ፍትሐት

ፍትሐት

ፍትሐት ማለት ከኃጢአት እስራት መፍታት ወይም መፈታት ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ለሞቱ ሰዎች የሚደረገው ጸሎት ጸሎተ ፍትሐት ይባላል።

የሙታን ነፍሳት ከሥጋ እንደተለዩ እስከ እለተ ምጽአት ድረስ በማረፊያ ቦታ ይቆያሉ እንጂ በቀጥታ ወደ መንግስተ ሰማይ ወይም ወደ ገሃነመ እሳት እንደማይላኩ ቤተ ክርስቲያን የምታምነውና የምታስተምረው ትምህርት ነው፤ እስከ ፍርድ ቀን ድረስ የሚቆዩበትም ቦታ ለጻድቃን ገነት ሲሆን ለኃጢአተኞች ደግሞ ሲኦል ነው። የጻድቃን ማረፊያ ቦታቸው ገነት መሆኑን ለማመልከት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ በነበረ ጊዜ ንስሐ ለገባው ወንበዴ፡ “በእውነት እልሃለው ዛሬውኑ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ብሎታል። ሉቃስ ፳፫፡ ፵፫። የኃጢአተኞች መቆያ ደግሞ ሲኦል መሆኑን ለማመልከት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሀብታሙ ሰውና በድኻው አልዓዛር ምሳሌ ትምህርቱ ሀብታሙ ሰው በሲኦል ውስጥ እንደነበረ ገልጿል። ሉቃስ ፲፮፡ ፳፫፡፡

በሙታን ትንሣኤ ጊዜ የምንነሳው በውርደት ወይም ክብር በሌለው ሁናቴ በመሬት ውስጥ እንደተቀበርነው ሳይሆን፣ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው በክብር፣ በኃይልና በመንፈሳዊነት ነው። ፩ኛ ቆሮንቶስ ፲፭፡ ፵፪-፵፬። ከዚያም በኋላ ወደ ክርስቶስ የፍርድ ፊት እንቀርባለን። ፪ኛ ቆሮንቶስ ፭፡ ፲፤ ራዕይ ፮፡ ፱-፲፩፡፡
ይቅርታ በዚሁ ዓለምና በሚመጣውም ዓለም መኖሩን ቅዱስ መጽሐፍ ያስረዳል። ማቴዎስ ፲፪፡ ፴፪፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቶ ለነበረው ለኦኔሲፎር “በመጨረሻው ቀን ምሕረትን ይስጠው” ብሎ ጸልዮለታል። ፪ኛ ጢሞቴዎስ ፩፡ ፲፰። ቤተ ክርስቲያንም ይህንኑ ጸሎት ለሞቱ ሁሉ ትጸልያለች።
ለሞቱ ሰዎች መጸለይ ደግሞ በጥንት በዘመነ ብሉይም ነበረ። ጀግናው ይሁዳ መቃብዮስ በጦርነት ለሞቱ ወታደሮቹ የኃጢአት መሥዋዕት ይደረግላቸው ዘንድ ሁለት ሺህ የብር ድራህም አሰባስቦ ወደ ኢየሩሳሌም ልኳል። ፪ኛ መቃብያን ፲፪፡ ፵፫፤ ዕዝራ ሱቱኤል ፮: ፴፭። አይሁድ ለሙታን ሲጸልዩ ዳዊት ይደግማሉ።
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች በተላከው የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ላይ ባደረገው ስብከቱ እንዲህ ብሏል “አንድ ሰው ኃጢአተኛ እንደሆነ ቢሞት የምንችለውን ያኽል ልንረዳው ይገባል። የምንረዳውም በለቅሶና በሐዘን ሳይሆን በጸሎት፣ በምጽዋትና በቁርባን ነው። የዓለምን ኃጢአት ወደ ተሸከመው የእግዚአብሔር በግ ስለ ሙታን የምንጸልየው እነርሱ መጽናናትንና እረፍትን እንዲያገኙ ብለን ነው እንጂ በከንቱ አይደለም። ጻድቁ ኢዮብ ስለልጆቹ ያቀርብ የነበረው ቁርባን ጠቀሜታ ከነበረው ስለ ሙታን የምናቀርበው ቁርባን ምንኛ የበለጠ ጠቀሜታ ይኖረው?

ጸሎተ ፍትሐት የሚደረግላቸው እነ ማን ናቸው ??

ጸሎተ ፍትሐት የሚደረገው ሳይታወቁ ለተፈጸሙ ኃጢአቶች፣ በድብቅ ለተፈጸሙ ኃጢአቶች፣ እንዲሁም ለተረሱ ኃጢአቶችና ኃጢአት ሰሪው ኃጢአት መስራቱ ሳይሰማው የሚሰራቸው ኃጢአቶች ናቸው። እንደነዚህ ያሉት ኃጢአቶች ከሰው ተፈጥሮ ደካማነት የተነሳ የሚፈጸሙ መሆናቸው ቢታመንበትም በእግዚአብሔር ፍትሕ በኩል ግን እንዲህ አይደለም። እግዚአብሔር ለሙሴ የነገረው “አንድ ሰው ባለማወቅ ከእግዚአብሔር ትእዛዝ አንዱን ቢተላለፍ በደለኛ ነው” ብሎ ነው፡፡ ዘሌዋ ፭፡ ፲፯።
ሰው አፈር የሆነውን ሥጋ የለበሰ እንደመሆኑ መቼም ቢሆን ሙሉ ለሙሉ ከኃጢአት የነፃ ሊሆን አይችልም። “ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናታልላለን፣ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም” እንዲሉ። ፩ኛ ዮሐንስ ፩፡ ፰። እግዚአብሔር በንስሐ የሚመለሰውን ሰው በማንኛውም ጊዜ ቢሆን ይቀበለዋል።፡ ለምሳሌ በሞት አፋፍ ላይ የነበረውና ከጌታችን ጋር ተሰቅሎ የነበረው ወንበዴ ንስሐው ተቀባይነት ያገኘው በመጨረሻው ደቂቃ ነው። ስለዚህ ንስሐ የገባ ሰውና በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያገኘው ማን እንደሆነ ስለማናውቅ ለሁሉም እንጸልያለን። ለሙታን የሚደረግ ጸሎት ወይም ጸሎተ ፍትሐት ዘወትር ጠቃሚ ነው። ወደ ገነት ለመግባት ላልታደሉት ጸሎቱ ዕድላቸውን ከመቃብር በላይ ያደርግላቸዋል። በሰማይ ስማ ሰምተህም ይቅር በል።; ፪ኛ ዜና ፮፡ ፳፩። በገነት ላሉትም እንደ ታላቅ ብርሃን እየፈነጠቀ ታላቅ ደስታን ይሰጣቸዋል። በዚህም መሠረት ቤተ ክርስቲያን በፍትሐት ጸሎት አምና ለልጆቿ ምህረትን ትለምናለች፣ ይህንኑም ታስተምራለች።

ለሙታን የሚደረግ ጸሎት አስፈላጊነት ?

ከሞትም በኋላ ቢሆን በሰዎች መካከል የሚኖረው መንፈሳዊ ግኑኝነት በጸሎት አማካይነት ይቀጥላል። ሉቃ ፲፮፡ ፲፱-፴፩። በእምነት የሚደረግ ጸሎት ኃይል እንዳለው ተራራንም ለማንቀሳቀስ እንደሚያስችል በወንጌል ተገልጾልናል። መጽሐፍ ቅዱስም የአንዱ ሰው ጸሎት ሌላውን እንደሚራዳ ያስተምረናል። ዮሐ ፬፡ ፵፮-፶፫፤ ማቴ ፲፭፡ ፳፩-፵፰፤ ማር ፱፡ ፲፯-፳፯፤ ማር ፪፡ ፪-፲፪፤ ማቴ ፰፡ ፭-፲፫፤ ዮሐ ፲፩፡ ፩። ጌታችን ከላይ ከተጠቀሱት ተአምራት በርካታዎቹን በአካል በቦታው ተገኝቶ ሳይሆን ሳይገኝ በኃይሉ ፈጽሟል። ጸሎት እንደ ብርሃን ነጸብራቅ የሚጓዝና የሚያበራ የፍቅር ውጤት ነው። እግዚአብሔርን አምነው የሚጸልዩትን ከምድር ጫፍ እስከ ምድር ጫፍም ይሁን የእርሱ አገር እስከ ሆነውም አልፎ ያገናኛል። ጸሎት እኛ የምንኖርባትን ዓለም ከመላእክት፤ ከቅዱሳንና በሞት የተለዩን ወገኖቻችን ከሚገኙባት ዓለም ጋር ያገናኛል።

ሞት በጌታችን ትንሳኤ የተነሳም የቀደመ ኃይሉን አጥቷል። ትንሳኤውም የአዲስ ሕይወት መጀመሪያ ሆኗል። ሮሜ ፰፡ ፴፰-፴፱። በዚህም የተነሳ እግዚአብሔርን ሁሉ ለእርሱ ሕያዋን ስለ ሆኑ፥ የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም; እያልን ሁሉ በሕይወት ይኖሩ ዘንድ እንጸልያለን። ሉቃስ ፳፡ ፴፰።
በዚህ ዓለም የነበሩ ክርስቲያኖች በሕይወት በነበሩበት ዘመን ከቤተ ክርስቲያናቸው ጋር የነበረው ግኑንነት ከአረፉም በኋላ አይቋረጥም። በገነት ከሆኑ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ስለ እኛ ሊጸልዩልን ነጻነት አላቸው። ወደ ሲኦል የወረዱም ከሆኑ በዚያ ሆነው የእኛን ጸሎት ይሻሉ። ቅዱስ ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያንን መሠረቶቿ በምድር ሆነው ጫፎቿ ከሰማይ ጋር የተያያዙ አድርጎ መመሰሉም ይህንኑ ለማስረዳት ጭምር ነው። ነገር ግን ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፥ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላዕክት፥ በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር፥ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር፥ ፍጹማንም ወደ ሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፥ የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል።; ዕብ ፲፪፡ ፳፪-፳፬። ይህም የሚያመለክተው በሰማይና በምድር ባሉት አብያተ ክርስቲያናት መካከል የማይጠፋ የጠበቀ ግኑኝነት ያለ መሆኑን ነው።
በምንጸልየውም ጸሎት የዘመናት ገደብ ሳይኖርብን የሐዋርያት፤ የሰማእታትና የቅዱሳን ሁሉ ጸሎትም እንዲረዳን እንጸልያለን።

ያዘኑትን ማጽናናት ?

ከጎናችን ያለ ሰው ሲያዝን እኛስ ማዘናችን ይቀራል? ጌታችን ወዳጁ አልዓዛር ሲሞት አዝኖለት እንባውን አፍስሷል። ይሁን እንጂ በሞት የተነሳ የሚገጥመን ሐዘን ግን በእግዚአብሔር እስከ ማጉረምረም ሊያደርሰን አይገባውም። ሞት ለጊዜው የነፍስ ከሥጋ መለየት እንጂ የሰው ለዘላለም መጥፋት አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስም እንቅልፍ እየተባለ ተጠቅሷል። የሐ. ሥራ ፲፫፡ ፴፮። ይህ በሥጋ የሚገጥም አካላዊ ሞት በምድር ካለ የዘወትር ድካም፤ ሐዘን፤ ሕመም፤ ፍርሐት ይህችን ዓለም ከሞላባት ድካም ሁሉ ማረፊያ መንገድ ነው። ራዕይ ፲፬፡ ፲፫።
ሞት የእግዚአብሔር እውነት ብቻ ወደ ነገሰችባት፤ ሰማያዊው ብርሃን ወደ ሚያበራባት፤ የሰው ነፍስ ፍጻሜ የሌለው ደስታ ወደ ምታገኝባት ዓለም መሻገሪያ ድልድይ ነው። ፩ኛ ተሰ ፬፡ ፲፫-፲፭፤ ፪ኛ ቆሮ ፭፡ ፩-፰። የወገኖቻችን ወደ ሌላ ዓለም በሞት መሻገር የኛም መጨረሻ መቃረቡን ያስታውሰናል። ስለዚህ መጨረሻችን ሕመምና ፍርድ የሌለበት ሰላማዊ የሆነ ክርስቲያናዊ ፍጻሜ እንዲሆንና በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት እንዳይፈረድብን ለነርሱ ስንጸልይ ለራሳችንም እንጸልይ። ሉቃ ፲፮፡ ፳፪።

ቤተክርስቲያንም ከላይ በሰፊው እንደተገለጸው ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩ ክርስቲያኖች ሃይማኖታዊ የፍትሐት አገልግሎት ትሰጣለች፣ እግዚአብሔር የሙታንን ነፍስ በገንት እንዲያሳርፍ ትጸልያለች።

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top