አራቱ ወንጌላት

✥ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እዚህ በመጫን ያንብቡ

✥ ፹፩ (81) መፅሐፍ ቅዱስ እዚህ በመጫን ያንብቡ

አራቱ ወንጌላት(ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ፣ ዮሐንስ)

ወንጌል የሚለው ቃል ትርጉም፦ በግእዝና በአማርኛ <ወንጌል> የምንለው ቃል ትርጉም፦ ብስራት፣ ስብከት፣ የምሥራች ማለት ነው። ይህ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ተገልጦ ከመታየቱ በፊት በግሪክ ቋንቋ
ለሚወዱት ሰው የምሥራች ተብሎ የሚሰጥ የደስታ መግለጫ የሆነ መልካም ስጦታን ያመለክት ነበር። ከክርስቶስ ልደት በኋላ ግን ወንጌል የሚለው ቃል በክርስትና እምነት በተለይም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሲነገር የሚከተሉትን ሁኔታዎች ያመለክታል።
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው ወይም ያስተማረው መልካም የምስራች ነው። ስለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚነገረው መልካም የምሥራች ዜና ሠናይ ነው። ትምህርቱንም <ወንጌል> ብሎ ለመጀመሪያ ጌዜ የጠራው ራሱ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ወንጌል ማለት የምስራች ወይም መልካም ዜና ለመሆኑ ተከታዩን የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ አምላካችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን መመልከት ያስፈልጋል፦
ኢየሱስ ክርስቶስ በትምህርቱ፦
􀂾 ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል። ማቴ. ፳፬፡፲፬
􀂾 እውነት እላችኋለሁ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በማናቸውም ስፍራ በሚሰበክበት እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ እንዲሆን ይነገራል። ማቴ. ፳፮፡፲፫
􀂾 ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ። ማር. ፲፮፡፲፭ ያለ ሲሆን ከጌታችን ቀጥሎም ሐዋርያትና የጌታ ደቀመዛሙርት ሁሉ ስለኢየሱስ ክርስቶስ የሚሰብኩትንና የሚጽፉትን <ወንጌል> ብለው ጠርተውታል።
ወንጌላዊው ማቴዎስ፦
􀂾 ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ በገሊላ ሁሉ ይዞር ነበር። ማቴ. ፬፡፳፫
􀂾 ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በከተማዎችና በመንደሮች ሁሉ ይዞር ነበር። ማቴ.፱፡፴፭
ወንጌላዊው ማርቆስ፦
􀂾 ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እየሰበከ ወደገሊላ መጣ። ማቴ. ፩፡፲፭
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦
ይህም ወንጌል በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለተወለደ እንደቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለተገለጠ ስለ ልጁ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሮሜ.፩፡፬ ስለዚህ <ወንጌል> ስለኢየሱስ ክርስቶስ የሚነገረው መልካም የምሥራች ነው።
ብንናገርም ወንጌል ስንል አንድ ወንጌል እንጂ ያለን ብዙ ወንጌላት አሉን ማለት አይደለም። ወንጌላት ስንል ጸሐፊዎቹ ፬ እንደመሆናቸው መጠን እያንዳንዳቸው የጻፉት ወንጌል በጸሐፊዎቹ ስም ስለተጠራ ነው።
ስለ ወንጌል የተነገሩ ትንቢቶች፦
በብሉይ ኪዳን ስለክርስቶስ የተነገሩ ትንቢትዎች ሁሉ ስለ ቅዱስ ወንጌል የተነገሩ መኾናቸውን መረዳት ያስፈልጋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ስለመወለዱም ሆነ በምድር ላይ ተመላልሶ ስለማስተማሩ እንዲሁም ለሰው ልጆች ሲል የመስቀል ሞት ስለመሞቱ አስቀድመው ነቢያት እያንዳንዱን ተናግረውት ነበር። ይህም በነቢዩ አሞጽ የተጻፈው ቃል ፍጻሜነትን ያገኝ ዘንድ ነው። በእውነት ጌታ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ለባሪያዎቹ ለነቢያት ካልነገረ በቀር ምንም አያደርግም። አሞጽ ፫፡፯ ከዚህ በታችም ፍጻሜአቸው በግልጽ የተነገረውን ሁለት ትንቢቶች ብቻ እንመለከታለን።
􀀩 የሚባርኩህንም እባርካለሁ፥ የሚረግሙህንም እረግማለሁ፤ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ። ዘፍጥ. ፲፪፡፫ ተብሎ በብሉይ ኪዳን የተጻፈው ቃል ፍጻሜነቱን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፎታል፦ መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ። በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ። ገላ. ፫፡፰
􀀩 የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና፤ ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ፥ ለተማረኩትም ነጻነትን ለታሰሩትም መፈታትን እናገር ዘንድ ልኮኛል። የተወደደችውን የእግዚአብሔርን ዓመት አምላካችንም የሚበቀልበትን ቀን እናገር ዘንድ፥ የሚያለቅሱትንም ሁሉ አጽናና ዘንድ፤ ኢሳ. ፷፩ ፡ ፩-፪ ተብሎ በብሉይ ኪዳን የተጻፈው ቃል ፍጻሜነቱን
ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ እንዲህ ሲል ጽፎታል፦ (ለጌታም)የነቢዩንም የኢሳይያስን መጽሐፍ ሰጡት፥ መጽሐፉንም በተረተረ ጊዜ። የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፥ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል ተብሎ የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ። ሉቃ. ፬ ፡ ፲፯-፲፱
የአራቱ ወንጌላት መልእክትና ይዘት፦
አራቱ ወንጌላት በየክፍላቸው መዝግበው የያዙት ስለአምላካችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታሪክና ሥራ ነው። ሁሉም ይህንኑ ታሪክና ሥራ ቢናገሩም እያንዳንዳቸው ከሌሎቹ የሚለዩበት የአመዘጋገብና ያገላለጽ ሁኔታ አለ። ለምሳሌው ያህል ለመጥቀስ በአንዱ የወንጌል ክፍል ተመዝግበው በሦስቱ ወንጌላት ላይ ያልተመዘገቡና የማይገኙ፣ በሁለቱ ወንጌላት ተመዝግበው በተቀሩት በሁለቱ ላይ የማይገኙ፣ እንዲሁም በሦስቱ ወንጌላት ተመዝግበው በቀሪው አንድ ላይ ያልተመዘገቡና የማይገኙ አንዳንድ የጌታ ታሪኮችና ሥራዎች ስለሚገኙ ነው። ይህንን ጠንቅቆ ለመረዳት በእያንዳንዱ መጽሐፍት ግርጌ ባለው የኅዳግ ማመሳከሪያ በመጠቀም ፬ቱንም ወንጌላት ማነጻጸር ይቻላል።
የማቴዎስ፣ የማርቆስና የሉቃስ ወንጌላት <ሲኖፕቲክ> ተብለው ይጠራሉ። <ሲኖፕቲክ> ማለት ተመሳሳይ ማለት ሲሆን ቃሉ የግሪክ ቃል ነው። ሦስቱ ወንጌላት በይዞታቸው በብዙ ክፍል ስለሚመሳሰሉ ይህንን መመሳሰላቸውን ለማስረዳት የተሰጣቸው ስያሜ ነው። ምክንያቱም ሦስቱም ወንጌላት አንድ ዓይነት መልእክታትን ጽፈው ይገኛሉና። ምንም እንኳን የጌታ ተመሳሳይ ታሪክና ሥራ በ፫ቱ ወንጌላት ጠቀስም የአንዱ ወንጌላዊ አገላለጽ ከሌሎቹ የተለየ ስለሚሆን ሁሉንም የወንጌል ክፍል ማንበቡ አስፈላጊ ነው።
የዮሐንስ ወንጌል ነው። ይህም ወንጌል የመዘገበው እንደ ሦስቱ ወንጌላት ስለጌታ ታሪክና ሥራ ቢሆንም በብዛት እነርሱ ያልመዘገቡትን አንዳንድ ታሪክና ሥራዎች መዝግቦ ይገኛል። ስለዚህ በይዞታው ከሦስቱ ወንጌላት ይለያል። ሦስቱ ወንጌላትና አራተኛው ወንጌል በሚከተሉት ሦስት ነገሮች ይለያያሉ። እነርሱም፦
􀀩 ሦስቱ ወንጌላት የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስን ምድራዊውን ታሪክ (የትስብእቱን ማለት የሰውነቱን ነገር) አጉልተው ይጽፋሉ።
ወንጌላዊው ማቴዎስ፦
አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፡ ይስሐቅም ያዕቆብን ወለደ፡…ማታንም ያዕቆብን ወለደ፡ ያዕቆብም ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን የወለደች የማርያምን እጮኛ ዮሴፍን ወለደ። ማቴ. ፩ ፡፩-፲፯ በማለት የጌታን የትውልድ ዝርዝር ጽፏል።
ወንጌላዊው ማርቆስ፦
ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም በፊልጶስ ቂሣርያ ወዳሉ መንደሮች ወጡ በመንገድም። ሰዎች እኔ ማን እንደ ሆንሁ ይላሉ? ብሎ ደቀ መዛሙርቱን ጠየቃቸው። እነርሱም። መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ከነቢያት አንዱ ብለው ነገሩት። እናንተስ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። ጴጥሮስም አንተ ክርስቶስ ነህ ብሎ መለሰለት። ማር.፰፡፳፯-፳፱ በማለት የጌታን የሰውነቱን ነገር ጽፏል።
ወንጌላዊው ሉቃስ፦
ኢየሱስም ሊያስተምር ሲጀምር ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ሆኖት ነበር፤ እንደመሰላቸው የዮሴፍ ልጅ ሆኖ የኤሊ ልጅ፡ የማቲ ልጅ፡…የሄኖስ ልጅ፡ የሴት ልጅ፡የአዳም ልጅ፡ የእግዚአብሔር ልጅ። ሉቃ.፫፡፳፫-፴፰። በማለት የጌታን የትውልድ ዝርዝር ጽፏል።
􀀩 አራተኛው ወንጌል ግን ጌታ ከሰማይ መውረዱንና የመለኮቱን ነገር አጉልቶ ይጽፋል።
ይኸውም፦ በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም። ዮሐ. ፩፡፩-፫
ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው። ዮሐ. ፫ ፡፲፫፤ እንግዲህ አይሁድ ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ ስላለ ስለ እርሱ አንጐራጐሩና
አባቱንና እናቱን የምናውቃቸው ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? እንግዲህ። ከሰማይ ወርጃለሁ እንዴት ይላል? አሉ። ኢየሱስ መለሰ አላቸውም። እርስ በርሳችሁ አታንጐራጕሩ። የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ ተብሎ በነቢያት ተጽፎአል፤ እንግዲህ ከአብ የሰማ የተማረም ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል።
አብን ያየ ማንም የለም፤ ከእግዚአብሔር ከሆነ በቀር፥ እርሱ አብን አይቶአል። እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው። የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ። አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ ሞቱም፤ ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ከሰማይ አሁን የወረደ እንጀራ ይህ ነው። ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው። ዮሐ. ፮፡፵፩-፶፩፤
እናንተ ከታች ናችሁ፥ እኔ ከላይ ነኝ፤ እናንተ ከዚህ ዓለም ናችሁ፥ እኔ ከዚህ ዓለም አይደለሁም። ዮሐ.፰፡፳፫ እንግዲህ ከላይ በተገለጹት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ምክንያት ሦስቱ ወንጌላት ምድራውያን ወንጌላት ሲባሉ አራተኛው ወንጌል ደግሞ ሰማያዊ ወንጌል ይባላል።
􀀩 ሦስቱ ወንጌላት ኢየሱስ ክርስቶስ በማስተማር ዘመኑ ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም ከወጣባቸው ጊዜያት አንዱን ብቻ ማለትም ሊሞት አንድ ሳምንት ሲቀረው ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ ተብሎ እየተዘመረለት ስለመግባቱ ብቻ መዝግበዋል። ወደ ኢየሩሳሌምም ቀርበው ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ ያንጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከ እንዲህም አላቸው። በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ። ማንም አንዳች ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል። ለጽዮን ልጅ እነሆ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሏት ተብሎ በነቢይ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ። ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፥ አህያይቱንና ውርንጫዋንም አመጡለት፥ ልብሳቸውንም በእነርሱ ላይ ጫኑ፥ ተቀመጠባቸውም። ከሕዝቡም እጅግ ብዙዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፥ ሌሎችም ከዛፍ ጫፍ ጫፉን እየቈረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር። የሚቀድሙትም ሕዝብ የሚከተሉትም። ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር። ወደ ኢየሩሳሌምም በገባ ጊዜ መላው ከተማ። ይህ ማን ነው? ብሎ ተናወጠ። ማቴ.፳፩ ፡፩-፲ ከማር.፲፩ ፡፩-፲፩ እና ከሉቃስ ፲፱፡፳፰-፵፭ ጋር በማነፃፀር ያንብቡ።
􀀩 አራተኛው ወንጌል ከገሊላ ኢየሩሳሌም የወጣበትን ፬ ጊዜያት መዝግቧል። ይኸውም፦
􀀩 የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር፥ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። ዮሐ. ፪፡፲፫
􀀩 ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ነበረ፥ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። ዮሐ. ፭፡፩
􀀩 ወንድሞቹ ግን ወደ በዓሉ (ወደ ኢየሩሳሌም)ከወጡ በኋላ በዚያን ጊዜ እርሱ ደግሞ በግልጥ ሳይሆን ተሰውሮ ወጣ። ዮሐ. ፯፡፲
􀀩 ከፋሲካም በፊት በስድስተኛው ቀን ኢየሱስ ከሙታን ያስነሣው አልዓዛር ወደ ነበረበት ወደ ቢታንያ መጣ። በዚያም እራት አደረጉለት፤ ማርታም ታገለግል ነበር፤ አልዓዛር ግን ከእርሱ ጋር ከተቀመጡት አንዱ ነበረ። ማርያምም ዋጋው እጅግ የከበረ የጥሩ ናርዶስ ሽቱ ንጥር ወስዳ የኢየሱስን እግር ቀባች፤ በጠጕርዋም እግሩን አበሰች፤ ቤቱም ከናርዶስ ሽቱ ሞላ። ነገር ግን ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ አሳልፎ ሊሰጠው ያለው
የስምዖን ልጅ የአስቆሮቱ ይሁዳ። ይህ ሽቱ ለሦስት መቶ ዲናር ተሽጦ ለድሆች ያልተሰጠ ስለ ምን ነው? አለ። ይህንም የተናገረ ሌባ ስለ ነበረ ነው እንጂ ለድሆች ተገድዶላቸው አይደለም፤ ከረጢትም ይዞ በውስጡ ከሚገባው ይወስድ ስለ ነበረ ነው። ኢየሱስም። ለምቀበርበት ቀን እንድትጠብቀው ተውአት፤ ድሆችስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፥ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም አለ። ከአይሁድም
ብዙ ሕዝብ በዚያ እንደ ነበረ አውቀው መጡ፥ ከሙታንም ያስነሣውን አልዓዛርን ደግሞ እንዲያዩ ነበረ እንጂ ስለ ኢየሱስ ብቻ አይደለም። የካህናት አለቆችም አልዓዛርን ደግሞ ሊገድሉት ተማከሩ፥ ከአይሁድ ብዙዎች ከእርሱ የተነሣ ሄደው በኢየሱስ ያምኑ ነበርና። በማግሥቱ ወደ በዓሉ መጥተው የነበሩ ብዙ ሕዝብ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመጣ በሰሙ ጊዜ፥ ዮሐ. ፲፪፡ ፩- ፲፪
ሦስቱ ወንጌላት ኢየሱስ ክርስቶስ በገሊላ እና በአካባቢዋ እንዲሁም በመጨረሻ ወደ ኢየሩሳሌም በመጓዝ ላይ እና ከገባ በኃላ ያስተማረውንና የሠራውን ነገር በስፋት መዝግበዋል። ይኸውም፦
􀀩 ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በገሊላ ሁሉ ይዞር ነበር። ማቴ.፬፡፳፫፤
􀀩 በምኵራባቸውም እየሰበከ አጋንንትንም እያወጣ ወደ ገሊላ ሁሉ መጣ። ማር.፩፡፴፱፤
􀀩 ኢየሱስም በመንፈስ ኃይል ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ስለ እርሱም በዙሪያው ባለችው አገር ሁሉ ዝና ወጣ። ሉቃ.፬፡፲፬፤
􀀩 አራተኛው ወንጌል ግን በገሊላ፣ በሰማርያና በይሁዳ እየተመላለሰ የሠራቸውን ሥራዎችና -ያስተማራቸውን ትምህርቶች በሰፊው መዝግቦ ይዟል።
􀀩 እንግዲህ ኢየሱስ ከዮሐንስ ይልቅ ደቀ መዛሙርት ያደርጋል ያጠምቅማል ማለትን ፈሪሳውያን እንደ ሰሙ ጌታ ባወቀ ጊዜ፥ ይሁዳን ትቶ ወደ ገሊላ ደግሞ ሄደ፤ ዳሩ ግን ደቀ መዛሙርቱ እንጂ ኢየሱስ ራሱ አላጠመቀም። በሰማርያም ሊያልፍ ግድ ሆነበት። ስለዚህ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ስፍራ አጠገብ ወደምትሆን ሲካር ወደምትባል የሰማርያ ከተማ መጣ፤ ዮሐ. ፬፡፩-፭
􀀩 ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ነበረ፥ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። ዮሐ. ፭፡፩
ከላይ እንደተገለጸው የ፬ኛው ወንጌል (የዮሐንስ ወንጌል) ከሦስቱ ወንጌላት ጋር ብዙ ልዩነት እንዳለው ተመልክተናል። ሆኖም ግን ከ፬ኛው ወንጌል ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ምንባባት በ፫ቱ ወንጌላት ውስጥ ይገኛሉ። ለምሳሌ፦
􀂾 የመጥምቁ ዮሐንስ ምስክርነት፣
􀂾 የጌታ ጥምቀት፣
􀂾 ፭ እንጀራና ፪ ዓሣ ማበርከቱ
􀂾 ሕማማቱ፣
􀂾 ስቅለቱና ትንሣኤው በአራቱም ወንጌላት የተመዘገቡ ናቸው።
ታዲያ እነዚህም ቢሆኑ በ፬ኛው ወንጌል ከተገለጡት ከ፫ቱ ወንጌላት አገላለጥ በተለየ መንገድ ነው። ፬ቱንም ወንጌላት የሚያገናኛቸው ግን ሁሉም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መናገራቸው ነው።
ከዚህ በታች ደግሞ የኢየሱስን ማንነት እና ታሪክ እንማራለን።
ኢየሱስ ማን ነው?
ጌታችን ሰው ከሆነ በኋላ የተጠራበት ስሙ <ኢየሱስ> የተባለው ስም ነው። <ኢየሱስ>
የሚለው አጠራር የግሪክ ቋንቋ አጠራር ሲሆን ትርጉሙ <አዳኝ> ማለት ነው። ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ>። ማቴ.፩፡፳፩ ከዚህ ስም ጋር እየተቆራኙ የኢየሱስን ማንነት የሚገልጡ ብዙ ክፍሎች አሉ። ከብዙዎቹ መካከል ዋና ዋናዎቹን ከአራቱ ወንጌላትና ከሌሎቹ የሐዲስ ኪዳን ክፍሎች ማስረጃዎችን በመጥቀስ እንደሚከተለው እንመለከታለን።
ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ነው፦
ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ስለመባሉ ከማቴዎስ ወንጌል እነዚህ ክፍሎች ይጠቁሙናል፦
􀂾 የካህናትንም አለቆች የሕዝቡንም ጻፎች ሁሉ ሰብስቦ ክርስቶስ ወዴት እንዲወለድ ጠየቃቸው። እነርሱም። አንቺ ቤተ ልሔም፥ የይሁዳ ምድር፥ ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሽም፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መስፍን ከአንቺ ይወጣልና ተብሎ በነቢይ እንዲህ ተጽፎአልና በይሁዳ ቤተ ልሔም ነው አሉት። ማቴ. ፪፡፬-፮፤
􀂾 እርሱም(ጌታ)እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ። አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ። እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም። የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል። ያን ጊዜም እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ለማንም እንዳይነግሩ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው። ማቴ.፲፭፡፲፮-፳
􀂾 ፈሪሳውያንም ተሰብስበው ሳሉ ኢየሱስ ስለ ክርስቶስ ምን ይመስላችኋል? የማንስ ልጅ ነው? ብሎ ጠየቃቸው። የዳዊት ልጅ ነው አሉት። እርሱም። እንኪያስ ዳዊት። ጌታ ጌታዬን። ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው ሲል እንዴት በመንፈስ ጌታ ብሎ ይጠራዋል? ዳዊትስ ጌታ ብሎ ከጠራው፥ እንዴት ልጁ ይሆናል? አላቸው። አንድም ቃል ስንኳ ይመልስለት ዘንድ የተቻለው የለም፥ ከዚያ ቀንም ጀምሮ ወደ ፊት ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም። ማቴ.፳፪፡፵፩-፵፮
􀂾 ሕዝቡም ሁሉ ተሰብስበው ሳሉ ጲላጦስ በርባንን ወይስ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው፤ በቅንዓት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና። እርሱም በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ ስለ እርሱ ዛሬ በሕልም እጅግ መከራ ተቀብያለሁና በዚያ ጻድቅ ሰው ምንም አታድርግ ብላ ላከችበት። የካህናት አለቆችና ሽማግሎች ግን በርባንን እንዲለምኑ ኢየሱስን ግን እንዲያጠፉ ሕዝቡን አባበሉ። ገዢውም መልሶ። ከሁለቱ ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው፤ እነርሱም በርባንን አሉ። ጲላጦስ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን እንግዲህ ምን ላድርገው? አላቸው፤ ሁሉም ይሰቀል አሉ። ማቴ.፳፯፡፲፯-፳፪
ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ስለመባሉ ከማርቆስ ወንጌል እነዚህ ክፍሎች ይጠቁሙናል፦
􀂾 ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም በፊልጶስ ቂሣርያ ወዳሉ መንደሮች ወጡ በመንገድም ሰዎች እኔ ማን እንደ ሆንሁ ይላሉ? ብሎ ደቀ መዛሙርቱን ጠየቃቸው። እነርሱም መጥምቁ ዮሐንስ ሌሎችም ኤልያስ ሌሎችም ከነቢያት አንዱ ብለው ነገሩት። እናንተስ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። ጴጥሮስም አንተ ክርስቶስ ነህ ብሎ መለሰለት። ስለ እርሱም ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው። ማር.፰፡፳፯-፴
􀂾 የክርስቶስ ስለ ሆናችሁ በስሜ ጽዋ ውኃ የሚያጠጣችሁ ሁሉ፥ ዋጋው እንዳይጠፋበት እውነት እላችኋለሁ። ማር. ፱፡፵፩
􀂾 ሊቀ ካህናቱም በመካከላቸው ተነሥቶ። አንዳች አትመልስምን? እነዚህስ በአንተ ላይ የሚመሰክሩብህ ምንድር ነው? ብሎ ኢየሱስን ጠየቀው። እርሱ ግን ዝም አለ አንዳችም አልመለሰም። ደግሞ ሊቀ ካህናቱ ጠየቀውና። የቡሩክ ልጅ ክርስቶስ አንተ ነህን? አለው። ኢየሱስም እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለ። ማር. ፲፬፡ ፷-፷፪
ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ስለመባሉ ከሉቃስ ወንጌል እነዚህ ክፍሎች ይጠቁሙናል፦
􀂾 በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። ሉቃ.፪፡፲፩
􀂾 አጋንንትም ደግሞ አንተ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ እያሉ እየጮኹም ከብዙዎች ይወጡ ነበር፤ ገሠጻቸውም ክርስቶስም እንደ ሆነ አውቀውት ነበርና እንዲናገሩ አልፈቀደላቸውም። ሉቃ. ፬፡፵፩፤
􀂾 በነጋም ጊዜ የሕዝቡ ሽማግሌዎችና የካህናት አለቆች ጻፎችም ተሰብስበው ወደ ሸንጎአቸው ወሰዱትና ክርስቶስ አንተ ነህን? ንገረን አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው። ብነግራችሁ አታምኑም፤ ሉቃ. ፳፪፡፷፮-፷፯፤
􀂾 ይህ ሕዝባችንን ሲያጣምም ለቄሣርም ግብር እንዳይሰጥ ሲከለክል ደግሞም። እኔ ክርስቶስ ንጉሥ ነኝ ሲል አገኘነው ብለው ይከሱት ጀመር። ሉቃ. ፳፫፡ ፪፤
􀂾 እርሱም(ጌታ) እናንተ የማታስተውሉ፥ ነቢያትም የተናገሩትን ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ፤ ክርስቶስ ይህን መከራ ይቀበል ዘንድና ወደ ክብሩ ይገባ ዘንድ ይገባው የለምን? አላቸው። ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን ተረጐመላቸው። ወደሚሄዱበትም መንደር ቀረቡ፥ እርሱም ሩቅ የሚሄድ መሰላቸው። እነርሱም ከእኛ ጋር እደር፥ ማታ ቀርቦአልና ቀኑም ሊመሽ ጀምሮአል
ብለው ግድ አሉት፤ ከእነርሱም ጋር ሊያድር ገባ። ከእነርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጦ ሳለ እንጀራውን አንሥቶ ባረከው፥ ቈርሶም ሰጣቸው፤ ዓይናቸውም ተከፈተ፥ አወቁትም፤ እርሱም ከእነርሱ ተሰወረ። ሉቃ. ፳፬፡፳፭-፴፩
􀂾 እርሱም (ጌታ) ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው አላቸው። በዚያን ጊዜም መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፤ እንዲህም አላቸው። ክርስቶስ መከራ ይቀበላል በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፥ በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል ተብሎ እንዲሁ ተጽፎአል። እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ። ሉቃ. ፳፮፡፵፬-፵፰
ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ስለመባሉ ከዮሐንስ ወንጌል እነዚህ ክፍሎች ይጠቁሙናል፦
􀂾 ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ። ዮሐ. ፩፡፲፯
􀂾 የተላኩትም ከፈሪሳውያን ነበሩና። እንኪያስ አንተ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካይደለህ፥ ስለ ምን ታጠምቃለህ? ብለው ጠየቁት። ዮሐንስ መልሶ እኔ በውኃ አጠምቃለሁ፤ ዳሩ ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሟል፤ እኔ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የማይገባኝ፥ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይልቅ የሚከብር ይህ ነው አላቸው። ይህ ነገር ዮሐንስ ያጠምቅበት በነበረው በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ በቤተ ራባ ሆነ። በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ

የእግዚአብሔር በግ። አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፥ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል ብዬ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነው። እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውኃ እያጠመቅሁ እኔ መጣሁ። ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መሰከረ። መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሆኖ ሲወርድ አየሁ፤ በእርሱ ላይም ኖረ። እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ። መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ። እኔም አይቻለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ መስክሬአለሁ። በነገው ደግሞ ዮሐንስ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ቆመው ነበር፥ ኢየሱስም ሲሄድ ተመልክቶ። እነሆ የእግዚአብሔር በግ አለ። ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት። ኢየሱስም ዘወር ብሎ ሲከተሉትም አይቶ ምን ትፈልጋላችሁ? አላቸው። እነርሱም ረቢ፥ ወዴት ትኖራለህ? አሉት፤ ትርጓሜው መምህር ሆይ ማለት ነው። መጥታችሁ እዩ አላቸው። መጥተው የሚኖርበትን አዩ፥ በዚያም ቀን በእርሱ ዘንድ ዋሉ፤ አሥር ሰዓት ያህል ነበረ።ከዮሐንስ ዘንድ ሰምተው ከተከተሉት ከሁለቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበረ። እርሱ አስቀድሞ የራሱን ወንድም ስምዖንን አገኘውና። መሢሕን አግኝተናል አለው፤ ትርጓሜውም ክርስቶስ ማለት ነው። ዮሐ. ፩፡፳፬-፵፪፤
􀂾 ሴቲቱም ክርስቶስ የሚባል መሲሕ እንዲመጣ አውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ይነግረናል አለችው። ኢየሱስ የምናገርሽ እኔ እርሱ ነኝ አላት። በዚያም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ መጡና ከሴት ጋር በመነጋገሩ ተደነቁ፤ ነገር ግን ምን ትፈልጊያለሽ? ወይም ስለ ምን ትናገራታለህ? ያለ ማንም አልነበረም። ሴቲቱም እንስራዋን ትታ ወደ ከተማ ሄደች ለሰዎችም ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ፤ እንጃ እርሱ
ክርስቶስ ይሆንን? አለች። ከከተማ ወጥተው ወደ እርሱ ይመጡ ነበር። ይህም ሲሆን ሳለ ደቀ መዛሙርቱ መምህር ሆይ፥ ብላ ብለው ለመኑት። እርሱ ግን እናንተ የማታውቁት የምበላው መብል ለእኔ አለኝ አላቸው። ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ የሚበላው አንዳች ሰው አምጥቶለት ይሆንን? ተባባሉ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው። እናንተ
ገና ፬ ወር ቀርቷል መከርም ይመጣል ትሉ የለምን? እነሆ እላችኋለሁ፥ ዓይናችሁን አንሡ አዝመራውም አሁን እንደ ነጣ እርሻውን ተመልከቱ። የሚያጭድ ደመወዝን ይቀበላል፥ የሚዘራና የሚያጭድም አብረው ደስ እንዲላቸው ለዘላለም ሕይወት ፍሬን ይሰበስባል። አንዱ ይዘራል አንዱም ያጭዳል የሚለው ቃል በዚህ እውነት ሆኗልና። እኔም እናንተ ያልደከማችሁበትን ታጭዱ ዘንድ ሰደድኋችሁ፤ ሌሎች ደከሙ እናንተም በድካማቸው ገባችሁ። ሴቲቱም ያደረግሁትን ሁሉ ነገረኝ ብላ ስለ መሰከረችው ቃል ከዚያች ከተማ የሰማርያ ሰዎች ብዙ አመኑበት። የሰማርያ ሰዎችም ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ በእነርሱ ዘንድ እንዲኖር ለመኑት፤ በዚያም ሁለት ቀን ያህል ኖረ። ስለ ቃሉ ከፊተኞች ይልቅ ብዙ ሰዎች አመኑ፤ ሴቲቱንም አሁን የምናምን ስለ ቃልሽ አይደለም፥ እኛ ራሳችን ሰምተነዋልና፤ እርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደ ሆነ እናውቃለን ይሉአት ነበር። ዮሐ. ፬፡፳፭-፵፪
􀂾 ስምዖን ጴጥሮስ። ጌታ ሆይ፥ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ፤ እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ አምነናል አውቀናልም ብሎ መለሰለት። ዮሐ. ፮፡ ፷፰-፷፱
􀂾 እንግዲህ ከኢየሩሳሌም ሰዎች አንዳንዶቹ እንዲህ አሉ። ሊገድሉት የሚፈልጉት ይህ አይደለምን? እነሆም፥ በግልጥ ይናገራል አንዳችም አይሉትም። አለቆቹ ይህ ሰው በእውነት ክርስቶስ እንደ ሆነ በእውነት አወቁን? ነገር ግን ይህን ከወዴት እንደ ሆነ አውቀናል፤ ክርስቶስ ሲመጣ ግን ከወዴት እንደ ሆነ ማንም አያውቅም። ዮሐ.፯፡፳፭-፳፯
􀂾 አይሁድም እስከ መቼ በጥርጣሪ ታቆየናለህ? አንተ ክርስቶስ እንደ ሆንህ ገልጠህ ንገረን አሉት። ኢየሱስም መለሰላቸው፥ እንዲህ ሲል። ነገርኋችሁ አታምኑምም እኔ በአባቴ ስም የማደርገው ሥራ ይህ ስለ እኔ ይመሰክራል፤ ዮሐ.፲፡፳፬-፳፭
􀂾 ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል። ዮሐ. ፳፡፴፩

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top