ኪዳነ ምሕረት
✍ በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
❖ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ “ቃል ኪዳን” የሚለው ቃል 257 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል፤ ኪዳን ማለት ቃል “ተካየደ” ከሚለው ከግእዝ ቃል የወጣ ሲኾን “ተዋዋለ፣ ተስማማ፣ ተማማለ” ማለትን ሲያሳይ እግዚአብሔር ሰውን ከማፍቀሩ የተነሣ ለሰው ልጅ እንደ ባልንጀራ አድርጎ መሐላን ይምላል፣ ቃል ኪዳንም ይገባል፡፡
❖ ክቡር ዳዊት በመዝ 88፡2-3 ላይ “ከመረጥኋቸው ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ” እንዳለ ከኹሉም ቅዱሳን በላይ ኾና ሰማይ ምድር የማይወስኑትን አምላክ በማሕፀኗ ለመሸከም፣ ኪሩቤል ሱራፌል ዙፋኑን በመፍራትና በመንቀጥቀጥ የሚሸከሙትን ሰማያዊ መለኮትን በዠርባዋ ለማዘል፣ በክንዷ ለመታቀፍ፣ ሰማይ ምድር ከፊቱ የሚሸሹትን የባሕርይ አምላክን በከናፍሮቿ ለመሳም፣ ፍጥረታትን ኹሉ በዝናብ አብቅሎ በፀሓይ አብስሎ የሚመግበውን፤ ለቅዱሳን መላእክት ርሱ የገለጸላቸው ምስጋና ምግብ ኹኗቸው እንዲኖሩ ያደረገውን ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የተካከለውን እግዚአብሔር ወልድን የድንግልና ጡቶቿን ለማጥባት ከተመረጠች ከእናቱ ጋር የገባው ጽኑዕ የምሕረት ቃል ኪዳን እጅግ ልዩ እና ለኃጥኣን ኹሉ ተስፋ የሚኾን ነው፡፡
❖ መልአከ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤልም በአምላክ እናት ፊት ቆሞ “ማርያም ሆይ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አግኝተሻልና አትፍሪ” በማለት ከፍጡራን ወገን ማንም ሊያገኘው የማይችለውን ይኸውም በልዑል እግዚአብሔር ዘንድ መወደድን በማግኘት ከባለሟልነት ኹሉ የላቀ ባለሟልነት ይኸውም የአምላክ እናት የመኾንን የማማለድ ልዩ ጸጋና ክብር እንደተሰጣት ነግሯታል፡፡
❖ መልአኩ በዚኽ ምስጋናው ላይ “ሞገስን አግኝተሻልና” አለ እንጂ “ወደ ፊት ታገኛለሽ” አለማለቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ጥንቱኑ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የተጠበቀችና በልዑል የተመረጠች መኾኗን የሚያረጋግጥም ነበር፡፡ ከዚኽ ከተሰጣት ታላቅ ባለሟልነት የተነሣ ልጇን በማሳሳብ ውሃው ወደ ወይን እንዲለወጥ አስደርጋለች (ዮሐ 2፡1-10)፡፡
❖ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ እንደምናነብበው በአምላካቸው ፊት ባለሟልነትን ያገኙ ብዙዎች ቅዱሳን ቢኖሩም ቅሉ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ግን ለነዚኽ ኹሉ ቅዱሳን ሰማያዊ ክብርን ቃል ኪዳንን የሰጠውን አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና በመውለዷ “ወላዲተ አምላክ” የመባል ታላቅና ልዩ ባለሟልነት ተሰጥቷታልና የርሷ ክብር ከማንም ቅዱሳን ክብር ጋር ፈጽሞ የማይነጻጸር ነው፡፡
❖ ከ 432-447 ዓ.ም ሴሌኡሲያ ላይ ጳጳስ የነበረው ሊቁ ባስልዮስም እግዚአብሔር ለእናቱ የሰጣት ልዩ ባለሟልነትን ከቅዱሳን ጋር በማነጻጸር ሲጽፍ “What encomiums can we offer her as she deserves, when everything of this world is beneath her merits?…” (የሚመጥናትን ምን ዐይነት ልዩ ምስጋና እናቅርብላት? የዚኽ ዓለም ነገር ኹሉ አይመጥናትምና፤ ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ቅዱሳን ሲናገር “ዓለም አልተገባቸውም” (ዕብ ፲፩፥፴፰) ካላቸው፤ ለአምላክ እናትማ ከከዋክብት በላይ ኾና እንደምታበራው ፀሓይ ለኾነችው ለርሷ ምን ልንል እንችል ይኾን? (ራእ ፲፪፥፩)… ምን ምስጢር እንደተከናወነ ተመልከት፤ ኅሊናንና አእምሮን የሚያልፍ ነገር እንደኾነ አስተውል፤ ታዲያ የአምላክን እናት ታላቅነት ኹሉም ሰው እንደምን አይናገር? ማንስ ነው ከቅዱሳን ኹሉ በላይ እንደኾነች ያላስተዋለ? እግዚአብሔር ላገልጋዮቹ የሚልቅ ጸጋን ከሰጠና የሚነኩት ኹሉ ሰው ከበሽታው ከተፈወሰ፤ ጥላቸው ያረፈበት ተአምር ከተፈጸመለት፤ ጴጥሮስ በጥላው ካደነ (የሐዋ ፭፥፲፭)፤ የጳውሎስ የልብሱ ጨርቅ ዕራፊ መናፍስትን ካወጣ (የሐዋ ፲፱፥፲፩)፤ ለእናቱማ ምን ዐይነት ሥልጣንና ኀይል ተሰጥቷት ይኾን?
✔ ለቅዱሳኑ ይኽነን ያኽል ድንቅ እንዲያደርጉ ባለሟልነትን ከሰጣቸው ወልዳ ላሰደገችው እናቱማ ምን ያኽል ይሰጣት ይኾን? በምን ዐይነትስ ስጦታ አስጊጧት ይኾን? ጴጥሮስ “ክርስቶስ አንተ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነኽ” ስላለው ብፁዕ ከተባለና የመንግሥተ ሰማያት ቊልፍ ከተሰጠው (ማቴ ፲፮፥፲፮-፲፱)፤ ርሷ ከኹሉም ይልቅ እንዴት የተባረከች (ብፅዕት) አትኾን? (ሉቃ ፩፥፵፭)፤ ጳውሎስ ታላቅ ክብር ያለውን የክርስቶስን ስም በመሸከሙ “ምርጥ ዕቃ” ከተባለ (የሐዋ ፱፥፲፭)፤ የአምላክ እናትማ የምእመናን ምግብ የኾነ መናውን ሳይኾን የሕይወት ሰማያዊ እንጀራን ያስገኘች ርሷ ምን ዐይነት ልዩ ዕቃው ትኾን?
✔ ነገር ግን ስለርሷ ብዙ እናገራለኊ ብዬ ስለክብሯ ጥቂት በመናገር ራሴን በኀፍረት ውስጥ እንዳልጨምር እፈራለኊ ስለዚኽ ካኹን ወዲኽ የንግግሬን መልሕቅ ስቤ በዝምታ ወደቤ ላይ ማረፍን መርጬአለኊ) በማለት በእግዚአብሔር ፊት የተሰጣት ባለሟልነት ፍጹም እንደኾነና ከቃላት በላይ እንደኾነ አስተምሯል፡፡
❖ ዳግመኛም ቅዱሳን መላእክትና ጻድቃን ካገኙት ሞገስ የተነሣ ወደ ፈጣሪያቸው እንዲያማልዱን ስንማጸናቸው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ግን የአምላክ እናት ናትና ካገኘችው ከዚኽ ታላቅ ባለሟልነት የተነሣ ወደተወደደው ልጇ እንድታማልደን እንማጸናታለን፤ ከዚኽም የተነሣ ነው ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬምም በእሑድ ውዳሴ ማርያም ላይ፦
✍ “ለኪ ይደሉ ዘእምኲሎሙ ቅዱሳን ትሰአሊ ለነ ኦ ምልእተ ጸጋ…” (ጸጋን የተመላሽ ሆይ ከቅዱሳን ኹሉ ይልቅ ትለምኚልን ዘንድ ላንቺ ይገባል፤ አንቺ ከሊቃነ ጳጳሳት ትበልጪያለሽ፤ ከነቢያትም ከመምህራንም ትከብሪያለሽ ከሱራፌልና ከኪሩቤል ግርማ የሚበልጥ የመወደድ ግርማ አለሽ፤ በእውነቱ የባሕርያችን መመኪያ አንቺ ነሽ) በማለት ያመሰገናት፡፡
❖ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም ካገኘችው ታላቅ ባለሟልነት የተነሣ ፭ሺሕከ፭፻ ዘመን ሲፈጸም ያለ ዘርዐ ብእሲ አካላዊ ቃል ክርስቶስን በኅቱም ድንግልና የፀነሰች፤ ፱ወር ከ፭ ቀን በማሕፀኗ የተሸከመች፣ በኅቱም ድንግልና የወለደች፣ በክንዷ የታቀፈች፣ በጀርባዋ ያዘለች ርሷ ብቻ ናትና፤ በርሷ አማላጅነት የምናቀርበው ጸሎት ምን ያኽል ታላቅ እንደኾነ በሰዓታት መጽሐፉ ላይ፡-
✍“ወፈድፋደሰ በእንተ ማርያም እምከ እንተ ይእቲ ትምክህተ ዘመድነ …” (ይልቁንም የባሕርያችን መመኪያ ስለምትኾን ስለ እናትኽ ስለ ማርያም አንተን በመፅነስና አንተን በመውለድ ዕድፍ ጒድፍ ስላላገኘው ስለ አልተለወጠ ድንግልናዋና ስለ ተሸከመኽ ማሕፀኗ፤ ስለ ታቀፉኽ ስለ ክንዶቿና፣ ስለ ዳሰሱኽ ስለ እጆቿ፤ ስለ ሳሙኽ ስለ ከንፈሮቿ ስለ አሳደጉኽ ስለ ጡቶቿ፤ ከአንተ ጋር ስለ ተመላለሱ ስለ እግሮቿና፤ ስለ ዐዘለኽ ስለ ጀርባዋ፤ ብሩሃት ስለሚኾኑ ስለ ዐይኖቿ በጎ መዐዛ ስላላቸው አፍንጮቿ፤ ጸዐዶች ስለሚኾኑ ጥርሶቿ፤ በመልአኩ በገብርኤል ቃል ስለ ተበሠሩ (ብሥራትን ስለ ሰሙ) ስለ ጆሮቿ፤ ከርሷ ስለነሣኸው ሥሮችና ጸጒር፣ ደምና፣ ዐፅም ስለ ነፍስና ሥጋ፤ አባቶቻችን እንደ አስተማሩን ፈጽሞ ያለመለየትና ያለመለወጥ ከመለኮትነትኽ ጋራ አንድ ያደረግኸው) በማለት እንዳስተማረ፤ በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ ባለሟልነት እንዳገኘች በብርሃናዊዉ መልአክ የተመሰከረላት የአምላካችን እናት ቅድስት ድንግል ማርያምን ከልጇ ታማልደን ዘንድ “ሰአሊ ለነ ቅድስት” (ቅድስት ሆይ ለምኝልን) እያልን እንማጸናታለን፡፡
❖ ይኸውም ታላቁ የነገረ ማርያም መጽሐፍ እንደሚያስረዳን ጌታችን ካረገ በኋላ እመቤታችን ጌታችን ወደ ተቀበረበት ጎልጎታ እየኼደች ትጸልይ ነበር፤ ከዕለታት ባንዳቸው በየካቲት ፲፮ ዕለት ስትጸልይ “አዕረግዋ ውስተ ሰማይ ከመ ያርእይዋ መካነ ዕረፍቶሙ ለጻድቃን ኀበ ሀለዉ አብርሃም ይስሐቅ ወያዕቆብ ወተቀበልዋ ኲሎሙ ነፍሳተ አበው እለ አዕረፉ እምአዳም እስከኔሁ ወሰገዱ ላቲ እንዘ ይብሉ ስብሐት ለእግዚአብሔር ዘፈጠረ ለነ ኪያኪ ሥጋ እምሥጋነ ወዐፅመ እምዐፅምነ” ይላል መላእክት አብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብ ያሉበትን የጻድቃን የማረፊያቸውን ቦታ ያሳዩዋት ዘንድ ወደ ገነት አሳረጓት፤ በዚያም ከአዳም ዠምሮ እስከዚያው ያረፉ ያባቶች ነፍሳት ተቀብለዋት “ከዐፅማችን አንቺን ዐጥንት ከሥጋችን አንቺን ሥጋ ለፈጠረልን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይግባው” እያሉ የአክብሮት ስግደት ሰግደውለታል፡፡
❖ ከዚያም መላእክት የጻድቅ ሰው ነፍስ ከሥጋው ሲለይ ያለውን ፍጹም ክብርና የሚወርሰውን የገነት ርስቱን መላእክት ካሳዩዋት በኋላ፤ ኃጥኣን ነፍሳቸው ከሥጋቸው ሲለይ ያላቸውን ጭንቅ ነፍሳቸው በሲኦል የምትቀበለውን ከፍተኛ መከራ አሳዩዋት፤ “ወሶበ ተስእኖሙ አምስጦ ይቤሉ እንዘ ይኬልሑ ኦ እግዝእትነ እሙ ለመድኅን ወለተ ብርሃን ንዒ ኀቤነ ከመ ትፍትሕነ እማእሰሪሁ ለሰይጣን ወኢትኅድግነ” ይላል ለማምለጥ ባልተቻላቸውም ጊዜ “የመድኅን እናቱ የብርሃን መገኛ እመቤታችን ሆይ ከዚኽ ከዲያብሎስ ቊራኝነት ታላቅቂን ዘንድ ድረሺልን ቸል አትበዪ” እያሉ ምልጃዋን ሽተው በታላቅ ጩኸት ያለቅሱ ዠመር፡፡
❖ ያን ጊዜ ርኅርኅት የኾነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም “ወይ ሎሙ ወአሌ ሎሙ መኑ እምዜነዎሙ ለውሉደ ሰብእ ኢይምጽኡ ዝየ” (ወዮላቸው ወዮታ አለባቸው ወደዚኽ እንዳይመጡ ለሰው ልጆች ኹሉ ማን በነገራቸው) እያለች ስታለቅስ፤ መላእክትም ለርሷ “ኢትፍርሂ ኦ ማርያም እስመ እግዚአብሔር ምስሌኪ ወምስለ እለ የአምኑ ብኪ” (እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ስለኾነና ባንቺ አማላጅነት ከአመኑት ኹሉ ጋር ስለ አለ አይዞሽ) በማለት ነገሯት፡፡
❖ ርሷም “እስእለከ እግዚኦ ወአስተበቊዐከ በእንተ ኲሉ ዘየአምን ብየ ረስዮ እግዚኦ ግዑዘ እምሲኦል ተዘኪረከ ረኃበ ወጽምዐ ወኲሎ መከራ ዘረከበኒ ኀቤከ ወምስሌከ” (አቤቱ በኔ ቃል ኪዳን ስላመነ ኹሉ እማልድኻለኊ እለምንኻለኊ፤ መራቤን መጠማቴንም ካንተ ጋር በምድረ ግብጽ ያገኘኝን ረኃብና ጥም ኹሉ አስበኽ አቤቱ ወደ ሲኦል ከመውረድ ነጻ አድርገው) በማለት ወደ ልጇ ፍጹም ልመናን አቀረበች።
❖ ጌታችን ተገልጾላት “ይኩን በከመ ትቤሊ እፌጽም ለኪ ኲሎ መፍቅደኪ አኮኑ ተሰባእኩ በእንተ ዝንቱ መሐልኩ ለኪ በርእስየ ከመ ኢይሔሱ ኪዳንየ” (የለመሺዉን ኹሉ ይደረግልሽ፤ የምትፈቅጂውን ኹሉ እፈጽምልሻለኊ የለመንሺዉን ኹሉ ላደርግልሽ ሰው ኹኜአለኹና፤ መሐላዬን እንዳላፈርስ አማንየ በርእስየ ብዬ በራሴ ማልኹልሽ) ሲል ለእናቱ የማያልፍ የምሕረት ቃል ኪዳንን ገብቶ ገብቶላታልና በዓሉ “ኪዳነ ምሕረት” በመባል ይታሰባል::
❖ ሊቁ ቅዱስ ያሬድም በዝማሬው ላይ ጌታ ለእናቱ ስለገባላት ቃል ኪዳን፡-
✍ “ይቤላ ለእ ማርያም እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ተካየድኩ ምስሌኪ ኪዳነ ምሕረት ከመ አድኅን ዘተአመነኪ መሐልኩ ለኪ በርዕስየ ዘመሐልኩ አነ ለኖኅ ገብርየ ወለአብርሃም ፍቁርየ፤ ዘመሐልኩ አነ ለዳዊት ኅሩይየ ብእሲ ምእመን ዘከመ ልብየ መሐልኩ ለኪ በርዕስየ በቅዱስ ሥጋየ ወበክቡር ደምየ መሐልኩ ለኪ በርዕስየ ከመ ኢይሔሱ ማእኰትየ”
✍(ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ ማርያምን እንዲኽ አላት በምልጃሽ ያመነብሽን አድን ዘንድ ካንቺ ጋራ የምሕረት ቃል ኪዳንን ተጋባኊ፤ ለአገልጋዬ ለኖኅና ለወዳጄ ለአብርሃም ቃል የገባኊ እኔ በራሴ ማልኹልሽ፤ እንደ ልቤ ለምለው ለታመነው ለዳዊት የማልኊ እኔ በራሴ ማልኹልሽ፤ በቅዱስ ሥጋዬና በክቡር ደሜ የማልኊ እኔ ምዬ እንደማልከዳ ማልኹልሽ) በማለት ጽፎታል፡፡
[በቀራንዮ ከፈጣሪያችን የተቀበልንሽ ስጦታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ ልጅሽ ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን]
✍ ከመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ