ሰባቱ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን

ሰባቱ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን
ምሥጢር ማለት ቃሉ የግሪክ ቋንቋ ሆኖ ቃሉ ከግዕዝና ከአማርኛ በቀጥታ የተወረሰ ሲሆን ትርጉሙም ድብቅ ፣ ስውር፣ ሽሽግ፣ ረቂቅ ፣ ለቅርብ ዘመድ ካልሆነ በቀር የማይገለጥ ማለት ነው፡፡ ለሁለት የሚከፈል ሲሆን ይኸውም የፍጡር ሚሥጢርና የፈጣሪ ሚስጥር በመባል ይታወቃል፡፡ የፍጡር ምስጢር ሁለት ይዘት አለው፡፡ የሰውና የመላዕክት ምስጢር ይባላል፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኘው የፈጣሪ የእግዚአብሔር ሚስጥር ይህ የከበረ የተወደደ የሚናፈቅ የበረከት ስጦታ ነው፡፡ ብርሃነ አለም ሀዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ ሲል በከበረ ቃሉ ገልፆታል፡፡ “እርሱንም ሳታዩት ትወዱታላችሁ አሁንም ምንም ባታዩት በእርሱ /በክርስቶስ/  አምናችሁ የእምነታችሁን ፍጻሜ እርሱን የነብሳችሁን መዳን እየተቀበላችሁ በማይናገርና ክብር በሞላበት ሀሴት ደስ ይበላችሁ”፡፡ በማለት ስውር ረቂቅ ከሆነው ጸጋ እግዚአብሔር የምንሰጠው ሀብት መሆኑን በማብራራት ገልፆታል፡፡ በዚህ መሰረት በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ከሚፈጸሙት ሚስጥራት በቁጥር 7 ተወስነው ተቀምጠዋል፡፡ ውሳኔነታቸው ለሰባቱ ሰማያት ስብዐተ እግዚአብሔር ለማይከፈልባቸው ከተሞች ገላጭ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰባት ሚስጥራት ቤተክርስቲያን የሚስጥርነታቸው ምክንያት በአይናችን ልናያቸው በእጃችን ልንዳስሳቸው የማንችል ልዩ ልዩ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች በእነዚህ ሚስጥራት አማካኝነት የሚሰጡን ስለሆነ ነው፡፡ አበው ሲናገሩ በንባብ የተሰወረ ብሂል ምስጢር ይባላል ብለው ስውርነቱን ረቂቅነቱን ይናገራሉ፡፡ 7ቱን ምሥጢራተ ቤተክርስቲያንም 7 መሆቸው በመጽሐፈ ምሳሌ 9፡1 ላይ ‹‹ጥበብ ቤቷን ሠራች ሰባቱንም ምሰሶዎችዋን አቆመች›› ይላል፡፡ ጥበብ የተባለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን ሰባት ምሰሶች የተባሉት ደግሞ የ7ቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ምሳሌ ነው፡፡

እነዚህም— 1.ምሥጢረ ጥምቀት፡- መንፈሳዊ ልደት

                   2.ምሥጢረ ሜሮን፡- መንፈሳዊ ዕድገት /በመንፈስ ቅዱስ መበልጸግ/

                   3.ምሥጢረ ቁርባን፡- መንፈሳዊ ምግብ /የዘለአለም ሕይወት/

                   4.ምሥጢረ ንስሐ፡- መንፈሳዊ ድኅነት /ሥርየተ ኀጢአት/

                   5.ምሥጢረ ተክሊል፡- የጋብቻ ጽናት

                   6.ምሥጢረ ክህነት፡- የማሠርና የመፍታት ፣ የማስተማር ፣ የማደስ ፣ የማጥመቅ ፣ ሥልጣን /መንፈሳዊ ኃይል/

                  7.ምሥጢረ ቀንዲል፡- ሥጋዊና መንፈሳዊ ኃይል /ከበሽታ መፈወስ/

የ7ቱ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን አከፋፈል
1) ለሁሉም የሚሰጡ ምሥጢራት
 • ምሥጢረ ጥምቀት
 • ምሥጢረ ሜሮን
 • ምሥጢረ ቁርባን
 • ምሥጢረ ንስሐ
2) ለሁሉም የማይሰጡ ምሥጢራት
 • ምሥጢረ ተክሊል
 • ምሥጢረ ክህነት
 • ምሥጢረ ቀንዲል
3) የሚደገሙ ምሥጢራት
 • ምሥጢረ ንስሐ
 • ምሥጢረ ቀንዲል
 • ምሥጢረ ቁርባን
4) የማይደገሙ ምሥጢራት
 • ምሥጢረ ጥምቀት
 • ምሥጢረ ሜሮን
 • ምሥጢረ ክህነት
 • ምሥጢረ ተክሊል
5) በአንድ ቀን የሚሰጡ ምሥጢራት
 • ምሥጢረ ጥምቀት
 • ምሥጢረ ሜሮን
 • ምሥጢረ ቁርባን
ምሥጢረ ጥምቀት
​መጠመቅ ማለት መነከር፣ መዘፈቅ፣ ውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣት ማለት ነው፡፡ ምሥጢረ ጥምቀት የሥላሴ ልጅነት የሚሰጥበት እና የኃጢአት ሥርየት  የሚገኝበትምሥጢርነው፡፡ጥምቀት የማትደገም፣  የማትከለስ አንዲት ናት፡፡ቅዱስ ጳውሎስ ልጅነትን የምናገኝባት ጥምቀት የማትደገምና የማትከለስ አንዲት ብቻ መሆንዋን ሲያስተምር  ኤፌ.4÷5 ‹‹አንድጌታአንድሃይማኖትአንዲትጥምቀት…አለ›› ብሏል፡፡ ክርስቲያኖች በአርባና በሰማንያ ቀን ለምን ይጠመቃሉ? ኩፋሌ 4:9 ‹‹በተፈጠረባት ምድር ለአዳም አርባ ቀን ከተፈጸመለት በኃላ ይገዛትም ይጠብቃትም ዘንድ ወደገነት አስገባው:: ሚስቱንም በሰማንያ ቀን         አስገባት፡፡ ይህንን መሰረት በማድረግ ክርስቲያን ወንዶች በአርባ ቀን ሴቶች በሰማንያ ቀን ይጠመቃሉ፡፡››
የጥምቀት አስፈላጊነት
 1. ድኀነት በጥምቀት ነው፤
 ማር 16:16 ‹‹ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል።››
 1. በጥምቀት ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ዳግም እንወለዳለን፤
ዮሐ. 3÷3-6 ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አይገባም፡፡ ››
ቲቶ.3÷5 ‹‹ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደድ በተገለጠ ጊዜ እንደምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለነበረው ሥራ አይደለም›› ብሏል፡፡ ‹‹ለአዲስ ልደት በሚሆን መታጠብ›› ማለቱ ጥምቀትን ማለቱ መሆኑ የተረጋገጠነው፡፡እንዲሁም ለኤፌሶን ሰዎች ቤተክርስቲያንን አስመልክቶ በጻፈው ክታቡ ‹‹በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለእርስዋ…›› በማለት በጥምቀት አማካኝነት ምእመናን መንጻታቸውንና መቀደሳቸውን አስተምሯል (ኤፌ 5.26)፡፡
 1. በጥምቀት የኃጢአት ሥርየት ይገኛል፡፡
ሐዋ.22÷16 ‹‹‹‹አሁንስ ለምን ትዘገያለህ? ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ፡፡ ከኃጢአትህም ታጠብ›› ፡፡ በዚህ መሠረት መጠመቁም ተገልጾአል (ሐዋ.9÷15-16)፡፡እንግዲህ ምን እንላለን? ታላቁ ሐዋርያ ከኃጢአቱ የነጻውና የተቀደሰው በእምነቱ ብቻ ሳይሆን አምኖ ጥምቀትን በመፈጸሙ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ኃጢአቱ የተወገደለት ሐዋርያ እንዲሆን በተጠራ ጊዜ ሳይሆን   ‹‹የእግዚአብሔርን ስም እየጠራ ቀ ጊዜ ነው፡፡ እርሱም ድኀነት የሚገኘው በጥምቀት መሆኑን እንዲህ ሲል ገልጾታል፡፡ ‹‹ከእናንተ አንዳንዶች እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም  በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፣ ተቀድሳችኋል፣ ጸድቃችኋል (1ቆሮ.6÷11)፡፡ በበዓለሃምሳ በቅዱስ ጴጥሮስ ስብከት ልቡናቸው ከተመሰጠው አንዳንዶቹ ‹‹ምንእናድርግ?›› ብለው ሊያደርጉት የሚገባቸውን ያሳውቃቸው ዘንድ በጠየቁት ጊዜ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ የመለሰላቸው ‹‹ንስሐ ግቡ ኃጢአታችሁ ይሠረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ›› የሚል መልስ ነው (ሐዋ.2÷37-38)፡፡
 1. በጥምቀት አዲስ ሕይወት ይገኛል፡፡
 ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሲያረጋግጥ ‹‹እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን›› ብሏል (ሮሜ.6÷4)፡፡ የቀደመው በኃጢአት ምክንያት ያደፈ ሰውነታችን የሚታደሰው፣ የሚቀደሰውና አዲስ ሕይወትን የምናገኘው በጥምቀት ነው፡፡
 1. በጥምቀት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ እንሆናለን፡፡
ገላ.3÷27 ‹‹ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና፡፡ ››በጥምቀት በደሙ ከዋጀን ከፈጣሪያችን ጋር አንድ እንሆናለን፡፡  በተጠመቅን ጊዜ አዲሱን ሕይወት እንጎናጸፋለን፤ ፈጣሪውን መስሎ በተፈጠረው በቀድሞው ሰው በአዳም በደል ምክንያት አጥተነው የነበረውን ንጽሕናና ቅድስና እናገኛለን፡፡
 1. በጥምቀት የቤተክርስቲያን አባል እንሆናለን፡፡
በዘመነ ኦሪት የእግዚአብሔር ሕዝብ ለመሆን መገረዝ ሃይማኖታዊ ግዴታ ነበር፡፡ አሕዛብ በቁልፈት፣ እስራኤል በግዝረት ይለዩ ነበር፡፡ለዚህም ነው የአብርሃም ልጆች ሁሉ በተወለዱ በስምንተኛው ቀን እንዲገረዙ ሕግ የወጣው፡፡ግዝረት ደግሞ ሊመጣ ላለው ለጥምቀት ምሳሌ ነው (ቈላ. 2÷11-13)፡፡
ግዝረት ለሕዝበ እግዚአብሔር የአብርሃም የቃልኪዳን ተሳታፊዎች የመሆናቸው መለያ ምልክት እንደሆነ ሁሉ፤ ጥምቀትም በክርስቶስ የሚያምኑትን ሁሉ የጸጋው ግምጃ ቤት ከሆነች ቅድስት ቤተክርስቲያን ከሚገኘው ጸጋ ተካፋይ ያደርጋቸዋል፡፡ ስለዚህ በጥምቀት የቤተክርስቲያን አባል መሆናችን ይረጋገጣል፡፡
​የጥምቀት ምሳሌ በብሉይ ኪዳን
 1. ግዝረት
ከፍ ብለን እንደገለጽነው፣ ግዝረትcየእግዚአብሔር ሕዝብ መለያ ምልክት ነበር፡፡ ያልተገረዘ ሁሉ የአብርሃም ልጅ አይባልም ነበር፡፡ ከሕዝቡም ተለይቶ እንዲጠፋ እግዚአብሔር አዝዞ ነበር (ዘፍ.17 ቁ. 14)፡፡እንደዚሁም ሁሉ ከውኃና ከመንፈስ ያልተወለደ ማለትም ያልተጠመቀ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አይገባም፡፡ ጽኑ ፍዳ ወዳለበት ገሃነም ይወርዳል እንጂ፡፡ምክንያቱም መንግሥተ ሰማይ ካልገባ ያለው ምርጫ ገሃነም መጣል ነውና (ዮሐ.3÷3-6)፡፡ ስለዚህ ግዝረት ለሕዝበ እግዚአብሔር ግዴታ እንደነበረ ሁሉ ጥምቀትም ለክርስቲያኖች ሊፈጽሙት የሚገባ ሃይማኖታዊ ግዴታ ነው፡፡ቈላ.2÷10-12 ‹‹በክርስቶስ ገዛሪነት የኃጢአትን ሕዋስ ሰንኮፍ ቆርጦ በመጣል ሰው ሠራሽ ያይደለ ግዝረትን የተገዘራችሁበት፤ በጥምቀት ከእሱ ጋር ተቀበራችሁ፣ ከሙታን ለይቶ ባስነሣው በእግዚአብሔር ረዳትነትም በሃይማኖት ከእሱ ጋር ለመኖር በእስዋ ተነሣችሁ›› ብሏል፡፡
 1. የእሥራኤል ባሕረ ኤርትራን ማቋረጥ
ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን እንዲህ ሲል ገልጦታል ‹‹ወንድሞች ሆይ ይህን ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ፡፡ አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች ነበሩ፡፡ ሁሉም በባሕር መካከል ተሻገሩ፡፡ሁሉም ሙሴ ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር ተጠመቁ›› (1ቆሮ.10÷1-12)፡፡ የሶርያ ንጉሥ ሠራዊት አለቃ ንዕማን ከለምጹ የነጻው በዮርዳኖስ ወንዝ ታጥቦ ነው፡፡በነቢይ በታዘዘው መሠረት በዮርዳኖስ ውኃ ሰባት ጊዜ ብቅጥልቅ በማለት ታጥቦ ሥጋው እንደገና እንደትንሽ ብላቴና ሥጋ ንጹሕም ሆኖ መመለሱን በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ እናገኘዋለን (2ነገ.5÷8-14)፡፡ እኛም ከኃጢአት ደዌ የምንነጻውና ያረጀው ሕይወታችን ሊታደስ የሚችለው በጥምቀት ነው፡፡ ስንጠመቅ የክርስቶስ ደም ከኃጢአታችን እንዳጠበን ማረጋገጣችን ነውና፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ሕዝቅኤል በመንፈስ ቅዱስ ተገልጦለት እንዲህ ብሏል ‹‹በውኃም አጠብሁሽ፤ ከደምሽም አጠራሁሽ፤ በዘይትም ቀባሁሽ›› (ሕዝ 16÷9)፡፡
ለምን በውኃ እንጠመቃለን
 1. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው በውኃ ነው እኛም እርሱን አብነት በማድረግ በውኃ ልንጠመቅ ይገባናል (ማቴ.3÷13-16)፡፡
 2. ጌታችን ለኒቆዲሞስ ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ ሰውከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም›› ስላለ እኛም የጌታን ትእዛዝ ለመፈጸም በውኃ እንጠመቃለን (ዮሐ.3÷5)፡፡
 3. ሐዋርያት ከጌታ በተማሩት መሠረት ያጠመቁት በውኃ ነው፡፡ጴጥሮስም መልሶ ‹‹እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እንዳይጠመቁ ውኃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማንነው? አለ›› (የሐዋ.10÷46ና 47)፡፡ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ አጠመቃቸውም (የሐዋ.8÷28)፡፡
 4. ውኃ የሰውነትን እድፍ እንደሚያጠራ ሁሉ እንዲሁም ጥምቀት የነፍስን እድፍ ያስወግዳል ያነጻል፡፡
 5. ውኃ መልክን ያሳያል እኛም በውኃ በመጠመቅ የሥላሴን ምሥጢር በዓይነ ኅሊናችን እናያለን፡፡
 6. ለንጊኖስ የተባለው ሐራዊ (ወታደር) የጌታን ቀኝ ጎን በጦር በወጋው ጊዜ ትኩስ ደምና ውኃ ባንድነት ፈሷል (ዮሐ. 19÷34)፡፡
ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎች
ሕዝ 36:25 “ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ እናንተም ትጠራላችሁ፥ ከርኵሰታችሁም ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ።”
ማቴ 3:5 “ያን ጊዜ ኢየሩሳሌም ይሁዳም ሁሉ በዮርዳኖስም ዙሪያ ያለ አገር ሁሉ ወደ እርሱ ይወጡ ነበር፤ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር።”
ማቴ 28:19 “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀመዛሙርት አድርጓቸው”
ማር 1:4 “ዮሐንስ በምድረ በዳ እያጠመቀ የንስሐንም ጥምቀት ለኃጢአት ስርየት እየሰበከ መጣ።”
ማር 16:16 “ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል።”
ሉቃ 3:21 “ሕዝቡም ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ኢየሱስ ደግሞ ተጠመቀ። ሲጸልይም ሰማይ ተከፈተ፥”
ዮሃ 3:5 “ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም።”
ዮሃ 3:22 “ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀመዛሙርቱ ጋር ወደ ይሁዳ አገር መጣ፥ በዚያም ከእነርሱ ጋር ተቀምጦ ያጠምቅ ነበር። ዮሐንስም ደግሞ በሳሌም አቅራቢያ በሄኖን በዚያ ብዙ ውኃ ነበርና ያጠምቅ ነበር፥
ሐዋ 2:38 “ጴጥሮስም፦ ንስሐግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።”
ሐዋ 8:38 “በመንገድም ሲሄዱ ወደ ውኃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም። እነሆ ውኃ፤ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው?  አለው። ፊልጶስም። በፍጹም ልብህ ብታምን፥ ተፈቅዶአል አለው። መልሶም። ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ አለ።ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፥ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ፥ አጠመቀውም።
ሐዋ 9:18 “ወዲያውም እንደ ቅርፊት ያለ ከዓይኑ ወደቀ፥ ያንጊዜም ደግሞ አየ፤ ተነሥቶም ተጠመቀ፥”
ሐዋ 10:47 “በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ፦ እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እንዳይጠመቁ ውኃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማንነው?  አለ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስምም ይጠመቁ ዘንድ አዘዛቸው። ከዚህ በኋላ ጥቂት ቀን እንዲቀመጥ ለመኑት።
ሐዋ 13:24 “ከመምጣቱ በፊት ዮሐንስ አስቀድሞ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የንስሐን ጥምቀት ሰብኮ ነበር።”
ሐዋ 18:8 “የምኵራብ አለቃ ቀርስጶስም ከቤተሰዎቹ ሁሉ ጋር በጌታ አመነ፥ ከቆሮንቶስ ሰዎችም ብዙ በሰሙ ጊዜ አምነው ተጠመቁ።”
ሐዋ 19:4 “ጳውሎስም፦ ዮሐንስስ ከእርሱ በኋላ በሚመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ ያምኑ ዘንድ ለሕዝብ እየተናገረ በንስሐ ጥምቀት አጠመቀ አላቸው።”
1ኛቆሮ 10:2 “ሁሉም ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር ተጠመቁ፤”
1ኛቆሮ 12:13 “አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና”
ገላ 3:26 “በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤ ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና።
ኤፌ 4:5 “አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት”
ሮሜ 6:3 “ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደተጠመቅን አታውቁምን?”
ምስጢረ ሜሮን
ሜሮን ማለት ቅዱስ ቅብዕ ነው፡፡ ሜሮን ቃሉ ግሪክ ሲሆን ትርጉሙም ቅብዕ ማለት ነው፡፡ ሜሮን ከጥምቀት በሁዋላ የሚፈጸም ነው፡፡ይህም ማለት ተጠማቂው ሰው ጥምቀት ከተፈጸመለት በሁዋላ ሳይውል ሳያድር ወዲያውኑ ጥምቀቱ እንደተቀበለ ሜሮን ይቀበላል ሜሮን ሲቀባም ከመንፈስ ቅዱስ መወለዱ ይረጋገጥለታል፡፡ ተጠማቂው ተጠምቆ ሜሮን መቀባቱ መንፈስ ቅዱስን መቀበሉን ያመለክታል፡፡ 
ምስጢረ ሜሮን ለምን ከጥምቀት ቀጥሎ እንዲፈጸም ይደረጋል?
ምስጢረ ሜሮን ከምስጢረ ጥምቀት ጋር ተያይዞ እንዲፈጸም የሚደረገው ተጠማቂው ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ መወለዱን ለማረጋገጥ ነው፡፡እንደዚሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሓንስ እጅ ተጠምቆ ወዲያው ከውኃ ሲወጣ መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ርግብ ማለት በርግብ ተመስሎ ከራሱ ላይ ማረፉ ማቴ 3:16 ዮሐ 1:32 ሜሮን ከጥምቀት ቀጥሎ ወዲያው መፈጸም ያለበት መሆኑን ያመለክታል ስለዚህ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሥርዓት መሠረት ምስጢረ ጥምቀት ምስጢረ ሜሮን ምስጢረ ቁርባን ያለመለያየት በተከታታይ በአንድ ቀን የሚፈጸሙ ምስጢራት ናቸው፡፡ ይኽውም ተጠማቂው ሰው በካህኑ እጅ እንደ ተጠመቀ ወዲያው ሜሮን ይቀባል ሳይውል ሳያድርም ቅዱስ ቁርባን ይቀበላል ማለት ነው፡፡ይህ ቅዱስ ሥርዓት ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ሲያያዝ የመጣ ነውና ሊለውጡት አይገባም፡፡ 
በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም በውኃ ተጠመቆ ወዲያው ሜሮን መቀባት መንፈስ ቅዱስን የመቀበል ምልክት መሆኑን በርከት ያሉ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት በየድርሳናቸው አረጋግጠዋል፡፡በጥምቀት ጊዜ ቅብዓ ሜሮን መቀባታችንን አስመልክቶ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ሲጽፍ 1ኛዮሐ 2:20 “እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ።” 
1ኛዮሐ 2:27 “እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ።”
የምስጢረ ሜሮን ምሳሌ የተጀመረው መቼ ነው? 
ዘጸ 30:22-  25 “ብርጕድም አምስት መቶ ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን፥ የወይራ ዘይትም አንድ የኢን መስፈሪያ ትወስዳለህ። በቀማሚም ብልሃት እንደ ተሠራ ቅመም፥ የተቀደሰ የቅብዓት ዘይት ታደርገዋለህ የተቀደሰ የቅብዓት ዘይት ይሆናል።”
በዘመነ ብሉይ የተቀደሰው ቅብዕ ለምን አገልግሎት ይውል ነበር? 
1ኛ/ አሮንና ልጆቹ ቅብዓ ቅዱስ ተቀብተው ስልጣነ ክህነትን ተቀብለዋል (ተክነዋል) 
2ኛ/ በደብተራ ኦሪት (በአገልግሎት ድንኮን) ውስጥ ለእግዚአብሔር አገልግሎት የሚውሉ የቤተመቅደስ ንዋያት (ዕቃዎች) በሙሉ በተቀደሰው ቅብእ ተቀብተው ንዋያተ ቅዱሳት ተብለው ለመንፈሳዊ አገልግሎት ይውሉ ነበር 
3ኛ/ የእስራኤል ነገሥታትና ካህናት የተቀደሰውን ቅብዕ (ዘይት) እየተቀቡ ነገሥታቱ ሥልጣነ መንግሥትን እጅ ሲያደርጉ ካህናቱ ደግኖ ክህነትን ይቀበሉት ነበር (1ኛሳሙ 10:1 1ኛነገሥ 19:15-21 ዘሌ 8:12)
ሜሮን ለምን ለምን አገልግሎት ይውላል? 
1ኛ/ በቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ሥጋና ደም ማቅረቢያ ይሆኑ ዘንድ አዳዲስ ዕቃዎች ማለት ጻሕል ጽዋ ጽርፈመስቀል መሶበወርቅ በጸሎት ሜሮን ተቀብተው ይከብራሉ 
2ኛ/ አዲስ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ታንጾ ሲያበቃለት በጸሎት ተባርኮ ቅብዓ ሜሮን ይቀባል 
3ኛ/ አዲስ ታቦትና አዲስ መንበረታቦት ቅብዓተሜሮን ተቀብተው ይከብራሉ 
4ኛ/ ሜሮን የጸጋን ልጅነት የሚያሰጥ ምስጢር ስለሆነ በጥምቀት ጊዜ {በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም} የተጠመቁ ምእመናን ወዲያው ሜሮን ሲቀቡ መንፈስ ቅዱስ ያድርባቸዋል።
የክርስትና አባት ወይም እናት አገልግሎት ምንድን ነው?
የክርስትና አባት እናት ለተጠመቁት ሰዎች የሃይማኖት ወላጆች ናቸው ስለዚህ በጥምቀት ክርስትና ያነሱአቸውን የሃይማኖት ልጆቻቸው ስለሆኑ የማሳደግና ትምህርተ ሃይማኖትን የማስተማር ኃላፊነት አለባቸው።
ምሥጢረ ቁርባን
 • የቃሉ ትርጉም
ቊርባን ቃሉ የሱርስትና የዓረብ ሲሆን ትርጉሙም በቁሙ መንፈሳዊ አምኃ፣ መሥዋዕት፣ መባዕ፣ ለአምላክ የሚቀርብ፣ የሚሰጥ ገንዘብ ማለት ነው፡፡ቃሉን በምልዓት ስንመለከተው ሰው ለአምላኩ የሚያቀርበውን ነገር ሁሉ የሚያካትት ሲሆን በዚህ ርዕሳችን የምንመለከተው ግን ስለአማናዊው ቁርባን ወይም መሥዋዕት ስለ ምሥጢረ ቁርባን ነው፡፡ምሥጢረ ቊርባን ማለት ካህኑ ኀብስቱን በጻሕል ወይኑን፣ በጽዋዕ አድርጎ በጸሎተ ቅዳሴ በባረከው ጊዜ ኀብስቱ ተለውጦ ሥጋ መለኮት፣ ወይኑ ተለውጦ ደመ መለኮት የሚሆንበትና እኛም የዘላለም ሕይወትን ለማግኘት ይህንን የክርስቶስን ሥጋና ደም የምንቀበልበት ዓቢይ ምሥጢር ነው፡፡
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ለእኛ ‹‹እንካችሁ›› ብሎ ከመስጠቱ ቀደም ብሎ የአማናዊው መሥዋዕት የቅዱስ ቁርባንን (ምሥጢረ ቁርባን) ምሳሌ በዘመነ ብሉይ እናገኘዋለን፡፡ብሉይኪዳንለሐዲስኪዳንአምሳልመርገፍነውና፡፡
በብሉይ ኪዳን የምሥጢረ ቊርባን ምሳሌ
 1. መልከጸዴቅ “(ዘፍ. 14:6-10፤ዕብ.7:1-3 እና 7)”
‹‹ክህነቱ የወልደ እግዚአብሔር ምሳሌ ሆኖ ለዝንተዓለም ይኖራል›› ተብሎ የተነገረለት የሰላም ንጉሥ መልከጸዴቅ በዘመነ ብሉይ ከቀደምት አበው ሁሉ ለየት ብሎ በቀራንዮ ኮረብታ ላይ ከእርሱ በፊትም ሆነ ከእርሱ በኋላ ያሉት አባቶች ያቀርቡት እንደነበረው የደም መሥዋዕት ሳይሆን በኀብስትና  በወይን ይሠዋ ነበር፡፡አበ ብዙኀን ተብሎ የሚጠራው አብርሃም ኮሎዶጎሞርንና ከእርሱ ጋራ የነበሩትን ነገሥታት ወግቶ ሲመለስ ይኸው የሳሌም ንጉሥ መልከ ጼዴቅ ኀብስትና ወይን ይዞ ተቀብሎታል፡፡የመልከጸዴቅ ኀብስተ አኰቴት ጽዋዐ በረከት የሥጋ ወደሙ ምሳሌ ሲሆን መልከ ጸዴቅ ደግሞ የልዑለ ባሕርይ የጌታችንና የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡
 1. የፋሲካው በግ (ዘጸ.12÷1-25)
እስራኤል በምድረ ግብፅ ለ43ዐ ዘመን ያህል በባርነት ሲማቅቁ ከኖሩ በኋላ በልዑል እግዚአብሔር ቸርነት በነቢዩ ሙሴ መሪነት ምድረ ግብፅን ለቀው ከመውጣታቸው በፊት ከሞተበኵር ይድኑ ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ አላቸው፡- … ይህ ወር የወሮች መጀመሪያ ይሁንላችሁ፡፡ የዓመቱም መጀመሪያ ወር ይሁንላችሁ፡፡ በዚህ ወር በአሥረኛው ቀን ሰው ሁሉ ለአባቱ ቤት አንድ ጠቦት ይውሰድ…የእናንተ ጠቦት ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ተባት ይሁን… በዚህም ወር እስከ አሥራ አራተኛ ቀን ድረስ ጠብቁት፡፡ የእስራኤልም ማኀበር ጉባኤ ሁሉ ሲመሽ ይረዱት፡፡ከደሙም ወስደው በሚበሉበት ቤት ሁለቱን መቃንና ጎበኑን ይቅቡት፡፡ በእሳት የተጠበሰውን ሥጋውንና ቂጣውን እንጀራ በዚያች ሌሊት ይብሉ፡፡ ከመራራ ቅጠል ጋር ይበሉታል፡፡ ጥሬውን በውኃም የበሰለውን አትብሉ፡፡ነገር ግን ከራሱ፣ ከጭኑ፣ ከሆድ ዕቃው ጋር በእሳት የተጠበሰውን ብሉት፡፡ ከእርሱም እስከጠዋት አንዳች አታስቀሩ፡፡ እስከጠዋትም የቀረውን በእሳት አቃጥሉት፡፡… እርሱ የእግዚአብሔር ፋሲካ ነው፡፡
እስራኤል ከሞተኵር የዳኑበት ተባት በግ ምሳሌነቱ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ብርሃን ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን በላከው ክታቡ ላይ ሲያረጋጋጥ ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዷልና ብሏል (1ቆሮ.6÷7)፡፡መጥምቀ መለኮት ዮሐንስም በዕለተዓርብ፣ ስለዓለሙ ድኀነት የተሠዋውን አማናዊ በግ ለደቀመዛሙርቱ ሲያስተዋውቅ እነሆ የዓለምን ኃጢአት የማያስወግድ የእግዚአብሔር በግ ሲል ገልጧል (ዮሐ.1÷29)፡፡
የዚህ ምሳሌነቱ ነጥብ የምታክል ነውር የሌለበት ማለትም ምክንያተ ኃጢአት የሌለበት ንጹሐባሕርይ ጌታ በቅንዓተ አይሁድ ታሥሮ፣ በመስቀል ላይ ራሱን ለመሠዋቱ ምሳሌ ነው፡፡በጉ የአንድ ዓመት ተባት ለመታረድ የደረሰ እንዲሆን እንደታዘዙ ሁሉ ጌታም ፍጹም የሠላሳ ዐመት ጐልማሳ ሳለ ለመሰቀሉ ምሳሌ ሲሆን በጉ በአሥረኛው ቀን ታሥሮ በአሥራ አራተኛው ቀን እንደተሠዋ ሁሉ ጌታም በአይሁዱ እጅ ተይዞ እንደ ወንጀለኛ ታሥሮ በዕለተ ዓርብ ለመሥዋዕት የመቅረቡ ምሳሌ ነው፡፡
 1. መና (ዘጸ16:33)
ሌላው ምሳሌ ለእስራኤል በምድረ በዳ የወረደላቸው መና ነው፡፡ የእስራኤል ልጀች ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት በሚጓዙበት ጊዜ በምድረ በዳምም የሚላስ የሚቀመስ ስላላገኙ ረሃብጸ ናባቸው፡፡በዚህ ጊዜ መሪያቸው ሙሴን አስጨነቁት፡፡ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ቢያመላክት መና ከደመና ወርዶላቸው ያንን ተመግበው ከረሃብ ድነዋል፡፡
ለእስራኤል በምድረ በዳ ከደመና የወረደላቸው መና የጌታ ሥጋና ደም ምሳሌ ሲሆን መናው የተገኘበት ደመና ደግሞ ጌታ ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍስዋ ነፍስ ነሥቶ ሰው የሆነባት የድንግል ማርያም ምሳሌ ነው፡፡
ጌታችን በመዋዕለ ትምህርቱ የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፡፡ አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ ሞቱም፡፡ ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ከሰማይ አሁን የወረደ እንጀራ ይህ ነው፡፡…እኔም ስለዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው በማለት መናው የሥጋውና የደሙ ምሳሌ መሆኑን አስተምሮል (ዮሐ.6÷49-51)፡፡
ምሥጢረ ቁርባን – መቼ ተጀመረ
ማቴ.26÷26-29 መሥዋዕተ ኦሪት አልፎ መሥዋዕተ ሐዲስ በመተካት ምሥጢረ ቁርባን የተጀመረው በምሴተ ሐሙስ ነው፡፡ ሐሙስ ምሽት በአልዓዛር ቤት ሥርዓተ ቁርባንን መሠረት፡፡ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ፡፡ ቆርሶም ለደቀመዛሙርቱ ሰጠና ‹‹እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው› አለ፡፡ ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው፡፡እንዲህም አለ ‹ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ ስለ ብዙዎች በኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው› አለ፡፡››
በምሴተ ሐሙስ ልዑለ ባሕርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ኀብስቱን፣ ወይኑን ባርኮ ቀድሶ አክብሮ ለውጦ ፍጹም ሥጋውና ደሙ አድርጐ ለደቀመዛውርቱ እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ፡፡ ጽዋውንም ኣንሥቶ…ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ ስለብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው፡፡በማለት በዕለተ ዓርብ በመልዕልተ መስቀል የሚፈተት ሥጋውንና የሚፈስ ደሙን ሰጥቷቸዋል (ማቴ.26÷26-29)፡፡
ይህን መሠረት በማድረግ ዛሬ ምካህናት ኀብስቱንና ወይኑን በጸሎተ ቅዳሴ አመስግነው ሲባርኩት ኀብስቱ ተለውጦ ሥጋ መለኮት፣ ወይኑም ተለውጦ ደመ መለኮት ይሆናል፡፡
ይህ ኀብስት የፈጣሪያችን የአማኑኤል ሥጋ ነው፡፡ይህ ጽዋዕ የአማኑኤል ደም ነው ብለው ሲያቀብሉን የጌታ ሥጋና ደም ነው ማለት እንደምን ይቻላል? ሳንል በእውነት አምነን የአምላካችንን ቃል መሠረት አድርገን እንቀበላለን፡፡ ባለቤቱ ራሱ ኀብስቱን ሥጋዬ ነው፣ ወይኑንም “ደሜ ነው” ብሎ ለሐዋርያቱ አቀብሏልና፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ትምህርቱ ይህን አስመልክቶ ሲያስተምር “ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፡፡ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፡፡” እኔም ስለዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው ብሏል፡፡ (ዮሐ.6÷51)፡፡ዳሩ ግን ልባቸው በጥርጥር ማዕበል የተመታ አይሁድ ይህ የጌታ ትምህርት አልዋጥ ብሏቸው በምጸት “ይህ ሰው ሥጋውን ልንበላ ይሰጠን ዘንድ እንዴት ይችላል” በማለት ትምህርቱን ለማስተባበል ሞከሩ (ዮሐ.6÷52)፡፡
ዛሬም ቢሆን ተረፈ አይሁድ የጌታን ቃል ለማስተባበል የማይቆፍሩት የክህደት ጉድጓድ፣ የማይፈነቅሉት የሐሰት ድንጋይ የለም፡፡ ይህ መሆኑ ግን ሊያስደንቀን አይገባም፡፡ሁሉን ቻይ ጌታ፣ ዘመን በማይሽረውና በማይለውጠው አማናዊ ቃሉ አስቀድሞ በአጽንዖት እንዲህ ብሎ አስገንዝቦናል፡- እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ሕይወት የላችሁም (ዮሐ. 6÷53)፡፡
ለዚህ ቅዱስ ቃል ተጻራሪ ሆኖ ሥጋ ወደሙ መታሰቢያ እንጂ አማናዊ (እውነተኛ የክርስቶስ ሥጋና ደም) አይደለም ብሎ የሚያስተምር የክርስቶስ ጠላት ነው፡፡ዘላለማዊ ሕይወትን ለማግኘትና የክርስቶስን መንግሥት ለመውረስ የጌታን ሥና ደም መቀበል ግዴታ መሆኑን ጌታችን እንዲህ ሲል አረጋግጦልናል፡- ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፡፡ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ፡፡ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና (ዮሐ.6÷54ና 55)፡፡
ጌታችን ራሱ በቃሉ ላስተማረውና ላረጋገጠው ዐቢይ ትምህርት ጀርባውን ሰጥቶ የጌታችንን ትዕዛዝ ጥሎ ሥጋውና ደሙን መታሰቢያ ወይም ምሳሌ ነው፤ ለድኀነት አስፈላጊ አይደለም የሚል ሁሉ ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት የወጣ ነው፡፡ ቁጥሩም የጌታን ትምህርት ይቃወሙ ከነበሩት ከአይሁድ እንጂ ከክርስቶሳውያን አይደለም፡፡ ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና ጌታ ኢየሱ ስአልፎ በተሰጠባት በዚያች ሌሊት እንጀራን አንሥቶ አመሰገነ ቆርሶም… ‹እንካችሁ ብሎ ይህ ስለእናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት› አለ፡፡ እንደዚሁም ከራት በኋላ ጽዋውን ደግሞ አንሥቶ ‹ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው፡፡ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት፡፡ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና› ብሏል (1ቆሮ.11÷23-26)፡፡
ቅዱስ ቁርባን መታሰቢያ ወይም ምሳሌ እንጂ እውነተኛ የጌታ ሥጋና ደም አይደለም ብለው የሚክዱ ክፍሎች ለክህደታቸው አስረጅ አድርገው ለማቅረብ ከሚጠቃቅሷቸው አንዱ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት የሚለው ቃል ነው፡፡ ዳሩ ግን ቃሉን በአንክሮ ለሚያጤነው ሰው ሁሉ የእነርሱን ስሕተታዊ ትምህርት የሚደግፍ ወይም የሚያንጸባርቅ አለመሆኑን ይገነዘባል፡፡ይኸውም ስናስተውለው ሥጋውና ደሙን ስንቀበል መድኃኒታችን ለእኛ ድኀነት ሲል ከቤተልሔም ዋሻ እስከቀራንዮ ኮረብታ የደረሰበትን ጸዋት ወመከራ፣ ሕማሙን፣ ሞቱን፣ ትንሣኤውን፣ ዕርገቱንና ዳግም ምጽአቱን እንድናስብና እንድናስተውል ለማስረዳት ነው፡፡ ትክክለኛ የቃሉ ትርጉም ከላይ የተገለጸው ለመሆኑ የሐዋርያውን ትምህርት በድጋሚ ብንመለከት …በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት፡፡ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁ በማለት ያረጋግጥልናል፡፡
ሥጋውን ደሙን በምንቀበልበት ጊዜ ሁሉ የጌታችንን መከራውን ሕማሙንና ሞቱን እናዘክራለን፡፡ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ የሰጠንን የአምላካችን ፍቅር በኀሊናችን ሰሌዳ ተሥሎ እስከ ዕለተ ሞታችን እንዲኖር ቅዱስ ቁርባን ታላቅ ማኀተም መሆኑን ማስገንዘቡ ነው፡፡ በቅዳሴአችንም ንዜኑ ሞተከ እግዚኦ ወትንሣኤከ ቅድስተ፣ አቤቱ ሞትህንና ቅድስት ትንሣኤህን እናገራለን የምንለውም ይኸንኑ ቃል መሠረት አድርገን ነው፡፡ በአጭር ቃል ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት የሚለው መከራዬን ሕማሜን ቤዛነቴን እያሰባችሁ፣ አምናችሁ ሥጋዬንና ደሜን ተቀበሉ ማለቱ ነው፡፡
ምስጢረ ክህነት
ክህነት ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የተቀደሰ አገልግሎት ነው።የክህነት አገልግሎት የተጀመረው በላይ በሰማይነው።
“አራቱም እንስሶች እያንዳንዳቸው ስድስት ክንፎች አሉአቸው፥ በዙሪያቸውና በውስጣቸውም ዓይኖች ሞልተውባቸዋል፤ ቅዱስ፥ቅዱስ፥ቅዱስ፥ የነበረውና ያለ የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ እያሉ ቀንና ሌሊት አያርፉም። …ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች በዙፋን ላይ በተቀመጠው ፊት ወድቀው፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም በሕይወት ለሚኖረው እየሰገዱ። ጌታችንና አምላካችን ሆይ፥ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል እያሉ በዙፋኑ ፊት አክሊላቸውን ያኖራሉ።”ራዕ 4:8-11 
በምድር ላይ የመጀመሪያው የእግዚአብሔር ካህን መልከ ጸዴቅ የተባለው ሰው ነው። 
“የሳሌም ንጉሥ መልከጼዴቅም እንጀራንና የወይን ጠጅን አወጣ እርሱም የልዑል እግዚአብሔር ካህን ነበረ።” ዘፍ 14:18 
በኃላ ዘመን በሥጋ ለተገለጠው ለማይሻረው ንጉሥና ለእውነተኛው ካህን ለክርስቶስ ምሳሌ እንደ ነበር መጻሕፍት ይመሰክራሉ። 
“እንደ መልከጼዴቅ ሥርዓት አንተ ለዘላለም ካህንነህ” መዝ 110:4 
“በዚያም ኢየሱስ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ሊቀካህናት የሆነው፥ ስለ እኛ ቀዳሚ ሆኖ ገባ።” 
ኦሪት ከተሰጠች በኃላ የመጀመሪያው ካህን ሆኖ የተሾመው አሮን ነው ዕብ 6:20 
“አንተም ወንድምህን አሮንን ከእርሱም ጋር ልጆቹን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለይተህ ካህናት ይሆኑል ኝዘንድ ወደ አንተ አቅርብ አሮንን የአሮንንም ልጆች፥ ናዳብን አብዮድንም አልዓዛርንም ኢታምርንም፥ አቅርብ።”ዘጸ 28:1 
ክህነት በሐዲስ ኪዳን ዘመን 
እውነተኛውን (አማናዊውን) ክህነት የተመሠረተው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ 
“ቅዱስና ያለተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ፥ እንደዚህ ያለ ሊቀካህናት… ነው”ዕብ 7:26-28 
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳን ሐዋርያትን ተከታዮቹ እንዲሆኑ ከመረጣቸው በኃላ ሰፊ ስላጣን ሰጥቶአቸዋል:- 
1ኛ.”በምድር የምታስሩት ኹሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል በምድር የምትፈቱት ኹሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል”ማቴ 18:16 
2ኛ.”ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው።”ዮሃ 20:23 
3ኛ.”አሥራ ሁለቱን ደቀመዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ፥ እንዲያወጡአቸው በርኩሳን መናፍስት ላይ ደዌንና ሕማምንም ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣን ሰጣቸው።”ማቴ 10:1 
ሐዋርያትም ከጌታችን የተቀበሉትን ሥልጣነክህነት በአንብሮተ እድ ለተከታዮቻቸው አስተላልፈዋል። 
“ወንድሞች ሆይ፥ በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብም የሞላባቸውን ሰባት ሰዎች ከእናንተ ምረጡ፥ ለዚህም ጉዳይ እንሾማቸዋለን፤ እኛ ግን ለጸሎትና ቃሉን ለማገልገል እንተጋለን። ይህም ቃል ሕዝብን ሁሉ ደስ አሰኛቸው፤ እምነትና መንፈስ ቅዱስም የሞላበትን ሰው እስጢፋኖስን ፊልጶስንም ጵሮኮሮስንም ኒቃሮናንም ጢሞናንም ጳርሜናንም ወደ ይሁዲነት ገብቶ የነበረውን የአንጾኪያውን ኒቆላዎስንም መረጡ። በሐዋርያትም ፊት አቆሙአቸው፥ ከጸለዩም በኋላ እጃቸውን ጫኑባቸው። ሐዋ 6:2-6 
በዚሁ በሐዋርያት ሥርዓት መሠረት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ኢጲስ ቆጶሳትን ቀሳውስትን ዲያቆናትን በአንብሮተ እድ ትሾማቸዋለች።
ምስጢረ ተክሊል
ሕጋዊ ጋብቻ የተመሠረተው በእግዚአብሔር ቡራኬ:: ሰው (አዳም) ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለምና የምትረዳው ጓደኛእንፍጠርለት” ብሎ እግዚአብሔር ሔዋንን አካል ፈጠራት:: 
ዘፍ 2:18 “እግዚአብሔር አምላክም አለ፦ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት።” 
አዳምም ከአካሉ የተፈጠረችውን ሰው አይቶ እንዲህ አለ 
“አዳምም አለ፦ይህች አጥንት ከአጥንቴናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል። ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ በሚስቱም ይጣበቃል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።” ዘፍ 2:23 
“እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም  አላቸው፦ ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው።” ዘፍ 1:26 
ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ ተገልጦ ወንጌል መንግሥትን እየሰበከ በዓለም ላይ በሚዘዋወርበት ወቅት ጋብቻ እጅግ የተቀደሰ መሆኑን በምስጢር ጋብቻ እግዚአብሔር አንድ አካል ያደረጋቸውን ባልና ሚስት ሰው ሊለያያቸው እንደማይገባ አረጋግጣል 
“ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፥ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ የሚለውን ቃል አላነበባችሁምን?  ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደፊት ሁለት አይደሉም። እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው።” ማቴ 19:3 
በተጨማሪም ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሕገ ቤተክርስቲያን የሚፈጸመው ጋብቻ ቅዱስ መሆኑን ለማረጋገጥ በሕግ የተጋቡትን ለመባረክ በቃና ዘገሊላ ከተማ በተደረገው ሠርግ ላይ ተገኝቶል። 
“በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ፥ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች፤ ኢየሱስም ደግሞ ደቀመዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ።” ዮሐ 2:1-11 
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በቤተክርስቲያን ሥርዓት ጋብቻቸውን የፈጸሙ ተጋቢዎች ጋብቻቸው የተቀደሰ መሆንን ካረጋገጠ በኃላ በተቀደሰ ጋብቻ አንድ የሆኑ ተጋቢዎች በመንፈሳዊ ሕይወት የተሳሰሩ አንድ አካል  መሆናችውገልጻል 
“የገዛ ሚስቱን የወደደ ራሱን ይወዳል ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና”። ኤፌ 5:21-33 
ሲል ባልና ሚስት አንድ አካል መሆናቸውን መስክሮል። በሌላ መልእክቱም በሕገ ቤተክርስቲያን የተፈጸመ ጋብቻ ንጹሕና ክቡር መሆኑን አስተምሮል 
እጅግ ጠቃሚ ምክር 
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከዚህ በታች የሰጠውን ምክር መመሪያ መከተል ይገባል። 
ኤፌ 5:26 33 “ባሎች ሆይ፥ ክርስቶስ ደግሞ ቤተክርስቲያንን እንደወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነችን ቤተክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ ፈለገ። እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፥ ነገር ግን የአካሉ ብልቶች ስለሆንን፥ ክርስቶስ ደግሞ ለቤተክርስቲያን እንዳደረገላት፥ ይመግበዋል ይከባከበውማል። ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ። ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፥ እኔ ግን ይህን ስለክርስቶስና ስለቤተክርስቲያን እላለሁ። ሆኖም ከእናንተ ደግሞ እያንዳንዱ የገዛ ሚስቱን እንዲህ እንደራሱ አድርጎ ይውደዳት፥ ሚስቱም ባልዋን ትፍራ።”
 
ምሥጢረ ንስሐ
ንስሐ የግዕዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙ ጸጸት ነው፡፡ ጸጸትነቱ ሰው በሠራው ኃጢአት ተጸጽቶ ኃጢአቱ ይሰረይለት ዘንድ እግዚአብሔርን በሐዘን በለቅሶ ሲለምን እንጂ የጐልማሳ ሚስት ሳልቀማ፣ የሰው ገንዘብ ሳልሰርቅ ቀረሁ …  በማለት የሚጸጸተው ጸጸት አይደለም፡፡
ንስሐ ለተጠመቁ ሰዎች ከጥምቀት በኋላ የተሰጠች ሀብት ናት። በጥምቀት ከእግዚአብሔር የምትገኝ የልጅነት ሁለተኛ ማዕረግ ናት፡፡በሃይማኖት ገንዘብ ያደረግነው የመንግሥተ ሰማያት አራቦን ማለትም መግዣ ናት። ንስሐ ለሚሿት ሰዎች የተከፈተች የይቅርታ በር ናት፡፡ በንስሐ በርነት ከፈጣሪ ወደ ሚገኝ ቸርነት እንቀርባለን። 
ምሥጢረ ንስሐ ማለት አንድ ሰው ከጥምቀት በኋላ የፈጸመውን ጥፋት አውቆ ሁለተኛ ጥፋቱን ላለመድገም ወስኖ በእግዚአብሔርና በካህኑ ፊት ተንበርክኮ ከልቡ ተጸጽቶ ኃጢአቱን በመናዘዝ ከኃጢአቱ እስራት የሚፈታበትና ከእግዚአብሔር ይቅርታን የሚያገኝበት ታላቅ የይቅርታ ምሥጢር ነው።
ንስሐ በሦስት ነገሮች ይፈጸማል
እንግዲህ ንስሐ ገብተን፣ የኃጢአትን ስርየት አግኝተን፣ ከሰውና ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀን በጽድቅ ጎዳና ለመራመድና በደህንነት ጸጋ ለመኖር እንድንችል ቢያንስ ሦስት ነገሮችን መፈጸም አለብን። የመጀመሪያው የንስሐ ሃዘን ማለትም እውነተኛና ልባዊ ጸጸት በቅድሚያ እንዲኖረን ያስፈልጋል። ሁለተኛው ኑዛዜ ሲሆን ሦስተኛው ደግሞ ስለኃጢአታችን የሚሰጠንን የንስሐ ቅጣት የሚያመለክት የቀኖናን ሥርዓት መፈጸምና እንደዚሁም በካህኑ በኩል የምናገኘው የፍትሐት ጸጋ ነው። 
የንስሐ ሃዘን /ጸጸት/
ንስሐ የሚገባ ሰው በመጀመሪያ ኃጢአቱን እያስታወሰሰውና ፈጣሪውን መበደሉን እያሰበ የሚያደርገው ሃዘን ወደ ንስሐ የሚወስድ እውነተኛ ሃዘን ስለሆነ ሃዘኑን እግዚአብሔር ይቆጥርለታል። «የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፣ መጽናናትን ያገኛሉና» /ማቴ. ፭፥፬/ የተባለው የራሳቸውንና የሌላውን ኃጢአት እያሰቡ የሚያዝኑትን ተነሳሒያን ያመለክታል። ንስሐ ማለት ጸጸትን የሚያመለክት ቢሆንም ቁጭትና ቅንዓት የሞላበት የዓለማዊ ጸጸት ሳይሆን እውነተኛው ሃዘንና መመለስ መሆኑን በቅድሚያ መገንዘብ ይኖርብናል። ስለ እውነተኛው ሃዘን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደሚከተለው ያስተምረናል። «አሁን ስለ ንስሐ ስላዘናችሁ ደስብሎኛል እንጂ ስላዘናችሁ አይደለም፤ በምንም ከእኛ የተነሳ እንዳትጎዱ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ አዝናችኋልና። እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ሃዘን ጸጸት የሌለበትን፣ ወደ መዳን የሚያደርሰውን ንስሐ ያደርጋልና፤ የዓለም ሃዘን ግን ሞትን ያመጣል።» /፪ኛቆሮ. ፯፥፱-፲/።እንግዲህ እውነተኛውን ሃዘን ከእንባ ጋር አድርጎ በንጹህ ልቦናና ጸሎት ለእግዚአብሔር በማቅረብ ተነሳሒው እንደገና ላለመበደል መወሰን ይኖርበታል። ውሳኔውንም ለመፈጸም የሚያስችለውን የመንፈስ ቅዱስን ረድኤት በማግኘት ሁልጊዜ ተግቶ መጸለይ አለበት።
ኑዛዜ
ከዚህ ቀጥሎ ተነሳሒው ኃጢአቱን ሥልጣነ ክህነት ላለው ካህን ይናዘዛል። ኑዛዜ ማድረግ በቅዱሳት መጻሕፍት የታዘዘ ነው። «ከነዚህ ነገሮች በአንዲቱ በደለኛ ቢሆን፥ የሠራውን ኃጢአት ይናዘዛል። ስለሠራው ኃጢአት ለእግዚአብሔር የበደልን መስዋዕት ያመጣል፤ … ካህኑ ስለኃጢአቱ ያስተሰርይለታል። … እርሱም ይቅር ይባላል።» /ዘሌ. ፭፥፭-፮፣፲/።ከዚህ ጥቅስ የኃጢአትን ስርየት ለማግኘት ለካህን መናዘዝ እንደሚገባ እንማራለን። ስለዚህ ኃጢአታችንን ለአናዛዡ ካህን ከበደሉ ዓይነትና ሁኔታ ጋር ማስረዳት ይገባናል። ስንናዘዝም ከእንባና ከጸጸት ጋር ሆነን ከካህኑ ጋር አብሮ እግዚአብሔር እንደሚሰማን አምነን በእውነት መናገር ያስፈልገናል። በሽታውን የሰወረ መድኃኒት አያገኝም ተብሏልና ለነፍስ ቁስል ሐኪም ለሆነው ለካህኑ ኃጢአታችንን ከሰወርን ለነፍስ የሚሆነውን ፈውስ ለማግኘት አንችልም። 
«ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል።» /ምሳ. ፳፰፥፲፫/ ተብሎ ተጽፏልና ስለዚህ እርስበርሳችን በቂም በቀል ሳንያያዝ የበደልነውን እየካስን፣ የበደለንን ይቅር እያልን ብንናዘዝና የሰማዩን አባታችን በጸሎት ብንጠይቀው ምሕረትና ፈውስን ይሰጠናል። ነገር ግን እኛ ማንንም አልበደልንም ኃጢአትም የለብንም ብንል እግዚአብሔርን ሐሰተኛ ማድረጋችን ስለሆነ እንጠንቀቅ። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ እንዳለው «ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፣ እውነትም በኛ ውስጥ የለም። በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው። ኃጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን ቃሉም በኛ ውስጥ የለም።» /፩ኛዮሐ. ፩፥፰-፲/።
ፍትሐትና ቀኖና
እንግዲህ ተነሳሒው በእውነት ኃጢአቱን አውቆ ለካህኑና በስውር ለሚያየውና ለሚሰማው ለእግዚአብሔር ከተናዘዘ በኋላ ከካህኑ ሁለት ነገሮችን ይቀበላል። እነሱም ፍትሐትና ቀኖና ናቸው። ፍትሐት ማለት ከኃጢአት እስራት የሚፈታበት ነው። ቀኖና ማለት ለኃጢአቱ ምክርና ተግሳጽ የሚያገኝበትን፣ በንስሐ ቅጣት የሚቀበልበትን፣ ካሳ መቀጫ የሚከፍልበትን ሁኔታ የሚያመለክት ነው።  ፍትሐት የሚሰጠው ካህኑ የንስሐውን ጸሎት ሥነ ሥርዓት ከፈጸመ በኋላ «እግዚአብሔር ይፍታህ» ሲል ተናዛዡ ወይም ተነሳሒው ከኃጢአቱ እስራት ይፈታል። ከእግዚአብሔርም ይቅርታን ያገኛል። ንስሐ የገባው ሰው ከኃጢአቱ ተፈትቶ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቁ ታላቅ ጸጋ ነው። 
ለኃጢአታችን ስርየት እንደዚህ ዓይነቱን ቀላል መንገድ ስላዘጋጅልን ክርስቶስን ማመስገን ይገባናል። ብዙ ሳንደክም ወንድማችንና አባታችን ለሆነው ካህን በመናዘዝና ምክሩንና ቀኖናውን በመቀበል በኃጢአት ከሚመጣብን የዘላለም ቅጣት መዳናችን እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነው። ይህንንም ሥልጣን ለካህናት የሰጣቸው እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ከላይ ተገልጿል። እንግዲህ ፍትሐት የተቀበለ ተነሳሒ ሁሉ ኃጢአቱ የተሰረየለት ስለሆነ ከዘላለም የሞት ቅጣት ነፃ ይሆናል። 
ምንም እንኳን ተነሳሒው ከዘላለም የሞት ቅጣት ቢድንም ዓይነቱና መጠኑ የተለያየ ጊዜያዊ ቅጣት መቀበል ይገባዋል። ይህም የንስሐ ቀኖና ይባላል። ጊዜያዊ ቅጣት ወይም ቀኖና ያስፈለገበት ምክንያት ኃጢአትን መሥራት ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ለተነሳሒው ለማሳሰብና ዳግመኛ እንዳይበድል ለማስጠንቀቅ እንዲሁም ደግሞ ሥጋን በመገሰጽ ለነፍሱ የጽድቅንና የደህንነትን ጎዳና ለማስተማር ነው። 
ምንጊዜም ፍቅሩና ምሕረቱ ከኛ ጋር ቢሆንም እግዚአብሔር በአባትነቱ ላጠፋነው ጥፋት በጊዜያዊ ቅጣት ይቀጣናል። መልካም አባት ልጁን እንደሚገስጽና እንደሚቀጣ ዓይነት ይቀጣናል። /ዕብ. ፲፪፥፭-፲፩/።እንግዲህ ያልተገራ ልቦና ካለን ለእግዚአብሔር በማስገዛት የኃጢአታችንንም ቅጣት በደስታ በመቀበል የበለጠ ጸጋና ረድኤትን እናገኛለን። «በዚያን ጊዜ ያልተገረዘው ልባቸው ቢዋረድ፣ የኃጢአታቸውንም ቅጣት ቢቀበሉ እኔ ለያዕቆብ የማልኩትን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ … ምድሪቱንም አስባለሁ።» ተብሎ ተጽፏልና /ዘሌ. ፳፮፥፵፩-፵፪/።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በዝሙት የተከሰሰውን የቆሮንቶሱን ሰው በሥጋው እንዲቀጠ ፍፈርዶበታል። «እንደዚህ በሠራው ላይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሁን ፈርጄበታለሁ … መንፈሱ በጌታ በኢየሱስ ቀን ትድንዘንድ እንደዚህ ያለው ሰው ለሥጋው ጥፋት ለሰይጣን እንዲሰጥ ፍርዴ ነው።» /፩ኛቆሮ. ፭፥፩-፭/።ይኸው ሐዋርያ ለሁለተኛ ጊዜ በጻፈው መልእክቱ ከላይ የተጠቀሰው የቆሮንቶስ ሰው ቅጣቱ የሚበቃው ስለሆነ ማኅበረ ክርስቲያኑ ይቅርታ እንዲያደርጉለት ጠይቋል። 
«እንደዚህ ላለ ሰው ይህ ከናንተ የምትበዙት የቀጣችሁት ቅጣት ይበቃዋልና እንደዚህ ያለው ከልክ በሚበዛ ሃዘን እንዳይዋጥ ይልቅ ተመልሳችሁ ይቅር ማለትና ማጽናናት ይገባችኋል። ስለዚህ ፍቅርን እንድታጸኑ እለምናችኋለሁ፤ ስለዚህ ደግሞ ጽፌ ነበርና፤ … » /፪ኛቆሮ. ፪፥፮-፲፩/።እንግዲህ የሐዋርያውን ምክር ሰምተን ዛሬ የምንገኘው ክርስቲያኖችን በበደላችን ምክንያት ካህኑ የሚሰጠንን ምክርና ተግሳጽ አዳምጠን የንስሐውንም ቅጣት ማለትም ቀኖናውን ተቀብለን በደስታ ብንፈጽመው መንፈሳዊ ደህንነታችን ይጠበቃል። መንፈሳዊ ግዴታችንንም እንወጣለን። 
በቤተክርስቲያናችን ቀኖና የሚሰጠው እንደ ተነሳሒው የኃጢአት ዓይነትና ሁኔታ ታይቶ ነው። ካህኑ የተነሳሒውን የኑሮ ሁኔታና ያጋጠመውን ፈተና በማስመልከት ምክርና ትምህርት ይሰጠዋል። እንደ መልካም የነፍስ ሐኪምም እንደበሽታው ሁኔታ ካህኑ አስፈላጊውን የነፍስ መድኃኒት ይሰጠዋል። የቀኖና አሰጣጥ መንገዱና ዓይነቱ ብዙ ነው። ለአንዳንዱ ተነሳሒ የቃል ምክርና ተግሳጽ ብቻ የሚበቃው አለ። ለሌላው ጾም ብቻ ወይም ከስግደት ጋር ቀኖና ይሰጠዋል። ልዩ የንስሐ ጸሎት፣ ምጽዋት፣ ለተበደለው ወገን ካሳ መክፈል፣ ለችግረኞች አገልግሎት መስጠት አስፈላጊም ከሆነ ለተወሰነ ጊዜ ከቁርባን መለየት ወይም ልዩ ልዩ አስቸጋሪ ነገሮችን መፈጸም ወይም ለቤተክርስቲያን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ኑሮ የሚጠቅሙ የጉልበትም ሆነ የአዕምሮ ሥራ መሥራትና የመሳሰሉት ሁሉ ከቀኖና ቤተክርስቲያን ይቆጠራሉ። 
እንግዲህ የሚሰጠንን ቀኖና ሁሉ በደስታ ተቀብለን ብንፈጽመው ለነፍሳችንም ሆነ ለሥጋችንም የሚጠቅም ጸጋና በረከትን እናገኛለን። እንዲያውም «ሞት የማይገባውን ኃጢአት» ያደረጉትን ዘመዶቻችንና ባልንጀሮቻችን ሁሉ እያሰብን፣ በጸሎት እየማለድን እነርሱም ንስሐ እንዲገቡ እየመከርን በገዛ ፈቃዳችን ካህኑ ለራሳችን ከሰጠን ቀኖና በመጨመር ብንፈጽመው በኃጢአት ለተጎዱት እህቶችና ወንድሞች የእግዚአብሔርን ምሕረት እንደሚያስገኝላቸው አያጠራጥርም። እንደዚህ አድርጎ ስለባልንጀራው ደህንነት እግዚአብሔርን ለሚለምን ሰው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ እንዳለው «ሞትም የማይገባውን ኃጢአት ላደረጉ ሕይወትን ይሰጥለታል» /፩ኛዮሐ. ፭፥፲፮/።
​መዝ 32:5 “ኃጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ፥ በደሌንም አልሸፈንሁም ለእግዚአብሔር መተላለፌን እነግራለሁ” እንዳለ ቅዱስ ዳዊት
መዝ 50:1 “አቤቱ፥ እንደቸርነትህ መጠን ማረኝእንደምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ። ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፥ ከኃጢአቴም አንጻኝ እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፥ ኃጢአቴም ሁል ጊዜ በፊቴ ነውና ።አንተን ብቻ በደልሁ፥ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ፥ በነገርህም ትጸድቅ ዘንድ በፍርድህም ንጹሕ ትሆን ዘንድ። እነሆ፥ በዓመፃ ተፀነስሁ፥ እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ። እነሆ፥ እውነትን ወደድህ የማይታይ ስውር ጥበብን አስታወቅኸኝ። በሂሶጵ እርጨኝ፥ እነጻማለሁ እጠበኝ፥ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ። ሐሤትንና ደስታን አሰማኝ፥ የሰበርሃቸውም አጥንቶቼ ደስ ይላቸዋል። ከኃጢአቴ ፊትህን መልስ፥ በደሌንም ሁሉ ደምስስልኝ።
ንስሐ ስንት ክፍሎች አሉት?
1ኛ.ጥምቀት ክርስትና ከመስራትዋ በፊት የበደሉ ሰዎች በየጊዜው ወደ እግዚአብሔር እየተመለሱ ሲፈጽሙት የነበረውን የንስሐና የኑዛዜ ሥርዓት ነው።
ሕዝ 18:30 “የእስራኤል ቤት ሆይ ፥ስለዚህ እንደ መንገዱ በየሰዉ ሁሉ እፈርድባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር ንስሐ ግቡ ኃጢአትም ዕንቅፋት እንዳይሆንባችሁ ከኃጢአታችሁ ሁሉ ተመለሱ።”
ማቴ 3:1-6 “በዚያም ወራት መጥምቁ ዮሐንስ። መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ ብሎ በይሁዳ ምድረ በዳ እየሰበከ መጣ። ….ያንጊዜ ኢየሩሳሌም ይሁዳም ሁሉ በዮርዳኖስም ዙሪያ ያለ አገር ሁሉ ወደ እርሱ ይወጡ ነበር፤ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር።”
 
2ኛ.ጥምቀት ክርስትና ከተሠራች በኃላ እያንዳንዱ ክርስቲያን ከፈጸመው ኃጢአትና ከሠራው በደል በንስሐ ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ የሚፈጽመው የንስሐና የኑዛዜ ሥርዓት ነው።
 
ማቴ 4:17 “ኢየሱስ፦ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እያለ ይሰብክ ጀመር።”
ማቴ 8:13 “ኢየሱስም ሰምቶ። ሕመምተኞች እንጂ ባለጤናዎች ባለመድኃኒት አያስፈልጋቸውም… ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁምና አላቸው።”
ኢሳ 1:18 “ኑና እንዋቀስ ይላል እግዚአብሔር ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነጻለች እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች። “
በንስሐ የተመለሱትን ምእመናን ስለሠሩት ኃጢአት እንዲጾሙ እንዲጸልዩ እንዲሰግዱ ማዘዝ የሚችል ማነው?
የቅስና ሥልጣን ያለው ሰው ንስሐ መስጠት መናዘዝና ሥርየት ኃጢአት ማሰጠት ይችላል። ይህንን ስልጣን የሰጠው ጌታ ኢየሱስ ነው
ማቴ 18:18 “እውነት እላችኋለሁ፥ በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል።”
ሉቃ 5:14 “ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፥ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ስለመንጻትህ ሙሴ እንዳዘዘ መሥዋዕት አቅርብ አለው።”
ኢሳ 46:8 “ይህን አስቡና አልቅሱ ተላላፊዎች ሆይ፥ ንስሐግቡ፥ ልባችሁንም መልሱ።”
ሐዋ 2:38 “ጴጥሮስም፦ ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።”
2ኛጴጥ3:9 “እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ጸጸት የሌለበትን፥ ወደ መዳንም የሚያደርሰውን ንስሐ ያደርጋልና፤ የዓለም ኀዘን ግን ሞትን ያመጣል።”
ራዕ 2:18 “እንግዲህ ንስሐ ግባ፤ አለዚያ ፈጥኜ እመጣብሃለሁ፥ በአፌም ሰይፍ እዋጋቸዋለሁ።”
 
ምስጢረ ቀንዲል
ምስጢረ ቀንዲል ማለት ቅብዐ ፈውስ ማለት ነው፡፡
ምስጢረ ቀንዲል የተጀመረው በጌታችን ዘመን በሐዋርያት ነው፡፡ ይኸውም ቅሁሳን ሐዋርያት በጌታችን ትእዛዝ ልዩ ልዩ ድውዮችን (በሽታዎችን) ቅብዐ ቅዱስ እየተቀቡ ይፈወሱ ነበር፡፡
ማር 6:12 “ወጥተውም ንስሐ እንዲገቡ ሰበኩ፥ ብዙ አጋንንትንም አወጡ፥ ብዙ ድውዮችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱአቸው።”
ሐዋርያው ያዕቆብ ምስጢረ ቀንዲልን አስመልክቶ ለምእመናን ሲጽፍ እንዲህ ብሎአል  ያዕ 5:13 “ከእናንተ መከራን የሚቀበል ማንም ቢኖር እርሱ ይጸልይ፤ ደስ የሚለውም ማንም ቢኖር እርሱ ይዘምር። ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተክርስቲያንን ሽምግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል ጌታም ያስነሣዋል፤ ኃጢአትንም ሠርቶ እንደሆነ ይሰረይለታል።”
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምስጢረ ቅብዐ ፈውስ የሚፈጸምላቸው ሕሙማን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቀኖና መሠረት የቤተክርስቲያኒቱ እምነትና ሥርዓት የሚከተሉ መሆን አለባቸው ምእመናን ልዩ ልዩ በሽታ ሲያድርባቸው ወደ ቤተክርስቲያናቸው ማለት ወደ አጥቢያ ቤተክርስቲያናቸው እየሄዱ ወይም መልእክተኞች እየላኩ ቀሳውስቱ በጸሎት ምስጢረ ፈውስ (ምስጢረ ቀንዲል) ይፈጽሙላቸው ዘንድ ይገባል።

 

 

 

 

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top