አልተሳሳትንም ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው

 አልተሳሳትንም ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው

 መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ

ብዙዎች በዘመናችን የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ባለመረዳትና “እኔና አብ አንድ ነን” ያለውን የአምላካቸውን የኢየሱስ ክርስቶስን የባሕርይ አምላክነትን፣ ፈጣሪነት፣ ፍጹም ተዋሕዶውን ፈራጅነቱን በመካድ ሎቱ ስብሐት ከአብ አሳንሰው ርሱን ለማኝ አብን ተለማኝ ያደርጋሉ፤ ቅድስት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ከበፊት ጀምሮ እስካሁን ከመናፍቃን የሚደርስባት ፈተና ለምን ኢየሱስ ክርስቶስን የባሕርይ አምላክ ነው? ለምን ከአባቱ ጋር የተካከለ ፈራጅ ነው? ብለሽ ታስተምሪያለሽ የሚል ነው፤

ይህም ዐዲስ አይደለም የባሕርይ አምላክነቱን፣ ተዋሕዶውን፣ ፈራጅነቱን ከካዱት ውስጥ ከቀድሞዎቹ እነ ጳውሎስ ሳምሳጢ፣ አርዮስ፣ ንስጥሮስ …. በ16ኛው መቶ ክ.ዘመን ወዲህ በየዘመናቱ የሚነሱ የእምነት ድርጅቶች ወ.ዘ.ተ ይገኛሉ፤ የእነዚኽን አስተምህሮ በማስተምርበት የነገረ መለኮት ኮሌጅ ውስጥ ከደቀ መዛሙርት ጋር በክፍል ውይይት ጊዜ በጥልቀት የምዳስሰው ቢኾንም፤ ለ ፌስ ቡክ (face book) ጓደኞቼ ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የምታስተምረውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጻፈውን አስተምህሮ ጥቂቱን ከዚኽ በታች አስፍሬዋለኊ፡- ይኸውም በብሉይ ኪዳን የተጠቀሰው እግዚአብሔር ከሦስቱ አካል አንዱ እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለመኾኑ የተጻፈውን የብሉይ ኪዳንና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትን እውነት በማንበብ አረጋግጡ፡-

ሀ) ኢየሱስ ክርስቶስ በእውነት እግዚአብሔር ነው እንላለን፡፡

►“በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” (ዘፍ 1፡1) ╬ “ጌታ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው” (ዕብ 1፡10)

►“እግዚአብሔርም ሙሴን፦ «ያለና የሚኖር» እኔ ነኝ አለው እንዲህ ለእስራኤል ልጆች። «ያለና የሚኖር» ወደ እናንተ ላከኝ ትላለህ አለው” (ዘፀ 3፡14) ╬ “ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ። አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ ይላል” (ራእ 1፡8)

►“ለአንተ ከአንተም በኋላ ለልጆችህ መልካም ይሆን ዘንድ፥ አምላክህም እግዚአብሔር ለዘላለም በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ ይረዝም ዘንድ፥ እኔ ዛሬ የማዝዝህን ሥርዓቱንና ትእዛዙን ጠብቅ” (ዘዳ 4፡40) ╬ “እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ይህን አዛችኋለሁ” (ዮሐ 15፡17)

►“አምላካችንን እግዚአብሔርን እናመልካለን፥ ድምፁንም እንሰማለን” (ኢያ 24፡24) ╬ “ከጌታ የርስትን ብድራት እንድትቀበሉ ታውቃላችሁና የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስ ነውና” (ቆላ 3፡24)

► “እግዚአብሔርን ብትፈሩ ብታመልኩትም፥ ቃሉንም ብትሰሙ፥ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ላይ ባታምፁ፥ እናንተና በእናንተ ላይ የነገሠው ንጉሥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ብትከተሉ፥ መልካም ይሆንላችኋል” (1 ሳሙ 12፡14) ╬ “ደግሞም ኢየሱስ፦ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም ብሎ ተናገራቸው” (ዮሐ 8፡12)

► “አንተ ብቻ የሰውን ልጆች ሁሉ ልብ ታውቃለህና ልቡን ለምታውቀው ሰው ሁሉ እንደ መንገዱ ሁሉ መጠን ክፈለውና ስጠው” (1ነገ 8፡39) ╬ “ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር፤ ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና” (ዮሐ 2፡25፤ 1ቆሮ 4፡5)

► “አንተ ብቻ እግዚአብሔር ነህ ሰማዩንና የሰማያት ሰማይን ሠራዊታቸውንም ሁሉ፥ ምድሩንና በእርስዋ ላይ ያሉትን ሁሉ፥ ባሕሮቹንና በእነርሱ ውስጥ ያለውን ሁሉ፥ ፈጥረሃል፥ ሁሉንም ሕያው አድርገኸዋል የሰማዩም ሠራዊት ለአንተ ይሰግዳሉ” (ነህ 9፡6) ╬ “ደግሞም በኵርን ወደ ዓለም ሲያገባ። የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ” (ዕብ 1፡6) ╬ “ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ” (ፊልጵ 2፡10)

► “ከእግዚአብሔር በቀር አምላክ ማን ነው? ከአምላካችን በቀር አምላክ ማን ነው?” (መዝ 17 (18)፡31 ╬ “እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው” (1ዮሐ 5፡20)

► “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፥ የሚያሳጣኝም የለም” (መዝ 22(23)፡1) ╬ “መልካም እረኛ እኔ ነኝ መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል” (ዮሐ 10፡11)

► “እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኃኒቴ ነው የሚያስፈራኝ ማን ነው?” (መዝ 26(27)፡1) ╬ “ደግሞም ኢየሱስ፦ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም ብሎ ተናገራቸው” (ዮሐ 8፡12)

► “አምላክ በእልልታ፥ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ” (መዝ 46፡5) ╬ “ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ” (ሉቃ 24፡51)

► “ከክብሩ ውበት ከጽዮን እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል” (መዝ 49፡2) ╬ “ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል” (የሐዋ 1፡11)

► “ለስሙም ዘምሩ ለምስጋናውም ክብርን ስጡ” (መዝ 65፡2)  “መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው” (ፊልጵ 2፡11)

► “እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ የወይን ስካር እንደ ተወው እንደ ኃያልም ሰው” (መዝ 77፡65) ╬ “እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤ የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ” (ማቴ 28፡6)

► “ይመጣልና በምድር ላይ ሊፈርድ ይመጣልና እርሱም ዓለምን በጽድቅ አሕዛብንም በቅንነት ይፈርዳል” (መዝ 95፡13) ╬ “ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም” (ዮሐ 5፡22)

► “በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ በመከራቸውም አዳናቸው ከጨለማና ከሞት ጥላ አወጣቸው፥ እስራታቸውንም ሰበረ” (መዝ 106፡13-14) ╬ “በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፥ በሞት አገርና ጥላ ለተቀመጡትም ብርሃን ወጣላቸው” (ማቴ 4፡16)

► “ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረት፥ በእርሱም ዘንድ ብዙ ማዳን ነውና እስራኤል በእግዚአብሔር ይታመን” (መዝ 129፡7) ╬ “ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና” (ቲቶ 2፡11)

► “እግዚአብሔር የወደደውን ይገሥጻልና፥ አባት የሚወድደውን ልጁን እንደሚገሥጽ” (ምሳ 3፡12) ╬ “እኔ የምወዳቸውን ሁሉ እገሥጻቸዋለሁ እቀጣቸውማለሁ፤ እንግዲህ ቅና ንስሐም ግባ” (ራእ 3፡19)

► “ እነሆ፥ አምላክ መድኃኒቴ ነው ጌታ እግዚአብሔር ኃይሌና ዝማሬዬ ነውና፥ መድኃኒቴም ሆኖአልና በእርሱ ታምኜ አልፈራም ትላለህ” (ኢሳ 12፡2) ╬ “መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና” (የሐዋ 4፡12)

► “እነሆ፥ አምላካችሁ በበቀል በእግዚአብሔርም ብድራት ይመጣልና፥ መጥቶም ያድናችኋልና በርቱ፥ አትፍሩ በሉአቸው” (ኢሳ 35፡4) ╬ “ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ሲገለጥ፥ መከራን ለሚያሳዩአችሁ መከራን፥ መከራንም ለምትቀበሉ ከእኛ ጋር ዕረፍትን ብድራት አድርጎ እንዲመልስ በእግዚአብሔር ፊት በእርግጥ ጽድቅ ነውና እግዚአብሔርን የማያውቁትን ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል” (2ተሰ 1፡7-8)

► “የአዋጅ ነጋሪ ቃል። የእግዚአብሔርን መንገድ በምድረ በዳ ጥረጉ ለአምላካችንም ጐዳና በበረሀ አስተካከሉ” (ኢሳ 40፡3) ╬ “እነሆ፥ መንገድህን የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ተብሎ በነቢዩ በኢሳይያስ እንደ ተጻፈ” (ማር 1፡2)

► “ እነሆ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ኃያል ይመጣል ክንዱም ስለ እርሱ ይገዛል እነሆ፥ ዋጋው ከእርሱ ጋር ደመወዙም በፊቱ ነው” (ኢሳ 40፡10) ╬ “እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ” (ራእ 22፡12)

► “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ አበረታሃለሁ፥ እረዳህማለሁ፥ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ” (ኢሳ 41፡10) ╬ “እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴ 28፡20)

► “ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ እኔም እንደሆንሁ ታስተውሉ ዘንድ፥ እናንተ የመረጥሁትም ባሪያዬ ምስክሮቼ ናችሁ ይላል እግዚአብሔር” (ኢሳ 43፡10) ╬ “ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ” (የሐዋ 1፡8)

► “የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር፥ የሚቤዥም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ፊተኛ ነኝ እኔም ኋለኛ ነኝ፥ ከእኔ ሌላም አምላክ የለም” (ኢሳ 44፡6) ╬ “ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ ሞቼም ነበርሁ እነሆም፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፥ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ” (ራእ 1፡17-18)

► “እናንተ የምድር ዳርቻ ሁሉ፥ እኔ አምላክ ነኝና፥ ከእኔም በቀር ሌላ የለምና ወደ እኔ ዘወር በሉ ትድኑማላችሁ ቃሌ ከአፌ በጽድቅ ወጥታለች፥ አትመለስም፤ ጕልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፥ ምላስም ሁሉ በእኔ ይምላል ብዬ በራሴ ምያለሁ” (ኢሳ 45፡22-23) ╬ “ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው” (ፊልጵ 2፡10-11)

► “እኔ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፥ እንደ ሥራው ፍሬ እሰጥ ዘንድ ልብን እመረምራለሁ ኵላሊትንም እፈትናለሁ” (ኤር 17፡10) ╬ “አብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ ኵላሊትንና ልብን የምመረምር እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፥ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እሰጣችኋለሁ” (ራእ 2፡23)

► “አቤቱ፥ የእስራኤል ተስፋ ሆይ፥ የሚተዉህ ሁሉ ያፍራሉ ከአንተም የሚለዩ የሕይወትን ውኃ ምንጭ እግዚአብሔርን ትተዋልና በምድር ላይ ይጻፋሉ” (ኤር 17፡13) ╬ “ እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፥ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል” (ዮሐ 4፡14)

► “እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር” (ኤር 31፡31) ╬ “እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል ይላል ጌታ” (ዕብ 8፡8)

► “በደላቸውን እምራቸዋለሁና፥ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብምና” (ኤር 31፡34) ╬ “እምነታቸውንም አይቶ። አንተ ሰው፥ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ አለው” (ሉቃ 5፡20)

► “እንዲህም ይሆናል የእግዚአብሔር ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ፥ በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም መድኃኒት ይገኛል። ደግሞም እግዚአብሔር የጠራቸው፥ የምስራች የሚሰበክላቸው ይገኛሉ” (ኢዩ 2፡32) ╬ “የጌታን ስም የሚጠራም ሁሉ ይድናል” (የሐዋ 2፡21፤ ሮሜ 10፡13)

► “አምላኬ እግዚአብሔርም ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ይመጣል” ╬ “ጌታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ሲመጣ፥ በአምላካችንና በአባታችን ፊት በቅድስና ነቀፋ የሌለበት አድርጎ ልባችሁን ያጸና ዘንድ” (1 ተሰ 3፡12)

ለ) ኢየሱስ ክርስቶስ በእውነት የባሕርይ አምላክ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ይኸውም፡-

► “ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይኾናል ስሙም ድንቅ መካር ኀያል አምላክ የዘላለም አባት የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል” (ኢሳ 9፡6)

► “በሌሊት ራእይ አየኊ እነሆም የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ ወደ ፊቱም አቀረቡት ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ኹሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው መንግሥቱም የማይጠፋ ነው” ዳን 7፡13-14

► “ቶማስም። ጌታዬ አምላኬም ብሎ መለሰለት” (ዮሐ 20፡28)

► “አባቶችም ለእነርሱ ናቸውና፤ ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ ርሱም ከኹሉ በላይ ኾኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው” (ሮሜ 9፡5)

► “የታላቁን የአምላካችንንና የመድኀኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን” (ቲቶ 2፡12-13)

►በአምላካችንና በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ ካገኘነው ጋር የተካከለ የክብር እምነትን ላገኙ የመለኮቱ ኀይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ” (2ጴጥ 1፡1-3)

► “የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ መጣ፥ እውነተኛም የኾነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በኾነው በርሱ አለን፥ ርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው” (1ዮሐ 5፡20)

ሐ) ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ የነበረ ዛሬም ያለ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር የኹሉ ፈጣሪ ነው እንላለን ይኸውም፡-

► “በመዠመሪያው ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ…ቃልም ሥጋ ኾነ” ዮሐ 1፡14

► “አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፥ ከእኔም በፊት ነበርና” ዮሐ 1፡30

► “አባታችኊ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤት አደረገ አየም ደስም አለው…እውነት እውነት እላችኋለኊ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለኊ” ዮሐ 8፡56-57

► “አኹንም አባት ሆይ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስኽ ዘንድ አክብረኝ” ዮሐ 17፡5

► “እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን” ኤፌ 2፡10

► “የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢኾኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ኹሉ በርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ኹሉ በፊት በኲር ነው፤ ኹሉ በርሱና ለርሱ ተፈጥሯል ርሱም ከኹሉ በፊት ነው ኹሉም በርሱ ተጋጥሟል” (ቆላ 1፡15-17)

► “ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ዘላለምም ያው ነው” (ዕብ 13፡8)

► “ብቻውን ለኾነ አምላክና መድኀኒታችን ከዘመን ኹሉ በፊት አኹንም እስከ ዘላለምም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኀይልም ሥልጣንም ይኹን አሜን” (ይሁ ቊ.25)

► “ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ ሞቼም ነበርኊ እነሆም፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፥ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ” (ራእ 1፡17-19)

► “አልፋና ዖሜጋ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መዠመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ” (ራእ 22፡13)

መ) ኢየሱስ ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ ከአብና ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በሥልጣን በአገዛዝ እኩል ነው ብለን እናምናለን፡-

► “እንግዲህ ኺዱና አሕዛብን ኹሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችኹንም ኹሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ኹልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴ 28፡19)

► “እኔና አብ አንድ ነን” (ዮሐ 10፡30)

► “እኔን ያየ አብን አይቷል…እኔ በአብ እንዳለኊ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ” (ዮሐ 14፡9-11)

► “የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከኹላችኊ ጋር ይኹን አሜን” (2ቆሮ 13፡14)

► “ክርስቶስ አይደለም ብሎ ኢየሱስን ከሚክድ በቀር ውሸተኛው ማን ነው? አብንና ወልድን የሚክድ ይኽ የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው ወልድን የሚክድ ኹሉ አብ እንኳ የለውም፤ በወልድ የሚታመን አብ ደግሞ አለው እናንተስ ከመዠመሪያ የሰማችኹት በእናንተ ጸንቶ ይኑር ከመዠመሪያ የሰማችኹት በእናንተ ቢኖር እናንተ ደግሞ በወልድና በአብ ትኖራላችኊ” (1ዮሐ 2፡22-24)

ሠ) የጌቶች ጌታ የአማልክት አምላክ ነው ብለን እናምናለን

► “ጌታ ጌታዬን፦ ጠላቶችህን ለእግርህ መቀመጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው” (መዝ 109፡1)

► “እርሱም እንኪያስ ዳዊት፦ ጌታ ጌታዬን ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው ሲል እንዴት በመንፈስ ጌታ ብሎ ይጠራዋል?’’ (ማቴ 22፡43)

► “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስኪገለጥ ድረስ ያለ እድፍና ያለ ነቀፋ ሆነህ ትእዛዙን ጠብቅ ያንም መገለጡን በራሱ ጊዜ ብፁዕና ብቻውን የሆነ ገዥ፥ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ፥ ያሳያል” (1ጢሞ 6፡15)

► “እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉም የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለ ሆነ እነርሱን ድል ይነሣል፥ ከእርሱም ጋር ያሉ የተጠሩና የተመረጡ የታመኑም ደግሞ ድል ይነሣሉ” (ራእ 17፡14)

► “በልብሱና በጭኑም የተጻፈበት የነገሥታት ንጉሥና የጌታዎች ጌታ የሚል ስም አለው” (ራእ 19፡11-16)

ረ) ኢየሱስ ክርስቶስ ኹሉን ዐዋቂ ነው ብለን እናምናለን

► “ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ። ተንኰል የሌለበት በእውነት የእስራኤል ሰው እነሆ አለ ናትናኤልም ከወዴት ታውቀኛለህ? አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ ፊልጶስ ሳይጠራህ፥ ከበለስ በታች ሳለህ፥ አየሁህ አለው” (ዮሐ 1፡48-49)

► “ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር፤ ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና” (ዮሐ 2፡24-25)

► “ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ ተንኰል የሌለበት በእውነት የእስራኤል ሰው እነሆ አለ ናትናኤልም። ከወዴት ታውቀኛለህ? አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ ፊልጶስ ሳይጠራህ፥ ከበለስ በታች ሳለህ፥ አየሁህ አለው” (ዮሐ 1፡48-49)

► “አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው” (ዮሐ 21፡15)

ሰ) ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለም ምሉዕ ነው

► “ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና” (ማቴ 18፡20)

► “ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው” (ዮሐ 3፡13)

ሸ) ለኢየሱስ ክርስቶስ የአምልኮት ስግደት ይገባዋል

► “በታንኳይቱም የነበሩት በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ብለው ሰገዱለት” (ማቴ 14፡33)

► “እነሆም፥ ኢየሱስ አገኛቸውና። ደስ ይበላችሁ አላቸው እነርሱም ቀርበው እግሩን ይዘው ሰገዱለት” (ማቴ 28፡9)

► “እነርሱም፤ ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ” (ሉቃ 24፡52)

► “ደግሞም በኵርን ወደ ዓለም ሲያገባ። የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ ይላል።” (ዕብራ 1፡6)

► “ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ” (ፊልጵ 2፡10)

ቀ) እውነተኛ ፈራጅ ነው ብለን እናምናለን፡-

► “የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ኹሉ፥ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል” (ማቴ 25፡31)

► “ሰዎች ኹሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ ፍርድን ኹሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም” (ዮሐ 5፡22-23)

► “ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለኊ” (ዮሐ 14፡14)

► “እኔም ስለ እናንተ አብን እንድለምን የምላችኊ አይደለኹም” (ዮሐ 16፡26)

► “አንተም በወንድምኽ ላይ ስለ ምን ትፈርዳለኽ? ወይስ አንተ ደግሞ ወንድምኽን ስለ ምን ትንቃለኽ? ኹላችን በክርስቶስ ፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለንና እኔ ሕያው ነኝ፥ ይላል ጌታ፥ ጉልበት ኹሉ ለእኔ ይንበረከካል መላስም ኹሉ እግዚአብሔርን ያመሰግናል ተብሎ ተጽፏልና እንግዲያስ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን” (ሮሜ 14፡10-12)

► “መልካም ቢኾን ወይም ክፉ እንዳደረገ፥ እያንዳንዱ በሥጋው የተሠራውን በብድራት ይቀበል ዘንድ ኹላችን በክርስቶስ በፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናልና” (2ቆሮ 5፡10)

► “እናንተ ደግሞ ታገሡ ልባችኹንም አጽኑ፤ የጌታ መምጣት ቀርቧልና ወንድሞች ሆይ እንዳይፈረድባችኊ ርስ በርሳችኊ አታጒረምርሙ፤ እነሆ ፈራጅ በደጅ ፊት ቆሟል” (ያዕ 5፡8-9)
……….. ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እኩል የሆንክ ጌታችን አምላካችን ሕይወታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የባሕርይ አምላክነትህን፣ የጌቶች ጌታ የአማልክት አምላክ መሆንህን፣ ፈጣሪነትህን ከአብ የማታንስ እውነተኛ ፈራጅ መሆንህን እስከ ዕለተ ምጽአት የምታስተምር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንን ጠብቅ፡፡ አሜን …..
……………. ይቀጥላል፡፡ ……………….
………… መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ ………….

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top