መላእክት

መላእክት

አምላካችን እግዚአብሄር የቸርነቱን ብዛት ካሳየባቸው መንገዶች አንዱ ስነ-ፍጥረት ነው፡፡ አምላክ ከቸርነቱ ብቻ ተነስቶ እሱ ያለውን ፍቅር በመጋራት ይደሰቱ ዘንድ የራሳቸው ነፃ ፍቃድ ያላቸው ፍጥረታትን በሰባት ቀናት ፈጥሮ እንደጨረሰ በኦሪት ዘፍጥረት እናነባለን፡፡ ታዲያ ከፈጠራቸው ፍጥረታት መካከል በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሁኔታቸው ጥቂት ብቻ ተጠቅሶ ከታለፉት ለየት ያለ አፈጣጠር ካላቸው ፍጥረታት ውስጥ አንዱ መላእክት ናቸው፡፡

*መላእክት ማለት ምን ማለት ነው? በስንት ይከፈላሉ?*

ከስም አሰያየሙ ብንነሳ “መላእክት” የግዕዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙም መላእክተኞች ወይም ተላላኪዎች ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እንደአገባቡ አለቆች ወይም አስተዳዳሪዎች የሚል ትርጉምም ሊኖረው ይችላል፡፡ አብዛኛው ጊዜ ሰዎች “መላእክት” የሚለውን ቃል ሲሰሙ ወዲያው ወደአእምሮአቸው የሚመጣው በብርሃን የተሸፈነ ባለ ትልቅ ክንፍ ፍጥረት ነው፡፡ በእርግጥ ትክክል ቢሆኑም “መላእክት” ሲባል የብርሃን ፍጥረታትን ብቻ የሚያመለክት ብቻ አድርጎም መውሰድ ትክክል አይደለም፡፡

መላእክት የሚለው ቃል መልእክተኞች ወይም ተላላኪዎች ማለት እንደሆነ አይተናል፡፡ ታዲያ ይህን በመመስረት “የሚላላኩት ማንን ነው” የሚለው ጥያቄ በመመለስ ለሁለት ስንከፍላቸው ፤ ለእግዚአብሄር አምላክ የሚላላኩትን ብርሃናዊ ፍጥረታት “ቅዱሳን መላእክት” ብለን ስንጠራቸው ለጠላታችን ዲያብሎስ የሚላላኩትን ጨለማ የተጎናፀፉ ፍጥረታትን ደግሞ “ርኩሳን መላእክት” በማለት እንጠራቸዋለን፡፡

*እግዚአብሄር አምላክ መላእክትን ለምን ፈጠረ?*

መላእክት የተፈጠሩበት ምክንያት ሰው ከተፈጠረበት ምክንያት የተለየ አይደለም፡፡ መላእክት የተፈጠሩት ልክ እንደ ሰው አምላካቸውን እያመሰግኑ እሱ እንደወደዳቸው እነሱም እየወደዱት ለዘለዓለም ይኖሩ ዘንድ ነው፡፡ አዳም ከተፈጠረ ቦሃላ እግዚአብሄር አምላክ ገነትን ይኖርባት ዘንድ ብቻ ሳይሆን ይጠብቃትም ዘንድ እንደሰጠው ሁሉ መላእክትም ከተፈጠሩ ቦሃላ ምስጋናቸው እረፍታቸው እረፍታቸው ደግሞ ምስጋናቸው ሆኖ እስካሁን ድረስ አሉ፡፡
አፈጣጠራቸው ከሰው የተለየ ቢሆንም ከክብራችን ሳንዋረድ በፊት ከመላዕክት ጋር የምንጋራቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ ፊታችን እንደነሱ የሚያበራ ፣ ማርጀትም ሆነ ሞት ፣ ድካምም ሆነ ስንፍና የማያጠቃን ፍጥረቶች ነበርን፡፡ በኛ መውደቅ አምላካችን ከልቡ ሲያዝን ቅዱሳን መላእክትም አብረው አዝነዋል፡፡ ታዲያ ከጥንት ጀምሮ አልተለዩንም፡፡ የአምላካችንን ግርማ መቋቋም አንችልምና ለኛ መልእክት ሲኖረው መላዕክቱ ያበስሩናል፡፡ በአደጋ ጊዜ ይጠብቁናል ፣ ስንደክም ያበረቱናል ፣ ወደ ልባችን ጥሩ ሃሳቦችን ልከው ለበጎ ስራ ያነሳሱናል ፣ ከቅዱሱ መንገድ ስንስት ፍፁም የሚያዝኑትን ያህል ወደፅድቅ መንገድ ስንመለስ ደግሞ በሰማይ ታላቅ ደስታን ያደርጋሉ፡፡ በቅዳሴ አምላካችንን ስናመሰግን አብረውን ያመሰግናሉ ፣ ነፍሳችን ስትጨነቅ ያረጋጓታል አልፎም ደግሞ እለተ ሞታችን ሲመጣ ነፍሳችንን ተንከባክበው ወደአምላክ ዘንድ ያደርሳሉ፡፡

*መላእክት ምን ይመስላሉ?*

“እከሌ ምን ይመስላል” ተብሎ ሲጠየቅ ቀይ፣ጠይም፣ ጥቁር ወዘተ… ብለን እንናገራለን፡፡ ለመላእክት ግን እንደዛ ብሎ መናገር አይቻልም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ መላእክት እንደኛ ስጋ ለባሾች ስላልሆኑ ነው፡፡ ስጋ ለባሽ ፍጥረታት ቀይ፣ጠይም ወይም ጥቁር የመሆንን ባህሪይ እንዳላቸው ሁሉ መላእክት ከብርሃን የተፈጠሩ በመሆናቸው የብርሃን ጠባይ ይኖራቸዋል፡፡ ስለዚህም መላእክት ምን ይመስላሉ ለሚለው ጥያቄ “ብርሃንን” የሚል መልስ ብንሰጥ ተገቢ ይሆናል፡፡ የመላእክትን ብርሃናዊነት ወንጌላዊው ዮሃንስ እንዲህ ብሎ ገልፆታል፡፡

“ከዚህ ቦሃላ ታላቅ ሥልጣን ያለው ሌላ መላእክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፡፡ ከክብሩም የተነሳ ምድር በራች” ራዕይ 18፡1

ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤም ቦሃላም የመቃብሩን ድንጋይ ስላንከባለለው መላእክ በማቴዎስ ወንጌል እንዲህ ተብሎ ተፅፏል፡፡

“መልአኩም እንደ መብረቅ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበር” ማቴ 28፡3

በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ የቅዱሳን መላእክትን ሁኔታ ከሚያመለክቱ ብዙ ጥቅሶች ውስጥ ሁለቱ ከላይ በመጥቀስ ብቻ የመላእክትን ብርሃናዊነት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

*መላእክት ስንት ናቸው?*

የመላዕክቶችን ቁጥር በተመለከተ በመፅሃፍ ቅዱስም ሆነ በአዋልድ መፅሃፍት ከበቂ በላይ የሆነ መረጃ አለ፡፡ ይህ ጥያቄ ሲነሳ አብዛኛው ጊዜ የሚጠቀሰው ነብዩ ዳንኤል በትንቢቱ ላይ የጠቀሰው ነው፡፡

“ሺህ ጊዜ ያገለግሉት ነበር፡፡ እልፍ አእላፋትም በፊቱ ቆመው ነበር፡፡” ዳን 7፡10

ከላይ ባለው ጥቅስ ውስጥ “እልፍ” የሚለው ቃል ነብዩ ዳንኤል በፃፈበት በእብራይስጥኛ ቋንቋ አስር ሺህ ማለት ሲሆን “አእላፍ” የሚለው ሲጨመርበት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እንደሆኑ እንረዳለን፡፡ ይህንንም ከላይ የተጠቀሰውን የነብዩ ዳንኤል ጥቅስ ላይ በመመስረት ቤተ-ክርስቲያናችን በቅዳሴ ጎርጎርዮስ፡

“የሺህ ሺዎች በፊትህ ይቆማሉ፡፡ አስር ሺሕ ጊዜ አስር ሺሕዎች ለአንተ አገልግሎታቸውን ያቀርባሉ፡፡” በማለት ታመሰግናለች፡፡

በራዕየ ዮሃንስ ላይም ስለቁጥራቸው

“አየሁም ፣ በዙፋኑም በእንስሶቹም በሽማግሌዎቹም ዙሪያ የብዙ መላዕክትን ድምፅ ሰማሁ ፤ ቁጥራቸውም አእላፋት ጊዜ አእላፋትን ሺህ ጊዜ ሺህ ነበር፡፡” በማለት በራዕይ 5፡11 ላይ ገልፆታል፡፡ ይህንን ሁሉ መረጃ የሚያጠቃልልን ነብዩ ኤርሚያስ ሲሆን በትንቢተ ኤርሚያስ ምዕራፍ 33 ቁጥር 22 ላይ “የሰማይን ሰራዊት የምድርንም አሸዋ መስፈር አይቻልም” በማለት ብዛታቸውን ገልፆታል፡፡

*መኖሪያቸውስ የት ነው?*

መላእክት የት ነው የሚኖሩት ተብሎ ሲጠየቅ ‹በሰማየ ሰማያት› ብቻ ብሎ ማለፉ በቂ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ተጨማሪ ማብራሪያ የሚያስፈልግ ከሆነም መጥቀሱ አስቸጋሪ አይሆንም፡፡
ከሰው ፍጥረት ጀምሮ እስከ ሃዋርያት ስርጭት ድረስ ያለውን የ አራት ሺህ አመት ታሪክ በሙሉ ከአንድ ሺህ በማይበልጡ ገፆች ውስጥ ለመፃፍ ምን ያህል ነገር መቀነስ እንደነበረበት ለመገመት አይከብድም፡፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ የሰውን ልጅ ለእምነት ይበቃ ያህል ተደርጎ ተፅፏል፡፡ አንድ ሰው ተጨማሪ እውቀት ማግኘት ከፈለገ ደግሞ አዋልድ መፅሃፍትን በማንበብ የሚያስፈልገውን መረጃ ማግኘት ይችላል፡፡ የመላእክት መኖሪያ የት ነው የሚለውን እና መሰል ጥያቄዎችን አብራርቶ መመለስ ካስፈለገም ታዲያ እያንዳንዱን የስነ-ፍጥረት ሂደት አንድም ሳይቀር የሚያብራራውን ‹‹መፅሃፈ አክሲማሮስ›› ማየቱ ግድ ይላል፡፡

የመጀመሪያው እለት በሆነችው እለተ እሁድ ከሁለተኛው ሰዓተ ለሊት እስከ ዘጠነኛው ሰዓተ ለሊት ድረስ እግዚአብሄር አምላክ ሰባቱን ሰማያት ፈጥሯል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ከአድማስ እስከ አድማስ የተዘረጉ ሆነው በሰባት የእሳት መጋረጃ የተጋረዱ እና በእሳት አጥር የታጠሩ ኢዮር ፣ ራማ እና ኤረር ተብለው የሚጠሩት ሰማያት ዓለመ-መላእክት ወይም የመላእክት ከተሞች በመባል ሲጠሩ የቅዱሳን መላእክት መኖሪያም በነዚህ ስፍራዎች ነው፡፡

*ቅዱሳን መላዕክት በስንት ይከፈላሉ?*

ቅዱሳን መላዕክት ለእግዚአብሄር የሚያገለግሉ በመሆናቸው አንድ ቢሆኑም ለአምላክ እንደሚሰጡት አገልግሎት አይነት (በተግባራዊ ተልዕኮ) በአስር ይከፋፈላሉ፡፡ መኖሪያቸውም በሶስቱ የመላእክት ከተሞች ውስጥ ነው፡፡ ከመቶው ነገድ ውስጥ አርባው በኢዮር ፣ ከተቀሩት ስድሳ ነገዳት ደግሞ ሰላሳው በራማና ሰላሳው ደግሞ በኤረር ይኖራሉ፡፡ በከተማቸው አርገን እንመልከታቸው፡፡

1. ኢዮር፡ ከመቶ የመላእክት ነገድ ውስጥ አርባው ነገድ የሚኖሩት በዚህ ከተማ ነው፡፡ የኢዮር ከተማ በአራት የተከፈለች ስትሆን አርባውም ነገድ መላእክት ለአራት ተከፍሎ የመጀመሪያው አስር ነገድ በመጀመሪያው የኢዮር ከተማ ፣ ሁለተኛው አስር ነገድ በሁለተኛው ከተማ ፣ ሶስተኛው አስር ነገድ በሶስተኛው ከተማ ሲኖሩ አራተኛው አስር ነገድ ደግሞ በአራተኛው ከተማ ይኖራሉ፡፡

• አጋዕዝት፡ በመጀመሪያው የኢዮር ከተማ የሚኖሩት አስር ነገዶች መጠሪያ ሲሆን የጥንት አለቃቸውም ሳጥናኤል ነበር፡፡

• ኪሩቤል፡ በሁለተኛው የኢዮር ከተማ የሚኖሩት አስር ነገዶች መጠሪያ ነው፡፡ የሰውና የአንበሳ መልክ ሲኖራቸው ዓይናቸው እንደ ነብር ቆዳ ዥንጉርጉር ሆኖ እንደ መስታወት ልሙጥ ነው፡፡ ተልዕኳቸውም የስላሴን መንበር መሸከም ሲሆን አለቃቸውም ኪሩብ ነው፡፡

• ሱራፌል፡ በሶስተኛው የኢዮር ከተማ የሚኖሩት አስር ነገዶች መጠሪያ ነው፡፡ የንስር እና የላም መልክ አላቸው፡፡ እነዚህ ባለስድስት ክንፍ መላእክት ልክ እንደ ኪሩቤል ሁሉ ተልዕኳቸው የስላሴን መንበር መሸከም ነው፡፡ አለቃቸውም ሱሪፍ ነው፡፡

• ሃይላት፡ በአራተኛው የኢዮር ከተማ የሚኖሩት አስር ነገዶች መጠሪያ ነው፡፡ ተልዕኳቸው በመንፈሳዊ ሃይል የዛሉና የደከሙ ክርስቲያኖችን ማበርታት ሲሆን አለቃቸውም ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡

2. ራማ፡ ከመቶው የመላእክት ነገድ ውስጥ አርባው በኢዮር ከተማ ከሰፈረ ቦሃላ እግዚአብሄር አምላክ ራማን ለሶስት ከፈለ፡፡ ከዛም ከተቀሩት ስድሳ የመላእክት ነገዶች ውስጥ ሶስቱን ወስዶ የመጀመሪያውን አስር ነገድ በላይኛው የራማ ከተማ ፣ ሁለተኛውን አስር ነገድ በሁለተኛው ፣ ሶስተኛውን አስር ነገድ ደግሞ በሶስተኛው የራማ ከተማ አስቀመጠ፡፡

• አርባብ፡ በመጀመሪያው የራማ ከተማ የሚኖሩት አስር ነገዶች መጠሪያ ነው፡፡ ‹አርባብ› የሚለው ቃል የሚሸፍኑ ወይም የሚጋርዱ የሚል ትርጉም ሲኖረው ተልዕኳቸውም የእግዚአብሄርን መንበር መሸፈን አልፎም ደግሞ የሰው ልጅ ከሚሰነዘርበት የጠላት ሃይል ይድን ዘንድ መጠበቅ ነው፡፡ አለቃቸውም ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡

• መናብርት፡ በሁለተኛው የራማ ከተማ የሚኖሩት አስር ነገዶች መጠሪያ ነው፡፡ ‹መናብርት› የሚለው ቃል በብርሃናዊ ቦታ የሚቀመጡ ማለት ሲሆን ተልዕኳቸውም የሰው ልጆችን ችግር ወደ እግዚአብሄር ዘንድ ማቅረብ ነው፡፡ አለቃቸውም ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡

• ስልጣናት፡ በሶስተኛው የራማ ከተማ የሚኖሩት አስር ነገዶች መጠሪያ ነው፡፡ ተልዕኳቸው መላው ፍጥረታትን መጠበቅ እና መላእክትን ለፀሎት ማትጋት ሲሆን የምፅዐት ቀን አብሳሪዎችም ናቸው፡፡ አለቃቸውም ቅዱስ ሱርኤል ነው፡፡

3. ኤረር፡ እግዚአብሄር አምላክ የኤረርን ከተማ ለሶስት ከከፈለ ቦሃላ የቀሩትን ሰላሳ ነገደ-መላእክት በሶስት ከፍሎ የመጀመሪያውን አስር ነገድ በመጀመሪያው የኤረር ከተማ ፣ ሁለተኛውን አስር ነገድ በሁለተኛው የኤረር ከተማ ፣ ሶስተኛውን አስር ነገድ ደግሞ በሶስተኛው የኤረር ከተማ አስቀመጠ፡፡

• መኳንንት፡ በመጀመሪያው የኤረር ከተማ የሚኖሩት አስር ነገዶች መጠሪያ ነው፡፡ እነዚህ ነገድ መላዕክት ተልዕኳቸው በተለይም በአደጋ ጊዜ የሰው ልጆችን መጠበቅ ነው፡፡ ሰዶምና ገሞራ በጠፉ ጊዜ ሎጥን ያዳኑትም የዚሁ ነገድ አባላት የሆኑ መላዕክት ናቸው፡፡ አለቃቸውም ቅዱስ ሰዳካኤል ነው፡፡

• ሊቃናት፡ በሁለተኛው የኤረር ከተማ የሚኖሩት አስር ነገዶች መጠሪያ ነው፡፡ በሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ የሚመሰሉት እነዚህ ነገደ መላዕክት ተልዕኳቸው በጽርሃ አርያም ባለው ቤተመቅደስ ውስጥ ማገልገል ነው፡፡ አለቃቸውም ቅዱስ ሰላታኤል ነው፡፡

• መላእክት፡ በሶስተኛው የኤረር ከተማ የሚኖሩት አስር ነገዶች መጠሪያ ነው፡፡ ተልዕኳቸውም ምድር የተሸከመችውን አምላካዊ ፍጥረት በሙሉ መጠበቅ ሲሆን አለቃቸውም ቅዱስ አናንኤል ነው፡፡

*ሊቀ-መላእክቶቹ ከአምላክ ቀጥሎ ታዛዥነታቸው ለማን ነው?*

ከመላዕክት ነገድ ሁሉ ቀድሞ የተፈጠረው የአጋዕዝት ነገድ ሲፈጠር አለቃ ተደርጎ የተሾመው ሳጥናኤል ነበር፡፡ ቦሃላ ግን ‹ፈጣሪያችሁ እኔ ነኝ› የሚለውን ክህደት ከተናገረ ቦሃላ እና በተደጋጋሚ ንስሃ እንዲገባ የተሰጠውን እድል አልጠቀምም ብሎ አሻፈረኝ ካለ ቦሃላ ፀጋው ተገፎ ከክብሩ ሊዋረድ ችሏል፡፡ በዚህን ጊዜ ታድያ በቦታው የሃይላት ነገድ አለቃ የነበረው ቅዱስ ሚካኤል ተሹሟል፡፡ ሌሎቹ ሊቀ-መላእክት አዛዥነታቸው በአንድ ነገድ ላይ ቢሆንም ሊቀ-መላዕክት ቅዱስ ሚካኤል ግን በሁሉም ነገዶች ላይ አልፎም ደግሞ በሌሎቹ ሊቀ መላዕክቶችም ላይ የአዛዥነት ስልጣን አለው፡፡ ለዛም ነው ‹‹ሊቀ ሊቀ-መላእክት ቅዱስ ሚካኤል›› ተብሎ የሚጠራው፡፡

*ሊቀ-መላዕክቶቹ በየራሳቸው ልዩ የሚያረጋቸው ምንድነው?*

ሊቀ-መላዕክቶቹ በአንድነት እግዚአብሄርን በትህትና ያመሰግናሉ፡፡ በሚያዛቸውም ጊዜ ከላይኛው ሰማይ ጽርሃ-አርያም እስከ ጥልቁ ሲኦል ባርባሮስ ድረስ ከአይን ጥቅሻ በፈጠነ ደርሰው ትእዛዛቸውን ይፈፅማሉ፡፡ ታዲያ በአንድነት ቢያመሰግኑም የራሳቸው ልዩ የሚያረጋቸው ነገር አላቸው፡፡ በራዕየ ዮሃንስ ላይ በሰባት ብርሃናት የተመሰሉት ሰባቱ ሊቀ-መላዕክት እና ልዩ የሚያረጓቸው ነገሮች የሚከተሉት ናቸው፡፡

1. ሊቀ ሊቀ-መላዕክት ቅዱስ ሚካኤል፡ ‹‹ሚካኤል›› የሚለው ስሙ ትርጉም ‹ማን እንደ እግዚአብሄር› ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ሚካኤል በእርጋታው እና በፈጥኖ ደራሽነቱ ይታወቃል፡፡ በራዕየ ዮሃንስ ላይም የሰማይ ሰራዊትን በመምራት ዲያብሎስን ድል የሚያደርግ መላዕክ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ከሌላው በተለየ ቤተ-ክርስቲያንን በመጠበቅ የሚታወቅ መላዕክ ነው፡፡

2. ሊቀ መላዕክት ቅዱስ ገብርኤል፡ ‹‹ገብርኤል›› የሚለው ስሙ ትርጉም ‹የእግዚአብሄር ሃይል› ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ገብርኤል አስፈላጊ መልዕክቶችን በማድረስና የተረበሹትን በማረጋጋት ይታወቃል፡፡ የመላእክት ነገዶች በሰማይ በተረበሹ ጊዜ ሰላም እንዲፈጥሩ ያደረገ እና እንኳን ሰውን መላዕክትን ጭምር የሚያፅናና መላዕክ ነው፡፡ ከኖህ ጥፋት ውሃ በፊት ታላላቅ ሃጥያት የሰሩትን ያጠፋ እና የቀሩትንም ያሳደደ መላዕክ ነው፡፡ ከሌላው በተለየ መልኩ በአረጋጊነቱ ይታወቃል፡፡

3. ሊቀ መላዕክት ቅዱስ ሩፋኤል፡ ‹‹ሩፋኤል›› የሚለው ስሙ ትርጉም ‹እግዚአብሄር ፈዋሽ ነው› ማለት ነው፡፡ ከኖህ የጥፋት ውሃ በፊት ከሰማይ ወርዶ ሃጥያትን ለሰው ልጆች ያስተማረውን አዛዝኤልን አስሮ ወደ ጭለማ ያጋዘው መላዕክ ሲሆን ‹‹የንስሃው መላዕክ›› ተብሎም ይጠራል፡፡ ይህ የመንገደኞች መሪ የተባለው መላዕክ ከሌላው በተለየ መልኩ ግን ለንስሃ በማቅናት እና በፈዋሽነቱ ይታወቃል፡፡

4. ሊቀ መላዕክት ቅዱስ ሱርኤል፡ ‹‹ሱርኤል›› የሚለው ስሙ ትርጉም ‹የእግዚአብሄር ትእዛዝ› ማለት ነው፡፡ የምፅአት ቀን አብሳሪ የሆኑት መላዕክት መሪ ነው፡፡ ከሌላው በተለየ መልኩ የእግዚአብሄርን ትእዛዝ በማስጠበቅ ይታወቃል፡፡

5. ሊቀ መላዕክት ቅዱስ ሰዳካኤል፡ ‹‹ሰዳካኤል›› የሚለው ስሙ ትርጉም ‹የእግዚአብሄር ቅድስና› ማለት ነው፡፡ ይህ የ ‹ይቅርታ መላዕክ› ተብሎ የሚታወቀው ሊቀ-መላዕክ ይቅርታን አብዝተው ለሚያረጉ ሰዎች እንደሚራራ ተፅፏል፡፡ በአንዳንድ ፅሁፎች ዘንድ አብርሃም ልጁን ከመሰዋት ያቆመው ስሙ በመፅሃፍ ቅዱስ ላይ ያልተጠቀሰው መላዕክ እሱ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከሌላው በተለየ መልኩ ይቅርታን በሰዎች ዘንድ በማስረፅ እና ይቅርታ አድራጊዎችን በመራዳት ይታወቃል፡፡

6. ሊቀ-መላዕክት ቅዱስ ሰላታኤል፡ ‹‹ሰላታኤል›› የሚለው ስሙ ትርጉም ‹የእግዚአብሄር ፀሎት› ማለት ነው፡፡ ይህ መላዕክ የሰዎችን ፀሎት ወደእግዚአብሄር የሚያቀርብ ነው፡፡ ከሌላው በተለየ ሰዎችን ለፀሎት በማትጋት እና በራሱም በፀሎት ትጋቱ ይታወቃል፡፡

7. ሊቀ መላዕክት ቅዱስ አናንኤል፡ ‹‹አናንኤል›› የሚለው ስሙ ትርጉም ‹የእግዚአብሄር ዝናብ› ማለት ነው፡፡ ይህ መላዕክ ከሌላው በተለየ ምድርን እና ፍጥረቶቿም በሙሉ በመጠበቅ ይታወቃል፡፡

*መላዕክትን እንዴት እንለያለን?*

አንድ ብርሃናዊ ፍጥረት ተገለጠልን እንበል፡፡ ሰይጣንም ቢሆን የብርሃን መላዕክ መስሎ መገለጥን ይችላልና እውነተኛ የእግዚአብሄር መላዕክት መስሎን ልንሳሳት እንችላለን፡፡ በመሆኑም ቅዱሳን መላዕክትን ልዩ የሚያረጓቸው የራሳቸው መለያ አሏቸው፡፡

• መጎናፀፊያ፡ ቅዱሳን መላዕክት የእግዚአብሄር ፍጥረት መሆናቸውን ያውቁ ዘንድ አምላክ መጎናፀፊያን አድርጎላቸዋል፡፡

• ዝናር፡ ጌታውን የሚያገለግል አገልጋይ ወገቡን ታጥቆ ለተልዕኮ እንደሚፋጠን ሁሉ መላዕክትም የብርሃን ዝናርን ይታጠቃሉ፡፡

• ጫማ፡ ለተልዕኮ መውረድ መውጣት እንዳለባቸው አምላክ ሲያስታውሳቸው ጫማን አድርጎላቸዋል፡፡

• ማህተመ መስቀል ያለበት የብርሃን ዘንግ፡ የሱ ሰራዊቶች መሆናቸውን ያውቁ ዘንድ ባለመስቀል በትርን ሰጥቷቸዋል፡፡

• የብርሃን አክሊል፡ የፀጋ መንግስትን እንደሚያወርሳቸው ሲነግራቸው የብርሃን አክሊልን አጥልቆላቸዋል፡፡

ቅዱሳን መላዕክትን በእነዚህ ምልክቶች ልንለያቸው እንችላለን፡፡ በተጨማሪም ቅዱሳን መላዕክት ሲገለጡ ከአነጋገራቸው ትህትና እና ከሚሰማን ፍፁም ሰላም ለይተን እናውቃቸዋለን፡፡ በዚህ እውቀቷ የዳነች አንድን ሴት እንመልከት፡፡ የሃይማኖተ ቀንዓው መኮንን አስተራኒቆስ ሚስት የነበረችው አፎምያ ታሞ በነበረበት ጊዜ የቅዱስ ሚካኤልን ምስል አሰርቶ እንዲሰጣት ትለምነዋለች፡፡ እሱም አሰርቶ ይሰጣታል፡፡ ባልዋም ከሞተ ቦሃላ ቀሪ ህይወቷን እግዚአብሄርን በማገልገል ለማሳለፍ የምትፈልገውን አፎሚያን ለማሳሳት ሰይጣን አንዴ ባልቴት ሌላ ጊዜ ደግሞ ባህታዊ እየመሰለ ሊያሳስታት ሞከረ፡፡ እሷ ግን በእምነቷ ፀናች፡፡ በመጨረሻም በቅዱስ ሚካኤል ምስል አዋርዳ ሸኘችው፡፡ እሱም ይህን ይዞ የሰኔ ሚካኤል አለት የብርሃን መላዕክ መስሎ ተገለፆ ‹ሚካኤል› ነኝ አላት፡፡ እሷ ግን አስተዋይ ስለነበረች ‹የብርሃን መላዕክ ከሆንክ ባለመስቀል ብርሃናዊ በትርህ የታለ› ብላ ጠየቀችው፡፡ እሱም ለማሳሳት በማሰብ ‹በኛ በመላዕክት ዘንድ እኮ የመስቀል በትር አይያዝም› አላት፡፡ እሷም ስለተጠራጠረች የቅዱስ ሚካኤልን ምስል ለማምጣት ወደ መኝታ ክፍሏ ስትገባ ዘሎ አነቃት፡፡ ሚካኤልም ከብርሃን በፈጠነ ፍጥነት ደርሶ አዳናት፡፡ ሰይጣንንም አዋረደላት፡፡

*ጠባቂ መላዕክቶች ምንድን ናቸው?*

እግዚአብሄር ለኛ ያለውን ፍፁም ፍቅር የምናውቅበት አንደኛው መንገድ ጠባቂ መላዕክቶች ናቸው፡፡ እግዚአብሄር አምላክ አንድ ሰው ከማህፀን ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ አንድ ጠባቂ መልአክ ለግሉ ያዝለታል፡፡ ታዲያ ይህ ጠባቂ መላዕክ ያ ሰው ከተፈጠረ ጀምሮ ነፍሱ ከስጋው እስከምትለየው ድረስ ለአንድም አፍታ ያህል አይለየውም፡፡ ይህ መላዕክ ሙሉ ጊዜውን የታዘዘለትን ያንን ሰው በመጠበቅ ፣ በማፅናናት እና ለጥሩ ስራ በማትጋት ያሳልፋል፡፡ ይህ መላዕክ ብዙውን ጊዜውን የሚያሳልፈው ደጋግ እና ጥሩ ሃሳቦችን ወደ ታዘዘለት ሰው ልብ በማስረፅ ነው፡፡ እንዚህም ሃሳቦች ወደተግባር ሲቀየሩ ያ መላዕክ ይመዘግበዋል፡፡ ይህ ሰውም በሚሞትበት ጊዜም ያ መላዕክ የተሰሩትን ጥሩ ስራዎች በሙሉ በእግዚአብሄር ፊት ተደፍቶ ይናዘዛል፡፡ ‹‹እንድጠብቃት የሰጠኸኝ ነፍስም ይችውት›› ብሎ በትህትና ያስረክባል፡፡

ይህ ሁሉ በሚደረግበት ጊዜ ግን ዲያብሎስ አያርፍም፡፡ እሱም የራሱን መላዕክ ወደዛ ሰው ይልካል፡፡ ያም የተላከው መላዕክተ ፅልመት ይህንን ሰው እስከህይወቱ ፍፃሜ ድረስ መጥፎ ስራዎችን እንዲሰራ ይመክረዋል፡፡ ያም ሰው በታዘዘ ቁጥር ይህ የፅልመት መላዕክ እየቀረበው ይመጣል፡፡ አልሰማም በማለት ከአምላክ የታዘዘለትን መላዕክ የሚሰማ ከሆነ ደግሞ የብርሃን መላዕክ እየቀረበው ይመጣል፡፡ ለዛም ነው ብዙ ጊዜ መጥፎ ድርጊትን የጀመረ ሰው ይባስ እየዘቀጠ ሲመጣ ጥሩ ስራ የጀመረ ሰው ደግሞ ስራው እያስደሰተው ሲመጣ የሚናስተውለው፡፡

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top