ወላዲተ አምላክ በነገር ድኅነት

ዳግሚተ ሔዋን (አዲሲቱዋ ሔዋን )

ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር  << በአንተና በሴቲቱ በዘርህና በዘርዋ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ : እርሱ እራስህን ይቀጠቅጣል አንተም ሰኮናውን ትነክሳለህ :: >> ( ኦሪት ዘፍጥረት ምህራፍ 3 ቁጥር 15 ) ሲል የተናገረው ይህ ተስፋ ትንቢት መፍቀሬ ስብእ የሆነው አምላክ ለሰው ልጆች ያለውን አምላካዊ የአድኅኖት ዕቅድና በጎ ፈቃድ የሚገልጥ መሪ ቃለ ተስፋ ነው :: በመሆኑም ይህ አምላካዊ ተስፋ ትንቢት በምክረ ከይሲ ተታለው በኃጢአት ተሰናክለው በመንጸፈ ደይን ወድቀው በእግረ አጋንንት ይጠቀጠቁ ለነበሩት ለአባታችን አዳምና ለእናታችን ሔዋን እንዲሁም ለልጆቻቸው ሁሉ የተሰጠ የመጀመሪያ አምላካዊ የድህነት ተስፋ ነው :: ስለሆነም መጽሐፍ “” ተፈጸመ ተስፋ አበው በማርያም ድንግል ወበቀራዮ ተተከለ መድኃኒት መስቀል : የቅዱሳን አበው ተስፋ ድኅነት በቅድስት ድንግል ማርያም ተፈጸመ : የድኅነተ ዓለም ሥራ የተፈጸመበት መድኃኒት መስቀልም በቀራንዮ ተተከለ “” እንዳለው ወላዲተ አምላክ የዚህ ቃለ ትንቢት ፍጻሜ መሠረት መሆኑዋን የመለክቱዋል :: ከላይ የተጠቀሰው ምስጢረ ድኅነተ አለም ቃለ ትንቢት ለጊዜው በቀዳሚነት ሔዋንና በጥንተ ጠላታችን በዲያቢሎስ መካከል ያለውን ጸብና ክርክር የሚያሳይ ሲሆን ፍጻሜ ምሥጢሩ ግን በዳግሚተ ሔዋን (አዲሲቱዋ ሔዋን ) በወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያምና ምክንያተ ስህተት በሆነው በሰይጣን መካከል የሚኖረውን ጠላትነት የሚገልጥ ነው :: (ራእይ ዮሐንስ ምህራፍ 12 ቁጥር 1-17) ከዚህም ሌላ የሴቲቱ (የድንግል ማርያም ) ዘር በሆነው በአምላካችን በመድኃኒታችን በፈጣሪያችን በኢየሱስ ክርስቶስና በሠራዊተ አጋንንት መካከል የሚኖረውን ጠላትነትም ያስረዳል :: ይህም ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “” አንተም የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥህ “” መዝሙረ ዳዊት ምህራፍ 73 ቁጥር 14 ባለው መሠረት የድንግል ማርያም ልጅ መድኅነ ዓለም ክርስቶስ ጥንተ ጠላታችን የሆነውን የዲያቢሎስን ራስ በመስቀል ላይ ቀጥቅጧል :: በአንጻሩ ደግሞ “” እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩኝ “” መዝሙረ ዳዊት ምህራፍ 21 ቁጥር 16 ተብሎ እንደተጻፈ ጠላት ዲያቢሎስ በአይሁድ ልቡና አድሮ የአምላካችን የመድኃኒታችን የፈጣሪያችንን ቅዱሳት እግሮች በቀኖት አስቸንክሯል :: ዮሐንስ ወንጌል ምህራፍ 19 ቁጥር 23 :: ታላቁ ሐዋርያ ብርሀነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም ይህንን ድንቅ ምስጢረ ድኅነት አስመልክቶ ሲናገር “” ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ እግዚአብሔር ልጁን ላከ ከሴትም ተወለደ :: እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ “” በገላትያ ምህራፍ 4 ቁጥር 4-5 በማለት መስክሯል :: በዚህም ሐዋርያዊ ቃል መሠረት ከላይ የገለጽነው የድኅነተ ዓለም ተስፋ በቅድስት ድንግል ማርያም እንደተፈጸመ ልብ ይሏል :: ዳግመኛም በቅዱስ ወንጌል እንደተጻፈው አምላካችን ጌታችን መድኃኒታችን ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያምን የመጀመሪያውን ተአምር ባደረገበት በገሊላ ቃና ሠርግ ቤት በዮሐንስ ወንጌል ምህራፍ 2 ቁጥር 4 እንዲሁም የድኅነተ ዓለም ሥራን በፈጸመበት በቀራንዮ መስቀል ላይ የዮሐንስ ወንጌል ምህራፍ 19 ቁጥር 26 “” አንቺ ሴት “” ሲል መጥራቱ አስቀድሞ ለሰው ልጆች የሰጠው የድህነት ተስፋ በእርዋ በኩል መፈጸሙን በምሥጢር ያጠይቃል :: በቀዳሚት ሔዋንና በዳግሚት ሔዋን በእመቤታችን መካከል ያለውን ምሥጢራዊ ንጽጽር በየዘመኑ የተነሡ የተለያዩ አበው ሊቃውንት መተርጉማን አምልተውና አስፍተው ገልጸዋል :: ይህውም ቀዳሚት ሔዋን ለፈቃደ እግዚአብሔር ባለመታዘዙዋ ምክንያት በመላው የሰው ዘር ላይ መርገምንና ሞትን አምጥታለች :: በአንጻሩ ደግሞ ዳግሚት ሔዋን የተባለችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለፈጣሪዋ ፈቃድ በመታመኑዋና በመታዘዙዋ ምክንያት በመርገምና በሞት ጥላ ሥር ወድቆ ለነበረው ዓለም በረከትንና ሕይወትን አስገኝታለች :: ይህንን አስመልክቶ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ሲናገር “” በእንተ ሔዋን ተዐጽወ ኖኅተ ገነት ወበእንተ ማርያም ድንግል ተርኅወ ለነ ዳግመ : በቀዳሚት ሔዋን ምክንያት የገነት ደጃፍ ተዘጋብን ዳግመኛም ስለ ዳግሚት ሔዋን ስለ ድንግል ማርያም ተከፈተልን “” በማለት አስገንባል :: ከዚህም ሌላ ሰፊና ጥልቅ በሆነው የነገረ ማርያም አስተምህሮው የዜና አበው ሊቃውንት “” የነገረ ማርያም አባት “” እያሉ የሚጠሩት ታላቁ የቤተክርስቲያን ሊቅ ቅዱስ ሔኔሬዎስ ከላይ የገለጥነውን ኃይለ ቃል መሠረት በማድረግ እመቤታችን “” የሔዋን ጠበቃ አለኝታ “” ብሏታል :: በዜና አበው ክፍለ ትምህርት እንደሚታወቀው ይህ አባት የነበረበት ዘመን “” የነገረ ማርያም ዘመነ ልደት “” በመባል ይታወቃል ::
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለነገር ድኅነት መሠረት መሆኗን በመግለጥ የተአምሯ መጽሐፍ “” እግዝእትነ ማርያም ነበረት እምቅድመ ዓለም በኅሊና አምላክ “” ይላል :: ከዚህም ኃይለ ቃል ድኅነተ ሰብእ የሆነው እግዚአብሔር አምላክ አስቀድሞ የፈቀደውና ያሰበው የቸርነቱና የመግቦቱ ሥራ መሆኑን እንረዳለን : እንገነዘባለን :: ከዚህም ጋር ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ “” ወበእንተ ዝንቱ አስተርእየ ወልደ እግዚአብሔር ከመ ይስዐር ግብሮ ለጋኔን : ስለዚህ የዲያቢሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ “” 1ኛ ዮሐንስ መልዕክት ምህራፍ 3 ቁጥር 8 ሲል እንደመሰከረው ጥንተ ጠላታችን የሆነው ዳያቢሎስ በሥጋ ከይሲ ተሠውሮ አዳምንና ሔዋንን እንዳሳተ ኦሪት ዘፍጥረት ምህራፍ 3 ቁጥር 1-14 አካላዊ ቃል አምላካችን ፈጣሪያችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ ብእሲ ተሠውሮ ወደ ቀደመው ጸግና ክብር መልሷቸዋል :: ይህንን ምስጢር ሊቃውንተ ቤተክርስቲና አሞንዮስና አውሳብዮስ በመቅደመ ወንጌል ሲገልጡ “” ወበከመ ተኃብእ ሰይጣን በጉሕሎቱ ውስተ ሥጋ ከይሲ ከማሁ ኮነ ድኅነትነ በሠውሮተ ቃለ እግዚአብሔር በዘመድነ :ሰይጣን በሥጋ ከይሲ ተሰውሮ አዳምን እንዳሳተው ጌታችን መድኃኒታችን ፈጣሪያችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም በስጋ ብእሲ ተሰውሮ መጥቶ ዓለምን አዳነ “” በማለት ተናግረዋል :: በዚህም ትርጉዋሜ ምስጢር መሠረት የሰው ልጅ በምክረ ከይሲ ተታሎ ሕገ እግዚአብሔርን አፈረሰ በሀጢያቱም ምክንያት ከፈጣሪው አንድነት ተለየ ሲባል በአካለ ተደልሎ በልሳነ ከይሲ ተታሎ መሳቱን መናገር ነው :: ስለሆነም ጥንተ ጠላታችን ዲያቢሎስ አካለ ከይሲን መሰወሪያ ልሳነ ከይሲን መናገሪያ አድርጎ በማሳቱ በማኅደሩ ኃዳሪውን መናገሩ እንጂ ለሰው ልጅ ስሕተት ምንጩና መሠረቱ ራሱ ዲያቢሎስ መሆኑን መረዳት ያሻል ::
ቤዛዊት ዓለም ድንግል ማርያም በዘመነ ብሉይ በተለአየ ኅብረ አምሳል መገለጧና በብዙ ዓይነት ኅብረ ትንቢት መነገሯም በነገረ ድኅነት ውስጥ ያላትን ሰፊ ድርሻ በጥልቀት ያስረዳል :: በዚህም መሠረት የነገረ ማርያም ትምህርት ከነገረ ድኅነት ትምህርት ጋር የተያያዘ ጥልቅ ምሥጢር እንዳለው ልብ ይሏል :: የመጋቤ ሐዲስ የቅዱስ ገብርኤል ዜና ብሥራትና የእመቤታችን ተአምኖና ተአዛዚተ እግዚአብሔር መሆን የመሲሕ ክርስቶስን ወደዚህ ዓለም መምጣትና የአዲስ ኪዳንን መጀመር ያበሥራል :: በአጠቃላይ ይህንን ታላቅና ድንቅ ምስጢር በተመለከት አራቱ ወንጌላውያን ይልቁንም ደግሞ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ የእመቤታችንን ሁለንተናዊ ሕይወት በመግለጥ በልዑል እግዚአብሕሄር ፊት ያላትን ክብርና የባለሟልነት ሞገስ እንዲሁም ከመልአከ ብሥራቷ ከቅዱስ ገብርኤል ጋር ያደረገችውን ቃለ ምልልስ በሰፊው ተናግሮላታል ::
በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የነገረ ማርያም አስተምህሮ አምላካዊ የድኅነት ዓለም ጉዞ በማህጸነ ድንግል እንዲጀምር ምክያትና መሠረት የሆነው የመልአከ ሰላም የቅዱስ ገብርኤል ዜና ብሥራት አስቀድሞ የሰው ልጆች በኃጢያት የወደቁበትን መርገምና ሞት ወደ ዓለም የገባበትን የመልአክ ጽልመት የዲያቢሎስን ተንኮል የሻረና ክፉ ምክሩንም ያፈረሰ የበረከትና የሕይወት መንገድ ነው :: በመሆኑም በእመቤታችን በድንግል ማርያም አማካይነት የተፈጸመው የሥጋዌ ምሥጢር መፍቀሬ ሰብእ የሆነው ቸሩ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን ጥልቅ ፍቅር የገለጠበት ታላቅ የድኅነት ምሥጢር ነው :: በቅዱስ መጽሐፍ እንደተገለጸው የመጀመሪያዪቱ ሔዋን በምክረ ከይሲ ተታልላ የጠላት ዲያቢሎስን ክፉ ምክር ሰምታ በመቀበሏ ምክንያት ለሰው ልጆች ድቀት (ውድቀት ) እንዲሁም የሞት ፍርድ ምክያት ሆናለች :: ኦሪት ዘፍጥረት ምህራፍ 3 ቁጥር 4 – 6 ::
በአንጻሩ ደግሞ ዳግሚት ሔዋን የተባለችው ቅድስት ድንግል እመቤታችን በልዑል እግዚአብሔር ፊት በባለሟልነት የሚቆመውን መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤልን ቃለ ብስራት ሰምታ “” ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ : እንደቃልህ ይሁንልኝ ይደረግልኝ “” ብላ በእምነት በመቀበሏ ምክንያት ድኅነት ሆነችን :: ይህን ቃሏን ምክንያት አድርጎም አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ከሥጋዋ ሥጋ :ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ በማኅጸኗ አደረ :: በመሆኑም
ቀዳሚት ሔዋንን ምክንያተ ስሕተት : ምክንያተ ሞት በመሆኗ ሲወቅሳትና ሲከሳት የነበረው የሰው ዘር በሙሉ ምክንያተ “” ድኅነት ምክንያተ በረከት ወሕይወት የሆነች ዳግሚት ሔዋን እመቤታችንን << ብጽዕት አንቲ እንተ ተአምኒ ከመ ይከውን ቃል ዘነገሩኪ እምኅበ እግዚአብሔር :ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልከው ከእግዚአብሔር ዘንድ አግኝተው የነገሩሽ ቃል እንዲፈጸም የምታምኚ አንቺ በእውነት ብጸዕት ነሽ ንዕድ ክብርት ነሽ የሉቃስ ወንጌል ምህራፍ 1 ቁጥር 28-38 እያለ የሚያመሰግናት ሆኗል :: ከላይ እንደተገለጠው ወላዲተ አምላክ የቅዱስ ገብርኤልን ዜና ብሥራት ሰምታ በማመኗ ምክንያት መድኅነ ዓለም ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም ስለመጣ ብሥራተ መልአክ የብሉይ ኪዳን አምሳልና ትንቢት ፍጻሜ ወይም መደምደሚያ ሆነ :: ይህንን ታላቅና ድንቅ ሚስጢር አስመልክቶ የቤተክርስቲያናችን የነገረ ማርያም መጽሐፍ ሲናገር “” ወቅዱስ ገብርኤል በቃለ ብሥራቱ ኅተመ ትንቢትዮሙ ለነቢያት :: ገብርኤል ውእቱ ዘአፈልፈለ ስቴ ፍሥሐ ለኩሉ ዓለም ወአብጠለ እማልባበ ሰብእ ኩሉ ስቴ ኃዘን መሪር ዘየአኪ እምሕምዘ አፍሀት ዘይቀትል “” ይላል :: ይህም ማለት “” ቅዱስ ገብርኤልም በምሥራቹ ቃል የቅዱሳን ነቢያትን ትንቢት አተመ :አጸና : ፈጸመ : ዘጋ : አረጋገጠ :: ለዓለም ሁሉ የደስታ መጠጥና ምንጭን ያፈለቀ : ያስገኘ : ያመነጨ : ገዳይ ከሆነ የእባብ (የአውሬ ) መርዝም የሚከፋ መራራ የኃዘን ውኃን (መጠጥን :ምንጭን ) ከሰው ሁሉ ልቡና ያስወገደ ያራቀ ይህ ቅዱስ ገብርኤል ነው “” ማለት ነው :: በዚህም መሠረት ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ የጻፈው የነገረ ብሥራት ምሥጢር ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን የንገረ ሥጋዌ ትምህርት ምንጭ ለሆነው የነገረ ማርያም ትምህርት ዐቢይ መሠረት ጥሏል :: ከዚህ በተጨማሪም ብሥራተ መልአክ የሰው ልጆችን አስከፊ የኃጢያትና የመርገም ታሪክ የቀየረ ታላቅ ክስተት በመሆኑ ለቤተክርስቲያናችን ጥልቅ የነገረ ድኅነት አስተምህሮ በቂ ማስረጃና ምስክር ነው :: እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለመልአኩ ዜና ብስራት በሰጠችው ቃለ ተአምንሮ ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር ከጥንት ያሰበውና የፈቀደው ያድህነተ ዓለም ሥራ እንዲፈጸምና አማናዊ እንዲሆን አድርጋለች :: ይህም ወላዲተ አምላክ በነገረ ድኅነት ውስጥ ያላትን ታላቅ ሱታፌ በጉልህ ያሳያል :: ይህንን ምሥጢር በተመለከተ ኢትዮጵያዊው ሊቅ በድርሰቱ “” ዘበቃለ ጉሕሎቱ ለሰይጣን መልአክ ስሕተት ተሰፍሐ ግላ ጽልመት ውስተ ኩሉ ዓለም :ወበቃለ ብሥራቱ ለገብርኤል መልአክ ጽድቅ ተሰፍሐ ብርሀነ ሕይወት ውስተ ኩሉ ዓለም : የስሕተት አለቃ በሆነው በሰይጣን የክፋትና የጥፋት ቃል ምክንያት የጨለማ መጋረጃ በዓለም ሁሉ እንደተዘረጋ : የእውነት መልአክ በሆነው በቅዱስ ገብርኤል የምሥራች ቃል ደግሞ የሕይወት ብርሀን በዓለም ሁሉ ተዘረጋ በማለት መስክሯል :: ኢትዮጵያዊው የዜማ ሊቅ ቅዱስ ያሬድም እመቤታችን በነገረ ድህነት ውስጥ ያላትን ልዩ ሥፍራ ሲናገር “” በእንተ ተሠግዎቱ ለወልደ አምላክ እምኔኪ ቀሩባነ ኮነ እምድር ውስተ አርያም :ብኪ ወበከመ ወልድኪ “” ብሏል :: የዚህ ኃይለ ቃል ትርጉዋሜ ምሥጢርም ቃለ እግዚአብሔር ወልድ ከሥጋሽ ሥጋ :ከነፍሥሽ ነፍስን ነሥቶ ካንቺ ሰው በመሆኑ ከምድር ወደ ሰማይ :ከሞት ወደ ሕይወት : ከመርገም ወደ በረከት : ከኃሳር ወደ ክብር : ከሲኦል ወደ ገነት የተሸጋገርንብሽ ማለት ነው :: ከላይ የተጠቀሰውን በቃዲምት ሔዋንና በዳግሚተ ሔዋን መካከል ያለውን ምሥጢራዊ ንጽጽር አስመልክቶ
” ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ “”በመባል የሚታወቀው ሊቁ ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ሲገልጽ “” ለእመ ኃሠሥላ ለሔዋን ትረክባ በህየ እንዘ ትትፌሣሕ በወለታ ዘእምጽአት ፈውሰ ለቁስሊሀ : ለእመ ኃሠሦኮ ለአዳም ረክቦ በህየ እንዘ ይትፌሣሕ ወይገብር በዓለ ምስለ ዳግማዊ አዳም “” በማለት በንጽጽሩ ውስጥ ያለውን ጥልቅና ረቂቅ ምሥጢረ ድህነት አስተምሯል :: እንደ ሊቁ አገላለጽ ዳግሚት ሔዋን የተባለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፍሬ ሕይወት ወመድኃኒት የሆነው ጌታ የተገኘባት አማናዊት ዕጸ ሕይወት በመሆኗ የዕጸ በለስን ፍሬ በልታ ሞትን ላመጣችብን ለቀዳሚቷ ሔዋን ካሣ ናት :: ምክንያቱም ከዳግሚት ሔዋን ከድንግል ማርያም የተወለደው የማኅጸኗ ፍሬ ጌታችን መድኃኒታችን አምላካችን ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሚያርቅ :በረከተ ሥጋ :በረከተ ነፍስን የሚያድል ሕይወተ ሥጋን ሕይወተ ነፍስን የሚሰጥ : ቀዳሴ ሥጋ ወነፍስ ወመንፈስ የሆነ ቡሩክ አምላክ ነውና ::
ያስተማረን የመከረን የእናቱን ክብር እንድንመሰክር የረዳን ቸሩ መድኃኔ ዓለም ክብር ምስግና ይድረሰው :: ለእናቱ ለእመብርሀን እመ አምላክ ቅድስት ንጽህይት ድንግል ማርያምም ክብር ምስግና ይድረሳት :: እግዚአብሔር ያከበራቸው ሁሉ እርሱ በሰጣቸው ክብር ይክበሩ ለሰይጣንና ለሰራዊቱ ግን አሁንም ሞት ይሁን አሜን ::
ሌሎችንም እግዚአብሔር እንደረዳን መጠን እንመለከታለን :: የዘወትር ጸሎታችሁ አይለየኝ ::
ወስብሀት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን ::
ይቆየን

ዘመነ ጽጌ (ማኅሌተ ጽጌ)

የእመቤታችንን ስደት ስናስብ «ሲነቅፏችሁና ሲያሳድዷችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲነግሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ፡፡ ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ ሐሴትም አድርጉ፡፡ ከእናንተም በፊት የነበሩትን ነብያት እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና» /ማቴ 5-11/ የሚለውን የስደት ዋጋ ጭምር እያሰብን መሆን ይገባል፡፡
ይህንንም የእመቤታችንን ስደት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 6 ድረስ በማኅሌትና በመዝሙር ትዘክራለች፡፡ ካህናቱም በዕለተ ሰንበት ከምሽት ጀምረው በማኅሌትና በመዝሙር ምስለ ፍቁር ወልዳን /የልጇ እና የእርሷ/ ሥዕል ይዘው ቤተክርስቲያኑን ይዞራሉ፡፡
ይህም የእመቤታችንን ስደት ለማጠየቅ ነው፡፡ ሌሎችም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የደረሰባቸውን መከራ ለማስታወስ የፍቃድ ጾም ይጾማሉ፡፡ ወርኃ ጽጌ ለሚከናወነው መንፈሰዊ አገልግሎት መነሻው “መልአኩ ሕፃኑንና እናቱን ወደ ግብፅ ይዘሃቸው ሽሽ፣ የሕፃኑን ነፍስ ሊገድሉት ይፈልጋሉና” ሲል ለዮሴፍ በሕልሙ በነገረው መሠረተ ዮሴፍም ሕፃኑንና እናቱን ድንግል ማርያምን ይዞ ወደ ግብፅ መሰደዱና እመቤታችንና ሕፃኑ ሦስት ዓመት ከመንፈቅ በስደት ከኖሩ በኋላ /ራእይ.12፣6/ ወደ አገራቸው ወደ ናዝሬት የመመለሳቸው መታሰቢያ ነው፡፡ /ማቴ. 2፣13-23፣ ት.ኢሳ.19፣1፣ እንባቆም 3፣6-7፣ መዝ.83፣3/፡፡
በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሡ አባ ጽጌ ብርሃን ፍሬ ከአበባ አበባም ከፍሬ እንደሚገኝ ሁሉ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምንና ልጇን ኢየሱስ ክርስቶስን በአበባና በፍሬ እየመለሰ በሚያስረዳው ድርሰታቸው እንዲህ በማለት ገልጸውለታል፡፡ “ አፈወ ሮማን ማርያም ጽጌ ቀናንሞ ወአበሜ፣ እስከ ተጸምሐየየ በጾም ዘመልክዕኪ ጊዜ ድክታሜ፣ እምተመነይኩ ተሳትፎ ከመ አኅትኪ ሰሎሜ፣ ወፍሥሓኪ ዘአልቦ ፍጻሜ”፡፡ ሲተረጎምም የሮማን ሽቱ የቀናንሞ አበባ የምትሆኚ ማርያም ሆይ፣ በርሃብ በጾም አበባ የመሰለ የመልክሽ ደም ግባት እስኪጠወልግ ድረስ በስደትና በልቅሶ የደረሰብሽን ችግርና ድካም መከራሽንም ሁሉ እንደ እኅትሽ እንደ ሰሎሜ አብሬሽ ብቀበል ምኞቴ ነበር፤ በዚህ ፍጻሜ የሌለውን ደስታሽን እሳተፍ ነበር፡፡ እንዲሁም አባ አርክ ሥሉስ በስደቷ የደረሰባትን ኀዘን ፣ ልቅሶና ሰቆቃ አስመልክተው በደረሱት ‘ሰቆቃወ ድንግል” በሚለው ድርሰታቸው እንዲህ አሉ፣ ፀሐይን የምትለብሽ የብርሃን ልጅ ቅድስት ድንግል ማርያም ከክፉ ከሄሮድስ ዘንድ ልጅሽን ባሸሸሽ ጊዜ የደረሰብሽን ችግሮች ጨረቃን የሚጫሙ እግሮችሽ በመንገድ ብዛትና በአሸዋ ግለት እንደ ጎበጎቡ ሲሰማ ሰው ይቅርና ድንጋዩም ባለቀሰ ነበር”

አባ ጽጌ ድንግል ማኅሌተ ጽጌ/ የተባለውን ድርሰት ደርሰዋል፡፡ የተወለደውም በሰሜን ሸዋ በይፋት አውራጃ ውስጥ ሲሆን መጀመሪያ ኢአማኒ (ያለመነና ያልተጠመቀ) ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ይህ ሰው በወጣትነት እድሜው አውሬ ለማደን ወደ ጫካ ሄደ በጫካ ውስጥም ፊቷ በጽጌረዳ አበባ የተከበበና ያጌጠ እጅግም ደስ የምታሰኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል አይቶ በሥዕሏ ውበት እየተደነቀ ሳለ ጓደኛው መጥቶ ምን እየፈለክ ነው ይህ እኮ የክርስቲያኖች ሥዕል ነው በማለት በያዘው በትር ሥዕሏን ሲመታት ወዲያው ተቀስፎ ሞተ፡፡ ከዚህ በኋላ ክንፎቹ በጽጌረዳ አበባ ያጌጡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል በነጭ ወፍ ተመስሎ ወደ እርሱ መጥቶ አንድ ቀይ መነኩሴ እስከሚመጣ ድረስ ይህችን ሥዕል ጠብቃት ብሎ ተሰወረ፡፡

ኢትዮጵያዊው ጻድቅ መነኩሴ አቡነ ዜና ማርቆስ በይፋት አውራጃ በነቢዩ ኢሳይያስ ትንቢት ምዕ11፡1 ትውፅእ በትር እምሥርወ እሴይ ወየዐርግ ጽጌ እምኔሃ የሚለውን በግእዝ ቋንቋ ሲያነብ በሰማ ጊዜ አባቶቼ አይሁድ የነቢያት ትንቢት ንባቡን አስተምረውኛል አውቀዋለሁ ትርጉሙ ግን አላውቀውምና ተርጉምልኝ አለው፡፡
አቡነ ዜና ማርቆስም ሲተረጉምለት እንዲህ አለ ትወፅእ በትር እምሥርወ እሴይ የሚለው ንባብ ከእሴይ ነገድ የሕይወት በትር የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትወለዳለች ማለት ነው፡፡ ወይወርድ ጽጌ እምኔሃ የሚለው ንባብ ደግሞ እመቤታችን ተወልዳ ከእርሷም ጌታ በድንግልና ይወለዳል፡፡ ከጌታም ክብር ይገኛል ማለት ነው፡፡ ይህም ጌታ ተወልዶ ትንቢቱ በእውነት ተፈጽሟል ብሎ ተረጎመለት፡፡ ትኢሳ7፡14 ማቴ18፡24

ይህ ሰው በዚህ ትርጉም ደስ ተሰኝቶ አባት የኢሳይያስን ትንቢት በመልካም ሁኔታ ተረጎምከው መልካም ነገር ተናገርክ አለውና ሥዕሏ ወዳለችበት ቦታ ወስዶ ታሪኩ ላይ እንደተገለጸው በጫካ ውስጥ ያያትን ሥዕል ጓደኛው በያዘው በትር ሲመታት ወዲያው እንደተቀሰፈና ክንፎቹ በጽጌረዳ አበባ የጌጡ አንድ ነጭ ወፍ የሆኑ (ቅዱስ ሩፋኤል) ወደ እርሱ መጥቶ ቀይ መነኩሴ እስከሚመጣ ድረስ ይህችን ሥዕል ጠብቃት ብሎ በሰው አነጋገር ያነጋገረውን ሁሉ ነገረው፡፡ አቡነ ዜና ማርቆስ የተደረገውን ሰምቶ እጅግ ደስ አለውና በል በመጀመሪያ እመቤታችን በድንግልና በወለደችው በአብ የባሕርይ ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን ይህችን ሥዕል ያስገኘው ሰማይና ምድር በውስጣቸው ያለውን ሁሉ የፈጠረ እርሱ እንደሆነ እወቅ አለውና በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቆ ጽጌ ብርሃን /ጽጌ ድንግል/ ብሎ ሰየመው፡፡

ማኅሌተ ጽጌ ማለት ማኅሌት የሚለው ቃል የግዕዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙም ምስጋና ማለት ነው፡፡ ጽጌ ማለት እንደሱ የግዕዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙ አበባ የፍሬ ምልክት ማለት ነው፡፡ ማኅሌት ጽጌ ተብሎ በአንድነት ሲነገር ሲተረጎም ደግሞ የአበባ ምስጋና ማለት ነው፡፡ ይህም ድንግል ማርያም የማኅጸኗ ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስ በጎ መዓዛ ባላቸው አበባዎችና ፍሬዎች እየተመሰሉ የሚመሰገኑበት ምስጋና ማለት ነው፡፡ ማኅሌተ ጽጌን በግጥም /ቅኔ/ ስንኝ በ5 በ5 የተደረሰ ድንቅ ኢትዮጵያዊ ድርሰት ነው፡፡

የእመቤታችን የስደቷ መታሰቢያ ወር በቤተ ክርስቲያናችን የሚከበረው በማኅሌት፣ በቅዳሴና በዝክር ነው፡፡ በወርኃ ጽጌ ባሉት ሳምንታት ከቅዳሜ ማታ እስከ እሑድ ጠዋት አበው ካህናት የሚያቀርቡት ዝማሬ ከቅዱስ ያሬድ ድጓ፣ ከማኅሌት ጽጌና ከሰቆቃው ድንግል የተውጣጣና ሦስት ወገን ያለው ነው፡፡ ዝክሩም፣ በአሁኑ ወቅት በከተሞች አካባቢ እየተረሳ ቢመጣም፣ ዘወትር እሑድ የአንድ አካባቢ ሰዎች ማዕከላዊ በሆነ ቦታ ተሰባስበው በእመቤታችን ስም የሚዘክሩት ነው፡፡ ዐቅመ ደካሞች፣ ድሆችና መንገደኞች ተጠርተው በእመቤታችን ስም እንዲበሉና እንዲጠጡ ይደረጋል፡፡ ይህም ትውፊት እመቤታችን ወደ ኢትዮጵያ በመጣች ጊዜ ኢትዮጵያውያን አባቶችና እናቶች ያደረጉላትን መስተንግዶ ለማሰብ ነው፡፡
በሃገራችን የመስከረምና የጥቅምት ወራት የአበባ ወራት /ዘመነ ጽጌ/ ይባላል፡፡ ይህም ወቅት ተራሮችና ሜዳዎች በአበባ የሚያጌጡበትና ለዓይን ማራኪ የሚሆኑበት ጊዜ ነው፡፡

በዚህ ዘመን ጌታችን ፈጣሪአችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለልብስ ለምን ትጨነቃላችሁ የሜዳ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፡፡ አይደክሙም አይፈትሉም ነገር ግን እላችኋለሁ ሰሎሞን እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም ብሎ በአበባ ምሳሌነት የሰው ልጆች ስለ ልብስ እንዳይጨነቁ አስተምሯል፡፡ ማቴ5፡28-33

ንጉሥ ዳዊትም ተዘከር እግዚኦ ከመ መሬት ንሕነ ወሰብእሰአ ከመ ሣዕር ወዋዕሊሁ ወከመጽጌ ገዳም ከማሁ ይፈሪ አቤቱ እኛ አፈር እንደሆነ አስብ ሰውስ ዘመኑ እንደ ሣር ነው እንደ ዱር አበባም እንዲሁም ያብባል ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ያልፋል /መዥ102፡1416/ በማለት እንደተናገረው ሣር በቅሎ አድጎ አብቦ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ይደርቅና በሞት ነፋስ ይወሰዳል፡፡

አባ ጽጌ ድንግል የደረሰው ማኅሌተ ጽጌም ምሥጢሩ ከእነዚሁ የቅዱሳት መጻሕፍት መልእክታት ጋር ተቀራራቢ ነው፡፡ የማኅሌተ ጽጌ ብዛቱ 150 ነው፡፡ ጽጌ አስተርአየ ሠረጸ አምአጽአሙ አበባ ከአጥንቱ ወጥቶ ታየ ብሎ ይጀምራል፡፡ አጥንት ያለው እንጨቱን ነው፡፡ ዕፅ እመቤታችን አበባው ልጅዋ ኢየሱስ ነው በማኅሌተ ጽጌ አበባ ጌታ ሲሆን እመቤታችን ዕፅ ትባላለች ፍሬ ጌታ ሲሆን እመቤታችን አበባ ትባላለች፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ከእመቤታችን ረድኤት በረከት ያሳትፈን

ነሐሴ 16 ፍልሰታ ለማርያም

ማርያም ስጋኪ ዘተመሰለ ባሕርየ ተሓፍረ ሞት አኮኑ ሶበ ነጸረ ወርእየ
እንዘ በደመና ብሩህ የዐርግ ሰማየ::
ፍልሰታ የሚለው ቃል የሚገልጸው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለቆ መሔድን መሰደድን መፍለስን ያመለክታል። ይህም የእመቤታችንን ሥጋ ከጌቴሴማኒ ወደ ገነት መፍለሱን በኋላም በገነት በዕፀ ሕይወት ስር ከነበረበት መነሳቱን ለማመልከት ይነገራል።
ጾመ ፍልሰታ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም 64 ዓመት በዚች ምድር ኖራ እንደ አንድ ልጇ መሞቷን መነሳቷንና ማዕረጓን ያዩ ዘንድ ሐዋርያት የጾሙት ጾም ነው። ጾሙ ከነሐሴ 1 ቀን እስከ ነሐሴ 16 ቀን ሲጾም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዋጅ ከደነገገቻቸው ሰባቱ አጽዋማትም አንዱ ነው።
እመቤታችን ከአባቷ ከኢያቄም እና ከእናቷ ከሐና ነሐሴ 7 ቀን ተጸንሳ ግንቦት 1 ቀን በሊባኖስ ተወልዳለች። እምቤታችን በእናት አባቷ ቤት ሦስት/፫/ ዓመት፤ በቤተ መቅደስ አሥራ ሁለት/12/ ዓመት፤ ከልጇ ከወዳጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር/33 ከ3 ወር/ ፡ ከዮሐንስ ወልደ ዘብዴዎስ ዘንድ አሥራ አራት ዓመት ከዘጠኝ ወር/14 ከ9 ወር/ ቆይታ በ 64 ዓመት ዕድሜዋ በ49 ዓ/ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች። የእመቤታችንን ስም የሚገልጹ የውዳሴ ጽሑፎችም በእድሜዋ ልክ ተደርሰዋል። ለምሳሌ የውዳሴ ማርያም ቁጥር 64 ነው፤ የመልክአ ማርያም ቁጥርም 64 ነው።
ባረፈች ጊዜ ቅዱሳን ሐዋርያት ተሰባስበው አስከሬኗን ይዘው ወደ ጌቴሴማኒ መቃብር ለማሳረፍ ሲሄዱ አይሁድ ለተንኮል አያርፉምና ተተናኮሏቸው። ቀድሞ ልጇ ሞቶ ተነሳ፣ አረገ እያሉ ሲያስቸግሩን ይኖራሉ: ደግሞ አሁን እሷም ተነሳች፣ አረገች ሊሉ አይደል በማለት አይሁድ ተሰባስበው አስከሬኗን ለማቃጠል ሲተናኮሉ እግዚአብሔር በተአምር ከነዚያ አይሁዶች አድኗቸዋል ። ከሁሉ አንዱ ታውፋኒያ የተባለው ተራምዶ አጎበሩን ጨበጠው የታዘዘ መልአክ ሁለት እጁን በሰይፍ ቀጣው። ከአጎበሩ ተንጠልጥሎ ቀረ። በድያለው ማሪኝ ብሎ ቢማጸናት ራሷን ዘንበል አድርጋ ጴጥሮስን እንደነበረ አድርግለት አለችው። ቢመልሰው ድኖ ተነስቷል። ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር የእመቤታችንንም አስከሬን ነጥቆ ከሐዋርያው ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር በገነት በዕፀ ህይወት ስር አኑሯቸዋል ። ከዚያ በኋላ ሐዋርያት ሥጋዋን አግኝተው ይቀብሩት ዘንድ በአረፈች በስምንተኛው ወር ከነሐሴ 1 ጀምሮ እስከ ነሐሴ 14 ቀን ድረስ ሁለት ሱባዔ ይዘው በአሥራ አራተኛው ቀን ሥጋዋን ከጌታ ተቀብለው በጸሎትና በምህላ በፍጹም ደስታ በጌቴሰማኔ አሳረፉት ። በሦስተኛውም ቀን ተነስታ ስታርግ ከሰዱቃውያን ወገን የሆነው ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ አያት። እርሱም በቀብር ስርዓቱ ጊዜም አልነበረም። ሀገረ ስብከቱ ህንድ ስለነበር ሊያስተምር ወደዛው ሂዶ ነበርና። በዚያም ሲያስተምር ሰንብቶ በደመና ተጭኖ ሲመጣ ያገኛታል። ትንሳኤዋን ከርሱ ሰውራ ያደረገች መስሎት አዝኖ «ቀድሞ የልጅሽን ትንሳኤ ሳላይ ቀረሁ አሁን ደግሞ ያንቺን ትንሳኤ ሳላይ ቀርቼ ነውን ?» ብሎ ቢያዝንባት እመቤታችንም ከርሱ በቀር ማንንም ትንሳኤዋን እንዳላየ ነግራ አጽናናችው። ለሌሎቹ ሐዋርያትም እንዲነግራቸው ለምልክትም /ለምስክርም እንዲሆነው ሰበኗን /መግነዟን ሰጥታው አረገች። ቶማስም ኢየሩሳሌም ደርሶ ሐዋርያትን «የእመቤታችን ነገርስ እንደምን ሆነ?» ሲል ቢጠይቅ «አግኝተን ቀበርናት እኮ» አሉት። እርሱ ምስጢሩን አዉቆ ደብቆ «ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር» እንዴት ይሆናል ? አይደረግም ይላቸዋል። ሊያሳያቸውም መቃብሩ ዘንድ ሂደው ቢከፍቱት አጧት። እርሱም «አታምኑኝም ብዬ እንጂ እርሷስ ተነስታ አርጋልች»በማለት ሁኔታውን ተረከላቸውና ለምስክር ይሁንህ ብላ የሰጠችውን ሰበኗን አሳያቸው። ከዚህ በኋላ ለበረከት ይሆናቸው ዘንድ ሰበኑን ተካፍለው ወደየአህገረ ስብከታቸው ሄዱ። ዛሬ በቅዳሴ ጊዜ ዲያቆኑ በሚይዘው የመጾር መስቀል ላይ በሁለት ቀዳዳዎች አልፎ ተጠምጥሞ የምናየው መቀነት መሰል ጨርቅ የዚያ ሰበን ምሳሌ ነው።
በዓመቱ ሐዋርያት ከያሉበት ተሰባስበው ቶማስ ትንሣኤሽን አይቶ እኛስ እንዴት ይቀርብናል ብለው ከነሐሴ 1 ቀን ጀምርው ሱባዔ ቢይዙ ከሁለት ሱባዔ በኋላ እንደገና ትንሳኤዋንና እርገቷን ለማየት በቅተዋል። ሐዋርያዊት የሆነች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናም ምእመኖቿ ከእመቤታችን በረከትን እንዲያገኙ ይጾሙ ዘንድ ይህን ሐዋርያት የጾሙትን ጾም እንዲጾሙ አውጃለች። ምእመናንም በተለየ መልኩ በጾም በጸሎት በሱባዔ ሆነው ይህን ወቅት ያሳልፋሉ።
የእመቤታችን ትንሣኤ ድንገት እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውሀ ፈሳሽ የተደረገ ሳይሆን በቅዱሳት መጻሕፍት በትንቢተ ነቢያት የተገለጸ ነው። ነቢዩ ዳዊት በመዝሙር 131፡1 ላይ «አቤቱ ወደ እረፍትህ ተነስ አንተና የመቅደስህ ታቦ» ይላል። በዚህም ምዕመናንን ወደ ምታሳርፍበት ወደ መንግሥተ ሰማያት የመቅደስህ ታቦት ድንግል ማርያምን ይዘህ ተነስ አለ። ታቦት የጽላት ማደርያ እንደሆነ ሁሉ እምቤታችንም ለክርስቶስ ማደርያ በመሆኗ አማናዊት ታቦት ትባላለች።
ንጉስ ሰሎሞንም መኃ 2፡10 ላይ «ውዴ እንዲህ ብሎ ተናገረኝ፤ ወዳጄ ሆይ ተነሽ፡ ውበቴ ሆይ ነይ» ብሏል። እዚህ ላይ«ወዳጄ …ዉበቴ» የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት ። ክቡር ዳዊት መዝሙር 44፡9 ላይ «በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች» እንደሚል ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለም ቤዛነቱን ከፈጸመ በኋላ ወደ ቀደመ ክብሩ እንዳረገ እመቤታችን ቅድስት ድንገል ማርያምም በቀኙ ትቀመጥ ዘንድ «ተነሽ ነይ» አላት ። እንግዲህ ይህንና የመሰለዉን ሁሉ ይዘን የእናታችንን እረፍቷን ትንሣኤዋን በጾም በጸሎት እንዘክራለን እንመሰክራለንም።
የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤቷ፣ በረከቷ፣ አማላጅነቷ አይለየን፡ አሜን።

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top