የእግዚአብሔር ፍጹም አንድነትና ልዩ ሦስትነት

“ሥላሴ” የሚለው ቃል “ሠለሰ” ሦስት አደረገ ካለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ሦስትነት ማለት ነው፡፡ ቅድስት ሥላሴ ስንል ለሥላሴ ቅድስት ብለን እንቀጽላለን፡፡ ቅድስት ሥላሴ ማለት ልዩ ሦስትነት ማለት ነው፡፡ ይህም ሦስት ሲሆኑ አንድ፣ አንድ ሲሆን ሦስት ስለሚሆኑ ልዩ ሦስትነት ተብሏል፡፡ ሥላሴ የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ያለና የሚኖረውን አምላክ ለመግለጽ የተጠቀመው የአንጾኪያው ቴዎፍሎስ በ169ዓ.ም ነው፡፡ኋላም በኒቅያ ጉባዔ 318ቱ ሊቃውንት አጽንተውታል፡፡ እነዚህ ሊቃውንት በቅዱሳት መጻሕፍት የተመሰከረውን የእግዚአብሔርን ፍጹም አንድነትና ልዩ ሦስትነት ለእኛ በሚረዳ ቋንቋ ገለጡት እንጂ አዲስ ትምህርት አላመጡም፡፡ ይልቁንም ነገረ ሥላሴን ሳይረዱ በሥላሴ መካከል የክብርና የተቀድሞ ልዩነት ያለ አስመስለው በክህደት ትምህርት የተነሱ መናፍቃንን ክህደት ለማስረዳት፣ የሐዋርያዊት ቤተክርስቲያንን የቀናች ሃይማኖት ለመግለጥ ምሥጢረ ሥላሴን አብራርተው አስተምረዋል፡፡

 

ምስጢረ ሥላሴ ማለት የአንድነት የሦስትነት ምስጢር ማለት ነው፡፡ ምሥጢር መባሉም በእምነት የተገለጠ፣ ያለ እምነትም የማይመረመር ስለሆነ ነው፡፡ ይኸውም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በስም፣ በአካል፣ በግብር ሦስት ሲሆኑ በባሕርይ በሕልውና፣ በመለኮት ደግሞ አንድ ናቸው፡፡ እንደዚህ ባለ ድንቅ ነገር አንድ ሲሆኑ ሦስት፣ ሦስት ሲሆኑ አንድ ይባላሉና፣ ይህም ልዩ ሦስትነት ረቂቅ እና በሰው አእምሮ የማይመረመር ስለሆነ ምስጢር ይባላል፡፡ ስለዚህም… ተጨማሪ ያንብቡ

ምስጢረ ሥላሴ

ስለ እግዚአብሔር የአንድነት የሦስትነት የምንማረው የምናስተምረው የሃይማኖት ትምህርት ምስጢረ ሥላሴ ብለን እንጠራዋለን፨

✔በመንግሥት፣ በቅድምና፣ በፈጣሪነት፣ በሥልጣን፣ በማሰገድ፣ በመመስገን፣ በዕበይ፣ በክብር፣ በኀይል፣ በክሂል፣ በፈቃድ፣ በሥምረት፣ በትእዛዝ አንድ የኾነው እግዚአብሔር የስም፣ የግብር፣ የአካል፣ የኩነታት ሦስትነት እንዳለው የሚገልጸው ትክክለኛው የወንጌለ ሰላም የቤተ ክርስቲያን ትምህርት “ምስጢረ ሥላሴ” (Mystery of Holy Trinity) ይባላል፡፡

✔ይኽ የአንድነት የሦስትነት ትምህርት “ምስጢር” መባሉ በዐይን የማናየው በእደ ሥጋ የማንዳስሰው በዐይነ ሕሊና የምናየው በልቡናችን የምናምነውና የምንቀበለው በሥጋዊ ምርምር ፈጽሞ የማንደርስበት ስለኾነ ነው፡፡

✔የስም ሦስትነታቸው አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ መባል ነው፤ ይኽነንም ከሦስቱ አካላት አንዱ ወልድ በማቴ ፳፰፥፲፱ ላይ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ”፤ በማለት የስም ሦስትነትን አስተምሯል፤
ዮሐንስም በራእዩ በምዕ 14፡1 ላይ “አየሁም፥ እነሆም፥ በጉ በጽዮን ተራራ ቆሞ ነበር፥ ከእርሱም ጋር ስሙና የአባቱ ስም የመንፈስ ቅዱስም ስም በግምባራቸው የተጻፈላቸው” በማለት ስለ ሥላሴ አካላትና ስለአካላቱ የስም ሦስትነትን አስተምሯል።

✔✔መሠረቱን በመጽሐፍ ቅዱስና በሊቃውንት ትምህርት ባደረገው በዶግማ ትምህርት አብም አብ ቢባል እንጂ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አይባልም፤ ወልድም ወልድ ቢባል እንጂ አብ መንፈስ ቅዱስ አይባልም፤ መንፈስ ቅዱስም መንፈስ ቅዱስ ቢባል እንጂ አብ ወልድ አይባልም፤ ስማቸው ፈጽሞ የማይፋለስ የማይተባበር ነው፡፡

✔በአንጾኪያ ከቅዱስ ጴጥሮስ ቀጥሎ በሦስተኛነት ተሹሞ የነበረው ቅዱስ አግናጥዮስም በሃይማኖተ አበው ላይ፡- (አብም አብ ነው ወልድን አይደለም መንፈስ ቅዱስንም አይደለም፤ ወልድም ወልድ ነው አብን አይደለም መንፈስ ቅዱስንም አይደለም፤ መንፈስ ቅዱስም መንፈስ ቅዱስ ነው አብን አይደለም ወልድን አይደለም፤ አብ ወልድንና መንፈስ ቅዱስን ለመኾን አይለወጥም፤ ወልድም አብንና መንፈስ ቅዱስን ለመኾን አይለወጥም፤ መንፈስ ቅዱስም አብንና ወልድን ለመኾን አይለወጥም) በማለት ሲያስተምር ዮሐንስ ዘአንጾኪያም “አስማትሰ ኢየኀብሩ” (ስሞች ግን አይተባበሩም) በማለት አስተምሯል፡፡

✔አንዳንድ የእምነት ድርጀቶች በዘመናችን ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ባግባቡ ስላልተረዱት “ኢየሱስ ብቻ” በማለት የአብንም ስም የመንፈስ ቅዱስንም ስም ለኢየሱስ ብቻ በመስጠት ስመ ተፋልሶ በማምጣት ኑፋቄን ይዘራሉ፤ እኛ ግን እንደ መጽሐፍ ቅዱሱ ትምህርት የአብ፣ የወልድ፣ የመንፈስ ቅዱስ ስም የማይፋለስ እንደኾነ እናምናለን፡፡

✔ይኽም የሥላሴ የአካል ስም አካል ቀድሞት እንደ ሰው ስም በኋላ የተገኘ አይደለም፤ የሰው ስሙን አካሉ ቀድሞት በኋላ ይገኛል፤ ወንዱን በ፵ ቀን “እገሌ” ሲሉት ሴቲቱን በ፹ ቀኗ “እገሊት” ይሏታል፤ የተወለደ ዕለትም እናት አባቱ ዓለማዊ የመጠሪያ ስም ያወጡለታል፡- ይኽ ግን በሥላሴ ዘንድ የለም፤ “ሰብእ” (ሰው) ማለት ስሙ ከአካሉ አካሉ ከስሙ ሳይቀድም እንደ ተገኘ የሥላሴም ስማቸው ከአካላቸው፤ አካላቸው ከስማቸው ሳይቀድም ቅድመ ዓለም የነበረ ስም ነው እንጂ ድኅረ ዘመን የተገኘ አይደለም፤ ይኽም ሲባል ቅድምናቸውም ዘመኑን ቢወስነው እንጂ ዘመኑ ቅድምናቸውን አይወስነውም፡፡

✔ሊቁ ቅዱስ ጎርጎሬዎስ ገባሬ መንክራትም በሃይማኖተ አበው ላይ ይኽነን ሲገልጽ፡- “ደግሞ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ እንላለን ግን አካላት ተቀድመው ተገኝተው እሊኽ ስሞች ኋላ የተጠሩባቸው አይደሉም፤ ሰው ማለት ኋላ የወጣ ስም አይደለም ባሕርዩ ነው እንጂ … የሥላሴ አካላቸው ተቀድሞ ስማቸው ከአካላቸው በኋላ የተገኘ አይደለም ጥንት ሳይኖራቸው ዘመን ሳይቀድማቸው ከዘመን አስቀድሞ የነበሩ ናቸው እንጂ) በማለት ሊቁ አስተምሯል (መዝ ፹፱፥፪፤ ኢሳ ፵፩፥፬፤ ራእ ፳፪፥፲፫)፡፡

በአጠቃላይ እግዚአብሔር በአንድነት የሚጠራባቸው ስሞች ሲኖሩት ለምሳሌ ያኽልም የአንድነቱ ስሞች
✔አምላክ – (መዝ 17(18)፡31) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “አምላክ” የሚለው ቃል 1037 ጊዜ ተጠቅሷል
✔እግዚአብሔር – (ዘፀ 15፡3) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “እግዚአብሔር” የሚለው ቃል 7361 ጊዜ ተጠቅሷል
✔እግዚእ (ጌታ፤ Lord) በዕብራይስጥ “ያህዌ” – (ዘፀ 6፡3-8) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ጌታ” የሚለው ቃል 1515 ጊዜ ተጠቅሷል
✔አዶናይ – ሕዝ 7፡2-5

✔እግዚአ ጸባዖት (የሰራዊት አምላክ የሰራዊት ጌታ) – (ኢሳ 6፡3) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የሰራዊት ጌታ” የሚለው ቃል 210 ጊዜ ተጠቅሷል
✔እግዚአብሔር አምላክ – (ዘፍጥ 2፡4፤8) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “እግዚአብሔር አምላክ” የሚለው ቃል 696 ጊዜ ተጠቅሷል
✔ኤሎሄ “ኤሎሂም” (’Elohim) – (መዝ 21(22)፡1፤ ማቴ 27፡46፤ ማር 15፡34)

✔✔✔[እነዚኽ ስሞች ግብራተ ባሕርይን እንደሚያመላክቱ ጠቅሰው ያስተማሩ መምህራን አሉ፤ ይኸውም ስለፈጠረ ፈጣሪ፤ ስለተመለከ አምላክ፤ ስለሚያስተዳድርና ስለሚመግብ ሠራዒ መጋቢ፣ ሁሉን ስለሚገዛ ንጉሥ፤ ሕያው ስለሚያደርግና ስለሚያድን ማሕየዊ፤ ስለሚረዳ ረድኤት፤ መጠጊያ ስለሚኾን ጸወን፣ ምስካይ፤ ስለሚታደግ ስለሚመክት ኀይል፣ ጋሻ በመባል ራሱን በሚገልጽበት ግብሩ መሠረት ይጠራል ይላሉ (መዝ 17፤ 90) ፡፡

✔✔የአካል ሦስትነታቸውንም ስናይ፡- አብ በተለየ አካሉ ፍጹም አካል፣ ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም መልክእ አለው፤ ወልድም በተለየ አካሉ ፍጹም አካል፣ ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም መልክእ አለው፤ መንፈስ ቅዱስም በተለየ አካሉ ፍጹም አካል፣ ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም መልክእ አለው (ዘፍ 18፡2፤ ማቴ 3፡17፤ ማር 1፡10-11፤ ሉቃ 3፡21-22፤ ዮሐ 1፡32-34፤ ዮሐ 16፡27-28፤ 15፡26-27፤ 2ቆሮ 13፡14)፡፡

✔✔ይኽነንም ምስጢር ሊቁ አቡሊዲስም በሃይማኖተ አበው ላይ “ነአምን በአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ከመ ፫ቱ ገጻት ፍጹማነ መልክእ ወአካል እሙንቱ እንዘ አሐዱ መለኮቶሙ” (ባሕርያቸው በእውነት አንድ ሲኾን በመልክ፣ በአካል ፍጹማን የሚኾኑ ሦስት ገጻት እንደኾኑ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን) በማለት በጥልቀት ገልጾታል፡፡

✔ይኽ አካላቸውም ምሉእ በኲለሄ (በኹሉ የመላ)፣ ስፉሕ፣ ረቂቅ ሲኾን ዳር፣ ድንበር፣ ወሰን፣ ዳርቻ የለውም፡- ከጽርሐ አርያም በላይ ቁመቱ፤ ከበርባሮስ በታች መሠረቱ፤ ከአድማስ እስከ ናጌብ ስፋቱ ተብሎ አይመረመርም፤ ቢመረመርም አይገኝም ኹሉንም ሥላሴ ይወስኑታል እንጂ የሚወስናቸው ማንም የለም፡፡

✔የሥላሴ አካላቸውም ምሉእ በኲለሄ፣ ስፉሕ፣ ረቂቅ ሲኾን ዳር፣ ድንበር፣ ወሰን፣ ዳርቻ የለውም፡- ከጽርሐ አርያም በላይ ቁመቱ፤ ከበርባሮስ በታች መሠረቱ፤ ከአድማስ እስከ ናጌብ ስፋቱ ተብሎ አይመረመርም፤ ቢመረመርም አይገኝም ኹሉንም ሥላሴ ይወስኑታል እንጂ የሚወስናቸው ማንም የለምና፤ በመጽሐፈ ቀሌምንጦስ እንደተጻፈ ቅዱስ ጴጥሮስ ምሉእ በኲለሄ መኾናቸውን በመረዳት ጌታውን “ይኽቺ ዓለም በአንተ ዘንድ እንዴት ናት?” በማለት ጠየቀው ጌታም ለወዳጆቹ ቸር ነውና ይኽነን ዓለም በመኻል እጁ ይዞ ነፋሳት ሲነፍሱ፣ ውሆች ሲፈስሱ፣ ብርሃናት ሲመላለሱ አሳይቶ “አይቴ ሀሎከ ጴጥሮስ” (ጴጥሮስ ወዴት አለኽ?) ቢለው ጴጥሮስም “አቤቱ ጌታዬ ከሰማይ ከምድር ጋር በመኻል እጅኽ ተይዣለኊ) ብሎታል፤ ሊቁ አባ ሕርያቆስም ከዚኽ በመነሣት “አኮ ዘቦቱ ለመለኮት ምድናን ወአትሕቶ ርእስ ከመ ይንሣእ እምድር ዘኮነ ውስቴታ አላ ኲሉ እኁዝ ውስተ እዴሁ በከመ አርአዮ ለጴጥሮስ” (ለመለኮት ከምድር የኾነውን ያነሣ ዘንድ ማጐንበስ የለበትም ለጴጥሮስ እንዳሳየው ኹሉ በእጁ የተያዘ ነው እንጂ) በማለት ምሉእነቱን አስተምሯል፡፡

✔✔በመጽሐፈ ቀሌምንጦስም ምሉእነቱን ሲገልጽ “ንሕነ ናገምሮ ለኲሉ ወአልቦ ዘያገምረነ አልቦ ወኢምንትኒ እምታሕቴነ አስመ ለኲሉ የዐውዶ ዕበየ ኀይልነ አልብነ ውሳጤ ወአፍኣ አልቦ ሰማይ ዘያገምረነ ወኢምድር ዘይጸውረነ” (ኹሉን እኛ እንሸከመዋለን እንጂ እኛን የሚሸከመን የለም፤ ከኛ በላይ ከኛም በታች ቦታ የለም፤ የባሕርያችን ምልአት ኹሉን ይወስናል እንጂ የሚወስነው የለም) በማለት አስተምሮታል፡፡

✔✔✔ርቀታቸውም እንዴት ነው ቢሉ? ከኹሉ ነፋስ ይረቃል፤ ከነፋስ ነፍሳት ይረቃሉ፤ ከነፍስ መላእክት ይረቃሉ “ኀለፈ መልአክ በመልአክ ሠጢቆ ነፋሰ” እንዲል ለተልእኮ ሲፋጠኑ አንዱ መልአክ በአንዱ ውስጥ ሲተላለፉ አይከላከሉም፤ ይኽም ብቻ ሳይኾን ሥላሴ ለተልእኮ ሲጠሯቸው ወደ ላይ እስከ ጽርሐ አርያም ወደ ታች እስከ በርባሮስ እንደ ዐይን ጥቅሻ ደርሰው የታዘዙትን ፈጽመው ወደ ቦታቸው ተመልሰው ፈጣሪያቸውን በአንድነት በሦስትነት ያመሰግናሉ፤ ከአካላቸው ኅሊናቸው በእጅጉ ይረቃል፤ ይኽ የኅሊናቸው ርቀት በሥላሴ ዘንድ ግን እንደ አምባ እንደ ተራራ የገዘፈ ነውና፤ ሊቁ አረጋዊ መንፈሳዊ በመጽሐፉ ላይ “ቅጥነተ ኅሊናሆሙ ለመንፈሳውያን በኀበ ቅጥነቱ ከመ እንተ ሥጋ ገዚፍ” (የመንፈሳዉያን የኅሊናቸው ርቀት በአንተ ዘንድ ካው ረቂቅነት እንደ ሥጋ የገዘፈ ነው) በማለት አስተምሯል፡፡ በዚኽም ርቀታቸው በፍጥረቱ ኹሉ ምሉኣን ኅዱራን ናቸው “ወውስተ ዓለም ሀሎ ወዓለምኒ ቦቱ ኮነ” (በዓለም ነበረ፤ ዓለሙም በርሱ ኾነ) እንዲል (ዮሐ ፩፥፲፤ ፬፥፳፩፤ መዝ ፻፴፰፥፯-፲፩፤ ፩ነገ ፰፥፳፯፤ ኢሳ ፵፥፫፤ ፷፮፥፩)፡፡

✔✔እውነታው ይኽ ኾኖ ሳለ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ በድፍረት ኾነው የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ከመሠረቱ ለማፍረስ በመነሣት ሰባልዮስና ተከታዮቹ የሥላሴን አካላት በየዘመናቱ በማቀያየር፤ አይሁዶች ይስማኤላውያን የሥላሴን አካላት በመካድ፤ አርዮስ፣ መቅዶንዮስ በጊዜያችን ደግሞ የጆባ ዊትነስ እምነት አራማጆች ደግሞ ከሦስቱ አካላት ኹለቱን አካላት ወልድና መንፈስ ቅዱስን ከእግዚአብሔር ሦስትነት ነጥለው ለማውጣት የተነሡ አሉ፤ እነዚኽንም “በምስጢረ ሥላሴ ላይ የተነሡ የስሕተት ትምህርቶችና መልሶቻቸው” በሚለው ውይይታችን ጊዜ ከነመልሳቸው በስፋት የምናያቸው ቢኾንም፤ ሊቃውንት ከነዚኽ የስሕተት ትምህርት እንድንርቅ ሲያስተምሩን:-

✔✔✔(በአይሁዳዊነትና በሰባልዮሳዊነት እምነት “አንድ አካል በማለት አላምንም”፤ ተጠንቀቅ በመረዳት ከችግረኛው ከሰባልዮስ እንሽሽ፤ ርሱ ሦስቱን አካላት ኹሉ አንድ ያደርጋልና፤ ለሦስቱም አንድ አካል ብቻ እንዳላቸው ያምናል፤ እኛ ግን ሦስቱ በየአካላቸው ህልዋን /ነዋሪዎች/ ናቸው ብለን እናምምንባቸዋለን) ቅዱስ ቴዎዶስዮስ ዘእስክንድርያ ሃይ.አበ ገጽ 466 ክፍል 1 ቊ8

✔✔✔(ቅድስት ሥላሴን አንድ ገጽ አንድ አካል አናድርግ ቅድስት ሥላሴን በአንድ አካል እንደሰበሰበ እንደ ዝንጉው እንደ ሰባልዮስ ማድረግ ነውና… በዚኹም ትምህርት ሰባልዮስን እናወግዘዋለን፤ ርሱ ሦስት ስሞች አንድ አካል ናቸው ብሏልና ርሱ ሥላሴን በየዘመናት ከፋፍሎ አብ የተባለበት አንድ ዘመን ነበረ፤ ወልድ የተባለበት አንድ ዘመን ነበረ፤ መንፈስ ቅዱስ የተባለበት አንድ ዘመን ነበረ እያለ፤ ይኽ ዝንጉ ሰው እነዚኽን ስሞች አንድ አካል ሊያደርጋቸው ይፈልግ ነበረ፤ እኛ ኦርቶዶክሳውያን ግን የተጸየፈች የማትረባን ትምህርቱን እንጠላለን፤ ይኸውም አብ ለዘላለሙ አብ ነው፤ ያለመለወጥ ያለመለዋወጥም በአካሉና በገጹ ነዋሪ ኾኖ የጸና ነውና፤ እንደዚኹም ወልድ በአካሉና በገጹ ጽኑዕ ነው፤ አብና መንፈስ ቅዱስ ለመኾንም አይለወጥም እንደዚኹም መንፈስ ቅዱስ በአካሉ በገጹ ጽኑዕ ነው፤ አብና ወልድን ለመኾንም አይለወጥም) ሱንትዩ ሊቀ ጳጳሳት ዘስእክንድርያ ሃይ. አበ ገጽ 489፤ 496፤ ክፍል 1፡8፤11-12

✔✔✔(የሰው ኹሉ መዠመሪያ እንደኾነ እንደ አዳም አንድ ነው አንልም፤ ነገር ግን በባሕርይ አንድ ሲኾን በአካሉ ሦስት ነው እንላለን እንጂ፤ ክፉዎች አይሁድን በደለኞች እስማኤላውያንን እነሆ እናያቸዋለንና እግዚአብሔርን አካል አንድ ገጽ ሲሉ ባለማወቃቸው በልቡናቸው የታወሩ ናቸውና) አባ ሕርያቆስ፤ ቅዳሴ ማርያም ቊ 70
(ለሥላሴ ፍጹም አካል፣ ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም መልክእ እንዳላቸው መጽሐፍ ቅዱስ በስፋት ያስተምራል፡- (ዘፍ ፫፥፳፪፤ መዝ ፴፫፥፲፭-፲፮፤ ፻፲፰፥፸፫፤ ፻፴፩፥፯፤ ኢሳ ፷፮፥፩፤ የሐዋ ፯፥፵፱፤ ራእ ፩፥፲፬ን ተመልከቱ)
ይቀጥላል
አዘጋጅ መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (በ2005 ዓ.ም የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የዶግማ መምህር በነበርኩበት ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ ካዘጋጀኹት ኖት በጥቂቱ የተወሰደ)

በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ 

የእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት ምስጢር

ምስጢር የሚለው ቃል አመሰጠረ፣ ሰወረ፣ አረቀቀ ከሚለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ፍቺውም ረቂቅ፣ ስውር፣ ኅቡዕ ማለት ነው፡፡ ምስጢር መባሉም የሥላሴን ባሕርይ ፍጡር መርምሮ የማይደርስበት በመሆኑ፣ በፍጡር ባሕርይ መወሰን፣ መጨረሻውን ማወቅ የማይቻልና ከፍጡር እውቀት አቅም በላይ በመሆኑ ነው፡፡ ሥላሴ የሚለው ቃል ደግሞ ሠለሰ ሦስት አደረገ ካለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ሦስትነት ማለት ነው፡፡ ቅድስት ሥላሴ: – ለሥላሴ ቅድስት ብለን እንቀጽላለን፡፡ ቅድስት ሥላሴ ማለት ልዩ ሦስትነት ማለት ነው፡፡ ይህም ሦስት ሲሆን አንድ፣ አንድ ሲሆኑ ሦስት ስለሚሆኑ ልዩ ሦስትነት ተብሏል፡፡
ስለዚህ ነገር መጽሐፈ ቅዳሴያችን ሥላሴ ሦስት ናቸው ስንል እንደ አብርሃም እንደ ይስሐቅ እንደ ያዕቆብ ማለታችን አይደለም ሦስት ሲሆኑ አንድ ናቸው እንጂ፣ አንድ ናቸውም ስንል ቀዳሚ ሆኖ እንደተፈጠረው እንደ አዳም ማለታችን አይደለም አንድ ሲሆኑ ሦስት ናቸው እንጂ፡፡ /ቅዳሴ ማርያም/፡፡ ቅድስት ተብሎ በሴት አንቀጽ መጠራቱ ደግሞ እናት ለልጇ ስለምታዝንና ስለምትራራ ሥላሴም ለፍጥረታቸው ምሕረታቸው ዘለዓለማዊ ነውና ቅድስት ይባላሉ፡፡
በዚህ መሠረት ምሥጢረ ሥላሴ ማለት የአንድነት የሦስትነት ምስጢር ማለት ነው፡፡
ይኸውም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በስም፣ በአካል፣ በግብር ሦስት ሲሆኑ በባሕርይ በሕልውና፣ በመለኮት ደግሞ አንድ ናቸው፡፡ እንደዚህ ባለ ድንቅ ነገር አንድ ሲሆኑ ሦስት፣ ሦስት ሲሆኑ አንድ ይባላሉና፣ ይህም ልዩ ሦስትነት ረቂቅ እና በሰው አእምሮ የማይመረመር ስለሆነ ምስጢር ይባላል፡፡
የሰው ልጅ ሁሉን የመመርመርና የመረዳት መብትና ሥልጣን… ተጨማሪ ያንብቡ

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top