ውዳሴ ማርያም

ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም የደረሰው ሰኞ የሚጸለይ አምላክን የወለደች የድንግል ማርያም ምስጋና መጀመሪያ ክፍል

፩. ጌታ ልቡ ያዘነና የተከዘ አዳምን ነፃ ያወጣውና ወደ ቀድሞ ቦታው ይመልሰው ዘንድ ወደደ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፪. ከድንግል ያለወንድ ዘር በሥጋ ተወለደና አዳነን ከይሲ (ዲያብሎስ) ያሳታት ሔዋንን እግዚአብሔር ምጥሽንና ጻዕርሽን አበዛዋለሁ ብሎ ፈረደባት ሰውን ወደደና ነፃ አደረጋት። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፫. ሰው የሆነና በእኛ ያደረ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ክብሩንም ለአባቱ አንድ እንደመሆኑ ክብር አየን። ይቅር ይለን ዘንድ ወደደ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፬. ነቢዩ ኢሳይያስ በመንፈስ ቅዱስ የአማኑኤልን ምስጢር አየ ስለዚህም ሕጻን ተወለደልን ወልድም ተሰጠልን ብሎ አሰምቶ ተናገረ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፭. ሰው ሆይ ፈጽመህ ደስ ይበልህ፤ እግዚአብሔር ዓለሙን ወዶታልና አንድ ልጁንም የሚያምንበት ሁሉ እስከ ዘለዓለም ፈጽሞ ይድን ዘንድ አሳልፎ ሰጥቷልና ልዑል ክንዱን ሰደደልን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፮. የነበረው የሚኖረው የመጣው ዳግመኛም የሚመጣው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ያለመለወጥ ፍጹም ሰው ሆነ። አንዱ ወልድ በሥራው ሁሉ አልተለየም የእግዚአብሔር ቃል መለኮት አንድ ነው እንጂ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፯. የነቢያት ሀገራቸው ቤተልሔም ሆይ ደስ ይበልሽ ሁለተኛው አዳም ክርስቶስ በአንቺ ዘንድ ተወልዷልና የቀድሞውን ሰው አዳምን ከምድር (ከሲኦል) ወደ ገነት ይመልሰው ዘንድ አዳም ሆይ መሬት ነበርክና ወደ መሬት ትመለሳለህ ብሎ የፈረደበትንም የሞት ፍርድ ያጠፋለት ዘንድ። ብዙ ኃጢአት ባለችበት የእግዚአብሔር ጸጋ ትበዛለች። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፰. የሰው ሁሉ ሰውነት ደስ ይላታል። በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በምድርም ሰላም ለሰውም እርሱ በሚፈቅደው እያሉ አሰምተው ንጉሥ ክርስቶስን ከመላእክት ጋር ያመሰግኑታል። የቀድሞውን እርግማን አጥፍቷልና የጠላትን ምክሩን አፈረሰበት። ለአዳምና ለሔዋን የእዳ ደብዳቤያቸውን ቀደደላቸው፤ በዳዊት ሀገር መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምንና ሔዋንን ነጻ አደረጋቸው። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፱. በዚህ ዓለም ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ የምታበራ እውነተኛ ብርሃን ስለ ሰው ፍቅር ወደ ዓለም የመጣህ ፍጥረት ሁሉ በመምጣትህ ደስ አለው አዳምን ከስህተት አድነኸዋልና ሔዋንንም ከሞት ጻዕረኝነት ነጻ አድርገኻታልና የምንወለድበትን መንፈስ (ረቂቁን ልደት) ሰጠኸን ከመላእክት ጋርም አመሰገንህ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

ማክሰኞ የሚጸለይ አምላክን የወለደች የእመቤታችን ድንግል ማርያም ምስጋና ፪ኛ ክፍል

፩. የመመኪያችን ዘውድ የደኅንነታችን መጀመሪያ የንጽሕናችንም መሠረት እኛን ስለማዳን ሰው የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል በወለደችልን በድንግል ማርያም ተገኘልን። ሰው ከሆነ በኋላም ፍጹም አምላክ ነው ስለዚህም በድንግልና ወለደችው ድንቅ የሆነ የመውለድዋ ችሎታ የማይመረመር (ሊነገር የማይቻል) ነው። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፪. በእርሱ ፈቃድ በአባቱ ፈቃድ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ መጥቶ አዳነን በድንግልና ፍጽምት የሆንሽ ማርያም ሆይ የድንግልናሽ ምስጋናና ክብር ታላቅ ነው። እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ቢሆን ባለሟልነትን አግኝተሻልና። ያዕቆብ ከምድር እስከ ሰማይ ደርሳ የእግዚአብሔር መላእክት ሲወጡባትና ሲወርዱባት ያያት መሰላል አንቺ ነሽ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፫. ሙሴ በነደ እሳት ሳትቃጠል ያያት ዕፅ አንቺ ነሽ ይኽውም መጥቶ በማሕጸንሽ ያደረው የእግዚአብሔር ልጅ ነው የመለኮቱ እሳትነት ሥጋሽን  አላቃጠለውም። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፬. ዘር ያልተዘራባት እርሻ አንቺ ነሽ የሕይወት ፍሬ ከአንቺ ወጣ ዮሴፍ የዋጃትና የከበረ ዕንቁን ያገኘባት ሣጥን አንቺ ነሽ ይኸውም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በማሕፀንሽ አደረ በዚህ ዓለምም ወለድሽው። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፭. የመላእክት ደስታቸው የሆነ ጌታን የወለድሽ ሆይ ደስ ይበልሽ የነቢያት ዜናቸው ንጽሕት ሆይ ደስ ይበልሽ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ቢሆን ባለሟልነትን አግኝተሻልና ደስ ይበልሽ የዓለም (የሰው) ሁሉ ደስታ የሆነ የመልአኩን ቃል ተቀብለሻልና ደስ ይበልሽ ዓለምን ሁሉ የፈጠረ ጌታን የወለድሽ ሆይ ደስ ይበልሽ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፮. በሚገባ የአምላክ እናት ተብለሻልና ደስ ይበልሽ የሔዋን መድኃኒትዋ ሆይ ደስ ይበልሽ ፍጥረቱን ሁሉ የሚመግበውን እሱን ጡትሽን አጥብተሽዋልና ደስ ይበልሽ የሕያዋን (የጻድቃን) ሁሉ እናታቸው ቅድስት ሆይ ደስ ይበልሽ ትለምኝልን ዘንድ ወደ አንቺ እናንጋጥጣለን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፯. ድንግል ሆይ ቅድስት ሆይ ጌታን የወለድሽ ሆይ እኛን ለማዳን ድንቅ ምሥጢር (ተዋሕዶ) በአንቺ ቢደረግ ንጉሥን ወልደሽልናልና ፍጥረታትን በልዩ ልዩ መልክ የፈጠረ የእርሱን የገናንነቱን ነገር ፈጽመን መናገር አይቻለንምና ዝም እንበል። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፰. ወደ ደብረ ሲና የወረደ ለሙሴ ሕግን የሰጠ የተራራውን ራስ በጽጋግ በጢስ በጨለማና በነፋስ የሸፈነ ፈርተው የቆሙትንም በነጋሪቶች ድምጽ የገሰጸ የአብ አካላዊ ቃል ነው። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፱. በትሕትና የተናገርሽ ተራራ ሆይ ይኸውም ወደ አንቺ የወረደው ነው ሰውን የወደደ እርሱ ያለመለወጥ በአንቺ ሰው ሆነ እንደ እኛ በሚናገር ሥጋ ፍጹም ሆኖ አምላክ በመንፈስ ቅዱስ በማሕፀንዋ አደረና ፍጹም ሰው ሆነ አዳምን ያድነው ዘንድ ኃጢአቱንም ያስተሠርይለት ዘንድ በሰማያት (በሰማያዊ መዓርግ) ያኖረው ዘንድ በቸርነቱና በይቅርታው ብዛት ወደ ቀድሞ ቦታው ይመልሰው ዘንድ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፲. የድንግል ገናንነቷ ሊናገሩት አይቻልም ጌታ መርጧታልና የሚቀርበው በሌለ ብርሃን ውስጥ የሚኖር እርሱ መጥቶ አደረባት። ዘጠኝ ወር በማኅፀንዋ አደረ። የማይታይና የማይመረመር (ታይቶ የማይታወቅ)እርሱን በድንግልና ወለደችው። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፲፩. ነቢዩ ዳንኤል ያየው ያለ እጅ ከረጅም ተራራ የተፈ ነቀለው ያ ደንጊያ ከአብ ዘንድ የወጣው ቃል ነውና መጥቶ ያለወንድ ዘር ከድንግል ተወልዶ አዳነን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፲፪. እንደ ንጹሕ ጫፍ ሆንሽ የሃይማኖትም መገኛ ነሽ የቀናች የቅዱሳን አባቶቻችን ሃይማኖታቸው ነሽ አምላክን የወለድሽና በድንግልና የታተምሽ ንጽሕት ሆይ የአብን ቃል ወለድሽልን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን መጣ።ቅድስት ሆይ ለምኝልን 

፲፫. የከበርሽ ጌታን የወለድሽ ሆይ የማይታይ ቃልን የተሸከምሽው የብርሃን እናቱ አንቺ ነሽ እሱን ከወለድሽው በኋላ በድንግልና ኖረሻልና በፍጹም ምስጋና ያገኑሻል። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፲፬. የአብ ቃል እናቱ ንጽሕት ድንግል ሆይ ስለአንቺ የሚነገረውን ነገር መናገር የሚቻለው ምን አንደበት ነው? ኪሩቤል ለሚሸከሙት ንጉሥ ዙፋኑ (ማደሪያው) ሆንሽ የተከበርሽ ሆይ እናመሰግንሻለን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ መልካሟ ርግብ ሆይ ስምሽን በልጅ ልጅ እንጠራለን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፲፭. እናትና ገረድ ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ። የታቀፍሽውን መላእክት ያመሰግኑታልና ኪሩቤልም በፍርሃት ይሰግዱለታልና ሱራፌልም ያለማቋረጥ ክንፋቸውን ዘርግተው የሚመሰገን ንጉሥ (የክብር ባለቤት) ይህ ነው በይቅርታው ብዛት የዓለምን ኃጢአት ያስተሠርይ ዘንድ የመጣው ይህ ነው ይላሉ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

ረቡዕ የሚጸለይ አምላክን የወለደች የእመቤታችን ድንግል ማርያም ምስጋና ፫ኛ ክፍል

፩. የምድር ሁለተኛ የሆንሽ ሰማይ ሆይ፤የሰማያት ሠራዊት (መላእክት) ንዕድ ነሽ ይላሉ፤ድንግል ማርያም የምሥራቅ ደጅ ናት። ሙሽራዋ ንጹሕ የሆነ ንጽሕት የሠርግ ቤት ናት። አብ በሰማይ አይቶ እንደ አንች ያለ አላገኘምና አንድ ልጁን ላከው በአንችም ሰው ሆነ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፪. አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ ትውልድ ሁሉ አንችን ብቻ ያመሰግኑሻል። የእግዚአብሔር ሀገር (ከተማ) ሆይ ነቢያት ድንቅ ድንቅ ነገርን ተናገሩልሽ፤ደስ የተሰኙ የጻድቃን ማደሪያ ሆነሻልና የምድር ነገሥታት ሁሉ በብርሃንሽ ይሄዳሉ፤ሕዝቡም ሠራዊቶቻቸውም በብርሃንሽ ይሄዳሉ፤ማርያም ሆይ ትውልድ ሁሉ ያመሰግኑሻል። ካንቺ ለተወለደውም ይሰግዱለታል ያገኑታልም። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፫. የዝናም ውሃ የታየብሽ የዕውነት ደመና አንች ነሽ። አብ የልጁ ምልክት አደረገሽ፤መንፈስ ቅዱስ አደረብሽ፤ የልዑል ኃይል ጋረደሽ ማርያም ሆይ ለዘላለም የሚኖር የአብን ልጅ ቃልን የወለድሽልን መጥቶም ከኃጢአት አዳነን። ደስ የተሰኘህ ሆነህ ምሥራችን የተናገርክ መልአኩ ገብርኤል ሆይ የተሰጠህ ክብር ታላቅ ነው፤ወደኛ የመጣ የጌታን ልደት ነገርኸን ለድንግል ማርያም ጸጋን የተመላሽ ሆይ እግዚአብሔር ካንች ጋር ነውና ደስ ይበልሽ ብለህ  አበሠርካት። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፬. ጸጋን አገኘሽ መንፈስ ቅዱስ አደረብሽ የልዑል ኃይልም ጋረደሽ (ጸለለብሽ) ማርያም ሆይ በእውነት ቅዱሱን ወለድሽ ዓለምን ሁሉ የሚያድን መጥቶ አዳነን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፭. አንደበታችን የድንግልን ሥራ ያመሰግናል። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዳዊት አገር ከእርሷ ስለተወለደ አምላክን የወለደች ማርያምን ዛሬ እናመስግናት። አሕዛብ ኑ ማርያምን እናመስግናት፤ እናትና ድንግልን ሁለቱንም ሆናለችና። ርኵሰት የሌለብሽ የአብ ቃል መጥቶ ካንች ሰው የሆነ ንጽሕት ድንግል ሆይ ደስ ይበ ልሽ፤ ነውር የሌለብሽ ፍጽምትና ጉድፍ የሌለብሽ ሙዳይ ሆይ ደስ ይበልሽ፤ስለቀደመ ሰው አዳም ሁለተኛ አዳም የሆነ የክርስቶስ ማደሪያው የምትናገሪው ገነት ሆይ ደስ ይበልሽ፤ከአባቱ ያልተለየ አንድ እሱን የተሸከምሽ ሆይ ደስ ይበልሽ፤ በክብር ጌጽ ሁሉ ያጌጠ እርሱ መጥቶ ሰው የሆነብሽ ንጽሕት የሠርግ ቤት ሆይ ደስ ይበልሽ የመለኮት እሳት (ባሕርይ) ያላቃጠለሽ ዕፀጳጦስ ሆይ ደስ ይበልሽ፤ በኪሩቤል ላይ የሚቀመጠውን ሰማያዊ መለኮትን በሥጋ የተሸከምሽ ገረድና እናት፤ድንግልና ሰማይ ሆይ ደስ ይበ ልሽ። ስለዚህ ንጹሐን ከሆኑ መላእክት ጋር በፍጹም ደስታ ደስ ተሰኝተን እናመስግን በሰማይም ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በምድርም ዕርቅ ይሁን እንበል ክብርና ምስጋና ጌትነት ያለው እርሱ አንችን ወድዋልና። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፮. ከቅዱሳን ክብር የማርያም ክብር ይበልጣል፤ የአብን ቃል ለመቀበል በተገባ ተገኝታለችና። መላእክት የሚፈሩትን ትጉሆች በሰማያት የሚያመሰግኑትን ድንግል ማርያም በማሕፀንዋ ተሸከመችው። ይህች ከኪሩቤል ትበልጣለች፤ ከሱራፌልም ትበልጣለች ከሦስቱ አካል ለአንዱ ማደሪያ ሆናለችና። የነቢያት ሀገራቸው ኢየሩሳሌም ይህች ናት። ለቅዱሳን ሁሉ የደስታቸው ማደሪያ ናት። በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ታላቅ ብርሃን  ወጣላቸው በቅዱሳን ላይ የሚያድር እግዚአብሔር እኛን ለማዳን ልዩ ከሆነች ድንግል ሰው ሁኗልና። ኑ ይህን ድንቅ እዩ። ስለተገለጠልን ምሥጢር ምስጋና አቅርቡ ሰው የማይሆን ሰው ሆኗልና፤ቃል ተዋሕድዋልና ጥንት የሌለው ሥጋ ጥንታዊ ቀዳማዊ ሆነ፤ዘመን የማይቆጠርለት መለኮት ዘመን ተቆጠረለት። የማይታወቅ ተገለጠ፤ የማይታይ ታየ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ በርግጥ ሰው ሆነ። ትላንት የነበረው ዛሬም ያለው መቼም የሚኖረው ኢየሱስ ክርስቶስ እንሰግድለትና እናመስግነው ዘንድ አንድ ባሕርይ ነው። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፯. ነቢዩ ሕዝቅኤል ስለ እርስዋ መሰከረ ድንቅ በሆነ ታላቅ ቍልፍ የተዘጋች ደጅ ከምሥራቅ አየሁ አለ ከኃያላን ጌታ በቀር ወደ እርሷ ገብቶ የወጣ የለም። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፰. ኆኅትም (ደጅም) መድኃኒታችንን የወለደች ድንግል ናት። እርሱን ከወለደች በኋላ እንደ ቀድሞው በድንግልና ኖራለችና። መጥቶ ምሕረት ከሌለው ጠላት እጅ ያዳነን ጌታን የወለድሽ ሆይ የማሕፀንሽ ፍሬ የተባረከ ነው፤ አንቺ ፍጽምትና የተባረክሽ ነሽ፤የእውነት አምላክ በሆነ በክብር ባለቤት ዘንድ  ባለሟልነትን አግኝተሻልና በምድር ላይ ከሚኖሩ ሁሉ ይልቅ ገናንነትና ክብር ላንቺ ይገባል። የአብ ቃል መጥቶ በአንቺ ሰው ሆነ። ከሰው ጋርም  ተመላለሰ። መሓሪ ይቅር ባይ ሰውን ወዳጅ ነውና በልዩ አመጣጡ አዳነን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

ኀሙስ የሚጸለይ አምላክን የወለደች የእመቤታችን ድንግል ማርያም ምስጋና ፬ኛ ክፍል

፩. ርኵሰት የሌለባት ድንግል ማርያም ሙሴ በበረሃ በነደ እሳት ጫፎቿ ሳይቃጠሉ ያያት ዕፅን ትመስላለች የአብ ቃል በርሷ ሰው ሆኗልና እሳት መለኮቱ (የመለኮቱ እሳት) አላቃጠላትምና። ከወለደችውም በኋላ ድንግልናዋ አልተለወጠምና ሰውም ቢሆን መለኮቱ አልተለወጠም በዕውነት አምላክ ነውና በዕውነት አምላክ የሆነ እርሱ መጥቶ አዳነን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፪. አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ ሁላችን እናገንሻለን። ይቅርታሽ ለሁላችን ይሆን ዘንድ ነውና። ሔዋን እንጨት በልታ ባደረገችው ዓመፅ በባሕርያችን ያደረ የቀድሞው እርግማን በርሷ የጠፋልን አምላክን የወለደች ድንግል ማርያም የሁላችን መመኪያ ናት። ስለ ሔዋን የገነት ደጅ ተዘጋ ዳግመኛም ስለ ድንግል ማርያም ተከፈተልን። ከዕፀ ሕይወት እንበላ ዘንድ አደለን። ይኸውም እኛን ስለመውደድ መጥቶ ያዳነን የክርስቶስ ክቡር ሥጋው ክቡር ደሙ ነው። ስለ እርሷ ድንቅ ሆኖ የሚነገረውን ይህን ምሥጢር ማወቅ የሚቻለው ምን ልቡና ነው? መናገር የሚቻለው ምን አንደበት  ነው? መስማት የሚቻለው ምን ጆሮ ነው? ሰውን የሚወድ እግዚአብሔር አንድ ብቻ የሆነ አምላክነቱ ሳይለወጥ ከዓለም በፊት የነበረ የአብ ቃል ከአብ ዘንድ መጥቶ ልዩ ከሆነች እናቱ ሰው ሆነ። ከወለደችው በኋላም ድንግልናዋ አልተለወጠም ስለዚህም አምላክን የወለደች እንደሆነች ታወቀች። እግዚአብሔር የጥበቡ ስፋት ምን ይጠልቅ? በጻእር በምጥ በልብ ጋር ትወልድ ዘንድ የፈረደባት ማኅፀን የሕይወት መገኛ ሆነች ከባሕርያችን እርግማንን የሚያጠፋልንን ያለ ወንድ ዘር ወለደችልን ስለዚህም ሰውን የምትወድ ሆይ ክብር ለአንተ ይገባል ቸርና የሰውነታችን መድኃኒትም ነህ እያልን እናመስግነው። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፫. ያለ ወንድ ዘር አምላክን የወለደች ድንግል የማኅፀንዋ ሥራ ምን የደንቅ? ለዮሴፍ የታየው መልአኩ ከርስዋ በመንፈስ ቅዱስ የሚወለደው ያለመለወጥ ሰው የሚሆነው የእግዚአብሔር ቃል ነው ብሎ መስክሯልና። ማርያም የዚህ ደስታ ዕፅፍ የሆነ እርሱን ወለደችው። መልአኩ ልጅ ትወልጃለሽ ስሙም ዐማኑኤል ይባላል አላት። ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ ማለት ነው። ዳግመኛ ወገኖቹን ከኃጢአታቸው የሚያድናቸው ኢየሱስ ይባላል። በችሎታው (በኃይሉ) ያድነን ዘንድ ኀጢአታችንንም ያስተሠርይልን ዘንድ ለዘላለም ክብር ይግባውና ሰው የሆነ እርሱን አምላክ እንደሆነ በተረዳ ነገር አውቀነዋልና። ልዩ ከሆነች ድንግል ማርያም ይህ የአምላክ መወለድ ምን ይደንቅ ቃልን ወሰነችው ልደቱንም ዘር አልቀደመውም በመወለዱም ድንግልናዋን አልለወጠውም። ቃል ከአብ ያለ ድካም ወጣ ከድንግልም ያለ ሕማም ተወለደ። ሰባ ሰገል ሰገዱለት አምላክ ነውና ዕጣን አመጡለት ንጉሥም ነውና ወርቅ አመጡለት ስለኛ በፈቃዱ ለተቀበለው መዳኛችን ለሆነ ሞቱም ከርቤ አመጡለት። ቸርና ሰውን ወዳጅ የሆነ አንድ እርሱ ብቻ ነው። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፬. ከአዳም ጐን አንዲት አጽም መንሣት ምን ይደንቅ? ከእርሱ ሴትን ፈጠረ የሰው ፍጥረትንም ፈጠረ። ጌታ የአብ ቃል ተሰጠ። ከልዩ ድንግልም ሰው ሆነና ዐማኑኤል ተባለ ስለዚህ ሁል ጊዜ እርሷን እንለምን ከተወደደ ልጅዋ ታማልደን ዘንድ። በቅዱሳንና በሊቃነ ጳጳሳት ሁሉ ዘንድ ቸር ናት ደጅ የሚጠኑትን ልዳላቸዋለችና ለነቢያትም ትንቢት የተናገሩለትን ወልዳላቸዋለችና ለሐዋርያትም እስከ ዓለም ዳርቻ በስሙ ያስተማሩለትን ወልዳላቸዋለችና  ሰማዕታትና ምእመናንም የተጋደሉለት የጥበቡ ጸጋ ብዛት የማይታወቅ ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሷ ተወልዷልና የይቅርታውን ብዛት መርምረን እንወቅ (እንፈልግ) መጥቶ አድኖናልና። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፭. እግዚአብሔር የባሕርይህን ፍሬ በዙፋንህ ላይ አኖራ ለሁ ብሎ ለዳዊት በእውነት ማለ አይጸጸትም። ጻድቅ እርሱ ዳዊት ክርስቶስ በሥጋ ከእርሱ  እንዲወለድ ባመነ ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል ማደሪያ ፈልጎ ያገኝ ዘንድ ወደደ ይህንንም በታላቅ ትጋት ፈጸመ፤ከዚህም በኋላ እነሆ በኤፍራታ ሰማነው ብሎ በመንፈስ ቅዱስ አሰምቶ ተናገረ። ይህቺውም ዐማኑኤል እኛን ለማዳን ይወለድባት ዘንድ የመረጣት የያዕቆብ አምላን ማደሪያ ናት። ዳግመኛም ከነቢያት አንዱ ሚክያስ አንቺ የኤፍራታ ክፍል የሆንሽ ቤተ ልሔም ከይሁዳ ነገሥታት መሳፍንት አገር አታንሽም ወገኖቼ እስራኤልን የሚጠብቃቸው ንጉሥ ከአንች ይወጣልና ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ ከቸር አባቱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ምስጋና ስለተገባው ስለ ክርስቶስ በአንድ መንፈስ ቅዱስ ትንቢት የተናገሩት የነዚህ የሚክያስና የዳዊት ነገር ምን ይረቅ? ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፮. ለእስራኤል የነገሠ ዳዊት ጠላቶቹ በተነሡበት ጊዜ ከቤተ ልሔም ምንጭ ውኃ ይጠጣ ዘንድ ወደደ፤የጭፍሮቹ አለቆች ፈጥነው ተነሡና በጠላቶቹ ከተማ ተዋግተው ሊጠጣ የወደደውን አመጡለት። ጻድቅ ዳዊት ግን ጨክነው ሰውነታቸውን ስለ እርሱ ለጦርነት ለሞት አሳልፈው እንደሰጡ ባየ ጊዜ ያን ውኃ አፈሰሰ ከእርሱም አልጠጣም ከዚህ በኋላ ለዘላለም ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት። ሰማዕታት የዚህችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ ደማቸውንም ስለ  እግዚአብሔር አፈሰሱ ስለ መንግሥተ ሰማያትም መራራ ሞትን ታገሱ እንደ ይቅርታህ ብዛት ይቅር በለን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፯. ከቅድስት ሥላሴ አንዱ ወልድ መዋረዳችንን አይቶ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ባሕርዩን ዝቅ አደረገና መጥቶ በድንግል ማኅፀን አደረ። ከብቻዋ ከኃጢአት በቀርም እንደ እኛ ሰው ሆነ ነቢያት ትንቢት እንደተናገሩለት በቤተ ልሔም ተወለደ ፈጽሞ አዳነን ወገኖቹም አደረገን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

ዓርብ የሚጸለይ አምላክን የወለደች የእመቤታችን ድንግል ማርያም ምስጋና ፭ኛ ክፍል

፩. ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ። የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው፤ ያለ ርኵሰት አምላክን የወለድሽ ድንግል ማርያም ሆይ እውነተኛ ፀሐይ ከአንቺ ወጣልን (ጌታ ተወለደልን) በክንፈ ረድኤቱም አቀረበን እርሱ ፈጥሮናልና። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፪. አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ የብርሃን እናት ነሽና፤አንችን ብቻሽን በክብር እናገንሻለን። የተባረክሽ አንቺ ከመላእክት ትበልጫለሽ፤ከአሳቦች ሁሉ ትበልጫለሽ፤ ገናንነትሽን መናገር የሚቻለው ማነው፤አንቺን የሚመስል የለምና። ማርያም ሆይ መላእክት ያገኑሻል ሱራፌልም ያመሰግኑሻል። በኪሩቤልና በሱራፌል ላይ አድሮ የሚኖር ጌታ መጥቶ በማኅፀንሽ አድሯልና። ሰውን የሚወድ ወደ እርሱ አቀረበን ክብር ምስጋና ያለው እርሱ የእኛን ሞት ተቀብሎ የእርሱን ሕይወት ለእኛ ሰጠን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፫. የደናግል መመኪያቸው አምላክን የወለድሽ ድንግል ማርያም ሆይ የተባረክሽ ነሽ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። ከዓለም በፊት የነበረ እርሱ ሰው ሆኗልና ከአንቺ የተወለደ ሥጋችንን ነሣ (ተዋሐደ) መንፈስ ቅዱስንም ሰጠን። በቸርነቱ ብዛት መሳዮቹ አደረገን ጸጋንና ክብርን ከተቀበሉ ብዙ ሴቶች አንቺ ትበልጫለሽ አምላክን የወለድሽ ማርያም ሆይ ልዑል እግዚአብሔር ያደረብሽ (የከተመብሽ) ረቂቅ ከተማ ነሽ። በኪሩቤልና በሱራፌል ላይ  የሚኖረውን ጌታን በመኻል እጅሽ ይዘሺዋልና። በቸርነቱ ብዛት ሥጋዊ ፍጥረትን ሁሉ የሚመግብ እርሱ ጡትሽን ይዞ ጠባ። ይኸውም ሁሉን የሚያድን አምላካችን ነው። ለዘላለሙ ይጠብቀናል። እንሰግድለትና እናመሰግነው ዘንድ እርሱ ፈጥሮናልና። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፬. ድንግል ማርያም የሽቱ መኖሪያና የሕይወት ውኃ ምንጭ ናት፤የማኅፀኗ ፍሬ ሰውን ሁሉ አድኗልና። ከእኛም እርግማንን አጠፋልን። በመካከላችንም ሆኖ በመስቀሉ አስታረቀን በልዩ ትንሳኤውም ሰውን ዳግመኛ ወደ ገነት መለሰው። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፭. ንጽሕት ድንግል ማርያም የታመነች አምላክን የወለደች ናት። ለሰዎች ልጆችም የምሕረት አማላጅ ናት ኃጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ ወደ ልጅሽ ወደ ክርስቶስ ለምኝልን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፮. ድንግል ማርያም በቤተ መቅደስ አሰምታ ትናገር ነበር መልአኩ ‹ቅድስት ድንግል ሆይ ሰላምታ ይገባሻል› ብሎ አክብሮ ከነገረኝ ነገር በቀር ምንም ምን ሌላ የማውቀው እንደሌለኝ እግዚአብሔር ያውቃል አለች። የማይቻለውን ቻልሽ፤ የማይወሰነውንና ምንም ምን የሚወስነው የሌለውን ወሰንሽ። በክብር ሁሉ ላይ ጸጋን የተመላሽ ሆይ ምስጋናሽ ይበዛል ክብርሽ ፍጹም ነው። የአብ ቃል ማደሪያ ሆነሻልና። የክርስቲያን ወገኖች ምእመናንን የምትሰበስቢያቸውና ማሕየዊ የሚያድኑን ለሆኑ ለሥላሴ ሰጊድን (መስገድን) የምታስተምሪላቸው ሰፊ መጋረጃ ሙሴ ያየውን የእሳት ዐምድ የተሸከምሽ አንቺ ነሽ። ይኸውም መጥቶ ማኅፀንሽ ያደረው የእግዚአብሔር ልጅ ነው። ሰማይንና ምድርን ለፈጠረ ጌታ ማደሪያ ሆንሽ። ዘጠኝ ወር በማኅፀንሽ ተሸከምሽው። ሰማይና ምድር ለማይወስኑት የታመንሽ አንቺ ነሽ። ከምድር ወደ ሰማይ ለማረግ መሰላል ሆንሽ ብርሃንሽ ከፀሐይ ብርሃን ይበልጣል። ቅዱሳን በፍጹም ደስታ ያዩት ኮከብ ካንቺ የተወለደ ምሥራቅ አንቺ ነሽ። ይኸውም በጻእርና በምጥ ትወልድ ዘንድ በሔዋን የፈረደ ባት ነው። አንቺ ማርያም ግን ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ  ይበልሽ የሚል ቃልን ሰማሽና መጥቶ ያዳነን የፍጥረት ሁሉ ገዥ የሆነ ንጉሥን ወለድሽልን። መሐሪ ነው ሰውንም ወዳጅ ነው። ስለዚህ ማርያም ሆይ  የተባረክሽ ነሽ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። ጸጋን የተመላሽ ሆይ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነውና ደስ ይበልሽ እያልን መልአኩ ገብርኤል እንዳመሰገነሽ እናመሰግንሻለን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

ቅዳሜ የሚጸለይ አምላክን የወለደች የእመቤታችን ድንግል ማርያም ምስጋና ፮ኛ ክፍል

፩. ንጽሕት ነሽ ብርህትም ነሽ። ጌታን በመኻል እጅሽ የያዝሽው ሆይ በሁሉ የተቀደስሽ ነሽ። ፍጥረቱ ሁሉ ቅድስት ሆይ ለምኝልን ብለው እየጮኹ ካንቺ ጋር ደስ ይላቸዋል። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፪. ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ ባለሟልነትን አግንተሻልና ደስ ይበልሽ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነውና ደስ ይበልሽ። ግርማ ያለሽ ድንግል ሆይ ገናንነትሽን እናመሰግናለን እናደንቃለን እንደ መልአኩ ገብርኤልም ምስጋና እናቀርብልሻለን የባሕርያችን መዳን በማኅፀንሽ ፍሬ ተገኝቷልና። ወደ አባቱ ወደ እግዚአብሔርም አቀረበን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፫. እንደ ሠርግ ቤት ጕድፍ የሌለብሽ ነሽ መንፈስ ቅዱስ አድሮብሻልና የልዑል ኃይልም ጸልሎሻልና። ማርያም ሆይ ለዘላለም የሚኖር መጥቶ ከኃጢአት ያዳነን የአብ ልጅ ቃልን በእውነት ወለድሽ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፬. ከዳዊት ሥር የተገኘሽ ባሕርይ (ዘር) አንቺ ነሽ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በሥጋ ወልደሽልናልና። ከአብ የተወለደ ከዓለም በፊት የነበረ አንዱ ቃል ራሱን (ባሕርዩን) ሰወረ ካንችም የተገዥን (የሰውን) አርኣያ ነሣ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፭. አምላክን ያለ ርኵሰት የወለድሽው ሆይ የምድር ሁለተኛ ሰማይን ሆንሽ እውነተኛ ፀሐይ ከአንቺ ወጥቶልናልና። እንደ ነቢያት ትንቢትም ያለዘርና ያለመለወጥ ወለድሽው። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፮. ከተለዩ የተለየሽ የተባልሽ የኪዳን ጽላት ያለብሽ የተሰወር መና ያለበት የወርቅ መሶብ ያለብሽ ደብተራ ድንኳን አንቺ ነሽ። ይኸውም መና የተባለው መጥቶ በድንግል ማርያም ማኅፀን ያደረው የእግዚአብሔር ልጅ ነው የአብ ቃል በርሷ ሰው ሆነ መጥቶ ያዳነን የባሕርይ ንጉሥን በዓለም ውስጥ ወለደችው የሚናገር በግ የክርስቶስ እናቱ ገነት ደስ ይላታል ለዘላለም የሚኖር የአብ ልጅ እርሱ መጥቶ ከኃጢአት አድኖናልና። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፯. የንጉሥ ክርስቶስ እናቱን ተባልሽ እርሱን ከወለድሽ በኋላም በድንግልና ኖርሽ። ድንቅ በሆነ ምሥጢር (ተዋሕዶ) ዐማኑኤልን ወለድሽው ስለዚህም ባለመለወጥ አጸናሽ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፰. እግዚአብሔር በላይዋ ተቀምጦባት ያዕቆብ ያያት መሰላል አንቺ ነሽ፤ በሁሉ በኩል የማይመረመር እርሱን ተፈትሖ በሌለበት ማኅፀንሽ ተሸክመሽዋልና። እኛን ስለማዳን ከአንቺ ሰው በሆነ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ሆንሽን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፱. የተባረክሽና ንጽሕት የሆንሽ አዳራሽ ሆይ እነሆ ጌታ የፈጠረውን ዓለም ሁሉ በይቅርታው ብዛት ያድን ዘንድ ካንቺ ወጣ (ተወለደ) ፈጽመን  እናመስግነው። ቸርና ሰውን ወዳጅ ነውና። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፲. ያለ ርኵሰት ድንግል የሆንሽ ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ የዓለም ሁሉ መክበሪያ ንጽሕት ጽዋ ነሽ፤ የማትጠፊ ፋና ነሽ፤የማትፈርሽ መቅደስ ነሽ። የቅዱሳን መደገፊያቸው (መጠጊያቸው) የማትለወጪ የሃይማኖት በትር ነሽ ቸር አዳኛችን ወደ ሆነ ልጅሽ ለምኝልን ፈጽሞ ይቅር ይለንና ይምረን ዘንድ ኃጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

በሰንበተ ክርስቲያን እሑድ የሚጸለይ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም ምስጋና። ፯ኛ ክፍል

፩. ከሴቶች ይልቅ ተለይተሽ የተባረክሽ ሆይ የተወደድሽ ተባልሽ ከተለዩ የተለየች በውስጧም የኪዳን የሕግ ጽላት ያለባት የምትባይ ሁለተኛ ክፍል አንቺ ነሽ። ኪዳንም በእግዚአብሔር ጣቶች የተጻፉ አሥሩ ቃላት ናቸው። ያለመለወጥ ከአንቺ ሰው የሆነ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደገኛ ስሙን መጀመሪያ ስሙን አስቀድሞ በየውጣ ነገረን ለአዲስ ኪዳንም አስታራቂ ሆነ በከበረ ደሙ ፈሳሽነት ወይም መፍሰስ ያመኑትንና ንጹሓን የሆኑትን ወገኖች አነጻቸው። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፪. ሁልጊዜ ንጽሕት የሆንሽ አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ ሁላችን ስለዚህ እናገንሻለን ሰውን በሚወድ በጌታ ዘንድ ይቅርታን እናገኝ ዘንድ  እንለምንሻለን ወደ አንችም እናንጋጥጣለን። ከማይነቅዝ ዕንጨት የተቀረፀ በውስጥና በውጭ በወርቅ የተለበጠ ታቦት ያለመለየትና ያለመለወጥ ሰው የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል ይመስልልናል ይኸውም መለወጥ የሌለበት ንጹሕ መለኮት ነው። ከአብ ጋር የተካከለ ነው። ለንጽሕት በራሱ አበሠራት በልዩ ጥበቡ ያለወንድ ዘር እንደ እኛ ሆነ መለኮቱን አዋሕዶ ያለርኵሰት በአንቺ ሰው ሆነ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፫. በግዚአብሔር ሥዕል የተሣሉ ኪሩቤል የሚጋርዱሽ መቅደስ አንቺ ነሽ ንጽሕት ሆይ ያለመለወጥ ከአንቺ ሰው የሆነው ቃል ኃጢአታችንን የሚያስተሠርይልንና አበሳችንን የሚደመስስልን ሆነ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፬. የተሠወረ መና ያለብሽ የንጹሕ ወርቅ መሶብ አንቺ ነሽ መናም ከሰማይ የወረደውና ለዓለም ሁሉ ሕይወትን የሚያድለው ኅብስት ነው። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፭. ሁልጊዜ ብርሃንነት ያለውን ፋና የተሸከምሽ የወርቅ መቅረዝ አንቺ ነሽ። ይኸውም ፋና የዓለም ብርሃን ነው። ጥንት ከሌለው ብርሃንም የተገኘ ብርሃን ነው ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ እውነተኛ አምላክ ነው ያለመለወጥም ከአንቺ ሰው የሆነው ነው። በመምጣቱም (ሰው በመሆኑም) በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ለምንኖር ለእኛ አበራልን በልዩ የጥበቡ ምሥጢር በሥጋዌ የልቡናችንን እግር ወደ ሰላም መንገድ አቀናልን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፮. ቡሩክ ከቤተ መቅደስ ይዞሽ የወጣ እሳትነት ያለውን ፍሕም የተሸከምሽ የወርቅ ማዕጠንት አንቺ ነሽ ፍሕም የተባለውም ኃጢአትን የሚያስተሠርይና በደልን የሚደመስስ ነው። ይኸውም ከአንቺ ሰው የሆነና ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ያሳረገ የእግዚአብሔር ቃል ነው። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፯. የእግዚአብሔርን ቃል የወለድሽልን መልካሟ ርግብ ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ። ከዕሴይ ሥር የወጣሽ መዓዛሽ ያማረ አበባ አንቺ ነሽ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፰. ሳይተክሏትና ውሃ ሳያጠጧት የለመለመች የአሮን በትር ነበረች ያለ ዘር ሰው ሆኖ ያዳነን እውነተኛ አምላካችንን ክርስቶስን የወለድሽልን ሆይ አንቺ እንደርሷ ነሽ ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፱. ጸጋን የተመላሽ ሆይ ከቅዱሳን ሁሉ ይልቅ ትለምኝልን ዘንድ ላንቺ ይገባል። አንቺ ከሊቃነ ጳጳሳት ትበልጫለሽ ከነቢያትም ከመምህራንም ትበልጫለሽ። ከሱራፌልና ከኪሩቤል ግርማ የሚበልጥ የመወደድ ግርማ አለሽ። በእውነቱ የባሕርያችን መመኪያ አንቺ ነሽ ለሰውነታችንም ሕይወትን የምትለምኝ ነሽ።ወደ ጌታችንና ወደ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምኝልን እርሱን በማመን በቀናች ሃይማኖት ያጸናን ዘንድ ይቅርታውንና ምሕረቱን ይሰጠን ዘንድ በቸርነቱ ብዛት ኃጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

አንቀጸ ብርሃን

፩. ኢትዮጵያዊው ቅዱስ ያሬድ የደረሰው የአምላክ እናት ምሥጋና። ለእውነተኛ ፈራጅ ለአምላክ እናት ምሥጋናና አገልግሎት ይገባታል። ቅድስት ሆይ ብፅዕት ነሽ የተመሰገንሽና የተባረክሽ ነሽ የከበርሽና ከፍ ከፍ ያልሽ ነሽ የብርሃን መውጫ የሕይወት መሰላል ነሽ አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ድንግል ማርያም ሆይ ከተለዩ የተለየሽ የመለኮት ማደሪያ ነሽ። ከፍጥረት ሁሉ ይልቅ የተከበርሽ ሆይ አብ የወደደሽ ወልድ ያደረብሽ መንፈስ ቅዱስ ያረፈብሽ (የጸለለብሽ) ተባልሽ። በምድር ላይ ከፍተኛ አርያምን የሆንሽ ከሰማያት በላይ ያለ የአርያም የልዑል ስፍራ ምትክ አንቺ ነሽ። ቅዱሳን ነቢያት ካህናትና ነገሥታት የአንቺ ምሳሌ አድርገው በውስጧ የኪዳን የሕግ ጽላት ያለባት ቅድስተ ቅዱሳን ከተለዩ የተለየችውን ሠሩ። ቅድስት ሆይ ልጅሽ ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን።

፪. የአምላክ ልጅ ከአንቺ ሰው ስለመሆኑ ስለ አንቺም ከምድር ወደ አርያም ወደ መንግሥተ ሰማያት የቀረብን ሆን በአንቺና በልጅሽ ስም የቀረብን ሆን። ዐሥሩ ቃላት በጣቶቹ የተጻፉ የፍጥረት ሁሉ ጌታ ያውም የአምላክ ልጅ በማኅፀንሽ አደረ። አብ በሥልጣኑ አጸናሽ መንፈስ ቅዱስም ጸለለብሽ አነፃሽ የልዑል ኀይልም አጸናሽ። ኢየሱስም የአንችን ሥጋ ለበሰ በታላቅ ቃል ጮኾ መጽሐፍ የሕይወት ውኃ ምንጭ ከሆዱ ይፈልቃል እንዳለ ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ መጥቶ ይጠጣ አለ። ቅድስት ሆይ ልጅሽ ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን።

፫. አብ አስቀድሞ በየውጣ ነገረን የውጣ የተባሉ በእግዚአብሔር ጣቶች የተጻፉ ዐሥሩ ቃላት ናቸው። ልጅህ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንተ ብቻ አባቱ እንደሆንክ እርሱም ብቻ ልጅህ እንደሆነ አስተማረን። እንዲሁም በሰማይ እናት በምድር አባት የለውም ብለን እናምናለን መምጣቱን ከአባቱና ከእውነት መንፈስ ከጰራቅሊጦስ በቀር  የሚያውቅ ሳይኖር ከሰማይ ወረደ ብለን እናምናለን፤ በማኅፀንሽ አደረ ዘጠኝ ወር ተሸከምሽው ሰማያት ደስ ተሰኙ ምድርም ደስ ተሰኘች። በልጅሽ መወለድ መልአክ ምሥራች ተናገረ። የሰማይ ጭፍሮችም መላእክትም ምስጋና በሰማይ ለእግዚአብሔር ይሁን  በምድርም ላይ ሰላም በሰውም እርሱ በሚፈቅደው እያሉ አመሰገኑ። እረኞችም በቤተ ልሔም ካዩትና ከሰሙት የተነሳ አደነቁ የጥበብ ሰዎች ብልሆች ሰዎች ለልጅሽ ሊሰግዱና አንቺን ሊያገለግሉ ኮከብን አይተው ከሩቅ አገር መጡ። ከምሥራቅ ጀምሮ መርቶ እስከ ቤተ ልሔም ያደረሳቸው ያ ኮከብ አንቺ ከሕፃንሽ ጋራ ባለሽበት

ቦታ ላይ ቆመ። እነዚያ ብልሆች ሰዎች አይተው በታላቅ ደስታ ደስ ተሰኙ ወደ እርሱ ወደ ሕፃንሽ ገቡና በፊቱ ቆሙ በምድር ላይ ወድቀው ሰገዱለት። ሣጥናቸውንም ከፈቱና ወርቅ ዕጣን ከርቤን እጅመንሻ አድርገው አገቡለት የወገኖችህን ልመናቸውንና መሥዋዕታቸውን ትቀበል ዘንድ ኃጢአታቸ ውንም ታስተሠርይላቸው ዘንድ የመጣህ አምላካችን ሆይ እጅ መንሻ አገባንልህ ለከበረ ስምህም ከአንተ የተገኘውን ዕጣን አቀረብንልህ አሉት። ቅድስት ሆይ ልጅሽ ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን።

፬. ከንጹሐን ይልቅ ንጽሕት የሆንሽ አንቺ ነሽ ከማይነቅዝ እንጨት እንደተሠራ በወርቅ እንደተጌጠና ዋጋው ብዙ በሆነ በሚያበራ ዕንቍ እንደተለበጠ ታቦት በቤተ መቅደስ ውስጥ የኖርሽ የተመረጥሽ ድንግል ነሽ። እንዲህ ሆነሽ በቤተ መቅደስ ውስጥ ኖርሽ መላእክትም ዘወትር ምግብሽን ያመጡ ነበር መላእክት እየጎበኙሽ እንዲህ ዓሥራ ሁለት ዓመት ኖርሽ። መጠጥሽም የሕይወት መጠጥ ነበር ምግብሽም የሰማይ ኅብስት ነበር አባትሽ ዳዊት በመሰንቆ አመሰገነ በትንቢት መንፈስም በመንፈስ ቅዱስም በገና እየደረደረ እንዲህ ብሎ ዘመረ ልጄ ሆይ ስሚ እዪም ጆሮሽንም አዘንብዪ ሕዝብሽንና የአባትሽን ቤት እርሺ ንጉሡም ውበትሽን ይወዳል እርሱ ጌታሽ ነውና ለእርሱም ስገጅ ትሰግጃለሽ። ቅድስት ሆይ ልጅሽ ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን።

፭. ከንጹሓን ካልበደሉ መላእክት ወገን የሆነና በደል የሌለበት በሁሉ ጌታ ፊት የሚቆም ከደጋጎቹ መላእክት ወገን የሆነ መልአኩ ገብርኤል አበሠረሽ እንዲህም አለሽ ጸጋን ያገኘሽ ሆይ ደስ ይበልሽ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው ከሴቶች ይልቅ የተባረክሽ ነሽ የሁሉ ገዥ በሆነ እግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አገኘሽ። እነሆ ትፀንሻለሽ ልጅም ትወልጃለሽ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ እርሱ ታላቅ ነው፤ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ይባላል እግዚአብሔር አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል ለዘላለሙ የያዕቆብን ወገን ይገዛል ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል የልዑል ኀይልም ይጸልልሻል። ከአንቺ የሚወለደውም ቅዱስ ነው። ቅድስት ሆይ ካንቺ የተወለደው ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን።

፮. የንጽሕና አዳራሽና ከተለዩ የተለየሽ መቅደስ አንቺ ነሽ የብርሃን መጋረጃና የማይመረመር የክብር (የጌትነት) ዙፋን አንቺ ነሽ ቅድስት ማርያም ሆይ መንፈስ ቅዱስ መጥቶ ስላደረብሽና የልዑል ኀይል ስለ ጸለለብሽ ቅድስተ ቅዱሳን (ከተለዩ የተለየች) በሆነች መቅደስ መሰልንሽ። የብርሃን መጋረጃ ነሽ ማለታችን ግን የአብ ቃል የሆነ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማኅፀንሽ ስለተሠወረ ነው። ይኸውም በላይ ያለ የሁሉ ጌታ ነው። መላእክትና የመላእክት አለቆች መናብርት ሥልጣናት አጋዕዝት ኃይላት ሊቃናት መኳንንት የሚያመሰግኑት ነው። ልጅሽንም በዚህ ዓለም በወለድሽው ጊዜ ዓይኖቻቸው ብዙዎች የሆኑ ኪሩቤልና ክንፎቻቸው ስድስት የሆኑ ሱራፌል በበረት ውስጥ ጋረዱልሽ። የብርሃን ደመናዎችም ከበቡሽ የመላእክት አለቆች የመላእክት ሠራዊትና የሰማይ ጭፍሮች በመፍራትና በመንቀጥቀጥ በፊትሽ ቆሙ። በዚህም ዓለም ኪሩቤልና ሱራፌል በሰማያት ካለው ምስጋናቸው ወይም ከቀድሞ ምስጋናቸው ወገን ባልሆነ በሌላ (በአዲስ) ምስጋና አመሰገኑሽ ፍጥረትን ሁሉ ሰብስቦ የያዘና ፍጥረቱን ሁሉ የሚመግብ ጌታቸው በብብትሽ (በክንድሽ) ተቀምጦ ጡትሽን እንደ ሕፃን ሲጠባ ባዩ ጊዜ በአርያም ፈለጉና በዚህ ዓለም እንደ ቀድሞው ከአባቱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አገኙት፤የጌታ ትሕትናውን ባዩ ጊዜም ዓይኖቻቸውን ወደ ላይ ወደ አርያም ከፍ ከፍ አደረጉ ክንፋቸውንም ዘርግተው ለሁሉ ጌታ ላንተ በሰማይ ምስጋና ይገባሃል እያሉ ጌታቸውን አመሰገኑ። ዳግመኛም በዋሻ በጎል ውስጥ አንቺን ከሕፃንሽ ጋር አይተው በምድር ላይ ሰላም (ፍቅር አንድነት ሆነ) አሉ። ካንቺ የነሣውን የእኛን ሥጋ ለብሶ ባዩት ጊዜም ሰውን ምንኛ ወደደው ብለው ሰገዱለት። ነቢዩ ዳዊትም እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ እግዚአብሔር በሰማይና በማደሪያው ቦታ ሆኖ በምድር ወደሚኖሩት ሁሉ ተመለከተ የሰውንም ልጆች ሁሉ አየ፤ ንጉሥ ውበትሽን ወደደ። ዘላለም ማረፊ ያዬ ይህች ናት መርጫታለሁና በእርሷ አድራለሁ አለ። ቅድስት ሆይ ልጅሽ ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን።

፯. የተለየሽና ደግ የሆንሽ የተመሰገንሽና የተባረክሽ የከበርሽና ከፍ ከፍ ያልሽ ሆይ የሕይወት ኅብስት ባለበት በወርቅ መሶብ መሰልንሽ። የሕይወት ኅብስትም(ይኸውም) በቀኙ ካሉ ጻድቃን ጋር እርሱን ለሚያምን በሃይማኖትና ፈቃደኛ በሆነ ልብ ከእርሱ ለሚበላም ሁሉ ሕይወትን የሚሰጥ ከሰማይ የወረደ ነው።

ቅድስት ሆይ ልጅሽ ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን።

፰. የብልሃተኛ እጅ ያልሠራት በውስጧም መብራት የማያበሩባት የወርቅ መቅረዝ አንቺ ነሽ፤ራሱ የአብ ብርሃን ያበራባታል እንጂ። ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ወደ አንቺ መጥቶ አደረ በአምላክነቱም በዓለም ሁሉ አበራ። ጨለማን ከሰዎች ላይ አራቀ፤እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ በብርሃኔ እመኑ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ ብሎ በሚያድን ቃሉ አዳነን። ቅድስት ሆይ ልጅሽ ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን።

፱. ከሁሉ ጌታ የተገኘ የሁሉ ጌታ ከብርሃን የተገነ ብርሃን በእውነት የሁሉ ጌታ (የባሕርይ አምላክ) ከሆነ የተገኘ ዕውነተኛ የሁሉ ጌታ የተወለደ እንጂ የተፈጠረ ያይደለ በህልውና በአኗኗር ከአባቱ ጋር የተካከለ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ በእርሱ የተፈጠረ እኛን ሰዎችን ስለማዳን ወረደው። ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ፈጽሞ ሰው ሆነ። በመምጣቱም አበራልን ፍጹም ደስታንም አበሠረን (ነገረን) ወደ አባቱም አቀረበን (አስታረቀን) ወደ ሕይወት ጐዳናም መራን የዘላለም ሕይወትንም ሰጠን። ነቢዩ ኢሳይያስ እርሱን በማመን፤ ከሕጉ የተነሣ በትንቢት እያደነቀ ሕግህ በምድር ላይ ብርሃን ነው አለ። አረጋዊ፤ ህንና የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የጠበቀ ጻድቅና ንጹሕ ዘካርያስ ፈጽሞ አደነቀ መናገርም ጀመረና እንዲህ አለ አምላካችን በይቅርታውና በምሕረቱ በአርያም (በልዕልና) ሆኖ ጐበኘን። በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ለሚኖሩትም ብርሃኑን ይገልጥላቸው ዘንድ ተወለደ ይቅር ይለን ይምረንም ዘንድ እግሮቻችንን ወደ ሰላም መንገድ አቀናልን። ቅድስት ሆይ ልጅሽ ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን።

፲. እመቤታችን ሆይ የቅዱሳንና የምእመናንን ሁሉ ጸሎት በማዕጠንታቸው ከምድር ወደ ሰማይ በሚያሳርጉ በሰማያውያን የካህናት አለቆች እጆች ውስጥ ባለ የወርቅ ማዕጠንት እንመስልሻለን። እንዲሁም ስምሽን በመጥራት የሰው ልጆችን ልመና ወደ ልዩ ሦስት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ያሳርጋሉ። የወገኖችሽንም ኃጢአት ታስተሠርይ ዘንድ ከአብ ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ ተፈቅዶልሻል፤ ለሰዎች ልጆች የዘላለም ሕይወት ድልድይ ትሆኝ ዘንድ። የዓለም ሁሉ መድኃኒት ሆይ ለምእመናን ወገኖችሽ መድኃኒታቸው ልትባይ ይገባሻል። ቅድስት ሆይ ልጅሽ ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን።

፲፩. አንቺ የተባረክሽ ዕፅ ነሽ የሕይወትና የደኅንነት ዕፅ ነሽ በገነት ውስጥ ባለው ዕፀ ሕይወት ፈንታ በዚህ ዓለም የሕይወት ዕፅ ሆንሽ ፍሬሽም የሕይወት ፍሬ ነው በሚወዱት (በሚያውቁት) በዓለም ሰዎች ዘንድ የሚሸት መልካም መዓዛ ያለው አበባ ከአንች ታየ ይኸውም ከርቤ ሚዓ፤ሰሊክ የተባሉ ሽቶዎች በልብሶችሽ ላይ አሉ ብሎ በበገና ነቢዩ ዳዊት የተናገረልሽ ነው። አባትሽ ሰሎሞንም የአፍንጫሽ መዓዛ እንደ ነጭ ዕጣን መዓዛ ነው አለ እቴ መርዓት ሙሽራዬ ሆይ የታጠርሽ ተክል ነሽ መንገድሽ የታጠረች ተክል የታተመች ጕድጓድ ናት። ከሽቱ ቅመም ጋራ ሽቱ አለሽ ቆዕ የሚባል ሽቱ ናርዶስ ከሚባል ሽቱ ጋር አለሽ ናርዶስ የሚባል ሽቱ መጽርይ ከሚባል ሽቱ ጋራ አለሽ ቀጺመታት ቀናንሞስ የተባሉ ሽቶዎች ከደጋ ሽቶዎች ጋራ አሉሽ። ከሽቶዎች ሁሉ  የሚበልጡ ከርቤና ዐልው የሚባሉ ሽቶዎች ከነዚህ ሁሉ ሽቶዎች ጋር አሉሽ የገነት ፈሳሽ ሆይ ከደጋ የሚፈስ የሕይወት ውኃ መገናኛ ነሽ። ቅድስት ሆይ ልጅሽ ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን።

፲፪. ሳይተክሏትና ውኃ ሳያጠጧት የለመለመች የአሮን በትር በቤተ መቅደስ ነበረች ለካህናት ዝግጁ ያደረጋት ነበረች። አንችም በቅድስናና በንጽሕና ጸንተሽ እንደ እርሷ በቤተ መቅደስ ኖርሽ ከቤተ መቅደስም በክብር በታላቅ ደስታ ወጣሽ። በእውነት የሕይወት ፍሬ የሆነ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአንቺ ተገኘ። ቅድስት ሆይ ከመልአኩ እንደ ተረዳሽው ከወንድ ያለመገናኘት ልጅን አገኘሽ መልአኩ መንፈስ ቅዱስ መጥቶ ያድርብሻል የልዑል  ኃይልም ይጸልልብሻል ብሎ ነግሮሽ ነበርና። ቅድስት ሆይ ልጅሽ ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን።

፲፫. ጸጋን የተመላሽና የደስታ መገኛ ሆይ በልጅሽ ስም ለአመንን ለእኛ ለወንዶችና ለሴቶች አገልጋዮችሽ ትለምኝልን ዘንድ ይገባሻል። ይልቁንም ዓይኖቻቸው ብዙዎች ከሆኑ ከኪሩቤልና ክንፎቻቸው ስድስት ከሆኑ ከሱራፌል ግርማ የሚበልጥ የመወደድ ግርማ አለሽ፤ እነዚያ ፊታቸውን ይሸፍናሉ። እግሮቻቸውም የትእምርተ መስቀል አምሳያዎች ናቸው፤ ከልጅሽ መለኮት ከሚወጣው እሳት ይድኑ ዘንድ አንቺ ግን ለመለኮት ማደሪያ ሆንሽ። የመለኮት  ባሕርይም አላቃጠለሽም፤ የእሳት ነበልባልን ተሸከምሽ። የመለኮት ባሕርይም አላቃጠለሽም። ሙሴ እንጨትነቷ በእሳት ሳይቃጠል ያያት ዕፀ ጳጦስን መሰልሽ። ሁለንተናው ፍጹም እሳት የሆነ የኀይላት ጌታ እንደ ዕፀ ጳጦስ አላቃጠለሽም ለክርስቲያን ወገኖች በእውነት መመኪያ የሆንሽ አንቺ ነሽ፤ የአምላክ ልጅ ካንቺ ሰው ስለመሆኑም በአንቺ ከምድር ወደ አርያም የቀረብን ሆንን። በጸሎትሽ ለሚያምኑ ምሕረትን የምታሰጪ ሆይ ለነፍሳችን ሕይወትን የምትለምኝ ነሽ ወደ ጌታችንና ወደ ድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምኝልን፤ እርሱን አባቱን መንፈስ ቅዱስን በማመን በቀናች ሃይማኖት ያጸናን ዘንድ። ይቅርታውንና ምሕረቱን ይሰጠን ዘንድ። በምሕረቱ ብዛት ኃጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ። የሁሉን ጌታ የወለድሽው ሆይ ምስጋና ይገባሻል። ዛሬም ዘወትርም ለዘላለምም ምስጋናና ክብር ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ይገባል አሜን። ቅድስት ሆይ ልጅሽ ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን።

፲፬. በቅዱስ ኤፍሬምና በኢትዮጵያዊው ቅዱስ ያሬድ ላይ ያደረ አምላክን የወለደች የእመቤታችን ድንግል ማርያም ልመናዋ ክብሯ የልጅዋ የወዳጅዋም ቸርነት ከወዳጆቿ ሕዝበ ክርስቲያን ጋራ ለዘላለሙ ይኑር አሜን።

ይዌድስዋ መላእክት

፩. መላእክት ማርያምን በመንጦላዕት ውስጥ ያመሰግኗታል ሐዳስ ጣዕዋ ለአንቺ ክብር ምስጋና ይገባሻል እያሉ። መልአክ ማርያምን ቃልን ተቀበይው አላት ከአንቺ ዘንድ ይመጣልና በማኅፀንሽም ያድራል እንዴት ከድኃ ቤት አደረ እንደ ምስኪን፤ ከሰማያት ወርዶ የእርሷን ባሕርይ ባሕርይ አድርጎ ተወለደ።

፪. በስድስተኛው ወር መልአኩ ገብርኤል ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ ተላከ ከአንዲት አገር ናዝሬት ገሊላ ከምትባል ለዮሴፍ እጮኛ ከሆነች ከድንግል ዘንድ የዚህች ድንግል ስሟ ማርያም ነው። መልአክ ወደ እርሷ ገብቶ እንዲህ አላት ደስታ ይገባሻል እግዚአብሔር ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነሥቶ ከአንቺ ሰው ሆኗልና ከሴቶች ይልቅ አንቺ ቡርክት ነሽ ከቃሉ አነጋገር አይታ ደነገጠች እንዲህም አለች እንዲህ ያለ የምስጋና እጅ መንሻ ይደረግልኛልን? መልአኩም እንዲህ አላት ማርያም ሆይ አትፍሪ ከእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሻልና እነሆ ትፀንሻለሽ ትወልጃለሽ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ እርሱም ታላቅ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል እግዚአብሔር አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል እርሱም በያዕቆብ ወገን ለዘላለሙ ይነግሣል መንግሥቱም አያልፍም፤ ማርያም መልአኩን እንዲህ አለችው ይህ ነገር እንደምን ይሆንልኛል እንዘ ኢየአምር ብእሴ መልአኩም እንዲህ አላት መንፈስ ቅዱስ ይጠብቅሻል የልዑል ኃይልም ያድርብሻል ይህ የሚወለደውም ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ ነው። እነሆ ኤልሳቤጥ ከአንቺ ወገን የምትሆን ከሸመገለች ከአረጀች በኋላ ፀነሰች ልጅም አገኘች እነሆ ይህ ስድስት ወር ሆነ መካን ሲሏት ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና። ማርያምም መልአኩን እንደ ቃልህ ይደረግልኝ እኔ ለእግዚአብሔር ባሪያው ነኝ አለችው።

፫. መልአኩ ገብርኤል ማርያም ድንግል ለአንቺ ክብር ምስጋና ይገባሻል አላት ወላዲተ አምላክ ምስጋና ይገባሻል ቅድስት ነሽና ምስጋና ይገባሻል የመለኮት ማደሪያ ነሽና ምስጋና ይገባሻል የተሸለመች ድንኳን ነሽና ምስጋና ይገባሻል የመላእክት እኅት የሕዝቡ ሁሉ እናት ነሽና ምስጋና ይገባሻል የሁሉ እመቤት ማርያም ምስጋና ይገባሻል የሁሉ ፍቅረኛ ማርያም ምስጋና ይገባሻል ልዑል ማደሪያው ትሆኝ ዘንድ መርጦሻልና ምስጋና ይገባሻል በወርቅ የተሸለምሽ የርግብ ክንፍ በብር ያጌጥሽ ምስጋና ይገባሻል ጐኖችሽ በወርቅ አመልማሎ የተሸለሙ ለአንች ምስጋና ይገባሻል የምሥራቅ ደጃፍ የብርሃን እናቱ ለአንች ምስጋና  ገባሻል ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበሪ ክብርሽ ከአድባራቱ ሁሉ ከፍ ከፍ ያለ ለአንች ምስጋና ይገባሻል ማርያም ሆይ ከተመረጡ የተመረጥሽ ከተከበሩ የተከበርሽ ለአንች ምስጋና ይገባሻል ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ለምኝልን ያድነን ዘንድ በአባቱ ምስጋና ከቅዱሳን መላእክቶቹ ጋር በመጣ ጊዜ ጻድቃንን በቀኙ ኃጥኣንን በግራው ባቆመ ጊዜ እኛን ከሰማዕቱ እስጢፋኖስ ከመጥምቁ ዮሐንስ ጋራ ከሁሉም ቅዱሳን ከሰማዕታት ጋራ ያቆመን ዘንድ ለምኝልን ለዓለመ ዓለም አሜን። ለዘላለሙ ይቅር ይበለን።

 

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top