ዳግም ምጽአት

ዳግም ምጽአት

   ( በዲ/ን ያሬድ መለሰ)

ምጽአት መምጣት ማለት ሲሆን ዳግም የሚለው ቃል ሁለተኛ ምጽአት (መምጣት) የሚለውን ያመለክተናል ይህም የድርጊቱን መደገም የሚያመለክት ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን የመጀመርያ መምጣት(ቀዳማዊ ምጽአት) ስንለው ዳግመኛ የጌታን ለፍርድ መምጣት ደግሞ ዳግም ምጽአት እንለዋለን፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የጌታችንን ዳግም መምጣት በዓመት ሦስት ጊዜያት ታስባለች የመጀመርያው በወርኃ ሕዳር /ዘመነ መጽው/ ሁለተኛው በዐቢይ ጾም አጋማሽ ደብረ ዘይት/ዘመነ ሐጋይ/ ሦስተኛው በዘመነ ክረምት ወርኃ ጳጉሜን ነው ።
በወርኃ ኅዳር አስተምህሮ አስተምህሮ ከሕዳር ስድስት እስከ ታኅሣሥ ስድስት ቀን ድረስ ያለውን ጊዜ የሚወክል ነው፡፡ በወርኃ ታህሳስ መግቢያ ላይ በእለተ እሑድ ዳግም ምጽአት ይከብራል፡፡ በዚህ ወቅት የጌታችን ቀዳማዊ ምጽአት ከዳግም መምጣቱ ጋር አብሮ ይታሰባል፡፡ ነቢያት የጌታችንን መምጣት እንደሰበኩ በስፋት ይተነተናል፡፡ ሌሎቹ ጊዜያት በዐቢይ ጾም እኩሌታ ከደብረ ዘይት በዓል ጋር የጌታ ትምህርት የሆነው ዳግም ምጽአት በስፋት ይተነተናል በዘመነ ክረምት ወርኃ ጳግሜንም አዲስ ዘመን ጋር ተያይዞ ቤተ ክርስቲያን የጌታን መምጣት ነገር በስብከቷ በቅዳሴዋ በዝማሬዋ በመዝሙሯ ታስባለች
ነገረ ምጽአቱ
ጌታችን እንዴት ይመጣል?
ጌታችን ለሁለተኛ ጊዜ ሲመጣ ከመጀመሪያ አመጣጡ ፍጹም በተለየ መልኩ ነው
1. በመጀመሪያ ምጽዓቱ ራሱን ዝቅ አድርጎ በትኅትና ነበር የመጣው በዳግም ምጽአቱ ግን በታላቅ ክብርና በልዕልና ይመጣል
2. በመጀመሪያ ምጽዓቱ ማረፊያ ቦታ አልነበረውም በዳግም ምጽአቱ ግን በስሙ ላመኑት ዘላለማዊ ማረፊያን ይሰጣል (ሉቃ 2፥ )
3. በመጀመሪያ ምጽዓቱ ወገን የሌለው ብቸኛ መስሎ ተወለደ በዳግም ምጽአቱ ግን በአእላፋት መላእክት ተከቦ በግርማ፤ በአሸናፊነት ይመጣል
4. በመጀመሪያ ምጽዓቱ ሰው ሆኖ ሰውን ለማዳን መጣ በዳግም ምጽአቱ ግን ሰው ሆነው የኖሩትን ለመለየት ይመጣል
5. በመጀመሪያ ምጽዓቱ ተሰዷል በዳግም ምጽአቱ ግን የአሳዳጅና ተሳዳጅነትን አሰራር ሊያጠፋ ይመጣል
6. በመጀመሪያ ምጽዓቱ በምድር የሚገዙ ብዙ ነገሥታት ነበሩ። በዳግም ምጽአቱ ግን በፍቅሩና በቸርነቱ የሚገዛን የነገሥታት ንጉሥ የሆነ እርሱ ብቻ ነው ።
7. በመጀመሪያ ምጽዓቱ ደካማ ሆኖ ተገለጠ በዳግም ምጽአቱ ግን በክብርና በኃይል ይመጣል

8. በመጀመሪያ ምጽዓቱ ስለ ስሜ ብዙ መከራ ይደርስባችኋል እንዳለ ተከተሉኝ ብሎ የጠራቸው በብዙ መከራ ተፈትነዋልና ለመከራ እንደተጠሩ መሰሉ በዳግም ምጽአቱ ግን ለዘላለማዊ ክብር ይጠራናል ደቀ መዛሙርቱም በዙፍን ተቀምጠው ይፈርዳሉ
9. በመጀመሪያ ምጽዓቱ ልዑለ ቃል ኢሳይያስ “በሸላቾቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም፡፡”( ኢሳ. 53፡7) እንዳለ ሄሮድስን እስኪደነቅ ዝም ብሎ ነበር ። በዳግም ምጽአቱ ግን ዝም አይልም ለመሰከሩለት ይመሰክርላቸዋል፤(ዮሐ 3፥17) ባላመኑት ላይ ደግሞ ይፈርድባቸዋል ለዚህም ነው ዳዊት እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም፡፡ መዝ. 49፥2-3 ያለው

በጳጉሜን ዳግም ምጽዓት ለምን ይታሰባል

1. ሁለቱም ፍጻሜዎች ስለሆኑ

ጳጉሜን የዓመቱ ፍጻሜ ሁሉብዳግም ምጽዓትም የዓለም ፍጻሜ ነውና….
ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ (1ኛዮሐ. 2፡17 )እንዳለ

2. ሁለቱም በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቁ ስለሆኑ

ጳጉሜን ከሌሎቹ ወራት በጣም አጭር እንደሆነ ሁሉ የጌታ ምጽዓትም አጭር(ቅርብ) ነውና ።
አንዳንዶች ዳግም ምጽዓት ዕሩቅ እንደሆነ የምናስባሉ ነገር ግን ጌታችን እንዲህ ይላል፡- “እነሆ በቶሎ እመጣለሁ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ፡፡”(ራዕ. 22፡12)

3. ሁለቱም የአዲስ ሕይወት መጀመሪያ በመሆናቸው

ጳጉሜን ያለፈውን ዘመን አሮጌ ብለን አዲሱን ዘመን የምንጀምርበት እንደሆነ ሁሉ እንደሆነ ሁሉ ዳግም ምጽዓትም “አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ”( ራዕ. 21፡1) እንዳለ የአዲስ ሕይወት መጀመሪያችን በመሆኑ በዚህ ይመሳሰላሉ፡፡

ደብረ ዘይት – ምጽዓተ እግዚእነ – መጋቤ ሀዲስ ሮዳስ

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top