በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ

በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ

 1ጢሞ.2:5 “አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤”

ይህ ምን ማለት ነው? አንድ እግዚአብሄር አለ ሲልስ ምን ስለማለት ነው? መካከለኛስ ሲባል እንዴት ነው?

የተወደደ አባታችን ቅዱስ ጳውሎስ << አንድ እግዚአብሄር አለ>> ይለናል ፤ ይህም አንዳንዶች ጣኦት አምላካውያን ብዙ እንደሚያደርጉት ያይደለ <<አንድ>> ብቻ አምላክ እርሱም እግዚአብሄር እንደሆነ ይነግረናል፡፡ ይህን ቅዱስ ጳውሎስ ሲጠቅሰው በእዉኑ ስለአንድ አምላክነት ሲገልፅ እንጂ ከልጁ አንፃር ነውን? አይደለም ፡ ምክንያቱም ልጁ ራሱ ክርስቶስ እግዚአብሄር አይደለምን?

<<በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ>> ይህስ ስለልጁ ስለክርስቶስ በግልፅ ይናገራል ፤ <<መካከለኛ>> እንዲሆን እግዚአብሄር ሰወች ሁሉ ይድኑ ዘንድ መውደዱን ለማረጋገጥ አንድያ ልጁን (ክርስቶስን) ወደ አለም ልኮታልና ፤ እግዚአብሄር አንድያ ልጁን ላከ ሲባል እንደምንድን ነው? አንድያ ልጁ ራሱ እግዚአብሄር አይደለምን? አስቀድመን እንዳልን ክርስቶስ ራሱ እግዚአብሄር ነው፡፡

1) እንግዲህ መካከለኛነት ስለወልድ ስለምን ተጠቀሰ? የክርስቶስ መካከለኛነት ዋና ተግባር <<ማስታረቅ>> ነው ፤ ማንን ከማን ለማስታረቅ ብንል ፦ እግዚአብሄርን ከሰው ጋር ለማስታረቅ፡፡ እንግዲህ እግዚአብሄርና ሰው ስለምን አስታራቂ አስፈለጋቸው? ምክንያቱም ሰው ራሱን ያስታርቅ ዘንድ በቅቶ አልተገኘምና እግዚኣብሄርም ራሱን ከሰው ጋር ያስታርቅ ዘንድ ይህን ሊቀበል የሚችል ሰው አላገኘምና ፤ ስለዚህም አስታራቂ አስፈለገ፡፡

2) አስታራቂ ለማስታረቅ ከየትኛው ወገን መሆን አለበት? ከሁለቱም ወገኖች ቀረቤታ ሊኖረው የሚገባ አይደለምን? የአንደኛው ወገን ብቻ ባለሟል ቢሆን ለአንደኛው ምን ይጠቅመዋል? ስለዚህም <<መካከለኛ (ከሁለቱም ወገን የተዛመደ)>> አስፈላጊ ነበር፡፡ ክርስቶስ እርሱ እግዚአብሄር ሲሆን (በመለኮት የእግዚአብሄር ልጅ ፡ አንድ አምላክ ነውና ) ሰው ሆኗልና (የሰውን ባህርይ በተዋህዶ ከድንግል እናቱ ተወልዷልና) የሰውም የእግዚአብሔርም ወገን ይባል ዘንድ ተገባው ፡ ስለዚህም መካከለኛ በመሆን ሰውንና እግዚአብሄርን አስታረቀ፡፡

3) እንግዲህ ክርስቶስ ካስታረቀ ለተበዳይ ምን ካሳ እንዲከፈል አስማማ(አስታረቀ)? ሰው ለእግዚአብሄር ምን መስዋእት(ካሳ) አቀረበ? እግዚአብሄርስ የትኛውን ካሳ ተቀበለ? ይህ ነገር እፁብ ነው ፡ ድንቅ ነው ፤ መካከለኛ ክርስቶስ ሰው ለእግዚአብሄር ሊያቀርብ የሚችለው አንዳች እንኳን እንደሌለው ሲያውቅ ራሱ ካሳ አቀረበ ፡ ይሄውም ደሙን ማፍሰሱ ነው ፡ ስጋውን መቁረሱን ነው ፡ ይሄውም እጅግ የሚደንቀው የቤዛነቱ ስራ ነው፡፡ አንድ ጊዜ ራሱን አሳልፎ ስለሰው ሁሉ በደል መስዋእት ሆነ ፡ በአንዱ ቁስል እኛ ሁላችን እንፈወስ ዘንድ ቆሰለ ፡ ደከመ ፡ ሞተ ፡ ተቀበረ ፡ ንፁህ መስዋእት ክርስቶስ ተሰዋ ፡ ለአለምም ቤዛ ሆነ ፤ እግዚአብሄርም ከሰው ጋር በልጁ ሞት ታረቀ ፤
እንግዲህ ምን እንላለን? እግዚአብሄር ስንል ስለአብ ብቻ የምንጠቅስ ነንን? አይደለም አብ እግዚአብሄር እንደሆነ ፡ ልጁ ክርስቶስም እግዚአብሄር ነው ፡ መንፈስ ቅዱስም እግዚአብሄር ነው እንጂ ፤ ስለዚህም ተወዳጁ አባታችን <<አንድ እግዚአብሄር አለ>> አለን፡፡

ስለዚህም ክርስቶስ (ራሱ እግዚአብሄር ነው) ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቀ( ከራሱም ጋር ከመንፈስ ቅዱስም ጋር አስታረቀ) ፤
አንዳንዶች ይህን የክርስቶስን መካከለኛነት (የቤዛነት አገልግሎት) ሳይረዱ ይቀሩና እንደፍጡር ፡ በራሱም ይቅር ማለት እንደማይችል ፡ የቤዛነቱም ስራ ገና እንዳልተፈፀመ ፡ ከባህርይ አባቱም በስልጣን ዝቅ እንደሚል አስመስለው አሁንም በሰማይ ይማልዳል ( ይሰቀላል ፡ ደሙን ያፈሳል ፡ ስጋውን ይቆርሳል ፡ ይሞታል) ይሉ ዘንድ ይደፍራሉ፡፡

እኛ ግን ክርስቲያኖች እንደመሆናችን በአንድ አምላክ እርሱም በእግዚአብሄር እናምናለን፡፡ እግዚአብሄርም ስንል አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ማለታችን ነው፡፡ ይህንም የቤዛነት አገልግሎት ቅዱስ ጳውሎስ ያፀናልን ዘንድ 1ጢሞ.2:6 “ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ፥ ይህም በገዛ ዘመኑ ምስክርነቱ ነበረ፤” በማለቱ የክርስቶስ መካከለኛነት ግብር ቤዛነቱ መፈፀሙም (የማስታረቁም አገልግሎት መፈፀሙ) ምስክርነቱ እንደሆነ ያትምልናል፡፡

የቅዱስ ዮሃንስ አፈወርቅን ትርጉም መሰረት በማድረግ የቀረበ

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top