ፆም ማለት ምን ማለት ነው?


ፆመ ፦ ተወ ” ታቀበ”ታረመ ካለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ነው። ፍቺውም ምግብን መተው ‘ መከልከል’ መጠበቅ ማለት ነው።
ፆም ማለት ሰውነት ከሚያስፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ መከልከል መወሰን ማለት ነው። ወይም ለሰውነት የሚያምረውን የሚያስጎመጀውን ነገር መተው ማለት ነው ።ይኸውም ከጥሉላት ማለትም ቅባትነት ካላቸው ሥጋ ነክ ምግቦች መከልከልን ያመለክታል።ቅዱስ ዳዊት፡-“ጉልበቶቼ በጾም ደከሙ፤ሥጋዬም ቅባት በማጣት ከሳ።” በማለት የተናገረው የሚያመለክተው ይኸንኑ ነው።መዝ፡፻፰፥፳፬።፤ ነቢዩ ዳንኤልም፡–“በዚያም ወራት እኔ ዳንኤል ሦስት ሳምንት ሙሉ ሳዝን ነበርሁ።ማለፊያ እንጀራም አልበላሁም፥ሥጋና የወይን ጠጅም በአፌ አልገባም፥ ሦስቱም ሳምንት እስኪፈጸም ድረስ ዘይት /ቅባት/ አልተቀባሁም።”ብሏል።ዳን፡፲፥፪-፫። ነቢዩ ዳንኤልና ሠለስቱ ደቂቅ (አናንያ፣ አዛርያ፣ ሚሳኤል) ፥ በባቢሎን ምርኰ በነበሩበት ዘመን ይህንን ሥርዓተ ጾም በመጠበቅ ጸጋ እግዚአብሔርን አግኝተውበታል፥ከመከራም ተሰውረውበታል።“ዳንኤልም ከንጉሡ ማዕድ እንዳይበላ ፥ ከሚጠጣውም ጠጅ እንዳይጠጣ በልቡ ጨከነ፤እንዳያበላውም የጃንደረቦ ችን አለቃ ለመነው።እግዚአብሔርም በጃንደረቦቹ አለቃ ፊት ለዳንኤል ሞገስንና ምሕረትን ሰጠው። የጃንደረቦ ቹም አለቃ ዳንኤልን ፡-መብሉንና መጠጡን ያዘዘላችሁን ጌታዬን እፈራለሁ፤በዕድሜ እንደ እናንተ ከአሉ ብላቴኖች ይልቅ ፊታችሁ ከስቶ ያየ እንደ ሆነ ከንጉሡ ዘንድ በራሴ ታስፈርዱ ብኛላችሁ አለው።ዳንኤልም……እኛን አገልጋዮችህን ዐሥር ቀን ያህል ፈትነን፤ የምንበላውንም ጥራጥሬ፥ የምንጠጣውንም ውኃ ይስጡን፤ከዚያም በኋላ የእኛን ሰውነትና ከንጉሡ ማዕድ የሚበሉትን የብላቴኖችን ሰውነት ተመልከት፤እንደ አየኸውም ሁሉ ከአገልጋዮችህ ጋር የወደድኸውን አድርግ አለው።”ይላል። ከዐሥር ቀን በኋላ ሥጋና ጠጅ ከተመገቡት ይልቅ አምረው ወፍረው የተገኙት ጾመኞቹ ብላቴኖች ናቸው።እግዚአብሔርም በትምህርትና በጥበብ ሁሉ ዕውቀትንና ማስተዋልን ሰጣቸው፤ዳንኤልም በራእይና ሕልምን በመተርጐም ሁሉ አስተዋይ ነበረ። ከሦስት ዓመታት ጾምና ጸሎት በኋላም በንጉሡ ፊት በቀረቡ ጊዜ ከሁሉም በልጠው ተገኝተዋል።ዳን፡፩፥፩-፳፬1።ስለዚህ እነርሱን አብነት አድርገን፥ እነርሱ ያገኙትን ጸጋና በረከት ለማግኘት፥ እንደ እነርሱ ያለ ጾም ለመጾም፥የጨከነ ቁርጥ ኅሊና ያስፈልገናል።

የጾም ነገር ሲነገር ሁልጊዜ እንደ አዲስ የሚጠየቀው፡-“ዓሣ ይበላል፥ ወይስ አይበላም?”የሚለው ነው።ጥያቄውን በጥያቄ ለመመለስም፡-“ዓሣ፡-ጐመን፣ ድንችና ሽንኩርት ነው? ወይስ ሥጋ?”ብለን እንጠይቃለን።ከዚህ በኋላ የምንመለከ ተው “ፍትሐ ነገሥት”የሚባለውን የሥርዓት መጽሐፍ ነው።በአንቀጽ አሥራ ስምንት በትርጓሜው ላይ፡-“ደም የሚወጣበት የእንስሳ ሥጋ አይበላባቸውም፤ከእንስሳት የሚገኝ ወተት፣ ቅቤ፣ አይብ፣እንቁላልም አይበላባቸውም፤ከእንስሳት ወገን ያይደለ እንበለ (ያለ) ዘር የሚባዛ ዓሣም አይበላባቸውም።”ይላል።ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በቃልም በመጽሐፍም እንዳስተማሩት “ኢትብልዑ ሥጋ ዘእንበለ ዓሣ፧”የሚለው ንባብ የሚተረጐመው “ዓሣ እንኳ ሳይቀር ሥጋን ሁሉ አትብሉ፤”ተብሎ እንጂ “ከዓሣ በስተቀር ሥጋን ሁሉ አትብሉ፤” ተብሎ አይደለም።
ሊቀ መዘምራን ሞገስ ዕቁበ ጊዮርጊስ የተባሉ የቤተክርስቲያን ሊቅ፥የዛሬ ፴፱ ዓመት፥በ፲፱፻፷፱ ዓ.ም. አሥመራ ከተማ ባሳተሙት፥“መርሐ ጽድቅ ባህለ ሃይማኖት፤” በተባለ መጽሐፋቸው ላይ፥ተጠራጣሪዎች የሚያነሡትን ጥያቄዎች ለቅመው በማውጣት ለሁሉም መልስ ሰጥተዋል።በዚህ ዘመን ተሻጋሪ በሆነ መጽሐፋቸው ነገረ ዓሣንም በገጽ፳፱ ላይ እንደሚከተለው መልስ ሰጥተውበታል።“የቤተክርስቲያን ሊቃውንት የዓሣ ሥጋ በጾም ይበላል፥ ወይስ አይበላም?በማለት እርስ በርሳቸው ይከራከራሉ። ምክንያታቸውም ፡-ዓሣዎች የሚራቡትና የሚባዙት በደመና ነው እንጂ በሩካቤ ዘር አይደለም፤ስለሆነም የዓሣ ሥጋ እንደ ንብ ማርና እንደ እንጨት ፍሬ ስለሚታይ በጾም ጊዜ ቢበላ ምንም አይደለም፥በሚል ነው።ሌሎቹ ደግሞ፡-ዓሣ እንደማንኛውም እንስሳ ደም የሚወጣው ሥጋ ስለሆነ በጾም ሊበላ አይገባም፥ ይላሉ። የዘመኑ ሊቃውንተ ዓለምም (ሳይንቲስቶች) ዓሣዎች በሩካቤ ዘር እንደሚራቡና እንደሚባዙ በምርምር ስለደረሱበት፥ዓሣ ቀጥ ያለ ሥጋ እንጂ የምን ማር ነው? ባዮች ናቸው። የኢትዮጵያ ሊቃውንት፡- የዓሣ ሥጋ ይበላል፥ አይበላም፤ እያሉ ሲከራከሩ የሚለዋ ወጡት መልስ፥ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንት፡-በፍትሐ ነገሥት አንቀጸ ጾም፥ ክፍል ፲፰ ላይ “ኢትብልዑ ሥጋ በመ ዋዕለ አጽዋም ዘእንበለ ዓሣ፤” ባለው መሠረት ነው።ይህ ዘእንበለ የተባለው አገባብ ወይም መስተዋድድ በሁለት መልክ ስለሚተረጎም እንደየስሜታቸውና እንደየአተረጓጐማቸው ተለያይተዋል። ምክንያቱም፡- “ይበላል፤”የሚሉት ክፍሎች፡-“ዘእንበለን፥ያለ ዓሣ፣ከዓሣ በስተቀር፤” ብለው ሲተረጉሙት፥ አይበላም የሚሉት ወገኖች ግን፡-“ዓሣ ሳይቀር፤” ብለው ተርጉመውታል። እነዚህም፡-“ወአልቦ ዘአትረፈ ሊተ ንዋይየ ዘእንበለ ብእሲትየ፤ ሚስቴ ሳትቀር ዘረፉኝ፤……ኢትንሥኡ ወርቀ ወብሩረ ዘእንበለ በትር፤ በትር ሳይቀር ወርቅንና ብርን አትያዙ፤” የሚለውን ማስረጃ አድርገው ይጠቅሳሉ። ጦቢ፡፩፥፳፣ ማር፡፮፥፰። ሊቃውንቱ እንደዚህ ሲጠቃቀሱ፥ሠለስቱ ምዕት ደግሞ “ተገዓዝክሙ በጾም አድልዉ ለጾም፤በጾም ምክንያት ብትከራከሩ ለጾም አድሉ፤”ብለዋል።ስለሆነም መቼም ቢሆን በጾም ምክንያት ክርክር ቢነሣ፥ቅዱሳን አባቶቻችን አንዳስተማሩን ለጾም ማድላት ይገባል። ሠለስቱ ደቂቅና ዳንኤል በጾማቸው ጊዜ ከሥጋ ብቻ ሳይሆን ከደረቅ እንጀራ እንኳ ተከልክለዋልና። ከዚህም ሌላ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘመነ ፕትርክና፥ የዓሣ ሥጋ ጾም መሆኑ በቅዱስ ሲኖዶስ ተወስኖአል።
ሀ፡-ጾም የእግዚአብሔር ትእዛዝ ነው፤
ጾም፡-ለሰው ልጅ የተሠራ የመጀመሪያው የእግዚአብሔር ሕግ ነው። እግዚአብሔር፡- የእርሱ ፈጣሪነትና የአዳም ፍጡርነት፥ የእርሱ ገዢነትና የአዳም ተገዢነት ይታወቅ ዘንድ፥“ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤(ጹም)፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ትሞታለህና።(በሥጋህ ወደ መቃብር፥ በነፍስህ ደግሞ ወደ ሲኦል ትወርዳለህና።)” ብሎታል። ዘፍ፡፪፥፲፯። አዳምና ሔዋን እግዚአብሔር የሠራላቸውን ጾም በመሻራቸው፡- ከማዕረጋቸው ተዋርደው፥ ከሥልጣናቸው ተሽረው፥ የሞት ሞት ተፈርዶባቸው ከገነት ተባርረዋል። ዘፍ፡፫፥፳፪-፳፬። እግዚአብሔር ቃል በቃል ፥በነቢያትም እያደረ ትእዛዘ ጾምን የሰጠበት ጊዜ ብዙ ነው። ለምሳሌ፡-ንጉሡን ኢዮርብአምን እንዲገሥጽ ከይሁዳ ወደ ቤቴል የላከውን አረጋዊ ሰው፡-“በዚህም ስፍራ እንጀራም አትብላ፤ ውኃም አትጠጣ፤ በመጣህበትም መንገድ አትመለስ።”ብሎታል። እርሱ ግን ጾምን ከጀመረ በኋላ በሐሰተኛ ነቢይ ተታልሎ ወደ መብላትና መጠጣት በመመለሱ እግዚአብሔር ገሥጾታል።በመጨረሻም የታዘዘ አንበሳ ሰብሮ ገድሎታል። ፩ኛ፡ነገ፡፲፫፥፩-፳፬። በነቢያት እያደረ ሲናገር ደግሞ፡-“ጾምን ቀድሱ፤ ምህላንም ዐውጁ፤ ሽማግሌዎች ንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ፤ ወደ እግዚአብሔርም በአንድነት ጩኹ።” ኢዩ፡፩፥፲፬። “አሁንስ፥ይላል፤ አምላካችሁ እግዚአ ብሔር፥ በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ። ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ፥ ቁጣው የዘገየ፥ ምሕረቱም የበዛ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና፥ ወደ እርሱ ተመለሱ።” ኢዩ፡፪፥፲፪-፲፫።እግዚአብሔር ጾምን ያዘዘ ብቻ ሳይሆን በተዋህዶ ሰው በሆነበት ዘመን፥ (በመዋዕለ ሥጋዌው)፥ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ጾሟል።እከብር አይል ክቡር፥ እጸድቅ አይል ጻድቅ ሲሆን በገዳመ ቆሮንቶስ የጾመው ለእኛ ምሳሌ ለመሆን ነው። ማቴ፬፥፪።
ለ፡-ጾም የቅዱሳን ኑሮ (ሕይወት)ነው፤
ቅዱሳን ከእግዚአብሔር ጋር የኖሩት በጾም እና በጸሎት ተወስነው ነው። ልዩ ጸሎት ለማድረግ፥ልዩ ልመና ለማቅረብ ሲፈልጉ ጾም ይይዛሉ፥ ሱባዔ ይገባሉ። እግዚአብሔርም ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው አስገዝተው የጾሙትን ጾም ተመልክቶ፥ የጸለዩትን ጸሎት ሰምቶ መልስ ይሰጣቸው ነበር። ነቢዩ ዳንኤል የሦስቱን ሳምንት ጾም በፈጸመ ጊዜ፥ በሚያስፈራ ግርማ የተገለጠለት የእግዚአብሔር መልአክ፥“ዳንኤል ሆይ፥ አትፍራ፤ ልብህ ያስተውል ዘንድ፥ ሰውነትህም በአምላክህ ፊት ይዋረድ ዘንድ ካደረግህበት ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ቃልህ ተሰምቶአል፥ እኔም ስለ ቃልህ መጥቻለሁ።”ያለው ለዚህ ነው። ዳን፡፲፥.፩-፲፪።የነቢያት አለቃ ሙሴም በደብረ ሲና፥ በእሳትና በደመና ውስጥ ሆኖ ከጠራው ከእግዚአብሔር ጋር እየ ተነጋገረ፥ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት በቆየበት ወቅት፥ ከእህል ከውኃ ምንም አልቀመሰም ነበር።“እግዚአ ብሔርም ሙሴን በእነዚህ ቃላቶች መጠን ከአንተና ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን አድርጌአለሁና እነዚህን ቃሎች ጻፍ አለው።በዚያም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ እንጀራም አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም። በጽላቶቹም ላይ አሥሩን የቃል ኪዳን ቃሎች ጻፈ።”ይላል። ዘጸ፡፴፬፥፳፰። ከዚህም፡- የጾም ወቅት፥ ሙሉ በሙሉ ከእግዚአብሔር ጋር የምንሆንበት ጊዜ እንደሆነ እናስተውላለን። ነቢዩ ኤልያስ ደግሞ የእግዚአብሔር መልአክ ከመገበው በኋላ፥ ምንም ሳይበላና ሳይጠጣ፥ እስከ እግዚአብሔር ተራራ እስከ ኮሬብ ድረስ፥ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ያለድካም ተጉዟል። ምክንያቱም ጾም በሰው ላይ ኃይል መንፈሳዊን ይሳድራልና ነው።1ኛ፡ነገ፡፲፱፥፩-፰። በአዲስ ኪዳንም ቅዱሳን ሐዋርያት እርሱን አብነት አድርገው እንደሚጾሙ ጌታ በተናገረላቸው መሠረት በጾም በጸሎት ተወስነው አገልግለውታል። “ሚዜዎች (ሐዋርያት)፥ ሙሽራው(ኢየሱስ ክርስቶስ) ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፥ (የማዳን ሥራውን ፈጽሞ የሚያርግበት ጊዜ አለ)፥ በዚያ ጊዜም ይጦማሉ።” ይላል። ማቴ፡፱፥፲፬-፲፮። ቅዱሳን ሐዋርያት ጾመ ኢየሱስን አብነት፥ ትምህርቱን ደግሞ መመሪያ በማድረግ ጾምን የሥራ መጀመሪያ፥ ከመንፈስ ቅዱስም ጸጋን መቀበያ አድርገው ታል።“ እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ፥ መንፈስ ቅዱስ፡- በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ። በዚያን ጊዜም ከጦሙ ከጸለዩም እጃቸውንም ከጫኑ (ከሾሟቸው)በኋላ አሰናበቱአቸው።” ይላል።የሐዋ፲፫፥፩-፫።ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስም እጅግ አብዝቶ ይጾም እንደነበረ በቆሮንቶስ መልእክቱ ላይ መናገሩ የሚያመለክተው ይኸንኑ ነው። ፪ኛ፡ቆሮ፡፲፩፥፳፯።ክርስቲያኖች ሃይማኖት ይዘን፥ ምግባር ሠርተን ከተገኘን በሰማይ የምንኖረው እንደ መላእክት ነው።“በትንሣኤስ እንደ እግዚአብሔር መላእክት በሰማይ ይሆናሉ፧”ይላልና። ማቴ፡፳፪፥፴። ስለዚህ ላይ የሚጠብቀንን ኑሮ እያሰብን፥ ገና በምድር እያለን እንደ መላእክት መኖርን እንጀምራለን። በመሆኑም ጾም፥ ጸሎት፥ስግደት፥መዝሙር፥ ቅዳሴና ማኅሌት፥ ቅዱሳን መላእክትን የምንመስልበት ጸጋ መሆኑን በማስተዋል በእነዚህ ጸንተን እንኖራለን።ቅዱስ ጳውሎስ ፡-“ልባችሁ በጸጋ ቢጸና መልካም ነው እንጂ በመብል አይደለም፥ በዚህ የሚሠሩባት አልተጠቀሙምና።” ያለው ለዚህ ነው። ዕብ፡፲፫፥፱። በተጨማሪም፡- “የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችምና። እንደዚህ አድርጎ ለክርስቶስ የሚገዛ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኛልና፥ በሰውም ዘንድ የተመሰገነ ነው።”የሚል አለ። ሮሜ፡፲፬፥፲፯-፲፰።
ሐ፡-ጾም ሰይጣንን የምናሸንፍበት መሣሪያ ነው፤
ጌታችን በገዳመ ቆሮንቶስ በጾመ ጊዜ፥ በፈቃዱ በሰይጣን ተፈትኖአል። በስስት፥ በፍቅረ ንዋይና በትዕቢት የፈተነውን ሰይጣን፡- በትእግሥት፥ በጸሊአ ንዋይና በትኅትና ድል አድርጐታል።እነዚህ ሥጋ ለባሽ ሁሉ የሚፈተንባቸው ሦስቱ ዋና ዋና ኃጢአቶች ናቸው። ማቴ፡፬፥፩-፲፩። በመሆኑም በእነዚህ የሚፈትነንን ጥንተ ጠላታችንን ሰይጣንን ድል የምናደርገው በጾም መሆኑን እርሱ መንገዱን አሳይቶናል። በመዋዕለ ሥጋዌው ደቀመዛሙርቱ፡- በሽተኛውን ለምን መፈወስ እንዳቃታቸው በጠየቁት ጊዜ፡- “ስለ እምነታችሁ ማነስ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ የሰናፍጭ ቅንጣት ያህል እምነት ቢኖራችሁ ይህንን ተራራ፡- ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም። ይህ ዓይነት ግን ከጸሎትና ከጾም በቀር አይወጣም።” ብሏቸዋል። ማቴ፡፲፯፥፲፬-፳፩። ከዚህም ጋር ሰይጣን አዳምንና ሔዋንን የጣላቸው፥ ከርስታቸው ከገነት የነቀላቸው ፥ ከእግዚአብሔር የለያቸው፥ በመብል ምክንያት እንደሆነ መርሳት አይገባም።
መ፡-ጾም ከታዘዘ መቅሠፍት ያድናል፤
ከመቶ ሃያ ሺህ በላይ የሆኑ የነነዌ ሰዎች፥ እግዚአብሔር ተቆጥቶባቸው፥ መቅሠፍት ታዝዞባቸው ነበር። እንደ ሰዶምና ገሞራም እሳትና ዲን ሊዘንብባቸው፥ እሳቱ እንደ ክረምት ደመና ተንጠልጥሎ ነበር። ነገር ግን የነቢዩን የዮናስን የንስሐ ስብከት ሰምተው፥ ከንጉሡ ጀምሮ ሁሉም ሕዝብ አመድ ላይ ተኝተው፥ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በመጾማቸው ከመቅ ሠፍት ድነዋል። ይህንን ጾም የቤት እንስሳትም በረት ተዘግቶባቸው ጾመውታል። ጡት የሚጠቡ ሕጻናትም ጾመውታል። ዮና፡ምዕ፡፩-ምዕ፡፬። በቤተክርስቲያናችንም ሕጻናት ከሰባት ዓመታቸው ጀምሮ እንዲጾሙ ሥርዓት ተሠርቶአል። በመሆኑም ከዚህ ተምረን “እንዴት አድርገው ጾሙን ይችሉታል?” የሚለውን ጥርጥር ልናስወግድ ይገባል። ምክንያቱም እንኳን የሰባት ዓመት ሕጻናት፥ የአርባና የሰማንያ ቀን ሕጻናት እንኳ ለሦስት መዓልትና ለሦስት ሌሊት ጡት ተከልክለው ጹመውታልና። በምክንያት የማይጾሙ ወላጆች ደግሞ ከነነዌ እንስሳት እና ሕጻናት አንሰው አንዳይገኙ፥ ክርስትናው ካለ፥ ወደ ጾምና ጸሎት መመለስ ይኖርባቸዋል።
አርጤክስስ የተባለው ንጉሥ፥ ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ በመቶ ሃያ ሀገሮች ላይ በነገሠበት ዘመን፡- በሐማ ተንኰል፥ በአይሁድ ላይ፥ በተገኙበት ሥፍራ እንዲገደሉ የሞት ዓዋጅ ታውጆባቸው ነበር። ነገር ግን ይኸንን የሰሙ አይሁድ፥ ከላይ እስከ ታች ሁሉም፥ ማቅ ለብሰው፥ አመድ ላይ ተኝተው በመጾማቸው ከመከራው ተሰውረዋል። “የንጉሡም ትእዛዝና አዋጅ በደረሰበት አገር ሁሉ በአይሁድ ላይ ታላቅ ኀዘንና ጾም ልቅሶና ዋይታም ሆነ፥ ብዙዎች ማቅና አመድ አነጠፉ።” ይላል። አስ፡፬፥፫።በዚያን ዘመን አይሁዳዊቷ አስቴር በቁንጅናዋ ለንጉሥ ሚስትነት ተመርጣ በቤተመንግሥት ትኖር ነበር።አጐቷ መርዶክዮስም፡-“አንቺ በንጉሥ ቤት ስለሆንሁ ከአይሁድ ሁሉ ይልቅ እድናለሁ ብለሽ በልብሽ አታስቢ። በዚህ ጊዜ ቸል ብትዪ ዕረፍትና መዳን ለአይሁድ ከሌላ ስፍራ ይሆንላቸዋል፥ አንቺና የአባትሽ ቤት ግን ትጠፋላችሁ፤ ደግሞስ ወደ መንግሥት የመጣሽው እንደዚህ ላለው ጊዜ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?”ብሎ ላከባት። እርሷም፡- “ሄደህ በሱሳ ያሉትን አይሁድ ሰብስብ፥ ለእኔም ጹሙ፥ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት አትብሉም፥አትጠጡም፥ እኔና ደንገጡሮቼ ደግሞ እንዲሁ እንጾማለን፤ ምንም ያለ ሕግ ቢሆን ወደ ንጉሡ እገባለሁ፥ ብጠፋም እጠፋለሁ።” ብላ መልሳ ላከችበት። መርዶክዮስም አደረገው። የቀድሞው የሞት ዓዋጅም ወደ ሕይወት ተለወጠ። ዛሬም የታዘዝናቸውን አጽዋማት ሁሉ በእምነት የምንጾም ከሆነ እንኳን ከታሰበው ከተሰነዘረውም እንድናለን። በሥልጣን ወንበር ላይ የተቀመጡ ሹማምንትም በሀገር በወገን ላይ መዓት ሲወርድ እያዩ ዝም እንዳይሉ፥ መርዶክዮስ ለአስቴር ከላከው መልእክት እና ከአስቴር ተግባር መማር አለባቸው። ዛሬ ተመችቷቸው ነገ በእግዚአብሔር ቁጣ ከሚጠፉ፥ ቢጠፉም፣ ቢድኑም ከወገናቸው ጋር ይሻላቸዋል። ደግሞም አይጠፉም፤ ምክንያቱም ለአስቴር ሞገስን የሰጠ አምላክ ለእነርሱም ይሰጣቸዋል፥ አስቴርንም አይሁድንም ያዳነ አምላክ ያድናቸዋል።
ሠ፡-ጾም ከራስ አልፎ ለልጆችም ለሀገርም ይጠቅማል፤
በመጽሐፈ እዝራ እንደተጻፈው፡-ነቢዩ ዳንኤል በጾም ራሱን በእግዚአብሔር ፊት እንዳዋረደ፥ የእስራኤልም ልጆች በጾም ራሳቸውን በአምላካቸው ፊት በማዋረዳቸው፥ ለልጆቻቸውና ለሀገራቸው የለመኑት ልመና ሁሉ ደርሶላቸዋል።“ስለዚህም ነገር ጾምን፥ወደ እግዚአብሔርም ለመንን፥እርሱም ተለመነን።”ይላል። ዕዝ፡፰፥፳፩-፳፫። ነህምያም በምርኰ እያለ የኢየሩሳሌምን ጥፋት በሰማ ጊዜ ማቅ ለብሶ፥ አመድ ላይ ተኝቶ፥ ጾመ፣ ጸለየ።“ይህንም ቃል በሰማሁ ጊዜ ተቀምጬ አለቀስሁ፥ አያሌ ቀንም አዝን ነበር፤ በሰማይም አምላክ ፊት እጾምና እጸልይ ነበር።” ይላል። ነህ፡፩፥፬። ከዚህ በኋላ ጠላት ያፈረሳትን ሀገሩን ለመሥራት ቆርጦ ተነሣ። ብዙዎች ተስፋ ሊያስቆርጡት ሞክረው ነበር። እርሱ ግን፡- “የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፤ እኛም ባሪያዎቹ ተነሥተን እንሠራለን፥ እናንተ ግን በኢየሩሳሌም እድል ፈንታና መብት መታሰቢያም የላችሁም አላቸው።”ነህ፡፪፥፳። ዙሪያቸውን ያሉ ጠላቶቻቸውም ቀን ከሌሊት እየተዋጉ ብዙ ተፈታትነዋቸው ነበር። እነ ነህምያ ግን በአንድ በኩል እየተዋጉ በሌላ በኩል ሀገራቸውን እንደገና ሠሯት። ነህ፡፯፥፩። በሰባተኛው ወር በሃያ አራተኛውም ቀን የእስራኤል ልጆች ጾመው፥ ማቅም ለብሰው፥ በላያቸውም ትቢያ ነስንሰው ተከማቹ። ኃጢአታቸውንና የአባቶቻቸውን ኃጢአት ተናዘዙ። ለእግዚአብሔርም ሰገዱ። ነህ፡፱፥፩-፬። በመሆኑም እነርሱን አብነት አድርገን የምንጾማቸው አጽዋማት ሁሉ ለኑሯችን፥ ለትዳራችን፥ ለልጆቻችንና ለሀገራችን፡- ሰላምን፣ፍቅርንና አንድነትን፥ በረከትንና ረድኤትን ያሰጡናል።
ረ፡-ጾምን በመጾማችን የሚጐድልብን፥ባለመጾማችን ደግሞ የምናተርፈው የለም፤
አብዝቶ ከመጾም ጋር መልካሙን ገድል የተጋደለ፥ መንፈሳዊ ሩጫውን የጨረሰ፥ ሃይማኖቱን የጠበቀ፥የጽድቅ አክሊ ልም የተሰጠው ሐዋርያ፥ ቅዱስ ጳውሎስ፡-“መብል ግን ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ባንበላም ምንም አይጐድልብንም፥ ብንበላም ምንም አይተርፈንም።”ብሏል።፩ኛ፡ቆሮ፡፰-፰።“ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ሁሉ ግን አይጠቅምም።ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ በእኔ ላይ ግን አንድ ነገር እንኳ አይሠለጥንብኝም። መብል ለሆድ ነው፥ ሆድም ለመብል ነው፥ እግዚአብሔር ግን ይህንም ያንም ያጠፋቸዋል።” በማለት የተናገረበት ጊዜም አለ። ፩ኛ፡ቆሮ፡፮፥፲፪። ሐዋርያው፡- “ሁሉ ተፈቅዶልኛል፤” ያለበት ምክንያት አለው። ይኸውም የሰው ልጅ ከነጻ ፈቃድ ጋር፥ ማለትም ከሙሉ ነጻነት ጋር መፈጠሩን ለማመልከት ነው። የሰው ልጅ ጽድቅን ልሥራ ቢል፥ ኃጢአትንም ልሥራ ቢል ሙሉ ነጻነት አለው። እግዚአብሔር የጽድቅን ዋጋ፥ የኃጢአትን ፍዳ ከመንገር ባለፈ አስገድዶ የሚገዛ አምላክ አይደለምና። አዳምን፡- “ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታው ቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ትሞታለህና።” አለው እንጂ አላስገደደውም። ዘፍ፡፪፥፲፮-፲፯።
ሰ፡-“ወደ አፍ የሚገባ አያረክስም፤”
ጻፎችና ፈሪሳውያን ወደ ኢየሱስ ቀርበው፡-“ደቀመዛሙርትህ ስለምን የሽማግሎችን ወግ ይተላለፋሉ? እንጀራ ሲበሉ እጃቸውን አይታጠቡምና።” ባሉት ጊዜ ፥“እናንተስ ስለ ወጋችሁ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስለ ምን ትተላለፋላችሁ?” ብሏቸዋል። ምክንያቱም አይሁድ ስለ ወጋቸው እንጂ ስለ እግዚአብሔር ትእዛዝ እምብዛም እይጨነቁም ነበርና ነው። ሕዝቡንም ጠርቶ፡- “ስሙ፥ አስተውሉም፤ ሰውን የሚያረክሰው ወደ አፍ የሚገባ አይደለም፥ ከአፍ የሚወጣው ግን ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው።” አላቸው። ይህ ትምህርት ከጾም ጋር የተገናኘ ወይም በጾም ምክንያት የተነገረ ሳይሆን ምሳሌያዊ ትምህርት ነው። በመሆኑም ቅዱስ ጴጥሮስ፡- “ምሳሌውን ተርጉምልን፤”ብሎታል። ጌታም “ወደ አፍ የሚገባ ሁሉ ወደ ሆድ አልፎ ወደ እዳሪ እንዲጣል አትመለከቱምን? ከአፍ የሚወጣ ግን ከልብ ይወጣል፥ ሰውን የሚያረክሰው ያ ነው። ከልብ ክፉ አሳብ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ ዝሙት፥መስረቅ፥ በውሸት መመስከር፥ ስድብ ይወጣልና። ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው እንጂ ባልታጠበ እጅ መብላትስ ሰውን አያረክሰውም።” በማለት ተርጉሞላቸዋል። ማቴ፡፲፭፥፩-፳።ምሥጢራዊ መልእክቱም፡-“የሰው ልጅ ከልቡ አመንጭቶ ክፉ በመናገሩ ይረክሳል እንጂ፥ በሐሰት የተነገረበትን ክፉ ነገር በመስማቱ አይረክስም፤ ምግብ በአፍ ገብቶ በሌላ በኩል ቆሻሻ ሆኖ እንደሚወጣ ፥በአንድ ጆሮ የሰማችሁትን ክፉ ነገር እንደ ቆሻሻ በሌለኛው ጆሮ አውጥታችሁ ጣሉት፤”ማለት ነው። አይሁድ ጌታን ያረከሱ መስሏቸው አያሌ ክፉ ነገር ይናገሩበት ነበር፥ በዚህም እነርሱ ይረክሳሉ እንጂ እርሱ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ቅዱስ ነው። ዋናው ነገር፡- የጾማቸውን ዋጋ ለቅዱሳን ነቢያት የሰጠ፥ በተዋህዶ ሰው ሆኖ የጾመ፥ “በዚያን ጊዜ ይጾማሉ፤” ብሎ ስለ ጾመ ሐዋርያት የተናገረ፥ “በጾምና በጸሎት እንጂ ሰይጣን እንዲሁ አይለቅም፧”ያለ፥ወደ አፍ የሚገባ አያረክስም፤”የሚለውንም የተናገረ፥ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

የእግዚአብሔር ቸርነት፣የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፧አሜን።

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top