ከሩካቤ ሥጋ የምንታቀብበት ጊዜያት/ቀናት/ እና ምክንያት

አሥራ አምስቱ ከሩካቤ ሥጋ የምንከለከልባቸው ጊዜያት/ቀናት/ እና ምክንያት ከነ ማብራሪያቸው

ፈታ ተደርገው በማያዳግም ሁኔታ ስለተጻፉ ተረጋግታችሁ በረዝምም በትዕግስት አንብቡ ‹‹ትዳር እና ሕገ ሩካቤ ችግሩ እና መፍትሔው›› ከሚለው በቅርቡ ከሚታተመው ያለሰስት እንድታነቡት የቀረበ

ቀሲስ መምህር ሄኖክ ወልደ-ማርያም

አንደ ቤተ ክርስትያን ቀኖና በአጽዋማት ወቅት ‹‹ሩካቤ ይፈጸማል ወይስ አይፈጸምም›› የሚለው ጥያቄ ‹‹በጾም ዓሳ ይበላል ወይስ አይበላም›› ብሎ እንደመጠየቅ ነው፡፡ የሁለቱ አንድነትን እና ልዩነት ክፉኛ የታመመን ሰው ይመስላል፡፡ በትዳር ውስጥ ያለ ሰው በጾም ወቅት ጾር ቢነሳበት ልክ እንደታመ ሰው ሁለት መፍትሔ ነው ያለው፡፡ አንደኛው ሕመምህን ቻል ሲሆን ሁለተኛው ለሕመምህ ማስታገሻ ጾሙን አፍረሰህ መድኃኒት ውሰድ ማለት ነው፡፡ ከሰውዬው ችግር/ሕመም አንጻር መፍትሔው ሕመምህን ቻል ብሎ የሰውዬውን ስቃይ ማብዛት ሳይሆን መድሃኒቱን ሰጥቶ ለጊዘው ሕመሙን ማስታገስ ነው፡፡ ሌላው ዓሳ በጾም እንደማይባላ እያወቀ የሚበላበት ምክንያት ሳይኖረው ዓሳ መብላት ማለት በጾም ወቅት የጾር ምክንያት ሳይኖርበት ሩካቤ ሥጋን የሚፈስጽም ሰውን ይመስላል፡፡

በጾም ወቅት ጾር ለሚያስቸግራቸው ባል እና ሚስት ሩካቤ ሥጋ በደፈናው ክልክል ነው ማለት በሰው ቁስል እንጨት እንደመስደድ ነው፡፡ ማንም የሰውን ፈተና ሳይረዳ ክልክል ነው በማለት የትዳር የፍቅር መሰላቸት ውስጥ ሰውን መክተት የለባቸውም፡፡ በእርግጥ በጾም ወቅት ሩካቤ ክልክል ቢሆንም ቀኖና ስለሆነ ከንስሃ አባት ጋር በመመካከር ለችግሩ እልባት ማበጀት ወይም መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

የሩካቤ ሥጋ ጉዳይ የመንፈሳዊ አባታቸው/ንስሐ አባታቸው/ ውሳኔ ወሳኝ ነው፡፡ መፍትሔውም ከቀኖና መጽሐፍ ይልቅ በእነሱ እጅ ነው ያለው፡፡ ምክንያቱም የቀኖና መጽሐፎች ቁርጥ ያለውን ውሳኔ ስለያዙ ችግሩ የበለጠ ለንስሐ አባታቸው መሬት ያለ ነገር ስለሚሆን ውሳኔ ሰጭነታቸው ላይ ሚናቸው ከፍተኛ ነው፡፡ የሩካቤ ሥጋ ጾር ትዳርን እስከ ማፍረስ የሚደርስ አንገብጋቢና ስስ ጉዳይ ስለሆነ ንስሐ አባት ትዳር የማይፈርስበትን ውሳኔና መፍትሔ መስጠት ይገባዋል፡፡ በተለይ ከቀኖና አንጻር ብቻ ሳይሆን ከችግርና ከፈተና አንጻር በሰፊው ማየት ይገባቸዋል፡፡

አንዳንድ የነፍስ አባትና ባለ ትዳሮች በጾም ወቅት ቀኖና በማፍረስ ሩካቤን ማይፈቅዱበት፣ ባለ ትዳሮችም ከሚፈሩበት ጉዳይ በጾም ወቅት የሚፈጠር ጽንስ እንደ ርኩስ ወይም እንዳልተባረከ የመቁጥር ጉዳይ አለ፡፡ ይሄ ታላቅ ስህተ ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈለገው ጽንስ ከሆነ እንኳን በሕጋዊ ሩካቤ ቀርቶ በዝሙት የመጣውን ጽንስ ባርኮ ለራሱ ዓላማ ያውለዋል፡፡ ስለዚህ በትዳር የሩካቤ ሥጋ ጉዳይ ቀኖናው በካህናት እጅ ነው፡፡ ግን ያለ ልዩ ፈተና ገና ለገና ቀኖናው በካህኑ እጅ ነው በማለት አጽዋማት ከበዓአላት፣ከሰንበታት ሳይሉ ሩካቤ ሥጋ መፈጸም አይቻልም፡፡ ፈተናው ቢበዛብንም፣ባንችልም የንስሐ አባታችንን ቃል ማክበር አለብን፡፡ ምናልባት ጾሩን መሸከም አቅቶን የንስሐ አባታችን ሩካቤ ሥጋን የመፈጸም ፈቃድ ቢሰጡን ተፈቅዶልኛል ተብሎ እንደፈለግነውና በፈለግነው ጊዜ አይፈጸምም፡፡ ፈተናችንን በምናልፍበት እና በምናስታግስበት መልኩ መሆን አለበት፡፡

ወዳጆቼ ፍትወት በአንዳንድ ሰዎች ላይ እጅጉን ይጸናል፡፡ ፍትወት የሚጸናባቸው ሰዎች በትዳራቸው የሚገጥማቸው አንዱ ፈተና ጾሙን ለመተግበር ብለው ከትዳር አጋራቸው ጋር ግጭት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ሩካቤ ሥጋ እያሰቡ በፍትወተ ሥጋ እየተሰቃዩ እየተቃጠሉ ከማደር መምህረ ንስሐን በማማከር ሩካቤን መፈጸም ይሻላል፡፡ መምህረ ንስሐችን የማናገር እድል እንኳን ባናገኝ በገዛ ሥጋችን በፍትወት እንዳንቃጠል ሩካቤ ሥጋን ፈጽሞ ከንስሐ አባታችን ጋር መመካከር ይገባል፡፡ ግን ንስሐ አባትን ሳያማክሩ በድንገተኛ የፍትወት ግፊት ሩካቤ ሥጋን ከፈጸማችሁ በኃላ የንስሐ አባታችሁን ማማከር ወይም መንገር ግድ ይላችኃል፡፡ እዚህ ላይ ልብ ልትሉት የሚገባው የፍትወት ፈተና በአጽዋማት ቢገጥማችሁና በዚህ ችግር ሩካቤ ሥጋ የመፈጸም ግዴታ ውስጥ ብትገቡም ወደ ረብዕ፣ዓርብ፣ቅዳሜና እሑድ ምሽት ግን መቆጠብ ይገባናል፡፡

ደግሞም ሰይጣን ትዳርን ለማፋታት ከሚጠቀምባቸው ምንገዶች አንዱ በአጽዋማት ጊዜ የፍትወት ጾር በማንሳት እና በማብዛት ነው፡፡ ታድያ ያንን ጾሩን የምናልፍበት አንዱ መፍትሔ ሩካቤው ነው፡፡ ሰይጣን የባልን የሩካቤ ፍላጎት በመቀስቀስ ሚስትን ሊፈትን ይችላል፡፡ በዚህን ጊዜ ሚስት የጾሙን የቀኖና ሕግ ለማስጠበቅ ሩካቤውን ትከላከላለች፡፡ ይህ ደግሞ ባልን በገዛ ሚስቱ ስልጣን ያሳጣው፣ችግሩን የማትጋራው ስለሚመስለው ከጭቅጭቅ እስከ ጸብ ያደርሳቸዋል፡፡ ባስ ሲልም ወደ ሌላ የመሄድና የዝሙት ጣጣን ያመጣል፡፡ ፈተናና ችግርን ያላገናዘብ ግን ለቀኖና ዘብ የቆመ መከላከል ለሰይጣን በር የሚከፍት እንዳይሆን ተጠንቀቁ መፍትሔውንም እወቁ፡፡

እስኪ ሩካቤ ሥጋ የሚከለከልበት ወቅት እና ምክንያት እንመልከት ፦

ጥያቄያችንን ከመመለሳችን በፊት ‹‹ሩካቤ ለምን በበዓላት መፈጸም ተከለከልን?›› የሚለውን አጥርተን እንለፍ፡፡ በዓላት የምንላቸው የጌታ ልደት/በዓለ ገና/ ትንሳኤ እና የዓመት ክብረ በዓላት ናቸው፡፡ በዚህ ውስጥ ግዝት በዓላት የሆኑት 12፣21፣ 29/ቅዱስ ሚካኤል፣እመቤታችን እና በዓለ ወልድ/ ይካተታሉ፡፡ በእነዚህ ቀናት ሕጋዊ ሩካቤ እንደ ቀኖና የምንከለከለው ወይም የምንታቀበው እነዚህ ቀናት ለመንፈሳዊ ሰው የሥጋ ተግባር የሚፈጽምበት ሳይሆን የነፍሱን ሥራ የሚያከናውንበት ስለሆነ ነው፡፡ ባለ ትዳሮች በእነዚህ ቀናት ቢቻል እራሳቸው ካልቻሉ ልጆቻቸውን የሚያቆርቡበት እና ቤተ ክርስትያን ሄደው ከወትሮ በተለየ ጸሎት የሚያደርጉበት ቀን ስለሆነ ከሩካቤ መታቀብ አለባቸው፡፡ በበዓላት የሚፈጸሙ ሕጋዊ የትዳር ሩካቤዎች ለመንፈሳዊ ሕይወት እንቅፋቶች ስለሆኑ መታቀብ ይገባናል፡፡

1ኛ/ የጾም ወቅቶች ፦ በአጽዋማት ጊዜ ሩካቤ ሥጋ መከልከሉ የነፍስን
ሥራ እድንሠራ እና በጾም በጸሎት እድንተጋ ነው፡፡ አጽዋማት በተለይ የነፍሳችንን ጉዳይ የምናዘወትርበት ጊዜ ስለሆነ ከሥጋ ፈቃድ መታቀቡ ለመንፈሳዊ ሰው ውዴታው ነው፡፡ እንዲሁም አባቶቻችን በፍትሐ ነገስት ላይ ሥርዓት አድርገው ስለ ሰሩልን ነው፡፡ ፍትሐ ነገ በአብይ ጾም፣በገና ጾም፣በሐዋርያት ጾም፣በፍልሰታ ጾም፣በነነዌ ጾም ወቅት ነገረ ሩካቤያችንን ጠቅልሎ ‹‹በተቀደሱ የጾም ወራት አታሳድፏቸው›› ይለናል፡፡ /ፍትሐ ነገ አንቀጽ 24 ቁጥ 922/

2ኛ/ በሰሞነ ሕማማት ፦ በሰሞነ ሕማማት አንዳንዶች በፍትወት ይፈተናሉ፡፡ በሰሞነ ሕማማት የፍትወር ጾር እጅጉን የሚያስቸግራቸው ይኖራሉ፡፡ ግን በሰሞነ ሕማማት የእኛን የሥጋ ደስታ ሳይሆን የጌታን ሕማም፣ስቃይ፣እንግልት፣ግርፋት፣ስቅለት እና ሞት የምናስብበት ስለሆነ ሩካቤ ሥጋ ክልክል ነው፡፡ ይህንንም ፍትሐ ነገ በአንቀጽ 24 በቁ. 923 ላይ ‹‹በሰሞነ ሕማማት ይህቺን ኃጢአት ለሚሠራት ወዮለት፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሠራው ጋብቻ ግን ልጆችን ለመውለድ ብቻ አይደለም፡፡ ስለማይጠበቅ ፈቃድም ነው እንጂ፡፡ እግዚአብሔር አንድ ጊዜ የሚጠበቁበትን አንድም ጊዜ ፈቃዳቸውን የሚፈጽሙበትን ሠራ፡፡ ነገር ግን በርኩሰት አይሁን›› ይላል፡፡ ወዳጆቼ በሰሞነ ሕማማት የሚፈጸም ሩካቤ ሥጋ ኃጢአት ነው፡፡ በትዳር ላይ ሩካቤ ሥጋ ኃጢአት ባይሆንም እንዲህ በተከለከሉ ቀናት ግን ኃጢአት ነው፡፡ ምክንያቱም ሩካቤው ርኩስ ይሆናልና፡፡

3ኛ/ ዓብይ ጾም ፦ በዓብይ ጾም ጌታችን በገዳመ ቆሮንጦ ተጋድሎ ገድልን ያስተማረበት፣በሰይጣን ተፈትኖ ድል መንሳትን ያሳየበት እና የጾም የጸሎትን ሥርዓትን የሠራልን ስለሆነ በዓብይ ጾም በጾም በጸሎት በስግደት የምንጋደልበት እንጂ ሩካቤ ሥጋ እየፈጸምን ሥጋችንን የምናስደስትበት ጊዜ አይደለም፡፡ ስለዚህ በዓብይ ጾም በመንፈሳዊ ሕይወት የምንበረታበት፣ከሩካቤ ሥጋ ደግሞ የምንታቀብበት ታላቅ ጊዜ ነው፡፡

4ኛ/ የነብያት ጾም ፦ ይህ በተለምዶ የገና ጾም የምንለው ነው፡፡ በመሠረቱ የገና ጾም ሳይሆን ጾመ ነብያት/የነብያት ጾም ነው የሚባለው፡፡ የገና ጾም የሚባል የለም፡፡ ገና የሚባል የጌታ የልደት በዓል ነው ያለው፡፡ ስለዚህ በዚህ ጾም ወቅት የሥጋ ተግባር የሆነውን ሩካቤ ሥጋ ትተን የነፍሳችን ሥራ የምንሠራበት ወቅት ነው፡፡

5ኛ/ ጾመ ሐዋርያት ፦ የሐዋርያትን ጾም በተለምዶ የቄሶች ጾም እያልን ከጾም የምንሳነፍበት ጊዜ ነው፡፡ ቄሶቹ በምን ዕዳቸው እንዲጾሙ በምዕመናኑ እንደተበየነባቸው ባላውቅም በጾመ ሐዋርያትም ከሩካቤ ሥጋ መታቀብ እንዳለብን ፍትሐ ነገሥቱ ይደነግጋል፡፡

6ኛ/ ጾመ ፍልሰታ ፦ ይህቺ የእመቤታችን ጾም ለአንዳንዶች ትልቅ ፈተና ትሆናለች፡፡ ሲሆን በጾመ ፍልሰታ እንኳን ሩካቤ ሥጋ ልፈጽም ቀርቶ ማሰብብ አይገባንም፡፡ ምክንያቱም ጾመ ፍልሰታ ብንችል ከቤታችን ወጥተን አንድ ገዳም በሱባኤ ተወስነን ለሐዋርያት የተለመነችውን እመቤታችንን እኛም የምንማጸንበት እና በሱባኤ የምናሳልፍበት ውድ ጊዜ ናት፡፡ ካልተቻለ ደግሞ በቤታችን ሆነን ሌሊት ሰዓታት እየገባን ቀን እያስቀደስን የወለላይቱን እመቤት በረከት የምናገኝበት እንጂ በሩካቤ ሥጋ ወድቀን በረከት የምናጣበት መሆን የለብንም፡፡

7ኛ/ ዓርብ እና ረቡዕ ፦ ዓርብ እና ረብዕ ከአዋጅ ጾሞች ውስጥ ናቸው፡፡ ስለዚህ ባል እና ሚስት አርብ እና ረብዕ እለት መቼም የፍስክ የሆነ ለምሳሌ ሥጋ አይበሉም፡፡ በዓርብ እና ረብዕ ሥጋ መብላት አስቡት ምን ሊሰማችሁና ሥጋው ምን ምን ሊላችሁ እንደሚችል፡፡ እንደውም ዓርብ እና ረብዕ ሥጋ እንብላ ብትሉ የአሕዛብ ሥጋ የበላችሁ ሊመስላችሁ ይችላል፡፡
ስለዚህ ዓርብ እና ረብዕ ዕለት ሥጋ እንደማንበላ ሁሉ ዓርብ እና ረብዕ እለት ሩካቤ ሥጋ አንፈጽምም፡፡ ይህም የሚሆንበት ምክንያት ዓርብ ጾመ ድኅነት ነው፡፡ ረብዕም ምክረ አይሁድ ነው፡፡ ዓርብ ቀን ነው ጌታ ለእኛ ብሎ ተገርፎ ተሰቅሎ በሞቱ ሕይወቱን የሰጠን፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ቀናት ቢቻል እንደ ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድና አቡነ መብዓ ጽዮን የጌታን መከራ በጾም፣በጸሎትና በስግደት የምናስብበት እንጂ የሥጋ ደስታችንን የምናስብበት ቀን መሆን የለበትም፡፡

8ኛ/ ሁለቱ ሰንበታት፦ እነሱም ቅዳሜ እና እሁድ ናቸው፡፡አንዳንዶች ቅዳሜ የአይሁድ ሰንበትና በዛላይ በእሁድ ተተክታለች ስለዚህ ቅዳሜ ሩካቤ ብንፈጽም ምን ችግር አለው ይላሉ፡፡ ችግሩ መፈጸሙ ላይ ብቻ ሳይሆን ቅዳሜ ሩካቤ ሥጋ ብንፈጽም በማግስቱ እሑድ ቤተ ክርስትያን አንገባም አንቆርብም፡፡ ስለዚህ ቅዳሜ ሩካቤ መፈጸም ቅዳሜ ለእሁድ እንቅፋት ትሆናለች፡፡ ዋናው ግን በቀኖና ተከልክላለች፡፡ ታላቋ እሑድም ነፍሳችን የእግዚብሔር ቃል እና ቅዱስ ቁርባን የምትመገብበት እንጂ ፈቃደ ሥጋን የምንፈጽምበት ቀን አይደለችም፡፡ በእሑድ እንኳን እኛ በሲኦል ያሉት ነፍሳት የነፍስ እረፍት የሚያገኙበት ስለሆነ እኛም ነፍሳችንን የምናሳርበት ብትሆንም በቀኖና ሩካቤ ሥጋ እንዳንፈጽምባት የተከለከለች ናት፡፡

እግዚአብሔር በነብዩ ኢሳይያስ አንደበት ‹‹ፈቃድህን በተቀደሰው ቀኔ ከማድረግ እግርህን ከሰንበት ብትመልስ፣ሰንበትንም ደስታ፣እግዚአብሔርም የቀደሰውን ክቡር ብትለው፣ የገዛ መንገድህንም ከማድረግ ፈቃድህንም ከማግኘት ከንቱ ነገርም ከመናገር ተከልክለህ ብታከብረው፣በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፣በምድር ከፍታዎች ላይ አወጣሃለሁ፣የአባትህንም የያዕቆብ ርስት አበላሃለሁ፡፡ የእግዚአብሔር አፍ ተናግሯል›› በማለት ሰንበትን ማክበር ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር ባዘዘን መልኩ ብናከብር እኛም እንደምንከብርና የያዕቆብ ርስት የተባለችውን ገነት መንግሥተ ሰማያትን እንደምንወርስ ነግሮናል፡፡ /ኢሳ 58÷13-14/ ተወዳጆች ሆይ በሁለቱ ሰንበታት በተቀደሰውንም ቀን ፈቃዳችን ከመፈጸምና በገዛ የሥጋ መንገዳችን ከመሄድ ተከልክለን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነገር እንተግብር፡፡ በዚህም ከዘላለማዊው ከያዕቆብ ርስት ተካፋይ እንሆናለን፡፡

9ኛ/ በዓበይት በዓላት እና በዓመታዊ በዓላት ፦ በጌታችን ዓበይት በዓላት ሩካቤ ሥጋ መፈጸም ክልክል ነው፡፡ የጌታ ዓበይት በዓላት የሚባሉት መጋቢት 29 ብሥራት፣ታህሳስ 29 ልደት፣ጥር 11 ጥምቀት፣ ነሐሴ 13 ደብረ ታቦር፣ሆሳዕና፣ስቅለት፣ትንሤኤ፣ዕርገት እና በዓለ ጰራቂልጦስ ናቸው፡፡ በእነዚህ ዓበይት የጌታ በዓላቶች ከሩካቤ ሥጋ ልንታቀብባቸው ይገባል፡፡
ዓመታዊ በዓላት የምንላቸው ለምሳሌ የሐምሌና እና የጥር ሥላሴ፣የታህሳስ እና የሐምሌ ቅዱስ ገብርኤል፣የታህሳስ እና የነሐሴ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣የሚያዝያ ጊዮርጊስ ወዘተ በእነዚህ ዓመታዊ የመላእክት፣የቅዱሳን የሰማዕታት በዓላት በተቻለን አቅም ከሩካቤ ሥጋ ታቅበን ብንችል ቅዱስ ቁርባን መቀበል ካልሆነልን ግን በገዳማቸው፣በደብራቸው ሄደን አስቀድሰን አንግሠን ተባርከን በረከታቸውን አግኝተን የምንውበት ቀን መሆን አለበት እንጂ ሩካቤ ሥጋ ፈጽመን ታቦታቸውን ለማንገሥ እና በበዓላቸው ለማስቀደስ የምንቸገርበት ቀን ሊሆንብን አይገባም፡፡

10ኛ/ የወር አበባ ጊዜ ፦ በወር አበባ ጊዜ ሩካቤ ሥጋን እንኳን ቅድስት ቤተ ክርስትያናችንም ሳይንሱም ይከለክላል፡፡ ሳይንሱ በጥናት የደረሰበት አንድ ወንድ የወር አበባ ላይ ካለች ሴት ጋር ሩካቤ ሥጋ ቢፈጽም ደዌ ሊሆንበት ይችላል፡፡ በወር አበባ ወቅት ሩካቤ ሥጋ መፈጸም ምቾች ማጣት ብቻ ሳይሆን ለአባለ ዘር በሽታ እና ላለመውለድ ችግረ ሊዳረጉ ይችላሉ፡፡

ፍትሐ ነገ አንቀጽ 24 ቁ. 922 ላይ ‹‹በደምዋ ወራት አትገናኛት፡፡ ጋብቻህ ያለ ሕግ እንዳይሆን እግዚአብሔር በሙሴ አንደበት እንዲህ ብሎ ያዘዘህን አስብ፡፡ አንድ ሰው ግዳጅ ወዳገኛት ሴት ቢቀርብ ያለ ልጅ ይጥፋ ይሙት ብለህ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው፡፡ እነርሱ ንጹሑን ዘር ከግዳጅዋ ደም ውስጥ በመጨመራቸው አላከበሩምና›› በማለት ዘሌ 20÷18 ላይ ያለውን ጠቅሶ ይከለክለናል፡፡ በዘሌ 20 ÷ 18 ላይ ‹‹ማንኛውም ሰው ከባለ መርገም ሴት ጋር ቢተኛ ኃፍረተ ሥጋዋን ቢገልጥ፣ፈሳሽዋን ገልጧልና፣እርስዋም የደምዋን ፈሳሽ ገልጣለችና ሁለቱ ከሕዝባቸው መካከል ተለይተው ይጥፉ›› ተብሎ ተጽፏል፡፡ በእርግጥ በሐዲስ ኪዳን ዘመን ግዳጅ ላይ ያለች ሚስት ጋር የደረሰ ወንድ እንደ ኦሪቱ ይጥፋ ባይባልም ኃጢአት በመሆኑ ንስሐ ይሰጠዋል፡፡ እንዳይደግምም ይመከራል፡፡

ፍትሐ ነገስት በወር አበባ የሚፈጸምን የሩካቤ ሥጋ ነገር በዚህ አያበቃም ሩካቤው ሌላ ችግር እና ጠንቅ እንዳለው ይነግረናል፡፡ ይህንንም በአንቀጽ 24 ቁ.25 ላይ ‹‹ሩካቤ መከልከል ግን በግዳጅዋና በአራስነቷ ወራት ነው፡፡ ይኸውም ዐባለ ዘርእን ከጥፋት ወገን ስለሚያገኘው ነው፡፡ ከዚህች ሥራ የተነሳ በማኅፀን የተፀነሱት ልጆች ሥጋ ደዌ ስለሚያገኛቸው ነው›› ይለናል፡፡ ይህም በሳይንሱ የተረጋገጠ ነው፡፡ አንድ ሴት በወር አበባዋ ጊዜ የመፅነስ እድል አላት፡፡ በዚህ ወቅት ብትፀንስ የምትወልደው ልጅ ጤናማ ላይሆንና ንቃተ ሕሊና የሌለው ልጅ ሊሆን ይችላል፡፡

11ኛ/ የአራሥነት ወቅት ፦ የሚገርመው ብዙዎች በአራሥነት ጊዜ ሩካቤ ሥጋ ክልክል መሆኑን እያወቁ ይስታሉ፡፡ በተለይ ሴት ልጅ ከተወለደች ክርስትና የምትነሳው በሰማንያ ቀኗ ነው፡፡ ይህ ማለት ሁለት ወር ከሃያ ቀን ማለት ነው፡፡ ታድያ ብዙዎች ባለትዳሮች በሁለት መንገድ ለአራሥነት ሩካቤ ይዳረጋሉ፡፡ አንደኛው ወራቶቹን ካለመታገስ ነው፡፡ ሁለተኛው ሴት ልጅ የወለደች እና ከአንድ ወር በኃላ ከአራሥነት ተነስታ ወደ ቀደመ ሕይወቷ ስለምትመለስ እና አራሥነቱ ስለሚረሳ ብዙዎች በእነዚ ቀናት ሩካቤ ሥጋ ይፈጽማሉ፡፡ ባስ ያለባቸውም ሚስታቸው ወንድ ከወለደች ከክርስትናው ቀድመው ሩካቤ ይፈጽማሉ፡፡ ግን ፍትሐ ነገ በአንቀጽ 24 በቁ. 922 ላይ ‹‹በአራስነቷ ወራት አትገናኛት›› ይላል፡፡ ስለዚህ ሚስት ወንድ ይሁን ሴት ብትወልድ በአራሥነቷ ወቅት ሩካቤ ሥጋ መፈጸም አይቻልም፡፡

12ኛ/ በንስሐ /በቀኖና ጊዜ ፦ የተነሳሂያን አንዱ ችግር ንስሐ ከገቡ በኃላ ከትዳር አጋራቸው ጋር ንስሐውን ጨርሰው ሳይፈቱ ሩካቤ ሥጋ ይፈጽማሉ፡፡ በካህኑ ትዕዛዝ የተሰጠንን ቀኖና ሳንጨርስ ‹‹ችግር የለውም ሚስቴና፣ባሌ ነው›› በማለት ሩካቤ ሥጋ ከፈጸሙ ንስሐውን ያፈርሱታል፡፡ ምክንያቱም በንስሐ ቀኖና የሚሰጣቸው አንዱ ጾም ነው፡፡ ይህ ጾም ደግሞ ሥጋ ከመብላት ብቻ ሳይሆን ከሩካቤ ሥጋም የምንታቀብበት ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ የንስሐ ቀኖናችንን እስክንጨርስና ጨርሰን እንክንፈታ ድረስ ከሩካቤ ሥጋ መታቀብ ይገባናል፡፡

13ኛ/ በእርግዝና ወቅት ፦ በቤተ ክርስትያናችን በተለይም አንዲት ሴት
አርግዛ በእርግዝናዋ ወቅት ሩካቤ ሥጋ መፈጸም አትችልም የሚለውን ትምህርት ለመንፈሳውያን እና ሳይንስ ለተጫነን እጅጉን ሲከብደን ይታያል፡፡ ሴት ልጅ አርግዛ ሩካቤ ሥጋ መፈጸም እንደ ቤተ ክርስትያን አስተምሮ እና እንደ ፍትሐ ነገስት ድንጋጌ ክልክል ነው፡፡ ይህንንም ‹‹ፅንሷ ከታወቀ በኃላ ከሚስት ጋራ ሩካቤ የሚያደርግ ሰው ቢኖር ይህ አግባብ አይደለም፡፡ ለእርሱም አይፈቀድለትም፡፡ የሚሻትም ለመረዳዳት ካልሆነ በቀር እርሷን አይሻ›› ይለናል፡፡ /ፍት.ነገ አን 24 ቁ 838/
በእርግዝና ወቅት ሩካቤ ሥጋ መፈጸም በቤተ ክርስትያናችን አስተምሮ ከመከልከሉ በተጨማሪ በራሱ በጽንሱ ላይ ከባድ ጉዳት ሊደርስ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በእርግዝና ወቅት በሚፈጠር ሩካቤ ሥጋ በማኅፀን ያለው ጽንስ ሊጎዳና አቀማመጡ ሊዛባና በእናቲቱ ላይ የጤና ጉዳት ሊያደርስ ይችላል፡፡ በእርግዝና ወቅት ከሩካቤ ሥጋ መከልከል ከባድ ቢሆንም ፅንስን ከማስባረክ እና ትዳራችን ሩካቤን ብቻ የተደገፈ እንዳይሆን ከማድረግ አንጻር ብንታቀብ መልካም ነው፡፡

ወዳጆቼ እንስሳት በጽንሳቸው ጊዜ እንደማይዳሩ ታውቃላችሁ? አንድ በሬ ያረገዘችን ላም አያጠቃም፡፡ አንድ በሬ አንዲትን ላም ሊያጠቃ ፈልጉ ይጠጋታል፡፡ ከተጠጋም በኃላ ፍላጎቱን በአካል እንቅስቃሴ እየገለጸ ወደ አፍረቷ በመጠጋት ያሸታታል፡፡ በሽታ ብቻ እንዳረገዘች በማወቅ ከማጥቃት ይከለከላል፡፡ ሕግ የሌላቸው በደመ ነፍስ ያሉት እንስሳት በእግዝና ወቅት ከማጥቃት የሚታቀቡ ከሆነ እኛ በሕግ ማዕቀፍ ያለን ሰዎችማ እንዴት አንታቀብም?

አፄ ናዖድ ከባለቤታቸው እና ከሠራዊታቸው ጋር መንገድ ይሄዳሉ፡፡ ሚስታቸው ማርገዟን ያወቁት ንጉሡ ከሚስታቸው ጋር ሩካቤ ሥጋ መፈጸም ካቆሙ ቆዩ፡፡ በዚህ ቅር ያላቸውና ሌላ ጥርጣሬ የጫረባቸው ሚስታቸው በመንገድ ጨዋታ በገደምዳሜ ጠየቋቸው፡፡ ነገሩ የገባቸው አፄ ናዖድ መንገድ ሲሄዱ አንድ በሬ ላሟን ሊያጠቃ ይሄድና አጠገቧ ደርሶ ወደ ጭራዋ ተጠግቶ አሽትቷት ትቷት ሲሄድ አይጠው ሚስታቸውን ‹‹አየሽ በሬው ላሟ እንዳረገዘች ስላወቅ ነው አጠገቧ ደርሶ ሳያጠቃት የተመለሰው፡፡ እንስሳት እንኳን በእርግዝና እንደማይገናኙ ያውቃሉ›› ቢሏት ሚስታቸው እኔን ሲለኝ ነው ብለው ቅሬታውንና ጥርጣሬያቸውን ትተዋል፡፡

14ኛ/ ክርስትና በምናስነሳና በምናነሳበት ጊዜ ፦ የራሳችንንም ልጅ ክርስትና ለማንሳት አልያም
የወዳጃችንን ልጅ ክርስትና አባት ወይም እናት ለመሆን በምናነሳበት ጊዜ ክርስትና ለማቋቋም በምንሄድ ጊዜ ሁለት ቀን ከሩካቤ ታቅበን ነው ወደ ቤተክርስያን የምንሄደው፡፡ በጥምቀተ ክርስትና፣ባል እና ሚስት ልጃቸውን ክርስትና በሚያስነሱበት ቀን ሩካቤ ሥጋ መፈጸም አይገባም፡፡ ይህንንም ፍትሐ ነገ አንቀጽ 24 ቁ. 921 ላይ ይከለክላል፡፡ ይህ ክልከላ ወላጆች ልጃቸውን በሚያስነሱበት ጊዜ ሩካቤ ሥጋ የተከለከለው ስለ ክብረ መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ይናገራል፡፡ በአጠቃላይ ፍትሐ ነገሥት ‹‹እግዚአብሔር ሩካቤን ለሰው የሠራው ልጅ ለመውለድ ብቻ አይደለም፤የማይወሰን የማይገታ የፈቲው ፆር ለማራቅ ጭምር ነው እንጂ፡፡ አንድ ጊዜ የሚከለከሉበት፣አንድ ጊዜ ፈቃዳቸውን የሚፈጽሙበትን ሠራ፡፡ ነገር ግን አንድ ወንድ ለአንድ ሴት፣አንዲት ሴት ለአንድ ወንድ ብለው ዘወትር ሊያደርጉት አይገባም፡፡ አጽዋማትን፣በዓላትን፣ኅርስን፣ትክትን ለይቶ ሊያደርጉ ይገባል እንጂ›› በማለት ደንግጎልናል፡፡ /ፍት ነገሥ አን 15÷ቁ 38-48/

15ኛ/ በሐዘን ጊዜ ፦ ባለ ትዳሮች ልጅ፣እናት፣አባት፣ወንድም እህት ወዘተ ሊሞቱ ይችላሉ፡፡ በዚህ ወቅት ሐዘን ክፉኛ ሊጸናባቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ አንዱ ሐዘንተኛውን ሐዘኑን እስኪረሳ በሩካቤ ሥጋ ፈቃድ ማስቸገር የለበትም፡፡ ምክንያቱም ሩካቤ ሥጋን ደስተኛ ሆኖ ለመፈጸም ሰላም እና መረጋጋት ብሎም ጥሩ ስሜት ሊኖራቸው ይገባልና፡፡ ሐዘንም ከሰውጥ ነው የሩካቤ ሥጋ ፍላጎትም ከውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው በሐዘን እጅጉን ከተጎዳ አብሮ የሩካቤ ሥጋ ፍላጎቱም ይጉዳል፡፡ ግን ሐዘንን የሩካቤ ሥጋ መቅጫ የሚያደርጉ አሉ፡፡ ሐዘንን ከልክ በላይ በማድረግ የሩካቤ ሥጋ መቅጫ ማድረግ ትልቅ ኃጢአት ነው፡፡

ወዳጆቼ ቤርሳቤህ ላይ የደረሰው ሐዘን እጅጉን አሳዛኝ ነው፡፡ ቤርሳቤህ ባሏን ኦርዮንን እና ልጇን በሞት አጥታ ነበር፡፡ ነገር ግን በአጭር ጊዜ ተጽናንታ ንጉሥ ዳዊትን አግብታ ተረጋግታ ኖራለች፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የቤርሳቤህን ሐዘን እና በዳዊት በኩል ያገኘችው መጽናናት ‹‹ዳዊትም ሚስቱን ቤርሳቤህን አጽናናት ወደ እርሷም ገባ ከእርሷም ጋር ተኛወንድ ልጅም ወለደች ስሙንም ሰሎሞን ብላ ጠራችው›› ይላል፡፡ ሰሎሞን ማለት ሰላም ደስታ ማለት ነው፡፡ ቤርሳቤህ ከሐዘን በኃላ ያገኘችው ሰላም እና ደስታ የሰጣት የዘሐንዋ ጊዜ ልጅዋ ነውና፡፡ /2ኛ ሳሙ 12÷24/ በሐዘን ጊዜ ከሩካቤ ሥጋ መታቀብ ቢጠበቅብንም ባል እና ልጅ ሞቶባት ሌላ ባል አግብታ ተጽናንታ ወደ ደስታ እንደተመለሰችው ቤርሳቤህ መጽናናት ይገባናል፡፡ የሩካቤ ሥጋ ማዕቀቡንም ልናነሳ የውዴታ ግዴታ አለብን፡፡

አንዳንዶች በሐዘን ምክንያት አልጋ በመለየት የሚሰነብቱ አሉ፡፡ ይህም ታላቅ ስህተት ነው፡፡ እንደውም ባል እና ሚስቱ አብረው መሆን ያለባቸው በሐዘናቸው ጊዜ ነው፡፡ በሐዘን ለሚመጣ የሩካቤ ሥጋ መታቀብ፣ለግጭት ሰበብ እንዳይሆን መጠንቀቅ አለባቸው፡፡ ሟችን የሚጠቅመው በሐዘን በሆን አልጋ መለየት ሳይሆን በስሙ ምፅዋዕት መስጠት፣ጸሎት እና ፍትሐት ነው፡፡ ሚስቶች እና ባሎች ሆይ በሐዘን ምክንያት ሐዘን በማብዛት ከሩካቤ ሥጋ በመራቅ ወደ ቅሬታ እና ጭቅጭቅ እንዳትገቡ ተጠንቀቁ፡፡

ታህሳስ 24/4/2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top