ጋብቻ በቤተክርስቲያን

ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፥(ኤፌ5:32)

ምስጢረ ተክሊል

ተክሊል የሚለው ቃል ከለለ ከሚለው ግስ የወጣ ሲሆን ትርጉሙም አከበረ ለየ ቀደሰ ለትልቅ ዓላማ ክብር አበቃ ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ተክሊል ማለት ክብር ማለት ነው፡፡ በእግዚአብሔር የሚያምኑ ወንድና ሴት በካህናት ሥርዓተ ጸሎት ሁለቱ አንድ የሚሆኑበት ምስጢር፣ በሚታይ አገልግሎት የማይታይ ጸጋ የሚቀበሉበት ምስጢር ነው፡፡
“ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፣ ይህ ምስጢር ታላቅ ነው፣ እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለቤተከርስቲያን እላለሁ” (ኤፌ 5÷31-32)

ምስጢረ ተክሊል የተጀመረው በመጀመሪያዎቹ ሰዎች በአዳምና በሔዋን ሲሆን ጋብቻውን የባረከውና የቀደሰው እግዚአብሔር ነው፡፡ ዘፍ 2÷18 “እግዚአብሔርም አለ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም
አይደለምና የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት” ዘፍ 2÷21-24 “እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ከባድ እንቅልፍ ጣለበት
አንቀላፋም ከጎኑ አንዲት አጥንት ወሰደ ሥፍራውን በስጋ ዘጋው እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ
ሠራት ወደ አዳምም አመጣት፡፡ አዳምም አለ ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት ሥጋም ከሥጋዬ ናት እርሷ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት
ትባል ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፡፡” በሐዲስ ኪዳንም አምላካችን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃና ዘገሊላ በሠርግ ቤት ተገኝቶ ጋብቻን በመባረክ የመጀመሪያውን ተአምር አድርጓል (ዮሐ 2÷1-11)

ይህ ያደረገበትም ምክንያት ከመልካም ምንጭ ንጹህ ውሃ እንዲቀዳ ከመልካም ቤተሰብም ለሀገርና ለወገን ብሎም ለቤተክርስቲያን የሚጠቅም መልካም ዜጋ ይገኛልና፣ ይህም የሚሆነው ከቅዱስ ጋብቻ ከመልካም ጋብቻ በመሆኑ እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮም ሆነ በሐዲስ ተፈጥሮ ጋብቻን ባርኮና ቀድሶ ለሰው ልጆች ሰጥቷል፣ ማቴ 19÷4-6″ ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው ስለዚህም ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደፊት ሁለት አይደሉም፡፡ እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው” በሌላው ጋብቻ ክቡር እንደሆነ በምሳሌ አስተምሯል ማቴ 25÷1″ በዚያን ጊዜ መንግስተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ አስር ቆነጃጅትን ትመስላለች”

የጋብቻ ዓላማ ምንድን ነው?

ጋብቻ ክቡርና ቅዱስ ከመሆኑም ባሻገር ለሀገርና ለወገን የሚጠቅሙ ለቤተክርስቲያን የሚበጁ ለትውልድ አለኝታና ተስፋ የሚሆኑ መልካም ፍሬዎችን መሪዎችን ካህናትን ነገስታትን ቅዱሳንን ማፍራትና ማግኘት የሚቻለው በቅዱስ ጋብቻ ስለሆነ እግዚአብሔርን የሚያምኑት በመልካም ሥራ በጥንቃቄ እንዲድኑ ይህን አስረግጦ መናገር ያሻል፡፡ (ቲቶ 3÷8) “እግዚአብሔርን የሚያምኑት በመልካም ሥራ በጥንቃቄ እንዲድኑ እነዚህን አስረግጠህ እንድትናገር እፈቅዳለሁ”

፩ኛ-መረዳዳት መፈቃቀር መተሳሰብ ነው፡፡

ጋብቻ ፍቅር ነው በመሆኑም በፍቅር ጸብ የለም ክርክር የለም፣ ራስ ወዳድነት የለም፡፡ ጋብቻ አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ በመባባል በትዕግስትና በይቅርታ በተሞላ ልብ የሚኖሩት ሕይወት ነው፡፡

(ዘፍ 2÷18) “እግዚአብሔር አምላክም አለ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት” ጋብቻ ከብቸኝነት ሕይወት ነፃ ሆኖ ከሚመች ረዳት ጋር አብሮ መኖር ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ወይም እግዚአብሔርን ይዘው ስለ እግዚአብሔር በብቸኝነት አይኖሩ ወይም የሚመቻቸውን ረዳት ፈልገው በጋብቻ ተወስነው አይኖሩ ዝም ብለው በንዝላልነት ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ፡፡ (መክ 4÷7-12)

“እኔም ተመለሰህ ከፀሐይ በታችም ከንቱን ነገር አየሁ አንድ ሰው ብቻውን አለ ሁለተኛም የለውም ልጅም ሆነ ወንድም የለውም ለድካሙ ግን መጨረሻ የለውም ዓይኖቹም ከባለጠግነት አይጠግቡም፡፡
ለማን እደክማለሁ ሰውነቴንስ መልካሙን ነገር ለምን እነፍጋታለሁ? ይላል፡፡ ይህ ደግሞ ከንቱ ነገር ክፉም ጥረት ነው፣ ድካማቸው
መልካም ዋጋ አለውና አንድ ብቻ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻል፣ በወደቁ አንዱ ሁለተኛውን ያነሳዋልና አንድ ብቻውን ሆኖ በወደቀ
ጊዜ ግን የሚያነሳው ሁለተኛው የለውምና ወዮለት ሁለቱም በአንድነት ቢተኙ ይሞቃቸዋል አንድ ብቻውን ግን እንዴት ይሞቀዋል፡፡
አንዱም አንዱን ቢያሸንፍ ሁለቱም በፊቱ ይቆማሉ፤ በሶስትም የተገመደ ገመድ ፈጥኖ አይበጠስም” ጋብቻ (ትዳር) ማትረፊያ መክሊት ነው በረከት ነው፡፡ “ሚስት ያገኘ በረከትን አገኘ ከእግዚአብሔርም ሞገስን ይቀበላል” (ምሳ 18÷22)

“ቤትና ባለጠግነት ከአባቶች ዘንድ ይወረሳሉ አስተዋይ ሚስት ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ናት” (ምሳ 19÷4) እንግዲህ በቀድሞ ዘመን በእግዚአብሔር ተስፋ ያደረጉት ቅዱሳን ሴቶች ደግሞ ለባሎቻቸው ሲገዙ ተሸልመው ነበርና እንዲሁም ሣራ ለአብርሃም ጌታዬ ብላ እየጠራችው ታዘዘችለት እናንተም ከሚያስደነግጥ ነገር አንዳች እንኳ ሳትፈሩ መልካም ብታደርጉ ልጆችዋ ናችሁ” (1ጴጥ 3÷5-6)በጋብቻ ውስጥ ሚስት ለባል በፍቅር መገዛት ማገልገል ይኖርባታል ባልም ለሚስት በፍቅርና በትሕትና ያገለግል ዘንድ ይገባል፡፡ “እንዲሁም እናንተ ባሎች ሆይ ደካማ ፍጥረት ስለሆኑ ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ፣ ጸሎታችሁ እንዳይከለከል አብረው ደግሞ የሕይወትን ፀጋ እንዲወርሱ አድርጋችሁ አክብሯቸው” (1ጴጥ 3÷7)

 

ቅዱስ ጴጥሮስ ሴቶችን ደካማ ፍጥረት ይላቸዋል ምክንያቱም በምቾት ደካሞች በመሆናቸው (ምኞታቸውን መጠበቅ ስለሚፈልጉ)፣ ለደስታም ለሐዘንም፣ ለክፉም ለበጎም ፈጣኖች በመሆናቸው እንዲሁም በደም ሥር ብዛት ከወንዶች በግማሽ ስለሚያንሱ የወንዶች የደም ሥር ብዛት (666)  ’‘Chromosome’ የሴቶች የደም ሥር ብዛት (333) በመሆኑ ደካማ ፍጥረት
ናቸው፡፡(2ኛጢሞ 2÷14) የተታለለም አዳም አይደለም ሴቲቱ ግን ተታላ በመተላለፍ ወደቀች ነገር ግን በእምነትና በፍቅር በቅድስናም ራሳቸውን እየገዙ ቢኖሩ በመውለድ ትድናለች” (2ጢሞ 3÷5-7) “ኃይሉን ግን ክደዋል ከእነዚህ ደግሞ ራቅ ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ ኃጢዓታቸው የተከመረባቸውን በልዩ ልዩ ምኞትም የሚወሰዱትን ሁል ጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች ይማርካሉ” ኤፌ 5÷21 “ለእያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ ሚስቶች
ሆይ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ ክርስቶስ ደግሞ የቤተክርስቲያን ራስ እንደሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደሆነ ባል
የሚስት ራስ ነውና” ለእግዚአብሔር በፍቅር በፍርሃት እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ ባል የሚስት ራስ ነውና፣

“ዳሩ ግን ቤተክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ እንዲሁ ሚስቶች ደግሞ በሁሉ ለባሎቻቸው ይገዙ” (ኤፌ 5÷24) መገዛት ሲል በትህትና በፍቅር በርህራሄ በክርስቶስ ፍርሃት አክሊልን ክብርን እናገኛለን በማለት ነው፡፡
“እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባል፣ የገዛ ሚቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና ነገር ግን የአካሉን ብልቶች ስለሆን ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገለት ይመግበዋል ይንከባከበዋልም” ባሎች እንደራሳቸው አድርገው የሚገባቸውን እያደረጉላቸው እያፈቀሩዋቸው እየተንከባከቡዋቸው አብረው ይኑሩ፡፡
(ማቴ 7÷12) ለአንተ ሊደረግብህ የማትፈልገውን በሌላው አታድርግ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው ህግም ነቢያትም ይህ ነውና” “ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ስጋ ይሆናሉ፣ ይህ ምስጢር ታላቅ ነው” (ኤፌ 5÷31) ይህም ማለት አገር ቀይረው እርስ በእርስ ተከታትለው ቆላ ወይም ደጋ ይጓዛሉ፡፡ በሌላው ፈቃዱን ከእርሷ ውጪ ከእናት ወይም ከእህት አይልም እርሷም ፈቃዷን ከባሏ ውጪ አይሆንላትም በሌላው ርስት መንግስተ ሰማያትን ለመውረስ በአንድ ሆነው በፍቅር እንደሚኖሩ ለማጠየቅ ነው፡፡
“ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፣” ሙሽራው የመለኮት  ሙሽሪት የትስብዕት (ሥጋ) ምሳሌ ሲሆን ከተዋህዶ በኋላ ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባህሪ እንደሆነ ሁሉ ሙሽራውና ሙሽሪት በጸሎተ ተክሊል በቅዱስ ጋብቻ ከተዋሃዱ በኋላ አንድ ሥጋ ይሆናሉ እንጂ ሁለት አይባሉም በጋብቻ ውስጥ በትዳር ውስጥ መከባበር መቻቻል ግድ ይላል ትዳር አስተዋይነትን አርቆ አሳቢነትን ይጠይቃል፡፡ ከምንም በላይ “ይህ ሚስጢር ታላቅ ነው” እንዲል ቅዱስ መጽሐፍ በእግዚአብሔር ፊት የገቡትን ቃል ኪዳን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ “በዝናብ ቀን የሚያንጠባጥብ ቤትና ጠበኛ ሴት አንድ ናቸው እርሷንም መከልከል ነፍስን መከልከልና ዘይትን በቀኝ እጅ መጨበጥ ነው” (ምሳ 27÷15) “ውበት ሐሰት ነው ደም ግባት ከንቱ ነው እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርሷ ትመሰገናለች” (ምሳ 31÷30)

፪ኛ. ዘር መተካት (ፍሬን ማፍራት ነው)

 ከጋብቻ ዓላማዎች መካከል አንዱ እግዚአብሔር አምላክ በሰጠን ጊዜ ፍሬን ለማፍራት ዓይንን በዓይን ለማየት ትውልድ ለመተካት ነው፡፡ ዘፍ 1÷28 “እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው እግዚአብሔርም ባረካቸው እንዲህም አላቸው ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት ግዙዓትም” የኖህንና የልጆቹንም ጋብቻ ከባረከ በኋላ ፍሬን እንዲያፈሩ ዘር እንዲተኩ አዝዟቸዋል፡፡ “እግዚአብሔርም ኖህንና ልጆቹን ባረካቸው እንዲህም አላቸው ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት” “እግዚአብሔር የሕይወትን መንፈስ አንድ አድርጎ ጠብቆልን የለምን? እርሱም የሚፈልገው ምንድር ነው? ዘር አይደለምን? ስለዚህ መንፈሳችሁን ጠብቁ ማንም የልጅነት ሚስቱን አያታልል መፉታትን እጠላለሁ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር (ሚል 2÷15) :(ፍትሐ-ነገስ 24-927) “ዘር መተካትን የማይፈልግ ከሆነ ሚስት ማግባትን መተው
ይገባዋል” ትዳርን የሚባረክ ማህፀንን የሚከፍት ፍሬን የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው፡፡ ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ጸንሶ መውለድም ሆነ ዘር መተካት አይቻልም “ያለ እኔ ምንም ማድረግ አትችሉም” (ዮሐ 15÷5) “እነሆ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው የሆድም ፍሬ የእርሱ ዋጋ ነው” መዝ 126÷3 አንዳንድ ሰዎች ዘር ላለመተካት ልጅ ላለመውለድ የሚፈልጉ የተለያዩ ነገሮችን በመጠቀም የሚከላከሉ ይኖራሉ ዘፍ 38÷8-10 “ወደ ወንድምህ ሚስት ግባ አግባትም ለወንድምህም ዘርን አቁምለት አለው አውናንም ዘሩ ለእርሱ እንዳይሆን አወቀ ወደ ወንድሙ ሚስት በገባ ጊዜ ለወንድሙ ዘር እንዳይሰጥ ዘሩን በምድር ያፈሰው ነበር ይህም ሥራው በእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ ሆነ እግዚአብሔርም ቀሰፈው፡፡” ;”ከሠሪው ጋር ለሚታገል ወዮውለት በምድር ሸክላዎች መካከል
ያለ ሸክላ ነው ጭቃ ሰሪውን ምን ትሠራለህ ወይስ ስራህ እጅ የለውም ይላልን? አባትን ምን ወልደሃል፣ ወይም ሴትን ምን አማጥሽ
ለሚል ወዮለት” (ኢሳ 45÷9)

አንዳንዶች ልጅ ላለመውለድ ዘር ላለመተካት በማህፀን ያለ ጽንስ የሚያስወርዱ ነፍስን የሚያጠፉ ሴቶች ወይም አጥፍተው የሚያጠፉ በነፍስ መግደል የሚተባበሩ ወንዶች ይኖራሉ፡፡ ይህ የዲያብሎስ ሥራ ነው፡፡ “ዲያብሎ ከመጀመሪያው ነፍሰገዳይ ነው” ዮሐ 8÷44 “የአምስተኛው ሰው ካዕድያዕ ይባላል ግዙፉንና ረቂቃኑን አጋንንት ያመጡትን ክፉ መቀራደድን ሁሉ ለው ልጆች ያስተማረ እሱ ነው፣ በእናቱ ማህጸን ያለ ጽንስ ወጥቶ ይወድቅ ዘንድ ፅንስ ማስወረድን ነፍስ መግደልን አስተማረ” (ሄኖ 19÷23)
ከትዕዛዛት መካከል አንዱ አትግደል ነው፡፡ የሚለው (ዘጸ 20÷13) ምናልባት አንዳንዶች በማህፀን ያለ ያልተወለደ ከሰው አይቆጠርም አይታወቅም፣ ወይም አንዳንዶች ዘመናዊነት የተጠናወታቸው እንደሚሉት ጽንሱ ከተጸነሰ እስከተወሰኑ ወራት ሙሉ ሰው ስለማይሆን ማስወጣት ይቻላል የሚሉ ይኖራሉ፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ለነርሱም እንዲህ ይላቸዋል
“የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ በሆድ ሳልሰራህ አውቄሃለሁ ከማህጸንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ” (ኤር 1÷4-5)
“አቤቱ አንተ ኩላሊቴን ፈጥረሃልና በእናቴም ሆድ ሰውረኸኛል ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፣ ሥራህ ድንቅ ነው ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች፡፡ እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ አካሌም በምድር ታች በተሠራ ጊዜ አጥንቶቼ ከአንተ አልተሰወሩም ያልተሰራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድስኳ ሳይኖር በመጽሐፍ ተፃፈ፡፡” (መዝ 138÷13-16)
በመሆኑም ፅንስ ማስወረድ ነፍስ መግደል ኃጢዓት ነውና እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ “የሰውን ደም የሚያፈስ ሁሉ ደሙ ይፈሳል ሰውን በእግዚአብሔር መልክ ፈጥሮታልና፣ እናንተም ብዙ ተባዙ በምድር ላይ ተዋለዱ እርቡበትም”
(ዘፍ 9÷6) አውቀውም ሆነ ሳያውቁ በዚህ በደል ውስጥ ላለፉ አሁንም ይህ ክፉ የኃጢዓት ሃሳብ በልቡናቸው ያለ እግዚአብሔር
እንዲህ ይላል፡- “እጆቻችሁ ደም ተሞልተዋል ታጠቡ ሰውነታችሁንም አንጹ የሥራችሁንም ክፋት ከዓይኔ ፊት አስወግዱ ክፉ መሥራትን ተው መልካም ማድረግን ተማሩ” (ኢሳ 1÷16)

፫ኛ ከፍትወት ጾር ወይም ከዝሙት ለመጠበቅ

በክርስትና ከጋብቻ በፊትም ሆነ በኋላ ያልተፈቀደ ግብረ ሥጋ ግንኙነት ሁሉ ዝሙትና ርኩሰት ነው፡፡
“ሥጋ ግን ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም ሥጋችሁ የክርስቶስ ብልቶች እንደሆነ አታውቁምን? እንግዲህ የክርስቶስን ብልቶች ወስጄ የጋለሞታ ብልቶች ላድርጋቸውን? አይገባም፡፡ ወይስ ከጋለሞታ ጋር የሚተባበር አንድ ሥጋ እንዲሆን አታውቁምን? ሁለቱ አንድ ሥጋ ይሆናሉ ተብሏልና፡፡ ከጌታ ጋር የሚተባበር ግን አንድ መንፈስ ነው፡፡ ከዝሙት ሽሹ፡፡ ሰው የሚያደርገው ኃጢዓት ሁሉ ከሥጋ ውጪ ነው ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢዓትን ይሠራል” (1ኛቆሮ 6÷13-18) ሐዋርያው ይህንን መልዕክት
ያስተላለፈበት ምክንያት ያልተፈቀደላቸውን የማይጠቅማቸውን ጸያፍ የሆነውንና ርኩሰትን ዝሙትን የሚሠሩ እንደነበረ ስላረጋገጠ
ነው፡፡ “በአጭር ቃል በእናንተ መካከል ዝሙት እንዳለ ይወራል የዚያን ዓይነት ዝሙት በአሕዛብስ እንኳ የማይገኝ ነው የአባቱን ሚስት የአገባ ሰው ይኖራልና፡፡ እናንተም ታብያችኋል ይልቅስ እንድታዝኑ አይገባምን? ይህን ሥራ የሠራው ከመካከላችሁ ይወገድ” (1ቆሮ 5÷1-2)
“ሁሉ ተፈቅዶልናል ሁሉ ግን አይጠቅመንም፣ ሁሉ ተፈቅዶልኛል በእኔ ላይ ግን አንድ ነገር እንኳ አይሰለጥንብኝም” (1ቆሮ 6÷12) ዝሙት እንደ ሱስ የተጠናወታቸው ከዚህም ከዚያም መድረስ የሚፈልጉ አሉና፣ ይህ አይጠቅምም፡፡ “ስለ ጻፋችሁልኝስ ነገር ከሴት ጋር አለመገናኘት ለሰው መልካም ነው ነገር ግን ስለዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ለራሱ ሚስት ትኑረው ለእያንዳንዲቱም ደግሞ ባል ይኑራት፡፡ (1ቆሮ7÷1-3)
ለሰው ልጆች እንዲመሩባቸው ከተሰጣቸው ትዕዛዛት መካከል አንዱ አታመንዝር ነው የሚለው (ዘዳ 20÷14) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ስብከቱ ይህንኑ አጽንቶ አስተምሯል፡፡ “አታመንዝር እንደተባለ ሰምታችኋል እኔ ግን እላችኋለሁ ወደ ሴት ያየ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርሷ ጋር አመንዝሯል” (ማቴ 5÷22)
(1ኛቆሮ 7÷8-9) “ላላገቡና ለመበለቶች ግን እላለሁ እንደ እኔ ቢኖሩ ለእነርሱ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን በምኞት ከመቃጠል መጋባት ይሻላልና ራሳቸውን መግዛት ባይችሉ ያግቡ”
“ዳሩ ግን ማግባት ወደሚገባው ዕድሜ በደረሠ ጊዜ ስለድንግልናው ያፈረ ሰው ቢኖር የወደደውን ያድርግ ኃጢዓት የለበትም ይጋቡ”
(1ቆሮ 7÷36) “ከሴት ጋር የሚያመነዝር ግን አዕምሮው የጎደለ ነው እንዲሁም የሚያደርግ ነፍሱን ያጠፋል” (ምሳ 6÷32)
“በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም ስለዚህ በስጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ” (1ቆሮ 6÷20) የሚያስተውል ሰው አዕምሮውን የሚያሠራ ሰው አያመነዝርም የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሆነውን መቅደስ ሰውነቱን በዝሙት አያረክስም”
(ዘፍ 39÷6) “መልከመልካምና ውብ ነበረ የጌታው ሚስት በዮሴፍ ላይ ዓይንዋን ጣለች ከእኔም ጋር ተኛ አለችው እርሱም እምቢ አለ ለጌታውም ሚስት እንዲህ አላት እነሆ ጌታዬ በቤቱ ያለውን ምንም ምን የሚያውቀው የለም ያለውንም ሁሉ ለእኔ አስረክቦኛል ለዚህ ቤት ከእኔ የሚበልጥ ሰው የለም፤ ሚስቱም ስለሆንሽ ካንቺ በቀር ያልሰጠኝ ነገር የለም” ዮሴፍ አዕምሮውን ገዛ ሕግ ባልተሰጠበት ዘመን በእግዚአብሔር ፊት ክፉን አልሰራም ኃጢአትን አላደርግም አላመነዝርም ነበር ያለው፡፡
(መሳ 19÷1-2) “በዚያን ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉስ በሌለበት ጊዜ በተራራማው በኤፍሬም ሀገር ማዶ የተቀመጠ ሌዋዊ ነበረ ከቤተልሔም ይሁዳ ምስት አገባ ሚስቱም አመነዘረችበት ትታውም ወደ ቤተልሔም ይሁዳ ሄደች በዚያም አራት ወር ተቀመጠች”
“እርሱ ግን ለጸሎት ካልሆነ አይለያዩም ተብሏልና ሊፈልጋት ሄደ አገኛትም ሲመለሱ ወደ ተራራማው ሃገር ከመድረሳቸው በፊት መሸባቸውና በብንያማውያን ሀገር በነብዓም ገብተው አረፉ፤ “የሀገሩ ሰዎች ግን ምናምንቴዎች ነበሩና በዚህ ቤት የገባውን
ሰው አውጣልንና እንገናኘው አሉ”( መሳ 19÷22-23) አመንዝራነት በተለይም ግብረሰዶማዊነት የአሕዛብ ሥራ ነው፡፡

“እንግዲህ ለሕዛብ ደግሞ በአዕምሯቸው ከንቱነት እንደሚመላለሱ ከእንግዲህ ወዲህ እንዳትመላለሱ እላለሁ በጌታም ሆኜ እመሰክራለሁ እነርሱ ባለማወቃቸው ጠንቅ በልባቸው ደንዳናነት ጠንቅ ልቡናቸው ጨለመ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ራቁ ደንዝዘውም በመመኘት ርኩሰትን ሁሉ በማድረግ ራሳቸውን ወደ ሴሰኝነት አሳልፈው ሰጡ” (ኤፌ 4÷17)
(ዘፍ 13÷13) “የሰዶም ሰዎች ግን ክፉዎችና በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ኃጢአተኞች ነበሩ” ዘፍ 19÷4 “ገናም ሳይተኙ የዚያች
ከተማ የሰዶም ሰዎች ከብላቴናው ጀምሮ እስከ ሽማግሌው ድረስ በየስፍራው ያለው ሕዝብ ሁሉ ቤቱን ከበቡት ሎጥንም ጠርተው በዚህ ሌሊት ወደ ቤትህ የገቡት ሰዎች ወዴት ናቸው? እናውቃቸው ዘንድ ወደ እኛ አውጣቸው አሉት”

(2ጴጥ  2-7) “ጻድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዓመፀኛ ሥራቸው
ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበርና” “እንዲሁ በሎጥ ዘመንም እንዲ ሆነ ይበሉ ይጠጡም ይገዙም ይሸጡም የተክሉም
ቤትም ይሠሩ ነበር ሎጥም ከሰዶም በወጣበት ቀን ግን እሳትና ዲን ዘነበ ሁሉንም አጠፋ” (ሉቃ17÷28)
(መዝ 48÷12÷20) “ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አያውቅም፣ አዕምሮ የሌለው ክቡር ሰው እንደሚጠፋ እንስሶች መሰለ” (ዘሌ
18÷22) “ለቀደመው ዓለም ሳይራራ ከሌሎች ሰባት ጋር ጻድቅ የሚሰብከውን ኖህን አድኖ በኃጢዓተኞች ዓለም ላይ የጥፋት ውሃ አወረደ” (2ጴጥ 2÷8) “ኖህ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ ይበሉና ይጠጡ ይገቡና ይገቡም ነበር የጥፋት ወሃም መጣ ሁሉንም አጠፋ” (ሉቃ17÷27-28)
(ይሁ 1-7 )”እንዲሁም እንደ እነርሱ ዝሙትን ያደረጉና ሌላን ሥጋ የተከተሉ ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸውም የነበሩ ከተማዎች በዘላለም እሳት እየተቀጡ ምሳሌ ሆነዋል” “ስለዚህ እርስ በእርሳቸው ሥጋቸውን ሊያዋርዱ እግዚአብሔር በልባቸው ፍትወት ወደ ርኩስነት አሳልፎ ሰጣቸው ይህም የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት ስለለወጡ በፈጣሪም ፈንታ የተፈጠረውን ስላመለኩና ስላገለገሉ ነው እርሱ ለዘላለም የተባረከ ነው አሜን፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው ሴቶቻቸውም በባሕሪያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕሪያቸው በማይገባ ለወጡ እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕሪያቸው
የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በእርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስህተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ተቀበለ” (ሮሜ 1÷24-27)

“እንደነዚህ ለሚያደርጉት ሞት ይገባቸዋል (ሮሜ 1-32) በምድርም ባለው ሕይወት አይጠቅሙም” “ለቅዱሳን እንደሚገባ ግን ዝሙትና ርኩሰት ሁሉ ወይም መመኘት በእናንተ ዘንድ ከቶ አይሰማ፣” (ኤፌ 5÷3) “የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁባት በመዳራትና በስጋ ምኞትም የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃል” 1ጴጥ 4÷3 ብዙዎች በዚህ ተፈትነው ወድቀዋል፣ በቤተክርስቲያን ሳይቀር አገልጋዮች በዝሙት ኃጢአት የተፈተኑ አሉ፡፡

1)የሶምሶን መፈተን፤

ሶምሶን የእግዚአብሔር መንፈስ የሞላበት በመላዕክ ብስራት የተወለደ የዳን ወገንና የዳርዓ ሀገር ሰው የሆነው የማኑሄ ልጅ ነው (መሳ 13÷2-6) “የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ በኃይል ስለወረደ የአንበሳ ደቦል ቆራርጦ ጥሏል” (መሳ 14÷6) “በአንድ የአህያ
መንጋጋ አንድ ሺህ ፍልስጤማውያንን ገድሏል” (መሳ 15÷15) “በእስራኤል ላይ ሃያ ዓመት ፈረደ መስፍን ሆኖ አስተዳደረ” (መሳ 15÷20)  ከዚህ በኋላ ነበረ ሶምሶን በዝሙት የተፈተነው ለዚያውም በጋለሞታ ሴት “ሶምሶን ወደ ጋዛ ሄደ በዚያም ጋለሞታ ሴት አይቶ ወደ እርሷ ገባ” መሳ 16÷1 “ከዚህም በኋላ በሶሬቅ ሸለቆ የነበረች ደሌላ የተባለች ጋለሞታ ሴት ወደደና ርስቱን ሁሉ አሳልፎ ሰጥቶ ተዋረደ ሞተም” (መሳ16÷4-31) “ሥጋችሁ የክርስቶስ ብልቶች እንደሆነ አታውቁምን? እንግዲህ የክርስቶስን ብልቶች
ወስጄ የጋለሞታ ብልቶች ላድርጋቸውን? አይገባም፡፡ ወይስ ከጋለሞታ ጋር የሚተባበር አንድ ስጋ እንዲሆን አታውቁምን? ሁለቱ አንድ ሥጋ ይሆናሉ ተብሏልና” (1ቆሮ 6÷15-17) “ርስትህን እንዳታጣ ለጋለሞታ ልብህን አትስጣት” (መጽሐፈ ሲራክ 9÷3) “የጋለሞታ ዋጋ እኮ አንዲት እንጀራ ነው አመንዝራም ሴት የሰውን ሕይወት ታጠምዳለችና ውበትዋን በልብህ አትመኘው ሽፋሽፍቱም አያጥምድህ” (ምሳ6÷25)

2)የአፍኒንና ፊንሐስ ሕይወት
አፍኒንና ፊኒሐስ የሊቀ ካህኑ የዔሊ ልጆች ናቸው፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ቤት እየኖሩ እግዚአብሔርን እያገለገሉ እግዚአብሔርን አያውቁም ነበር፣”እግዚአብሔር በባሕሪው ቅዱስ ነው ቤቱ የሰላምና የፍቅር ቅዱስ አደባባይ(አውደ ምህረት) ስለሆነ አገልጋዮቹም ሆነ በውስጡ የሚመላለሱት በሥርዓትና በቅድስና እንዲሁም በፍርሃት ይመላለሱ ዘንድ ይገባል” “ይህች የእግዚአብሔር
ደጅ ናት ወደ እርሷ ጻድቃን ይገባሉ” (መዝ 117÷20) “ፈጥኜ ወደ አንተ እንድመጣ ተስፋ አድርጌ ይህን እጽፍልሃለሁ፡፡ ብዘገይ ግን በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፡፡ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው” (1ጢሞ3÷14)
“አፍኒና ፊንሐስ ግን ምናምንቴዎች ነበሩ እግዚአብሔርን አያውቁም ነበር” (1ሳሙ 2÷12)
በመቅደስ በቤተክርስቲያን ከሚመጡት ሴቶች ጋር ያመነዝሩ ነበርና ምናምንቴዎች አላቸው “ዔሊም እጅግ አረጀ
ልጆቹም በእስራኤል ሁሉ ላይ ያደረጉትን ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ከሚያገለግሉት ሴቶች ጋር እንደ ተኙ ሰማ” (1ሳሙ
2÷22) በእነሱ የዝሙት ኃጢዓት ምክንያት ክብር ከእስራኤል ለቀቀ ከ30,000 በላይ እስራኤል ሞቱ ታቦተ ጽዮን ተማረከች፡፡

3)ዳዊት በዝሙት ኃጢዓት ተፈትኗል
(2ሳሙ 11÷1) “እንዲህም ሆነ ማታ ጊዜ ዳዊት ከምንጣፉ ተነሳ በንጉሱም ቤት በሠገነት ላይ ተመላለሰ በሰገነቱም ላይ አንዲት ሴት ስትታጠብ አየ ሴቲቱም መልከ መልካም ነበረች ዳዊትም ልኮ ስለ ሴቲቱ ጠየቀ “ይህች የኤልያብ ልጅ የኬጢያዊው የኦርዮ ሚስት ቤርሳቤህ ናት” አሉት ዳዊት ግን መልዕክተኞችን ልኮ አስመጣት ወደ እርሱም ገባች ከርኩሰትዋም ነጽታ ነበርና ከእርስዋ ጋር ተኛ ወደ ቤቷም ተመለሰች ሴቲቱም አረገዘች”(መጽ ሲራ 9÷3) በዝሙቷ እንዳትሰናከል የሰው ሚስት አታባብል” ዳዊት ከእግዚአብሔር ዘንድ በሳይር ተቀጥቷል፡፡ “በጉያው እሳትን የሚታቀፍ ልብሶቹስ የማይቃጠሉ መነው? በፍም ላይ የሚሄድ
እግሮቹስ የማይቃጠሉ ማነው? ወደ ሰው ሚስት የሚገባም እንዲሁ ነው የሚነካትም ሁሉ ሳይቀጣ አይቀርም” (ምሳ
6÷27) “ጋብቻ (መጋባት) በሁሉ ዘንድ ክብር መኝታውም ንጹህ ይሁን ሴሰኞችንና አመንዝራዎችን
ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል” (ዕብ 13÷3)
(ኢዮ 31÷1) “ከዓይኔ ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ፣ እንግዲህስ ቆንጆይቱን እንዴት እመለከታለሁ?” ከጋብቻ በኋላ ዓይንንም እጅንም (ልብን) እግርንም መሰብሰብ ይገባል በቤተክርስቲያን ጋብቻ ከዘመድ ጋር ፈጽሞ የተከለከለ ነው፡፡ “ከእናንተ ማንም ሰው ኃፍረተ ሥጋውን ይገልጥ ዘንድ ወደ ዘመዱ ሁሉ አይቅረብ እኔ እግዚአብሔር ነኝ” (ዘሌ 18÷6) (2ኛ ሳሙ 13÷1) (1ቆሮ 15÷33)
ባልና ሚስት መኝታቸው ንጹህ ነው፣ በመሆኑም:

፩. ለጸሎት ይተጉ ዘንድ በአጽዋማት ጊዜ ካልሆነ በስተቀር
(1ቆሮ 7÷5)
፪. ወደ ቤተክርስቲያን ለቅዳሴ በሚሄዱበት ጊዜ ካልሆነ
፫. ወደ ቅዱስ ቁርባን የሚቀርቡ ካልሆነ
፬.ሴቲቱ በመርገምዋ ጊዜ (በአደፏ ጊዜ)፡- (ዘሌ18÷19) ካልሆነ በቀር እርስ በራሳቸው አይከላከሉ፡፡ ባል ለሚስቱ የሚገባትን ያድርግላት እንደዚሁም ደግሞ ሚስት ለባሏ ሚስት በገዛ ሥጋዋ ላይ ስልጣን የላትም፣ ሥልጣን ለባልዋ ነው እንጂ እንዲሁም ደግሞ ባል በገዛ ሥጋው ላይ ሥልጣን የለውም ሥልጣን ለሚስቱ ነው እንጂ” (1ኛ ቆሮ 7÷3-5)
“እግዚአብሔር ጋብቻን የሠራ ልጆችን ለመውለድ ብቻ አይደለም እንዲሁም ራሳቸውን ከማይገባ ግንኙነት ይጠብቁ የማይገባ ግንኙነት ግን ለሚጸነሰው ፅንስም ሆነ ለሚወለደው ልጅም ጤና አይሆንምና” (ፍት ነገ 24÷922-25) “አታመንዝር የሚለውን ሕግ ተላልፈው በዝሙት ለሚረክሱት እግዚአብሔር እንዲህ ይላል”

“ንስሐ እንድትገባ ጊዜ ሰጠኋት ከዝሙቷ ንስሐ እንድትገባ አልወደደችም እነሆ በአልጋ ላይ አጥላቻለሁ ከእርሷም ጋር የሚያመነዝሩት ከሥራዋ ንስሐ ባይገቡ በታላቅ መከራ እጥላቸዋለሁ ልጆችዋን በሞት እገድላቸዋለሁ” (ራዕ 2÷21)
 (ኢዮ33÷14-22 )”እግዚአብሔር በአንድም በሌላም መንገድ ይናገራል ሰው ግን አያስተውልም….
በአልጋ ላይ በደዌ ይገስጸዋል አጥንቱንም ሁሉ ያደነዝዛል ሕይወቱም እንጀራን ነፍሱም ጣፋጭ መብልን ትጠላለች”
“ኑና እንዋቀስ ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነፃለች እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች” ኢሳ 1÷18 “ተመለሱና በሕይወት ኑሩ” ሕዝ 18-30

ክፍል ፪

ለመጋባት የሚከለክሉ ምክንያቶች፤
እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት ቅዱሳንም እንዳስተማሩን በመንፈስ ቅዱስም ተመርተው በቅዱሱ መጽሐፍ መዝግበው እንዳስቀመጡልን:
፩. በሃይማኖት አለመመሳሰል ወይም በሃይማኖት ልዩነት ካለ መተጫጨትም ሆነ
ጋብቻን መመስረት አይፈቀድም፡፡

ዘፍ 2÷24 “ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል በሚስቱም ይጣበቃል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ስለዚህ አሕዛብ የሚያገባ እርሱም አሕዛብ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ማቴ 19÷5 “ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” መጽሐፍ ቅዱስ “ከጌታ ጋር የሚተባበር አንድ መንፈስ ነው” 1ቆሮ 6÷17 ምክንያቱም አንድ ጌታ አንድ ኃይማኖት በሁሉም የሚሠራው መንፈቅስ
ቀዱስ አንድ ነው፡፡ (ኤፌ 4÷5) “በመጠራታችን በአንድ ተስፋ እንደተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ
አንድ ጌታ አንድ ኃይማኖት አንዲት ጥምቀት ከሁሉም በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉ አባት አለ፡፡”
“ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመድ ጽድቅ ከአመድ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? ወይስ ከሚያምኑ ከማያምን ጋር ክፍል አለው?” (2ኛ ቆሮ 6÷14)
(ዘዳ 7÷3 )እግዚአብሔር እስራኤልን ከሰባቱ አሕዛብ ጋር አትጋባ ሴት ልጅህን ለወንድ ልጁ አትስጥ ሴት ልጁንም ለወንድ ልጅህ አትውሰድ፣ እኔን እንዳያመልክ ሌሎችንም አማልክት እንዲያመልክ ልጅህን ያስታልና”
ዘጸ 34÷15-17 “በዚያች ምድር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን አታድርግ እነርሱ አምላኮቻቸውን ተከትለው ባመነዘሩና በወድላቸው ጊዜ እንዳይጠሩህ ከመስዋዕታቸውም እንዳትበላ ሴት ልጆቻቸውንም ከወንድ ልጆችህ ጋር እንዳታጋባ ልጆቻቸው አምላኮቻቸውን ተከትለው ሲያመነዝሩ ከአምላኮቻቸው በኋላ ሄደው አመንዝረውም ልጆችህን እንዳይከቱ ተጠንቀቅ”

አባቶቻችን ሲያስተምሩ ሰው ውሎውን ጓደኛውን ይመስላል “ከቸር ሰው ጋር ቸር ሆነህ ትገኛለህ፣ ከቅን ሰው ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ፣ ከንጹህ ጋር ንጹህ ሆነህ ትገኛለህ ከጠማማ ጋር ጠማማ ሆነህ ትገኛለህ” (መዝ 17÷26)
(1ኛ ቆሮ 15÷33)  “አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል። “ንጉስ ሰሎሞንም ከፈርኦን ልጅ ሌላ በምዓባውያንና በአሞናውያን በኤዶማውያንም በሊደራውያንና በኬሚያውያን ሴቶች ልጆች በብዙ እንግዶች ሴቶች ፍቅር ተነደፈ፡፡ እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች አምላኮቻቸውን ትከተሉ ዘንድ ልባችሁን በእውነት ያዘንበላሉና ወደ እነርሱ አትግቡ፣ እነርሱም ወደ እናንተ አይግቡ ካላቸው ከአሕዛብ ከእነዚህ ጋር ሰሎሞን በፍቅር ተጣበቀ” (1ኛ ነገ 11÷1-3) “ከእርሱም ወይዛዝርት የሆኑ ሰባት መቶ ሚስቶች ሶስት መቶ ቁባቶች ነበሩት ሚስቶቹም ልቡን አዘነበሉት”
“ሰሎሞን ሲሸመግል ሚስቶቹ ሌሎችን አማልክት ይከተል ዘንድ ልቡን አዘነበሉ :የአባቱ የዳዊት ልብ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም እንደነበረ የሱ ልብ ፍጹም አልነበረም” (2ኛ ነገ11÷4)

“ሰለሞን የሲደናውያንን አምላክ አስታሮትን የአሞናውያንንም ርኩሰት ሚልኮምን ተከተለ ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገርን አደረገ፡፡ እንደ አባቱም እንደ ዳዊት እግዚአብሔርን በመከተል ፍጹም አልሆነም፡፡ በዚያን ጊዜም ሰሎሞን ለካምን ርኩሰት ለካምሽ፣ ለኦምንም ልጆች ርኩሰት ለሞሎክ በኢየሩሳሌም ፊት ለፊት ባለው ተራራ ላይ መስገጃ ሠራ ለአማልክቶቻቸው ዕጣን ለሚያጥኑ መስዋዕትም ለሚሠዉ ለእንግዶች ሚስቶቹ ሁሉ እንዲሁ አደረገ” (1ኛ ነገ11÷4-8)

** ከኤሳም ልጆች ወገን የነበረም የይሄኤል ልጅ ዕዝራ እያለቀሰና በእግዚአብሔር ቤት ፊት እየወደቀ በጸለየ ጊዜ አምላካችንን በድለናል የምድርን አሕዛብ እንግዶች ሴቶችን አግብተናል፣አሁን ግን ስለዚህ ነገር ገና ለእስራኤል ተስፋ አለ” (ዕዝ 10÷2-3)
**(ነህ 13÷23-27) “ደግሞም በዚያ ወራት አዛጠንና የአሞንን የምዓብንም ሴቶች ያገቡትን አይሁድ አየሁ፣ ከልጆቻቸውም እኩሌቶቹ በአዛጦን ቋንቋ ይናገሩ ነበር. በአይሁድም ቋንቋ መናገር አያውቁም ነበር፣ ከእነርሱም ጋር ተከራከርሁ ረገምኳቸውም፣ ከእነርሱም አያሌዎቹን መታህ ጸጉራቸውንም ነጨሁ፣ እንዲህም ብዬ በእግዚአብሔር አማልኳቸው ሴቶች ልጆቻችሁን አትስጡ፣ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለእናንተ ለልጆቻችሁ አትውሰዱ፣ የእስራኤል ንጉስ ሰሎሞን በዚህ ነገር ኃጢዓት አድርጎ የለምን በብዙ አሕዛብ መካከል እንደ እርሱ ያለ ንጉስ አልነበረም በአማላኩም ዘንድ የተወደደ ነበረ እግዚአብሔርም በእስራኤል ሁሉ ላይ አንግሶት ነበረ፣ እሱን እንኳ እንግዶች ሴቶች አሳቱት”

**”እናንተ ግል ተመልሳችሁ በመካከላችሁ ወደ ቀሩት ወደ እነዚህ አሕዛብ ብትጠጉ ከእነርሱም ጋር ብትጋቡ እናንተም ወደ እነርሱ እነርሱም ወደ እናንተ ብትደራረሱ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ከዚህችም ከመልካሚቱ ምድር እስክትጠፋ ድረስ መውደቂያና ወጥመድ በጎናችሁ መግረፊያ በአይናችሁ እሾህ ይሆንባችኋል….” (ኢያ 23÷12-13) “ከእነርሱ ጋራ እንዳትተባበሩ፣
እንደነዚህ ካሉት ጋር መብል እንኳ እንዳትበሉ አጽፍላችኋለሀ” 1ቆ 5÷11-12

(1ኛ ነገ 16÷29-34) “በይሁዳም ንጉስ በኦሳ በሰላሳ ስምንተኛው ዓመት የዘንበሪ ልጅ አክዓብ በእስራኤል ላይ ነገሠ፣ በሰማሪያ እስራኤል ሃያ ሁለት ዓመት ነገሠ አክዓብ ከእርሱ በፊት ከነበሩት ሁሉ ይልቅ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደገ በናባጥም ልጅ በኢዮብዓም ኃጢዓት መሄድ ታናሽ ነገር መሠለው፣ የሲደናውያንንም ንጉስ የቤት በዓልን ልጅ ኤልዛቤል አገባ፣ ሄደም በዓልን አመለከ ሰገደለትም በሠማሪያም በሠራው በበዓል ቤት ውስጥ ለበዓል መሠዊያ አቆመ፣ የማምለኪያ አጸድ ተከለ፣ ከእርሱ በፊት ከነበሩት ሁሉ ይልቅ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን የሚያስቆጣው ነገር አበዛ”

፪. ዘመድማማች መጋባት አይፈቀድም
በቤተክርስቲያናችን ሥርዓት እስከ ሰባት ቤት የዘር ሐረግ ድረስ ዘመድ መጋባት ፈፅሞ የተከለከለ ነው፡፡
ከእናንተ ማንም ሰው ኃፍረተ ስጋውን ይገልጥ ዘንድ ወደ ዘመዱ ሁሉ አይቅረብ እኔ እግዚአብሔር ነኝ” (ዘሌ 18÷6):
 (ዘሌ 20÷10-21) “ማናቸውም ሰው ከሌላ ሰው ሚስት ወይም ከባልንጀራው ሚስት ጋር ቢያመነዝር አመንዝራውም(ይቱም) ይነዳሉ” (1ቆሮ5÷11) “ወንድሞች ከሚባሉት አንዱ ሴሰኛ ቢሆን ከእርሱ ጋር አትተባበሩ መብል እንኳ ቢሆን አትብሉ”
(ማር 6÷11) “ከማይቀበላችሁና ከማይስማችሁ ስፍራ ሁሉ ከዚያ ወጥታችሁ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ ከእግራችሁ በታች ያለውን ትቢያ አራግፉ እውነት እላችኋለሁ ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ በፍርድ ቀን ይቀበላቸዋል”ሄሮድስ በወንድሙ በፊልጶስ ሚስት በሄሮዳይዳ ምክንያት ዮሐንስን አስይዞ አሳስሮት በወህኒ አኑሮት ነበርና “ዮሐንስ እርሷ ለአንተ ትሆን ዘንድ አልተፈቀደም ይለው ነበርና፣ ሊገድለውም ወደ ሳለ ሕዝቡ እንደ ነቢይት ስላዩት ፈራቸው፡፡”ማቴ14:3

፫. የዕድሜ አለመመጣጠን
እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት ቅድመ ጋብቻ ወይም ከጋብቻ በፊት ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገቡት ነገሮች፡-

ሀ) አካላዊ የብስለት ደረጃ
ለ)መሠረታዊ የሆነ ቅድመ ሁኔታ ዝግጅት
ሐ) መንፈሳዊ የብስለት ደረጃ መካከል አንዱ የዕድሜ ብስለትና መመጣጠን ነው፡፡
የልጅነት ጊዜያቸውን ያልጨረሱ ሰዎች ለትዳር ብቁ ሊሆኑ አይችሉም፣ ምክንያቱም ትዳር ኃላፊነትን መሸከም ይጠይቃልና፡፡ ወንዶች ከ15 – 18 ባለው ጊዜያቸው የተቃራኒ ጾታ ፍላጎት ይኖራቸዋል ነገር ግን በዚህ ዕድሜ ኃላፊነትን መሸከም አይፈልጉም፡፡ ሴቶችም ከ12-15 የተቃራኒ ጾታ ፍላጎት ይኖራቸዋል፣ ከ15-18 መቀራረብና ግንኙነት ይፈልጋሉ ነገር ግን ኃላፊነትን መቀበል አይፈልጉም አይችሉም፡፡በአጠቃላይ በወንድና በሴቷ መካከል ከ15 ዓመት በላይ ልዩነት ካለ ለመንፈሳዊ ጋብቻ ጥሩ አይሆንም (1ኛ ቆሮ 13÷11)፡፡

ክፍል ፫

ጋብቻን ላለመመስረት ወይም ለማፍረስ ምክንያት የማይሆኑ ነገሮች

ጋብቻ ክቡርና ቅዱስ ከመሆኑም ባሻገር ሁለቱ አንድ ሥጋ ይሆናሉ ተብሎ ስለተጻፈ ከባድ ችግር ምክንያት ማለትም በሞት፣ በዝሙትና፣ በኃይማኖት ልዩነት ካልሆነ በቀር በምንም ነገር ቢሆን የተመሠረተ ጋብቻ አይፈርስም፡፡ ትዳርን ለመመስረትም ቢሆን ፈሪሃ እግዚአብሔር ዓላማ መስፈርት ሊሆኑ ይገባል፡፡ (ምሳ 31÷30)

፩ኛ. ተክለ ሰውነት (ገጽ፣ ቁመና)

መልክ ቁመና ትዳር ላለመመስረት መስፈርት አይሆንም ትዳር ለማፍረስም ምክንያት አይሆንም፡፡
(ዘፍ 29÷16-20) “ለላባም ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩት የታላቂቱ ስም ልያ የታናሽቱ ስም ራሔል ነበረ ልያም ዓይነ ልም ነበረች ራሔል ግን መልከ መልካም ነበረች ፊቷም ውብ ነበረ፡፡ ያዕቆብም ራሔልን ወደደ ስለታናሽቱ ልጅ ስለ ራሔል ሰባት ዓመት እገዛልሃለሁ አለው፡፡ ያዕቆብ ስለ ራሔል ሰባት ዓመት ተገዛ እርስዋንም ይወድዳት ስለነበር በእርሱ ዘንድ እንደ ጥቂት ቀን ሆነለት፡፡”
ዘፍ 4÷4 “አዳም ዝምድና ለማራራቅ የአቤልን መንትያ ለቃኤል፣ የቃኤልን መንያ ለአቤል አጋባ ነገር ግን የአቤል መንትያ መለከ ጥፉ ነበረችና ቃኤል በአቤል ቀና፣ ወንድሙንም ገደለው”
“ለእናንተም ጠጉርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጪ የሆነ ሽልማት አይሆንላችሁ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ” (1ጴጥ 3÷3) (ኢዮ 14÷1-2) ከሴት የተወለደ ሰው የሕይወቱ ዘመን ጥቂት ቀን ነው መከራም ይሞላዋል እንደ አበባም ይወጣል ይረግፋልም” “እንደ ጥላም ይሸሻል እርሱም አይጸናም” (ኤር14÷2)
(1ጴጥ 1÷24) “ሥጋ ሁሉ እንደ ሣር ክብሩም ሁሉ እንደ ሣር አበባ ነውና ሣሩ ይጠወልጋል አበባውም ይረግፋል” (ኢሳ
40÷6) ጩኹ የሚል ድምጽ መጣ ምን ብየ ልጩኽ አልሁ ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሣር ነው ክብሩም ሁሉ እንደ ምድረ በዳ አበባ ነው የእግዚአብሔር እስትንፋስ ይነፍስበታልና ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል በእውነት ህዝቡ ሣር ነው ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል”
፪ኛ. ምድራዊ ሃብት ንብረት
ምድራዊ ሃብት ንብረት ኃላፊ ጠፊ ነው፣ ስለዚህ ቁሳቁስ ትዳር ለመመስረትም ሆነ የተመሠረተውን ቅዱስና ክቡር ጋብቻ ለማፍረስ መሠረት አይሆንም፡፡ (ኢዮ 1÷21) “ራቁቴን ከእናቴ ማህፀን ወጥቻለሁ ራቁቴንም ወደዚያ እመለሳለሁ እግዚአብሔር ሰጠ እግዚአብሔር ነሳ የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን”
(መክ 5÷15) ከእናቱ ሆድ ራቁቱን እንደ ወጣ እነዲሁ እንደመጣው ይመለሳል ከጥረቱም በእጁ ሊወስድ የሚችለውን ምንም አያገኝም ይህም ደግሞ የሚያሳዝን ክፉ ነገር ነው እንደመጣ እንዲሁ ይሄዳል”
(መዝ 61÷10) “ዓመጻን ተስፋ አታድርጉ ቅሚያምንም አትተማመኑት ባለጸግነት ቢበዛ ልባችሁ አይኩራ” (ምሳ 11÷28) “በበለፀግነቱ የሚተማመን ሰው ይወድቃል” (ኤር 9÷23) እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ጠቢብ በጥበቡ አይመካ ኃያልም
በኃይሉ አይመካ ባለጸጋም በብልጽግናው አይመካ ነገር ግን የሚመካው ምህረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋል በዚህ ይመካ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና ይላል እግዚአብሔር”

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስትጸልይ “የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቧልና ባለጠጎችንም ባዶ እጃቸውን ሰዷቸዋል” ሉቃ 1÷53 (2ቆሮ 6÷10) “ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለጠጎች እናደርጋለን አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው” እግዚአብሔርን የያዘ ሰው ሁሉ ነገር አለው፣ መንፈሳዊ ሰው ባለጸጋ ነው፣ በፍቅር በትህትና በትዕግስት በማስተዋል ሆኖ ብዙዎችን በሕይወቱ ባለጸጋ ያደርጋል፣ “እግዚአብሔርን ከመፍራት ጋር ያለ ጥቂት ነገር ሁከት ካለበት ከብዙ መዝገብ ይሻላል፡፡ የጎመን ወጥ በፍቅር መብላት የሰባ ፍሪዳን ጥል ባለበት ዘንድ ከመብላት ይሻላል” ምሳ15÷16-17 (ራዕ 2÷9) “መከራህንና ድህነትህን አውቃለሁ ነገር ግን ባለጸጋ ነህ”

፫ኛ) መሃንነት (ልጅ አለመውለድ)
ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው፣ ማህፀንን የሚከፍትና የሚባርክ እግዚአብሔር ነው፤ የሆድም ፍቴ የእርሱ ዋጋ በመሆኑ ክቡር የሆነውን ጋብቻ ለማፍረስ መሀንነት ምክንያት ሊሆን አይገባም፡፡
(መዝ 126÷3) ደግሞም እግዚአብሔር ጊዜ አለው፡፡ በጊዜው ሁሉ ይሆናል በትዕግስትና በጽናት በእምነት ሆነው ከጠበቁት (መክ
3÷1) *** (መጽሐፈ ሲራክ 2÷10) **
(ዘፍ 18÷9) “ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት? እርሱም በድንኳን ውስጥ ናት አለ፣ የዛሬ ዓመት እንደ ዛቴው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች” (ዘፍ17÷1) አብርሃም የዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሰው በሆነ ጊዜ እኔ ኤልሻዳይ ነኝ እጅግም አበዛሃለሁ አለው” (ዘፍ 21÷1)* እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ ሣራን አሰበ እግዚአብሔር እንደተናገረ ለሣራ አደረገላት ሣራም ፀነሰች እግዚአብሔርም በተናገረው ወራት ለአብርሃም በእርጅናው ወንድ ልጅን ወለደችለት”

“1ሳሙ 1÷1 ህልቃና ሁለት ሚስቶች ነበሩት የአንዲቱ ስም ሐና የሁለተኛይቱም ፍናና ነበረ፣ ለፍናና ልጆች ነበሩአት ሐና ግን ልጅ አልነበራትም፡፡ ህልቃና ሓናንም ይወድ ነበረና ለሐና ሁለት እጥፍ ዕድል ፈንታ ሰጣት እግዚአብሔር ግን ማህፀንዋን ዘግቶ ነበርና ጣውንታ ታስቆጣት ታበሳጫትም ነበር”

(1ሳሙ 1÷19-20)** እግዚአብሔር አስባት የመጸነሷም ወራት ካለፈ በኋላ ሐና ወንድ ልጅ ወለደች” (መሳ 13÷2)** “ከዳን ወገን የሆነ ማኑሄ የሚባል አንድ የዓርዓ ሰው ነበረ ሚስቱም መካን ነበረች ልጅም አልወለደችም የእግዚአብሔርም መልአክ ለሴቲቱ ተገልጦ እንዲህ አላት እነሆ አንቺ መካን ነሽ ልጅም አልወለድሽም ነገር ግን ትጸንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ”(ሉቃ 1÷5-7)** በይሁዳ ንጉስ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ ሚስቱም ከአሮን ልጆች ነበረች ስምዋም ኤልሳቤጥ ነበረ፡፡ ሁለቱም በጌታ ትዕዛዝና ህግጋት ሁሉ ያለነቀፋ እየሄዱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፡፡ ኤልሳቤጥም መካን ነበረችና ልጅ አልነበራቸውም ሁለቱም በዕድሜያቸው አርጅተው ነበር” **ከዚህም ወራት በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰችና ነቀፌታዬን ከሰው መካከል ያስወግድልኝ ዘንድ ጌታ በተመለከተበት ወራት እንዲህ አድርጎልኛል ስትል ራስዋን አምስት ወር ሰወረች” (ሉቃ1÷24-25) “ችግረኛን ከመሬት የሚያነሣ ምስኪኑንም ከፍንድያ ከፍ ከፍ የሚያደርግ መካኒቱን በቤት የሚያኖራት ደስ የተሰኘችም የልጆች እናት የሚያደርጋት፡፡ (ሃሌ ሉያ) እግዚአብሔር ይመስገን፡፡” (መዝ112÷9)

 

ቀለበት

 

እንደ ቤተክርስቲያን ሥርዓት ሙሽሮች መጽሐፈ ተክሊል ጸሎት ከተደረሰላቸው በኋላ ቀለበት ያጠልቃሉ ከዚያም ቃል ኪዳን ይገባሉ፣ ቀለበት የቃል ኪዳን ምሳሌ ነው፣ በሌላው ከዚህ በኋላ በአንተ ታስሬአለሁ በአንቺ ታስሬአለሁ ለማለት የሚደረግ ነው፡፡ እንዲሁም ፍጹም ክብ እንደሆነ እስከመጨረሻው ያለምንም ክፍተት በሙሉ ልብ አምኜ ተቀብየዋለሁ፣ ተቀብያታለሁ በነገር ሁሉ ልረዳና ልረዳ ቃል ገብቻለሁ ማለት ነው፡፡ (ሉቃ 15÷22)** አባቱ ግን ባሪያዎቹን ጠርቶ ፈጥናችሁ
ከሁሉ የተሸለ ልብስ አምጡና አልብሱት ለእጁም ቀለበት ለእግሩም ጫማ ስጡ አለ”

 

**ቀለበት የቃል ኪዳን ምልክት ነው**

ፍች የሚፈቀድባቸው ምክንያቶች

በቤተክርስቲያን ሥርዓት ጋብቻ ክብርና ቅዱስ ከመሆኑም
ባሻጋር ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፣ ይህ ምስጢርም ታላቅ ነው ይላልና (ኤፌ5÷31-32) በዝሙትና፣ በኃይማኖት ልዩነት ካልሆነ በስተቀር ፍች ፈጽሞ
አይፈቀድም፡፡ (ማቴ 5÷32) “እኔ ግን አላችኋለሁ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ አመንዝራ ያደርጋታል የተፈታችውንም የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል” (1ቆሮ 7÷39)* “ሴት ባልዋ በሕይወት ሳለ የታሰረች ናት ባልዋ ቢሞ ግን በጌታ ይሁን እንጂ የወደደችውን ልታገባ ነፃነት አላት፡፡” 1ቆሮ 7÷27 “በሚስት ታስረህ እንደሆነ መፍታትን አትሻ” 1ቆሮ 11÷11 “ነገር ግን በጌታ ዘንድ ሴት ያለወንድ ወንድም ያለ ሴት አይሆንም” (ማቴ 2÷16)** መፍታትን እጠላለሁ ይላል የእስራኤል
አምላክ እግዚአብሔር ልብሱንም በግፍ ሥራ የሚከድነውን ሰው እጠላለሁ ይላል የሠራዊት ጌታ ለዚህ እንዳታታልሉ መንፈሳችሁን ጠብቁ” (1ቆሮ7÷10-11)** “ሚስት ከባልዋ አትለያይ ብትለያይ ግን ሳታገባ ትኑር ወይም ከባልዋ ትታረቅ ባልም ሚስቱን አይተዋት ብየ የተጋቡትን አዛቸዋለሁ”
(ማቴ 19÷3-9) “እኔ ግን እላችኋለሁያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን ፈትቶ ሌላይቱንም የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል የተፈታችውንም የሚያገባ ያመነዝራል”

 

ምንጭ ፤፟ http://ttewahedo.blogspot.com

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top