የእግዚአብሔር ፍጹም አንድነትና ልዩ ሦስትነት

የእግዚአብሔር ፍጹም አንድነትና ልዩ ሦስትነት

“ሥላሴ” የሚለው ቃል “ሠለሰ” ሦስት አደረገ ካለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ሦስትነት ማለት ነው፡፡ ቅድስት ሥላሴ ስንል ለሥላሴ ቅድስት ብለን እንቀጽላለን፡፡ ቅድስት ሥላሴ ማለት ልዩ ሦስትነት ማለት ነው፡፡ ይህም ሦስት ሲሆኑ አንድ፣ አንድ ሲሆን ሦስት ስለሚሆኑ ልዩ ሦስትነት ተብሏል፡፡ ሥላሴ የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ያለና የሚኖረውን አምላክ ለመግለጽ የተጠቀመው የአንጾኪያው ቴዎፍሎስ በ169ዓ.ም ነው፡፡ኋላም በኒቅያ ጉባዔ 318ቱ ሊቃውንት አጽንተውታል፡፡ እነዚህ ሊቃውንት በቅዱሳት መጻሕፍት የተመሰከረውን የእግዚአብሔርን ፍጹም አንድነትና ልዩ ሦስትነት ለእኛ በሚረዳ ቋንቋ ገለጡት እንጂ አዲስ ትምህርት አላመጡም፡፡ ይልቁንም ነገረ ሥላሴን ሳይረዱ በሥላሴ መካከል የክብርና የተቀድሞ ልዩነት ያለ አስመስለው በክህደት ትምህርት የተነሱ መናፍቃንን ክህደት ለማስረዳት፣ የሐዋርያዊት ቤተክርስቲያንን የቀናች ሃይማኖት ለመግለጥ ምሥጢረ ሥላሴን አብራርተው አስተምረዋል፡፡

 

ምስጢረ ሥላሴ ማለት የአንድነት የሦስትነት ምስጢር ማለት ነው፡፡ ምሥጢር መባሉም በእምነት የተገለጠ፣ ያለ እምነትም የማይመረመር ስለሆነ ነው፡፡ ይኸውም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በስም፣ በአካል፣ በግብር ሦስት ሲሆኑ በባሕርይ በሕልውና፣ በመለኮት ደግሞ አንድ ናቸው፡፡ እንደዚህ ባለ ድንቅ ነገር አንድ ሲሆኑ ሦስት፣ ሦስት ሲሆኑ አንድ ይባላሉና፣ ይህም ልዩ ሦስትነት ረቂቅ እና በሰው አእምሮ የማይመረመር ስለሆነ ምስጢር ይባላል፡፡ ስለዚህም በአንድ አምላክ፣ በሦስቱ አካላት እናምናለን፡፡

 

የክርስትና ዶግማ (መሠረተ እምነት) በምስጢረ ሥላሴ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ምስጢረ ሥላሴ የእምነታችን ዋነኛው ምሰሶ ነው፡፡ በመዳን ትምህርት ውስጥ የመጀመሪያውን ደረጃ የሚይዘው ምስጢረ ሥላሴ ነው፡፡ ለመዳናችንም መሠረት ነው፡፡ ክርስቲያኖች ሁላችን የተጠመቅነው በሥላሴ (በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ) ስም ነው (ማቴ 28፡19)፡፡ የሥራችን ሁሉ መጀመሪያም አድርገን በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ስንልም በሥላሴ ማመናችንን እየመሰከርን ነው፡፡ በሥራችን መጨረሻም “ምስጋና ይሁን አንድ አምላክ ለሚሆን ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን” ብለን ሥራችንን በሥላሴ ስም ጀምረን በሥላሴ ስም እንፈጽማለን፡፡ሆኖም ግን ምስጢረ ሥላሴ ለሰው አእምሮ እጅግ የረቀቀ ስለሆነ የሰው አእምሮ ሊያውቅ የሚችለው እግዚአብሔር በገለጠለት መጠን ብቻ ነው፡፡

 

የአንድነት ምስጢር – አንድ አምላክ

ስለ ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት ስናነሳ ቀድመን የምንመለከተው ”አንድነትን” ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት ለአንድነታቸውና ለሦስትነታቸው መቀዳደም ኑሮበት ሳይሆን የቁጥር መሠረት አንድ ስለሆነ በዝያው ለመጀመር ነው /እንዘ አሐዱ ሠለስቱ ወእንዘ ሠለስቱ አሐዱ/፡፡ ሥላሴ ሦስት ናቸው ስንል እንደ አብርሃም፣ እንደ ይስሐቅ እንደ ያዕቆብ የተነጣጠለና በክብርም ሆነ በዘመን የሚበላለጥ የሚቀዳደም ማለታችን አይደለም፡፡ ሦስት ሲሆኑ አንድ ናቸው እንጂ፡፡ አንድ ናቸውም ስንል ከሰው ሁሉ ቀዳሚ ሆኖ እንደተፈጠረው እንደ አዳም ሦስትነትን የሚጠቀልል መቀላቀል ማለታችን አይደለም፡፡ አንድ ሲሆኑ ሦስት ናቸው እንጂ፡፡ /ቅዳሴ ማርያም/፡፡ ሥላሴ ቅድስት ተብሎ በሴት አንቀጽ መጠራታቸው ወላድያነ ዓለም (ዓለምን ያስገኙ) መሆናቸውን ለማጠየቅ ነው፤ እናት ለልጇ ስለምታዝንና ስለምትራራ ሥላሴም ለፍጥረታቸው ምሕረታቸው ዘለዓለማዊ ነውና ቅድስት ይባላሉ፡፡

 

ባህርይ ማለት ምንነትን የሚያሳይ ሲሆን የእግዚአብሔር ባህርይ የሚባሉትም የመለኮትነቱ ባህርያት ናቸው፡፡ አካል የምንለው ደግሞ ማንነትን የሚገልጽ ሲሆን ሦስቱ አካላት የምንላቸው የአምላክን ማንነት የሚገልጹ ናቸው፡፡ ባሕርይ ማለት “ብሕረ ተንጣለለ፥ ሰፋ፥ ዘረጋ” ከሚለው ግስ የወጣ ነው። በቲኦሎጂ /በነገረ መለኮት/ ቋንቋ ሲፈታም ባሕርይ ማለት ሥርው፥ ነቅዕ አዋሃጅ /የሚያዋሕድ/ አስተገባኢ ማለት ነው። ባሕርይ አካል ሥራውን የሚሠራበት መሣሪያ ነው። ባሕርይና አካል እንደ አጽቅና እንደ ሥር አንድ ናቸው፤ አይለያዩም፣ አንዱ ያለ አንዱ መኖር አይችልም። እግዚአብሔር በአንድነቱ የሚታወቅበት ስሞች ፈጣሪ፣ አምላክ፣ ጌታ፣ መለኮት፣ እግዚአብሔር፣ ጸባኦት፣ አዶናይ፣ ኤልሻዳይ የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ሥላሴ በባሕርይ ረቂቅ ናቸው፡፡ ርቀታቸውስ እንዴት ነው? ቢሉ ከፍጥረት ሁሉ ነፋስ ይረቃል፡፡ ከነፋስ የሰው ነፍስ ትረቃለች፡፡ ከነፍስ መላእክት ይረቃሉ፡፡ ከነፍሳትና ከመላእክት ደግሞ ኅሊናቸው ይረቃል፡፡ ይህ የኅሊናቸው ርቀት በሥላሴ ዘንድ እንደ አምባ እንደ ተራራ ነው፡፡ በዚህም ርቀታቸው በፍጥረት ሁሉ ምሉዓን፣ ኅዱራን ናቸው፡፡ ባሕርያቸውም የማይራብ፣ የማይጠማ፣ የማይደክም፣ የማይታመም፣ የማይሞት ሕያው ነው፡፡ «ስምከ ሕያው ዘኢይመውት ትጉህ ዘኢይዴቅስ ፈጣሪ ዘኢይደክም» እንዳለ /ቅዲስ ባስልዮስ በማክሰኞ ሊጦን/፡፡

 

እግዚአብሔር አንድ መለኮታዊ ባህርይ፣ ዘላለማዊ የሆነ አምላክ ነው፡፡ መለኮት ማለት “መለከ – ገዛ” ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሆኖ ”ግዛት” ማለት ነው። መለኮት (ወይም ማለኹት) በዕብራይስጥ ቋንቋ መንግሥት ማለት ነው፡፡ በግዕዝ ግን ባሕርይ፣ አገዛዝ፣ ሥልጣን ማለት ነው፡፡ እንግዲህ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በመለኮት ይህም ማለት በግዛት በመንግስት አንድ ናቸው።  አብ አልተፈጠረም፣ ወልድም አልተፈጠረም፣ መንፈስ ቅዱስም አልተፈጠረም፡፡ ሦስቱም አካላት ከዚህ ጀምሮ ነበሩ የማይባልላቸው ዘላለማዊ ናቸው፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የሚለው የተለያዩ ክፍሎች ስም አይደለም የአንድ አምላክ ስም እንጂ፡፡ ሦስቱ አካላት በህልውና ተገናዝበው ይኖራሉ እንጂ አይከፋፈሉም አይነጣጠሉም፡፡ እያንዳንዳቸው አካላት በመለኮታዊ ባህርይ አንድ ናቸው፡፡ ሐዋርያው ይህንን ሲያስረዳ ‹‹ከአንዱም በቀር ማንም አምላክ እንደሌለ እናውቃለን›› በማለት ገልጾታል (1ኛ ቆሮ 8፡4)። በአጠቃላይ ሥላሴ አንድ ሲሆኑ ሦስት፣ ሦስት ሲሆኑ አንድ ናቸው፡፡ አንድነቱ ሦስትነቱን ሳይጠቀልለው፣ ሦስትነቱ አንድነቱን ሳይከፋፍለው በሕልውና ተገናዝበው የሚኖሩ ናቸው፡፡ ሥላሴ በአካላት ሦስት ሲሆኑ በባሕርይ በመለኮት አንድ ናቸው፡፡ አንድ እግዚአብሔር፤ አንድ አምላክ ናቸው፡፡ ይህን ሲያስረዱ መጻሕፍት እንዲህ ይላሉ፤ እስራኤል ሆይ ስማ እግዚአብሔር አምላካችን አንድ እግዚአብሔር ነው፡፡ ዘጸ.6÷4 እግዚአብሔር አንድ ነው፡፡ ኤፌ. 4÷5 ሦስት ስም አንድ እግዚአብሔር ነው፡፡

 

ሥላሴ በሕልውና አንድ ናቸው፡፡ ሕልውና ማለት “ነዋሪነት፥ ኑሮ፥ አነዋወር” ማለት ነው። በነገረ መለኮት ቋንቋ አፈታት ግን አብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ኅልው ሆኖ፣ ወልድም በአብና በመንፈስ ቅዱስ ኅልው ሆኖ፣ መንፈስ ቅዱስም በአብና በወልድ ኀልው ሆኖ በመኖር አንድ ናቸው ማለት ነው። በሌላ አባባልም ህልውና ሦስትነታቸውን ሳይጠቀልለው፣ ሦስትነትም አንድነታቸውን ህልውናውን ሳይከፍለው አንዱ ከአንዱ ጋራ ተገናዝቦ ባንድነት መኖር ነው። ይህም በኲነት የበለጠ ይብራራል፡፡ የኩነት /የሁኔታ/ ሦስትነታቸውን በተመለከተም በህልውና /በአኗኗር/ እያገናዘቡ በአንድ መለኮት የነበሩ፣ ያሉ፣ የሚኖሩ ናቸው፡፡

 

የሦስትነት ምስጢር -ሦስት አካላት

ሥላሴ በግብር ሦስት ናቸው፡፡ የአብ ግብሩ መውለድ፣ ማስረጽ ሲሆን የወልድ ግብሩ መወለድ፣ የመንፈስ ቅዱስ ግብሩ መስረጽ ነው፡፡ አብ ወላዲ፣ ወልድ ተወላዲ፣ መንፈስ ቅዱስ ሠራፂ /የወጣ፣ የተገኘ/ ነው፡፡ አብ አባት ነው፣ ወልድ ልጅ ነው፣ መንፈስ ቅዱስ ከአብ ብቻ የሠረፀ ነው፡፡ /ዮሐ.14-26/፡፡ ሦስቱ አካላት አንድ መለኮት ናቸው፡፡ ሠለስቱ ስም አሐዱ እግዚአብሔር እንዳለ /አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው/፡፡ አብ ወልድን የወለደ መንፈስ ቅዱስን የሚያሰርጽ (አስገኛቸው) ነው፡፡ እንዲህ ቢሆንም ግን አይቀድማቸውም፤ አይበልጣቸውምም፡፡ መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው መጀመሪያውና መጨረሻው እርሱ የሆነ ዘላለማዊ ነው፡፡ አብ ይወልዳል እንጂ አይወለድም፣ ያሰርጻል እንጂ አይሰርጽም፡፡ አብም ‹‹ከእኛ በላይ ያለው አምላክ›› ተብሎ ይታወቃል፡፡ ወልድ የእግዚአብሔር (የአብ) ልጅ፣ ቃል ተብሎ ይጠራል፡፡  ሊቃውንትም ‹‹የአብ ክንዱ/እጁ›› ይሉታል፡፡ ቅድመ ዓለም ከአብ የተወለደ ነው፡፡ ተወለደ ሲባልም አብ ቀድሞት የነበረበት ጊዜ አለ ማለት አይደለም፡፡ ከእኛ ጋር ያለው አምላክ ይባላል፡፡ መወለዱም እንደሰው መወለድ ሳይሆን ‹‹ከብርሃን የተገኘ ብርሃን›› ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስም አምላክ ጌታ ነው፡፡ ሕይወትን የሚሰጥ አምላክ ነው፡፡ ከአብ የሠረፀ ከአብ ከወልድ ጋራ በአንድነት የምንሰግድለትና የምናመሰግነው አምላክ ነው፡፡ እርሱም በነቢያት አድሮ የተናገረ ነው። መንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ ይባላል፡፡ ሊቃውንት አባቶችም ‹‹የአብ ምክሩ›› ብለውታል፡፡ መንፈስ ቅዱስ የሚሰርጸውም ከአብ ብቻ ነው፡፡ የሚሰርጸውም ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው አይባልለትም፡፡ ከአብ ቢሰርጽም አብ ከእርሱ ቀድሞ የነበረበት ጊዜ የለም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ‹‹በውስጣችን ያለው አምላክ›› ይባላል፡፡

 

የአካል ሦስትነታቸውም ለአብ ፍጹም አካል፣ ፍጹም መልክ፣ ፍጹም ገጽ አለው፤ ለወልድም ፍጹም አካል፣ ፍጹም መልክ፣ ፍጹም ገጽ አለው፤ ለመንፈስ ቅዱስም ፍጹም አካል፣ ፍጹም መልክ፣ ፍጹም ገጽ አለው፡፡ነገር ግን አይከፋፈሉም፣ አይነጣጠሉም፣ ፍጹም አንድ ናቸው፡፡ አካል የተባለውም ምሉእ ቁመና ነው፤ ገጽ ከአንገት በላይ ያለው ፊት ነው፤ መልክዕ ልዩ ልዩ ሕዋሳት ዓይን ጆሮ፣ እጅ፣ እግር ከዚህም የቀሩት ሕዋሳት ሁሉ ናቸው፡፡ እንዲህ ሲባል ግን የሥላሴ አካል አንደ ሰው አካል ውሱን፣ ግዙፍ፣ ጠባብ አይደለም፡፡ ምሉዕ፣ ስፉሕ፣ ረቂቅ ነው እንጂ፡፡ ምሉዕነታቸውና ስፋታቸው እንዴት ነው? ቢሉ ከአርያም በላይ ቁመቱ፣ ከበርባኖስ በታች መሠረቱ፣ ከአድማስ እስከ አድማስ ስፋቱ ተብሎ አይነገርም፣ አይመረመርም፡፡ ምክንያቱም ሥላሴ ዓለሙን ይወስኑታል እንጂ ዓለሙ ሥላሴን አይወስናቸውምና፡፡

 

በኩነትም የአብ ከዊንነቱ ልብነት ነው፤ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ልባቸው እርሱ ነው፤ የወልድ ከዊንነቱ ቃልነት ነው፤ ለአብ ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው እርሱ ነው፤ የመንፈስ ቅዱስ ከዊንነቱ ሕይወትነት ነው፡፡ የአብ የወልድ ሕይወታቸው እርሱ ነው፡፡ ይህም በአብ መሠረትነት ለራሱ ለባዊ /አዋቂ/ ሆኖ ለወልድ፣ ለመንፈስ ቅዱስ ልብ፣ ዕውቀት መሆን ነው፡፡ ወልድ በአብ መሠረትነት ለራሱ ነባቢ /ቃል/ ሆኖ ለአብ፣ ለመንፈስ ቅዱስ ቃል መሆን ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስም በአብ መሠረትነት ለራሱ ሕያው ሆኖ ለአብ፣ ለወልድ ሕይወት መሆን ነው፡፡ ስለዚህ በአብ ልብነት ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ህልዋን ናቸው ያስቡበታል፤ በወልድ ቃልነት አብ፣ መንፈስ ቅዱስ ህልዋን ናቸው ይናገሩበታል፤ በመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስነት አብ፣ ወልድ ህልዋን ናቸው ሕያዋን ሆነው ይኖሩበታል፡፡

 

ሥላሴ (3ቱ አካላት) በአንድ ልብ በአብ ያውቃሉ፣ በአንድ ቃል በወልድ ይናገራሉ፣ በአንድ ሕይወት በመንፈስ ቅዱስ ሕያዋን ሁነው ይኖራሉ፡፡ ጌታችን ይህን ምስጢር “እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ”፤ ሲል ለሐዋርያት አስተምሯል (ዮሐ. 14፡11)፡፡ ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ እግዚአብሔርም ቃል ነበረ፤ ይህ አስቀድሞ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ሲል ገልጾልናል (ዮሐ. 1፡1-2)፡፡ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ ቃል በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ በማለቱ ወልድ በቃልነቱ በአብ ህልውና መኖሩን ያስረዳል፡፡ ይህ አስቀድሞ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ በማለቱ በመንፈስ ቅዱስ ህልው ሆኖ መኖሩን ያስረዳል፡፡ ዮሐንስ ከሦስቱ አካላት አንዱ ወልድ ቃልን በቃልነት በአብና በመንፈስ ቅዱስ አለ በማለቱ ሁለቱን አብ በልብነት በወልድ በመንፈስ ቅዱስ እንዳለ፤ መንፈስ ቅዱስ በሕይወትነት በአብና በወልድ እንዳለ ይታወቃል፡፡ እግዚአብሔር በሦስትነቱ የሚታወቅባቸው ስሞች ደግሞ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር በግብር ሦስትነቱ የሚታወቀው አብ ወላዲ፣ አሥራፂ በመባል፣ ወልድ ተወላዲ በመባል፣ መንፈስ ቅዱስ ሠራፂ በመባል ነው፡፡

 

የእግዚአብሔርን አንድነት የምናምነው በፈጣሪነት፣ በአምላክነት፣ በአገዛዝ፣ በፈቃድ፣ በሥልጣን እነዚህን በመሳሰሉት የመለኮት ባሕርያት ነው፡ ሦስትነቱን የምናምነው ደግሞ በስም፣ በግብር /በኩነት/ በአካል ነው፡፡ «እንዘ አሐዱ ሠለስቱ ወእንዘ ሠለስቱ አሐዱ፣ ይሤለሱ በአካላት ወይትዋሐዱ በመለኮት» እንዳለ /ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ/፡፡ ታላቁ ሐዋርያ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ 10-17 ላይ «እምነት ከመስማት ነው፣ መስማትም ከእግዚአብሔር ቃል ነው» ብሎ እንደተናገረው ከላይ የተጠቀሱትን መጠነኛ ማስረጃዎች በሙሉ ለመገንዘብ እንዲቻል የእግዚአብሔር እስትንፋስ የሆኑትን የቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃዎችን መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ሥላሴ የሚለው ስም እንዲያው የመጣ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በአንድነቱና በሦስትነቱ የሚጠራበት የከበረና ከስም ሁሉ በላይ የሆነ ስም ነው፡፡ ለዚህም የመጽሐፍ ቅዱስ /ዐሥራው ቅዱሳት መጻሕፍት/ ማስረጃዎችን በዝርዝር እንመለከታለን፡፡

 

ምስጢረ ሥላሴ በብሉይ ኪዳን

እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር፡ እግዚአብሔርም አለ፡- «ሰውን በመልካችን እንደምሳሌአችን እንፍጠር» ዘፍ.1-26 እዚህ ላይ «እግዚአብሔርም አለ» ሲል አንድነቱ፣ «እንፍጠር» ሲል ከአንድ በላይ መሆኑን ግሱ /ቃሉ/ ያመለክታል፡፡ በዚህ ንባብ እግዚአብሔር የሚለው ሥመ አምላክ ከአንድ በላይ የሆኑ አካላትን የሚመለከት መሆኑን ከተረዳን ስለ ሥላሴ ኃልወት በሌሎች የቅዱሳት መጻሕፍት  ከተጻፉት ምንባባት ጋር በማገናዘብ ይህ ጥቅስ ፍጹም አንድነቱንና ልዩ ሦስትነቱን እንደሚመሰክር በግልጽ መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህ አንቀጽ እንፍጠር በመልካችን እንደምሳሌያችን የሚለው ንግግር የሦስት ተነጋጋሪዎች ነው እንጂ ያንድ ተናጋሪ ቃል አይደለም፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር፤ ሰውን እንፍጠር በመልካችን እንደምሳሌያችን፤ ሲል ሦስትነቱን ማስተማሩ ነው፡፡ ሙሴም ይህን የእግዚአብሔርን ነገር ሲጽፍልን ሰውን እንፍጠር በመልካችን እንደ ምሳሌያችን ያለውን የብዙውን አነጋገር ለአንድ ሰጥቶ፤ እግዚአብሔር አለ፤ ብሎ መጻፉ በአካል ሦስት ሲሆን በባሕርይ በህልውና አንድ ስለሆነ በአንድ ቃል መናገሩን ከእግዚአብሔር ተረድቶ ለእኛ ሲያስረዳን ነው፡፡

 

እግዚአብሔርም ለሰው ልጅ ቃል ኪዳን ሲሰጥ፡ እግዚአብሔር አምላክ አለ፡- «እነሆ አዳም መልካሙንና ክፉውን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ» ዘፍ.3-22 በማለት ባለቤቱን አንቀጽን አንድ፣ አሳቡን ዝርዝሩን የብዙ አድርጐ ይናገራል፡፡ «እግዚአብሔር አለ» ሲል አንድነቱን፣ «ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ» ሲል ደግሞ ከአንድ በላይ መሆኑን ያመለክታል፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ በማለቱ ሦስትነቱን ያስረዳል፡፡ ምንአልባትም እግዚአብሔር አለ፤ አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፤ የሚለው ቃል ሦስት ተነጋጋሪዎች በአንድ ቦታ ቢኖሩ አንዱ ሁለቱን ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ ብሎ ሲነገር ከአንድ የበዙ ተናጋሪዎች ቃል መሆኑን ነው የሦስትነት ተነጋጋሪዎች መሆኑን ስለሚያስረዳ እግዚአብሔር ሦስት አካል መሆኑ በዚህ አነጋገር ግልጽ ነው፡፡

 

በባቢሎን ግንብ ወቅት፡ እግዚአብሔርም አለ፡- «ኑ እንውረድ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው፡፡» ዘፍ.11.6-8፡፡ «እግዚአብሔር አለ» ብሎ አንድነቱን፣ «ኑ እንውረድ» ብሎ ደግሞ ከአንድ በላይ መሆኑን ያመለክታል፡፡በዚህ አንቀጽ እግዚአብሔር ኑ እንውረድ ብሎ በመናገሩ ከሁለትነት የተለየ ሦስትነቱን ያስረዳል፡፡ መረጃውም ሦስት ተነጋጋሪዎች በአንድ ቦታ ሁነው ሲነጋገሩ ሦስተኛው ሁለቱን ኑ እንውረድ ሊላቸው ይችላል፤ ምክንያቱም ሁለት ሆነው ግን አንዱ ሁለተኛውን ና እንውረድ ቢለው እንጂ ኑ እንውረድ ሊለው ስለማይችል ነው፡፡ ከዚህ በላይ የተጠቀሱት የእግዚአብሔር ቃላት ተገልጸው ሲተረጐሙ፤ አካላዊ ልባቸው አብ አካላዊ ቃሉ ወልድንና አካላዊ ሕይወቱ (እስትንፋሱ) መንፈስ ቅዱስን፤ ሰውን እንፍጠር በመልካችን እንደ ምሳሌያችን፤ እነሆ አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፤ እንዲሁም ኑ እንውረድ፤ ብሎ እንዳነጋገራቸው ይታወቃል፡፡

 

ለአብርሃም በተገለጠለት ጊዜ፡ የአንድነቱና የሦስትነቱ ማስረጃ ሁነው የታመኑ እነዚህ ሦስቱ ቃላት ከአንድ የበዙ የሁለት ተነጋጋሪዎች፤ ከሁለትም የበዙ ተነጋጋሪዎች ቃላት መሆናቸው ይታወቃል እንጂ ከሦስት ያልበለጡ የሦስት ብቻ ተነጋጋሪዎች ቃላት እንደ ሆኑ ቃላቶቹ በማያሻማ ሁኔታ ስለማያስረዱ፤ እግዚአብሔር በእነዚህ አነጋገሮች ከሦስት ያልበዛ ሦስት አካላት ብቻ መሆኑ አይታወቅም የሚል አሳብም ቢነሳ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህም በሌላ አንቀጽ ይመልሳል፡፡ «በቀትርም ጊዜ እግዚአብሔር ለአብርሃም ተገለጠለት አብርሃም ሦስት ሰዎችን በፊቱ ቆመው አየ» ዘፍ.18.1-15 በማለት እግዚአብሔር አንድ መሆኑንና ሦስት አካል ያለው መሆኑን ወስኖ ያስረዳናል፡፡

 

የነቢያት ምስክርነት፡ እግዚአብሔር ለሙሴ በተገለጠለት ጊዜ «እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅም አምላክ፣ የያዕቆብም አምላክ እግዚአብሔር ነኝ» ዘጸ.3-6 ሲል «አምላክ፣ አምላክ፣ አምላክ» ብሎ ሦስትነቱን፣ «እኔ እግዚአብሔር ነኝ» ብሎ ደግሞ አንድነቱን ገልጾ ተናግሯል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊትም «የእግዚአብሔር ቸርነት ምድርን ሞላች፣ በእግዚአብሔርም ቃል ሰማዮች ጸኑ፣ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ» በማለት የሥላሴን ምስጢር ተናግሯል (መዝ.32-6)፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስም «ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በልዑል ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ አየሁት… ሱራፌልም ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያሉ ይጨሁ ነበር፡፡» ኢሳ.6.1-8 በማለት ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ብሎ ሦስትነቱን፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአበሔር ብሎ ደግሞ አንድነቱን አይቶ መስክሯል፡፡ እንዲሁም “የጌታንም ድምፅ ‘ማንን እልካለሁ? ማንስ ወደዚያ ሕዝብ ይሄድልናል’ ሲል ሰማሁ” (ኢሳ. 6፡8) በማለት ፍጹም አንድነቱንና ልዩ ሦስትነቱን አመልክቷል፡፡  የእግዚአብሔር ቀራቢዎች አገልጋዮች ሱራፌል በምስጋናቸው ሦስት ጊዜ ብቻ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ማለታቸው የሦስትነቱን አካላት መጥራታቸው ነው፤ እግዚአብሔር የሠራዊት ጌታ በማለት በአንድ ስም ጠርተው ምድር ሁሉ ምስጋናህን መልታለች በማለት ያንድ ተመስጋኝ ምስጋናን መስጠታቸው ሦስቱ አካላት አንድ ሕያው እግዚአብሔር፤ አንድ ገዥ፤አንድ አምላክ፤ አንድ ተመስጋኝ አምላክ መሆኑን መመስከራቸው ነው፡፡ ሱራፌልም በዚህ ምስጋናቸው እግዚአብሔር በአካል ከሦስትነት ያልበዛ ሦስት ብቻ እንደ ሆነ በባሕርይ በህልውና ከአንድነት ያልበዛ ሦስት አካል አንድ አምላክ ብቻ መሆኑን ይመሰክሩልናል፡፡

 

ምስጢረ ሥላሴ በሐዲስ ኪዳን

በሐዲስ ኪዳንም የእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት /ምስጢረ ሥላሴ/ በምስጢረ ሥጋዌ (በጌታችን በተዋህዶ ሰው መሆን) በሚገባ ታውቋል፡፡

 

በብስራት ጊዜ፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም እመቤታችንን ባበሠራት ጊዜ «መንፈስ ቅዱስ በአንች ላይ ይመጣለ፣ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንች የሚለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል፡፡» ብሎ የሥላሴን ሦስትነት በግልጽ ተናግሯል፡፡ሉቃ.1-35፡፡

 

በጥምቀት ጊዜ፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተለየ አካሉ /ሰው ሆኖ/ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ፣ አብ በደመና ሆኖ «የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚላችሁን ስሙት» ሲል፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በራሱ ላይ በርግብ አምሳል ሲወድቅበት ታይቶአል፡፡ /ማቴ.3.16-17፣ ማር.1.9-11፣ ሉቃ.3.21-22፣ ሉቃ.1.32-34/ በዚህም እግዚአብሔር በአካል ሦስት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

 

በደብረ ታቦር፡ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በገለፀበት በደብረ ታቦር ተራራም ምስጢረ ሥላሴ ተገልጿል፡፡ ወልድ በተለየ አካሉ ሥጋን ተዋህዶ በደብረ ታቦር ተገኝቶ፣ አብ በሰማያት ሆኖ ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ እርሱ ነው፤ እርሱን ስሙት›› የሚል ቃል ተናግሮ፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በደመና ጋርዷቸው ተለግጠዋል፡፡ ማቴ 17፡1-10

 

ሐዋርያዊ ተልዕኮ ሲሠጥ፡ እራሱ ባለቤቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የማዳን ሥራውን ፈጽሞ ከማረጉ በፊት ለደቀመዛሙርቱ ቋሚ ትዕዛዝ ሲሰጥ «እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀመዛሙርት አድርጓቸው» ብሏል ማቴ.28.19-20፡፡ በዚህም ‹‹ስም›› ብሎ አንድነታቸውን ‹‹አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ›› ብሎ ሦስትነታቸውን ገልጿል፡፡ ስለመንፈስ ቅዱስም ሲናገር «ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፡፡» በማለት አንድነትና ሦስትነቱን በግልፅ ተናግሯል (ዮሐ.15.26፣ 14.16-17፣ 25-26)፡፡

 

በሐዋርያት አንደበት፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ የሥላሴን ሦስትነት ገልጾ «የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእግዚአብሔርም ፍቅር፣ የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን» (2ኛ ቆሮ.13-14) በማለት ተናግሮአል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በጻፈው መልእክቱ በማያሻማ ሁኔታ «በሰማይ የሚመሰክሩ ሦስት ናቸው፡፡ እነርሱም አብ፣ ልጁም፣ መንፈስ ቅዱስም ናቸው፡፡ 1ኛ.ዮሐ.5-7፡፡ እነዚህ ሦስቱም አንድ ናቸው፡፡» በማለት የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት በግልጽ ያስረዳናል፡፡ ወንጌላዊው ቅድስ ዮሐንስም «በራእዩ እነሆም በጉ በጽዮን ተራራ ቆሞ ነበር፣ ከእርሱም ጋር ስሙና የአባቱም ስም የመንፈስ ቅዱስም ስም በግምባራቸው የተጻፈላቸው መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ» ራእ.14-1፡፡ በማለት በገጸ-ልቡናቸው ስመ ወላዲ፣ ስመ ተወላዲና ስመ ሠራፂ የተጻፈባቸውን የሥላሴን ልጆች አይቷል፡፡ በዚህም የሥላሴን ልዩ ሦስትነት በግልጽ መስክሯል፡፡ ከላይ በዝርዝር የተገለጹትና እነዚህን የመሳሰሉት ሁሉ እግዚአብሔር አንድነቱንና ሦስትነቱን የገለጸባቸው ምስክሮች ናቸው፡፡

 

የምስጢረ ሥላሴ አስረጂ ምሳሌዎች

ምስጢረ ሥላሴ በሊቃውንትም ትምህርት የአብ ወላዲነት፣ የወልድ ተወላዲነትና የመንፈስ ቅዱስ ሠራፂነት ነው፡፡ አብ ተወላዲ አይባልም፣ ወልድ ወላዲ አይባልም፡፡ ወላዲ፣ ተወላዲ፣ ሠራፂ የሚባሉት ቃላት ሦስት አካላት ለየብቻ የሚታወቁባቸው የግብር ስሞች ናቸው፡፡ ሊቃውንት አባቶቻችን በሃይማኖተ አበው ምሳሌ ሲመስሉ ምሳሌ ዘይሐጽጽ /ጎደሎ ምሳሌ/ በማለት አንዳንድ ምሳሌዎችን ያቀርባሉ፡፡ ምሳሌውንም ጎደሎ የሚሉበት ምክንያት ለምስጢረ ሥላሴ ሙሉ በሙሉ ምሳሌ የሚሆን ሲያጡ ነው፡፡ ይሁንና ምሳሌ ከሚመሰልለት ነገር እንደሚያንስ ቢታወቅም ለማስተማር ግን ይጠቅማልና ቤተክርስቲያን ነገረ ሃይማኖትን በምሳሌ ታስረዳለች፡፡ ይህንንም የሥላሴን ሦስትነትና አንድነት ሐዋርያት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በተማሩት መሠረት በሚከተሉት ሦስት ምስሌዎች በሚገባ ገልጸውታል፡፡

 

የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በሰው ምሳሌ ይገለጻል፡፡ ሰው በነፍሱ ሦስትነት አለው፡፡ የኸውም ልብነት፣ ቃልነት፣ ሕይወትነት ነው፡፡ ስለዚህ በሰው ነፍስ በልብነቷ አብ፣ በቃልነቷ ወልድ፣ በሕይወትነቷ መንፈስ ቅዱስ ይመስላሉ፡፡ የነፍስ ልብነቷ፣ ቃልነቷን፣ ሕይወትነቷን ከራሷ ታስገኛለችና፡፡ ቃልና ሕይወት ከአንዷ ልብ ስለተገኙ በከዊን /በመሆን/ ልዩ እንደሆኑ በመናገርም ይለያሉ፡፡ እንዲሁም አብ ወልድን በቃል አምሳል ወለደው፣ መንፈስ ቅዱስንም በእስትንፋስ አንጻር አሰረጸው፡፡ ነፋስ ስትገኝ በሦስትነቷ በአንድ ጊዜ ተገኘች አንዷ ልብነቷ ቀድሞ ቃልነቷና እስትንፋስነቷ በኋላ አልተገኙም፡፡ ሰው በዚህ አኳኋን በነፍሱ የሚመስለው ስለሆነ እግዚአብሔር «ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር» ዘፍ.1-26 ብሎ ተናገረ፡፡ ስለዚህ ነፍስ ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ /ሕይወት/ መሆን የከዊን /የመሆን/ ሦስትነትን ነገር በተናገረበት ድርሳን እንዲህ አለ፡፡ «አምላክ ውእቱ አብ፣ ወአምላክ ውእቱ ወልድ፣ ወአምላክ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ ወኢትበሀሉ ሠለስተ አማልእክተ አላ አሐዱ አምላክ ብሏል፡፡ ይህም ማለት አብ አምላክ ነው፣ ወልድም አምላክ ነው፣ መንፈስ ቅዱስም አምላክ ነው ነገር ግን ሦስት አማልክት አይባሉም፣ አንድ አምላክ እንጂ፡፡» ማለት ነው፡፡

 

የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በፀሐይ ይመሰላል፡፡ ፀሐይ አንድ ሲሆን ሦስትነት አለው፡፡ ይኼውም ክበቡ ብርሃኑ፣ ሙቀቱ ነው፡፡ በክበቡ አብ፣ በብርሃኑ ወልድ፣ በሙቀቱ መንፈስ ቅዱስ ይመሰላሉ፡፡ «አብ ፀሐይ፣ ወልድ ፀሐይ፣ መንፈስ ቅዱስ ፀሐይ አሐዱ ውእቱ ፀሐየ ጽድቅ ዘላዕለ ኩሉ» እንዳለ /ቅዱስ አባ ሕርያቆስ/፡፡ እነዚህ ሦስቱ በአንድ ላይ መኖራቸው አንድ ፀሐይ እንጂ ሦስት ፀሐዮች አያስብላትም፡፡ ከፀሐይ ክበብ ብርሃኗና ሙቀቷ ያለመቀዳደም እንደሚገኝ እንዲሁ ከአብ ወልድ ተወለደ፣ መንፈስ ቅዱስም ሰረጸ፤ ይህም ያለመቀዳደም ያለመበላለጥ ነው፡፡ ከፀሐይ ሦስት ኩነታት ብርሃኗ ብቻ ከዓይናችን ጋር እንደሚዋሀድ ከሥላሴም ብርሃን ዘበአማን (እውነተኛ ብርሃን) የተባለ ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ በተለየ አካሉ የሰውን ባህርይ ተዋህዷል፡፡

 

የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በእሳት ይመሰላል፡፡ እሳት አንድ ሲሆን ሦስትነት አለው፡፡ ይኼውም አካሉ፣ ብርሃኑ፣ ዋዕዩ /ሙቀቱ/ ነው፡፡ በአካሉ አብ፣ በብርሃኑ ወልድ፣ በዋዕዩ መንፈስ ቅዱስ ይመሰላሉ፡፡ «አብ እሳት ወልድ እሳት ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ እሳተ ሕይወት ዘእምአርያም፡፡» እንዳለ /አባ ሕርያቆስ/ «አምላክህ እግዚአብሔር የሚባላ እሳት ቀናተኛም አምላክ ነው፡፡» ዘዳ. 4-24፡፡ሥላሴ በፀሐይና በእሳት መመሰላቸውንም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ለሐዋርያት «እኔና አባቴ መንፈስ ቅዱስም እሳትና ነበልባል ፍሕምም ነን» በማለት አስተምሮአቸዋል፡፡ ሐዋርያትም ይህንን ጽፈውት ቀሌመንጦስ በተባለው መጽሐፍ ይገኛል፡፡ /ቅዳሴ ሠለስቱ ምእትን/ ይመልከቱ፡፡

 

የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በባህር ከዊን ይመሰላል፡፡ ባህር አንድ ባህር ሲሆን ሦስት ከዊን አለው፡፡ ይህም ስፍሐት (Sphere)፣ ርጥበት (Moisture) እና እንቅስቃሴ (Tide) ነው፡፡ በስፍሐቱ አብ፣ በርጥበቱ ወልድ፣ በእንቅስቃሴው መንፈስ ቅዱስ ይመሰላሉ፡፡ ሰው ከባህር ገብቶ ዋኝቶ ሲወጣ በአካሉ ላይ ርጥበት ይገኛል እንጂ ስፍሐትና እንቅስቀሴ አይገኝም፡፡ ወልድም በቃልነቱ ከዊን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ በተለየ አካሉ ሰው በሆነ ጊዜ በመለኮት አንድ ስለሆነ አብና መንፈስ ቅዱስ ሥጋ ለበሱ አያሰኝም፡፡ ሊቃውንትም ‹‹የሁሉ መገኛ አብን ነፋስ በሚያማታት ባህር ባለች ውኃ እንደመሰሉት እወቅ፡፡ በሁሉ ዘንድ የሚመሰገን ወልድንም በውኃ ርጥበት እንደመሰሉት በሁሉ ዘንድ የሚመሰገን መንፈስ ቅዱስንም በውኃ ባለ ባህር እንቅስቃሴ ይመሰላል›› በማለት አስረድተዋል፡፡

 

ነገር ግን እነዚህ ሁሉ አንድ ነፍስ፣ አንድ ፀሐይ፣ አንድ እሳት፣ አንድ ባህር እንጂ ሦስት ነፍስ፣ ሦስት እሳት፣ ሦስት ፀሐይ፣ ሦሰት ባህር አይባሉም፡፡ ሥላሴም በአካል፣ በስም፣ በግብር ሦስት ቢባሉ በባሕርይ፣ በሕልውና፣ በፈቃድ፣ በመለኮት አንድ ናቸው አንጂ አማልክት አይባሉም፡፡ የቂሣርያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ባስልዮስ «እንዘ አሐዱ ሠለስቱ ወእንዘ ሠለስቱ አሐዱ ይሤለሱ በአካላት ወይትዋሐዱ በመለኮት» እንዳለ፡፡ ይህም ማለት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ ሲሆኑ ሦስት ሦስት ሲሆኑ አንድ ናቸው፡፡ በአካል ሦስት ሲሆኑ በመለኮት አንድ ናቸው፡፡ ማለት ነው፡፡ ይህም ሰው በሚረዳው መጠን ለመግለጽ ያህል ነው እንጂ ከፍጥረት ወገን ለሥላሴ የሚሆን በቂ ምሳሌ የለም፡፡ የተመሰለ ቢመስል ሕጹጽ /ጎደሎ/ ምሳሌ ነው፡፡

 

ምስጢረ ሥላሴ ላይ የሚነሱ የስህተት ትምህርቶች

መለዋወጥ (Modalism): ይህ ስህተት የሰባልዮሳውያን ነው፡፡ ስህተቱም አንድ እግዚአብሔር አለ በማለት የአካል ሦስትነትን አይቀበልም፡፡ በዚያ ፈንታ አንዱ እግዚአብሔር ራሱን በተለያየ መንገድ ይገልጻል በማለት ይናገራል፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የሚባሉት አካላት ሳይሆኑ ራሱን የገለጠባቸው መንገዶች ናቸው ይላል፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር አንድ ጊዜ አብ፣ ሌላ ጊዜ ወልድ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ሆኖ ተገለጠ በማለት የሥላሴን ምስጢር አዛብቶ ያቀርባል፡፡ ምሳሌም ሲሰጥ ይህም ውኃ ፈሳሽ፣ በረዶ፣ እንፋሎት እንደሚሆነው ነው በማለት ያቀርባል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር በባህርይው አይለወጥምና (ሚል 3፡6) ይህ የተወገዘ የስህተት ትምህርት ነው፡፡

 

መነጣጠል (Tri-theism):ይህ ስህተት የሥላሴን አንድነት ካለመረዳት የሚመጣ ነው፡፡ አመለካከቱም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ሦስት አማልክት ናቸው ይላል፡፡ ልዩ በሆነ መንገድ የተጣመሩ አማልክት ናቸው በማለትም ኅብረት አላቸው ይላል፡፡ ይህ ስህተት ሦስት አካላት የሚለውን በትክክል ባለመረዳት አንዳንዶች ‹‹ክርስቲያኖች ሦስት አማልክት ያመልካሉ›› የሚሉት አይነት ስህተት ነው፡፡ ነገር ግን ሥላሴ የተለያዩ/የተነጣጠሉ/ አይደሉም፡፡ ሊቃውንት አባቶችም ‹‹አንድ አምላክ እንጂ ሦስት አማልክት አንልም›› ብለው በግልጽ መልስ ሰጥተውበታል፡፡

 

መከፋፈል (Partialism): ይህ ስህተት ደግሞ አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ አንድ ላይ ሲሆኑ አምላክ ይሆናሉ ይላል፡፡ ይህም ማለት እያንዳንዳቸው የአምላክ ክፍል ናቸው እንጂ ሙሉ አምላክ አይደሉም የሚል ትርጉም አለው፡፡ ሦስቱ በአንድ ላይ ሲሆኑ ብቻ ሙሉ አምላክ ይሆናሉ ማለትም እያንዳንዳቸው አካላት አምላክ ሳይሆኑ ‹‹የአምላክ ክፍል›› ናቸው የሚል ፍጹም የክህደት ትምህርት ነው፡፡ እኛ ግን ሥላሴ ግን አይከፋፈሉም እንላለን፡፡ቅዱስ አትናቴዎስ እንደተናገረውም ‹‹“አብ አምላክ ነው፣ ወልድም አምላክ ነው፤ መንፈስ ቅዱስም አምላክ ነው፡፡››

 

የአርዮስ ክህደት (Arianism): ይህ ደግሞ የወልድን ፍጹም አምላክነት የሚክድ ትምህርት ነው፡፡ ወልድ በአብ በልዕልና የተፈጠረ ነው ይላል፡፡ ፈጥሮ ፈጠረበት ይላል፡፡ አብ ወልድን ስለፈጠረው አብ ይቀድመዋል ይላል፡፡ስለዚህም ወልድ ያልነበረበት ጊዜ ነበር የሚል ክህደት ነው፡፡ ለዚህም ክህደቱ በምሳ 8፡22-25 ቆላ 1፡15 ዮሐ 14፡28 ያሉትን በተሳሳተ መንገድ በመተርጎም ተጠቅሞባቸዋል፡፡ የአርዮስ ክህደትም በኒቅያ ጉባዔ (በ325 ዓ.ም) የተወገዘ ትምህርት ነው፡፡ እኛም እንደ አባቶቻችን ‹‹ቃልም እግዚአብሔር ነበረ›› የሚለውን መሠረት አድርገን ‹‹የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ›› የሚለውን የኒቅያ ጉባዔ ድንጋጌ እንከተላለን፡፡

 

የመቅዶንዮስ ክህደት (Mecedonianism): የመቅዶንዮስ ክህደት ከአርዮስ ክህደት የቀጠለ ሲሆን የመንፈስ ቅዱስን ፍጹም አምላክነት የካደ ትምህርት ነው፡፡ ክህደቱም መንፈስ ቅዱስ ፍጡር (ሕፁፅ) ነው ይላል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ያንሳል ይላል፡፡ እኛ ግን በሦስቱ አካላት መበላለጥ የለም ብለን እናምናለን፡፡ የመቅዶንዮስ ትምህርት በቁስጥንጥንያ ጉባዔ (381 ዓ.ም) የተወገዘ ትምህርት ነው፡፡ የቀናችውን ሃይማኖት ያስተማሩ አባቶችም በዚህ ጉባዔ ‹‹በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን፤ እርሱ ጌታ ሕይወትን የሚሠጥ ከአብ የሰረፀ ከአብና ከወልድ ጋር እንሰግድለታለን፤ እናመሰግነለዋለን፤ እርሱም በነቢያት አድሮ የተናገረ ነው›› በማለት የመንፈስ ቅዱስን አምላክነት በተረዳ ነገር መስክረዋል፡፡

 

የሁለት ሥርፀት ትምህርት (Dual procession):ይህ የስህተት ትምህርት ቆይቶ በምዕራባውያኑ ዘንድ የተጨመረ ነው፡፡ እርሱም መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ይሰርፃል የሚል የስህተት ትምህርት ነው፡፡ የኒቅያ ጉባዔ ድንጋጌ ላይ ከጊዜ በኋላ የተጨመረ ነው፡፡ በጥንታዊያን አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ያልነበረ ምዕራባዊያኑ ያስገቡት ነው፡፡ መሠረታዊ ነገሩም ከምስጢረ ሥላሴ ጋር ይጣረሳል፡፡ ጌታችንም ያስተማረው መንፈስ ቅዱስ ከአብ እንደሚሰርፅ እንጂ ከአብና ከወልድ እንደሚሰርፅ አይደለም፡፡

 

ስለ ምሥጢረ ሥላሴ ከቀደሙ ሊቃውንት ምስክርነቶች ጥቂቶቹ

 

“እግዚአብሔር አንድ ነው፤ የማትከፈል የማትፋለስ መንግስትም አንዲት ናት፤ ከሥላሴ ምንም ምን ፍጡር ደኃራዊ የለም፤ በእነርሱ ዘንድ አንዱ ለአንዱ መገዛት የለም፡፡ አብ ከወልድ ተለይቶ የኖረበት ዘመን የለም፣ ወልድም ከመንፈስ ቅዱስ ተለይቶ የኖረበት ዘመን የለም፤ መንፈስ ቅዱስም ከአብ ከወልድ ተለይቶ የኖረበት ዘመን የለም፤ ሥሉስ ቅዱስ በዘመኑ በቀኑ ሁሉ በግብርም በስምም ሳይለወጥ ሳይፋለስ ጸንቶ ያለ ነው እንጂ፡፡” (ሃይማኖተ አበው ዘሠለስቱ ምዕት ምዕራፍ 19፡5-6)

 

“ወንድሞቻችን እኛስ እንዲህ እናምናለን፤ ያልተወለደ እግዚአብሔር አብ በተለየ አካሉ አንድ ነው፤ የተወለደ እግዚአብሔር ወልድ ዋሕድ ኢየሱስ ክርስቶስም በተለየ አካሉ አንድ ነው፤ በወደደው የሚያድር የአብ የወልድ እስትንፋስ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም በተለየ አካሉ አንድ ነው እንላለን፡፡…አብ አምላክ ነው፤ ወልድም አምላክ ነው፤ መንፈስ ቅዱስም አምላክ ነው፡፡ ግን ሦስት አማልክት አይባሉም አንድ አምላክ እንጂ፡፡” (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ምዕራፍ 25፡2-4)

 

“ከሦስቱ ፍጡር የለም ፍጡራን አይደሉምና፡፡ ከዕውቀት ከሃይማኖት የተለዩ መናፍቃን ከቅድስት ሥላሴ መለኮት መከፈልን በአካላት መጠቅለልን ሊያመጡ አይድፈሩ ሦስት አማልክት ብለን አንሰግድም አንድ አምላክ ብለን እንሰግዳለን እንጂ፡፡ በስም ሦስት ናቸው እንላለን፤ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ ባህርይ አንድ ሥልጣን ናቸው፤ በአንድ መለኮት በባህርይ አንድነት የጸኑ ሦስት አካላት ሲሆኑ ከሦስቱ አንዱ የሚበልጥ አንዱ የሚያንስ አይደለም፤ በማይመረመር በአንድ ክብር የተካከሉ ናቸው እንጂ፡፡” (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ ምዕራፍ 60፡6-7)

 

“ወልድ ሳይኖር አብ ከአዝማን በዘመን ፈጽሞ አልነበረም፤ ወልድም ከመንፈስ ቅዱስ ተለይቶ በዘመን አልነበረም፤ ሳይለወጡ ሳይለዋወጡ በገጽ በመልክ ፍጹማን በሚሆኑ በሦስት አካላት ጥንት ሳይኖራቸው በዘመን ሁሉ የነበሩ፤ ፍጻሜ ሳይኖራቸው የሚኖሩ ናቸው እንጂ፡፡” (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ቴዎፍሎስ ምዕራፍ 68፡5)

 

“አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በአካል ሦስት በባህርይ አንድ ነው ብሎ ማመን ይህ ነው፤ የማይመረመር በቅድምና የነበረ አብ በገጹ በአካሉ ፍጹም ነው፤…የማይመረመር በቅድምና ነበረ ወልድም በገጹ በአካሉ ፍጹም ነው፤….የማይመረመር በቅድምና የነበረ መንፈስ ቅዱስም በገጹ በአካሉ ፍጹም ነው፤ ሐዋርያት ያስተማሩዋት ቅድስት ቤተክርስቲያን የተቀበለቻቸው ቅዱሳት መጻሕፍት እንደተናገሩ፡፡” (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ቄርሎስ ምዕራፍ 70፡14-17)

 

“እኛ ግን በሥላሴ ዘንድ በማዕረግ ማነሥና መብለጥ የለም በመለኮት አንድ ወገን ናቸው እንላለን” (አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ተግሳጽ ዘሰባልዮስ

 

ማጠቃለያ

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምስጢረ ሥላሴን በተረዳ ነገር ‹‹ሥላሴ አንድ ሲሆኑ ሦስት፣ ሦስት ሲሆኑ አንድ ናቸው፡፡ አንድነቱ ሦስትነቱን ሳይጠቀልለው፣ ሦስትነቱ አንድነቱን ሳይከፋፍለው በሕልውና ተገናዝበው የሚኖሩ ናቸው፡፡›› ብላ ታምናለች፤ ታስተምራለችም፡፡ ይህም እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ራሱን የገለጠበት፣ ነቢያት የመሰከሩት፣ ወልደ እግዚአብሔር በተለየ አካሉ ሰው ሆኖ ያስተማረው፣ ሐዋርያትም በዓለም ዞረው የሰበኩት ምስጢር ነው፡፡ ስለዚህ እኛም እንደ አባቶቻችን  “ምንም እንኳን ሥላሴን በስም፣ በአካል በግብር ሦስት ናቸው ብንልም ሦስቱ በባህርይ፣ በመለኮት፣ በህልውና፣ በፈቃድ አንድ ናቸው፡፡ አንድ አምላክ እንጂ ሦስት አማልክት አንልም፡፡ አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ አላቸው፡፡ ነገር ግን በህልውና አንድ ናቸው፡፡” ብለን እናምናለን፤ እንታመናለን፡፡

 

ስብሃት ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፡፡ አሜን፡፡

ምንጭ ;- https://astemhro.com/2018/10/18/trinity/

 

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top