ሰባቱ አፅዋማት

1.ፆመ ኢየሱስ፦ ዓብይ ፆም (ሁዳዴ)

አብይ ፆም መባሉ ትልቅና ታላቅ መሆኑን ለማሳወቅ ነው። ይህ ፆም ታላቅ መባሉም ለ55 ቀናት ያህል መፆሙ እና ከሌሎች አፅዋማት ጋር ሲነፃፀር በቁጥር መብለጡ ብቻ ሳይሆን ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገዳመ ቆሮንቶስ መፆም ሳይገባው ለእኛ አርአያና ትልቅ ምሳሌ ለመሆን የፆመው ፆምም በመሆኑ ነው። {የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቷልና} የተሰኘውን አምላካዊ ቃል (ሉቃ ፲፱፥፲) አስፍሮልን ስንመለከት አምላካችን ወደ ምድር መምጣቱ የሰውን ልጅ ከውድቀቱ ሊያነሳ መሆኑን ሳይናገር የታወቀ ሳይታለም የተፈታ ነው። ዲያብሎስም በበኩሉ ባለው የማጥመጃ መሳሪያና የማሰሪያ ሰንሰለት ተጠቅሞ የሰውን ልጅ ከአምላክ አለያይቶ፣ ከተድላው አርቆ፣ ከገነት አውጥቶ፣ የመንግስተ ሰማያትን መንገድ አዘግቶ እና ዘላለማዊ ሕይወትን አሳጥቶ መኖርን ስለሚፈልገው በተቻለው ሁሉ ይህንን ግብሩን ሲያደላድል ይኖራል። መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሕይወት እንድንደርስ ሳያሸልብ እንደሚጠብቀን ሁሉ ከሳሽ ዲያብሎስም ሳያሸልብ መውደቂያችንን ሲያመቻች ይኖራል። (ማቴ ፬፥፩-፲፬) ጌታችን አምላካችን መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ከተጠመቀ በኋላ በገዳመ ቆሮንቶስ በመሄድ 40 ቀንና 40 ለሊት እንደ ፆመ በዚያም በዲያብሎስ እንደተፈተነና ዲያብሎስን ድል እንዳደረገው ተዘግቦ እናገኛለን። በፆም ድል ማድረግን ጌታ ያስተማረን ከሳሽ ዳያብሎስ አዳምና ሔዋንን ባሳተበት ግብሩ ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው የሆነውን ጌታ ስጋ ለብሶ ቢያየው ከመጽሐፍ ጥቅስ እየጠቀሰ እና የእግዚአብሔርን ቃል እየተናገረ ሊያስተው ቢሞክርም አሳች እቅዱ መክኖ መቅረቱን እንመለከታን። ፆም የነፍስን ቁስል ትፈውሳለች {የዲያብሎስን ስራ ሊያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ} (1ኛዮሐ ፫፣፰) እንዳለው ሁሉ በ40 ቀንና በ40 ለሊት ፆም ዲያብሎስ ስራ ሲፈራርስ ታየ። አዳምን በመብል ያሳተ የቀደመው እባብ ሰይጣን ዲያብሎስ ዳግም በመብል ፈትኖ ገነት እንደተዘጋች እንድትኖር ቢያልምም ኅልሙ እውን፣መከራውምአዎንቲዊ፣ጥረቱ ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል። የዲያብሎስን ስራ ሊያፈርስ የተገለጠው የእግዚአብሔር ልጅም በፆም ድል ማድረግን ለኛም አስተምሮናል።

በዚህ ጾም በቤተ-ክርስቲያን ዕለታቱም፤በሳምንት ተከፍለው ልዩ ስያሜ ተሰጥቷቸው ስርዓተ አምልኮ ይፈጸምባቸዋል፡፡

1ኛ ሰንበት (እሁድ)፡- ዘወረደ ይባላል 

በዚህ ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማያት ወደ ምድር መውረድና የሰው ልጅ እግዚአብርን በመፍራት እንዲኖር የሚያስገነዝብ ዝማሬ እየተዘመረ አምልኮ ይፈጸማል፡፡

ዕለቱም ሰው ለጾም እንዲዘጋጅ ትምህርት የሚሰጥበትና በጾሙ ውስጥ ምን ማድረግ እንደሚገባና እግዚአብሔርን በመፍራት እንዲኖር የምንማርበት ዕለት ነው፡፡

መዝ፡2፤-11 ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ በመገዛታችሁም ደስ ይበላችሁ ዋጋ የምታገኙበት ነውና ከፍቅር በመነጨ ፍርሃት ደስ እያላችሁ ለእግዚአብሔር ተገዙ ወንጌልን በሰራት ልጁ እመኑ ኋላ አላመናችሁም ብሎ እንዳይፈርድባችሁ ወንጌልን አምናችሁ ንስሐ ገብታችሁ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ በማለት ትምህርት የሚሰጥበት ዕለት ነው፡፡ (ሳምንቱ ጾመ ህርቃል ይባላል)

2ኛ- ሰንበት እሁድ  (ቅድስት)   

ስያሜውን የሰየመው ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ ከዚህ ዕለት ጀምሮ ጾመ ኢየሱስ ይባላል፡፡ ከዚህ ዕለት አንስቶ ለእግዚአብሔር መቀደስ እንደሚገባን፤ ቅድስናን እንድንይዝ ቤተ-ክርስትያን የምታስተምርበት ሳምንት ነው፡፡ በንጽህና በቅድስና ሆነን ወደ ቤተመቅደሱ እንድንገባ ወደ እግዚአብሔር እንድንቀርብ በመዝሙር በቅዳሴም ስለቅድስና ታስተምራለች፤በተጨማሪም በዚህ ዕለት ስለ ሰንበት ክብር ስለ እግዚአብሔር ምህረት ዝማሬ ይዘመራል፤ ምንባባትም ይነበባሉ፤ ስለ ቅድስና ሰፊ ትምህርት ይሰጣል፡፡  (ማቴ ፡ 6፤16 -25)

3ኛ- ሰንበት እሁድ ምኩራብ

የዚህ ዕለት ስያሜ ምኩራብ ይባላል

ምኩራብ አይሁድ ተሰብስበው አምልኮ የሚፈጽሙበት ኦሪትን የሚያስተምሩባት የተለየች ቦታ ነበረች፤መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ ምኩራብ ተገኝቶ በኃጢአት ለታሰሩት ነጻነትን፤በኃጢአት ለሞቱት ህይወትን፤ለድሆች ወንጌልን፤ለተጠቁት ነጻነትን፤በፍርድ ላሉት ምህረት መስጠቱን፤ ማስተማሩን ይህን ትምህርቱን የሰሙ ሁሉ መገረማቸውን መደነቃቸውን ይነገርበታል ይህን የተመለከተ ዝማሬም ይቀርብበታል፤ስለ ቤተ መቅደስ ክብር ተቆርቁሮ በቤተ መቅደሱ የተሰራውን ገበያ ያፈረሰበት ዕለት መሆኑ የሚዘከርበትና ስለዚሁ የቤትህ ቅናት በላኝ እየተባለ የሚዘመርባት ዕለት ስለ ቤተ መቅደስ አገልግሎትና ክብር በሰፊው ትምህርት የሚሰጥበት ዕለት ናት፡፡(ዮሐ ፡ 2 ፡ 12) (ሉቃ 4፡14 – 23)

4ኛ ሰንበት መጻጉዕ

ይህ ሳምንት ለዐቢይ ጾም 4ኛ ሳምንት ነው ዕለቱንም ልክ እንደሌሎች ሁሉ መጻጉዕ ብሎ የሰየመው ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ በዚህ ዕለትም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ህሙማንን ስለመፈወሱ፤ለምጻሞችን ስለማንጻቱ፤ተአምራትን ስለማድረጉ ጎባጣዎችን ስለማቅናቱ እየተዘመረ ይመለካል፡፡

መጻጉዕ ፡- በጽኑ ደዌ የተያዘና በአልጋ ላይ ተጣብቆ የሚኖር በሽተኛ (ህሙም) ማለት ነው፡፡

መዝ 40፡ 3 – 4

እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ላይ ሳለ ይረዳዋል መኝታውንም ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል፡ እኔም አቤቱ ማረኝ እልሀለሁ በማለት ዝማሬ ይቀርባል፡፡

በሰንበት ከተፈወሱት ድውያን (ህሙማን) መካከል

  •   የ፲ አለቃው ልጅ  ማቴ 8፡ 1 – 15

  •   ዓይኑ የበራለት ዕውር ማቴ 20 ፡ 29

  •   የቤቱን ጣራ በስተው ያገቡት ህሙም  ማር 2፡3 -12

5ኛ-ሰንበት ደብረዘይት፡-

ይህ ዕለት ጾመ ኢየሱስ ከተጀመረ 5 ሰንበት ሲሆን ስያሜውም ‹‹ ደብረ ዘይት›› ይባላል፡፡

በዚህ ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ  ክርስቶስ ‘በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት’ ይህም ማለት በመለኮታዊ ግርማ በሚያስደነግጥ፣ በሚያንቀጠቅጥ በሚያስፈራ ሁኔታ በሰው መጠን እንደሚመጣ የዓለምም ፍፃሜ እንደሚሆን ለሐዋርያት ደብረ ዘይት በሚባል ስፍራ ማስተማሩን፤ እንዲሁም በክብር ያረገውን ጌታ ዳግመኛ እንደሚመጣ፤ ለሚጠባበቁት ዋጋቸውን፤ ላልተቀበሉትም ፍዳቸውን ሊከፍል/ሊፈርድ/ በምድር ያለ ሥርዓትን ሁሉ ሊሽር፤ ሰማይንና ምድርን አሳልፎ በእርሱ አምነው ሕጉን ፈቃዱን  ለፈፀሙ ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ ያዘጋጀላቸውን መንግሥቱን ሊያወርስ፤ ጻድቃንን በቀኙ ሊያቆም፤ ኃጥአንን በግራው አቁሞ ሊወቅስ እንደሚመጣ እያሰበች ይህንኑም በሊቃውንቱ እየተዘመረ፤ በመምህራኗ እየተሰበከ ሥርዓተ አምልኮን ትፈጽማለች፡፡

እግዚአብሔር ወልድ የእመቤታችንን ድንግል ማርያምን ሥጋ እንደተወሐደ ይመጣል መጥቶም ዝም አይልም ‹‹እናንተ የአባቴ ቡሩካን ወደ እኔ ኑ›› ብሎ ይጠራል፡፡ ‹‹እናንት እርጉማን ከእኔ ወግዱ›› ብሎ ያሰናብታቸዋል፡፡ማቴ.25፤32-34

በፊቱ እሳት ይነዳል ፤ይህም ጻድቃን የሚድኑበት/ የዘለዓለም ህይወት/ ፤ኃጥአን የሚጠፉበት/የዘለዓለም ቅጣት/ፍርድ/ሥልጣን/ በባሕርዩ አለ›› እየተባለ ይዘመራል፤ ይሰበካል፡፡ በዚህ ዕለት ቅዱስ ያሬድ ያዘጋጃቸው ዝማሬዎች ሌሊቱን  ሙሉ ይደርሳሉ፡፡

‹‹ከክብሩ ውበት ከጽዮን እግዚአብሔር ግልጥ ሁኖ ይመጣል ፤አምላካችን ይመጣል ዝም አይልም፤እሳት በፊቱ ይነዳል››መዝ.ዳዊት 49፤3

6ኛ ሰንበት ገብር ኄር

ይህ ዕለት አገልጋዮች ስለተሰጣቸው አደራ፤በታማኝነት ለሰሩትም ዋጋ የሚሰጥ እግዚአብሔር አገልጋዮችን ‹‹ ገብር ኄር /ቸር አገልጋይ/ ገብር ምዕመን/ በጎ ባርያ/እያለ ዋጋ የሚሰጥ አምላክ መሆኑን እየታሰበ የሚመለክበት፤ የሚመሰገንበት ቀን ነው፡፡

በዚህ ዕለት በማቴ 25÷14-31 ያለው ኃይለ ቃል ተነቦ አገልጋቹ እነማን እንደሆኑ መክሊታቸውን እንዴት እንደ ተጠቀሙበት የሚተረጎምበትና የሚብራራበት ዕለት ነው፡፡

7ኛ ሰንበት ኒቆዲሞስ

ኒቆዲሞስ የፈሪሳውያን አለቃቸውና መምህር ሲሆን ቀን ወደ ጌታ መጥቶ የምስራቹን ቃል ለመማር ይሻ ነበር፡፡ ነገር ግን አይሁድን ይፈራ ነበርና በሌሊት ወደ ጌታ መጥቶ እንደተማረ ጌታም በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 3 ላይ የተፃፈውን ምስጢረ ጥምቀትን /ዳግም ልደትን/ ለኒቆዲሞስ እንዳስተማረው በማውሳት በዕለቱ ሌሊቱን ዝማሬ ተቁሞ በማሕሌት፤ ማለዳ በቅዳሴና በስብከት ይከበራል፡፡ዮሐ.3፤1

8ኛ ሰንበት ሆሣዕና

ቤተ፡ክርስትያን በዚህ ዕለት የምትፈጽመው ሥርዓተ አምልኮ ከሌሎቹ ሰንበታት የሰፋ ነው፡፡ ይኸውም ከዋዜማው ቅዳሜ እስከ እሑድ ጀምሮ ከመጽሐፍ  ቅዱስ ዕለቱን የሚያወሱ ምንባባት እየተነበቡ ቤተ ክርስትያን እየተዞረ በ4ቱም አቅጣጫ ምስባክ እየተሰበከ፤ ወንጌል እየተነበበ ሥርዓተ አምልኮ የሚፈፀምበት ዕለት ነው፡፡

ሆሣዕና-መሲህ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ የተዘመረ መዝሙር ነው፡፡‹‹ ሆሣዕና›› ለዳዊት ልጅ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው ሆሣዕና በአርያም ‹‹ በማለት መዘመራቸውን በማሰብ እንደዚያው በዚህ ዕለት ቤተክርስቲያንም ሆሣዕና በአርያም እያለች ሌሊቱን በማኅሌት፤ ጧት በቅዳሴ እያመሰገነች አምልኮ የምትፈጽምበት ዕለት ነው፡፡ማቴ.21

2.ፆመ ድህነት(ረቡእ አርብ ፆም )፦

ከበአለ ሀምሳ ውጭ በሳምንት ረቡእ እና አርብ የምንፆመው ነው። ፆሙ
የሚፆምበት ምክንያትም ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሰቀል የተወሰነበት ቀን ሮብ በመሆኑ እና የተሰቀለውም አርብ በመሆኑ ነው።

 3.ፆመ ገሀድ፦

ፆመ ገሃድ ምንድነው?

ገና እና ጥምቀት ዓርብ እና ረቡዕ ቢውሉ ይበላባቸዋል ወይስ ይጾማሉ?

ፍትሐ ነገሥት፡ ዳግመኛ በየሳምንቱ ዓርብ እና ረቡዕን መጾም ነው፡፡ በዓለ ሃምሳ፣ የልደት እና የጥምቀት በዓል የተባበሩባቸው ጊዜ ካልሆነ በቀር /ዐንቀጽ 15፣ ቁ566/

የዓርብን እና የረቡዕን ጾም ግን ከልደት፣ከጥምቀት እና ከበዓለ ሃምሳ በቀር ዘወትር ይጹሙ /ዐንቀጽ 15፣ቁ 603/

የገና እና የጥምቀት ቅዳሴ ስንት ሰዓት ነው?

ፍትሐ ነገሥት፡ ስለ ልደት እና ጥምቀት ግን በዚያ ዘመን በኒቂያ የተሰበሰቡ ሊቃውንት ቅዳሴው በሌሊት ይሆን ዘንድ አዘዙ /ዐንቀጽ 15፣ ቁ 595/

ልደት ጋድ አለው?

ፍትሐ ነገሥት፡ የልደት እና የጥምቀት በዓላት ጋድ አላቸው /ዐንቀጽ 15፣ ቁ 566/

ትንታኔ፡ የገና ጾም 44 ቀናትን ይይዛል፡፡

40 ጾመ ነቢያት

3 ጾመ አብርሃም ሶርያዊ

1 ጋድ

ድምር 44

የገና ጋድ ከጾሙ ተያይዞ የተቀመጠ እንጂ ለብቻው የተቀመጠ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ሰሙነ ሕማማት ለብቻው የሚቆጠር ጾም ነው፡፡ /ዐንቀጽ 15፣ቁ 565/ ነገር ግን አንድ ሰው ዐቢይ ጾምን ሳይጾም ከርሞ ሕማማትን ለብቻው መጾም አይችልም፡፡ የገናም ጋድ እንዲሁ ነው፡፡

ይህንን ጋድ የልደትን ጾም የማይጾሙ ሰዎች እንዲጾሙት የተሠራ ነውን?

መልስ፡ በቤተ ክርስቲያን ላልተጠመቁ፣ ለማይቆርቡ፣ ንስሐ ለማይገቡ፣ ለማያስቀድሱ፣ ለማይጾሙ ሰዎች ተብሎ የተሠራ ልዩ ሥርዓት የለም፡፡ በፍትሐ ነገሥት ዐንቀጽ 15፣ ቁ 565 እንደተገለጠው ሰባቱ አጽዋማት «ለክርስቲያን ሁሉ» የታዘዙ ናቸው፡፡ ስለዚህም የገናን ጾም ክርስቲያን ሁሉ ጾመው በበዓለ ልደት ሊገድፉ ይገባቸዋል፡፡ ፍትሐ ነገሥት ስለ ገና ጾም ሲገልጥ «መጀመርያው የኅዳር እኩሌታ ፋሲካው የልደት በዓል ነው» ይላል /ዐንቀጽ 15፣ ቁ 568/፡፡ ይህም ከገና ጾም ተሸርፎ የሚጾም ነገር እንደሌለው ያሳያል፡፡

  4.ፆመ ሀዋርያት፦

ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ከተነሳ በሃላ ቅዱሳን ሀዋርያት ሰማያዊ ተልእኮ ስለተሰማቸው ከ50ቀን በሃላ በበአለ ጰራቅሊጦስ ማግስት መፆም ጀመሩ። የአበው ቀደምትን አስረ ፍኖትን የምትከተል ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ትንሳኤ በዋለ በ50ኛው ቀን የፆሙን አዋጅ ለልጆቿ አውጃለች።ፆመ ሐዋርያት

 አንዳንዶች የሰኔ ፆም የቄስ ፆም ነው በሚል ከመፆም ወደኋላ ሲሉ ይታያሉ ነገር ግን ቅድስት ቤተክርስቲያን በአዋጅ ከምትፆማቸው ሰባት አፅዋማት አንዱ እንደመሆኑ መጠን እያንዳንዱ ክርስቲያን ቢፆመው እጅግ በርካታ በረከቶችን ያገኝበታል ከነዚህም ጥቂቶችን እነሆ

 1.በረከተ ሐዋርያት ይገኝበታል ይህን ፆም መጀመርያ ፆመው እንድንፆመው ሰርዐት የሰሩልን ሐዋርያት ናቸዉ ስለዚህም ፆሙ መታሰቢያነቱ የሐዋርያት ነው የጻድቅ መታሰቢያ ደግሞ ለበረከት ነው ። ምሳ.10፥7 እኛም የሰኔን ፆም ብንፆም የሐዋርያቱን በረከት እናገኛለን ሐዋ.13፥1-3 ሐዋ.14፥23

 በስራችንና በአገልግሎታችን በረከት እናገኛለን ሐዋርያት ይህን ፆም የፆሙት አገልግሎታቸው እንዲከናወንላቸው እንዲባረክላቸው ነው ነብዩ ነህምያም እየሩሳሌምን የመስራት ተግባሩ እንዲባረክለት በፆመው ፆም ስራው ሁሉ ተባርኮለታል። ነህም.1፥4። እኛም የሰኔን ፆም ብንፆም በዕለት ተዕለት ተግባራችን በረከት እናገኛለን።

 ዝናብ ምህረትን ጠለ በረከትን እናገኛለን የሰኔ ፆም በአገራችን የክረምቱ መግቢያ ላይ የሚፆም ፆም ነው ይህም መጪው የክረምቱ ወራት የተስተካከለ የምህረት ዝናም እንዲኖረው ያደርጋል በነብዩ ኢዩኤል ዘመን ዝናብ ጠፍቶ ዛፎቹ ሳይቀር በደረቁ ጊዜ በፆም በፀሎት ወደ እግዚአብሔር በተማፀኑ ሰዓት ዝናመ በረከትን አግኝተዋል። ኢዩ.1፥13-14  

  1. በረከተ ምርትን እናገኛለን የሰኔ ፆም በሃገራችን ገበሬው ዘር መዝራት በሚጀምርበት ጊዜ የሚፆም ፆም ነው ሰለዚህም በዚህ ሰዓት የሚፆመው ፆም ዘርን እንዲባረክ በረከት እንዲበዛ ያደርጋል ይህም አገር ወገን ከረሃብ ከችግር ነፃ እንዲወጣ ያደርጋል በነብዩ ኢዩኤል እንደተገለጸው በፆም የዕህል የመጠጥ በረከት ይገኛል ። ኢዩ.2፥12-14

 የነፋስ በረከትን እናገኛለን ፆም በመንፈስ የደከመች የዛለች ነፍስን ያበረታል የነፍስን ቁስል ይፈውሳል ስጋዊ ኃይልን ያደክማል የሥጋን ፈቃድ ለነፍስ ያስገዛል መዝ.108፥24 ፤ ገላ.5፥24 የዓለምን ሃሳብ ያስወግዳል ከእግዚአብሔር ያስታርቃል ማቴ. 17፥21 ሚስጥር ይገልጣል ዘስ.34፥27-28 ፤ ዳን. 10፥1-3 “በአምላካችን ፊት እራሳችንን እናዋርድ ዘንድ ከርሱም የቀናውን መንገድ ለእኛና ለልጆቻችን ለንብረታችንም ሁሉ እንለምን ዘንድ …… ፆምን አውጃለሁ ” መጽሐፈ ዕዝራ.8፥21

 5.የገና-ፆም-ፆመ-ነብያት

ነብያት ስለ እየሱስ ክርስቶስ መወለድ ፣ ወደ ግብፅ ስለ መሰደድ ፣ በባህረ ዮርዳኖስ ስለመጠመቅ፣በትምህርት ወንጌል ጨለማውን አለም ስለ ማብራቱ ፣ ለሠው ልጆች ድህነት ጸዋትወ መከራ ስለ መቀበሉና ስለ መስቀሉ ፣ ስለ ትንሳኤው ፣ስለ ዕርገቱና ስለ ዳግም ትንሳኤው ፣ ስለ ዕርገቱና ስለ ዳግም ምጽአቱ ትንቢት ተናግረው አላቆሙም ፤ ለአዳም የተሰጠው ተስፋ ተገልፆላቸው ለተናገሩት ትንቢት ፍፃሜ እንዲያደርሳቸውም ፈጣሪያቸውን ተማፀኑትም እንጂ ።

በየዘመናቸው ” አንሥእ ኃይለክ ፣ ፈኑ እዴክ ፤ ኃይልህን አንሳ እጅህንም እጅህንም ላክ” እያሉ ጮሁ ። በፆምና በፀሎት ተወስነውም ሰው የሚሆንበትን ግዜ በቀናት ፣ በሳምንታት ፣ በወራትና በወራትና በዓመታት ቆጠሩ ። ለምሳሌ ነብዩ ኤርሚያስ ስለ ሥጋዌ ትንቢት በተናገረ በ446 አመት ጌታችን ከእመቤታችን ከሥጋዋ ስጋን ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው ሆነ።

ነብያት ተስፋው በዘመናቸው ተፈፅሞ በአይነ ሥጋ ለማየት ባይችሉም እግዚአብሔር ” የማያደርገውን አይናገር የተናገረውን አያስቀር ” ብለው አምነው ከወዲሁ ተደሰቱ ። ለዘመነ ሥጋዌ ቅርብ የነበሩት እነ ኢሳያስ ጾሙ እንዴት መፈፀም እብዳለበት ተናግረዋልም ። ኢሳ 58-1

በመሆኑም በጌታ ልደት ትንቢት ነብያት ስለ ተፈፀመበት ይህ ፆም {የነቢያት ፆም } ይባላል ። የወልደ እግዚአብሔር ሰው መሆን ያስተማሩበት የሰው ልጆች ተስፋ የተመሰከረበት የምስራቹ የተነገረበት ስለሆነም <<ጾመ ስብከት>> ይባላል ።

ነብዩ ኤርሚያስ
ሰው በሐጥያት ቢወድቅም ፈጣሪው ሊያነሳው ፤ ቢጠፋ ሊፈልገው እንደሚመጣ በተስፋ ሲጠብቀው ወልደ አምላክ ሰው መሆኑ የተረጋገጠ እውነት ነው ። ስለዚህ አዳም የልደቱን ነገር በትንቢት መነፀርነት ሲመለከተው /በነብያቱ ትምህርትና ስብከት / ፣ በሚኖርበት ዓመተ ፍዳ የሚስጢረ ሥጋዌ ብርሃን ከሩቅ ሲመለከተው ኖረ ። ምሥጥረ ሥጋዌ ብርሃን ከሩቅ በትንቢት መነፀርነት ማየቱም መከራውን እንዲቋቋመው የተስፋ ሥንቅ ሆነው።

በክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር በፀጋ እንደተወለዱ በማመን ለእግዚአብሔር ያላቸውን ፍቅር ከሚገልጡባቸው ነገሮች አንዱ ጾም ነው ። ጾም የፍቅር ስጦታ ከመሆኑም በተጨማሪ ታዛዥነትንና የገቡትን ቃል ኪዳን ጠባቂነትንም ማሳያ ነው። የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አርአያ ተፈጥሯል ። ኃጥያት ሰርቶ የእግዚአብሔር አርአያነቱን ቢያጠፋውም እግዚአብሔር ግን በአርአያው ሲፈጥረው ምን ያህል እንደሚወደው ማረጋገጫ ሥለነበር በሐጥያት ሲወድቅም እንደወጣ ይቅር ሳይል ሊፈልገው መጣ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሊፈልግ የመምጣቱ ተስፋ የተነገረበትንና ሱባኤ የተቆጠረበትን ዕለት ለማየት በመናፈቅ ከቀረበው መስዋዕት አንዱ ፆም ነበር ።

ፆም ሰው ለእግዚአብሔር ያለውን ፍቅርና ታዛዥነት መግለጫ ማረጋገጫ ብቻም ሳይሆን ሲወድቁ መነሻ ከብልየት ( እርጅና ) መታደሻ ፥ ከሐጥያት ቆሻሻ መታጠቢያ / ከንሰሃ ጋር አብሮ ሲፈፀም/ ሳሙናም ነው ። ሊቀ ነብያት ሙሴ በሲና ተራራ ላይ እግዚአብሔር ወደነበረበት ጨለማ የገባው ፣ አስፈሪውን መብረቅ እና ነጎድጓድ የተቋቁመው ፣ ጨለማውን አልፎ የሰው ልጅ ያልሰራትን ሰማያዊ መቅደስ የተመለከተና ወደ አለቱ ድንጋይ የቀረበው እራሱን ለእግዚአብሔር በፆም በመቀደስ ጭምር ነው ። ( የወገን ፍቅርና ለእግዚአብሔር ታዛዥነቱ እንዳለ ሆኖ) ።

ፆም የስጋ ምኞት እስከመሻቱ ቆርጦ የሚጥል ፣ ለመንፈስ ልዕልና የሚያበቃውን መሳርያ የሚያስታጥቅ ነው። ክርስቲያን ይህን መሰል መንፈሳዊ የጦር እቃ እንዳይለየው አጥብቆ ይለመናል። የጦር ልምድ እንደሌለው ወታደር ጠላቱን የሚቋቋምበት የጦር ትጥቅ ሳይዝ አውላላ ሜዳ ላይ ባዶውን አይቆምም ። መንፈሳዊ ውጊያን በሥጋዊ ጥበብ ማሸነፍ ስለማንችል ነው አበው ፍቅረ አፅዋማትን በአስተምሮአቸውና በህይወታቸው የሰበኩልን ።

ፆም እነዚህንና መሰል መንፈሳዊ በረከትን ስለሚያስገኝ በክርስቲያኖች ይመጣላቸው ዘንድ ይናፍቁታል ። ከእነዚህ የሚናፈቁ አፅዋማት መካከል አንዱ ፆመ ነብያት ነው ። ፆመ ነብያት የሚባለው ፆመ ግና ፣ ፆመ ማርያም ፣ ፃመ አዳም ፣ ፆመ ፊሊጶስ ተብሎ እንደሚጠራ መምህር ቃኘው ወልዴ ፆምና ምጽዋት በተሰኘው መፅሐፋቸው ገልፀውታል ። ፆመ ነብያት ለአዳም የተነገረው ትንቢት ፣ የሚጠቅመው ሱባኤ እንደደረሰ የሚያበስር በመሆኑ ፆመ አዳም ይባላል ። አዳም ቢበድልም ንሰሐ ገብቶ በማልቀሱ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሀለሁ ብሎ የተነገረው ተስፋ መድረሱን ፣ ሚስጢረ ስጋዌ እውን ሊሆን መቃረቡን የሚያስረዳ ፆም ነው ።

ነብያትም የሚስጢረ ስጋዌ ነገር ተገልጦ ስለታያቸው ፣ ክርስቶስ ለሰው ልጆች የሚከፍለውን የፍቅር ዋጋ በትንቢት ተመልክተው ፆመውታልና ፆመ ነብያት ይባላል ። ይህ ፆም የራቀውን አቅርቦ ፣ የረቀቀውን አጉልቶ ስላሳያቸው እስከ ሞት ድረስ ቢደበደቡም ፣ ከመከራው ጽንአት የተነሳ ዋሻ ለዋሻ ፣ ፍርኩታ ለፍርኩታ ቢንከራተቱም ፣ የፍየል ሌጦ ለብሰው ቢዞሩም የተስፋው ቃል ሁሉን አስረስቶአቸዋል ከትንቢቱ ባለቤት ጋር በመንፈስ ተዋህደው አልፈዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ሐዋርያትምን ሠርተን የክርስቶስን ልደት እንቀበለው ብለው ስለፆሙት ጾመ ሐዋርያት ተብሎ ይጠራል ።

ፆመ ነብያት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ወልደ አብን ፀንሼ ምን ሰርቼ እወልደዋለሁ በማለት ፆማለችና ፆመ ማርያም ይባላል ። ይህን ያለችው በመደነቅ ፣ አንድም በትህትና ፣ አንድም ቀደምት አባቶቿ ነብያት ሲፆሙት አይታ ጾመዋለች ። እንዴት ፀንሼ እወልደዋለሁ ማለት ጥርጥር ሳይሆን ተደሞ ፣ መደነቅ የነገረ ልደቱን አይመረመሬነት ይገለፃል ። ነሌላ ነኩል ደግሞ ትህትና ነው። እግዚአብሔር አምላክ ቅድስናዋን አይቶ በብስራተ መልአክ አማካኝነት ክርስቶስን እንደምትወልድ ቢነግራትም የትህትና እናት ናትና ምን ሠርቼ የሰማይና የምድርን ፈጣሪ እችለዋለሁ ስትል ፆመዋለች ።

ይህ ፆም ፊሊጶስም ይባላል። ሐዋርያው ፊሊጶስ በአርማውያን ዘንድ ገብቶ ሲያስተምር በሰማዕትነት ሲሞት አስክሬኑ ከደቀ መዛሙርቱ ስለተሰወረ እግዚአብሔር የተሰወረውን የመምህራችውን አስክሬን እንዲገልፅላቸው ከህዳር 16 ጀምረው ሲጾሙ በ3ኛው ቀን የመምህራቸውን አስክሬን ቢመልስላቸውም ፆሙን ግን እስከ ልደት ቀጥለዋል ። ፆምን ትዕዛዝ ድለሆነ ብቻ ሳይሆን የፍቅርና የበረከት ምንጭ በመሆኑ ጭምር ደስ እያለን ብንፆመው የቅዱሳኑ በረከት ያድርብናል ።

6.ፆመ ነነዌ፦

የነነዌ ሰዎች ለሰሩት ሐጢያት የእግዚአብሔርን ምህረትና ይቅርታ ለመጠየቅ የፆሙትን ለማስታወስ ነው። እኛ የምንፆመው የበፊቱን ለማስታወስ ብቻ ሳይሆን ዋናው በአንድ ላይ የህብረት ንስሃ ለመግባት እና አምላክን ይቅርታ ለመጠየቅ ነው። በክርስቲያን ህይወት ውስጥ ንስሐ ትልቅ የእምነት አካል ነው። የነነዌ ሰዎች እንዳጠፉ ሁሉ እኛም እናጠፍለን፤ የነነዌ ሰዎች ንስሐ እንደገቡ እኛም ንስሐ እንገባለን፤ እግዚአብሔርም ይቅር ይለናል።

የነነዌ ፆም ታሪክ

  1. ዮናስ ወደ ነነዌ ከተማ እንዲሄድ ታዘዘ
    እግዚአብሔር ነብዩ ዮናስን ወደ ነነዌ ከተማ እንዲሄድ አዘዘው፡፡ ዮናስ ግን ወደ ነነዌ ሂድና ስበክ ሲባል እምቢ ብሎ ወደ ተርሴስ ለመኰብለል በመርከብ ተሳፈረ፡፡ ማዕበል በመነሳቱም ወደ ባህር ተወረወረ፡፡ እግዚአብሔር ግን ዮናስን ሊያርመው፤ አስተምሮ ሊልከው ባህር ውስጥ አሳ አንበሪን አዘጋጀለት፡፡ ዮናስም ወደባህር ሲጣል አሳ አንበሪ ሆድ ለሶስት ቀን በመቆየት የጌታ ምሳሌ ሆነ፡፡ ትንቢተ ዮናስ 1፤ ትንቢተ ዮናስ 2፡1-3፤

  2. ዮናስ ነነዌ ገብቶ አጭር የሆነ ስብከት ሰበከ
    ከአሳ አንበሪ ሆድ ከሶስት ቀን በኋላ የተተፋው ዮናስ ወደ ነነዌ ከተማ በቀጥታ ሄደ፡፡ አሱም ወደ ነነዌ ከተማ ከገባ በኋላ አጭር ቃል ብቻ ተናገረ…‹‹በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች አለ።›› ትንቢተ ዮናስ 3፡4

  3. በነነዌ የ 3 ቀን ፆም ታወጀ
    ንጉሱ ታላቅ አዋጅ አወጣ እኛ በበደልነው በደል ሕጻናት ሆኑ እንሰሳት መቀጣታቸው አይቀርምና ሁሉም ይጹሙ በእጃቸው ካለው ግፍ ይመለሱ፤ ንጉሱም ከዙፋኑ ተነሥቶ መጐናጸፊያውን አወለቀ ማቅም ለበሰ፥ በአመድም ላይ ተቀመጠ፡፡ ትንቢተ ዮናስ 3፣ 5-6

  4. እግዚአብሔርም ለነነዌ ምህረት አደረገ፤ ዮናስ ግን ተበሳጨ
    ‹‹እግዚአብሔርም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውን አየ እግዚአብሔርም ያደርግባቸው ዘንድ በተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም።››ት.ዮ 3፡10 ዮናስ ግን ተበሳጨ ‹‹ አቤቱ፥ እለምንሃለሁ በአገሬ ሳለሁ የተናገርሁት ይህ አልነበረምን? አንተ ቸርና ይቅር ባይ፥ ታጋሽም፥ ምሕረትህም የበዛ፥ ከክፉው ነገርም የተነሣ የምትጸጸት አምላክ እንደ ሆንህ አውቄ ነበርና ስለዚህ ወደ ተርሴስ ለመኰብለል ፈጥኜ ነበር።››ት.ዮናስ 4፡2

  5. እግዚአብሔርም ዮናስን አስተማረው
    ፈጣሪም የከተማውን መቃጠል ለማየት ተራራ ላይ የተቀመጠውን ዮናስን በዕለት በቅላ ከጸሀይ ሙቀት ኣሳርፋው በዕለት በደረቀችው ቅል ሲበሳጭ እንዲህ ብሎ አስተማረው፡፡ ‹‹ አንተ ትበቅል ዘንድ ላልደከምህባት ላላሳደግሃትም፥ በአንድ ሌሊት ለበቀለች፥ በአንድ ሌሊትም ለደረቀችው ቅል አዝነሃል። እኔስ ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ ከመቶ ሀያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሶች ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ አላዝንምን? አለው።››ትንቢተ ዮናስ 4፡10-11

7.ፆመ ፍልሰታ፦

ፆመ ፍልሰታ /ከነሐሴ 1 እስከ ነሐሴ 14 ቀን/ የእመቤታችን ዕረፍት፣ ትንሣኤና ዕርገቷ የሚታሰብበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅት ምእመናንን በፆም በጸሎት ተወስነው የልጇን ቸርነት የድንግልን አማላጅነት ይማጸናሉ፡፡ ሁሉም እንደሚደረግላቸው ያምናሉ፡፡ የሱባኤው ወቅት ሲፈጸም «በእውነት ተነሥታለች» ብለው በደስታ የፆሙን ወቅት ይፈጽማሉ፡፡

 

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሞትና ትንሣኤ ነገረ ማርያም፣ ስንክሳር እና ተኣምረ ማርያም እንደሚያስረዱት፤ ጥር 21 ቀን ዐርፋለች፡፡ ሞቷ የሚያስደንቅ መሆኑን ታላቁ የቤተክርስቲያናችን አባት ቅዱስ ያሬድ  «ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የሐጽብ ለኲሉ፤ ሞት ለማናቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል» በማለት ገልጾታል፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያት የእመቤታችንን የከበረ ሥጋዋን ገንዘውና ከፍነው ለማሳረፍ ወደ ጌቴሴማኒ መካነ ዕረፍት (የመቃብር ቦታ) ይዘው ሲሄዱ አይሁድ በቅንአት መንፈስ ተነሣሥተው «ቀድሞ ልጇን በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተነሣ፤ በዐርባኛው ቀን ወደ ሰማይ ዐረገ እንደገናም ተመልሶ ይህን ዓለም ለማሳለፍ ይመጣል  እያሉ ሲያውኩን ይኖራሉ፡፡ አሁን ደግሞ እርሷንም እንደ ልጇ ተነሣች፣ ዐረገች እያሉ ሲያውኩን ሊኖሩ አይደለምን) ኑ ተሰብሰቡና ሥጋዋን በእሳት እናቃጥላት» ብለው ተማክረው መጡ፡፡

  ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ የከበረ ሥጋዋን የተሸከሙበትን አጎበር (የአልጋ ሸንኮር) በድፍረት ያዘ፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ በእሳት ሰይፍ ሁለት እጆቹን ቆረጣቸው፡፡ እጆቹ ተንጠልጥለው ከቆዩ በኋላ በእውነት የአምላክ እናት ናት በማለት ስለ አመነ እጆቹ ተመልሰው እንደነበሩ ሆነውለታል፡፡ ከዚህ በኋላ መልአከ እግዚአብሔር የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ  ከሐዋርያው ዮሐንስ ጋር ነጥቆ ወስዶ በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጠው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ ሐዋርያት ሲመጣ የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ በገነት መኖሩን ነገራቸው፡፡  ሐዋርያትም የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ አግኝተው  ለመቅበር በነበራቸው ምኞትና ጉጉት  ዮሐንስ አይቶ እኛ እንዴት ሳናይ እንቀራለን ብንጠየቅስ ምን እንመልሳለን በማለት በነሐሴ አንድ ቀን ሱባኤ ጀምረው ሲጾሙና ሲጸልዩ ከሰነበቱ በኋላ በ14 (በሁለተኛው ሱባኤ መጨረሻ) ጌታችን የእመቤታችንን ትኩስ የከበረ ሥጋ አምጥቶ ስለሰጣቸው በታላቅ ዝማሬ፣ በውዳሴ ወስደው ቀድሞ በተዘጋጀው መካነ ዕረፍት  በጌቴሴማኒ ቀበሯት፡፡

 የእመቤታችን የቀብር ሥነ ሥርዐት በተፈጸመ ጊዜ ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ የሆነው ቅዱስ ቶማስ አልነበረም፡፡ ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ፣ እመቤታችን በተቀበረች በሦስተኛው ቀን  እንደ ልጇ ትንሣኤ ተነሥታ ስታርግ ያገኛታል፡፡ ቀድሞ የልጅሽን አሁን ደግሞ የአንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ ብሎ ቢያዝን እመቤታችን ከእርሱ በቀር ሌሎች ሐዋርያት ትንሣኤዋን እንዳላዩ ነግራው ቅዱስ ቶማስን አጽናናችው፡፡ ሄዶም ለሐዋርያት የሆነውን ሁሉ እንዲነግራቸው አዝዛው ለምልክት ይሆነው ዘንድ የተገነዘችበትን ሰበኗን ሰጥታው ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡

  ቅዱስ ቶማስም ሐዋርያት ወደ አሉበት ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ «የእመቤታችን ነገር እነዴት ሆነ?»  ብሎ ቢጠይቃቸው፤ «እመቤታችንን እኮ ቀበርናት» ብለው ነገሩት፡፡ እርሱም ዐውቆ ምስጢሩን ደብቆ «አይደረግም ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር  እንደምን ይሆናል?» አላቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ አንተ መጠራጠር ልማድህ ነው፡፡ ቀድሞ የጌታን ትንሣኤ ተጠራጠርክ አሁንም አታምንም ብሎ  የእመቤታችን መካነ መቃብር ሊያሳዩት ይዘውት ሔዱ፡፡ መቃብሩን ቢከፍቱ የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ አጡት፤ ደነገጡም፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ቶማስ «አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ተነሥታ ዐርጋለች» ብሎ  የሆነውን ሁሉ ተረከላቸው፡፡ ከዚያም ምልክት እንዲሆን የሰጠችውን ሰበኗን አሳያቸው፡፡ እነርሱም ማረጓን አምነው ሰበኗን ለበረከት ከተከፋፈሉ በኋላ ወደየአህጉረ ስብከታቸው ሄዱ፡፡ በየሀገረ ስበከታቸውም ሕሙማንን ሲፈውሱበትና ገቢረ ተአምር ሲያደርጉበት ኖረዋል፡፡

በዓመቱ ትንሣኤሽን ቶማስ አይቶ እንዴት ይቅርብን ብለው ነሐሴ አንድ ቀን ጀምሮ ሱባኤ ገቡ፡፡ በሱባኤው መጨረሻ ነሐሴ 16 ቀን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የለመኑትን ልመና ተቀብሎ እመቤታችንን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ንፍቀ (ረዳት) ቄስ)፣ ቅዱስ እስጢፋኖስን ገባሬ ሰናይ (ዋና) ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ አቁርቦአቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ እመቤታችንን ሐዋርያት በግልጽ ትንሣኤዋን ዕርገቷን እያዩዋት ከጌታችን ጋር በክብር በይባቤና በመዝሙር ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡ ቅዱስ ያሬድ በመዝሙሩ «እመቤታችን ድንግል ማርያም ከምድር ወደ ሰማይ ዐረገች በሰማይም ከልጇ ጋር በአብና በመንፈስ ቅዱስ ቀኝ ተቀመጠች»፡፡

የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ የክብርና የሕይወት ትንሣኤ ሲሆን ሁለተኛ ሞትን አያስከትልም ትንሣኤ ዘጉባኤንም አይጠብቅም፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤያችን በኩር ሆኖ በሞተ በሦስተኛው  ቀን ተነሥቷል፡፡ እናቱ እመቤታችንም በልጇ ሥልጣን፤  እንደ ልጇ ትንሣኤ በሦስተኛው ቀን ተነሥታ ትንሣኤ ዘጉባኤን ሳትጠብቅ በክብር ዐርጋለች፡፡  እንደዚህ ያለውን ትንሣኤ ከእርሷ በቀር ሌሎች ቅዱሳን ወይም ነቢያትና ሐዋርያት አላገኙትም በዚህም ሁኔታ የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ ከማናቸውም ትንሣኤ ልዩ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህም ትንሣኤ ዘለዓለማዊ የሆነ ከዳግም ሞተ ሥጋ ነጻ የሆነ ትንሣኤ ነው፡፡

ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ከመቃብር መነሣት ነሐሴ 16 ቀን የሚነበበው መጽሐፈ ስንክሳር እንደሚያስረዳን አባቷ ዳዊት በገናውን እየደረደረ ጸሐፊው የነበረው ዕዝራም መሰንቆውን ይዞ ቅዱሳን መላእክት ነቢያትና ጻድቃን እያመሰገኗት በብሩህ ደመና ወደ ሰማይ ዐረገች ከዚያም በክብር ተቀመጠች፡፡ በዚያም ስፍራ ሁለተኛ ሞት ወይም ሐዘን ጩኸትና ስቃይ የለም የቀደመው ሥርዐት አልፎአልና (ራዕ 21፥4-5)፡፡

 የእመቤታችን ዕርገትም በመጽሐፍ ቅዱስ ከተገለጸው ከእነ ሄኖክና ኤልያስ ዕርገት የተለየ ነው፡፡  ሄኖክ ወደ ሰማይ ያረገው በምድር ሳለ እግዚአብሔርን በእምነቱና በመልካም ሥራው ስለአስደስተና በሥራውም ቅዱስ ሆኖ ስለተገኘ ሞትን እንዳያይ ዐረገ፡፡ ወደፊት ገና ሞት ይጠብቀዋል ሞቶም ትንሣኤ ዘጉባኤ ያስፈልገዋል፡፡ «ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም» (ዕብ 11፥5)፡፡

ነቢዩ ኤልያስም በእሳት ሠረገላ ተነጥቋል «እነሆ የእሳት ሠረገላና የእሳት ፈረሶች በመካከላቸው ገብተው ከፈሉአቸው፤ ኤልያስም በአውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ወጣ»  (2ኛ ነገ 2፥10)፡፡ ነቢዩ በእሳት ሠረገላም ቢነጠቅም ወደፊት ሞት ይጠብቀዋል፤ ትንሣኤ ዘጉባኤም ያስፈልገዋል፡፡

 ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም በድርሰቱ ስለ ዕርገትዋ ጽፏል፡፡ በቃልዋ የታመነች በሥራዋም የተወደደች ቅድስት ድንግል ማርያምን መላእክት እያመሰገኗትና በመንፈሳዊ ደስታ እያጀቧት ወደ ሰማይ አሳረጓት ሲል በዘመረው መዝሙር አስረድቶናል፡፡

 

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top