ሰባቱ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን
ምሥጢር ማለት ቃሉ የግሪክ ቋንቋ ሆኖ ቃሉ ከግዕዝና ከአማርኛ በቀጥታ የተወረሰ ሲሆን ትርጉሙም ድብቅ ፣ ስውር፣ ሽሽግ፣ ረቂቅ ፣ ለቅርብ ዘመድ ካልሆነ በቀር የማይገለጥ ማለት ነው፡፡ ለሁለት የሚከፈል ሲሆን ይኸውም የፍጡር ሚሥጢርና የፈጣሪ ሚስጥር በመባል ይታወቃል፡፡ የፍጡር ምስጢር ሁለት ይዘት አለው፡፡ የሰውና የመላዕክት ምስጢር ይባላል፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኘው የፈጣሪ የእግዚአብሔር ሚስጥር ይህ የከበረ የተወደደ የሚናፈቅ የበረከት ስጦታ ነው፡፡ ብርሃነ አለም ሀዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ ሲል በከበረ ቃሉ ገልፆታል፡፡ “እርሱንም ሳታዩት ትወዱታላችሁ አሁንም ምንም ባታዩት በእርሱ /በክርስቶስ/ አምናችሁ የእምነታችሁን ፍጻሜ እርሱን የነብሳችሁን መዳን እየተቀበላችሁ በማይናገርና ክብር በሞላበት ሀሴት ደስ ይበላችሁ”፡፡ በማለት ስውር ረቂቅ ከሆነው ጸጋ እግዚአብሔር የምንሰጠው ሀብት መሆኑን በማብራራት ገልፆታል፡፡ በዚህ መሰረት በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ከሚፈጸሙት ሚስጥራት በቁጥር 7 ተወስነው ተቀምጠዋል፡፡ ውሳኔነታቸው ለሰባቱ ሰማያት ስብዐተ እግዚአብሔር ለማይከፈልባቸው ከተሞች ገላጭ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰባት ሚስጥራት ቤተክርስቲያን የሚስጥርነታቸው ምክንያት በአይናችን ልናያቸው በእጃችን ልንዳስሳቸው የማንችል ልዩ ልዩ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች በእነዚህ ሚስጥራት አማካኝነት የሚሰጡን ስለሆነ ነው፡፡ አበው ሲናገሩ በንባብ የተሰወረ ብሂል ምስጢር ይባላል ብለው ስውርነቱን ረቂቅነቱን ይናገራሉ፡፡ 7ቱን ምሥጢራተ ቤተክርስቲያንም 7 መሆቸው በመጽሐፈ ምሳሌ 9፡1 ላይ ‹‹ጥበብ ቤቷን ሠራች ሰባቱንም ምሰሶዎችዋን አቆመች›› ይላል፡፡ ጥበብ የተባለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን ሰባት ምሰሶች የተባሉት ደግሞ የ7ቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ምሳሌ ነው፡፡
እነዚህም— 1.ምሥጢረ ጥምቀት፡- መንፈሳዊ ልደት
2.ምሥጢረ ሜሮን፡- መንፈሳዊ ዕድገት /በመንፈስ ቅዱስ መበልጸግ/
3.ምሥጢረ ቁርባን፡- መንፈሳዊ ምግብ /የዘለአለም ሕይወት/
4.ምሥጢረ ንስሐ፡- መንፈሳዊ ድኅነት /ሥርየተ ኀጢአት/
5.ምሥጢረ ተክሊል፡- የጋብቻ ጽናት
6.ምሥጢረ ክህነት፡- የማሠርና የመፍታት ፣ የማስተማር ፣ የማደስ ፣ የማጥመቅ ፣ ሥልጣን /መንፈሳዊ ኃይል/
7.ምሥጢረ ቀንዲል፡- ሥጋዊና መንፈሳዊ ኃይል /ከበሽታ መፈወስ/
የ7ቱ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን አከፋፈል
1) ለሁሉም የሚሰጡ ምሥጢራት
ምሥጢረ ጥምቀት
ምሥጢረ ሜሮን
ምሥጢረ ቁርባን
ምሥጢረ ንስሐ
2) ለሁሉም የማይሰጡ ምሥጢራት
ምሥጢረ ተክሊል
ምሥጢረ ክህነት
ምሥጢረ ቀንዲል
3) የሚደገሙ ምሥጢራት
ምሥጢረ ንስሐ
ምሥጢረ ቀንዲል
ምሥጢረ ቁርባን
4) የማይደገሙ ምሥጢራት
ምሥጢረ ጥምቀት
ምሥጢረ ሜሮን
ምሥጢረ ክህነት
ምሥጢረ ተክሊል
5) በአንድ ቀን የሚሰጡ ምሥጢራት
ምሥጢረ ጥምቀት
ምሥጢረ ሜሮን
ምሥጢረ ቁርባን
ምሥጢረ ጥምቀት
መጠመቅ ማለት መነከር፣ መዘፈቅ፣ ውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣት ማለት ነው፡፡ ምሥጢረ ጥምቀት የሥላሴ ልጅነት የሚሰጥበት እና የኃጢአት ሥርየት የሚገኝበትምሥጢርነው፡፡ጥምቀት የማትደገም፣ የማትከለስ አንዲት ናት፡፡ቅዱስ ጳውሎስ ልጅነትን የምናገኝባት ጥምቀት የማትደገምና የማትከለስ አንዲት ብቻ መሆንዋን ሲያስተምር ኤፌ.4÷5 ‹‹አንድጌታአንድሃይማኖትአንዲትጥምቀት…አለ›› ብሏል፡፡ ክርስቲያኖች በአርባና በሰማንያ ቀን ለምን ይጠመቃሉ? ኩፋሌ 4:9 ‹‹በተፈጠረባት ምድር ለአዳም አርባ ቀን ከተፈጸመለት በኃላ ይገዛትም ይጠብቃትም ዘንድ ወደገነት አስገባው:: ሚስቱንም በሰማንያ ቀን አስገባት፡፡ ይህንን መሰረት በማድረግ ክርስቲያን ወንዶች በአርባ ቀን ሴቶች በሰማንያ ቀን ይጠመቃሉ፡፡››
የጥምቀት አስፈላጊነት
ድኀነት በጥምቀት ነው፤
ማር 16:16 ‹‹ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል።››
በጥምቀት ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ዳግም እንወለዳለን፤
ዮሐ. 3÷3-6 ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አይገባም፡፡ ››
ቲቶ.3÷5 ‹‹ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደድ በተገለጠ ጊዜ እንደምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለነበረው ሥራ አይደለም›› ብሏል፡፡ ‹‹ለአዲስ ልደት በሚሆን መታጠብ›› ማለቱ ጥምቀትን ማለቱ መሆኑ የተረጋገጠነው፡፡እንዲሁም ለኤፌሶን ሰዎች ቤተክርስቲያንን አስመልክቶ በጻፈው ክታቡ ‹‹በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለእርስዋ…›› በማለት በጥምቀት አማካኝነት ምእመናን መንጻታቸውንና መቀደሳቸውን አስተምሯል (ኤፌ 5.26)፡፡
በጥምቀት የኃጢአት ሥርየት ይገኛል፡፡
ሐዋ.22÷16 ‹‹‹‹አሁንስ ለምን ትዘገያለህ? ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ፡፡ ከኃጢአትህም ታጠብ›› ፡፡ በዚህ መሠረት መጠመቁም ተገልጾአል (ሐዋ.9÷15-16)፡፡እንግዲህ ምን እንላለን? ታላቁ ሐዋርያ ከኃጢአቱ የነጻውና የተቀደሰው በእምነቱ ብቻ ሳይሆን አምኖ ጥምቀትን በመፈጸሙ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ኃጢአቱ የተወገደለት ሐዋርያ እንዲሆን በተጠራ ጊዜ ሳይሆን ‹‹የእግዚአብሔርን ስም እየጠራ ቀ ጊዜ ነው፡፡ እርሱም ድኀነት የሚገኘው በጥምቀት መሆኑን እንዲህ ሲል ገልጾታል፡፡ ‹‹ከእናንተ አንዳንዶች እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፣ ተቀድሳችኋል፣ ጸድቃችኋል (1ቆሮ.6÷11)፡፡ በበዓለሃምሳ በቅዱስ ጴጥሮስ ስብከት ልቡናቸው ከተመሰጠው አንዳንዶቹ ‹‹ምንእናድርግ?›› ብለው ሊያደርጉት የሚገባቸውን ያሳውቃቸው ዘንድ በጠየቁት ጊዜ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ የመለሰላቸው ‹‹ንስሐ ግቡ ኃጢአታችሁ ይሠረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ›› የሚል መልስ ነው (ሐዋ.2÷37-38)፡፡
በጥምቀት አዲስ ሕይወት ይገኛል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሲያረጋግጥ ‹‹እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን›› ብሏል (ሮሜ.6÷4)፡፡ የቀደመው በኃጢአት ምክንያት ያደፈ ሰውነታችን የሚታደሰው፣ የሚቀደሰውና አዲስ ሕይወትን የምናገኘው በጥምቀት ነው፡፡
በጥምቀት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ እንሆናለን፡፡
ገላ.3÷27 ‹‹ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና፡፡ ››በጥምቀት በደሙ ከዋጀን ከፈጣሪያችን ጋር አንድ እንሆናለን፡፡ በተጠመቅን ጊዜ አዲሱን ሕይወት እንጎናጸፋለን፤ ፈጣሪውን መስሎ በተፈጠረው በቀድሞው ሰው በአዳም በደል ምክንያት አጥተነው የነበረውን ንጽሕናና ቅድስና እናገኛለን፡፡
በጥምቀት የቤተክርስቲያን አባል እንሆናለን፡፡
በዘመነ ኦሪት የእግዚአብሔር ሕዝብ ለመሆን መገረዝ ሃይማኖታዊ ግዴታ ነበር፡፡ አሕዛብ በቁልፈት፣ እስራኤል በግዝረት ይለዩ ነበር፡፡ለዚህም ነው የአብርሃም ልጆች ሁሉ በተወለዱ በስምንተኛው ቀን እንዲገረዙ ሕግ የወጣው፡፡ግዝረት ደግሞ ሊመጣ ላለው ለጥምቀት ምሳሌ ነው (ቈላ. 2÷11-13)፡፡
ግዝረት ለሕዝበ እግዚአብሔር የአብርሃም የቃልኪዳን ተሳታፊዎች የመሆናቸው መለያ ምልክት እንደሆነ ሁሉ፤ ጥምቀትም በክርስቶስ የሚያምኑትን ሁሉ የጸጋው ግምጃ ቤት ከሆነች ቅድስት ቤተክርስቲያን ከሚገኘው ጸጋ ተካፋይ ያደርጋቸዋል፡፡ ስለዚህ በጥምቀት የቤተክርስቲያን አባል መሆናችን ይረጋገጣል፡፡
የጥምቀት ምሳሌ በብሉይ ኪዳን
ግዝረት
ከፍ ብለን እንደገለጽነው፣ ግዝረትcየእግዚአብሔር ሕዝብ መለያ ምልክት ነበር፡፡ ያልተገረዘ ሁሉ የአብርሃም ልጅ አይባልም ነበር፡፡ ከሕዝቡም ተለይቶ እንዲጠፋ እግዚአብሔር አዝዞ ነበር (ዘፍ.17 ቁ. 14)፡፡እንደዚሁም ሁሉ ከውኃና ከመንፈስ ያልተወለደ ማለትም ያልተጠመቀ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አይገባም፡፡ ጽኑ ፍዳ ወዳለበት ገሃነም ይወርዳል እንጂ፡፡ምክንያቱም መንግሥተ ሰማይ ካልገባ ያለው ምርጫ ገሃነም መጣል ነውና (ዮሐ.3÷3-6)፡፡ ስለዚህ ግዝረት ለሕዝበ እግዚአብሔር ግዴታ እንደነበረ ሁሉ ጥምቀትም ለክርስቲያኖች ሊፈጽሙት የሚገባ ሃይማኖታዊ ግዴታ ነው፡፡ቈላ.2÷10-12 ‹‹በክርስቶስ ገዛሪነት የኃጢአትን ሕዋስ ሰንኮፍ ቆርጦ በመጣል ሰው ሠራሽ ያይደለ ግዝረትን የተገዘራችሁበት፤ በጥምቀት ከእሱ ጋር ተቀበራችሁ፣ ከሙታን ለይቶ ባስነሣው በእግዚአብሔር ረዳትነትም በሃይማኖት ከእሱ ጋር ለመኖር በእስዋ ተነሣችሁ›› ብሏል፡፡
የእሥራኤል ባሕረ ኤርትራን ማቋረጥ
ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን እንዲህ ሲል ገልጦታል ‹‹ወንድሞች ሆይ ይህን ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ፡፡ አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች ነበሩ፡፡ ሁሉም በባሕር መካከል ተሻገሩ፡፡ሁሉም ሙሴ ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር ተጠመቁ›› (1ቆሮ.10÷1-12)፡፡ የሶርያ ንጉሥ ሠራዊት አለቃ ንዕማን ከለምጹ የነጻው በዮርዳኖስ ወንዝ ታጥቦ ነው፡፡በነቢይ በታዘዘው መሠረት በዮርዳኖስ ውኃ ሰባት ጊዜ ብቅጥልቅ በማለት ታጥቦ ሥጋው እንደገና እንደትንሽ ብላቴና ሥጋ ንጹሕም ሆኖ መመለሱን በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ እናገኘዋለን (2ነገ.5÷8-14)፡፡ እኛም ከኃጢአት ደዌ የምንነጻውና ያረጀው ሕይወታችን ሊታደስ የሚችለው በጥምቀት ነው፡፡ ስንጠመቅ የክርስቶስ ደም ከኃጢአታችን እንዳጠበን ማረጋገጣችን ነውና፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ሕዝቅኤል በመንፈስ ቅዱስ ተገልጦለት እንዲህ ብሏል ‹‹በውኃም አጠብሁሽ፤ ከደምሽም አጠራሁሽ፤ በዘይትም ቀባሁሽ›› (ሕዝ 16÷9)፡፡
ለምን በውኃ እንጠመቃለን
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው በውኃ ነው እኛም እርሱን አብነት በማድረግ በውኃ ልንጠመቅ ይገባናል (ማቴ.3÷13-16)፡፡
ጌታችን ለኒቆዲሞስ ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ ሰውከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም›› ስላለ እኛም የጌታን ትእዛዝ ለመፈጸም በውኃ እንጠመቃለን (ዮሐ.3÷5)፡፡
ሐዋርያት ከጌታ በተማሩት መሠረት ያጠመቁት በውኃ ነው፡፡ጴጥሮስም መልሶ ‹‹እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እንዳይጠመቁ ውኃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማንነው? አለ›› (የሐዋ.10÷46ና 47)፡፡ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ አጠመቃቸውም (የሐዋ.8÷28)፡፡
ውኃ የሰውነትን እድፍ እንደሚያጠራ ሁሉ እንዲሁም ጥምቀት የነፍስን እድፍ ያስወግዳል ያነጻል፡፡
ውኃ መልክን ያሳያል እኛም በውኃ በመጠመቅ የሥላሴን ምሥጢር በዓይነ ኅሊናችን እናያለን፡፡
ለንጊኖስ የተባለው ሐራዊ (ወታደር) የጌታን ቀኝ ጎን በጦር በወጋው ጊዜ ትኩስ ደምና ውኃ ባንድነት ፈሷል (ዮሐ. 19÷34)፡፡
ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎች
ሕዝ 36:25 “ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ እናንተም ትጠራላችሁ፥ ከርኵሰታችሁም ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ።”
ማቴ 3:5 “ያን ጊዜ ኢየሩሳሌም ይሁዳም ሁሉ በዮርዳኖስም ዙሪያ ያለ አገር ሁሉ ወደ እርሱ ይወጡ ነበር፤ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር።”
ማቴ 28:19 “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀመዛሙርት አድርጓቸው”
ማር 1:4 “ዮሐንስ በምድረ በዳ እያጠመቀ የንስሐንም ጥምቀት ለኃጢአት ስርየት እየሰበከ መጣ።”
ማር 16:16 “ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል።”
ሉቃ 3:21 “ሕዝቡም ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ኢየሱስ ደግሞ ተጠመቀ። ሲጸልይም ሰማይ ተከፈተ፥”
ዮሃ 3:5 “ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም።”
ዮሃ 3:22 “ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀመዛሙርቱ ጋር ወደ ይሁዳ አገር መጣ፥ በዚያም ከእነርሱ ጋር ተቀምጦ ያጠምቅ ነበር። ዮሐንስም ደግሞ በሳሌም አቅራቢያ በሄኖን በዚያ ብዙ ውኃ ነበርና ያጠምቅ ነበር፥
ሐዋ 2:38 “ጴጥሮስም፦ ንስሐግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።”
ሐዋ 8:38 “በመንገድም ሲሄዱ ወደ ውኃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም። እነሆ ውኃ፤ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው? አለው። ፊልጶስም። በፍጹም ልብህ ብታምን፥ ተፈቅዶአል አለው። መልሶም። ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ አለ።ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፥ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ፥ አጠመቀውም።
ሐዋ 9:18 “ወዲያውም እንደ ቅርፊት ያለ ከዓይኑ ወደቀ፥ ያንጊዜም ደግሞ አየ፤ ተነሥቶም ተጠመቀ፥”
ሐዋ 10:47 “በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ፦ እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እንዳይጠመቁ ውኃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማንነው? አለ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስምም ይጠመቁ ዘንድ አዘዛቸው። ከዚህ በኋላ ጥቂት ቀን እንዲቀመጥ ለመኑት።
ሐዋ 13:24 “ከመምጣቱ በፊት ዮሐንስ አስቀድሞ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የንስሐን ጥምቀት ሰብኮ ነበር።”
ሐዋ 18:8 “የምኵራብ አለቃ ቀርስጶስም ከቤተሰዎቹ ሁሉ ጋር በጌታ አመነ፥ ከቆሮንቶስ ሰዎችም ብዙ በሰሙ ጊዜ አምነው ተጠመቁ።”
ሐዋ 19:4 “ጳውሎስም፦ ዮሐንስስ ከእርሱ በኋላ በሚመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ ያምኑ ዘንድ ለሕዝብ እየተናገረ በንስሐ ጥምቀት አጠመቀ አላቸው።”
1ኛቆሮ 10:2 “ሁሉም ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር ተጠመቁ፤”
1ኛቆሮ 12:13 “አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና”
ገላ 3:26 “በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤ ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና።
ኤፌ 4:5 “አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት”
ሮሜ 6:3 “ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደተጠመቅን አታውቁምን?”
ምስጢረ ሜሮን
ሜሮን ማለት ቅዱስ ቅብዕ ነው፡፡ ሜሮን ቃሉ ግሪክ ሲሆን ትርጉሙም ቅብዕ ማለት ነው፡፡ ሜሮን ከጥምቀት በሁዋላ የሚፈጸም ነው፡፡ይህም ማለት ተጠማቂው ሰው ጥምቀት ከተፈጸመለት በሁዋላ ሳይውል ሳያድር ወዲያውኑ ጥምቀቱ እንደተቀበለ ሜሮን ይቀበላል ሜሮን ሲቀባም ከመንፈስ ቅዱስ መወለዱ ይረጋገጥለታል፡፡ ተጠማቂው ተጠምቆ ሜሮን መቀባቱ መንፈስ ቅዱስን መቀበሉን ያመለክታል፡፡
ምስጢረ ሜሮን ለምን ከጥምቀት ቀጥሎ እንዲፈጸም ይደረጋል?
ምስጢረ ሜሮን ከምስጢረ ጥምቀት ጋር ተያይዞ እንዲፈጸም የሚደረገው ተጠማቂው ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ መወለዱን ለማረጋገጥ ነው፡፡እንደዚሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሓንስ እጅ ተጠምቆ ወዲያው ከውኃ ሲወጣ መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ርግብ ማለት በርግብ ተመስሎ ከራሱ ላይ ማረፉ ማቴ 3:16 ዮሐ 1:32 ሜሮን ከጥምቀት ቀጥሎ ወዲያው መፈጸም ያለበት መሆኑን ያመለክታል ስለዚህ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሥርዓት መሠረት ምስጢረ ጥምቀት ምስጢረ ሜሮን ምስጢረ ቁርባን ያለመለያየት በተከታታይ በአንድ ቀን የሚፈጸሙ ምስጢራት ናቸው፡፡ ይኽውም ተጠማቂው ሰው በካህኑ እጅ እንደ ተጠመቀ ወዲያው ሜሮን ይቀባል ሳይውል ሳያድርም ቅዱስ ቁርባን ይቀበላል ማለት ነው፡፡ይህ ቅዱስ ሥርዓት ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ሲያያዝ የመጣ ነውና ሊለውጡት አይገባም፡፡
በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም በውኃ ተጠመቆ ወዲያው ሜሮን መቀባት መንፈስ ቅዱስን የመቀበል ምልክት መሆኑን በርከት ያሉ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት በየድርሳናቸው አረጋግጠዋል፡፡በጥምቀት ጊዜ ቅብዓ ሜሮን መቀባታችንን አስመልክቶ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ሲጽፍ 1ኛዮሐ 2:20 “እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ።”
1ኛዮሐ 2:27 “እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ።”
የምስጢረ ሜሮን ምሳሌ የተጀመረው መቼ ነው?
ዘጸ 30:22- 25 “ብርጕድም አምስት መቶ ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን፥ የወይራ ዘይትም አንድ የኢን መስፈሪያ ትወስዳለህ። በቀማሚም ብልሃት እንደ ተሠራ ቅመም፥ የተቀደሰ የቅብዓት ዘይት ታደርገዋለህ የተቀደሰ የቅብዓት ዘይት ይሆናል።”
በዘመነ ብሉይ የተቀደሰው ቅብዕ ለምን አገልግሎት ይውል ነበር?
1ኛ/ አሮንና ልጆቹ ቅብዓ ቅዱስ ተቀብተው ስልጣነ ክህነትን ተቀብለዋል (ተክነዋል)
2ኛ/ በደብተራ ኦሪት (በአገልግሎት ድንኮን) ውስጥ ለእግዚአብሔር አገልግሎት የሚውሉ የቤተመቅደስ ንዋያት (ዕቃዎች) በሙሉ በተቀደሰው ቅብእ ተቀብተው ንዋያተ ቅዱሳት ተብለው ለመንፈሳዊ አገልግሎት ይውሉ ነበር
3ኛ/ የእስራኤል ነገሥታትና ካህናት የተቀደሰውን ቅብዕ (ዘይት) እየተቀቡ ነገሥታቱ ሥልጣነ መንግሥትን እጅ ሲያደርጉ ካህናቱ ደግኖ ክህነትን ይቀበሉት ነበር (1ኛሳሙ 10:1 1ኛነገሥ 19:15-21 ዘሌ 8:12)
ሜሮን ለምን ለምን አገልግሎት ይውላል?
1ኛ/ በቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ሥጋና ደም ማቅረቢያ ይሆኑ ዘንድ አዳዲስ ዕቃዎች ማለት ጻሕል ጽዋ ጽርፈመስቀል መሶበወርቅ በጸሎት ሜሮን ተቀብተው ይከብራሉ
2ኛ/ አዲስ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ታንጾ ሲያበቃለት በጸሎት ተባርኮ ቅብዓ ሜሮን ይቀባል
3ኛ/ አዲስ ታቦትና አዲስ መንበረታቦት ቅብዓተሜሮን ተቀብተው ይከብራሉ
4ኛ/ ሜሮን የጸጋን ልጅነት የሚያሰጥ ምስጢር ስለሆነ በጥምቀት ጊዜ {በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም} የተጠመቁ ምእመናን ወዲያው ሜሮን ሲቀቡ መንፈስ ቅዱስ ያድርባቸዋል።
የክርስትና አባት ወይም እናት አገልግሎት ምንድን ነው?
የክርስትና አባት እናት ለተጠመቁት ሰዎች የሃይማኖት ወላጆች ናቸው ስለዚህ በጥምቀት ክርስትና ያነሱአቸውን የሃይማኖት ልጆቻቸው ስለሆኑ የማሳደግና ትምህርተ ሃይማኖትን የማስተማር ኃላፊነት አለባቸው።
ምሥጢረ ቁርባን
የቃሉ ትርጉም
ቊርባን ቃሉ የሱርስትና የዓረብ ሲሆን ትርጉሙም በቁሙ መንፈሳዊ አምኃ፣ መሥዋዕት፣ መባዕ፣ ለአምላክ የሚቀርብ፣ የሚሰጥ ገንዘብ ማለት ነው፡፡ቃሉን በምልዓት ስንመለከተው ሰው ለአምላኩ የሚያቀርበውን ነገር ሁሉ የሚያካትት ሲሆን በዚህ ርዕሳችን የምንመለከተው ግን ስለአማናዊው ቁርባን ወይም መሥዋዕት ስለ ምሥጢረ ቁርባን ነው፡፡ምሥጢረ ቊርባን ማለት ካህኑ ኀብስቱን በጻሕል ወይኑን፣ በጽዋዕ አድርጎ በጸሎተ ቅዳሴ በባረከው ጊዜ ኀብስቱ ተለውጦ ሥጋ መለኮት፣ ወይኑ ተለውጦ ደመ መለኮት የሚሆንበትና እኛም የዘላለም ሕይወትን ለማግኘት ይህንን የክርስቶስን ሥጋና ደም የምንቀበልበት ዓቢይ ምሥጢር ነው፡፡
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ለእኛ ‹‹እንካችሁ›› ብሎ ከመስጠቱ ቀደም ብሎ የአማናዊው መሥዋዕት የቅዱስ ቁርባንን (ምሥጢረ ቁርባን) ምሳሌ በዘመነ ብሉይ እናገኘዋለን፡፡ብሉይኪዳንለሐዲስኪዳንአምሳልመርገፍነውና፡፡
በብሉይ ኪዳን የምሥጢረ ቊርባን ምሳሌ
መልከጸዴቅ “(ዘፍ. 14:6-10፤ዕብ.7:1-3 እና 7)”
‹‹ክህነቱ የወልደ እግዚአብሔር ምሳሌ ሆኖ ለዝንተዓለም ይኖራል›› ተብሎ የተነገረለት የሰላም ንጉሥ መልከጸዴቅ በዘመነ ብሉይ ከቀደምት አበው ሁሉ ለየት ብሎ በቀራንዮ ኮረብታ ላይ ከእርሱ በፊትም ሆነ ከእርሱ በኋላ ያሉት አባቶች ያቀርቡት እንደነበረው የደም መሥዋዕት ሳይሆን በኀብስትና በወይን ይሠዋ ነበር፡፡አበ ብዙኀን ተብሎ የሚጠራው አብርሃም ኮሎዶጎሞርንና ከእርሱ ጋራ የነበሩትን ነገሥታት ወግቶ ሲመለስ ይኸው የሳሌም ንጉሥ መልከ ጼዴቅ ኀብስትና ወይን ይዞ ተቀብሎታል፡፡የመልከጸዴቅ ኀብስተ አኰቴት ጽዋዐ በረከት የሥጋ ወደሙ ምሳሌ ሲሆን መልከ ጸዴቅ ደግሞ የልዑለ ባሕርይ የጌታችንና የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡
የፋሲካው በግ (ዘጸ.12÷1-25)
እስራኤል በምድረ ግብፅ ለ43ዐ ዘመን ያህል በባርነት ሲማቅቁ ከኖሩ በኋላ በልዑል እግዚአብሔር ቸርነት በነቢዩ ሙሴ መሪነት ምድረ ግብፅን ለቀው ከመውጣታቸው በፊት ከሞተበኵር ይድኑ ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ አላቸው፡- … ይህ ወር የወሮች መጀመሪያ ይሁንላችሁ፡፡ የዓመቱም መጀመሪያ ወር ይሁንላችሁ፡፡ በዚህ ወር በአሥረኛው ቀን ሰው ሁሉ ለአባቱ ቤት አንድ ጠቦት ይውሰድ…የእናንተ ጠቦት ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ተባት ይሁን… በዚህም ወር እስከ አሥራ አራተኛ ቀን ድረስ ጠብቁት፡፡ የእስራኤልም ማኀበር ጉባኤ ሁሉ ሲመሽ ይረዱት፡፡ከደሙም ወስደው በሚበሉበት ቤት ሁለቱን መቃንና ጎበኑን ይቅቡት፡፡ በእሳት የተጠበሰውን ሥጋውንና ቂጣውን እንጀራ በዚያች ሌሊት ይብሉ፡፡ ከመራራ ቅጠል ጋር ይበሉታል፡፡ ጥሬውን በውኃም የበሰለውን አትብሉ፡፡ነገር ግን ከራሱ፣ ከጭኑ፣ ከሆድ ዕቃው ጋር በእሳት የተጠበሰውን ብሉት፡፡ ከእርሱም እስከጠዋት አንዳች አታስቀሩ፡፡ እስከጠዋትም የቀረውን በእሳት አቃጥሉት፡፡… እርሱ የእግዚአብሔር ፋሲካ ነው፡፡
እስራኤል ከሞተኵር የዳኑበት ተባት በግ ምሳሌነቱ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ብርሃን ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን በላከው ክታቡ ላይ ሲያረጋጋጥ ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዷልና ብሏል (1ቆሮ.6÷7)፡፡መጥምቀ መለኮት ዮሐንስም በዕለተዓርብ፣ ስለዓለሙ ድኀነት የተሠዋውን አማናዊ በግ ለደቀመዛሙርቱ ሲያስተዋውቅ እነሆ የዓለምን ኃጢአት የማያስወግድ የእግዚአብሔር በግ ሲል ገልጧል (ዮሐ.1÷29)፡፡
የዚህ ምሳሌነቱ ነጥብ የምታክል ነውር የሌለበት ማለትም ምክንያተ ኃጢአት የሌለበት ንጹሐባሕርይ ጌታ በቅንዓተ አይሁድ ታሥሮ፣ በመስቀል ላይ ራሱን ለመሠዋቱ ምሳሌ ነው፡፡በጉ የአንድ ዓመት ተባት ለመታረድ የደረሰ እንዲሆን እንደታዘዙ ሁሉ ጌታም ፍጹም የሠላሳ ዐመት ጐልማሳ ሳለ ለመሰቀሉ ምሳሌ ሲሆን በጉ በአሥረኛው ቀን ታሥሮ በአሥራ አራተኛው ቀን እንደተሠዋ ሁሉ ጌታም በአይሁዱ እጅ ተይዞ እንደ ወንጀለኛ ታሥሮ በዕለተ ዓርብ ለመሥዋዕት የመቅረቡ ምሳሌ ነው፡፡
መና (ዘጸ16:33)