አራቱ ዓለም ዐቀፍ ጉባዔያት

አንደኛው ዓለም ዐቀፍ ጉባዔ /የኒቂያ ጉባኤ/ (ሲኖዶስ) 325 .

 

መንስኤው አርዮስ የሚባል ካህን የምንፍቅና አስተምህሮ ነው፡፡

መንስኤው አርዮስ የሚባል ካህን የምንፍቅና አስተምህሮ ነው፡፡
አርዮስ ፡- በ 260 ዓ.ም በሊቢያ ከግሪካዊ ክርስቲያን ቤተሰብ ተወለደ፡፡
በእስክንድርያም በአንጾኪያም በከፍተኛ ደረጃ የመጽሐፍቶችን የስነ መለኮት ትምህርት ተምሯል፡፡
የአንጾኪያው መምህሩ ሉቅያኖስ (የአርጌንስ ደቀመዝሙር እና የአንጾኪያ ትምህርት ቤት መስራች)ነበር፡፡
የክህደት ትምህርቱ ለአንጾኪያዊያን አስተምህሮ የቀረበ ነው፡፡
የንግግር ችሎታ ያለው እና ሰውን ማሣመን የሚችል አንደበተ ርቱዕ ሲሆን፤ በዚህም በተፍጻሚተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ ድቁናን ተሾመ፡፡
ከመንፈሣዊ ትምህርት በተጨማሪ የግሪክ ፍልስፍናም በደምብ የተማረ ነው፡፡
ከሉቅያኖስ በተጨማሪ የተሳሳቱ የሥላሴ አስተምሮዎቹን ከእስክንድሪያው ሊቅ ከአርጌንስም እንደተጠቀመ ይጠቀሳል፡፡

የአርዮስ ትምህርት

አብ ብቻ ዘለዓለማዊ (ዘአልቦ ጥንት ወኢተፍፃሜት)ወልድ ዘለዓለማዊ አይደለም፡፡ ያልነበረበት ጊዜ ነበር (ሀሎ አመ ኢሄሎ) ስለዚህ አብ ከዘመናት በፊት ‘አብ’ አይባልም ፤ አብ መባል የጀመረው ከወልድ መፈጠር በኋላ ነው፡፡ በመሆኑም ‘ወልድ ፍጡር ነው’
ለወልድ ጥበብ ፣ ቃል የሚባሉ የኃይላት ስሞች አሉት፡፡ ለዚህም እንደ ማስረጃ የሚጠቅሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ምሳ 8÷22 ፣ ዩሐ 14÷28 ‘‘አብ ከእኔ ይበልጣል’’ ፣ “ጥበብ ከፍጥረቱ ሁሉ አስቀድሞ እኔነረ ፈጠረኝ አለች ’’ የሚለውን ነው፡፡
ወልድ በባሕርይው ከአብ ጋር አንድ አይደለም ፤ ይሁን እንጂ ከሌሎች ፍጡራን ይበልጣል፡፡ ለዚህም “ወልድ’’ በጸጋ የአብ ልጅ ይባላል፤ የፀጋ አምላክ ይባላል፡፡ ስለዚህ ም እንደፍጡርነቱ የአብን ባሕርይ ማየትም ማወቅም አይችልም፡፡
መንፈስ ቅዱስ ለወልድ የመጀመሪያ ፍጥረቱ ነው፡፡

ምክር እና ተግሣጽ

ይህን የተሳሳተ ትምህርቱን የሰማው ቅዱስ ጴጥሮስ (ተፍጻሜተ ሰማዕት) ጠርቶ በመምከርና ስህተቱን እንዲያስተካክል ቢነግረውም እምቢ በማለት ትምህርቱን በስፋት መናገር ቀጠለ፡፡ በዚህም አውግዞ ከዲቁናው ሽሮታል፡፡ ይህን ሲያደርግ በራዕይ ጌታ አርዮስ ልብሱን ሲቀድ በማየቱ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህን ራዕይ ያየው በድዮቅሊጥያኖስ ተይዞ ለመገደል በእስር ላይ እያለ ነበር፡፡
አርዮስ ይህን አውቆ (ቅዱስ ጴጥሮስ ሊገደል እንደሚችል) ከእስራቱ እንዲፈታው ሽማግሌ ቢልክበትም ከጌታ በተሰጠው ማስጠንቀቂያ መሠረት ከውግዘቱ ሳይፈታው ቀርቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለደቀመዛሙርቱ ለእለእስክንድሮስ እና ለአርኬላዎስ አርዮስን ከውግዘቱ እንዳይፈቱት አስጠንቅቋቸዋል፡፡
ከቅዱስ ጴጥሮስ በኋላ በእስክንድርያ መንበር ላይ ፓትሪያርክ ሆኖ የተሾመው አርኬላዎስ አርዮስ የተፀፀተ መስሎ ስለቀረበውና ጓደኞቹም በምልጃ ስለለመኑት የመምህሩን ማስጠንቀቂያ ትቶ ከውግዘቱ የፈታው ሲሆን ቅስናም ሾሞታል፡፡
ከአርኬላዎስ በኋላ ዘመኑን ሁሉ ስለ ቤተ ክርስቲያን ሲጋደል የኖረው ስመጥሩው እለእስክንድሮስ በእርሱ ቦታ በእስክንድርያ መንበር ላይ ፓትሪያርክ ሆኖ ተመርጧል፡፡
እርሱም የአርዮስን ትምህርት ተቃውሞ አወገዘው፡፡ እንደቀድሞው ብዙ አማላጅ ቢልክለትም ጌታ በራዕይ መመለሱን ሲያሳየኝ ብቻ ነው የምፈታው በማለት አሻፈረኝ ብሏል፡፡
አርዮስም ብዙ ሰው በቀላሉ ሊከተለው እና በትምህርቱ ሊማረክ በሚችል መልኩ ትምህርቱን በግጥም በዘፈን (በመዝሙር) በመነባንብ እያደረገ ማሰራጨት ችሎ ነበር፡፡ ይህም ሥራው “ታሊያ ወይም ማዕድ›› ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡

 

የኒቂያ ጉባዔ ሂደት

ከተፍፃሜተ ሰማዕት እና ከእለእስክንድሮስ በግል ማውገዝ በኋላ ቅዱስ እለእስክንድሮስ ሦስተኛውን ውግዘት በማህበር በ 318 100 የሚሆኑ የእስክንድርያ እና የሊቢያ ኤጲስ ቆጶሳትን ሰብስቦ የስህተት ትምህርቱን ካስረዳቸው በኋላ በአንድ ድምፅ አውግዘውታል፡፡
በዚህም ወደ ሶርያና አንጾኪያ በመሄድ እለእስክንድሮስ የሰባሊዮስን ኑፋቄ እንደሚያስተምር እና እሱንም ያለ አግባብ እንዳወገዘው የቀድሞ የት/ቤት ጓደኞቹ ለሆኑት ለኒቆሞድያው አውሳቢዮስ እና ለቂሳርያው አውሳቢዮስ በመንገር በእነሱ አካባቢ ትምህርቱን ማስፋፋት ቀጠለ፡፡
በ 322 እና በ 323 ሁለት ጊዜ የእርሱ ደጋፊዎች ተሰብስበው ትምህርቱን በመደገፍ እና እርሱን ከውግዘት በመሻር ትምህርቱን እንዲያስፋፋ ፈቀዱለት፡፡ በትምህርቱም መስፋፋት ከሮም ጀምሮ መላው ዓለም በትምህርቱ ታወኩ፡፡ መምህራን ከመምህራን መነታረክ ጀመሩ፡፡ ይህም ንትርክ ከቤተክርስቲያን አልፎ ለሀገር ጭምር የሚያሳስብ ሆነ፡፡
ንጉሥ ቆንስጠንጢኖስም ይህን ውዝግብ በዲፕሎማሲ እና በሰላም ሊፈታው ቢሞክርም የማይሆንለት ስለሆነ ዓለም አቀፍ ጉባኤ እንዲደረግ ጥሪ አደረገ፡፡
ጉባኤው << በአንካራ >> እንዲካሄድ ተወሠነ ፤ በኋላ ለመናገሻ መንግሥቱ (ቆስጠንጥንያ) ቅርብ ወደሆነችው እና ለመጓጓዝ ወደ ምታመቸው ‹‹ኒቂያ›› ተዘዋወረ፡፡
318 ኤጲስ ቆጶሳት እና ተከታዮቻቸው ሙሉ ወጪያቸው በመንግሥት ተሸፍኖ በጉባኤው ተገኙ፡፡ እነዚህ ጳጳሳት በንጽሕናቸው/በቅድስናቸው/ የተመሠከረላቸው ገቢረ ተአምራትን የሚያደርጉ ከዘመነ ሰማዕታት ስደት የተለያየ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው የተረፉ ነበሩ፡፡ በዚህም ምክንያት (አብዛኞቹ አካለ ጎዶሎዎች) እንደሆኑ ታሪክ ያስረዳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም 20 አርዮሳውያን ፣ አርጌንሳዊያንችና ፈላስፋዎችም በጉባኤው ላይ ነበሩ፡፡
ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤው ከሰኔ 14 -ሐምሌ 25 ነው ሲሉ፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጉባኤው ከመስከረም 21- ህዳር 9 ነው ብላ ታስተምራለች፡፡ (ከቄልቄዶን ጉባኤ በፊት በአንድነት ይህንን ጉባዔ የምንቀበል (የሮም፣ የምስራቅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እና የእህት ቤተክርስቲያኖች) ይህንን ነው ጉባዔ ስለምንቀበል ምርመራ ተደርጎ አንድ ወደ ሚያደርገን ቀን መምጣት ይቻላል)
የጉባኤው ፕሬዝዳንት ንጉሠ ነገሥቱ ነው ቅዱስ አትናቲዮስ

ሊቃነ መናብርቱ እለ-እስክንድሮስ ከእስክንድርያ ቤተክርስቲያን ኤዎስጣቴዎስ == ከአንጾኪያ ቤተክርስቲያን

ኦስዮስ == የኮርዶቫ (ስፔን)ቤተክርስቲያን ናቸው።
ከ 318 ኤጲስ ቆጶሳት በተጨማሪ በኦርቶዶክስ አስተምሮ የጠለቀ እውቀት የነበራቸው ሰዎች ነበሩ ፡- ከነዚህም በዋናነት የሚጠቀሰው የእለእስክንድሮስ ጸሐፊ ቅዱስ አትናቴዎስ ነው፡፡

በጉባኤው ላይ ከተገኙ ኤጴስ ቆጶሳት መካከል በከፊል

የኢየሩሳሌሙ መቃርዮስ ፤የእንቆራው ማርሴሎስ ፤የቲቤቱ(ቴባስ) ፓፋንተስ-፤ የሔራቅሊጠሱ ጶጣምን ሁለቱም አካል ጉዳተኞች ነበሩ ፤የአዲስቱ ቂሳርያ – ጳውሎስ ፤ የኒሲቢው ያዕቆብ – በጳጳስነት ዘመኑ እንኳን የበግ እረኛ ነበር፡፡የፋርሱ ዩሐንስ ፤ የጎቲክ ፤ቴዎፍሎስ እና ስታራቶፊለስ ከምዕራብ ፤ የካላበራው ማርቆስ(ኢጣሊያ)የሊቢያ(ቅርጣግ/ካርቴጅ/) – ሲሲሊየን
የስፔኑ – ሆስየስ የኮርዶቫው

የጉባኤው አጀንዳ

ከእርዮስ የምንፍቅና አስተመህሮ በተጨማሪ ከዛ በፊት የነበሩ እና እስከዚህ ጉባኤ የዘለቁ ቤተክርስቲያንን ሲለያዩ እና ሲያበጣብጡ የነበሩ የተለያዩ ጉዳዮች የዚህ ጉባኤ አጀንዳዎች ነበሩ፡፡
የአርዮስ ኑፋቄ (የምንፍቅና አስተምህሮ) ጥያቄ

የፋሲካ አከባበር
የሜሊጢዮስ ኑፋቄ(መለያየት)
የአብ እና የወልድ አንድነት በአካል ወይስ በሥራ
የመናፍቃን ጥምቀት ናቸው


የጉባኤው ቡድኖች

በትምህርቱ ሚስጢራዊነት እና በወቅቱ በነበረው የትምህርቱ ክብደት ምክንያት በጉባኤው ላይ ሦስት ዓይነት ቡድኖች ነበሩ፡-
ኦርቶዶክሳዊያን፡
እለእስክንድሮስ
ኤዎስጣቴዎስ
ኦስዮስ
ማርሴሎስ
አትናቴዎስ (ዲያቆን)
አርዮሳውያን
አርዮስ
የኒቆሞዲያሱ አውሳብዮስ (የንጉሡ ወዳጅ)
የኒቂያው ቴአግኒስ
የኬልቄዶኑ ማሬስ (በኋላ የተመለሠ)
የኤፌሶኑ ሜኑፋንቱስ
መንፈቀ አርዮሳውያን(መሀል ሠፋርያን)
-የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊው የቄሳርያው አውሳቢዮስ በኋላ ኦርቶዶክሳዊ የሆነ ክርክሩ
አርዮሳዊያን ፡- ወልድን “ዋሕድ ባሕርየ ምስለ አብ / ከአብ ጋር አንድ ባሕርይ” “Omoousious” የማይል የተወገዘ ይሁን የሚል የሃይማኖት መግለጫ አቅርበው ተቃውሞ ደርሶባቸዋል፡፡
አርዮስም በጉባኤው ተጠይቆ ከላይ የአርዮስ አስተምሮ የሚለውን ገልጿል፡፡
አርዮስ ፡- ወልድ የጸጋ አምላክ ስለሆነ ስግደት ይገባዋል፡፡


የቅዱስ አትናቲዮስ መከራከሪያ

*** ወልደ-አብ ኢየሱስ ክርስቶስ መድኃኒት ነው ፤ አዳኛችን ነው፡፡
የሚያድን እግዚአብሔር (አምላክ) ብቻ ነው ፤ መጽሐፍት የሚያስተምሩት ይህንን ነው፡፡
ወልድ አምላክ ካልሆነ እኛም አልዳንም፡፡
በእርሱ መዳናችንን ካመንን ያዳነን እርሱ አምላክ ነው ፤ ፍጡር ማዳን አይችልምና፡፡
*** አትናትዮስ ፡- ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ አንድ ነው ፡፡ ወልድ ፍጡር ከሆነ ለእርሱ የአምልኮ ስግደት ማቅረብ ባዕድ አምልኮ ነው፡፡
‘ቦ አመ ኢሀሎ’ ወልድ ያልኖረበት ጊዜ የለም ዘላለማዊ ነው፡፡
የአርዮስ ደጋፊዎቹ/መንፈቀ አርዮሳውያን/ ወልድን Omo-ousious (ከአብ ጋር አንድ ባሕርይ) በማለት ፈንታ Omoi-ousious (የወልድ ባሕርይ ከአብ ባሕርይ ጋር ተመሳሳይ) ነው ብለው ሀሳብ አቀረቡ፡፡
በመጨረሻም አርዮስን እና መንፈቀ አርዮሳውያንን በማውገዝ ወልድ በባሕርይው ከአብ ጋር አንድ ነው ብለው አጽድቀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም 7 አንቀጽ ያለው ‘በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን’ እስከሚለው ድረስ ያውን የሃይማኖት መግለጫ አዘጋጁ፡፡
ከዚህም ባሻገር፡-የትንሳኤ በዓል መቼ መከበር እንዳለበት ተወሠነ፡፡
ቀድሞ ምዕራባዊያን Dec -25 ልደቱ ታህሣስ -29 በምስራቅ ሲሆን ፋሲካ ግን ቀኑ የተወሠነ ባለመሆኑ ሚያዚያ- 14 በማናቸውም ቀን ቢውል (የአይሁድ ፋሲካን መሠረት በማድረግ) ይከበር ነበር እነዚህም Quarto Decmians (ባለ 14ኛ ቀናት) ተብለው ይጠሩ ነበር፡፡
የጉባኤው ውሳኔ ፡- ከሚያዚያ 14 በኋላ በሚውለው እሁድ እንዲከበር ይህንንም የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን እንድታሳውቅ
ሜሊጢያስ መለያየት ፡-በዲዮቅልጢያኖስ ስደት ምክንያት የተሠወረው (ስደቱን ሽሽት) ጴጥሮስ (ተፍጻሜተ ሰማዕት) ጊዜ ሜሊጢዮስ በእስክንድርያ ጣልቃ በመግባት (ያለ ክልሉ) ኤጲስ ቆጶሳትን ሕግ በመተላለፍ መሾም ጀመረ፡፡ አንዳንዶችንም አወገዘ ፤ ጴጥሮስ ከተሠወረበት ሲመጣም ሜሊጢየስን አወገዘው፡፡ እርሱ ግን ይቅርታም ሳይጠይቅ ሥራውን ዝም ብሎ ቀጠለ፡፡ በዚህም ምክንያት ውዝግቡ እና ፀቡ እስከ ኒቂያ ጉባኤ ድረስ ቀጥሎ ነበር፡፡
ጉባኤውም ሰላም ለማውረድ 29 የሜሊጢየስን ጳጳሳት ሹመታቸውን ቢቀበልም በኋላ ላይ ከአርዮሳውያን ወግነዋል፡፡
ጉባኤው በተጨማሪም በስደት ጊዜ ሃይማኖታቸውን የቀየሩ ኦርቶዶክሳዊያንን በንስሐ እና በጥምቀት መልሷል፡፡
ሌሎች ጉዳዮች
እራስን ጃንደረባ ማድረግን መከልከል
ለንዑስ ክርስትያኖች የአመክሮ ጊዜ
አንድን ጳጳስ ለመሾም ሦስት ጳጳሳት መኖር እንዳለባቸው
የቅዱስ ቁርባን ተቀባዮች ቅደም ተከተል – ጳጳስ ፣ ካህን ፣ ዲያቆን …..
ስግደት ፡- በቅዳሴ ሰዓት ፣ በሰንበት ፣ በበዓለ አምሳ እንደማይገባ ጉባኤው ወስኗል፡፡

ድኅረ ኒቂያ ጉባኤ

በ 328ዓ.ም የእስክንድርላ ሊቀ ጳጳስ እለእስክንድሮስ ከዚህ ዓለም በሞት ስለተለየ በእርሱ ምትክ የኒቂያ ጉባኤው ሻምፒዮን ቅዱስ አትናቲዮስ በሊቀ ጳጳሱ ኑዛዜ እና በመላው ሕዝብ በሙሉ ድምጽ የእስክንድርያ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ሆኖ ተሾመ፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ አባ ሰላማም (ከሳቴ ብርሃን) በዚህ ወቅት ነበር ለኢትዮጵያ ተሹሞ የመጣው
አርዮሳዊያን ተቃውሞአቸውን ከበፊቱ አስበልጠው አጠንክረው የቀጠሉ በመሆኑ እስከ እለተ ሞቱ ሲታገላቸው ኖሯል፡፡ ለዚህም በመላው ሕዝበ ክርስቲያን ‘ታላቁ አትናቴዎስ’ (Atnatisus the Great) በመባል ይታወቃል፡፡
ከአርዮሳውያን ጋር በሚያደርገው ትግል ብቻውን የሆነ ያህል የነበረበት ጊዜ ስለነበረ (አርዮሳውያን በጣም ከማየላቸው የተነሣ) ‘ዝም ብለህ ነው የምትደክመው አንተ እኮ ብቻህን ነህ ዓለም በሙሉ ከእኛ ጋር ነው’ ተብሎ ሲዘበትበት ያለው ነገር “አንድ ብቻዬንም ሆኜ ዓለምን እቃወማለሁ ብቻዬንም እታገላችኋለው›› ያላቸው ሲሆን ያን ያህል ብዙ ተከታይ ማፍራት ችለው እንደነበር ያሳያል፡፡
አርዮሳውያን ከንጉሡ ጋር በመወዳጀት እንዲሁም አርዮሳውያንን የሚደግፍ ንጉሥ በተነሣ ወቅት ሁሉ በተደጋጋሚ ቅዱስ አትናቴዎስን ከመንበሩ አባርረው የሕዝቡን ተቃውሞ ሁሉ ቸል በማለት አርዮሳዊ የሆነ ጳጳስ ሲሾሙ ነበር፡፡
አትናቴዎስንም በተለያዩ ወንጀሎች እየከሰሱ ከነገሥታቱ ሊያጣሉ ሲሞክሩ ኦርቶዶክሳዊ ንጉስ ወይም ለዘብተኛ ንጉሥ ሲሾም ከተደበቀበት ወደ መንበሩ እየተመለሠ ሲከፋም እየሸሸ ወይም እየተያዘ እየተጋዘ(እየታሠረ) ለ 46 ዓመታት ጳጳስ ሆኖ ሲቆይ ከእነዚህ ዓመታት ውስጥ 15 ቱን ዓመታት ያሳለፈው በግዞትና በስደት ነበር፡፡ ይህም 5 ጊዜ በተደጋጋሚ ለስደት እና ለግዞት ተዳርጓል፡፡
በእነዚህ ዓመታት አርዮሳዊ የሆነ ጳጳስ ተሹሞ ለኢትዮጵያዊያን አባት አርዮሳዊ ጳጳሽ ለመሾም ደብዳቤ የጻፈ ቢሆንም የወቅቱ ነገሥታት ጥያቄውን ሳይቀበሉ ቀርተዋል፡፡
ቅዱስ አትናቴዎስ ‘ቅዱስ እንጦስ’ የሚለውን የመጀመሪያውን መነኩሴ አባት ታሪክም የጻፈው በዚህ ወቅት በስደት እያለ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቅዱስ አትናቴዎስ
Againest Ariars (ለአርዮስ መልስ)
Againest The Athen (ለአሕዛብ መልስ) እና
ብዙ ደብዳቤዎችን በዘመኑ ጽፏል፡፡ በታላቅ ስራዎቹም ምክንያት አትናቴዎስ ሐዋርያዊ በመባል ይታወቃል፡፡
የአርዮስ ሞት ፡- አትናቴዎስ በስደት እያለ አርዮስ ከክህደቱ ተመለስ በሚል ጓደኞቹ በእስክንድርያ ታላቅ አቀባበል አድርገውለት በቁስጥንጥያ ከሊቀ ጳጳሱ ጋር እንዲቀድስና በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ለማድረግ ሲዘጋጅ የሆድ ህመም ተሰምቶት መፀዳጃ ቤት ሲሄድ በዛ ሆዱ ተዘርግፎ ሞተ፡፡
ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ምንም እንኳን ለቤተክርስቲያን ነጻነትን የሰጠ እና ብዙ እገዛ ያደረገ ቢሆንም የሃይማኖት ሰው አልነበረም እና ኃይል ወደ አመዘነበት እያጋደለ በስተመጨረሻም ወደ ክርስትና የሚያስገባውን ጥምቀት የተጠመቀው በሞት አፋፍ ላይ በነበረበት ወቅት በአርዮሳዊው ወዳጁ እጅ ተጠምቆ ነው፡፡

ጉባኤ ቁስጥንጥንያ


ጉባኤው የተካሄደው በ381 ዓ.ም በቁስጥንጥንያ ነው፡፡ ምክንያት የሆነ መቅዶኒዮስ መንፈስ ቅዱስ ሕጹጽ ነው በማለት ባስተማረው ትምህርት ነው፡፡ ይህ ክህደት ሲነሳ የቁስጥንጥንያ ንጉስ የነበረው ቴዎዶስዮስ ቀዳማዊ ይህ የቤተክርስቲያን ችግር በጉባኤ እንዲፈታ ባስተላለፈው መልእክት መሠረት 150 ሊቃውንት ተሰብስበዋል፡፡
በዚህ ጉባኤ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን የተወያዩባቸው መሠረታዊ ጉዳዮችም የሚከተሉት ናቸው፡፡

 1. መቅዶንዮስና ትምህርቱን ለማውገዝ

  2.አቡሊናርዮስንና ትምህርቱን (በምሥጢረ ሥጋዌ ቃል እግዚአብሔር ሰው በሆነ ጊዜ ሥጋን እንጂ ነፍስን አልተዋሃደም የሚለውን ክህደት) ለማውገዝ

  3.ወልድ የተዋሃደው የአዳምን ሥጋ አይደለም ሌላ በቅድምና የነበረ ሥጋ ነው እንጂ የሚሉ መናፍቃንን ለማውገዝ፡፡

  4.በኒቅያ ጉባኤ ላይ በተረቀቀው ጸሎተ ሃይማኖት ላይ የተጨመሩ 5ቱን የሃይማኖት ቀኖናዎችን ማርቀቅ

  በዚህ ጉባኤ ላይ መቅዶንዮስ መንፈስ ቅዱስ ሕፁጽ፣ ፍጡር ነው ያለበትን ምክንያት ሲጠየቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ አላቀረበም፡፡ ከዚህም በኋላ ጉባኤው በኢሳይያስ 6-3፣ በማቴዎስ 28-19 በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አንድነትንና ሦስትነን በማስረዳት ቢነገረው ከኑፋቄው አልመለስም በማለቱ 150ው ሊቃውንት የክህደት ትምህርቱንና እርሱን አውግዘው ለይተውታል፡፡

  ሌላው ጉባኤው የአቡሊናርዮስን በምሥጢረ ሥጋዌ ቃል እግዚአብሔር ሰው በሆነ ጊዜ ሥጋን እንጂ ነፍስን አልተዋሃደም የሚለውን የክህደት ትምህርት አውግዘዋል፡፡ ለዚህም በዮሐንስ 1-14 ላይ “ቃል ሥጋ ሆነ” የሚለውን በመጥቀስ በትክክል የቃልና የሥጋን ውህደትና መጽሐፍ ቅዱሳዊነት ሊቃውንት አስረድተዋል፡፡

  ቅዱስ ጎርጎሪየስ ዘኢንዝናዙም ሰው ማለት ነፍስና ሥጋ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን እንጂ ነፍስ አልነሳም ከተባለ ያዳነው ሥጋን እንጂ ነፋስን አይደለም ብሎ በመመለስ የአቡሊናርዮስን ክህደት ተናግሯል፡፡ ከዚህም በማያያዝ ጉባኤው በኒቅያ ጉባኤ አንቀጸ ሃይማኖት ከተጠቀሱት ተጨማሪ 5 አንቀጾችን አስቀምጧል፡፡ እነርሱም

  1. በጌታ በአዳኝ ከአብ በሠረፀ ከአብና ከወልድ ጋር በነቢያት በተናገረ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን፣ እንስገድለት እናመስግነው

  2. በሁሉ ባለች በሐዋርያት ጉባኤ በአንዲት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን፡፡

  3. ለኃጥያት ማስተሰርያ በምትሆን በአንዲት ጥምቀት እናምናለን

  4. የሙታንን ትንሳኤ ተስፋ እናደርጋለን

  5. የሚመጣውንም ሕይወት እንጠባበቃን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

 

ሁለተኛው የኤፌሶን ሲኖዶስ (449)

አውጣኪ በቊስጥንጥንያ እጅግ የተከበረ ሰው ስለነበረና ብዙም ደጋፊዎች ስለነበሩት የእርሱ በ448 ዓ.ም. ጉባኤ መወገዝ ብዙዎችን አስቆጥቶ ነበር፡፡ እንደውም ያወገዘው ፓትርያርክ ፍላብያኖስ ንስጥሮሳዊ ነው እየተባለ ይወራና ይወቀስ ጀመር፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም የነገሩን ክብደት ተመልክቶ ምናልባትም በአውጣኪ ንስሓ-ልጅ በጠቅላይ ምኒስትሩ ተጽእኖ ይሆናል ዓለም-አቀፍ የአብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳት ሲኖዶስ በኤፌሶን እንዲደረግ ለጳጳሳቱ ሁሉ ጥሪ አስተላለፈ፡፡ ስብሰባውም በነሐሴ ወር 449 ዓ.ም. በኤፌሶን እንዲሆን ተወሰነ፡፡ ባለፉት ሲኖዶሶች እንደተደረገው ሁሉ የእስክንድርያው ፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ ሰብሳቢ እንዲሆን ንጉሠ ነገሥቱ ወሰነ፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ሰብሳቢ በመሆኑ ሃያ ሦስት ከሚሆኑ ከግብጽ ጳጳሳት ጋር ቀደም ብሎ ኤፌሶን ደረሰ፡፡

ፖፕ ልዮን ግን ይህ ስብሰባ እንዲደረግ አልፈለገም ነበር፡፡ እንደውም ለንጉሠ ነገሥቱ ታላቅ እኅት ለብርክልያ ንጉሡ ጉባኤውን እንዳይጠራ እንድታግባባው ጠይቋት ነበር፡፡ ሆኖም ንጉሠ ነገሥቱ በሐሳቡ ጸንቶ ጉባኤውን ስለጠራ ፖፑም ሦስት መልእክተኞች ላከ፡፡ በጉባኤው ላይ አንድ መቶ ሠላሳ አምስት ጳጳሳት ተሰብስበው ነበር፡፡ ምንም እንኳ ጉባኤው ስብሰባውን የጀመረው አንድ ሳምንት ዘግይቶ ቢሆንም የሮሙ ፖፕ እንደራሴዎች በዚህ ጊዜ ሊገኙ አልቻሉም፡፡ የቊስጥንጥንያው ፓትርያርክ ፍላብያኖስም በጉባኤው ላይ እንዲገኝ ተጠርቶ አልመጣም፡፡ የቀረበትንም ምክንያት አልገለጠም፡፡ ምናልባትም በእሱ ሰብሳቢነት የተሰበሰበው አህጉራዊ ሲኖዶስ ያወገዘው የአውጣኪ ጉዳይ እንደገና እንዲታይ በመደረጉ ቅር ብሎት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ይህ ደግሞ አዲስ ነገር አልነበረም፡፡ ከዚህ በፊትም ብዙ መናፍቃን አርዮስም ጭምር መጀመሪያ በአህጉራዊ ሲኖዶሶች ከተወገዙ በኋላ ነበር ጉዳያቸው እንደገና በዓለም-አቀፍ ሲኖዶሶች እንዲታዩ የተደረገው፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ጳጳሳት ተጠብቀው ባይመጡም ፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ የተገኙትን አንድ መቶ ሠላሳ አምስት ጳጳሳት ይዞ በነሐሴ ወር 449 ዓ.ም. ስብሰባውን ጀመረ፡፡ ጉባኤው የተደረገው እንደበፊቱ በኤፌሶን በቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ነበር፡፡ ጉባኤውም እንደተጀመረ አውጣኪ ተጠርቶ ስለተከሰሰበት ጉዳይ መልስ እንዲሰጥ ተጠየቀ፡፡ አውጣኪ በቊስጥንጥንያ ሕዝብ እጅግ የተወደደና የተደነቀ ከመሆኑም በላይ በቃላት የሚጫወት ቅንነት የጐደለው ሰው ነበር፡፡ አውጣኪ በጉባኤው ፊት ቀርቦ በራሱ እጅ የተጻፈና የፈረመበት የእምነት መግለጫ አቀረበ፡፡ መግለጫውም ከመነበቡ በፊት ራሱ እንዲህ ሲል ጮኾ ተናገረ፡- ‹‹ከልጅነቴ ጀምሮ በግልጥ በምነና (በብሕትውና) ለመኖር ነበር የምፈልገው፡፡ ዛሬ በሕዝብ መካከል በመገኘቴ ታላቅ ሐዘን ይሰማኛል፡፡ ሆኖም እምነቴን ለመመስከር ስለሆነ ደስታ ይሰማኛል፡፡ በኒቅያ ጉባኤ የተወሰነውንና አባታችን የእስክንድርያው ፓትርያርክ ቅዱስ ቄርሎስ ያስተማረውን እምነት በትክክል እቀበላለሁ፤›› አለ፡፡ ከዚህ በኋላ የጉባኤው ጸሓፊ የሚከተለውን የአውጣኪ የእምነት መግለጫ ማንበብ ጀመረ፤ መግለጫውም እንዲህ ይላል፡-

‹‹ሁሉን በያዘ፣ የሚታየውንና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ አምናለሁ፡፡ በመለኮቱ ከአብ ጋር አንድ በሚሆን በአንድ ልጁ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ፤ ለእኛ ለሰዎች ሲል ለድኅነታችን ከሰማይ ወረደ፡፡ ሥጋ ለበሰ፤ ሰውም ሆነ፡፡ ታመመ፤ ሞተ፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ ዳግመኛም በሕያዋንና በሙታን ላይ ለመፍረድ ይመጣል፡፡ እርሱ ያልነበረበት ጊዜ ነበረ የሚሉ፣ ከመወለዱም በፊት አልነበረም፤ ካለምንም ተፈጠረ የሚሉት፣ ከአብ ጋር በባሕርዩ የተለየ ነው የሚሉት፣ የእርሱ ሁለቱ ባሕርያት ተቀላቅለዋል ወይም ተዋውጠዋል የሚሉት፣ እነዚህ ሁሉ በአንዲት ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን የተወገዙ ናቸው፡፡ እኔም የምከተለው እምነት ይህ ነው፡፡ በዚህ እምነት እስካሁን ኖሬአለሁ፤ ወደፊትም እስክሞት ድረስ በዚሁ እኖራለሁ፡፡›› የሚል ነበር፡፡

አውጣኪ ይህንን ለጉባኤው ሲያስረዳ ተከትለዉት የመጡትም መነኰሳት አውጣኪ ያቀረበውና የተናገረው ትክክል መሆኑን ከዚያው በጉባኤው ፊት አረጋገጡ፡፡ ስለዚህ ይህን የሃይማኖት መግለጫ ከአዩና ከሰሙ በኋላ አራት ሊቃነ ጳጳሳት ማለት የኢየሩሳሌሙ፣ የአንጾኪያው፣ የኤፌሶኑና የቂሣርው ዘቀጰዶቅያ አውጣኪ በእምነቱ ኦርቶዶክስ ነው በማለት ለጉባኤው አጽንተው ሲናገሩ ሁሉም አውጣኪ ከተከሰሰበት ኑፋቄ ንጹሕ መሆኑን በአንድ ድምፅ ወሰኑ፡፡ ከተላለፈበትም ውግዘት ፈቱት፡፡ ሥልጣነ ክህነቱንም መልሰውለት ወደ ቀድሞው የሓላፊነት ሥራው እንዲመለስ ውሳኔ አስተላለፉ፡፡ የሁለት ባሕርይን ሐሳብ ይቀበል የነበረው የዶሪሊያም ጳጳስ አውሳብዮስ አውጣኪን በመወንጀል መግለጫ ሲያቀርብ በዚያ የተሰበሰቡት መነኰሳትና ምእመናን በታላቅ ድምፅ ‹‹አውሳብዮስ ይቃጠል! አውሳብዮስ በሕይወቱ ይውደም! ክርስቶስን ለሁለት እንደ ከፈለ እሱም ለሁለት ይከፈል!›› እያሉ ይጮኹ ጀመር፡፡

የቊስጥንጥንያን ፓትርያርክ ፍላብያኖስንና አውጣኪን ያወገዙትን ጳጳሳት የሮሙን ፖፕ ልዮን 1ኛን ጭምር አውጣኪን ያለ አግባብ በማውገዛቸውና ሥልጣናቸውን ያለ አግባብ በመጠቀማቸው ጉባኤው ካወገዛቸው በኋላ፣ የሚከተለውን አጭር መግለጫ አወጣ፡- ‹‹ከኒቅያ እስከ ኤፌሶን አባቶቻችን በጉባኤ ተሰብስበው ከወሰኑት ሃይማኖት ሌላ የሚጨምር፣ የሚቀንስ ወይም የሚያሻሽል ቢኖር የተወገዘ ይሁን፡፡›› ዘግይተው የደረሱት የፖፑ መልእከተኞች ዩልዮስና ሬናቱስ የተባሉት ጳጳሳትና ዲያቆን ሂላሩስ ከፖፑ የተላከውን የሃይማኖት መግለጫ ደብዳቤ እንዲነበብ ጠይቀው ነበር፡፡ ነገር ግን ደብዳቤው ‹‹ክርስቶስ ሁለት ባሕርያት አንድ አካል አለው›› ስለሚልና ይህም ከንስጥሮስ ኑፋቄ ጋር ስለሚመሳሰል ጉባኤው እንዲነበብ አልፈቀደም፡፡ በዚህም ምክንያት የፖፑ መልእከተኞች ተቀይመው ወዲያውኑ በድብቅ ከጉባኤው ወጥተው ወደመጡበት ተመለሱ፡፡ የጉባኤውም ውሳኔ በንጉሠ ነገሥቱ በዳግማዊ ቴዎዶስዮስ ጸደቀ፡፡ የቊስጥንጥንያ ፓትርያርክ ፍላብያኖስ በኤፌሶን 2ኛ ጉባኤ እንደተወገዘ ወዲያውኑ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡

የዚህን ጉባኤ ውሳኔ ሲሰማ የሮሙ ፖፕ ልዮን ቀዳማዊ እጅግ ተናዶ ጉባኤውን ‹‹ጉባኤ ፈያት (የወንበዴዎች ጉባኤ)›› ብሎ ጠራው፡፡ የጉባኤውንም ሊቀ መንበር ቅዱስ ዲዮስቆሮስን አወገዘው፡፡  ከእስክንድርያ ጋር የነበረውንም ግንኙነት ጨርሶ አቋረጠ፡፡ ፖፑ ይህን ሁሉ ያደረገው እሱ የላከው የሃይማኖት ነክ ደብዳቤ በጉባኤው ላይ ስላልተነበበና የእርሱም መልእክተኞች በጉባኤው ላይ በሙሉ ባለመካፈላቸው ነበር፡፡ በተጨማሪም ፖፑ ለንጉሠ ነገሥቱ ለዳግማዊ ቴዎዶስዮስ የኤፌሶኑን ጉባኤ የዲዮስቆሮስ ጉባኤ ብሎ በመጥራት በጉባኤው ላይ ያለውን ቅሬታ ከገለጸ በኋላ፣ ሌላ ዓለም አቀፍ ሲኖዶስ (ጉባኤ) እንዲጠራ ጥብቅ ሐሳብ አቀረበ፡፡ እንዲረዳውም የምዕራቡን ክፍል ገዥ (ንጉሥ) የነበረውን ሣልሳዊ ዋሌንቲኒያኖስን (Valentinianus III) እና ሚስቱን ንግሥት አውዶቅሲያን አጥብቆ ለምኖ ነበር፡፡

እነዚህም ባለሥልጣኖች እያንዳንዳቸው ሐሳቡን በመደገፍ ለንጉሠ ነገሥቱ ለዳግማዊ ቴዎዶስዮስ ደብዳቤ ጽፈው ነበር፡፡ ዳግማዊ ቴዎዶስዮስ ግን ሁለተኛው የኤፌሶን ጉባኤ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላቸው የቅዱሳን አባቶች ጉባኤ መሆኑን ገልጦ በመጻፍ ስለ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ምንም የሚያሳስብ ነገር አለመኖሩን ገልጦ አሳስቧቸዋል፡፡ በተጨማሪም የምዕራቡን ንጉሥና ንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ መክሯቸው ነበር፡፡ ፖፕ ልዮን ግን ሌላ ዓለም-አቀፍ ሲኖዶስ እንዲደረግ ዳግማዊ ቴዎዶስዮስን አጥብቆ መጠየቁን ቀጠለ፡፡ ሆኖም የፖፑ ጥረት ሁሉ ውጤት አላስገኘም፡፡ ምክንያቱም ዳግማዊ ቴዎዶስዮስ ለ2ኛው የኤፌሶን ጉባኤ ታላቅ አክብሮት ስለነበረውና ውሳኔውንም በሚገባ ስላጸደቀው ነበር፡፡

 

የኬልቄዶን ጉባኤ

ሁለተኛው የኤፌሶን ጉባኤ ከአለፈ ከአንድ ዓመት በኋላ በሐምሌ ወር 450 ዓ.ም. ዳግማዊ ቴዎዶስዮስ በድንገት ከፈረስ ላይ ወድቆ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡ ቴዎዶስዮስ ወራሽ ስላልነበረው ለአልጋው ቅርብ የነበረች ታላቅ እኅቱ ብርክልያ (Pulcheria) ነበረች፡፡ ብርክልያ ግን በድንግልና መንኵሳ ነበር የምትኖረው፡፡ ሆኖም ብርክልያ ለሥልጣን ስለጓጓች ምንኵስናዋን አፍርሳ የሮም መንግሥት የጦር አዛዥ ጄኔራል የነበረውን መርቅያን (Marcianus) አግብታ በነሐሴ ወር 450 ዓ.ም. እሱ ንጉሠ ነገሥት እሷ ንግሥት ሆነው የሮምን ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ማስተዳደር ጀመሩ፡፡ ይህ የብርክልያ ምንኵስናን ማፍረስ በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ በተለይም በግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ተቀባይነትን አላገኘም ነበር፡፡ የሮሙ ፖፕ ግን ከአዲሶቹ የሮም መንግሥት ንግሥትና ንጉሠ ነገሥት ዘንድ ተወዳጅነትን ለማግኘት ሲል ጋብቻቸውን በማወደስ አጸደቀላቸው፤ ቡራኬውንም ላከላቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ፖፕ ልዮን ከቊስጥንጥንያ ንጉሣዊ ቤተሰብ ጋር ወዳጅነትን መሠረተ፡፡ እንኳን ደስ አላችሁ ብሎም በጻፈው ደብዳቤ መጨረሻ ላይ እሱ የፈለገው ዓለም አቀፍ ሲኖዶስ እንዲሰበሰብ አሳሰበ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በንጉሠ ነገሥቱ በመርቅያንና በፖፕ ልዮን መካከል ብዙ የወዳጅነት ደብዳቤዎች ተጻጽፈዋል፡፡

ንጉሠ ነገሥቱ መርቅያን በሥልጣኑ በ2ኛው በኤፌሶን ጉባኤ የተወገዘው የፍላብያኖስ አስከሬን ፈልሶ በቊስጥንጥንያ በሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ክብር እንዲቀበር አደረገ፡፡ የተጋዙት ጳጳሳትም ከግዞት ወጥተው ወደየሥራቸው እንዲመለሱ አደረገ፡፡ በመሠረቱ በሲኖዶስ የተወገዙት ወደ ቀድሞ ሥራቸው መመለስ የሚችሉት በንጉሥ ትእዛዝ ሳይሆን በጳጳሳት ሲኖዶስ መሆን ስለነበረበት ንጉሡ ያደረገው ሕገ-ወጥ ሥራ ነበር:: ፖፑም የሱ ፍላጎት ስለነበረ ይህንን አልተቃወመም፡፡ በተቃራኒው ንጉሡ የተወገዙት ጳጳሳት ወደየሀገረ ስብከታቸው እንዲመለሱ የፍላብያኖስም አስከሬን ወደ ቊስጥንጥንያ ፈልሶ በክብር እንዲቀበር በማድረጉ ፖፕ ልዮን ለንጉሠ ነገሥቱ ልባዊ ምስጋና አቅርቧል፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ መርቅ ያንና ንግሥቲቱ ብርክልያ 2ኛው የኤፌሶን ሲኖዶስ ባቀረበው የሃይማኖት መግለጫ መሠረት ነፃ ያደረገውን አውጣኪንም ያለ ሲኖዶስ ውሳኔ ወደ ሰሜን ሶርያ እንዲጋዝ አደረጉ፡፡

ፖፕ ልዮን በአሳሰበው መሠረት ንጉሥ መርቅያን ጥቅምት 8 ቀን 451 ዓ.ም. ዓለም-አቀፍ ሲኖዶስ እንዲደረግ ለጳጳሳት ሁሉ ጥሪ አስተላለፈ፡፡ ጉባኤውም እንዲደረግ የታሰበው ከቊስጥንጥንያ 96 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኝ በኒቅያ ነበር፡፡ ነገር ግን በጸጥታ ምክንያት ከቊስጥንጥንያ 3 ኪሎ ሜትር ብቻ ርቃ በምትገኘው በኬልቄዶን እንዲሆን ንጉሡ ስለ ወሰነ ጉባኤው በኬልቄዶን ሆነ፡፡ ንጉሥ መርቅያንና ንግሥት ብርክልያ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ተገኝተዋል፡፡ ጉባኤው በሥነ ሥርዓት መካሄዱን የሚቆጣጠሩ 18 ዳኞች በንጉሡ ተሠይመው ነበር፡፡ እነዚህ ሁሉ ዳኞች መሠየማቸው መንግሥት ሲኖዶሱን ምን ያህል እንደተቈጣጠረው ያመለክታል፡፡ የጉባኤው አባላት አቀማመጥ እንደሚከተለው ነበር፤

ዳኞቹ በመኻል ከዳኞቹ በስተግራ የፖፑ መልእክተኞች፣ ቀጥሎ የቊስጥንጥንያው አናቶልያስ፣ የአንጾኪያው ማክሲሙስ፣ የቂሣርያውና የኤፌሶኑ ጳጳሳትና ሌሎች የምሥራቅና የመካከለኛው ምሥራቅ አህጉር ጳጳሳት ሲሆኑ፣ በቀኝ በኩል ቅዱስ ዲዮስቆሮስ፣ የኢየሩሳሌም፣ የተሰሎንቄ፣ የቆሮንቶስ፣ የግብጽ፣ የኢሊሪኩም፣ የፍልስጥኤም ጳጳሳትና ሌሎች ጳጳሳት ተቀምጠዋል፡፡ በኤፌሶን ጉባኤ የተወገ ዙትን ንስጥሮሳውያን መናፍቃንን የቂሮስ ኤጲስቆጶስ ቴዎዶሪጦስንና የኤዴሳን ኤጲስቆጶስ ኢባንን የዚህ ጉባኤ አባላት አድርገው ተቀበሏቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ብዙ ብጥብጥ ተነሣ፤ የግብጽ ጳጳሳት በኤፌሶን ጉባኤ የተወገዙትን ንስጥሮሳውያን ቴዎዶሪጦስንና ኢባንን ጉባኤው በአባልነት በመቀበሉ ‹‹አይሁዶችን፣ የክርስቶስን ጠላቶች ከዚህ አስወጡ!›› እያሉ በመጮኽ ተቃውሟቸውን አሰሙ፡፡ ጉባኤው ግን የእነሱን ጩኸት ከቁም ነገር አልቈጠረውም፡፡

ጉባኤውን በሊቀ መንበርነት በተራ የመሩት ከመንግሥት የተሠየሙት ዳኞችና የሮሙ ፖፕ መልእከተኞች ነበሩ፡፡ የሮሙ ተወካዮች ጉባኤውን ሲመሩ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ነበር፡፡ ከአሁኑ በስተቀር ባለፉት ዓለም-አቀፍ ሲኖዶሶች ሁሉ የእስክንድርያው ፓትርያርክ ከሊቃነ መናብርቱ ዋናው ነበር፡፡ አሁን ግን የእስክን ድርያውን ፓትርያርክ ዲዮስቆሮስን ለመኰነን የተሰበሰበ ሲኖዶስ ስለሆነ ዲዮስቆሮስ ከሊቃነ መናብርቱ አንዱ አልሆነም፡፡ የጉባኤው አባላት ቦታቸውን ይዘው እንደተቀመጡ የሮሙ ፖፕ ተወካይ ፓስካሲኑስ (Paschasinus) ተነሥቶ ለዳኞቹ ፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ ከተቀመጠበት ቦታ ማለት ከጉባኤው እንዲነሣና ሌላ ቦታ እንዲቀመጥ አመለከተ፡፡ የመንግሥቱ ዳኞች ለምን ይነሣል ብለው በጠየቁ ጊዜ፣ ሌላው የፖፑ መልእክተኛ ሊሴንቲያስ (Licentius) የተባለው ዲዮስቆሮስ ከዚህ በፊት የሮሙ ፖፕ ሳይፈቅድ በሥልጣኑ ሲኖዶስ (የ449 ሲኖዶስን ማለቱ ነው) እንዲካሄድ አድርጓል በማለት ክስ አቀረበ፡፡

ይህ ግን መሠረት የሌለው ክስ ነበር፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በፊት የተደረጉት ሲኖዶሶች ሁሉ የተጠሩትና የተካሄዱት በሮም ንጉሠ ነገሥት ፈቃድና ትእዛዝ እንጂ በሮሙ ፖፕ ፈቃድ አልነበረም፡፡ ያለፈውም የሁለተኛው የኤፌሶን ሲኖዶስ የተጠራው በዳግማዊ ቴዎዶስዮስ ትእዛዝ እንጂ በፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ ሥልጣን አልነበረም፡፡ ስለዚህ የቀረበው ክስ ዳኞቹን አላረካ ቸውም፡፡ በዚህ ጉዳይ ብዙ ጭቅጭቅ ስለተፈጠረ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በፈቃዱ ቦታውን ለቆ ተከሳሾች በሚቀመጡበት ቦታ ሄዶ ተቀመጠ፡፡ የሮሙ ፖፕ ተወካዮች በሁለተኛው የኤፌሶን ጉባኤ ፓትር ያርክ ዲዮስቆሮስ የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና አፍርሷል ሲሉ ከሰሱ፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ሲመልስ እሱ በንጉሠ ነገሥቱ በቴዎ ዶስዮስ ትእዛዝና ጥያቄ መሠረት ነው ጉባኤውን የመራው፡፡ እሱ ቀኖናን አፈረሰ? ወይስ በኤፌሶን ጉባኤ የተወገዙትን ንስጥሮሳውያን መናፍቃንን የቂሮስ ኤጲስ ቆጶስ ቴዎዶሪጦስንና የኤዴሳን ኤጲስቆጶስ ኢባንን የዚህ ጉባኤ አባላት አድርገው የተቀበሉት እነሱ ናቸው ቀኖና አፍራሾች? ብሎ ጥያቄ አቀረበ፡፡ ሆኖም ይህ የፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ ጥያቄ ምንም መልስ ሳይሰጠው በዝምታ ታለፈ፡፡

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top