✥ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እዚህ በመጫን ያንብቡ
✥ ፹፩ (81) መፅሐፍ ቅዱስ እዚህ በመጫን ያንብቡ
✥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት_የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክና ትርጉም እዚህ በመጫን ያንብቡ
✝የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መግቢያ ✝
ክፍል አንድ
መጽሐፍ ቅዱስ ምንድነው? 🗝
መጽሐፍ ቅዱስ ቃሉ እንደሚያመለክተው መጽሐፍ እና ቅዱስ የሚሉ የሁለት ቃላት ጥምረት ነው ፡፡
★“መጽሐፍ” ለሚለው ምንጭ በግሪክ ቋንቋ ቢብሎስ (byblos) ከደንገል በተሠራ ወረቀት ወይም በብራና ከተጻፈ በኋላ በሁለት በትሮች የሚጠቀለል መጽሐፍ ያመለክታል፡፡ ይህ ስም ቢብሎስ (byblos) ከተባለ ከተማ ስም የተገኘ ነው ፤ እርሱም ከኒቂያ ወደቦች መካከል በቤይሩት 25 ማይል ያህል ርቆ የሚገኝ አገር ነው ፡፡ ለመጽሐፍ ያገለግል ዘንድ ፓፒረስ (ደንገል) የተባለውን ተክል እንደ ወረቀት አድርገው ይሠሩበት የነበረ ቦታ ነው ፡፡ቢብሎስ በእንግሊዘኛው ባይብል ተብሎ ሲተረጎም በአማርኛው ደግሞ መጽሐፍ በሚለው የግብር ስም ቃል ተተረጐመ ፡፡
★“ቅዱስ” (holy)የሚለውን ስናይ ደግሞ ልዩ፣ክቡር ለእግዚአብሔር የተለየ ማንኛውንም ነገርን ያመለክታል፡፡እግዚአብሔር በራሱ ከፍጥረታት ልዩ ነው፣ ከጣኦታት የተለየ ነው መንፈሱም(ሐሳቡም) ከክፋት ሐሳብ የተለየ ስለሆነ ቅዱስ ነው፡፡ጠቅለል አድርገን ስናየው ስለ ቅዱሱ እግዚአብሔር ያለፈውም መጪውም ስራ፣በመረጣቸውና ባመኑበት ሰው ልጆች ላይ ያደረገውንና ያለው ሐሳቡ ፈቃዱ ወዘተ ላይ የሚያወራ መጽሐፍ ስለሆነ ቅዱስ መጽሐፍ ተብሏል፡፡በእንግሊዘኛውም “holy bible” በማለት ይጠራል፡፡
☞ መጽሐፍ ቅዱስ ሁለት ክፍሎችን የያዘ ነው::የመጀመርያው ክፍል #ብሉይኪዳን ሲሆን የእግዚአብሔር የድሮው መሐላ(የአብርሐም ዘር እንደሚበዛና ከንአን ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ያለው ምድር እንደሚሰጠው በዘሩም አለሙ ሁሉ እንደሚባረክ)የሚገልጽ ሲሆን
✡ እግዚአብሔር ፍጥረታትን ከመፍጠሩ ጀምሮ ስለ ሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ክብር መለየት አወዳደቅና በምድር ላይ መብዛት
✡በእግዚአብሔር ስለ ተወደደ አብርሐምና በዘሩ ዓለም እንደሚባረክ መሐላ
✡ስለ የያእቆብ ልጆች ወደ ግብጽ መሰደድና ከባርነት በእግዚአብሔር ድንቅ ረዲኤት መመለስ
✡ስለ እስራኤል መንግስት መመስረት መስፋትና የነገሥታቱ ታሪክ
✡መዝሙራትና ምሳሌያዊ የጥበብ ትምህርቶችን
✡ስለ ሰው ልጅ ወደ እግዚአብሔር ክብርና ፍቅር መመለስ ትንቢት ማለትም እግዚአብሔር ዓለሙን እንደሚያድንና ስለ እስራኤል ህዝብ ትንቢቶችን ይዟል::
☞ሁለተኛው ክፍል ደግሞ #ሐዲስኪዳን ሲሆን ለአብርሐም በዘርህ አሕዛብ ይባረካሉ ያለውን ያ ዘር ክርስቶስ በስጋ ተገልጦ አለሙን በደሙ መስዋዕትነት ቀድሶ የሰውን ልጅ እንዳዳነ ያመኑበትም የእግዚአብሔር ልጆች የቅዱስ መንፈሱም ማደርያ ማድረጉን ለዓለሙ ሁሉ በደሙ በኩል አዲስ መሐላን ማድረጉ የሚገልጽ ሲሆን
❖ከእመቤታችን ብስራትና ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ጀምሮ ስላስተማራቸው ትምህርቶች ስላደረጋቸው ተአምራት ስለ ሰው ልጆች ሐጢአት ዋጋ ካሳ እንዲሆን መከራ መቀበሉ መሞቱ ሞትን ድል አድርጎ መነሳቱ ለብዙዎች መታየቱን ማረጉን #በወንጌላት
❖ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ እንደተቀበሉና በጌታችን ኢየሱስ ስም የሐጢአት ስርየት መስበካቸውን ብዙ መከራ መቀበላቸውንና ብዙዎችን ማጥመቃቸውን #በሐዋርያት ሥራ
❖ስለ ጌታችን ኢየሱስ ማንነት፣ስለ አዲሱ መሐላ፣ስለ አማኞች ስነ ምግባር በእምነትም ስለመጽናት ፣በክርስቲያኖች መኖር ያለበት ፍቅር #በመልእክታት
❖ስለ መጪዋ ቤተ ክርስቲያን፣ ዲያብሎስ በዚህ ምድር ስለሚኖረው የክፋት አሰራርና ስለ ቤተ ክርስቲያን ፈተናዎች፣ስለ ሐሳዊው ክርስቶስና ስለ አዲሱ የአለም መንግስት አሰራር፣ ስለ ጌታችን ክርስቶስ ዳግም መምጣትና ስለዚህ አለም ማለፍ፣ስለ ክርስቲያኖች ተስፋ በአዲሲቷ ምድርና ሰማይ ከክርስቶስ ጋር ያለው ኑሮ #በራእይ ይዟል፡፡
በቀጣዩ የመግቢያ ክፍል መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ጥራዝ መቼና እንዴት ተደረገ የሚለውን እናያለን
✞❀✞❀✞❀✞❀✞❀✞❀✞
“የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው።”
(ወደ ኤፌሶን ሰዎች 6:17፤)
✞❀✞❀✞❀✞❀✞❀✞❀✞
“የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን።”
(2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13:14፤)
✞ክፍል ሁለት✞
መጽሐፍ ቅዱስ መቼ በአንድ ጥራዝ ተጠቀለለ?
ከክርስቶስ ልደት በፊትም ይሁን በኋላ የተጻፉት ሁሉንም መጻሕፍቶች ለየብቻቸው ነበሩ፡፡ከ500ዎቹ ዓ.ዓ አጋማሽ ጀምሮ ማለትም እስራኤላውያን ከምርኮ ከተመለሱና ቤተ መቅደሱም ካነጹ በኋላ እዝራ መጻሕፍቶችን አሰባሰበ የአይሁድ መምህራንም (ረበናት)ጉባኤ አድርገው መጻሕፍቶቹን በማጥናት በአንድ ጥራዝ ባይጠቀልሉትም 39 የብሉይ ኪዳን መጻሕፍቶችን ለይተው አጸደቁ፡፡በኋላ በግሪክ ግዛቶች ይኖሩ የነበሩ አይሁዳውያን ዕብራይስጥ ስለማይችሉ በግሪክ እንዲተረጉሙላቸውና መጻሕፍቱ በቤተ መጻሕፍት ተተርጉመው እዲቀመጡ በንጉስ ትእዛዝ ዕብራይስጥና ግሪክኛ አቀላጥፈው የሚናገሩና የሚጽፉ 72(ሰባ ሊቃናት) ሰዎች ተመርጠው በ300ዓ.ዓ ገደማ ወደግሪክኛ ሲተረጉሙ ከ39 ሌሎች ተጨማሪ መጻሕፍትንም ጨምረው ተረጎሙ፡፡ነገር ግን ይህ በ90 ዓ.ም የግሪኮቹና የእየሩሳሌሞቹ አይሁዶች ከ39ኙ መጻሕፍት ውጭ በተጨመሩት ላይ ተነጋግረው በአንድ ሐሳብ ተስማሙ እሱም “የተዛባ የታሪክ አቀራረብና የሐሳብ መቃረን አለባቸው፣ከባቢሎን ስደት መልስ በኋላ ማለትም ከ539 ዓ.ዓ በኋላ ደግሞ እግዚአብሔር ነቢይ አልላከም የእግዚአብሔር ዝምታ ጊዜ ስለነበር በመንፈሱ መሪነት ተጽፈዋል ብለን አንቀበልም” በሚል 39ኙን አጸኑ፡፡
አንዳንድ ክርስቲያኖች ከሰባ ሊቃናቱ ግሪክኛ ቅጂ አይሁዳውያኑ ያልተቀበሏቸውንም ጭምር ይጠቀሙ ነበር፡፡ በብሉይ ኪዳን ማለትም የሙሴ ሕግ፣ መዝሙራትና ነቢያት ስለ ክርስቶስ ስለሚመሰክሩ ይጠቀሙባቸው ነበር(ሉቃ 24፥44) ፡፡በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ግን ምንም አገልግሎት አልነበረም የጋራ አምልኮም ቢሆን ትምህርት ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ብቻ እንጂ በመጽሐፍ አልነበረም፡፡የኋላ ኋላ ግን በተለያየ ሁኔታና በተለያየ ምክንያት ወንጌልና መልእክታት ከ50-100 ዓ.ም ባሉት በተለያዩ ዓመታትና በተለያዩ ቦታዎች ውስጥ በሐዋርያቱ ተጻፉ፡፡መልእክታቱ ከአንዷ ቤተ ክርስቲያን ወደ ሌላኛይቱም ይተላለፉ ነበር ፡፡ ሐዋርያት በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ላይ እንደ አይሁዳውያኑ የተወሰነ የመጻሕፍት ቁጥር አላስቀመጡም፡፡ከሐዋርያት በኋላ ማለትም ከ100 ዓ.ም ወዲህ በሐዋርያት ሥም ብዙ መጻሕፍቶች ይጻፉ ጀመር ይህም ማለት የሐዋርያው እገሌ ወንጌል ወይም መልእክት እየተባለ ይጻፍ ነበር::በዛን ጊዜ የነበሩት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በብሉይ ኪዳን ላይ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ማለትም ወንጌላትና መልእክታት ወስነው እውቅና ለመስጠት በጣም ተቸገሩ ምክንያቱ በሐዋርያት ስም የተጻፉት መጻሕፍት ከመብዛታቸውና የሐሰት ትምህርቶችን ከመያዛቸው የተነሳ ብዙ ክርክር በማስነሳታቸው ነበር::የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ማለትም ወንጌላትና የሐዋርያት ትምህርት ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ጋራ አንድ ላይ በማድረግ በሙሴ ሕግ በነቢያትና በመዝሙራት የተነገረለት መሲሕ ፍጻሜው በወንጌላትና በመልእክታት እንዴት እንደሆነ እያስማሙ አማኞችን ለማስተማር ለማንበብም እንዲያመች በአንድ ጥራዝ መሆን አስፈለገ::
✍የተገኙት መጻሕፍት ብዙ ጥናትና ምርምር ከተካሄደባቸው በኋላ ግን ቅዱስ አትናቴዎስ በስሩ ያስተዳድራቸው ለነበሩ የእስክንድርያ አብያተ ክርስቲያናት ከ39ኙ የአይሁድ ብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ላይ 27 የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በማጽደቅ እንዲጠቀሙ ወሰነ::
✍የሎዶቅያ ሲኖዶስ በ364 ዓ.ም ከአይሁድ ቀኖና 22 የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እንዲሁም ባሮክና የኤርሚያስ መልእክት በመጨመር ከ26 የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት(ራዕየ ዮሐንስን በማውጣት) ሲያጸድቅ
✍የካርቴጅ ሲኖዶስም በ397 ዓ.ም በአይሁድ ቀኖና ላይ አንዳንድ ተጨማሪ መጻሕፍትን በማስገባት 44 የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትና 27 የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት አጸደቀ::በጉባኤያቱ የአይሁዱ ብሉይ ኪዳን ቀኖና 39 ኙን መጻሕፍትና የአዲስ ኪዳን 27 መጻሕፍት የዶግማ መጻሕፍት ተብለው ሲጸድቁ ሌሎቹ ከሰባ ሊቃናት የተጨመሩ መጻሕፍትን ደግሞ የቀኖና መጻሕፍት በመባል ጸድቀዋል::በተጨማሪ የቀኖና መጻሕፍቱ ላይ በየዶግማዎቹ ላይ እንደተደረገው ጥልቅ ምርምርና ጥናት የማመሳከርም ስራ አልተደረገም በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ያሉት የቀኖና መጻሕፍት የውስጣዊ ይዘት መለያየት የሚታይባቸው ለዚህ ነውና::
☞ቅዱሳት መጻሕፍትን የጻፉ ነቢያትና ሐዋርያት በተራ ጽሑፍ መልክ እንጂ ምዕራፍና ቁጥር አድርገው አልጻፉም ይህ መቼ ማንና ለምን አደረገው?
☞መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎች ፈጠራ አለመሆኑ እውነተኛነቱ በምን ይታወቃል?
☞የአሁኑ መጽሐፍ ቅዱስ ከድሮው በዘመን ሂደት ተበርዟል?
የሚሉት የርዕሳችንና ከተከታታዮች የመጡልንን ጥያቄዎችን በቀጣዩ ክፍል እናያለን
❀✞❀✞❀✞❀
(ወደ ኤፌሶን ሰዎች 6)
———-
23፤ ከእግዚአብሔር አብ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምና ፍቅር ከእምነት ጋር ለወንድሞች ይሁን።
24፤ ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ባለመጥፋት ከሚወዱ ሁሉ ጋር ጸጋ ይሁን፤ አሜን
✞ክፍል ሶስት✞
✨መጽሐፍ ቅዱስ በቁጥርና በምዕራፍ ማንና ለምን ከፈለው?
መጽሐፍ ቅዱስ በምዕራፍ መከፋፈሉ ከመጻሕፍቶቹ አንዱ ክፍል የያዘውን ሐሳብ በደምብ ለማጥናትና የት እንደሚገኝ ለማስታወስ ጥቅሙ ስለተረዳ የእንግሊዝ ካንተር በሪ ካርዲናል(ሊቀ ጳጳስ) ስቴቨን ላንግተን በ13ኛው ክ.ዘ. የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን በምዕራፍ ከፋፈለው።ሶስት መቶ ዓመታት አለፍ ብሎም በ1551ዓ.ም ሮበርት ስቴፋነስ የተባለ ፈረንሳዊ በምዕራፍ ያሉትን ሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በቁጥር ከፋፈላቸው ይህም በምዕራፍ ውስጥ ያሉትን ሐይለ ቃላት ቶሎ ለማግኘት በጣም አጋዥ ሆነ።የእነዚህ ሁለት ሰዎች ስራ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለቤተ ክርስቲያን ትልቅ ውለታ ነው።ውለታቸውም በስነ መለኮት ትምህርት(theology)፣በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ከመጽሐፍ ቅዱስ እያጣቀሱ በሚጻፉ መጻህፍት እንዲሁም በሰባክያን ዘንድ የጀርባ አጥንት በመሆን በቤተ ክርስቲያን አሰራር ላይ የማይረሳና የማይቀየር የሚመሰገንም አሻራ ሆኗል። እግዚአብሔር የድካማቸውን ዋጋ ይስጣቸው።
✨መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎች ፈጠራ አለመሆኑና እውነተኛነቱ በምን ይታወቃል? ተብሎ ለቀረበው ጥያቄ፡-
☞በመጻሕፍቱ አንድነት ይታወቃል ይህም በተለያዩ ፀሐፊዎችና በተለያዩ ጊዜያት ውስጥ ቢፃፍም አንድ ሐሳብ አንድ ዓይነት ስሜት አላቸው።በዚህም አንዱ የእግዚአብሔር መንፈስ እንዳፃፋቸው እናውቃለን።
ስለ ነቢያቱ መጻሕፍት “21፤ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።”
(2ኛ የጴጥሮስ መልእክት 1:21፤)
በሐዋርያት ላይ መንፈስ ቅዱስ እንደሚሞላና እንደሚመራቸው እንጂ ከራሳቸው ፈጥረው እንደማይናገሩ
(የዮሐንስ ወንጌል 16)
———-
“13፤ ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል።
14፤ እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና።
15፤ ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህ። ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልሁ። “
ደግሞም
(የዮሐንስ ወንጌል 15)
———-
“26፤ ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤
27፤ እናንተም ደግሞ ከመጀመሪያ ከእኔ ጋር ኖራችኋልና ትመሰክራላችሁ።”
✅ከዚህ እንደምንረዳው ነቢያቱን የመራውና የተናገረው የእግዚአብሔር መንፈስ፤ሐዋርያቱንም የመራና የተናገረው ነው ስለዚህ መጻሕፍቱ የሐሳብ አንድነት አላቸው ከእግዚአብሔር እንጂ ከሰው ፈቃድ እንዳልሆኑ እናውቃለን።
☞በተለይም በመጻሕፍቱ አንድነት ውስጥ የምናየው ስለ ክርስቶስ ያላቸው ምስክርነት ነው ለምሳሌ
ዘፍ፡-የሴቲቱ ዘር
ዘጸ፡-የፋሲካው በግ
ዘሌ፡-የመጨረሻው መስዋዕት
ዘኁ፡-የያዕቆብ ኮከብ
መዝ፡-መልካሙ እረኛ
ኢሳ፡-የሰላም አለቃ የዘላለም አምላክ የድንግል ልጅ
ኤር፡-የጽድቅ አምላክ
ዳን፡-የተቀባው(መሲሕ)
ሐጌ፡-የሁሉም ሕዝቦች ምኞት
ዘካ፡-የጌቶች ጌታ የአማልክት አምላክ
ሚል፡-የኪዳኑ መልእከተኛና የጽድቅ ፀሐይ
ማቴ፡-አማኑኤል የድንግል ልጅ
ማር፡-የእግዚአብሔር ልጅ፣የሰው ልጅ
ሉቃ፡-የመዳን ቀንድ
ዮሐ፡-ቃል፣የሕይወት ውሃ፣ትንሣኤና ሕይወት፣የዓለም ብርሃን፣የእግዚአብሔር በግ፣መልካሙ እረኛ
ሐዋ፡-የሚፈርደው
መልእክታት፡-ፋሲካችን፣የማዕዘን ድንጋይ፣የማይታይ አምላክ ምሳሌ፣አስታራቂ መስዋዕት፣በስጋ የተገለጠ
ራዕ፡-የይሁዳ አንበሳ፣አልፋና ኦሜጋ፣ፊተኛና ኋለኛ፣የሚያበራ የንጋት ኮከብ፣በብረት በትር የሚገዛ፣የአማልክት አምላክ የጌቶችም ጌታ፣የታመነው ምስክር ወዘተ
(የዮሐንስ ወንጌል 5)
———-
“46፤ ሙሴንስ ብታምኑት እኔን ባመናችሁ ነበር፤ እርሱ ስለ እኔ ጽፎአልና።
47፤ መጻሕፍትን ካላመናችሁ ግን ቃሌን እንዴት ታምናላችሁ?”
ስለዚህ በእግዚአብሔር መንፈስ ምሪት ስለተፃፉ የሐሳብ አንድነት ኣላቸው፡፡
(የሉቃስ ወንጌል 24)
———-
“44፤ እርሱም። ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው አላቸው።
45፤ በዚያን ጊዜም መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፤
46፤ እንዲህም አላቸው። ክርስቶስ መከራ ይቀበላል በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፥
47፤ በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል ተብሎ እንዲሁ ተጽፎአል።
48፤ እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ።”
እንዳላቸው በወንጌልና በመልክታቸው ስለ ክርስቶስ ይመሰክራሉ፡፡ አጠር ባለ መልኩ ይህን ይመስላል።
☞የአሁኑ መጽሐፍ ቅዱስ ከድሮው በዘመን ሂደት ተበርዟል?
አልተበረዘም!!
መጽሐፍ ቅዱስ ሶስት ቅጂዎች ማለትም ዕብራይስጥ፣ ግሪክ፣ ሱርስት(ኣራማይክ) ቅጂዎች አሉት እነዚህ ቅጂዎች ቀዳሚ እንደ መሆናቸው በተለይም ግሪኩና ዕብራይስጡ ማመሳከሪያም ናቸው።በሌላ ቋንቋ ሲታተምም በነዚህ ሚዛንነት ነው።ወደ ሌላ ቋንቋ ተርጓሚው እንደ ትውልድ ቋንቋው ተናጋሪ(native speaker) ካልሆነ የትርጉም ክፍተት ሊፈጠር ይችላል።ከቀደምት መጻሕፍት ጋር በማስተያየት ግን በታተመው ላይ ያለው ልዩነት ይታወቃል።ስለዚህ እነዚህ ማመሳከሪያዎች ስላሉ ትርጉም ስራ ላይ የቃላት ለውጥ ቢፈጠር ይታረማል እንጂ ለመበረዝ ክፍተት የለውም።ጌታም እንዳለው ቃሉ ሕያውና የታመነ ነው አይሻርም አይበረዝም
“ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም” ማቴ24፥35
✞ክፍል አራት✞
☞🔐አጭር የጥናት መመሪያ🔐☜
መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች ቋንቋ እንደ መጻፉ እግዚአብሔር የጸሐፊዎቹን ቋንቋ፣ ባህል፣ የሚኖሩበት አካባቢ መልክዐ ምድራዊ አቀማመጥ፣ስነ ቃል ወዘተ ተጠቅሞ ስላፃፋቸው የመጽሐፉን ክፍል ስናጠና መጀመሪያ ስለፀሐፊው ማንነት ቀጥሎም የስነ ጽሑፉ ቅርፅ ባሕርይ(ዓይነት)፣ የሐገሩ ሰዋስው(አገባብ) ወዘተ መረዳት ያስፈልጋል።ለዛሬ በጥናት ጊዜ የሚጠቅሙን አንኳር ሐሳቦችን እንይ
1ኛ.መመልከት ፦ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ግምታዊ አሰተሳሰብ ሳንሰጥ እንዲሁም ከሌሎች ወይም በስብከት የሰማነውን ትርጉም ቶሎ ሰጥተን አንለፍ ይልቅ ጥቅሶቹ በደምብ ሐሳባቸውን መረዳት “የተባለውን ነገር እውነት ይገልፃሉ?”ብሎ ማንበብ እንጂ ትርጉም ለመስጠት አለመቸኮል።ጸሐፊው በዚህ ክፍል ምን ማለት እንደፈለገ አንብበን በጥሞና መረዳት። በሚከትሉት ጥያቄዎችም በመደገፍ እውነቱን ማስተዋል ይገባል
★ባለታሪኮቹ እነማን ናቸው? ምን ተሰራ ምንስ ተደረገ? የት ቦታ በምንስ ሁኔታ? መቼ? እንዴት? ለምንስ? ውጤቱስ ምን ነበር? ምንስ ተፈጠረ?
የምናጠናውን ክፍል ከአውደንባቡ ለይተን ማውጣት የለብንም!!
★2ኛ.መተርጎም ፦ምን ማለቱ ነው? የሚለውን በመጠየቅ ፍቺ መስጠት። በአሁኑ ጊዜስ ተመሳሳይ የሆነው ፍቺው ምንድነው? መዝገበ ቃላት በመጠቀም ቃላቶቹን ፣ ሐረጎቹን፣ ቅኔያዊ አነጋገሮችንና ዐረፍተ ነገሮችን መተንተን
★3ኛ.ማዛመድ
ለምን ይህንን ሃሳብ ፣ ሐረግ፣ ቃል ተጠቀመ? ለምንስ ይህንን እዚህ መጥቀስ አስፈለገው? ያሉት የተለያዩ ሃሳቦችስ እንዴት ይዛመዳሉ?
ጠቃሚውን ሃሳብ ማግኘት።
ጎልቶ የሚታየውን መንፈሳዊ ሃሳብ ወይም መልዕክት ለይተን ማውጣት።ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ጋረ መስማማቱን ማረጋገጥ።
ዋናውን መልዕክት ቸል ብለን በጥቃቅን ነገሮች ላይ እንዳናተኩር ያልገባንን ለሌላ ጊዜ ጥናት ማስተላለፍ ወይም ሌሎችን በመጠየቅ መረዳት።
★4ኛ.የተለያዩ ሊቃውንት ትንታኔዎችን መመልከት
የአንዱን ሊቅ ሐሳብ ብቻ በመያዝ ትርጉም ሰጥቶ አይታለፍም!! ምክንያቱም በሊቃውንቱ አፈታት ወይም አተናተን ላይ መራቀቅ ሊኖር ይችላል ማለትም የአውደንባቡ ሐሳብ ሌላ ሊሆን ይችላል ነገር ግን በመራቀቅ እንዲህ ብለን ብንገልፀውም ያስኬዳል በሚል ንጽጽር ሐሳቡን ሊያሳዩን ይችላሉ።
★እዚህ ላይ ቅድሚያ ርቀ’ታዊ ሀሳቡ ሳይሆን የሚፈለገው ቀዳሚ አውደ ንባባዊ ትንታኔው ወይም ትርጉሙን ነው መጀመርያ የጸሐፊው(የነቢዩ ወይም የሐዋርያው) ሐሳብ ማግኘትና መረዳት ነው ያለብን። ስለዚህ ምክንያት የተለያዩ ትንታኔዎችን ማየት አለብን።አንዱ ሊቅ ምን ብሎ ተነተነው?ሌላውስ ምን አለ? ማእከላዊ (ሁሉንም ሊቃውንት የሚያቀራርበው) ትንታኔስ የትኛው ነው? በሚሉት ላይ በማተኮር ማጥናት።
እነዚህ ጠቅለልና አጠር ባለ መልኩ በጥናት ሂደት የሚጠቅሙን መመሪያዎች ናቸው።
በቀጣይ ክፍል ኦሪት ዘፍጥረት ትንታኔ እንጀምራለን
✞❀✞❀✞❀✞❀✞❀✞
“19፤ ደግሞ የወንጌልን ምሥጢር በግልጥ እንዳስታውቅ አፌን በመክፈት ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ስለ እኔ ለምኑ፤”
(ወደ ኤፌሶን ሰዎች 6:19፤)
✞❀✞❀✞❀✞❀✞❀✞
መዝሙረ ዳዊት 118(119)
“76. ምሕረትህ ለመጽናናቴ ትሁነኝ፥ እንደ ቃልህም ለባሪያህ ይሁነው።
- የቃልህ ፍቺ ያበራል፥ ሕፃናትንም አስተዋዮች ያደርጋል።
- አፌን ከፈትሁ፥ አለከለክሁም፤ ወደ ትእዛዝህ ናፍቄአለሁና።”
✞❀✞❀✞❀✞❀✞❀✞
“5፤ ቆማችሁ ከዘላለም እስከ ዘላለም አምላካችንን እግዚአብሔርን ባርኩ። እንዲህም በሉ። በበረከትና በምስጋና ሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያለው ክቡር ስምህ ይባረክ። “
(መጽሐፈ ነሀምያ 9:5፤)
አሜን!!