የሰባቱ ቀን ፍጥረታት
በመጀመሪየው ቀን እሁድ፦ ስምንት ፍጥረታትን ፈጠረ እነዚህም ሰማይ፣ መሬት፣ ውኃ፣ ነፋስ፣ እሳት ጨለማ፣ ብርሃን እና መላእክትናቸው።
ሁለተኛው ቀን ሰኞ:- ምድርና ሰማይን ሞልቶ የነበረውን ውኃ ወደ ላይና ወደ ታች በመክፈል ጠፈርን ፈጠረ። በምድር ላይ ያሉ የውሃ ክፍሎች ውቂያኖስ፣ባህር፣ሐይቅ እና ወንዝ ይባላሉ።
በሦስተኛው ቀን ማክሰኞ:- ዕፅዋትን እህልና ጥራጥሬ (አዝርዕት)፣ አትክልት፣ ፍራፍሬዎችን ሁሉ ፈጠረ።
በአራተኛው ቀን ረቡዕ፦ ፀሐይ፣ ጨረቃንና ከዋክብትን ፈጠረ።
በአምስተኛው ቀን ሐሙስ:- በባህር የሚኖሩትን እንስሳት ፤ እንዲሁም አእዋፋትን ማለትም በውሃ ውስጥ እና በውሃ አከባቢ የሚኖሩ ወፎችን ፈጠረ።
በስድስተኛው ቀን ማለትም አርብ ዕለት:- በየብስ የሚኖሩ እንስሳትን (የቤት እንስሳትና የዱር አራዊት እንዲሁም በሰማይ የሚበሩ አእዋፋትን) ፈጠረ።
እግዚአብሔር አምላካችን ከላይ የተዘረዘሩትን ሁሉ አመቻችቶ ከፈጠረ በኋላ አርብ ዕለት ሰውን ማለትም የሁላችን አባት የሆነውን አዳምንና የሁላችን እናት የሆነቺውን ሄዋንን ፈጠረ። እግዚአብሔርም አዳምና ሔዋንን ለፈጠራቸው ፍጥረታት ማለትም ለባሕር እንስሳት፣ ለሰማይ ወፎች፥ ለምድር እንስሳት ሁሉ ገዢ (አዛዥ) አደረጋቸው።
በሰባተኛው ቀን ማለትም ቅዳሜ:- በዚህ እለት ግን ፍጥረት መፍጠሩን ጨርሶ የዕረፍት ቀን አደረገው።
22ቱን ሥነ-ፍጥረት እና 22ቱ የእግዚአብሔር ኅቡዕ ስሞች
22ቱን ሥነ-ፍጥረት ምሳሌ በማድረግ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት የእግዚአብሔርን ኅቡዕ ስሞች እንደሚከተለው በዝሙሩ አመስግኖታል። በመዝሙረ ዳዊት 118
1. አሌፍ ፡ ዓለምን ከነጓዟ ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ የፈጠረ እግዚአብሔር ማለት ነው።
2. ቤት፡ እግዚአብሔር ሁሉን መስጠት የሚችል ቸር ለጋስ ባለጸጋ ማለት ነው።
3. ጋሜል፡ እግዚአብሔር ሊመረመር የማይችል ግሩም ድንቅ ማለት ነው።
4. ዳሌጥ፡ እግዚአብሔር በጌትነቱ ዙፋን ለዘለዓለም ይኖራል ማለት ነው።
5. ሄ፡ እግዚአብሔር በአንድነቱ በሦስትነቱ ለዘለዓለም ይኖራል ማለት ነው።
6. ዋው፡ እግዚአብሔር በመንግሥት በሥልጣን በአገዛዝ በባህርይ አንድ አምላክ የሆነ ማለት ነው።
7. ዛይ፡ እግዚአብሔር በሥራው ሁሉ እየታሰበ ሲመሰገን የሚኖር ፈጣሪ ማለት ነው።
8. ሔት፡ እግዚአብሔር በመንግሥቱ ሽረት በባሕርዩ ኅልፈት የሌለበት ለዘለዓለም ሕያው የሆነ ማለት ነው።
9. ጤት፡ እግዚአብሔር ጥበብን የሚገልጽ ከጥበበኞች ይልቅ ጥበበኛ የሆነ አምላክ ማለት ነው።
10. ዮድ፡ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለ እሱ ኃያልና ጽኑዕ የሆነ ማለት ነው።
11. ካፍ፡ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የሌለ ሁሉን ማድረግ የሚቻለው አምላክ ማለት ነው።
12. ላሜድ፡ እግዚአብሔር ልዑለ ባሕርይ የሆነ ማለት ነው።
13. ሜም፡ እግዚአብሔር ንጹሕ ባሕርይ የሆነ አምላክ ማለት ነው።
14. ኖን፡ እግዚአብሔር የነገሥታት ንጉሥ የገዥዎች ገዥ የሆነ አምላክ ማለት ነው።
15. ሳምኬት፡ እግዚአብሔር ሁሉን የሚገዛ አምላክ ማለት ነው።
16. ዔ፡ እግዚአብሔር ታላቅና ገናና የሆነ አምላክ ማለት ነው።
17. ፌ፡ እግዚአብሔር ተወዳጅ የሆነ አምላክ ማለት ነው።
18. ጻዴ፡ እግዚአብሔር ሐሰት የሌለበት እውነተኛ አምላክ ማለት ነው።
19. ቆፍ፡ እግዚአብሔር ለልበ ቅኖችና ለየዋሃኖች ቅርብ የሆነ አምላክ ማለት ነው።
20. ሬስ፡ እግዚአብሔር ክብሩ ከእርሱ ለእርሱ የተገኘ የሁሉ ጌታ ማለት ነው።
21. ሳን፡ እግዚአብሔር በሥራው ሁሉ የተመሠገነ ማለት ነው።
22. ታው፡ እግዚአብሔር እንቅልፍ የሌለበት ትጉህ፤ ድካም የማይሰማው ጽኑዕ የሆነ ፈጣሪ ማለት ነው።