“አንትሙሰ ሶበት ጸልዩ ስመ ዝበሉ፡፡” ማቴ.6፥
እናንተስ በምትጸልዩበት ጊዜ እንዲህ በላችሁ ጸልዩ “አባታችን ሆይ በሰማያት የምትኖር ስምህ ይቀደስ መንግሥትህ ትምጣ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነ እንዲሁ በምድር ይሁን….
በዚህ የጸሎት ክፍል ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከ81 መጻሕፍት የተገኙ አምስት ቁም ነገሮችን አስተምሯል፡፡
ሃይማኖት
ተስፋ
ፍቅር
ትሕትና
ጸሎት
1. ሃይማኖት፡- ሃይማኖት ማለት በዐይናችን ያላየነውን አምላክ አባታችን ሆይ ሲሉ መኖር ነው ቀደም ሲል የነበሩ አበው ነቢያት ሲጸልዩ እግዚእነ አምላክነ ንጉሥነ እያሉ ይጸልዩ ነበር፡፡ ይህም ከግብርናተ ዲያብሎስ /ለዲያብሎስ ከመገዛት/ እንዳልዳኑ ለማጠየቅ ነው፡፡ እኛን ግን ከግብርናተ ዲያብሎስ ነጻ አውጥቻችኋለሁ ሲል አባታችን ሆይ ብላችሁ ጸልዩ ብሎ አስተማረን፡፡ “ልጆች እንደመሆናችሁ መጠን እግዚአብሔር አባ አባቴ ብላችሁ የምትጠሩትን የልጁን መንፈስ በልባችሁ አሳደረ” /ገላ.4፥6፣ ሮሜ.8፥15/፡፡ አባትነቱንም በሁለት ነገር ከምድራዊ አባት ለይቶታል፡፡
በመውለድና በመግቦት ከምድራዊ አባት ይለያል፡፡ ምድራዊ አባት በዘር በሩካቤ ይወልዳል፡፡ በማር፣ በወተት፣ በፍትፍት ያሳድጋል፤ ኋላም በሞት ሲያልፍ የምታልፍ ርስትን ያወርሳል፡፡ እርሱ ግን ሲወልደን በርቀት ሲያሳድገንም በሥጋውና በደሙ ነው፡፡ “ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው ዮሐ. 3፥6፡፡ ኋላም የማታልፍ ርስት መንግሥተ ሰማያትን “በክርስቶስ ደግሞ ርስትን ተቀበልን” ኤፌ.1፥11፣ 1ኛጴጥ.3፥5፡፡ በአበው ነቢያት ሐዋርያትን፣ በሐዋርያትም እኛን አቅርቦ አባታችን ሆይ ብለን እንድናመሰግነው አዞናል፡፡
ምድራዊ አባት የሚመግበው እግዚአብሔር ስለሚሰጠው ለልጁ በመስጠት ተቀብሎ በማቀበል ነው፡፡ እርሱ ግን መመገብ የባሕርዩ ስለሆነ ከሌላው ነስቶ አይደለም፡፡ ምድራዊ አባት ሲያጣ አጣሁ ይላል እርሱ ግን አያጣም፡፡ ምድራዊ አባት ሰጥቶ ሲያልቅ አለቀ ይላል፡፡ የእርሱ ግን ስጦታው አያልቅም፡፡ “በሰማያት የማያልቅ መዝገብ የሚሆኑትን የሚያረጁትን ኮረዶች ለራሳችሁ አድርጉ” ሉቃ.12፥33፡፡ ምድራዊ አባት ከትልቁ ልጁ ይልቅ ለትንሹ የደላል እርሱ ግን ዓለምን በእኩል ምግብና ይመግባል፡፡ ምድራዊ አባት ትዕዛዙን ካልተጠበቀለት ልጁን ከቤት ያስወጣል፣ ያባርረዋል እርሱ ግን ሁል ጊዜ በትዕግስት ይመለከተናልና፡፡ “በጻድቃንና ለኀጥአንም ዝናምን ያዘንማልና” ማቴ.5፥45፡፡ እኛ አባትነቱን አምነን አባታችን ሆይ ብንለው እኛ ልጆቹ መሆናችን የልጅነት ሥልጣን እንዳገኘን እንመሰክራለን፡፡ “ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፡፡ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም” እንዲል ዮሐ.1፥12፡፡ “የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደሰጠን እዩ 1ዮሐ.3፥1፡፡
ከላይ ያየናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የሚያስረዱን የእግዚአብሔር ፍቅር ከምድራዊ አባት የተለየ መሆኑን ነው፡፡ ምድራዊ አባት ልጁን ቢወደውም ሥልጣን አይሰጠውም፡፡ እግዚአብሔር ግን ለልጆቹ አጋንንትን እንዲያወጡ ድውያንን እንዲፈውሱ ለምጽ እንዲያነጹ ሙታን እንዲያስነሡ ሥልጣን ሰጥቷል፡፡ “አሥራ ሁለቱን ደቀመዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲያወጡአቸው በርኩሳን መናፍስት ላይ ደዌንና ሕማምንም ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣን ሰጣቸው” እንዲል ማቴ.10፥1፡፡
በመኖሪያው /በሰማያት/ በመኖሩ ከምድራዊ አባት ይለያል፡፡ በሰማያት የምትኖር ብሎ በመኖሪያው ከምድራዊ አባት ለይቶታል፡፡ አሁን እግዚአብሔር በምድር የሌለ በሰማይ ብቻ የተወሰነ ሆኖ አይደለም በሰማይም በምድርም የመላ አምላክ ነው፡፡ “ከመንፈስ ወዴት እሔዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ አንተ በዚያ ነህ ወደጥልቅም ብወርድ በዚያ አለህ፡፡ እንደንስር ክንፍን ብወስድ /ቢኖረኝ/ እስከባሕር መጨረሻም ብበርር በዚያ እጅህ ትመራኛለች፡፡” መዝ.139፥7 በማለት ቅዱስ ዳዊት እግዚአብሔር የሌለበት ቦታ እንደሌለ ገልጿል፡፡
በሰማያት የምትኖር በሉኝ ያለን ብዙ ጊዜ መገለጫው፣ መቀመጫው፣ ለቅዱሳን እርሱ በወደደ እነርሱ በሚችሉት መጠን የተገለጠና የታየ በሰማይ ስለሆነ ነው፡፡
“ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀመጦ አየሁት የልብሱን ዘርፍ መቅደሱን መልቶት ነበር” ኢሳ.6፥1-6፡፡
“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ሰማይ ዙፋኔ ነው ምድርም የእግሬ መርገጫ ናት” ኢሳ.66፥1፡፡
ኢሳይያስ ምልአቱን፣ ክብሩን፣ ልዕልናውን በአየው መጠን ነገረን፡፡ ይህን የአገልጋዩ የኢሳይያስን ምስክርነት ሳይለውጥ ነቢያት የተናገሩልኝ የስተማሩልኝ፣ የሰበኩልኝ እኔ ነኝ በማለት እነ “ኢሳይያስ ሰማይ ዙፋኔ ነው” ያለውን እንደአስተማሩ እርሱም በሰማያት የምትኖር ብላችሁ አመስግኑኝ አለን፡፡ ስለ ልዕልናው ስለ ክብሩ በሰማይ አለ ይባላል፡፡ “በእንተ ዕበይከ ትትሜሰል በደመናት” እና ትርጓሜ ወንጌል “ስለ ልዕልናህ በደመናት ትመሰላለህ” ከዚህም የተነሣ ጌትችን ሲያስተምር “በሰማያ አትማሉ የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና በምድርም አትማሉ የእግሩ መረገጫ ናትና” ማቴ.5፥32 ብሏል፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ ጌቶችን ኢየሱስ ክርስቶስን በአየው ጊዜ እንዲህ መስክሯል “ወደሰማይ ትኩር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና እነሆ ሰማያት ተከፍታው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ አለ” ሐዋ.7፥55፡፡
ስለዚህ ብዙ ጊዜ በሰማይ ለወዳጆቹ ከመገለጡ የተነሣ አባታችን ሆይ በሰማያት የምትኖር ብላችሁ አመስግኑኝ አለን፡፡
2. ተስፋ፡- ተስፋ ማለት የወደፊት አለኝታ እናገኘዋለን ብለን የምንጠብቀው መከራ የምንቀበልለት፣ በዚህ ዓለም ባይመቸን መከራ ቢጸናብን፣ ብንገፋ ብንከፋ ብናዝን ብንጨነቅ ያልፋል ብለን የምንጽናናበት ነው፡፡ ይህን ተስፋ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ገልጾታል፡፡ “በእግዚአብሔር ክብርም ተስፋ እንመካለን፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ነገር ግን መከራ ትዕግሥትን እንዲያደርግ ትዕግሥትም ፈተናን ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን በመከራችን ደግሞ እንመካለን፡፡ በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም” ሮሜ.5፥2-5 ተስፋ ከላይ ቅዱስ ጳውሎስ እንደነገረን ሰማዕታት ከነደደ እሳት ገብተው፤ የተሳለ ስዕለትን ታግሰው፤ የዓላውያን ነገሥታትን ግርማ አይተው ሳይደነግጡ፣ ሃይማኖታቸውን ሳይለውጡ፣ ሹመቱን ሽልማቱን ወርቁን ብሩን ምድራዊ ክብራቸውን ትተው መከራ የተቀበሉት ለተስፋ መንግሥተ ሰማያት ነው፡፡ ጻድቃንም ድምጸ አራዊትን ግርማ ሌሊትን ፍትወታት እኩያትን ታግሰው፣ በምናኔ በተባሕትዎ ከዘመድ ባዳ ከሀገር ምድረ በዳ ይሻለናል ብለው የኖሩት ለዚሁ ተስፋ ነው፡፡ ይህንንም ቅዱስ ጴጥሮስ በሃይማኖት ምክንየት ተበትነው ለነበሩ ምዕመናን ሲጽፍ እንዲህ ብሎአል፡፡ “እስመ በእንተ ዝንቱ ተጸዋእክሙ ከመ በረከተ ትረሱ በእንተ ዛቲ ተስፋክሙ” ለዚች ተስፋችሁ መከራን ትቀበሉ ዘንድ ተጠርታችኋልና 1ጴጥ.2፥22 የህ ተስፋ መጻሕፍት የተባበሩበት ነው” በተስፋ ያጽናናልና ነገር ግን ተስፋ የሚደረግበቱ ነገር ቢታይ ተስፋ አይደለም፡፡ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? የማናየውን ግን ተስፋ ብናደርገው በትዕግስት እንጠባበቃለን” ሮሜ. 8፥24፡፡ ስለዚህ ተስፋ የምንለው የማናየውን መንግሥተ ሰማያትን ነው፡፡ ይህን ተስፋ በጸሎታችን ውስጥ መንግሥትህ ትምጣ ብለን እንድንለምን ጌታችን አስተማረን፡፡ አሁን መንግሥትህ ትምጣ ስንል መንግሥተ ሰማያት ክንፍ ኖሯት በራ፣ እግር ኖሯት ተሽከርክራ የምትመጣ ሆኖ አይደለም ትሰጠን በሉኝ ሲል ተስፋ የምናደርጋት መንግሥትን እንዲያወርሰን ለምኑ አለን፡፡
3. ፍቅር ፡- ፍቅር ማለት አንዱ ለሌላው መጸለይ ነው፡፡ ይኸውም “የዕለት ምግባችንን ዛሬ ስጠን” የሚለው ነው፡፡ ሰው ሁሉ አባታችን ሆይ የሚለውን ጸሎት ሲጸልይ የዕለት እንጀራዬን ሰጠኝ ብሎ” አይጸለይም ለጠላቶቹም ለወዳጆቹም ጠቅላላ ሰው ሆኖ የተፈጠረ የተፈጥሪሮ ወንድምና እኅት ሁሉ ነው፡፡ ምክንያቱም ለእገሌ የሚል አደለም፡፡ ጠቅል አድርጎ የዕለት ምግባችንን ስጠን የሚል ነውና፡፡ ይህ ፍቅር ነው ሊቃውንት በትርጓሜያቸው ይህን ሲተረጉሙት ዕለት ዕለት እንድንማር፣ ሥጋውን ደሙን እንድንቀበል፣ ንሰሓ እንድገባ አድርግ ማለት ነው ይላሉ፡፡ ከምግበ ሥጋ ያለፈ ጸሎት ነው፡፡ ይህም ጸሎት ለሕዝቡ ለአሕዛቡ ለጠላት ለወዳጅ ለዘመድ ለባዕድ ሳይባል ለሁሉም የሚጸለይ ጸሎት ሲሆን እግዚአብሔር እኛን እንደወደደን እርስ በእርሳችንም እንዋደድ ዘንድ ተዋደዱ “ጠላቶቻችሁንም ውደዱ ለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ” ብሎ አስተምሮኗል፡፡ ለሁሉም የሚሆን የጸሎት ፍቅርን የሚገልጽ ጸሎት “የዕለት ምግባችንን ስጠን” በሉኝ አለን፡፡
4. ትሕትና፡- ትሕትና ማለት ራስን ዝቅ ማድረግ ማዋረድ ከሁሉ በታች ማድረግ ትዕቢትን ኩራትን ትዝህረትን ማስወገድ ነው፡፡ “ትዕቢትን ግን አታስቡ ራሲን የሚያዋርደውን ሰው ምሰሉ ሮሜ.12፥16፡፡ ይህም “ኀጢአታችንን ይቅርበለን” የሚለው ነው ይህን ጸሎት የበቃውም ያልበቃውም ይጸልየዋል፡፡ የበቃው የነጻው ከኃጢአት አልፎ ከአስረኛው መዓርግ የደረሰው ሁሉ ይጸልየዋል፡፡ ይህንን ሲጸልይ ግን ራሱን ዝቅ አድርጎ ከእኛ መደብ ውስጥ አስገብቶ ኀጢአታችንን ይቅር በለን ይላል፡፡ እርሱ ግን ከኀጢአት አልፎአል ስለትሕትና እኛን መስሎ እንደኛ ሆኖ ይጸልየዋል፡፡ ጌታችን ብዙ ጊዜ ስለትሕትና አስተምሯል፣ “እንግዲህ እንደዚህ ሕፃን ራሱን የሚያዋርድ ሁሉ በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጥ እርሱ ነው” ማቴ 18፥4 “ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን ከእናንተ ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን” ማቴ 20፥26-28፡፡
“ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላል” ማቴ 23፣11 እነዚህና ጌታችን ያስተማራቸውን በተግባር የሚያውሉ ቅዱሳን በቅተው ሳለ እንዳልበቁ ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ ይጸልያል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ከጌታው ከኢየሱስ ክርስቶስ እንደተማረው የትሕትና ጥቅምን ጽፎአል “እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኀይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ” 1ጴጥ 5፥6፡፡ በዚህ ጸሎት ውስጥ ይህ ጠቃሚ የሆነ ጸሎት ተአምኖ ኀጣውእ (ኀጢአትን ማመን) ያለበት በደላችንን ይቅር በለን የሚለው ትሕትና ነው፡፡
5. ጸሎት ፡- ጸሎት አባታችን ሆይ ብሎ እስከ መጨረሻው ያለው ነው አባችን ሆይ ስምህ ይቀደስ መንግሥት ትምጣ ፈቃድ ይሁንልን ይደረግልን የዕለት እንጀራችንን ስጠን በደላችንን ይቅር በለን ጸሎት ነው ታዲያ ይህን በንባብ አጭር በምሥጢር ጌታ መጻሕፍት ያጠቃለለ ታላቅ ጸሎት አፍ ንባብ ይነዳ ልብ ጓዝ ያስናዳ እንዲሉ አበው ኅሊናን በማባከን ሳይሆን በንቃት፣ በትጋት ሆነን ብንጸልይ እንጠቀማለን፡፡ ስለዚህ ነው ክብር ምሥጋና ይግባውና አባታችን ሆይ ብላችሁ ጸልዩ ያልን፡፡