የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሃገር ባለውለታ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሃገር ባለውለታ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ግንባታ የማይተካ ሚና እንደ ነበራት ግልጽ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት፣ ታሪካዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን እንደመሆኗ መጠን አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ከደረሰችበት የሥልጣኔና የእድገት ደረጃ ከመድረሷ በፊት ብራና ዳምጣ፣ ቀለም በጥብጣና ፊደል ቀርጻ ትምህርትና ሥልጣኔን ያስጀመረች፣ መጀመሪያው ዩኒቨርሲቲና የትምህርት ሚኒስቴር፣ ሆና አገልግላለች

የፍትሕ ሥርዓቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ መዋቅራዊ አደረጃጀት ገና ሳይኖረው ፍርድ እንዳይጓደልና ደሃ እንዳይበደል በማሰብ የፍትሐ-ነገሥት መምህራኖቿን በዳኝነት መድባ የፍትሕ ሥርዓትን የመሠረተች፣ ዜጎችን በሥነ-ምግባርና በግብረ-ገብነት ትምህርት ኮትኩታ በማሳደግ ሀገር ወዳድ ትውልድ በማፍራት መሠረት ጥላለች፡፡

በውጭ ወራሪ ኃይል የሀገር ሉዓላዊነት በተደፈረ ወቅት የእምነቱ ተከታይ ምእመናኖቿና አገልጋይ ካህናቶቿ እንዲሁም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የእምነታችን መገለጫ የሆነውን የቃልኪዳኑን ታቦት ይዘው በየጦር ግንባሩ በመሰለፍና በመሰዋት እንኳንስ ሕዝቦቿ ምድሪቱም ለወራሪ ጠላት እንዳትገዛ በማውገዝ የሀገር ሉዓላዊነት ያስከበረችና ኢትዮጵያ ሀገራችን ከሌሎች አፍሪካ አገራት በብቸኝነት ቅኝ ገዥዎች ያልደፈሯት አገር ተብላ በታሪክ ድርሳናት እንድትመዘገብ ግንባር ቀደም ሚና የተጫወተች ነጻነትን ከነክብሩ፣ ሃገርን ከነዳር ድንበሩ ጠብቃ ያቆየች የሀገር ባለውለታ እናት ቤተ ክርስቲያን መሆኗን እንኳንስ እኛ ልጆቿ ይቅርና የታሪክ ምሁራን ዘወትር በየአደባባዩ የሚመሰክሩት በብዕር ሳይሆን ለነጻነት በተከፈለ በአበው አባቶቻችን ደም የተጻፈ አኲሪ ታሪካችን ነው፡፡

በቱሪዝም፤- ከ80 እና ከ90 በላይ በሀገሪቱ የሚጎበኙ ቅርሶች ታሪካዊ ቦታዎች የቤተ ክርስቲያኒቷ ናቸው፡ይህ ማለት ቤተ ክርስቲያኗ ሃይማኖትን ከሀገር ፍቅር ጋር አያይዛ ስትሰራ መቆየቷንና አሁንም እየሰራች እንደሆነ ያመላክታል፡፡ በዩኔስኮ የተመዘገቡ የቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ በዓላት ለቤተ ክርስቲያን ፤ ለሀገርም ብዙ ጥቅሞችን እያስገኙ ነው፡፡ 

በዜማና ቅኔ:-በማንኛውም የማሕበረሰብ ክፍል የስሜት መግለጫ ሆኖ እንደ ቋንቋ ሁሉ ለረጅም ዘመናት ማስቆጠሩ በሰምና በወርቅ ፣ በሕብረ ቃል ፣በውስጠ ወይራ፣ በምርምርና በአንጻር ቅኔ የተቀመረ “የግዕዝ ቅኔ ለኢትዮጵያውያን ብቻ የተሰጠ ጸጋ” መሆኑ ታላላቅ ምሁራን እንደ እነ ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን የመሳሰሉትን ሀገራችን እንድታፈራ አድርጓታል፡፡ በዓለም ላይ ለሚታወቁ ቅኔዎች መሠረት የጣለው ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡

የቅዱስ ያሬድ ዜማ በሐገር ሐብትነትና በጎብኝዎች መስብህነት ቀዳሚ ነው ይህ ቅዱስ አባት ያበረከተው ዜማ በየትኛውም ክፍለ ዓለማት የማይገኝና ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ብቸኛ ከእግዚአብሔር የተበረከተ ጸጋ ሲሆን ሀገራችን ኢትዮጵያም የዚህ ሐብት ብቸኛ ባለቤት ያደርጋታል፡፡
በተለይም በዋናነት በከበሮ፣ በጸናጽልና በመቋሚያ ቅንጅት የሚዜመው ዝማሬ ከመንፈሳዊ ጥቅሙ ባሻገር ሽብሸባው ዕይታን የሚስብና ለጎብኚዎች እጅግ አስደናቂ መኾኑ በሀገር ገጽታ ግንባታ ላይ ያለው ድርሻ ጉልህ ነው፡፡

በሥነ ጥበብ፣ በኪነ ሕንፃ፣ በሥነ ሥዕል፣ በሥነ ጽሑፍ፣በአካባቢ ጥበቃ (ደን ልማት) በሕግ ቀረጻና ሀገራዊ ክብርና እሴትን በማስጠበቅ ከፍተኛ ሚና የተጫወተች መንፈሳዊ ተቋም ናት።ሥነ ጽሑፍ ከነፊደሉ፣ ነጻነት ከነክብሩ፣ ዘመን ከነቀመሩ፣ ሀገር ከነድንበሩ፣ አንድነት ከነጥብዓቱ ያስረከበች በአጠቃላይ ሃገር እንደ ሃገር የምትሰራበትን ማገርና ምሰሶ ያቆመች ጠንካራ መሰረት በጽኑ ዓለት ላይ የጣለች ቅድሥት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ነች።

 

 

 

 

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top