አምስቱ አእማደ ምሥጢር
አምድ ፤ ማለት ምሰሶ ማለት ሲሆን አእማድ ማለት ምሰሶዎች ማለት ነው ። ቤት በአምድ (በኮለም) እንደሚፀና ፤ ሃይማኖትም በነዚህ ምሥጢራት ተጠቃሎ ይገለጻል ፤ ምዕመናንም እነዚህን ምሥጢራት በመማር ፀንተው ይኖራሉ ።
ምሥጢር ፤ ማለት ለተወሰነ ጊዜ በተወሰኑ ሰዎች ብቻ ተጠብቆ የሚቆይ ሲሆን ፤ በዚህ ትምህርታችን ግን በሚታዩ ምሳሌዎች የማይታየውን የሃይማኖት ምሥጢር መረዳት ፤ በሚታይ አገልግሎት የማይታይ ፀጋ ማግኘት ማለት ነው ።
አምስት ፤ ቁጥራቸው አምስት ብቻ ሆኖ የተወሰነው ፤ በ1 ሳሙ 17 ፥ 40 ። እና በ 1ቆሮ 14 ፥ 19 ። ባለው ቃል መሠረት ሲሆን ፤ አምስት መሆናቸውና የተደረጉባቸው ድንቅ ሥራዎች የአምስቱ አእማደ ምሥጢር ምሳሌነታቸውን ያስረዳል
✥ ምሥጢረ ሥላሴ (የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት) Mystery of Holy Trinity
✥ ምሥጢረ ሥጋዌ (የአምላክን ሰው መሆን) Mystery of Incarnation
✥ ምሥጢረ ጥምቀት (ስለ ዳግም መወለድ) Mystery of Baptism
✥ ምሥጢረ ቁርባን (ስለ ክርስቶስ ሥጋና ደም) Mystery of Holy Eucharist
✥ ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን (ስለ ዳግም ምጽዓት) Mystery of Resurrection of the dead
አምስቱ አዕማደ ምሥጢር በአፈጻጸማቸው በሦስት ይከፈላሉ ። ፩) ምሥጢረ ሥላሴና ምሥጢረ ሥጋዌ አምነን የምንቀበላቸው፤ ፪) ምሥጢረ ጥምቀትና ምሥጢረ ቁርባን አምነን የምንተገብረው፤ ፫) ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን አምነን በተስፋ የምንጠብቀው።
እነዚህን ምሥጢራት በቅደም ተከተል እንመለከታለን፤
ምሥጢረ ሥላሴ
ሠለሰ ሶስት አደረገ ፤ ካለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ፤ ሥላሴ ማለት ሶስትነት ማለት ነው ። በዚህ ትምህርት የአምላክን አንድነት ሶስትነት እንማራለን ።
የምሥጢረ ሥላሴን ትምህርት በምንማርበት ጊዜ ከሂሳብ ቀመር ህግ አስተሳሰብ ውጭ ሆነን ነው ። ምክንያቱም መንፈሳዊዉ ሥጋዊዉን ጥበብ (ፍልስፍና) ይመረምረዋል እንጅ መንፈሳዊ ጥበብና ምሥጢር በዓለማዊ ዕውቀት ምርምር ሊደረስበት አይቻልምና ። የሃይማኖት ነገር ቁሳዊ ሳይሆን መንፈሳዊና በሃይማኖት ሆኖ በመንፈሳዊነት የሚታወቅና የሚታመን ነው ።
የምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት በብሉይ ኪዳን “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር አለ” ዘፍ 1 ፥ 26 ። ። ከዚህ ቃል በፊት እግዚአብሔርን የሚመስል ፍጡር መኖሩን የሚገልጽ ባለመኖሩ “በመልካችን…” የሚለው አምላክ ከአንድ በላይ የሆነ የራሱ መልክ እንዳለው ያስረዳል። እግዚአብሔር ዓለምን ሲፈጥር ማንም ረዳት እንዳላስፈለገው በኢሳ ፡ 40 ፥ 12 ። ላይ ተጽፎ እናገኛለን ። በመሆኑም “በመልካችን..”የሚለው ሶስትነቱን (ከአንድ በላይ መሆኑን) ፤ “አለ” የሚለው ደግሞ አንድነቱን ይገልጽልናል ።
“አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” ዘፍ 3 ፥ 22 ። እግዚአብሔር በአካልና በስምና በግብር ሶስትነት ባይኖረው ኖሮ “እንደ እኔ ሆነ” በማለት ይናገር ነበር ። “ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” የሚለው ግን ብዙ ቁጥርን አመላካች በመሆኑ እግዚአብሔር አንድ ብቻ እንዳልሆነ ያስረዳናል ።
ዘፍ 11፥7 ። “ኑ እንውረድና ቋንቋቸውን እንደባልቀው አለ” ይህ ቃል አንዱ ሌሎቹን ኑ እንደሚል እንረዳለን ። በዚህም እግዚአብሔር ለአምላክነት ሥራው የማንንም እርዳታ እንደማይፈልግ የሚታወቅ ሲሆን በውስጡ ከሁለት በላይ እንደሆነ አንዱ ሌሎቹን “ኑ” በማለቱ ያስረዳል ።
ዘፍ 18 ፥ 1 ። እግዚአብሔር በመምሬ ዛፍ ስር ለአብርሐም ተገለጠለት ። አብርሐምም ዓይኑን አነሳና ሶስት ሰዎችን አየ የሚለው እግዚአብሔር በሶስትነቱ በሰዎች አምሳል ለአብርሐም መገለጡን በቁጥር ሶሰት ብሎ ያስረዳል ። ሀሳቡን ግልጽ ለማድረግ እግዚአብሔር ከሶስት ሰዎች ጋር ወይም ከሁለት መላእክት ጋር ተገለጠለት አይልም ። መላእክትም ሆኑ ሰዎች በዚህ ሥም አይጠሩም ኢሳ 42 ፥ 8 ። እስከዚህ ድረስ ብዛትን ብቻ ሲያመልክት የነበረው በዚህ ላይ ሶስት ብሎ ለይቶ ስለተናገረ እግዚአብሔር ሶስትነት ያለው መሆኑን በግልጽ ያስረዳል ።
የእግዚአብሔር ሶስትነት
እግዚአብሔር ፤ በስም ፤ በግብር ፤ በአካል ፤ ሶስት ነው ።
የስም ሶስትነት == አብ ፡ ወልድ ፡ መንፈስ ቅዱስ፡በመባል ነው ። “ሂዱና በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቋቸው” ማቴ ፳፰ ፥ ፲፱ ። የአብ ፍቅር ፤ የወልድ ፀጋ ፤ የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ፤ የሚለው ቃል ሶስትነቱን በግልጽ ያስረዳል ። 2ቆሮ 13 ፥ 14 ።
ስሙ (የወልድ) ፤ የአባቱ ስም ፤ የመንፈስ ቅዱስ ስም ፤ የተጻፈባቸው ። ራዕ 14 ፥ 1 ። ከላይ የተገለጹት የእግዚአብሔርን የስም ሶስትነት ያስረዳሉ ።
አብ ፤ በራሱ ሥም አብ ይባላል እንጅ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አይባልም ። ሶስቱም በየስማቸው ይጠራሉ ። ሃይ አበው ምዕ 11. ክፍል 1 ፡ 7 ።
“ሥላሴ” ማለት ሶስትነት ማለት ሲሆን ፤ የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ የሶስትነት ጥቅል ስም ነው ። “ሥላሴ” በምን ልበት ጊዜ አብ ፤ ወልድ ፤ መንፈስ ቅዱስ ፤ ማለታችን ነው ።
የግብር ሶስትነት == ግብር ሥራ ማለት ሲሆን ፤ በዚህ ትምህርት የእግዚአብሔርን የግብር ሶስትነት አብ አባት ፤ ወልድ ልጅ ፤ መንፈስ ቅዱስ ሰራጺ መሆናቸውን እናያለን ።
አብ ማለት አባት (ወልድን የወለደ) ። ማቴ 3፥17 ። አስራጺ ፡ መንፈስ ቅዱስን ያሰረጸ ። ዮሐ 15፥26 ።
ወልድ ፤ ተወላዲ (ከአብ የተወለደ) ። ሉቃ 1 ፥ 35 ። መንፈስ ቅዱስ ማለት ፤ ሰራጺ (ከአብ የሰረጸ) ። ዮሐ ፲፭ ፥ 26 ። ማለት ነው ።
አብ አባት ፣ ወልድ ልጅ ፣ መንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ (ሕይወት) ፣ በማለቱ ። የግብር ሶስነቱ የስሙን ሶስትነት ይገልጻል ። ይህ ማለት ግን አብ አባትና አስገኝ ፣ ስለተባለ ከአብና ከወልድ አይቀድምም አይበልጥም ፤ ወልድም ከአብ አያንስም ፤ ከመ ንፈስ ቅዱስ አያንስም ፤ መንፈስ ቅዱስም ከአብ ከወልድ አያንስም ። ሁሉም እኩል በአንድነትና በሶስትነት ይመሰገናሉ ።
የአካል ሶስትነት == ለአብ ፣ ለወልድ ፣ ለመንፈሰ ቅዱስ ለየራሳቸው ፍፁም ገጽ ፣ ፍፁም መልክ ፣ ፍፁም አካል፣ አላቸው ።
ገጽፊት ማለት ሲሆን፣ ከአንገታችን በላይ የሚታዩት የሰውነት ክፍሎቻችንን ዓይን ፣ ጆሮ…. የመሳሰሉትን ያጠቃልላል ።
መልክበእያንዳንዳቸው የሰውነታችን ክፍሎች (እግር ፣ እጅ ፣ ራስ ፣ ፀጉር ፣ ዓይን ፣ ጆሮ…..) ተብለው ሲቆጠሩ ነው ።
አካል በአጠቃላይ ሙሉው የሰውነታችን ክፍል ነው ። የፍጡራን አካል የሚታይ ፣ የሚዳሰስ ፣ የሚመጠን ፤ የሚወሰን ፣ ሲሆን የሥላሴ አካል ግን ፤ የማይታይ ፣ በእጅ የማይዳሰስ ፣ በቦታ የማይወሰን ፣ በሁሉም ሙሉ ነው ። መዝ 138 ፥ 7 ።
የእግዚአብሔር የአካል ሶስትነት ። በማቴ 3 ፥16 ። እንደተገለጠው አብ በደመና ፣ ወልድ በለበሰው ሥጋ ፣ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል በመሆን በግልጽ ታይቷል ። በሌላም በኩል ለአብርሐም በሶስት ሰዎች አምሳል የተገለጠለት ፣ በአካል ሶስት መሆኑን ሲያስረዳው ነው ። የሥላሴ ሶስትነት ከሰዎች የሂሳብ ቀመር ልዩ ስለሆነ (ቅድስት ሥላሴ) ልዩ ሶስትነት ይባላል ። በሂሳብ ህግ አንድ ሲሆን ሶስት…. የሚሆን ነገር የለምና ። የየራሳቸው የሶስትነት ፣ ሥም ፣ ግብር ፣ አካል ፣ አላቸው ።
የእግዚአብሔር አንድነት == የእግዚአብሔር ሶስትነት በሶስት ነገሮች በስም ፣በግብር፣በአካል፣ ብቻ ሲሆን በሌላው ሁሉ ለምሳሌ በባህርይ በህልውና ዮሐ 14 ፥ 8 ። በፈቃድ ፣ በሥልጣን ፣ በመፍጠር… ፣ አንድ ነው ። ለአብ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ በተለያየሥራና ደረጃ ተጽፎ ብናገኝም የስማቸውን የግብራቸውንና የአካላቸውን ሶስትነት ለመግለጽ እንጅ በአንዱ ሥራ ሁሉም አሉበት ። ዓለምን ፈጥሮ እየገዛ ያለ ፣ ሰው ሆኖ ዓለምን ያዳነ ፣ አምላክ አንድ ብቻ ነው ። ኤፌ 4 ፥ 5 ።
ኩነት (ከዊን) == ኩነት ወይም ከዊን ማለት ሁኔታ ወይም መሆን ማለት ሲሆን ፣ ይህም በሰው ነፍስ ምሳሌ ይገለጻል ። ነፍስ አንዲት ስትሆን ሶስት ባህርያት (ኩነታት) አሏት ፤ እነሱም ፤ ልብ (ማሰብ) ፤ ቃል (መናገር) ፤ እስትንፋስ (ሕይወት) ናቸው ። ከሶስቱ ባህር ያት አንዱ ከተጓደለ ነፍስ የሚለውን ስም ልታገኝ አትችልም ።
የእግዚአብሔር ሶስትነት በሰው ነፍስ ምሳሌ ሆኖ ቀርቧል ። ይኸውም አብ በልብ (ማሰብ) ፣ ወልድ በቃል (መናገር) ፣ መን ፈስ ቅዱስ በእስትፋስ (ሕይወት) ሲሆን አብ ለራሱ ልብ ሆኖ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ልባቸው ነው ። ወልድም ለራሱ ቃል ሆኖ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ነው ። መንፈስ ቅዱስም ለራሱ ሕይወት ሆኖ ለአብና ለወልድ ሕይወታቸው ነው ። በእግዚአብሔርነቱ ፤ ልብ ፣ ቃል ፣ ሕይወት አለ ። ነፍስ ሶስት ባህርያት ቢኖሯትም አንድ እንደምትባል እግዚአብሔርም ሶስት ስም፤ ሶስት ግብር ፤ ሶስት አካል ፤ ቢኖረውም አንድ አምላክ እንጅ ሶስት አማልክት አይባልም ። ዘዳ 6 ፥፬ ። ሚል 2 ፥ 10 ።
የእግዚአብሔርን አንድነትና ሶስትነት ለማስረዳት የቀረቡ ምሳሌዎች
ፀሀይ == አካል (መጠን) ብርሃን ሙቀት አላት ። በአካሏ አብ ፣ በብርሃኗ ወልድ ፣ በሙቀቷ መንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ሆነው ቀርበዋል ። ፀሀይ ሶስት ሁኔታዎች ሲኖሯት አንድ እንደሆነች እግዚአብሔርም አንድ ሲሆን ሶስት ፤ ሶስት ሲሆን አንድ አምላክ ነው ።
ውሃ == ይዘት(ስፋት) ፣ እርጥበት ፣ ቅዝቃዜ አለው ። በይዘቱ (በስፋቱ) አብ ፣ በእርጥበቱ ወልድ ፣ በቅዝቃዜው መንፈስ ቅዱስ ይመሰላሉ ። ውሃ አንድ እንደሆነ እግዚአብሔርም አንድ ሲሆን ሶስት ፤ ሶስት ሲሆን አንድ አምላክ ነው ። ሌሎቹም በምሳሌነት የሚቀርቡ ፍጥረታት አሉ ። ነገር ግን በምሳሌነታቸው ለማስተማር እንጅ የአምላክን ባህርይ የፍጡር ባህርይ ሊያስረዳ አይችልም ።
ምሥጢረ ሥጋዌ
ሥጋዌ : ተሰገወ ሰው ሆነ ካለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን : ምሥጢረ ሥጋዌ ማለት ሰው የመሆን ምሥጢር ማለት ነው::
አምላክ ለምን ሰው ሆነ?
አዳምን ከበደል ሊያነጻው አዳም የሰይጣንን ምክር በመስማት እግዚብአሔር አትብላ ያለውን ዕፀ በለስ በልቶ ትእዛዙን በማፍረሱ ከፈጣሪው በተጣላ
ጊዜ የሞት ፍርድ (ሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ) ተፈረደበት ። ዘፍ 3፥1 ። ለጥፋቱ ምክንያት የነበሩት ዕባብና ሄዋንም እንደ ጥፋታቸው መጠን ተረግመዋል ። ዘፍ 3፥14 ።
አዳምም ጥፋቱን አምኖ ንስሓ ስለገባ አምላክ ሰው ሆኖ እንደሚያድነው ቃል ገባለት ። ዘፍ 3 ፥ 22 ። ቃል ኪዳኑም “አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” የሚለው ሲሆን እግዚአብሔር ወልድበተለየ ስሙ ፣ በተለየ ግብሩ ፣ በተለየ አካሉ ፣ ሰው ሆኖ እንደሚ ያድነው ቃል መግባቱን ይገልጻል ።
ለአዳም በገባው ቃሉ መሰረት ጊዜው ሲደርስ ከተፈረደበት ፍርድ ነፃ ሊያወጣው (ሊያድነው) ሰው ሆነ ። ገላ 4 ፥ 4 ። ጊዜው ማለት አምስት ሺህ አምስት መቶ (አምስት ቀን ተኩል ሲፈጸም) ማለት ነው ። መዝ 84 ፥ 4 ።
የሥጋን በደል ለመካስ አዳም ፤ ዕፀ በለስን በበላህበት ቀን ሞትን ትሞታለህ (ዘፍ 2፥ 17) ያለውን አምላካዊ ቃል ተላልፎ በለስን በመብላቱ የሞት ፍርድ ከተፈረደበት በኋላ ንስሃ በመግባቱ አምላክ ትሞታለህ ያለው ፍርዱ ሳይሻር ይቅር ይለው ዘንድ ወደደ ። በመሆ ኑም በመለኮታዊ ባህርዩ ሞት ስለማይስማማው የሚሞት ሥጋን ለብሶ (ሰው ሆኖ) ቅጣቱን ሊቀበልለት ። ኢሳ 53፥1 ። የእግዚአብሔር ቸርነቱ የባህርዩ ስለሆነ ሞቱን ሞቶ ፍርዱን በመፈጸም ይቅር ብሎ ቸርነቱን በማድረግ ፍርዱንም ይቅር ባይነቱንም በአንድ ጊዜ ሊገልጽ ፈቃዱ ስለሆነ
ፍቅሩን ለመግለጽ እኛ ሰዎች ምንም ያህል ሰውን ብንወድ ቁሳዊ ነገር ልንሰጥ እንችላን ። እርሱንም ቢሆን ጥቅማችንን (ትርፋችንን)አይተን ነው ። አምላካችን ግን ከእኛ ምንም ላያገኝ ባህርዩን ዝቅ አድርጎ ደካማ ባህርያችችንን በመዋሃድ በአዳም የተፈረደውን ፍርድ እርሱ ተቀብሎ በማዳን እውነተኛ ፍቅሩን ሊገልጽልን ስለወደደ ። ዮሐ 15 ፥ 13 ። ዮሐ 10 ፥ ፲፩ ። ኢሳ 40 ፥ 11 ።
እንዴት ሰው ሆነ ?
የሚወለድበት ጊዜው ከመድረሱ አስቀድሞ በነቢያት አድሮ ምሳሌ አመስሏል ትቢት አናግሯል ። ምሳሌ የመልከ ጼዴቅ ክህነት። መልከ ጼዴቅ የጌታ ፤ አብርሐም የምዕመናን ። ዘፍ 14 ፥ 18 ። ዕብ 7፥ 1 ።
የይስሐቅ ቤዛ ሆኖ የተሰዋው በግ። ዘፍ 22 ፥18 ። ይስሐቅ የአዳም ፣ በግ የጌታ ምሳሌ ። ዮሐ 1፥29 ።
የእሥራኤል መና ። ዘፀ 16 ፥ 13 ። እሥራኤል የአዳም ፣ መና የጌታ ምሳሌ ። ዮሐ 6 ፥ 32 ። ግብፅ የሲኦል ፤ ከነዓን የመንግስተ ሰማያት ፤ ባህረ ኤርትራ የኃጢአት ፤ የሙሴ በትር የመስቀል ፤ ምሳሌ ሲሆን ሌሎችም በርካታ ምሳሌዎች አሉ።
ትንቢት
እግዚአብሔር በሴም ቤት ይደር ። ዘፍ 9፥26 ። እግዚአብሔር የተባለው ወልድ ቤት እመቤታችን ።
በዘርህ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ። ዘፍ 20፥17 ። ዘር የተባለ ጌታ አሕዛብ የተባሉ ሰዎች ። ገላ 3 ፥16 ።
ኮከብ ከያዕቆብ ይወጣል ። ዘኁ 24፥17 ። ኮከብ የጌታ ፤ ያዕቆብ የሰው ልጅ ምሳሌ ። ማቴ 2 ፥ 7 ።
2 ብስራተ መልአክን በተቀበለችበት ሰዓት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ባበሰራት ጊዜ እንደ ቃልህ ይደረግልኝ ብላ ስትቀበል ቃሏን ምክንያት አድርጎ መለኮታዊ ባህርዩን ከሰው ደካማ ባህርይ ጋር በማዋሀድና ከሁለት አካል አንድ አካል ፤ ከሁለት ባህርይ አንድ ባህርይ በመሆን ፍፁም ሰው ፤ ፍፁም አምላክ ሆነ ። ይህም ማለት መለኮታዊ ባህርዩን ከሰው ባህርይ ጋር አንድ አድርጎ(አዋህዶ) ሰውና አምላክ (ፍጹም ሰው ፤ ፍጹም አምላክ) ሆነ ። ሉቃ 1 ፥ 30 ። ማቴ 1 ፥ 23 ። ዮሐ 1 ፥ 14 ።
3 ሲዋሃድም
እንበለ ውላጤ፤ ያለ መለወጥ።
እንደ ሎጥ ሚስት ። ዘፍ 19 ፥ 26 ። እንደ ቃና ውሃ ። ዮሐ ፡ 2 ፥ 1 ። ያይደለ ።
እንበለ ቱሳሄ ፤ ያለመቀላቀል።
እንደ ማርና ውሃ ሳይቀላቀሉ ፤ በመጠባበቅ ቃልም ሥጋም ባህርያቸው ሳይለወጥ ።
እንበለ ቡዓዴ ፤ ያለ መለያየት።
እንደ ጥሬ እህል መለያየት ሳይኖር ከሥጋዌ በኋላ በተዋህዶ ይኖራል ።
እንበለ ኅድረት ፤ ያለ ማደር።
እንደ ልብስና ሳጥን ሳይሆን ፤ እንደ እሳትና እንደ ብረት ባለ ተዋሕዶ ።
እንበለ ትድምርት ፤ ያለ መጨመር። ዕቃ በዕቃ ላይ እንደሚደራረብና ሲፈለግ እንደሚለያይ ሳይሆን ፤ መለኮቱ ከትስብዕቱ (ከተዋሃደው ነፍስና ሥጋ) ጋር በፍፁም ተዋሕዶ አንድ በመሆን ተወለደ ።
ከማን ተወለደ ?
አምላክ የተወለደው ከእመቤታችን ከቅድስተ ቅዱሳን ከንጽህተ ንጹሃን ከድንግል ማርያም ሲሆን ፤ ከሷ እንደሚወለድም ፤ በእግዚአብሔር መነንፈስ በተቃኙ ቅዱሳን አማካኝነት አስቀድሞ ፤ ምሳሌ ተመስሏል ፤ ትንቢት ተነግሯል ።
ምሳሌ
እግዚአብሔር በሴም ድንኳን ይደር ። ዘፍ 9 ፥ 26 ። ድንኳን የእመቤታችን ፤ እግዚአብሔር ሰው የሆነው ጌታ ምሳሌ ። የአብርሐም ድንኳን ። ዘፍ 10 ፥ 18 ። ድንኳን የእመቤታችን ፤ በአብርሐም ቤት የተስተናገደው እንግዳ የራሱ ጌታ ምሳሌ የያዕቆብ መሰላል ። ዘፍ 28 ፥12 ። መሰላል የእመቤታችን ፤ በመሰላሉ ላይ የተቀመጠው ንጉሥ የክርስቶስ ምሳሌ ። የሙሴ ዕፅ ፥ሐመልማልና ነበልባል ። ዘፀ 3 ፥ 2 ። ሐመልማል የእመቤታችን ነበልባል የመለኮት ምሳሌ ። ውዳ ማር ። የሙሴ ጽላት ። ዘፀ 31 ፥ 18 ። የጽላቱ ማደሪያ የሆነው ታቦት የእመቤታችን ፤ ጽላት የጌታ ምሳሌ ። የጌዴዎን ፀምርና ጠል ። መሳፍ 6 ፥ 36 ። ፀምር የእመቤታችን ፤ ጠል የጌታ ፤ ምሳሌ ።
ትንቢት
“ሄዋን ትባል ” ። ዘፍ 2 ፥ 22 ። ሄዋን ማለት እመህያዋን ማለት ነው ። ይህ ስም የተሰጠው ለእመቤታችን ነው ። የመጀ መሪያዋ ሄዋን ሞትን ያመጣች ስትሆን ፤ እመቤታችን ግን የሕይወት ባለቤት የሆነው ጌታ ከእሷ ስለተገኘ መሠረተ ሕይወት የሕይወት መገኛ ብለን እንጠራታለን ። መዝ 45 ፥4 ። ልዑል ማደሪያውን ቀደሰ ። ልዑል የተባለው አምላክ ሲሆን ፤ ማደሪያው የተባለች ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማህፀኗ ተሸክማ የወለደችው የአምላክ እናት እመቤታችን ናት ።
የተቆለፈች ገነት ። መኃ 4 ፥ 45 ። ይህ እመቤታችን አምላክን በድንግልና መውለዷንና ዘለዓለማዊ ድንግልናዋን የሚያስረዳ ሲሆን ፤ በተጨማሪም በህዝቅኤ 44 ፥ 1 ። ላይ ያለው ይህን ግልጽ ያደርገዋል ።
እነሆ ድንግል ወልድን ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ይሉታል። ኢሳ 7 ፥ 14 ።ይህ ቃል በቀጥታ የእመቤታችንን የአምላክ እናትነቷን ይገልጻል ። ድንግል የተባለች እሷ ፤ ወልድ (ልጅ) የተባለ ልጇ አማኑኤል ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና ።
የነቢያት ትንቢት ሲፈጸም ፤ በህጋዊና በተቀደሰ ጋብቻ ከሚኖሩ ኢያቄምና ሐና በብሥራተ መልአክ እመቤታችን እንድት ወለድ አደረገ የተወለደችውም አዳምና ሄዋን ሳይበድሉ በነበራቸውና መርገም (ጥንተ አብሶ የመጀመሪያ በደል) ባልተላለፈበት ንፁህ አካል ነው ። ከእሷ የሚወለደው አምላክ ለባህርዩ ኃጢአት ስለማይስማማው ፤ የሰዎችን ሁሉ በደል ለመቀበልም ንፁህ መሆን ስላለበት ፤ ይህንም ከአምላክ በቀር የሚያሟላ ባለመኖሩ ፤ ከእሷ ሊወለድ ከመርገም ንፁህ እንድትሆን አደረገ ።
እመቤታችን ነሐሴ 7 ተፀንሳ ግንቦት 1 ሊባኖስ በሚባል ቦታ ተወለደች ። ኢያቄምና ሐና የወለዷት በስለት ስለነበረ በተወለደች ከሶስት ዓመቷ ጀምሮ ለ12 ዓመታት ያህል በቤተ መቅደስ አደገች ። 15 ዓመት ሲሆናት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ተልኮ መጥቶ አምላክን ትውልጃለሽ ብሎ ባበሰራት ጊዜ እንደ ቃልህ ይደረግልኝ ብላ ስትቀበል ቃሏን ምክንያት አድርጎ አምላክ ከሥጋዋና ከነፍሷ ከፍሎ ከመለኮቱ ጋር በማዋሃድ መጋቢት 29 ተፀንሶ ታህሳስ 29 ተወለደ ። በዚህም ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባህርይ አንድ ባህርይ ሆነ የሃይማኖታችን ስያሜም ኦርቶዶክስ ተዋሕዶመባሉ በዚህ ምክንያት ነው ።
የት ተወለደ ?
በሚክያስ 5 ፥2 ። እንደተነገረው ጌታችን የተወለደው በቤተ ልሔም ከተማ በከብቶች በረት ውስጥ ነው ። ህዝቡ ሁሉ እን ዲጻፍ(እንዲቆጠር) ትእዛዝ ተላልፎ ስለነበረ ዮሴፍ እመቤታችንን ይዞ ሊመዘገብ ከናዝሬት ወደ ቤተ ልሔም በሄደበት ወቅት ከህዝቡ ብዛት የተነሳ ቤት አጥተው በከብቶች በረት ተጠግተው አደሩ በዚያም እያሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰና የዓለም መድኃኒት የሆነ ክርስቶስን በድንግልና ወለደች ። ማቴ 1 ፥ 18 ። ሉቃ 2 ፥ 1 ። በተወለደ ጊዜ አስቀድሞ ትንቢት ተነግሮላቸው የነበሩ ሰብአ ሰገል ፤ እስከ ቤተ ልሔም ድረስ ኮከብ እየመራቸው መጥተው ወድቀው ሰገዱለት ፤ ዕጅ መንሻውንም (ወርቅ ዕጣን ከርቤ) ሰጡት ። ማቴ 2 ፥ 11 ።
በአካባቢው የነበሩ እረኞችም በዙሪያው የሚያበራውን ብርሃን አይተው መልአኩ እየመራቸው ጌታ ከተወለደበት ዋሻ ደር ሰው የጌታን መወለድ አይተዋል ። ከመላእክት ጋር ሆነው ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር፤ በሰማያት ምስጋና ተደረገ በምድርም ሰላም ሆነ ለሰው ልጅ በጎ ፈቃድ
በማለት ዘምረዋል ። ሉቃ 2 ፥ 14 ።
ምሥጢረ ጥምቀት
ጥምቀት ማለት ፤ መጠመቅ ፤ መነከር ፤ መደፈቅ ፤ በውሃ ውስጥ ብቅ ጥልቅ ማለት ነው ።
የጥምቀት ምሳሌዎች
በብሉይ ኪዳን ዘመን የተፈጸሙና ለአማናዊው የሐዲስ ኪዳን ጥምቀት ምሳሌ ከነበሩት መካከል የሚከተሉትን እናያለን ።
የጥፋት ውሃ በኖኅ ዘመን በበደላቸው ተጸጽተው ንስሓ ያልገቡ ሰዎችንና (ከኖኅና ቤተሰቡ እንዲሁም ለዘር እንዲቀሩ ከተደረጉት ፍጥረታት በቀር) በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ያጠፋው ማየ አይኅ(የጥፋት ውሃ) የጥምቀት ምሳሌ ሲሆን ፤ ከጥፋት ውሃ የዳኑት ኖኅና ልጆቹ ፤ ከክርስቶስ ጎን ለጥምቀታችን በፈሰሰው ትኩስ ውሃ በጥምቀት ከእግዚአብሔር ተወልደው ከፍርድ ለሚድኑ ምዕመናን ምሳሌ ነው። ዘፍ 7 ፥ 1 ። ዘፍ ፥ 19 ፡ 1 ። 1ዼጥ 3 ፥ 28 ።
ግዝረት ዘፍ 17 ፥ 14 ። ግዝረት ለጊዜው ለእስራኤል ዘሥጋ መለያ ሲሆን ፤ ፍጻሜው ግን ሊመጣ ላለውና ለእሥራኤል ዘነፍስ ምዕመናን መክበሪያ ለሆነው ለጥምቀት ምሳሌ ነው ። ቆላ 2 ፥ 14 ።
የኤርትራ ባህር (ቀይ ባህር) ዘፀ 14 ፥ 21 ። 1ቆሮ 10 ፥ 1 ። ሙ ሴ የክርስቶስ ፤ ባህሩን የከፈለባት በትር የመስቀል ፤ ባህረ ኤርትራ የፍርድና የሲኦል ፤ በተከፈለው ባህር የተሻገሩት እስራኤል በመስቀሉ ላይ በፈሰሰው ደሙ በጥምቀት ከእግዚአ ብሔር ተወልደው ባህረ ኃጢአትን የሚሻገሩ ምዕመናን ምሳሌ ነው ።
የዮርዳኖስ ባህር ኢያሱ 3 ፥14 ። ኢያ 4 ፥ 15 ። ኢያሱ የክርስቶስ ፤ ዮርዳኖስ የጥምቀት ፤ ይርዳኖስን የተሻገሩ እስራ ኤል በክርስቶስ አምነው በመጠመቅ የዳኑ ምዕመናን ምሳሌ ነው ።
የዮሐንስ ጥምቀት ማቴ 3 ፥1 ። ዮሐንስ ህዝቡን የንስሓ ጥምቀት እያጠመቃቸው ከቆየ በኋላ ጌታ በሚመጣበት ጊዜ ግን እነሆ የእግዚአብሔር በግ በማለት ወደ ጌታ መርቷቸዋል ስለዚህ የዮሐንስ ጥምቀት ምሳሌ ሆኖ ለአማናዊዉ የጌታ ጥምቀት የሚያዘጋጅ ነው
የጥምቀት አመሰራረት
ጥምቀትን የመሠረተው ጌታችን ሲሆን ፤ የተጠመቀበትም ምክንያት ።
በብሉይ ኪዳን ያልተገለጸ አንድነት ሶስትነቱን (ምሥጢረ ሥላሴን) ለመግለጽ ። ማቴ 16 ፥ 17 ።
እንዴት በማንና የት መጠመቅ እንዳለብን ሊያስተምረን አብነት ሊሆነን ። ዮሐ 13 ፥ 12 ።
ጠላት ዲያብሎስ በዮርዳኖስ የጣለውን የዕዳ ደብዳቤያችንን ለመደምሰስ ። ቆላ 2 ፥ 16 ።
አዳምና ሄዋን ዕፀ በለስን በልተው የአምላካቸውን ትእዛዝ በመተላለፋቸው የተወሰደብንን ልጅነት የምናስመስልበትንና ከእግዚአብሔር የምንወለድበትን አማናዊ ጥምቀት በዮሐንስ እጅ ተጠምቆ ከመሰረተልን በኋላ ፤ በጸሎተ ሐሙስ ማታ የሐዋርያትን እግር በማጠብ አሳይቷቸዋል። ምክንያቱም በዚያ ሰዓት ቅዱስ ዼጥሮስ እኔ አጥብሀለሁ እንጅ አንተ የእኔን እግር አታጥበኝም ብሎ በተከራከረበት ጊዜ ፤ ካላጠብሁህ ከእኔ ጋር አንድነት የለህም ማለቱ ከእግዚአብሔር አንድ የምንሆንበት በመንፈስ የምንወለድበት ብቸኛው መንገድ ጥምቀትመሆኑን እንረዳለን ።
ጌታችን ጥምቀትን ከመሠረተልን በኋላ እኛም ከውሃና ከመንፈስ በመወለድ ልጅነትን ተቀብለን መንግስቱን እንደምንወርስ ለኒቆዲሞስ ያስተማረውን እናስታውሳለን ። ዮሐ 3 ፥ 1።
ለሐዋርያትም ሥጢረ ጥምቀት በጸሎተ ሐሙስ ይፈጸምላቸው እንጅ መንፈስ ቅዱስ የወረደላቸው ጌታ በተነሳ በአምሳኛው ፤ ባረገ በአስረኛው ቀን ነው ። ከነሱ በኋላ ምዕመናን ሲጠመቁ መንፈስ ቅዱስ በእሳት አምሳል ሲወርድባቸው በግልጽ ይታይ ነበር ። የሐ ሥ 2 ፥ 1 ። የሐ ሥ 8 ፥ 14 ።
ጌታችን በዮርዳኖስ የተጠመቀው የተነገረውን ትንቢት የተመሰለውን ምሳሌ ለመፈጸም ነው ።
ምሳሌ
አብርሐም የአሕዛብን ነገሥታት ድል አድርጎ ሲመለስ ዮርዳኖስን መሻገሩ ፤ የምዕመናን ጥምቀት መልከ ጼዴቅ የጌታ ም ሳሌ ። ዘፍ 14 ፥ 17 ። ዕብ 6 ፥ 1 ።
እሥራኤል ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ርስታቸው ከነዓን መግባታቸው ፤ ምዕመናን አምነው ተጠምቀው ወደ ሰማያዊቷ ርስታቸው መንግስተ ሰማያት የመግባታቸው ምሳሌ ። ኢያ 3 ፥ 14 ።
ኤልያስ ዮርዳኖስን ተሻግሮ ማረጉ ምዕመናን ተጠምቀው ዕርገተ ነፍስ የማግኘታቸው ምሳሌ ። 2ነገ 2፥8 ።
ንዕማን በዮርዳኖስ ተጠምቆ ከለምጽ መዳኑ ፤ ምዕመናን ተጠምቀው ከነፍስ ለምጽ የመዳናቸው ምሳሌ ። 2ነገ 5 ፥ 14 ።
ትንቢት
ባህርም አይታ ሸሸች : ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ : ተራሮች እንደ ኮርማዎች ዘለሉ ። መዝ 113፥3 ።
በውሃ የተጠመቀበት ምክንያት
ውሃ በየትም ቦታ ስለሚገኝ ፤ ሰዎች በቀላሉ ልጅነትን አግኝተው መንግስተ ሰማያት እንዲወርሱ ።
ውሃ የደረቁ ዕፀዋትን እንደሚያለመልም ፤ ምዕመናን ተጠምቀው ልምላሜ ነፍስ እንዲያገኙ ።
ውሃ ከእድፍ እንደሚያነጻ ፤ ምዕመናንም ተጠምቀው ከኃጢአት እንዲነጹ ። የሐ 2፥38 ። ህዝ 36 ፥25 ።
ውሃ እሳትን እንደሚያጠፋ ፤ ምዕመናንም ተጠምቀው ከገሃነመ እሳት እንዲድኑ ። ማቴ 3 ፥ 6-12 ።
በጥምቀት የሚገኝ ጥቅም
በምንጠመቅበት ጊዜ በመርገም ከተላለፈብን ኃጢአት ሥርየት እናገኛለን ። ህዝ 36፥25 ። የሐ 2፥38 ።
በጥምቀት ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ስንወለድ ፤ የተወሰደብን ልጅነታችን ይመለስልናል ዮሐ 3 ፥ 1 ።
ያላመነ ያልተጠመቀ ይፈረድበታል ። ከሚለው የገሃነመ እሳት ፍርድ እንድናለን ። ማር 16 ፥ 16 ።
በውሃው ስንደፈቅ ከክርስቶስ ጋር የመሞታችን ፤ ከውሃ ስንወጣ የመነሳታችን ምሳሌ ። ሮሜ 6 ፥ 3 ።
በጥምቀት ከጌታችን ጋር: ገላ 3 ፥ 27 ፤ ከምዕመናን ጋር አንድ እንሆናለን ። ቆላ 2 ፥ 11 ።
ለጥምቀት የተወሰነ ዕድሜ
በሐዋርያት ስብከት ያመኑና በማንኛውም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሁሉ ይጠመቁ ነበር የሐ ሥራ 16 ፥ 15 ። 1ቆሮ 1 ፥ 15 ። በኋላ ግን ወላጆቻቸው ሊያስተ ምሯቸው ቃል እየገቡ ልጆቻቸውን ወንዶችን በአርባ ሴቶችን በሰማንያ ቀናቸው ማጥመቅ ተጀመረ ።
ለዚህም መሠረቱ የእስራኤል ልጆች በተወለዱ ወንድ በአርባ ሴት በሰማንያ ቀናቸው ወላጆቻቸው መባዕ (ስጦታ) ይዘውላቸው ወደ ቤተ መቅደስ እየሄዱ በእስራኤልነት (የዜግነት) መዝገብ እያስመዘገቡ የተስፋዋ ምድር ከነዓን ባለመብቶች (ወራሾች) ያደርጓቸው እንደነበረ ሁሉ ፤ ዛሬም ህጻናት ወላጆቻቸው ሃይማኖታቸውን ሊያስተምሯቸው ሃላፊነት ወስደው የክርስትና አባት ወይም እናት በተጨ ማሪ ቃል ገብተው ክርስትና በመነሳት (በመጠመቅ) የወላጆቻቸውን ርስት መንግስተ ሰማያትን ይወርሳሉ ።
ከአርባ እና ከሰማንያ ቀን በኋላ የሚመጡ ተጠማቂዎች ግን ሃይማኖታቸውን ተምረው ካመኑ በኋላ በማንኛውም የዕድሜ ክልል መጠ መቅ ይችላሉ ። በሕይወት እስካሉ ድረስ መቸም ቢሆን ከመጠመቅ የሚያግዳችው ነገር የለም ።
አንድ ተጠማቂ የሚያሟላቸው ነገሮች ከመጠመቁ በፊት ተጠማቂው ሃይማኖቱን በሚገባ ተምሮ ማመንና መመስከር አለበት ። ተጠማቂው ህጻን ከሆነ ወላጆቹ ወይም የክርስታና አባት እናት ቀርበው ሊያስተምሩት ቃል መግባት አለባቸው ።
በሚጠመቅበት ጊዜ በውሃ ውስጥ ሶስት ጊዜ ብቅ ጥልቅ ማለት አለበት ፤ የክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ ምሳሌ ነውና ። ተጠማቂው የሚጠመቀው በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ነው ። ማቴ 28 ፥ 19 ። ተጠማቂዎች ባለትዳሮች ከሆኑና ቤተሰብም ካላቸው ሁሉም ተምረው አምነው በአንድነት መጠመቅ አለባቸው::
ከተጠመቀ በኋላ መቁረብ (ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል) ይገባል ። ይህ ካልሆነ ጥምቀቱ ህያው አይሆንም ። ቃሉ ሥጋዬን ካልበላችሁ ደሜንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም ይላልና። እያንዳንዱ ለእርሱ ሲል የተቆረሰውን ቅዱስ ሥጋና የፈሰሰውን ክቡር ደም ተቀብሎ ከበደሉ መንጻት አለበት። በጥምቀት የተቀበልነው ልጅነት የሚረጋገጠው ሥጋውንና ደሙን ስንቀበል ብቻ ነውና ።
ጥምቀት አንዲት ናት ። ኤፌ 4፡5
ከወላጆቻችን በሥጋ የምንወለደው አንድ ጊዜ ብቻ እንደሆነ ሁሉ ከውሃና ከመንፈስም ከእግዚአብሔር የምንወለደውም (የምንጠመቀው) አንድ ጊዜ ብቻ ነው ። በመሆኑም ጥምቀት አንዲት ናት አትደገምም ።
የጥምቀት ምሳሌ የነበረው ግዝረት አንድ ጊዜ ብቻ እንደነበረ ሁሉ ጥምቀትም አንድ ጊዜ ነው ። ቆላ 2 ፥ 11 ።
ከጌታ ሥጋና ደም የምንሳተፍበት ምሥጢር በመሆኑ ጌታም የሞተውና የተነሳው አንድ ጊዜ ነውና አንድ ጊዜ ብቻ እንጠመ ቃለን ። ሮሜ 6 ፥ 3 ። በእኛ ቤተ ክርስቲያን ከተጠመቀ በኋላ በሌላ ሃይማኖት ገብቶ እንደገና ቢጠመቅ ወይም ከሌላ እምነት ተከታይ ጋር ጋብቻ ቢመሠርት በንስሓ ከተመለሰ በኋላ መጽሐፈ ቄድር ተጸልዮለት ይጠመቃል ። ይህ ግን ሁለተኛ ጥምቀት ሳይሆን የንስሓ ጥምቀት ይባላል ።
ከኦርቶዶክሳውያን ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት (Oriental Churches) በቀር በሌላ ማንኛውም ቤተ ክርስቲያን ከተጠመቀ በኋላ አምኖ የሚመጣ ሰው ቢኖር እንደገና ይጠመቃል ።
ምሥጢረ ቁርባን
ቁርባን ፤ ማለት ፣ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ አምኃ ፣ መስዋዕት ፣ መንፈሳዊ ነገር ሁሉ ማለት ሲሆን ፤ በዚህ ትምሕርታችን ግን ፤ ስለ ሐዲስ ኪዳን መስዋዕት (የክርስቶስ ሥጋና ደም) እንማራለን ።
በብሉይ ኪዳን ለሐዲስ ኪዳን ቁርባን (መስዋዕት) ምሳሌዎች
የመልከ ጼዴቅ መስዋዕት ዘፍ 14 ፥ 18 ። ዕብ 5 ፥ 6 ። ዕብ 6 ፥ 1 ። ህብስቱ የሥጋው ፤ ወይኑ የደሙ ምሳሌ ፤ መልከ ጼዴቅ የክርስቶስ ፤ አብርሐም የምዕመናን ።
የእስራኤል ፋሲካ ። ዘፀ 12 ፥ 1 ። ሞት የዲያብሎስ ፤ እስራኤል የምዕመናን ፤ በጉ የክርስቶስ ምሳሌ ።
የእስራኤል መና ። ዘፀ 16 ፥ 13 ። መና የጌታችን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ፤ እስራኤል የምዕመናን ፤ ደመና የእመቤታችን
በብሉይ ኪዳን መስዋዕት ቁርባን ያቀረቡና በረከት ያገኙ አባቶች አዳም አባታችን አዳም ባቀረበው መስዋዕት ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን በኋላ ሰው ሆኖ እንደሚያድነው ቃል ገባለት ። ዘፍ 3 ፥ 22 ። ገላ 4 ፥ 4 ።
ኖኅ ባቀረበው መስዋዕት ለኖኅና ለልጆቹ ምድርን ዳግም በመቅሰፍት እንደማያጠፋት በቀስተ ደመና ምልክት ቃል ገባላቸው ። ዘፍ 9 ፥ 1 ። ዘፍ 9 ፥ 8 ።
አብርሐም ዘፍ 18 ፥ 3 ። አባታችን አብርሐም ባቀረበው መስዋዕት በዘርህ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ የሚለውን የተስፋ ቃል ሰማ ፤ ያም ዘር የተባለው ለጊዜው ይስሐቅ ሲሆን፤ ፍጻሜው ግን ለጌታ ነበር ።
መልከ ጼዴቅ ዘፍ 14 ፥ 17 ። መዝ 109 ፥ 4 ። ዕብ 5 ፥ 6 ። በእግዚአብሔር ፊት ባቀረበው መስዋዕት ክህነቱ ለዘለዓለም ተብሎለት የክርስቶስ ምሳሌ ሆነ ። ዕብ 7 ፥ 1 ።
ዳዊት መዝ 131 ፥ 11 ። መስዋዕት ባቀረበበት ሠዓት ከአብራክህ የተገኘው ልጅህ በዙፋንህ ይነግሣል ተባለለት ፤ ይህም ለጊዜው የተነገረው ለሰሎሞን ሲሆን ፍጻሜው ለክርስቶስ ነበር ። መዝ 71 ፡1 ። ሌሎችም በእግዚአብሔር ፊት ንጹህ መስዋዕታ ቸውን እያቀረቡ በረከት ተቀብለዋል።
ምሥጢረ ቁርባን በሐዲስ ኪዳን
በብሉይ ኪዳን ዘመን ይቀርብ የነበረው የመስዋዕት ቁርባን ፤ ከበግ ፤ ከላምና ፤ ከተለያዩ እንስሳት ነበር ። በሐዲስ ኪዳን ግን እንስሳት በቤተ መቅደስ ውስጥ መስዋዕት (ቁርባን) ሆነው አይቀርቦም መስዋዕት ሁሉ በክስቶስ ሥጋና ደም ተጠቃሏል ። ይህንም የአዲስ ኪዳን መስዋዕት የመሠረተው ራሱ ጌታችን ሲሆን ፤ በጸሎተ ሐሙስ ማታ አስራ ሁለቱ ሐዋርያት እንዳሉ በመጀመሪያ መስዋዕተ ኦሪትን ሰርቶ ካሳለፈ በኋላ ኅብስቱና ወይኑን ባርኮ “ነገ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬና የሚፈሰው ደሜ ይህ ነው ብሉ ጠጡ ብሎ ሰጣቸው” ። ማቴ 26 ፥ 26 ።
ዛሬ ካህኑ ኅብስቱን በጻህል ወይኑን በጽዋ አድርጎ ጸሎተ ቅዳሴውን እየጸለየ.. ሲባርከው እንደዚያ ጊዜው ኅብስቱ ተለውጦ ሥጋ መለኮት ወይኑም ተለውጦ ደመ መለኮት ይሆናል ። ይህንም ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም በምንቀበልበት ጊዜ ለእኛ ሲል የተቀበለውን መከራና ስቃይ እያሰብን ራሳችንን በንስሓ ከኃጢአት ንጹህ አድርገን ከንስሓ የቀረውን በደላችንን እንደሚደመስ ስልን ፤ ከበደል እንደሚያነጻንና የዘለዓለም ሕይወት እንደሚሰጠን አምነን መሆን አለበት ።
በ1ቆሮ 11 ፥ 23 “ይህንም ለመታሰቢያዬ አድርጉት ” የሚለው ቃል ሥጋውንና ደሙን በምንቀበልበት ጊዜ ስለሰው ልጆች ሲል በቀራንዮ አደባባይ የተበውን መከራና በልባችን ውስጥ የተሳለውን አምላካዊ ፍቅሩን እያስታወስን እንድንኖር ነው መታሰቢያ የሚለው ቃል የሚያመለክተው የማይረሳ ነገርን ነውና ። ገላ 3፥1
ጌታችን ይህን ምሥጢር ከማሳየቱ (ከመመስረቱ) በፊት በዮሐ 6 ፥ 25-8 ። “ሥጋዬን ካልበላችሁ ደሜንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም ሥጋዬን የበላ ደሜንም የጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ (ሕይወትን የሚሰጥ) ነው ” በማለት ስለምሥጢረ ቁርባን በስፋት አስተምሯል ።
የቅዱስ ቁርባን ጥቅም
ከዚህ ዓለም በሞት ብንለይም እንኳን በሰማያዊ መንግስት የማያልፈውን የዘለዓለም ሕይወት እናገኛለን ። ዮሐ 6 ፥ 54 ።
ለኃጢአታችን ስርየት (ፍጹም ድኅነት) እናገኛለን ። ማቴ 26 ፥ 26 ።
ከጌታችን ጋር ከቅዱሳንም ጋር ያለንን አንድነት እናረጋግጠጣለን ። 1 ቆሮ 10 ፥ 17 ።
ሥጋውን በስንዴ ደሙን በወይን ያደረገበት ምክንያት ትንቢቱንና ምሳሌውን ለመፈጸም ነው
ትንቢት በልቤ ደስታ ጨመርሁ ከስንዴ ፍሬና ከወይን ፍሬ በዛ ። መዝ 4 ፥ 7 ። ይህም ቃል እውነተኛና ፍጹም የሆነው ዘለዓለማዊ መድኃኒት ቅዱስ ቁርባን በስንዴና በወይን እንደሚደረግ ያመለክታል ።
ምሳሌ የክርስቶስ ምሳሌ፤ መልከ ጼዴቅ መስዋዕት የሚያቀርበው በስንዴና በወይን ስለነበረ ምሳሌውን ለመፈጸም ። ዘፍ 14 ፥ 17 ።
ሥጋውንና ደሙን በምግብ ያደረገበት ምክንያት
ምግብ ከሰውነት ጋር እንደሚዋሃድ ሥጋውንና ደሙን ስንቀበል በእውነት እንደሚዋሃደን ለማስረዳት።
ምግብ ለሥጋችን ኃይል እንደሚሆነን ሥጋውና ደሙም ለነፍሳችን መንፈሳዊ ኃይል ይሰጠናል።
አዳምና ሄዋን በምግብ የእግዚአብሔር ልጅነታቸውን እንዳስወሰዱ ፤ በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ ልጅነታችንን ሊመልስልን ። ዘፍ 3 ፥ 1 ። ዮሐ 6 ፥ 49።
ቅዱስ ቁርባንን ፤ በበላችን ንስሓ ከገባን በኋላ ሁልጊዜ መቀበል ይገባናል ። የኃጢአታችን ስርየት የሚረጋገጠው በቅዱስ ቁርባን ነውና ። ማቴ 27 ፥ 27።
ምዕመናን በሕይወት እስካሉ ደረስ ወንድም ይሁን ሴት ፣ ታናሽም ይሁን ታላቅ ከቅዱስ ቁርባን መለየት የለባቸውም ይህ ምሥጢር በፆታ በዕድሜ የማይገደብ ለሁሉ የተሰጠ ነውና ። ዮሐ 6 ፥ 54 ። በሰራነው ስህተት ተጸጽተን ንስሓ ሳንገባ በድፍረት ሥጋውንና ደሙን መቀበል የለብንም ፤ ይህን የሚያደርጉ ሰዎች ዕዳ አለባቸው ። 1ቆሮ 11 ፥ 27 ። የምንቀበለው ቅዱስ ቁርባን ጌታችን በቀራንዮ አደባባይ ተሰቅሎ ከዋለ በኋላ ፤ ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን በራሱ ሥልጣን ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው ለይቷል ። ዮሐ 10 ፥ 18 ። ዮሐ 19 ፥ 30 ። በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ሄዶ በዚያ የነበሩ ነፍሳትን ወደ ገነት ከመለሰ በኋላ ሶስት መዓልትና ሶስት ሌሊት በከርሠ መቃብር ከነበረው ሥጋ ጋር በፈቃዱ አዋህዶ ተነሳ ፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ግን(ሥጋውና ደሙ በተለያዩበት ወቅት) መለኮት ፣ ከነፍ ስም ከሥጋም ጋር አልተለየም ። 1ዼጥ ። ስለዚህ እኛ የምንቀበለው ሥጋና ደም ፤ ነፍስ የተለየችው መለኮት የተዋሃደው ነው ። 1ዼጥ 3 ፥ 18 ።
ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን
1 የጌታችን ትንሣኤ
ስለ ጌታችን ሞትና ትንሣኤ የተነገረ ትንቢት ፤ የተመሰለ ምሳሌ
ትንቢት
እኔ ተኛሁ አንቀላፋሁ ፤ እግዚአብሔር (እግዚአብሔርነቴ) ደግፎኛልና ነቃሁ ። መዝ 3 ፥ 5 ።
እግዚአብሔር ይነሣ ፤ ጠላቶቹም ይበተኑ ፤ የሚጠሉትም ከፊቱ ይሽሹ ። መዝ 27 ፥ 1 ።
እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሳ ። መዝ 77 ፥ 65 ።
ምሳሌ
ዮናስ ፤ ሶስት ቀንና ሶስት ሌሊት በዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ ማደሩ ፤ ለጌታችን ሞትና ትንሣኤ ምሳሌ ፤ እንደነበረ ጌታችን ተናግሯል ። ዮና 3 ፥ 1 ። ማቴ 12 ፥ 40 ።
በዮርዳኖስ ባህር ውስጥ ገብቶ መጠመቁ የሞቱ ፤ ከባህር መውጣቱ የትንሣኤው ምሳሌ ነበር ።
ጌታችን ዓርብ ከቀኑ በዘጠኝ ሠዓት ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በፈቃዱ ከለየ በኋላ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከዺላጦስ አስፈቅ ደው ዮሴፍ ለራሱ ባዘጋጃት መቃብር ከቀኑ በ11 ሠዓት ቀበሩት ።
ሥጋው ሶስት መዓልትና ሶስት ሌሊት በከርሠ መቃብር ሲቆይ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ሄዶ በግዞት የነበሩ ነፍሳትን (አዳምን ከነልጆቹ) ወደ ቀደመ ቦታቸው ከመለሰ በኋላ ቅድስት ነፍሱንና ቅዱስ ሥጋውን በፈቃዱ አዋሕዶ ቅዳሜ ማታ ለእሑድ አጥቢያ ከሌሊቱ በ6 ሠዓት ተነሳ። መለኮት ግን(ሳይከፈል) ከነፍስ ጋር በሲኦል ፤ ከሥጋ (በመቃብር) ጋር አልተለየም ። ጌታችን በአካለ ነፍስ በሲኦል የቆየው (ዓርብ ከቀኑ ዘጠኝ ሠዓት እስከ ቅዳሜ ሌሊት ስድስት ሠዓት) ለ32 ሠዓታት ያህል ነው ። በሥጋው 33 ዓመታት በምድር ፤ ነፍሱ ከሥጋው እስክትዋሃደችበትና እስከተነሳበት ጊዜ 33 ሠዓታት በሲኦል መቆየቱን እንረዳለ ።
ጌታችን ሶስት ቀንና ሌሊት በመቃብር ቆየ ማለት ዓርብ ከአስራ አንድ ሠዓት በኋላ ያለው እንደ ሃያ አራት ሠዓት ተቆጥሮ አንድ ቀንና ሌሊት ሲባል ፤ ዓርብ ማታና ቅዳሜ ቀን ሁለተኛ ቀንና ሌሊት ፤ የቅዳሜ ሌሊት ስድስቱ ሠዓት ከእሑድ ቀን ጋር ተቆጥሮ ሶስተኛ ቀንና ሌሊት ይሆናል።
ይህም በባህረ ሐሳብ ትምህርት መዓልት ይስህቦ ለሌሊት ፤ ወሌሊት ይስህቦ ለመዓልት ። ቀን ሌሊትን ፤ ሌሊትም ቀን ፤(የኋለኛው የፊተኛውን ፤ የፊተኛው የኋለኛውን) ይስበዋል ፤ በሚለው አቆጣጠር ነው።
የጌታችን ትንሣኤ ለሰዎች ትንሣኤ አብሳሪ(በኩር) ነው ። 1 ቆሮ 15 ፥ 20 ። እኛም እንደ እሱ ባለ ሞት (እርሱን በማመን ፀንተን) ከሞትን እንደ እርሱ ባለ የክብር ትንሣኤ ያስነሳናል ። ሮሜ 6፥5 ። ጌታችን ቅዳሜ ሌሊት ለእሑድ አጥቢያ ከከሌሊቱ በ6 ሠዓት ከተነሳ በኋላ ለሐዋርያት ሶስት ቀን ተገልጾላቸዋል ። ይኸውም
በተነሳበት ቀን እሑድ ከቀኑ በ11 ሠዓት ደቀ መዛሙርቱ በዝግ ቤት ወስጥ ተቀምጠው እያሉ ተገለጠላቸው ። ሉቃ 24 ፥ 36 ። ዮሐ 20 ፥ 19 ።
በተነሳ በሳምንቱ እንደዚሁ በዝግ ቤት ውስጥ እንዳሉ ሰላም ለእናንተ ይሁን ብሎ በድጋሚ ተገለጠላቸው ። ዮሐ 20 ፥ 26 ።
በተነሳ በ25ኛው ቀን (ርክበ–ካህናት) ለሶስተኛ ጊዜ በጥብርያዶስ ባህር አጠገብ ተገልጦ ከእነሱ ጋር ማዕድ በላ ። ዮሐ 21 ፥ 1-14 ።
በነዚህ ጊዜያት ውስጥ ሰባቱን ኪዳናት እያስተማራቸው ከቆየ በኋላ ፤ መንፈስ ቅዱስን እስክልክላችሁ በኢየሩሳሌም ቆዩ ብሏቸው በአርባኛው ቀን በቢታንያ አደባባይ እያዩት ወደ ሰማይ ዐረገ ፤ በአምሳኛው ቀን መንፈስ ቅዱስን ላከላቸው ።
2 የሰው ልጆች ትንሣኤ
የሰው ልጆች ሁሉም ከዚህ ዓለም በሞት ይለያሉ ። ይሁንና እግዚአብሔር የወሰናት የምጽዓት (የዓለም ፍጻሜ) ቀን ስትደርስ ሁሉም ሰዎች ከሙታንነታቸው ህያዋን ሆነው ይነሳሉ ። ሲነሱ እኩሌቶቹ (ጻድቃን) ለክብር ፤ እኩሌቶቹ (ኃጥዓን)ለፍርድ(በሰሩት ክፉ ሥራ ሊፈረድባቸው) ነው ። ዮሐ 5 ፥ 29 ።
ስለ ሰው ልጆች ትንሣኤ አስቀድሞ ትንቢት ተነግሯል፥ ምሳሌ ተመስሏል
ትንቢት
ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ ፤ ሬሳዎችም ይነሳሉ ፤ ምድርም ሕያዋንን ታወጣለችና ። ኢሳ 26 ፥ 19 ።
በምድርም ዙሪያ ካንቀላፉት ብዙዎች ይነቃሉ ፤ እኩሌቶቹ ወደ ዘለዓለም ሕይወት እኩሌቶቹ ወደ ዘለዓለም ሀፍረትና ጉስቁልና ይሄዳሉ ። ዳን 12 ፥ 1 – 3 ።
እርሱ ሰብሮናልና ይጠግነናል ከሁለት ቀን በኋላ ያድነናል ፤ በሶስተኛውም ቀን ያስነሳናል ። ሆሴ 6፥2 ።
ምሳሌ የአቤል ሞት ለሞታችን ። ዘፍ 4፥ 8 ። የሄኖክ ዕርገት ለትንሣኤያችን ። ምሳሌ ነው ። ዘፍ 5 ፥ 24 ።
እስራኤል ወደ ግብጽ መውረዳቸው ለሞታችን ። ዘፍ 46 ፥ 1 ። ከግብጽ ወጥተው ከነዓን መግባታቸው ለትንሣኤያችን ምሳሌ ነው ። ግብጽ የመቃብር ፤ ከነዓን የትንሣኤ (የመንግስተ ሰማያት) ምሳሌ ናትና ። ዘፀ 14 ፥ 21 ።
የአልዓዛር ሞቱ ለሞታችን ፤ በአራተኛው ቀን መነሳቱ ለትንሳኤያችን ምሳሌ ነው ። ዮሐ 11 ፥ 1- 44 ። ሌሎችም ትንሣኤ ሙታንን የሚያመለክቱ በርካታ ምሳሌዎች አሉ ።
ሰው የተፈጠረው እንዲሞት ሳይሆን በሕይወት እንዲኖር ነበር ። ይሁን እንጅ በቃኝን በማያውቀው ፍላጎቱ የተሰጠው ሥልጣን አልበቃ ብሎት በዕባብ ውስጥ ባደረው በሰይጣን ምክር ተታሎ ፤ ያልተሰጠውን አምላክነት ሲፈልግ በመገኘቱ ሞት ተፈረደበት ። በአንዱ ሰው አዳም በደል ምክንያትም ሞት ወደ ዓለም መጣ ። ሮሜ 5 ፥ 12 ። በአዳምና በልጆቹ (በሰው ዘር ሁሉ) ላይ የተፈረደው የሞት ፍርድ ሁለት ማለትም ሞተ ነፍስና (ወደ ገሃነም መውረድ) ሞተ ሥጋ (ወደ መቃብር መውረድ) ሲሆን ሞተ ነፍስ አምላካችን ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን በቀራንዮ አደባባይ ተሰቅሎ ባፈሰሰው ደሙና በቆረሰው ሥጋው ስለተደ መሰሰ አምነው ከተጠመቁ በኋላ ይህን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ለሚቀበሉ ምዕመናን ቀርቶላቸዋል ። የሥጋ ሞት ግን ሁሉም ሰዎች እስኪጠናቀቁ ግዛቱ ይቀጥላል ፤ ሁሉንም ይገዛ ዘንድ ሥልጣን ተሰጥቶታልና ። 1 ቆሮ 15 ፥ 26 ።
የሙታን አነሳስ
ሙታን ከመነሳታቸው በፊት መልአኩ 3 ጊዜ የመለከት አዋጅ (ንፍሐተ ቀርን) ያሰማል ። 1 ተሰ 4 ፥ 16
በመጀመሪያው (ንፍሐተ ቀርን) የመለከት ድምጽ የሞቱ ሰዎች አጠቃላይ የሰውነት ክፍላቸው በሙሉ ይሰባሰባል ።
በሁለተኛው የመለከት አዋጅ ፦ የሰውነት ክፍሎቻቸው ከደምና ከሥጋ ጋር ተገጣጥመው የማይንቀሳቀስ በድን ይሆናሉ ።
በሶስተኛው የመለከት አዋጅ ፦ የሰው ልጆች ሁሉ በሕይወት ዘመናቸው የሠሩትን መልካምም ሆነ ክፉ ሥራቸውን ይዘው ፤ ወንዶች የሰላሳ ፤ ሴቶች የአስራ አምስት ዓመት ዕድሜ ያህል ሆነው ይነሳሉ ። ሲነሱም ጻድቃን ፈጣሪያቸውን ክርስቶስን መስለው ፤ ኃጥዓንም አለቃቸውን ዲያብሎስን መስለው ይነሳሉ ።
ከዚህ በኋላ ጌታችን በክበበ ትስብዕት (በለበሰው ሥጋ እየታየ) በግርማ መነግሥት (በሚያስፈራ የመለኮት ግርማ) ሆኖ በመላእክት ታጅቦ የተሰቀለበትን መስቀል ፊት ለፊቱ አደርጎ ይመጣል ። መስቀል የፍርድ ምልክት ነውና በዚህ ጊዜ በቀራንዮ አደባባይ በግፍ ሰቅለው የገደሉት አይሑድ ያፍራሉ ። ማቴ 25፥31 ።
ጌታችን ፤ ጻድቃንን በበግ ፥ ኃጥዓንን በፍየል ይመስላቸዋል
ይህም ማለት የሰውነት ባህርያቸው ተለውጦ በጎችና ፍየሎች ይሆናሉ ማለት ሳይሆን በሕይወት ዘመናቸው በዚህ ዓለም ሲኖሩ የሰሩት ሥራቸው በበጎችና በፍየሎች ምሳሌ ሆኖ ስለቀረበ ያንኑ ለማስረዳት ነው ።
በጎች፦ እረኛቸው ባሰማራቸው ቦታ ረግተው ይውላሉ፤ ጻድቃንም እውነተኛ እረኛቸው ክርስቶስ በሰራላቸው ህግ ጸንተው ይኖራሉና ። ዮሐ 10 ፥ 1 ። ዮሐ 21 ፥ 15 ።
ፍየሎች ፦ ለእረኛ አስቸጋሪዎች ናቸው ፣ በአንድ ቦታ መርጋትም አይችሉም ። ኃጥዓንም በተፈቀደላቸው ህግ አይኖሩም ወረተኞች ቀላዋጮች ናቸው ።
በጎች ፦ ጥቂት ሳር ካገኙ ተስማምተው ይበላሉ ። ጻድቃንም ኑሮዬ ይበቃኛል ፡ በማለት ያለቻቸውን ከድሆች ጋር ተካፍለው ይበላሉ ።
ፍየሎች ፦ የሚበሉት ሳሩ ቅጠሉ እያለ እርስ በእርሳቸው ሲጣሉ ፤ ሲያጉረመርሙ ይውላሉ ። ኃጥዓንም ሁሉ እያላቸው ሲጣሉ ሲካሰሱ ፤ ሲገዳደሉ ፤ የሌላውን ሲመኙ ፤ ሲሰርቁ ፤ ይኖራሉ ። የበጎች ፦ ኀፍረተ ሥጋቸው በላታቸው የተሸፈነ ነው ። የጻድቃንም ኃጢዓታቸው በንስሓ የተሰወረ ነው ።
የፍየሎች ፦ ኀፍረተ ሥጋቸው የተገለጠ ፤ ላታቸው የተሰቀለ ነው ። ኃጥዓንም ነውራቸው ለሁሉ የተገለጠ ኀፍረት የሌላቸው ደፋሮች ፤ በነውራቸውና በክፉ ሥራቸው የሚመኩና የሚኩራሩ ፤ ናቸው ። በጎች ፦ ሲሄዱ አንገታቸውን ወደ ታች አቀርቅረው ነው ፤ ጻድቃንም ሲኖሩ አንገታቸውን ደፍተው ራሳቸውንዝቅ አድርገው በትህትና ነው ።
ፍየሎች፦ ሲሄዱ አንገታቸውን አቅንተው ሽቅብ እያዩ ነው ፤ ኃጥዓንም ሲኖሩ ከአቅማቸው በላይ በማሰብ በትዕቢት ተወጥረው ፤ ከእኛ በላይ አዋቂ ለኀሳር እያሉ የሌላውን ሥራ በማኮሰስ ነው ።
በጎች ፦ ከጓደኛቸው አንዱን ተኩላ ፡ ቀበሮ ፡ ከበላባቸው ፡ አካባቢውን ለቀው ይሄዳሉ ፡ በረው ይጠፋሉ ። ጻድቃንም ከመካከላቸው አንዱ በሞት ቢነጠቅ ነገም ለእኛ ብለው ራሳቸውን ለንስሐ ያዘጃሉ
ፍየሎች ፦ ከጓደኛቸው አንዱን አውሬ ቢነጥቀው ለጊዜው ዘወር ይሉና ፥ በኋላ ረስተውት ተመልሰው በአካባቢው ሳሩን ቅጠሉን ሲበሉ ይገኛሉ ። ኃጥዓንም ከመካከላቸው አንዱ በሞት ሲነጠቅ ለጊዜው ያዘኑ ይመስሉና ጥቂት ቆይተው የሞተውን ሰውዬ ረስተውት ፤ ጥሎት በሄደው በሃብቱና በንብረቱ ሲጣሉ ሲካሰሱ ይታያሉ ።
ጌታችን ለፍርድ ሲቀመጥ ጻድቃንን በቀኙ ኃጥዓንን በግራው ያቆማቸዋል ። ማቴ 25 ፥ 31 ።
ምሳሌነቱም ፦
ቀኝ ፈጣን ነው ። ጻድቃንም ለበጎ ሥራ ፈጣኖች ፡ ትጉኃን ናቸውና ።
ግራ ዳተኛ ነው ። ኃጥዓንም ለመልካም ነገር ዳተኞች ናቸው ፤ አይመቻቸውም ።
ቀኝ ከግራ ይልቅ ጠንካራ ነው ። ጻድቃንም ለበጎ ሥራ ብርቱዎች ናቸው ።
ግራ ከቀኝ ይደክማል ። ኃጥዓንም ጹሙ ጸልዩ ሲባሉ ፣ አይችሉም ይሰንፋሉ ።
ቀኝ ለሥራ ይመቻል ቀና ነው ። ጻድቃንም ለበጎ ነገር ቅኖች ናቸውና ።
ግራ ጠማማ ነው ለሥራ ብዙም አይመችም ። ኃጥዓንም ሃሳባቸው የተወላገደ ፤ በቃላቸው የማይገኙ ፤ በባህርያቸው ተለዋዋጮች ናቸው ።