ስለ ታቦት

ስለ ታቦት

ታቦት ማለት ቤተ፣ አደረ ከሚለው የግዕዝ ቃል የወጣ ነው፡፡ ታቦት ማደሪያነቱ ለጽላተ ኪዳኑ ማደሪያና የእግዚአብሔርም መገለጫ ነው፡፡ ስለዚህ ያሉትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶች እንይ፡፡
1. ኦሪት ዘጸአት 24÷8
እግዚአብሔርም ሙሴን፦ ወደ እኔ ወደ ተራራው ውጣ፥ በዚያም ሁን እነርሱን ታስተምር ዘንድ እኔ የጻፍሁትን ሕግና ትእዛዝ የድንጋይም ጽላት እሰጥሃለሁ አለው።
ሙሴና ሎሌው ኢያሱ ተነሡ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወጣ።
2. ኦሪት ዘጸአት 25÷8-30
8፤እያንዳንዱም፡መጋረጃ፡ርዝመቱ፡ሠላሳ፡ክንድ፥እያንዳንዱም፡መጋረጃ፡ወርዱ፡አራት፡ክንድ፡ይኹን፤የዐሥራ፡አንዱም፡መጋረጃዎች፡መጠናቸው፡ትክክል፡ይኹን።
9፤ዐምስቱ፡መጋረጃዎች፡አንድ፡ኾነው፡ይጋጠሙ፥ስድስቱም፡መጋረጃዎች፡ርስ፡በርሳቸው፡አንድ፡ኾነው፡ይጋጠሙ፤ስድስተኛውም፡መጋረጃ፡በድንኳኑ፡ፊት፡ይደረብ።
10፤ከተጋጠሙት፡መጋረጃዎች፡በአንደኛው፡መጋረጃ፡ዘርፍ፡ላይ፡ዐምሳ፡ቀለበቶች፡አድርግ፤ደግሞ፡ከተጋጠሙት፡ከሌላዎቹ፡በአንድኛው፡መጋረጃ፡ዘርፍ፡ላይ፡እንዲሁ፡ዐምሳ፡ቀለበቶች፡አድር።
11፤ዐምሳም፡የናስ፡መያዣዎችን፡ሥራ፥መያዣዎችንም፡ወደ፡ቀለበቶች፡አግባቸው፥ድንኳኑም፡አንድ፡እንዲኾን፡አጋጥመው።
12፤ከድንኳኑ፡መጋረጃዎች፡የቀረ፡ትርፍ፡ግማሽ፡መጋረጃ፡በማደሪያው፡ዠርባ፡ይንጠልጠል።
13፤ማደሪያውን፡እንዲሸፍን፡ከርዝመቱ፡ባንድ፡ወገን፡አንድ፡ክንድ፥ባንድ፡ወገንም፡አንድ፡ክንድ፡
ከድንኳኑ፡መጋረጃዎች፡የቀረው፡ትርፍ፡በማደሪያው፡ውጭ፡በወዲህና፡በወዲያ፡ይንጠልጠል።
14፤ለድንኳኑም፡መደረቢያ፡ከቀይ፡አውራ፡በግ፡ቍርበት፥ከዚያም፡በላይ፡ሌላ፡መደረቢያ፡ከአቍስጣ፡ቍርበት፡አድርግ።
15፤ለማደሪያውም፡የሚቆሙትን፡ሳንቃዎች፡ከግራር፡ዕንጨት፡አድርግ።
16፤የሳንቃው፡ዅሉ፡ርዝመቱ፡ዐሥር፡ክንድ፥ወርዱም፡አንድ፡ክንድ፡ተኩል፡ይኹን።
17፤ለያንዳንዱም፡ሳንቃ፡አንዱን፡በአንዱ፡ላይ፡የሚያያይዙ፡ኹለት፡ማጋጠሚያዎች፡ይኹኑለት፤ለማደሪያው፡ሳንቃዎች፡ዅሉ፡እንዲሁ፡አድርግ።
18፤ለማደሪያውም፡በደቡብ፡ወገን፡ኻያ፡ሳንቃዎችን፡አድርግ።
19፤ከኻያውም፡ሳንቃዎች፡በታች፡አርባ፡የብር፡እግሮችን፡አድርግ፤ከያንዳንዱ፡ሳንቃ፡በታች፡ለኹለት፡ማጋጠሚያዎች፡ኹለት፡እግሮች፡ይኹኑ።
20፤ለማደሪያው፡ለኹለተኛው፡ወገን፡በሰሜን፡በኩል፡ኻያ፡ሳንቃዎች፥
21፤ለእነርሱም፡አርባ፡የብር፡እግሮች፡ይኹኑ፤ከያንዳንዱም፡ሳንቃ፡በታች፡ኹለት፡እግሮች፡ይኹኑ።22፤ለማደሪያውም፡በምዕራቡ፡ወገን፡በስተዃላ፡ስድስት፡ሳንቃዎችን፡አድርግ።
23፤ለማደሪያውም፡ለኹለቱ፡ማእዘን፡በስተዃላ፡ኹለት፡ሳንቃዎችን፡አድርግ።
24፤ከታችም፡እስከ፡ላይ፡እስከ፡አንደኛው፡ቀለበት፡ድረስ፡አንዱ፡ሳንቃ፡ድርብ፡ይኹን፤እንዲሁም፡ለኹለቱ፡ይኹን፤እነርሱም፡ለኹለቱ፡ማእዘን፡ይኾናሉ።
25፤ስምንት፡ሳንቃዎችና፡ዐሥራ፡ስድስት፡የብር፡እግሮቻቸው፡ይኹኑ፤ከያንዳንዱም፡ሳንቃ፡በታች፡ኹለት፡እግሮች፡ይኾናሉ።
26፤ከግራርም፡ዕንጨት፡በማደሪያው፡ባንድ፡ወገን፡ላሉት፡ሳንቃዎች፡ዐምስት፡መወርወሪያዎች፥
27፤በማደሪያውም፡በኹለተኛው፡ወገን፡ላሉት፡ሳንቃዎች፡ዐምስት፡መወርወሪያዎች፥በማደሪያውም፡በስተዃላ፡
በምዕራብ፡ወገን፡ላሉት፡ሳንቃዎች፡ዐምስት፡መወርወሪያዎች፡አድርግ።
28፤መካከለኛውም፡መወርወሪያ፡በሳንቃዎች፡መካከል፡ከዳር፡እስከ፡ዳር፡ይለፍ።
29፤ሳንቃዎቹንም፡በወርቅ፡ለብጣቸው፤ቀለበቶቻቸውንም፡የመወርወሪያ፡ቤት፡እንዲኾኑላቸው፡ከወርቅ፡
ሥራቸው፤መወርወሪያዎችንም፡በወርቅ፡ለብጣቸው።
30፤ማደሪያውንም፡በተራራ፡እንዳሳየኹኽ፡ምሳሌ፡አቁም።
31፤መጋረጃውንም፡ከሰማያዊ፡ከሐምራዊም፡ከቀይም፡ግምጃ፡ከተፈተለ፡ከጥሩ፡በፍታም፡አድርግ፤ብልኅ፡
ሠራተኛ፡እንደሚሠራ፡ኪሩቤል፡በርሱ፡ላይ፡ይኹኑ።
32፤በወርቅ፡በተለበጡት፡ከግራር፡ዕንጨትም፡በተሠሩት፡በአራቱ፡ምሰሶዎች፡ላይ፡ስቀለው፤ኵላቦቻቸውም፡
ከወርቅ፥አራቱም፡እግሮቻቸው፡ከብር፡የተሠሩ፡ይኹኑ።
33፤መጋረጃውንም፡ከመያዣዎቹ፡በታች፡ታንጠለጥለዋለኽ፥በመጋረጃውም፡ውስጥ፡የምስክርን፡ታቦት፡
አግባው፤መጋረጃውም፡በቅድስቱና፡በቅድስተ፡ቅዱሳኑ፡መካከል፡መለያ፡ይኹናችኹ።
34፤በቅድስተ፡ቅዱሳኑም፡ውስጥ፡የስርየት፡መክደኛውን፡በምስክሩ፡ታቦት፡ላይ፡አድርግ።
ለተጨማሪ ፡- ዘጸ.13÷21-22 ፣ 19÷16-18፣ 24÷16-17፣ 33÷10-11፣ 25÷22 ፣16÷17 . ዘዳ.5÷4 ፣ ዘሌዋ.16÷2፣ 9÷6-23፣ 14÷10.

ለታቦት ሊደረግ የሚገባ ስግደትና ክብር 1. መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 7÷6
ኢያሱም ልብሱን ቀደደ፥ እርሱና የእስራኤልም ሽማግሌዎች በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እስከ ማታ ድረስ በግምባራቸው ተደፉ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነሰነሱ።
2. ኦሪት ዘኍልቍ 7÷89
ሙሴም ወደ መገናኛው ድንኳን እርሱን ለመነጋገር በገባ ጊዜ በምስክሩ ታቦት ላይ ካለው ከስርየት መክደኛ በላይ ከኪሩቤልም መካከል ድምፁ ሲናገረው ይሰማ ነበር እርሱም ይናገረው ነበር።
3. መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ 13÷9-14
የእግዚአብሔርም ቍጣ በዖዛ ላይ ነደደ፥ እጁንም ወደ ታቦቱ ስለ ዘረጋ ቀሠፈው በዚያም በእግዚአብሔር ፊት ሞተ።
እግዚአብሔርም ዖዛን ስለ ቀሠፈው ዳዊት አዘነ እስከ ዛሬም ድረስ የዚያን ስፍራ ስም የዖዛ ስብራት ብሎ ጠራው።
በዚያም ቀን ዳዊት፦ የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ እኔ እንዴት አመጣለሁ ብሎ እግዚአብሔርን ፈራ።
ዳዊትም ታቦቱን ወደ ጌት ሰው ወደ አቢዳራ ቤት አሳለፈው እንጂ ወደ እርሱ ወደ ዳዊት ከተማ አላመጣውም።
የእግዚአብሔርም ታቦት በአቢዳራ ቤተሰብ ዘንድ በቤቱ ውስጥ ሦስት ወር ተቀመጠ እግዚአብሔርም የአቢዳራን ቤትና ያለውን ሁሉ ባረከ።
4. መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 4÷5
የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ሰፈር በገባ ጊዜ እስራኤል ሁሉ ታላቅ እልልታ አደረጉ፥ ምድሪቱም አስተጋባች።
5. መጽሐፈ ሳሙኤል ካልዕ 6÷16-23
የእግዚአብሔርም ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ በገባ ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ሆና ተመለከተች፥ ንጉሡም ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ሲዘልልና ሲዘፍን አየች በልብዋም ናቀችው።
የእግዚአብሔርንም ታቦት አገቡ፥ ዳዊትም በተከለለት ድንኳን ውስጥ በስፍራው አኖሩት ዳዊትም የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕትን በእግዚአብሔር ፊት አሳረገ።
ዳዊትም የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕት ማሳረግ ከፈጸመ በኋላ ሕዝቡን በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም መረቀ።
ለሕዝቡም ሁሉ ለእስራኤል ወገን ለወንዱም ለሴቱም ለእያንዳንዱ አንዳንድ እንጀራ አንዳንድም የሥጋ ቍራጭ አንዳንድም የዘቢብ ጥፍጥፍ አከፋፈለ። ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ ወደ ቤቱ ሄደ።
ዳዊትም ቤተ ሰቡን ሊመርቅ ተመለሰ። የሳኦልም ልጅ ሜልኮል ዳዊትን ለመቀበል ወጣችና። ምናምንቴዎች እርቃናቸውን እንደሚገልጡ የእስራኤል ንጉሥ በባሪያዎቹ ቈነጃጅት ፊት እርቃኑን በመግለጡ ምንኛ የተከበረ ነው! አለችው።
ዳዊትም ሜልኮልን፦ በእግዚአብሔር ፊት ዘፍኛለሁ በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ አለቃ እሆን ዘንድ ከአባትሽና ከቤቱ ሁሉ ይልቅ የመረጠኝ እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን ስለዚህም በእግዚአብሔር ፊት እጫወታለሁ።
አሁንም ከሆንሁት ይልቅ የተናቅሁ እሆናለሁ፥ በዓይንሽም እዋረዳለሁ ነገር ግን በተናገርሽው ቈነጃጅት ዘንድ እከብራለሁ አላት።
የሳኦልም ልጅ ሜልኮል እስከ ሞተችበት ቀን ድረስ ልጅ አልወለደችም።
6. መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 3÷3-6
ሕዝቡን፦ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦትና ሌዋውያን ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ፥ ከሰፈራችሁ ተነስታችሁ ተከተሉት።
በእናንተና በታቦቱ መካከል ያለው ርቀት በስፍር ሁለት ሺህ ክንድ ያህል ይሁን በዚህ መንገድ በፊት አልሄዳችሁበትምና የምትሄዱበትን መንገድ እንድታውቁ ወደ ታቦቱ አትቅረቡ ብለው አዘዙ።
ኢያሱም ሕዝቡን፦ ነገ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ድንቅ ነገር ያደርጋልና ተቀደሱ አለ።
ኢያሱም ካህናቱን፦ የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክማችሁ በሕዝቡ ፊት እለፉ ብሎ ተናገራቸው የቃል ኪዳኑንም ታቦት ተሸክመው በሕዝቡ ፊት አለፉ።
በታቦት ላይ የሚነሱ የፕሮቴስታንት ጥያቄዎች
ጥያቄ.1 በዘዳ 31፣18፣32፣15፣134፣1-5፡፡2ኛዜና 5፣10 ያሉትን ጥቅሶች በመጥቀስ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠው ሁለት ጽላቶችን ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እነዚህን እልፍ አእላፋት ጽላቶች ከየት አመጣቻቸው? አራብታችሁ ቅረጹ የሚል አለ ወይ?

መልስ፡- በዘዳ 32፥19፡፡ ስንመለከት እግዚአብሔር ራሱ አዘጋጅቶ ለሙሴ የሰጠውን ሁለቱን ጽላቶች እሥራኤል ጣዖት ሲያመልኩ ስላገኛቸው ሙሴ ተበሳጭቶ ሰብሯቸዋል፡፡ነገር ግን ቸርነቱ ለዘለዓለም የሆነ እግዚአብሔር አምላክ ለሙሴ የመጀመሪያዎቹን አስመስሎ እንዲሰራ ነገረው፤ ሙሴም አስመስሎ ሠራ፡፡ ዘዳ 34፥1-5 መሥራት ብቻ ሳይሆን ዐሥሩን የቃል ኪዳን ቃላትም በጽላቶቹ ላይ እንዲጽፍ ሙሉ ሥልጣን ከእግዚአብሔር ተሰጠው፡፡ ሙሴም ተፈቅዶለታልና አሥሩን ቃላት በጽላቶቹ ላይ ጻፈ፡፡ ዘዳ 34፥27-28 ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ጽላትንም ሆነ ታቦትን እያስመሰሉ ለመሥራት ሙሉ ሥልጣንን አግኝተናል፡፡እንዲሁም ዐሠርቱ ትእዛዛት የተጻፉባቸው ሁለቱ ጽላቶች መባዛት መራባት የለባቸውም ከተባለ በጽላቶቹ ላይ የተጻፉት ዐሠርቱ ትእዛዛት መባዛት የለባቸውም፡፡ ከኢየሩሳሌምም መውጣት የለባቸውም ማለት አይደለም? ትእዛዛቱም ተከለከሉ ማለት ነውና፡፡

ጥያቄ.2 ታቦት በብሉይ ኪዳን ነው በአዲስ ኪዳን ታቦት የለም ይላሉ፡፡
መልስ 2.
የማቴዎስ ወንጌል 5÷17-18
እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም።
እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፥ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፥ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ።
የዮሐንስ ራእይ 11÷19
በሰማይም ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ፥ የኪዳኑም ታቦት በመቅደሱ ታየ፥ መብረቅና ድምፅም ነጐድጓድም የምድርም መናወጥ ታላቅም በረዶ ሆነ።

በመጨረሻም
ጌታ ኢየሱስ በማቴዎስ ወንጌል {5፥17 }እንዲህ አለ “እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም።” ታቦት በእግዚአብሔር ታዝዞ ለእስራኤላውያን የተሰጠ እንጂ በፍጹም ጣኦት አይደለም። በአዲሱ ኪዳን ታቦት አያስፈልግም ብሎ ጌታ ያስተማረበት ቦታ አንድም የለም።
ታቦት፦ ሰማያዊ ምሳሌ ነው ሙሴን “በተራራ ላይ እንዳሳየሁህ ምሳሌ እንድትሰራ ተጠንቀቅ” ብሎታል በዘፀ {25፥40} ይህኑ ደግሞ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ያብራራዋል ” እነርሱም ሙሴ ድንኩዋኑን ሲሰራ ሳለ እንደተረዳ ለሰማያዊ ነገር ምሳሌና ጥላ የሚሆነውን ያገለግላሉ በተራራው እንደተገለጠልህ ምሳሌ ሁሉን ታደርግ ዘንድ ተጠንቀቅ ብሎት ነበርና ” ዕብራ { 8፥5}
የዘመናችን ፈሪሳውያን ታቦትን ጣኦት እያሉ ኦርቶዶክስ ጣኦትን ታመልካለች በማለት ቢቻላቸው በድንጋይ ሊያስወግሩን ደፋ ቀና ይላሉ ..ነገር ግን ታቦትን እና ጣኦትን ምን አንድ አደረገው? በ1ኛ ሳሙ { 5፥1-12} ላይ ብንመለከት ጣኦት በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ውድቆ ሲሰባበር ሲሰግድም እናያለን ምክንይቱም ታቦት የእግዚአብሔር መገለጫ ነው ዘጸ. {25፥ 22 } “በዚያም ከአንተ ጋር እገናኛለሁ፤ የእስራኤልንም ልጆች ታዝዝ ዘንድ የምሰጥህን ነገር ሁሉ፥ በምስክሩ ታቦት ላይ ባለው በሁለት ኪሩቤል መካከል፥ በስርየት መክደኛውም ላይ ሆኜ እነጋገርሃለሁ።” እንዲሁም በዘኁ.{ 7፥89} ላይ እንዲህ ይላል ” ሙሴም ወደመገናኛው ድንኩዋን እርሱን ለማነጋገር በገባ ጊዜ በምስክሩ ታቦት ላይ ካለው ከስርየት መክደኛ በላይ ከኪሩቤልም መካከል ድምፅ ሲናገረው ይሰማ ነበር እርሱም ይናገረው ነበር”
ዘዳ {31፣18፣32፣15፣134፣1-5፡፡2ኛዜና5፣10 }ያሉትን ጥቅሶች በመጥቀስ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠው ሁለት ጽላቶችን ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እነዚህን እልፍ አእላፋት ጽላቶች ከየት አመጣቻቸው? አራብታችሁ ቅረጹ የሚል አለ ወይ? ብለው የሚሞግቱም አሉ ለዚህ ሙሴ የተሰበሩትን አስመስለህ ሁለት ጽላቶች ቅረጽ ከሚል በቀር ጽላቶችን አብዝታችሁ፤ አራብታችሁ ተጠቀሙ የሚል ቀጥተኛ ቃል አምጡ ለሚለው ግን ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን የጽላትም ሆነ የቤተ መቅደስ ሥርዐት፤ የመስዋዕቱ የዕጣኑ አገልግሎት፤ በኢየሩሳሌም ብቻ ስለነበረና፤ የሌላውም አገር ሕዝብ የሚከተለው የጣዖትን ሥርዓት እንጂ የሙሴን ሥርዐት ባለመሆኑ ጽላቱ ተባዝቶ ተራብቶ ለሌላው አገር ሕዝብ አልተሰጠም፡፡ እግዚአብሔርም ከኢየሩሳሌም ውጭ አልፈቀደም የተቀደሰውን ጣዖታውያኑ አሕዛብ ያረክሱታልና ስለዚህ ስግደቱም የቤተመቅደስ ሥርዐቱም በኢየሩሰሳሌም ብቻ ነበር። {ዮሐ 4፥18-24}
ሌላው በኢትዮጵያ ኦርቶኮክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የማርያም፣ የቅዱሳን፣የሰማዕታት፣ የመላዕክት ወዘተ…. ታቦት እየተባለ የተሰየመበት ምክንያቱና የዚህ ስያሜ ከየት ነው የመጣው ምንድን ነው የሚሉ ጥያቄዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ እርግጥ ነው፡፡
እንዲህ ተብሎ መሠየሙ በትንቢተ ኢሳይያስ {56፥46} በተገለጸው መሠረት የእግዚአብሔርን ሰንበቱን ለሚጠብቁ ደስ የሚያሰኘውንም ለሚመርጡ ቃል ኪዳኑንም ለሚይዙ ጃንደረቦች (ስለእግዚአብሔር መንግሥት ራሳቸውን ጃንደረባ ያደረጉ ቅዱሳን) ማቴ {19፥12} በእግዚአብሔር ቤትና በቅጥሩ የዘለዓለም መታሰቢያ እንደሚደረግላቸው የተገለጠ በመሆኑ ይህን አብነት በማድረግ ጌታ ሥጋው፣ ደሙ የሚከብርበት ሆኖ ለቅዱሳኑም መታሰቢያ ለማድረግ ነው፡፡ {መዝ 111፥7} እንዲሁም የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነውና ምሳ {10፥7፡} በዚህ ምክንያት እንጂ በታቦታቱ የሚከብረው መድኃኒተ ዓለምክርስቶስ መሆኑ ግልጽ ሊሆን ያስፈልጋል፡፡

2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 6÷14-15
ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው?ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው?

አስተዋይ ልቦና ይስጠን ተባረኩ…….ይቆየን፡፡

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top