ነገረ ድኅነት

ነገረ ድኅነት በመጽሐፍ ቅዱስ እዚህ በመጫን ያንብቡ

 

ነገረ ድኅነት በመጽሐፍ ቅዱስ 

 በዳዊት አብርሃም          መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻፲ .

ስለ ነገረ ድኅነትም ኾነ ስለማናቸውም ሃይማኖታዊ ጉዳይ ስናጠና አንዲት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ብቻ መመርኮዝ የለብንም፡፡ አንዲቷን ጥቅስ ከአጠቃላዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ዐሳብ ለይተንና ከሌሎች ጥቅሶች ነጥለን መመልከት የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ያደርሳል፡፡ ኦርቶዶክሳዊውን የነገረ ድኅነት አስተምህሮ የሚቃወሙና በተቃራኒውም ስሕተት የኾነ ትምህርት በማስተማር የሚከራከሩ ወገኖች በዚህ ዓይነቱ ስሕተት ሊጠመዱ የቻሉበት አንዱ ምክንያት በአንዲት ነጠላ ጥቅስ ላይ ሙጥኝ ብለው ሌሎቹን ግን ችላ ማለት ስለሚቀናቸው ነው፡፡ ደካማ ሰው አንድን ጥቅስ ብቻ ነጥሎ በማንጠልጠል የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ሲደርስ ብልህ፣ ጠቢብና ዕውቀት ፈላጊ ሰው ግን አንዱን ከአንዱ ጋር እያነጻጸረ በማጥናት፣ በመታገሥ ምርምሩን ይቀጥላል፡፡ በዚህም ትክክለኛ ዕውቀት ላይ ይደርሳል፤ እውነትን ወደ ማወቅም ይመጣል፡፡

ከነገረ ድኅነት አስተምህሮ አንጻር ይህን ነገር በምሳሌ እንመልከት፤ “እነርሱም ‹በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ› አሉት” (ሐዋ. ፲፮፥፲፫)፡፡ አንዳንዶች ይህን ጥቅስ በመምዘዝ “ለመዳን ማመን ብቻ በቂ ነው” ይላሉ፡፡ ይህን ንግግር ቅዱስ ጳውሎስ እና ቅዱስ ሲላስ በፊልጵስዩስ የእስር ቤት ጠባቂ ለነበረው ሰው የተናገሩት ኀይለ ቃል ነው፡፡ “ጥቅሱ የተነገረው ለማን ነው? ለምን ተነገረ? ከዚያስ ወረድ ብሎ ምን ይላል? ከሌሎች ጥቅሶች ጋር ያለው ተዛምዶ ምን ይመስላል?” ብለው ሳይጠይቁ ለውሳኔ መቻኮል ትክክል አይደለም፡፡ እስኪ ጥቅሱን በእርጋታ እንመርምረው፤

፩ኛ. ይህ ቃል የተነገረው ከአሕዛብ ወገን ለኾነ ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው እምነት የለሽ ነው፡፡ ስለዚህም ምንም ዓይነት በጎ ሥራ ቢሠራ ዋጋ አያገኝም፡፡ ለመዳን አስቀድሞ ማመን አለበትና፡፡ ሳያምን ወደ ሌላ በጎ ሥራ ቢጓዝ መዳንን አያገኝምና፡፡ ስለዚህም ጳውሎስ እና ሲላስ አስቀድመው የመዳን በር የኾነውን ቃል ነገሩት፤ ‹‹እመን›› አሉት፡፡ እምነት ለመዳን የመጀመሪያው ደረጃ ነው፤ ሌሎች ለመዳን ከሰው የሚጠበቁት ዂሉ ከማመን በኋላ የሚመጡ ናቸው፡፡

፪ኛ. መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ጊዜ የመጀመሪያ ደረጃ ተግባርን የሒደቱን አጠቃላይ ኹኔታ የሚያሳይ አድርጎ ያቀርበዋል፡፡ ለዚህም ዓይነተኛው ምሳሌ ስምዖን አረጋዊ ነው፡፡ ስምዖን አረጋዊ “ዓይኖቼ በሰዎች ዂሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋል” (ሉቃ. ፪፥፴-፴፩) በማለት የተናገረው ጌታ ተሰቅሎ፣ ሞቶ የሚፈጽመውን ማዳን አይቶ አይደለም፡፡ እርሱ ለማየት የቻለው የጌታን መወለድ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን የጌታችን መወለድ የማዳን ሥራው አካል መኾኑን ስለተረዳ “እንግዲህ ባርያህን አሰናብተው” አለ፡፡ የጳውሎስ እና የሲላስ ዐሳብም ተመሳሳይ ነው፡፡ ለእስር ቤቱ ጠባቂ “አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችኁ” ሲሉ የእርሱና የቤተሰቡ መዳን በእርሱ ማመን ብቻ ፍጻሜ ያገኛል ብለው አይደለም፡፡ ነገር ግን በምግባር፣ በተጋድሎ፣ ምሥጢራትን በመፈጸምና በሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ፍጻሜ የሚያገኘውን የመዳን ጉዞ በእምነት እንደሚጀምር መናገራቸው ነው፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዘኬዎስ የተናገረው ኃይለ ቃልም ተመሳሳይ መልእክት ያለው ነው፤ “እርሱ ደግሞ የአብርሃም ልጅ ነውና ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል፤” (ሉቃ. ፲፱፥፱)፡፡ ይህ ማለት የዘኬዎስ የመዳን ጉዞ ዛሬ ተጀመረ ማለት እንጂ ዘኬዎስ ጌታን በመኖሪያ ቤቱ ተቀብሎ ስላስተናገደው ብቻ መዳንን ወርሷል ወይም ድኗል ማለት አይደለም፡፡

፫ኛ. ጳውሎስና ሲላስም ይህን ሲሉ አሁን ባመንክበት ቅጽበት ትድናለህ ማለታቸው ሳይኾን የመዳኑን መንገድ ይዘኸዋል ማለታቸው መኾኑን የሚያረጋግጥ አንዱ አባባል “ትድናለህ” ብለው በትንቢት አንቀጽ መናገራቸው ነው፡፡

፬ኛ. ሌላው የእርሱ እምነት ለመዳኑ የመጀመሪያ ርምጃ መኾኑን የምናውቀው “ቤተሰቦችህ ይድናሉ” በሚለው የሐዋርት ንግግር ነው፡፡ “እርሱ ባመነው ቤተሰቦቹ እንዴት ይድናሉ?” የሚል ጥያቄ ብናነሣ ሐዋርያት የተናገሩት አሁን በዚያ ቅጽበት ለሚኾነው ሳይኾን ከዚያ ቅጽበት ለሚጀመረውና ወደፊት ለሚጠናቀቀው መዳን መኾኑን እንረዳለን፡፡ እርሱ ካመነ በኋላ ቤተሰቦቹን ሲያሳምን ደግሞ እነርሱም ልክ እንደ እርሱ የመዳንን ጉዞ አንድ ብለው ይጀምራሉ፡፡ ይህም ማመን ለመላው ቤተሰብ የመዳን ጉዞ የመጀመሪያ ምዕራፍ መኾኑን ይገልጣል፡፡

፭ኛ. ኃይለ ቃሉን ዝቅ ብለን ስናነብም ይህን የሚያጠናክር ማስረጃ እናገኛለን፤ “ለእርሱና በቤቱም ላሉት ዂሉ የእግዚአብሔርን ቃል ተናገሯቸው። በሌሊትም በዚያች ሰዓት ወስዶ ቍስላቸውን አጠበላቸው፤ ያን ጊዜውንም እርሱ ከቤተሰዎቹ ዂሉ ጋር ተጠመቀ፤” (ሐዋ. ፲፮፥፴፪-፴፫)፡፡

“እመን፤ ትድናለህ” የሚለውን ኃይለ ቃል ብቻ መዝዘን በማውጣት “ለመዳን የሚያስፈልገው ማመን ብቻ ነው” ከሚል ድምዳሜ ከደረስን በተጠቀሱት ስሕተቶች ላይ እንወድቃለን፡፡ ይህም የበለጠ ግልጽ እንዲኾንልን ሌላ ምሳሌ ከመጽሐፍ ቅዱስ እንመልከት፤

አንድ ወጣት ወደ ጌታችን ቀርቦ “መምህር ሆይ፥ የዘላለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ላድርግ?” ሲል ጠየቀው (ማቴ. ፲፱፥፲፮)፡፡ ጌታችን ሲመልስለትም “እመንና ትድናለህ” አላለውም፡፡ ነገር ግን “ወደ ሕይወት መግባት ብትወድ ግን ትእዛዛትን ጠብቅ” ነው ያለው (ማቴ. ፲፱፥፲፯)፡፡ ታዲያ ከዚህ የወንጌል ጥቅስ ተነሥተን “ትእዛዞችን መጠበቅ (ሕግጋቱን መጠበቅ) ብቻውን ለመዳን በቂ ነው” ብሎ መደምደም ይቻላል? በፍጹም አንችልም፡፡ አንድ ጥቅስ ብቻ አንጠልጥሎ ለመደምደም መቸኮል ግን ይህን ከመሰለው ስሕተት ላይ ሊጥለን እንደሚችል ልብ እንበል፡፡

በዚሁ ጥቅስ ላይ ንባባችንን ስንቀጥል ጥያቄውን ያቀረበው ወጣት “እነዚህን ዂሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄያቸዋለሁ” ብሎ መለኮታዊውን ትእዛዝ መጠበቁን ሲያረጋግጥ እናገኘዋለን፡፡ እንግዲህ አስቀድሞ ጌታችን “ለመዳን መሥፈርቱ ትእዛዛትን መጠበቅ ነው” ብሎ የተናገረውን ይዘን አሁን ወጣቱ “‹ፈጽሜያቸዋለሁ› በሚል ምላሹ ምክንያት ድኗል” ብለን ልንደመድም አንችልም፡፡ ጌታችን ለወጣቱ “ፍጹም ልትኾን ብትወድ ሒድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ፤ መዝገብም በሰማያት ታገኛለህ፤ መጥተህም ተከተለኝ” በማለት ለመዳን ማድረግ የሚገባውን ዂሉ እንደ ነገረው መዘንጋት የለብንም (ማቴ. ፲፱፥፳፮)፡፡

ከዚህ ላይ ለመዳን እምነት ወይም ጸጋው አልተጠቀሰም፡፡ በዚህ ጥቅስ መሠረት ሕግጋትን መፈጸም ወይም በጎ መሥራት እንኳን ቢኾን በቂ አይደለም፡፡ ከዚያ ያለፈ ተግባር ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ በዚህ አንድ ጥቅስ ላይ ብቻ መመሥረትን የመረጠ ሰው “ያለውን ዂሉ ሸጦ ለችግረኞች አከፋፍሎ ጌታን ካልተከተሉ በቀር መዳን አይቻልም” ብሎ ለመደምደም ይገደዳል ማለት ነው፡፡

አንዳንድ ስሑታን ስለ ነገረ ድኅነት ሲከራከሩ የሚያነሡት ሌላው ጥቅስ “እንግዲህ በእምነት ከጸደቅን በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንያዝ” የሚለው ኃይለ ቃል ነው (ሮሜ. ፭፥፩)፡፡ አንዳንዶች ይህን ጥቅስ እያነሡ “ከዚህ በላይ ማስረጃ ምን ትፈልጋለህ? በእምነት ብቻ እንደሚጸደቅ በግልጥ ተጽፏል፤ ይህን ጥቅስ ምን ታደርገዋለህ? ወይስ እንዴት ልትክደው ትችላለህ?” በሚል ዐሳብ ይከራከራሉ፡፡

የእኛ ምላሽም እንዲህ ነው፤ ይህንን ትምህርት አንክድም፤ አናስተባብልምም፡፡ ነገር ግን ለብቻው ነጥለን አንመለከተውም፡፡ እዚያው ከአጠገቡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የጻፈው ሌላ ትምህርት አለና እርሱን አምጥተን አብረን እናጠናዋለን፡፡ ትምህርቱም እንዲህ የሚል ነው፤ “በእግዚአብሔር ፊት ሕግን የሚያደርጉ ይጸድቃሉ እንጂ ሕግን የሚሰሙ አይደለም” (ሮሜ. ፪፥፲፫)፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ ሐዋርያው ጽድቅ (መዳን) የሚገኘው ሕግን በማድረግ መኾኑን ያስተምረናል፡፡

ታዲያ በዚህ ጥቅስ ላይ ብቻ ተመሥርተን “መዳን ሕጉን በመተግበር ብቻ የሚገኝ ነው” ልንል እንችላለን? አንልም፡፡ ነገር ግን ሁለቱንም የሐዋርያውን ጥቅሶች ሳንነጣጥል በአንድነት እንወስዳቸዋለን፡፡ ሐዋርያው በሁለቱም ቦታዎች በሮሜ. ፪፥፲፫ እና ፭፥፩ ላይ የጻፈልንን ለድኅነታችን አስፈላጊ የኾኑትን ተግባራት እንማራለን፡፡ በዚህ መሠረት ለመዳናችን ማመናችን የሚኖረውን ዋጋ መልካም ሥራ አይተካውም፤ እንደዚሁም መልካም ሥራ ለመዳናችን አስፈላጊ መኾኑ የእምነትን አስፈላጊነት አይሽረውም፡፡ “ሰው በእምነት ብቻ ሳይኾን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ፡፡ እንደዚሁም ጋለሞታይቱ ረዓብ ደግሞ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን?” (ያዕ. ፪፥፳፬-፳፭) ተብሎ እንደ ተጻፈው ለመዳን ሁለቱንም እምነትንና ሥራን አዋሕደን መያዝ እንዳለብን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡

ሌላ ኃይለ ቃል ደግሞ እንመልከት፤ “ነገር ግን ለማይሠራ፥ ኃጢአተኛውንም በሚያጸድቅ ለሚያምን ሰው እምነቱ ጽድቅ ኾኖ ይቈጠርለታል” (ሮሜ. ፬፥፭) በዚህ ኃይለ ቃል መነሻነት ሌሎቹን የትምህርት ዓይነቶች ወይም ኃይለ ቃሉን በምልዓት ለመረዳት ስንሞክር አንድ ሰው ኃጢአተኛ ኾኖ ሳለ፣ ኃጢአት መሥራቱንም ሳያይተው ወይም ንስሐ ሳይገባ “ይጸድቃል” ብለን መደምደም እንችላለን? ይህንን ኃይለ ቃል በትክክል ለመረዳት ጥቅሱን ግልጽ ሊያደርጉ የሚችሉ ሌሎች ነጥቦችን መረዳት ይኖርብናል፡፡

ለምሳሌ ከዚያው ከሮሜ መልእክት አንድ ሌላ ጥቅስ እንመልከት፤

  • “እውነትን በዓመፃ በሚከለክሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በዓመፃቸው ዂሉ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ከሰማይ ይገለጣል”(ሮሜ. ፩፥፲፰)፡፡

  • “ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለ ጠግነት ትንቃለህን? ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቍጣ ቀን ቍጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ”(ሮሜ. ፪፥፭)፡፡

ነገረ ድኅነት በትንቢተ ነቢያት 

ታኅሣሥ ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም      በመ/ር ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ

ቅዱሳን ነቢያት ሀብተ ትንቢትን ከእግዚአብሔር የተቀበሉ፣ ፈጣሪያቸውን የተከተሉ፣ በመንፈሰ ረድኤት የተቃኙ እንደ መኾናቸው እግዚአብሔር በሰጣቸው ሀብተ ትንቢት ተመርተው ስለ እግዚአብሔር አዳኝነት መስክረዋል፤ ስለ ሰው ልጅ ድኅነትም አስቀድመው ትንቢት በመናገር የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን የማዳን ቀን በተስፋ እንዲጠባበቅ አስተምረዋል፡፡ በትምህርታቸውም እንደ ብረት የጠነከረውን፣ እንደ ዐለት የጠጠረውን፣ በአምልኮ ጣዖትና በገቢረ ኃጢአት የሻከረውን የሰው ልጆችን ልቡና ወደ እግዚአብሔር አቅርበዋል፡፡ ነቢያት መንፈሳዊነትን የተላበሱ፤ በትንቢታቸውና በትምህርታቸው የአሕዛብን ልቡና ያስደነገጡ፤ ዓላውያን ነገሥታትን ያንቀጠቀጡ የእግዚአብሔር መልእክተኞች ናቸው፡፡

በዘመናቸውም አምላክ ከሰማይ ወርዶ (ሰው ኾኖ) ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከጥፋት ወደ ድኅነት እንዲመልሳቸው እግዚአብሔርን ለምነዋል፤ ሱባዔ እየቈጠሩ፣ ትንቢት እየተናገሩም የተስፋውን ዕለት ሲጠባበቁ ኑረዋል፡፡ ለዚህም ነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹እውነት እላችኋለሁ፤ ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን የምታዩትን ሊያዩ ተመኝተው አላዩም፡፡ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ተመኝተው አልሰሙም፤›› (ማቴ. ፲፫፥፲፯) በማለት ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸው፡፡ የነቢያቱ የትንቢታቸው ፍጻሜ፣ የልመናቸው መደምደሚያም ነገረ ድኅነት ነው፡፡ በመኾኑም ሰውን ለማዳን ወደ ዓለም የሚመጣውን እግዚአብሔርን በትንቢታቸው በሚከተሉት ምሳሌያት ገልጸውታል፤

. እጅ (ክንድ)

እጅ ቢወድቁ ተመርጕዘው ይነሡበታል፡፡ እጅ የወደቀውን ንብረት ከአካል ሳይለይ ለማንሣት፣ የራቀውን ለማቅረብ፣ የቀረበውን ለማራቅ ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ወልድም ከባሕርይ አባቱ ከአብ፣ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ ከእግዚአብሔር ርቆ የነበረውን አዳምን ወደ እርሱ አቅርቦታል፤ ከወደቀበት አንሥቶታል፡፡ ስለዚህም ነው ቅዱሳን ነቢያት እግዚአብሔር ወልድን ‹‹እጅ (ክንድ)›› እያሉ የሚጠሩት፡፡ ‹‹ፈኑ እዴከ እምአርያም አድኅነኒ ወባልሐኒ እማይ ብዙኅ ወእምእዴሆሙ ለደቂቀ ነኪር እለ ከንቶ ነበበ አፉሆሙ ወየማኖሙኒ የማነ ዐመፃ፤ እጅህን ከአርያም ላክ፤ አድነኝም፡፡ ከብዙ ውኆች፣ በአፋቸውም ምናምንን ከሚናገሩ፣ ቀኛቸው የሐሰት ቀኝ ከኾነ ከባዕድ ልጆች አስጥለኝ፤›› እንዲል (መዝ. ፻፵፫፥፯-፰)፡፡ ከዚህ ላይ ነቢዩ ዳዊት ‹‹እጅ›› በማለት የጠራው ከሦስቱ አካላት አንዱን እግዚአብሔር ወልድን ነው፡፡ ‹‹አፋቸው ምናምን የሚናገር፣ ቀኛቸው የሐሰት ቀኝ የኾነው ውኆች›› የሚላቸው ደግሞ ዲያብሎስንና ሠራዊቱ አጋንንትን ነው፡፡ ደቂቀ ነኪር (የባዕድ ልጆች) ማለቱም አጋንንት ከክብራቸው ስለ ተዋረዱ በባሕርያቸው ለሰው ልጆችም ለብርሃናውያን መላእክትም ባዕዳን ናቸውና፡፡

እስራኤል ዘሥጋ በጸናች እጅ፣ በተዘረጋች ክንድ ከግብጽ ባርነት፣ ከፈርዖንና ከሠራዊቱ ግዞት ነጻ መውጣታቸው ነገረ ድኅነትን የሚመለከት ምሥጢር ይዟል፡፡ ‹‹በጸናች እጅ፣ በተዘረጋች ክንድ ይለቃችኋል፤ ከአገሩም አስወጥቶ ይሰዳችኋል›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ዘፀ. ፮፥፩)፡፡ ከዚህ ላይ ‹‹የጸና እጅ፣ የበረታ ክንድ›› የተባለው ዓለምን በሙሉ ከኃጢአት ባርነት፣ ከዲያብሎስ ቁራኝነት ነጻ ያወጣው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ክንዱን በመስቀል ዘርግቶ በትረ መስቀሉን አንሥቶ በልዩ ሥልጣኑ ዲያብሎስን የቀጣው፣ ሞትን የሻረው፣ ሲኦልን የበረበረው ኃይለኛውን አስሮ ያለውን ዅሉ የነጠቀው እርሱ ነውና፡፡ ‹‹እሙታን ተንሢኦ ሲኦለ ከይዶ በሞቱ ለሞት ደምሰሶ፤ ከሙታን መካከል ተለይቶ ተነሥቶ፣ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ሞትን በሞቱ አጠፋው (ደመሰሰው)›› እንዲል መጽሐፈ ኪዳን፡፡

መድኀኒታችን ክርስቶስ ‹‹አልቦ ዘይክል በዊአ ቤተ ኀያል ወበርብሮተ ንዋዩ ለእመ ኢቀደመ አሲሮቶ ለኀያል፤ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኀይለኛው ቤት ገብቶ ገንዘቡን መዝረፍ የሚቻለው የለም›› (ማቴ. ፲፪፥፳፱) በማለት እንደ ተናገረው እርሱም ዲያብሎስን አስሮ በሲኦል ተግዘው ይኖሩ የነበሩ ነፍሳትን ዅሉ ነጻ አውጥቷቸዋል፡፡ አምላካችን ‹‹የጸና እጅ›› የተባለ አምላክነት፣ አለቅነት፣ ጌትነት በአጠቃላይ መለኮታዊ ሥልጣን ገንዘቡ ነውና፡፡ ይህ የጸና እጅ ሰማያትን የዘረጋ፣ ምድርን የመሠረተ፣ ሰውን ለማዳን በመስቀል ላይ የተዘረጋ ኃያል ክንድ ነው፡፡ ዓለም የሚድንበት በእጅ የተመሰለው አካላዊ ቃል ወልደ እግዚአብሔር ሕያው መኾኑን ‹‹የእግዚአብሔር እጅ ከማዳን አላጠረችም፤ ጆሮውም ከመስማት አልደነቆረችም፤›› (ኢሳ. ፶፱፥፩) በማለት ልዑለ ቃል ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ ተናግሯል፡፡ ስለዚህም ነቢያቱ ‹‹እጅህን ላክልን›› እያሉ እግዚአብሔርን ሲማጸኑት ቆይተዋል፡፡ ይህን ብርቱ ክንድ ዓለም እንዳልተረዳውም በትንቢታቸው አስገንዝበዋል፡፡ ነገረ ድኅነት ከብዙዎች አእምሮ የተደበቀ ምሥጢር ነበርና፡፡

ነቢዩ ኢሳይያስ በነቢያት የተነገረውን የነገረ ድኅነት ትንቢት የሰው ልጅ አምኖ እንዳልተቀበለው ሲያስረዳ ‹‹ጌታ ሆይ፣ ነገራችንን ማን ያምነናል? የእግዚብሔርስ ክንድ ለማን ተገልጧል?›› (ኢሳ. ፶፫፥፩) በማለት ተናግሯል፡፡ ጌታችን በሕዝቡ ፊት አምላክነቱን የሚገልጹ ተአምራቱን ቢያደርግም አስራኤል ግን አምላክነቱን አምነው አለመቀበላቸው ለዚህ ማስረጃ ነው (ዮሐ. ፲፪፥፴፮-፵)፡፡ ቅዱስ ዳዊትና ኢሳይያስ እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ኾነው የሰውን ልጅ ለማዳን ወደዚህ ዓለም የሚመጣውን አምላክ ነገረ ድኅነትን በሚመለከት ምሥጢራዊ ቃል ‹‹እጅ ክንድ›› እያሉ ጠርተውታል፡፡

. የመዳን ቀንድ

ቀንድ የሥልጣን፣ የኀይል መገለጫ ነው፡፡ የነቢዩ ሳሙኤል እናት ሐና ‹‹ወተለዓለ ቀርንየ በአምላኪየ ወመድኃኒየ፤ ቀንዴ በአምላኬና በመድኃኒቴ ከፍ ከፍ አለ›› (፩ኛ ሳሙ. ፪፥፩) ማለቷ ለጊዜው ስላገኘችው ክብርና የልጇን የሳሙኤልን ሥልጣን (ነቢይነትና ምስፍና) ስትናገር፤ ፍጻሜው ግን ቀንድ የተባለ ዓለም የዳነበት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መኾኑን ስታመለክት ነው፡፡ ቅዱሳን ነቢያትም እግዚአብሔር ወልድን ‹‹የመዳን ቀንድ›› ብለውታል፡፡ በመዝሙረ ዳዊትም ከዳዊት ወገን ተወልዶ ዓለምን የሚያድነው ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ቀንድ›› በሚል ቃል ተጠቅሷል፡፡ ‹‹ወበህየ አበቊል ቀርነ ለዳዊት ወአስተዴሉ ማኅቶተ ለመሲሕየ፤ በዚያም ለዳዊት ቀንድን አበቅላላሁ፡፡ ለቀባሁትም ሰው መብራትን አዘጋጃለሁ፤›› ተብሎ እንድ ተጻፈ (መዝ. ፻፴፩፥፲፯)፡፡

እንስሳት ጠላታቸውን የሚከላከሉት፣ ኀይላቸውንም የሚገልጡት በቀንድ ነው፡፡ እኛ የሰው ልጆችም ከጠላታችን ሰይጣን ውጊያ ራሳችንን የምንከላከለውና ድል የምናደርገው በእርሱ ኀይል ነውና ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹የመዳን ቀንድ›› ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ‹‹ብከ ንዎግዖሙ ለኵሎሙ ፀርነ፤ ጠላቶቻችንን ዅሉ በአንተ እንወጋቸዋለን፤›› እንዳለ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ (መዝ.፵፫፥፭)፡፡ ካህኑ ዘካርያስም በቅዱሳን ነቢያት ‹‹የመዳን ቀንድ›› እየተባለ የተጠራው ክርስቶስ በሥጋ የሚገለጥበት ጊዜ መድረሱን ሲያስረዳ ‹‹አንሥአ ለነ ቀርነ መድኃኒትነ እምቤተ ዳዊት ገብሩ በከመ ነበበ በአፈ ነቢያቲሁ ቅዱሳን እለ እምዓለም፤ ከጥንት ጀምሮ በነበሩት በቅዱሳን ነቢያት አፍ እንደ ተናገረ ከባርያው ከዳዊት ቤት የምንድንበትን ቀንድ አስነሣልን፤›› (ሉቃ.፩፥፷፱) በማለት ተናግሯል፡፡ ‹‹እምቤተ ዳዊት ገብሩ›› ማለቱም ነቢዩ ዳዊት ‹‹ቀንድ›› እያለ ትንቢት የተናገረለት ክርስቶስ የዳዊት ወገን ከኾነችው ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንደሚወለድ ሲያመለክት ነው፡፡

. የማን (ቀኝ)

ቀኝ የኃይል፣ የሥልጣን፣ የመልካም ነገር ምሳሌ ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን መሪዎች ሰዎችን ለአገልግሎት ሲልኳቸው ቀኝ እጃቸውን ዘርግተው ይጨብጧቸው ነበር፡፡ በሥራቸው ዅሉ ከእነርሱ እንደማይለዩ የሚያረጋግጡላቸውም ቀኝ እጃቸውን በመስጠት ነበር፡፡ በዚህ ትውፊት መሠረትም ቅዱሳን ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ቅዱስ ጳውሎስን በቀኝ እጃቸው ጨብጠውታል፡፡ ይህንንም ‹‹የተሰጠኝን ጸጋ ዐውቀው አዕማድ የሚሏቸው ያዕቆብና ኬፋ፣ ዮሐንስም እኛ ወደ አሕዛብ፣ እነርሱ ወደ ተገረዙት ይሔዱ ዘንድ ለእኔና ለበርናባስ ቀኝ እጃቸውን ሰጡን፤›› በማለት ቅዱስ ጳውሎስ ገልጦታል (ገላ.፪፥፱)፡፡

ቅዱሳን ነቢያት ዲያብሎስን ከነሠራዊቱ ድል ነስቶ ዓለምን የሚያድነውን፤ ኀያል፣ ጽኑዕ የኾነውን አምላካችንን ክርስቶስን ‹‹ቀኝ›› ብለውታል፡፡ ‹‹የማነ እግዚአብሔር ገብረት ኃይለ የማነ እግዚአብሔር አልዓለተኒ፤ የማነ እግዚአብሔር ገብረት ኃይለ፤ የእግዚአብሔር ቀኝ ኃይልን አደረገች፡፡ የእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ አደረገችኝ፡፡ የእግዚአብሔር ቀኝ ኃይልን አደረገች፤›› እንዲል (መዝ.፻፲፯፥፲፮)፡፡ ይህም ‹‹የእግዚአብሔር ቀኝ›› የተባለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በድንቅ ጥበቡ፣ በልዩ ሥልጣኑ አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ ዘመን በሲኦል ተጥለው የነበሩ ነፍሳትን ከፍ ከፍ እንዳደረጋቸው (ወደ ገነት እንደመለሳቸው) የሚያስረዳ ምሥጢር አለው፡፡ ቅዱስ ዳዊት የተስፋውን ቃልና የመዳኛውን ቀን መድረስ እየተጠባበቀ ‹‹ወይድኃኑ ፍቁረኒከ አድኅን በየማንከ ወስምዓኒ፤ ወዳጆችህ እንዲድኑ፣ በቀኝህ አድን፤ አድምጠኝም፤›› በማለት ይጸልይ ነበር (መዝ.፶፱፥፭)፡

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top