የቅዱሳን መላእክት አማላጅነት

የቅዱሳን መላእክት አማላጅነት

 በዲያቆን ኅብረት የሺጥላ

ቅዱሳን መላእክት አማላጆቻችን ናቸው፡፡ ስለ ቅዱሳን መላእክት አማላጅነት በመጽሐፍ ቅዱስ በስፋት ተጽፏል፡፡ ይህንንም የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በመጥቀስና ትክክለኛ ትርጉማቸውን በምንረዳበት ጊዜ የምናገኘው ነው፡፡

የመላእክትን አማላጅነት በስድስት ዋና ዋና መንገዶች ከፍለን ለማየት እንችላለን፡፡

1ኛ. መቆም የሚለውን ቃል ትክክለኛ ትርጉም በመረዳት፡- መቆም የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በልዩ ልዩ ቦታዎች አገልግሎት ላይ ውሏል፡፡ እንደየአገባቡም ትርጉሙ የተለያየ ነው፡፡ መቆም የሚለው ቃል ከያዛቸው ትርጓሜዎች አንዱ ማማለድ የሚል ነው፡፡ መቆም ከተኙበት ወይም ከተቀመጡበት መነሣት፣ በእግር ቀጥ ማለት፣ መጽናት፣ በክብር መቀመጥ ወዘተ የሚሉ ሌሎች ትርጓሜያትም አሉት፡፡ ስለዚህ እንደየአገባቡ ታይቶ ይፈታል እንጂ ሁል ጊዜ ቃሉን በአንድ ዓይነት መንገድ ብቻ መመልከት ከስሕተት ላይ ይጥላል፡፡

ለዚህ ሁሉ አገባብ ማስረጃ ብትሻ እነዚህንና ሌሎችንም ጥቅሶች በሚገባ ፈትሽ፡፡ ‹‹የደምዋም ፈሳሽ በዚያን ጊዜ ቆመ›.፣ ‹‹የደመናው ዓምድ ቆመ››፣ ‹‹በሃይማኖት ቁሙ›› (ሉቃ8.44፤ ዘዳ31.15፤ ዘኁ10.12፤ 1ቆሮ16.13) በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ መቆም የሚለው ቃል የተለያየ ሐሳብ ይዞ መገኘቱን ልብ ማለት ያሻል፡፡

አሁን ከዚህ ቦታ ከርእሳችን አንጻር እኛ የምንፈልገው ቆመ የሚለው ቃል ማማለድ የሚል ትርጉም ይዞ መገኘቱን መረዳት ነው፡፡ መቆም ሲባል ማማለድ የሚል ትርጓሜ እንዳለው ለመረዳት ስለ ሊቀ ነቢያት ሙሴ የተጻፈውን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ እስራኤላውያን ጣዖት በማምላክ ፈጣሪቸውን አስቆጡት፡፡ እርሱም ሊያጠፋቸው ጀመረ፡፡ ነገር ግን ሙሴ እነዚህን ሕዝቦች ከምታጠፋ እኔን ከሕይወት መጽሐፍ ደምስኝ በማለት በራሱ ፈርዶ አማለዳቸው፡፡ ፈጣሪም የሙሴን ልመና ሰምቶ መዓቱን በትዕግሥት መለሰ፡፡ ይህ ታሪክ በዘፀአት የኦሪት ክፍል ተመዝግቧል፡፡ (ዘፀ32.32)

ይህንን የሙሴ ምልጃ ቅዱስ ዳዊት በሌላ ጊዜ በድጋሚ ተርኮታል፡፡ ይኸውም በዳዊት መዝሙር የምናገኘው ነው፡፡ ነገር ግን አተራረኩ መቆም ማማለድ መሆኑን በግልጽ በሚያሳይ መንገድ ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ያዳናቸውን እግዚአብሔርን ረሱ፡፡ እንዳያጠፋቸው ቁጣውን ይመልስ ዘንድ የተመረጠው ሙሴ በመቅሠፍት ጊዜ በፊቱ ባይቆም ኖሮ ያጠፋቸው ዘንድ ተናገረ፡፡›› የተሰመረበትንና ደምቆ የተጻፈውን ኃይለ ቃል ልብ ብለህ ተመልከት፡፡ (መዝ015.23) ባይቆም ኖሮ ሲል ባያማልዳቸው፣ ባይለምንላቸው፣ ባይጸልይላቸው ኖሮ ማለቱ ነው፡፡ ስለዚህ መቆም የሚለው ቃል ማማለድ የሚል ትርጉም እንደሚኖረው እንረዳለን፡፡

ዳግመኛም መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹የእግዚአብሔር ልጆች (መላእክት) በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም መጡ፡፡ ሰይጣንም ደግሞ በመካከላቸው መጣ›› ይለናል፡፡ ‹‹ለመቆም›› ሲል ለመለመን፣ ለማማለድ ማለት ነው፡፡ አብሮአቸውም ሰይጣን መምጣቱን ልብ በል፡፡ ሰይጣን የመጣው ለምን ነበር? ጻድቁ ኢዮብን ለመፈተን ፈቃድ ያገኝ ዘንድ ፈጣሪውን ለመለመን አልነበረምን? የመላእክትም አመጣጥ ፈጣሪቸውን ስለሰው ለመለመን እንጂ ለሌላ አልነበረም፡፡ ይህን ሲገልጥ ‹‹ለመቆም መጡ›› ይለናል፡፡ መቆም መለመን፣ ማማለድ ማለት ነውና፡፡ (ኢዮ1.6)

መቆም ማለት መጸለይ፣ ማማለድ የሚል ፍቺ እንዳለው ካስጨበጡ በኋላ ይህንን ቃል በመጠቀም የመላእክትን አማላጅነት ማስረዳት ቀላል ይሆናል፡፡

ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እኛ ከምናውቀው ውጭ አንዳንድ ጊዜ በተቃራኒ አቅጣጫም እንኳን ፍቺ ይዘው ይገኛሉ፡፡ አገባባቸውን እንደመጽሐፍ ቅዱስ ዘይቤና ምሥጢር መማር የሚያስፈልገው ከዚህ የተነሣ ነው፡፡ ለብዙ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ የተቀመጡ ቃላትን ትክክለኛ መንፈስ አለመረዳት የመላእክትን አማላጅነት እንዳይረዱ አድርጓቸዋልና፡፡

ለምሳሌ፡- ቅዱስ ገብርኤል ራሱ ‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው መልአኩ ገብርኤል ነኝ፡፡›› በማለት ተናግሯል፡፡ ይህም በቅዱስ ወንጌል የተጻፈ ኃይለ ቃል ሲሆን አብዛኞቻንን እናውቀዋለን፡፡ ልዩ የሚሆነው ግን የቃሉን ትክክለኛ አገባባዊ ትርጉም ባለማወቃችን ምክንያት መልአኩ ይህን ባለ ጊዜ ‹‹እኔ አማላጅ ነኝ›› እንዳለን አድርገን አለመረዳታችን ነው፡፡ መቆም ማለት ማማለድ የሚል ትርጉም ካለው ‹‹በእግዚአብሔር ፊት የምቆም›› ማለት ደግሞ ‹‹የማማልድ›› ማለት መሆኑ አይጠረጠርም፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ገብርኤል አማላጅነቱን ራሱ ግልጽ በሆነ መንገድ ነግሮናል ማለት ነው፡፡

እስኪ እናንተ ፍረዱ! በዚህ ስፍራ ቅዱስ ገብርኤል አማላጅ ነኝ ማለቱን ካላመንን ‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው›› ማለቱን ምን ብለን እንረዳዋለን? የእግዚአብሔር ፊቱ ወደ ሁሉም አቅጣጫ ነው እንጂ እንደፍጡር ወደ አንድ ገጽ የተወሰነ አይደለም፡፡ መላእክት ደግሞ በተፍጥሯቸው እንደ ሰው ልጅ የሚታጠፍና የሚዘረጋ እግረ ሥጋ ስለሌላቸው አይቀመጡም፤ አይተኙምም፡፡ ታዲያ አማላጃችሁ ነኝ ማለቱ ካልሆነ በቀር መልአኩ ‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው›› ሲል ምን ማለቱ ነው? መልአኩ እግዚአብሔርን እንደ ምድራዊ ንጉሥ ራሱን ደግሞ እንደ ንጉሥ ወታደር ቆጥሮ በንጉሡ ፊት ቀጥ ብዬ የምውል ዘበኛ ነኝ ማለቱ ነውን? በፍጹም አይደለም፡፡ በእግዚአብሔር ቤት ደጅ አፍ መቆምና በእግዚአብሔር ፊት መቆም ሁለት የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ምሥጢራቸውም እንዲሁ የተለያየ ነው፡፡ (ራእ21.12፤ ዘፍ3.24) ይልቅ ሊሆን የሚችለው እኔ በፊቱ ባለሟልነት ያለኝ ሁሉ ጊዜ ስለ እናንተ የማማልድ ነኝ የሚል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

መልአኩ በእግዚአብሔር ፊት የሚቆመው ለምንድን ነው? ለማመስገን ነው እንዳንል ይህንን ሐሳብ ለካህኑ ለዘካርያስ መንገር ለምን አስፈለገው? የሚል ጥያቄ ያስነሣል፡፡ ትርጉሙ እንዲህ ቢሆን ወደ ካህኑ ወደ ዘካርያስ ከመጣበት ጉዳይ ጋር ንግግሩ ምንም ግንኙነት አይኖረውምና ይህን መናገር አያስፈልገውም፡፡ ከዚህ ይልቅ እኔ ሰዎችን ሁሉ ለማማለድ በእግዚአብሔር የምቆም ባለሟልነት ያለኝ መልአክ በመሆኔ የለመንከው ልመና መድረሱን የምሥራች ልነግርህ ብመጣ ቃሌን እንዴት ትጠራጠራለህ? ለማለት ‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው መልአኩ ገብርኤል ነኝ›› በማለት መልአኩ ይህን ተናገረ ብንል ከሁሉ በላይ የሚያስኬድና ለአእምሮ የሚመች ትክክለኛ ትርጓሜ ነው፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ስለ ቅዱስ ሚካኤልም በትንቢተ ዳንኤል ላይ እንዲህ ተጽፏል፡፡ ‹‹በዚያ ወራት ስለ ሕዝብ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል›› ይላል፡፡ (ዳን12.1) በዚህ ጥቅስ ቅዱስ ሚካኤል ‹‹ስለ ሕዝብ ልጆች የሚቆመው›› ተብሏል፡፡ እረ ለመሆኑ ቅዱስ ሚካኤል ስለ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት ‹‹የሚቆመው›› ለምንድር ነው? ለማማለድ አይደለምን? ይህን ካልተቀበልን ቃሉን ምን ብለን እንተረጉመዋለን? ለማመስገን ይቆማል እንዳንል ቃሉ የሚለው ‹‹ስለ ሕዝብ ልጆች የሚቆመው›› ነው፡፡ ስለ እኛ ጥብቅና ይቆማል እንዳንል ወደ ባሰ ስሕተት ይወስደናል፡፡ ሚካኤል በእግዚአብሔር ፊት ጥብቅና አይቆምምና፡፡ እግዚአብሔርም በጠበቃ የሚሟገቱት አምላክ አይደለምና፡፡ ጥብቅና ይቆማል ከማለት ይልቅ ትክክለኛውና የሚስማማው ወደ ፈጣሪ ሊለምንልን ወይም እኛን ለማማለድ ይቆማል የሚለው ትርጓሜ ነው፡፡ አስቀድሞ እንደተመለከትነው ‹‹መቆም›› የሚለው ቃል ማማለድ የሚል ትርጉም አለውና፡፡

ይህ ለምሳሌ ያህል ተጠቀሰ እንጂ በፈጣሪ ፊት እልፍ አእላፋት መላእክት ለምልጃ ይቆማሉ፡፡ ቅዱስ ዳንኤል ‹‹ሺህ ጊዜ ሺህ ያገለግሉት ነበር፡፡ እልፍ አእላፋትም በፊቱ ቆመው ነበር፡፡›› በማለት የገለጸው ይህንን እውነት ነው፡፡ (ዳን7.9-11)

ከዚህ በላይ ከብሉይ ስለ ቅዱስ ሚካኤል ከሐዲስ ደግሞ ስለ ቅዱስ ገብርኤል የተጻፉት ለማስረጃነት ተጠቅሰዋል፡፡ የተማሩትንና ያነበቡትን በልብ ለመክተብ መላልሶ ማንበብና ማጥናት እንደሚያስፈልግ እሙን ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ብትሻ የቅዱስ ገብርኤል ዝክረ በዓል ወር በገባ በአሥራ ዘጠኝ እንደሚውል ታውቃለህ፡፡ ስለ እርሱም የተጠቀሰው በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 1.19 መሆኑን ልብ በልና ጥቅሱ ከወርኃዊ በዓሉ ጋር ያለውን ዝምድና መርምር፡፡ ማለትም ቁጥር 19 ላይ መጻፉን አስተውል፡፡ ስለ ቅዱስ ሚካኤልም እንዲሁ አድርግ፡፡ ጥቅሱ በትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ 12 ላይ ይገኛል፡፡ የቅዱስ ሚካኤል ወርአዊ ክብረ በዓሉም በ12ኛው ቀን ላይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ጽንሰ ሐሳብ፡- መቆም ማማለድ ማለት ይሆናል፡፡ የዚህ ማስረጃው (መዝ105.23፤ ኢዮ1.6) ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ መላእክት ስለ እኛ በፈጣሪ ፊት ይቆማሉ ማለት ያማልዳሉ ማለት ነው፡፡

  1ኛ.ሉቃ1.19    2ኛ.ዳን12.1     3ኛ.ዳን7.9-11

መቆም እንደሚለው ቃል ሁሉ ‹‹ማየት›› የሚለው ቃልም በመጽሐፍ ቅዱስ የራሱ የሆነ አገባባዊ ፍቺ አለው፡፡ በዓይን መለማመጥ፣ ማሳዘን፣ መቆጣት፣ ተስፋ ማድረግ እና ማስፈራራት ይቻላል፡፡ ‹‹የሁሉ ዓይን አንተን ተስፋ ያደርጋል፡፡›› እንዲል፡፡ (መዝ 144.15) ስለዚህ ‹‹ማየት›› መመርመር ወይም ንስሐ መግባት፣ መለመን፣ መጸለይ፣ ተስፋ ማድረግ፣ ማማለድ፣ መስማት፣ መቀበል፣ መቆጣት ወዘተ የሚሉ ፍቺዎች አሉት፡፡

በተለይ ከእግዚአብሔር አንጻር ካየነው ማየት የሚለው ቃል መስማት፣ መቀበል፣ ይቅር ማለት የሚል ትርጉም ይይዛል፡፡ “እግዚአብሔር እገሌን በዓይነ ምሕረት አየው” ማለት አሰበው፣ ጎበኘው፣ ማረው፣ ሰማው ፣ ይቅር አለው ማለት ይሆናል፡፡ እንደ አገባቡ ተቆጣው ማለትም ሊሆን ይችላል፡፡ ለጠቀስናቸው ሐሳቦች ከመጽሐፍ ቅዱስ ‹‹እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፡፡››፤ ‹‹እነሆ የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደሚፈሩት ናቸው፡፡››፤ ‹‹የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮውም ወደ ጩኸታቸው ነው፡፡›› የሚሉትን ማስረጃዎች መመልከት ብቻ እንኳን ይበቃል፡፡ (ዘፍ 4.4፤ መዝ 32.18፤ 33.15)

“ማየት” የሚለውን ቃል ከሰው አንጻር ወይም ከፍጥረት ሁሉ አንጻር ካየነው ደግሞ ሌሎች ፍቺዎች ይኖሩታል፡፡ ‹‹አቤቱ አምላኬ እየኝ ስማኝም፡፡›› ሲል ማረኝ ለማለት ነው፡፡ “ማየት” መመርመር ሲሆን ‹‹ራስህን ለካህን አሳይ›› ይላል፡፡ ይህ ደግሞ ራስህን አስመርምር፣ ንስሐ ግባ ማለት ነው፡፡ (ማቴ8.4፤ መዝ12.3) በእንግሊዝኛውም ይህን የመሰለ ነገር አለ፡፡ ነጮቹ ሕክምና ላድርግ ወይም ልመርመር ለማለት ‹‹ሐኪሜን ልይ›› ይላሉ፡፡

ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ‹‹ማየት›› የሚለውን ቃል ትርጉም በትክክል በመረዳት የመላእክትን አማላጅነት በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡

ለሰው ልጆች በሙሉ ለየራሳቸው ጠባቂ መላእክት አሏቸው፡፡ ይህንንም ያደረገው ፈጣሪ ነው፡፡ ‹‹መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና›› የሚለው የነቢዩ የዳዊት መዝሙር ፈጣሪ ለሰው ልጆች የሚጠብቋቸው መላእክትን እንዳዘጋጀ ያስረዳል፡፡ (መዝ90.11) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌያዊ ትምህርቱ ለበለሱ አትክልተኛ መቅጠሩ በበለስ ለተመሰሉ የሰው ልጆች ለእያንዳንዳቸው ጠባቂና ተንከባካቢ መልአክ ማዘጋጀቱን የሚያስረዳ ነው፡፡ (ሉቃ13.6-9) በትንቢተ ዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ መልአኩ ‹‹ቅዱስ ጠባቂ›› የተባለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ (ዳን4.13፤ 4.23) በተጨማሪም ለሰው ልጆች ሁሉ ጠባቂ መልአክ እንዳላቸው በወንጌል ‹‹መላእክቶቻቸው›› በሚል የተቀመጠው ቃል ብቻ ምስክር ነው፡፡ (ማቴ18.10)

መላእክት እንደ ታላላቅ ወንድሞቻችን የምንቆጥራቸው እነርሱም ደግሞ እኛን እንደ ታናናሽ ወንድሞቻቸውና እኅቶቻቸው የሚያዩን ቤተሰቦቻችን ናቸው፡፡ እነርሱ ከእኛ በፊት በዕለተ እሑድ የተፈጠሩ የአምላክ ልጆች ሲሆኑ እኛ ደግሞ በዕለተ ዐርብ የተፈጠርን የእግዚአብሐር ልጆች ነንና፡፡ (ኢዮ1.6፤ 2.1፤ ዮሐ1.12) የአንድ አባት ልጆች ደግሞ ወንድሜ እኅቴ እንደሚባባሉ የታመነ ነው፡፡ ስለዚህ መላእክት እየሳሱ ይጠብቁናልና እኛ የእነርሱ ገንዘብ ነን፡፡ እነርሱም የእኛ ገንዘቦች በመሆናቸው ‹‹መላእክቶቻቸው›› ተብለዋል፡፡ ይህም ከወንጌሉ ትረካ የምናታገነው ነው እንጂ በብልሃት የተፈጠረ ቃል አይደለም፡፡

እነዚህ ጠባቂ መላእክት ስለ ሰው ልጅ የእግዚአብሔርን ፊት እንደሚያዩ ወንጌል ይናገራል፡፡ ‹‹መላእክቶቻቸው ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉና›› እንዲል፡፡ (ማቴ18.10) ይህም ዐረፍተ ነገር ያለ ምንም ጥርጥር የመላእክትን አማላጅነት የሚያሳይ ነው፡፡ ማየት መጸለይ ማማለድ የሚል ትርጉም እንዳለው ቀደም ሲል በሚገባ ተቀምጧልና፡፡ ካልሆነ ግን በምን ሊተረጎም ይችላል? የጥቅሱን ሙሉ ሐሳብ ስንወስድ ሰዎችን አትናቁ! የምትንቋቸውን ሰዎች የሚጠብቁ መላእክት ዘወትር የአባቴን ፊት ያያሉ የሚል ነው፡፡ ይህም ለተናቁት ሰዎች ለምነው ያማልዷቸዋል፡፡ የምትንቁትን እናንተን ደግሞ ጸልየው ያስፈርዱባችኋል የሚል ማስጠንቀቀቂያ ቃል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ጽንሰ ሐሳብ፡- “ማየት” መጸለይ፣ ማማለድ፣ መስማት፣ መቀበል፣ ይቅርታ ማድረግ ማለት ይሆናል፡፡ እንዲህ ከሆነ መላእክት ስለ እኛ የፈጣሪን ፊት ያያሉ ማለት ያማልዳሉ ማለት ነው፡፡

1ኛ. “ማየት” መስማት፣ መቀበል ሲሆን በፈጣሪ አንጻር (ዘፍ4.4፤ መዝ32.18፤ 33.15)

2ኛ.”ማየት” መጸለይ፣ ማማለድና ይቅርታ መጠየቅ ሲሆን ከፍጡር አንጻር (ማቴ18.10፤ ማቴ8.4፤ መዝ12.3)

‹‹አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ›› ያለው የትንቢት ቃል ይፈጸም ዘንድ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው በምሳሌ አስተምሯል፡፡ /መዝ77.2/ በምሳሌ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል አንዱ የመላእክትን አማላጅነት የሚያሳይ ነው፡፡ ሙሉ የወንጌሉ ቃል ከዚህ ቀጥሎ የምናነበው ሲሆን ነጥቦቹን አንድ በአንድ እንመለከታለን፡፡

“ይህንም ምሳሌ አለ። ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው፥ ፍሬም ሊፈልግባት መጥቶ ምንም አላገኘም። የወይን አትክልት ሠራተኛውንም። እነሆ፥ ከዚህች በለስ ፍሬ ልፈልግ ሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም አላገኘሁም፤ ቍረጣት፤ ስለ ምን ደግሞ መሬቱን ታጐሳቍላለች? አለው። እርሱ ግን መልሶ፦ ጌታ ሆይ፥ ዙሪያዋን እስክኰተኵትላትና ፋንድያ እስካፈስላት ድረስ በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት።ወደ ፊትም ብታፈራ፥ ደኅና ነው፤ ያለዚያ ግን ትቈርጣታለህ አለው።” /ሉቃ13.6-9/

ይህን ቃል ጽፎ ያቆየልን ሐዋርያ ቅዱስ ሉቃስ ቢሆንም ትምህርቱን ያስተማረው ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ‹‹ይህንም ምሳሌ አለ›› ብሎ ታሪኩን በመጀመሩ ትምህርቱ ምሳሌያዊ መሆኑን ለመረዳት አያስቸግርም፡፡

የበለሲቱ ጌታ /ባለቤት/ ከአንድም ሁለት ሦስት ጊዜ ተመላልሶ ፍሬ ቢፈልግባት ምንም ስላላገኘባት እንድትቆረጥ ለሠራተኛው ጥብቅ ትእዛዝ ሰጠ፡፡ በዚህ ጊዜ ሠራተኛው በፍጥነት ሊቆርጣት ይችል ነበር፡፡ ያን ቢያደርግም በጌታው ዘንድ  ሊመሰገን ይችላል፡፡ ምክንያቱም የታዘዘውን አድርጓልና፡፡

ነገር ግን ጌታውን ‹‹በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት›› በማለት ስለ በለሲቱ ለመነላት፡፡ አማለዳት ማለት ነው፡፡ ለሌላ ወገን የሚደረግ ልመና ምልጃ ነውና፡፡ የሚገርመው ደግሞ በለሲቱ እንዲለምንላት አልተማጸነችም፡፡ ሠራተኛው በራሱ ደግነት በፈቃዱ ተነሣስቶ ለመነላት እንጂ፡፡ ብትለምነው ደግሞ የበለጠ ሊያደርግ እንደሚችል መረዳት አያዳግትም፡፡ ሊያማልድ ያልተዘጋጀ ወይም ያላሰብ ሰው እንኳን እባክህ አማልደን ብለው ሲልኩት እምቢ እንደማይል ሁሉ ይህ ሠራተኛ ቢለመን የበለጠ ሊያደርግ መቻሉ እሙን ነው፡፡

የበለሲቱም ጌታ የቀጠርኩህ እንድትታዘዘኝ እንጂ እንድትለምነኝ አይደለም ሳይል የሠራተኛውን ምልጃ ተቀበለ፡፡ ይህም ምልጃ ተቀባይ ጌታ መሆኑን ያሳያል፡፡

ምሳሌው እንዴት እንደሚተረጎም እንመልከት፡- የበለሷ ጌታ /ባለቤት/ ፈጣሪ እግዚአብሔር ነው፡፡ በለሲቱ ደግሞ እስራእላውያንን ቀጥሎም የሰውን ዘር በሙሉ ያመለክታል፡፡ ሠራተኛ የተባለውም ሰውን የሚጠብቅ መልአክ /ዑቃቢ መልአክ/ ነው፡፡ ከበለሲቱ በተስፋ የተጠበቀው ፍሬ ደግሞ ከሰው ዘር በሙሉ ፈጣሪ የሚፈልገው የቀና ሃይማኖትና መልካም ምግባርን ነው፡፡ ሦስት ጊዜ ተመላልሶ ፍሬ ማጣቱ ፈጣሪ በታዳጊነት፣ በወጣትነትና በጎልማስነት ጊዜ ሁሉ ፍሬ እንደሚፈልግብን ያሳያል፡፡ ‹‹ቁረጣት›› ማለቱ ፍሬ ሲያጣብን ያለ ዕድሜም መቀሠፍ እንዳለና ሞት እንደሚፈረድብን ያሳያል፡፡ በአጠቃላይ ይህ ሠራተኛ ለበለሲቱ እንደለመነላት መላእክትም ለእኛ እንደሚለምኑልን እንደሚያማልዱን ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን መመልከት አለብን፡፡ ይህን ካልተቀበልን ምን ብለን ልንተረጉመው ነው? ‹‹ቅዱስ ጠባቂ›› የሚባል መልአክ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ /ዳን4.13፤4.23/ እንዲጠብቁንም ያዘዛቸው ፈጣሪ ነው፡፡ ‹‹መላእክቱን ስለ አንተ ያዛቸዋል፡፡›› ተብሏልና፡፡ /መዝ90.11/

ይህ ምሳሌያዊ ትምህርት በርካታ መልእክቶችን ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡ እያንዳንዱ ቃልና ዐረፍተ ነገርም ብዙ ምሥጢር ይዟል፡፡ የእኛ ርእስ ግን ስለ ምልጃ ስለሆነ በዚህ እንወሰናለን፡፡ ይሁን እንጂ ጎላ ያለ ጥያቄ መልሶ ለማለፍ ያህል አንድ ሰው የበለሲቱ ባለቤት ‹‹ትቆረጥ›› ሲል ሠራተኛው ደግሞ ‹‹በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት›› ማለቱ ለበለሲቱ ከባለቤቱ ይልቅ ሠራተኛው ያዘነላት አያስመስልም? ሊል ይችላል፡፡

ለበለሲቱ ከሠራተኛው ይልቅ ያዘነላት ጌታዋ ነው እንጂ ሠራተኛው አይደለም፡፡ እንዴት ቢባል ጌታዋ ከአንድም ሦስት ጊዜ ሳይቆርጣት አልፎአታል፡፡ በተጨማሪም ሠራተኛው የለመነላት ለአንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ እንዲያው ከዚያ በኋላ ካላፈራች ‹‹ትቆርጣታለህ›› ሲል ተናገረ፡፡ ጌታዋ ለሦስት ጊዜ የታገሣትን እርሱ ግን አንዴ ከለመነላት በኋላ ብትቆረጥም ቅር እንደማይለው አስረዳ፡፡ ታዲያ ከጌታዋ ይልቅ እርሱ ራራ ለማለት እንዴት ይቻላል? በዚያውም ላይ ያ ሠራተኛ ቢለምንላትም ይቅር ያላት ግን ጌታዋ መሆኑን መርሳት አይገባም፡፡ ከዚህ ሁሉ ጋር እንዲህ አዝኖ የሚያማልዳትን ሠራተኛ ያዘዘላት እኮ ጌታዋ ነው፡፡ በመጨረሻ ትምህርቱ ምሳሌያዊ ነው፡፡ ‹‹ቁረጣት›› ያለው ጌታዋ የፈጣሪ ምሳሌ እንደመሆኑ መጠን ሠራተኛው የሚያቀርብለትን የምልጃ ጥያቄ አስቀድሞ ያውቃልና በለሲቱ እንደማትቆረጥ ያውቅ ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እርሱ በበለሲቷ ላይ ያለውን የማዘዝ ሙሉ ሥልጣን እና የሠራተኛውን ማለትም የጠባቂ መልአኩን የማማለድ ሥራ ሊያሳይ በሚችል መንገድ ምሳሌውን እርሱ ባወቀ መስሎ ተናገረ፡፡

ሀ. ማስታረቅ መንፈሳዊ አገልግሎት ነው፡፡ ይህን የሚክድ ካለም ‹‹የማስታረቅንም አገልግሎት ከሰጠን›› የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ጠቅሰን አፉን እናሲዘዋለን፡፡ (2ቆሮ5.18) መላእክት ደግሞ አገልጋዮች ናቸው፡፡ ይህን ሲያስረዳ መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ቦታ ‹‹መላእክቱን መንፈስ የሚያደርግ፤ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል›› እያለ ሲጠቅሳቸው በሌላ ስፍራ ደግሞ ‹‹ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?›› ይላቸዋል፡፡ (መዝ103.4፤ዕብ1.14) ስለዚህ ማገልገል ማስታረቅን የሚያካትት ከሆነ መላእክት ደግሞ አገልጋዮች ከሆኑ አስታራቂዎች /አማላጆች/ መሆናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ነገረን ማለት ነው፡፡

ለ. ይህም ብቻ አይደለም! ዕጣን በጸሎት ይመሰላል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ጸሎቴን በፊትህ እንደ ዕጣን ተቀበልልኝ›› ይላልና፡፡ (መዝ140.2) እንዲህ ከሆነ ‹‹ሌላም መልአክ መጣና የወርቅ ጥና ይዞ በመሠዊያው አጠገብ ቆመ፤ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሰዊያ ላይ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን ተሰጠው።›› ይላልና፡፡ (ራእ8.3) በዚህ ጥቅስ መሠረት የእግዚአብሔር መልአክ የቅዱሳንን /የምእመናንን/ ጸሎት በዕጣን አምሳል እንደሚያሳርግ ከተረዳን አማላጅነቱን አወቅን ማለት ነው፡፡ አንድ መልአከ ጸሎታችንን ቅድመ እግዚአብሔር የሚያደርስ ከሆነ አማለደ ከማለት ውጭ ምን ትርጉም ይኖረዋል? ያማልዱናል ማለት ልመናችንን ወደ እግዚአብሔር ያደርሱልናል ማለት አይደለምን?

ሐ. እስራኤላውያን በባቢሎን ምርኮ ለበርካታ አመታት በተሰቃዩ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ስለ እነርሱ በግልጽ ቃል ምልጃ አቅርቧል፡፡ ይህም ምልጃው በዚህ መልኩ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቧል፡- ‹‹የእግዚአብሔርም መልአክ መልሶ፦ አቤቱ፥ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ እነዚህ ሰባ ዓመት የተቈጣሃቸውን ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ነው? አለ።›› (ዘካ1.12) መልአኩ ይህን ልመና ባቀረበ ጊዜ ‹‹እግዚአብሔርም መልሶ ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረው መልአክ በመልካምና በሚያጽናና ቃል ተናገረው።›› ይላል፡፡ (ዘካ1.13)

ታሪኩን ልብ ብሎ ያነበበ ሰው ይህ ‹‹መልካምና የሚያጽናና ቃል›› ምን ይሆን? ማለቱ አይቀርም፡፡ መቼም ‹‹የማትምራቸው እስከ መቼ ነው?›› ለሚለው የልመና ቃል ‹‹ምሬአቸዋለሁ ወይም እምራቸዋለሁ›› ከሚል ውጭ የሚያጽናና ቃል ሊኖር አይችልም፡፡ ይህም በግምት የቀረበ ሐሳብ ሳይሆን መልአኩ ለዘካርያስ ባስተላለፈው የመጨረሻ ቃል ይታወቃል፡፡ ‹‹ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወደ ኢየሩሳሌም በምሕረት ተመልሻለሁ ቤቴ ይሠራባታል በኢየሩሳሌምም ላይ ገመድ ይዘረጋበታል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፦ ደግሞም እንዲህ ስትል ስበክ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከተሞቼ ደግሞ በበጎ ነገር ይረካሉ እግዚአብሔርም ደግሞ ጽዮንን ያጽናናል፥ ኢየሩሳሌምንም ደግሞ ይመርጣል።›› ብለህ ስበክ ብሎ ልኮታል፡፡ (ዘካ1.16-17

መልአኩ የለመነው ምን ነበር? ምሕረት አልነበርምን? ፈጣሪ ደግሞ በምሕረት ተመልሻለሁ ሲል መለሰ፡፡ የመልአኩ አማላጅነት ተቀባይነት አግኝቷ ማለት ነው፡፡ መላእክት ያማልዳሉ ስንል ይህን የመሳሰሉ ጠንካራና በርካታ መረጃዎችን ከመጽሐፍ ቅዱስ አግኝተን ነው እንጂ ከራሳችን ፍላጎት ተነሥተን አይደለም፡፡

በነገራችን ላይ ይህን ጥቅስ በተመለከተ ገጠመኜን ላውጋችሁ፡፡ አንድ ቀን ከአንድ መናፍቅ ጋር በአጋጣሚ የሃይማኖት ጉዳይ ተነሣና መነጋገር ጀመርን፡፡ ርእሱም ስለመላእክት አማላጅነት ሆነ፡፡ በዚህ ጊዜ ለማስረዳት ይህን ጥቅስ ጠቀስኩለት፡፡ ምን አለ መሰላችሁ? ‹‹መላአኩ እኮ የማትምራቸው እስከ መቼ ነው? አለ እንጂ አልለመነላቸውም፤ ማራቸውም አላለም፡›› ብሎኝ እርፍ፡፡ እኔም እሺ ታዲያ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር? አልኩት፡፡ እርሱም መልሶ ‹‹መቼ ልትምራቸው አስበሃል? ብሎ ቀጠሮ ነው የጠየቀው›› ሲል ደመደመ፡፡ ምንም እንኳን የምንማረው ለመናፍቃን መልስ ለመስጠት ብለን ባይሆንም እንዲህ ዓይነት ዓይን ያወጣ ድርቅና ሊያጋጥማችሁም እንደሚችል አትርሱ፡፡

እንደዚህ መናፍቅ አተረጓጎም መልአኩ የጠየቀው ‹‹እስከ መቼ›› ብሎ ቀጠሮ ከሆነ መልሱ ‹‹በዚህ ጊዜ›› የሚል እንጂ ‹‹በምሕረት ተመልሻለሁ›› የሚል አይሆንም ነበር፡፡ ጥያቄው ምን እንደነበር ከመልሱ በመነሣት ማወቅ ይቻላል፡፡ ሌላው ቋንቋው አማርኛ እስከሆነ ድረስ በሌላም ምሳሌ ማስረዳት ይቻላል፡፡ አንድ አባት በማምሸትና በመስከር ያስቸገረውን ልጁን ‹‹ልጄ እንደዚህ የምትሆነው እስከመቼ ነው?›› ቢለው ቀነ ቀጠሮ ስጠኝ እንጂ አለው ብለን እንደማንፈታው የታወቀ ነው፡፡ ይህ ሐረግ በስድሳ ስድስቱ መጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ ብቻ ከ50 ጊዜ በላይ ስለተጠቀሰ በርካታ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ ስለዚህ ምሳሌውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስናደርገው ቅዱስ ዳዊት ‹‹አቤቱ እስከመቼ ፈጽመህ ትረሳኛለህ?›› እያለ ሲጸልይ ቀን ቅጠርልኝ ማለቱ ሳይሆን አትርሳኝ እንጂ እያለ መለመኑ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ (መዝ12.1) ስለዚህ መልአኩም ‹‹የማትምራቸው እስከመቼ ነው?›› ሲል ‹‹ማራቸው እንጂ፤ አባክህ ማራቸው!›› እያለ እንደለመነላቸው ከምላሹም መረዳት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ቅዱሳን መላእክት በእውነት አማላጆቻችን ናቸው፡፡

ይቆየን!

በዲያቆን ኅብረት የሺጥላ

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top