ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው

ቤተ ክርስቲያን ስለ ክርስቶስ የምትመሰክራቸው እውነቶች

በኒቅያ የተሰበሰቡት አባቶቻችን በአርዮስ የቀረበላቸውን የስህተት ትምህርት ፊት ለፊት በእግዚአብሔር ቃል ሲቃወሙት በሌላ በኩል ደግሞ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን ተከትላ የምታስተምረውን ትምህርት በሚገባ መግለጥ ነበረባቸው። በሚቀጥሉት ክፍሎች የምናገኛቸው ሐረጎችና ቃላት አባቶቻችን መጽሐፍ
ቅዱስ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያስተምራቸው እውነቶች ጠቅለል አድርገው የገለጡበት ክፍል ነው። እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች በመያዝ ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ሁሉ አምላክነቱን አስተምራለች ዋጋም ከፍላበታለች።
1. በአንዱ ጌታ እናምናለን። (ወነአምን በአሐዱ እግዚእ፤)
መጽሐፍ ቅዱስ በሥጋ የተገለጠውን እግዚአብሔር ወልድን ከሚጠራበት ስሞች አንዱ ጌታ ብሎ ነው። ሃይማኖታቸው የቀና አባቶችም « በአንዱ ጌታ» ብለው ተናግረዋል። ጌትነቱን የምንናገረው በመንፈስ ቅዱስ ተመርተን ነው። « በመንፈስ ቅዱስም ካልሆነ በቀር ኢየሱስ ጌታ ነው ሊል አንድ እንኳ እንዳይችል
አስታውቃችኋለሁ። » (1 ቆሮንቶስ 12፥3) በአፋችን ጌትነቱን መናገራችን የደኅንነታችን ምክንያት ነው። « ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና » ሮሜ 10፥9። የአባቶችን ነገረ መለኮት በምዕራቡ ዓለም በማስተዋወቅ የተመሰገነው ቶማስ
ኦዴን እንዳሳሰበን ክርስቶስን በምድር ሲመላለስ ብቻ ጌታ ብንለው ኖሮ ምናልባትም አስተማሪ ወይም አለቃ መሆኑን ማስተዋወቂያ ነው። ነገር ግን ከትንሣኤ በኋላ ጌታ መባሉ በአሁኑ ዓለምም በሚመጣውም የእግዚአብሔር መንግሥት እርሱ ገዢ መሆኑን የሚያመለክት ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ
በበዓለ ሐምሳ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ « እናተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ።» በማለት የተናገረው። (ሐዋ ሥራ 2፥6 ) ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም በነገረ ጥምቀት ትምህርቱ እንዳለው « እርሱ ጌታ ነው፤ ጌትነቱም ደረጃ በደረጃ ያገኘው
ሳይሆን በባሕርዩ ጌታ በመሆኑ ያገኘው ክብር ነው።» ጌታ ኢየሱስ ስንል ምን ማለታችን ነው? በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ዘመን በተለይም በመጀመሪያዎቹ ሦስት መቶ ዓመታት ጌታ ኢየሱስ የሚለው ቃል ዋጋ የሚያስከፍል ቃል ነበር። ለሮም ግዛት (Roman Empire) በሰዎች ሥጋዊና መንፈሳዊ ሕይወት ጌታ የነበረው ቄሣር ነበር። በመሆኑም ቄሣር ይሰገድለት ይመለክ ነበር።
በብሉይ ኪዳን የሰብአ ሊቃናትን ትርጕም (ሰብትዋጀንት) ከተከተልን ከስድስት ሺ ጊዜ በላይ ያህዌ የሚለውን የእብራይስጥ ቃል « ጌታ» ተብሎ ተተርጉሞአል። ስለሆነም ጌታ ኢየሱስ ማለት ከቄሣር ተቃራኒ አድርጎ የሚያስቆም « ፓለቲካዊ አቋም» ብቻ ሳይሆን፥ ይህ ኢየሱስ በብሉይ ኪዳን ሙሴን የተናገረው « እኔ ነኝ »
ያለውና ነቢያቱን የላከው መሆኑን ነው። ይህ « እኔ ነኝ » ማለት አቻ ወይም ተቃራኒ አልባ ብቸኛ አምላክ ማለት ነው።በጥንት አማርኛ የተጻፈው የቤተ ክርስቲያናችን ጸሎተ ሃይማኖት ትርጓሜ ስለዚህ ቃል ሲናገር «በሐንድ ጌታ ምን አሰኛቸው፥ ሌላ ጌታ አለን ያሉ እንደሆን። ጌታስ መኰንንም፥ ካበላ ካጠጣ ጌታ ይልዋል።
እርሱ ግን አጋዙን ቀድሞም ከሰው ያላመፃው፥ ኋላም ለሰው ያያሳልፈው፥ በባሕርዩ በጠባይዕ ገዢ በሐንድ አምላክ ነአምናለን አሉ።» ይለናል።
ኢየሱስ ክርስቶስ
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በሥጋ የተገለጠው ቃል የተጠራባቸው ብዙ መጠሪያዎች ቢኖሩም በዋናነት የሚታወቁት ሁለቱ ናቸው፤ እነርሱም ኢየሱስና ክርስቶስ የሚሉት ስሞች ናቸው። ኢየሱስና ክርስቶስ የሚሉት ስሞች ያላቸውን የነገረ መለኮት አንድምታዎች በሚገባ በመተንተን ከጻፉ ቀደምት ጸሐፊዎች
መካከል « የቤተ ክርስቲያን ታሪክ አባት» (the father of church history) ተብሎ የሚታወቀው አውሳብዮስ ዘቂሳርያ ዋናው ነው። አውሳብዮስ ስለ ጌታ ስሞች ሲያብራራ የሚከተሉትን ዋና ዋና ነገሮች ይነግረናል። አንደኛው ኢየሱስ እና ክርስቶስ የሚለው ስም ከጥንት ጀምሮ በነቢያት የተነገሩና በመላእክት
የተበሠሩ ስሞች ናቸው። ሁለተኛው እነዚህ ስሞች የጌታን አምላክነት የሚያሳዩ ናቸው ሦስተኛው እነዚህ ስሞች የጌታን አዳኝነት የሚያመለክቱ ናቸው። ለዚህ ዋና ምሳሌ አድርጎ የሚያነሣልን ሙሴን ነው። ሙሴ እስራኤልን በመሪነት ሲያስተዳድር ከእግዚአብሔር በተቀበለው ትእዛዝ መሠረት ከሾማቸው የአገልግሎት
ሹመቶች መካከል ዋና የሚባሉት ሁለት እንደሆኑ ይጠቅስልናል፤ እነዚህም ሊቀ ካህናቱን አሮንንና ራሱን ሙሴን የተካውን ኢያሱን የሾመበት ነው። አውሳብዮስ እንደሚለን « « በተራራ ላይ እንዳሳየሁህ ምሳሌ እንድትሠራ ተጠንቀቅ» በማለት እንዳዘዘው ቃል የሰማያዊ ነገሮችን አምሳልና ምልክቶች፥
በመጠቀም ክርስቶስ የሚለውን ስም የተለየ ታላቅነት እና ክብር ያለው ስም እንደሆነ እንዲታወቅ በማድረግ የመጀመሪያው ሙሴ ነው። (ዘፀአት 25፥40)ከሰዎች ሁሉ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን ሊቀ ካህን በገለጠበት ወቅት ” ክርስቶስ” ወይም ” የተቀባ” ብሎ ጠርቶታል። በእርሱ እይታ ከሰዎች ሁሉ ክብር ከፍ
ባለው በዚህ የሊቀ ካህንነቱ አገልግሎት ሊቀ ካህኑ የክብርና የከፍታ ምልክት ይሆንለት ዘንድ ክርስቶስ የሚለውን ስም ሰጥቶታል። (ሌዋውያን 4፥5፡16፤ 6፥22) » ለኢያሱ ሲነግረንም፥ ራሱ « ኢያሱ» የሚለው ስም ኢየሱስ ከሚለው ስም ጋር እንዴት ዓይነት ግንኙነት እንዳለው ሲነግረን ኢያሱ « ወላጆቹ ባወጡለት በሌላ ስም አውሴ በመባል ነበር የሚታወቀው። ሙሴ ግን ከነገሥታት ዘውድ የሚበልጠውን፥ ገንዘብ የማይገዛውን እጅግ ክቡር የሆነውን ስም ሊሰጠው ኢየሱስ (ኢያሱ) ብሎ ጠራው።ከሙሴ በኋላና አምሳላዊው አምልኮ ለሰዎች ሁሉ በሙሴ በኩል ተሰጥቶ ከተፈጸመ በኋላ በእውነተኛው ንጹሕ በሆነው እምነት ላይ በመሪነት የተቀመጠው የነዌ ልጅ ኢያሱም የአዳኛችንን ምሳሌ ተሸክሞ ነበር። » ይህ የአውሳብዮስ ትንተና መልክአ ኢየሱስን በጻፈው የቤተ ክርስቲያናችን ደራሲ በግልጥ ተቀምጦአል
« አክሊለ ስምከ እንዘ ይትቄጸል በርእሱ፤ 
« አኅጉረ ፀር ወረሰ ኢያሱ፤»
የስምህን አክሊል በራሱ ላይ አድርጎ
የጠላትን ሀገሮች ኢያሱ ወርሶአል።
ኢየሱስ የሚለው ስሙ
ይህ የአውሳብዮስም ሆነ የመልክአ ኢየሱስ ደራሲ ትንተና የሚያሳየን ኢየሱስ የሚለው ስም የእግዚአብሔር ሕዝብን ከማዳን ጋር የተገናኘ ስም መሆኑን የሚያመለክት ነው። ምክንያቱም በእብራይስጥ የሹኣ፥ ኢያሱ ወይም ኢየሱስ የሚለው ስም በእብራይስጡ « ያሕዌ መድኃኒት ነው» የሚል ትርጉም አለው። ማቴዎስ ወንጌሉን በተለይ ለአይሁድ የጻፈ እንደመሆኑ፥ በአይሁድ ዘንድ ተስፋ የተነገረለትን የዚህን ስም ትርጉም በመልአክ እንደተነገረው በጽሑፍ አስፍሮታል። የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ሲነግረው « ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። » ነበር ያለው። ማቴዎስ 1፥21። አውሳብዮስም ሆነ ከእርሱ በኋላ የተነሡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከዚህ የመልአኩ ቃል ያስተዋሉት፤ (ወንጌላዊውም ጭምር ማለት እንችላለን) የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ የነገረው ስም የእግዚአብሔር ስም መሆኑን ነው። እርግጥ ነው፥ በትንቢት፥ በምሳሌና በጥላ ቀድሞ ለተነሡት « አዳኞች» ኢያሱዎች ተሰጥቶአል። (ለምሳሌ ዘካርያስ 3፥1 ላይ የተጠቀሰውን ከምርኮ በኋላ እስራኤልን የመራው ሊቀ ካህናቱን ኢያሱን ያስታውሷል።) ሆኖም ግን እነዚህ « አዳኞች» ያዳኑት የእግዚአብሔርን ሕዝብ ነው። ያዳኑትም የእግዚአብሔርን ኃይል እና ረድኤት አጋዥ በማድረግ ነው። ይህን የእግዚአብሔር ሕዝብ ያዳኑት ወይም የታደጉት ከምድራዊ ጠላቶቻቸው ስለሆነ ማዳናቸው ውሱን ነው። አማናዊው ኢያሱ አዳኛችን ግን ያዳነው « ሕዝቡን» ነው። የራሱን ሕዝብ ነው። ያዳነውም እግዚአብሔር ተጠቅሞበት ሳይሆን ራሱ እግዚአብሔር ስለሆነ መድኃኒት ሆኖ ነው። ሕዝቡን ያዳነውም « ከኃጢአታቸው» ነው። ይህ አነጋገር የሚገባው ለእግዚአብሔር ብቻ ነው። በመሆኑም እንደበፊቱ እግዚአብሔር በምሳሌና በጥላ ሳይሆን ራሱ በመካከላችን በማደሩ « አማኑኤል እግዚአብሔር ከእኛ ጋር » እንደ ሆነና በዚህም የነቢዩ የኢሳይያስ ትንቢት ፍጻሜ እንዳገኘ ነበር የእግዚአብሔር መልአክ የገለጠው። ማቴዎስ 1፥23። ቅዱስ ጴጥሮም በመንፈስ ቅዱስ ተመልቶ ስለዚህ ሲናገር « መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና፤» ሐዋ 4፥12። ሉቃስም ልደቱን ለእረኞች ሲያበስር ይህን የአዳኝነቱን ስም ነበር የነገራቸው « ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና» ሉቃስ 2፥11።
ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ማዳኑ የአምላክነቱ መገለጫ ነው። ከዚህ በፊት እንዳየነው፥ በማርቆስ 2፥3-12 ላይ ሽባውን ሰው በፈወሰው ወቅት በመጀመሪያ ለዚያ ሰውነቱ በሕመም ለተጠቃው ሰው ያለው « ኃጢአትህ ተሠረየለችልህ» ነበር፤ በዚህ ወቅት በዚያ የነበሩት ጻፎች ያሉት ነገር ቢኖር « ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአት ሊያስተሠርይ ማን ይችላል?» የሚል ነበር። ጻፎቹ ስለ እግዚአብሔር ያሰቡት አሳብ ትክክል ነበር፤ የተሳሳቱት ነገር ቢኖር የሚያዩት ራሱ በሥጋ የተገለጠውን እግዚአብሔርን መሆኑን አለማወቃቸው ነው።
ኃጢአትን ይቅር የሚል አዳኝ ጌታ በሥጋ ተገልጦአልና።
የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ለዚህ ኢየሱስ ለሚለው ስም ታላቅ ክብር ነው የነበራት፤ ለምሳሌ በበዓለ ሃምሳ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ስብከቱን የደመደመው «እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ።» በማለት ነበር ስብከቱን የሰሙ ሦስት ሺ ሰዎች በሰሙት ነገር ልባቸው ተነክቶ « ምን እናድርግ? » ብለው በጠየቁ ወቅት፥ « ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ። » ነበር ያላቸው፤ (ሐዋ ሥራ 2፥3-38) ኢየሱስ የሚለው ስም የቤተ ክርስቲያን የስብከትዋና የአምልኮዋ ማዕከል እንደሆነ በዚህ የሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ስብከትና ምላሽ እናያለን። ገና ከመነሻው የአይሁድ ሊቃውንት ለሐዋርያት የነገሩዋቸው « በኢየሱስ ስም ፈጽመው እንዳይናገሩና እንዳያስተምሩ ነው።»( ሐዋ 4፥18) ሐዋርያት ግን ለዚህ አልታዘዙም ነበር።ከዚያ ይልቅ ስለ ስሙ መከራን መቀበልን ነበር የመረጡት። ሉቃስ ስለዚህ ሲነግረን «ሐዋርያትንም ወደ እነርሱ ጠርተው ገረፉአቸው፥ በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቱአቸው። እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለ ተቈጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ፤» ሐዋ ሥራ 5፥40-41። ይህ ኢየሱስ የሚለው ስም የቤተ ክርስቲያን የጸሎትዋ ቁልፍ ቃል ነው። ራሱ ጌታ « ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ። » በማለት እንደተናገረው (ዮሐንስ 14፥14) ቤተ ክርስቲያን የጸሎትዋ መደምደሚያ ኢየሱስ የሚለው ስም ነው። « በአሐዱ ወልድከ በአንድ ልጅህ» የሚለው ቃል የቤተ ክርስቲያናችን የተለመደው የጸሎት
መደምደሚያ ነው። ቅዱስ እስጢፋኖስ በድንጋይ እየተደበደበ የጠራው ይህን ታላቅ ስም ነበር፤ « ጌታ ኢየሱስ ሆይ ነፍሴን ተቀበል ብሎ ሲጠራ ይወግሩት ነበር፤» ( ሐዋ ሥራ 7፥59) ኢየሱስ የሚለው ስም የፈውስ ስም መሆኑን ቤተ ክርስቲያን የተገነዘበችው ገና ከመጀመሪያው ነው። አርባ ዘመን ሽባ ሆኖ የኖረውን ሰው ጴጥሮስ ያለው « ብርና ወርቅ የለኝም፤ ይህን ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ » (ሐዋ ሥራ 3፥ 6፤) ኢየሱስ የሚለውን ስም ዲያብሎስ እጅግ አጥብቆ የሚፈራው ስም ነው፤ ሉቃስ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስለተደረገው አስደናቂ ተአምራት ሲናገር እንዲህ ይለናል፤
« እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት ያደርግ ነበር፤ ስለዚህም ከአካሉ ጨርቅ ወይም ልብስ ወደ ድውዮች ይወስዱ ነበር፥ ደዌያቸውም ይለቃቸው ነበር ክፉዎች መናፍስትም ይወጡ ነበር። አጋንንትንም እያወጡ ይዞሩ ከነበሩት አይሁድ አንዳንዶች። ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ እናምላችኋለን እያሉ ክፉዎች መናፍስት ባሉባቸው ላይ የጌታን የኢየሱስን ስም ይጠሩባቸው ዘንድ ሞከሩ። የካህናትም አለቃ ለሆነ አስቄዋ ለሚሉት ለአንድ አይሁዳዊ ይህን ያደረጉ ሰባት ልጆች ነበሩት።ክፉው መንፈስ ግን መልሶ፦ ኢየሱስንስ አውቀዋለሁ ጳውሎስንም አውቀዋለሁ፤ እናንተሳ እነማን ናችሁ? አላቸው።» ሐዋ 19፥ 11-15።
ክርስቶስ የሚለው ስሙ
ክርስቶስ ወይም መሲህ የሚለው ስም በሰባ ሊቃናቱ የብሉይ ኪዳን ትርጉም (ሰብቱዋጀንት) ከ45 ጊዜ በላይ ተጠርቶ እናገኛለን። በብሉይ ኪዳኑ ትርጉም ክርስቶስ ወይም መሲህ ማለት ለተለየ አገልግሎት በእግዚአብሔር የተቀባ ወይም የተሾመ ማለት ነው። ቅብዓቱ እግዚአብሔር የመረጠውና የጠራው ለመሆኑ ምልክት ነው። በመሆኑም በብሉይ ኪዳን ሦስቱ አገልግሎቶች ማለትም ካህንነት፥ ንግሥና እና ትንቢት በቅብዓት ለተለያዩ ሰዎች የሚሰጥ ነበር። ቀደም ሲል የጠቀስነው አውሳብዮስ ዘቂሳርያ እንዲሁም ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌምና ከእነርሱም በኋላ የተነሱ አባቶች እንደሚነግሩን እነዚህ ሦስቱ አገልግሎቶች በብሉይ ኪዳን የተሰጠቱ በምሳሌና በጥላ ሲሆን፥ በአዲስ ኪዳን ግን ሦስቱም በአንዱ በክርስቶስ በምልዓት ተገኝተዋል። እነዚህ ሦስቱ አገልግሎቶች ለምን አስፈለጉ? ክርስቶስስ እነዚህን አገልግሎቶች እንዴት ፈጸመ? በብሉይ ኪዳን ከምንመለከታቸው ዋና አገልግሎቶች አንዱ የትንቢት አገልግሎት ነው። ነቢይ ማለት በሕዝቡ ፊት የእግዚአብሔር አፍ ነው። እግዚአብሔር ነቢያትን በየጊዜው እያስነሣ መልእክቱን ለሰዎች እንዲናገሩ ሲያደርግ እናያለን። ይህ ዓይነቱ አገልግሎት ለምን አስፈለገ ብለን ስንጠይቅ ኃጢአት በሰዎች ላይ ካመጣቸው ጉዳቶች አንዱ ሰዎች « አእምሮአቸው እንዲጨልምና የእግዚአብሔርን እውነት በትክክል አንዳይመለከቱ፥ እና እውነተኛውን እና ትክክለኛውን በማስተዋል ክፉውንና ደጉን መለየት እንዳይችሉ» ማድረጉ ነው። በመሆኑም ነቢያት የእግዚአብሔርን እውነት በጨለማው ዓለም ላይ ለሰዎች የሚገልጡ የእግዚአብሔር መልእክተኞች ናቸው። በቤተ ክርስቲያናችን ሙሴ ሊቀ ነቢያት ወይም የነቢያት አለቃ በመባል ይታወቃል ። ሙሴ ራሱ ለእስራኤላውያን ስለሚመጣው የነቢያት ነቢይ ሲናገር « እግዚአብሔር ከአንተ መካከል ከወንድሞችህ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣልሃል እርሱንም ታደምጣለህ» ብሎአል።(ዘዳግም 18፥15 ) ጴጥሮስም በኢየሩሳሌም ለነበሩት ሕዝቦች እንደሰበከው ያ « ከወንድሞችህ እንደኔ ያለ ነቢይ ያስነሣልሃል» የተባለለት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ሐዋ ሥራ 3፥22) የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የነቢይነት አገልግሎት መዳን የሚገኝበትን የእግዚአብሔርን እውነትና፥ ለሰው ልጆች ያዘጋጀውን የመዳን እቅድ መግለጥ ወደዚህም መዳን ሰዎችን ሁሉ መጥራት ነው። ራሱ እግዚአብሔር ስለሆነ እንደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርን በምልዓት የገለጠው ማንም የለም። ዮሐንስ 1፥18፥ እግዚአብሔርን የገለጠው ደግሞ በእውነትና በጸጋ ነው። ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለዚህ የነቢይነት አገልግሎቱ በናዝሬት ምኩራብ ባነበበው የኢሳይያስ ምንባብ ላይ በግልጥ አስቀምጦታል። ይኸውም ለድሆች ወንጌልን ይሰብክ ዘንድ መቀባቱን ነው። (ሉቃስ 4፥21)ሆኖም እዚህ ላይ ልናስተውል የሚገባን ከእግዚአብሔር ተልከው የቀደሙት ነቢያት የእግዚአብሔር መልእክተኞች ናቸው እርሱ ግን ራሱ መልእክት ነው። የቀደሙት ነቢያት የመጡት እግዚአብሔር እንዲህ ይላል እያሉ ነው እርሱ ግን የመጣው « እኔ ግን እላችኋለሁ» በማለት ነው። ( ማቴዎስ 5፥22) ምክንያቱም ራሱ የእግዚአብሔር መገለጥ የእግዚአብሔር ክብር እና እውነት ነው።
ሁለተኛው በብሉይ ኪዳን የምናገኘው አገልግሎት የክህነት አገልግሎት ነው። ካህን ማለት ስለ ሕዝቡ የሚቆም ማለት ነው። ካህኑ በእግዚአብሔር ፊት የሚቆመው ከእግዚአብሔር ስለ ሕዝቡ ይቅርታ ለመጠየቅ ነው። ኃጢአታቸውን ለማስተሥረይ ( ለመክደን) ጸሎት፥ መባና መሥዋዕት ያቀርባል። ይህ አገልግሎት ለምን አስፈለገ በምንልበት ወቅት አሁንም የምንመለሰው ኃጢአት ወደ ዓለም በገባ ወቅት ወዳስከተለው ነገር ነው። የኃጢአት ጉዳት ሰዎች እውነትን እንዳይረዱ፥ ወይም ደግንና ክፉን መምረጥ እንዳይችሉ አእምሮአቸውን ማደብዘዝ ብቻ ሳይሆን፥ በኃጢአት ውስጥ በመውደቅ ጥፋተኛ እንዲሆኑ ማድረግ ነበር።
ይህ የኃጢአተኝነትና የጥፋተኝነት ሕይወት ያስከተለው ነገር ቢኖር ሰው ከእግዚአብሔር እንዲለይ ነበር፤ ኢሳይያስ ስለዚህ ሲናገር « በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለይታለች፥ እንዳይሰማም ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል።» ብሎአል። ኢሳይያስ 59፥1፤ በሌላም ሥፍራ « ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም አሳቡን ይተው ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ እርሱም ይምረዋል፥ ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ።

አሳቤ እንደ አሳባችሁ መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለምና ይላል እግዚአብሔር፦ ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው።(ኢሳይያስ 55፥7-9።) በመሆኑም በብሉይ ኪዳን ይህን በእግዚአብሔርና በሕዝቡ መካከል ያለውን የኃጢአት ግድግዳ ለማፍረስ የእንስሳት መሥዋዕት ይቀርብ ነበር። ነገር ግን ይህ የብሉይ ኪዳኑ መሥዋዕት በሦስት መንገዶች ፍጹም የሆነ የኃጢአት ሥርየት ሊያመጡ አልቻሉም። አንደኛ ሊቀ ካህኑ ራሱ በኃጢአት ተጽእኖ ሥር ያለ ስለሆነ፥ አስቀድሞ ስለ ራሱ መሥዋዕት የሚያቀርብ፥ አገልግሎቱም በሞት የሚገደብ፥ ወይም ሞት የሚሽረው ነው ነው። ሁለተኛ መሥዋዕቶቹ ፍጹማን አይደሉም፤ ከሰው ወገን የሚቀርቡ እንጂ ከእግዚአብሔር በኩል የተዘጋጁ ስላይደሉ፥ መሥዋዕቶቹ ሥጋን ብቻ የሚቀድሱ ነበሩ። ሦስተኛ ልክ እንደ ካህኑ መሥዋዕቶቹም ሞት የሚገድባቸው ስለሆኑ ሊቀ ካህኑ በየዓመቱ ደሙን ይዞ ወደቅድስተ ቅዱሳኑ መግባት ነበረበት።
ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት ሆኖ እንደመጣ ቅዱሳት መጻሕፍት በግልጥ ይነግሩናል። ስለ ሊቀ ካህንነቱ በምልዓት በተነገረበት በዕብራውያን መልእክት ላይ እነዚህን ከላይ ያየናቸውን ሦስት የብሉይ ኪዳን መሥዋዕቶች ጉድለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት እንዴት ወደፍጻሜ እንዳመጣው ይነግረናል።
አንደኛው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደመልከ ጼዴቅ ባለ ሹመት የዘላለም ሊቀ ካህናት ነው። የእርሱ ሹመት እንደ መልከጼዴቅ የሆነበትን ምክንያት የዕብራውያን ጸሐፊ ሲናገር « እንግዲህ ሕዝቡ በሌዊ ክህነት የተመሠረተን ሕግ ተቀብለዋልና በዚያ ክህነት ፍጹምነት የተገኘ ቢሆን እንደ አሮን ሹምት የማይቆጠር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ግን የሆነ ሌላ ካህን ሊነሣ ወደ ፊት ስለምን ያስፈልጋል? ክህነታቸው ታልፍ ዘንድ አላትና፤ ክህነታቸው ካለፈችም ኦሪታቸው ታልፋለች. . . ስለዚህ የምትደክም የማትጠቅምም ስለሆነች የቀደመችው ትእዛዝ ተሽራለች። ኦሪት ምንም ግዳጅ አልፈጸመችምና፤ ነገር ግን በእርስዋ ፈንታ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት ከእርስዋ የሚሻል ተስፋ ገብቶአል እርሱ ያለ መሐላ አልሆነም፤ ያለ መሐላ የተሾሙ ካህናት አሉና። በመሐላ የሾመውን ግን « እግዚአብሔር ማለ፥ አይጸጸትምም፤ አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት የዘልዓለም ካህን ነህ» አለው። ኢየሱስ ይህን ያህል በምትበልጥና ከፍ ባለች ሹመት ተሾመ ለእነዚያ ብዙዎች ካህናት ነበሩአቸው ሞት ይሽራቸው፥ እንዲኖሩም አያሰናብታቸውም ነበርና። እርሱ ግን ለዘለዓለም ይኖራል፤ ክህነቱ አይሻርምና። ዘወትር በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡትን ሊያድናቸው ይቻለዋል ለዘለዓለምም ሕያው ነውና ያስታርቃቸዋል። » ዕብራውያን 7፥11-25

ሁለተኛው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ንጹሕ መሥዋዕት ሆኖ ራሱን ለዘላለም ያቀረበ ነው። « ቅዱስና ያለ ተንኰል፥ ነውርም የሌለበት፥ ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ፥ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባናል። እርሱም እነደ እንደ እነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና።» ዕብራውያን 7፥11-25

 

ሦስተኛው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹምና ሰማያዊ መሥዋዕት ስለሆነ በእግዚአብሔር ፊት የኃጢአት ይቅርታን አሰጥቶናል። « ክርስቶስ ግን ለምትመጣይቱ መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፥ የሰው እጅ ወደ አልሠራት፥ በዚህ ዓለም ወደ አልሆነችው ከፊተኛይቱ ወደምትበልጠውና ወደምትሻለው ድንኳን የዘለዓለም መድኃኒትን ገንዘብ አድርጎ፥ በገዛ ደሙ አንድ ጊዜ ወደ መቅደስ ገባ እንጂ በላምና በፍየል ደም አይደለም፤» ካለ በኋላ « ስለዚህ ኢየሱስ ሞትን ተቀብሎ በቀደመው ሥርዓት ስተው የነበሩትን ያድናቸው ዘንድ ወደ ዘለዓለም ርስቱም የጠራቸው ተስፋውን ያገኙ ዘንድ ለአዲሲቱ ኪዳን መካከለኛ ሆነ፤» ዕብራውያን 9፥11-15 ይህን የሊቀ ካህንነቱን ሥራ እንዴት አድርጎ በመስቀል ላይ እንደፈጸመ ሞትን በምንናገርበት ወቅት እናመጣዋለን።

ሦስተኛው በብሉይ ኪዳን የምናገኘው አገልግሎት የንግሥና አገልግሎት ነው። ለንግሥና እግዚአብሔር የሚመርጣቸው ሰዎች በነቢያት ይቀቡ ነበር። ይህ አገልግሎት ያስፈለገውም ልክ እንደሌሎቹ አገልግሎቶች ኃጢአት የእግዚአብሔር ሕዝብን ባሪያ አድርጎት ስለነበር፤ በኃጢአት ተመርተው በምድራዊ ነገር ባሪያ ካደረጉት ነጻ ለማውጣት እግዚአብሔር ነገሥታቱን ያስነሣ ነበር። ሆኖም እነዚህ ነገሥታት ራሳቸው በኃጢአት ተጽእኖ ሥር ስለሚሆኑ አንዳንድ ጊዜ ነጻ አወጣዋለሁ ያሉት ሕዝብ ለሌላ አደጋ ያጋልጡ ነበር፤ ሕዝባቸውንም ነጻ የማውጣታቸው ነገር በምድራዊ ነገር ብቻ የተወሰነ ነው።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ተብሎ በብዙ ቦታ ተጠርቷል። ይህም ያለ ምክንያት አይደለም። አውሳብዮስ ዘቂሣርያ ስለዚህ ሲናገር ጌታ በተወለደበት ጊዜ ንግሥና ከአይሁድ የተወሰደበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በአይሁድ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አይሁዳዊ ያይደለ ሰው (ሄሮድስ) የአይሁድ ንጉሥ ተብሎ የተጠራበት ሊቀ ካህንነቱም የአገልግሎት ሹመት የሆነበትና ትንቢት በሙሉ የተቋረጠበት ጊዜ ነበር። በመሆኑም እስራኤልን ከምድራዊ ባርነት ብቻ ሳይሆን ከመንፈሳዊ ባርነት ነጻ የሚያወጣ ለዳዊት የተሰጠውን የተስፋ ቃል የሚፈጽም ንጉሥ እንደሚነሣ ሕዝቡ ይጠብቅ ነበር፤ ሰብአ ሰገልና የእነርሱን ዜና የሰሙ ጸሐፍት በአንድነት የተነጋገሩት ስለሚወለደው « የአይሁድ ንጉሥ» ነበር።( ማቴዎስ 2፥1። )
የእግዚአብሔር መልአክ ለቅድስት ድንግል ማርያም ሲያበሥራት « እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።» ነበር ያላት( ሉቃስ 1፥32፡33)
ጌታ በንጉሥነቱ ምን አድርጎአል ብለን ስንጠይቅ፥ ለዘመናት የሰው ልጆችን ባሪያ አድርጎ የነበረውን ሞትን ድል አድርጎአል። (1ኛ ቆሮንቶስ 15) ሁለተኛ በባርነት በዲያብሎስ ተይዘው የነበሩትን ነጻ አውጥቶአል። (ዕብራውያን 2፥10-18፤ እነዚህን የተዋጁትንና ነጻ የወጡትን ወደ አባቱ መንግሥት አፍልሶአቸዋል።
« እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን።» ቆላስይስ 1፥13። ይህ በሞቱና በትንሣኤው የሆነውን የንጉሥነቱን ሥራ ወደፊት ትንሣኤውን በምናይበት ወቅት በሰፊው እንመለከታለን ።
እንግዲህ እነዚህ ሦስቱ አገልግሎቶች ሳይነጣጠሉ በክርስቶስ የማዳን ሥራ ውስጥ ታይተዋል ። ክርስቶስ የሚለው ስሙ የሚያመለክተውም ይህን ነው። እዚህ ላይ የዛሬውን ትምህርታችንን አንድ ኦርቶዶክሳዊ ሊቅ በተናገሩት ለምን አንደመድመውም፤ « የወደቀው ሰው እውነትን በመማርና ለአእምሮ አብርሆትን በማግኘት ካልሆነ በስተቀር ራሱን ፍጹም ያድርግ ዘንድ በፍጹም አልቻለም። ኃጢአታችንን ከፍ ከፍ አድርጎ በመስቀል ላይ የሚጠርቅና እኛን የሚቀድስ ራሱን በመስቀል ላይ መሥዋዕት የሚያደርግ ሊቀ ካህናት ያስፈልግ ነበር። ይህ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር አንድያ ልጁ « ስለ ኃጢአታችን የሞተው» ክርስቶስ ነው። . . . ይህ በክርስቶስ ሞት ቤዛነትን ያገኘው ሰው ሥልጣን ያለው ንጉሣዊ ቤዛ ያስፈልገው ነበር። . . .
ሰው የሆነው አምላክ ትህትና በመስቀል ላይ ተፈጸመ ባለው ቃል ተደመደመ፤ በመስቀሉ ላይ ድል አድራጊነቱና ንጉሣዊው ሥልጣኑ አበራ፤ ክርስቶስ ወደሲኦል ወረደ፤ የሲኦልን ደጆች ሰባበረ፤ የሲኦልን መንግሥትና የሞትን ግዛት በታተነ፤ ለዘመናት በሞት ተዘግተው የነበሩትን አስነሣ፤ ከሙታን ሲነሣ ሁሉን ቻይ የሕይወትና የሞት ጌታ ሆኖ ተነሣ። « የሕይወት ባለቤት በሙስና መቃብር መያዝ አይችልምና። ከሙታን ተነሥቶም ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ አለ። ( ማቴዎስ 28፥18) ወደ ሰማይ አረገ፤ እውነተኛ ንጉሥ ሆኖ በሰማይ ድል አድራጊ በምድር ደግሞ ተዋጊ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያንን እየመራ በአባቱ ቀኝ ተቀምጦአል። በሕያዋንና በሙታን ላይ ለመፍረድ ዳግም ሲመጣ የሰው ልጆች ሁሉ የንጉሥነቱን ሥልጣን ያውቃሉ።

«እውነተኛው የበጎች በር እኔ ነኝ፤» ዮሐ ፲፥፱።

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእርሱን ማንነት ገልጦ ያስተማረበት ትምህርት ነው። በዚህም ትምህርቱ፥ እርሱ የበጎች እረኛ እንደሆነ፥ የበረቱም በር እርሱ መሆኑን ተናግሯል። እውነት የባህርይ ገንዘቡ ስለሆነም፥ ትምህርቱን «እውነት እውነት እላችኋለሁ፤» በማለት ጀምሯል። በዚህም አማናዊ በሆነ ትምህርቱ «ወደ በጎች በረት በበሩ የማይገባ፥ በሌላም በኲል የሚገባ ሌባ፣ ወንበዴም ነው፤» ብሏል። ይኽንንም ስለ ሦስት ነገር ተናግሮታል።
፩ኛ፦ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ዕውር ሆኖ የተወለደውን ብላቴና በምራቁ ጭቃ አድርጐ፥ በሰሊሆም ጠበልም እንዲጠመቅ በማድረግ ፈጽሞ ስለፈወሰው፥ አይሁድ ብላቴናውንም ወላጆቹንም አስቸግረዋቸው ነበር። ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ፦ «ይህ ሰው (ኢየሱስ) ከእግዚአብሔር አይደለም፥ ሰንበትንም አይከብርምና፤» እያሉ ብላቴናውን ተከራክረውታል። እርሱ ግን፦ «ኃጢአተኛ ሰው እንዲህ ያለ ተአምራት ማድረግ (በደረቅ ግንባር ላይ ዓይን መፍጠር) እንዴት ይችላል? . . . እርሱ ነቢይ ነው፤» አላቸው። ይኸውም፦ የነቢያት አለቃ ሙሴ፥ ከእግዚአብሔር አግኝቶ፥ «እግዚአብሔር ከወንድሞቻችሁ መካከል (ከእናንተ ወገን) እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣላችኋልና እርሱን ስሙት፤» በማለት ለእስራኤል ዘሥጋ የነገራቸው ቃለ ትንቢት ነው። የሐዋ ፯፥፴፯። ምክንያቱም በብዙ መንገድ ሙሴ ለኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነውና። የነቢያት አምላካቸው ኢየሱስ ክርስቶስ «ነቢይ» መባሉም ነቢያት በአንድም ሆነ በሌላ ምሳሌዎቹ በመሆናቸው ነው።
የብላቴናው ወላጆች ደግሞ አይሁድ ወጥረው በጠየቋቸው ጊዜ፥ «ይህ ልጃችን እንደሆነ፥ እውር ሆኖም እንደተወለደ እናውቃለን። አሁን ግን እንዴት እንደሚያይ፥ ዓይኖቹንም ማን እንደ አበራለት እናውቅም፥ እርሱን ጠይቁት፥ አዋቂ ነውና፥ ስለራሱም መናገር ይችላልና፤» አሉ። እንዲህም ማለታቸው «እርሱ ክርስቶስ ነው፥ ብሎ በእርሱ የሚያምን ቢኖር ከምኲራብ ይውጣ፤» የሚለውን የአይሁድን ዓዋጅ ፈርተው ነው። ብላቴናው ግን ደጋግመው በጠየቁት ጊዜ «አትሰሙኝም እንጂ ነገርኋችሁ፥ እንግዲህ ምን ልትሰሙ ትሻላችሁ? እናንተም ደቀመዛሙርቱ ልትሆኑ ትሻላችሁን?» ብሎ ሳይፈራ ተከራከራቸው። በዚህን ጊዜ «ራስህ በኃጢአት የተወለድህ አንተ እኛን ታስተምራለህን?» ብለው ከምኲራብ አወጡት። በዚህም ንግግራቸው በጌታ ቃል፦ «የእግዚአብሔር ሥራ ሊገለጥበት ነው እንጂ እርሱ አልበደለም፥ ወላጆቹም አልበደሉም፤» የተባለውን ሰው በልበ ደንዳናነት ኰነኑት። ከቤተ መቅደስም አስወጡት። ዮሐ ፱፥፫። ጌታችንም አግኝቶት «አንተ በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህን?» አለው። ብላቴናውም፦ «አቤቱ፥ አምንበት ዘንድ እርሱ ማነው?» ብሎ መለሰለት። ጌታችን ኢየሱስም «የምታየው፥ ከአንተ ጋርም የሚነጋገረው እርሱ ነው፤» አለው። ይኸውም «ነቢይ ነው፤» እንዳለ በምሳሌው እንዳይቀር «አምላክ ወልደ አምላክ» ብሎ እንዲያምን ነው። እርሱም «አቤቱ ፥ አምናለሁ፤» ብሎ ሰገደለት። ከዚህ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «እኔ የማያዩት እንዲያዩ (አላዋቆች ነን የሚሉ ሐዋርያት አዋቆች ይሆኑ ዘንድ) የሚያዩትም እንዲታወሩ (አዋቆች ነን የሚሉ ፈሪሳውያን አለዋቆች ይሆኑ ዘንድ) ለፍርድ መጥቻለሁ። (ላመነብኝ ልፈርድለት ላላመነብኝ ልፈርድበት፥ ለሰው መፈራረጃ ለመሆን ከሰማይ ወርጃለሁ)። አለው። በዚህን ጊዜ ይኽንን የሰሙ ፈሪሳውያን፦ «እኛ ደግሞ ዕውሮች ነን?» አሉት። ጌታችን ኢየሱስም ዕውሮችስ ብትሆኑ ኃጢአት ባልሆነባችሁ ነበር፤ (ነውረ ሥጋ ከመንግሥተ ሰማይ አያወጣምና)፤ አሁን ግን እናያለን (እናውቃለን) ትላላችሁ፥ አታዩምም፤ (አታውቁምም)፤ ስለዚህም ኃጢአታችሁ ጸንቶ ይኖራል፤ (ንስሐ ስለማትገቡ ኃጢአታችሁ አይሰረይላችሁም)፤ አላቸው። ዮሐ ፱፥፩፥፵፩። እንግዲህ በዚህ ምክንያት «ለሰው መፈራረጃ እሆን ዘንድ መጥቻለሁ።» በማለቱ፥ ለምሕረትም እንደመጣ ለማጠየቅ በዮሐንስ ወንጌል በምዕራፍ አሥር ያለውን አስተምሯል።
፪ኛ፦ ይህ ዕውር ሆኖ ተወልዶ ጌታ የፈወሰው ብላቴና፥ ፈሪሳውያን፦ እንዴት እንዳየ ደጋግመው በጠየቁት ጊዜ፥ ደጋግሞ እውነቱን ነግሯቸዋል። በተጨማሪም፦ «እናንተም ደቀ መዛሙርቱ ልትሆኑ ትሻላችሁን?» ብሎም ጠይቋቸዋል። እነርሱ ግን፥ «አንተ የእርሱ ደቀመዝሙር ሁን፥ እኛስ የሙሴ ደቀመዛሙርት ነን። እግዚአብሔር ሙሴን እንደተነጋገረው እናውቃለን፥ ይህን ግን ከወዴት እንደሆነ አናውቅም፤» አሉት። በዚህን ጊዜ «. . . ከወዴት እንደሆነ፥ አታውቁምና እጅግ ድንቅ ነው፤ ነገር ግን ዓይኖቼን አበራልኝ። ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ኖሮ ምንም ማድረግ ባለቻለም ነበር፤» ብሎአቸዋል። እንግዲህ፦ «ከወዴት እንደሆነ አናውቅም፤» ብለውት ስለነበረ ከወዴት እንደሆነ ለማጠየቅ አንቀጸ አባግዕን አስተምሯል።
፫ኛ፦ «ቸር እረኛ አይደለህም፤» ብለውት ስለነበር፥ ቸር እረኛ መሆኑን ለማጠየቅ ነው። ይኽንንም፦ «ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ፥ ቸር ጠባቂ ስለ በጎቹ ነፍሱን ይሰጣል። ጠባቂ ያይደለ፥ በጎቹም ገንዘቡ ያይደሉ ምንደኛ ግን፥ ተኲላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሻላል፤ ተኲላም መጥቶ በጎቹን ይነጥቃቸዋል፥ ይበትናቸዋልም። ምንደኛስ ይሸሻል፥ ስለ በጎቹም አያዝንም፥ ምንደኛ ነውና።» በማለት ነግሯቸዋል።
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ በጎች ያላቸው ምእመናንን ነው። የዕለተ ምጽአት ፍርድ እንዴት እንደሆነ ለደቀመዛሙርቱ በነገራቸውም ጊዜ፥ ጻድቃንን በበጎች መስሎ፥ «በጎቹን በቀኝ ያቆማቸዋል፤» ብሏል። ማቴ ፳፭፥፴፫። ቅዱስ ጴጥሮስንም፦ «በጎቼን ጠብቅ፤» ብሎታል። ዮሐ ፳፩፥፲፭። ተኲላ ያለው ደግሞ ሰይጣንን እና መልክተኞቹን ነው። ቅዱስ ዳዊት፦ በልዑል ረድኤት የሚያድር፥ በሰማይ አምላክ ጥላ ውስጥ የሚቀመጥ፥ እግዚአብሔርን፦ «አንተ መጠጊያዬና አምባዬ፥ አምላኬና ረዳቴ ነህ፥ በአንተ እታመንብሃለሁ፤» የሚል ሰው፥ የሚያገኘውን ጸጋ ሲናገር፥ «ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም፥ መቅሠፍትም ወደ ቤትህ አይገባም። በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፥ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል። በተኲላና በእባብ ላይ ትጫናለህ፥ አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ፤» ብሏል። መዝ ፺፥፩-፲፫። ካልተጠነቀቁ በስተቀር ተኲላት (መናፍቃን) አደገኞች ናቸው። ይኽንንም ጌታችን «የበግ ለምድ ለብሰው ወደ እናንተ ከሚመጡ ከሐሰተኞች ነቢያት (ከመናፍቃን) ተጠንቀቁ፥ በውስጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኲላዎች ናቸው።» በማለት ነግሮናል። ማቴ ፯፥፲፭። ከዚህም ሌላ «እነሆ እኔ እንደ በጎች በተኲላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ . . . ከክፉዎች ሰዎች ተጠበቁ፤» ብሎናል።
ተኲላ ተንኰለኛ አውሬ ነው፥ ተመሳስሎ ከበጎች ጋር መደባለቅ ያውቅበታል፥ ሥጋ በል ሲሆን ሣር እንደሚነጭ እንስሳ አንገቱን ቀብሮ ይውላል፥ ቢርበውም ምቹ ጊዜ እስኪያገኝ ይታገሣል። በጎች በራሳቸው አቅም ይኽንን መከላከል አይችሉም፥ ምክንያቱም የዋሃን ናቸውና። በመሆኑም ተግቶ የሚጠብቅ እረኛ ያስፈልጋቸዋል። እረኛ ከሌላቸው ግን ይጠፋሉ። ይኽንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ከምእመናን ሕይወት ጋር በማገናዘብ፦ «እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበርና፥ አሁንም ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመለሱ፤» ብሏል። ፩ኛ ጴጥ ፪፥፳፭። በጎች የምእመናን ብቻ ሳይሆን የክርስቶስም ምሳሌዎች ናቸው። መጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስ፦ «እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ፤» ያለው ለዚህ ነው። ዮሐ ፩፥፳፱። ነቢዩ ኢሳይያስም፦ «እርሱ ግን በመከራው ጊዜ አፉን አልከፈተም፥ እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፥ የበግ ጠቦትም በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል እንዲሁ አፉን አልከፈተም።» በማለት አስቀድሞ ተናግሯል። ኢሳ ፶፫፥፯።
፩፥፩፦ በበሩ የሚገባና የማይገባ፤
በበሩ የሚገባ ማለት፦ ትንቢት ተነግሮለት፥ እግዚአብሔር አብ መስክሮለት፥ ምእመናን ወደ አሉበት ወደ ኢየሩሳሌም በመምሕርነት የሚመጣ ማለት ነው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣው ትንቢት ተነግሮለት፥ ሱባዔ ተቆጥሮለት ነው። ኢሳ ፯፥፲፬፤ ፱፥፪-፮፤ ፲፩፥፩። የባህርይ አባቱም በዮርዳኖስ፦ «በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤» በማለት መስክሮለታል። ማቴ ፫፥፲፯። ከዚያም በፊት የልደቱን ብሥራት ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የነገረ፥ ቅዱስ ገብርኤል፥ «ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆ ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ። እርሱም ታላቅ ነው፥ የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል፤» ብሏል። ሉቃ ፩፥፴-፴፪። በተወለደ ጊዜም ቅዱሳን መላእክት፥ ለእረኞች ተገልጠው፥ «እነሆ፥ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ እነሆ፥ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል፥ ይኸውም ቡሩክ ጌታ ክርስቶስ ነው።» በማለት መስክረውላቸዋል። ሉቃ ፪፥፲፥፲፩። መጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስም፦ «ጫማውን እሸከም ዘንድ ከማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፥እርሱ በእሳትም በመንፈስ ቅዱስም ያጠምቃችኋል፤ መንሹም በእጁ ነው፥ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፥ ስንዴውን በጎተራ ይከታል፥ ገለባውን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።» ማቴ ፫፥፲፩። «ተጐንብሼ የጫማውን ጠፍር መፍታት ከማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ በኋላዬ ይመጣል።» ማር ፩፥፯፣ ሉቃ ፫፥፲፭። «ዳሩ ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል፤ እኔ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የማይገባኝ፥ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይልቅ የሚከብር ይህ ነው። . . . አንድ ሰው ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል ብዬ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነው። እኔም አላውቀውም ነበር፥ ነገር ግን ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውኃ እያጠመቅሁ መጣሁ።» ዮሐ ፩፥፳፮። «ከሰማይ ካልተሰጠው ሰው አንዳች ሊቀበል አይቻለውም። እናንተ እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፥ ነገር ግን ከእርሱ በፊት ተልኬአለሁ እንዳልሁ ራሳችሁ ትመሰክሩልኛላችሁ። ሙሽራይቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው፥ ቆሞ የሚሰማው ሚዜው ግን በሙሽራው ድምፅ እጅግ ደስ ይለዋል። እንግዲህ ይህ ደስታዬ ተፈጸመ። እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ይገባል።» ብሏል። ዮሐ ፫፥፳፯።
ከእግዚአብሔር አብ፥ ከነቢያት ትንቢት፥ ከቅዱሳን መላእክት ብሥራትና የምሥራች፥ እንዲሁም ከመጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስ ምስክርነት እንደተማርነው፦ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ በበሩ የገባ ቸር እረኛ ነው። በመሆኑም «ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፥ በጎቹም ቃሉን ይሰሙታል፥ እርሱም በጎቹን በየስማቸው ይጠራቸዋል፥ አውጥቶም ያሰማራቸዋል።» ብሎአል። በረኛ የተባለ መንፈስ ቅዱስ ነው፤ ሕዋሳቱን በሰበሰበ፥ ዐሠርቱ ቃላትን በያዘ፥ በሰቂለ ኅሊና፥ በነቂሐ ልቡና በሚኖር ሰው የሚያድር እርሱ ስለሆነ የሰውን አእምሮ ለበጎ ይከፍተዋል። አንድም በረኛ የተባለ ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ምክንያቱም፥ ለጊዜው አምስት ሺ አምስት መቶ ዘመን የተዘጋች ገነትን በቤዛነቱ የሚከፍት፥ ለፍጻሜውም በዕለተ ምጽአት መንግሥተ ሰማያትን የሚከፍት እርሱ ነውና። «በጎቹ ቃሉን ይሰሙታል፥» እንዳለ፥ አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት፥ ሰባ ሁለቱ አርድእት፥ ሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት ትምህርቱን ተቀብለውታል። በየስማቸውም ዮሐንስ፥ ያዕቆብ፥ ስምዖን፥ ታዴዎስ፥ ዲዲሞስ፥ ቶማስ እያለ ጠርቶአቸዋል። «አውጥቶም ያሰማራቸዋል፤» የተባለው ደግሞ፦ «በጠባቢቱ በር ግቡ፤ . . . እኔን ሊከተል የሚወድ ራሱን ይካድ፥ ጨክኖም የሞቱን መስቀል ተሸክሞ ይከተለኝ፤» እያለ ያስተምራቸዋል ማለት ነው። መሰማሪያ የተባለው ትምህርተ ወንጌል ነው፥ አንድም መከራ ነው፥ አንድም በመጨረሻ የሚወርሱት ክብረ መንግሥተ ሰማያት ነው።
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ካስተማራቸው በኋላ ይሰቀልላቸዋል (ነፍሱን አሳልፎ ይሰጥላቸዋል)። «በጎቹም ይከተሉታል»፤ እርሱን አብነት አድርገው ወንጌልን ያስተምራሉ፥ መከራን ይቀበላሉ፥ በመከራ ይመስሉታል። «ቃሉን ያውቃሉና።» ትምህርቱን ተቀብለውታልና። «ሌላውን ግን ይሸሹታል እንጂ አይከተሉትም፥ የሌላውን ቃሉን አያውቁምና።» ትንቢት ሳይነገርለት፥ መጻሕፍት ሳይመሰክሩለት የመጣውን ግን ሌባ ወንበዴም በመሆኑ አብነት አያደርጉትም፥ አይመስሉትም፤ ይነቅፉታል፥ ያወግዙታል እንጂ ትምህርቱን አይቀበሉም። ጌታችን ይኽንን ምሳሌ ቢነግራቸውም እረኛ የተባለ እርሱ፥ አባግዕ የተባሉ ደግሞ እነርሱ እንደሆኑ አልገባቸውም።
ዳግመኛም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ «እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የበጎች በር እኔ ነኝ። ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፥ ነገር ግን በጎች አልሰሙአቸውም። እውነተኛው የበጎች በር እኔ ነኝ፥ በእኔ በኲልም የሚገባ ይድናል፤» (ወደ ሃይማኖት ወደ ወንጌል ይገባል)፤ «ይወጣልም፤» (ከፈቃደ ሥጋ ይወጣል፤ አንድም በጎ ሥራ ለመሥራት ለማስተማር ይወጣል)፤ መሰማሪያም ያገኛል። (መከራን ማለትም እስራቱን፣ ግርፋቱን፣ እሳቱን፣ ስለቱን፣ ያገኛል)። አንድም በጉባኤ ምእመናንን ያገኛል፤ አንድም ክብረ ሥጋን ክብረ ነፍስን ያገኛል)። ሌባ ግን ሊሰርቅና ሊያርድ፥ ሊያጠፋም ካልሆነ በቀር አይመጣም። (ሌባው ወንበዴው ግን በነፍስም በሥጋም ሊጐዳ ሊያጠፋ ነው እንጂ ሊያለማ ሊጠቅም አይመጣም)። እኔ ግን የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኙ፥ እጅግም እንዲበዛላቸው መጣሁ።» አላቸው።
በበሩ የማይገባ ማለት ደግሞ፦ ትንቢት ሳይነገርለት፥ ሱባዔ ሳይቆጠርለት፥ እግዚአብሔር አብ ሳይመሰክርለት፥ ቅዱሳን መላእክትም ብሥራቱንም የምሥራቹንም ሳይናገሩለት የመጣ ማለት ነው። ይኸውም እንደ ይሁዳ ዘገሊላ አንድም እንደ ቴዎዳስ ዘግብፅ ነው። የአይሁድ ሸንጎ በቅዱሳን ሐዋርያት ተቆጥተው ሊገድሉአቸው በወደዱ ጊዜ፥ በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ የከበረ ስሙ ገማልያል የሚባል የኦሪት መምህር ነበረ። እርሱም ቅዱሳን ሐዋርያትን ፈቀቅ እንዲያደርጉአቸው ካዘዘ በኋላ፥ «እናንተ የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ በእነዚህ ሰዎች በምታደርጉት ነገር ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ቀድሞም ከዚህ ዘመን በፊት ቴዎዳስ ተነሥቶ ራሱን ከፍ ከፍ አደረገ፤ (እኔ አምላክ ነኝ አለ)፤ አራት መቶ ሰዎችም ተከተሉት፥ ነገር ግን እርሱም ጠፋ፥ የተከተሉትም ሁሉ ተበታተኑ፥ እንደ ኢምንትም ሆኑ። ከእርሱም በኋላ ሰዎች ለግብር በተቈጠሩበት ወራት ገሊላዊ ይሁዳ ተነሣ፥ ብዙ ሕዝብም ተከተሉት፥ እርሱም ሞተ፥ የተከተሉትም ሁሉ ተበታተኑ። አሁንም እላችኋለሁ፥ ከእነዚህ ሰዎች (ከቅዱሳን ሐዋርያት) ራቁ፥ ተዉአቸውም፥ ይህ ምክራቸው ይህም ሥራቸው ከሰው የተገኘ ከሆነ ያልፋል፥ ይጠፋልም። ከእግዚአብሔር የመጣ ከሆነ ግን ልታፈርሱት አትችሉም፥ ከእግዚአብሔርም ጋር እንደሚጣላ አትሁኑ።» ብሎአል። የሐዋ ፭፥፴፬፥፴፱።
፩፥፪፦ ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ፤
ቅዱስ ዳዊት እግዚአብሔር እረኛ ጠባቂ መሆኑን ሲናገር፦ «እግዚአብሔር ይጠብቀኛል፥ የሚያሳጣኝም የለም። በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፥ በዕረፍት ውኃ ዘንድ አሳደገኝ፤» ብሎአል። መዝ ፳፪፥፩። ቸር እረኛ የጠፋውን በግ እስኪያገኘው ድረስ ይፈልገዋል። ይኽንንም፦ «የሰው ልጅ (ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ) የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአልና። ምን ትላላችሁ? መቶ በጎች ያለው ሰው ቢኖር፥ ከመካከላቸውም አንዱ ቢጠፋው፥ ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ላይ ትቶ የጠፋውን ሊፈልግ ይሄድ የለምን? እውነት እላችኋለሁ፥ ባገኘው ጊዜ ካልጠፉት ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ ጠፍቶ ስለተገኘው ፈጽሞ ደስ ይለዋል፤» በማለት ነግሮናል። ማቴ ፲፰፥፲፩-፲፫። እግዚአብሔር ቅዱሳን መላእክትን የፈጠራቸው በነገድ መቶ አድርጎ ነበር። አንደኛው ነገድ (የሳጥናኤል ነገድ) በክህደት በመጉደሉ ምክንያት አዳም መቶኛ ሆኖ ተቈጥሯል። በመሆኑም የጠፋው በግ የተባለው አዳም ነው። ነቢዩ ኢሳይያስም፦ «እነሆ እግዚአብሔር በኃይሉ ይመጣል፥ በክንዱም (በሥልጣኑ፥ በባህርይ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ) ይገዛል፥ እነሆ ዋጋው ከእርሱ ጋር ሥራውም በፊቱ ነው። መንጋውን እንደ እረኛ ይመራል፥ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል፥ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል።» በማለት እርሱ አምላካችን የሕይወታችን እረኛ እንደሆነ ተናግሯል። ኢሳ ፵፥፲፩። ነቢዩ ሕዝቅኤል ደግሞ፦ «ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ እኔ ራሴ በጎቼን እሻለሁ፥ እጎበኛቸዋለሁ። ከአሕዛብም ዘንድ አወጣቸዋለሁ፥ ከሀገሮችም ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ፥ ወደ ገዛ ሀገራቸውም አመጣቸዋለሁ፥ በእስራኤልም ተራሮች ላይ፥ በፈሳሾችም አጠገብ፥ በምድርም ላይ ሰዎች በሚኖሩባት ስፍራ ሁሉ አሰማራቸዋለሁ። በመልካም ማሰማርያ አሰማራቸዋለሁ፥ ጉሮኖአቸውም በረዥሞቹ በእስራኤል ተራሮች ላይ ይሆናል፥ በዚያ በመልካም ጉረኖ ውስት ይመሰጋሉ፥ በእስራኤልም ተራሮች ላይ በለመለመ መሰማሪያ ይሰማራሉ። እኔ ራሴ በጎቼን አሰማራለሁ፥ አስመስጋቸውማለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የጠፋውንም እፈልጋለሁ፥ የባዘነውንም እመልሳለሁ፥ የተሰበረውንም እጠግናለሁ፥ የደከመውንም አጸናለሁ፥ የወፈረውንና የበረታውንም እጠብቃለሁ፥ በፍርድም እጠብቃቸዋለሁ።» ብሏል። ሕዝ ፴፬፥፲፩-፲፮።
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጎቹን ፍለጋ የመጣ ቸር እረኛ በመሆኑ፥ «ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ፥ ቸር ጠባቂ ስለ በጎቹ ነፍሱን ይሰጣል። ጠባቂ ያይደለ፥ በጎቹም ገንዘቡ ያይደሉ ምንደኛ ግን ተኲላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፥ ተኲላም መጥቶ በጎቹን ይነጥቃቸዋል፥ ይበትናቸዋልም። ምንደኛስ ይሸሻል፥ ስለ በጎቹም አያዝንም፥ (የምእመናን ጥፋት አያሳዝነውም)፥ ምንደኛ ነውና። (ሥጋዊ፥ ዓለማዊ በመሆኑ መናፍቅ ጳጳስ፥ አላዊ ንጉሥ በተነሣ ጊዜ ይክዳል፤ ምዕመናንን አሳልፎ ይሰጣቸዋል፥ ሐሰተኛ ነውና)። ቸር ጠባቂ (እውነተኛ መምህር) እኔ ነኝ፥ የእኔ የሆኑትን መንጋዎቼን (ወልድ ዋሕድ ብለው ያመኑብኝን) አውቃለሁ፥ የእኔ የሆኑትም ያውቁኛል፤ (በእኔ ያመኑብኝ እኔን አብነት አድርገው መከራን ይቀበላሉ)፤ ብሏል።
፩፥፫፦ አብ እኔን እንደሚያውቀኝ እኔም አብን አውቀዋለሁ፤
አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ህልዋን ናቸው። አብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነው፥ ወልድም በአብ በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነው፥ መንፈስ ቅዱስም በአብ በወልድ ህልው ነው። «እኔ በአብ እንዳለሁ፥ አብም በእኔ እንዳለ እመኑ፤» ብሏል። ዮሐ ፲፩፥፲፩። በስም በአካል በግብር ሦስት የሆኑ ሥላሴ በህልውና አንድ እንደሆኑ ሁሉ በመለኰት፥ በሥልጣን፥ በባህርይ፥ በፈቃድ አንድ ናቸው። «እኔና አብ አንድ ነን፤» ያለው ለዚህ ነው። ዮሐ ፲፥፴። እንግዲህ፥ አይሁድ በክፋታቸው «ይህ ከወዴት እንደመጣ፥ ማን እንደሆነ አናውቅም፤» ብለውት ስለነበረ፥ እናንተ ባታውቁኝ የባህርይ አባቴ አብ ያውቀኛል፥ እንደማለት፥ «አብ እኔን እንደሚያውቀኝ እኔም አብን አውቀዋለሁ፤» ብሎባቸዋል። ይኸውም፦ «እኔ ልሰቀል ልሞት መምጣቴን አብ እንደሚያውቅ ሁሉ እኔም የመጣሁበትን ዓላማ አውቃለሁ፤» ሲል ነው። ለዚህ ነው ከዚያው አያይዞ፥ «ለበጎችም ቤዛ አድርጌ ሰውነቴን አሳልፌ እሰጣለሁ፤»ያለው። በማቴዎስ ወንጌልም፦ «ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቀው የለም፤ (ያለ አብ ወልድን በባሕርዩ የሚያውቀው የለም፥ በባሕርይ አንድ ናቸውና)፤ አብንም ከወልድ በቀር፥ ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅደው በቀር የሚያውቅ ማንም የለም። (ያለ ወልድ አብን በባሕርዩ የሚያውቀው የለም)፤» የሚል አለ። ማቴ ፲፩፥፳፯።
ትንቢት ተነግሮለት፥ ሱባዔ ተቆጥሮለት፥ ወደዚህ ዓለም የመጣ ቸር እረኛ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ «ከዚህ ቦታ ያይደሉ ሌሎች በጎችም አሉኝ፤ (በኢየሩሳሌም የሌሉ በአራቱ ማዕዘን ያሉ ሌሎች አሉኝ)፤ ቃሌንም ይሰሙኛል፤ (ትምህርቴን ይቀበሉኛል)፤ ለአንድ እረኛ አንድ መንጋም ይሆናሉ። (ለአንድ ለክርስቶስ አካሉ ይሆናሉ፤ አንድም ለአንድ ሊቀ ጳጳስ አንድ ማኅበር፥ አንድ ቤተሰብእ ይሆናሉ)፤ ብሎአል። ይህም ወደዚህ ዓለም መምጣቱ ለቤተ አይሁድ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም መሆኑን ያስተምረናል።
፩፥፬፦ ሥልጣን አለኝ፤
ነፍስንም ሥጋንም ከእመቤታችን ነስቶ (ወስዶ) በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ዓለምን ለማዳን መከራ የተቀበለው፥ የሞተውም በፈቃዱ ነው። ይህም ይታወቅ ዘንድ፦ «ስለዚህም አብ ይወድደኛል፤» ካለ በኋላ «እንደ ገና አስነሣት ዘንድ እኔ ነፍሴን እአጣለሁና። ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤ ነገር ግን እኔ በፈቃዴ እሰጣታለሁ፥ እኔ ላኖራት ሥልጣን አለኝ፤ (ነፍሴን በገነት፥ ሥጋዬን በመቃብር ላኖራቸው ሥልጣን አለኝ)፤ መልሼ እወስዳት ዘንድ ሥልጣን አለኝ። (ነፍሴን ከሥጋዬ አዋሕጄ በማስነሣት፥ በዕርገት፥ በየማነ አብ፥ በዘባነ ኪሩብ አስቀምጣት ዘንድ ሥልጣን አለኝ)፤ ብሏል። መከራውን፥ ትንሣኤውን እና ዕርገቱን በተመለከተም ነቢያት አስቀድመው ተናግረውታል።
– «እርሱ ስለ ኃጢአታችን ቈሰለ፥ ስለበደላችንም ታመመ፤ የሰላማችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቊስል እኛ ተፈወስን። . . . እግዚአብሔርም ስለ ኃጢአታችን ለሞት አሳልፎ ሰጠው።» ኢሳ ፶፫፥፭-፮።
– «እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፤» መዝ ፸፯፥፷፭።
– «እግዚአብሔር በእልልታ፥ ጌታችንም በመለከት ድምፅ አረገ።» መዝ ፵፮፥፭።
በመጨረሻ የምንመለከተው፥ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «እውነተኛ የበጎች በር እኔ ነኝ፤»ያለበትን ዋና ምክንያት ነው። ይኸውም በር የተከፈተለት እንደሚገባ፥ የተዘጋበት ደግሞ በአፍአ እንደሚቀር ሁሉ፥ በጌታችን ያመነ የመንግሥተ ሰማያት በር ይከፈትለታል፥ ያላመነበት ደግሞ በሩ ተዘግቶበት በአፍአ እንደሚቀር ነው። በመሆኑም በር የተባለው በእርሱ ላይ ያለን እምነት እንደሆነ ከትርጓሜው እንረዳለን። የበሩንንም ቊልፍ ለቅዱሳን አስረክቧል። ይኸውም ይታወቅ ዘንድ ቅዱስ ጴጥሮስን «አንተ ብፁዕ ነህ፥ በሰማይ ያለው አባቴ ነው እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና። እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ዐለት ነህ፥ በዚያች ዐለት ላይም ቤተክርስቲያኔን እሠራታለሁ፥ የሲኦል በሮችም (ደጅ ጠባቂ አጋንንት) አይበረቱባትም። የመንግሥተ ሰማያትም መክፈቻ እሰጥሃለሁ፥ በምድር የምታስረው በሰማይ የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው በሰማይ የተፈታ ይሆናል።» ብሎታል። ማቴ ፲፮፥፲፯-፲፱። ሌሎችን ግን፦ «መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ ወዮላችሁ! እናንተም አትገቡም፥ የሚገቡትንም ከመግባት ትከለክላላችሁ።» ብሏቸዋል። ማቴ ፳፫፥፲፬። ስለዚህ በር በተባለ በኢየሱስ ክርስቶስ ፈጽመን ልናምን ይገባል። እናምናለን ማለት ብቻም ሳይሆን የምናምነውስ ማን እና ምን ብለን ነው ማለትም ያስፈልጋል። ምክንያቱም ስሙን እየጠሩ፥ እንምንበታለን እያሉ፥ ስለ እርሱ የሚያስተምሩት ትምህርት ፈጽሞ መስመር የለቀቀባቸው ብዙዎች ናቸውና። የእኛ ግን መስመሩን የጠበቀው ፍጹም እምነታችን እንደሚከተለው ነው።
፩ኛ፦ ፈጣሪ ነው፥ ብለን እናምንበታለን። «ሁሉም በእርሱ ሆነ፥ (በእርሱ ተፈጠረ)፥ ከሆነውም (ከተፈጠረውም) ሁሉ ያለ እርሱ ምንም የሆነ የለም። ዮሐ ፩፥፫።
፪ኛ፦ የፈጠረውን ፍጥረት የሚገዛ የባሕርይ አምላክ ነው። «የእግዚአብሔር ልጅ እንደመጣ፤ እውነተኛም የሆነውን እግዚአብሔርን እናውቅ አንድ ልቡናን እንደሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛውም በሆነው በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንኖራለን፤ እርሱም እውነተኛ አምላክና የዘለዓለም ሕይወት ነው።» ፩ኛ ዮሐ ፭፥፳።
፫ኛ፦ ፈጣሪ፥ የባሕርይ አምላክ በመሆኑም እግዚአብሔር ነው። «በመጀመሪያ ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ (በፈጣሪነት ከአብ ተካክሎ) ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህም በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ (በፈጣሪነት ከመንፈስ ቅዱስም ተካከልሎ) ነበረ። . . . ያም ቃል ሥጋ ሆነ፥ በእኛም አደረ፤ (ነፍስንና ሥጋን ነስቶ በተዋሕዶ ሰው ሆነ)።» ዮሐ ፩፥፩፣ ፩። «አሁንም በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ትጠብቁ አንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤» የሐዋ ፳፥፳፰።
፬ኛ፦ ወልድ በተለየ አካሉ ከሰማይ ወርዶ፥ በተዋሕዶ ሰው ሆኖ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በመወለዱ በሥልጣን ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ አላነሰም። «እኔና አብ አንድ ነን፤» ዮሐ ፲፥፴። በሕልውናም አንድ ነው። «እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑ፤» ዮሐ ፩፥፲፩። «እኔን የሚጠላ አቤን ይጠላል። . . . አሁን ግን እኔንም አባቴንም አይተዋል፥ ጠልተውማል።» ዮሐ ፲፭፥፳፫።
፭ኛ፦ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ የተወለደ እርሱ የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ነው። «እነሆም፥ በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው።» ማቴ ፫፥፩።
፮ኛ፦ ሰው የሆነው በተዋሕዶ ነው፥ በመሆኑም ከተዋሕዶ በኋላ ሁለትነት የለም፥ ይህ የሥጋ ነው፥ ይህ ደግሞ የመለኰት ነው ተብሎ መከፈል የለበትም። አብ «ልጄ ነው፤» ያለው በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። ወደ ሠርግ ቤት የተጠራውም ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ የለወጠውም ከተዋሕዶ በኋላ ሁለትነት የሌለበት አንድ እርሱ ነው። ዮሐ ፪፥፩-፲። ሥጋን እንደተዋሐደ ለማጠየቅ «አልዓዛርን የት ቀበራችሁት?» ያለም ከሞት ያስነሣም አንድ እርሱ ነው። ዮሐ ፲፩፥፴፬፣፵፫። ከዚህም ሌላ መቃብሩ ሳይከፈት ከመቃብር የወጣው (ሞትን ድል አድርጐ የተነሣው) አንዱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ማቴ ፳፯፥፷፮፣፳፰፥፩። በተዘጋ ቤትም በሩ ሳይከፈት ከአንዴም ሁለት ጊዜ የገባው አንዱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ዮሐ ፳፥፲፱፣፳፮።
፯፦ ኢየሱስ ክርስቶስ ፈራጅ ዳኛ ነው። «አሁንም በእግዚአብሔር ፊትና በመንግሥቱ በሚመጣበት ጊዜ፥ በሕያዋንና በሙታን ይፈርድ ዘንድ ባለው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እመክርሃለሁ። . . . እንግዲህስ የጽድቅ አክሊል ይቆየኛል፥ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው እግዚአብሔር በዚያ ቀን ለእኔ ያስረክባል።» ፪ኛ ጢሞ ፬፥፩፣፰።
፰፦ እኛ የምንለምነውን በቅዱሳንም ጸሎት የምናስለምነውን ሁሉ እርሱ ያደርገዋል። «እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና፤ አብ በወልድ ይከብር (ይገለጥ) ዘንድ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርግላችኋለሁ። በስሜ የምትለምኑት ነገር ቢኖር ያን አደርግላችኋለሁ።» ዮሐ ፲፬፥፲፪-፲፫። እንግዲህ ሥጋን መዋሐዱን ለማጠየቅ የተናገረውን ቃል፥ አብነት ለመሆንም የሠራውን የትህትና ሥራ ሁሉ በትርጓሜ እያስታረቅን በትክክለኛው እምነት ጸንተን ልንቆም ይገባናል። በአምልኮታችን ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስን፥ እንደ ቅዱስ እስጢፋኖስ፥ ከአብ ተካክሎ ልናየው ይገባል እንጂ ዝቅ ልናደርገው አይገባም። «እነሆ ሰማይ ተከፍቶ፥ የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ፤» ይላል። ጸሎታችንም፦ ጌታዬ ኢየሱስ ሆይ፥ ነፍሴን ተቀበል፤ . . . አቤቱ ይህን ኃጢአት አትቊጠርባቸው፤» የሚል መሆን አለበት። የእግዚአብሔር ቸርነት፥ የድንግል ማርያም አማለጅነት አይለየን። አሜን።

ኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅ ነው ወይስ ተማላጅ ?

ኢየሱስን ክርስቶስ ክብር ይግባውና አማላጅ ነው የሚሉ ወገኖች የሚከተሉትን ጥቅሶች ማስረጃ ነው ብለው ያቀርባሉ።

“እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።” ዮሐ 14፥6 ይህን በመጥቀስ አማላጃችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው ይላሉ። ነገር ግን ይህን ጥቅስ የሚያስረዳን ስለ አማላጅነቱ ሳይሆን አብን ለማወቅ ክርስቶስን በቅድሚያ ማወቅና ማመን እንደሚገባ ነው። ዛሬ የይህዋ ምስክሮች ነን እንደሚሉት እንደ ጆቫዊትነሶች ወይም እንደ አሕዛቦች ክርሰቶስን ሳያምኑና አምላክነቱንና ፈጣሪነቱን ሳንቀበል አምላካችን አብ ብቻ ነው እያልን ብናወራ ዋጋ እንደሌለው የሚገልፅ ቃል ነው። ይህንንም ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያረጋግጥልን በዚሁ ጥቅስ ቀጥሎ “እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር።” ዮሐ 14፥7 ብሏል።

“በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።” ስላለ ወደ አብ የሚወስደን አማላጅ ክርሰቶስ ነው የምንል ከሆነ፦ “አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፥ ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም” /ዮሐ 6፥37/ “አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም” /ዮሐ 6፥44/ ከአብ የተሰጠው ካልሆነ ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም። /ዮሐ 6፥65/ ሲል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሯናልና እዚህ ጋር ደግሞ አማላጁ አብ ሊሆን ነው ማለት ነው። ይህ ደግሞ ትልቅ ስህተትና ኑፋቄ ነው። በሌላ ጥቅስ ላይ ደግሞ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለእኛ “መንፈስ ቅዱስ” ይቃትታል የሚል ፅፏልና “መንፈስ ቅዱስንም አማላጅ” ልንለው ይሆን? ታዲያ አብንም፣ ወልድንም፣ መንፈስ ቅዱስንም፤ አማላጅ እያሉ እንዴት ይዘልቁታል?

ነገር ግን ልብ ልንለው የሚገባን፣ በሁሉም ጥቅሶች ላይ ጌታችን የሚመጣ እንጂ የሚሄድ አለማለቱን ነው፣ ይህም ከአብ በአንድነትና በእኩልነት ያለ መሆኑን የሚያሳይ ነው። “የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፥ የሚኰንንስ ማን ነው? የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው (የሚፈርደው) ክርስቶስ ኢየሱስ ነው።” /ሮሜ 8፥33-34/ ይላል። አሁን እኮ ግልጽ ነው የሚኮንነው ክርስቶስ ከሆነ መኮነን ደግሞ በፍርድ ውስጥ የተጠቃለለ ነው፣ የመኮነን ሥልጣን ያለው እንዴትና ወዴት ለማንስ ያማልዳል፣ቅዱስ ዳዊት ግን “የቃልህ ፍቺ ያበራል” /መዝ 119፥130/ እንዳለ ፍቺው ይመሰክርባቸዋል።

አማላጅ ቢሆን ኖሮ ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ በግልጽ አማርኛ “ያማልዳል” ብሎ በጻፈ ነበር። ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ የሚኮንን ክርስቶስ እየሱስ ነው አለ እንጂ የሚያማልድ አላለም። ከመፍረድ አለፎ የሚኮንን ጌታ አማላጅ እንዴት ይሆናል? እስቲ ፍረዱኝ፣ ቅዱስ ጳውሎስ ራሱ ዝቅ ብሎ /በሮሜ 9፥5/ ላይ “ክርስቶስ በሥጋ (በችመቤታችን) በኩል መጣ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው አሜን። እንዲሁም ቅዱስ ዮሐንስም በመልዕክቱ /በ1ኛ ዮሐ 5፥20/ “ክርስቶስ እየሱስ የተባረከና የዘላለም አምላክ ነው” ብሏል፤ ቶማስም ጌታዬ አምላኬ ሲል መስክሯል፣ እነ ኢሳያስም አማኑኤልነቱን ወይም እግዚአብሔርነቱን ተናግረዋል ታዲያ እንዴት አማላጅ ይሉታል? ።

“እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።” /ዕብ 7፥24-25/ ማዳን እየቻለ አድንልኝ ብሎ ወዴት ይለምን ይሆን? ። “ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ።ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።” /በ1ኛ ዮሐ 2፥1/ እነዚህን እና የመሳሰሉትን ጥቅሶችን በመጥቀስ አማላጅ ነው ይኸው በግልጽ ተጽፏል በማለት ክርስቲያኖችን ለማሳሳት የሚሞክሩ አሉ።

በእርግጥም ለአዲስ አንባቢ (ለወጣኒነት) በግልጽ የተጻፈና የማያጠራጥር መስሎ ይታየው ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስና ትርጓሜው ሕይወቱ ስለሆነ ክርስቲያን ግን የቃሎቹ ትርጉም ይገለፅለታል። የሦስቱ ጥቅሶች አጠቃላይ ትርጉማቸው ኢየሱስ ክርስቶስ፦ በስጋው ወራት በመስቀል ላይ ተሰቅሎ፣ ደሙን አፍስሶና ስቃይ ተቀብሎ እኛን ከእግዚአብሔር (ከራሱ) ጋር ያስታረቀን (የማለደን) በመሆኑ ያ የማስታረቅ ሥራ አሁንም በቋሚነት እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሕያው ሆን ይኖራል ማለት ነው።

ከላይ የተጠቀሱስ ጥቅሶች ክርስቶስ በምድር ላይ ሳለ የፈፀመው የማስታረቅ አገልግሎት ዛሬም ነገም እንደሚያገለግል (መሐሪነቱን፣ ታራቂነቱን፣ ይቅር ባይነቱን፣ ቂም በቀል የሌለበት) መሆኑን የሚመሰክሩ እንጂ ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬ፦ አብን እና መንፈስ ቅዱስ እባክህ ወይም እባካቹ ይቅር በሏቸው (በላቸው) እያለ ያማልዳል ማለት አይደለም። ይልቁኑ ራሱ ጌታችን /በዮሐ 16፥26/ ላይ “በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ እንጂ እኔ ስለ እናንተ አብን ማርልኝ፣ ይቅር በልልኝ፤ ብዬ እንድለምን አይምሰላችሁ” ሲል አስተምሮናል። ስለዚህ ስለእኛ ዘወትር ሊማልድ ሲል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረው ጌታ አንድ ጊዜ ዓለሙን ከራሱ ጋር ለማስታረቅ የፈጸመው የማስታረቅ ሥራ ዘወትር ያገለግላል (ቃሉ ሕያውና የታመነ) ሆኖ ይኖራል ሲል እንጂ ክርስቶስ አሁን ስለእኛ ይቅር በላቸው እያለ ይለምናል ማለት አይደለም።

* ጠበቃ አለን ያለውም ጌታችን “ሥጋዬን የበላ ደሜንም የጠጣ እኔ ከርሱ ጋ እኖራለሁ” /ዮሐ 6፥56/ ባለው ቃል መሰረት የበላነው የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና የጠጣነው ክቡር ደሙ በፍርድ ወቅት (በእለተ መፅዓት) እንደሚቆምልን ለማመልከት ነው። አንዳንድ ወገኖቻችን (አሰተኞች ወንድሞች) እንደሚሉት ክርሰቶስ ራሱ ጠበቃ ነው ቢባልማ ዳኛው (ፈራጁ) ማን ሊሆን ነው? ።

* መጽሐፍ ቅዱስስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅድስ ብዙ ይላል፣ ብዙም ይናገራል (ያስተምራል) ታማሪ ብቻ ሳይሆን አስተዋይ ከተገኘ። እየሱስ ክርስቶስ የማስታረቅን ሥራ አንድ ጊዜ ስለፈፀመ አሁን አማላጅ ነው እንደማይባል ቅዱስ ጳውሎስ አበዝቶ ጽፏል።

“እርሱም (ክርስቶስ) በስጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ” /ዕብ 5፥7/ ይላል። ይህ አባባል በለበሰው ሥጋ ስለመከራውና ስለደረሰበት እንግልት ቢጮኸም ማርልኝ፣ ይቅር በልልኝ ማለቱ ለእኛ አርአያውንና ምሳሌውን ሲተውልን ነው። እናንተም መከራ ሲበዛባቹ ወደ እኔ ጩኹ ስለሚያሳድዷችሁ እንኳ ጸልዩ ማለቱ አንጂ ከእርሱ ሌላ አምላክ ወይም ይቅር ባይ ኖሮ መጮኹ አይደለም።

“እንደሌሎቹ ሊቃነ ካህናት… ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና።” /ዕብ 7፥27/ እንዲሁም “እርሱ ግን ስለ ኃጢያታችን አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ (በአንድነትና በሦስትነት በመለኮት፣ ክቡሩ በአምላክነቱ፣ በፈራጅነቱ፣ በአፅዳቂነቱና በኮናኝነቱ )ተቀመጠ።” /ዕብ 10፥12/

ክርስቶስ እየሱስ በሥጋው ወራት ስለእኛ ያቀረበው ምልጃ እንደ ፍጡራን ዓይነት ምልጃ (እንደ ቅዱሳን ፀሎትና ምልጃ) አይደለም፤ ትህትናን፣ ጸሎትን፣ ፆምን አብነት ሆኖ ለእኛ እንዳስተማረን ሁሉ ምልጃንም እንዲሁ አስተምሮናል እንጂ። ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው ቅዱስ እስጢፋኖስ ነው። እሱም ልክ ከጌታው (ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ) እንደተማረው እኛን ለማስተማር “የሚያደርጉትን አያቁምና ይቅር በላቸው” ሲል ምልጃ አቅርቧል። በመሆኑም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ያስተማረን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ጊዜ የደሙን መስዋዕት አቅርቦ ያ የደም መስዋዕት ለዘለዓለም ከእግዚአብሔር ጋር እንደሚያስታርቀን እንጂ እንዳንድ ወገኖች (አሰተኞች ወንድሞች) እንደሚሉት ክርሰቶስ ዕለት ዕለት ይቅር በላቸው እያለ ስለእኛ አይለምንም (አያማልድም)።

እንዲያማ ቢሆን እኛ ኃጢያት በሰራን ቁጥር ከሰማይ እየወረደ (እየተወለደ) መከራንም እየተቀበለ፣ ዕለት ዕለትም ደሙን እያፈሰሰ፣ የሾህ አክሊል ደፍቶ በጦር አየተወጋ፣ በጅራፍም እየተገረፈ፤ ሊሰቃይልን ነው ማለት ነው። ይህንን ቅዱስ ጳውሎስ ሲያረጋግጥ “ ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሰራች፥ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደ ምትሆን ቅድስት አልገባምና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ። ሊቀ ካህናትም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ፥ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም፤ እንዲህ ቢሆንስ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር።” ሲል /ዕብ 9፥24-26/ ላይ ይገልጻል።

የበሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት የሰውችን ኃጢያት ለማስወገድ በየዕለቱ የእንስሳ ደም እየያዘ ደወ መቅደስ በመግባት ለእግዚአብሔር ይሰዋ ነበር። እየሱስ ክርስቶስ ግን የራሱን ደም አንድ ጊዜ ወደ ማትታይ ቤተ መቅደስ ይዞ ገባ፣ ታዲያ ያ አንድ ጊዜ የፈሰሰ ደም እስከ ዓለም ፍፃሜ ያድናል እንጂ በየዕለቱ ኃጢያት በሰራን ቁጥር እየመጣ (እየተወለደ) ደሙን አያፈስልንም። ስለዚህም ክርስቶስ አማላጅ ነው አይባልም። በደሙ ድነናል ስንልም በእኛ ሥራ ሳይሆን በእሱ ቸርነት፣ እሱ በስጠን ፀጋ፣ በመስቀል ሞት፤ አዳነን ማለታችን እንጂ እንዳንድ ወገኖች (አሰተኞች ወንድሞች) እንደሚሉት በፀጋው ድነናል ብለን፦ ከፆም፣ ከጸሎት፣ ከስግደት፣ ከምጽዋት፣ ከቅዳሴ፤ በአጠቃለይ ከክርስቲያናዊ ሥነ ምግባራት ተቆጥበን ጌታ ጾሞልናል በማለት ብቻ እጅ እግራችንን አጣጥፈን እንቀመጥ ማለት አይደለም። ሐዋርያው ያዕቆብ አባቻችን ሥራ ወይም በጎ ምግባር የሌለው እምነት የሞተ ነው ይለናል። /ያዕ 2፥17/ ይልቁንም በብዙ ቦታ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ” /ዮሐ 6፥35 እና 48/ “እናንተ ሸክማቹ የከበደ ወይም ኃጢያታችሁ የበዛ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ።” /ማቴ 11፥28/ “ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ።” /ዮሐ 14፥14/ አለ እንጂ እኔ አብን፣ መንፈስ ቅዱስን ለምኜ አስደርገላችኋለሁ (አማልዳችኋለሁ) አላለም። ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ተማላጅ (ተለማኝ) እንጂ አማላጅ (ለማኝ) እንዳልሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይመሠክራል። ስለ ቃሉ የተመሰገነ ይሁን። አሜን!!!

ዋቢ መጽሐፍ፦ ማንም እንዳያስታቹ ተጠንቀቁ! /ማቴ 24፥1-51/

……. ” የቃልህ ፍቺ ያበራል!! ” መዝ 119፥130

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top