የቅዱሳን አማላጅነት በአፀደ ሥጋ እና በአጸደ ነፍስ

የቅዱሳን አማላጅነት በአፀደ ሥጋ እና በአጸደ ነፍስ

የአማላጅነት ትምህርት በዘመነ አበው በሕገ ልቡና፣ በዘመነ ኦሪት በመጻሕፍተ ብሉያት በዘመነ ሐዲስ በመጻሕፍተ ሐዲሳት የነበረና አሁንም ያለ ወደፊትም የሚቀጥል ትምህርት እንጂ ከጊዜ በኋላ ድንገት የመጣ አይደለም፡፡ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችንም የቅዱሳት መጻሕፍትን የሐዋርያትንና የሊቃውንትን ትምህርትና ትውፊት ታስተምራለች፡፡ አማላጅነት እግዚአብሔር የሚፈቅደውና የሚወደው እንጂ ሰው ሰራሽ ልማዳዊ ወግ አይደለም ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደምንረዳው ክርስትና ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ የአማላጅነት ትምህርት ያለ እንጂ በኋላ ጊዜ ብቅ ያለ አይደለም፡፡

ዛሬ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በተለይ በሀገራችን ውስጥ በየአውቶቢስ ማቆሚያው በመናፈሻዎች፣ በሠረግ ቤት፣ በለቅሶ ቤት፣ በሆቴሎች፣ በመሥሪያ ቤቶች ፣ በትምህርት ቤቶች፣ በመኖሪያ አካባቢዎች በገጠር በከተማ እጅግ አከራካሪና አወዛጋቢ የሆነው አቢይ ጉዳይ በአማላጅነት ላይ የሚነሳው አቢይ ጥያቄ ነው፡፡ ሰዎች ስለአማላጅነት ያላቸው አቋም የሚከተሉትን እምነት የሚጠቁም በመሆኑ ያ ብዙ ውጣ ውረድ የሰዎችን እምነት አቋም መለያ ሆኗል ከዚህም የተነሣ ወላጆችና ልጆች ባል ከሚስት ጓደኛ ከጓደኛ ጎረቤት ከጎረቤት ወዘተ ተቆራርጧል ተለያይቷል፡፡

እኛ ኦርቶዶክሳውያን ፃድቃን ሰማዕታት ቅዱሳን መላእክት ይልቁንም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያማልዱናል ከፈጣሪያችን ዘንድ ያስታርቁናል ብለን የምናምነው እምነት የምንቀበለው ትምህርት የቅዱሳንን አማላጅነት ለማይቀበሉት ወገኖች ጆሮን የሚያሳክክ የእግዚአብሔርን ክብር የሚነካ ትምህርት መስሎ ይታያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ የቅዱሳንን አማላጅነት የሚቃወሙት ወገኖች ክብር ምስጋና ይግባውና የባሕሪ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስን አማላጃችን ነው የሌሎችን ፍጡራን ረዳትነት አንሻም የሚለው ትምህርት ለእኛ ለኦርቶዶክሳውያን ጆሮ የሚዘገንንና የሚቀፍ ከመሆኑ ባሻገር ምንፍቅናና ክህደትም ጭምር ነው፡፡

በሃይማኖት የምንመስላቸው ጥንታውያን የሆኑት የእስክንድርያ ፣ የሦርያ፣ የሕንድና የአርመንያ አቢያተ ክርስቲያናት የቅዱሳንን አማላጅነት በሚገባ ይቀበላሉ፡፡ እንዲሁም በሃይማኖት ቀኖና ዶግማ ከእኛ የሚለዩት ጥንታውያን የሆኑት የሮም ካቶሊክና የግሪክ ፣ የራሽያ፣ የሮማንያ ኦርቶዶክስ አቢያተ ክርስቲያናትም እንዲህ የአማላጅነትን ትምህርት ተቀብለዋል የቅዱሳንን አማላጅነት የሚቃወመው ትምህርት ብቅ ማለት የጀመረውና በኋላም የተስፋፋው ከ13ኛው -16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ውስጥ ይልቁንም በተሃድሶ (Reformation) እንቅስቃሴ ጊዜ ነው፡፡

የታሪክ ምስክርነት ካየን ይህ ትምህርት በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ በተለያዩ ዘመናት እንደተነሱ የኑፋቄ አስተሳሰቦች በፍፃሜ ዘመን እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውሃ ፈሳሽ የተፈጠረ እንግዳ ትምህርት እንጂ ከጥንት ከመሠረት የመጣ አይደለም፡፡ በመሆኑም በየጊዜው የጥንቱን ትምህርት እየተው በእንግዳ ትምህርት መወሰድ እንደማይገባ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስጠነቅቃሉ፡፡ (ዕብ 13፡8)

  1. ማማለድ ምንድን ነው?

ማማለድ የሚለው ቃል በግዕዝ ቋንቋ “ተንበለ” ለመነ አማለደ ከሚለው ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም አንዱ ስለሌላው ለመነ ጸለየ ማለት ነው፡፡ ማማለድ ማለት አንዱ ስለሌላው ችግር መቃለል መጸለይ መለመን ማለት ነው ፡፡ ይህ ትርጉም በማንኛውም ኅብረተሰብና ግለሰብ ዘንድ ግልጽና የተረዳ ነው ምክንያቱም በቀን ተቀን ሕይወታችን የምናየውና የምንተገበረው ጉዳይ ስለሆነ ነው፡፡ ከትርጉሙ ስንነሣ በአማላጅነት ተግባር ውስጥ ሦስት ወገኖች ያሉ ሲሆን እነሱም አማላጅ ተማላጅና የሚማለዱለት ናቸው ሦስቱም ለአማላጅነት ስምረት የተለያየ ድርሻ አላቸው፡፡

ሀ/ አማላጅ
ማማለድ ለፍጡራን ባሕርይ የሚስማማ የትህትና ሥራ በመሆኑ አማላጆች ብዙ ናቸው በአጠቃላይ ሲነገር ቅዱሳን ሰዎችና ቅዱሳን መላዕክት ሲሆኑ እመቤታችን ደግሞ የአማላጆች ሁሉ የበላይ ነች የአማላጆች ተግባር በኃጢአን ፈንታ ስለኃጥአን ወደ እግዚአብሔር ምልጃ ማቅረብ ነው ቅዱሳን ሰዎች በሕይወተ ሥጋ ሳሉ በጾም በስግደት በቁመት ወዘተ በጠቅላላ አስጨናቂ የሆኑ መከራዎችን እየተቀበሉ ልክ ለራሳቸው እንደሚለምኑ አድርገው ስለኃጥአን ያማልዳሉ እንዲያውም አንዳንዱ ቅዱሳን የራሳቸውን ዘላለማዊ ደኅንነት በኃጥአን መጽደቅ በመለወጥ ወደ ፈጣሪያቸው እንደሚለምኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግቦ እናነባለን፡፡

‹‹ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ ወዮ አኒህ ሕዝብ ታላቅ ኃጢአት ሠርተዋልና ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል አሁን ይህን ኃጢአታቸውን ይቅር በላቸው ያለዚያ ግን ከጻፍከው መጽሐፍ እባክህ ደምስሰኝ›› አለ (ዘዳ “2-“1)
በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ብዙ ኀዘን የማያቋርጥ ጭንቀት በልቤ አለብኝ ስል በክርስቶስ ሆኜ እውነት እናገራለሁ አልዋሽም ኅሊናዬም በመንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልኛል በሥጋ ዘመዶቼ ስለሆኑ ስለወንድሞቼ ከክርስቶስ ተለይቼ እኔ ራሴ የተረገምሁ እንደሆን እጸልይ ነበርና በማለት ገልጸአል›› (ሮሜ9፡1-3)፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስም ስለ ጣዖት አምላኪ ወገኖች ተነክቶ ከአባቶቼ አልበልጥምና ውሰደኝ አለ››

ለ/ ተማላጅ
ተማላጅ ማለት የአማላጆችን ጸሎት ልመና ወይም ምልጃ ተቀባይ ወይም የምልጃ የልመና የጸሎት መድረሻ ማለት ነው፡፡ በሃይማኖታችን ትምህርት ውስጥ የጸሎት ሁሉ መድረሻ እግዚአብሔር ነው ተማላጄ እግዚአብሔር እንደ አማላጆች ብዙ አይደለም አንድ ነው እንጂ አንድ እግዚአብሔር ስንል አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስን ማለታችን ነው እግዚአብሔር አንድ ሲሆን ሦስት፣ ሦስት ሲሆን አንድ ነው ይህም አንድነቱ ሦስትነቱን ሳይጠቀልለው ሦስትነቱ አንድነቱን ሳይከፍለው፣ ሦስቱ አካላት በአንድ ጌትነት፣ በአንድ ስልጣን ፣ በአንድ ክብር ፣ በአንድ መለኮት፣ በአንድ መንግስት፣ በአንድ ፈቃድ በሰማይና በምድር የሚገኙ የፍጡራንን ምስጋናና ልመና ጸሎት ተቀብለው የፈቃዳቸውንና የቸርነታቸውን ሥራ ይፈጽማሉ፡፡ በሦስቱ አካላት በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ መካከል የበላይና የበታች ጸሎት አቀባይ የለም ‹‹በሰማይና በምድርም ከምድርም በታች በባሕርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለበጉ ይሁን ሲሉ ሰማሁ፣ አራቱም እንሰሶች አሜን አሉ ሊቃናቱም ወድቀው ሰገዱ›› (ራእ 5:.13-14)

ሐ/ የሚማለዱለት
አማላጆች ወደ እግዚአብሔር ምልጃ የሚያቀርቡት ስለኃጥአን ሰዎች መዳን ነው ርኩሳን መናፍስት ቢኖሩም የአማላጅነት በረከትና ቸርነት የተፈቀደውና የሚያገለግለው ለኃጢአን ሰዎች ብቻ ነው የሚጸለይለት ወይም የሚማለድለት ሰው ወይም ሕዝብ በአማላጅነት ስራ ውስጥ የራሱ ድርሻ አለው ይኸውም በአማላጁ ጸሎት በተማላጅ ችርነት ማመንና ከሚሠራው ኃጢዓት የሚመለስ ተነሣሒ ልቡና ያለው መሆን አለበት፡፡

ነገር ግን አማላጆች አሉልኝ ብሎ በኃጢአት ላይ ኃጢአት ቢሠራ አማላጆች ቅዱሳንን የኃጢአታችን ተባባሪ እግዚአብሔርን ደግሞ የማይፈርድ ፈጣሪ ማድረግ ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር የአማላጆችን ምልጃ የማይቀበልበት ጊዜ አለ ይህም የሚሆነው የሚማለድለት ኀጥኡ በሠራው ኃጢዓት የማይጸጸትና በዚያው የሚጸና ሲሆን ነው፡፡ ለዚህም ቅዱስ መጽሐፍ ‹‹እግዚአብሔርም ሳሙኤልን በእስራኤል ላይ እንዳይነግሥ ለናቅሁት ለሳኦል የምታለቅስላት እስከመቼ ነው›› (1ሳሙ 16:1) እንዲሁም እንግዲህ አልሰማህምና ስለዚህ ሕዝብ አትጸልይ ስለ እነርሱም ልመናና ጸሎት አታድርግ አትማልድላቸው እነርሱስ በይሁዳ ከተሞች ውስጥና በኢየሩሳሌም አደባባይ ላይ የሚያደርጉትን አታይምን ያስቆጡኝ ዘንድ ለሰማይ ንግስት እንጎቻ እንዲያደርጉ ለሌሎችም አማልክት የመጠጥ ቁርባን እንዲያፈሱ ልጆች እንጨት ይሰበስባሉ አባቶችም እሳት ያነዳሉ ሴቶችም ዱቄት ይለውሳሉ እኔ ያስቆጣሉን? ይላል እግዚአብሔር ……….›› (ኤር 7.17) በተጨማሪ ‹‹እግዚአብሔርም እንደዚህ አለኝ ሙሴና ሳሙኤል በፊቴ ቢቆሙም ልቤ ወደ ዚህ ሕዝብ አይዘነበልም ከፊቴ ጣላቸው ይውጡ›› (ኤር15.1) በማለት ያስረዳል፡፡

  1. የቅዱሳን አማላጅነት ለምን አስፈለገ?የቅዱሳን አማላጅነት ያስፈለገበት ምክንያት አንድም ጸሎታችን በፍጥነት ወደ እግዚአብሔር ስለሚደርስልን ሌላው ፈጣሪያችን የወዳጆቹን ይልቁንም የእናቱን የድንግል ማርያምን ጸሎት ተቀብሎ ስለቅዱሳን ፣ በተለይም ስለ እናቱ ብሎ የቸርነቱን ሥራ ስለሚሠራልን ችግራችንን ስለሚያቃልልን ነው፡፡ የቅዱሳንን ጸሎት ከኀጥአን ጸሎት ይልቅ እንደሚሰማ መጽሀፍ ቅዱስ እንዲህ ይገልፃል፣ ‹‹የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮቹም ወደ ጩኸታቸው (ልመናቸው) ናቸው›› (መዝ 33.13-20) በተጨማሪም (ምሳ 10.24) ፣ (ምሳ 15፡8) ፣ (ምሳ 15፡29) ፣ (ዮሐ 15፡7) ፣ (ያዕ 5፡16-18)፣ (ራዕ 8፡3-4) ያሉትን ያገናዝቡ፡፡

የቅዱሳን ጸሎትና ልመና በፈጣሪ ዘንድ ተወዳጅ ሊሆን የቻለው ቅዱሳን ሰውነታቸውን ከቂም ከበቀል ከኀጢዓት ስላነጹ እግዚአብሔር የማይወደውን ልመና ስለማይለምኑና ልመናቸው እንደሚፈጸም በፍጹም ልብ አምነው ስለሚጸልዩ ነው፡፡ ይህንንም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይገለጽልናል፡፡
‹‹የጻድቃን ምኞት በጎ ብቻ ነው የኀጥአን ተስፋ ግን መቅሰፍት ነው›› ፣ ‹‹የጻድቃን ሐሳብ ቅን ነው የኀጥአን ምክር ግን ተንኮል ነው››፣
‹‹ስለዚህ እላችኋለሁ የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ ይሆንላችሁማል›› (ምሳ 11፡23 ፣ ምሳ 12፡5 ፣ ማቴ 20፡20-22፣ ማር 11፡24) ቅዱሳን ሰዎችና ቅዱሳን መላእክት ኀጥአን ምህረትን ሲያገኙ እጅግ ደስ ይላቸዋል፡፡ እግዚአብሔርም የሚወዳት ቅድስት እናቱና የሚወዳቸው ቅዱሳን ወዳጆቹ ስለኀጥአን ምህረት ሲለምኑት እናቱና ወዳጆቹን ለማስደሰት ሲል ልመናቸውን ሰምቶ ይፈጽምላቸዋል፡፡

ይህንም ጌታችን በወንጌል ‹‹እላችኋለሁ ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኙ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል›› ‹‹እላችኋለሁ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላዕክት ፊት ደስታ ይሆናል›› (ሉቃ 15፡7) ‹‹በዚያን ቀንም ከእኔ አንዳች አትለምኑም እውነት እውነት እላችኋለሁ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል እስካሁን በስሜ ምንም አለመናችሁም ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ለምኑ ትቀበሉማላችሁ›› (ዮሐ 16፡23)

የቅዱሳን አማላጅነት የእግዚአብሔርን ክብር የሚጋፋ ሳይሆን የበለጠ ፈጣሪን የማክበር ምልክት ነው ይህም በመሆኑ እግዚአብሔር ራሱ ሰውን ወደ አማላጅ የመራበት ጊዜም አለ አምላካችን እግዚአብሔር በሰው ልጆች ላይ መቅሰፍት ከማምጣቱ በፊት ለወዳጆቹ ያሳውቃል፡፡ ለምሣሌ ዓለምን በደመሰሰውን የጥፋት ውሃ መምጣት ለኖህ፣ የሰዶምና የገሞራን ጥፋት ለአብርሃም የነነዌን ሰዎች ኃጢዓት ለዮናስ፣ የእስራኤልንም መማረክ መበዝበዝና ቅጥር መፍረስ ለነቢያት ገልጽዋል፡፡
እግዚአብሔር ለወዳጆቹ አስቀድሞ የሚገልጽበት ምክንያት፡-

  1. ሕዝቡን አስተምረውና መክረው ከገቢረ ኃጢዓት ወደ ገቢረ ጽድቅ ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር በንስሐ እንዲመልሱትና የማይመለሰውንም በተሰጣቸው ሥልጣን እንዲዘልፍና እንዲገስጽ (ዘዳ 14፡27፣ ሐዋ 5፡5ና10)

  2. ስለ ሕዝቡ ኃጢዓት እግዚአብሔርን መዓቱን በምህረት ቁጣውን በትዕግስት እንዲያማልዱ እና

  3. ሕዝቡ እንዲመለስ በትምህርታቸው ከማስተማራቸው ባሻገር በሕይወታቸው ብርሃን ሆነው በጨለማው ዓለም እንዲያበሩ ነው፡፡

በአፀደ ሥጋ (በሕይወተ ሥጋ) ያሉ ቅዱሳን እንደሚያማልዱ በርካታ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎች አሉ በመሠረቱ ማንኛውም ክርስቲያን ለሌላው ወንድሙ እንዲፀልይ ታዟል (ያዕ 5፡16) ባለቤቱ መድኃኔዓለም ያስተማረን ‹‹አቡነ ዘበሰማያት›› ጸሎት ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለሌላውም ጭምር የምንጸልየው ጸሎት ነው ምልጃ በክርስቲያኖች የጸሎት ተግባር ውስጥ ሰፊ ሥፍራ አለው፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን በመጽሐፍ ሲያብራራ ‹‹እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለሰዎች ሁሉ ስለነገስታት ስለመኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው›› (1ጢሞ 2፡1-
4) ‹‹ጌታ ቅርብ ነው በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ›› (ፊልጵ 4፡6) ብሏል፡፡
ነቢዩ ኢሳይያስም ‹‹እግዚአብሔርም ላይ ፍርድም ስለሌለ ተስፋ ሰውም እንደሌለ አየ ወደ እርሱም የሚማልዱ እንደሌለ ተረዳ ተደነቀም (ኢሳ 59፡16) ብሏል፡፡ ጌታችንም በወንጌል በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ የሚረግሟችሁን መርቁ ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ፣ ስለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ›› (ማቴ 5፡43-47) በማለት እንኳን ለወዳጆቻችን ለጠላቶቻችንም ቢሆን መፀለይ እንደሚገባ አዘናል አማላጅነት በሁሉ የታዘዘ ቢሆንም የቅዱሳን አማላጅነት ግን የላቀና የከበረ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ፈጣን ምላሽ የሚያስገኝ ስለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽና በማያሻማ መልኩ ይተርክልናል፣
ለምሳሌ ያህልም የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎች እንመልከት፣
1. በዘፍ 18፡16-33 ውስጥ ቅድስት ሥላሴ በአብርሃም ቤት በእንግድነት ከተገኙ በኋላ ወደ ሰዶምና ገሞራ ሲሄዱ ‹‹እኔ የማደርገውን ከአብርሃም እሰውራለሁን በማለት ስለሰዶም ኃጢዓት በነገሩት ጊዜ አብርሃም እንዴት እንደ ማደማለደ ይገልጻል›› የአብርሃም ምልጃ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ቢኖረውም በከተማይቱ 1 ፃድቃን ስላልተገኘ አንድ ሎጥ ብቻ በመገኘቱ ከተማይቱ ወደመች

  1. ‹‹በዘፍ 19፡18-22 የተናገርካትን ከተማ እንዳላጠፋት እነሆ በዚህ ነገር የለመንከኝን ተቀብያለሁ›› በማለት እንደሰዶምና ገሞራ ልትጠፋ የነበረች ከተማ ሎጥ ሸሽቶ ስላረፈባት መላዕክት ስለሎጥ ልመና ሳያጠፏት ትቷታል፡፡

  2. ‹‹በዘፍ 20፡1-18›› የጌራራ ንጉሥ አቤሚሊክ የአብርሃምን ሚስት ሳራን ለሚስትነት ስለወሰዳት እግዚአብሔር ተቆጥቶ ቤተሰቡን በሙሉ እንደሚቀስፍ እንዲህ አለው ‹‹እኔ ደግሞ በፊቴ ኃጢዓት እንዳትሠራ ከለከልሁህ ስለዚህም ትነካት ዘንድ አልተውኩህም አሁንም የሰውየውን ሚስት መልስ ነብይ ነውና ስለአንተ ይጸልያል ትድናለህም ባትመልሳት ግን አንተ እንድትሞት ለአንተ የሆነውም ሁሉ እንዲሞት በእርግጥ እወቅ›› አለው ንጉሡም እንደታዘዘው አደረገ ‹‹አብርሃምም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ እግዚአብሔርም አቤሚሊክን ሚስቱንም ባሪያዎቹንም ፈወሳቸው በአብርሃም ሚስት በሣራ ምክንያት በአቤሚሊክ ቤት ማህፀኖችን ሁሉ በፍጹም ዘግቶ ነበርና›› በማለት ተገልéEል፡፡

  3. ዘፀአ “2-7-04 ላይ እስራኤላውያን የወርቅ ጥጃ ባመለኩ ጊዜ ‹‹እግዚአብሔር ሙሴን እኔ ይህን ሕዝብ አየሁት እነሆም አንገተ ደንዳና ሕዝብ ነው አሁንም ቀጣዬ እንዲቃጠልባቸው እንዳጠፋቸውም ተወኝ አንተንም ታላቅ ሕዝብ አደርግሀለሁ›› ብሎታል ነገር ግን እግዚአብሔር ሙሴን ሳያማክር ማጥፋት ይችል ነበር ‹‹እንዳጠፋቸውም ተወኝ›› የሚለው አነጋገር አትማልድላቸው እንደማለት ነው፣ ሙሴ ግን ወደ ፈጣሪው ስለማለደ ‹‹እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ ሊያደርግ ስላሰበው ክፋት ራራ›› ይላል ይህን የሙሴን አማላጅነት ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ በእግዚአብሔር ፊት መቆም ብሎታል ‹‹በኮሬብ ጥጃን ሠሩ ቀልጦ ለተሠራ ምስልም ሰገዱ ሣር በሚበላ በበሬ ምሣሌ ክብራቸውን ለውጠውታል ነገርንም በግብፅ ድንቅ ነገርንም በካም ምድር ግሩም ነገርንም በኤርትራ ባሕር ያደረገውን ያዳናቸውንም እግዚአብሔርን ረሡ እንዳያጠፋቸውም ቁጣውን ይመልስ ዘንድ የተመረጠው ሙሴ በመቅሠፍት ጊዜ በፊቱ ባይቆም ኖሮ ያጠፋቸው ዘንድ ተናገረ›› (መዝ 105፡19-23)

  4. በኢትዮጵያዊት ሚስቱ ምክንያት አሮንና ማርያም በወንድማቸው በሙሴ ላይ ስላንጎራጎሩበት እግዚአብሔር ለሙሴ ተቆርቁሮ ከገሠጻቸው በኋላ እህቱ ማርያም ለምጻም ሆነች በዚህን ጊዜ አሮን ደንግጦና ተጸጽቶ ‹‹ጌታዬ ሆይ ስንፍና አድርገናልና በድለንማልና እባክህ ኃጢዓት አታድርግብን›› በማለት ወንድሙን ሙሴን ለመነው ሙሴም ወደ ፈጣሪው አማልዶ ከለምéE ተፈውሳለች›› (ዘኁ 12፡1-15)

  5. እስራኤላውያን ስለዔናቅ ልጆች በሰሙ ጊዜ ግብፅ ለመመለስ አሰቡ በሙሴና በአሮንም ላይ አንጎራጎሩ እግዚአብሔርም ሙሴን ‹‹ይህ ሕዝብ እስከመቼ ይንቀኛል በፊቱ ባያረግሁት ሁሉ እስከመቼስ አያምንብኝም ከርስታቸው አጠፋቸው ዘንድ በቸነፈር እመታቸዋለሁ›› ሲለው ሙሴ እንደወትሮው ወደ አምላክ ጸለየ ‹‹ይህ ሕዝብ ከግብፅ ምድር ካወጣህ ጊዜ ጀምሮ ይቅር እንዳልካቸው እባክህ እንደ ምህረትህ ብዛት የዚህን ሕዝብ ኀጢዓት ይቅር በል አለው›› ‹‹እግዚአብሔርም እንደቃልህ ይቅር አለሁ›› አለው ይላል፡፡ (ዘኁ 14፡1-20)

  6. ዳታንና አቤሮን በምቀኝነታቸው ከነቤተሰቦቻቸው ምድር ስለዋጠቻቸው ሁለት መቶ ሃምሳ ሰዎች ደግሞ በትዕቢታቸው እሳት ከሰማይ ወርዶ ስለበላቸው ‹‹የእስራኤል ልጆች ማህበር ሁሉ እናንተ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ገድላችኋል ብለው በሙሴና በአሮን ላይ አንጎራጎሩ›› ‹‹እግዚአብሔርም ተገልጾ ሙሴን ከዚህ ማህበር መካከል ፈቀቅ በሉ እኔም በቅጽበት አጠፋቸዋለሁ አለ›› ሙሴና አሮንም በግንባራቸው ወድቀው ጸለዩ፣ ሙሴም አሮንን ‹‹ፍጠንና ውሰድ ከመሰዊያውም ላይ እሳት አድርግበት ዕጣንም ጨምርበት ወደ ማህበሩ ፈጥነህ ውሰደው አስተሰርይላቸው ከእግዚአብሔር ፊት ቁጣ ወጥቷልና መቅሠፍትም ጀምሯል›› አሮንም ሙሴ እንዳለው አደረገ መቅሠፍቱም ተከለከለ (መኁ 16፡41-50)

  7. እግዚአብሔር አልያዝ፣ በልዳዲስና፣ ሶፋር የተባሉትን የኢዮብን ጓደኞች እንደ ባሪያዬ እንደ ኢዮብ ቅንን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና ቁጣዬ ነድዷል አሁን እንግዲህ ሰባት ወይፈኖችንና ሰባት አውራ በጎች ይዛችሁ ወደ ባሪያዬ ወደ ኢዮብ ዘንድ ሂዱ የሚቃጠልንም መስዋዕት ለራሳችሁ አሳርጉ ባሪያዬም ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልያል እኔም እንደ ስንፍናችሁ እንዳላደርግባችሁ ፊቱን እቀበላለሁ እንደ ባሪያዬ ቅን ነገር አልተናገራችሁምና›› ስላላቸው በአምላክ እንደታዘዘ አደረጉ ኢዮብም ስለጓደኞቹ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ እግዚአብሔርም የኢዮብን ፊት (ጸሎት) ተቀበለ ይላል (ኢዮ 42፡1-9)

  8. በትንቢተ ኤርሚያስ 42፡1-12 ላይ እንደተለጸው ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቅ ድረስ ሕዝቡ ሁሉ ወደ ኤርሚያስ ቀርበው ‹‹እባክህ በፊትህ ልመናችን ትድረስ አምላክህም እግዚአብሔር የምንሄድበትን መንገድና የምናደርገውን ነገር ያሳየን ዘንድ ስለእኛ ስለዚህ ቅሬታ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ አሉት›› ‹‹ኤርሚያስም እነሆ እንደቃላችሁ ወደ እግዚአብሄር እጸልያለሁ የሚመልስላችሁን ሁሉ እነግራችኋለሁ ከእናንተ ምንም አልሸሽግም አላቸው፡፡

  9. በሐዲስ ኪዳን ውስጥ አንዲት ከነአናዊት ሴት ‹‹ጌታዬ የዳዊት ልጅ ማረኝ ልጄን ጋኔን ክፉኛ ይዟታል ብላ ጮኸች ፣ ጌታችንም ምንም ሳይመልስላት ዝም ባለ ጊዜ ሐዋርያት ቀርበው እንደባለሟልነታቸው በኋላችን ትጮኀለችና አሰናብታት እያሉ ለመኑት›› ጌታም የሐዋርያትን ልመና ሰምቶ የሴትየዋን እምነት አይቶ የለመነችውን ልጇን ፈወሰላት (ማቴ 15፡21-28)

  10. ቅዱስ እስጢፋኖስ አይሁድ በሚወግሩት ወቅት ተንበርክኮ ‹‹ጌታ ሆይ ይህን ኃጢዓት አትቁጠርባቸው›› በማለት ለምኖላቸዋል (ሐዋ 7፡60)

  11. ቅዱስ ያዕቆብም ‹‹ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ሰው ስለ ሌላው ይጸልይ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች›› በማለት ሐዋርያዊ መመሪያ ሰጥቷል በተጨማሪም 2ቆሮ 5፡18-21 እና ዮሐ 5፡16 ይመልከቱ በዚህ መሠረት ቅዱሳን ሰዎች ስለኃጥአን የሚለምኑት ልመና ተቀባይነት ስላለው በአማላጅነት መጠቀም ታላቅ ብልህነት ነው፡፡

ቅዱሳን በአፀደ ሥጋ ሳሉ ማማለድ ብቻ ሳይሆን ይፈርዳሉ እግዚአብሔር ሙሴን ‹‹በፈርኦን ላይ አምላክ አድርጌሃለሁ›› (ዘፀ 7፡11) ነው ያለው፣ ጌታችንም ሐዋርያትን በአስራ ሁለቱ ነገድ ላይ እንዲፈርዱ (ማቴ 19፡28-29) ነግሯቸዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ቅዱሳን በዓለም ላይ እንዲፈርዱ አታውቁምን? በማለት አስተምሯል (1ቆሮ 6፡2) ስለዚህ ቅዱሳን የመፍረድ ሥልጣን (የጸጋ አማልክት) ከሆኑ ይልቁንስ ስለኃጥአን ከጌታ ዘንድ በጸሎትና በምልጃቸው እንደምን ምህረትን አያሰጡም?

የቅዱሳን አማላጅነት በአፀደ ነፍስ
ባለፈው ጽሑፋችን አማላጅነት ከመቼ ጀምሮ እንደነበረ የአማላጅነት ትርጉም ቅዱሳን በአፀደ ስጋ እንደሚያማልዱ እግዚአብሔር የወዳጆቹን ጸሎት እንደሚስማና የለመኑትን ሁሉ እንደሚፈጽሙላቸው አይተናል በዚህ ክፍል ደግሞ ቅዱሳን በአፀደ ነፍስ ማማለድ ይችላሉን? ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት እንሞክራለን፤ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ያስችለን ዘንድ አስቀድመን የሰውን ተፈጥሮና ከሞት በኋላ የሚገጥመውን ሁኔታ ምን እንደሚመስል በመግቢያት እናያለን፡፡

የሰው ልጅ በአርአያ ስላሴ የተፈጠረ ክቡር ፍጡር ነው (ዘፍ 1፡26) ሰው ሥጋው ከምድር አፈር የተሠራ ቢሆንም ሥጋ ብቻ አይደለም ከሥጋ ጋር የተዋሃደች ነፍስ ደግሞ አለችው ፡፡ ስለዚህ ሰው በሥጋው የሚራብ የሚጠማ የሚበላ የሚጠጣ የሚደክም የሚታመም የሚዋለድና የሚሞት ሲሆን በነፍሱ ደግሞ የማይሞት የማይራብ የማይፈርስ የማይበሰብስ አሳቢ አዋቂ ተናጋሪ ሕያው ነው፡፡ ሰው ሲሞት ሥጋው ወደ ተፈጠረበት አፈርነቱ ይመለሳል ይፈርሳል ይበሰብሳል ነፍሱ ግን ሕያው ስለሆነች እንደ ስራዋ ወደ ገነት ወይም ወደ ሲዖል ትሄዳለች፡፡ በዚህ መሠረት ቅዱሳን ሥጋቸው በምድር እግዚአብሔር ከፈቀደላቸው ሥፍራ ሲቀበር ነፍሳቸው ደግሞ በገነት ውስጥ እንደመላእክት በደስታ ይኖራሉ፡፡

ይህ ከሆነ ዘንዳ ጻድቃን በአፀደ ነፍስ ሆነው መለመን ይችላሉን? በምድር የሚደረገውንስ ያውቃሉ? የሚሉትንና ሌሎችንም ጥያቄዎች ለመመለስ እንሞክር፡-

  1. ከሞት በኋላ ነፍስ የማትሞት ህያው እንደሆነች ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ‹‹ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ›› (ማቴ 10፡28) ትንሳኤና ሕይወት እኔ ነኝ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፡፡ ሕያው የሆነው የሚያምንብኝም ለዘላለም አይሞትም፡፡ (ዮሐ 11፡26-26) ‹‹እኔ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ የሚል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እናንተ የተባለውን አላነበባችሁምን የሕያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አምላክ አይደለሁም›› (ማቴ 22፡23-33) በማለት የሞቱ ቅዱሳን በነፍስ ሕያዋን እንደሆኑ አስረድቶናል ከዚህም ሌላ ቅ/እስጢፋኖስ ‹‹ጌታ ኢየሱስ ሆይ ነፍሴን ተቀበል›› (ሐዋ 7፡59) ሲል ቅ/ጳውሎስ ደግሞ በአፀደ ሥጋ ከመኖር በአፀደ ነፍስ መኖር የበለጠ እንደሆነ ሲያስረዳ ‹‹በእነዚህ በሁለቱ እጨነቃለሁ ልሔድ ከክርስቶስ ጋር ልኖር እናፍቃለሁ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና›› (ፊሊጵ 1፡22-23) በማለት ጽፏል፡፡

  2. ሰው ከሞተ በኋላ በአፀደ ነፍስ እያለ በምድር የሚደረገውን ያውቃል ወይ? ለሚለውና ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ቃል አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል፡፡ (በሉቃስ 16፡19-31) ያለውን ጌታችን የተናገረውን ታሪክ ልብ በለው ያንብቡት በወንጌሉ መሠረት አብርሃምና አልዓዛር በገነት በደስታ ባለጸጋው ነዌ ደግሞ በሲዖል በአፀደ ነፍስ እንዳሉ እንረዳለን፡፡

ሀ) ባለፀጋው ከሥቃይ የተነሣ አባቴ አብርሃም ሆይ አልዓዛርን ላከውና አንድ ጠብታ ውሃ ይስጠኝ ሲለው አብርሃም ግን በአፀደ ስጋ ስላችሁ አንተ መልካም እንደተቀበልህ አልዓዛር ደግሞ ክፉ እንደተቀበለ አስብ አሁንም አንተ ብድርህን ሥቃይ አልዓዛር ዋጋውን ተቀብላችኋል በማለት ነግሮታል፡፡
አብርሃም ከሞተ የቆየ ቢሆንም አልዓዛርና ነዌ በምድር ሳሉ በምን ዓይነት ሁኔታ ይኖሩ እንደነበር አውቆ እንደተናገሩ አስተውሉ፡፡

ለ) ባለፀጋው ነዌ ሥቃይ ቢበዛበት በሲኦል ሆኖ ወደ አብርሃም ጮሆ እንደለመነና ልመናው ተቀባይነት እንዳላገኘ ከተረዳ በኋላ ተስፋ ቆርጦ ዝም አላለም በምድር ያሉትን ወንድሞቹን አስቦ አባቴ አብርሃም በምድር አምስት ወንድሞች አሉኝና አልዓዛርን ወደ እነርሱ ልከህ ወደ እዚህ ስቃይ እንዳይመጡ ይንገራቸው በማለት ስለወንድሞቹ እንደለመነ እንደማለደ እናያለን ባለፀጋው በአፀደ ነፍስ ሆኖ በምድር ስላሉት ወንድሞቹ ማሰቡ ኃጢዓተኛም ቢሆን ነፍሱ አዋቂ ስለሆነች ወንድሞቹ በንስሐ እንዳልተመለሱ በቀዱሞ ኑሯቸው ያሉ መሆኑን ስላወቀ አይደለም? ኃጢዓተኛው ባለፀጋ ለወንድሞቹ አዝኖ ወደ መከራ እንዳይገቡ ካለመነላቸው ቅዱሳን በገነት እያሉ በምድር የሚኖሩ ምዕመናን በፀሎትና በትሕትና በፍቅር በአክብሮት ስማቸውን ጠርተን መታሰቢያቸውን በማድረግ ቢለምኗቸው አይረዷቸውም ጨርሶም አይሰሟቸውም ተብሎ እንዴት ይታሰባል?

ሐ) ባለፀጋው ለለመነው ልመና አብርሃም ኦሪትና ነቢያት አሉላቸው ማለትም መፃሕፍት ተጽፎላቸዋል ሕግ ተሰርቶላቸዋል ብሎ መለሰለት፡፡ ባለፀጋው ከሙታን አንዱ ቢሄዱ ያምናሉ ቢለው ኦሪትና ነቢያትን የማይሰሙ ከሆነ ከሙታን አንዱ ቢሄድላቸው አያምኑም ማለቱ እስከመጨረሻው ድረስ የሚሠሩትን ቢያውቅ አይደለምን?

  1. (በሉቃ 9፡28-31) በተጻፈው ቃል ጌታችን በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን በገለፀ ጊዜ ‹‹ሙሴና ኤልያስ ከጌታ ጋር ይነጋገሩ ነበር በኢየሩሳሌም ይፈፀም ስላለው ስለመውጣቱ ይናገር ነበር›› ማለት ያልሞተው ኤልያስና በአፀደ ነፍስ ያለው ሙሴ ጌታ በኢየሩሳሌም ስለሚቀበለው ሕማማተ መስቀል አስቀድመው እንደተናገሩ እናያለን ሙሴ በአካለ ነፍስ በክብር ተገልጾ ወደፊት የሚሆነውን መናገሩ ሀብተ ትንቢት እንዳልተነሣውና አዋቂነቱን ያሳያል፡፡

  2. ቃየል በቅንዓት ምክንያት አቤልን ቢገድለው እግዚአብሔር ቃየልን ‹‹የወንድምህ የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮሃል›› በማለት እንደመለሰለት እናያለን (ዘፍጥ 4፡9-10) ቅዱስ ጳውሎስም (በዕብ 11፡4-5) ላይ አቤል ከቃየል ይልቅ የሚበልጥ መስዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ በዚህም እግዚአብሔር ስለ ስጦታው ሲመሰክር እርሱ ፃድቅ እንደሆነ ተመሠከረለት ሞቶም ሳለ እስካሁን ይናገራል በማለት አቤል በነፍሱ እንደሚናገር ገልጽዋል፡፡ጌታችንም በወንጌል ‹‹ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተመቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ እውነት እላችኋለሁ፡፡›› (ማቴ 23፡35) በማለት የቅዱሳን ደም በከንቱ ፈሶ እንደማይቀር ከሞቱ በኋላ እንደሚያስፈርዱ ገልጽዋል ለዚህም የአቤልና የሌሎች ቅዱሳን ነፍስ ጠላቶቻቸውን እንዴት እንደተፋረዱ እንመለከታለን፤በመጽሐፈ ሔኖክ እንደተፃፈው መልአኩ ቅ/ሩፋኤል ለነቢዩ ሄኖክ ነፍሳት ያሉበትን ቦታ እየዞረ ሲያሳየው እንዲህ ብሏል ‹‹የደጋግ ሰዎች ልጆች ነፍሳትንም አየሁ እነሱ ሞተው ሳሉ ቃላቸው እስከሰማይ ይደርሳል ወንድሞቻቸውንም ይከሳሉ ያንጊዜም ከኔ ጋር ያለ ሩፋኤል ቃሉ እስከ ሰማይ ድረስ የሚደርስ የሚከስ ይህ ነፍስ የማን ነው? ብዬ ጠየቅሁት እሱም ይህ ነፍስ ወንድሙ ቃየል በግፍ ከገደለው ከአቤል የተለየ ነፍስ ነው ልጆቹ ከዚህ ዓለም እስኪጠፋ ድረስ የልጅ ልጁም ከሰው ተለይቶ እስኪጠፋ ቃየልን ይከሳል ብሎ መለሰልኝ ›› በማለት ያየውን ጽፎልናል (ሄኖክ 6፡26-28) የአቤልና የሌሎቹም ነፍሳት በምድር የሚገኙትን ጠላቶቻቸውን ለመበቀል የሚከሱ ከሆነ ይልቁንም ለማዳን ወደ ፈጣሪያቸው ሊለምኑ አይችሉም ማለት ምክንያታዊ አይሆንም፡፡

  3. በሐዲስ ኪዳን ውስጥ ከላይ የተጠቀሰውን የመሰለ ጽሑፍ እናገኛለን ‹‹አምስተኛውን ማኅተም በፈታ ጊዜ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሰዊያው በታች አየሁ በታላቅ ድምጽም እየጮኹ ቅዱስና እውንተኛ ጌታ ሆይ እስከመቼ ድረስ አትፈርድም ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም? አሉ ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው እንደነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና ወንድሞቻቸው ቁጥር እስኪፈፀም ድረስ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፍ ተባለላቸው›› (ራዕ 6፡9-11) በማለት ቅዱስ ዮሐንስ በራዕይ ያየውን ጽፎልናል፡፡

ከነዚህ ጥቅሶችም የምንረዳው፡

ሀ) ቅዱሳን በአፀደ ነፍስ ሆነው ፈጣሪያቸውን መጸለይ (መለመን) እንደሚችሉ የአቤልም ሆነ የሌሎች ሰማዕታት ነፍሶች በታላቅ ድምፅ እየጮሁ እንደለሙ ያሳያል

ለ) ቅዱሳን በአፀደ ነፍስ ሆነው በምድር የሚደረገውን እንደሚያውቁ የአቤልም ሆነ የሌሎች ቅዱሳን ነፍሶች ጠላቶቻቸው ጨርሰው እንዳልተፈረደባቸው አሁንም በምድር እንዳሉ አውቀው ፈጣሪያቸው እንዲበቀልላቸው እንደለሙ ለመረዳት ይቻላል፡፡

ሐ) ቅዱሳን በአፀደ ነፍስ ሆነው የሚለምኑት ልመናቸው ተሰሚ ጸሎታቸው ግዳጅ ፈጻሚ እንደሆኑ የአቤል ነፍስ ተካሰ የቃየልን ልጆች በጥፋት ውሃ አስጠፍታለች ዮሐንስም ያያቸው የቅዱሳን ነፍስ የለመኑት ልመና ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን እንደነሱ አክሊለ ሰማዕት የሚቀበሉ ወንድሞቻቸው ሰማእታት እስከሚገደሉ ብቻ እንዲታገሱ ከዚያ እንደሚፈረድላቸው ተነግሯቸዋል የንጽሕና ምልክት የሆነ ነጭ ልብስም አጎናጽፏቸዋል እንግዲህ እነዚህ ቅዱሳን ጠላቶቻቸውን ለመበቀል ከጸለዩ የእነሱን ሰማዕትነት ለሚቀበሉ በእነሱ ሃይማኖት ለሚያምኑ በጸሎቻቸውም ለሚማጸኑ መታሰቢያቸውን ለሚያደርጉ ለሚያከብሯቸው ምእመናን ወዳጆቻቸው ወደ እግዚአብሔር ‹‹ማርልን›› ይቅር በልልን ከጠላታቸው ከሰይጣን ጠብቅልን ለመንግስተ ሰማያት አብቃልን……›› ብለው ለመለመን አይችሉም፤ እግዚአብሔር አይሰማቸውም አይባልም፡፡ (ማቴ 23፡35) ላይ ጌታችን እንዳስተማረን ከአቤል ጀምሮ እስከ ዘካሪያስ ድረስ የፈሰሰው የቅዱሳን ደም በዚህ ትውልድ ይፈለጋል ያለው በአፀደ ነፍስ እነዚህ ቅዱሳን ራሱን ጌታችንን አቤቱ እስከመቼ ደማችንን በምድር በሚኖሩት ላይ አትፈርዱም ብለው እንደጠየቁትና እርሱም ልመናቸውን ሰምቶ ፈታሂ በጽድቅ ኩናኒ በርትዕ ነውና እንደሚፈርድ የገለፀው በዚህ ምክንያት ነው (ኤር 26፡15፣ ሄኖ 39፡40)

  1. ቅዱሳን በአፀደ ነፍስ ሆነው በምድር ያሉ ኃጢዓተኞችን እንደሚገዙ ጥበበኛው ሰሎሞን በመጽሀፍ ጥበብ ‹‹የደጋግ ሰዎች ነፍስ ግን በእግዚአብሔር እጅ ናት የኃጢዓተኞች መከራ አላገኛቸውም ለአላዋቂዎች ግን የሞቱ መስሎ ሞታቸው ጥፋት መሠለ እነርሱ ግር በተድላ በደስታ አሉ በሰው ፊት ሞቱ ቢባል አለኝታቸው ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ሞት የሌለበት ፍጽምት ሕይወት ናት›› (ጥበብ 3፡1-4) ብሎ ከጻፈ በኋላ በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ‹‹ደግ ሰው ግን ከሞተ በኋላ በደኅንነት ሳሉ እግዚአብሔር የዘነጉ ሰዎችን ይገዛል›› (ጥበብ 4፡16) በማለት ለቅዱሳን የተሠጣቸውን ክብር ጽፎልናል ነቢዩ ዳዊት ቅዱሳን በአፀደ ሥጋ ሳሉ ኃጢአተኞችን እንደሚገዙ ሲናገር ‹‹ቅዱሳን በክብር ይመካሉ በምንጣፋቸውም ላይ ሐሴትን ያደርጋሉ የእግዚአብሔርም ምስጋና በጉሮሮአቸው ነው ሁለት አፍ ያለው ሰይፍ በእጃቸው ነው በአሕዛብ ላይ በቀልን በሰዎችም መካከል ቅጣትን ያደርጉ ዘንድ ንጉሦቻቸውንም በሰንሰለት አለቆቻቸውንም በእግር ብረት ያስሩ ዘንድ የተጻፈውንም ፍርድ ያደርጉባቸው ዘንድ ለቅዱሳን ሁሉ ይህች ክብር ናት፤ ሃሌ ሉያ›› ብሏል (መዝ 149፡5-9) በምድር እያሉ የተሰጣቸው ጸጋና ክብር በሰማይ በአፀደ ነፍስ ፈተና በሌለበት ድል ካደረጉ በኋላ ክብራቸው የሚጨምር (የሚበዛ) እንጅ የሚቀንስ አይደለም በምድር ሳሉ በእግዚአብሔር ኃይል ወደሱ ጸልየው አመፀኞችን የሚቀጡ ትሑታን ምዕመናንን የሚረዱ ከሆነ ይህን በአፀደ ነፍስ የማይፈጽሙበት አንዳችም ምክንያት የለም (ራዕይ 6፡9-11)

  2. እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ለቅዱሳን ሙታነ ሥጋን በተአምራት ሙታነ ነፍስን በትምህርት እንዲያስነሱ ‹‹ድውያችን ፈውሱ ሙታንን አስነሱ ለምጻሞችን አንጹ አጋንንትን አውጡ (ማቴ 10፡8)›› በማለት ጽኑ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል በዚህ መሠረት በነቢዩ ኤልሳዕ በአፀደ ስጋ ሳለ አንድ ሙት አስነስቷል (2ነገ 4፡32-37) ኤልሳዕ ስለሞተው ሕፃን ወደ ፈጣሪው አማልዶ (ለምኖ) የህፃኑን ነፍስ ከአፀደ ነፍስ አምጥቶ በአፀደ ሥጋ ከሚገኘው አስከሬን ጋር በማዋሐድ አስነስቶታል ይኸው ነቢይ ኤልሳዕ ከሞተም በኋላ በአፀደ ነፍስ ሆኖ ተመሳሳይ ሥራ ሠርቷል፡፡‹‹ኤልሳዕ ሞተም ቀበሩትም ከሞዓብም አደጋ ጣዮች በየዓመቱ ወደ አገሩ ይገቡ ነበር ሰዎችም አንድ ሰው ሲቀብሩ አደጋ ጣዮችን አዩ ሬሳውንም በኤልሳዕ መቃብር ላይ ጣሉት የኤልሳዕንም አጥንት በነካ ጊዜ ሰውየው ድኖ በእግሩ ቆመ›› (2ነገ 13፡20-21) ኤልሳዕ በኤልያስ ያደረው ሀብተ መንፈስ ቅዱስ እጥፍ ድርብ ሆኖ እንደተሰጠው ለማጠየቅ ኤልያስ አንድ ሙት ሲያስነሣ ኤልሳዕ ግን ሁለት ሙት አስነስቷል፡፡ አንዱን በአፀደ ሥጋ ሳለ ሁለተኛውን ግን በአፀደ ነፍስ እያለ አስነስቷል ውጤቱ ማለትም የሞቱት ሰዎች መነሣት አንድ፤ ሲሆን ኤልሳዕ በአፀደ ሥጋ ሆኖ የሰራውን ከሞተ በኋላም ያንኑ ተመሳሳይ ስራ መሥራቱ ቅዱሳን ከሞቱ በኋላ ቢለምኗቸው አይረዱም የሚለውን ሐሳብ ውድቅ ያደርገዋል፡፡

  3. (በ1ነገስ 13፡1-32) በተጻፈው ታሪክ መሠረት በቤቴል መሠዊያ ላይ ትንቢት የተናገረው ነቢይ በሐሰት ያሳሳተውና ያስቀሰፈው ሽማግሌው ነቢይ የነቢዩን አስከሬን ወደ ገዛ ከተማው አምጥቶ በራሱ መቃብር ቀበረው አለቀሰለትም በመጨረሻም ሽማግሌው ነቢይ ልጆቹን ሰብስቦ ‹‹በሞትህ ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው በቤቴል ትንቢት የተናገረው ነቢይ በተቀበረበት መቃብር ቅበሩኝ አጥንቶቼንም በአጥንቶቹ አጠገብ አኑሩ በቤቴል ባለው መሠዊያ ላይ በእግዚአብሔር ቃል የጮኸው ነገር በእውነት ይደርሳልና›› በማለት ተናዘዘ ይህ ሽማግሌ ነቢይ ይህንን መናዘዙ በሐሰት ያሳሳተው ነቢይ እውነተኛ መሆኑን አውቆ በፈጸመው ኃጢዓት በአካለ ነፍስ እንዲረዳው አይደለምን? ቅዱሳን ከተቀበሩበት ቦታ የሚቀበር ከቅዱሳን ረድኤት በረከት እንደሚሳተፍ የኤልሳዕና የዚህ ነቢይ ታሪክ አስረጅ ነው፡፡ ስለ ቅዱሳን ሰዎች መቃብር በተመለከተ ነቢዩ ዳዊት ‹‹የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው እግዚአብሔርም ከሁሉ ያድናቸዋል እግዚአብሔር አጥንቶቻቸውን ሁሉ ይጠብቃል ከእነርሱም አንዱ አይሰበርም›› (መዝ 33፡19-20) በማለት እግዚአብሔር ከቅዱሳን መቃብር እንኳ እንደማይለይ ተናግሯል፡፡ስለዚህ ቅዱሳን በተቀበሩበት ቦታ መቀበር ሳይቀር ጥቅም እንዳለው ይህ ጉልህ ማስረጃ ነው ዛሬም ቅዱሳን ከተቀበሩበት ቦታ ለምሳሌ ደብረ ሊባኖስ ወስዳችሁ ቅበሩኝ በማለት ብዙ ሰዎች የሚናዘዙትና በኑዛዜው መሠረት የሚቀበሩት ከላይ በተጠቀሱት የቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃዎች ላይ በመመሥረት እንጂ ልማድ አይደለም ደግሞም የፃድቃነ ብሉይ መቃብር ይህን ያህል ከጠቀመ የፃድቃነ ሐዲስ መቃብርማ አብልጦ እንዴት አይጠቅም፡፡

  4. በ (ኤር 15፡1) ላይ እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ ‹‹ሙሴና ሳሙኤል በፊቴ ቢቆሙም ልቤ ወደ እዚህ ሕዝብ አያዘነብልም ከፊቴ ጠላቸው ይውጡ›› በማለት ጽፏል ሙሴና ሳሙኤል በአፀደ ሥጋ ሳሉ ለወገኖቻቸው ያማልዱ እንደነበር ታሪካቸው ያስረዳል እስራኤላውያን በኃጢዓታቸው ሰለጸኑ ኤርሚያስም ቢጸልይላቸው እግዚአብሐየር ‹‹አልሰማህምና አትጸልይላቸው!›› እንዳለው ተጽፏል (ኤር 7፡16-20) ኤርሚያስ በአፀደ ሥጋ ስለወገኖቹ ሊፀልይ ሙሴና ሳሙኤል በአፀደ ነፍስ ሆነው እንደሚጸልዩ ጥቅሱ ያስረዳል ‹‹በፊቴ ቢቆሙም›› የሚለው አባባል ቢፀልዩም፣ ቢለምኑም ፣ ቢያማልዱም ማለት እንደሆነ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹ያዳናቸውንም እግዚአብሔርን ረሱ እንዳያጠፋቸውም ቁጣውን ይመልስ ዘንድ የተመረጠው ሙሴ በመቅሰፍት ጊዜ በፊቱ ባይቆም ኖሮ ያጠፋቸው ዘንድ ተናገረ›› (መዝ 105፡19-23) በማለት ሙሴ በኦሪት ዘጽዓት 32፡1-14 ላይ ያለውን እስራኤላውያንን በጸሎቱ ከመቅሠፍት ያዳነበትን ታሪክ ገልጾታል በዚህ መሠረት ሙሴ በአፀደ ነፍስ ከሳሙኤል ጋር እንደለመደው እግዚአብሔር ሕዝቡን እንዳይቀስፍ በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ ይጸልይ ነበር ማለት ነው፡፡

  5. የእስራኤል ንጉሥ ሳዖል ፍልስጤማውያን ከበውት በተጨነቀ ጊዜ ወደ ፈጣሪው ጸለየ እግዚአብሔርም በሕልምም በነቢይም አልመለሰለትም፡፡ ስለዚህ በተጨነቀ ጊዜ በዓይንዶር ወዳለች አንዲት ሴት ሄዶ የነቢዩ የሳሙኤልን ነፍስ እንድትጠራለት ጠየቃት (1ሳሙ 28፡1-25) እሷም በተባለችው መሠረት ሳሙኤልን ጠርታ ባየችው ጊዜ ደነገጠች ‹‹አንድ ሽማግሌ ሰው ወጣ መጎናፀፊያም ተጎናጽፏል›› አለች ሳኦልም ሳሙኤል እንደሆነ አውቆ በምድር ላይ ተጎንብሶ እጅ ነሣው ሳሙኤልም ሳኦልን ‹‹ለምን አወከኝ ለምንስ አስነሳኸኝ አለው›› ሳኦልም ‹‹እነሆ ፍልስጤማውያን ከበውኛል እጅግ ተጨንቄአለሁ እግዚአብሄርም አልመለሰልኝም ከእኔ ርቋል አለው›› ‹‹ሳሙኤልም እግዚአብሔር በቃሌ እንደተናገረ እንዲሁ መንግስትህ ከአንተ ወስዶ ለዳዊት ሰጥቶታል በአማሌቅ ላይ ያለው ታላቅ ቁጣውን አላደረግህምና እስራኤላውያንን ከአንተ ጋር አሳልፎ ይሰጣል አንተና ልጆችህ ነገ ከእኔ ጋር ትሆናላችሁ›› በማለት ወደፊት የሚደርስበትን ሁሉ ነገረው ከዚህ የምንረዳው በዘመነ ኦሪት በዓመተ ፍዳ በዓመተ ኩነኔ የነበረ ሳሙኤል በአካለ ነፍስ ተገኝቶ ካነጋገረውና የሚደርስበትን ነገር አስቀድሞ ካሳወቀው ከተፈፀመ በዘመነ ሐዲስ በዓመተ ምህረት በገነት ያሉ ቅዱሳን ነፍሳት በተጨነቅን ጊዜ በጸሎታቸው አምነን በቃል ኪዳናቸው ተማጽነን ብንጠራቸው በአካለ ነፍስ በረድኤት እንደሚጎበኙንና ከችግራችን እንደሚታደጉን ለእኛ ለኦርቶዶክሳውያን ጥርጥር የሌለበት በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ሁል ጊዜ የምናረጋግጠው እውነተኛ ቃል ነው፡፡

  6. በማቴ 19፡27-30 ላይ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹እነሆ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ እንግዲህ ምን እናገኝ ይሆን?›› ብሎ ጌታን ጠየቀው ጌታችንም ‹‹እውነት እላችኋለሁ እናንተስ የተከተላችሁኝ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ እናንተ ደግሞ በአስራሁለቱ የእስራኤል ነገድ ልትፈርዱ በአስራ ሁለቱ ዙፋን ትቀመጣላችሁ›› በማለት በአፀደ ሥጋና በአፀደ ነፍስ የሚያገኙትን ክብር ገልጾላቸዋል እንግዲህ በአስራ ሁለቱ ወንበር ተቀምጠው እንዲፈርዱ ስልጣን ከሰጣቸው ለምኖ ማስታረቅን ይቅርታን ማሰጠትን ይነፍጋቸዋል ተብሎ አይታሰብም ከማማለድ ይልቅ መፍረድ ይበልጣልና፡፡ኦርቶዶክስ መልስ አላት ከሚለው ፔጅ የተወሰደ

 

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top