐፍት(ብሉይና ሀዲስ)
ዮሃ20 ፥30-31
፪ኛ. ቅዱስ ትውፊት(ያልተጻፈ ሀዋርያዊ ትምህርት) 2ተሰ 2፥15
2ኛ ሐዋርያዊ ስልጣን ምንምን ናቸው?
የቤተክርስቲያን ራስ ከሆነው ክርስቶስ ለቤተክርስቲያን ጥቅም የተሰጠ ኃላፊነት ነው። ይህ ኃላፊነት ሶስት ነው ክህነት/ዮሃ 20፥20 እረኝነት/ሐዋ 20፣28 እና ስብከት/ማቴ 28፥28 ናቸው። ይህን ኃላፊነት መጽሃፍ ቅዱስ ሹመት ይለዋል ሐዋ 1፥20 ሹመት የሚለው በግሪኩ ኤጲስ ቆጶስነት(ጵጵስና) ይለዋል። በክህነት ብቻ የሚከናወኑ ጌታችን ከድህነት ጋር አስተሳስሮ ያስተማራቸው ውስጥ ጥምቀት ማር 16፣16፣ ማቴ 28፣28 ሁለተኛ ንስሃ ሉቃ 13፥5 እንዲሁም ቁርባን ዮሃ 6፣54 ፣ 1ቆሮ 10፡16 ናቸው።
 
  • ይህ ሹመት መቼ ይቆማል ወይም እንዴት ይቀጥላል?
ኢየሱስ ክርስቶስ በማይቋረጥ ግንኙነት ከሐዋርያትና ከእነርሱም ብኋላ ከሚተኩ ጋር አብሮ ይስራል።ማቴ 28፥28
1ቆሮ15 የመጀመሪያ ተሿሚዎች ሹመቱን ከጌታ ተቀብለዋል
2ጢሞ 1፥6 እጅ በመጫን ይተላለፋል
2ጢሞ 2፥2 የተሾመውም እንዲሾም ታዟል
1ጢሞ 5፥22 ሹመቱ ጥንቃቄ ያሻል
 
  • የክህነት የእረኝነት እና የስብከት ሥልጣን የሌለው ስብስብ ቤተክርስቲያን አይባልም።
👉ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሶስቱንም ታሟላለች
👉ካቶሊክና ምስራቃውያን የክህነትና እረኝነት አላቸው ስብከት ላይ ግን ዶግማ ሰብረዋል
👉ፕሮቴስታንት ሶስቱም የላቸውም።
  • ስለዚህ በሐዋርያዊ መስመር ወደ ኋላ ጉዞ ቢጀመር አብዛኛው 50 ዓመት ወይም ቢበዛ 500 ዓመት ላይ የሚቆሙ ናቸው።
ቤተክርስቲያን በዚህ መልኩ የምትገለጽ ከሆነ አሁን ህብረት የምናደርግበት ቤ/ክ በዚህ ሚዛን ስትመዘን የቆምንበትን እንድንረዳ ያግዘናል።
እግዚአብሔር የቀናውን ያመላክተን፡ አሜን!
+++
መንፈስ፡ግን፡በግልጥ፦በኋለኛዎች፡ዘመናት፡አንዳንዶች፡የሚያስቱ፡መናፍስትንና፡በውሸተኛዎች፡ግብዝነት፡ የተሰጠውን፡የአጋንንትን፡ትምህርት፡እያደመጡ፥ሃይማኖትን፡ይክዳሉ። 1ጢሞ 4፣2
እንግዲህ፡ከወዴት፡እንደ፡ወደቅኽ፡ዐስብ፡ንስሓም፡ግባ፡የቀደመውንም፡ሥራኽን፡አድርግ፤አለዚያ፡
እመጣብኻለኹ፡ንስሓም፡ባትገባ፡መቅረዝኽን፡ከስፍራው፡እወስዳለኹ።ራዕ 2፥5
ክህነት ምሥጢራት ሁሉ የሚፈጸሙበት የማይደገም የማይከለስ የማይታደስ ምሥጢር ነው፡፡ ከነገረ ድኅነት ጋራ ቀጥተኛ ግንኙነት አለው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተራ ዲያቆናት እስከ ቅዱስ ፓትርያርኩ ያሉ ውሉደ ክህነትን፣ በተለይም መነኮሳትን መንቀፍን እንደ ልማድ ስለወሰድነው ኀዳሪው በማኅደሩ እየተፈተነ ይመስላል፡፡ ከልጅነት ሥርዓት መውጣትና ተቈርቋሪነትም ሳይምታቱ አልቀረም፡፡ ካህኑ ለካህናት የተጻፈውን ግብር አጉድሎ ቢገኝ እርሱ ይወቀስበታል እንጂ ክህነቱ ሊራከስ አይችልም፤ አይገባምም፤ በአገልጋዩ ድክመት አገልግሎቱ አይነቀፍም፡፡ ምሥጢረ ክህነት በካቶሊካውያንም፣ በምሥራቃውያንም፣ በአሲርያ ንስጥሮሳውያንም፣ በኦሪየንታልና በተወሰነ ደረጃ በአንግሊካኖችም ዘንድ አለ፡፡ እነዚህ ሁሉ ቅዳሴ፣ ሜሮን፣ ቁርባን፣ ንስሐ … የመሳሰሉ ምሥጢራትን ለመፈጸም ካህን ይጠቀማሉ፡፡ የካህኑ ክህነት ሐዋርያዊ ክትትልን ከጠበቀ አባት እንዲሆንም ግድ ነው ይላሉ፡፡ የገዳማውያንና የመናንያን መናኽሪያ በሆነችው በቤተ ክርስቲያናችንም ይህ ቤተ ክርስቲያንን ‹‹ሐዋርያዊት›› የሚያሰኝ ምሥጢር እንዳይፋለስ ሲባል አንድ ሚሊኒየም ተኩል የወሰደ የትዕግሥት ጊዜ ተከፍሏል፡፡ ስለዚህ፡- የሐዋርያዊ ቅብብሎሽን መጽሐፋዊ መነሻ፣ ቀኖናዊ መሠረት፣ የሲመተ ጵጵስናውን አፈጻጸምና የጳጳሱን ግብር፣ የመንበሩን ነገር፣ ምሥጢረ ክህነትን ማስተሐቀር የሚያመጣውን ፈተና ከመጽሐፍም፣ ከአዋልድም፣ ከአኃት አብያተ ክርስቲያናት ተሞክሮም እያዛመድን በሚጢጢ ንባብ ብናይ ጊዜው ይፈቅድልናል፡፡ ወሩ ወርሐ ሰኔ ነው፡፡ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ የተሾሙልን በዚህ ወር ነው – ሰኔ 21 ቀን 1951 ዓ.ም.፡፡

ትርጓሜው

ቅዱሳን ሐዋርያት ከጌታ ተቀብለውት ያለማቋረጥ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የክህነት ሲመታዊ ክትትልን ያሳያል፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ተፈጥሮ ነፍስን ከሐዋርያዊ ክትትል ያመሳስላል፡፡ በመጽሐፈ ምሥጢርና በመዝገበ ሃይማኖት እንደተመለከተው ከአባት ዘር፣ ከእናት ደም ተከፍሎ ሲዋሐድ ነፍስ ከወላጅ ወደ ልጅ ታልፋለች፡፡ በፀናው ሲነገር (እንበለ ዘርዐ ብእሲ /ያለወንድ ዘር/ ከተፀሰነው ጌታ በቀር) የአዳም ዘር ሁሉ በዚህ ያለፈ ነው፡፡ የነፍሳችንን ጥንተ ፍጥረት ወደኋላ ብንቆጥር የመጨረሻው መገናኛችን አዳም ይሆናል፡፡ የሐዲስ ኪዳኑ ክህነትም እንዲሁ ነው፡፡ የእያንዳንዳችን ውሉደ ክህነት የሥልጣን ምንጭ ወደኋላ ቢቈጠር የመጨረሻ መገናኛችን የጌታ እስትንፋስ /ንፍሐት/ና ቡራኬ ነው፡፡ የክህነት ክትትሉ ሲቈጠር በዚህ ሐዋርያዊ ሰንሰለት ያልተገኘ ሥልጣን ‹‹ውጹእ/ውዱቅ›› /invalid/ ነው፡፡ በትክክለኛው መስመር አልመጣምና የሥልጣን ውርሱ አይጸድቅም፤ አያጸድቅም!

መነሻው፡ በቃለ መጽሐፍና በቀኖና አበው

በብሉይ ኪዳን በሌዊ ቤት ሐረገ ትውልድን ጠብቆ በዘር ይተላለፍ እንደነበረ ነጋሪ አያሻም፡፡ በሐዲስ ኪዳን በዘር መሆኑ ቀረና ከ12ቱ ነገድ የተውጣጡ ቅዱሳን ሐዋርያትን መረጠ፤ ጠራ፡፡ ‹‹በዚያም ወራት ጌታችን ኢየሱስ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ፤ ሌሊቱን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ነበር፤ ሲነጋም ደቀ መዛሙርቱን እርሱ ጠራቸው፤ ከውስጣቸውም ዐሥራ ሁለቱን መረጠ፤ ሐዋርያትም ብሎ ሰየማቸው፡፡›› እንዲል ሉቃ.6፡12-13፡፡ ለተመረጡትና በሐዋርያነት ለተሰየሙት ደቀ መዛሙርት ሥልጣን እንዴት እንደ ተሰጠ ደግሞ ‹‹ጌታችን ኢየሱስም ዳግመኛ እንዲህ አላቸው ሰላም ለእናንተ ይሁን አብ እንደላከኝ እንዲሁ እልካችኋለሁ፡፡ ይህንም ብሎ እፍ_አለባቸው፤ እንዲህም አላቸው ‹መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፡፡ ኃጢኣታቸውን ይቅር ያላችሁላቸው ይሰረይላቸዋል፤ ይቅር ያላላችኋላቸው ግን አይሰረይላቸውም፡፡›› በሚል ሰፍሯል (ዮሐ.20፡210-23)፡፡ ሲመት፡- መመረጥን፣ ንፍሐትን፣ ተልእኮን እንደሚያካትት ከጥቅሶቹ እንረዳለን፡፡ ንፍሐቱ የጌታ ነው፤ እስትንፋሱ የእርሱ ነው፡፡ በሕየወታዊ ሕላዌያችን ከአዳም እንደ ተገኘን በክህነትም ከጌታ ተገኝተናል፡፡ አባ ጊዮርጊስ ይናገራል፡- ‹‹ለአዳም የተሰጠ የሕይወት እስትንፋስ የሰው ልጅ ለመሆን በዘሩና በዘር ዘሩ ለልጅ ልጅ እንደ ፈሰሰ ሌላ የእውነት ምስክር አለኝ፡፡ ሌላ የሕይወት እትንፋስ (ከአዳም በቀር) የተቀበለ ምንም ማንም የለም፡፡ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ ይቅር ላላችኋቸው ኃጢአታቸው ይቀርላቸዋል፤ ይቅር ላላችኋቸው አይቀርላቸውም ብሎ እፍ_ባለባቸው_ጊዜ_ከጌታ_ከኢየሱስ_አፍ_የመንፈስ_ቅዱስ_መቀበል_ሆነ፡፡ ከዚያን ጊዜ በኋላ በኤጲስ ቆጶሳቱ ላይ በቀሳውስትም ላይ በክርስቲያን ታላላቆችም ላይ ቢሆን እፍ ያለበት ጊዜ የለም፡፡ ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ በደረሱበት ኤጲስቆጶሳትና ቀሳውስትን ዲያቆናትንም ይሾማሉ … ዲያቆን አድርገው የሚሾሙትን_እፍ_ቢሉበት የዲቁና መንፈስ ይቀበላል፤ ለማጥመቅም እፍ ቢሉበት የክርስቲያን ታላቅ ለመሆን መንፈስን ይቀበላል፤ የኢየሱስ ክርስቶስም መንፈስ ወደ ወደዱት ሹመት መዓርግ_ይተላለፍላቸዋል፡፡›› (መጽሐፈ ምሥጢር፣ ምዕ፣23፡28-29፣ ገጽ 242)፡፡ ‹‹ይተላለፍላቸዋል›› የሚለው ይሠመርበት! መተላለፉ የሚቋረጥ አይደለም፤ እስከ ሐሳዊ መሲሕ መምጣ ይቀጥላል እንጂ! አባ ጊዮርጊስ ይቀጥላል፡- ‹‹ከጌታ ኢየሱስ አፍ ለሐዋርያት የሆነ የመንፈስ ቅዱስ መቀበል እርሱ በፊት ላይ እፍ በማለት ከአንዱ_ወደ_ሁለተኛው፣ ከሁለተኛው_ወደ-ሦስተኛው፣ ከዚያን_ጊዜ_ጀምሮ_እስካሁን_እስከ_ሐሳዊ_መሲሕም_መምጣት_ድረስ_የሚተላፍ_ሆነ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም ከደቀ መዛሙርቱ ሌላ ሁለተኛ እፍ እንዳላለ ዳሩ ግን (ቀድሞ) ከተሾሙት አፍ (አዲስ) ወደሚሾሙት ያለመቋረጥና_ያለመከልከል_ይተላለፋል፡፡›› ይለናል ብሔራዊው ሊቅ (መጽ.ምሥጢር፣ ምዕ.23፡31፣ ገጽ 243)፡፡ ፍትሐ ነገሥቱም ‹‹ሊቃነ ጳጳሳት ግን የክርስቶስና እናንተን የተቀበለ እኔን መቀበሉ ነው ያላቸው የሐዋርያት_ተከታዮች ናቸው፡፡›› (ፍትሐ ነገሥት፣ አንቀጽ 4፡39)፡፡ የሐዋርያዊ ክትትል ድንጋጌው ሥልጣነ ክህነቱን ከቅዱስ ጴጥሮስ የተቀበለው ቅዱስ ቀሌምንጦስ ዘሮምም ባኖርልን ትእዛዙ ምዕራፍ 8፡4 ከመምህሩ ተቀብሎ አስቀድሞ የነገረን ነውና የታመነ ነው፡፡
ቃለ ጸሐፍት

ዐሥራት ገብረ ማርያም፡- ‹‹ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት ነች የተባለው የሐዋርያትን ትውፊትና ትምህርት ስለምታስተምርና ይህንንም ለመጠበቅ እንዲቻል ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ ተከታታይነቱ ያልተቋረጠ የካህናት አሹዋሹዋምን ሥርዓት ስለምትከተል ነው፡፡ … ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት የተባለችው የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁሉ ከሐዋርያት ተቀብለው ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የእርስዋን መመሪያ እንዲከተሉ ነው እንጂ መመሪያዎችን ችላ ብለው መረን እንዲለቀቁ አይደለም፡፡›› (ዐሥራት ገብረ ማርያም፣ ትምህርተ መለኮት፣ 1991 ዓ.ም.፣ ገጽ 203)፡፡
አቡነ ሺኖዳ፡- ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ‹‹Apostolic Succession and Laying of Hands – ሐዋርያዊ ክትትልና አንብሮተ ዕድ›› በሚል ርእስ በመጽሐፋቸው እንዲህ ብለውናል፡- ‹‹It is clear that that God’s gift was passed on from Saint Paul to his disciple Timothy [2Tim.1:6]. Also, Timothy passed on this to gift to others, by laying on of the Hands.

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

Copyright © 2010 – 2026 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top