ሌሎች እንደ አርዮስ ክህደት ያሉት በየዘመኑ የሚነሱት ልዩ ልዩ አዳዲስ ትምህርቶች የምንፍቅና መሆናቸውን ለማረጋገጥ ይህችን ሃይማኖት ኦርቶዶክስ ብለዋታል፡፡
ተዋሕዶ (Miaphysite)
ተዋሕዶ የሚለው ቃል ከልሣነ ግእዝ የመነጨ ቃል ነው፡፡ ትርጒሙም “አንድ ሆነ” ማለት ነው።በዚህ ትርጉም ውስጥ አንድ የሆኑት መለኮታዊና ሰብዓዊ ባሕርይ (መለኮትና ትስብዕት) ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት የተዋሕዶ ትርጓሜ በአጭሩ “ወልድ ዋሕድ” የሚለው ነው፡፡ክርስቶስ ሰው የሆነው ያለሚጠት (ያለመመለስ)፣ ያለ ውላጤ (ያለ መለወጥ)፣ ያለ ቱሳኤ (ያለ መቀላቀል)፣ ያለትድምርት (ያለ መደመር)፣ ያለ ቡዓዴ (ያለመለያየት)፣ ያለ ኅድረት (ያለ ማደር) ነው፡፡
ክርስቶስ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ፣ ከሁለት አካል አንድ አካል የሆነው በተዋህዶ ነው፡፡ ስለዚህ ተዋሕዶ የሚለው ቃል ክርስቶስ ሰው የሆነበትን ምስጢር የሚገልፅ ታላቅ ቃል ነው፡፡ ክርስቶስ ሰው የሆነው በተዋሕዶ ነው
የተዋሕዶ ምሳሌዎች (Examples of Miaphysite)
የነፍስና የሥጋ ተዋሕዶ፡- ነፍስና ሥጋ ተዋሕደው አንድ ሰው ይባላል እንጂ ሁለት አይባልም፡፡
የብረትና የእሳት ተዋህዶ፡- ብረት በእሳት ሲግል የጋለ ብረት እንጂ ይህ ብረት ነው፣ ይህ ደግሞ እሳት ነው ተብሎ አይለይም፡፡
የሲና ሐመልማል፡- እሳቱ ሐመልማሉን ሳያቃጥለው፣ ሐመልማሉም እሳቱን ሳያጠፋው በአንድነት (በተዐቅቦ) መታየታቸው የተዋህዶ ምሳሌ ነው (ዘፀ 3፡2)፡፡