ጠበል እና ጥምቀት
ጥምቀት ምንድነዉ?
ብዙ ሊቃውንት እንደሚስማሙበት ጥምቀት የግዕዝ ቃል ሲሆን “ውሃ ውስጥ መዘፈቅ” የሚል ትርጉም አለው። ይህ ነጠላ ትርጉሙ ሲሆን ምሥጢራዊ ትርጉሙ ደግሞ “በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም በውሃ ተጠምቆ ስመ ክርስትናን መቀበል” ነው። የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማናዊ ጥምቀት ከመጽሐፍ ቅዱስና ከእምነት አንጻር ሲታይ ሞታችን፣ መቀበሪያችን፣ ትንሣኤያችን በመሆኑ ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ህብረት የሚፈጥርልን ምሥጢር ነው።
“ከክርስቶስ ጋራ አንድ ትኾኑ ዘንድ የተጠመቃችኹ ዅሉ ክርስቶስን ለብሳችዃልና።
አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም ዅላችኹ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችኹና” ገላ 3፥27
ጥምቀት በመረጨት ወይም በማፍሰስ የሚፈጸም ሰይሆን ሰውነት በሙሉ በማጥለም በሥላሴ ስም 3 ጊዜ ብቅ ጥልም በማለት የሚፈጸም ምሥጢር ነው።
የጥምቀት ምሳሌ
1. ግዝረት
2. የእስራኤል ቀይ ባሕርን ማቋረጥ
3. አብርሃም ባሕረ ዮረዳኖስን ተሻግሮ ለመልከጼደቅ ጽዋዕ በረከት ሕብስት አኮቴት ማቅረቡ
4. የኖሕ መርከብ
ጠበልምንድነዉ?
ጠበል ማለት ቃሉ የግዕዝ ሲሆን ትርጉሙም አፈር ( አቧራ) ማለት ነው ። ነገር ግን በቤተ ክርስቲያናችን ጠበል ብለን የምንጠራው በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ሕሙማን የሚፈወሱበት ተአምራት የሚደረግበት ቅዱስ ውሃ ማለት ነው።
ጠበል ማለት በግእዙ ቅዱስ ውሃ ማለት ከሆነ ሕሙማን የሚፈወሱበት ተአምራት የሚደረግበት ለምን አፈር ተባለ ቢሉ?መልሱ በዮሐንስ ወንጌል ላይ የሚገኘው ቃል ነው ÷
👉ዮሐ ምዕ 9÷6
ይህን ብሎ ወደ መሬት እንትፍ አለ በምራቁም ጭቃ አድርጎ በጭቃው የዕውሩን ዓይኖች ቀባና።
ሂድና በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ አለው፤ ትርጓሜው የተላከ ነው። ስለዚህ ሄዶ ታጠበ እያየም መጣ። ይሕ ተአምር የተደረገው ሥጋን የተዋሐደው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምራቁ ለውሶ ጭቃ ባደረገው መሬትና በሰሊሆም መጠመቂያ ከሚገኘው ቅዱስ ውሃ ድብልቅ በመሆኑ ሕሙማን የሚፈወሱበት ቅዱስ ውሃ ተብሎ ተጠርቷል ።
ከጥምቀት ለክርስቲያኖች ምን ይገኝበታል
1. ጽድቅ ይገኝበታል። “ያመነ የተጠመቀ ይድናል።” ማር 16፥16
2. እንደገና እንወለድበታለን። ሁለተኛ ከእግዚአብሔር የምንወለድበት ረቂቅ ምሥጢር ነው፤ የሚፈጸመውም በውሃና በመንፈስ ነው። ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግስት አያይም። “ከውሃና ከመንፈስ ልትወለዱ ግድ አላችኹ” ዮሐ 3፥3 እንዲል። በክርስቶስ ክርስቲያን በወልድ ዉሉድ የሚያሰኝ ነው።
3. የኃጢአት ሥርየት ይገኝበታል። “ኃጢአታችሁ ይሠረይ ዘንድ ንስሐ ግቡ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ስም ተጠመቁ።” ሐዋ 2፥3
4. ክርስቶስን እንመስልበታለን። አርዓያ ሆኖ ያሳየንን በመፈጸም በሥራ እንመስለዋለን። “ከክርስቶስ ጋራ አንድ ትኾኑ ዘንድ የተጠመቃችኹ ዅሉ ክርስቶስን ለብሳችዃልና።” ገላ 3፥27። “ወይስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋራ አንድ እንኾን ዘንድ የተጠመቅን ዅላችን ከሞቱ ጋራ አንድ እንኾን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን፧” ሮሜ 6፥3
5. አድስ ሕይወት ይገኝበታል። “እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በዐዲስ ሕይወት እንድንመላለስ ፥ከሞቱ ጋራ አንድ እንኾን ዘንድ በጥምቀት ከርሱ ጋራ ተቀበርን። ሮሜ 6፥4
ጥምቀት በመፅሐፍ ቅዱስ
1. የብሉይ ኪዳን አባቶች በዓላቸውን ከማክበራቸው በፊት በውሃ በመረጨት በመነከርና በመጥለቅ ይነጹ ነበር። የዝግጅቱ ዕቃዎችንም በውሃ ማንጻት አለባቸው ከርኩሰት መንጻት በዚህ ነበርና። ዘሌ 6፥27
2. ኢዮብና ንዕማን በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቀው ተፈውሰዋል። 2ነገ 5፥8
3. ለ 38 ዓመት አልጋ ቁራኛ የነበረው ሰው እንደመሰከረው በሰሊሆም ቤተሳይዳ ውኃ ሰዎች እየተጠመቁ ፈውስ ያገኙ እንደነበረ እርሱ ግን ወደ ውኃው የሚወስደው በማጣቱ በዚያ እንዳለ ለጌታ መንገሩ ሌላው ማስረጃ ነው። ዮሐ 5፥2
4. በዚያን ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ከገሊላ ክፍል ከናዝሬት ወደ ዮርዳኖስ መጣ። ማር 1፥9።
ስለ ጠበል መፅሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎችን ስንመለከት
👉2ኛ ነገ ምዕ 5÷1-15
👉ዮሐ ምዕ 5÷2-5
👉ሕዝ ምዕ 36÷25
መናፍቃን በጠበል ላይ የሚያነሱትን ጥያቄ ስናይ ደግሞ ለምን ጠበሎች በቅዱሳን ስም ይሰየማሉ?አዳኙ እግዚአብሔር ሆኖ ሳለ ለምን የድንግል ማርያም ጠበል: የቅዱስ ሚካኤል :የቅዱስ ገብርኤል ጠበል ወዘተ….. ተብሎ ተሰየመ? ቢሉ መልሱ ግልፅ ነው
የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም:የቅዱሳን መላእክት የፃድቃን ሰማዕታት የነቢያት ሐዋርያት እና የሁሉም ቅዱሳን ክብራቸው ይገለጥ ዘንድ, መታሰቢየቸው ይሆን ዘንድ እንዲሁም ረድኤት በረከታቸው ለኛ ይሆን ዘንድ ጠበሎች በቅዱሳን ስም ይሰየማሉ ። መፅሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎችን ስንመለከት
👉ምሳሌ 10÷7
👉ኢሳ 56÷4-6
ስለዚሕ ጠበል(አፈር) ከጥንትም የነበረ አሁንም ያለ ወደፊትም ሕሙማንን እየፈወሰ ተአምራትን እያደረገ የሚኖር የተቀደሰ ውሃ ነው ።