ስለ እመቤታችን ቅዱሳን መጻሕፍት ምን ይላሉ

ብዙኃን_ማርያም

“እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦአታልና፥ ማደሪያውም ትሆነው ዘንድ ወድዶአታልና፥ እንዲህ ብሎ። ይህች ለዘላለም ማረፊያዬ ናት፤ መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ”( መዝ 132÷13-14)
በቤተ ክርስቲያናችን ከሚዘከሩ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በዓላት መካከል መስከረም ፳፩ ቀን የሚውለው በዓል ‹ብዙኃን ማርያም› በመባል ይታወቃል፡፡
በዓሉ በ፪ ዐበይት ምክንያቶች ይከበራል፤
፩ኛ. ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ውሳኔ ለማዘጋጀት ከሩቅም ከቅርብም የተሰባሰቡት ቀን ሲሆን።
፪ኛ .ደግሞ ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ዕፀ መስቀል በግሸን ደብረ ከርቤ የተቀመጠበት ዕለት መኾኑ ነው፡፡ ሁለቱንም ታሪኮች ከዚህ ቀጥለን እንመለከታቸዋለን፤
በ፫፻፳፭ ዓ.ም አርዮስ የሚባል መናፍቅ የእግዚአብሔር ወልድን የባሕርይ አምላክነት አልቀበልም በሚል ክህደት እርሱ ተሰናክሎ ለሌሎችም መሰናክል ኾነ፡፡ – – ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት አርዮስ ክህደቱን እንዲተው ቢመክሩትም ሊመለስ አልቻለም፡፡ ይህ የአርዮስ ክህደትም በሊቃውንቱ መካከል መለያየትን ፈጠረ፡፡
– ጊዜው ታላቁ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ‹‹ የጣዖታት ቤቶች ይዘጉ፤ አብያተ ክርስቲያናት ይከፈቱ!› › የሚል ዐዋጅ የነገረበት ወቅት ነበርና ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ በአርዮስ ክህደት ምክንያት በኒቅያ የሃይማኖት ጉባኤ እንዲካሔድ በየሀገሩ ላሉ ሊቃውንት መልእክት አስተላለፈ፡፡ በዚህም መሠረት ከሚያዝያ ፳፩ ቀን ጀምሮ እስከ መስከረም ፳፩ ቀን ድረስ ፳፫፻፵፰ (ሁለት ሺሕ ሦስት መቶ ዐርባ ስምንት) ሊቃውንት በኒቅያ ተሰበሰቡ።
ኒቅያ ለዚህ ጉባኤ የተመረጠችበት ምክንያትም ጳጳሱን ከማኅበረ ካህናቱ፤ ንጉሡን ከሠራዊቱ ጋር አጠቃላ ለመያዝ የምትችልበት ሰፊና ምቹ ቦታ ከመኾኗ ባሻገር ለኹሉም አማካይ ሥፍራ ስለነበረች ነው፡፡
°√ በጉባኤው ከተሰበሰቡ ሊቃውንት መካከልም እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ሙታንን ያስነሡ፣ ለምጽ ያነጹ፣ አንካሳ ያረቱ፣ የዕውራንን ዓይን ያበሩ ድውያንን የፈወሱ፣ ሌላም ልዩ ልዩ ተአምራት ያደረጉ፤ እንደዚሁም ስለ ርትዕት ሃይማኖታቸው በመጋደል ዐይናቸው የፈረጠ፣ እጃቸው የተቈረጠ አበው ይገኙበታል፡፡
°√ ሊቃውንቱ ሱባዔ ይዘው በጸሎት ከቆዩ በኋላ ኅዳር ፱ ቀን በንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ሊቀ መንበርነት፣ በእለእስክንድሮስ አፈ ጉባኤነት ጉባኤው ተጀመረ፡፡ ንጉሡ ሊቃውንቱን ‹‹ስማችሁን፣ አገራችሁንና ሃይማኖታችሁን ጽፋችሁ ስጡኝ›› ባላቸው ጊዜም ከ፳፫፻፵፰ቱ መካከል ፫፻፲፰ (ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ) ሊቃውንት ሃይማኖታቸውን ሲገልጹ እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ኾነው ‹‹ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ፤ ወልድ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በመለኮት፣ በሥልጣን፣ በፈቃድ፣ በህልውና አንድ ነው›› ብለው ጽፈው ሰጡት፡፡
°√ ንጉሡም ‹‹ሃይማኖት እንደ ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት ይኹን›› ብሎ ዐዋጅ አስነግሯል፡፡፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት በጉባኤው አርዮስን አውግዘው በመለየት ‹‹ነአምን በአሐዱ አምላክ፤ በአንድ አምላክ እናምናለን›› የሚለውን የሃይማኖት ጸሎት (የሃይማኖት መሠረት) እና ሌሎችንም የሃይማኖት ውሳኔዎች ደንግገዋል፡፡
‘°√ ሊቃውንቱ ጉባኤውን ያካሔዱት ኅዳር ፱ ቀን ይኹን እንጂ በአንድነት የተሰባሰቡት መስከረም ፳፩ ቀን ስለ ነበረ ይህ ዕለት ‹ብዙኃን ማርያም› እየተባለ ይጠራል፡፡ ብዙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ለሃይማኖታዊ ጉባኤ የተሳባሰቡበት ዕለት ነውና፡፡ እነዚህ ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት በኦሪት ዘፍጥረት የተጠቀሱት የአብርሃም ብላቴኖች ምሳሌዎች ናቸው (ዘፍ. ፲፬፥፲፬)፡፡
-°√በሌላ በኩል መስከረም ፳፩ ቀን የጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በደቡብ ወሎ በአምባሰል ተራራ በግሸን ደብረ ከርቤ የገባበትና በዓሉ የከበረበት ዕለት ነው፡፡ ታሪኩም በአጭሩ የሚከተለው ነው፤ ዐፄ ዳዊት መንፈሳዊና ደግ ንጉሥ ነበሩ፡ በዘመናቸው በኢትዮጵያ ቸነፈር ተከሥቶ ሕዝቡ ስለ ተሰቃየባቸው እጅግ አዘኑ፤ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክቱም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላኩ ባሕታዊ መጥተው‹‹የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል አስመጥተህ በሀገርህ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አሠርተህ ብታስቀምጥ ረሃቡ፣ ቸነፈሩ ኹሉ ይታገሥልሃል›› አሏቸው፡፡
°√•ዐፄ ዳዊትም ከብዙ ገጸ በረከት (ስጦታ) ጋር ‹‹የጌታችንን መስቀል ላኩልኝ›› የሚል መልእክት አስይዘው መልእክተኞችን ወደ ኢየሩሳሌም ሰደዱ፡፡ መልእክተኞቹም በታዘዙት መሠረት መስቀሉን ይዘው መምጣታቸውን ዐፄ ዳዊት ሲሰሙ ‹‹ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት›› ብለው አሳውጀው መስቀሉን ለመቀበል ጉዞ ጀመሩ፡፡ ዐፄ ዳዊት ስናር (ሱዳን) ደርሰው ከመልእክተኞቹ ጋር ተገናኝተው መስቀሉን በክብር አጅበው ወደ መካከል ኢትዮጵያ ለማስገባት ሲነሡም ከበቅሏቸው ወድቀው ጥቅምት ፱ ቀን ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፤ በዚህም ሠራዊታቸው ተደናግጠው የጌታችንን መስቀል እዚያው ትተው የዐፄ ዳዊትን አስከሬን ይዘው ተመለሱ፡፡ መስቀሉ በስናር ከቆየ በኋላ የዐፄ ዳዊት ልጅ ዘርዐ ያዕቆብ ሲነግሡ ወደ መሃል ኢትዮጵያ አምጥተው ቤተ ክርስቲያን አሠርተው ለማስቀመጥ ቢያስቡም ምቹ ቦታ ግን ሊያገኙ አልቻሉም ነበር፡፡ ንጉሡና ሠራዊታቸው ምቹ ቦታ ሲፈልጉ መስቀሉን በኤረር ተራራ፣ በደብረ ብርሃን፣ በመናገሻ ማርያም ዓምባ፣ በእንጦጦ ጋራ ብዙ ጊዜ አስቀምጠውት ቆይተዋል፡፡መስቀሉ በእንጦጦ ጋራ ሳለ እግዚአብሔር አምላክ‹‹አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤መስቀሌን በመስቀለኛ ተራራ ላይ አስቀምጥ›› የሚል ቃል ለንጉሡ በራእይ ነገራቸው፡፡ መስቀሉን ወደወሎ ሀገረ ስብከት እንዲወስዱትም አዘዛቸው፡፡ ንጉሡና ሠራዊታቸው በእግዚአብሔር መሪነት መስቀሉን ይዘው ወሎ ሲደርሱም ጌታችን ወደ አምባሰል እያመለከተ ‹‹አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀለኛ ተራራ ላይ አስቀምጥ›› ይላቸው ነበር፡፡ ንጉሡ መስቀሉን ይዘው ወደ ቦታው ሲያመሩ መስቀለኛው የግሸን ተራራን አገኙ፤ በዚያም ቤተ ክርስቲያን አሠርተው በ፲፬፻፵፮ (1446) ዓ.ም የጌታችንን መስቀል በክብር አስቀምጠውታል፡፡

-ከዚህ በኋላ ንጉሡ ‹‹መካከሏ ገነት፤ ዳሯ እሳት ይኹን! የበረረ ወፍ፣ የሠገረ ቆቅ አይታደንባት! በድንገት ሰው የገደለ፣ ቋንጃ የቈረጠ ወንጀለኛ አይያዝባት!›› ብለው ዐዋጅ አስነግረዋል፡፡ የእመቤታችን ጽላትም አብሮ በግሸን ደብረ ከርቤ እንዲቀመጥ አድርገዋል፡፡ ስለዚህም መስከረም ፳፩ ቀን በየዓመቱ በቤተ ክርስቲያናችን በድምቀት ይከበራል፡፡ ኀጢአታቸውን ለካህን ተናዘው፣ ንስሐ ገብተው በዚህ ዕለት ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ በመሔድ የሚጸልዩና የሚማጸኑ ምእመናን ኹሉ እስከሰባት ትውልድ ድረስ የምሕረት ቃል ኪዳን እንደሚያገኙም ጤፉት በተባለችው መጽሐፍ ተጠቅሷል፡፡
እመቤታችን በረድኤት አለየን!

“እምነ ጽዮን ይብል ሰብእ” (ሰው እናታችን ጽዮን ይላል) መዝ 76፤ 5

ጽዮን ማናት?
ጽዮን ማለት አምባ መጠጊያ መሸሸጊያ ማለት ሲሆን ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት የገዛ ልጁ አቢሴሎም ሊገድለው በተነሳ ጊዜ ከሞት ያመለጠው የጽዮንን ተራራ አምባና መሸሸጊያ በማድረግ ነው፡፡ ለጊዜው ቅዱስ ዳዊት የጽዮንን ተራራ መከታ በማድረግ ከሞት ድኗል፡፡ ለፍጻሜው ግን ፍጥረት ሁሉ አማናዊት ጽዮን በተባለች በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አምባና መጠጊያነት ከሞት ወደ ሕይወት ተሸጋግሯልና እርሷ እውነተኛ መሸሸግያና መከታ ሆናለች፡፡ ነገር ግን ብዙዎች የአብዬን ወደ እምዬ በማድረግ ጽዮን የሚለው ቃል ለተራራው ብቻ እንጂ ለድንግል ማርያም ሊጠቀስ አይገባም በማለት ይናገራሉ፡፡ እስኪ መጽሐፉ ይገለጥና ጽዮን እየተባሉ ስለሚጠሩት አካላት እውነቱን ይንገረን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ጽዮን የሚለውን ቃል ለአራት ነገሮች ተጠቅሞባቸዋል፡፡
1ኛ) በኢየሩሳሌም የሚገኘው የጽዮን ተራራ
“ዳዊትም አምባይቱን ጽዮንን ያዘ እርሷም የዳዊት ከተማ ናት” 2ኛ ሣሙ 5÷7
2ኛ) ሕዝበ እሰራኤል በጽዮን ስም ይጠራሉ
“አንተ ተነስ ጽዮንንም ይቅር በላት የምሕረትዋ ጊዜ ነውና ዘመንዋም ደርሷልና” መዝ 101÷13
3ኛ) መንግስተ ሰማያት ጽዮን ትባላለች
“ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው የእግዚአብሔር ከተማ ደርሳችል ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም” ዕብ 12÷22
4ኛ) እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጽዮን ትባላለች
“ሰው እናታችን ጽዬን ይላል በውስጥዋም ሰው ተወለደ” መዝ 76÷5
+++የአራቱ ጽዬኖች አከፋፈል
ከላይ ያየናቸው ጽዮኖች በሑለት ይከፈላሉ
1ኛ) የሚያልፉ
• የጽዮን ተራራ እና
• ጽዮን የእስራኤል ሕዝብ (እነዚህ ሰማይና ምድር ሲያልፉ ይጠፋሉ)
2ኛ) የማያልፉ (ዘለዓለማውያን)
• ጽዮን መንግሥተ ሰማያት እና
• ጽዮን ድንግል ማርያም
+++የአራቱ ጽዬኖች መሰረታዊ ልዩነት
በጽዮን ተራራ ፣ በእስራኤል ሕዝብ እና በጽዮን መንግሥተ ሰማያት ላይ እግዚአብሔር ቢያድር በመንፈስ ብቻ ነው፡፡ በአማናዊት ጽዮን በድንግል ማርያም ላይ ግን እግዚአብሔር ያደረው በሥጋም በመንፈስም ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በጽዮን ስም የተጠሩት አካላት ሁሉ ምሳሌነታቸው ለድንግል ማርያም ነው፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ስለጽዮን ተናገረ ስንል ስለ አራት ነገሮች መናገሩን ማስተዋል ይኖርብናል፡፡ ምን አልባትም ስለ ጽዮን ስንነጋገር ስለተራራና ስለ እስራኤል ሕዝብ ለመነጋገር እንዳልሆነ ይገንዘቡ፡፡ ነገር ግን ስለ አማናዊት ጽዮን ስለ ድንግል ማርያም የተነገሩትን ቃላት ለተራራና ለእስራኤል ሕዝብ ነው እያሉ የመጽሐፍትን ቃል ለሚሸቃቅጡት መናፍቃን ግንዛቤ ይሆናቸው ዘንድ የምንነጋገረው ስለ አማናዊት ጽዮን ስለ ድንግል ማርያም ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን እኛ ኦርቶዶክሳውያን ጽዮን የሚል ቃል ስላገኘን ብቻ ይሄ ቃል ለድንግል ማርያም ተናግሯል የሚል አስተሳሰብ የለንም ይልቁንም ለማን እንደተናገረ እንመረምራለን እንጂ!!!
+++ ለምሳሌ “ዳዊትም አምባይቱን ጽዮንን ያዘ እርሷም የዳዊት ከተማ ናት” 2ኛ ሳሙ 5÷7
የሚለውን ቃል አንድ ሰው ወስዶ ይሄ የተናገረው ለድንግል ማርያም ነው ቢል ተሳስቷል ምክንያቱም ይሄ ቃል እየተናገረ ያለው ስለ ጽዮን ተራራ ነው፡፡
+++ እንዲሁም “አንተ ተነስ ጽዮንንም ይቅር በላት የምህረትዋ ጊዜ ነውና ዘመንዋም ደርሷልና” መዝ 101(102)÷13 የሚለው ቃል ፈጽሞ ለድንግል ማርያም የተናገረ አይደለም ምክንያቱም ድንግል ማርያም ምን አጥፍታ ነው ጽዮንን ይቅር በላት ያለው፡፡ ነገር ግን ተደጋጋሚ ስህተት ስለሰሩት ስለ እስራኤል ሕዝብ ተናገረ እንጂ፡፡
+++ በተጨማሪ “ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው የእግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም” ዕብ 12÷22 ሲል ስለ ጽዮን መንግሥተ ሰማያት መናገሩ እንጂ ስለ ድንግል ማርያም አይደለም፡፡
+++ ነገር ግን “ሰው እናታችን ጽዮን ይላል በውስጧም ሰው ተወለደ እርሱ ራሱም ልዑል መሠረታት” መዝ87÷5 የሚል ቃል ካገኘን ግን ይህንን ክብር ለማንም አንሰጥም ከጽዮን ድንግል ማርያም በቀር፡፡ ለምን ቢሉ
• ተራራ ሰው አይወልድም!
• የእስራኤል ሕዝብም እንደዚያው!
• በመንግሥተ ሰማያትም ቢሆን ሰው ተወልዶ አያውቅም አይወለድምም!!! በአማናዊት ጽዮን በድንግል ማርያም ግን አምላክ ሰው ሆኗል ተወልዶማል፡፡ ደግሞም ማንም ተራራን እናታችን አይልም፡፡ የእስራኤል ሕዝብንና መንግሥተ ሰማያትንም እንደዛው ፡፡ ነገር ግን ድንግል ማርያም በመስቀል ስር እናት ተብላ ተሰጥታናለችና እናታችን ጽዮን እንላታለንዬሐ 19÷27 :: በዚህ ዓይነት አረዳድ በታች ያሉትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃላት መመልከቱ አስፈላጊ ነውና በማስተዋል ያንብቡ፡፡
+++“እግዚአብሔር ጽዮንን መርጧታልና ማደሪያውም ትሆን ዘንድ ፈቅዷልና ንዲህም ብሎ ይህች ለዘለዓለም ማረፍያዬ ናት መርጫታለሁ በእርሷ አድራለሁ” መዝ 131÷13-14 :: የሚለው ቃል ለማንም አልተነገረም ለድንግል ማርያም እንጂ!!!
***ማስረጃ፣ በጽዮን ተራራና በእስራኤል ሕዝብ ላይ እግዚአብሔር ለዘለዓለም ማደር አይችልም፡፡ እነርሱ ሰማይና ምድር ሲያልፉ ይጠፋሉና፡፡በመንግስተ ሰማያት ደግሞ የሰው ልጆች የወደፊት መኖሪያ ስፍራ ናት እንጂ የእግዚአብሔር የዘለዓለም ማደሪያ አይደለችም ነገር ግን በመንፈስ ያድርባታል፡፡ ድንግል ማርያምን ግን ለዘለዓለም ማደሪያው ትሆን ዘንድ ከአንስተ ዓለም ለይቶ ማኅፀኗን ዓለም አድርጐ እግዚአብሔር መርጧታል፡፡ በተጨማሪም እርሷ የማታልፍና የማትናወጽ ዘለዓለማዊት ናት፡፡
+++“የአስጨናቂዎችሽም ልጆች አንገታቸውን ደፍተው ወደ አንቺ ይመጣሉ የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ የእግዚአብሔርም ከተማ የእስራኤልም ቅዱስ የሆንሽ ጽዮን ይሉሻል” ኢሳ 60÷14::
ይህን ቃል ብዙዎቻችን እናውቀዋለን ለብዙ ዘመናትም ስንጠቅሰው ኖረናል፡፡ እኛ ለጽዮን ድንግል ማርያም ተጽፏል ስንል ሌሎች (መናፍቃን) ደግሞ ለተራራ ነው ሲሉ ኖረዋል :: እስኪ መጽሐፍ ቅዱስ ዳኛ ይሁንና እውነቱን ይመስክር፡፡ ቃሉንም ጽዮን ተብለው ከተጠሩት አካላት ጋር በማነጻጸር እንመልከት፡፡
***ይህን ጥቅስ ለተራራ ነው እንዳንል
• ለተራራ መስገድ ከባድ ኃጢአት ነው ጣዖት እንደማምለክ ይቆጠራል!!!
• ተራራ ጫማ እና እግር የለውም!!!
***ለእስራኤል ሕዝብ ነው እንዳንል
• ለእስራኤል ሕዝብ አይሰገድም!!!
• የእስራኤል ሕዝብ ከተማ አይደለም!!!(የእግዚአብሔር ከተማ ይላልና)
***ለመንግሥተ ሰማያት ነው እንዳንል ደግሞ
• መንግሥተ ሰማያትን የሚንቅ የለም!!! (የናቁሽ ሁሉ ይላልና)
• መንግሥተ ሰማያት ጫማና እግር የላትም!!! (ወደ እግርሽ ጫማ ይላልና)
• መንግሥተ ሰማያት የእግዚአብሔር ከተማ አይደለችም!!! (የእግዚአብሔር ከተማ ይላልና) ነገር ግን ይህንን ቃል ለእመቤታችን ለድንግል ማርያም ተገቢ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
+++“ጽዮንን የሚጠሉ ሁሉ ይፈሩ ወደ ኋላቸውም ይመለሱ” መዝ 128(129)÷5:: “ጽዮንን የሚጠሉ” ሲል ተራራን አልያም የእስራኤልን ሕዝብ የሚጠሉ ለማለት አይደለም ማንም ከመሬት ተነስቶ ተራራን ወይም ሕዝብን የሚጠላ የለም መንግስተ ሰማያትንም ቢሆን ማንም አይጠላትም ይመኛታል እንጂ !!! ድንግል ማርያምን ግን ሰይጣን በመናፍቃን ልብ አድሮ ጥላቻን ዘርቷልና ድንግል ማርያምን የሚጠሉ ሁሉ ይፈሩ ወደኋላቸውም ይመለሱ ሲል ነው፡፡ እንግዲህ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ተቃዋሚዎች ግን የድንግል ማርያምን ስም ለመቃወም ብቻ ጽዮንን የሚለውን ቃል ለተራራ ነው ሲል ይሰማሉ፡፡ እውነት ለተራራ ፍቅር ኖሯቸው ነው ወይስ ለተቃውሞ??? እንደው መከራከርስ ካለብን ለግዑዙ ፍጥረት ለተራራ ወይስ ለመዳናችን መሰረት ለድንግል ማርያም??? ደግሞስ ተራራ ለኛ ምናችን ነው??? ተራራ እኮ የድንጋይ እና አፈር ክምር ነው!!! ታዲያ ለኃላፊና ጠፊው ነገር ጽዮን የሚለውን የክብር ስም ከሰጠን ለማታልፈውና ለአማናዊቷ ጽዮን ለድንግል ማርያም መስጠቱ ምነው ተራራ ሆነብን??? ለምንስ ከበደን??? ፍርዱን ለሕሊናችን፡፡ ውድ አንባቢያን መሠረታዊ የሆኑ የጽዮንን አንድምታዎችን በጥቂቱ አቀረብኩ እንጂ እጅግ ብዙ የሆኑ ሌሎች ስለ ጽዮን ድንግል ማርያም የተጻፉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃለት መኖራቸውን ሳልገልጽ አላልፍም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ‹‹ታቦተ እና ቤተክርስቲያን›› ጽዮን በመባል ይጠራሉ፡፡

 ክብር ለእናታችን ጽዮን ድንግል ማርያም ይሁን አሜን፡፡

አባ ገ/ሚካኤል

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመፅሐፍ ቅዱስ

“እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል” የሉቃስ ወንጌል 1:48

“እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦታልና ማደራያውም ትሆነው ዘንድ ወዶታልና።ይቺ የዘላለም ማረፊያዬ ናት መርጫታለሁና በዚችም አድራለሁ።” መዝ 131: 12-14

“ታላቅ ምልክት በሰማይ ታየ። ፀሀይ ተጎናስፋ ጨረቃ በእግሮቾ በኩል ያላት በራሶ ላይ አስራ ሁለት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች” ራዕ፡ዮሐ 12:1-3

“ለአንቺም የማይገዛ ሕዝብና መንግሥት ይጠፋል፥ እነዚያ አሕዛብም ፈጽመው ይጠፋሉ ። ኢሳይያስ 60፤12

“በወርቅ ልብስ ተጎናስፋና ተሸፋፍና ንግስቲቱ በቀኝህ ትቆማለች። ልጀ ሆይ ስሚ እይ ጆሮሽንም ኣዘንብይ ወገንሽን ያባትሽንም ቤት እርሺ ንጉስ ውበትሽን ወዷልና እርሱም ጌታሽ ነው። የምድር ባለጠጎች፡ አህዛብ በፊትሽ ይማለላሉ።” መዝ 44/45 : 9-10

“በአባቶችሽ ፋንታ ልጆች ተወለዱልሽ።በምድር ላይ ገዠሆች አድርገሽ ትሾሚአቸዋለሽ።ለልጅ ልጅ ሁሉ ስምሽን ይሳስባሉ ስለዚህ ለአለምና ለዘላለም አህዛብ ይገዙልሀል።” መዝ 44 : 12-14

“ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።” ትንቢተ ኢሳይያስ 7:14

“በገነቱ የምትቀመጪ ሆይ፥ ባልንጀሮች የአንቺን ቃል ያደምጣሉ፤ ቃልሽን አሰሚኝ። መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን 8:13”

“እግዚአብሔር ዘር ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆንን እንደ ገሞራም በመሰልን ነበር።”ትንቢተ ኢሳይያስ 1-9

“ጽዮንን ክበቡአት፥ በዙሪያዋም ተመላለሱ፥ ግንቦችዋንም ቍጠሩ” መዝ 48:12

“ሰው ሁሉ እናታችን ጽዮን ይላል፥ ከውስቶም ሰው ተወልዶባታል።”መዝ 68:15

“በአንቺ የሚኖሩ ሁሉ ደስተኞች ናችው።” መዝ 86:7

“ወደ ምስራቅ ወደሚመለከተው በስተውጪ ወዳለው በር አመጣኝ ተዘግቶም ነበር።እግዚአብሔርም ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም ሰውም አይገባበትም የእስራዬል አምላክ ቅዱስ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል።” ትንቢተ እስቄል 44-1

“ስለ ጽዮን ዝም አልልም፥ ስለ ኢየሩሳሌምም ጸጥ አልልም፥ ጽድቅዋ እንደ ጸዳል መዳንዋም እንደሚበራ ፋና እስኪወጣ ድረስ።አሕዛብም ጽድቅሽን ነገሥታትም ሁሉ ክብርሽን ያያሉ፤ የእግዚአብሔርም አፍ በሚጠራበት በአዲሱ ስም ትጠሪያለሽ።በእግዚአብሔር እጅ የክብር አክሊል፥ በአምላክሽም እጅ የመንግሥት ዘውድ ትሆኛለሽ።”ኢሳ 62:1-3

“አቤቱ ወደረፍትህ ተነስ አንተና የመቅደስህ ታቦት” መዝ.131፡8

“ሰው እናታችን ጽዮን ይላል፥ በውስጥዋም ሰው ተወለደ እርሱ ራሱም ልዑል መሠረታት።”መዝ 87:5

“ጽዮንን የሚጠሉ ሁሉ ይፈሩ፥ ወደ ኋላቸውም ይመለሱ።”መዝ 129:5

“እህቴ ሙሽራ የተቆለፈ ገነት፣ የተዘጋ ምንጭ፣ የታተመ ፈሳሽ ናት” መኃ.4፣12

“ለአንቺ የማይገዛ ሕዝብና መንግሥት ይጠፋል” ኢሳ.60፣12

“ከአንቺ ጋር የሚጣሉትን እጣላቸዋለሁ” ኢሳ.49፣25

“እነኋት እናትህ› ብሎ በዮሐንስ አማካይነት ሰጥቶናልና” ዮሐ.19፣26

“በአዳምና በሄዋን አማካኝነት ወደ ዓለም የገባውን መርገም የሻረ ጌታ እግዚአብሔር ከእርስዋ በመወለዱ እምቤታችን /የብዙዎች እመቤት/ ትባላለች፡፡ “ሮሜ.5-6-11፡፡

“አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፥ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው።የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል? እነሆ፥ የሰላምታሽ ድምጽ በጆሮዬ በመጣ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና።ከጌታ፤ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት።” የሉቃስ ወንጌል 1:41-45

“የአስጨናቂዎችሽም ልጆች አንገታቸውን ደፍተው ወደ አንቺ ይመጣሉ፥ የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ፤ የእግዚአብሔርም ከተማ፥ የእስራኤል ቅዱስ የሆንሽ ጽዮን ይሉሻል። ከሰውም ማንም እስከማያልፍብሽ ድረስ የተተውሽና የተጠላሽ ነበርሽ፤ ነገር ግን የዘላለም ትምክሕትና የልጅ ልጅ ደስታ አደርግሻለሁ።” ትንቢተ ኢሳይያስ 60:14-15

“መልካም ነገር ያደረጉ ብዙ ሴቶች አሉ፥ አንቺ ግን ከሁሉ ትበልጫለሽ።” መ.ምሳሌ 31:29

ዳውንሎድ ሞባይል አፕ

ሶሻል ሚድያ ላይ ያግኙን

 

Copyright © 2010 – 2023 zetewahedo.com | All rights reserved.
error: Content is protected !!
Scroll to Top