ታቦት ምንድነው ጽላትስ

ስለ ታቦት(ጽላት) የሚነሱ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች እና መልሶቻቸው!

1.ታቦት ምንድነው ጽላትስ?
መልስ፡- ጽላት ማለት ቅዱስ ቃሉ
የተጻፈበት ሰሌዳ ማለት ነው(አስርቱ ትዕዛዛት የተጻፈበት)፡፡ ዘጸአት 34፥27-28፡፡
ታቦት ደግሞ የጽላት ማደሪያ ነው፡፡(ጽላቱ የሚቀመጥበት) ዘጸ 40፥20፡፡
2, እንደ ሙሴ ህግ አሰራራቸው ምን ይመስል ነበር?
መልስ፦ ታቦት እንደሙሴ ሕግ የሚዘጋጀው ከግራር እንጨት ሆኖ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፤ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል ቁመቱም አንድ ተኩል ይሁን ይልና በውስጥና በውጭም በጥሩ ወርቅ ለብጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ አክሊል አድርግለት ይላል፡፡ ደግሞም ታቦቱን የሚሸከሙት ከወርቅ በተሠሩ መሎጊያዎች አራት ሰዎች እንደሆኑ እንረዳለን፡፡
ጽላትም እንደሙሴ ሕግ ከሆነ መዘጋጀትና መጠረብ ያለበት ከከበረ ድንጋይ ነው፡፡ በአንድ ታቦት ውስጥም መቀመጥ ያለባቸው ሁለት ጽላቶች ናቸው፡፡ ዘጸአት 34፥1፡፡ 
3,የአዲስ ኪዳን ጽላት(ታቦት) አሰራሩ እንዴት ነው?
የሐዲስ ኪዳን የታቦትና የጽላት አቀራረጽም ሆነ አጠቃቀሙ የተወሰነውና የሚወሰነው በቀኖና ነው፡፡ ቀኖና ደግሞ እንደ ሁኔታው የሚሻሻል ነው፡፡ (ዶግማ ከሆነ መቀነስም ሆነ መቀነስ አይቻልም ለምሳሌ የ ሥላሴ በአካል ሶስትነት በስልጣን አንድ መሆን ዶግማ ነው።ከጊዜ ጋር የምናሻሽለው አይደለም። ታቦት በአዲስ ኪዳን ግን ቀኖና ስለሆነ አሰራሩን እንደምንችለው መጠን ማድረግ እንችላለን)
እንግዲህ በቤተክርስቲያናችን ቀኖና ካበረከታቸው ነገሮች አንዱ የሐዲስ ኪዳን የታቦትና የጽላት አቀራረጽንና አጠቃቀምን ነው፡፡
ስለዚህ በሐዲስ ኪዳን ታቦትን ለመቅረጽ የግራር እንጨት ባይገኝ በዘፍ 1፥31 ላይ ‹‹ እግዚአብሔርም የፈጠረውን (ያደረገውን) ሁሉ እጅግ መልካም እንደሆነ አየ›› ስለሚልና እግዚአብሔር የፈጠረውን ስለማይንቅ ከግራር ሌላ ከማይነቅዝ እንጨት መቅረጽ እንችላለን፡፡ ቁመቱ ወርዱና ዙሪያውም እንደችሎታችን ይሆናል፡፡ በውስጥና በውጭ ስለሚሆነው የወርቅ ክብርም
እንደችሎታችን ይወሰናል፡፡ ከሌለንም ወርቁ ይቀራል ቀኖና ነውና፡፡
ስለጽላቱም እንደዚሁ ነው ከቻልን ከከበረ ድንጋይ፣ ከዕብነ በረድ መቅረጽ እንችላለን፤ ካልቻልን ጽላቱን ከማይነቅዝ እንጨት መቅረጽ እንችላለን፡፡ በሌላ በኩልም ከቻልን እንደ ብሉይ ኪዳኑ በአንድ ታቦት ሁለት ጽላት ማስቀመጥ እንችላለን፤ ካልቻን በአንድ ታቦት አንድ ጽላት ብቻ ይሆናል፡፡ቀኖና ነውና!
4, ለሙሴ የሰጠው አንድ ታቦት ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እነዚህን እልፍ አእላፋት ጽላቶች ከየት አመጣቻቸው? አራብታችሁ ቅረጹ የሚል አለ ወይ?
መልስ፡- በዘጸ 32፥19፡፡ ስንመለከት እግዚአብሔር ራሱ አዘጋጅቶ ለሙሴ የሰጠውን ሁለቱን ጽላቶች እሥራኤል ጣዖት ሲያመልኩ ስላገኛቸው ሙሴ ተበሳጭቶ ሰብሯቸዋል፡፡ነገር ግን ቸርነቱ ለዘለዓለም የሆነ እግዚአብሔር አምላክ ለሙሴ የመጀመሪያዎቹን አስመስሎ እንዲሰራ ነገረው፤ ሙሴም አስመስሎ ሠራ፡፡ ዘጸአት 34፥1-5 መሥራት ብቻ ሳይሆን ዐሥሩን የቃል ኪዳን ቃላትም በጽላቶቹ ላይ እንዲጽፍ ሙሉ ሥልጣን ከእግዚአብሔር ተሰጠው፡፡
ሙሴም ተፈቅዶለታልና አሥሩን ቃላት በጽላቶቹ ላይ ጻፈ፡፡ ዘጽአት 34፥27-28
ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ጽላትንም ሆነ ታቦትን እያስመሰሉ ለመሥራት ሙሉ ሥልጣንን አግኝተናል፡፡
5, ሙሴ የተሰበሩትን አስመስለህ ሁለት ጽላቶች ቅረጽ ከሚል በቀር ጽላቶችን አብዝታችሁ፤ አራብታችሁ ተጠቀሙ የሚል ቀጥተኛ ቃል አምጡ?
መልስ፦ በብሉይ ኪዳን የጽላትም ሆነ የቤተ መቅደስ ሥርዐት፤የመስዋዕቱ የዕጣኑ አገልግሎት፤ በኢየሩሳሌም ብቻ ስለነበረና፤ የሌላ አብዛኛው አገር ሕዝብ የሚከተለው የጣዖትን ሥርዓት እንጂ የሙሴን ሥርዐት ባለመሆኑ ጽላቱ ተባዝቶ ተራብቶ ለሌላው አገር ሕዝብ አልተሰጠም ነበር።
ያም ሆነ ይህ በሐዲስ ኪዳንም በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው በአብ፤ በወልድ፤ በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠምቀው ፤ሁለተኛ የድኅነት ልደት ተወልደው የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ሥልጣን ሰጣቸው።
ለክርስቲያኖችም ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መግቢያ ድረስ እንደሚበዙና በአዲስ ኪዳን በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ንጹሕ የሆነውን ቁርባን ከኢየሩሳሌም ውጭ በየቦታው ለእግዚአብሔር ማቅረብ እንደሚችሉ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡፡
1. ‹‹ ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ይከበራልና፤ በየስፍራው ለስሜ ዕጣን ያጥናሉ፤ ንጹሕንም ቁርባን ያቀርባሉ፤ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና ይላል ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር›› ሚል 1፥11፡፡
2. ‹‹ ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎ የለምን? እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችኋት ብሎ አስተማራቸው›› ማር11፥17
ይህ ትንቢት በቀጥታ ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች መሆኑ ግልጥ ነው፡፡
ምክንያቱም በብሉይ ኪዳን ቤተ መቅደስም ሆነ የዕጣን፤ የቁርባን አገልግሎት እንኳን ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መግቢያ ድረስ ላሉ አሕዛብ በኢየሩሳሌም ከሚኖሩ የእግዚአብሔር ሕዝቦች በቀር ለእስራኤል ጎረቤት አገሮች እንኳ አልተፈቀደምና፡፡ ነቢዩ ሚልክያስ ንጹሕ ዕጣን ያለው በማቴ 2፥11፡፡ ወንጌል እንደተናገረው ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሰብአ ሰገል በቤተልሔም ዋሻ ለክርስቶስ ካቀረቡት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በዓለም ያለን ክርስቲያኖች በክርስቶስ ስም ለክርስቶስ የምናቀርበው ቅዱስ ዕጣን ነው፡፡
ንጹሕ ቁርባን የሚለውንም በማቴ 26፥26፤” ጌታ ኅብስቱን አንሥቶ ነገ የሚቆረሰው ሥጋዬ ይህ ነው፤ ወይኑንም አንሥቶ ነገ ስለብዙዎች ሀጢአት የሚፈሰው ደሜ ይህ ነው” ብሎ ለሐዋርያት የሰጣቸው የክርስቶስ ሥጋና ደም ነው፡፡ ንጹሕ የተባለው እርሱ በባሕርዩ ንጹሕ ሆኖ የእኛን የኃጢአት እድፍ ስለሚያነጻ ነው፡፡(ዛሬ በታቦቱ ላይ ነው ይህ ስጋ እና ደም የሚፈተተው (የሚቀርበው) )
በብሉይ ኪዳን በኢየሩሳሌም ብቻ መሆን የሚገባቸው ቤተ መቅደሱ፤ ዕጣኑ፣ ቁርባኑ፣ በክርስቶስ ደም በአዲስ ሕይወት፣ በአዲስ ተፈጥሮ፤ በአዲስ ሥርዓት፣ ክርስቲያኖች ለሆንን ለዓለም ሕዝቦች በየሥፍራው (በያለንበት) እንድንጠቀምባቸው ከተፈቀዱልን በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩት ሁለቱ ጽላቶች ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መግቢያ ተባዝተው በዓለም ያለን ክርስቲያኖች በያለንበት በየቤተ መቅደሳችን ለሥጋውና ለደሙ የክብር ዙፋንነት ብንገለገልባቸውና የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ብናከብርባቸው ምን የሚጎዳ ነገር ተገኘ? የሚያስደነግጠውስ ምኑ ነው? ስህተቱስ የቱ ላይ ነው

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top