ምን ዓይነት ጸሎት በየትኛው ሰዓት እንጸልይ

ምን ዓይነት ጸሎት በየትኛው ሰዓት እንጸልይ?

  1. የጸሎት ጊዜያት 

ልበ  አምላክ ነቢየ  ልዑል ቅዱስ ዳዊት”ስብዓ ለእለትየ እሴብሐከ በእንተ ኵነኔ ጽድቅከ ፣ስለ ጽድቅህ ፍርድ በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሃለው”/መዝ 118-164/ብሎ እንደተናገረ  ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ሰባት ጊዜ በየእለቱ  እንዲጸልይ ቤተ ክርስቲያን ታስተምረናለች፡፡ሰባቱ የጸሎት ጊዜያትም የሚከተሉት ናቸው፡፡

1.1   ጸሎተ ነግህ

ቅዱስ ዳዊት “አምላኬ አምላኬ በማለዳ ወደ አንተ እገሰግሳለሁ” መዝ 62÷11 እንዳለ ሌሊቱ አልፎ ቀኑ ሲተካ፣ከመኝታችን ስንነሳ ምንጸልየው የጸሎት ዓይነት ጸሎተ ነግህ ይባላል፡፡በዚህ ጊዜ የሚከተሉትን ምስጢራት እያሰብን መጸለይ ይገባናል፡፡

.ሌሊቱን አሳልፎ ቀኑን ስለተካልን እያመሰገንን ወጥተን እስክንገባ በሰላም ጠብቆ ውሎአችንን የተባረከ እንዲያደርግልን እንጸልያለን።

  • የመጀመሪያው ሰው አዳም የተፈጠረበትም ሰዓት በመሆኑ ያንን እያሰብን እንጸልያለን፡፡

  • የሰውን  ልጅ  በመዓልትና  በሌሊት  የሚጠብቁ  መላእክት  ለተልዕኮ  ሲፋጠኑ  የሚገናኙበት  ሰዓት  ነው፡፡የሌሊቱ  መልአክ  ሲሄድ የቀኑ መልአክ ሲቀርብና ሲተካ የሚገናኙበት በመሆኑ በዚህም ሰዓት እንጸልያለን፡፡

  • ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች በደል በጲላጦስ አደባባይ የቆመበት ሰዓት በመሆኑ እንጸልያለን።

  1.2 ጸሎተ ሠለስት (3 ሰዓት)

ከነግህ በመቀጠል የምንጸልየው ጸሎት ጸሎተ ሠለስት (የሦስት ሰዓት) ጸሎት ይባላል፡፡ይህ የጸሎት ጊዜ

. ሔዋን የተፈጠረችበት

. እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የቅዱስ ገብርኤልን ብሥራት የሰማችበት

. ጌታችን መድኃኒታችን  ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች ሲል በጲላጦስ አደባባይ የተገረፈበት

. ነቢዩ ዳንኤል ፊቱን ወደ ኢየሩሳሌም አቅጣጫ መልሶ የቤቱን መስኮት ከፍቶ የጸለየበት

. ለአባቶቻችን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ የወረደበት /በኢየሩሳሌም ጸንተው በመቆየታቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ ይህንን ታላቅ ጸጋ የተቀበሉበት /ሰዓት ነው፡፡

1.3  ቀትር(6 ሰዓት)

በእለቱ  እኩሌታ ላይ የምናገኘው ይህ ሰዓትም እንደዚሁ የጸሎት ጊዜ ነው፡፡ይህም ጊዜ

.ሰይጣን አዳምን ያሳተበት

.በዕፀ በለስ ምክንያት ለስሕተት የተዳረገውን አዳምን ለማዳን ጌታችን  መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ  አደባባይ  የዋለበት

.የቀን  እኩሌታ  በመሆኑ የፀሐይ ሙቀት የሚያይልበት የሰው ልጅ ለድካም የሚዳረግበት በዚህም ምክንያት አጋንንት የሚበረታቱበት  ጊዜ ነው።

.ስለዚህ የአዳምን ስሕተት፣ የዳግማዊ አዳም የኢየሱስ ክርስቶስ መሰቀልና መሞት፣እያሰብን የቀን እኩሌታ በመሆኑ መዳከማችንን  ተገን አድርጎ አጋንንት እንዳይሰለጥንብን  እየለመንን እንጸልያለን፡፡

 1.4  ተሰዓተ  ሰዓት (9 ሰዓት)

ዘጠኝ  ሰዓት  ላይ  አራተኛውን  ጸሎት  እናደርሳለን።በዚህ  ጊዜ

.ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምን ነጻ ለማውጣት በፈቃዱ ቅዱስ ሥጋውን ከቅድስት ነፍሱ የለየበት ሰዓት ነው።

  • ቅዱሳን መላእክት የሰው ልጆችን  በጎም ሆነ ክፉ ተግባር  ወደ ፈጣሪ የሚያሳርጉበት ነው

  • ቆርኖሌዎስ  የተባለ  መቶ አለቃ በጸሎት ጸንቶ ደጅ ሲጠና ከሰነበተ በኋላ ከፈጣሪው ምላሽ ያገኘበት ሰዓት ነው (ሐዋ  10÷ 9)

በዚህ ጊዜ የጌታችን የመድኃኒታችን  የኢየሱስ ክርስቶስን መከራ እና ሞት አያሰብን ቅዱሳት መላእክት ከፈጣሪያቸው  እንዲያስታርቁን እየለመንን  የቆርኖሌዎስ  እድል  እንዲገጥመን  እየተማጸንን  እንጸልያለን፡፡

1.5  ጸሎተ  ሰርክ (11 ሰዓት)

አምስተኛው  የጸሎት  ጊዜ  የሠርክ  ጸሎት  ነው፡፡ስለዚህ  የጸሎት  ሰዓት  ቅዱስ  ዳዊት  እንዲህ  ይላል፡፡”ጸሎቴን እንደ ዕጣን በፊትህ ተቀበልልኝ  እጅ  መንሳቴም  እንደ  ሠርክ  መሥዋዕት  ትሁን” (መዝ  140 ÷2)

  • ጌታችን  መድኃኒታችን  ኢየሱስ  ክርስቶስ ዓለምን  ለማዳን በፈቃዱ  ነፍሱን  ከሥጋው ከለየ በኋላ ወደ  መቃብር  የወረደበት ሰዓት  ነው፡፡ (ማቴ. 27÷ 57)

 1.6  ጸሎተ  ንዋም (የመኝታ  ጊዜ  ጸሎት)

ይህ  ጊዜ  ዕለቱን  በሰላም  አሳልፈን  ለሌሊቱ  ዕረፍት  የምንዘጋጅበት ነው፡፡በሰላም  ላዋለን  ፈጣሪ  በሰላም  አሳድረን  ብለን ራሳችንን በእምነት የምናስረክብበት ነው፡፡እኛ ተኝተን የሚሆነውን አናውቅም እርሱ ግን የማያንቀላፋ እረኛ  ስለሆነ  ይጠብቀናል።ስለዚህ  ከመተኛታችን በፊት  ሊሌሊቱን እንዲባርክልን እንጸልያለን።

በዚህ ጊዜ፡-

  • ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ  ክርስቶስ  ደቀ ዛሙርቱን በጌቴሴማኒ ጸሎት አስተምሯቸዋል፡፡

  • ቀኑ አልፎ  በሌሊቱ  ይተካል

ስለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለጸሎት ማስተማሩን እያሰብን እንጸልያለን፡፡ሰላም አሳድረንም ብለን ለፈጣሪ ራሳችንን  በእምነት  አደራ  እናስረክባለን፡፡

 1.7  መንፈቀ ሌሊት (እኩለ ሌሊት)

  • እኩለ  ሌሊትም  እንደ  ቀናቱ  የጸሎት  ሰዓታት  የተለያዩ  ትርጉሞች  አሉት ።

 ቅዱሰ ዳዊት ‘’መንፈቀ ሌሊት እትነሣእ ከመ እግነይ ለከ በእንተ ኵነኔ ጽድቅከ”“ስለ  ጽድቅህ ፍርድ  በእኩለ ሌሊት አመሰግነህ ዘንድ  እነሳለሁ”/መዝ 118-62/በማለት ይህ ሰዓት ከእግዚአብሔር ጋራ የሚነጋገርበት እንደሆነ ገልጿል፡፡

  • ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም ዋሻ የተወለደበት ሰዓት ነው።

  • ሞትን ድል አድርጎ በታላቅ ኃይልም የተነሳው በሌሊት ነው።

  • ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ ለፍርድ ሚመጣበትም ሰዓት ነው።

   ከዚህ  የተነሳ  ለእኛ  ሲል ከሰማየ  ሰማያት መውረዱን፣ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ  ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ መወለዱን  በማሰብ  ሞትን ድል እንደነሳልንም  አስበን  በማመስገን  ዳግመኛ  ለፍርድ ሲመጣ በቀኙ ከሚያቆማቸው ወገን እንዲያደርገን  እየለመንን በዚህ  ሰዓት  እንጸልያለን፡፡

 ሰባቱን  የጸሎት  ጊዜያት ጠብቀን መጸለይ ካልተቻለንስ?

በሰባቱ የጸሎ ሰዓታት የታቻለንን ያህል እንድንጸልይ  ታዘናል፡፡እነዚህን የጸሎት ሰዓታት በገዳም ያሉ መነኮሳት በየበረሃው የሚዞሩ ባሕታውያን  ይጠብቋቸዋል፡፡ይጸልዩባቸዋልም፡፡በከተማ  በሥራ  ምክንያት  ሩጫ በዝቶበት  በሁሉም  ሰዓት መጸለይ የማይችል ክርስቲያን ግን ቢያንስ በማለዳ ከእንቅልፉ ሲነሳ እና ማታ ወደ መኝታው ሲያመራ መጸለይ ይገባዋል።ጠዋት እና ማታ  በመጸለይ ከፈጣሪ ጋራ ያለው የአባትና ልጅ ግንኙነት እንዳይቋረጥ ማድረግ ይገባዋል፡፡

 ምን እንጸልይ?

በመደበኛነት ልንጸልያቸው የሚገቡ ጸሎታት  /በቤተክርስቲያናችን አባቶች በገዳማቱ በአድባራቱ የሚዘወተሩ  እለታዊ ጸሎታት/ እነኚህ ናቸው፡፡

1.መዝሙረ  ዳዊት

 መዝሙረ ዳዊት በገዳማት ከሚኖሩ አበው መነኮሳት  ባህታውያን ጀምሮ  በካህናት፣ምእመናን በሁሉም ዘንድ በየእለቱ የሚጸለይ ጸሎት ነው።አባቶች ከፊደል ቆጠራው ቀጥሎ ዳዊቱን ያጠኑና ከዚህ ጊዜ ጀምረው እየደገሙት፣እየጸለዩበት ይኖራሉ።ዳዊት  ሳይደግሙ  ወደ  ዕለታዊ  ተግባራቸው አይሰማሩም።መዝሙረ ዳዊት  እንደሌሎች ጸሎታት ሁሉ በየዕለቱ ተለይቶ የሚጸለይ አለው።ቀጥለን እንመልከት

ሰኞ ከ 1  – 30፣

ማክሰኞ ከ 31 – 60፣

ረቡዕ ከ  61 – 80፣

ሐሙስ ከ 81 – 110፣

አርብ  ከ 111 – 130፣

ቅዳሜ  ከ 131 – 150

እሁድ- ጸሎተ ነቢያት እና መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ይጸለያል፡፡

 አንድ ንጉሥ

መዝሙረ ዳዊትን ስንጸልይ ለዕለቱ የታዘዘውን ሃያ እና ሰላሳ መዝሙር ማድረስ ባንችል እንኳን አንድ ንጉሥ ማድረስ  ይገባናል። አንድ  ንጉሥ  የሚባለው፡-አስር መዝሙር  ነው፡፡ለምሳሌ ሰኞ አንድ ንጉስ ለማድረስ ከፈቀዱ ከ 1 – 10 ያለውን ያደርሳሉ፡፡ከማክሰኞ ከሆነ ደግሞ ከ 30 -40 ያውን የመጀመሪያውን አስር መዝሙር ያደርሳሉ ማለት ነው፡፡ይህን ሁሉ ማድረስ ያልተቻለው ግን የተወሰኑ መዝሙራትን መርጦ በየእለቱ ያደርሳል፡፡

2. ውዳሴ ማርያም

ውዳሴ ማርያም ከተቻለ የሰባቱን ዕለታት ካልተቻለ የእለቱን ማድረስ ተገቢ ነው።የዘወትር ጸሎት ካደረስን በኋላ የዕለቱን ውዳሴ ማርያም አድርሰን ይዌድስዋ መላዕክትን  ደግመን ከእመቤታችን  በረከት ተሳታፊ መሆን ተገቢ ነው፡፡በዋልድባ የሚኖሩ መነኮሳት ውዳሴ ማርያም ከቅዳሴ ማርያም ሳያደርሱ ውለው አያድሩም፡፡በየአብነት ትምህርት ቤቱ የሚገኙ መምህራንና ተማሪዎች እና በየገዳማት ያሉ መነኮሳት ሁሉ ውዳሴ ማርያምን በየዕለቱ ያደርሳሉ፡፡እኛም ከአበው ተምረን ማታ ከመኝታ በፊት ወይም ጠዋት ስንነሳ ይህን ጸሎት ማድረስ ተገቢ ነው፡፡

3. ወንጌል ዘዮሐንስ

የዮሐንስ ወንጌልን በየምዕራፍ ከፋፍለን በየእለቱ ማንበብ ሌላው  ጸሎት ነው፡፡አባቶች ይህንን ጸሎት በየእለቱ እያደረሱ ብዙ  ተጠቅመውበታል።

 4. ሌሎች ጸሎታት

ውዳሴ አምላክ፣ ሰኔ ጎለጎታ፣ መልክአ ኢየሱስ፣ መልክአ ማርያም ፣ በመዝገበ ጸሎት እንዲሁም በመዝሙረ ዳዊት መጽሐፍት ላይ ያሉትን ሌሎች ጸሎታት፣እንዲሁም ገድላት፣ተአምራትን፣እንደ ችሎታችን በየዕለቱ እናደርሳለን፡፡ቢያንስ ግን ይህ ሁሉ ባይሆንልን ከላይ የጠቀስነውን  የመዝሙረ  ዳዊትና ፣ውዳሴ ማርያምን  ጸሎት ማድረስ ይገባናል፡፡

 አጭር ጸሎት

 በተቻኮልን እና መጻሕፍትን ለማንበብ  ጨርሶውን  ጊዜ  በማይኖረን  ሰዓት  ይህንን  እንድንጸልይ አንዳንድ አባቶች ይመክሩናል።አቡነ ዘበሰማያት፣ጸሎተ ሃይማኖት፣ሰላም ለኪ /ስለ ውዳሴ ማርያም ፈንታ/፣አቡነ ዘመሰማያት፣አንድ ከመዝሙረ ዳዊት/ መዝሙር 150/ በመዝሙረ ዳዊት ፈንታ/በመጨረሻም አቡነ ዘበሰማያት ማድረስ ብንችል መልካም ነው ።ጸሎተ ሃይማኖት የህይማንት መግለጫ በምህኑ እንጸልየዋለን። በመካከል ሰላም  ለኪ በመድገማችንም  የውዳሴ  ማርያም  በረከት  ይደርሰናል።  መዝሙረ  ዳዊት  150  ስናደርስ  ደግሞ  ሁሉንም  መዝሙራት  የደገምን  ያህል  ይሆንልንና  የዳዊቱን  በረከት  እናገኛለን፡፡ይህንን ሁሉ ማድረስ ካልተቻለን  ግን ቢያንስ  ጌታችን  ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን አቡነ ዘበሰማያት ብለን ከቤታችን ልንወጣ ይገባናል።አጭር ጸሎት ከሥፍራ ሥፍራ ሊለያይ ይችላል፡;ዘጠኝ ሰላም ለኪ፣አስራ ሁለት አቡነ ዘበሰማያት በገዳማት ያሉ አበው ያደርሳሉ።

     አጭር  ጸሎትን  እነደ  መደበኛ  ማድረግ   ለፈተና  ያጋልጣል

አጭር  ጸሎት የምንጸልየው በጣም በተቸገርንበት፣ጊዜ ባጣንበት  ሰዓት ነው።ይህንን  ጸሎት እንደመደበኛ ይዞ  በየእለቱ  አንድ አቡነ ዘበሰማያት ብቻ መድገም ግን ስንፍና እንዳይሆን ያስፈራል።ይልቁንም በክርስትና ሕይወት ጅማሬ ላይ ያሉ  ምእመናን/ወጣንያን/ክርስትናውን እስኪላመዱ ጸሎታቸው አጭር ሊሆን ይችላል።እየቆዩ ሲሄዱ ግን በጸሎት እየበረቱ ወደ መደበኛው ጸሎት መድረስ አለባቸው።ሁል ግዜ ወተት መመኘት  ሁል ግዜ  አልበረታውም  እያሉ  አጭር  ጸሎት እያደረሱ መተኛት  ተገቢ አይደለም።ይህ አይነቱ አካሄድ  የእግዚአብሔርን ቸርነት  ለስንፍና ምክንያት አድርጎ መጠቀምም ነው።ከዚህ ጋር በቤተክርስቲያን አገልገሎት ላይ ያለንም ዳዊት መድገም ውዳሴ ማርያም ማድረስ ይጠበቅብናል።የሰንበት ት/ቤት  ወጣቶች ፣ዲያቆናት፣ቀሳውስት፣ሰባክያነ ወንጌል፣መዘምራን……እነዚህን ጸሎታት መጸለይ ይጠበቅባቸዋል።አልያ ግን እያወቅን ጸሎት ማድረስ እንዳለብን ብዙ ጊዜ ተምረን እንዳልተምርን ቸል ብንል ለፈተና መጋለጥ ይመጣል።ከእግዚአብሔርም  ቸርነት  እንድንርቅ ያደርገናል።

አቡነ  ዘበሰማያት  የጸሎታችን  መነሻና  መድረሻ

ጸሎት ስናደርስ የጸሎታችን  መነሻ (መጀመሪያ) አቡነ ዘበሰማያት ነው፡፡በመካከል ጸሎት  አቋርጠን  ከሰው  የምንነጋገርበት ጉዳይ ቢገጥመን በአቡነ ዘበሰማያት ማሰር ተገቢ ነው፡፡በአቡነ ዘበሰማያት አስረን የገጠመንን  ጉዳይ  ፈፅመን እንመለሳለን፡፡ከዚያም አቡነ ዘበሰማያት ብለን ካቆምንበት እንቀጥላለን።ጸሎታችንን  በአቡነ ዘበሰማያት ሳናስር በመሃል  እንዳሻን  እንዳናቋርጥ አበው  ያስተምሩናል፡፡

የማህበር  ጸሎት

 በቤታችን ከምንጸልየው ጸሎት በተጨማሪ በቤተክርስቲያን ተገኝተን ጸሎት ማድረስ ተገቢ ነው።ቤተ ክርስቲያን  የእግዚአብሔር  ቤት  እንደመሆና  በእርሱአ የሚጸለይ ጸሎት ከጸሎታት ሁሉ የላቀ ነው።በካህናት እየተመራ ፣በሕብረት ሆነን የምናደርሰው በመሆኑ ታላቅ  ኃይል አለው።እግዚአብሔር በቤተ መቅደስ የምንጸልየውን ጸሎት  እንደሚሰማ  ሲያመለክተን እንዲህ በማለት  ነግሮናል።”አሁንም በዚህ ሥፍራ  ለሚጸለይ  ጸሎት ዓይኖቼ  ይገለጣሉ ፣ጆሮቼም ያደምጣሉ።ስሜ ለዘላለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤት  መርጫለሁ  ቀድሻለሁም  ዓይኖቼ  እና  ልቤም  ዘወትር  በዚያ  ይሆናሉ።”/2 ዜና መዋ 7-15/ ከዚህ አንጻር  በቤተ መቅደስ እየተገኘን መጸለይ  ተገቢ ነው።በሰንበት ቀን  ኪዳን ማድረስ ፣ ቅዳሴ ማስቀደስ  የመጀመሪያው እና ዋነኛው ተግባራችን  መሆን አለበት።በሰንበት  ያለ በቂ ምክንያት ቅዳሴ  የሚያስታጉል  በቀደሙ አባቶች /አባ ሚካኤል ወአባ ገብረኤል/ቃል  መወገዙን  የተአምረ ማርያም መቅድም ይነግረናል።ከዚህ ጋር በሰዓታት ፣በማኅሌት ጸሎታት  ላይ በመገኘት  ቤተ ክርስቲያናችን  ካዘጋጀችልን የማይጠገብ ማእድ ልንሳተፍም ይገባናል።

ጸሎት

መጋቢት 18/2004 ዓ.ም.  በመ/ር ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ

ጸሎት ጸለየ፡- ለመነ፣ ጠየቀ አማለደ፣ ማለደ ካለው የግዕዝ ቃል የወጣ ቃል ነው፡፡ ጸሎት ማለት ጠቅለል አድርገን ስንመለከተው ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር እግዚአብሔርን ማመስገን መለመን፣ መጠየቅ፣ መማለድ፣ መማፀን ነው፡፡ “ጸሎት ብሂል ተናግሮ ምስለ እግዚአብሔር፡፡” አባታችን አዳምም ከመላእክት ተምሮ በየሰዓቱ ይጸልይ ያመሰግን ነበር፡፡ ዲያብሎስ በእባብ አድሮ ወደ አዳም በመጣ ጊዜ ጸሎት እያደረገ ስለነበር ዲያብሎስን ድል ነሥቶታል ሔዋንን ግን ሥራ ፈትታ እግሯን ዘርግታ ስለአገኛት ድል ነስቷታል፡፡

ጸሎት ሰማእታት ከነደደ እሳት፣ ከተሳለ ስለት፣ ከአላውያን መኳንንት፣ ከአሕዛብ ነገሥታት ከዲያብሎስ ተንኮል እና ሽንገላ ዲያብሎስ በእነርሱ ላይ ከአጠመደው አሽከላ የዳኑበት ጋሻ ነው፡፡ ኤፌ.6፥10 21 ጸሎት፣ ሰው አሳቡን ለእግዚአብሔር የሚገልጥበት እግዚአብሔርም የሰውን ልመና ተቀብሎ ፈቃዱን የሚፈጽምበት ረቂቅ ምስጢር ነው፡፡

የጸሎት መሠረቱ “ዕሹ ታገኛላችሁ ለምኑ ይሰጣችኋል ደጁ ምቱ ይከፈትላችኋል” የሚለው የጌታችን ትምህርት ነው ማቴ.7፥7

ጸሎት፡- በሦስት ክፍል ይከፈላል

  1. ጸሎተ አኰቴት

  2. ጸሎተ ምህላ

  3. ጸሎተ አስተብቊዖት

  1. ጸሎተ አኰቴት፡- ማለት እግዚአብሔርን ከሁሉም አስቀድሞ ስለተደረገልን ነገር በማመስገን የሚጀመር ጸሎት ነው ይህም ዓይነት ጸሎት የቅዱስ ባስልዮስን የምስጋና ጸሎት የመሰለ ነው፡፡

“ነአኲቶ ለገባሬ ሠናያት ላዕሌነ እግዚአብሔር መሐሪ”

“ለእኛ በጎ ነገርን ያደረገ ይቅርባይ እግዚአብሔር አምላካችንን እናመሰግነዋለን” ይልና ምክንኀያቱን ሲገልጥ ጠብቆናልና፥ አቅርቦናልና፥ ወደ እርሱም ተቀብሎናልና፥ እስከዚችም ሰዓት አድርሶናልና” ይላል፡፡ /ሥርዐተ ቅዳሴ/ ይህ ጸሎት የምስጋና ጸሎት /ጸሎተ አኰቴት/ ይባላል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ይህንን የምስጋና ጸሎት ለፊልጵስዮስ ክርስቲያኖች ሲጽፍላቸው “ነገር ግን በሁሉ ነገር ጸልዩ ማልዱም እያመሰገናችሁም ልመናችሁን ለእግዚአብሔር ግለጡ” ይላል፡፡ ፊል.4፥6 ዳግመኛም “ስለእናንተ በኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ ስለተሰጣችሁ ጸጋ ዘወትር እግዚአብሔርን አመስግነዋለሁ” 1ቆሮ.1፥4 ብሎ ከመለመን አስቀድሞ እግዚአብሔርን ማመስገን አስፈላጊ መሆኑን አስተምሯል፡፡ በዚህ መሠረት ሰው የተደረገለትን በጎ ነገር ሁሉ በማሰብ ፈጣሪውን ማመስገን ከማመስገንም ቀጥሎ የሚያስፈልገውን ከፈጣሪው መለመን አስፈላጊ ነው፡፡

ከቅዱስ ጳውሎስ የምንማረው ለእኛ ስለተደረገልን ብቻ ማመስገንን አይደለም፤ ሌሎች ስለተደረገላቸውም ማመስገን ተገቢ መሆኑን እንጂ፡፡ “ለእናንተ ስለተሰጣችሁ ጸጋ ዘወትር እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ” ሲል ለወገኖቹ ስለተደረገላቸው በጎ ነገር በደስታ ማመስገኑ ነው፡፡ ክርስትና ማለት ለእኔ ብቻ ማለት ሳይሆን ለሌሎችም መኖር፣ ለሌሎች በተደረገው የእግዚአብሔር ስጦታም ደስ መሰኘት ነው፡፡ ይህን የምስጋና ጸሎት /ጸሎተ አኮቴት/ ብዙ አባቶች፣ እናቶች ተጠቅመውበታል፡፡ ለምሳሌም ያህል ዘካርያስንና ኤልሳቤጥን መመልከት እንችላለን፡፡ ቅድስት ኤልሳቤጥ እግዚአብሔር ያደረገላትን በጎ ነገር ስትመሰክር “እግዚአብሔር በዚህ ወራት ከሰው ስድቤን ያርቅ ዘንድ በጎበኘን ጊዜ እንዲህ አደረገልኝ” ብላለች፡፡ ሉቃ.1፥25 እግዚአብሔር ጎበኘኝ ብላ ቸርነቱን አደረገለኝም በማለት የተደረገላትን መልካም ስጦታ ዮሐንስን መጽነሷን ገልጣ አመስግናለች፡፡ ዘካርያስም እንዲሁ አመስግኗል፡፡ “ያን ጊዜም አፉ ተከፈተ አንደበቱም ተናገረ እግዚአብሔርንም አመሰገነ” ሉቃ.1፥65 “ከዚህ ጊዜ ያደረስከኝ፥ ከደዌ የፈወስከኝ፥ ዮሐንስን የሰጠኸኝ ብሎ ፈጣሪውን አመስግኗል በመቀጠልም ይቅር ያለን ለወገኖቹም ድኅነትን ያደረገ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን ከባሪያው ከዳዊት ቤት የምንድንበትን ቀንድ አስነሣልን፡፡” ሉቃ.1፥68 በዘካርያስ ጸሎት ውስጥ ምስጋናውን አስቀድሞ ትንቢቱን አስከትሎ እናገኘዋለን፡፡ በዚህ ምስጋናውና ትንቢቱ አምላክ ለእኛ ያደረገው የቤዛነቱን ሥራ በመግለጥ ሲያመሰግን እንመለከታለን፡፡

2. ጸሎተ ምህላ፡- ጸሎተ ምህላ ስለፈውሰ ሕሙማን …… ስለ ሀገርና ስለነገሥታት ስለ ጳጳሳት፣ ካህናት ዲያቆናት፣ ምዕመናን ሕይወት ቸነፈር፣ ጦርነት፣ ረሀብ፣ ድርቅ ወይም ሌላ አስጊ ነገር በሆነ ጊዜ በብዛት፣ በማኅበር የሚጸለይ ጸሎት ነው፡፡ የምህላ ጸሎት ሲጸለይ በእስራኤል ላይ ቸነፈር በተነሣ ጊዜ አሮን በሽተኞን ባንድ ወገን ጤነኞችን ባንድ ወገን አድርጎ የክህነት ልብሱን ለብሶ ማዕጠንተ ወርቁን ይዞ በራስህ የማልክላቸውን አብርሃምን፣ ይስሐቅን፣ ያዕቆብን አስበህ የወገኖችህን ኀጢአት ይቅር በል”  እንደጸለየላቸው ነው፡፡ ዘኁ.16፥46-50

ዛሬም ካህናት ከጠቀስናቸው አስጊ ነገሮች ማንኛውም በሀገር ላይ ቢመጣ ወደ ሀገር እንዳይገባ ገብቶ ቢሆን ከፍ ያለ ጉዳት እንዳያመጣ የክህነት ልብስ ለብሰው ማዕጠንቱ ይዘው ሥዕለ ማርያም፣ መስቀል አቅርበው ማኅበረ ክርስቲያንን ሰብስበው፣ ኢየሱስ ክርስቶስን “ስለእኛ ከድንግል ማርያም መወለድህን ስለእኛ መሠቀል መሞትህን አስበህ የህዝብን ኀጢአት ይቅር በል ከመዓት ወደ ምሕረት ተመለሰ” እያሉ በምህላ ይጸልያሉ፡፡

የምህላ ጸሎት መአትን መቅሰፍትን ይመልሳል ጦርን፣ ቸነፈርን ያስታግሳል መሠረቱም፡፡
“ጾም ለዩ ምህላ ስበኩ” ያለው ቃል ነው፡፡ ይህ ጸሎት በሰላም ጊዜ ሰላሙ ዘላቂ እንዲሆን በጦርነት ጊዜ ለመከላከያነት ዋና መሣሪያ ነው፡፡ ስለዚህ አጥብቀን ልንከተለው ይገባል፡፡

የምህላ ጸሎት ነገሠታት ከዙፋናቸው ወርደው ወንድ ሙሽራ ሴት ሙሽራ ከጫጉላቸው፣ ከመጋረጃቸው ለምግብ የደረሱ ልጆች ከምግብ ለምግብ ያልደረሱ ከጡት ተከልክለው ሕዝብ ሁሉ ምንጣፍ ለብሰው አመድ ነስንሰው የሚጸልዩት ከፍተኛ ጸሎት ነው ኢዩ.2፥12-18፣ ዮና.3፥5

3.    ጸሎተ አስብቊዖት

ይህ ጸሎት አንድ ሰው ስለሚፈልገው ነገር ቦታ ለይቶ ሱባኤ ገብቶ የሚጸልየው ጸሎት ነው፡፡ ይህ ጸሎት በተለይ ጣዕመ ጸጋን በቀመሱ በተባሕትዎ፣ በምናኔ በገዳም በሚኖሩ አበው ዘንድ የተለመደና የሚደረግ ጸሎት ነው፡፡ ወጣንያን እግዚአብሔርን ጠይቀው አድርግ አታድርግ የሚል መልስን አይጠብቁም፡፡ ፍጹማን አባቶች ግን እግዚአብሔር ጠይቀው አድርግ ወይም አታድርግ የሚል ፈቃደ እግዚአብሔርን ሳይቀበሉ የሚያደርጉት ነገር የለምና ቦታ፣ ጊዜ ወስነው ፈቃደ እግዚአብሔር ይጠይቃሉ፡፡ ይህ ጸሎተ አስተብቊዖት ይባላል፡፡ ይህም ማለት መላልሶ ደጋግሞ ያለ ዕረፍት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሚደረግ ጸሎት ነው፡፡ ለምሳሌ ትልቁ መቃርስ ዓለምን ዞሮ ለመጎብኘት ለተከታታይ አምስት ዓመታት እግዚአብሔርን ከለመነ በኋላ እየዞረ መካነ ቅዱሳንን እንዲጎበኝ ከእግዚአብሔር ፈቃድ አግኝቷል በዚህም ከእርሱ ከገድል በትሩፋት የሚበልጡ መናንያን በማግኘቱ መነኮሳትማ እነርሱ እንጂ እኔ ምንድን ነኝ? እያለ ራሱን እየወቀሰ እንደተመለሰ በመጽሐፈ መነኮሳት ተጽፎ እናገኛለን፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን “መስተበቊዕ” የሚባል የጸሎት ክፍል፡፡ አለ ይህ ጸሎት በካህናት አባቶቻችን ስለሙታን፣ ስለሕያዋን፣ ስለነገሠታት፣ ስለ ጳጳሳት ስለ ንዑሰ ክርስቲያን፣ ስለ ምእመናን መባዕ ስለሚያቀርቡ ስለነጋድያን፣ ስለዝናም ስለ ወንዞች የሚጸለይ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የጸሎት ክፍል ነው፡፡

ጠቅላላውን በቤተ ክርስቲያን የሚጸልዩ ጸሎታት ጸሎተ ፍትሐት፣ ጸሎተ ተክሊል፣ ጸሎተ ህሙማን፣ ጸሎተ ቅዳሴ፣ ጸሎተ ሰዓታት፣ የግል ጸሎት፣ የማኅበር ጸሎት እነዚህ ሁሉ ከላይ ከዘረዘርዓቸው ሦስቱ የጸሎት ክፍሎች አይወጡም፡፡ ከጸሎተ አኰቴት ከጸሎተ ምህላ፣ ከጸሎተ አስተበቊዖት ይመደባሉ፡፡ እነዚህን ጸሎታት በሰቂለ ኅሊና በአንቃዕድዎ /ዐይንን ወደ እግዚአብሔር በማንሳት/ መጸለይ ታላቅ ዋጋ የሚያሰጥ ከሰይጣን ወጥመድ የሚታደግ ሕይወትን የሚስተካከል ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቅ አጋንንትን የሚያርቅ ኀይለ እግዚአብሔርን ለሚጸልየው የሚያስታጥቅ መላእክትን የሚያስመስል ነው፡፡

 

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top