ሥርዓተ ቤተ-ክርስቲያን
ሥርዓት ማለት ምን ማለት ነው
ሥርዓት ማለት ‹‹ሠርዐ›› ሰራ ካለው የግእዝ ግስ ወጣ፡፡ ትርጉሙም ደምብ፣ አሠራር መርሐ ግብር ማለት ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያን ማለትስ ምን ማለት ነው
ቤተ ክርስቲያን፡- በዘርፍና በባለቤትነት የተቀመጠ ስም ነው ሦስት አይነትም ትርጉም አለው፡፡
1ኛ የክርስቲያን ቤት፣የክርስቲያን መሰብሰቢያ፣ የክርስቲያን መገናኛ ማለት ነው፡፡ (ኢሳ56፡7) ፣ (ኤር7፡10-11)፣ (ማቴ 26፡13)፣ (ማር 11፡17)፣ (ሉቃ 19፡46) ሕጻን ሽማግሌ፣ድሀ ሀብታም፣ወንድ ሴት፣የተማረ ያልተማረ በመባባል ሳንለያይ በአንዲት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ እምነት ጸንተን የምንኖባት ናት፡፡ (ማቴ 18፡20) የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን በፍልጲስዩስ ሃገር ሰኔ 20 ቀን በእመቤታችን ስም በጌታችን ፈቃድ ከተሠራ በኋላ ክርስቲያኖች ሥጋውንና ደሙን የሚቀበሉበት ቤት ሆነ፡፡ ቅዳሴ ቤቱም በነጋታዉ ሰኔ 21 ቀን ነበር፡፡
2ተኛ የክርስቲያን ወገን ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ቤተ ያዕቆብ፣ ቤተ አሮን እና የእስራኤል ወገን፣ የያዕቆብ ወገን፣ የአሮን ወገን እየተባለም ተጠርቷል፡፡ (መዝ 117፡3)፣ (ማቴ 16፡18)፣ (የሐዋ 18፡22) ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ማለት የክርስቲያኖች ስብስብ፣ የክርስቲያኖች ኅብረት ማለት ነው፡፡
3ተኛ የሚወክለው ምእመናንን ነው፡፡(1ቆሮ 3፡10)፣ (ዮሐ14፡23) ቅዱስ ጳውሎስ እናደተናገረው እያንዳንዱ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን ይባላል፡፡
ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን
ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ስንል ደግሞ የቤተ ክርስቲያን እቅድ፣ የቤተ ክርስቲያን አሠራር፣ መርሐ ግብር ደንብ ማለታችን ነው፡፡
የሥርዓት አስፈላጊነት
ሁሉም ሥራ ወጥና ዘላቂ በሆነ መልኩ ለመሥራትና ከየት ተነስቶ ወዴት እንደሚሄድ ለመከታተል፡፡አንድ ሃሳብና አንድ ልብ ሆኖ ሥራን ለመከታተል
የሃይማኖት ምስጢራትን ለመፈጸም ሥርዓት የሃይማኖት መገለጫ ስለሆነ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የመማር ጥቅም የቤተ ክርስቲያን ንዋያተ ቅድሳት ከሌሎች ይለያል፡፡
ለንዋያተ ቅድሳት የሚገባቸውን ክብር ይሰጣል
የቤተ ክርስቲያን ንዋያተ ቅድሳት ትውፊት ተጠብቀው እንዲቆዩ ያደርጋል፡፡
የሥርዓት ቤተ ክርስቲያን ምንጮች
መጽሐፍ ቅዱስ፣የሲኖዶስ (የቅዱሳን አባቶች ጉባኤ) ውሳኔዎች ወዘተ…
ከላይ የጠቀስናቸው ምንጮች በሙሉ ሰፊ ትንታኔ ያላቸው ናቸው ነገር ግን አብዛኛውን በቀዳማይ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ላይ በስፋትና በትኩረት ስለተማራችሁት አሁን ለምንማረው ለሥርዓ ተ ቤተ ክርስቲያን ቅድሚያ እንሰጣለን፡፡
ለቤተ ክርስቲያን የሚደረግ ክብርና ጥንቃቄ
ለጸሎትና ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል ወደ ቤተ ክርስቲያን በሚሄድባቸው ዕለታት ባልና ሚስት ከተራክቦ መከልከል አለባቸው፡፡ ከተገናኙ ግን አይገቡም ነገር ግን በዓላትንና አጽዋማትን ሊጠብቁ ይገባል፡፡ (ዘጸ 19፡15) (1ቆሮ 7፡5-7) (ኩፋ 34፡12)
ሴት የወር አበባዋ ሲመጣ እስከ 7 ቀን ድረስ ስትወልድ ወንድ ከወለደች እስከ 40 ቀን ሴት ከወለደች እስከ 80 ቀን ቤተ ክርስቲያን አትገባም እነዚህ ቀናት በተፈጸሙ ጊዜ ገላዋን ታጥባ ትገባለች (ዘሌ 12፡4)፣(ፍት መን. ዘኒቅያ 29)
ወንድ ሕልመ ሌሊት (ዝንየት) ከመታው በዕለቱ ወደ ቤተ ክርስቲያን አይገባም በማግስቱ ግን ገላውን ታጥቦ ይገባል፡፡ (ዘሌ 15፡2-18)
ቤተ መቅደስ ውስጥ ከገቡ በኋላ በጸጥታ የሚነበበውን የሚተረጎመውን መስማት ተሰጥዖ መቀበል ይገባል፡፡ ወሬ ማውራት ማውካካት መንጫጫት ነውር ነው፡፡
የሕንጻ ቤተ ክርስቲያን አተካከልና አሠራር
ሦስት ዓይነት የቤተ መቅደስ አሠራር አለ፡፡ መላእክት እግዚአብሔርን የሚያገለግሉበት የእግዚአብሔር የክብሩ መገለጫ ነው፡፡ ይህች ቤተ ክርስቲያን ምድራዊ ብቻ አይደለችም ሰማያዊት ናት ለዚህም አበው በአሰራሩ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጉለታል፡፡ በዝርዝር እንመልከት፡-
1. ክብ
የተለመደና በአብዛኛው የሃገሪቱ ክፍል የሚገኝ አይነት ነው
ዙርያው ክብ ሆኖ ውስጡ በሦስት የተከፈለ ነው 3 በሮች አሉት
ቤተ ንጉሥ ቅርጽ ይባላል፡፡ አንድ ጉልላት አለው ከጉልላቱም ላይ አርማችን መስቀል ይታያል
የመጀመሪያይቱ ቤተ ክርስቲያን በፊሊጵስዮስ የተሰራችው ቤ/ክ ክብ ቅርጽ ነበራት፡፡
ሙሉ ክብነቷ የፍጹምነቷ ምልክት ነው
የቅዱሳን ሥዕላቸው ሲሳል ዓይንና ፊታቸው ክብ ሆኖ የሚሳለው ሃይማኖትን ከምግባር አዋሕደው የተገኙና ከሕግ በላይ የሆኑ ፍጹማን መሆናቸውን ለመግለጽ ነው፡፡
2. ሰቀልማ ወይም ሞላላ ቅርጽ
4 ማዕዘን ቅርጽ ያለው ሞላላ የሆነና ከፍ ብሎ የሚታነጽ ነው፡፡
ሃሳቡ የተወሰደው ከጠቢቡ ሰሎሞን ካሰራው ቤተ-መቅደስ ነው
ለምሳሌ የአክሱም ጽዮን፣ ደብረ ብርሃን ሥላሴ እና ደብረ ዳሞ፣ ዐፄ ዮሐንስ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ያሰሩት የጻድቁ አቡነ ተ/ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ዐሥራ ስምነት ጉልላት ያለውና ሰቀልማ ቅርጽ ነበረው፡፡
የሞላላነቱ ምስጢርም ጌታችን የፈጸመውን የድኅነት ስራ እንድናስብበት ነው፡፡ ከመስቀል ጋር የሚያያይዙበት ወቅትም አለ፡፡
መሠረቱ የመስቀል ምልክት አለው
ምሳሌ፡- መንበረ ጸባኦት ቅ.ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ምስካየ ኀዙናን መድኃኔዓለም ገዳም
3. ዋሻ ቅርጽ
ሰማዕታት ከዓላውያን ነገሥታት ሸሽተው በዋሻ ሲሸሸጉ የጀመሩት ቤተ መቅደስ ዓይነት ነው፡፡
በሩ አንድ ነው በውስጥ ያሉትን ክፍሎች በአብዛኛውን ጊዜ በመጋረጃ ይከፈላል፡፡
ጉልላት የለውም
የሚታነጸው ተራራ በመፈልፈል በዋሻ ውስጥ ነገር ግን ከዋሻ ተነጥሎ ለብቻው የቆመ ድንጋይን (አለትን) በመፈልፈል ሊሠራ ይችላል
ምሳሌ፡-አቡነ ሀብተ ማርያም ገዳም፣አዳዲ ማርያም፣የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት
አንድነታቸውና ልዩነታቸው
v አንድነታቸው
ቅኔ ማኅሌት፣ ቅድስትና መቅደስ አላቸው፡፡
በውስጣቸው የሚፈጸመው የቅዳሴ፣ የማኅሌት፣ የሰዓታት፣yጸሎት ሥርዓት አንድ ዓይነት ነው
v ልዩነታቸው
ሰቀላማና ክብ ቅርጽ ቤተ-መቅደስ ጉልላት ሲኖራቸው ዋሻ ግን ጉልላት የለውም፡፡
ሰቀላማና ዋሻ ቅርጽ በመጋረጃና በደረጃ ሲከፈሉ ክብ ቅርጽ ግን በግድግዳ ይከፈላል፡፡
በሰቀላማና ዋሻ ቅርጽ የሴቶችና የወንዶች መቆሚያ ሲኖረው የሚከፈለውም በመጋረጃ ነው፡፡ ነገር ግን በክብ ቅርጽ ግን የተለያየ ቦታ አላቸው፡፡
የቤተ ክርስቲያን ክፍሎችና ትርጉማቸው
ሦስቱ የቤተ ክርስቲያን ክፍሎች ጎልተው የሚታዩት በክብ ቤተ ክርስቲያን ነው ቅኔ ማኅሌት፣ ቅድስትና መቅደስ በመባል ይታወቃል፡፡
ሦስት የሆኑበትን ምክንያት፡
v በሦስቱ ዓለማተ መላእክት፡- ኢዮር፣ራማ፣ኤረር
v በሦስቱ መዓረጋት ክህነት ምሳሌ፡- ዲቁና፣ቅስና፣ኤጲስቆጶሳት
v በሦስቱ ጾታ ምእመናን፡- ካህናት፣ወንዶች፣ሴቶች
v የሦስቱ ኆኅተ ገነት (የገነት በሮች) ምሳሌ
v በታቦተ አዳም፣በታቦ ሙሴና በታቦተ መላእክት አምሳል
v በጽርሐ አርም፣በኢዮር፣በጠፈር አምሳል
አገልግሎቸው
1. ቅኔ ማኅሌት
ስያሜው ከግብሩ የተወረሰ ነው፡፡ መዘምራን፣ ደባትር ካህናት ስብሐተ እግዚአብሔር ማኅሌተ እግዚአብሔር የሚያደርሱበት መዝሙር የሚዘምሩበት ክፍል ነው፡፡
ዳዊት ያስተዛዝሉበታል፡፡ በመስዕ (ሰሜን ምስራቅ) ንዑስ ማዕዘን በኩል ቀሳውስትና ዲያቆናት በመንፈቀ ሌሊት ሰዓታት በነግህ ኪዳን ያደርሱበታል፡፡
በጥንት ዘመን ሥርዓተ ጥምቀት የሚፈጸመው በዚሁ ክፍል ነበር፡፡
ለጥምቀት ለቁርባን ያልበቁ በትምህርት በንስሐ የሚፈተኑ /ንዑስ ክርሰቲያን/ ‹‹ፃኡ ንዑስ ክርስቲያን›› እስከሚባል ድረስ የሚቆዩበት ነው
ወንዶች ምእመናንም ቆመው የሚያስቀድሱበት ነው
በዚህ ክፍል በሌብ /ደቡብ ምስራቅ/ ንዑስ ማእዘን በኩል የሚገኘው ቦታ የሴቶች መቆሚያ ነው
ከውጭ ወደ ቤተ መቅደስ ስንገባ የምናገኘው የመጀመሪያው ክፍል ነው ሦስት በሮች አሉት የካህናት፣ የወንዶች እና የሴቶች ምእመናት መግቢያዎች ናቸው፡፡
2. ቅድስት
ትርጉሙ የተለየ ልዩ ማለት ነው የቤተ ክርስቲያኒቱ ማዕከላዊ ክፍል ነው፡፡
ካህናት በድርገት ጊዜ ምእመናንን የሚያቆርቡበት ክፍል ነው
በስብከተ ወንጌል ሰዓት መምህራን ቆመው የሚያስተምሩበት ክፍል ነው፡፡
በተክሊልና በቁርባን አንድ ለሚሆኑ ሙሽሮች ጸሎት የሚደርስበትና በካህናት እጅ የሚባረኩበት ክፍል ነው
በስቅለት ዕለት ሥርዓተ ጸሎት ይፈጸምበታል
በምዕራብ በኩል ቆሞሳት፣ዲያቆናት፣ቀሳውስት ይቆሙበታል፣ በሰሜን መነኮሳትና የሚያቆርቡ ወንዶች ምእመናን ይቆሙበታል፣በደቡብ የሚቆሙት ደናግል መነኮሳዮያት፣ የቀሳውስትና የዲያቆናት ሚስቶች ናቸው፣ በምስራቅ በምዕራብ በሰሜንና በደቡብ አራት በሮች ይኖሩታል
የማይቆርቡ ምእመናን በዚህ ክፍል ቆመው ማስቀደስ የለባቸውም
3. መቅደስ
በብሉይ ቅድስተ ቅዱሳን የሚል ስያሜ አለው፡፡
የቃል ኪዳኑ ታቦት የሚገኝበት ክፍል ነው፡፡
ከመንበረ ታቦቱ ጋር ሌሎች ንዋያተ ቅድሳት በዚህ ክፍል ይገኛሉ፡፡
ከዲያቆናትና ሥልጣነ ክህነት ካላቸው በቀር ማንም መግባት አይችልም
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት የሚያስቀድሱበት በዚህ ክፍል ቆመው ነው፡፡
በምዕራብ በሰሜንና በደቡብ ሦስት በሮች አሉት እያንዳንዱ በር መንጦላዕት ነው፡፡
የጌታችን ሥጋና ደም የሚፈተተው በዚሁ ክፍል ነው፡፡
በቤተ ክርስቲያን ዙርያ የሚሠሩና አገልግሎት የሚሰጡ ቤቶች
1. ቤተ ልሔም፡- በቤተ ክርስቲያን ምስራቅ ዲያቆናቱ ለመሥዋዕት የሚሆነውን ኅብስትና ወይን የሚያዘጋጁበት ሁለተኛ ቤት ይሠራል፡፡ ስያሜውም ‹ቤተ ልሔም› ይባላል፡፡ የእንጀራ ቤት እንደማለት ነው፡፡ ጌታችን የተወለደበትን ቤተ ልሔም ያስታውሰናል፡፡ መቅደሱ ደግሞ የቀራኒዮ ምሳሌ ነው፡፡
2. የግብር ቤት፡- ሌላው ለመሥዋዕት የሚቀርበው (መገበሪያ) የሚሰየምበት ነው፡፡
3. ዕቃ ቤት፡- የቤተ ክርስቲያን ንዋተ ቅድሳት የሚቀመጡበት ቤት ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን መገልገያ የሆኑት አልባሳትም መጻሕፍትም የሚቀመጡት በዚህ ቤት ነው፡፡ (ሕዝ 44፡19)፣ (ፍት.መን. 16)
4. ክርስትና ቤት፡ ሥስርዓተ ጥምቀት የሚፈጸምበት የማጥመቂያ ቤት ነው፡፡ ከዚህም ሌላ በገጠር አብያተ ክርስቲያናት የሙታን በድን የሚያርፍበትና ጸሎት ፍትሐት የሚደረግበትም ቤት አለ፡፡
ከዚህም በተቸማሪነገር ግን እንደ ምዕመናኑ አቅም ሊገነቡ የሚገባቸው ቤቶች አሉ፡፡
የሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት፣ የሰ/ት/ቤቶች ክፍሎች፣ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ፣ የእንግዶችና የካህናት ማረፊያ ቤቶች፣ የመንፈሳዊ ት/ቤትና የተግረ እድ መማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ-መጻሕፍት፣ የንዋየ ቅድሳትና ጧፍ ዕጣን መሸጫ ክፍሎች ወዘተ… ናቸው፡፡
በቤተ ክርስቲያን ዙርያ የሚገኙ ቅዱሳት ንዋያትና ምሳሌያዊ ትርጉማቸው
v አዕማድ፡-ምሰሶ ማለት ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን በውስጣዊ ክፍል በኩል የሚተከሉ ናቸው፡፡ ምሳሌውነቱ 1ኛ የቅዱሳን መላእክት ነው፡- መላእክት በእግዚአብሔር ፊት በቤተ መቅደስ ዙርያ ለምስጋና ጸሎትን ለማሳረግ ለጥበቃ ሌትና ቀን ሳያርፉ እንደሚቆሙ ሁሉ ምሰሶዎቹም ሌትና ቀን ተተክለው ይታያሉ (ራዕ 4፡8) 2ተኛ በቅዱሳን ሐዋርያት፡- ቅዱሳን ሐዋርያት ሌሊትና ቀን በአገልግሎት ጸንተው ቤተ ክርስቲያን እንዳገለገሉ ለማሳየት ጸንተው ምሰሶዎቹም ይታያሉ (ገላ 2፡9)
v ጉበን ወይም /ደረጃ/ ፡- ወደ ቤተ-መቅደስ የሚመራ ነው፡፡ ምሳሌውም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ነው የእርሱን አርአያ አብነት አድርገን የምንኖር ስለሆነ ነው፡፡
v የቤተ ክርስቲያን ሳር ክዳን፡- ሄሮድስ በጭካኔ ያስፈጃችው ሕጻናት የቤተ ልሔም ምሳሌ ነው፡፡ (ማቴ 2፡16)
v የቤተ መቅደስ ቅጽር (የግቢው ከለላ)፡- የቅዱሳን መላእክት ምሳሌ ናቸው፡፡ ዕጽዋት ብዙ ሆነው በቤተ ክርስቲያን ቅጽር እንደሚታዩ ሁሉ ቅዱሳን መላእክትም በብዛት ሆነው ሰውንም ሕንጻውንም ይጠብቃሉ እንዲሁም እጽዋት ሞገስ ይሆናሉ (መዝ 90፡11)
v ማገር፡- የቅድስት ሥላሴ ምሳሌ ነው፡፡ ማገር ሕንጻውን ከክዳኑ ጋር አገናኝቶ አጽንቶ የሚያቆመው ነው፡፡ቅድስት ሥላሴም ቤተ መቅደስ በሆነው በሰው ሰውነት ላይ አድረው ሃይማኖት አጽንተው ይኖራሉ፡፡
v የቤተ ክርስቲያን መክፈያ ግድግዳ፡- የነቢያት ምሳሌ ነው፡፡የቤተ መቅደስ ግድግዳ ከአንዱ ክፍል ወደ ሌላ ስንሸጋገር የምናገኘው ነው፡፡ ነቢያትም ከዘመን ዘመን ‹‹መሲሕ ይወርዳል ይወለዳል›› እያሉ ትንቢት ሲናገሩ የምናገኛቸው ናቸው (ማቴ 3፡1)
v የተጠረቡ ድንጋዮች የለዘቡ እንጨቶች፡- የሰማዕታት ምሳሌዎች ናቸው እዚህ ድንጋዮችና እንጨቶች ተጠርበው በቤተ መቅደስ ሥራ ይውላሉ፡፡ ሰማዕታትም በእሳት እየተፈተኑ በስለት እየተመሩ ለሃይማኖታቸው ማገር ምሰሶ ግድግዳ ሆነዋል፡፡ (ዕብ 11፡36)
v ጉልላት፡- የቀራኒዮ ምሳሌ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን አናት ላይ እንደተራራ ሆኖ የምናየው ጉልላት ጌታችን የሰውን ልጆች ለማዳን የተሰቀለበት የቀራኒዮ ኮረብታ ምሳሌ ነው፡፡ (ዮሐ 19፡17)
v በጣሪያው ዙርያ የሚደረጉ የሚንhሹ ሽኩራዎች፡- የቅዱሳን መላእክት ምሳሌ ናቸው፡፡ ሽኩራዎች እየተወዛወዙ ድምጽ የሚያወጡ ሁሉ ቅዱሳን መላእክትም በቤተ ክርስቲያን ዐጸድ ሌሊትና ቀን ያሸበሽባሉ ይዘምራሉም፡፡ (ዘፍ 28፡11-17) ሄሮድስ በጭካኔ ያስፈጃችው ሕጻናት ምሳሌ ነው
v የሰጎን እንቁላል፡- ሰጎን እንቁላሏን እንዲፈለፈል የምታደርገው በመታቀፍ ሳይሆን ወዲያ ወዲህ ሳትል ትኩር ብላ በማየት ነው፡፡ሰጎን እንቁላሏን ያለማቋረጥ እንደምትመለከት እግዚአብሔርም ፍጥረቱን የማይረሳ፣ በደጋውና በረድኤቱ ከፍጥረቱ የማይለይ መሆኑን ለመጠየቅ የሰጎን እንቁላል በቤተ ክርስቲያን አናት ላይ ይሰቀላል፡፡
v ሦስቱ በሮች፡- በምስራቅ፣ በሰሜንና፣ በደቡብ የሚገኙ የገነት በሮች ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ገነት ሦስት በሮች ነበሯት፡፡ በምስራቁ በር እግዚአብሔር ይገባበታል በሰሜኑ በር አዳም፣ በደቡብ በር ደግሞ ሔዋን ይገቡበት ነበር፡፡
v ቤተልሔም፡- ከቤተ መቅደስ በስተምስራቅ በኩል የሚሠራ ቤት ነው፡፡ምሳሌነቱም ጌታችን የተወለደበት ዋሻ (ጎል) ነው፡፡ዲያቆናት ለተልእኮ ይፋጠኑበታል ሥጋ ወ ደሙ ያዘጋጃሉ፡፡
v ቤተ-ምርፋቅ፡- የሰደቃ ቤት፣ የምግብ ቦታ ደስ ማለት ነው፡፡ ካህናትና ዲያቆናት ከቅዳሴ በኋላ እህል ውሃ የሚቀምሱበት ነው፣በተለምዶ ደጀ ሰላም በመባል ይታወቃል፣ በጥንት ጊዜ ከቤተ ክርስቲያን መግቢያ በር ጋር ተያይዞ የሚሠራ ነበር፡፡
v ሰንበቴ ቤት፡- በዕለተ ሰንበት ምዕመናን ተሰብስበው የሰንበትን ጽዋ እየጠጡ ከካህናት የሚሰጠውን ትምህርት የሚከታተሉበት የሚጠያየቁበት ቤት ነው፡፡ ከቤተ ክርስቲያን 40 ክንድ ተጠግቶ ይሰራል
v ደወል (መጥቅዕ)፡- ካህናትና ምእመናን ወደ ቤተ መቅደስ እንዲሰበስቡ ለማድረግ እየተመታ የሚያገለግል የቤተ ክርስቲያን ንዋየ ቅዱስ ነው፡፡
የአደዋወሉ አይነት፡- የተጋበኦ ደወል፣የቅዳሴ መግቢያ ደወል፣የወንጌል ደወል ፣እግዚኦታ ደወል፣ የድርገት ደወል፣የፍትሃት ደወል ፣ለአደጋ ጊዜ የሚደወል ደወል
በቤተ መቅደስ ውስጥ ለአገልግሎት የሚውሉ ንዋያተ ቅድሳት
v ታቦት (ጽላት)
ü በብሉይ ኪዳን፡- ከእስራኤል የነጻነት ሕይወት ጋር የተያያዘ ታሪክ አለው፡፡ኢትዮጵያ ከብሉይ ኪዳን ከወሰደችው አንዱ ጽላተ ኪዳን ነው፡፡ በኦሪት ታቦት የሚባለው ጽላቱ የሚቀመጥበት ማሕደሩ ነው፡፡(ዘጸ 40፡21)፣(መዝ131፡10)፣(2ቆሮ6፡16) (ዕብ9:4)፣ (ራእ11:19) ትርጉሙም ማደሪያ መሰወሪያ ማለት ብቻ ሳይሆን መታያ መገለጫም ነው (ዘጸ 13፡26) ጽላት የሚባለው እግዚአብሔር ለሙሴ አስቀድሞ አሰርቱን ቃላትን በእጁ ጽፎ የሰጠው የተጠረበው ድንጊያ ነው (ዘጸ 24፡12)
ü በሐዲስ ኪዳን ፡-የታቦትና የጽላት ነገር ምንም ለውጥ የለውም ክርስቶስ በተገለጠ ጊዜ እነዚህ ቃላት በመጽሐፍት ተጽፈው በሕግነት ለማገልገል ብቻ ተወሰኑ፡፡ ክርስቶስ ራሱ መሥዋዕት በመሆኑም ምክንያትም በታቦቱ ላይ የሚፈሰው የላሕምና የበግ ደም ቀርቷል፡፡ በጽላቱ ላይ ‹‹አልፋ መግ፣ ቤጣ የወጣ›› የሚለው የጌታ ስም ይቀረጽበታል፣ ከላይ ሥዕለ ሥላሴ፣ ቀጥሎ ምስለ ፍቅረ ወልዳ፣ ዮሐንስ ፍቀረ እግዚእ፣ እንዲሁም መቅደሱ የተሠራለት ጻድቅም ሆነ ሰማዕት፣ መልአክም ሆነ ሐዋርያ፣ ሥዕሉ ይሳላል ስሙ ይጻፋል፡፡ በመቀጠልም በኤጲስ ቆጶሱ እጅ ተባርኮና ሜሮን ተቀብቶ በመንበሩ ይሰየማል፡፡ያለ ታቦት መሥዋዕት አይሰዋም፡፡ ሕብስቱ ሥጋ መለኮት ወይኑ ደመ መለኮት ወደ መሆን የሚለወጠው በዚህ በታቦቱ ላይ ነው፡፡
v መስቀል፡- የእርግማን ምልክት የሆነ የወንጀለኞች መቀጫ ነበር፡፡(ዘዳ 21፡23) ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለሙን ከኃጢአትና ከሞት ለመዳን በቀራኒዮ የተሰቀለበት ነው፡፡የእንጨት መሆኑ በቀደመው ጊዜ ኃጢአት በዕፅ ገብቷልና፡፡ ስለዚህ ለመካስ በዚህ ምክንያት አድርጓል፡፡ ክርስቶስ በደሙ ስለቀደሰው ግን ቅዱስ መስቀል ተብሏል፡፡ በመስቀል ድኅነትን አግኝተናል፡፡ (1ጴጥ 2፡24-25) ንዋያተ ቅዱት ይባርኩበታል መስቀል የነጻነታችን ግርማ፣ የድህነታችን መገኛ፣ ጠላትን ድል የምንነሣበት መሳሪያችን ነው፡፡ሰውን በመስቀል ላይ መቅጣት የተጀመረው በጥንቱ ፋርስ በዛሬዋ ኢራን ነው፡፤ (ከክርስቶስ ልደት በፊት 339-33 ዓመት ነው)ይህም የሆነው ‹‹ከመሬት አምላክ›› ወይም አርሙዝድ የተባለው አምላክ በነበረበት ወቅት ነው፡፡
ü ለመስቀል ክብር ለምንድን ነው የሚያስፈልገው
ክርስቶስ መስዋዕት ሆኖ ራሱን የሠዋበት እውነተኛ መንበር በመሆኑ
የክርስቶስ ደም የፈሰሰበት፣ እኛ የዳንበት የነጻነት አርማችን የክርስቲያኖት አንድት የተመሠረተበት የድኅነት አርማችን ስለሆነ
መስቀል መለኮታዊ ፍቅር የተገለጠበት መሳሪያ በመሆኑ
ü የመስቀል ዓይነቶች
1. የመጾር መስቀል፡- በቅዳሴ እና በማዕጠንት ጊዜ ሠራዒው ዲያቆን የሚይዘው ነው፡፡
2. የእጅ መስቀል፡-ካህናት ምእመናንን የሚባርኩበት በእጅ የምትያዝ የመስቀል ዓይነት ናት
3. የአንገት መስቀል፡- ምእመናን ለአምላካቸው ያላቸውን ፍቅር ለመግለጽ ከባዕተባቸው ጋር በአንገታቸው የሚያደርጉት ነው
4. እርፈ መስቀል፡- በማንኪያ ቅርጽ ተሠርቶ በእጀታው ላይ የመስቀል ምልክት ያለበት ነው፡፡ ሠራዒው ዲያቆን በቅዳሴ ጊዜ ክቡር ደሙን ለምእመናን የሚያቀብልበት ነው፡፡ ጌታችን በእለተ አርብ የተወዳበት ጦር ምሳሌ ነው ፡፡
ü መስቀል የሚሰራባቸው ንዋያት በተመለከተ
መስቀል ከተለያዩ ነገሮች ሊሰራ ይችላል ምሳሌነትም አለው
1. የእንጨት መስቀል፡-ጌታችን ለሰው ልጆች ብሎ በእንጨት መስቀል ላይ ለመሰቀሉ ምሳሌ
2. የብረት መስቀል፡- ጌታችን በአምስቱ ቅንዋት ለመቸንከሩ ምሳሌ
3. የብር መስቀል፡- ይሁዳ በሠላሳ ብር አሳልፎ ስለመስጠቱ ምሳሌ
4. የወርቅ መስቀል፡-ወርቅ ንጹሕ ነው የጌታችንን ንጹሐ ባሕርይነት ለመግለጽ
5. የመዳብ መስቀል፡-መዳብ ቀለሙ ቀይ ይመስላል፤ ጌታችን ለእኛ ብሎ ያፈሰሰው ደም ምሳሌ
v መብራት
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትውፊና ምሳሌነት አለው፡፡
በቀድሞ ጊዜ ለሙሴ ሥርዓት አድርጎ ሰጥቶታል፡፡ (ዘጸ 40፡2-4)
መቅረዝ ማለት የሻማ ማብሪያ ነው ቀንዲል ማለትም የሻማ የዘይት መብራት ነው፡፡
ሙሴ መቅረዙን የሚያበራው በገበታው ፊት ለፊት በማደሪያው በደቡብ በኩል ያኖረዋል፡፡ (ዘጸ 40፡24-25)
በአሁኑ የቤ/ክ ስርዓት ጡዋፍና ዘይት ነው (ፍት መን አንቀጽ 1)
መብራቱ የሚበራበትም ወቅት በተለይ ቅዱሳት መጽሀፍት ማትም መልእክተ ጳውሎስ መልእክታተ ሐዋርያት፣ ግብረሐዋርያት ሲነበብ እንዲበራ ታዟል፡፡ በተለይም ወንጌል ሲነበብ ይበራል፡፡ (ፍት መን አንቀጽ 1)
አልባሳት
የቀሳውስት ልብስ፡- ይህ ልብስ የተቀደሰ ልብስ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱሰሳዊ ትውፊትና ምሳሌ አላቸው፡፡ በእግዚአብሔር ለአሮንና ለልጆች ሥርዓት ተሰርቶላቸዋል፡፡ (ዘጸ 40፡12-16) በብሉይ ኪዳን፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ በብልሃት የተሰራ፣ ከወርቅ የተሰራ ነው፡፡ (ዘጸ 391) በዚህ ትውፊትና ምሳሌ መሠረት በሐዲስ ኪዳንም ቀሳውስትና ዲያቆናት የሚለብሱት ልብሰ ተክህኖ አለ፡፡በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት ቀዳስያን ለመቀደስ የለበሱትን አልባሳት ቅዳሴው ሳይጠናቀቅ ማውለቅ አይገባቸውም አልባሳቱም በንጽሕና በቤተ ክርስቲያኒቱ እቃ ቤት ውስጥ እንዲቀመጥ ታዞዋል፡፡ (ሕዝ 44፡19) ልብሰ ተክህኖን ክህነት የሌለው ቢለብስ እንደ ዳታንና አቤሮን ያስቀጣል፡፡
v ቀሚስ፡- ከማነኛውም ጌጥነት ካለው ጨርቅ ይሠራል፡፡ በመጀመሪያ የሚለበስ ልብስ ነው ቀሚስም በልክ እንዲሆንም ታዟል፡፡ ቀዳስያን የሚሆናቸውን መርጠው ይለብሳሉ ቢረዝም እን£ን ማሳጠሪያ ልክ እንዲሆን ሰውነትን ማጠናከሪያ መታጠቂያ (ዝናር) አለው በዚያ ይጠቀማሉ እንጂ አንድ ጊዜ ካደረጉት ቅዳሴው እስኪጠናቀቅ ማውለቅ አይችሉልም፡፡ (ፍት ነገ መን አን 12)
v ካባ ላንቃ፡- መደረቢያው ልብስ ካባ ላንቃ ይባላል፡፡ ላንቃ የተባለበት ምክንያት ከካባው ጋር ለምድ አብሮ ስለተሰፋ ነው፡፡ ከልዩ ልዩ ቀለማት ካላቸው ጨርቆች ይሰራል፡፡ በሙካሽ ቢሰራ ግን ይመረጣል፡፡ከካባው ለምድ ላይ የሚደረቡ ለምድ ላይ የሚገኙት አምስቱ መንዲል የአምስቱ አዕማደ ምስጢራት ምሳሌ ናቸው፡፡
v ሞጣሕት፡- በአንገት ተጠልቆ ፊት ለፊት የሚወርድ የደረት ልብስ ነው፤ በኦሪት የአሮን ልብስ አምሳል ነው፡፡ከቀሚሱና ከካባው ላይ ይደረባል ምሳሌነቱ የፍኖተ ቅዱሳን ነው፡፡
v መጎናጸፊያ፡-
ትልቅና አራት ማዕዘን ያለው ባላ ገበር ከወርቀ-ዘቦ እና ከሌሎች ነገሮች የሚሰራ ሲሆን
ለአክብሮተ ሥጋ ወደሙ በቅዳሴ ጊዜ መንበሩ (መሠዊያው) የሚለብሰው፣ ታቦት በወጣ ጊዜ የሚጎናጸፈው ነው፡፡
v ቀጸላ፡- ለታቦቱ ክብር ከመጎናጸፊያዉ በላይ የሚደረብ ባለ ዘርፍ ልብስ ነው፡፡
v አክሊል፡-
v ቆብ ፡-
v መጋረጃ፡-
v ምንጣፍ፡- በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚነጠፍ ነው፡፡ እስራኤላውያንን እሾህ እንዳይወጋቸው እንቅፋት እንዳይመታቸው እግዚአብሔር አምላክ ከእግራቸው በታች ያነጠፈላቸው ደመና ምሳሌ ነው፡፡
v ማክበሪያ፡-ማክበሪያ የሚባለው የቃልኪዳኑን ታቦት የሚያከብረው(የሚሸከመው) ካህን በራሱ ላይ የሚያደርገው የቆብ አይነት ነው፡፡
እስከ አሁን የቆየው ግን ቀጸላ ብቻ ተጎናጽፎ መቅደስ ነበር፡፡
የመነኩሴና የሕጋዊ ቄስ በቅዳሴ ጊዜ የሚዳፉ ቅብ ቅርጹ ይለያያል ከቅዳሴ ጊዜ ውጭ ግን ቆብ ለመነኩሴ እንጂ ለቄስ አልታዘዘም
አክሊል ወይም ቆብ በታላላቅ አድባራትና ገዳማት አልፎ አልፎ በገጠር አብያተ ክርስቲያናትም ዲያቆናት አክሊል ቆብ ደፍቶ ይቀድሳል
የልብሱ ቀለምም ነጭ እንዲሆን ሥርዓተ ቅዳሴ ያዛል፡፡
ለሌሎቹ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚለብሰውን ልብስ ቀለም ቢለያይ ምንም ችግር የለውም፡፡
v ማኅፈዳት፡- አምስት የልብስ መጠቅለያዎች (መሸፈኛዎች) ናቸው፡፡ አንደኛው በጻሕሉ ሥር በታቦቱ ላይ ይነጠፋል፣ሁለተኛው በጽሕሉ ላይ ይነጠፋል ኅብሰቱ የሚጠቀለልበት ነው፣ ሦስተኛው የመሥዋዕቱ ልብስ ነው፡፡ ቁመቱ ከምስራቅ ወደ ምዕራብ ሆኖ ይለበሳል፣ አራተኛው፡- ከሰሜን ወደ ደቡብ ሆኖ ይለበሳል፣ አምስተኛው ከመስዕ (ከሰሜናዊ ምስራቅ) ወደ አዜብ (ደቡባዊ ምዕራብ) ሆኖ ይለብሳል፡፡
ምሳሌነቱም፡- ክርስቶስ በበረት ሲወለድ በጨርቅ መጠቅለሉንና በበለስ ቅጠል መሸፈኑን ለማስታወስ፤በእለተ ዓርብ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ የገነዙበትን ድርብ በፍታ የሚያመለክት ነው፡፡
v መንጦላዕት፡- በ
ሦ
ስቱም የመቅደስ በር የሚጋረዱ መጋረጃዎች ናቸው፤ለመቅደሱ ክብርን ይሰጣሉ፡፡ በቅዳሴ ጊዜ መጋረጃዎቹ የሚዘጉበትና የሚከፈቱበት ጊዜ አለ፡፡
በቅዳሴና በሌሎች የጸሎት ጊዜያት የሚያገለግሉ ንዋያተ ቅድሳት
v መንበረ ታቦት፡- የጽላት ወይም የታቦት መቀመጫ ዙፋን ነው ‹‹ወይዑዱ ታቦተ›› ሲል መንበሩን ይዙሩ ማለቱ ነው፤ መስዋዕተ ኦሪቱ ይቃጠልበት፣ ይሠዋበት በነበረው ፈንታ መንበሩ የገባ ስለሆነ ከታቦቱ ጋር ምሥዋዕ ይለዋል፡፡ ትርጉሙም መሠዊያ ማለት ነው፡፡
v ጻሕል፡- የቅዱስ ሥጋው ማስቀመጫና ማክበሪያ ነው፡፡ከወርቅ ከብርና ከብረት የሚሰራ ነው፤ የተለየ ቅርጽና ምልክት አለው
ምሳሌነቱም ክርስቶስ የተወለደበት የከብቶች በረት ነው እንዲሁም የመቃብሩ ምሳሌ ነው ቅዳሴው ‹‹አንበርነ ዲበ ዝንቱ ጻሕል በአምሳለ መቃብር›› እንዳለ፡፡ የእመቤታችን ማኅፀን ምሳሌም ነው፡፡
v ጽዋዕ፡-የክርስቶስ ክቡር ደም የሚቀርብበት ነዋየ ቅዱስ ነው፡፡ከወርቅ፣ ብር፣መዳብ፣ከነሐስ፣ከብረት ሊሠራ ይችላል፡፡
ምሳሌነቱ፡- ‹‹ይህ ደሜ ነውና ሁላችሁ ጠጡት›› ብሎ የሰጠበት ጽዋ የሚያስታውስ ነው፡፡ (ማቴ 26፡27) ሌንጌኖስ በጦር ጎኑን በወጋበት ጊዜ የፈሰሰውን ውሃና ደም የተደባለቀውን ፈሳሽ መልአኩ በጽዋ ብርሃን የቀዳውን ምሳሌ በማድረግ ነው፡፡ ዛሬም ዲያቆናቱ በጦር በተመሰለው እርፈ መስቀል ለምዕመናኑ ደሙን ያቀብሉበታል፡፡ ጽዋው የሚሸፈንበት ልብስ አይሁድ ጌታችን በኩርኩምና በጥፊ ሲመቱት ዐይኑን የሸፈኑበትና /ያሰሩበት/ ጨርቅ ምሳሌ ነው
v ዕርፈ መስቀል፡ ዕርፈ መስቀል የሚባለው እንደ ማንኪያ ያለ ሆኖ ከበስተ ኋላው የመስቀል ቅርጽ ያለው፣ አገልግሎቱም ለክቡር ደሙ ማቀበያነት የሚያገለግል የመስቀል ቅርጽ ያለው ነው፡፡
ምሳሌነቱም፡- የሱራፊ ጉጠት ነው – የኢሳያስን ከለምጽ ያዳነበት ነውና ዛሬም እኛ ከኃጢአት በሽታ የምንድ ንበትን የክርስቶስን ክቡር ደም እንቀበልበታለን፡፡ (ኢሳ 6፡6-8)
v ዐውድ፡- ማለት አደባይ ማለት ነው፡፡ ከብረት ከነሐስ የሚሰራና በድርገት ጊዜ ጻሕሉ የሚቀመጥበት ሰፋ ያለ ትልቅ ሳሕን ነው፡፡ ሥጋው እንዳይነጥብ ያደርጋል፡፡
ምሳሌነቱም ፡- የጲላጦስን አደባባይ ያመለክታል
v አጎበር፡ ከብረት ወይም ከእንጨት ይሠራል፡፡ በድርገት ጊዜ በአውዱ ላይ የሚደፋ አራት ማዕዘን የሆኑ ሦስት እግሮች ያሉት ንዋይ ነው
ምሳሌነቱም፡- የማኅተመ መቃብር (የመቃብር መክደኛ) ምሳሌ ነው፤ የሦስቱ እግሮችም ምሳሌ የሥላሴን ሦስትነት የሚገልጥ ነው፡፡
v አትሮኖስ፡- ከእንጨትና ከብረት የሚሰራ መጽሐፍ ሲነበብ የሚዘረጋበት ንዋይ ነው፡፡ በቅዳሴ ጊዜ መጽሐፍትን ያነቡበታል
ምሳሌነቱም፡- የእመቤታችን ሲሆን መጽሐፉ ደግሞ የክርስቶስ ነው፡፡
v ጽንሐሕ፡- የዕጣን ማጠኛ (ማሳረጊያ) ማለት ነው፡፡ ከወርቅ ክብር ከብረትና ከነሐስ ሊሠራ ይችላል (ዘጸ 30፡6-10)
ምሳሌነቱም፡- የእመቤታችን ምሳሌ ነው፤ ዕጣኑ የትስብእት (የሥጋ) ፍሕም የመለኮት የወርቅ ዘንግ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነው
ü የጽንሐሕ የተለያዩ ክፍሎችና ምሳሌያዊ ትርጉማቸው
1. ሙዳይ የሚመስለው የጽንሐሕው ክፍል፡- ዕጣንና እሳቱ የሚዋሐዱበት ክፍል ነው፤ ክዳን ከበላዩ አለው፡፡ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ማኅጸን ምሳሌ ነው፡፡ እሳቱ በዚህ ክፍል ተቀምጦ ጽንሐውን እንደማያቃጥለው ሁሉ እመቤታችንም እሳተ መለኮትን በማኅፀኗ ተሸክማው አላቃጠላትም፡፡
2. የሙዳዩ መክደኛ፡-በክዳኑ በላይ መስቀል አለበት ይህም የቀራኒዮ ምሳሌ ነው፡፡ (ገላ 3፡1)
3. በመካከል የሚገኝ አንድ ዘንግ፡- በሦስቱ ዘንጎች መካከል የሚገኝ ዘንግ ነው፡፡ የቅድስት ሥላሴ የአንድነታቸው ምሳሌ ነው፡፡ ከላይ ወደታች መውረዱ ቃለ እግዚአብሔር ወልደ እግዚአብሔር በተወላዲነት ግብሩ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ የመወለዱ ምሳሌ፣ ከታች ወደ ላይ መውጣቱ ደግሞ የጌታችንን የክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቶ የማረጉ፣ ከላይ ወደ ታች የመውረዱ በድጋሚ ለፍርድ የመመለሱ ምሳሌ ናቸው፡፡
4. ሸኩራዎችን የያዙ ሦስት ዘንግ፡- እግዚአብሔር በመለኮት በሕልውና አንድ ቢሆንም በስም፣ በግብር፣ በአካል ሦስት መሆኑን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ የመካከለኛውን ዘንግ ተመልክተን አንድነቱን ስናስብ ዘንጎች ተመልክተን ሦስትነቱን እናስባለን
5. በዘንጎቹ ላይ የሚገኙት ሸኩራዎች፡- በቁጥር 12 ወይም 24 መሆን አለባቸው፡፡ 12 ከሆኑ የ12ቱ ሐዋርያት 24 ከሆኑ ደግሞ የ24ቱ ካህናት ሰማይ ምሳሌ፣ ጽንሐሕው ሲወዛወዝ የሚያወጣው ድምጽ የሐዋርያትን ስብከት ምሳሌ፣ 24ቱ ካህናተ ሰማይ ምስጋናም ይመስላል (ራእ 4፡7)
v ሙዳይ፡- መኖሪያ መጨመሪያ መክተቻ ማለት ነው፡፡ ልዩ አገልግሎቱም የዕጣን ማስቀመጫነት (ማቅረቢያነት) ነው፡፡ ካህኑ በሥርዓተ ቅዳሴ ጊዜ በመጀመሪያው ቅዳሴና በሁለተኛው ቅዳሴ ከመጀመሩ በፊት አምስት የዕጣን ፍሬዎችን መርጦ ቅዳሴ ከመጀመሩ በፊት መርጦ ያስቀምጣል
ምሳሌነቱም፡- ሙዳዩ የእመቤታችን እጣኑ የጌታ ምሳሌነው፡፡ እንዲሁም አምስቱ ዕጣኖች የአምስቱ ኪዳናት ምሳሌ ናቸው፡፡ አምስቱ ኪዳናት የሚባሉት፡- ኪዳነ (ቁርባነ አቤል) መስዋዕተ ኖኅ፣ ኂሩተ አብርሃም፣ መብዐ ይስሐቅና ተልእኮተ ሙሴ ወአሮን ናቸው፡፡
v መሶብ (መሶበ ወርቅ)፡- ዲያቆኑ መሥዋዕቱ ከቤተልሔም ወደ ቀራኒዮ ወደ ምትመስለው ቤተመቅደስ የሚወስድበት ነው፡፡ ከስንደዶ ከአክርማና ከአለላ ከወርቅና ከብር ሊሠራ ይችላል፡፡ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ለሙሴ እንዲሠራ አዞት ነበር፡፡
ምሳሌነቱም፡- መሶቡም የእመቤታችን በላዩ ላይ ያለው ወርቅ የንጽሕናዋ የቅድስናዋ ምሳሌ ነው፣ መሶቡ ውስጥ ያለው መና የአማናዊው የክርስቶስ ምሳሌ ነው
v ሰን(መቁረርት ወይም ኩስኩስት)፡- ቆረ- ቀዘቀዘ ካለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ማብረጃ¤ ማብረጃ ማለት ነው::አገልግሎቱ ለምዕመናን የቅዳሴ ጸበል ማደያ ነው:: እንዲሁም በቅዳሴ ጊዜ ካህኑ እጁን የሚታጠብበት ቅዱስ ንዋይ ነው:: በብሉይ ኪዳን ለሙሴ እንዲሠራው ታዞ ነበር::(ዘጸ.30:17)
ምሳሌነቱም፡- ጲላጦስ “እኔ ከደሙ ንጹሕ ነኝ” ብሎ የታጠበበት ምሳሌ እንዲሁም ጌታችን በእል ኃሙስ የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበበት ምሳሌ ነው፡፡
v ቃጭል (ቃለ ዐውደ ወይም መረዋ)፡- በቅዳሴ ጊዜ የሚደወልና ድምጽ የሚሰጥ ነው፡፤ ከደወል ያነሰ ሲሆን ከህረት፣ ከመዳብ፣ከብር ፣ከነሐስና ከመሳሰሉት ሊሰራ ይችላል፡፡
– የሚደወልበትም ጊዜ፡- ቀዳስያን ከቤተ ልሄም ወደ ቤተ መቅደስ ሲገቡ፣ ‹‹ፃዑ ንዑስ ክርስቲያን›› ሲባል በእግዚኦታ ጊዜ፣ ድርገት ሲወርዱ፣ በምሕላ ጊዜ ይመታል፡፡ በሰሞነ ሕማማት ጊዜም አገልግሎት ላይ ይውላል፡፡
ምሳሌነቱም፡- “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” ያለውን የመጥምቁ ዮሐንስ ስብከትና በእግረ መስቀሉ ተገኝቶ ያለቀሰው የዮሐንስ ወጌላዊ ልቅሶ ምሳሌ ነው፡፡
v ዣንጥላ፡- ከነጭ ወይም ወርቃማ ቀለም ካለው ጨርቅ ይሠራል ዘንጉ ከብረት፣ ከብር ይሠራል፡፡ አገልግሎቱ ታቦቱ ወደ ዐውደ ምሕረት ሲወጣ፣ ካህናቱ መሥዋዕቱን ለማክበር ወደ ቤተልሔም ሲወርዱና መሥዋዕቱን አክብረው ከቤተልሔም ወደ ቤተ-መቅደስ ሲወጡ ወዘተ… ይጠቀሙበታል፡፡ ወንጌል ሲነበብ ይዘረጋል ይህም ለመሥዋዕቱ ለታቦቱ ለወንጌሉ ክብር ነው
ምሳሌነቱም፡- እስራኤላዉያን በሲና ምድረ በዳ ሲÕዙ ይጋርዳቸው የነበረ ደመና ምሳሌ እንዲሁም ሙሴ ከእግዚአብሔር ጽላተ ኪዳኑን ሲቀበል የጋረደው ደመና ምሳሌ ነው፡፡
v ተቅዋመ ወርቅ(መቅረዝ)፡- የመብራት ዕቃ፣ የቀንዲል፣ የሻማ ማኖሪያ የሚቆም ወይም የሚንጠለጠል ባለ ብዙ አጽቅ ማለት ነው (ዘካ 4፡2) መክሊተ ወርቅ ወስዶ ተቅዋሙን እንዲሰራ እግዚአብሔር ሙሴን አዞት ነበር፡፡(ዘጸ 25፡31-40) አሠራሩም ተቅዋሙ ከወደ ታች ቀጥ ብሎ እንዲቆም እንዳይወድቅም እንደ ጽዋዕ ያለ እግር እንዲያወጣለት ከዚያም በላዩ ላይ መሸቢያ ቃትቶ እንዲተወው ሦስቱን የመቅረዙን ቅርንጫፎች ከወዲህና ከወዲያ ጎን አድርጎ የመካከለኛውን ወጥ አድርጎ እንዲሰራው የተዘጋጀውንም ዘይት በስድስቱም ሁሉ እንዲመላ አዞት ነበር፡፡
ምሳሌነቱም፡- ተቅዋም የዘምነ ምሳሌ ታቹን አንድ ወጥ አድርገህ በሦስት መሸቢያ ሰባት አዕጹቅ አውጣለት ማለቱ በሦስት ክፍለ ዘመናት (ዘመነ አበው፣ ዘመነ መሳፍንት፣ ዘመነ ካህናት) የተጻፉ መጻሕፍት ምሳሌ፣ መካከለኛው አጽቅ የወንጌል፣ ጫፎቹ የሐዋርያት የመምህራን ምሳሌ ናቸው፡፡ አጽቅ ብርሃኑን ያመለክታል ብርባን የሆነውን የመጻሕፍትን ምስጢር የሚያስረዱ መምህራን ናቸውና፡፡ ጫፎቹ ሰባት መሆናቸው የፍጹምነት ምሳሌ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ተቅዋም የእመቤታችና የሚበሩት ሻማዎች የቅዱሳን መላእክት ምሳሌ ናቸው፡፡
v ድባብ፡- እንጨቶች እንደ ምሰሶ ቆመው በላዩ ጨርቅ በመስፋት የሚሰራ ትልቅ ጥላ ነው፡፡ ላዩ በነሐስ፣ በብር በመሳሰሉት ይሰራል፡፡ በክብረ በዓላት ጊዜ ከፊት ተዘርግቶ ይሄዳል፡፡
ምሳሌነቱም፡- እግዚአብሔር ለነሙሴ ይገለጥ የነበረበት ዓምደ ደመና ምሳሌ ነው በደመናው መካከል ክብና ልዩ ብርሃን ወጥታ በታቦቱ ትረብ ነበር፡፡ ድባቡ የዚህች ብርሃን ምሳሌ ናው፡፡ (1ነገ 8፡3) (ዘጸ 33፡10)
v መነሳንስ (ጭራ)፡- ከጻሕልና ከጽዋው ውስጥ ተሐዋስያን እንዳይገቡ ለመከላከያነት ያገለግላል
የማኅሌት መሳሪያዎች
v ከበሮ፡- ንዋየ ማኅሌት፣ አታሞ፣ ነጋሪት ስለ ክብረ በዓል የሚመታ ክብራዊ ትእምርተ ክብር ጯሂ፣ ተሰሚ ማለት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትውፊትና ምሳሌነት አለው (መዝ 150)፣ (ኤር 38፡4)፣ (ዳን 3፡10)፣ (ኢሳ 5፡12)፣ (2ሳሙ 6፡5)፣ (ዘጸ 15፡20) ከበሮ ከከብት ቆዳ ተጨፍቆ ከእንጨት ወይም ከብር የሚሠራ የዜማ መሳሪያ ነው፡፡ ለደስታም ሆነ ለኀዘን ቀን የሚመታ መሳሪያ ነው
ምሳሌነቱም፡- ከበሮ የጌታችንን መከራ ስቅለቱን የምናስታውስበትና የክርስቶስ ምሳሌ ነው፤ ግራና ቀኝ ሲመታ ጌታችን በእይሁድ እጅ በጥፊ መመታቱን ያስታውሰናል ፡፡ይህንንም በዝርዝር ስንመለከተው፡-
የከበሮው ሰፊ አፍ፡- የጌታችንን መለኮታዊ ባሕርይ ምሳሌ ነው፤ ማለትም ጌታችን በሥልጣኑ ወሰን ድንበር የሌለው ሙሉ በኩለሄ መሆኑን ያስታውሰናል፡፡
የከበሮው ጠባቡ አፍ፡-የትስብእት ምሳሌ ነው፤ጠባቡ አፍ ወልደ እግዚአብሔር በጠባብ ደረት በአጭር ቁመት ተወስኖ የመገለጡ ምሳሌ ነው፡፡
ከበሮው የሚለብሰው ጨርቅ፡- ይህም ጌታችን በእለተ ዐርብ የለበሰው የቀይ ከለሜዳ ምሳሌ ነው፡፡
በከበሮው ላይ የተጠላለፈው ጨርቅ፡- ጌታችን በእለተ አርብ ለእኛ ሲል የተገረፈው የግርፋቱ ሰንበር ምሳሌ ነው፡፡
የከበሮው ማንገቻ፡- ጌታችንን አስረው የጎተቱበት ገመድ ምሳሌ ነው፡፡
ü የከበሮ አመታት ሥርዓትና ምሳሌነቱ
1. ከበሮውን ግራና ቀኝ መምታት፡-ጌታችን በአይሁድ እጅ ግራና ቀኝ ጉንጮቹ መመታታቸው ምሳሌ (ማቴ 27፡21)
2. እየተንቀሳቀሱ(እያሸበሸቡ) መምታት፡- አይሁድ ጌታችንን እያንገላቱ ወደ ቀራንዮ የመውሰዳቸው ምሳሌ
3. ከእርጋታ ወደ ፍጥነት እያሸጋገሩ መምታት፡-ይህም አይሁድ በመጀመርያ እያፌዙ የመምታታቸው በላም ሰንበት እንዳይገባባቸው ጲላጦስም ተመራምሮ እንዳያድነው በማለት እያጋፉ እያንገላቱ የመምታታቸው ወደ ቀራንዮም የመውሰዳቸው ምሳሌ
4. መሬት አስቀምጦ መምታት፡- ጌታችን በዕለተ ዐርብ በምድር ላይ ወድቆ የመንገላታቱ ምሳሌ ነው፡፡
v ጽናጽል፡- ጸነጸለ – መታ ካለው ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ሸኩራ ቃጭል እንደማለት ነው፡፡ ከነሐስ፣ ከብርና ከሌሎችም ማዕድን ሊሰራ ይችላል፡፡ ጽናጽል ያማረ ድምጽ ያለው ሆኖ መልክና ልዩ ጌጥ ያለው ሲሆን በጥንት ዘመን ግብጻውያን እግዚአብሔርን ያመሰግኑበት ነበር፡፡(መዝ150፡5) አሠራሩ ላዩ ቀስተ ደመና ይመስላል፡፡ ከታች መጨበጫው አንድ ሆኖ የላም ምስል የነበረበት ነው፤ ዕብራውያንም ይገለገሉበት ነበር፡፡
ምሳሌነቱም፡- በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ጽናጽል ላይ ቀስተ ደመና መምሰሉ ‹‹እሰይም ቀስትየ በውስተ ደመና››ብሎ በተናገረው መሠረት ነው፡፡(ዘፍ 9፡12) ይህም እግዚአብሔር ለኖኅ የገባለት ቃል ኪዳን ምሳሌ ነው፡፡
አራቱ ዘንጎች በአራቱ ባሕርያተ ሥጋ ቅጠሎቹ የፍጥረታት ምሳሌ ይኸውም ከአራቱ ባሕርያት የተፈጠሩትን ፍጥረታት ‹‹ሰውንም አላጠፋም ብሎ ቃል ኪዳን እንደገባ ለማሰብ›› መሰላሉ ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ ድንጋይ ተንተርሶ ያየውን መሰላል ምሳሌ ነው፡፡ (ዘፍ 28፡ 11-13)
ሁለቱ ቀጫጭን ዘንጎቹ (ጋድሞች) የመወጣጫው ምሳሌዎች ናቸው፤ ቅጠሎቹ የመላእክት ምሳሌዎች ናቸው፤ በግራና በቀኝ የቆሙት ዓምዶች የብሉይና የሐዲስ ምሳሌዎች ናቸው ፤ሁለቱ ጋድሞች የፍቅረ ቢጽና የፍቅረ እግዚአብሔር ምሳሌዎች ናቸው፡፡
v መቋሚያ፡- መደገፊያ መመርኮዣ ማለት ነው፤ አገልግሎቱም በቅዳሴ ጊዜ ምእመናኑ እና ካህናት ደግሞ በማኅሌቱ ጊዜ እግዚአብሔርን በከበሮና ጽናጽል በዐቢይ ጾም ጊዜ ያገለግሉበታል፡፡
ምሳሌነቱም፡- ለአዳም ተስፋ ተደርጎ የተሰጠው የመስቀል ምሳሌ ነው፤በሙሴ በትርነትም ይመሰላል፡፡ መዘምራኑ በትከሻቸው ላይ አድርገው ሲያስረግጡ የክርስቶስን መከራ መስቀል ያስታውሳል፡፡
ለፍቁረ እግዚእ መንፈሳዊ ሰንበት ት/ቤት የተዘጋጀ
የስርዓተ ቤተክርስቲያን ምንጮች
ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በምንጭነት ወይም በመሠረትነት የሚጠቀሱ መጻሕፍት በርካታ ናቸው፡፡ ሆኖም ቤተክርስቲያን በቀኖናዋ የተቀበለቻቸው እና ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉትናቸው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ
መጻሕፍተ ሊቃውንት
የሲኖዶስ ውሳኔዎች
ሦስቱ ዓለም አቀፍ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤያት ወዘተ ናቸው፡፡
1- መጽሐፍ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ለምትወስናቸው ማንኛውም ዓይነት ትምህርትና ሥርዓት እንደ ምንጭነት ከምትጠቀምባቸው አንዱ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ስለሆነም የቤተ ክርስቲያንሥርዓት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በይዘቱ ልዩ የሆነ አምላካዊ መጽሐፍ ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ይዘትን እንዲህ ነው ብሎ መናገር የሚያስቸግር በርካታ እምቅ ትምህርቶችን የያዘ ሰፊመጽሐፍ ነው፡፡ በውስጡም ትምህርተ ሃይማኖት፣ ማኅበራዊ ጉዳይ፣ የልዩ ልዩ ሕብረተሰብእ አኗኗር፣ ዘዬ፣ ሥርዓት፣ባሕልና ቋንቋቸውን ይዟል፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የምንላቸው ሁለት ናቸው፡፡
የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ፨፬፮፨ እና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ፨፫፭፨ በጠቅላላ ፰፩ ቅዱሳት መጻሕፍትንም በውስጡ ይዟል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት ሥርዓቶች መካከል ለመጥቀስ ያህል እግዚአብሔር በሰዎች ኃጢአት ባዘነና ሊያጠፋቸው በወሰነ ጊዜ ለአምልኮው ቀናኢ ሆኖ ሕጉን ለጠበቀው ለኖኅ ግን ከጥፋት ውኃ የሚድንበትን መርከብ እንዲያዘጋጅ ነገረው «ከጐፈር እንጨት መርከብን ለአንተ ሥራ በመርከቢቱም ጉርጆች፨ክፍሎችን ፨ አድርግ በውስጥም በውጭም ለቅልቃት፡፡ እርስዋንም እንዲህ ታደርጋለህ ።።።» ፨ዘፍ ።፮ ኮ ፩፬፨ እያለ የመርከቢቱን ስፋት፣ቁመት፣ የውስጥ አከፋፈልና ጠቅላላ ሥርዓቱን በአዘዘው መሠረት አዘጋጀ፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴ ሕዝበ እስራኤልን ከግብጽ ካወጣቸው በኋላ የወጡበትን ቀን የነፃነት ቀን ፨ፋሲካ ፨ ለእግዚአብሔር በዓል እንዲያደርጉ አዘዛቸው ከዚህም ጋር በዓሉ የሚከበርበት ምክንያትና የአከባበር ሥርዓቱ በዝርዝር ተገልጾላቸዋል፡፡ ዘዳ ።፩፪÷ ፩
በአጠቃላይ መጽሐፍ ቅዱስ አያሌ ሥርዓቶችን በመያዙ ለዛሬዋ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ዋናው መሠረት ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ማወቅ ያለብን ነገር ቢኖር የትኛውምየ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ከተቃረነ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ የትኛውም ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አይጋጭም፣ በመጽሐፍ ቅዱስ መስፈሪያ የተሰፈረ ነውና፡፡
2- የሲኖዶስ ውሳኔዎች ፨ቀኖናተ ሲኖዶስ ፨
ሲኖዶስ ማለት ቃሉ የግሪክ ቃል ሲሆን ትርጉሙም የጳጳሳት አንድነት ወይም ጉባኤ ማለት ነው፡፡ አበው ከዘመነ ሐዋርያት አንስቶ በቤተ ክርስቲያን የተለያዩ ችግሮች ሲከሰቱ ተሰብስበው ውሳኔ ያስተላልፋሉ፡፡ ለምሳሌ የመጀመሪያው የሲኖዶስ ስብሰባ የተካሔደው በ ፶ ዓ ።ም በኢየሩሳሌም ሲሆን ለስብሰባቸው ምክንያት የነበረው ከአሕዛብ ወደ ክርስትና በመጡና ከይሁዲነት ወደ ክርስትና በመጡት አማንያን ፨ምእመናን ፨ መካከል በተፈጠረ ችግር ነበር፡፡ ከተለያየ ሥርዓተ ማኅበር የመጡ እንደመሆናቸው መጠን ወደ ክርስትና ሲገቡ ይኸው ጉዳይ አከራከራቸው ፡፡ ከይሁዲነት የመጡት ከአሕዛብነት የተመለሱትን «ካልተገረዛችሁና የሙሴን ሕግ ካልፈጸማችሁ ትድኑ ዘንድ አትችሉም» ብለው ያስተምሩ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት በእነርሱና በጳውሎስ በበርናባስም መካከል ጥልና ክርክር ሆነ፡፡ ይህንን ጉዳይ ለመወሰን ቅዱሳን ሐዋርያት በሙሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው በሐዋርያው ያዕቆብ ሰብሳቢነት ተወያይተው ውሳኔ በመስጠታቸው ክርክሩ አግባብ አገኘ፡፡ ዛሬም በልዩ ልዩ ምክንያቶች እንዳንለያይ የሐዋርያት ውሳኔ መሠረታችን ነው፡፡ የሐዋ።፩፭ ኮ ፩፡፪፱፡፡
ጌታም ለሐዋርያት «እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ እኔ ከናንተ ጋር እሆናለሁ» ባለው ዘለዓለማዊ ቃል መሠረት ይህ የአበው ሲኖዶስ ዛሬም ድረስ በሐዋርያት እግር በተተኩ አባቶች አማካኝነት የቀጠለ ሲሆን የተለያዩ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ አገልግሎት ያጠናክራሉ፡፡
በዚህ መሠረት የአባቶቻችን የሐዋርያት ሲኖዶስ የሥርዓት መጻሕፍት የሚባሉት አራቱ መጻሕፍት
ኦ ሥርዓተ ጽዮን ፨ዓይን ፨
ኦ ትዕዛዝ ሲኖዶስ ፨ረስጠብ ፨
ኦ ግጽው ሲኖዶስ ፨ረስጠጅ ፨
ኦ አብጥሊስ ሲኖዶስ ፨ረስጣ ፨
የሐዋርያት ሲኖዶስሲባሉ ጌታ ከዕርገቱ በፊት ከትንሣኤው በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ያስተማራቸው ሁለቱ ኪዳናት ፨መጽሐፈ ኪዳን ቀዳማዊና ካልዕ ፨ እንዲሁም ዲድስቅልያና ቀሌምንጦስሲ ጨመሩ ደግሞ ስምንቱ የሐዲስ ኪዳን የሥርዓት መጻሕፍት ፨ከ ፫፭ ቱ የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት መካከል የሥርዓት ክፍል መጻሕፍት ፨ ይባላሉ፡፡ እነዚህም ቤተክርስቲያን ከምትቀበላቸው ፰፩ ዱ መጻሕፍት ውስጥ ስምንቱ የሥርዓት መጻሕፍት የሚባሉት ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በነዚህ የሲኖዶስ መጻሕፍት ውስጥ ለቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት የሆኑ ውሳኔዎች ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ በሥርዓተ ቅዳሴ መግቢያ ላይ ካህናትና ዲያቆናት ከቤተልሔም ወደ ቤተ መቅደስ ኅብስትና ጽዋውን ይዘው ሲገቡ የሚያውጁት አዋጅ አለ፡፡ ሃሌ ሉያ እመቦ ብእሲ እምእመናን ዘቦአ ቤተክርስቲያን በጊዜ ቅዳሴ ወኢሰምዐ መጻሕፍተ ቅዱሳት ወኢተዐገሰ እስከ ይፌጽሙ ጸሎተ ቅዳሴ ።።። ሃሌሉያ በቅዳሴ ጊዜ ከምእመናን ወገን ወደ ቤተክርስቲያን የገባ ሰው ቢኖር ቅዱሳት መጻሕፍትን ሰምቶ የቅዳሴውን ጸሎት እስኪጨርሱ ባይታገስ ከቁርባንም ባይቀበል ከቤተ ክርስቲያን ይለይ የእግዚአብሔርን ሕግ አፍርሷልና የነፍስና የሥጋ ንጉሥበሚሆን በሰማያዊ ንጉሥ ፊት መቆምንም አቃሏል፡፡ ሐዋርያት በሲኖዶስ ውስጥ እንዲህ አስተማሩን፡፡» ይላል ይህ ሥርዓት በቀጥታ የተወሰደው ለሥርዓተ ቤተክርስቲያን ምንጭ ከሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አብጥሊስ ሲኖዶስ ፨ረስጣ ፨ ከሚለው መጽሐፍ ነው፡፡
3- ሦስቱ ጉባኤያት ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ምንጭነት ከሚጠቀሱት ውስጥ የአበው ጉባኤያት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ከሐዋርያት በኋላ በእግረ ሐዋርያት የተተኩ አበው ምእመናንን እያስተማሩና እየመሩ ወንጌል እያስፋፉ ሲኖሩ የሐዋርያትን ትምህርት ለመበረዝ ምእመናንን ለመከፋፈልና ለመበታተን በየጊዜው መናፍቃን ይነሱ ነበር ሐዋርያው ቅዱስጳውሎስ አስቀድሞ «የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ ኃጢአታቸው የተከመረባቸውን በልዩ ልዩ ምኞትም የሚወሰዱትን ሁልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች የሚማርኩ ከእነዚህ ዘንድ ናቸውና» ፨፪ጢሞ ።፫ ኮ ፭፡፰፨ እንዳለ እንደነዚህ ያሉመናፍቃን ሲነሱ አባቶች በአንድነት ተሰብስበው ጉባኤ ሠርተው ያመኑትን መልሰው አልቀበል አላምን ያለውን ለመለየት ልዩ ልዩ ጉባኤያት አካሒደዋል፡፡ ምንም እንኳ በጉባኤያቱ ለመናፍቃን ትምህርት መልስ መስጠትና በማይመለሱ ላይ የተወሰኑት ውሳኔያት ጎልተው ቢወጡም አብሮ ግን የተለያዩ ጉዳዮች ላይ በመወያየት ሥርዓት ይሠሩ ነበር፡፡ ስለዚህ እነዚህ ጉባኤያት ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያን የምትቀበላቸው ዓለም አቀፍ ጉባኤያት ሦስት ሲሆኑ ጉባኤ ኒቂያ፣ ጉባኤ ቁስጥንጥንያና ጉባኤ ኤፌሶን ይባላሉ፡፡
፩። ጉባኤ ኒቂያ
የኒቂያ ጉባኤ በ ፫፪፭ ዓ ።ም ኒቂያ ከተማ የተካሄደው የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የቤተክርስቲያን ጉባኤ ነው፡፡ በጉባኤው የተሰባሰቡት አባቶች ፫፩፰ ነበሩ፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ ፫፩፰ ቱ ሊቃውንት የመወሠን መብት ያላቸው ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት ይሁኑ እንጂ ጠቅላላ የጉባኤው ተሳታፊዎች ግን ከ ፪፲፻ በላይ እንደነበሩ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ ለምሳሌም የምእመናን ተወካዮች፣ የሕግ አማካሪዎች የሀገር መሪዎች በጉባኤው ላይ በታዛቢነት ነበሩ፡፡ የኒቂያ ጉባኤ ዓላማ «ወልድ ፍጡር» ብሎ የተነሳውን አርዮስን ከሽተቱ ለመመለስ ወይም በትምህርቱ ምክንያት ከቤተ ክርስቲያን አንድነት ለመለየት ነበር በተጨማሪም የትንሣኤ በዓል አከባበር በየዓመቱ የተለያየ ቀን ይውልና በተዘበራረቀ ሁኔታ ይከበር ስለነበር ሰፊ ውይይት ካደረጉ በኋላ ቀኑ እሑድ ብቻ ንዲውልና በአንድነት እንዲከበር ወሰኑ፡፡ አርዮስን ካወገዙ በኋላ የጸሎተ ሃይማኖትን የመጀመሪያውን ክፍል በማጽደቅ ኦርቶዶክስ ፨ቀጥተኛ እምነት ፨ በማለት አንዲቱንሃይማኖት አጽንተዋል፡፡ በመጨረሻም ፪0 አንቀጽ ያለውን ሥርዓት ወስነዋል፡፡
፪። የቁስጥንጥንያ ጉባኤ
መቅዶንዮስ ቁጥሩ ከመንፈቀ አርዮሳውያን ነው፡፡ ምክንያቱም አርዮስ የወልድን አምላክነት ሲክድ መቅዶንዮስ ደግሞ ከቅድስት ሥላሴ ሦስተኛው አካል መንፈስቅዱስ ሕጹጽ ፨መለኮትነት የሌለው ፨ ፍጡር ነው በማለት በመላዋ ቁስጥንጥንያ አስተምሯል፡፡ የቁስጥንጥንያ ጉባኤ የተካሔደው በ ፫፰፩ ዓ.ም ቁስጥንጥንያ ፨ግሪክ ፨ ሲሆን በታላቁ ንጉሥ ቴዎድሮስ ዘመን የተደረገ ነው፡፡ በጉባኤው የተሳተፉ ጳጳሳት ብዛት ፩፶ ያህል ሲሆን የጉባኤው መሰብሰብም ምክንያቱ የመቅዶንዮስ፣ የአቡሊናርዮስ፣ የአውሳብዮስ ክህደቶች ናቸው፡፡ በዚህ ጉባዔ መናፍቃኑ ከተወገዙ በኋላ ውሳኔዎች ተላልፈዋል፡፡ በዚህ ጉባዔ ለመናፍቃኑ ትምህርት መልስ ለመስጠት በተካሄደው ውይይት ከኒቅያ ጉባኤ የቀጠለ የሃይማኖት ድንጋጌናሌሎች በርካታ ሥርዓቶች ተደንግገዋል፡፡
፫። የኤፌሶን ጉባዔ
ንስጥሮስ ያስተማረው ትምህርት ምንታዌ ወይም ሁለት ባህርይን ነው በርሱ ትምህርት ከማርያም የተወለደው የዳዊት ልጅ ከእግዚአብሔር የተወለደው የእግዚአብሔር ልጅ ነው አለ፡፡ ስለዚህ ከእግዚአብሔር አብ የተወለደው ቃል ከማርያም በተወለደው የዳዊት ልጅ ማደርያ ነው፡፡ ይህ በአጠቃላይ ቃል ሥጋ ሆነ የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስና የቤተ ክርስቲያንን ጽኑህ እምነት የሚቃወም ነው፡፡ የኤፌሶን ጉባኤ የተካሄደው በ ፬፫፩ ዓ ።ም በትንሹ ቴዎድሮስ ዘመን ሲሆን የተሰባሰቡት አበው ብዛት ፳0 ነው፡፡ የስብሰባው ዋና ዓላማም ንስጥሮስን ከክህደት ለመመለስ ሲሆን የጉባኤው አፈ ጉባኤ ቅዱስ ቄርሎስ ነበር፡፡ በዚህ ጉባኤም ንስጥሮስ ከተወገዘ በኋላ ስምንት ቀኖናዎች ተወስነዋል፡፡
4- መጻሕፍተ ሊቃውንት የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የጻፏቸው መጻሕፍት «መጻሕፍተ ሊቃውንት» በሚል ስም ይታወቃሉ፡፡ ከነዚህም ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው ፡፡
ሃይማኖተ አበው
መጽሐፈ ቅዳሴ
መጽሐፈ ቄርሎስ
ድርሳን ወተግሣጽ ዘዮሐንስ አፈወርቅ ወዘተ ተጠቃሾች ናቸው፡፡