ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ ነው

ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ ነው

(ሊቀ ካህናት ኃይለ ሥላሴ አለማየሁ)

የጌታችን እና የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት ለማወቅ  የአምላክነትን የመለኮትንና የባህሪይን ትርጉምና ምሥጢር በትክክል መረዳት ያስፈልጋል:: ከዚህም ጋር አምላክ  ሰው የሆነበትን ምሥጢርና ምክንያት በሚገባ መረዳት ተገቢ ነው:: አምላክ ማለት ፈጣሪ ገዥ  ፈራጅ መጋቢ ሠራዒ ከሃሊ ማለት ነው:: አምላክነት የባሕርይ ገንዘቡ የሆነም እግዚአብሔር ብቻ  በመሆኑ  እሱ ብቻ የባሕርይ አምላክ ይባላል::  ፈጣሬ ዓለማት አምጻኤ ዓለማት መጋቤ ዓለማት እሱ ብቻ ነው::  ከእግዚአብሔር በቀር አምላክነት የባሕርዩ የሆነ ማንም የለም:: ኢሳ ፵፭፥፳፩- ፳፪  ፩ኛ ቆሮ ፰፥፬-፮
ሌሎች የባሕርያቸው ባልሆነ ስያሜ አማልክት እየተባሉ ቢጠሩም “አማልክት ዘበጸጋ” የጸጋ አማልክት እየተባሉ ይጠራሉ:: አማልክት ዘበጸጋ ያልሆኑትም “አማልክት ሐሰት” ሐሰተኛ አማልክት ይባላሉ እንጂ ባሕርያዊ ከሃሊነትና መለኮታዊ ሥልጣን ፈጽሞ የላቸውም ::
ዘጸ ፯፥፩ :: ዘሌ ፲፱፥፬ :: መዝ ፵፱፥፩ , ፹፩፥፩-፯ :: ኢሳ ፵፥፲፰-፲፱  ሐዋ ፲፯፥፯-፳፱

የቅዱስ እግዚአብሔር የባሕርይ አምላክነት መገለጫው መለኮቱ ነው፤ መለኮት ማለትም ሥልጣን ልዩና ክቡር ስም፤ ከፈጣሪ በቀር ማንም ፍጡር ሊጠራበት የማይችል እግዚአብሔር ብቻውን ፈጣሪ ፥ ከሃሊ በቃሉ ፥ ገዥ አምላክ አማልክት እግዚአ አጋእዝት ንጉሠ ነገሥት፥ ጥንትና ፍጻሜ የሌለው፥ ዘለዓለማዊ፥ ወጣኔ ኩሉ፥ ፈጻሜ ኩሉ፥ መላኤ ኩሉ ፥ምሉእ ውስተ ኩሉ መሆኑ የሚታወቅበት ሥልጣኑ ባህርየ መለኮት ነው::
መለኮት :- ቅድስት ሥላሴን አዋሕዶ እግዚአብሔርን አንድ አምላክ ሦስት አካላት የሚያሰኝ የአካል የግብርና የስም መሠረት ነው:: አካላት ከባሕርያቸው ከመለኮት ስምን ይነሳሉ እንጂ ባሕርየ መለኮት አይከፈልም:: ባሕርየ መለኮት ሳይከፈል ለእግዚአብሔር ሦስት አካላት ሦስት ስም ሦስት ግብር አለው:: የአካለ ሥላሴ የባሕርይ አንድነት ምሥጢርም በመለኮት ይገለጻል:: “እሉ ሠለስቱ አካላት ፍጹማን ዲበ መንበረ ስብሐት ወእኁዛን በጽምረተ አሐዱ መለኮት ዘውእቱ አሐዱ ብርሃነ ዘይሠርቅ እምኔሁ::”  ሥላሴ :- እሊህ ሦስቱ አካላት በጌትነት (በፈጣሪነት) በክብር ፍጹማን ናቸው : በአንድ መለኮት አንድነትም አንድ ናቸው :: ይኸውም ሦስትነት (ሥላሴ) ከእርሱ (ከመለኮት) የሚገኝ አንድ ብርሃን ነው:: በዓለሙ ሁሉ ምሉዕ ነው:: እንዳለ ቅዱስ አግናጥዮስ (ሃይ አበው ዘአግና)
ባሕርይ:- የአካል የስምና የህላዌ ጥንት የግብር መሠረት ነው:: ባሕርየ እግዚአብሔር (ባሕርየ መለኮት) እንደ ፍጡር ባሕርይ ከአባት ወደ ልጅ  አይከፈልም ፤ አይቀዳም::  በመሆኑም አብ ወልድን ይወልደዋል ብሎ አይቀድመውም  አይበልጠውም ማለቱ ባሕርየ መለኮት ፈጽሞ የማይከፈል ባሕርይ መሆኑን ያረጋግጣል::  የማይከፈለው ባሕርየ መለኮት ግዙፉንና ረቂቁን የሚታየውንና የማይታየውን ዓለም እም ሀበ አልቦ ፈጥሮ መግዛት የእግዚአብሔር መለኮታዊ ሥልጣንና ከሀሊነት ነው:: መጽ.ጥበ ፲፪፥፲፫-፲፮:: ዘፍ ፩፥፩ ዮሐ ፩፥፩-፫
ቃል ሥጋ ኮነየምሥጢረ ሥጋዌ ጥንቱና መሠረቱ “ቃል ሥጋ ኮነ” ነው:: ጥንትና  ፍጻሜ የሌለው ጥንትና ፍጻሜ እሱ ራሱ የሆነ ብሉየ መዋዕል አካላዊ ቃል በፈቃዱ ከልዕልናው  ወርዶ ባሕርየ ሰብእን ከአካሉ አዋሕዶ ለመለኮታዊ ባሕርዩ በሚገባ ልደት ተወልዶልናል:: ለዚሁም ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ “በመጀመሪያ ቃል ነበረ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ ሁሉ በእርሱ ሆነ (ተፈጠረ) ከሆነውም አንዳች እንኳን ያለእርሱ አልሆነም :: …… ቃልም ሥጋ ሆነ :: ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ  በእኛ አደረ :: ….. ” ብሎአል:: ዮሐ ፩፥፩-፲፬ ሁሉን የፈጠረ ሁሉ በእርሱ የሆነ አምላክ ወልደ አምላክ ሥግው ቃል በተለየ አካሉ ጠባይዓተ ሥጋንና ባሕርያተ ነፍስን ገንዘብ አድርጎ ንጽሕተ ንጹሐን  ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያምን ለእመ አምላክነት መርጦ በክበበ ትስብእት ሲወለድ የተዋሕዶው ምስጢር ሰው ሆኖ የመወለዱ ነገር ምን ይረቅ ምን ይደንቅ ይባላል:: (፩  ጢሞ ፫፥፲፮) ለዚሁም አምላክ ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ሰውሆኖ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ይረቃል ተብሎአል::  አምላክ በሥጋ ሲወለድ አካለ መለኮት ወደ አካለ ሥጋነት ወደ ግዘፍ ሳይቀየር አካለ ሥጋ  ወደ አካለ መለኮትነት ወደ ርቀት ሳይለወጥ አንዱ ባሕርይ ወደ ሌላ ከዊንነት ሳይለወጥ ሳይፋለስ ሳይበረዝ ሳይቀላቀል  በፍጹም ተዋሕዶ ወልድ ዋሕድ ወልደ አብ ወልደ ማርያም ተብሎአል:: ቅድመ ሥጋዌ ወልደ አብ የተባለው አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ቃል ሥጋ ኮነ ከተባለበት ዓረፍተ ዘመን ጀምሮ ሥግው ቃል ወልደ አብ ወልደ ማርያም ተብሎአል:: (“አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወለድሁህ” መዝ ፪፥፮-፯: “ከአንቺ የሚወለደውም ቅዱስ ነው: የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል::” ሉቃ ፩፥፴፭)
የአምላክ ሰው የመሆን ምሥጢር ዋና ምክንያት በበደሉ ምክንያት ሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ ተፈርዶበት በፍዳ ተይዞ በግብርናተ ዲያቢሎስ ስር ወድቆ ፥ከእግዚአብሔር ርቆ የነበረውን የሰው ዘር ወደ ጥንተ ክብሩ ይመልስ ዘንድ ነውና ኂሩቱና መሐሪነቱ ከፈታሒነቱ ጋር በማይቃረን ጥበቡ ሰው ሆኖ ሰውን ይዋጅ ዘንድ ወዶ ፈቅዶ ተወልዶልናል:: ገላ ፬፥፫-፭:: ሮሜ ፭፥፮-፲፯::
•    የመወለዱ ምክንያት ሰውን ከራሱ ጋር ለማስታረቅ ነውና አምላክና ሰው በመሆኑ አማኑኤል ተብሏል::
•    ንጉሠ ነገሥት እግዚአ አጋእዝት ካህን ሊቀ ካህናት በመሆኑ ክርስቶስ መሲሕ ተብሏል::
•    የዓለም መድኅን በመሆኑ ኢየሱስ ተብሏል:: እነዚህም ስሞች ስመ ሥጋዌ ይባላሉ :: “አምላክ ሰው ሆነ ሰው አምላክ ሆነ”  የመባሉ ምሥጢር ዕጹብ ድንቅ ረቂቅ ምጡቅ የሚያሰኘውም ባሕርየ መለኮት ከባሕርየ ሥጋ ሳይቀላቀል በአካለ ቃልና በአካለ ሥጋ ውላጤ ሳይኖር በፍጹም ሰውነትና በፍጹም አምላክነት መወለዱ ነው:: በዚህ ምሥጢር ተዋሕዶ አካልን ከባሕርይ ባሕርይን ከአካል ሳይቀላቅሉ ለይቶ አጥርቶ ማወቅ የክርስቲያን ሁሉ የእምነት ግዴታ ነው:: ይህን ጠንቅቆ ማወቅ ካልተቻለ ባሕርይ ያለአካል አካል ያለባሕርይ ህልውና የለውም ወደሚል መደምደሚያ ይወስድና “ሥላሴ ሰው ሆኑ” የሚል የምሥጢር ተፋልሶና የእምነት ሕፀፅ ያስከትላል:: ትክክለኛው ግን አካላዊ ቃል በተለየ አካሉ ባሕርየ ሰብእን ተዋሕዶ ሥግው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ተብሎ መወለዱን አምላክ ወልደ አምላክ የባሕርይ አምላክ መሆኑን ጠንቅቆ ማወቅ ነው:: ይህን ጠንቅቆ ለማወቅም የሦስቱም አካላት የግብር ከዊንነት ለይቶ በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል:: (ሃይማኖተ አበው ዘአግናጥዮስን ይመልከቱ)
ሥጋንና ነፍስን ተዋሕዶ አምላክ ሰው የመሆኑ ምሥጢር የተፈጸመው በአካለዊ ቃል ብቻ ነው::  የሥጋዌ ነገር ለአካለ አብና ለአካለ መንፈስ ቅዱስ ፈጽሞ አይሰጥም:: ዮሐ. ፩፥፲፬:: ለመንግሥቱ ጥንትና ፍጻሜ የሌለው ሥግው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምንና ልጆቹን ለማዳን በሰጠው ተስፋ ድኅነት መሠረት ተወለደ ሲባልም የባሕርይ አምላክነቱንና ሥጋዊ ልደቱን የሚያረጋግጥ ትንቢት ተነግሮለት ሱባኤ ተቆጥሮለት ፈጣሪነቱንና የባሕርይ አምላክነቱ በቅዱሳት መጻሕፍት ተረጋግጦለት እንጂ ልደቱ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ አልነበረም:: እግዚአብሔር ወልድ ይወርዳል ይወለዳል እያሉ የእግዚአብሔር ነቢያት ከተናገሩለት ትንቢት ጥቂቱን እንመልከት::

  • “ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል እነሆ ድንግል ትጸንሳለች ወልድም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች::” ኢሳ ፯፥፲፬

  • “ሕፃን ተወልዶልናል:: ወልድም ተሰጥቶናል:: አለቅነቱም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ መካር አባት የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል::” ኢሳ ፱፥፮

  • “ይናገሩ ይቅረቡም በአንድነትም ይማከሩ::ከጥንት ይህን ያሳየ ከቀድሞስ የተናገረ ማነው? ያሳየሁም የተናገርኩም እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? :: ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም:: እኔ ድንቅ አምላክና መድኃኒት ነኝ:: ከእኔም በቀር ማንም የለም:: ..” ኢሳ ፵፭፥፳፩-፳፪

  • “አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታም ሆይ አንቺ በይሁዳ አእላፍ መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘለዓለም የሆነ በእስራኤል ላይ አለቃ (ገዥ) የሚሆን ይወጣልኛልና::” ሚክ ፭፥፪

የትንቢቱ ፍጻሜ    እግዚአብሔር ለፍጥረቱ የሰጠው ተስፋ ድኅነት በደረሰ ጊዜ ትንቢት ይፈጸም ዘንድ የባህርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ተወለደ ሲባልም ለአካለዊ ቃል ለእግዚአብሔር ወልድ ሁለት ልደት አለው ማለት ነው:: ይኸውም:-
1ኛ ዘመናት የማይቆጠሩለት አዝማናት የማይወስኑት ብሉየ መዋዕል አካለዊ ቃል ቅድመ ዓለም ከባሕርይ አባቱ ያለ እናት በቃልነት አምሳል ተወልዶ ወልደ አብ የተባለበት ቀዳማዊ ልደቱ::
2ኛ ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል እያሉ በተናገሩለት ትንቢት መሠረት ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነሥቶ በፍጹም ተዋሕዶ ያለ አባት በመወለድ ወልደ ማርያም የተባለበት ልደትነው:: ይህም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፈጣሪዋን በመውለዷ ምክንያት እመአምላክ ወላዲተ ቃል ድንግል ወእም ያሰኘበት ደኃራዊ ልደቱ ነው:: “ቀዳማዊ ልደቱ ተዓውቀ በደኃራዊ ልደቱ” እንዲል::
አካላዊ ቃል ቅድመ ዓለም ከአብ የተወለደበት ቀዳማዊ ልደቱ እንደ ደኃራዊ ልደቱ ዘመን የሚቀመርለት ሱባኤ የሚቆጠርለት ትንቢት የሚነገርለት ባይሆንም ባሕርይ ዘእም ባሕርይ መወለዱን በማረጋገጥ ግን ቅዱሳት መጻሕፍት በስፋት ገልጸዋል:: ለምሳሌም መዝ. ፪፥፯ , ፻፱፥፪ , ሉቃ ፫፥፳፩-፳፪, ዮሐ፩፥፳፱, መመልከት ይቻላል:: የባሕርይ አምላክ ኢየሱ
ስ ክርስቶስ በተነገረለት ትንቢት መሠረት ተወልዶ ዓለምን ማዳኑን መጻሕፍተ ሐዲሳት አምልተው አስፍተው ጽፈዋል:: ከብዙ በጥቂቱ :-

  • “በመጀመሪያ ቃል ነበር ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ ሁሉ በእርሱ ሆነ (ተፈጠረ) ከሆነውም  (ከተፈጠረውም) አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም’ (አልተፈጠረም) ….. ቃልም ሥጋ ሆነ:: (ሰው ሆነ) ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ:: … ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን:: ” ዮሐ፩፤፲፬ ዘፍ. ፩፥፲፫

  • “ዘመኑ በደረሰም ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም ላከ ከሴትም ተወለደ በኦሪትየታዘዘውን ሕግም ፈጸመ በኦሪት የነበሩትን  ይዋጅ ዘንድ እኛም የልጅነትን ክብር እናገኝ ዘንድ:: ገላ ፬፥፬-፭

  • “… ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ እርሱም ከሁሉ በላይ የሆነ ለዘለዓለም የተባረከ አምላክ ነው አሜን::” ሮሜ ፱፥፭, ኢሳ ፵፭፥፳፩-፳፪

  • “በእውነት ታላቅ ነው የአምላክ ምሥጢር አምላክ በሥጋ ተገለጠ:: …” ፩1ኛ ጢሞ ፫፥፲፮ ( ይህን ኃይለ ቃል ለማግኘት በ1879 ዓ.ም የታመውን የጥንቱን የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስና (king james Version የእንግሊዘኛ  መጽሐፍ ቅዱስ መመልከት ያስፈልጋል)

  • “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ ::” ሐዋ ፳፥፳፰

  • “የእግዚአብሔር ልጅ (እግዚአብሔር ወልድ) ሰውሆኖ ዕውቀትን እንደሰጠን እናውቃለን:: እውነተኛ እግዚአብሔርን እናውቀው ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን አለን:: እሱም በእውነት እግዚአብሔር ነው:: ”  ፩ኛ ዮሐ ፭፥፳ ፊሊ ፪፥፭-፯

  • “… ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ ሞቼም ነበርሁ እነሆም ከዘለዓለምእስከ ዘለዓለምድረስ ሕያው ነኝ”  ራእ ፲፯፥፲፰ ዘጸ ፫፥፲፫-፲፬ ዕብ ፲፫፥፰

እንግዲህ ጥልቅና እሙን ከሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ውቅያኖስን በጭልፋ ያህል አቅርበናል:: ለወደፊቱ ግን ዕድሉ ከገጠመን በስፋት በምልአት ለመጻፍ እንሞክራለን:: እስከዚያው ወልድ ዋሕድ በምትል የከበረች ሃይማኖታችን እስከመጨረሻው ያጽናን አሜን !

ምንጭ: ፍኖተ ሰላም መጽሔት ጥር ፲፱፻፺፱  ዓ/ም

መዳን በሌላ በማንም የለም

መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና (የሐዋ. 4፣12)።

ከበዓለ ኀምሳ በኋላ በተደረገ አገልግሎት ከእናቱ ማኅፀን አንስቶ ሽባ የነበረው ሰው በመፈወሱ ምክንያት ሐዋርያት ታሥረው በማግስቱ በካህናት አለቆች ፊት ቆመው ለተጠየቁት ጥያቄ ምላሽ በሰጡ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ የተናገረው ቃል ነበር። ቅዱስ ጴጥሮስ ይህን ምላሽ በሰጠበት በዚህ ክፍል በግልጥ ያስቀመጣቸው ሁለት ዐበይት መልዕክቶች፦

  1. መዳንም በሌላ በማንም የለም

  2. እንድንበት ዘንድ የተሰጠን ሌላ ስም የለም

በመጀመሪያ ደረጃ መዳንን ያገኘው ይህ ሽባ ሰው ከተወለደ ዕለት አንስቶ ሽባ እንደ ነበረ ተጽፏል። ዕድሜውም ከ40 ዓመት በላይ ሲሆን ቤተሰቦቹ ወደተለያየ ቦታ ወስደውት ግን መዳንን ያላገኘ ተስፋ ቆርጦ ሽባነቱን አምኖ የተቀበለ ከዚህም የተነሣ በልመና ይተዳደር ነበር። ጴጥሮስና ዮሐንስ በዘጠኝ ሰዓት ወደ ቤተ መቅደስ ሲገቡ አግኝቶ የለመናቸው ገንዘብ ነበር። እነርሱ ግን አንተ ሰው ወደኛ ተመልከት እንደምታየው እንሰጥህ ዘንድ ብርና ወርቅ የለንም ሆኖም ግን በናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ ብለው ቢያነሡት ቁርጭምጭሚቱ ጸንቶ ድኖ እየዘለለ ሊያመሰግን ወደ መቅደስ እንደ ገባ ታሪኩ ያስረዳናል። ከሰውየው መዳን በኋላ ግን በኢየሱስ እንደ ዳነ ሰምተው የተከፉት አይሁድና የካህናት አለቆች ተቆጡ፤ ይዘውም አሥረው ሁለት ጊዜ ያህል በዚህ ስም (በኢየሱስ ስም) እንዳያስተምሩ ዝተው፣ አስጠነቀቋቸው። ሆኖም ግን በሁለተኛው ቀን ግን መዳን በማንም በሌላ እንደሌለ ቅዱስ ጴጥሮስ በድፍረት አስረግጦ ነግሯቸዋል።

እውነተኛ አዳኝ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። እግዚአብሔር አብም በምንም መንገድ መዳን ያልቻለውን ሰው ለማዳን ሲወስን ለዓለም የሰጠው ውድ ልጁን ነበር። በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና (ዮሐ. 3፣16)። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለም መድኃኒት ሆኖ ከመምጣቱ በፊት ለሕዝቡ የነፍስ እረፍት ባያመጡም ሰው ለመዳን የተጠቀመባቸው መንገዶች ነበሩት። ጴጥሮስ ይህንን ያውቅ ስለነበር የቀደሙትን አመለካከቶች በመጣል መዳን በሌላ በማንም የለም አላቸው። እነርሱ ግን በሕጉ ወይም በመሥዕቶቹ በኩል እንድናለን ብለው ያስቡ ነበር።

ሕጉ፦ ለሕዝበ እስራኤል በሙሴ አማካኝነት የተሰጠ ነበር። በዚህም ሕግ በመመራት ሰው ወደ እግዚአብሔር ይደርስ ዘንድ ታስቦ ቢሰጥም ሰው ግን በሕጉ እንኳን ወደ እግዚአብሔር ሊደርስና ፍጹም ሊሆን ይቅርና ሕጉ ከተሰጠ ጀምሮ ኃጢአትን የሚገልጥና በኃጢአት የሚከሰስ ሆነ፤ ከዚህም በተጨማሪ ሕጉ በአፍአ (በውጪ) ጽላቱ ላይ ተጻፈ እንጂ በሰው ልብ ውስጥ ግን አልታተመም፤ በልብ የተጻፈ ባለመሆኑ ሰው ሊፈጽመው አልቻለም። ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ ሕጉ ምንም ፍጹም አላደረገምና በማለት ገልጾታል (ዕብ. 7፣18፤ 10፣1)። ኢየሱስ ግን ከሕግ በላይና የሕግ ፍጻሜ ሆኖ መጣ። አሁን ግን በሕግና ተገልጦአል፥ እርሱም፥ ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው (ሮሜ 3፣21-22)።

መሥዋዕቶቹ፦ በብሉይ ዘመን ስለ ኃጢአት፣ ስለ ደኅንነት፣ ለእግዚአብሔር የምስጋና መሥዋዕት ብዙ በሬዎችና በጎች ተሰዉ (ተቃጠሉ)፣ ብዙ ፍየሎችም የሰውን ኃጢአት ተሸክመው ይቅበዘበዙ ዘንድ ወደ ምድረ በዳ ተሰደዱ፤ ሆኖም ግን ለጊዜው በኃጢአት ምክንያት ከሚገለጥ ለምጽ፣ እባጭና ቁስል በሥጋ ቢፈውሱም የነፍስን እረፍት ማምጣት፣ ሰውን ከዲያቢሎስ ቀንበር፣ ከሞትና ከሲኦል ኃይላት ነጻ ማውጣት ግን አልተቻላቸውም። እንደዚህም መባና መስዋዕት ይቀርባሉ፤ እነዚህም እስከ መታደስ ዘመን ድረስ የተደረጉ፥ ስለ ምግብና ስለ መጠጥም ስለ ልዩ ልዩ መታጠብም የሚሆኑ የሥጋ ሥርዓቶች ብቻ ናቸውና የሚያመልከውን በህሊና ፍጹም ሊያደርጉት አይችሉም (ዕብ. 9፣9-10)። ሊቀ ካህናትም ሁሉ ዕለት ዕለት እያገለገለ ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ብዙ ጊዜ እያቀረበ ቆሞአል (ዕብ. 10፣11)። ይህን የተረዳው መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ ጌታ ኢየሱስን ሲያየው አማናዊው በግ መገለጡን ተረድቶ “ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘየአትት ኃጢአተ ዓለም” እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ (ዮሐ 1፣29) በማለት አወጀ። ኢየሱስም በሰው ኃጢአት ስለ ሰው ተገብቶ እንደ መስዋዕት ፍየል በምድረ በዳ ተቅበዝብዞ፤ እንደ በጎቹም ዝም ብሎ በመነዳት በጎልጎታ አደባባይ በመሰቀል ላይ ተሠውቶ የነፍስን እረፍት ሰጠን። ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቾቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም (ኢሳ. 53፣7)። ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፤ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ። እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበርና፥ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል (1ጴጥ. 2፣24-25)።

የራስ ጽድቅ፦ መዳንም በሌላ በማንም የለም ያለበት ምክንያት ሰው በገዛ ጽድቁ አይድንም ለማለት ነው። ቅዱስ ጳውሎስም በራሳቸው ጽድቅ የሚድኑ መስሏቸው የራሳቸውንም ጽድቅ ሊያቆሙ የሚሞክሩ አይሁድን ይህ እንደማይቻል አስተምሯል (ሮሜ 10፣3-4)። ሰው በኃጢአት ከእግዚአብሔር ከተለየ ጀምሮ በራሱ ሥራ ለመጽድቅ ብዙ ጥሯል፤ ፈሪሳውያን ራስን መጨቆን፣ ብዙ መጾም፣ መመጽወት አልበቃ ቢላቸው የሙሴን ሕግ ፈጽመናል ሲሉ በልብሳቸው ላይ ጽፈው በየአደባባዩ በመዞር ብዙ ደክመዋል። ሆኖም ግን የሰው ጽድቅ በእግዚአብሔር ጽድቅ ሲመዘን የብርሃንና የጨለማ ያህል ልዩነት ነበረው። ስለዚህም በራሱ ሥራ መጽደቅ ያልቻለውን የሰው ልጅ ለማዳን ኢየሱስ የእግዚአብሔር ጽድቅ ሆኖ ተገለጠ። በዚህም እግዚአብሔር ጽድቃችን ይባላል (ኤር. 23፣6) የሚለው የነብዩ ትንቢት ተፈጸመ።እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጸጋ ስለ ሆነ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በራሱ ጥረት መጽደቅ ያልቻለውን የሰው ልጅ በሙሉ እንደያው በጸጋው አደደቀ።በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ … ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥ በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም። እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን (ኤፌ. 1፣5-10)።

ፍጡራን፦ በዘመነ ብሉይ የተነሡ ደጋግ ነቢያት፣ ካህናትና፣ ነገሥታት ነበሩ። ሆኖም ግን ሕዝቡን ከዘላለም ሞት ሊያድኑ ያልቻሉ የራሳቸውም ጽድቅ በኃጢአት የተበከለባቸው ነበሩ። ነቢዩ ኢሳይያስ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው (ኢሳ. 64፣6) ብሎ መስክሯል። ሰው በሰው (በፍጡር) በኩል በፍጹም መዳን አይችልም፤ ኢየሱስ ግን ሰው ሆኖ እኛን ማዳን ተችሎታል። ቅዱሳን ሰዎች ቅዱስ ያሰኛቸው በክርስቶስ ደም መቀደሳቸው ነው፤ ጻድቃንንም ጻድቅ ያሰኛቸው በክርስቶስ ደም መጽደቃቸው ነው። ለመቀደስና ለመጽደቅ እንደነርሱ በክርስቶስ ቤዛነት ማመን እንጂ ክርስቶስን ሳያውቁ፣ በስሙ ሳያምኑ በፍጡራን በኩል መዳንን አገኛለሁ ብሎ ማሰብ ከንቱ ነው። የሰው ልጅ መዳን በቅዱሳን መላእክትም በኩል የማይሆን ነው፤ ይህ ቢሆን ኖሮ ወልደ እግዚአብሔር ከክብሩ ዝቅ ማለት፣ ሰው መሆንና የውርደት ሞት መሞት ባልተገባው ነበረ።

እንድንበት ዘንድ የተሰጠን ሌላ ስም የለም፦ ሽባው ሰው የተፈወሰው በሆነው በኢየሱስ ስም እንጂ በጴጥሮስ ወይም በዮሐንስ ብቃት አይደለም፤ ፈዋሽ። የኢየሱስ ስም አዳኝነቱንም ያረጋግጠልንና የማንነቱ መገለጫ ስም ነው። ኢየሱስ ማለት መድኃኒት ማለት መሆኑን ወንጌላዊው ማቴዎስ በግልጽ ነግሮናል። ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ (ማቴ. 1፣21)። በዘመነ ብሉይ እነ ኢያሱ በዚህ ስም ቢጠሩም ሕዝቡን ከዘለላም ሞት አላዳኑም። ኢየሱስ ግን አዳኝ በመሆኑ በስሙ ከዲያቢሎስ ግዛት፣ ከሞትና፣ ከሲኦል አድኖናል። እነ ኢያሱ ግን አካል ሆኖ ሊገለጥ ላለው ለኢየሱስ ጥላዎች ነበሩ። እንዲያውም የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ኢያሱ ሕዝቡን ከነዓን ማስገባት የቻለው የኢየሱስን አምሳለ ስም በመያዙ እንደ ሆነ ሲገልጹ፦ “ሰላም ለዝክረ ስምከ ስመ መሀላ ዘይሄሉ ዘአንበረ ቅድመ እግዚአብሔር በአትሮንሱ። ኢየሱስ ክርስቶስ ለዳዊት ባሕርየ ከርሱ አክሊል ስምከ እንዘ ይትቀጸል በርዕሱ አህጉረ ጸር ወረሰ ኢያሱ” የዳዊትን ባሕርይ ባሕርይህ ያደረግህ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ለስምህ ሰላምታ (ምስጋና) ይገባል። ኢያሱ ኢየሱስ የሚለውን ስምህን ተሸክሞ የጠላትን ምደር (የተስፋውን አገር) ወረሰ ይላሉ (መልክአ ኢየሱስ)።

የጌታ ኢየሱስ ስም

† የዳንንበት ስም ነው፦ የሐዋ. 4፣12፤ የሐዋ. 16፣16

† በአብ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘንበት ስም ነው፦ ዮሐ. 19፣23፤ ዮሐ. 14፣13

† የእግዚአብሔር ልጆች የሆንንበትና የዘላለም ሕይወት ያገኘንበት ስም ነው፦ ዮሐ. 1፣12፤ 1ዮሐ. 5፣13

† የምንሰበሰብበት ስም ነው፦ ማቴ. 18፣20

† የምናመልክበት (የምንሰግድበት) ስም ነው፦ ፊል. 2፣9

† የምንታማበት፣ የምንከሰስበት፣ ለሞት ተላልፈን የምንሰጥበት ስም ነው፦ የሐዋ. 5፣40፤ 21፣13

† የመንግሥተ ሰማያት መግቢያ መንገዳችን ነው፦ ራእ. 3፣13፤ 22፣3

† ሁሉን የምናደርግበት ስም ነው፦ ቆላ. 3፣17

ቃሉን ለምናምንና መለኮታዊ ሥልጣን እንዳለው ለምንቀበል መጽሐፍ ቅዱስ መዳን በኢየሱስ ብቻ መሆኑን በብዙ ቦታ ይመሰክርልናል (ዮሐ. 3፣36፤ 3፣18፤ 10፣7፤ 14፣6፤ ሮሜ 8፣1)።

እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው። ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም። የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ (1ዮሐ. 5፣11-13)።

“ስለእኛ ሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” ሮሜ 8፡34 ብዙ ጊዜ ብዙ ወገኖቻችን ይህንን ጥቅስ በመያዝ ኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅ ነው ከእርሱ ውጪ ማንም ስለእኛ እግዚአብሄርን የሚለምንልን የለም ይላሉ ቃሉም እንዲህ ሲል ይጀምራል “እግዚአብሄር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል” ይህ ማለት እግዚአብሄር ተከተሉኝ ብሎ በመጥራት የመረጣቸውን አይ እነርሱ አንተን ሊከተሉ አይገባቸውም ሊመረጡም አይችሉም ብሎ የሚከሳቸው ማን ነው ? በማለት ይጠይቃል በመቀጠልም “የሚያጸድቅ እግዚአብሄር ነው” በማለት የመረጣቸውን ሰዎች መንግስቱን ለማውረስ እናንተ የአባቴ ብሩካን ብሎ የሚያጸድቃቸው እግዚአብሄር ነው አለ እንዲሁም “ የሚኮንን (የሚፈርድ ) ማነው ” በማለት ይጠይቃል ፡፡ “መኮነን ” ከግእዙ ሳይተረጎም ቀጥታ የተወሰደ ቃል ሲሆን መኮነን ማለት መፍረድ ማለት ነው ምክንያቱም “ኮነነ” ከሚለው የግእዝ ስርወ ቃል የወጣ ሲሆን “ኮነነ” ማለት ደግሞ ፈረደ ፣ገዛ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ማጽደቅና መኮነን የአማላጅነት ስራ ሳይሆን የፈራጅነት ስራ እንደሆነ ልብ እንበል በመቀጠልም “የሚኮንንስ ማነው ?” ብሎ ለጠየቀው ጥያቄ መልስ ሲሰጥ ቁጥር 34 ላይ “የሞተው ይልቁንም ከሙታን የተነሳው በእግዚአብሄር ቀን ያለው ” በማለት አሁን ያለበትን የእግዚአብሄርነት የስልጣን ስፍራ ይገልጻል ፡፡ የሞተውና ሞትን ድል አድርጎ በስልጣኑ የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሄር ቀኝ ( በእግዚአብሄርነት ስልጣን) አለ ማለት ነው፡፡ መቼም እግዚአብሄር ቀኝና ግራ ፊትና ኋላ እንደፍጡር የለውም እርሱ ስፍራ የማይወስነው ረቂቅ ነው የነፋስን ቀኝና ግራ የሚያውቅ ማነው ? ከነፋስ ይልቅ ነፍስ ትረቃለች ከነፍስ ደግሞ መላእክት ይረቃሉ ከመላእክት የበለጠ ደግሞ እግዚአብሄር ይረቃል ስለዚህ እግዚአብሄር በአለም ሁሉ ምሉእ ነው ፡፡ ታዲያ በእግዚአብሄር ቀኝ ሲል ምን ማለት ነው ? ብለን ስንጠይቅ በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ቀኝ የተለያየ ትርጉም ቢኖረውም በዚህ ምእራፍ ላይ ግን ክብርን ፣ስልጣንን ያመለክታል ፡፡ በመዝ 117፡16 ላይ “የእግዚአብሄር ቀኝ ሃይልን አደረገች ” ይላል ይህ ማለት እግዚአብሄር በስልጣኑ ኃይልን እንዳደረገ የሚገልጽ ነው ምክንያቱም እግዚአብሄር ኃይልን የሚያደርገው ሰዎችንም ከፍ ከፍ የሚያደርገው በስልጣኑ በመለኮታዊ ኃይሉ መሆኑ ግልጽ ነው :: በመሆኑም የእግዚአብሄር ቀኝ ሲል ስልጣኑን (መለኮታዊ ክብሩን ) ያመለክታል፡፡ በዘጸ 15፡12 ላይ “ቀኝህን ዘረጋህ ምድርም ዋጠቻቸው ” ይላል ከዚህም የምንረዳው ግብጻውያንን እግዚአብሄር በስልጣኑ ምድር እንድትውጣቸው ማድረጉን ነው፡፡ ስለዚህ “በእግዚአብሄር ቀኝ ያለው ” ማለቱ በስልጣንና በክብር በሰማያት ያለው ማለቱ ነው፡፡ ይህም ማለት ክርስቶስ ቀድሞ ስጋ ከመልበሱ በፊት ክብር የሌለው ሆኖ በኋላ ክብር አገኘ ለማለት አይደለም ክብርና ስልጣኑ ቅድመ ተዋህዶ ጊዜ፣ ተዋህዶ ፣ድህረ ተዋህዶ ከባህርይ አባቱ ከአብ ከባህርይ ህይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ትክክል ነው ፡፡ በመቀጠል እንዲህ ይላል “በእግዚአብሄር ቀኝ ያለው ደግሞም ስለእኛ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው ” በክፍት ቦታው ላይ ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረውን ሙሉ ብንባል ያለጥርጥር የምንሞላው የሚፈርደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው የሚለውን ነው፡፡ ምክንያቱም ከላይ በዝርዝር እንዳየነው ጥቅሱ የሚያመለክተው ፈራጅነቱን እንጂ አማላጅነቱን በፍጹም አይደለም ፡፡ ማጽደቅና መኮነን ከቻለ እንዲሁም በእግዚአብሄር ቀኝ (ክብር) ካለ እርሱ ክርስቶስ ፈራጅ እንጂ አማላጅ አይሆንም፡፡ ደግሞ “የሚኮንን ማነው ?” የሚለውና “ስለእኛ የሚማልደው ” የሚሉት ሁለት ቃላት (ሃሳቦች) እርስ በእርሳቸው እንዳይጋጩ አስማምቶ መተርጎም ያስፈልጋል፡፡ ሌላው ልንረዳ የሚያስፈልገው ነጥብ “የሚኮንንስ ማነው የሞተው ይልቁንም ከሙታን የተነሳው በእግዚአብሄር ቀኝ ያለው ደግሞ ስለእኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው ” ያለው ለትስብእት ነው ምክንያቱም ትስብእት (ስጋ) መለኮት ስለተዋሃደ ቢሞትም ከሞት በሃይል ተነሳ መነሳት ብቻም አይደለም የመለኮት ገንዘብ ለስጋ ገንዘቡ ስለሆነ እግዚአብሄርነትን አግኝቶ አሁንም በእግዚአብሄር ቀኝ ማለትም በእግዚአብሄርነት ክብር አለ ደግሞም ስለእኛ ይማልዳል እዚህ ላይ ልብ እንበል ስለእኛ የሚማልደው ሲል አሁን ስጋ በሰማይ የተዋሃደውን መለኮት እየወደቀ እየተነሳ እያነባም የሚማልድ የሚለምን ነው ማለት አይደለም በስጋው ወራት ማለትም በዚህች ምድር በፈጸመው የአንድ ጊዜ ልመና አሁንም ድረስ የሚያድን መሆኑን ሚገልጽ ነው ፡፡ አንዳንድ ሰዎች “ስለእኛ የሚማልደው ” የሚለውን ቃል ይዘው አሁንም እየወደቀ እየተነሳ የሚማልድ ነው ብለው የሚያስቡ አሉ …አይደለም የመስቀሉን ምልጃ ነው አሁን የሚደረግ አስነስሎ የጻፈው ፡፡ ለምሳሌ ጌታ ከመወለዱ ከ 700 አመታት በፊት የነበረው ኢሳይያስ በትንቢቱ መጽሃፍ ላይ ስለጌታ የእለተ አርብ እንግልት ሲጽፍ እንዲህ አለ “ከአመጸኖች ጋር ተቆጥሯል ….ስለአመጸኖች ማለደ ” ይላል ኢሳ 53፡12 አሁን ይህን ቃል ስንመለከተው ያለፈ ድርጊት ነው እንጂ ወደ ፊት የሚፈጸም ድርጊት አይመስልም ኢሳይያስ ግን በዘመኑ እየተናገረ ያለው ወደፊት ከ 700 አመታት በኋላ ጌታ ላይ ስለሚደርሰው መከራና የማዳን ስራ ነበር፡፡ ቅዱስ ዳዊትም “እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩኝ አጥንቶቼ ሁሉ ተቆጠሩ እነርሱም አዩኝ ተመለከቱኝም ልብሶቼንም ለራሳቸው ተከፋፈሉ በቀሚሴም ላይ እጣ ተጣጣሉ ” ይላል ፡፡ መዝ 21፡16-18 መዝሙረኛው ዳዊት በዘመኑ ወደፊት ሚሆነውን እንደ ክርስቶስ ሆኖ ይናገር ነበር ከ 800 አመት በኋላ ሚሆነውን የጌታ ስቃይ እርሱ ግን እንደሆነ አድርጎ መግለጹ ስህተት እንዳልሆነ ሁሉ የተፈጸመውን ወደፊት እንደሚፈጸም አድርጎ ቅዱስ ጳውሎስ “ስለእኛ የሚማልደው ” ብሎ ቢገልጸውም ትክክልና የመጽሃፍ ቅዱስ ዘይቤ መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል ፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ዛሬም ክርስቶስ በሰማይ እየወደቀ እየተነሳ ይማልዳል ብሎ ማሰብ በዚህ ምድር ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የፈጸመውን የማዳን ስራ እንዳልተሟላ በሰማይም የሚቀጥል አድርጎ መቁጠር ነው፡፡ ይህንን እንዳንል ደግሞ ክርስቶስ እራሱ በመስቀል ላይ በመጨረሻው ሰአት ላይ “ተፈጸመ ” ብሏል ፡፡ ዮሃ 19፡ 30 ቅዱስ ጳውሎስም በ2ኛ ቆሮ 5፡16 ላይ “ክርስቶስን በስጋ እንደሆነ ያወቅነው እንኳን አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ በስጋ አናውቀውም ” ብሏል ይህም ማለት ክርስቶስ ስጋን እንደተዋሃደ ቢያርግም አሁን ግን በስጋ የሚማልድ ፣ሚወድቅ፣ የሚነሳ በምድር ላይ ሲያደርግ እንደነበረው የሚያነባ አይደለም በክብር ዙፋኑ ተቀምጦ የሚፈርድ ነው እንጂ፡፡ መጽሃፍ እንዲህ ይላል “ሁላችን በክርስቶስ ፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለን” ሮሜ 14፡10 “ሁላችን በክርስቶስ በፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናል ”2 ቆሮ 5፡10 ፣ዮሃ 5፡ 22 “ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው ” ክርስቶስ ከእርገቱ በኋላ በምድር ሲያደርግ እንደነበረው የመለመን ፣የመማለድ አገልግሎት እንደማይፈጽም እንዲህ ሲል ተናግሯል “እኔም ስለእናንተ አብን እንድለምን የምላችሁ አይደለሁም ፡፡” ዮሃ 15፡25 ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ይፈርዳል እንጂ አይማልድም፡፡ ነገር ግን ብዚህ መልኩ መጽሃፍን ካልተረዳን “ይማልዳል” የሚል ቃል የያዙ በመሆናቸዉ ብቻ አማላጅ የሚል ትርጉም ከሰጠን ወደ አልሆነ ምንፍቅና ይወስደናልና እንጠንቀቅ። ለዚህ ማስረጃ የሚከተሉትን ጥቅሶች መመልከት ይቻላል:- ሮሜ ምዕራፍ 8፡ 26 – 27 እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፤ ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደ ሆነ ያውቃል፥ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና። /ግንዛቤ መንፈስ ቅዱስ ይማልድልናል/ ሮሜ 8፡34 የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። /ግንዛቤ ኢየሱስ ይማልዳል/ ኤር 7 ፡23-25ነገር ግን። ቃሌን ስሙ፥ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ፤ መልካምም ይሆንላችሁ ዘንድ ባዘዝኋችሁ መንገድ ሁሉ ሂዱ ብዬ በዚህ ነገር አዘዝኋቸው። ነገር ግን በክፉ ልባቸው አሳብና እልከኝነት ሄዱ ወደ ፊትም ሳይሆን ወደ ኋላቸው ሄዱ እንጂ አልሰሙም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም። አባቶቻችሁ ከግብጽ ምድር ከወጡበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፥ በየዕለቱ እየማለድሁ ባሪያዎቼን ነቢያትን ሁሉ ልኬባችሁ ነበር። /ግንዛቤ እግዚአብሔርም ይማልዳል/ እነዚህን ሦስቱንም ኃይለ ቃሎች አስማምተንና አስታርቀን ለመጠቀም እንድንችል በጸሎታችን ማለት የሚገባን አብ ፣ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አማልዱን ማለት ሊያስፈልግ ይመስላልና ።ይህ ደግሞ ታላቅ ስህተት ነዉ።ስለዚህ አንድ ቃል በመያዝ ድምዳሜ ላይ መድረስ ይብቃ እንላለን። ወስብሃት ለእግዚአብሄር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር ይትአኮት ወይሴባህ ስሙ ለእግዚአብሄር ወትረ በኩሉ ጊዜ ወበኩሉ ሰአት አሜን።

በኢየሱስ ክርስቶስ ዙሪ ለሚነሳው በተለይም አማላጅ ነው በሚል እሰጣ ገባ ለሚፈጠረው ጥያቄና መጽሐፍ ቅዱስ ስለእርሱ አማላጅነት ይጠቅሳል ተብሎ የተሰጡትን 6 ዋና ዋና ጥቅሶችንና እንዲሁም አምላክነቱ ላያ ያላቸውን እልውን ከቅዱሳት መጽሐፍ በማመሳከር የቀረበ ነው፡፡

ለምሳሌ አማላጅ ነው ካልን

  1. ማን? 2.ለማን? 3.ከማን? (ወደ ማን) የሚሎትን የመሳሰሉ ጥያቄዎች ያስነሳል፡፡

    ታዲያ ይሄ ከአምላክነቱ ጋራ ምን ያገናኘዋል ልንል እንችላልን እነዚህ ሶስቱ ጥያቄዎች እስካሉ ድረስ ይህን ቃል አምነውና አዘውትረው ሽንጣቸውን ገትረው በሚከራከሩት ሰዎች ዘንድ የአምላክነቱን እውነታ ጥያቄ ላይ ነው የሚጥሉት፡፡

    ምልጃ ማለት፡- ‹‹በሶስት ወገን መካከል የሚፈጸም ድርጊት ነው፡፡ ይህም ማለት አጥፊው፤ ማላጁ፤ እንዲሁም ተማላጁ፡፡ በሌላ አገላለጽ፡- አንዱ ስለአንዱ ሌላውን መለመን ማለት ነው፡፡ ይህም ለራስ ጥቅም ሳይሆን ለሌላው ጥቅም ማለት ነው››፡፡

    ደግሞ እሰቲ አማላጅ የሚለውን እንየው፡- ‹‹አጥፊውን (አንድን) ሰው ውክሎ በመሄድ ያለውን ችግር እንዲወገድ ተበዳዩን የሚለምን ማለት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ አስታራቂ ማለት ነው፡፡›› ለምሳሌ በአንድ አከባቢ (በንጉስ ግዛት) የሚኖሩ ሕዝቦች ለንጉሱ የሚገባውን ግብርና ከእነርሱ የሚጠበቅባቸውን ነገር ሳያደርጉ ቢቀሩና ንጉሱም በዚህ ድርጊታቸው በበሳጭ ደግሞም ክብሩ በመነካቱ ቢከፈው ለነዚያ ሕዝቦች ከዚህ ቀደም ይደረግላቸውን የነበረውን ጥበቃና እንዲሁም የሕግ ከለላ ቢከለክል፡፡ ከዚህም የተነሳ ያንን ሕዝብ ሌባና ቀማኛ ደግሞም አመጸኛ መጥቶ ቢያስመርረው ወደ ንጉሱ ዘንድ የግድ ለሰላማቸው ሲሉ ማላችና መማለጃ (እጅ መንሻ) ይዞ ሚገባ ባለሟል ይፈለግና፤ ያባለሟል የሕዝቡን ጸጸትና እሮሮ ይዞ በንጉሱ ፊት ባለው ግርማና ሞገስ ቆሞ ስለሕዝቡ የንጉሱን ልብ ያራራል፡፡ ንጉሱም የእርሱ ባለሟል ነውና ልመናውን ሳይከለክል ዳግመኛ እንዳይበድሉ በማስጠንቀቅ ምህረት ያደርጋል፡፡ ታዲያ ያ ባለሟል ሕዝቡን ከንጉሱ ጋራ አስታረቀ እንጂ እርሱ ንጉስ ሆነ ማለት አይደለም፡፡ የማላጅ ስራ ሁሌም ለማኝነት ነው ለሌላው ጥቅም ሲል፡፡

    እንግዲህ እንዲህ ከላይ እንደጠቀስነው አይነት ድርጊት የተለመደ ነው ደግሞም ያለና የሚኖር ነው፡፡ እኛ ሰዎች እግዚአብሔርን ከመበደላችን የተነሳ እኛን ከእግዚአብሔር ጋራ የሚያስታርቀን ወይም የመጣብንን ቁጣ ሊያስቀር የሚችል ማላጅ እንፈልጋለን፡፡ ለምሳሌ በብሉይ ኪዳን ዘመን እንደነበር ዓይነት ስርዓት ብንመለከት፡፡ ሙሴ ስለ ሕዝቡ ሁሉ ኃጢያት በመገናኛው ድንኳን መስዋዕትን ይዞ ይቀርብና የሕዝቡን ሁሉ ኃጢያት በዓመት አንዴ በሚደረገው ስርዓት በደም መረጨት ከእግዚአብሔረ ጋራ ሕዝቡን ያስታርቅ ነበር፡፡ ይህንንም እግዚአብሔር ሲናገር እንዲህ ይላል እኮ፡- ‹‹የታመነው ሙሴ በፊቴ ባይቆም ኖሮ…..››

    እንግዲህ ስለምልጃ ይህን ያክል ትርጉምና መረዳት በጥቂቱ ካከኘን ዘንዳ እውነተኛ ማላጅና ተማላጅ ዙሪያ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነታዎች በቅንነት ለመመልከት እንሞክራለን፡፡ የእኔ አላማ የሚያተኩረው የእውነተኛይቱን የቤተክርስቲያን እምነትና ትምህርት ግልጽ በሆነ ነጻ አቀራረብ ለምእመናን ማስነበብ ማሳወቅና መማማር ነው፡፡ ከዚያ በተረፈ ወደ አልባሌ እሰጣ ገባዎች ውስጥ ገብቶ ያላስፈላጊ የሆነውን እንካ ሰላምቲያን ማናፈስ ሳይሆን የመጸሐፍ ቅዱሱን እውነታ መረዳትና ማስረዳት ነው፡፡ ከዚያ የተረፈው ስድብና ውግዘት ደግሞ የመንፈሳዊነቱን ለዛ ስለሚያሳጣው አግባብ አይደለምና ‹‹እናንት ክርስቲያኖች ሲርግሟችሁ መርቁ ሲሰድቧችሁ የቅዱሳኑን ትህግስት ተላብሳችሁ በትህትና መልሱ፡ እንዲያስ ካልሆነ ማነው ሊረዳችሁ የሚችል፡፡ ከስሜት ውጪ ሁኑና ሁሉንም በመንፈሳዊነት አድረጉት፤ ይሄ የእናንተ የእምነት መሰረት የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ ድርጊት ነውና ይህን ከእርሱ ተማሩ፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ሁኔታዎች ሲያስገድዱና እምነት አቋማችንን በይፋ አቅጣጫ የሚያስቀይሩ ነገሮች ሲመጡብን በተለይም ቁስን ተገን ያደረገ ክህደት ሲመጣ እሊናችን ሊሸከመው የማይችል መሆኑ የተወቀ ነው፡፡ በዚህ ላይም ቢሆን በሚገባ ትረት ሰጥተን እንድናይ ይሁን፡፡››

    እውነት ኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅ ነውን?

    እንደ ምክኒያት ከሚቀርቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መካከል ያሉትንና ሁሉ ሁሌ የሚጠቅሷቸውን ጥቅሶች እስቲ በምላት እንያቸው፡፡ ትንሽ ትህግስት የሚፈልግ ይሆናል እንጂማ በጣም ብዙዎቹን አውጥተን ብንተረጉማቸውና ብናያቸው በርካቶቾ ከአተረጓጎምና ከአረዳንድ አንጻር ጉድለት ይታይባቸዋል፡፡

    1. ት.ኢሳ 53÷12 ‹‹……… እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ።››
    2. ዩሐ.10÷9 ‹‹በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፥ ይገባልም ይወጣልም መሰማርያም ያገኛል።››
    3. ዩሐ.14÷6 ‹‹ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።››
    4. ሮሜ 8÷34 ‹‹የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው።››
    5. 1ኛ ጤሞ 2÷5 ‹‹አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤››
    6. ዕብ 7÷25 ‹‹ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።››
    እንግዲህ እነዚህን ጥቅሶች በማንሳት ኢየሱስ ክርስቶስ አማላጃችን ነው በሚል ከብዙ ጊዜ ጀምሮ አተካሮ በመፍጠር የሚለዩንና እንዲሁም ትርጉሙና ምስጢሩ ያልገባቸውን ሲለዩ ይስተዋላል፡፡ እስቲ አንድ በአንድ ጥቅሱን እንመልከተውና እኛም ቅዱሳችን በደማቸው ከጻፉት ቅዱሳት መጽሐፍት ጋራ እናመሳክራለን፡፡

    1. ‹‹…ስለ ዓመፀኞችም ማለደ›› ኢሳ. 53÷12

    መቼም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን እንደሚመጣ እንዲሁም ሕዝቡን ሁሉ ከጨለማው ዓለም ነጸ እንደሚያወጣ ነቢያት በትንቢታቸው በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው የተናገሩት፡፡ የማዳኑንንም ትንቢት ሲጠብቁ ቃል ተገብቶላቸው ‹‹ጌታ ሆይ አሁን ባሪያህን በሰላም አሰናብተው›› ብሎ ያለው ስምዖንም ጨምሮ በርካቶች ይህን ትንቢት ይናፍቁ እንደነበር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እራሱ ተናግሯል፡፡ ‹‹እላችኋለሁና፥ እናንተ የምታዩትን ብዙዎች ነቢያትና ነገሥታት ሊያዩ ወደዱ አላዩምም፥ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ወድደው አልሰሙም አለ።›› ሉቃ 10÷24፡፡ ስለ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ስራ ትንቢት ላይ በሚገባ ካሰፈሩ ነቢያት መካከል አበይት ሆነው ነብይ ነብየ ኢሳያስ ነው፡፡ ኢሳያስ ጌታችን ኢየሱስ ከመወለዱ በሚት 7 መቶ ዓመት ቀደም ብሎ ሁሉን በትንቢት ተመልክቶ በሚገባ አስፍሮታል፡፡ በተለይም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ እና ስቃይ በተለይም ለሰዎች ልጆች ሲል በሚከፍለው መስዋዕትነት፡ ከሰዎችም የሚደርስበትን አጻፋ ሁሉ አስፍቶ ተንብዮታል፡፡ ከትንቢት ፍሉ መካከል አንዱ ደግሞ ይህ ምልጃን የሚመለከተው ክፍል ነው፡፡

    ይህ ትንቢት ሙሉውን ስናየው ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢያትና በደል ሳይኖረበት እኛን መስሎ ዓለምን ለማዳን የከፈለውን ሙሉ የቤዛነት አገልግሎት ይወክላል፡፡ በተለይም ደግሞ ከቁጥር 1 ጀምረን ስናነበው ክርስቶስ የሚቀበለውን መከራና ችግር ይተርካል፡፡ በመስቀል ላይ የሚከፍለውን መስዋዕትነት ሚተነብይበት ክፍል ነው፡፡ ሙሉ ክፍሉን በተለይ ብናነብ ስለማዳን ስራው ከፍተኛ ግንዛቤ ያስጨብጠናል፡፡ ታዲያ ከዚህ ክፍል ውስጥ አንዱን ዐረግ ወስዶ ‹‹ስለ ዓመፀኞች ማለደ›› የሚለውን ክፍል ገንጥሎ ‹‹አማላጅ›› ነው ማለት አይቻልም፡፡ ቆይ መጽሐፉ ማለደ ካለ አማላጅ የማይሆንበት ምክኒያት ምንድን ነው? ቢሉ ሙሉ ክፍሉን ማንብብ ለዚህ ይበጃል ባይ ነኝ፡፡ ምክኒያቱም በዚህ ክፍል ውስጥ ያለው ሙሉ ንባብ ላይ የምናየው ነገር ሁሉ የቤዛነት ስራውን ነው፡፡ ስለዚህ እዚህ ላይ ማለደ የሚለው ክፍል አማላጅ ነው እንዳንል ከሚያደርጉን ምክኒያቶች መካከል አንዱና ዋነኛው ኢሳያስ ያስቀመጠው የቤዛነቱን ስራ በሙሉ ነበር፡፡ በጠቅላላም የማዳን ስራውን አይወክልምና፡፡ ይህን በይበልጥ ሌሎችን ምህራፎች ስናይ በሚገባ እንረዳዋለን፡፡

    ጌታ ቤዛነቱን በመስቀል ላይ ለሰው ልጆች እስኪፈጽም ድረስ ለሰው ልጆች ሁሉ ለዘራቸውም አብነት በመሆን ስጋችንን በመልበሱ በአብነት የፈጸመውን ስራ ለማውሳት ነው፡፡ በዚህም እርሱ በሄደባቸው የመልካምነት እና የትሩፋት ጎዳናዎች ላይ አርአያ ሆኗል፡፡ በመሆኑም ይህን ፍኖት በመከተል ተጋድሎዋቸውን የፈጸሙ በረካታ ቅዱሳን ናቸው፡፡ ለምሳሌ በኢሳያስ 53 ላይ የተጠቀሰው ሁሉ ክርስቶስ በነበረበት ዘመን ሁሉ ሆኗል፡፡ ስለዚህ ኢሳያስ እንደጻፈው ብቻ ሳይሆን መንፈስም እንደሚያስረዳው ስንወስደው፡፡ ማለደ ማለቱ ከቤዛነት ክፍል አንዱ መሆኑን ልብ ይለዋል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ እንዲህ ያለው አጻጻፍ መጽሐፍትን ሂደት የሚያሳይ ሲሆን መጽሐፍት ብዙ ጊዜ ምስቲር እንጂ ዘይቤ ላይ ጥንቃቄ አያደርጉም፡፡ የምክኒያቱም ነብዩ በኃላፊ ግስ ተጠቅሞ ክርስቶስን ዘመን የቤዛነቱን ድትጊት ማለደ አለ፡፡

    ለምሳሌ በሌላ መልኩ ደግሞ ከዚህ ትንቢት ጋራ ተመሳሳይነት ያለውን የአዲስ ኪዳን ንባብ መውሰድ እንችላለን፡፡ ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራዉያን መልዕክቱ ላይ በምዕራፍ 7÷25 ‹‹ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና…›› ብሎ ይመዝግባል፡፡ ታዲያ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ካሳ ሙሉ ለሙሉ በመስቀል ላይ ከፈጸመ በኋላ ወደፊትም እንደሚያማለድ አድርጎ በትንቢት አንቀጽ መዝግቦታል፡፡ ነገር ግን ድርጊቱ በእለተ አርብ መፈጸሙን ልብ ልንል ያስፈልጋል፡፡ ምክኒያቱም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን የማዳን ስራውን ሙሉ ለሙሉ በመስቀል ላይ መፈጸሙን በእለተ ዓርብ እንዲህ ሲል ራሱ ከሰጠው ምስክርነት (መረዳት) እንችላለን፡- ‹‹ ተፈጸመ ›› ዩሐ 19÷30፡፡ እንግዲህ ከዚህ የተጣሪ ቃል በላይ ሌላ ምስክር አያስፈልግም፡፡

    ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ ‹‹ተፈጸመ›› ማቱ ነቢያት ስለሱ የተናገሩት ትንቢቶች ሁሉ አንዳች እንኳን ሳይጎደል በእርሱ በኩል መፈጸሙንና የማዳኑንም ቃል እንደጠበቀና ሰውን ሁሉ እንደተቤዥው የማዳኑም ተግባር ፍጻሜውን እንዳገኘ ሲገልጥ ነው፡፡ እንጂ እንደ ስጋ ለባሽ የሰው ልጅ ሁሌ በበደለ ቁጥር በአባቱ ፊት ሁሌ ቆሞ ይቀር በል ማር እያለ ዘወትር ይማልዳል ማለት አይደለም፡፡ ይህማ ከሆነ ምኑን አምላክ ሆነ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ትልቁ የነጥብ ልዩነት ያለው በንባብና በመረዳት ላይ እንደሆነ ልብ በሎ ከዚያ ሌላ በራስ ስሜት ብቻ መጽሐፍትን መርምሮ መረዳት አዳጋች መሆኑን ልብ እንበል፡፡ ለዚህ ነው ሂንዴኬ ንግስት ባለሟል የነበረው ጃንደረባው በሰረገላው ላይ ቁጭ ብሎ የትንቢት መጽሐፍን ሲያነብ መንፈስ ቅዱስ ፊሊጶስን ወደ እርሱ እንዲሄድ ያነሳሳው፡፡ ልብ በሉ ፊሊጶስም ‹‹የምታነበውን ታስተውለዋለህ›› ባለው ጊዜ ያ ጃንደረባ እኮ እንዲህ ነው ያለው ‹‹የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይሆንልኛል›› የሐ.ስራ 8÷26-33፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ይህን አባባል ያጠነክረዋል ‹‹ፊደል ይገድላል መንፈስ ግን ያድናል›› ይላል፡፡ በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን ለእያንዳንዱ ጥያቄ መቀነቷ በፈታች ቁጥር ምራቅ የሚያስውጥ ድንቅ የሆኑ መልሶችን ሊያስገኙ የሚችሉ በርካታ መጽሐፍት አሉዋት ስለዚህ እነዚህን መመሪያ ብናደርግ ከስህተትም ከክህደትም ነጻ እንሆናለን፡፡

    አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዲስ ኪዳን ሊቀ ካህን እንደመሆኑ መጠን በጸሎተ ሐሙስ ስርዓተ ቁርባንን ሰርቶ ሐዋሪያትን የእርሱን አሰረ ፍኖት እንዲከተሉና መንጋውን እንዲጠብቁ አስጠንቅቆና የመጨረሻ ምክሩን ሰጥቶ ለጸሎት ወደ ጌተ ሰማኒ ከሐዋሪያት መካከል ሶስቱን ይዞ መሄዱን እና በዚያም ደም እስኪያልበው ድረስ በጭንቀት ሲጸልይ እንደነበር መጸሐፍ ይናገራል፡፡ ልብ አድርጉ እንግዲህ በአምላክ ዘንድ እንዲህ ያለ ጭንቀት የለም ነገር ግን የእኛን ስጋ ስጋው አድርጎ እኛን ለማዳን የቤዛነቱን ስራ ለመፈጸም ሲል ይህ ሁሉ ሆነ፡፡ የሚያበረታው መልአክ እስኪመጣለት ድረስ ክርስቶስ በጭንቀት ይጸልይ ነበር፡፡ ‹‹አባት ሆይ ቢቻልህ ይህን ጽዋ ከእኔ ይለፍ የአንተ ፍቃድህ ይሁን›› ችቀትና ፍርሀት የሰው ልጆች የሰጋ ለባሾች ችግር መሆኑ ይታወቃል እንግዲህ በሁሉ እኛን መምሰሉን ሲያጠይቅ ተጨነቀ፡፡ ኢሳያስ በትንቢት የተናገረው ቃል ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ጌታ የተናገራቸውን እና እንዲሁም የተናገራቸውን ነገሮች እንይ እስቲ፡፡ ማለደ የሚለውን ቃል በይፋ እንይ እንግዲህ ተፈጸመ ከማለቱ በፊት፡፡

    1) ‹‹ጌታ ኢየሱስም፡- አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁም እና ይቅር በላቸው››ሉቃ 24÷34
    2) ‹‹ኢየሱስም በታላቅ ድምጽም ጮኸ፡- አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ አለ›› ሉቃ 24÷7
    እንግዲህ እነዚህ ሁለት ንግግሮች ኢየሱስን ከአምላክነት ዝቅ አድርገው ከነቢያት ተርታ እንደሚመድቡት አድርገው የሚያዩ ብዙዎች ናቸው፡፡ በዚህም ቃል በርካቶች ሲሰናከሉ እንመለከታለን፡፡ ይህም የሚያሳየው በንባብ ውስጥ ያለው የግል መረዳትና የማስተንተን ችግር ነው እንጂ ይህ ቃል ለብዙዎች የመሰናከያ ውይም አማላጃችን ነው የሚለውን የድፍረት ንግግር እንዲናገሩ በር አይከፍትም ነበር፡፡ በተለይ የመጀመሪያው ቃል ነብዬ የተናገረውን ተፈጸመ ብሎ ነፍሱን ከመስጠቱ በፊት የነበረውን በስጋ ወራት ያደረገውን ምልጃ ያመላክታል፡፡ ተዲያ ያ ታሪክ ተፈጸመ ሲል አበቃ ማለት ነው፡፡ ያ ማለት ደግሞ ፈራጅ እንጂ ከእንግዲህ ማላጅ አይደለም ማለት ነው፡፡

    እንደ ትንቢት ቃሉ ደግሞ ክርስቶስ የፈጸማቸው ሁሉ የሰውን ለጆች ነጻ የማውጣት ሂደት ከበሕሪ አባቱ አብ የሚያንስ ስልጣን ያለው ውይም ምህረትን ማድረግ በራሱ የማይቻል መስሎ የሚታያቸው ሰዎች መኖራች አያጠራጥርም፡፡ በይፋ እንዲህ ባይሉም በእጅ አዙር ግን ዘወትር ሲያማልድ ይኖራል ካለ አንድ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ አምለክነት ያል ጥርጥር አለው ማለት ነው፡፡ ይህ ዓይነት አስተሳሰብ ከአንድ መጸሐፍ እየገለጠ ጥቅስ የቆነጸለ እመነኝ ብሎ ከሚከራከር ሰው አይጠበቅም፡፡ ይህ ማለት እኮ ክርስቶስ ከቤዛነት ድርጊቱ በኋላ ያለው ኃይል ስልጣን ቅድስና እልውና ሁሉ የማዳና የመግደል ስልጣን ሁሉ አሳንሶ በማየት ምስጢረ ስላሴን ማፋለስ ማለት ነው፡፡ ለዚህ ጽሁፍ መሰረታዊ የሆነ ጽንሰ አሳብ አድርጊ አንድ ነገር ማስገንዘብ እፈልጋለሁኝ በሚስጥረ ስላሴ ላይ ጥልቀት ያለው እውቀት ካለን ከሞቱ በኋላ ባለው የክርስቶስ ኢየሱስ ስራ ላይ አሁንም ይማልዳል ብለን የምናስብ ከሆነ ልብ በሉ ምን ያክል ክህደት እየፈጸምን እንደሆነ፡፡

    ኢየሱስ ክርስቶስ ከአባቱ ከአብ ጋራ በስልጣን ብክብር በአገዛዝ ትክክል ነው፡፡ በባሕሪ ይተካከለዋል አባቱ የሚሰራውን እርሱ ይሰራል፡፡ ይህን እንዲህ ልናይ እንችላለን በሰው ልጆች ጥፋትና ፍጥረት ላይ በአንድነት ይሰሩ እንደነበሩ መጸሐፍት ይናገራሉ ‹‹ሰውን በምሳሌያችን እንፍጠረ›› ‹‹ኑ እንውረድ አንዱም ከአንዱ በቋንቋ እንዳይግባቡ …..›› ስለዚህ ባሕሪይ አባቱ ገንዘብ ሁሉ ገንዘቡ ነው፡፡ ጸሎትን ይቀበላል ምህረት ያደርጋል፡፡ ይገድላል ያድናል ያከብራል ያዋርዳል እንጂ በስልጣን መበላለጥ የለም፡፡ ከሞቱ በፊት በመስቀል ላይ የሆነው ሁሉ በምስጢረ ስጋዌ ትምህርት መስረት ክርስቶስ ወዶ እና ፈቅዶ ዓለሙን ለማዳን ያሳየውን የማዳን ትህትና ራስን ዝቅ የማድርግ ተግባር ነው፡፡ ይህም ደግሞ በይበልጥ የሚገለጠው በሚስጥረ ተዋሕዶ የሚገለጽ ሲሆን ይህን እንዘርዝር ብንል ጊዜ ስለሚወስድብን በጥቂቱ ካየነው በቂ ነው፡፡ ‹‹ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።›› ዩሐ. 1÷14 ሲቀጥል ደግሞ በዚሁ ምዕራፍ ላይ ከቁጥር 1 እስከ 3 ድረስ ያለውን ደግሞ ብንመለከት እንዲህ ይነበባል ‹‹ በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም። ›› ብዙ መጥቀስ ይቻል ነበር ግን ለጊዜው ይበቃናል፡፡ እንዳንሰናከል ይህን ታክል ይበቃናል፡፡ ‹‹ዳሩ ግን ይህ መብታችሁ ለደካሞች ዕንቅፋት እንዳይሆንባቸው ተጠንቀቁ። ›› 1ኛ ቆሮ 8÷9፡፡

    2. ‹‹በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፥ ይገባልም ይወጣልም መሰማርያም ያገኛል።›› ዩሐ.10÷9
    3. ‹‹ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።›› ዩሐ.14÷6
    እንዚህ ሁለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅ እንደሆነ ለማስረዳት ከሚያመጡዋችን ማስረጃዎች መካከል ዋናዎቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ክፍሎች ደግሞ በትርጓሜም ሆነ በምንም ዓይነት ይዘትና ሁኔታ ስለ ምልጃ አያወሩም ምልጃ ከሚለው ጽንሰ አሳብ እጅግ በጣም የራቁ ናቸው፡፡

    እስቲ ልብ ብለን ደረቅ ንባቡን እንየው 2ኛ ላይ የተጠቀሰውን ጥቅስ ‹‹በሩ እኔ ነኝ በእኔም የሚገባ ቢኖር ይድናል….›› እንግዲህ እዚህ ንባብ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው በር እና በዚያ የመግባትን ሂደትና ከገቡ በኋላም ስላለው ሰላምና ድህነት ያወሳል፡፡ እንጂ በምንም መልኩ እኔ ካልማለድኩላችሁ አላለም ይህ ከሆነ የዚህ ንባብ ጽንሰ ሐሳብ ይፋለሳል ማለት ነው፡፡ ይህ ንባብ ሙሉ ለሙሉ የሃይማኖት አንቀጽ ነው፡፡ ልብ አድርጉ ወደ እግዚአብሔር መንግስት መግባት የማይፈልግ ሰው ይኖራል ብዬ አላምንም ታዲያ መግባት ካለበት የግድ መግቢያው ይሄ በር መሆኑን መረዳት አለበት፡፡ ይህውም በክርስቶስ በማመን ስለሚገኝ ጸጋ የሚያመለክት ሲሆን በኦርቶዶክሳዊ ትርጉም ስናየው ደግሞ እንዲህ ነው፡፡

    የንባቡ ኦርቶዶክሳዊ ምሳሌ፡- እንካችሁ

    1. ማንኛው ሰው ወደ ቤቱ ለመግባት ግድ ቤትን ቤት እንዲባል ሙሉ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል አንዱ በር በመሆኑ በበር ማለፍ አለበት፡፡ እንዲሁ ሁሉ መንግሰተ ሰማይ ለመግባት በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕሪ ልጅነትና አምላክነት ማመን ይገባልና፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት ሳያምኑ መንግስቱን መውረስ ስለማይቻል፡፡ እንግዲህ የበጎች በር ክርስቶስ ሲሆን በጎቹ ደግሞ ምዕመናን ናቸው፡፡ በእኔ የገባ ሰው ይድናል ማለቱ በእኔ አምላክነት የሚያምን ከመከራና ከክህደት ይድናል ማለቱ ነው፡፡ ይገባል የወጣል መሰማሪያም ያገኛል ሲል ደግሞ ወደ ሃይማኖት ይገባል በዚያም ለመልካም ምግባር ልቦናው ይከፈታል መልካሙንም ያደርጋል ሲል ነው፡፡ ይህን መልካም ነገር ሃይማኖቱን በምግባር በመግለጡ ደስተኛ ይሆናል ሲል ነው፡፡

    2. ሲቀጥል ደግሞ እኔን አብነት ያደረገ መመሪያው ያደረገ መንገዴን የሚከተል ከመከራ ስጋት ያርፋል ሲል ነው፡፡ ከእርሱም የተማረውን ወንጌል በዓለም ላሉት ሁሉ ይሰብካል ያስተምራል፡፡ በዚህም እምነቱ በርካቶቹን ለክርስቶስ መንግስት ሙሽራ ያደርጋል ሲል ነው፡፡ ‹‹ትእዛዛቱንም ብንጠብቅ በዚህ እንዳወቅነው እናውቃለን።›› 1ኛ ዩሐ 2÷3፡፡ ሲቀጥል ደግሞ እኔን የሕይወቱ በኩር ያደረገ ከመከራ ከቅጣት ይድናል ማለቱ ነው፡፡ የነፍሱንም ፍቃድ ያደርጋል የነፍስና የሰጋን ፍቅር ያገኛል መንግስተ ሰማያትንም ይወርሳል ማለት ነው፡፡ ‹‹ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ። ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም። በመንፈስ ብትመሩ ግን ከሕግ በታች አይደላችሁም። የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት፥ ርኵሰት፥ መዳራት፥ ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥ መለያየት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት፥ ይህንም የሚመስል ነው። አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ፤ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው። እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም። የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ። በመንፈስ ብንኖር በመንፈስ ደግሞ እንመላለስ።እርስ በርሳችን እየተነሣሣንና እየተቀናናን በከንቱ አንመካ።››
    በአጠቃላይ ከላይ ያየናቸው ንባቦች አንቀጸ ሃይሞኖቶች ናቸው፡፡ እንጂ ከምልጃ ጋራ ምንም ዓይነት ግኑኝነት የላቸው፡፡
    3. ‹‹ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።›› ዩሐ.14÷6

    ሌላው ደግሞ የመከራከሪያ ነጥብ እንዲሆን ከሚቀርበው ጥቅስ መካከል በዮሐ14÷6 ላይ ያለው ይህ ክፍል ነው፡፡ እስቲ ይህን ምህራፍ ከቁጥር አንድ ጀምረን እንመልከተው በቁጥር 1 ‹‹ ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ።›› ይህ የሚያሳየው ሰዎች በማመንና ባለማመን ውስጥ በሁለት አሳብ እንዳይኖሩ የሚያደርግ ተጸህኖ ፈጣሪ የእምነት ቃል ነው፡፡ በዚህ ክፍል እንደተገለጸው በእግዚአብሔርም ማመን በክርስቶስም አምላክነት ማመን የእምነት መሰረት ነውና፡፡ በመሆኑንም ይህ አረፍተ ነገር እምነትን የሁሉ መስረትና አድርጎ የሚነሳ ይመስላል፡፡ ሲቀጥል ደግሞ በማነቻው ክርስቶስንም አባቱንም በመከተላቸው ሐዋርያት ከእርሱ መንግስ ምን ሊጠብቃቸው እንደሚችል፡፡ ይህ እምነታቸው ደግሞ እርሱ በሚኖርበት ሊያኖራቸው እንደሚችል ይገልጣል፡፡ በአጣቃላይ በበሐሪይ አባቱ ዘንድ ብዙ መኖሪያ እንዳለን በዚያም ሄዶ ለእነርሱ መኖሪያ ሊያዘጋጅ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ሲቀጥል ደግሞ በቁጥር 4 ላይ እንዲህ ይላል ‹‹ ወደምሄድበትም ታውቃላችሁ፥ መንገዱንም ታውቃላችሁ።›› ይህን ጥያቄ ሲጠይቃቸው ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የሆነው ቶማስ በቁጥር 5 ላይ እንዲህ ብሎ መንገዱን እንደማያውቅ መጠየቁን እናነባለን ‹‹ ቶማስም። ጌታ ሆይ፥ ወደምትሄድበት አናውቅም፤ እንዴትስ መንገዱን እናውቃለን? አለው።›› ልብ እናድርግ እንግዲህ፡፡ ስለሃይማኖት የጽድቅ መንገድ ሲጠይቃቸው ይህን መንገድ እንደማያውቁት እንዲያሳውቃቸውም መጠየቃቸው ነው፡፡

    ወደ ማስረጃው ወይም አማላጅ ነው ለሚለው ንግግር አስረጂ ነው ብለው ወዳቀረቡት ቃል ስንመጣ ደግሞ፡ እንዴት እንደሆነ እናገኘዋለን፡፡ ሐዋሪያት ውደ ወንጌልና ሃይማኖት ሊወስዳቸው የሚችለውን መንገድ ባለማወቃቸው ያ መንገድ ከእነርሱ ዘንድ መሆኑንና መንገዱም እርሱ መሆኑን ሲገልጥላቸው እንመለከታለን እስቲ እንመልከተው ቁጥር 6 ላይ ያለውን ቃል፡ እንዲህ ይላል ‹‹ ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።›› ልብ አድርጉ መንገድና ሕይወት ነኝ አለ እንጂ በዚህ ንባብ ውስጥ ስለ አማላጅነት የሚያሳይ ምንም ዓይነት ቃል የለም፡፡ ክርስቶስም የሕይወት መንገድ መሆኑን ወደ አብ ሊያደርስ የሚችል ብቸኛ መንገድ መሆኑን ተናገረ እንጂ አማላጅ ነኝ አላለም፡፡ እስቲ አንድ የሚገርም ነገር ደግሞ ከዚሁ ክፍል ላይ እንመልከት፡፡

    የሰው ልጆች እግዚአብሔርን ካለማወቅ የተነሳ እንደሳቱ ደግሞም ጥበብና እውቀት ከማጣት የተነሳ እንደረከሱ በትንቢት መጽሐፍት ላይ ተመዝግቦ የምናገኝው አውነት ነው ‹‹ ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል›› ት/ሆሴ 4÷6፡፡ እንግዲህ እውቀት ከማጣት የተነሳ ጥፋት አለ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ውስጥ የተጻፈውን መልዕክት በሚገባ ለመረዳት ሙሉውን በማንበብ ተዋረዱንም በማየት እኛ ያነሳነው ወይም የወሰድነው አንድ አረፍተ ነገርን በይበልጥ ሊያስገነዝብ ይችላልና ለመከራከሪያ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስን ለእውቀትና ለመመሪያነት ብለን እናንብበው፡፡

    ሌላው አስገራሚ ነገር በዚህ ምዕራፍ ወስጥ የምናየው ነገር ኢየሱስ ክርስቶስ መንገድና ሕይወት እኔ ነኝ ካለ በኋላ ይቀጥልና በቁጥር 8 ላይ እንዲህ ይላል ፡- ‹‹ እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር። ከአሁንም ጀምራችሁ ታውቁታላችሁ አይታችሁትማል አለው።›› እንግዲህ ከዚህ ምንባብ ላይ የምንረዳው ነገር ቢኖር ማመንና ማወቅን ነው ይህን ተግባር መፈጸም ወልድን በሃያማኖት ማወቅ አብንና መነፈስ ቅዱስን ማወቅ መሆኑንና በእምነትም ማየትን ያመለክታል፡፡ ታዲያ ይህ ንባብ ሙሉውን ብናየው አንድም እንኳን ስፍራ ላይ ስለ ማማለድ አይናገርም፡፡ እስቲ የሐዋሪያትን ሌላ ጥያቄ ደግሞ እንመልከት በቁጥር 8 ‹‹ ፊልጶስ። ጌታ ሆይ፥ አብን አሳየንና ይበቃናል አለው።›› እግዲህ ለማየት ማመን እንዳለባቸው ሲናገር ይህ ምስጢር ያልተረዳው ሐዋሪያ አብን አሳየነ ብሎ ጠይቆታል፡፡ አስቀድመን እንዳልነው ነው መጽሐፍት ምስጢር ላይ እንጂ ዘይቤ ላይ ትኩረት እንደማያደርጉ፡፡ ክርስቶስም እኔና አብ አንድ ነን ሲል በአገዛዝ በስልጣን በመለኮት…. ይህን ምስጢረ ስላሴ ላይ ይመለከቷል፡፡ ክርስቶስም እንዲህ ነበር ያለው ለቶማስ በቁጥር 9 ‹‹ ኢየሱስም አለው፦ አንተ ፊልጶስ፥ ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ አንተ። አብን አሳየን ትላለህ?›› ይህ ንግግር ወቀሳም ማስታወሻም ጭምር ነበር፡፡

    እንግዲህ በዚህ ምዕራፍ ላይ ያለውን ንባብ ወስዶ አማላጅ ነው ማለት እኔ እንደሚመስለኝ ልክ እንደ ፊልጶስ መሆን ነው ባይ ነኝ፡፡ ምክኒያቱም ሲጀምር የእምነት ጥያቄ በማንሳት ይጀምራል በእኔም እመኑ በአባቴም እመኑ ብሎ ሲቀጥል በእምነት ወልድን ያየ አብን ያያል አለ፡፡ ይህም የሚሆነው መንገድ የሆነውን ሃይማኖት ውስጥ በእምነት ስንኖር መሆኑን ይነግረናል፡፡ እንግዲህ ይህን ያህል ያለመረዳት ከሆነ እንግዲህ የማስረጃው እውነት ይህ ነው፡፡ ነገር ግን አውቆ በድርቅነ ከሆነ ይህ ራሱን የቻለ ችግር ነው ማለት ነው፡፡

    ይህን ክፍል ሙሉ በሙሉ ስናነበው ውደ አንድ አቅጣጫ ያደርሰናል ይህም በክርስቶ ማመን እርሱ ሊያደርግ የሚችለውን ማድረግ መሆኑን እርሱ እራሱ ተናገረ እንዲህ ሲል ‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፥ ›› ዮሐ. 14÷12፡፡ የቀረውን ሙሉውን እንድታነቡት በማለት እስቲ ወደ ሚቀጥለው የዚህ ክፍል ትርጓሜ እንሂድ፡፡ ይህ ትርጓሜ በሊቃዎት አባቶቻችን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊው ትርጓሜ ደግሞ እንዲህ ያስረዳል ከአባቶቻችን የተቀበልነው፡፡

    የግዕዙ ንባብ እንዲህ ይላል ‹‹ ወይቤሎ እግዚዬ ኢየሱስ አነ ውእቱ ፍኖተ ጽድቅ ወሕይወት ወአልቦ ዘይመጽእ ኀበ አበ እንተ ኀቤየ ኪያየ አእመርክሙኒ እመአእመርክዎ ለአቡየኒ›› ይላል የዚህ ነባብ ነጠላ ትርጓሜ ስንመለከት እንዲህ ይላል፡- ‹‹ የሕይወትና የጽድቅ መንገድ እኔ ነኝ፡፡ ያለ እኔ ወደ አብ የሚመጣ የለም፡፡ እኔን አውቃችሁኝ ቢሆን አባቴን ባወቃችሁት ነበር››፡፡

    1. የመጀመሪያው የምስጢር ትርጓሜ እንደሚያሳየው ከሆን የሚስጥረ ስላሴን ሲሆን ‹‹ በክርስቶስ የሚያምን ሁሉ በአንድነትና በሶስትነት፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ መሆናቸውን ይረዳል ያውቃል ማለት ነው፡፡›› ስለ ምስጢረ ስላሴ ስናነሳ ምስጢረ ስላሴ በሙላት የታየውና የተገለጣው በዘመነ አዲስ ኪዳን መሆኑን ከዚህ ንባብ መረዳት እንችላለን፡፡ በዘመነ ብሉይ ኪዳን ለጥቂት አባቶቻችንም መገለጡን እርግጥ ነው፡፡ ለአባታችን ለአብርሃም በመምሬ የአድባር ዛፍ ስር በእንግድነት ወደ ቤቱ የገቡት ሶስቱ ሰዎች፡፡ እንዲሁም ለኢሳያስ የተገለጡት ሰማይ ተከፍቶ አንዱም ለአንዱ ቅዱስ፤ ቅዱስ፤ ቅዱስ እያሉ ሲያመሰግኑ እንደሰማውና እንዳየው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝቧል፡፡ በመሆኑም ከዚህ በመነሳት ማንም ወልድን ልጅ ካለ አብን አባት ማለቱ ማለቱ አይቀርም፡፡ አብ ማለት አባት ከሆነ ዘንድ የማን አባት ቢሉ የወልድ የባሕርይ አባቱ ነው መልድም ለአብ የባሕርይ ልጁ ነው ይላል፡፡ በመሆኑንም በወልድ ልጅነት የማያምን በአብ አባትነት አያምንም ማለት ነው፡ ስለዚህ በአብ ወላዲነት ለማመን የወልድን ተወላዲነት ማመን ያስፈልጋል፡፡

    ክርስቶስን ማወቅ አብን ማወቅ ነው ይህም የእርሱ ትምህርት እንደሆነ ይህንንም አምነን እንድንቀበል ሐዋሪያት ያሳስባሉ፡፡ በተለይም በዚህ ዙሪያ ከማንም ጋራ ምንም አይነት ድርድር ማድርግ አያስፈልግም ሁላ ይለሉ፡፡ምክኒያቱም ከዚህ የተለየ ትምህር ይዞ የሚመጣ ካለ በእንግድነትም በቤታችሁ ቢገኝ ይህን ትምህርት ካላመጣ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት ሰላምም የሚለውም ካለ በክፋት ስራው ከእርሱ ጋራ ይተባበራል ይላል፡፡ ‹‹ ለሚወጣ ሁሉ በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት። ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት፤ ሰላም የሚለው ሰው በክፉ ሥራው ይካፈላልና።›› 2ኛ ዮሐ 1÷19-11፡፡ በመቀጠልም ያለውን ጥቅስ እንመልከት በማመን ምን ያክል ለአብ ቅርብ እንደሆንን ዮሐንስ ወንጌላዊ ስናገር እንዲህ ይላል፡፡ ይህ መልዕክቱ ማንም በራሱ አብን ሊያይ አይችልም አልቻለምም ‹‹ መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው።›› ዮሐ 1÷18፡፡ ‹‹ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፥ ከወልድም በቀር ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም።›› ማቴዎስ 11÷27፡፡ በመጨረሻም ለሐዋሪያት የሰጠውን ስልጣን እንመልከታለን ‹‹እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።›› ማቴዎስ 28÷19-20፡፡

    2. ሌላኛው ትርጓሜ ደግሞ እኔን አብነት አድርጋችሁ እኔ የምስራውን ከአብ ዘንድ ለመስራት ትችላላችሁ ሲል ነው፡፡ ነገር ግን ማንም ወልድን አብነት ሳያደርግ ምንም ሊሳራ አይችልም ማለት ነው፡፡ ይህም ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም ከሚለው ጋራ ስናስታያየው ትርጓሜው የእኔን አሰረ ፍኖት በመከተል እኔ ያደረኩትን ሁሉ ማድርግ ትችላላችሁ ሲል ነው፡፡ ‹‹እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ፥ እንዲህም አላቸው፦ ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን?›› ዮሐ 13÷12፡፡ እንግዲህ ይህ እርሱ ለእኛ ያደረገውን ነገር አስታውሰን እርሱን በመከተል ካደረግነው እራሱ እንደተናገረው እኔ ከማደርገው በላይ ያደርጋል ይላል እና ይህን ፍኖቱን ስለመከተል ያወሳል፡፡ ‹‹እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል። በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፥ ያቃጥሉአቸውማል። በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል። ›› ዮሐ. 15÷5-7፡፡ ‹‹የትሩፋት ስጋ የትሩፋት ነፍስ አብነት እኔ ነኝ፡፡ አረኔነረ አበረነተረ ካላደረገ አባቴን ስራ አሰራኝ የሚለው ማንም የለም፡፡ እኔንስ አብነት አድርጋችሁ ቢሆንስ ኖሮ አባቴን ስራ አሰራኝ ባላችሁት ነበር፡፡›› ሲለን ነው፡፡

    3. ላለው ትርጓሜ ደግሞ ‹‹የከበረ ስጋ የከበረ ነፍስ ባለቤት እኔ ነኝ፡፡ እኔን በኩር ያላደርገ አብን አክብረኝ ማለት አይችልም፡፡ እኔን በኩር አድርጋችሁኝስ ቢሆን አባቴን አክብረን ባላችሁትስ ነበር፡፡›› እንግዲህ ማንም ከእግዚአብሔር ለሚፈልገው ክብርና ሞገስ ከወልድ ማግኘት እንደሚችል ሲያሳይ ይህም ማለት ወልድን ማመን አብን ማመን መሆኑን ሲያስቀምጥ ነው፡፡ እንግዲህ በዚህ ክፍል ውስጥ እንዲህም አልን እንዲያ የምናየው እውነት የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት የሚያሳይ እንጂ ስለምልጃ የሚያወራበት ምንም አይነት ነገር የለውም፡፡

    እንግዲህ እንዳየነው ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ በዮሐንስ የወንጌል ክፍል ላይ ተናገረው ንግርር ሙሉ ለሙሉ ስናየው የሃይማኖትን መግቢያ የሆነውን መንገድ መሆኑንና በእርሱ ማመን እኛን ወደ እግዚአብሔር መንግስት እንድንገባ ይረዳናል ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ያለምንም ጥርጥር በእርሱ ማመን አብን ማመን ነውና፡፡ እርሱን ማመን አብን ማየት ነውና፡፡ ስለዚህ እመኑብኝ እንጂ አማልዳቹዋለሁኝ አይልም መልዕክቱም ስለዚህ በሚገባ መረዳት ይኖርብናል ማለት ነው፡፡

    4. ‹‹የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው።›› ሮሜ 8÷34
    እንግዲህ ሌላው ኢየሱስ ክርስቶስን አማላጅ ነው ብለው ሲናገሩ የሚያቀርቡት ማስረጃ ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልዕክቱ ላይ ያስቀመጠውን ይህን መልዕክት ነው፡፡ እንግዲህ ከላይ እንዳየነው ሁላ ምልጃ የሚለውን ነገር ስናነሳ አብሮ ሊታዩ የሚገባቸው ነገሮች አሉ፡፡

    ከዚህ በፊት እንዳየነው ክርስቶስ ከንጽህት ቅድስት ድንግል ማርያም በስጋ መገለጡ በሰው ዘር ላይ የመጣውን የኃጢያት ምክኒያት ከስሩ ለመንቀል መሆኑን ግልጽ ነው፡፡ ከጽንስ ጀምሮ እስከ መስቀል ሞት ድረስ ተጉዞ የሰውን ሁለንታዊ ባሕርይ ተላብሶ የእኛን ኃጢያት ያስወግድ ዘንድ በስጋ ተገለጠ እንጂ ክርስቶስ እግዚአብሔርነት የሌለው አስመስሎ ሩቅ ብእሲ ይመስል አማላጅ ነው ማለት ይህ የአምላክነት እልውናውን የሚጋፋ በመሆኑ አጠያያቂ ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ ጌታ በማዳን ስራውስጥ ያደረጋቸውን ጸሎቶች እንዲሁም የምልጃ ንግግሮች ወስዶ ሳይረዱ አማላጅ ነው ማለት አይቻለም፡፡ ይህ አስቀድመን እንዳልነው ከጽንስ እስከ መስቀል ድረስ የተደረገ የቤዛነት ሳራ ነው እንጂ፡፡ ስለዚህ ክርስቶስ ተሰቃይቶ እና መከራን ተቀብሎ ከባሕርይ አባቱ ከባሕርይ ሕይወቱ ከራሱም ጋራ በሞቱ አስታረቀን እንጂ፡፡ ቤዛ ሆነን እንላለን ወይም ስለበደላችን ካሳ ሆነልን እንላለን እንጂ አማላጃችን ነው አንልም፡፡ አማላጅ አለመባሉንም እንግዲህ በጥቂቱ ለመመልከት እንደሞከርነው አሁሉ አሁን እንደ ቀደመው እንቀጥላለን፡፡

    እስቲ ምልጃ ሲነሳ የሚነሱትን ሶስት ነገሮች አብረን እንመልከታቸው፡፡
    1. የሚማለድለት (የሚማልዱለት/የሚለምኑለት)
    2. የሚማልድ (አማላጅ/የሚለምን)
    3. ምልጃን ተቀባይ (የሚምር/ ይቅርታ የሚያደርግ)
    እነዚህ ክፍሎች በቅዱሳን የምልጃ ትምህርት ውስጥ በሚገባ ተብራርተው የሚገኙ ናቸው፡፡ ምናልባት ፈጣሪ ፍቃዱ ከሆነ በቅዱሳን ምልጃ ዙሪያ የምናየው ይሆናል፡፡ ምልጃ ጠያቂ የሚማለድለት ሰው በእግዚአብሔር ይቅርታ ይጎበኝ ዘንድ ቀዱሳን ስለእርሱ ይማልዱለት ዘንድ ይጠይቃል፡፡ ይህም ቅዱሳን በእግዚአብሔር ፊት ለመቅረብ ከተራ ምዕመን የተሻለ ስልጣን ስለተሰጣቸው፡፡ ይህን ልመና በጸሎት ያቀርባሉ፡ ንጹሀንና በእግዚአብሔርም ዘንድ ሞገስ ስላላቸውም እነርሱን አማለጅ እንላቸዋለን፡፡ ምክኒያታችንም እግዚአብሔር ቃል ስለገባላቸው ነውና፡፡ ስለዚህ ክርስቶስን አማላጅ ነው ካልነው ስህተት ውስጥ መውደቃችንም አይደል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም እንኳን እኛን መስሎ ከኃጢያት በስተቀር ሁሉን ቢሰራም ይህ ሁሉ እኛን ለማዳን እንጂ ሌሎች እንደሚሉት አማላጅ የሚለውን ቃል በድፍረት እንድንናገር አያደርግም፡፡ ይህን ሁሉ ያደረገው የሰውን ልጆች በወጥመዱ ውስጥ ያደረገውን ሰይጣንን በትህትና ለማቅደብና ልጆቹንም ነጻ ለማውጣት ሲሆን በዚህም ስራው ስልጣኑን ገፎና ነፍሳትን ሁሉ ነጻ አውጥቶ በእኛ ላይ የነበረውንም ስልጣኑንም ገፎ ባዶውን ሰዶታል፡፡ ስለዚህ ተለማኙ ምህረት አድራጊና በዜዛችን መባል ሲገባው ልክ እንደ ፍጡር አማላጅ ማለቱ እጅግ ከባድ ነው፡፡ አማላጅም ሊባል አይገባውም እንጂ፡፡

    አንዳንዶች እንግዲህ እንዲህ የመጸሐፍን ክፍል በማንሳት አንድ ሐረግ በመምዝዝ ሲስቱና ሲያሳስቱ እናያለን፡፡ ለመሆኑ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን መልዕክት ሲጽፍ ምን ማለት እንደፈለገና ከዚህ መልዕክት በፊትስ ምን ብሎ እንደነበር ስንቶቻችን ነን ልብ የምንለው፡፡ እስቲ ይህን ክፍል በጥቂት በጥቂቱ እንየው፡፡

    ‹‹እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም።›› ይህ ከመስቀል ሞት በኋላ ያለውን የሰውን ልጆች ነጻ መውጣትና በማዳኑም ስራ የሚያምኑትን ሰዎች ሲወክል ነው፡፡ ይህም ማለት በአምላክነቱና በደሙ መዳኑን አምኖ ተቀብሎ የሚመሰክር እርሱ በክርስቶስ ውስጥ እንዳለ ክርስቶስም በእርሱ እንዳለ ያስረዳናል፡፡ እንግዲህ እንዲህ ብሎ የሚጀምረው ይህ መልዕክት ይቀጥልና አብዛኞቹ ማላጅ ነው የሚለውን ንግግራቸውን ለማስረዳት እንደ ማስረጃ አድርገው የሚጠቅሱት ጥቅስ ላይ ያደርሰናል፡፡ ‹‹የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው።›› እንግዲህ በዚህ ምንባብ መሰረት ከሄደን ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ሳይሆን ሌላም አማላጅ መኖሩን ቅዱስ ጳውሎስ ይጠቅሳል ‹‹ እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፤›› ሮሜ 8÷26፡፡ እንደገና በዚሁ አያይዞ ሲቀጥል እንዲህም ይላል፡- ‹‹ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደ ሆነ ያውቃል፥ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና።›› ሮሜ 8÷27፡፡ ስለዚህ ይህ ጥያቄ በራሱ ሌላ ጥያቄ ማንሳቱ አይቀርም፡፡

    እስቲ ተጨማሪ ሊላ ነገር ደግመ እንመለክት ከዚሁ ምንባብ ላይ፡፡ እነርሱ እንደሚሉት ከሆነ ለምን ኢየሱስ ክርስቶስን ብቻ አማላጅ ብለው ጠሩት መጽሐፉ እንደሚል ከሆነ መንፈስ ቅዱስም አማለጅ ነው እኮ፡ ስለዚህ አንድ ብቻ ሳይሆን ሁለት ማለጅ ሁለት ጠበቃ ሁለት አስታራቂ ነው ያለን እነርሱም ኢየሱስ ክርስቶስና መንፈስ ቅዱስ፡፡

    ነገር ግን እውነታው እንዲህስ አይደለም እኛ ግን እንዲህም እናምናለን እንዲህም እንታመናለን፡፡ እርግጥ አሁን ዘመን ላይ በአብዛኞቻችን እጅ ላይ ያለው መጽሐፍ ቅዱስ አብዛኛውን ቃል በቀላል አማርኛ ከሚለው ምክኒያተዊነት በመነሳት በርካታ ቃላት ትርጉማቸው እንዲፋለስና ውላቸውን እንዲያጡ ተደረገው ተመዝገበዋል፡፡ እስቲ የእኛ መጸሐፍ ቅዱስ ደግሞ የሚለውን እውነታ እንመልከት የግዕዙም የአማርኛውም መጽሐፍ ቅዱሳችን እንዴት እንደሚያስነብበን እንይ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከድካማችን ይረዳናል፡ እንግዲህ ተስፋችንን ካላወቅን ጸሎታችን ምንድን ነው?፡ ነገር ግን እርሱ እራሱ ስለመከራችን ስለ ችግራችን ይመልስልናል እርሱ ልቦናችንን ይመረምራል ልባችንን እርሱ ያውቃል፡ ስለ ቅዱሳንም ይፈርዳል እንጂ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያማልዳል የሚል ንባብ የለም ይህን እያረሙ ሊያነቡት ይገባል፡፡

  2. ‹‹አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤›› 1ኛ ጤሞ 2÷5

    ይህ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቲዎስ ክርስቲያን የጻፈላቸው መልዕክት ልክ እንደከዚህ ቀደሙ ከላይ እንዳየናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባት ዓይነት ነው፡፡ ይህም ላት ከመወለድ እስከሞት ድረስ የነበረውን ሂደት የሚያሳይና የእኛን ለማዳን የነበረውን ብርቱ የሆነ ስራና አድጋሚ የነበረውን ተጋድሎ ለማሳየት ነው፡፡ ልብ አድርጉ አዳም በሰራው ስህተት ከገነት መሰደዱ ይታወቃል፡፡ ታዲያ ከአዳም ከተሰደደ በኋላ ያጣውን ገነት ለማግኘት ሲል ሱባኤ እንደቆጠረና ደግሞም ብዙ መሰዋዕቶችን ይሰዋ እንደነበር ዘመኑንንም በጸጸትና በለቅሶ ይገፋ እንደነበር ቅዱሳት መዛግብት ይዘግባሉ፡፡ ይህ በአዳም በኩል የመጣው ሞት ለሁሉም በእኩል መልኩ ይደርስ እንደነበረም መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ ሐዋርያው ይህን ሲገልጥ ‹‹ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኖአልና። ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና።›› 1ኛ ቆሮ 15÷21-22፡፡

    እግዲህ ሕዝብ እንዴት ባለ ኃጢያት ውስጥ እንደነበር ያሳያል የቆሮንቶስ መልዕክቱ ያስረዳናል፡፡ የግዞቱ ዘመንና የባርነቱ ዘመን በአንዱ በአዳም ምክኒያት ወደ ዓለም መጣ በዚህም ሁሉም እርኩሰትን እንደተላበሱ እንመለከታለን፡፡ ከሰው ዘር አንዳች እንኳን ንጹሕ ባልነበረበት ወቅት (በእግዚአብሔር እሊና ከታሰቡት ውጪ ማለቴ ነው) በእኛ እና በእግዚአብሔር መካከል ሊሆን የሚችለው አንድ እርሱ መሆኑን ሲያመለክት ‹‹መካከል›› አለው፡፡

    እስቲ የሰውን እርኩሰትና የክርስቶስን የማዳን ለአፍታ ትንሽ እናስበው፡፡ ከትንቢት የማዳኑ መገለጥ የድንግል ማርያምን መመረጥ፤ የመላኩ ቅዱስ ገብርኤል ብስራት፤ የሄሮድስ አሳዳጅነት፤ የሕጻኑ ከአባቱና ከእናቱ ጋራ መሰደድ፤ እንደ ተፈጥሮ ጸባይ እናቱና አባቱን ሲታዘዝ ማደጉ፤ በዮሐንስ እጅ መጠመቅ፤ ተከታዮች ስለማፍራቱን ድሆችን በቸርነቱ ምግበ ስጋ ምግበ ነፍስ መግቦ ስለማጥገቡ፤ በፍርድ ሸንጎ ፊት ከሶ መቅረቡን እነኚህን ሁሉ ለአፍታ ብናስባቸው አንድ ጥያቄ ወደ ውስጣችን መምጣቱ አይቀርም፡፡ በተለይም በመጨረሻዎቹ አንድ ሳምንታት ውስጥ በክርስቶስ ላይ የነበረው ጭንቀት እና መረበሽ በጌቴ ሰማኒ የጸሎት ሰዓጥ፤ በቀይ አፋ ግቢ ውስጥ በእለተ አርብ ሳይነጋ መስቀል ተሸክሞ የሆነውን የተገረፈውን የተተፋበትን በጥፊ የተመታበትን የተሰደበበትን በአሽሙር የተዘለፈበትን ሁኔታ እስቲ ለአፍታ እናስበው፡፡ ይህ ሁሉ ከምንና ለምን ይመስላቹዋል?፡፡ ይሄ ሁሉ ለእኛ እንደሆነ እንገነዘበው ይሆን፡፡

    ታዲያ ይህን ሁሉ ለእኛ እንደሆነ ከተገነዘብነው ዘንድ ሐዋሪያው የጻፈው መልዕክት ምስጢሩ ይገባናል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ይህ መልዕክት በምንም ተዓምር አማላጅነትን አይመለከትም ይልቁንስ ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ጋራ ካመሳከርነው ፈራጅ የሚለውን እውነታ ነው የሚያመሳክረው፡፡ በሂደት እናየዋለን እንግዲህ፡፡

    የንባቡ መሰረታዊ አላም ምንድን ነው? የሰው ልጅ በበደሉና በእርኩሰቱ ምክኒያት ከእግዚአብሔር ዘንድ ተለይቶ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስም ታሪክም ያወሳል፡፡ እንግዲህ ይህ በእንዲህ እንዳለ በእኛ በኃጢያተኞቹ ምክኒያትን በቅዱሱ እግዚአብሔር መካከል አንድ ሊያደርገን የሚችል ያጣነውን ሰላም የሚመለስልን ከባርነት ቀንበር ነጻ ሊያወጣን የሚችል ከሞት ሰንሰለት የሚፈታን የሲኦልን መዝጊያዎች የሚሰባብረው ሞትንም በሞቱ የሚያሸንፈው አንድ ያለው ብቸኛው እርሱ ኢሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው ሲል ነው፡፡ ዓለምን ሁሉ ከኃጢያት የሚያድነው ነብያት ቅዱሳን በደም ስርዓት ከበደል እንደነጹ ነገር ግን ይህ የሚሆነው ለዘለቄታው መፍትሄ ሳይሆን ጊዜያዊ ነጻነት ይሰጣቸው እንደነበር እንመለከታለን፡፡ ‹‹…እንደ ሕጉ ከጥቂቶች በቀር ነገር ሁሉ በደም ይነጻል፤ ደምም ሳይፈስ ስርዬት የለም፡፡›› ዕብ. 9÷22፡፡ ታዲያ ይህ የመንጻት ስርዓት ሁሌም በየዓመቱ አንድ ጊዜ እንደሆነ እንመለከታለን፡፡ ታዲያ ይህም ቢሆን ከእሊና ነጻነት በቀር ሌላ ለሰዎች ምንም ዘለቄታዊ መፍትሄ የሰጠም የድህነት ስራ እንዳልነበር ያሳያል፡፡ ታዲያ ይህ በእንዲህ እንዳለ የቀደመውን ኪዳን መሻር የሚችል መካከለኛው እርሱ ብቻ ነው ሲል ነው፡፡

    በባለጸጋወና በድሀው አላዛር መካከል በጥም ትልቅ ልዩነት ነበር ደሀው አላዛር ሞተ መልአክትምውደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት ባለ ጸጋውም ደግሞ ሞተና ተቀበረ በሲኦል በስቃይ ሳላ አሻቅቦ አብርሃምን አዬ ደሀውን አላዛርንም በእቅፉ እርሱም እየጮኽ፡- ‹‹አብርሃም አባት ሆይ ማረኝ፡- በዚህ ነበልባል እሰቃያለሁና የጣቱን ጫፍ ውኃ ነክሮ ምላሴን እንዲያበርድ አላዛርን ስደድልኝ አለው፡፡›› አብርሃምም እንዲህ ነበር ያለው ‹‹…በእኛና በእናንተ መካከል ታላቅ ገደል ተደርጎአል አለ›› ሉቃ 16÷19-31፡፡ እስቲይህን ከፍል በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ሆናችሁ ሙሉውን አንብቡት፡፡ አሁን ግን ለተነሳንበት አላማይጠቅመንዘንድ ‹‹…በእኛና በእናንተ መካከል ታላቅ ገደል ተደርጎአል…›› የሚለውን ክፍል እንወስዳል፡፡ ታዲያ በዚህ ታሪክ መስረት ማንም ወደዚያ መሄድ አይችልም ማንም ደግሞ ወደ አብርሃም እቅፍ መምጣት አይችልም ምክኒያቱም ታላቅ ጥልቅ የሆነ ገደል አለ፡፡ አብርሃም ቢራራ እንኳን ይህን ለማድረግ እንደማይችል ያሳያል ያ በመካከል ያለው ገደል የልዩነታቸው ገደብ ነው እንግዲህ፡፡

    አሁን ወደተነሳንበት እውነት ስንጠጋ ደግሞ ይህን ገደል መሻገር የሚችለው አንድ አለና ሲለን ቅዱስ ጳውሎስ ይህን አለ፡፡ በቆሸሸው በሰው ልጅ መካከልና በቅዱሱ እግዚአብሔር መካከል ያለው የጠብ ግድግዳ እንዲፈርስ ምክኒያቱ እርሱ እንደሆነ እንመለከታለን የእርሱ ሞትና ደም እንደሆነ እናያለን፡፡ በዚህ ባደፈው እና በነውረኛው ማንነታችን ወደ እግዚአብሔር የምናልፈበት በራች እርሱ እንደሆነ እንመለከታለን ይህንን እራሱ ጌታ እንዲህ ሲል ተናግሮታል ፡- ‹‹እኔ መንገድና ሕይወት ነኝ›› ዮሐ 14÷4፡፡ ሌላም ምሳሌ ማየት እንችላለን በዮሐ 10÷9 ‹‹በሩ እኔ ነኝ››፡፡ ብዙ መጥቀስ ይቻላል ታዲያ ይህ እኛን ወደ እግዚአብሔር የጽድቅ መንገድ እንገባ ዘንድ በር የሆነን እርሱ እንድንደርስ ደግሞ መንገድ የሆነን እርሱ እንዳንሞትም ሕያው እንድንሆንም ያደረገን እርሱ ነው፡፡ መካከል ያለው፡፡
    ሌላ ምሳሌ፡- መካከል የሚለው ቃል በራሱ ፈራጅ የሚል መሆኑን እናውቅ ይሆንን፡፡ ዳኛ ፍትህን የሚያስፍን እውነተኛ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ሁለት ሰዎች ውል ቢኖራቸው በስራ ጉዳይ የሆለቱን ሰዎች የስራ ሂደት በየግላቸው እንዳያስኬዱት ማለትም ያም በራሱ መንገድ ይህም በራሱ መንገድ ስራውን እንዳያስኬድ አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ሁለቱም በጋራ ተስማምተው እንዲሰሩ የሚያደርጋቸው ይህ በሁለቱ መካከል ያለው የጋራ ውላቸው ነው፡፡ አንዱን አንዱ ባይስማማ በመካከል ያለው ውላቸው ፈራጅ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በውሉ መሰረት አንደኛው አንደኛውን ሊቀጣው ይችላል ማለት ነው፡፡

    ባልና ሚስት ሲጋቡ እንዲሁ ተስማምተው መኖር ቢችሉም ነገር ግን ይህ ዓይነቱ ዘለቄታዊ ዋስትና ስለሌለው የግድ በሁለቱ መካከል አስተማማኝ የሆነ ነገር ያስፈልጋል ስለዚህ ይህን የሚያደርጉት ወይም በመካከላቸው የሚያኖሩት የስምምነት ፊርማ ያስፈልጋል ታዲያ በሁለቱ መካከል የሚፈጠረውን ነገር የሚዳኘውና የሚፈርደው በመካከላቸው ያለው ያ የጋብቻ ውላቸው ነው፡፡ ውላቸው ለእነዚህ ሰዎች ምንድነው ቢባል መካከለኛ ፈዳጅ ዳኛ ነው ማለት ነው፡፡ ለዚህም የመጽሐፍ ክፍሎችን ማየት እንችላለን፡፡ ‹‹ዮናታንም ዳዊትን፦ በደኅና ሂድ እነሆ፥ እኛ ሁለታችን በእኔና በአንተ፥ በዘሬና በዘርህ መካከል ለዘላለም እግዚአብሔር ይሁን ብለን በእግዚአብሔር ስም ተማምለናል አለው። ዳዊትም ተነሥቶ ሄደ ዮናታንም ወደ ከተማ ገባ።›› 1ኛ ሳሙ 20÷42፡፡ ‹‹እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ይፍረድ፥ እግዚአብሔርም አንተን ይበቀልልኝ እጄ ግን በአንተ ላይ አትሆንም።›› 1ኛ ሳሙ 24÷12፡፡ ‹‹እንግዲህ እግዚአብሔር ዳኛ ይሁን፥ በእኔና በአንተም መካከል ይፍረድ፥ አይቶም ይምዋገትልኝ፥ ከእጅህም ያድነኝ።›› 1ኛ ሳሙ 24÷15 ፡፡ እንግዲህ ይህን ያህል ካልን በቂ ነው ብዬ አስባለሁኝ፡፡ ብዙ ማለትና ማከል ይቻላል በተለይም በቤተ ክርስቲያናችን ቅዱሳት መጽሐፍት ብንዳስሰው እጅግ በቂና የማያዳግም ምላሾችን እናገኛለን፡፡

    አንዳንድ ጊዜ መካከል ልዬነት የሚለውንም ለመግለጥ ይጠቅማል፡፡ ይህም ማለት ቦታውን ሁኔታውን ለማመላከት የሚጠቀሙበትም የአነጋገር ዘይቤ መሆኑን ከመጽሐፍ ቅዱስ መመልከት እንችላለን፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሔር ዓለማትን ሲፈጥር ‹‹እግዚአብሔርም፦ በውኆች መካከል ጠፈር ይሁን፥ በውኃና በውኃ መካከልም ይክፈል አለ።›› ዘፍ.1÷6፡፡ ሲል እንመለከታለን ይህ ማለት ታዲያ ቅድም ከላይ እንዳየነው በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን የሚያሳየን ነው፡፡ ታዲያ የእግዚአብሔርን መጠን የሌለው ቅድስናና የሰውን ልጆች መጠን የሌለውን እርኩሰት የሚያስቃኝ ሲሆን ይህን ልዩነት ለማጥበብ ያለው ብቸኛ መንገድ እርሱ ነው ማለት ነው፡፡ ማነው ቢሉ? ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ››

    6. ‹‹ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።›› ዕብ 7÷25

    የመጨረሻውና ብዙ ጊዜም በተከራካሬዎች ከሚጠቀሱ ጥቅሶች መካከል አንዱ ይህ ነው፡፡ እንግዲህ ምናልባት ይህን ጥቅስ ከመመልከታችን በፊት ከላይ በክፍል አንድ ንባብ ውስጥ በትንቢተ ኢሳያስ ላይ በምዕራፍ 53 ቁጥር 12 ላይ ያለውን ትንቢት ስንተነትን ይህን ቃል አብረን አያይዘን ተመልክተነዋል፡፡ ምናልባት ያንን ማየቱ በቂ ነው ብዬ አስባለሁኝ፡፡ ምክኒያቱም ይህ ትንቢታዊ ንባብ ነውና፡፡ ይኖራል ካለ ወደፊት ያለውን ነገር ነው የሚያሳየን፡፡ ነገር ግን እዚህ ላይ ያለው ሊያማልድ ይኖራል ሲል መቼ ነው ይህ የሚሆነው ወይም የሆነው የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀሪ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ጥቂት ነካክቶ ማለፉ የሚበጅ ይመስለኛል፡፡

    ስለ ማማለድ የሚጠቅሰው ወይም የሚነበበው ንባብን እስቱ ሙሉ ቃሉን ቃል በቃል እንውሰደ ‹‹ሊያማልድ›› በዚህ ቃል ውስጥ ያለችውን ‹‹ሊ›› የምትለዋን ፊደል እንውሰዳት እስቲ ተከራካሪዎች የሚያዋጣቸው ይህቺ ቃል በ‹‹ሲ›› በትቀየር ነበር ሊያማልድ የሚለውን ሲያማልድ ብላችሁ አንብቧቸው ስሜቱ ብቻ ሳይሆን መሰረታዊው አሳብ እራሱ ይለወጣል፡፡ ‹‹ሊያማልድ›› ካለ ትንቢት ነው ማለት ነው ‹‹ሲያማልድ›› ካለ ይህ ድርጊት አሁን እየተደረገ ነውና እውነት ነው ክርክራቸውም ውጤት አለው ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው መጸሐፍት ምስጢራት ላይ እንጂ ዘይቤያው አነጋገር ላይ ትኩረት ያማያደርጉት፡፡

    በሌላ በኩል ደግሞ ሊያማልድላቸው ያላቸው እነማን ናቸው የሚለውን ለመመልከት ይህን ንባብ ልብ ብለን እንይ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ካህናት ያወራ እንደነበር መጀመሪያ ልብ እንበል፡፡ ከመልከ ጼዲቅ ጀምሮ ስለነበረው ክህነት ያነሳና አማናዊ ካህን ስለሆነው ስለኢየሱስ የዘላዓለም የክህነት ስልጣን ለመናገር ሲል ይህን ብሎ እንደጻፈ ተመልከቱ፡፡ ሕዝቡን ከእግዚአብሔር ጋራ ሲያስታርቁና ሲማልዱ የነበሩት ካህናት እነ ሙሴ፤ እነ አሮን…. እንዳይኖሩ ሞት ከለከላቸው መልከ ጼዲቅንም ቢሆን ስለሕዝቡ መስዋዕትን እየሰው ማር ይቅር በል እያለ እንዳይኖር ሞተ ከለከለው ይላል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ነው እንግዲህ ታላቁ ምስጢር ይፋ የሚሆነው፡፡ ከላይ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ነበር፡- ‹‹አንተ እንደ መልከ ጼዲቅ ሹመት ለዘለዓለም ካህን ነህ፡›› ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘለዓለማዊ ክህነት እንዳለው ከጠቀሰ በኋላ በሞት እንዳማይረታ ለማስረዳት ሲል ይህን ቃል ተጠቀመ፡፡ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በስጋው ወራት ሕዝቡን ከራሱ ጋራ አስታረቀ የሚለውን አሳብ ያጠነክርልን ዘንድ ድርጊቱን በትንቢታዊ ዘይቤ አስቀመጠው፡፡ ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራል፡፡ ታዲያ ይህን ቃል ይዘው የሚሳሳቱ ሰዎች ችግር ምንድን ነው፡፡

    ኢሳያስ ላይ ያለው ቃል ‹‹ስለሕዝቡም ማለደ›› ብሎ ገና ያልተፈጸመውን ትንቢት አስቀመጠ ይህም ማለት ገና የሚሆን መሆኑን ሲያሳይ ነው፡፡ ከመጀመሪያው የስደት አደጋ እስከ ቀራኒዎ ተፈጸመ እስከምትለው ቃል ድረስ ያለውን የቤዛነት አገልግሎት በትንቢት ሲያትት ይህን አለ፡፡ በዚህም መሰረት ቅዱስ ጳውሎስ የጻፈውን መልዕክት በደረቁ ተመልክተው የሚጠቅሱ ሰዎች መኖራቸው የማይካድ ነው፡፡ ለምሳሌ ከላይ ያለውን ቃል ሙሉውን ወስደን ‹‹ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራል›› ካልን ሌላ ችግር መኖሩን ተመልከቱ ድርጊቱ ገና አልተፈጸመም ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት ሊሄድ ካለን ገና አልሄደም እየተዘጋጀ ነው ማለት ነው ግን ዘይቤው ሊሄድም ላይሄድም ይችላል ማለት ነው፡ ሲሄድ ካልን ደግሞ በቃ ሄዷል ማለት ነው ወይም መንገድ ላይ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህን እንዲህ ባለ መልኩ መረዳት የክርስቶስን አዳኝነት ገደል መክተት ነው ልክ እንደ ሙሐመዳውያን፡፡ በመሰረቱ ከአንድ ክርስቲያን ነኝ ባይ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ድኛለው ብሎ ከሚያምን ሰው እንዲህ ያለ አመለካከት አይጠበቅም፡፡ ምክኒያቱም የማዳኑንስራ የሆነውን ነገር ሁሉ ከገደል መክተት ነውና፡፡

    ሌላው ደግሞ ከዚህ ንባብ ጋራ ፍጹም ተቃርኖ የሚፈጥር ነገር እናያለን ይህን ንባብ ወስደው አማላጅ ነው ለሚሉ ሰዎች ዮሐንስ 16÷26 ‹‹በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ስለ እናንተ አብን እንድለምን የምላችሁ አይደለሁም፤›› እንግዲህ እንደመከራከሪያ የያዝነው ቃል ይህን ያህል ችግር ውስጥ ሊከተን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ሌላ መጥቀስ እንችላለን በሐዋሪያት ስራ ላይ የተጻፈውን ቃል ይህም የሚያወራው ‹‹ለሕዝብም እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ በእግዚአብሔር የተወሰነ እርሱ እንደ ሆነ እንመሰክር ዘንድ አዘዘን።›› ሐዋ 10÷42፡፡ እንግዲህ ምን እንላለን ይህን ቃል ይህን ያክል የሚያጋጨን ከሆነ የተረዳንበት አቋም ፍጹም መቀየር አለብን፡፡ እንዴት ቢሎ ከሞቱ በፊት የነበረውን እውነተኛና ዘለቄታዊነት ያለውን የቤዛነት ስራ ለመስራት ያደረገውን ተጋድሎና አንድ ጊዜ በእኛ እና በእርሱ መካከል ያለውን የጠብ ግድግዳ ማልዶ እንዳፈረስ ሲያስረዳ ነው፡፡ ‹‹አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው›› ብሎ

    እንግዲህ ከዚህ በኋላ ደግሞ ሊሆን የሚችለው ነገር ምንድን ነው ቢሉ እንደ ቃሉ መሰረት የስጋውን ወራት ሲጨርስ ሕዝቡንም በደሙ ነጻ ካወጣ በኋላ ወደ እግዚአብሔርም መንግስት ካስገባና ሲኦልን ከበዘበዘ በኋላ እንዲህ ብሎ ጌታ እራሱ እውነታውን በትንቢታዊ ዘይቤ ጠቅሶት ይህም መሆኑን ከላይ በገለጽናቸው ንባቦች ውስጥ መረዳት እንችላለን፡፡ ‹‹እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ፤ አሁንም፥ አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ።›› ዮሐ 17÷4-5፡፡ ስለዚህ በዚህ ንባብ መሰረት ወደ ቀደመ ክብሬ እመለሳለሁ እንደሚል ምንም ጥርጥር የለውም ይህም ደግሞ እውነት ነው ዳግመኛ ሊማልድ ሳይሆን በሕይወት የሞኖረው ሊፈርድ እና ሊገዛ ሊያስተዳድር ነው፡፡ ዳግም ሲመጣም ተሰቅሎ ሊገደልና ሊሞት ሳይሆን ሊፈርድ እንጂ የሚመጣው፡፡ እንዲያማ ካለን የእምነት መሰረታችን ሲጀምር ችግር አለበት ማለት ነው፡፡ ከላይ የተመለከተውን ጥቅስ ይዘው የሚከራከሩ ሰዎች ትልቁ ችግር ምንድን ነው?

    ችግር አንድ

    ማንኛውም ሰው አሁን በሚሰራው ኃጢያት እና በደለ ሁሌም በሚሰራው ርኩሰት ኢየሱስ ክርስቶስ ቁጭ ብድግ እያለ ስለዚህ ሰው ዘወትር ይቅርታን (ይማልዳል) ይለምናል ማለታቸው፡፡ ለዚህም ማጠናከሪያ ሐዋሪያው ቅዱስ ዮሐንስ የጠቀሰውን ቃል ማንሳታቸው ነው ቃሉም እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።›› 1ኛ ዮሐ 2÷1፡፡

    ይህ ንባብ ችግር እንዳለበትስ ስንቶቻችን ነን የምናውቀው በመጀመሪያ ደረጃ ጠበቃ ማለት በራሱ ትርጉሙ ምንድን ነው፡፡ ጠበቃ ተከራካሪ ነጻ አውጪ ተሟጋች ማለት ነው፡፡ ወዳጆች ጥብቅናና ምልጃ እንግዲህ ልዩነት አለው ማለት ነው፡፡ ምልጃ ማለት ከላይ ተመልክተነዋል እንግዲህ፡፡ ስለዚህ ይህ ክፍል የሚያሳየው ክርስቶስን አማላጅነት አይደለም ይህም ማለት ነጻ አውጪነት ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የማይከራከሩበት አቅ ነው፡፡ እንዴት ቢሉ ጌታ እኛን ለማዳን ያደረገው የዘመነ ስጋዌ ተጋድሎ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ ከጠላት ቀንበር ከጨለማው አለም እንዴት ባለው ሙግት ነጻ እንዳወጣን ልብ በሉ እንግዲህ፡፡

    በሌላ መልኩ ደግሞ ይህ ንባብ እንዲሁ ከተረዳነው እንግዲህ ሰውን ለአንድ ነገር ያበረታታል ኃጢያትን ላለመስራት ከመጠንቀቅ ይልቅ የፈቀደውን ነገር እንዲሆን ምክኒያቱም ጠበቃ አለኝ ብሎ ዘመኑን በኃጢያት እንዲጨርስ ብርታት ይሰጠዋል ማለት ነው፡፡ እውነታው ግን ይህ አይደለም፡፡ ስንበድል ስናጠፋ የሚያጽናናን መንፈስ ቅዱስ ዳግመኛም ወደ ኃጢያት እንዳንገባ መንፈስ ቅዱስ ያግዘናል ማለት ነው፡፡

    ችግር ሁለተኛ

    ቅዱሳት መጽሐፍትን ለመመሪያነት ሳይሆን በክርክር ውስጥ ለመጥቀስ ሲሉ መጠቀማቸው፡ ይህም የሚያሳየው አንዱ ላይ ያለውን እውነታ ሳይረዱ ሌላ የጥቅስ ናዳ መጨመርና ሰውን በመንፈስ ቅዱስ ትህዛዝ ሳይሆን በስጋዊ ጥበብና በቃላት ሽንገላ ለመመለስ መሞከራቸው፡፡ እውነታውን እንዳይረዱት አድርጓቸዋል ማለት ነው፡፡ ‹‹….ፊደል ይገድላል መንፈስ ግን ሕይወት ይሰጣል›› 2ኛቆሮ 3÷6፡፡

    እንግዲህ ብዙ ብንለ እንችላለን ነገር ግን ይህን ተከታታይ መልዕክት በንቃት የተከታተል ማንኛውም ሰው አሁን የራሱን ውሳኔ ለመወሰን የሚያውቀውን በሚገባ መመርመር ይኖርበታል ብዬ አስባለሁኝ ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታና አዳኝ እንጂ ማላጅ አይደለም ብዬ የዚህን መልዕክት አሳብ አጠቃልላለሁኝ፡፡ አምላካችን ለሁላችንም አስተዋይ መንፈስን ያድለን፡፡ አሜን አሜን አሜን

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top