የኢየሱስ ክርስቶስ ታሪክ

የኢየሱስ ክርስቶስ ታሪክ፦
የጌታችን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ ታሪክ የምናጠናው በአራቱ ወንጌላት አቀራረብ መሠረት ነው። ስናጠናም የታሪኩን ቅደም ተከተል በመጠበቅ ይሆናል።
የኢየሱስ ክርስቶስ ቀዳማዊነት፦
ከአራቱ ወንጌላት ውስጥ የኢየሱስ ክርስቶስን ቀዳማዊነት በመተረክ የሚጀምረው የዮሐንስ ወንጌል ነው። ቀዳማዊነት ስንል ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት የነበረ፤ አልፋና ዖሜጋ፤ መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው፤ ሁሉ በእርሱ የሆነ፤ ማንም የማይቀድመው፤ ለዘመኑ ጥንት ወይም ፍጻሜ የሌለው ማለታችን ነው። በዚሁ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ተጽፎ የምናገኘው ታሪክ ገና ከመግቢያው ሲል እንዲህ ሲል ይጀምራል፦ በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም። በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም አላሸነፈውም። ዮሐ. ፩፡ ፩ በዚህ ክፍል ዮሐንስ ጌታን <ቃል> ብሎ ይጠራዋል። ይህም በግሪክኛ <ሎጎስ> ይባላል። የኢየሱስ ክርስቶስ ህልውና የሚጀምረው በቤተልሔም ከተወለደ ጀምሮ አይደለም። ነገር ግን ዓለም ከመፈጠሩ በፊት በአምላክነቱ (በእግዚአብሔርነቱ) የነበረው ነው።
􀂾 በኋለኛው ዘመን ግን ስለመዳናችን ከኃጢአት በቀር እንደ እኛ ሰው ኾነ። ዕብ. ፩፡፲፭
􀂾 ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ። ገላ፤፬፡፬
የኢየሱስ ክርስቶስ ሐረገ-ትውልዱ፦
የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሐረገ-ትውልዱ የተመዘገበው ሁለት ቦታ ላይ ነው። ማቴዎስ ከአብርሃም ጀምሮ እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ድረስ ወደፊት ፵፪ ትውልድ ይቆጥራል። የትውልዱ አቆጣጠር በጌታችን እናት በማርያም በኩል ሳይሆን በዮሴፍ በኩል ነው። የዚህም ምክንያቱ በአይሁድ የሐረግ-ትውልድ አቆጣጠር ልማድ መሠረት ትውልድ የሚቆጠረው በወንድ በኩል ስለሆነ ነው። በተጨማሪም ዮሴፍ ከማርያም ጋር በአንድ የትውልድ ሐረግ ውስጥ ስለሆነ በዮሴፍ በኩል በመቆጠሩ ሐረገ-ትውልዱ ስለማይለወጥ ነው። ማቴ. ፩፡፩-፲፯ ነው። ሉቃስ <እንደመሰላቸው> ብሎ በመግለጥ ከዮሴፍ ጀምሮ እስከ አዳም ድረስ ፸፰ ትውልድ ወደኋላ ይቆጥርለታል። ከማቴዎስ አቆጣጠር ጋር የሚገናኝበትም የሚለያይበትም ቦታ አለ። በአመዘጋገብም ማቴዎስ የጌታን ሐረገ-ትውልድ የመዘገበው ልጅነቱን ታሪክ መዝግቦ ከማቅረቡ በፊት ሲሆን ሉቃስ የመዘገበው ግን ጌታ በማስተማር ዘመኑ ያደረገውንና ያስተማረውን ነገር መዝግቦ ከማቅረቡ በፊት ነው። የኢየሱስ ክርስቶስን ሐረገ-ትውልድ እነዚህ ወንጌላውያን መቁጠራቸው ፍጹም ሰውነቱን በግልጽ ያስረዳል።
የኢየሱስ ክርስቶስ ፅንሰቱ፦
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተፀነሠው በመንፈስ ቅዱስ ነው። ወንጌላዊው ሉቃስ ይህንን ታላቅ ምስራች ለዓለም ሲገልጽና ጌታ በምን ዓይነት ሁኔታ ወደ ምድር እንዲመጣ ሲያሳውቀን፦
􀂾 በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል ወደ ገሊላ ከተማ፥ ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፥ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ። መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ። ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት። እርስዋም ባየችው ጊዜ ከንግግሩ በጣም ደነገጠችና። ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው? ብላ አሰበች። መልአኩም እንዲህ አላት። ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም። ማርያምም መልአኩን። ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል? አለችው። መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት። መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር
ልጅ ይባላል። እነሆም ዘመድሽ ኤልሳቤጥ፥ እርስዋ ደግሞ በእርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፥ ለእርስዋም መካን ትባል ለነበረችው ይህ ስድስተኛ ወር ነው፤ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና። ማርያምም እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ አለች። መልአኩም ከእርስዋ ሄደ። ማርያምም በዚያ ወራት ተነሥታ ወደ ተራራማው አገር ወደ ይሁዳ ከተማ ፈጥና ወጣች፥ ወደ ዘካርያስም ቤት ገብታ ኤልሳቤጥን ተሳለመቻት። ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ውስጥ ዘለለ፤ በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት፥ በታላቅ ድምፅም ጮኻ እንዲህ አለች። አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፥ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል? እነሆ፥ የሰላምታሽ ድምጽ በጆሮዬ በመጣ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና። ከጌታ፤ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት። ማርያምም እንዲህ አለች። ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤ የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና። እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤ ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጎአልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው። ምሕረቱም ለሚፈሩት እስከ ትውልድና ትውልድ ይኖራል። በክንዱ ኃይል አድርጎአል፤ ትዕቢተኞችን በልባቸው አሳብ በትኖአል፤ ገዥዎችን ከዙፋናቸው አዋርዶአል፤ ትሑታንንም ከፍ አድርጎአል፤ የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአል፤ ባለ ጠጎችንም ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል። ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፥ ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘላለም ምሕረቱ ትዝ እያለው እስራኤልን ብላቴናውን ረድቶአል።
ማርያምም ሦስት ወር የሚያህል በእርስዋ ዘንድ ተቀመጠች ወደ ቤትዋም ተመለሰች። ሉቃ. ፩፡፳፮-፶፮
􀂾 ዮሴፍም የእመቤታችንን የመፅነስ ሁኔታ በውል ስላልተረዳ የጌታ መልአክ ቅዱስ የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፥ ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ። ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። ማቴ. ፩፡ ፳።
የኢየሱስ ክርስቶስ ልደቱ፦
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደትን አስመልክቶ ወንጌላዊው ሉቃስ ይህንን ታላቅ ምስራች ለዓለም ሲገልጽና ጌታ በምን ዓይነት ሁኔታ እንደተወለደ ሲያሳውቀን፦
􀂾 በዚያም ወራት ዓለሙ ሁሉ እንዲጻፍ ከአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ ወጣች። ቄሬኔዎስ በሶርያ አገር ገዥ በነበረ ጊዜ ይህ የመጀመሪያ ጽሕፈት ሆነ። ሁሉም እያንዳንዱ ይጻፍ ዘንድ ወደ ከተማው ሄደ። ዮሴፍም ደግሞ ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበረ ከገሊላ ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ ቤተ ልሔም ወደምትባል ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ይሁዳ፥ ፀንሳ ከነበረች ከእጮኛው ከማርያም ጋር ይጻፍ ዘንድ ወጣ። በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፥ የበኵር ልጅዋንም ወለደች፥ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው። በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ
በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ። እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፥ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ። መልአኩም እንዲህ አላቸው። እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ። ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ። ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ። መላእክትም ከእነርሱ ተለይተው ወደ
ሰማይ በወጡ ጊዜ፥ እረኞቹ እርስ በርሳቸው እንግዲህ እስከ ቤተ ልሔም ድረስ እንሂድ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንይ ተባባሉ። ፈጥነውም መጡ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ። አይተውም ስለዚህ ሕፃን የተነገረላቸውን ነገር ገለጡ። የሰሙትን ሁሉ እረኞቹ በነገሩአቸው ነገር አደነቁ፤ ማርያም ግን ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ እያሰበች ትጠብቀው ነበር። እረኞችም እንደ ተባለላቸው ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ ተመለሱ። ሉቃ. ፪፡፩-፳
􀂾 ኢየሱስም በይሁዳ ቤተ ልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ እነሆ ሰብአ ሰገል የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። ንጉሡ ሄሮድስም ሰምቶ ደነገጠ፥ ኢየሩሳሌምም ሁሉ ከእርሱ ጋር የካህናትንም አለቆች የሕዝቡንም ጻፎች ሁሉ ሰብስቦ ክርስቶስ ወዴት እንዲወለድ ጠየቃቸው። እነርሱም አንቺ ቤተ ልሔም፥ የይሁዳ ምድር፥ ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሽም፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መስፍን ከአንቺ ይወጣልና ተብሎ በነቢይ እንዲህ ተጽፎአልና በይሁዳ ቤተ ልሔም ነው አሉት። ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገልን በስውር ጠርቶ ኮከቡ የታየበትን ዘመን ከእነርሱ በጥንቃቄ ተረዳ፥ ወደ ቤተ ልሔምም እነርሱን ሰድዶ። ሂዱ፥ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ አላቸው። እነርሱም ንጉሡን ሰምተው ሄዱ፤ እነሆም፥ በምሥራቅ ያዩት ኮከብ ሕፃኑ ባለበት ላይ መጥቶ እስኪቆም ድረስ ይመራቸው ነበር። ኮከቡንም ባዩ ጊዜ በታላቅ ደስታ እጅግ ደስ አላቸው። ወደ
ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፥ ወድቀውም ሰገዱለት፥ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት። ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ በሕልም ተረድተው በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ሄዱ። ማቴ. ፪፡፩-፲፪
􀂾 እነርሱም ከሄዱ በኋላ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ። ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፥ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ አለው። እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በሌሊት ያዘና ከጌታ ዘንድ በነቢይ። ልጄን ከግብፅ ጠራሁት የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብፅ ሄደ፥ ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ። ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገል እንደ ተሣለቁበት ባየ ጊዜ እጅግ ተቆጣና ልኮ ከሰብአ ሰገል እንደ ተረዳው ዘመን በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የነበሩትን፥ ሁለት ዓመት የሆናቸውን ከዚያም የሚያንሱትን ሕፃናት ሁሉ አስገደለ። ያን ጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ፥ ድምፅ በራማ ተሰማ፥ ልቅሶና ብዙ ዋይታ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፥ መጽናናትም አልወደደችም፥ የሉምና የተባለው ተፈጸመ። ሄሮድስም ከሞተ በኋላ፥ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በግብፅ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ። የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑን እናቱንም ይዘህ ወደ እስራኤል አገር ሂድ አለ። እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ያዘና ወደ እስራኤል አገር ገባ። በአባቱም በሄሮድስ ፈንታ አርኬላዎስ በይሁዳ እንደ ነገሠ በሰማ ጊዜ፥ ወደዚያ መሄድን ፈራ፤ በሕልምም ተረድቶ ወደ ገሊላ አገር ሄደ፤ በነቢያት። ናዝራዊ ይባላል የተባለው ይፈጸም ዘንድ፥ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ። ማቴ.፪፡፲፫-፳፫
የኢየሱስ ክርስቶስ እድገቱ፦
ጌታ በተወለደ በስምንተኛው ቀን በመልአኩ እንደተነገረ ስሙ <ኢየሱስ> ተብሎ ተጠራ፦
􀂾 ልጅም ትወልዳለች እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። በነቢይ ከጌታ ዘንድ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው። ዮሴፍም ከእንቅልፉ ነቅቶ የጌታ መልአክ እንዳዘዘው አደረገ እጮኛውንም ወሰደ የበኩር ልጅዋንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም፤ ስሙንም ኢየሱስ አለው። ማቴ. ፩፡፳፩-፳፭፤
􀂾 እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። ሉቃ.፩፡፴፩
􀂾 ሊገርዙት ስምንት ቀን በሞላ ጊዜ፥ በማኅፀን ሳይረገዝ በመልአኩ እንደ ተባለ፥ ስሙ ኢየሱስ ተብሎ ተጠራ። ሉቃ. ፪፡፳፩
ጌታ በተወለደ በአርባኛው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም ወደ ቤተ መቅደስ ተወሰደ፦
􀂾 እንደ ሙሴም ሕግ የመንጻታቸው ወራት በተፈጸመ ጊዜ፥ በጌታ ሕግ። የእናቱን ማኅፀን የሚከፍት ወንድ ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ይባላል ተብሎ እንደ ተጻፈ በጌታ ፊት ሊያቆሙት፥ በጌታም ሕግ ሁለት ዋሊያ ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች እንደ ተባለ፥ መሥዋዕት ሊያቀርቡ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት። እነሆም፥ በኢየሩሳሌም ስምዖን የሚባል ሰው ነበረ፥ ይህም ሰው የእስራኤልን መጽናናት ይጠባበቅ ነበር፤ ጻድቅና ትጉህም ነበረ፥ መንፈስ ቅዱስም በእርሱ ላይ ነበረ። በጌታም የተቀባውን ሳያይ ሞትን እንዳያይ በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ነበር። በመንፈስም ወደ መቅደስ ወጣ፤ ወላጆቹም እንደ ሕጉ ልማድ ያደርጉለት ዘንድ ሕፃኑን ኢየሱስን በአስገቡት ጊዜ፥ እርሱ ደግሞ ተቀብሎ አቀፈው እግዚአብሔርንም እየባረከ እንዲህ አለ። ጌታ ሆይ፥ አሁን እንደ ቃልህ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ፤ ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና፤ ይህም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው። ዮሴፍና እናቱም ስለ እርሱ በተባለው ነገር ይደነቁ ነበር። ስምዖንም ባረካቸው እናቱን ማርያምንም።
እነሆ፥ የብዙዎች ልብ አሳብ ይገለጥ ዘንድ፥ ይህ በእስራኤል ላሉት ለብዙዎቹ ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሞአል፥ በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል አላት። ከአሴር ወገንም የምትሆን የፋኑኤል ልጅ ሐና የምትባል አንዲት ነቢይት ነበረች፤ እርስዋም ከድንግልናዋ ጀምራ ከባልዋ ጋር ሰባት ዓመት ኖረች፤ እርስዋም ሰማኒያ አራት ዓመት ያህል መበለት ሆና በጣም አርጅታ ነበር፤ በጾምና በጸሎትም ሌሊትና ቀን እያገለገለች ከመቅደስ አትለይም ነበር። በዚያችም ሰዓት ቀርባ እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ የኢየሩሳሌምንም ቤዛ ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ እርሱ ትናገር ነበር። ሉቃ. ፪፡፳፪-፴፰
ጌታ በተወለደ በአሥራ ሁለት ዓመቱ ወደ ናዝሬት ኢየሩሳሌም ሄደ፦
􀂾 ሕፃኑም አደገ፥ ጥበብም ሞልቶበት በመንፈስ ጠነከረ፤ የእግዚአብሔርም ጸጋ በእርሱ ላይ ነበረ። ወላጆቹም በየዓመቱ በፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ይወጡ ነበር። የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ በሆነ ጊዜ፥ እንደ በዓሉ ሥርዓት ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ፤ ቀኖቹንም ከፈጸሙ በኋላ፥ ሲመለሱ ብላቴናው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር፥ ዮሴፍም እናቱም አላወቁም ነበር። ከመንገደኞች ጋር የነበረ ስለ መሰላቸው የአንድ ቀን መንገድ ሄዱ፥ ከዘመዶቻቸውም ከሚያውቋቸውም ዘንድ ፈለጉት፤ ባጡትም ጊዜ እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። ከሦስት ቀንም በኋላ በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲሰማቸውም ሲጠይቃቸውም በመቅደስ አገኙት፤ የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ተገረሙ። ባዩትም ጊዜ ተገረሙ፥ እናቱም። ልጄ ሆይ፥ ለምን እንዲህ አደረግህብን? እነሆ፥ አባትህና እኔ እየተጨነቅን ስንፈልግህ ነበርን አለችው። እርሱም ስለ ምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን? አላቸው። እነርሱም የተናገራቸውን ነገር አላስተዋሉም። ከእነርሱም ጋር ወርዶ ወደ ናዝሬት መጣ፥ ይታዘዝላቸውም ነበር። እናቱም ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ ትጠብቀው ነበር። ኢየሱስም ደግሞ በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያድግ ነበር። ሉቃ. ፪፡፵-፶፪
􀂾 ይህስ ጸራቢው የማርያም ልጅ የያዕቆብ የዮሳ የይሁዳ የስምዖን ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ በዚህ በእኛ ዘንድ አይደሉምን? አሉ፤ ይሰናከሉበትም ነበር። ማር.፮፡፫
የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀቱ፦
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመጠመቁ በፊት መጥምቁ ዮሐንስ ሦስት ነገሮችን ያደርግ ነበር፦
፩- ንስሐን ይሰብክ ነበር
፪- የንስሐ ጥምቀትን ያጠምቅ ነበር
፫- ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ይመሰክር ነበር። ለዚህም አራቱም ወንጌላውያን የጻፉትን ይመልከቱ። ማቴ.፫፡፩-፲፪፤ ማር.፩፡፩-፱፤ ሉቃ.፫፡፩-፳፩ እና ዮሐ.፩፡፳፱-፴፬
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትን አስመልክቶ አራቱም ወንጌላውያን ይህንን ታላቅ ምስራች ለዓለም ሲገልጹና ጌታ በምን ዓይነት ሁኔታ እንደተጠመቀ ሲያሳውቁን፦
􀂾 ያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ። ዮሐንስ ግን እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን? ብሎ ይከለክለው ነበር። ኢየሱስም መልሶ አሁንስ ፍቀድልኝ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና አለው። ያን ጊዜ ፈቀደለት። ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ እነሆም ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ እነሆም፥ ድምፅ ከሰማያት መጥቶ። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ። ማቴ. ፫፡፲፫-፲፯
􀂾 በዚያ ወራትም ኢየሱስ ከገሊላ ናዝሬት መጥቶ ከዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ። ወዲያውም ከውኃው በወጣ ጊዜ ሰማያት ሲቀደዱ መንፈስም እንደ ርግብ ሲወርድበት አየና የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፥ በአንተ ደስ ይለኛል የሚል ድምፅ ከሰማያት መጣ። ማር. ፩፡፱-፲፩፤
􀂾 ሕዝቡም ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ኢየሱስ ደግሞ ተጠመቀ። ሲጸልይም ሰማይ ተከፈተ፥ መንፈስ ቅዱስም በአካል መልክ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ወረደ፤ የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፥ በአንተ ደስ ይለኛል የሚል ድምፅም ከሰማይ መጣ። ሉቃ.፫፡፳፩-፳፪
􀂾 እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውኃ እያጠመቅሁ እኔ መጣሁ። ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መሰከረ። መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሆኖ ሲወርድ አየሁ፤ በእርሱ ላይም ኖረ። እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን በውኃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ። መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ። ዮሐ. ፩፡፴፩-፴፬።
የኢየሱስ ክርስቶስ በገዳመ ቆሮንቶስ መፈተን፦
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዲያብሎስ መፈተንን አስመልክቶ ማቴዎስና ሉቃስ ይህንን ሁኔታ ለዓለም ሲገልጹ ጌታ በምን ዓይነት ሁኔታ እንደተፈተነና ድልም እንዳደረገ ሲያሳውቁን፦
ፈተና ፩
􀂾 ፈታኝም ቀርቦ። የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል አለው። ማቴ. ፬፡፫
􀂾 ዲያብሎስም። የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ ይህን ድንጋይ እንጀራ ሁን ብለህ እዘዝ አለው። ሉቃ. ፬፡፫
መልስ ፩
􀂾 እርሱም መልሶ። ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል አለው። ማቴ. ፬፡፬፤ ዘዳ. ፰፡፫
􀂾 ኢየሱስም። ሰው በእግዚአብሔር ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል ብሎ መለሰለት። ሉቃ.፬፡፬፤ ዘዳ. ፰፡፫
ፈተና ፪
􀂾 ከዚህ በኋላ ዲያቢሎስ ወደ ቅድስት ከተማ ወሰደውና እርሱን በመቅደስ ጫፍ ላይ አቁሞ መላእክቱን ስላንተ ያዝልሃል እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል ተብሎ ተጽፏልና የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ ወደ ታች ራስህን ወርውር አለው።ማቴ.፬፡፭-፮
􀂾 ወደ ኢየሩሳሌም ደግሞ ወሰደው፤ በመቅደስም ጫፍ ላይ አቁሞ። ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል፥ እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፥ ከዚህ ወደ ታች ራስህን ወርውር አለው። ሉቃ. ፬፡፱-፲፩
􀂾 በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፤ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል። መዝ. ፺፡፲፩-፲፪
መልስ ፪
􀂾 ኢየሱስም። ጌታን አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል አለው። ማቴ. ፬፡፯
􀂾 በማሳህ እንደ ፈተናችሁት አምላካችሁን እግዚአብሔርን አትፈታተኑት። ዘዳ. ፮፡፲፮
􀂾 ኢየሱስም መልሶ። ጌታን አምላክህን አትፈታተነው ተብሎአል አለው። ሉቃ. ፬፡፲፪
􀂾 በማሳህ እንደ ፈተናችሁት አምላካችሁን እግዚአብሔርን አትፈታተኑት። ዘዳ. ፮፡፲፮
ጥያቄ ፫
􀂾 ደግሞ ዲያቢሎስ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ ወሰደው፥ የዓለምንም መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም አሳይቶ። ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ አለው። ማቴ. ፬፡፰-፱
􀂾 ዲያብሎስም ረጅም ወደ ሆነ ተራራ አውጥቶ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በቅጽበት አሳየው። ዲያብሎስም። ይህ ሥልጣን ሁሉ ክብራቸውም ለእኔ ተሰጥቶአል ለምወደውም ለማንም እሰጠዋለሁና ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ስለዚህ አንተ በእኔ ፊት ብትሰግድ፥ ሁሉ ለአንተ ይሆናል አለው። ሉቃ. ፬፡፭-፯
መልስ ፫
􀂾 ያን ጊዜ ኢየሱስ። ሂድ፥ አንተ ሰይጣን ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና አለው። ያን ጊዜ ዲያቢሎስ ተወው፥ እነሆም፥ መላእክት ቀርበው ያገለግሉት ነበር። ማቴ. ፬፡፲-፲፩
􀂾 አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ፤ እርሱንም አምልክ፤ በስሙም ማል። ዘዳ. ፮፡፲፫
ኢየሱስም መልሶ። ለጌታ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአል አለው። ሉቃ. ፬፡፰
􀂾 አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ፤ እርሱንም አምልክ፤ በስሙም ማል። ዘዳ. ፮፡፲፫
ኢየሱስ ክርስቶስ ስለማስተማሩ፦
አምላካችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገሊላ በሰማርያና በይሁዳ እየተመላለሰ አስተምሯል። አብዛኛውን ጊዜ ግን ያስተማረው በገሊላና በአካባቢዋ በተለይም በገሊላ ዋና ከተማ በቅፍርናሆም ነበር። (ሉቃ.፬፡፴፩)በምኩራብና በመቅደስ፣ በቤት ውስጥ፣ እንዲሁም በባሕር ዳር በተራራና በሜዳ ላይ ሕዝብ እየተሰበሰበ ያስተምር ነበር። ሲያስተምርም ከንግግሩ ጣእም ባሻገር አስገራሚ ታምራትን በማድረግ ነበር። ስለሆነም በተለያየ ፈተና ይፈትኑትና ሊያጠፉትም ይሞክሩ የነበሩ ጠላቶቹ እንኳ ሳይቀሩ <ዓለሙ ሁሉ በኋላው ተከትሎት ሄዷል> እስኪሉ ድረስ ብዙ ሕዝብ ይከተለው ነበር። ዮሐ. ፲፪፡፲፱
በወንጌላት ከተመዘገቡት የጌታ ትምህርቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፦
የተራራው ስብከት (አንቀፀ ብፁዓን)
ሕዝቡንም አይቶ ወደ ተራራ ወጣ፤ በተቀመጠም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ አፉንም ከፍቶ አስተማራቸው እንዲህም አለ።
􀂙 በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።
􀂙 የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፥ መፅናናትን ያገኛሉና።
􀂙 የዋሆች ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን ይወርሳሉና።
􀂙 ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና።
􀂙 የሚምሩ ብፁዓን ናቸው፥ ይማራሉና።
􀂙 ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው፥ እግዚአብሔርን ያዩታልና።
􀂙 የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና።
􀂙 ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።
􀂙 ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ።
􀂾 ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና። እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም። እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም። መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል። መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ። እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም። እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፥ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፥ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ።
እንግዲህ ከነዚህ ከሁሉ ካነሱት ትእዛዛት አንዲቱን የሚሽር ለሰውም እንዲሁ የሚያስተምር ማንም ሰው በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ ታናሽ ይባላል፤ የሚያደርግ ግን የሚያስተምርም ማንም ቢሆን እርሱ በመንግሥተ ሰማያት ታላቅ ይባላል። እላችኋለሁና። ጽድቃችሁ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም። ለቀደሙት አትግደል እንደ ተባለ ሰምታችኋል፤ የገደለም
ሁሉ ፍርድ ይገባዋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፤ ወንድሙንም ጨርቃም የሚለው ሁሉ የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል፤ ደንቆሮ የሚለውም ሁሉ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይገባዋል። እንግዲህ መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ፥ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ፥ በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፥ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፥
በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ። አብረኸው በመንገድ ሳለህ ከባላጋራህ ጋር ፈጥነህ ተስማማ፤ ባላጋራ ለዳኛ እንዳይሰጥህ ዳኛም ለሎሌው፥ ወደ ወህኒም ትጣላለህ፤ እውነት እልሃለሁ፥ የመጨረሻዋን ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከቶ ከዚያ አትወጣም።
አታመንዝር እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል። ቀኝ ዓይንህም ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት፤ ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻልሃልና። ቀኝ እጅህም ብታሰናክልህ ቆርጠህ ከአንተ ጣላት፤ ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻላልና። ሚስቱን
የሚፈታት ሁሉ የፍችዋን ጽሕፈት ይስጣት ተባለ። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ አመንዝራ ያደርጋታል፥ የተፈታችውንም የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል። ደግሞ ለቀደሙት። በውሸት አትማል ነገር ግን መሐላዎችህን ለጌታ ስጥ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ። ከቶ አትማሉ፤ በሰማይ አይሆንም የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና፤ በምድርም አይሆንም የእግሩ መረገጫ ናትና፤
በኢየሩሳሌምም አይሆንም የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና፤ በራስህም አትማል፥ አንዲቱን ጠጉር ነጭ ወይም ጥቁር ልታደርግ አትችልምና። ነገር ግን ቃላችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን፤ ከነዚህም የወጣ ከክፉው ነው። ዓይን ስለ ዓይን ጥርስም ስለ ጥርስ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ክፉውን አትቃወሙ፤ ዳሩ ግን ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ
አዙርለት፤ እንዲከስህም እጀ ጠባብህንም እንዲወስድ ለሚወድ መጎናጸፊያህን ደግሞ ተውለት፤ ማንም ሰው አንድ ምዕራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለተኛውን ከእርሱ ጋር ሂድ። ለሚለምንህ ስጥ፥ ከአንተም ይበደር ዘንድ ከሚወደው ፈቀቅ አትበል። ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና። የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ
ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ። ማቴ. ፭፡፩-፵፰
ለሕዝቡ ያስተማረው የምሳሌዎቹ ትምህርት፦
􀂾 በዚያን ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕር አጠገብ ተቀመጠ፤ እርሱም በታንኳ ገብቶ እስኪቀመጥ ድረስ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፥ ሕዝቡም ሁሉ በወደቡ ቆመው ነበር። በምሳሌም ብዙ ነገራቸው እንዲህም አላቸው። እነሆ፥ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። እርሱም ሲዘራ አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፥ ወፎችም መጥተው በሉት። ሌላውም ብዙ መሬት በሌለበት በጭንጫ ላይ ወደቀ፤ ጥልቅ መሬትም ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፥ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ፥ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ። ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፥ እሾህም ወጣና አነቀው። ሌላውም በመልካም መሬት ወደቀ፤ አንዱም መቶ፥ አንዱም
ስድሳ፥ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው። ስለ ምን በምሳሌ ትነግራቸዋለህ? አሉት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው። ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፥ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። ላለው ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። ስለዚህ እያዩ ስለማያዩ እየሰሙም ስለማይሰሙ ስለማያስተውሉም በምሳሌ እነግራቸዋለሁ። መስማት ትሰማላችሁና አታስተውሉም፥ ማየትም ታያላችሁና አትመለከቱም። በዓይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአልና ጆሮአቸውም ደንቁሮአል ዓይናቸውንም ጨፍነዋል የሚል የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል። የእናንተ ግን ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ ብፁዓን ናቸው። እውነት እላችኋለሁ፥ ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን የምታዩትን ሊያዩ ተመኝተው አላዩም፥ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ተመኝተው አልሰሙም። እንግዲህ እናንተ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ።
የመንግሥትን ቃል ሰምቶ በማያስተውል ሁሉ፥ ክፉው ይመጣል፥ በልቡ የተዘራውንም ይነጥቃል፤ በመንገድ ዳር የተዘራው ይህ ነው። በጭንጫ ላይ የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ ወዲያው በደስታ የሚቀበለው ነው፤ ነገር ግን ለጊዜው ነው እንጂ በእርሱ ሥር የለውም፥ በቃሉ ምክንያትም መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላል። በእሾህ መካከል የተዘራውም ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው፥ የዚህም ዓለም አሳብና
የባለጠግነት መታለል ቃሉን ያንቃል፥ የማያፈራም ይሆናል። በመልካም መሬት የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ነው፤ እርሱም ፍሬ ያፈራል አንዱም መቶ አንዱም ስድሳ አንዱም ሠላሳ ያደርጋል። ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው እንዲህም አለ። መንግሥተ ሰማያት በእርሻው መልካም ዘርን የዘራን ሰው ትመስላለች። ሰዎቹ ሲተኙ ግን ጠላቱ መጣና በስንዴው መካከል እንክርዳድን ዘርቶ ሄደ። ስንዴውም በበቀለና በአፈራ ጊዜ እንክርዳዱ ደግሞ ያን ጊዜ ታየ። የባለቤቱም ባሮች ቀርበው። ጌታ ሆይ፥ መልካምን ዘር በእርሻህ ዘርተህ አልነበርህምን? እንክርዳዱንስ ከወዴት አገኘ? አሉት። እርሱም። ጠላት ይህን አደረገ አላቸው። ባሮቹም። እንግዲህ ሄደን ብንለቅመው ትወዳለህን? አሉት። እርሱ ግን። እንክርዳዱን ስትለቅሙ ስንዴውን ከእርሱ ጋር እንዳትነቅሉት አይሆንም። ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ፤ በመከር ጊዜም አጫጆችን እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ልቀሙ በእሳትም ለማቃጠል በየነዶው እሰሩ፥ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱ እላለሁ አለ። ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው እንዲህም አለ። መንግሥተ ሰማያት ሰው ወስዶ በእርሻው የዘራትን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤ እርስዋም ከዘር ሁሉ ታንሳለች፥ በአደገች ጊዜ ግን፥ ከአታክልቶች ትበልጣለች የሰማይም ወፎች መጥተው በቅርንጫፎችዋ እስኪሰፍሩ ድረስ ዛፍ ትሆናለች። ሌላ ምሳሌ ነገራቸው እንዲህም አለ። መንግሥተ ሰማያት ሁሉ እስኪቦካ ድረስ ሴት ወስዳ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች። ኢየሱስም ለሕዝቡ ይህን ሁሉ በምሳሌ ተናገረ፤
በነቢዩም። በምሳሌ አፌን እከፍታለሁ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውንም እናገራለሁ የተባለው ይፈጸም ዘንድ ያለ ምሳሌ አልተናገራቸውም። በዚያን ጊዜ ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ገባ። ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው። የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ተርጕምልን አሉት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው። መልካምን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ እርሻውም ዓለም ነው፤ መልካሙም ዘር የመንግሥት ልጆች ናቸው፤ እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው፥ የዘራውም ጠላት ዲያብሎስ ነው፤ መከሩም የዓለም መጨረሻ ነው፥ አጫጆችም መላእክት ናቸው። እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፥ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል። የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፥ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ይበራሉ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ። ደግሞ መንግሥተ ሰማያት በእርሻ ውስጥ የተሰወረውን መዝገብ ትመስላለች፤ ሰውም አግኝቶ ሰወረው፥ ከደስታውም የተነሣ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ያን እርሻ ገዛ። ደግሞ መንግሥተ ሰማያት መልካምን ዕንቁ የሚሻ ነጋዴን ትመስላለች፤ ዋጋዋም እጅግ የበዛ አንዲት ዕንቁ በአገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ገዛት። ደግሞ መንግሥተ ሰማያት ወደ ባሕር የተጣለች ከሁሉም ዓይነት የሰበሰበች መረብን ትመስላለች፤ በሞላችም ጊዜ ወደ ወደቡ አወጡአት፥ ተቀምጠውም መልካሙን ለቅመው በዕቃዎች ውስጥ አከማቹ
ክፉውን ግን ወደ ውጭ ጣሉት። በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል፤ መላእክት መጥተው ኃጢአተኞችን ከጻድቃን መካከል ይለዩአቸዋል፥ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። ኢየሱስም። ይህን ሁሉ አስተዋላችሁን? አላቸው አዎን አሉት። እርሱም። ስለዚህ የመንግሥተ ሰማያት ደቀ መዝሙር የሆነ ጻፊ ሁሉ ከመዝገቡ አዲሱንና አሮጌውን የሚያወጣ ባለቤትን ይመስላል
አላቸው። ኢየሱስም እነዚህም ምሳሌዎች ከጨረሰ በኋላ ከዚያ ሄደ። ወደ ገዛ አገሩም መጥቶ እስኪገረሙ ድረስ በምኩራባቸው ያስተምራቸው ነበር፤ እንዲህም አሉ። ይህን ጥበብና ተአምራት ይህ ከወዴት አገኘው? ይህ የጸራቢ ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብና ዮሳ ስምዖንም ይሁዳም አይደሉምን? እኅቶቹስ ሁሉ በእኛ ዘንድ ያሉ አይደሉምን? እንኪያስ ይህን ሁሉ ከወዴት አገኘው? ተሰናከሉበትም። ኢየሱስ ግን። ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ቤቱ በቀር ሳይከበር አይቀርም አላቸው። በአለማመናቸውም ምክንያት በዚያ ብዙ ተአምራት አላደረገም። ማቴ. ፲፫፡ ፩-፶፪
ለጻፎችና ለፈሪሳውያን የሰጠው የተግሣጽ ትምህርት፦
በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለሕዝቡና ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሎ ነገራቸው። ጻፎችና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ተቀምጠዋል። ስለዚህ ያዘዙአችሁን ሁሉ አድርጉ ጠብቁትም፥ ነገር ግን እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደ ሥራቸው አታድርጉ። ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ፥ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም። ለሰውም እንዲታዩ ሥራቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፤ ስለዚህ ሽንክታባቸውን ያሰፋሉ ዘርፉንም ያስረዝማሉ፥ በምሳም የከበሬታ ስፍራ፥ በምኵራብም የከበሬታ ወንበር፥ በገበያም ሰላምታና። መምህር ሆይ መምህር ሆይ ተብለው እንዲጠሩ ይወዳሉ። እናንተ ግን መምህር ተብላችሁ አትጠሩ፤ መምህራችሁ አንድ ስለ ሆነ እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ። አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም። አባት ብላችሁ አትጥሩ። ሊቃችሁ አንድ እርሱም ክርስቶስ ነውና። ሊቃውንት ተብላችሁ አትጠሩ። ከእናንተም የሚበልጠው አገልጋያችሁ ይሆናል። ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፥ ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላል። እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ፥ ወዮላችሁ እናንተ አትገቡም የሚገቡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ። እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በጸሎት ርዝመት እያመካኛችሁ የመበለቶችን ቤት ስለምትበሉ፥ ወዮላችሁ፤ ስለዚህ የባሰ ፍርድ ትቀበላላችሁ። እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ አንድ ሰው ልታሳምኑ በባሕርና በደረቅ ስለምትዞሩ፥ በሆነም ጊዜ ከእናንተ ይልቅ ሁለት እጥፍ የባሰ የገሃነም ልጅ ስለምታደርጉት፥ ወዮላችሁ። እናንተ ማንም በቤተ መቅደስ የሚምል ምንም የለበትም፤ ማንም በቤተ መቅደስ ወርቅ የሚምል ግን በመሐላው ይያዛል የምትሉ፥ ዕውሮች መሪዎች፥ ወዮላችሁ። እናንተ ደንቆሮዎችና ዕውሮች፥ ማናቸው ይበልጣል? ወርቁ ነውን? ወይስ ወርቁን የቀደሰው ቤተ መቅደስ? ደግማችሁም። ማንም በመሠዊያው የሚምል ምንም የለበትም፤ ማንም በላዩ ባለው መባ የሚምል ግን በመሐላው ይያዛል ትላላችሁ። እናንተ ደንቆሮዎችና ዕውሮች፥ ማናቸው ይበልጣል? መባው ነውን? ወይስ መባውን የሚቀድሰው መሠዊያው? እንግዲህ በመሠዊያው የሚምለው በእርሱና በእርሱ ላይ ባለው ሁሉ ይምላል፤ በቤተ መቅደስም የሚምለው በእርሱና በእርሱ በሚኖረው ይምላል፤ በሰማይም የሚምለው በእግዚአብሔር ዙፋንና በእርሱ ላይ በተቀመጠው ይምላል። እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ከአዝሙድና ከእንስላል ከከሙንም አሥራት ስለምታወጡ፥ ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተዉ፥ ወዮላችሁ፤ ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉ ይገባችሁ ነበር። እናንተ
ዕውሮች መሪዎች፥ ትንኝን የምታጠሩ ግመልንም የምትውጡ። እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በውስጡ ቅሚያና ስስት ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ስለምታጠሩ፥ ወዮላችሁ። አንተ ዕውር ፈሪሳዊ፥ ውጭው ደግሞ ጥሩ እንዲሆን አስቀድመህ የጽዋውንና የወጭቱን ውስጡን አጥራ። እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጡ ግን የሙታን አጥንት ርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ፥ ወዮላችሁ። እንዲሁ እናንተ ደግሞ በውጭ ለሰው እንደ ጻድቃን ትታያላችሁ፥ በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ዓመፀኝነት ሞልቶባችኋል። እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ የነቢያትን መቃብር ስለምትሠሩ የጻድቃንንም መቃብር ስለምታስጌጡና። በአባቶቻችን ዘመን ኖረን በሆነስ በነቢያት ደም ባልተባበርናቸውም ነበር ስለምትሉ፥ ወዮላችሁ። እንግዲያስ የነቢያት ገዳዮች ልጆች እንደሆናችሁ በራሳችሁ ላይ ትመሰክራላችሁ። እናንተ ደግሞ የአባቶቻችሁን መስፈሪያ ሙሉ። እናንተ እባቦች፥ የእፉኝት ልጆች፥ ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ? ስለዚህ፥ እነሆ፥ ነቢያትንና ጥበበኞችን ጻፎችንም ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም ትገድላላችሁ ትሰቅሉማላችሁ፥ ከእነርሱም በምኵራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዳላችሁ፤ ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ በዚህ
ትውልድ ላይ ይደርሳል። ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም። እነሆ፥ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል። እላችኋለሁና፥ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም። ማቴ. ፳፫፡ ፩-፴፱
ስለ ዳግም ምጽዓት በደብረ ዘይት ያስተማረው ሰፊ ትምህርት፦
ኢየሱስም ከመቅደስ ወጥቶ ሄደ፥ ደቀ መዛሙርቱም የመቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ቀረቡ። እርሱ ግን መልሶ። ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው። እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው ንገረን ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። ብዙዎች። እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፥ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤ እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው። በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሉአችሁማል፥ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። በዚያን ጊዜም ብዙዎች ይሰናከላሉ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ
እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ፤ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ፤ ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች። እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፥ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል። እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፥ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ፥ በሰገነትም ያለ በቤቱ ያለውን ሊወስድ አይውረድ፥ በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ። በዚያችም ወራት ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው። ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ፤ በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና። እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፤ ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለ ተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ። በዚያን ጊዜ ማንም። እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ ወይም። ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ። እነሆ፥ አስቀድሜ ነገርኋችሁ። እንግዲህ። እነሆ፥ በበረሀ ነው ቢሉአችሁ፥ አትውጡ፤ እነሆ፥ በእልፍኝ ነው ቢሉአችሁ፥ አትመኑ፤ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና፤ በድን ወዳለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ። ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፥ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፥ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤ መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፥ ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ። ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ።
እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም። ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም። የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና። በዚያች ወራት ከጥፋት ውኃ በፊት፥ ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ፥ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡም እንደ ነበሩ፥ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ፥ የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል። በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል አንዱም ይቀራል፤ ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱ ትወሰዳለች አንዲቱም ትቀራለች። ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ። ያን ግን እወቁ፤ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ ቤቱም ሊቈፈር ባልተወም ነበር። ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና። እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎች ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው? ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባሪያ ብፁዕ ነው እውነት እላችኋለሁ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል። ያ ክፉ ባሪያ ግን ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል ብሎ በልቡ ቢያስብ፥ ባልንጀሮቹን ባሮች ሊመታ ቢጀምር ከሰካሮችም ጋር ቢበላና ቢጠጣ፥ የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቃት ቀን ባላወቃትም ሰዓት ይመጣል፥ከሁለትም ይሰነጥቀዋል፥እድሉንም ከግብዞች ጋር ያደርግበታል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። ማቴ.፳፬፡፩፤ ፳፭፡፵፮
ስለ መንፈስ ቅዱስ በደርቡ ቤት ያስተማረው ሰፊ ትምህርት፦
ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ። በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤ ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ። ወደምሄድበትም ታውቃላችሁ፥ መንገዱንም ታውቃላችሁ። ቶማስም። ጌታ ሆይ፥ ወደምትሄድበት አናውቅም፤ እንዴትስ
መንገዱን እናውቃለን? አለው። ኢየሱስም። እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር። ከአሁንም ጀምራችሁ ውቁታላችሁ አይታችሁትማል አለው። ፊልጶስ። ጌታ ሆይ፥ አብን አሳየንና ይበቃናል አለው። ኢየሱስም አለው። አንተ ፊልጶስ፥ ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ አንተ። አብን አሳየን ትላለህ? እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም፤ ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል። እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ፤ ባይሆንስ ስለ ራሱ ስለ ሥራው እመኑኝ። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፥ እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና፤ አብም ስለ ወልድ እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ። ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ። ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም
ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ። ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ። ገና ጥቂት ዘመን አለ ከዚህም በኋላ ዓለም አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፤ እኔ ሕያው ነኝና እናንተ ደግሞ ሕያዋን ትሆናላችሁ። እኔ በአባቴ እንዳለሁ እናንተም በእኔ እንዳላችሁ እኔም በእናንተ እንዳለሁ በዚያን ቀን ታውቃላችሁ። ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል እኔም እወደዋለሁ ራሴንም እገልጥለታለሁ። የአስቆሮቱ ያይደለ ይሁዳ። ጌታ ሆይ፥ ለዓለም ሳይሆን ራስህን ለእኛ ልትገልጥ ያለህ እንዴት ነው? አለው። ኢየሱስም መለሰ አለውም። የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን። የማይወደኝ ቃሌን አይጠብቅም፤ የምትሰሙትም ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም። ከእናንተ ዘንድ ስኖር ይህን ነግሬአችኋለሁ፤ አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል። ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም። እኔ እሄዳለሁ ወደ እናንተም እመጣለሁ እንዳልኋችሁ ሰማችሁ። የምትወዱኝስ ብትሆኑ ከእኔ አብ ይበልጣልና ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር። ከሆነም በኋላ ታምኑ ዘንድ አሁን አስቀድሞ ሳይሆን። ነግሬአችኋለሁ። ከእንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋር ብዙ አልናገርም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ይመጣልና፤ በእኔ ላይም አንዳች የለውም፤ ነገር ግን አብን እንድወድ ዓለም ሊያውቅ፥ አብም እንዳዘዘኝ፥ እንዲሁ አደርጋለሁ። ተነሡ፤ ከዚህ እንሂድ። ዮሐ. ፲፬፡፩-፴፩ እንዳትሰናከሉ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። ከምኵራባቸው ያወጡአችኋል፤ ከዚህ በላይ ደግሞ የሚገድላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን እንደሚያገለግል የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል። ይህንም የሚያደርጉባችሁ አብንና እኔን ስላላወቁ ነው። ነገር ግን ጊዜው ሲደርስ እኔ እንደ ነገርኋችሁ ታስቡ ዘንድ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። ከእንናንተም ጋር ስለ ነበርሁ በመጀመሪያ ይህን አልነገርኋችሁም። አሁን ግን ወደ ላከኝ እሄዳለሁ ከእናንተም። ወዴት ትሄዳለህ? ብሎ የሚጠይቀኝ የለም። ነገር ግን ይህን ስለ ተናገርኋችሁ ኀዘን በልባችሁ ሞልቶአል። እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ። እርሱም መጥቶ ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል፤ ስለ ኃጢአት፥ በእኔ ስለማያምኑ ነው፤ ስለ ጽድቅም፥ ወደ አብ ስለምሄድ ከዚህም በኋላ ስለማታዩኝ ነው፤ ስለ ፍርድም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ስለ ተፈረደበት ነው። የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤
የሚመጣውንም ይነግራችኋል። እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና። ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህ። ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልሁ። ጥቂት ጊዜ አለ፥ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፥ ታዩኛላችሁም፥ እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና። ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንዶቹ እርስ በርሳቸው። ጥቂት ጊዜ አለ፥ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፥ ታዩኛላችሁም፤ ደግሞ። ወደ አብ እሄዳለሁና የሚለን ይህ ምንድር ነው? ተባባሉ። እንግዲህ። ጥቂት የሚለው ይህ ምንድር ነው? የሚናገረውን አናውቅም አሉ። ኢየሱስም ሊጠይቁት እንደ ወደዱ አውቆ እንዲህ አላቸው። ጥቂት ጊዜ አለ፥ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፥ ታዩኛላችሁ ስላልሁ፥ ስለዚህ እርስ በርሳችሁ ትመራመራላችሁን? እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እናንተ ታለቅሳለችሁ ሙሾም ታወጣላችሁ፥ ዓለም ግን ደስ ይለዋል፤ እናንተም ታዝናላችሁ፥ ነገር ግን ኀዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል። ሴት በምትወልድበት ጊዜ ወራትዋ ስለ ደረሰ ታዝናለች፤ ነገር ግን ሕፃን ከወለደች በኋላ፥ ሰው በዓለም ተወልዶአልና ስለ ደስታዋ መከራዋን ኋላ አታስበውም። እንግዲህ እናንተ ደግሞ አሁን ታዝናላችሁ፤ ነገር ግን እንደ ገና አያችኋለሁ ልባችሁም ደስ ይለዋል፥ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም። በዚያን ቀንም ከእኔ አንዳች አትለምኑም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል። እስከ አሁን በስሜ ምንም አልለመናችሁም፤ ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ለምኑ ትቀበሉማላችሁ። ይህን በምሳሌ ነግሬአችኋለሁ፤ ነገር ግን ስለ አብ ለእናንተ በግልጥ የምናገርበት እንጂ ከዚያ ወዲያ በምሳሌ የማልናገርበት ሰዓት ይመጣል። በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ስለ እናንተ አብን እንድለምን የምላችሁ አይደለሁም፤ እናንተ ስለ ወደዳችሁኝ ከእግዚአብሔርም ዘንድ እኔ እንደ ወጣሁ ስላመናችሁ አብ እርሱ ራሱ ይወዳችኋልና። ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ደግሞ ዓለምን እተወዋለሁ ወደ አብም እሄዳለሁ። ደቀ መዛሙርቱ። እነሆ፥ አሁን በግልጥ ትናገራለህ በምሳሌም ምንም አትነግርም። ሁሉን እንድታውቅ ማንምም ሊጠይቅህ እንዳትፈልግ አሁን እናውቃለን፤ ስለዚህ ከእግዚአብሔር እንደ ወጣህ እናምናለን አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው። አሁን ታምናላችሁን? እነሆ፥ እያንዳንዳችሁ ወደ ቤት የምትበታተኑበት እኔንም ለብቻዬ የምትተዉበት ሰዓት ይመጣል፥ አሁንም ደርሶአል፤ ነገር ግን አብ ከእኔ ጋር ስለ ሆነ ብቻዬን አይደለሁም። በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ። ዮሐ.፲፮፡፩-፴፫

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ቆሞስ አባ ኃይለሚካኤል ሙላት ግንቦት ፳፻፩ ዓ.ም.

ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት ክፍል ሚኒያፖሊስ ሚኒሶታ (U.S.A.) www.debreselam.net

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top