ቅዱሳን፣ጻድቃን፣ሰማዕታት በመፅሓፍ ቅዱስ

ቅዱሳን፣ጻድቃን፣ሰማዕታት በመፅሓፍ ቅዱስ

በብሉይ ኪዳን

• ኢያሱ ጸሐይን አቆመ።(ኢያ.10፣13) ሕዝቡም ጠላቶቻቸውን እስኪበቀሉ ድረስ ፀሐይ ቆመ፥ ጨረቃም ዘገየ።
• ሶምሶን የመኳንንቱን ቤት አፍርሷል።(መሳ.16፣30) ምሰሶቹን በሙሉ ኅይሉ ገፋ፥ ቤቱም በውስጡ በነበሩት በመኳንንቱም በሕዝቡም ሁሉ ላይ ወደቀ።
• ኤልያስ ሰማይን ለጉሟል ደግሞም መልሶ ዝናብ እንዲዘንብ አድርጓል።(1ኛ ነገ18፣41-45) ከጥቂትም ጊዜ በኋላ ሰማዩ ከደመናውና ከነፋሱ የተነሣ ጨለመ፥ ብዙም ዝናብ ሆነ፤
• አልያስም ኤልሳዕም የዮርዳኖስን ባሕር ከፍለዋል(2ኛ ነገ.2፡8 2፣19)
• አልያስ በሰራፕታ የባልቴቷን ቤት በበረከት ሞልቷል።(1ኛ 17፣14) በምድር ላይ እግዚአብሔር ዝናብ እስከሚሰጥበት ቀን ድረስ፥ ዱቄቱ ከማድጋ አይጨረስም፥ ዘይቱም ከማሰሮው አይጎድልም።
• አልያስ የሞተ ልጇን አስነስቷል።(1ኛነገ 17፣22) እግዚአብሔርም የኤልያስን ቃል ሰማ፤ የብላቴናው ነፍስ ወደ እርሱ ተመለሰች፥ እርሱም ዳነ።
• ኤልሳዕም ለሱነማዊት ሴት በረከት ሰጥቷል የሞተ ልጇንም አስነስቷል(2ኛ ነገ 4 1-35 ) መጥቶም በሕፃኑ ላይ ተኛ፤ አፉንም በአፉ፥ ዓይኑንም በዓይኑ፥ እጁንም በእጁ ላይ አድርጎ ተጋደመበት፤ የሕፃኑም ገላ ሞቀ።ተመልሶም በቤቱ ውስጥ አንድ ጊዜ ወዲህና ወዲያ ተመላለሰ፤ ደግሞም ወጥቶ ሰባት ጊዜ በሕፃኑ ላይ ተጋደመ፤ ሕፃኑም ዓይኖቹን ከፈተ።
• ኤልሳዕ ንዕማንን ከለምጹ አንጽቶታል።2ኛ ነገ 4፣42-44 በባህር የሰጠመውን መጥረቢያ በውሃ ላይ እንዲሳፈፍ አድርጓል። 2ኛ ነገ 6፣6
• ኤልሳዕ የደቀመዝሙሩን ዓይነልቡና ተከፍቶ መላዕክትን ለማየት እንዲበቃ አድርጓል።(2ኛ ነገ 6፡17) የሶርያውን ሰራዊት አይናቸው እንዲታወር አድርጓል።
• ኤልሳዕ በተቀበረበት ቦታ የወደቀ የሞተ ሰው ከሞት ተነስቷል።ከሞተ በኋላ እንኳ ሙት አስነስቷል።(1ኛ ነገ 13፣21) ሰዎችም አንድ ሰው ሲቀብሩ አደጋ ጣዮችን አዩ፥ ሬሳውንም በኤልሳዕ መቃብር ጣሉት፤ የኤልሳዕንም አጥንት በነካ ጊዜ ሰውዮው ድኖ በእግሩ ቆመ።
• ሰለስቱ ደቂቅ ከሚነድ እሳት ውስጥ ምንም ሳይሆኑ ወጥተዋል።(ዳን3፣23)
• ዳንኤል ከአናብስት ጉድጓድ በሰላም ወጥቷል።(ዳን 6፤22) መልአኩን ልኮ የአንበሶችን አፍ ዘጋ፥ እነርሱም አልጐዱኝም አለው።
• ዮናስ በአሳአንበሪ ሆድ 3 መዓልት 3 ልሊት ቆይቶ ምንም ሳይሆን ወጥቷል።(ዮና 2፣1) ዮናስም በዓሣው ሆድ ውስጥ ሆኖ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፥ እንዲህም አለ።

በሐዲስ ኪዳን
• ጴጥሮስ ጣቢታን ከሞት አስነስቷል።(ሐዋ.9፣40) ጣቢታ ሆይ፥ ተነሺ አላት። እርስዋም ዓይኖችዋን ከፈተች ጴጥሮስንም ባየች ጊዜ ተቀመጠች።
• ጴጥሮስ ሃናንያና ሰጲራ እንዲሞቱ አድርጓል።(ሐዋ.5፣5-10) ሐናንያም ይህን ቃል ሰምቶ ወደቀ ሞተም…. ያን ጊዜም በእግሩ አጠገብ ወደቀች ሞተችም
• ጴጥሮስና ዮሐንስ ሽባውን ተርትረዋል/ፈውሰዋል/።(ሐዋ 3፣2-11)
• ጳውሎስም አውጤኪስን ከሞት አስነስቷል።(ሐዋ20፣9) ከሦስተኛው ደርብ ወደ ታች ወደቀ፥ ሞቶም አነሡት። ጳውሎስም ወርዶ በላዩ ወደቀ፥ አቅፎም። ነፍሱ አለችበትና አትንጫጩ አላቸው።
• ጳውሎስ እባቢቱ እንዳልጎዳቸው ምንም ሳይሆን እዳራገፋት ይናገራል።(ሐዋ.28፣5) እርሱ ግን እባቢቱን ወደ እሳት አራገፋት አንዳችም አልጐዳችውም፤
• የቅዱስ ጴጥሮስ ጥላው ይፈውሳቸው ዘንድ ድውያንን ያሰልፉ ነበር።(ሐዋ 5፣ 15) ስለዚህም ጴጥሮስ ሲያልፍ ጥላውም ቢሆን ከእነርሱ አንዱን ይጋርድ ዘንድ ድውያንን ወደ አደባባይ አውጥተው በአልጋና በወሰካ ያኖሩአቸው ነበር።
• ፊሊጶስ ከጃንደረባው ዓይን በመንፈስ ተነጥቆ እንደተሰወረ መጽሐፍ ይነግረናል።(ሐዋ.8፣39)

እንግዲህ ከላይ በጥቂቱ የተመለከትነው በብሉይም በሐዲስ ኪዳንም የነበሩ አባቶቻችን ታላላቅ ድንቅ የሆኑ ተአምራት ሲያደርጉ ነው። ታዲያ በእነዚያ ዘመናት ሁሉ ታላለቅ ድንቅ ተአምራትን እንዲያደርጉ ሲያደርጋቸው የነበረ መንፈስ ቅዱስ ዛሬ እየሰራ መሆኑን የምናምን ከሆነ ለምን የገብረመንፈስ ቅዱስ ፣የአቡነተክለሃይማኖት ፣የእነ ቂርቆስ ኢየሉጣን ድንቅ ተአምራት መቀበል አቃተን?

ሰለስቱ ደቂቅ ከእሳት ምንም ሳይሆኑ መውጣታቸውን ካመኑ ለምን የቂርቆስ እና ኢየሉጣ ከፈላ ውሃ ምንም ሳይሆኑ መውጣት ይጎረብጣቸዋል?
ለኢያሱ ግዑዝ ፍጥረት ጸሐይ ታዝዛ ከቆመች ለአቡነገብረመንፈስ ቅዱስ አናብርቱ አናብስቱ መታዘዛቸው ምን ያስገርማል?
የኤልሳዕ አጽም ሙት ካስነሳ ፤በሕይወት የነበሩ አባቶቻችን ሙት ማስነሳታቸው ምን ያስገርማል?

ጌታችንም እኮ ያለው(ዮሐ.14፤ 12) እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል።

ታዲያ በእርሱ ካመኑ ምን ማድረግ ይሳናቸዋል? እኛም እኮ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለውን ታሪክ እንድንተርክ ሳይሆን እንድንኖረው ነው የሚጠበቅብን። ቅዱስ ጴጥሮስ ሙት ካስነሳ ፣እኛም ሕይወታችንን ብናስተካክል ፍጹም ክርስቲያኖች ብንሆን በቅዱስ ጴጥሮስ ላይ የሰራ መንፈስ ቅዱስ በእኛም ላይ ይሰራልና ሙታን ማስነሳት እንችላለን።ስለዚህ አባቶቻችን ምንም ዓይነት ተአምራት ቢፈጽሙ በእነርሱ አድሮ ስራ የሚሰራ መንፈስ ቅዱስ ነውና ሊሆን አይችልም የሚስብል ነገር አይኖርም።

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top