ሥነ ፍጥረት

ሥነ ፍጥረት (የዓለም አፈጣጠር)

እግዚአብሔር በስድስት ቀናት ውስጥ የፈጠራቸው ፍጥረታት በየወገናቸው ሲቆጠሩ ሃያ ሁለት ሲሆኑ :: በመጀመሪያው ቀን እሑድ የተፈጠሩት ፍጥረታት ስምንት ናቸው ::
1  ጨለማ        3  ውሃ        5  ነፋስ (አየር)     7  መላእክት
2  መሬት        4  እሳት       6  ሰባቱ ሰማያት     8 ብርሃን

ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደተፈጠሩ የሚታየውም ከማይታው እንደሆነ (እንደተፈጠረ) እናምናለን ። ዕብ 11 ፥ 3 በማለት ቅዱስ ዻውሎስ እንደተናገረ:: እነዚህም ዓለሞች የተባሉት (ዓለመ ምድር ፤ ዓለመ ሰማይ) ተብለው በሁለት ይከፈላሉ ።

ዓለመ ምድር 

1 ጨለማ (ጊዜ) ፤ እግዚአብሔር በመጀመሪያ የፈጠረው ጨለማን ነው ።ጨለማን የፈጠረውም  ከምንም (ካለመኖ ወደ መኖር አምጥቶ በአምላክነት ጥበቡ በማስገኘት) ነው ። እኛ ሰዎች አንድን ነገር ለመስራት ጥሬ ዕቃ የግድ ያስፈልገናል ከምንም ተነስተን ምንም ነገር መስራት አንችልም በዓለም ላይ የምናያቸው የሰው ልጅ ሥራዎች (ታሪካውያን መዛግብትና የሳይ ንሰ ውጤቶች) ሁሉ የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን በማሰባሰብ የተሠሩ ናቸው ። ሰው ምን ቢያውቅ መሥራት የሚችለው ካለው ነገር ላይ ተጠቅሞ ነው ። እግዚአብሔር ግን ዓለማትን የፈጠራቸው (ያስገኛቸው) ያለምንም ነገር (እምኀበ አልቦ) ከምንም ነው  ።

ይህም ጊዜ መቆጠር የተጀመረበት ሲሆን ፤ ሌሎቹ ፍጥረታት የተፈጠሩትም በጊዜ ውስጥ ነው ። ጊዜ ከመፈጠሩ በፊት ስለ ነበረው ሁኔታ ለሰዎች የማወቅ ችሎታ የላቸውም ። ሰዎች እንዲያውቁና እንዲመራመሩ የተፈቀደላቸው ከሥነ ፍጥረት በኋላ ያለውን ብቻ ነው ። ያንም ቢሆን የቻሉትን ያህል ይሞክራሉ እንጅ ሁሉንም ተመራምረው አይደርሱበትም ።

2 መሬት (ምድር)፤ በውስጡ ለሚገኙት ሁሉ መኖሪያ እንዲሆን የተፈጠረውና ከአራቱ ባህርያት አንዱ የሆነው መሬት ተፈ ጥሮው ከምንም ነው ። መሬት ብትን (አፈር) ሲሆን ፤ ምድር የተባለውና ዛሬ እንደምናየው የፀና የሆነው ከውሃ ጋር ተዋህዶ በመጠንከሩ ነው መሬት በዓይን ይታያል ፣ በእጅ ይጨበጣል ፣ በውስጡ ሶስት ባህርያት አሉት ።እነሱም ደረቅነት (የብስነት) ፤ ክብደት (ግዙፍነት) ፤ ጥቁርነት (ጽሉምነት) ፤ ናቸው ።

3 ውሃ  ለፍጥረታት ሁሉ ሕይወት የሆነውና ከአራቱ ባህርያት አንዱ የሆነው ውሃ የተፈጠረው ከምንም ነው ። ውሃ በምድር ለሚኖሩ ፍጥረታት ሕይወታቸው ነው ። ከእሳት በቀር በሁሉም ፍጥረታት ውስጥ አለ ። ውሃ በዓይን ይታያል ፣ በእጅ ይዳሰሳ ል ፣ ግን አይጨበጥም ። በባህርዩ ከመሬት ረቂቅ ነው ። በውስጡ ሶስት ባህርያት ፡ ቅዝቃዜ ፣ እርጥበት ፣ ብርሃን ፤ ናቸው

4 እሳት ከአራቱ ባህርያት አንዱ ሲሆን የተፈጠረው ከምንም ነው ። በዓይን ይታያል ግን በእጅ አይጨበጥም አይዳሰስም ከመሬትና ከውሃ ይረቃል ። የእሳት ሶስት ባህርያት ፤ ብርሃን ሙቀት (ዋዕይ) ደረቅነት (ይብሰት) ናቸው ።

5 ነፋስ (አየር) ከአራቱ ባህርያት የመጨረሻ የሆነው ነፋስ በባህርዩ ከመሬት ከውሃና ከእሳት ይረቃል ። እንቅስቃሴው ይሰ ማል ። ነገር ግን በዓይን አይታይም ። በእጅ አይዳሰስም ። ዮሐ 3 ፡ 8 ። የነፋስ (አየር) 3 ባህርያት እርጥበት (ርጡብነት) ፣ ረቂቅነት ፣  ጸሊምነት (ጥቁርነት) ናቸው ።
ጥቁርነት የነፋስ ባህርይ ነው መባሉ ፤ በዓይን ታይቶ ሳይሆን ፤ ከጨለማ ባህርይ ጋር በመስማማቱና ተለይቶ ባለመታወቁ ነው ። እስመ ነፋስ ጸሊም በአርአያሁ እንዲል ። ነፋስ የተፈጠረው ከምንም ነው ።
የአራቱ ባህርያት የየራሳቸው ዋና ባህርይ መሬት ደረቅነት ፣ ውሃ ቀዝቃዛ ነት ፣ እሳት ብሩህነት ፣ ነፋስ ረቂቅነት ፣ ነው ።

አራቱ ባህርያት ለፍጥረታት ሁሉ መሠረት ናቸው ። እግዚአብሔር በምድር ያሉ ፍጥረታትን የፈጠራቸው ከአራቱ ባህርያት ሲሆን ፤ እነሱን ግን ያስገኛቸው ከምንም (ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ) ነው ።

ዓለመ ሰማይ

ሰባቱ ሰማያት ፤ እግዚአብሔር ሰማያትን ከእሳት ዋዕዩን (የማቃጠል ባህርዩን) ትቶ ብርሃኑን ብቻ በመውሰድ ፈጠራቸው ስማ ቸውም ከላይ ወደ ታች በሚከተለው መልኩ ይገለጻል ።

  1.  ጽርሐ አርያም       3.  መንበረ መንግሥት 5.  ራማ2.  ሰማይ ውዱድ         4.  ኢየሩሳሌም ሰማዊት         6.  ኢዮር        7. ኤረር ናቸው ።

  2. ጽርሐ አርያምለሰባቱም ሰማያት የመጨረሻ ክፍል ሲሆን ፤ ከላይ ወደታች ሲቆጠር የመጀመሪያ ደረጃያለው ነው ።

  3. መንበረ መንግሥትእግዚአብሔር በወደደው መጠን ለወዳጆቹ የሚገለጥበት ፤ የክብሩ ዙፋን የተዘረጋበት ፤ ቅዱሳን መላ እክት በፊቱ እየሰገዱ ምስጋና የሚያቀርቡበት ፤ የሞቱ ሰዎች ነፍሳቸው ሰግዳ ፍርድ የምትቀበልበት ነው ። ኢሳ 6 ፥ 1 ። ሕዝቅ 1 ፥ 22 – 27 ። ራዕ 4  ፥ 2 ።

  4. ሰማይ ውዱድበአራቱ መዐዝን ቁመው ዙፋኑን የተሸከሙ አርባዕቱ እንስሳ (የሰው ፤ የላም ፤ የንሥር ፤ የአንበሳ) ምስል ያላቸውና ዘወትር ዙፋኑን የሚያጥኑ ፳፬ ካህናተ ሰማይ ያሉበት የሰማይ ክፍል ነው ። ሕዝቅ 1 ፡ 4 – 75 ። ራዕ 4 ፥ 4

  5. ኢየሩሳሌም ሰማያዊት (መንግስተ ሰማያት) በመጀመሪያ ሳጥናኤል (የዛሬው ዲያብሎስ) የነበረባት ፤ ጻድቃን ከምጽአት በኋላ የሚወርሷት ርስታቸው ናት ። ገላ 4 ፥ 26 ። ዕብ 12 ፥ 22 ። ዮሐ 14 ፥ 2 ።

  6. ኢዮር ፤ 6 ራማ ፤ 7  ኤረር፤ሦሥቱም የመላእክት ዓለማት (መኖሪያዎች) ሲሆኑ ፤ ከዳግም ምጽዓት በኋላ ወዳለመኖር ሲያልፉ ቅዱሳን መላእክት ከጻድቃን ጋር በመንግስተ ሰማያት ይጠቃለላሉ (ይኖራሉ) ። ማቴ 22 ፥ 30 ። ከሰባቱ ሰማያት ቀጥሎ ያለውና ምጽንዓት የሚባለው የሰባቱ ሰማያት መሠረት ነው ።

እነዚህን ሰማያት በሃይማኖት እንጅ ዛሬ በሥጋ ዓይን ልናያቸው አንችልም ። በሰማያት ይቅርና በዓለማችን ያሉ በዓይናችን የማናያቸው ብዙ ጥቃቅን ነገሮች መኖራቸው ይታወቃል ።
ቁሳዊ አስተሳሰብ ላላቸው ሰዎች ይህ ምሥጢር ይከብዳቸል ፤ የሃይማኖት ሰዎች ግን ሁሉንም ሳይጠራጠሩ በሃይማኖት እውነት ነው ብለው ይቀበላሉ ። ሃይማኖት ለብዙ እንቆቅልሾች መልስ ስለሚሰጥ ለሚያምኑ ሰዎች ታላቅ እፎይታ ነው ።

ቅዱሳን መላእክት
መልአክ የሚለው ቃል ተመልአከ አለቃ ሆነ ካለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ይህም ቃል ቅዱሳን መላ እክት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ክብሩን ወርሰው ለመኖር የተመረጡና የተሾሙ መሆናችውን ይገልጻል ።
በሌላም በኩል ለአከ ፡ ላከ ካለው ግሥ የተገኘ ሆኖ መላእክት የእግዚአብሔር መልእክተኞች መሆናቸውን
ያስረዳል ።

የመላእክት አፈጣጠር
መላእክት የተፈጠሩት ከምንም ነው ። በመዝ 103 ፡4 ። እና በዕብ 1 ፡7 ። ላይ ከእሳትና ከነፋስ እንደተፈጠሩ የተገለጠው ረቂቅነታቸውንና ለአገልግሎት ፈጣን መሆናቸውን ለማስረዳት ነው ። ከእሳትና ከነፋስ ተፈጥረው ቢሆን ኖሮ የሚሞቱ ይሆኑ ነበር ።
መላእክት ግን – አይይሞቱም የሥጋ ባህርይ የላቸውምና ።
–  ፆታ የላቸውም ፤ ነገር ግን የሚጠሩት በወንድ ፆታ ነው ።
–  ረቂቃን(መናፍስት) ስለሆኑ በዓይን አይታዩም ።

የመላእክት አገልግሎት
ያለ እረፍት እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ ። መዝ 148 ፥ 2 ። ኢሳ 6 ፥ 3 ።
– ከእግዚአብሔር ወደ ሰዎች ይላካሉ ። ሉቃ 1 ፥ 11 ። ሐዋ 10 ፥ 3 ።                   ዘፍ 19 ፥ 1 ።
– የሰዎችን ጸሎት ያሳርጋሉ ። ዘካ 1 ፥ 14 ። ራዕ 8 ፥ 3 ።
– የእግዚአበሔርን ወዳጆች ይጠብቃሉ ። መዝ 90 ፥11 ። 2ነገ 19 ፥ 35

መላእክት የተፈጠሩት በመጀመሪያው ቀን እሑድ ነው ። ከብዛታቸው የተነሳ ቁጥራቸው አይታወቅም አይወሰንም ። በመቶ ነገድ የተከፋፈሉ ሲሆኑ ለየነገዱ አለቃ አለው ። ሳጥናኤል የዛሬው ዲያብሎስ ለመጀመሪያው ነገድ አለቃ ነበረ ። ሳጥናኤል የመጀመሪያ የክብር ስሙ ነው ። ሲክድ ስሙም ተወሰደበትና ‹‹ዲያብሎስ (ፈታዌ አምላክና አምላክነትን ፈላጊ፤ ዖፍ ሰራሪ ለማሳት የሚፋጠን በራሪ ወፍ)ጋኔን(ዕቡይ ትዕቢተኛ ውዱቅ የተጣለ) ሰይጣን (ባለጋራ ከሳሽ) ። የሚባሉና ግብሩን የሚገልጹ ስሞች ተሰጡት>> ።

እግዚአብሔር መላእክትን ፈጥሮ በተሰወራቸው ጊዜ አእምሯቸው ጠያቂ አገናዛቢ ነውና ማ ን ፈጠረን ከየት መጣን ? እያሉ እርስ በእርሳቸው ሲጠያየቁ በቦታና በመዓርግ ታላቅ የነበረው ሳጥናኤል ማንም ሳያሳስተውና ሳይመክረው ሐሰትን ለመጀመሪያ ጊዜ ከልቡ (ከአእምሮው) አንቅቶ እኔ ፈጠኋችሁ ብሎ በድፍረት ተናገረ ። ዮሐ 8 ፥ 44 ። በዚህ ጊዜ ቅዱስ ገብርኤል (ንቁም በበኅላዌነ እስከንረክቦ ለአምላክነ) የፈጠረን አምላካችንን እስክናገኘው (እስኪገለጥልን) ድረስ በያለንበት እንጽና በማለት ብሎ ባረጋጋቸው ጊዜ በመላእክት መካከል መለያየት ተፈጠረ ይህም ዲያብሎስ በመላእክት መካከል የዘራው የመጀ መሪያ መከፋፈል ነው ። ማቴ 13 ፥ 28 ። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ብርሃን ይሁን ብሎ ብርሃንን ፈጠረ ። ዘፍ 1 ፥ 3 ።

ብርሃን በተፈጠረ ጊዜ ሳጥናኤል ምንም መፍጠር የማይችል የውሸት (የምኞት)አምላክ መሆኑ ተገለጠበት ። በስህተቱም ተፀፅቶ ሊመለስ ስላልቻለ ቅዱሳን መላእክት በሰልፍ (በጦርነት) ተዋግተው መዓርጉን ተነጥቆ ከነበረበት የክብር ቦታ ከመንግስተ ሰማያት ከነሠራዊቱ (ከነተከታዮቹ) ወደ ጥልቁ ተጣለ ። ራዕ 12 ፥ 6 ። ኢሳ  14 ፥ 12 ። ይሁ 1 ፥ 13 ።
አጋንንት መልካቸውን እየለዋወጡ በብርሃን መልአክና ፣ በተለያየ የሰው መጠን ፤ መስለው ሰዎችን ከእግዚአብሔር መንገድ ያሳስታሉ ። ኢዮ 1 ፥ 6 ። ሉቃ 22 ፥ 3 ። 2 ቆሮ 11 ፥ 14 ። 1 ዼጥ 5 ፥ 8 ።

እሑድ ፦ ሌሊቱ አሥራ ሁለት ፣ ቀኑ አሥራ ሁለት ፣ በድምሩ 24 ሠዐታት አንድ ቀንተብሎ የመጀመሪያ
ቀን ተቁጠረ ።

ሰኑይ (ሰኞ)

ሰኑይ (ሰነየ አማረ ፤ በጀ ፤ ተስተካከለ) ፤ ካለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ቃል ሲሆን እግዚአብሔር በዚህ ቀን የፈጠረው አንድ ፍጥረት ጠፈርን (ሰማይ) ብቻ ነው ። ከመሬት (አፈር) ጋር ተዋህዶ የነበረውን ውሃ ከሶስት ከከፈለ በኋላ አንደኛውን ባለበት እንዲረጋ አድርጎ፤ ጠፈር (ሰማይ) አለው ፤ ሁለተኛውን ከመሬት ጋር እንደተቀላቀለ (ድፍርስ እንደሆነ) ከጠፈር በላይ አደረገው ስሙም ሐኖስ ይባላል ። ዘፍ 1 ፡ 6 ። ሶተኛውንም ከውሃ ጋር እንደተቀላቀለ ከጠፈር በታች ተወው ።

ሰሉስ (ማክሰኞ)

ሰሉስ ሰለሰ ሶስት አደረገ ፤ ካለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ሆኖ ለፍጥረት ሶስተኛ ቀን ማለት ነው ። ይህ ቀን እግዚአብሔር ከአፈር ጋር ተቀላቅሎ የነበረውን ውሃ በምድር ዙርያ ከወሰነው በኋላ ፤ የመሬት ገጽ የታየበት እና ሰማይና ምድር ዛሬ በምናየው ሁኔታ የተዘጋጁት ፤ ምድርም የዛሬ ቅርጿን የያዘችበት ብሩህ ዕለት (ቀን) ነው ። እሑድ የተፈጠሩት ፍጥረታት (ሃያውን ዓለ ማት)  በየቦታቸው የተከናወኑትም በዚሁ ቀን ነው ። ሃያው ዓለማት የሚባሉትም ።
–  ዓለማተ መሬት   5     የጋራ ስማቸው     ዱዳሌብ
–  ዓለማተ ማይ    4     የጋራ ስማቸው     ናጌብ
–  ዓለማተ እሳት   9     የጋራ ስማቸው     ኮሬብ
–  ዓለማተ ነፋስ   2     የጋራ ስማቸው     አዜብ ናቸው ።

ገሐነመ እሳት ፡ ሲኦልና ገነት ፡ ብሔረ ህያዋን ብሔረ ብፁዓን ። ተብለው የተሰየሙት በዚህ ቀን ነው ። እግዚአብሔር አስቀድሞ እነዚህን ዓለማት በየቦታቸው ካዘጋጀ በኋላ ፤ በመሬት ላይ ሶስት ፍጥረታትን ብቻ ፈጥሯል ።

እነዚህም
–  በእጅ የሚለቀሙ አትክልት (በመሬት ውስጥ የሚያፈሩ እንደ ካሮት ድንች …)
–  በማጭድ የሚታጨዱ  አዝርዕት (የአገዳ እህሎች እንደ ገብስ ስንዴ በቆሎ ጤፍ …)
–  በመጥረቢያ የሚቆረጡ   ዕፀዋት    (የዛፍ ዓይነቶች እንደ ዋርካ ወይራ ሾላ…) የመሳሰሉት ናቸው ።

የተፈጠሩትም ከአራቱ ባህርያት ነው ። ከመሬት እንደ መፈጠራቸው ሲጣሉ አፈር ይሆናሉ ። ከውሃ እንደ መፈጠራቸው በውስጣቸው ፈሳሽ አላቸው ። ከእሳት እንደመፈጠራቸው ይቃጠ ላሉ ። ከነፋስ እንደመፈጠራቸው አየር (ነፋስ) ያስገባሉ ያስወጣሉ ፤ ከአራቱ ባህርያት አንዱ ከተጓደለ ግን ይደርቃሉ እነዚህም የምድር ጌጦች ሲሆኑ ሰውም ለምግቡም ሆነ ለሚፈልገው አገልግሎት ይጠቀምባቸዋል

ረቡዕ

ረቡዕ “ረብዐ አራት አደረገ“ ካለው ግሥ የተገኘ ሲሆን ፤ ለፍጥረት አራተኛ ቀን ማለት ነው ። እስከዚህ ቀን ድረስ እሑድ  የተፈጠሩት ብርሃንና ጨለማ በየ12 ሰዓት ቀንና ሌሊት እየተፈራረቁ ከቆዩ በኋላ ብርሃኑን ወደ ሰባቱ ሰማያት ፤ ጨለማውን ወደ ከርሰ ምድር (ወደ እንጦርጦስ) አጠቃሎ በጠፈር (በህዋ) ላይ ሆነው የሚያበሩ ሶስት ፍጥረታትን ፈጠረ ።

እነዚህም  ፀሀይን  ፈጥሮ ከእሳት ብርሃኑንና ሙቀቱን ከሳለበት በኋላ በቀን እንዲያበራ ሾመው።
ጨረቃን  ሰሌዳውን አዘጋጅቶ በፀሀይ ብርሃን ነፀብራቅ በሌሊት እንዲያበራ አደረገው ።
ከዋክብትን  በተለያየ መጠን ካዘጋጀቸው በኋላ ብርሃን ስሎባቸው በሌሊት እንዲያበሩ ሾማቸው ።
ጨረቃና ከዋክብት በሌሊት በማብራታቸው ሌሊቱን ማስቀረት አይችሉም ። ሁሉም ሥርዓታቸውን ጠብቀው የሚገኙ ሲሆን እነዚህም ለሠዓታት ፤ ለወራትና ፤  ለዓመታት ፤ መታወቂያና መለያ ናቸው ። ዘፍ 1 ፡ 14 – 20 ።

ሐሙስ

ሐሙስ ፤ ሐመሰ አምስት አደረገ ካለው ቃል የተገኘ ሲሆን ፤ ለፍጥረት አምስተኛ ቀን ነው ። በዚህ ቀን እግዚአብሔር ከባህር በደመ ነፍስ ህያዋን ሆነው የሚኖሩ ፤ ሶስት ተንቀሳቃሽ ፍጥረታትን ፈጠረ ። ዘፍ 1 ፥ 20 ፡23 ።
እነዚህም  – በልብ የሚሳቡ እንስሳትና አራዊት
– በእግር የሚሽከረከሩ እንስሳትና አራዊት
– በክንፍ የሚበሩ አእዋፍ   ናቸው ።
ከነዚህም  ውስጥ ከባህር ውጭ መኖር የማይችሉ እንደ ዓሣ ያሉና ፤ በባህርም በየብስም መኖር የሚችሉም አሉባቸው ።

ዐርብ

ዐርብ ፤ ዐረበ ፤ ገባ ፤ ተካተተ ፤ ካለው የወጣ ሲሆን ፤ መካተቻ ማለት ነው ፤ ለፍጥረት ስድስተኛ ቀን ነው ። እግዚአብሔር በዚህ ቀን በመጀመሪያ ከየብስ በደመ ነፍስ ህያዋን ሆነው የሚኖሩ ሶስት ተንቀሳቃሽ ፍጥረታትን ፈጠረ ። ዘፍ 1 ፡24 ።

እነዚህም  –  በልብ  የሚሳቡ      እንስሳትና አራዊት
–  በእግር የሚሽከረከሩ  እንስሳትና አራዊት
–  በክንፍ የሚበሩ      አእዋፍ  ናቸው

በመጨረሻም  እግዚአብሔር “ ሰውን በመልካችንና እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር ” ብሎ ከሰባቱ ባህርያት ፈጠረው ። ሰባት ባህርያት የሚባሉት አራቱ ባህርያተ ሥጋ(መሬት : ውሃ: እሳት : ነፋስ) ሲሆኑ ሶስቱ ባህርያተ ነፍስ የሚባሉት ደግሞ ልብ (ማሰብ) ቃል (መናገር) እስትንፋስ (በሕይወት መኖር) ናቸው ። ዘፍ 1 ፥26 ።

ሰው በሥጋው እንደ እንስሳት ይበላል ይጠጣል ይተኛል ይነሳል ። በነፍሱ እንደ መላእክት ረቂቅ (መንፈስ) ነው ። ፈጣሪውን ያመሰግናል ። የነፍስ ምግቧ የእግዚአብሔር ቃል ነው ። አሞ 8 ፥ 11 ። ነፍሱ አትሞትም ለዘለዓለም ህያው ሆና ትኖራለች ። ስለዚህም ሰውን የፈጠረው በሥጋው እንደ እንስሳት ፤ በነፍሱ እንደ መላእክት ረቂቅ አድርጎ ነው ::

በመጀመሪያ የተፈጠረው ሰው ስሙ አዳም ይባላል ፤ አዳም ማለት ያማረ የተዋበ.. ፍጡር ማለት ነው ። አዳም ሲፈጠር የሰላሳ ዓመት ያህል ሆኖ ነው ። ሌሎቹ (ሐሙስና ዐርብ የተፈጠሩ እንስሳት አራዊትና አእዋፍ) የተፈጠሩት ሁሉም ወንድና ሴት ፆታ እየሆኑ ነው ። አዳም ግን ሲፈጠር ረዳት ስላልነበረው ። ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም…። ዘፍ 2 ፥ 18 ። ብሎ በአዳም ላይ እንቅልፍ በማምጣት ከግራ ጎኑ አንዲት አጥንት ወስዶ እሱን ከፈጠረው ከአንድ ሳምንት በኋላ ፤ በተ ፈጥሮ የምትመስለው ፤ በፆታ የተለየች ሴት ፈጠረለት ፤ አዳምም ስሟን ሄዋን አላት ። ትርጉሙም የህያዋን (የሰው ልጆች) ሁሉ እናት ማለት ነው ። ሄዋን የተፈጠረች የአስራ አምስት ዓመት ያህል ሆና ነው ። ሴት ልጅ ለአቅመ ሄዋን ደረሰች የሚባለውም ከዚህ ዕድሜ  ጀምሮ ነው ።

ሔዋንን ከጎኑ የፈጠረበት ምክንያት ከወገብ በላይ ቢፈጥራት የወንድ የበላይ ፤ ከወገብ በታች ቢፈጥራት ደግሞ የበታች ፤ እንዳትሆን ጎን (ወገብ) መካከለኛ እንደሆነ ሁሉ በተፈጥሮ ከወንድ እኩል ሙሉ ሰው መሆኗን ለማስረዳት ነው ። አዳምና ሄዋን የሚቆጠሩት እንደ አንድ ሲሆን ከእሑድ እስከ ዐርብ የተፈጠሩት ፍጥረታት ሃያ ሁለት ናቸው ። ይህም ዝርዝር ቁጥራቸው ሳይሆን ፤ በዓይነታቸው (በየወገናቸው) ተቆጥረው ነው ።

ሰውን በመጨረሻ የፈጠረበት ምክንያት

1 ኛ አምላክ ፤ ለሰው ልጅ የሚያስፈልገውን ሁሉ ስለሚያውቅ አስቀድሞ በማዘጋጀት ፍቅሩን ለመግለጽ ፤
ማቴ 6 ፥ 32 ።
2 ኛ ሰው አስቀድሞ ተፈጥሮ ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር ሌሎችን ፍጥረታት ሲፈጥር ረድቻለሁ አማክሬያለሁ እንዳይል ። እግዚአብሔር ዓለማትን ሲፈጥር የማንም አማካሪነት ሳያስፈለገው ፤ በራሱ ጥበብና ማስተዋል ሁሉን አዘጋጀ ። ኢሳ 40 ፥12 ። እግዚአብሔር አዳምን በተፈጠረ በአርባ ሄዋንን በተፈጠረች በሰማንያ ቀናቸው በልጅነት አክብሮ ብርሃን አልብሶ በይባቤ  መላእክት (በመላእክት አጅቦ) ወደ ገነት አስገባቸው ። ገነት ከገቡ በኋላ በገነት ያለውን አትክልትና ፍራፍሬ ሁሉ ብላ ፤ ክፉና በጎ የምታስታውቀውን ዕፀ በለስን ግን አትበላ ፤ እሷን በበላህ ቀን ትሞታለህ ብሎ አዘዘው ። ዘፍ 2 ፥ 16 ። ይህን ያለበት ምክንያት አዳም ፍጡር (ተገዢ) ፤ እግዚአብሔር ፈጣሪ (ገዢ) መሆኑን ለማስረዳት ነው ።

ቅዳሜ (ቀዳሚት ሰንበት)

ቅዳሜ  ይህ ቀን የሳምንቱ መጨረሻ ሰባተኛ ቀን ነው ። እግዚአብሐር በዚህ ቀን ምንም አልፈጠረም ። አረፈ ይህም ማለት እንደ ፍጡር የሚደክምና እረፍት የሚያስፈልገው ሆኖ ሳይሆን መፍጠሩን ተወ : ማለት ነው ። ይህንም ቀን ሰዎች የሚያርፉበት የእረፍት ቀን ሰንበት አደረገው ። ለእረፍታችን ሳይቀር የሚያስብ አምላክ ነውና ። ዘፍ 2 ፥ 1 ። ለሙ ሴ “ሰንበትን አክብር” ብሎ ያዘዘውም ይህንኑ ቀን ነው ። ዘፀ 28 ፥ 11 ።
ቀዳሚት ሰንበት ፤ ቀዳሚት፤ የግዕዝ ቋንቋ ሲሆን ትርጉሙ የመጀመሪያዋ (ፊተኛዋ)ማለት ነው ። ሰንበተ አይሑድ ተብላም ትታወቃለች ፤ እለተ እሑድ (ሰንበተ ክርስቲያን) በሐዲስ ኪዳን ሰንበት ሆና መከበር ስትጀምር ቀዳሚት ሰንበት (ቅዳሜ) ተባለች በሐዲስ ኪዳን ሁለቱም ቀናት (ቅዳሜና እሑድ) ሰንበታት ሆነው ይከበራሉ ።

የሰባቱ ቀን ፍጥረታት

በመጀመሪየው ቀን እሁድ፦ ስምንት ፍጥረታትን ፈጠረ እነዚህም ሰማይ፣ መሬት፣ ውኃ፣ ነፋስ፣ እሳት  ጨለማ፣ ብርሃን እና መላእክትናቸው። 

ሁለተኛው ቀን ሰኞ:- ምድርና ሰማይን ሞልቶ የነበረውን ውኃ ወደ ላይና ወደ ታች በመክፈል ጠፈርን ፈጠረ። በምድር ላይ ያሉ የውሃ ክፍሎች ውቂያኖስ፣ባህር፣ሐይቅ እና ወንዝ ይባላሉ።

በሦስተኛው ቀን ማክሰኞ:- ዕፅዋትን እህልና ጥራጥሬ (አዝርዕት)፣ አትክልት፣ ፍራፍሬዎችን ሁሉ ፈጠረ።

በአራተኛው ቀን ረቡዕ፦ ፀሐይ፣ ጨረቃንና ከዋክብትን ፈጠረ።

በአምስተኛው ቀን ሐሙስ:- በባህር የሚኖሩትን እንስሳት ፤ እንዲሁም  አእዋፋትን ማለትም በውሃ ውስጥ እና በውሃ አከባቢ የሚኖሩ ወፎችን ፈጠረ።

በስድስተኛው ቀን ማለትም አርብ ዕለት:- በየብስ የሚኖሩ እንስሳትን (የቤት እንስሳትና የዱር አራዊት እንዲሁም በሰማይ የሚበሩ አእዋፋትን) ፈጠረ።

እግዚአብሔር አምላካችን ከላይ የተዘረዘሩትን ሁሉ አመቻችቶ ከፈጠረ በኋላ አርብ ዕለት ሰውን ማለትም የሁላችን አባት የሆነውን አዳምንና የሁላችን እናት የሆነቺውን ሄዋንን ፈጠረ። እግዚአብሔርም አዳምና ሔዋንን ለፈጠራቸው ፍጥረታት ማለትም ለባሕር እንስሳት፣ ለሰማይ ወፎች፥ ለምድር እንስሳት ሁሉ ገዢ (አዛዥ) አደረጋቸው።

በሰባተኛው ቀን ማለትም ቅዳሜ:- በዚህ እለት ግን ፍጥረት መፍጠሩን ጨርሶ የዕረፍት ቀን አደረገው።

22ቱን ሥነ-ፍጥረት እና 22ቱ የእግዚአብሔር ኅቡዕ ስሞች

22ቱን ሥነ-ፍጥረት ምሳሌ በማድረግ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት የእግዚአብሔርን ኅቡዕ ስሞች እንደሚከተለው በዝሙሩ አመስግኖታል። በመዝሙረ ዳዊት 118

1. አሌፍ ፡ ዓለምን ከነጓዟ ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ የፈጠረ እግዚአብሔር ማለት ነው።
2. ቤት፡ እግዚአብሔር ሁሉን መስጠት የሚችል ቸር ለጋስ ባለጸጋ ማለት ነው።
3. ጋሜል፡ እግዚአብሔር ሊመረመር የማይችል ግሩም ድንቅ ማለት ነው።
4. ዳሌጥ፡ እግዚአብሔር በጌትነቱ ዙፋን ለዘለዓለም ይኖራል ማለት ነው።
5. ሄ፡ እግዚአብሔር በአንድነቱ በሦስትነቱ ለዘለዓለም ይኖራል ማለት ነው።
6. ዋው፡ እግዚአብሔር በመንግሥት በሥልጣን በአገዛዝ በባህርይ አንድ አምላክ የሆነ ማለት ነው።
7. ዛይ፡ እግዚአብሔር በሥራው ሁሉ እየታሰበ ሲመሰገን የሚኖር ፈጣሪ ማለት ነው።
8. ሔት፡ እግዚአብሔር በመንግሥቱ ሽረት በባሕርዩ ኅልፈት የሌለበት ለዘለዓለም ሕያው የሆነ ማለት ነው።
9. ጤት፡ እግዚአብሔር ጥበብን የሚገልጽ ከጥበበኞች ይልቅ ጥበበኛ የሆነ አምላክ ማለት ነው።
10. ዮድ፡ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለ እሱ ኃያልና ጽኑዕ የሆነ ማለት ነው።
11. ካፍ፡ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የሌለ ሁሉን ማድረግ የሚቻለው አምላክ ማለት ነው።
12. ላሜድ፡ እግዚአብሔር ልዑለ ባሕርይ የሆነ ማለት ነው።
13. ሜም፡ እግዚአብሔር ንጹሕ ባሕርይ የሆነ አምላክ ማለት ነው።
14. ኖን፡ እግዚአብሔር የነገሥታት ንጉሥ የገዥዎች ገዥ የሆነ አምላክ ማለት ነው።
15. ሳምኬት፡ እግዚአብሔር ሁሉን የሚገዛ አምላክ ማለት ነው።
16. ዔ፡ እግዚአብሔር ታላቅና ገናና የሆነ አምላክ ማለት ነው።
17. ፌ፡ እግዚአብሔር ተወዳጅ የሆነ አምላክ ማለት ነው።
18. ጻዴ፡ እግዚአብሔር ሐሰት የሌለበት እውነተኛ አምላክ ማለት ነው።
19. ቆፍ፡ እግዚአብሔር ለልበ ቅኖችና ለየዋሃኖች ቅርብ የሆነ አምላክ ማለት ነው።
20. ሬስ፡ እግዚአብሔር ክብሩ ከእርሱ ለእርሱ የተገኘ የሁሉ ጌታ ማለት ነው።
21. ሳን፡ እግዚአብሔር በሥራው ሁሉ የተመሠገነ ማለት ነው።
22. ታው፡ እግዚአብሔር እንቅልፍ የሌለበት ትጉህ፤ ድካም የማይሰማው ጽኑዕ የሆነ ፈጣሪ ማለት ነው።

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top