ምሥጢረ ጥምቀት

ምሥጢረ ጥምቀት

ጠመቅ ማለት መነከር፣ መዘፈቅ፣ ውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣት ማለት ነው፡፡ ምሥጢረ ጥምቀት የሥላሴ ልጅነት የሚሰጥበት እና የኃጢአት ሥርየት የሚገኝበት ምሥጢር ነው፡፡

የጥምቀት አመሠራረት

የምስጢረ ጥምቀት መሥራች ጌታችንና አምላካችን መድድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። የመሠረተውም በሦስት መንገድ ነው። እነርሱም፡-

 

በተግባር፡- ራሱ ተጠምቆ እንድንጠመቅ አስተምሮናል /አርአያ ሆኖናል/ ማቴ 3፡13

በትምህርት፡- “ያመነ የተጠመቀ ይድናል” / ማር 16፡16 / ”እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔር መንግሥት ሊያይ አይችልም” / ዮሐ 3፡3-6 /

በትዕዛዝ፡- “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኌቸው ደቀ መዛሙርት አድርጔቸው”

በማለት ለቅዱሳን ሐዋርያት ትዕዛዝ በመስጠት መስርቶታል። / ማቴ 28፡19-20 /

 

የጥምቀት አከፋፈል / ዓይነቶች /

ጥምቀት በሁለት ይከፈላል።

ሀ. የንስሐ ጥምቀት ማቴ 3፡11 ፡ ማር 1፡4 ፡ ሐዋ 19፡4

ለ.ልጅነት የምታሰጠዋ ጥምቀት ገላ 3፡26 ፡ ቲቶ 3፡5 ፡ 1ኛጴጥ 1፡23

ልጅነት የምታሰጠዋ ጥምቀት አንዲት ናት / ኤፌ 4፡4-5 / ነገር ግን በሦስት ዋና ዋና መንገዶች ልትፈጸም ትችላለች። እነርሱም

የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት፡- ማለት በውሃ ሳንጠመቅ እግዚአብሔር በፍቃዱ ጸጋውን በመላክ የሚሰጠን ልደት ነው። ለዚህም ምሳሌ የሚሆነን ቅዱሳን ሐዋርያት የተጠመቁት ጥምቀት ነው። ሉቃ 3፡16 ፡ ሐዋ 1፡5 ፡ ሐዋ 2፡1-4 ፡ 1ኛ ቆሮ 12፡13

የውሃ ጥምቀት፡- ማለት በካህናት አማካኝነት በተጸለየበት ውሃ ውስጥ በሥላሴ ስም ተጠምቀን በመንፈስ ቅዱስ ግብር ከእግዚአብሔር የምንወለድበት ነው። ዮሐ 3፡3-6

የደም ጥምቀት፡- ይህ የሰማዕታት የጥምቀት ዓይነት ነው። የክርስትናን እምነት በመማር ላይ ሳሉ ወይም ተምረው ሳይጠመቁ ወይም ሁለቱንም ሳያውቁ ክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስ ብለው መሥዋዕት መሆናቸውን ተመልክተው “የእነዚህ የክርስቲያኖች እምነት እውነተኛ ነው” በማለት መስክረው በሰማዕትነት የሚሞቱ ሰዎች ደማቸው /ስቃያቸው/ በእግዚአብሔር ቸርነት እንደ ጥምቀት ይቆጠርላቸዋል። ኃጢአታቸውም ይሰረይላቸዋል።

 

 

የጥምቀት አፈጻጸም

የተጠማቂው ግዴታ፡- ተጠማቂው ንዑሰ ክርስቲያን ከሆነ መሠረታዊ የሃይማኖት ትምህርቶችን ተምሮ እምነቱ የተመሰከረለት መሆን አለበት። ሕጻናት የሆኑ እንደሆኑ ግን ለሕጻናቱ የክርስትና እናትና አባት ሊሆኑ የመጡት ሰዎች ስለሕጻናቱ እምነት መስክረውላቸው እንዲጠመቁ ይደረጋል።

 

አጥማቂው ማን ነው

እንዲያጠምቁ ስልጣን ያላቸው ከክህንት ደረጃዎች ውስጥ ኢጲስቆጶስና ቀሳውስት ብቻ ናቸው ዲያቆናት እንዲያጠምቁ አልተፈቀደላቸውም። ማቴ 28፡19 እና ፍት ነገ አን 3 ተመልከቱ።

 

የክርስትና ስም አወጣጥ

ስም አንድ ሰው ከሌላው ተለይቶ የሚታወቅበት ነው። አንድ ክርስቲያን ሁለት ዓይነት ስሞች ሊኖሩት ይችላል።

አባትና እናት የሚያወጡለት ስም / የተጸውኦ ስም /

በጥምቀት ጊዜ የሚወጣለት ስም / የክርስትና ስም /

 

በክርስቶስ የሚያምን ሰው ክርስቲያን ሲባል እምነቱ ደግሞ ክርስትና ይባላል። ክርስቲያን ማለት የክርስቶስ ወገን የሆነ ማለት ነው። በመሆኑም በክርስቶስ አምነን በሥላሴ ስም መጠመቃችንን የሚገልጸው ስም ስመ ክርስትና ይባላል። ስያሜውም ተጠማቂው ከተጠመቀበት ዕለት ጋር ተያይዞ ሊሰየም ይችላል።

 

የክርስትና አባትና እናት

በኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ በ40 እና በ80 ቀናቸው ለሚጠመቁ ሕጻናት ስለ እምነታቸው ባለው ነገር ሁሉ ኃላፊነት የሚወስዱ የክርስትና አባትና እናት እንዲኖራቸው ያደረጉት በ4ኛው መ/ክ/ዘ የነበረው የቤተ ክርስቲያናችን የመጀመሪያው ኢጲስ ቆጶስ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ናቸው። ዓላማውም መንፈሳዊ ዝምድናን / አበ ልጅነትን / ማጠናከሪያ መንገድ ነው። በአበ ልጅነት የተዛመዱ ሰዎች በጋብቻ መዛመድ አይችሉም። በሥጋ የተዛመዱ ከ7ተኛ የዝምድና ሐረግ በኌላ መጋባት የሚፈቀድ ሲሆን በአበ ልጅ ግን የተዛመደ ግን የቁጥር ገደብ የለውም / ፈጽሞ መጋባት አልተፈቀደለትም / ይህ የሚያሳየው ከሥጋ ዝምድና ይልቅ ክብር የሚሰጠው ለመንፈሳዊ ዝምድና መሆኑን ነው።

 

ከክርስትና አባትነትና እናትነትን የሚከለክሉ ነጥቦች

የሥጋ ዝምድና ያላቸው

የጋብቻ ዝምድና ያላቸው

ዕድሜያቸው ለማስተማር ለማሳመን ያልደረሰ

እምነት ትምህርት ችሎታ የሌላቸው

እምነታቸው ከተጠማቂው ጋር ተመሳሳይ ያልሆነ

የጾታ ሁኔታ በተመለከተ ወንድ ወንድን ሴት ሴትን ያነሣል እንጂ ወንድ ሴትን፡ ሴት ወንድን ክርስትና ማንሣት አይፈቀድላቸውም

 

የክርስትና አባትና እናት ያለባቸው ኃላፊነት

ክርስትና ያነስዋቸው ልጆች በሥጋ ከወለድዋቸው ልጆች ሳይለዩ ሕጻናቱ ዕድሜያቸውም ለትምህርት ሲደርስ መሠረታዊ የሃይማኖት ትምህርት የማስተማር ግዴታ እንዳለባቸው ቃል ይገባሉ። በገቡት ቃል መሠረት በተግባር የመተርጎም ኃላፊነት አለባቸው።

 

ማዕተብ /ክር/ ማሰር

ማዕተብ – ዐተበ ካለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም አመለከተ ማለት ነው። ስለዚህ ማዕተብ ማለት ምልክት ማለት ነው። በሃይማኖት አምነው ለተተመቁ ክርስቲያኖች የሚሰጠ ምልክት / መታወቂያ / ወይም ማኅተም ስለሆነ። ስለ ማዕተብ በመጽሐፍ ቅዱስ የተለያየ ምሳሌዎች ተጠቅሰዋል። በብሉይ ኪዳን የነበሩ አባቶች ለእምነታቸው መገለጫ ምልክት ነበራቸው። ለምሳሌ ለአበ ብዙኃን አብርሃም ግዝረት ተሰጥቶት ነበር። ሮሜ 4፡13 ፡ ዘፍ 17፡9-14

የማዕተበ ሦስት ዓይነት ቀለም ምክንያቶች፡- ይህ የሦስትነት ምሳሌ ነው። ሦስቱ ክሮች ደግሞ በአንድ ተገምደው መሠራታቸው የአንድነቱ ምሳሌ ነው።

ክርስቲያን ማዕተብ ማሰሩ ያለው ተቀሜታ፡-

ስለ ክርስቲያንነቱ ሳያፍር ይመሰክርበታል

አጋንንትን ድል ይነሣበታል – ተጸልዮበት ተባርኮ የሚታሠር ነውና

ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ያገኝበታል

 

በምስጢረ ጥምቀት የሚታይ አገልግሎት

ተጠማቂው ውሃ ውስጥ ብቅ ጥልቅ ሲል

ሥርዓተ ጸሎቱ

ተጠማቂው ነጭ ልብስ ሲጎናጸፍ ወዘተ. . .

 

በምስጢረ ጥምቀት የሚገኝ የማይታይ ጸጋ

ውሃው ወደ ማየ ገቦነት ሲለወጥ

የእግዚአብሔር ልጅነትን ሲያገኝ

የመንፈስ ቅዱስ ጸጋን ፡ ንጸሕናን ቕዽስናን ገንዘብ ሲያደርግ ወዘተ. . .

ጥምቀት ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማህፀነ ዮርዳኖስ ተወልደን የሥላሴን ልጂነት የምናገኝበት ምሥጢር ነው።

ማር 16÷16 ==== ዩሐ 3÷5 === ቲቶ 3÷5 === 1ፔጥ 3÷21

 

ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በ30 አመቱ በዮርዳኖስ ፣ በዩሐንስ እጂ ተጠምቆ ጥምቀታችንን መሰረተልን፣ ባረከልን፣ ቀደሰልን።

ማቴ 3÷15   ቆላሲስ 2÷14

የሚከተሉት በጥምቀት የሚገኙ የማይታዩ ጸጋዎች ናቸው፡

ድኅነት

“ያመነ የተጠመቀ ይድናል” ማር. ፲፮፥፲፮፡፡ የድኅነት ባለቤት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በግልጽ እንደተናገረው ዘላለማዊ ድኅነትን ለማግኘት የሚሻ ሁሉ ወልድ ዋሕድ በምትለው ሃይማኖት አምኖ መጠመቅ ግድ

ይለዋል፡፡

ከጌታ ከቃሉ የተማረ ቅዱስ ጴጥሮስ የመምህሩን ትምህርት መሠረት አድርጎ “ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ፤ የእግዚአብሔር ትዕግስት በኖኅ ዘመን በቆየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም፡፡

ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም” ብሏል፡፡

፩ኛ ጴጥ. ፫፥፳-፳፩፡፡ ኖኅና ቤተሰቡ የዳኑበት ውኃ ምሳሌነቱ የጥምቀት መሆኑን ገልጾ አሁንም በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ያመኑ ሁሉ በጥምቀት ድኅነትን እንደሚያገኙ በግልጽ ቃል ተናግሯል፡፡

መዳን ስንል

የእግዚአብሄርን መንግሥት ወርሶ የዘላለም ሕይወት ባለቤት መሆን ማለት ነው፡፡ ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ አይሁድ ለነበረው ለኒቆዲሞስ ዘርግቶለት በነበረው የሌሊት

የትምህርት መርሐ ግብር ትምህርቱን በተመስጦ ኅሊና በሰቂለ ልቡና ይከታተል ለነበረው ለኒቆዲሞስ የድኅነት በሩ ጥምቀት እንደሆነ ገልጾለታል “እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ

እግዚአብሔር መንግስት ሊገባ ይችልም” ዮሐ. ፫፥፭፡፡

ዳግም ልደት

 

ዳግም ልደት ያስባለው ከሥጋ ልደት የተለየ በመሆኑ ነው፡፡ በአዳምና በሔዋን ስህተት ምክንያት አጥተነው የነበረውን የልጅነት ጸጋ የምናስመልሰው በውኃ በምናደርገው ጥምቀት ነው፡፡ ዳግም ከሥላሴ የምንወለደው በውኃ በምናደርገው ጥምቀት ነው ጌታችን “እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አይገባም” ዮሐ. ፫፥፭ በማለት ለኒቆዲሞስ መናገሩን ልብ ይሏል፡፡ ጌታችን እንደተናገረው ጥምቀት የልጅነትን ጸጋ የምናገኝበት ምሥጢር ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ጥምቀት ዳግም ከእግዚአብሄር

የምንወለድበት ታላቅ ምሥጢር መሆኑን እንዲህ ሲል አስተምሯል “ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፉ ዘር አይደለም” ፩ኛ ጴጥ. ፩፥፳፫፡፡ ይህ ጥምቀት የዘላለም ሕይወት እንደሚያሰጥ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ደግሞ

“ነፍሴም ስለ እርሱ በሕይወት ትኖራለች” አለ፡፡ መዝ. ፳፩፥፳፱”፡፡ አቡቀለምሲስ ዮሐንስም “እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ” ብሏል ዮሐ ፩፥፲፫፡፡ ጌታችን በግልጽ ቃል እንደተናገረው የልጅነት ጸጋ የሚገኘው በውኃ

ውስጥ ብቅ ጥልቅ በማድረግ በሚፈጸመው ገቢር እንጂ አንዳንዶች ከልቦናቸው አንቅተው እንደሚናገሩት ቃለወንጌልን በመስማት ብቻ የሚገኝ እይደለም፡፡

ሥርየተ ኃጢአት

 

“ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኃጢአት” የቁስጥንጥንያ አንቀጸ ሃይማኖት፡፡ በ381 ዓ.ም. በቁስጥንጥንያ በመቅዶንዮስ ክህደት ምክንያት ከመላው ዓለም የተሰባሰቡት 150 ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን መቅዶንዮስን ካወገዙ በኋላ ባወጡት አንቀጸ ሃይማኖት ላይ ካሰፈሩት አንቀጽ አንዱ በጥምቀት ሥርየተ ኃጢአት እንደሚገኝ ነው፡፡

እነዚህ አባቶች በቅዱስ መጽሐፍ የሰፈረውን በአንዳንድ የቤተ ክርስቲያን የውስጥ ጠላቶች አማካይነት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሾልኮ የገባን የስህተት ትምህርት ለማጥራት፣ እምነትን ለማጽናትና ምእመናንን ከውዥንብር ለመታደግ አንቀጸ ሃይማኖትን ወስነዋል፡፡ የአበው ውሳኔ መጽሀፍ ቅዱስን መሠረት ያደረገ መሆኑን ከሚከተሉት ማስረጃዎች እምንገነዘበው እውነታ ነው፡- በድንቅ አጠራሩ ለአገልግሎት የተጠራው ቅዱስ ጳውሎስ ከኃጢአቱ ይነጻ ዘንድ“አሁንስ ለምን ትዘገያለህ? ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ ከኃጢአትህም ታጠብ”መባሉን አስተውሉ፡፡

የሐዋ. ሥራ ፳፪፥፲፮፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በበዓለ ሃምሣ ተሰብስበው ለነበሩት አይሁድና ወደ ይሁዲ እምነት ለገቡት በትምህርቱ ልቡናቸው በተነካ ጊዜ “ምን እናድርግ?” ብለው ሲጠይቁት የመለሰላቸው “ንስሐ ግቡ

ኃጢአታችሁ ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ” የሚለውን ነበር፡፡ የሐዋ. ሥራ ፪፥፴፯-፴፰፡፡ ይህ ታዲያ ከሌላ በረት ለመጡ በጎች እንጂ በበረቱ ተወልደው በበረቱ ላደጉት በጎች አይደለም፡፡

በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ ማለቱ የእርሱን የባሕርይ አምላክነት ለመግለጽ እና ዓለም እንዲቀበለው ለማስተማር እንጂ ጥምቀት መፈጸም የሚገባው በሥላሴ ስም መሆኑን ጌታችን ራሱ አስተምሯል፡፡ ማቴ ፳፰፥፲፱፡፡

 

ክርስቶስን በሞቱ የምንመስልበትና በትንሣኤው የምንተባበርበት

 

“ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን? እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደተነሣ እንዲሁ እኛ በአዲስ ሕይወት ንድንመላለስ

ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን” ሮሜ. ፮፥፫-፬፡፡ ማጥመቅ በፈሳሽ ውኃ ነው፤ጥልቅ ውኃ በማይገኝበት ጊዜ ግን ውኃ በሞላበት ገንዳ ይፈጸማል ይህም ካልሆነ ውኃ ቀድቶ የተጠማቂውን መላ አካል ውኃው እንዲያገኘው በማድረግ በእጅ እየታፈኑ ያጠምቁታል፡፡ በጥምቀት ጊዜ የተጠማቂው አካል በውኃ እንዲጠልቅ መደረጉ “ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን” ሮሜ. ፮፥፬ የሚለውን

በገቢር ለመግለጽ ነው፡፡ እንዲሁም ተጠማቂው ከውኃ ውስጥ ብቅ ማለቱ “በጥምቀት ደግሞ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር ሥራ በማመናችሁ ከእርሱ ጋር ተነሳችሁ” ቆላ. ፪፥፲፪ ያለውን እንዲሁ በድርጊት ለማሳየት ነው፡፡

አጥማቂው ካህን “አጠምቀከ በስመ አብ አጠምቀከ በስመ ወልድ አጠምቀከ በስመ መንፈስ ቅዱስ” እያለ ሦስት ጊዜ ብቅ ጥልቅ እያደረገ ድርጊቱን ሦስት ጊዜ መፈጸሙ በሥላሴ አንድነትና ሦስትነት አምኖ መጠመቁን ለማጠየቅ

ሲሆን እንዲሁም የጌታን ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በመቃብር አድሮ መነሳቱንና ተጠማቂዎችም ኋላ በትንሣኤ ዘጉባኤ ንቃ መዋቲ የሚለው አዋጅ ሦስት ጊዜ በሚታወጅበት ጊዜ በቀዋሚ አካል በምትናገር አንደበት ከራስ ጠጉራቸው እስከ እግር ጥፍራቸው ከቁጥር ሳይጎድሉ ከሰውነታቸው ሳይከፈሉ ወንድ በአቅመ አዳም ሴት በአቅመ ሔዋን መነሳታቸውን ለማዘከር ነው፡፡ ስለዚህ “ከክርሰቶስ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንድንኖር እናምናለን” ሮሜ. ፮፥፰ በሚለው የሐዋርያው ቃለ ትምህርት መሠረት ጥምቀት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በሞቱ የምንመስልበት በትንሣኤውም የምንተባበርበት ታላቅ ምሥጢር ነው፡፡

 

የክርስቶስ አካል መሆናችን የሚረጋገጥበት

 

በዘመነ ብሉይ የአብርሃም ወገኖች የአብርሃም ልጆች መሆናቸው ይረጋገጥ የነበረው በግዝረት ነበር፡፡ግዝረት በኦሪቱ የእግዚአብሔር ሕዝብ መለያ ነበር፡፡ ያልተገረዘ ሁሉ ከሕዝቡ ተለይቶ እንዲጠፋ የእግዚአብሔር ትዕዛዝ

ነበር፡፡ ዘፍ. ፲፯፥፲፬፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በአምሳልነት ሲፈጸም የኖረው ግዝረት በዘመነ ሐዲስ በጥምቀት መተካቱን አበክሮ ያስገነዝባል “በክርስቶስ ገዛሪነት የኃጢአትን ሕዋስ ሰንኮፍ ቆርጦ በመጣል ሰው ሰራሽ

ያይደለ ግዝረትን የተገዘራችሁበት፤በጥምቀት ከእሱ ጋር ተቀበራችሁ ከሙታን ለይቶ ባስነሣው በእግዚአብሔር ረዳትነትም በሃይማኖት ከእሱ ጋር ለመኖር በእስዋ ተነሣችሁ” ቆላ. ፪፥፲፩-፲፪፡፡ ግዝረት ለሕዝበ እግዚአብሔር የአብርሃም የቃል ኪዳን ተሳታፊዎች የመሆናቸው መለያ ምልክት እንደነበር ሁሉ ጥምቀት ደግሞ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያምኑ ሁሉ የጸጋው ግምጃ ቤት ከሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኘው ጸጋ ተሳታፊ ያደርጋቸዋል፡፡ በጥምቀት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ እንሆናለን “ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ ትሆኑ

ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና” ገላ. ፫፥፳፯ በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው በጥምቀት ከእግዚአብሔር ጋር አንድ እንሆናለን፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር ያደሰውን አዲሱን ሰውነት የምንለብሰውና የክርስቶስ ተከታዮች የምንሆነው በጥምቀት ነው፡፡ ግዝረት አንድ ጊዜ ብቻ እንደሆነ ሁሉ ጥምቀትም አንዲት ናት፤ አትከለስም፣ አትደገምም፡፡ ኤፌ. ፬፥፭፡፡

 

ሀ-አስፈላጊነት

በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከኒቂያ ጉባኤ በኋላ ከተነሱት አባቶች አንዱ “በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም” ራእይ ፳፥፮ የሚለውን የወንጌላዊው ዮሐንስን አባባል በተረጎመበት የእግዚአብሔር ከተማ በሚለው መጽሐፉ ላይ ፊተኛው ትንሣኤ የተባለው ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና የምናገኝበት ጥምቀት እንደሆነ ገልጿል

 

ክርስቶስን መሠረት ያደረገ እምነት ሁሉ “ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” ዮሐ. ፫፥፫ የሚለው የጌታ ትምህርት መመሪያው ሊሆን ግድ ነው፡፡ ጌታ እንዳስተማረውም ያለጥምቀት ድኅነት የለም፡፡

ጥምቀት በሚታየው አገልግሎት በውኃ ውስጥ ገብቶ መነከር፣ መዘፈቅ፣ ውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣት ማለት ሲሆን በሚታየው አገልግሎት የሚገኘው የማይታይ ጸጋ ግን ብዙ ነው፡፡

 

  1. ድኀነት በጥምቀት ነው፤

ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን ያልተጠመቀ ሰው አይድንም፡፡ የተጠመቀ ግን እንደሚድን በመዋዕለ ትምህርቱ እዲህ ሲል አስተምራል # ያመነ የተጠመቀም ይድናል$ ማር.16 ቁ 16፡፡ ያመነ ይድናል ብቻ አለማለቱን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ጥምቀት ለድኀነት ባያስፈልግ ኖሮ ጌታ ያመነ የተጠመቀም ይድናል ባላለ ነበር፡፡

  1. በጥምቀት ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ዳግም እንወለዳለን፤

 ኒቆዲሞስ የተባለው የአይሁድ አለቃ በሌሊት ወደ ጌታ ዘንድ ሊማር በሄደ ጊዜ ጌታ ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም›› አለው፡፡ ይህ የጌታ ትምህርት ለኒቆዲሞስ ስለረቀቀበትና ስለተቸገረ ‹‹ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኀፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን?›› የሚል ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡ ዳሩ ግን ዳግም ልደት ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኝ መሆኑን ጌታችን እንዲህ ሲል አስተምሮታል ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አይገባም (ዮሐ. 3÷3-6)፡፡ ከጌታችን ትምህርት የምንገነዘበው በሚታይ ሥርዓት በውኃ በሚደረገው ጥምቀት አማካኝነት ከሥላሴ ልጅነት ካላገኘን በስተቀር እንኳን መንግሥተ ሰማያት ልንገባ ልናያትም እንደማንችል ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹ከውኃና ከመንፈስ መወለድ›› ሃይማኖታዊ ግዴታ ነው፡፡ ምናልባት አንዳንድ ሰዎች ‹‹ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ›› አለ እንጂ ‹‹መቼ ካልተጠመቀ›› አለ ብለው ለመከራከር ይከጅሉ ይሆናል፡፡ ዳሩ ግን አስተዋይ አእምሮ ያለው ሰው #ከውኃና ከመንፈስ መወለድ$ ማለት መጠመቅ ማለት እንደሆነ አይጠፋውም፡፡ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ፣ ከማኀፀነ ዮርዳኖስ ዳግም የምንወለደው በጥምቀት ነው፡፡ መወለድ ከእናት ማኀፀን መውጣት እንደሆነ ሕፃኑም ከውኃው ጠልቆ ይወጣልና፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በጥምቀት የሚገኘውን ጸጋና ክብር ለቲቶ ሲገልጽለት ‹‹ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደድ በተገለጠ ጊዜ እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለነበረው ሥራ አይደለም›› ብሏል (ቲቶ. 3÷5)፡፡ ‹‹ለአዲስ ልደት በሚሆን መታጠብ›› ማለቱ ጥምቀትን ማለቱ መሆኑ የተረጋገጠ ነው፡፡ እንዲሁም ለኤፌሶን ሰዎች ቤተ ክርስቲያንን አስመልክቶ በጻፈው ክታቡ ‹‹በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ…›› በማለት በጥምቀት አማካኝነት ምእመናን መንጻታቸውንና መቀደሳቸውን አስተምሯል (ኤፌ 5.26)፡፡

  1. በጥምቀት የኃጢአት ሥርየት ይገኛል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጌታን ከማሳደድ ተመልሶ የእርሱ ምርጥ ዕቃ ሊሆን በተጠራ ጊዜ ሐናንያ እንዲህ ብሎታል፡፡ ‹‹አሁንስ ለምን ትዘገያለህ? ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ፡፡ ከኃጢአትህም ታጠብ›› (የሐዋ.22÷16)፡፡

በዚህ መሠረት መጠመቁም ተገልጿል (ሐዋ.9÷15-16)፡፡

እንግዲህ ምን እንላለን? ታላቁ ሐዋርያ ከኃጢአቱ የነጻውና የተቀደሰው በእምነቱ ብቻ ሳይሆን አምኖ ጥምቀትን በመፈጸሙ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ኃጢአቱ የተወገደለት ሐዋርያ እንዲሆን በተጠራ ጊዜ ሳይሆን ‹‹የእግዚአብሔርን ስም እየጠራ በተጠመቀ$ ጊዜ ነው፡፡ እርሱም ድኀነት የሚገኘው በጥምቀት መሆኑን እንዲህ ሲል ገልጾታል፡፡ ‹‹ከእናንተ አንዳንዶች እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፣ ተቀድሳችኋል፣ ጸድቃችኋል (1ቆሮ.6÷11)፡፡ በበዓለ ሃምሳ በቅዱስ ጴጥሮስ ስብከት ልቡናቸው ከተመሰጠው አንዳንዶቹ ‹‹ምን እናድርግ?›› ብለው ሊያደርጉት የሚገባቸውን ያሳውቃቸው ዘንድ በጠየቁት ጊዜ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ የመለሰላቸው ‹‹ንስሐ ግቡ ኃጢአታችሁ ይሠረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ›› የሚል መልስ ነው (ሐዋ.2÷37-38)፡፡

  1. እምነት መሠረት ነው፡፡

 ፍጹም የሚሆነው ግን በጥምቀት ነው፡፡ እምነት ብቻ በቂ ቢሆን ኖሮ ‹‹እመኑ ብቻ ኃጢአታችሁ ይሠረይላችኋል›› ባላቸው፣ እንዲጠመቁም ባላስገደዳቸው ነበር፡፡ በሃይማኖት ጸሎታችንም ‹‹ኃጢአት በሚሠረይባት በአንዲት ጥምቀት እናምናለን›› የምንለው በዚህ መሠረት ነው፡፡

5-በጥምቀት ከክርስቶስ ጋር አብረን እንሞታለን ከእርሱም ጋር እንነሣለን፡፡

ማንኛውም ክርስቲያን በማናቸውም ነገር ክርስቶስን ሊመሰል ይገባዋል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹እኔን ምሰሉ›› ብሏልና፡፡ ስለዚህ ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን ሮሜ.6÷ 8፡፡

በጥምቀት ከጌታ ጋር አብረን ልንሞትና ልንቀበር ያስፈልጋል፡፡ እንዴት? ቅዱስ ጳውሎስ የዚህን መልስ እንዲህ ሲል ገልጾታል፡፡ ‹‹ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን? እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን›› (ሮሜ.6÷3-4)፡፡ ወደ ቈላስይስ ሰዎች በላከው መልእክቱም ላይ ‹‹በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀበራችሁ በጥምቀት ደግሞ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር ሥራ በማመናችሁ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ›› ብሏል (ቆላ.2÷12)፡፡ ስለዚህ ከክርስቶስ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት አንድንኖር እናምናለን ሮሜ.6÷8፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በጥምቀት ከጌታ ጋር መቀበራችንን ለማረጋገጥ አጥማቂው ካህን ተጠማቂውን በተጠራቀመ (ለመጠመቅ በተሞላ) ውኃ ውስጥ መላ አካሉን በማጥለቅ ነው የሚያጠምቀው፡፡

6-. በጥምቀት አዲስ ሕይወት ይገኛል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሲያረጋግጥ ‹‹እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን›› ብሏል (ሮሜ.6÷4)፡፡ የቀደመው በኃጢአት ምክንያት ያደፈ ሰውነታችን የሚታደሰው፣ የሚቀደሰውና አዲስ ሕይወትን የምናገኘው በጥምቀት ነው፡፡

7-. በጥምቀት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ እንሆናለን፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የገላትያ ክርስቲያኖችን ሲያስትምር ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና ገላ.3÷27፡፡ በጥምቀት በደሙ ከዋጀን ከፈጣሪያችን ጋር አንድ እንሆናለን፡፡ በተጠመቅን ጊዜ አዲሱን ሕይወት እንጎናጸፋለን፤ ፈጣሪውን መስሎ በተፈጠረው በቀድሞው ሰው በአዳም በደል ምክንያት አጥተነው የነበረውን ንጽሕናና ቅድስና እናገኛለን፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር ያደለውን አዲሱን ሰውነት የምንለብሰውና የክርስቶስ ተከታዮች የምንሆነው በጥምቀት ነው፡፡

8- በጥምቀት የቤተ ክርስቲያን አባል እንሆናለን፡፡

በዘመነ ኦሪት የእግዚአብሔር ሕዝብ ለመሆን መገረዝ ሃይማኖታዊ ግዴታ ነበር፡፡ አሕዛብ በቁልፈት፣ እስራኤል በግዝረት ይለዩ ነበር፡፡ ለዚህም ነው የአብርሃም ልጆች ሁሉ በተወለዱ በስምንተኛው ቀን እንዲገረዙ ሕግ የወጣው፡፡ ግዝረት ደግሞ ሊመጣ ላለው ለጥምቀት ምሳሌ ነው (ቈላ. 2÷11-13)፡፡ ግዝረት ለሕዝበ እግዚአብሔር የአብርሃም የቃል ኪዳን ተሳታፊዎች የመሆናቸው መለያ ምልክት እንደሆነ ሁሉ፤ ጥምቀትም በክርስቶስ የሚያምኑትን ሁሉ የጸጋው ግምጃ ቤት ከሆነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከሚገኘው ጸጋ ተካፋይ ያደርጋቸዋል፡፡ ስለዚህ በጥምቀት የቤተ ክርስቲያን አባል መሆናችን ይረጋገጣል፡፡

ለ-የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት

የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት በብሉይ ኪዳን እንደነበሩት እንደ አይሁድና እንደ ዮሐንስ ያለ ጥምቀት አይደለም፡፡ አይሁድ ትዕዛዘ ኦሪትን ለጣሰ ሰው ይደረግ የነበረ የውኃ መታጠብ ነው፡፡ ከርኵሰት የሚነጻው በውኃ በመታጠብ ነበር (15÷1-18)፡፡ የዮሐንስ ጥምቀት ደግሞ የንስሐ ነበር (ማቴ.3÷5 እና 6)፡፡

ጌታ በዮሐንስ እጅ በባሕረ ዮርዳኖስ የተጠመቀው እንደ አይሁድ ሥርዓት ለመንጻት እንደ ዮሐንስም ጥምቀት ለሥርየተ ኃጢአት አልነበረም፡፡ ዳሩ ግን ስለሚከተሉት ምክንያቶች ተጠምቋል፡፡

1ኛ. ትሕትናን ለማስተማር

በአገልጋዩ (በፍጡሩ) በዮሐንስ እጅ መጠመቁ መምህረ ትሕትና መሆኑን ይገልጣል፡፡

2ኛ. ለእኛ አርአያ ለመሆን

ሁለተኛም በጥምቀት ዳግም ከእግዚአብሔር ለምንወለድ ለእኛ አርአያ ለመሆን ሊጠመቅ በቅቷል፡፡

3ኛ. ዲያብሎስ በዮርዳኖስ ወንዝ ደብቆት የነበረውን የዕዳ ደብዳቤ ለመደምሰስ፡፡

4ኛ. አንድነቱንና ሦስትነቱን ለመግለጥ፦ በብሉይ ኪዳን በተለያየ ኀብርና ምሳሌ የነበረውን አንድነቱንና ሦስትነቱን ለመግለጥ ጌታ ተጠምቋል፡፡ ‹‹ሰማያት ተከፈቱ›› የሚለው አነጋገር ሥውር የነበረው ይህ ምሥጢር መገለጡንና ገሃድ መውጣቱን የሚያስረዳ ነው፡፡ የተዘጋ ቤት ሲከፈት በውስጥ ያለው የተሠወረው እንደሚታይ ሁሉ ከሰው ከእምሮ ረቅቆ የነበረው የሥላሴ ምሥጢርም በጌታ ጥምቀት መገለጡን ያረጋግጣል፡፡ በዚህም ጊዜ የክርስቶስ እውነተኛ አምላክነት በባሕርይ አባቱና በባሕርይ ሕይወቱ በመንፈስ ቅዱስ ተመስሯል፡፡

ሐ-የጥምቀት ምሳሌ በብሉይ ኪዳን

ኖኀና ቤተሰቡ ከጥፋት የዳኑባት መርከብ የአማናዊቱ ቤተክርስቲያን ምሳሌ መሆንዋ በመጽሐፍ ቅዱስ የተረጋገጠ ነው፡፡ ፈሪሃ እግዚአብሔር በልቡናቸው ያደረው ኖኀና ቤተሰቡ ከጥፋት ሲድኑ እግዚአብሔርን ድምፅ ያልሰሙት የኖኀ ዘመን ለአማናዊው ጥምቀት ምሳሌነት እንዳለው ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ሲገልጽ (ሲያስተምር) # ጥቂቶች ማለትም ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኀ ዘመን በቆየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም፡፡

ፈሪሃ እግዚአብሔር በልቡናቸው ያደረው ኖኀና ቤተሰቡ ከጥፋት ሲድኑ እግዚአብሔርን ድምፅ ያልሰሙት የኖኀ ዘመን ለአማናዊው ጥምቀት ምሳሌነት እንዳለው ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ሲገልጽ (ሲያስተምር) ‹‹ጥቂቶች ማለትም ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኀ ዘመን በቆየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም፡፡ ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድናል፡፡ የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም ለእግዚአብሔር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ›› 1ጴጥ.3÷20-12፡፡

ኖኀና ቤተሰቡ የዳኑባት መርከብ ምሳሌዋ በሆነው በአንዲቱ ቤተክርስቲያን የሚደረገው ጥምቀት ከፍዳ ያነጻናል ከዲያብሎስ ቁራኝነት ያላቅቀናል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ድኀነት በጥምቀት መሆኑን ሲገልጽ ይህም ውኃ ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድናል ብሏል፡፡

  1. ግዝረት

ግዝረት የእግዚአብሔር ሕዝብ መለያ ምልክት ነበር፡፡ ያልተገረዘ ሁሉ የአብርሃም ልጅ አይባልም ነበር፡፡ ከሕዝቡም ተለይቶ እንዲጠፋ እግዚአብሔር አዝዞ ነበር (ዘፍ.17 ቁ. 14)፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ከውኃና ከመንፈስ ያልተወለደ ማለትም ያልተጠመቀ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አይገባም፡፡ ጽኑ ፍዳ ወዳለበት ገሃነም ይወርዳል እንጂ፡፡ ምክንያቱም መንግሥተ ሰማይ ካልገባ ያለው ምርጫ ገሃነም መጣል ነውና (ዮሐ.3÷3-6)፡፡

 ስለዚህ ግዝረት ለሕዝበ እግዚአብሔር ግዴታ እንደነበረ ሁሉ ጥምቀትም ለክርስቲያኖች ሊፈጽሙት የሚገባ ሃይማኖታዊ ግዴታ ነው፡፡

ግዝረት ሊመጣ ላለው ለጥምቀት ምሳሌው መሆኑን ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስረዳ ‹‹በክርስቶስ ገዛሪነት የኃጢአትን ሕዋስ ሰንኮፍ ቆርጦ በመጣል ሰው ሠራሽ ያይደለ ግዝረትን የተገዘራችሁበት፤ በጥምቀት ከእሱ ጋር ተቀበራችሁ፣ ከሙታን ለይቶ ባስነሣው በእግዚአብሔር ረዳትነትም በሃይማኖት ከእሱ ጋር ለመኖር በእስዋ ተነሣችሁ›› ብሏል (ቈላ.2÷10-12)፡፡

ግዝረት ማለት ከአካል ላይ ሥጋን ቆርጦ መጣል እንደሆነ ሁሉ ጥምቀትም ሐዋርያው እንዳስተማረን የኃጢአትን ሰንኮፍ ከሕይወታችን ቆርጦ መጣል (ማስወገድ) ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን ግዝረት በሰው አማካኝነት የሚፈጸም ሲሆን የኃጢአት ሥሩ ተቆርጠ ተመንግሎ የሚጣልባት ጥምቀት ደግሞ በካህናት አማካኝነት ይፈጸማል፡፡ ዳሩ ግን የኃጢአትን ሰንኮፍ ቆርጦ ከሕይወታችን የሚያስወግደው (የሚጥለው) በስሙ አምነን የተጠመቅንበት መድኃኒተ ዓለም ክርስቶስ ነው፡፡ በሰው እጅ ያልተደረገ በክርስቶስ ገዛሪነት የኃጢአት ሥር ተቆርጦ የሚወገድበት ግዝረት ጥምቀት ነው፡፡

አንድ ሰው ሲገረዝ ከአካሉ ደም ይፈሳል፡፡ እደዚሁም ሁሉ በክርስቶስ ደም የተዋጀን ክርስቲያኖች ከኃጢአታችን የታጠብንበትን የጌታ ደም በጥምቀት እናገኘዋለን፡፡ ግዝረት ከአንድ ጊዜ በላይ እንደማይሆንና ሊደገምም እንደማይችል ሁሉ ጥምቀትም የማትደገም፣ የማትከለስ አንዲት ናት፡፡ ሁለት ጊዜ መጠመቅ አይቻልም (ኤፌ.4÷5)፡፡ መጠመቅ ከክርስቶስ ጋር በሞቱ መተባበር ነው (ሮሜ.6÷8)፡፡ ጌታ የሞተው አንድ ጊዜ ነውና ጥምቀትም አንድ ጊዜ ነው፡፡

  1. የእሥራኤል ባሕረኤርትራን ማቋረጥ

ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን እንዲህ ሲል ገልጦታል ‹‹ወንድሞች ሆይ ይህን ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ፡፡ አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች ነበሩ፡፡ ሁሉም በባሕር መካከል ተሻገሩ፡፡ ሁሉም ሙሴ ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር ተጠመቁ›› (1ቆሮ.10÷1-12)፡፡

እሥራኤል ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር እንደተጠመቁ እኛም አንድነታችን በደሙ ከኃጢአታችን ካጠበን ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንዲሆን እንጠመቃለን፡፡ እስራኤል ከዘመናት የባርነት ቀንበር የተላቀቁትና ነፃ የወጡት የኢርትራን ባሕር ተሻግረው ነው፡፡ ከኃይለኛው ከፈርዖን እጅ የዳኑትም የኤርትራን ባሕር ተሻግረው ነው፡፡ የኤርትራ ባሕር ለፈርዖንና ለሠራዊቱ ሞትን ሲያስከትልባቸው ለእስራኤል ግን ሕይወት፣ ደስታ፣ ነፃነትን አጎናጽፏዋቸዋል፡፡ እኛም ለርኵሳን አጋንንት ከመገዛትና ከፍዳ፣ ከመርገም፣ ከዘላለም ሞት፣ ነፃ ምንሆነው በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነን ስንጠመቅ ነው፡፡ የኤርትራ-ባሕር ለፈርዖንና ሠራዊቱ መጥፊያ እንደሆነ በጥምቀትም አጋንንት ድል ይመታሉ፡፡ ለዚህ ነው በሥርዓተ ጥምቀታችን ተጠማቂው ከተጠመቀ በኋላ ከምዕራብ (ሲዖል) ወደ ምሥራቅ (ገነት) የሚዞረው፡፡

የሶርያ ንጉሥ ሠራዊት አለቃ ንዕማን ከለምጹ የነጻው በዮርዳኖስ ወንዝ ታጥቦ ነው፡፡ በነቢይ በታዘዘው መሠረት በዮርዳኖስ ውኃ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ በማለት ታጥቦ ሥጋው እንደገና እንደ ትንሽ ብላቴና ሥጋ ንጹሕም ሆኖ መመለሱን በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ እናገኘዋለን (2ነገ.5÷8-14)፡፡

እኛም ከኃጢአት ደዌ የምንነጻውና ያረጀው ሕይወታችን ሊታደስ የሚችለው በጥምቀት ነው፡፡ ስንጠመቅ የክርስቶስ ደም ከኃጢአታችን እንዳጠበን ማረጋገጣችን ነውና፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ሕዝቅኤል በመንፈስ ቅዱስ ተገልጦለት እንዲህ ብሏል ‹‹በውኃም አጠብሁሽ፤ ከደምሽም አጠራሁሽ፤ በዘይትም ቀባሁሽ›› (ሕዝ 16÷9)፡፡

ለጊዜው ይህ አነጋገር በኃጢአት ለተመላችው ለኢየሩሳሌም የተነገረ ቢሆንም ፍጻሜው ግን በኃጢአት ለተበላሸው ለሰው ሁሉ ሕይወት የተነገረ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ‹‹ባንቺ ዘንድ ባለፍሁና ባየሁሽ ጊዜ እነሆ ጊዜሽ የፍቅር ጊዜ ነበር፡፡ እኔም መጎናጸፊያዬን በላይሽ ዘረጋሁ፡፡ ኀፍረተ ሥጋሽንም ከደንሁ፤ ማልሁልሽም፡፡ ከአንቺም ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፡፡ አንቺም ለእኔ ሆንሽ፡፡›› (ሕዝ 16÷8)፡፡

እግዚአብሔር በምሕረቱ ሰውን በጎበኘበት ወቅት በፍጹም ፍቅሩ ስቦ ነው የሰውን ልጅ ያቀረበው፡፡ ጌታችንም እርቃኑን በመሰቀል የእኛን ከኃጢአት መራቆት አስቀርቶልናል፡፡ የክብር የሕይወት መጎናጸፊያ አጎናጽፎናል፡፡ ስለ እኛ መከራን ተቀበለ፡፡፡ የእርሱ አደረገን፡፡ ‹‹በውኃ አጠብሁሽ›› የሚለው ‹‹ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ መወለድን›› ያስረዳናል፡፡ ይኸውም በጥምቀት ነው፡፡ በጥምቀት ከዘላለም የኃጢአት ባርነት መላቀቃችንን ሲያስገነዝበን ‹‹ከደምሽም አጠራሁሽ›› ብሏል፡፡ በተጨማሪም ጥምቀት በቅብዐ ሜሮን ማኀተምነት እንደሚፈጸም ‹‹በዘይትም ቀባሁሽ›› በማለት አረጋግጦልናል፡፡ ‹‹አንቺም የእኔ ሆንሽ›› እንዳለው ሁሉ ተጠማቂውም በጥምቀት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፈጸመውን የቤዛነት ሥራ ሁሉ አግኝቶ የእርሱ ወገን መሆኑን ያስረዳል፡፡

መ፦ የሕፃናት ጥምቀት

አንዳንድ ሰዎች የሕፃናትን ጥምቀት ሲነቅፉና ትክክለኛ ጥምቀትም እንዳልሆነ ሲናገሩ ይሰማሉ፡፡ ተራ ትችት ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌለው ነው፡፡ እነዚህ ክፍሎች ራሳቸው ከአእምሮአቸው አመንጭተው ላስተማሩት ሐሰተኛ ትምህርት መጽሐፍ ቅዱስ ያስተማረው አስመስለው ለማቅረብ ሲሞክሩም ይስተዋላሉ፡፡

ለምሳሌ ያህል #ያመነ የተጠመቀ ይድናል$ የሚለውን በመጥቀስ ‹‹በመጀመሪያ እምነት ይቀድማል፡፡ ለማመን ደግሞ መማር፣ ማወቅ፣ ማገናዘብና አምኛለሁ ተቀብያለሁ ሊባል ይገባል፡፡ ሕፃናት ግን የሚያውቁት ነገር ስለሌለ አላመኑም ስለዚህ ያላመኑ ሕፃናትን ማጥመቅ ተገቢ አይደለም›› ይላሉ፡፡ ዳሩ ግን ቤተክርስቲያን ወንዶችን በተወለዱ በ4ዐ ቀናቸው ሴቶችን በተወለዱ በ8ዐ ቀናቸው የምታጠምቀው መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጋ ነው፡፡

ሀ. ሕፃናት የዘላለምን ሕይወት እንዲያገኙ ወላጆቻቸውና ቤተክርስቲያን የሚሹት ነው፡፡

ያለ ጥምቀት ደግሞ ዘላለማዊ ሕይወት አይገኝም፡፡ ጌታ እንዳስተማረው # ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም$ (የሐ.3÷5)፡፡ ስለዚህ ሕፃናት በወላጆቻቸው እምነት የተነሣ የወላጆቻቸውን እምነት የእነርሱ እምነት በማድረግ ገና በሕፃንነት ጊዜያቸው ከእግዚአብሔር መንግሥት ውጭ እንዳይሆኑ ታጠምቃቸዋለች፡፡ ዳሩ ግን ሳይጠመቁ ቢሞቱ ጌታ እንደተናገረው መንግስተ ሰማይን አያዩአትም፡፡ እንደ ጌታ ትምህርት የምንሄድ ከሆነ #ሰው# ብሎ ባጠቃላይ ሕፃናትን አዋቂዎችን ሁሉ ጨምሮ ተናገረ እንጂ ከሕፃናት በስተቀር አላለም፡፡ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም፡፡

ለ. ሕፃናት በመጠመቃቸው የቤተ ክርስቲያን አባል ስለሚሆኑ የእግዚአብሔር ጸጋ ተከፋዮች ይሆናሉ፡፡ ገና ከሕፃንነታቸው ጀምሮ የቤተ ክርስቲያንን ሕይወት ይለማመዳሉ፡፡ በዚህ ፈንታ ከሕፃንነታቸው ጊዜ ጀምረው ከእግዚአብሔር ጸጋ ተራቁተው የሚያድጉ ከሆነ ለመጥፎ ሕይወት ይዳረጋሉ፡፡

ሐ. ‹‹ሕፃናት ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው›› እንዲሁም ጌታችን ‹‹ያመነ የተጠመቀ ይድናል›› ሲል በዚያን ዘመን ገና ወንጌል መስበክ በጀመረበት ላሉት ሰዎች የተነገረ ሲሆን ከክህደታቸውና ከጥርጥራቸው ተመልሰው የሚመጡ ሁሉ አምነው መጠመቅ እንዳለባቸው የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ሕፃናት የእግዚአብሔር ልጆች ሊሆኑ እንደሚገባ ጌታችን ሲገልጽ ‹‹ሕፃናት ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተውአቸው አትከልክሏቸው መንግሥተ ሰማያት እንደ እነርሱ ላሉት ናትና›› ብሏል (ማቴ.19÷14)፡፡ በዚህ የጌታ ትምህርት መሠረት ቤተክርስቲያንም የመሪዋንና የመሥራችዋን የክርስቶስን ቃል መርሕ በማድረግ ወላጆቻቸው ታቅፈው ወደ ቤተክርስቲያን ይዘው በመምጣት ተጠምቀው የእግዚአብሔር ልጆች የቤተክርስቲያን አባላት እንዲሆኑ ሲያደርጉ እርሷ ከልካይ አትሆንም፡፡ ጌታ ተውአቸው ይምጡ ልጅነትን፣ ጸጋን፣ በረከትን ያግኙ ብሏልና፡፡

ሕፃናት ንጹሐነ አእምሮ መሆናቸውን ጌታ ሲያስተምር እንደ ሕፃናት ካልሆናችሁ መንግሥተ ሰማይ አትገቡም ብሏል፡፡

መ. መጽሐፍ ቅዱስ ሕፃናት መጠመቃቸውን ያስተምረናል፤ የሚከተሉት ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

  1. 1. በእሥር ቤቱ በተደረገው ተአምር የተደነቀውና ወደ ክርስትና እምነት የተሳበው የወኀኒ ጠባቂ ጳውሎስና ሲላስ ካስተማሩትና ካሳመኑት በኋላ ከነቤተሰቡ መጠመቁ ተገልጾአል፡፡ እግዲህ የተሰበከውና ያመነው የወኀኒ ጠባቂው ሲሆን የተጠመቁት ግን ሕፃናትን ጨምሮ መላው ቤተሰቡ ነው (የሐዋ.16÷33)፡፡

  2. ልብዋን ጌታ የከፈተላትና ቃሉን አድምጣ ሕይወትዋን ለክርስቶስ የሰጠችው ልድያ ባመነች ጊዜ የተጠመቀችው ብቻዋን ሳይሆን ከመላው ቤተሰብዋ ጋር ነው፡፡ ከቤተሰቡ መካከል ሕፃናት መኖራቸው የማይቀር ነው (የሐዋ.16÷15)፡፡

  3. ቅዱስ ጳውሎስ የእስጢፋኖስንም ቤተሰቦች ደግሞ አጥምቄያለሁ በማለት የእስጢፋኖስን መላ ቤተሰብ ማጥመቁን ገልጿል (1ቆሮ.1÷16)፡፡ እነዚህ የእስጢፋኖስ ቤተሰቦች ሁሉ ትላልቆች ብቻ ናቸውን? ሕፃናት የሉበትም ይሆን?

  4. በሐዋ.ሥራ 2 ላይ እንደተገለጸው በበዓለ ሃምሳ ከ3ዐዐዐ ያላነሱ ሰዎች በጴጥሮስ ተሰበኩ፡፡ ከእነዚያ ውስጥ ብዙዎቹ መጠመቃቸው ተገልጿል፡፡ የተጠመቁት ግን አዋቂዎች ብቻ መሆናቸውን የሚገልጽ ቃል የለም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሕፃናትን ጥምቀት የሚነቅፍ ባንዱም ክፍል ተጽፎ አናገኝም፡፡

እስከ አሁን እንደተገለጸው መጽሐፍ ቅዱስ የሕፃናትን ጥምቀት ያልነቀፈ ሲሆን በብሉይ ኪዳን የጥምቀት ምሳሌ የነበሩትን ስንመለከት ይበልጥ የሕፃናትን ጥምቀት ትክክለኛነት ያረጋግጡልናል፡፡ ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ ሕፃናት በተወለዱ በስምንተኛው ቀን ይገረዙ ነበር (ዘፍ. 17÷12)፡፡ እንግዲህ ሕፃናቱ የሚገረዙት በወላጆቻቸው እምነት እንጂ እነርሱ አውቀው ግረዙን ብለው አይደለም፡፡ የእሥራኤል ቀይ ባሕርን ማቋረጥ የጥምቀት ምሳሌ መሆኑ በ1 ቆሮ.10÷2 የተገለጸ ሲሆን ባሕሩን ያቋረጡት አዋቂዎች ብቻ ሳይሆኑ ሕፃናትም ጭምር ናቸው፡፡ ከባርነት ከፈርዖን አገዛዝ ነፃ የወጡት ሕፃናቱም ጭምር ናቸው፡፡

እሥራኤል ከበኲረ ሞት የዳኑበት የአንድ ዓመት ጠቦት በግ ደግሞ ምሳሌነቱ የጌታ መሆኑ የታወቀ ሲሆን በዚያን ጊዜ በበጉ ደም አማካኝነት ከሞት የዳኑት የታዘዙትን እሺ ብለው የፈጸሙት አዋቂዎች ብቻ ሳይሆኑ የእነርሱ ልጆችም ጭምር ናቸው፡፡ እንግዲህ በወላጆቻቸው እምነት ሕፃናቱ መዳናቸውን ልናስተውል ይገባናል፡፡ ስለዚህ ሕፃናት በአእምሮ ባልበሰሉበትና ስለ ጥምቀታቸው አምነው ተቀብየዋለሁ ሳይሉ የሚደረገው ጥምቀት እውነተኛ ጥምቀት አይደለም የሚሉ በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ከላይ እንደተገለጸው ሁሉ መሳሳታቸው የተረጋገጠ ነው፡፡

እግዚአብሔር ሰውን ይመርጣል እንጂ ሰው እግዚአብሔርን አይመርጥም፡፡ ራሱ ባለቤቱ እንዳስተማረው ሁሉ #እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም$ ብሏል (ዮሐ.15÷16)፡፡ ድኀነት በእግዚአብሔር ቸርነት የሚገኝ እንጂ በሰው ትምህርትና ዕውቀት የሚሸመት ወይም የሚገበይ ዕቃ አይደለም፡፡ ስለሆነም ቤተ ክርስቲያናችን ሕፃናትን ማጥመቋ ከመጽሐፍ ቅዱስና ከቀደሙት አበው ባገኘችው ትምህርት መሠረት ነው፡፡

በማን ስም ልንጠመቅ ይገባል

ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰዎች የእግዚአብሔርን ልጆች ይሆኑ ዘንድ በሥላሴ ስም ታጠምቃለች፡፡ ይህም ጌታ ራሱ ለሐዋርያቱ ‹‹ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ያጠመቃችኋቸው፡፡›› (ማቴ. 28÷19) ብሎ የሰጠውን አምላካዊ ቃል መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ደም ከተመሠረተችበት ዘመን አንስቶ በሥላሴ (በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ) ስም መጠመቅ የድኀነት በር ቁልፍ መሆኑን ስታስተምርና ተግባራዊ ስታደርግም ኖራለች፡፡ ይህንን የወንጌል ቃል የሚያጣምሙ መናፍቃን በኢየሱስ ስም ብቻ መጠመቅ አለብን እንጂ በአብ፣ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅ የለብንም ይላሉ፡፡ ለዚህም ማስረጃ አድርገው ለማቅረብ የሚሞክሩት የሐዋርያው የቅዱስ ጴጥሮስን አነጋገር ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በበዓለ ሃምሳ ከየሃገሩ ለተሰበሰቡት አይሁድ የምሥራቹን ቃል ድምጹን ከፍ አድርጐ ባሰማቸው ጊዜ ልባቸው ተነካ፡፡ ስለዚህም ‹‹ምን እናድርግ›› ብለው ሊያደርጉት የሚገባቸውን እንዲነግራቸው ጠየቁት፡፡

እርሱም ‹‹ንስሐ ግቡ፣ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ አላቸው›› (የሐዋ ሥራ 2÷38 ሐዋርያው ‹‹በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ›› ብሎ ማስተማሩ ለምን ነበር? ለምን ጌታ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ ያለውን ተከትሎ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠመቁ አላለም? የሚል ጥያቄ ለሚያነሣ ሁሉ ምክንያቱ እንደሚከተለው ነው፡፡በበዓለ ሃምሳ ከየሃገሩ የተሰበሰቡት አይሁድ ከጥንት ጀምሮ በነቢያት አንደበት ይወርዳል ይወለዳል እየተባለ የተነገረለትን መሲሕን ተስፋ ያደርጉ ነበር፡፡

ሐዋርያውም ያ የተስፋው ቃል ዛሬ መፈጸሙንና በተስፋው ቃል መሠረት ከድንግል ማርያም በሥጋ ተወልዶ 33 ዓመተ ከ3 ወር በምድር ላይ ተመላልሦ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የሰውን ልጅ በደሙ የዋጀው ኢየሱስ ክርስቶስ ትንቢት የተነገረለት ሱባዔ የተቆጠረለት መሆኑን አምነው በሰው ካልተጠመቁ በስተቀር አብርሃም አባታችን እግዚአብሔር አምላካችን በሚለው እምነት ብቻ አምነው ጌታን በሰቀሉት አይሁድ መንገድ የሚጓዙ ከሆነ እንደማይድኑ በመሲሕ አምነው በስሙም ከተጠመቁ ግን እንደ ሚድኑ ሊያስተምራቸው ስለፈለገ የጌታን ስም ለይቶ ጠራ፡፡ በዚህም የጌታን አዳኝነትና መሲሕነት አምነው እንዲቀበሉ በአጽንዖት መናገሩ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ሐዋርያት ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት ቤዛ የሆነልንን ጌታ ሰው ሁሉ አምኖ እንዲድን በየሄዱበት የጌታን አዳኝነትና የባሕርይ አምላክነት አሰተምረዋል፡፡ የስብከታቸው ማዕከል የነበረው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር፡፡ ምክንያቱም ክህደቱ ጸንቶ የነበረው በጌታ የባሕርይ አምላክነት ላይ ነበርና፡፡ በዚህ የተነሣ የእርሱን አዳኝነትና የባሕርይ አምላክነት ለማሳመን ጌታን የስብከታቸው ማዕከል አደረጉ፡፡

አጥማቂው ማነው?

ሊያጠምቁ የሚገባቸው ሥልጣነ ክህነት ያላቸው ሰዎች ማለትም ቄስ ወይም ጳጳስ መሆን እንዳለባቸው የቤተክርስቲያን ቀኖና ያዛል፡፡ ግን ‹‹በክርስቶስ ያመነ ሁሉ ካህን ነውና ሊያጠምቅ ሥልጣን አለው›› የሚለው አመለካከት የተሳሳተ ነው፡፡ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን መፈጸም የሚገባቸው ሥልጣነ ክህነት የተሰጣቸው ብቻ እንጂ ሥልጣነ ክህነት የሌላቸው ምእመናን ሊሆኑ አይገባም፡፡ አይሆኑምም፡፡

ሥልጣነ ክህነት በሌለው ሰው የተደረገ ጥምቀት አማናዊ ጥምቀት አይደለም፡፡ ከሥላሴም ልጅነትን አያሰጥም፡፡ምክንያቱም ጌታ ‹‹አጥምቁ›› ብሎ የላካቸው ከሌላው ሁሉ መርጦ የሾማቸውን ሐዋርያቱን እንጂ ያመኑትን ሁሉ አይደለም (ማቴ.28÷19፤ ማር.16 ÷16)፡፡

ሐዋርያት ሥልጣነ ክህነትን ከጌታ መቀበላቸው በወንጌል ተመዝግቧል፡፡ # ይህንንም ብሎ እፍ አለባቸውና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ$ ይላል (ዮሐ. 2ዐ÷22)፡፡ ይህም ሥልጣነ ክህነት ለመሆኑ ማረጋገጫችን ‹‹ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፡፡ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው›› (ዮሐ.20÷23) በማለት ልጅነትን ሳይሆን ሥልጣነ ክህነትን እንደሰጣቸው ቅዱስ ወንጌል ያስተምረናል፡፡

ምክንያቱም ልጅነት ኃጢአት ሊያስተሠርይ፣ ከኃጢአት ሊፈታ፣ ሊያስር፣ አይችልምና ነው፡፡ ሥልጣነ ክህነት ግን ኃጢአትን ሊያስተሠርይ፣ ከኃጢአት ሊፈታና ሊያስር ይችላል፡፡

ስለዚህ ለማጥመቅም ሆነ ሌሎችንም ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ለመፈጸም ሥልጣኑ ያላቸው ካህናት እንጂ ሁሉም ምእመን አይደለም፡፡

በዚህም የተነሣ ቤተክርስቲያን በምእመናን የሚፈጸመውን ጥምቀት እውነተኛ ጥምቀት አድርጋ አትቀበለውም፡፡

ጥምቀት አንዲት ናት

ጥምቀት የማትደገም፣ የማትከለስ አንዲት ናት፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ልጅነትን የምናገኝባት ጥምቀት የማትደገምና የማትከለስ አንዲት ብቻ መሆንዋን ሲያስተምር ‹‹አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት…አለ›› ብሏል (ኤፌ.4÷5)፡፡ ሃይማኖታቸው የቀና 318ቱ ሊቃውንትም ‹‹ኃጢአትን በምታስተሠርይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን፡፡›› ብለው አስተምረዋል፡፡ በዚህ የተነሣ ኣርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንድ ጊዜ ያጠመቀችውን ድጋሚ አታጠምቅም፡፡ ነገር ግን አማናዊቷን ጥምቀት ቀድሞም አልፈጸሙምና ከቤተ ክርስቲያናችን ውጪ በሌላ በማናቸውም ሁኔታ ‹‹ተጠምቀን ነበር›› የሚሉትን ወደ ቤተ ክርስቲያናችን ሲቀርቡ በሥርዓቷ መሠረት አስተምራ አሳምና ታጠምቃቸዋለች፡፡

በሌላ መልኩ ደግሞ ቀድሞ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ተጠምቆ ኋላ ግን ወደ ሌላ እምነት ቢገባ ተናዞ (ንስሐ ገብቶ) በማየ ጸሎት (መጽሐፈ ቄደር ተደግሞለት) ይረጫል እንጂ ድጋሚ አይጠመቅም፡፡ቄደር የንስሐ እጽበት ነው፡፡ ያደፈ ልብስ እንደሚታጠብ ሁሉ ይህም ሰው ንጽሕት እምነቱን አሳድፏልና ከኃጢአቱ ለመታጠቡ ምልክት ይሆን ዘንድ በማየ ጸሎት ይታጠባል፡፡

ጥምቀት የማይደገምበት ምክንያት

ሀ. ጥምቀት ከእግዚአብሔር ዳግም የምንወለድበት ምሥጢር ነው፡፡ የሥጋን ልደት ስንመለከት ሰው ከእናቱ ማኀፀን የሚወጣ (የሚወለደው) አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ እንዲሁም እግዚአብሔርም በእውነት አንድ ጊዜ ወልዶናል፡፡ ስለዚህ አንድ ጊዜ ብቻ እንጠመቃለን፡፡

ለ. ጥምቀት ከጌታ ሞትና ትንሣኤ ተሳታፊ የምንሆንበት ምሥጢር ነው፡፡ ‹‹በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ በጥምቀትም ደግሞ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ›› (ቈላ.2÷12)፡፡ ጌታ የሞተውና የተነሣው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ እንዲሁም እኛ ከእርሱ ጋር የምንቀበረውና የምነሣው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡

ለምን በውኃ እንጠመቃለን

  1. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው በውኃ ነው እኛም እርሱን አብነት በማድረግ በውኃ ልንጠመቅ ይገባናል (ማቴ.3÷13-16)፡፡

  2. ጌታችን ለኒቆዲሞስ ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም›› ስላለ እኛም የጌታን ትእዛዝ ለመፈጸም በውኃ እንጠመቃለን (ዮሐ.3÷5)፡፡

  3. ሐዋርያት ከጌታ በተማሩት መሠረት ያጠመቁት በውኃ ነው፡፡ ጴጥሮስም መልሶ ‹‹እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እንዳይጠመቁ ውኃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማን ነው? አለ›› (የሐዋ.10÷46ና 47)፡፡ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ አጠመቃቸውም (የሐዋ.8÷28)፡፡

  4. ውኃ የሰውነትን እድፍ እንደሚያጠራ ሁሉ እንዲሁም ጥምቀት የነፍስን እድፍ ያስወግዳል ያነጻል፡፡

  5. ውኃ መልክን ያሳያል እኛም በውኃ በመጠመቅ የሥላሴን ምሥጢር በዓይነ ኅሊናችን እናያለን፡፡

  6. በጥንተ ፍጥረት መንፈስ እግዚአብሔር በውኃ ላይ ረብቦ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ይገልጿል፡- ‹‹የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር›› (ዘፍ.1÷2)፡፡ እንዲሁም በውኃ፣ በሕይወትና በመንፈስ ያለውን ግንኙነት ማስተዋል ይገባል፡፡ ልዑለ ባሕርይ ጌታ በነቢዩ በኤርምያስ አንደበት እንዲህ ሲል ተናግሯል ‹‹ሕዝቤ ሁለቱን ክፉ ነገሮች አድርገዋልና እኔን የሕያውን ውኃ ምንጭ ትተውኛል…›› (ኤር.7÷13)፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ትምህርቱ በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ብሎ አስተምሯል (ዮሐ.7÷39)፡፡ ለሳምራዊቷ ሴትም ‹‹እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፡፡ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ አላት›› (ዮሐ.4÷14)፡፡

ከላይ በተገለጸው መሠረት ውኃ የሕይወት ምልክት ነው፡፡ በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እንደምናነበው ውኃ ለሰማያዊው መንግሥት፣ ለዘላለም ሕይወት ምሳሌ ሆኖ ተገልጿል፡፡ ‹‹እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር አንደተተከለች ፍሬዋን በየጊዜው እንደምትሰጥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል›› (መዝ. 1÷3) እና የመሳሰሉትን ሁሉ እናገኛለን (ራእይ.2÷16፣ 22÷1፣ 22÷17)፡፡

እንግዲህ ውኃ ከክፉ ኀሊና ለመንጻታችንና ለመቀደሳችን ማረጋገጫ መሆኑን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ሲል አስተምሯል፡- ‹‹ከክፉ ሕሊና ለመነጻት ልባችንን ተረጭተን፣ ሰውነታችንንም በጥሩ ውኃ ታጥበን፣ በተረዳንበት እምነት በቅን ልብ እንቅረብ›› (ዕብ.10÷22)፡፡

  1. ለንጊኖስ የተባለው ሐራዊ (ወታደር) የጌታን ቀኝ ጎን በጦር በወጋው ጊዜ ትኩስ ደምና ውኃ ባንድነት ፈሷል (ዮሐ. 19÷34)፡፡ ደሙ ለመጠጣችን፣ ውኃው ለጥምቀታችን መሆኑን ሲያጠይቅ ነው፡፡ ይህንንም ፍቁረ እግዚእ ዮሐንስ እንዲህ ሲል ገልጾታል ‹‹በውኃና በደም የመጣ ይህ ነው፡፡ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ በውኃና በደሙ እንጂ በውኃው ብቻ አይደለም፡፡… የሚመሰክሩት መንፈሱና ውኃው ደሙም እንጂ በውኃው ብቻ አይደለም፡፡… የሚመሰክሩት መንፈሱና ውኃው ደሙም ሦስት ናቸውና፡፡ ሦስቱም በአንድ ይስማማሉ›› (1ዮሐ.5÷6-8)፡፡

  2. ውኃ በሁሉም ቤት ይገኛል፡፡ በሀብታሙም በድኃውም ጥምቀትም ላመነ ሁሉ የተፈቀደ መሆኑን ለማጠየቅ በውኃ ሆኗል፡፡ ስለዚህም በውኃ ብቻ እንጠመቃለን፡፡ ሥርዓተ ጥምቀቱን የሚፈጽመው ካህን አሐዱ አብ ቅዱስ፣ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ ብሎ በእግዚአብሔር ቃል ሲባርከው ውኃው ተለውጦ በዕለተ ዓርብ ከጌታችን ቀኝ ጐን የፈሰሰውን ውኃ ይሆናል፡፡

 

 

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top