ማህተብ

ማዕተብ በቤተክርስቲያን ምን ማለት ነው? ማህተብ ለምን እናስራለን ?

“ማህተብህን በአንገትህ እሰረው ስትሔድ ይመራሃል ስትተኛ ይጠብቅሃል ” ምሳ 6÷21

ማዕተብ (አተበ፤ አመለከተ ፤ባረከ)

ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ነው፡፡ይህም ማለት መታወቂያ ፤ ምልክት ማለት ነው፡፡ይህም ያመኑትንና የተጠመቁትን ካላመኑትና ካልተጠመቁት የሚለዮበት የክርስቲያን መታወቂያ ነው፡፡

የዚህ ምልክት መሠረቱና ምሳሌውም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተቀበለው ጸዋትወ መከራ አንዱ በገመድ ታሥሮ መጎተቱ መሆኑንየሚያመለክት ነው፡፡

ዮሐ19፤12 ቅዱስ ዳዊትም በመዝ59፤4 ላይ ”ወወሀብኮሙ ትእምርተ ለእለ ይፈርሁከ ከመያምሥጡ እምገጸ ቅስት ፤ ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ ለሚፈሩ ምልከትን ሰጠሃቸው”ይላል፡፡

ደቀ መዝሙሩ ቅዱስ ያዕቆብ አልባሌ መስሎ በሶርያ ብቻ ሳይኾን በእስክንድርያ የሴት ቀሚስ ሳይቀር ለብሶ ሲያስተምር ንስጥሮሳውያን ከጉባኤው እየገቡ ስላስቸገሩት ኦርቶዶክሳውያንን ከመናፍቃን ለመለየት ከእግዚአብሔር ባገኘው ምልክት ጥቁር ቀይ ቢጫ ክሮች አንድ ላይ ፈትሎ በአንገታቸው ላይ ያስርላቸው ጀመር፡፡ ሌሊት ሌሊት ሲያስተምርና ሲጸልይ የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ጥርሶቹ እንደ ፋና ያበሩለት ነበር፡፡ ይህም በተኣምራት የተፈጸመ ነው፡፡

ሦስት ቀለማት ያላቸው ክሮች የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ሲኾኑ አንድ ላይ መፈተላቸው ወይም አንድ መኾናቸው ቅድስት ሥላሴ ማለት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በመለኰት በህልውና አንድ አምላክ መኾናቸውን ያመለክታል፡፡ ጥቁሩ፡- ክርስቲያን ስለ ሃይማኖት የሚቀበለው መከራ የሚሸከመው መስቀል፣ ቀዩ፡- በሰማዕትነት ደም የማፍሰስ ሲኾን ቢጫው ደግሞ የክርስቲያን ተስፋ የሃይማኖት ምልክት ነው፡፡

ቆይቶ ግን በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሕፃናት ክርስትና ሲነሡ፣ ኢአማንያን አምነው ሲጠመቁ ቀይ፣ ነጭና ሰማያዊ ፈትሎች በአንድ ላይ ተገምደው መታሰር ጀመረ፤ ትርጓሜውም የሦስቱ አንድ ላይ መገመድ የሥላሴን አንድነት ሦስትነት የሚያመለክት ምሳሌ ነው፡፡ ይኽንንም ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ጠቅለል ባለ መልኩ ሲያስረዱ፡- ሥላሴ ማዕተበ ብርሃን ኃይለ ሃይማኖቶሙ ለክርስቲያን፤ ሥላሴ ለክርስቲያን ኹሉ የሃይማኖታቸው ጉልበት መታወቂያ የብርሃን ማዕተብ (ምልክት) ናቸው፤ ብለዋል፡፡

ቀለሞቹ ደግሞ ቀይ፡- ክርስቶስ ደሙን አፍስሶ አድኖናል፤ ስለ ስሙም በሰማዕትነት ደማችንን ማፍሰስ ይገባናል የማለት፤ ነጩ፡– የጥምቀት በጥምቀትም የሚገኝ ስርየተ ኃጢአት፤ ሰማያዊ፡-በጸጋ ልጅነት አግኝቻለኹ፤ ሰማያዊ አባት አለኝ፤ ሰማያዊ ርስት መንግሥተ ሰማይ ይቆየኛል፤ ስለዚኽም በሰማያዊ ግብር ጸንቼ መኖር በሰማያዊት ሕግ ሕገ ክርስቶስ ወንጌል ተመርቼ መኖር ይገባኛል እንደማለት ነው፡፡

ክርስቲያን ለክርስቶስ ታማኝ በመኾኑ በነፍሱ ሞግዚት በቄሱ እጅ ከሕፃንነቱ ጀምሮ የድኅነቱ ምልክት በሚኾን አንገቱ በማዕተበ ክርስትና ይታሰራል፡፡ ማዕተብ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ ስለ እኛ ቤዛ ለመኾን የብረት ሀብል /የብረት ገመድ/ በአንገቱ ታስሮ በአይሁድ መጎተቱን ስለሚያስታውሰን ለታማኝነታችንና ለክርስቲያንነታችን ምልክትነቱ ማረጋገጫ ስለኾነ አናፍርበትም፡፡

አንዲት ሀገር ነፃና ሉዓላዊ መኾኗ የሚታወቀው ወይም ራሷን የቻለች መንግሥት ያላት ከባዕድ ቀንበር ቅኝ ግዛት ነፃ የወጣች መኾኗ በቀዳሚነት የሚለየው በባንዴራዋ ምልክትነት እንደኾነ እንደዚኹም አንድ ክርስቲያን በክርስቶስ አምኖ በጥምቀት ከዲያብሎስ ቁራኝነት ነፃ መውጣቱ፣ ነፃነት ያለው አማኝ መኾኑ የሚታወቀው በማተቡ ምልክት ነው፡፡

አጋንንት የክፋትን ቀስት በዚህ ዓለም በመወርወር የሰውን ልብ ስለሚወጉ ከዚህ ለመዳን ማዕተብን ማድረግ ታላቅ መንፈሳዊ እውቀት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ሲያስረዱ ሥላሴ ማዕተበ ብርሃን ኃይል ሃይማኖቶሙ ለክርስቲያን፤ሥላሴ ለክርስቲያን ሁሉ የሃይማኖታቸው ጉልበት መታወቂያ የብርሃን ማዕተብ (ምልክት) ናቸው ብለዋል፡፡

ማዕተብ ያላሠረ ኦርቶዶክሳዊ በውግዘት ከቤተክርስቲያኒቱ እንደ መናፍቅ ተቆጥሮ ባይለይም ማዕተብ አለማሠሩ ግን የአባቶቹ ትውፊት እንዳልተቀበለ ያስቆጥረዋል፡፡

በምሳሌያዊ አነጋገርም ሃይማኖት አልባውን ማለትም ክርስቲያን ያልሆነውን ማዕተብ የለሽ ያልተጠመቀ አረማዊ ይሉታል ክርስቲያን በማተቡ መነኩሴ በቆቡ እንዲታወቅ ማዕተብ አልባ መሆን። ደግሞ ክርስቲያን ይሁን ያልተጠመቀ መሆኑ ለማወቅ ያስቸግራል፡፡

በመለዮዋቸው ሌሎች እንዲታወቁ ክርስቲያን በማዕተቡ ክርስትናውን ሲያሳውቅ ኖሯል፡፡ በተለመደው አነጋገር እገሌ ማዕተብ አለው ባለማዕተብ ነው ሲባል እገሌ ታማኝ ክርስቲያን ነው።

“እኔ የኢየሱስን ማኅተም በሥጋዬ ተሸክሜአለሁና ከእንግዲህ ወዲህ አንድ ስንኳ አያድክመኝ።” (ገላትያ 6፡17) ለተጠመቁ ክርስቲያኖች የክር ማተብ ለሃይማኖት ምልክትነት ወይም መታወቂያ ከመኾኑ በፊት፣ በብሉይ ኪዳን ዘመን የሃይማኖት አባቶች ከጣዖት አምላኪዎች ተለይተው የሚታወቁበት ምልክት ነበራቸው፡፡ ስለ ታላቁ የሃይማኖት አባት ስለ ጻድቁ አብርሃም የሃይማኖት ማኅተም(ምልክት) ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ሳይገረዝም በነበረው እምነት ያገኘው የጽድቅ ማኅተም የኾነ የመገረዝን ምልክት ተቀበለ፡፡›› (ሮሜ ፪÷፲፩፤ ዘፍጥ.፲፯÷፱ – ፲፬) በሥርዐተ ኦሪት ብኵርና ከጥንት ጀምሮ ለእግዚአብሔር የተለየ ገንዘብ ኾኖ ስለሚቆጠር ብኵርና ላለው ኹሉ የአባት በረከት ከሌሎች ይልቅ በይበልጥ ምርቃት ዕጥፍ ድርብ ኾኖ ስለሚሰጠው ብኵርና ይወደዳል፤ ይፈቀራል፡፡ ብኵርና ማቃለል ዋጋ የሌለው ጸጸትን ያስከትል ነበር፡፡ ብኵርና ለዘመነ ሐዲስ ክርስትና ምሳሌ እንደኾነ ይታመናል፡፡ ክርስትናውን ንቆ አቃሎ ዓለምን መስሎ የሚኖር ሰው፣ ለጊዜያዊ መብል ፍለጋ ብኵርናውን በሸጠው በያዕቆብ ወንድም ዔሳው ተመስሏል፤ ‹‹. . .ስለ አንድ መብል በኵርነቱን እንደ ሸጠ እንደ ዔሳው ለዚኽ ዓለም የሚመች ሰው እንዳይኾን ተጠንቀቁ፡፡ ከዚያ በኋላ እንኳ በረከቱን ሊወርስ በወደደ ጊዜ እንደተጣለ ታውቃላችኹና በእንባ ተግቶ ምንም ቢፈልገው ለንስሐ ስፍራ አላገኘምና፡፡›› (ዕብ.፲፪÷፲፮፤ ዘፍጥ. ፳፭÷፳፱ – ፴፬፤ ፳፯÷፴ – ፵) ብኵርና ለክርስትና ምሳሌ መኾኑ ከላይ ተገልጧል፡፡ ትዕማር ከይሁዳ መንትያ ልጆችን ፀንሳ በምትወልድበት ጊዜ በኵሩ እጆቹን ሲያወጣ አዋላጅቱ ቀይ ፈትል ለምልክት አስራበታለች፡፡ ይህ ምሳሌያዊ ድርጊት በሐዲስ ኪዳን ሲተረጎም ከትዕማር የተወለደው በኵሩ ዛራ ለክርስቲያን ምሳሌ ሲኾን ቀዩ ፈትል ለክርስትናው ምልክት፤ ለማዕተብ ምሳሌ ኾኗል፡፡ አዋላጅቱ ለአጥማቂው ቄስ ምሳሌ ናት፡፡ ትዕማር የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ስትኾን በኋላ የመጣው ፋሬስ በኵሩን ጥሶ ቀድሞ መወለዱና ከቀይ ፈትል አልባ መኾኑ በምሳሌያዊ ትንቢትነት፣ ከቤተ ክርስቲያን በጥምቀት ከተወለዱ በኋላ ክርስትናቸውንና ጥምቀታቸውን ክደው የእውነተኞቹ ክርስቲያኖች ተቃዋሚዎች በመኾን ፊት ከተፈጠረ ጆሮ እንደ ቀንድ ብቅ ያሉ የመናፍቃንና የኢጥሙቃን (ኢአማንያን) ምሳሌ እንደኾኑ ያስረዳል፡፡ (ማቴ.፩÷፫፤ ዘፍጥ.፴፰÷ ፳፮ – ፴) በዛራ ልማድ ጌታችን ከድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ እመቤታችን አውራ ጣቱን በክር አስራዋለች፡፡ ቅዱስ ገብርኤል ለኖሎት ተገልጦ ምልክቱን እንዲህ ሲል ነግሯቸዋል፡- ‹‹ወከመዝ ትእምርቱ ለክሙ ትረክቡ ሕፃነ እሱረ መንኮብያቲኹ፤ ምልክቱ ይህ ነው፡፡ ሕፃኑ አውራ ጣቱን ታስሮ ታገኙታላችኹ፡፡›› (ሉቃ.፪÷፲፪) እመቤታችን አውራ ጣቱን በክር እንዳሰረችው ‹‹ወወለደት ወልደ ዘበኵራ ወአሰርቶ መንኮብያቲኹ፤ የበኵር ልጅዋን ወለደች፤ አውራ ጣቱን አሰረችው፡፡›› ( ሉቃ.፪÷፯፤ የግእዝና አማርኛ ነጠላ ትርጉም አማርኛ ሒዲስ ኪዳን ይመልከቱ) ድንግል እመቤታችን አውራ ጣት ማሰሯ ለክርስቲያኖች ማዕተብ ማሰር አብነት ኾኗል፡፡ ጣቱን ማሰሯ ያለምክንያት አልነበረም፡፡ ይኸውም፡- ፩ኛ/ ሕፃን ስለኾነ እንዲያጸናው፤ ፪ኛ/ ጣቱን ባይታሰር ምትሀት ነው፤ ሰው አልኾነም ለሚሉ መናፍቃን ለክሕደታቸው ምክንያት ባገኙ ነበርና ምክንያት ለማሳጣት፤ ፫ኛ/ ቀደም ብለን እንደገለጽነው ልማዳችንን አስቀረብን እንዳይሉ በዛራ ልማድ፤ ፬ኛ/ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በዕለተ ዓርብ ከመስቀል አውርደው እንዲኽ አድርገው ይገንዙሃል ለሰው ቤዛ ለመኾን ልትታሰር መጣኽን፣ ስትል ነው በማለት መምህራነ ቤተ ክርስቲያን በአንድምታ ትርጓሜያቸው ያትታሉ፡፡

እውነተኛ ሐቀኛ ነው የሚል ትርጉምን ይሰጣል “ባለማዕተቢቱ” ሲባል ከአሚን ባሏ የረጋች ከባሏሌላ የማታውቅ እውነተኛ ታማኝ ክርስቲያን የሚል ፍች አለው፡፡በዚህ ምክንያት በክርስቲያኑ ኅብረተሰብ የማዕተብ ትርጉም ከፍተኛ ቁም ነገርን አዝሎ ይገኛል፡፡ አንዲት ሀገር ነፃ መሆኗ የሚታወቀው ወይም ራሷን የቻለች የራሷ መንግሥት ያላት ከባዕድ ቀንበር ቅኝ ግዛት ነፃ የወጣች መሆኗ የሚታወቀው በባንዲራዋ ምልክትነት እንደሆነ እንደዚሁም አንድ ክርስቲያን በክርስቶስ አምኖ በጥምቀት ከዲያብሎስ ቁራኝነት ነፃ መውጣቱ ነፃነት ያለው አማኝ መሆኑ የሚታወቀው በማዕተቡ ምልክት ነው፡፡

ለደብዳቤ ለጽሑፍ ዓርማ ማኅተም ፊርማ እንደሚያስፈልገው ያም ለመተማመኛ እንደሚያገለግል ጥቅሙ ታውቆ ይሠራበታል፡፡

የክርስቲያን ማዕተብም በዚሁ አንፃር ብዙ ኃይማኖታዊ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡

መጀመሪያ በልቡ የሚያምነው ሃይማኖት ክርስትናን ሳያፍርበት በአንገቱ ባለው ማተብ መግለጹ በክርስትናው አለማፈሩን ክርስትናህን ካድ ማተብህን በጥስ የሚል ዓላዊ ቢመጣና ያንን ምልክት ዓይቶ ቢሰዋው የሰማዕትነትን ክብር ያገኝበታል፡፡ ያም ባይሆን በማተቡ ምልክትነት በመናፍቃንና በኢአማንያን የሚቀበለው ዘለፋ ስለ ክርስቶስ መስቀል እንደተሸከመ ያስቆጥረዋል፡፡

ሁለተኛው ከክርስቲያን ወገኖች ጋር ያለጥርጥር ማለትም የክርስቲያን መሆኑ ታውቆለት በቀላሉ ክርስቲያናዊ ተሳትፎውን ማከናወን ይችላል፡፡ ማተብ ከሌለው ግን ክርስቲያን ይሁን ያልተጠመቀ ስለማይታወቅ በሃይማኖት ዜጎች ዘንድ በቀላሉ ተቀባይነት ማግኘት አይችልም ሦስተኛ ከማይታወቅበት ሀገር በአደጋም ይሁን በበሽታ እንደወጣ ሞት ቢደርስበት በማዕተቡ መታወቂያነት የክርስቲያን ሥርዓት ተፈጽሞለት አስክሬኑ ተፈርቶ በቤተክርስቲን ሊቀበር ይችላል፡፡

ማተብ ከሌለው ምስከር በአካባቢው ለክርስቲያንነቱ ማረጋገጫ የሰው ያውም በሰበካው ቤተክርስቲያን የሚታመን ክርስቲያን ከሌለ እንደአልተጠመቀ ተቆጥሮ እንደ አሕዛብ ሥጋው ዱር ከበረሃ ወድቆ ይቀራል፡፡

ዐራተኛ ማተብና መስቀል ያለው ክርስቲያን በውሃ ዋና ወይም በበረሃ ጎዳና በውሃ የሚኖሩ ወይም በበረሃ ያሉ አጋንንት በቀላሉ ሊለክፉት አይችሉም፡፡ ይህም በየጠበሉ ሥፍራ በተአምራት ተረጋግጧል፡፡ አጋንንት የለከፋቸው ሰዎች ማተብና መስቀል አይወዱም፡፡ የሠፈረባቸው ርኩስ መንፈስ ማተብ እንዲበጥሱ መስቀል እንዲጥሉ ያደርጋቸዋል፡፡

ማተብ በሰይጣን ዘንድ ከተጠላ በአጋንንት ላለመለከፍ የማተቡ መኖር ይጠቅማል ማለት ነው፡፡

አንዳንድ ሰዎች የማዕተብ ሥርዓትን ለመቃወምና ዘመናውያን መስለው ለመታየት “ሃይማኖት በልብ ነው” ይላሉ ተሳስተዋል፡፡ ሃይማኖት የልብ ብቻ አይደለም የጠቅላላው ሕዋሳት ሁሉ ናት እግዚአብሔርን ስንወደውና ስናመልከው በልባችን ብቻ ሳይሆን በአፋችንም በአንገታችንም በጠቅላላው ሰብአዊ ተፈጥሮአችን ሁሉ መሆን ይገባዋል፡፡

ምክንያቱም እግዚአብሔር የጠቅላላው ሰውነታችን አምላክና ፈጣሪ ስለሆነ ነው፡፡ “ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ፡፡ “ማቴ ፲፤፴፪-፴፫በዚህ ቃል

መሠረት በኢአማንያን ዘንድ ክርስቲያን መሆናችንን የምንገልፀው በልባችን ብቻ ሳይሆን በቃላችንና በሥራችንም ጭምር ነው፡፡

በአንገታችንስ እንዳንመሰክርለት ማን ያግደናል? በአንገታችን ባለው ማዕተብም ለእግዚአብሔር እንመሰክራለን የስሙን ምልክት በአንገታችን እናኖራለን አናፍርበትም ፡፡ የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ በጥምቀታችን እንደምንመሰክር የጥምቀታችንንም አርማ በማተባችን እናረጋግጣለን፡፡ (ሮሜ ፲፤፮-፲፫፡፡ ኢዮኤል ፪፤፴፪፡፡ ሮሜ ፮÷፩-፭ ፣ ማቴ ፭÷፲፩-፲፪፡፡ ፩ጴጥ ፫÷፳፩-፳፪ ፩ጴጥ ፬÷፲፪-፲፮)ተመልከት፡፡

የማዕተብ ጥቅም

  1. የክርስትናን ማዕተብ በአንገት ማሰር በልብ ያለውን እምነት ሳያፍሩ በኃጢአተኛው ትውልድ መካከል ስለ ክርስቶስ መመስከር እንዲሁም ለሰይፍ ለመከራ መዘጋጀትን ማመልከት ነው፡፡

  2. ክርስቲያን ከሆኑ ምእመናን ጋር ሃይማኖታዊ የሆነውን ተሳትፎ በቀላሉ ለማከናወንና በክርስቲያን ወገኖች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት

  3. በጉዞ ላይ ያልታሰበ አደጋ ቢያጋጥምና ሞት ቢደርስ አደጋው ደርሶበት ያረፈው ክርስቲያን ቤተሰቦቹ ባይገኙ በቅርበት በማዕተቡ ክርስትናው ተረጋግጦ ጸሎተ ፍትሐት ተደርጎለት በእምነቱ ተከብሮ አስከሬኑ በክርስቲያኖች መካነ መቃበር ያርፋል፡፡

ወስበሐት ለእግዚአብሔር!

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top